-
AuthorSearch Results
-
December 2, 2023 at 4:12 am #60175
In reply to: ትምህርት፣ ጤና እና ሕብረተሰብ ― ሰሞነኛ ዜናዎች፣ መረጃዎች
SemonegnaKeymasterጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ የክብር ዶክትሬታቸውን ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተቀበሉ
ባሕር ዳር፥ ኢትዮጵያ (ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ) – ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሐምሌ 16 ቀን፥ 2015 ዓ.ም ባካሄደው የተማሪዎች ምረቃ ለጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ የክብር ዶክትሬት መስጠቱ ይታወሳል። በዕለቱ ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ በሥራ መደራረብ ምክንያት በምረቃ ዕለቱ ተገኝተው ባለመቀበላቸው፥ ኅዳር16 ቀን፥ 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ስካይላይት ሆቴል በአካል ተገኝተው ተቀብለዋል።
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የ2015 ዓ.ም የተማሪዎች ምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ የመጀመሪያዋ የክብር ዶክትሬት ተሸላሚ የጠንካራ ጋዜጠኝነት ተምሳሌቷ እና የባለታሪኮች ባለአደራ ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ ናት።
የክብር ዶክተር መዓዛ ብሩን ለክብር ዶክትሬት ሽልማት ያበቋቸው ሥራዎች በዝርዝር:-
- በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የግል ኤፍ ኤም ሬዲዮ (ሸገር ኤፍ ኤም 1) መሥራች እና ባለቤት፤
- የመጀመሪያዋ ሴት የሬዲዮ ማሰራጫ ድርጅት መሥራችና ባለቤት፤
- በእንግዶች ምርጫዋ፤ በምርምር በተደገፈ የመጠይቅ ዘይቤዋ፣ በትህትናዋ፣ በአነጋገር ለዛዋ በቀጥታ አዘጋጅታ ከምታቀርባቸው መርሃ ግብሮች (የቅዳሜ ጨዋታ እና ሸገር ካፌ) በተጭማሪ በተለያዩ የሸገር ሬዲዮ መርሃ ግብሮች እንዲሁም በሌሎች ሬዲዮም ሆነ ቴሌቪዥን መርሃ ግብሮች ላይ አሻራ የተወች እና ባጠቃላይ በዚህ ዘርፍ ለተሰማሩ ጋዜጠኞች አርአያ የሆነች፤
ምናልባት ከሁሉ በላይ ታዋቂ የሆነችበትና አምሳያ የሌለው የላቀ አስተዋፅኦ ተብሎ ሊወሰድ ከሚችሉት ሥራዎቿ ውስጥ አንዱ፥ በቀላሉ ተተኪ የማይገኝላቸውን በርካታ ባለታሪክ ምሁራን፣ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች፤ የኪነ-ጥበብ ሰዎች፤ ጋዜጠኞች እና ሌሎች ባለሙያዎች የህይውት ታሪክ፣ ሥራ፣ አስተሳሰብ እና ለሌሎች አርአያ የሚሆነውን የሕይወት ፍልስፍናቸው በራሳቸው አንደበት ተሰናድቶ ለታሪክ እንዲቆይ ማድረጓ ነው። በዚህም ለኢትዮጵያውያን በዓይነቱ ተወዳዳሪ የሌለውና ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ የሚሄድ የታሪክ የድምጽ መዘክር አበርክታለች ማለት ይቻላል። የጨዋታ እንግዳ መሰናዶ እንግዶቿ ያካበቱት ልምድ፤ አበርክቶታቸው፤ ያልተጻፉ ሃገራዊ ጉዳዮች እና ሚስጥሮች ከኃላፊ ባለታሪኮቹ ጋር እንዳያልፉ፤ በመቅረጸ-ድምጽ ተሰንቀው በሰፊው እንዲታወቁ እና ከትውልድ ትውልድ እንዲተላለፉ አድርጋለች። በእርግጥም ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ ከየተደበቁበት ፈልጋ ቃለ መጠይቅ ካደረገቻቸው ጉምቱ እንግዶች መካከል ጥቂት የማይባሉት አሁን በመሃከላችን አይገኙም፤ ታሪካቸው ግን ህያው ሆኗል።
ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ በ1950 ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማ የተወለደች ሲሆን፥ ዘጠኝ ዓመት ገደማ እስኪሆናት በምዕራብ ሃረርጌ በምትገኘው ሂርና ከተማ አደገች። ሂርና ሳለች ጎረቤቶቿ የኦሮሞ፣ የሃረሪና የሶማሌ እንዲሁም የየመን ተወላጆች ስለነበሩ በተለያዩ ባሕላዊ ዕሴቶች እና እርስ በእርስ ትስስር የዳበረ አስተዳደግ ነበራት። ይህም ለሥነ-ጽሁፍ ከነበራት ዝንባሌ ጋር ተዳምሮ ለዛሬው ማንነቷ መሠረት ሆኗታል።
- ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩዘጠኝ ዓመት ሲሆናት ወላጆቿ አዲስ አበባ ወደሚገኘው የቅድስተ ማርያም የልጃገረዶች ካቶሊክ አዳሪ ትምህርት ቤት አሰገቧት።
- 1967 ዓ.ም. የሁለትኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ እያለች በእድገት በሕብረት ዘመቻ ወደ ውቅሮ፥ ትግራይ ተልካ ለስድስት ወራት አገልግላለች።
- በ1970 ዓ.ም. አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብታ በሥነ ልሳን ትምህርት ዘርፍ የመጀመሪያ ዲግሪዋን ተቀብላለች።
- ከሬዲዮ ሥራ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋወቀችው የመጨረሻ ዓመት ተማሪ ሳለች በአጋጣሚ ሲሆን፥ በወቅቱ ተወዳጅ ከነበረው የእሁድ ፕሮግራም ጋር ለነበራት ለስምንት ዓመታት ያክል የቆየ ትስስር ምክንያት ሆኖታል። ይሁን እንጂ በመጀመሪያ በቋሚነት የተመደበችበት ሥራዋ በባህል ሚኒስቴር ስር የመርሃ ስፖርት ጋዜጣ የስፖርት ዘጋቢነት ነበር።
- በመቀጠልም በኢትዮጵያ ሬዲዮ የእሁድ ፕሮግራም ተሳትፎዋን ሳታቆም በባህል ሚኒስቴር የዓለም አቀፍ አግልግሎት ክፍል አገልግላለች።
- ከዚያም በብሔራዊ ባንክ የብሪቱ መጽሄት ዋና አዘጋጅ በመሆን የፋይናንስ ዜናዎችን እና አጫጭር ታሪኮችን በመጻፍ እና በአርትኦት አገልግላለች።
- በ1984 ዓ.ም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ተቀላቅላ የፕሬስ እና ኮሚኒኬሽን ኦፊሰር በመሆን ለአራት ዓመታት ሠርታለች።
- ከዚያም በግል በአማካሪነት እና በሕዝብ ግንኙነት እና ማስታወቂያ ስትሠራ ከቆየች በኋላ፤ በ1987 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ሬዲዮ በ1 የሬዲዮ ጣቢያን የአየር ሰዓት በመጠቀም የቅዳሜ ከሰዓት የጨዋታ መርሀ ግብርን ከባለቤቷ ከአርቲስት አበበ ባልቻ እና ከረዥም ጊዜ ጓደኛዋ አርቲስት ተፈሪ ዓለሙ ጋር የማዘጋጀት ዕድል አግኝታ መርሀ ግብሩን ለስምንት ዓመታት ያክል ስታቀርብ ቆይታለች።
- በመጨረሻም በ2000 ዓ.ም. አንጋፋና ተወዳጅ የሆነውን ሸገር ኤፍ ኤም1ን እዉን ለማድረግ በቅታለች።
በአጠቃላይ ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩ በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ሙያ የጥንካሬ ተምሳሌትና በዘርፉ ለበርካቶች አርአያ ለመሆኗ ተገቢ ዕውቅና ይሆን ዘንድ የባሕር ዳር ዩኒቨርሰቲ ሴኔት በከፍተኛ ትምህርት አዋጅ ቁጥር 1152 / 2011 በተሰጠው ስልጣን መሠረት በአርት የዓመቱ የክብር ዶክትሬት እንዲሰጣቸው ወስኗል።
ምንጭ፦ ባሕር ዳር ዩኒቨርሰቲ
September 3, 2022 at 1:11 am #50372In reply to: የፖለቲካ ፓርቲዎች ድምጽ (ኢትዮጵያ ውስጥ የሚነቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች)
SemonegnaKeymasterከኢትዮጵያ ዳያስፖራ የተግባር ምክር ቤት የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ
ሀገራችን ኢትዮጵያ ተገዳ የገባችበትን የህልውና ጦርነት በጋራ ለመመከት በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊን ከሕዝባቸው ጎን በቆራጥነት በመቆም የሀገርን ሉአላዊነት ለማስከበር በሚደረገው ዘመቻ የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
ይህ የህልውና ጦርነት በውጭ ሀገር የምንገኘውን ኢትዮጵያውያን እንቅልፍ የነሳና ሀገራችን እንደ ሀገር እንዳትቀጥል በወያኔ ጁንታ ቡድን፣ በአልሸባብ፣ እና በሸኔ እንዲሁም በውጭ ሀገር የሚገኙ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች በቅንጅት የከፈቱብን ጦርነት ብሔራዊ ክብራችንና የሚነካ የሀገራችንን ሰላም የሚያውክ በመሆኑ በእጅጉ አሳስቦናል።
ስለዚህ መንግሥት በሆደ ሰፊነት ቀደም ሲል የወሰዳቸውን ቁርጠኛ የሰላም ፍላጎቶቹን በማድነቅ የሰላም ድርድሩ ውጤታማ እንዲሆን ሙሉ ድጋፍ ስንሰጥ መቆየታችን እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በአሸባሪነት የተፈረጀቱ ፀረ-ሰላም ኃይሎች ከሰላም ይልቅ ጦርነትንና እልቂትን መርጠው የከፈቱብንን የአጥፍቶ መጥፋት ጦርነትን በጥብቅ አውግዘን መንግሥት እየወሰደ ያለውን እርምጃ እንደግፋለን።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የተግባር ምክር ቤት የአሸባሪውን ጁንታ ቡድን እንዲሁም አልሸባብና ሸኔን ማውገዝ ብቻ ሳይሆን ለሀገር ሕልውናና ለሕዝባችን ሰላምና ጥቅም ስንል ከመንግሥትና እንዲሁም ከመከለከያ ሠራዊታች ጎን በመቆም የዜግነት ድርሻችንን ለመወጣት የትግባር ምክር ቤቱ ዝግጁ መሆናችንን እናረጋግጣለን።
በእርግጥ ዲያስፖራው ዛሬም ነገም ለሀገሩ ለወገኑ ድጋፉን አጠናክሮ እንደቀጠለ ቢሆንም በሀገራችን ውስጥ በተፈጠረው ሀገር የማዳን ዘመቻ በዘር፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ እምነት ሳንከፋፈል ከስሜታዊነትና ከኩሪፊያ በመውጣት ለነገዋ ኢትዮጵያ የተሻለ ነገር ለማምጣት፣ የተሻለችውን ኢትዮጵያ ለማየት ትግሉን የሚጠይቀውን ማንኛውንም ድጋፉ እንድናደርግ ምክር ቤታችን በድጋሚ በመላው ዓለም ለሚገኙ የኢትዮጵያዊያንና ለኢትዮጵያ ወዳጆች ሁሉ ጥሪ ያቀርባል።
መንግሥት ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ከፍታ ለማድረስ፣ ችግሮችን በውይይት በመፍታት፣ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት፣ የሀገራችንን ፖለቲካ ለማዘመን፣ ውስጣዊ ችግሮቻችን በተገቢው መንገድ ለመፍታት ግጭቶችና የጦርነትን ውድመት እንዳይቀጥል በቁርጠኝነት ተነሳስቶ ለሀገረ መንግሥት ግንባታው መሠረት ለመጣል ፖለቲካዊ ችግሮችን በአግባቡ ፈትሾ ሁሉን አቀፍ ውይይትና ድርድር ማድረግ፤ በሀገሪቱ ምክር ቤት በአሸባሪነት የተፈረጁትን ቡድኖች ወደ ዘላቂ ሰላም የጠረንጴዛ ድርድር እንዲቀመጡ ወስዶት የነበረውን የሰላም ጥረት አሁንም ወደፊትም እንዲቀጥል ምክር ቤታችን መደገፉን ይቀጥላል።
ነገር ግን ከጦርነት በተሻለ ሰላምን መምረጥ ትርፋማነቱ ቢያዋጣም አሸባሪውና ጎጠኛው የጁንታው ቡድን የአማራና አፋርን ሕዝብ በመውረር የትግራይን ሕዝብ አግተው በሰላማዊ ሕዝብና በመሠረተዊ የልማት ተቋማት ላይ ያደረሱትን መጠነ ሰፊ ውድመት መልሰን ለማቋቋም እርብርብ በምናደርግበት ወቅት የሀገርን ሉአላዊነት አደጋ ላይ ለመጣል ለሦስተኛ ዙር የተከፈተብን ታሪክ ይቅር የማይለው ጦርነት በእጅጉ አስቆጥቶናል። ስለዚህ፦
1ኛ የአማራና የአፋር ክልልን በመውረር ሲዋጉና አመራር ሲሰጡ የነበሩትን እንዲሁም እድሚያቸው ለውትድርና ሞያ ያልደረሱ የትግራይ ህፃናትን በመመልመል ለጦርነት ያሰልፉትን የወያኔ ጁንታ አመራሮች ተለይተው በጦር ወንጀለኝነትና በሀገር ክህደት ክስ ተመሥርቶባቸው በአስቸኳይ ለፍርድ እንዲቀርቡ መንግሥትን እንጠይቃለን።
2ኛ ሀገራችን በገጠማት የሰላም ማጣት ችግርና ተገዳ ከገባችበት የህልውና ጦርነት በተጨማሪ የሕዝብ ሞትና የሥነ ልቦና ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ የሐሀት ቅስቀሳና የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ በሚያደርጉ ቅጥረኛ ሚዲያዎች፣ አለአግባብ ለመበልፀግ የኢኮኖሚ አሻጥር በሚፈፅሙ ነጋዴዎች፣ በተለይ የመንግሥት ሙሰኞችና ሌቦች ላይ ያለምንምንም ይቅርታ ጠንካራ እርምጃ መንግሥት እንዲወስድ እናሳስባለን።
3ኛ መንግሥት የሚቻለው ሁሉ ጥረት በማድረግ ለሀገር ጠቀሜታ ሲል ዘላቂ መፍትሔ የሚያመጡ አካሄዶችና አዳዲስ ስልቶችን (strategies) መንደፍ አለበት። በተለይ ከዲያስፖራው ማኅበረሰብ ጋር እጅ ለእጅ ተያይዞ በጋራ የዓለም አቀፉን ሕብረተሰብ በተሳሳተ ፕሮፖጋንዳ የሚያውኩትን የሚዲያ ተቋማትን ተጠያቂ ለማድረግ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለድፕሎማቶቹን ጥብቅ መመሪያ እንዲሰጥና ለተግባራዊነቱም ልዩ ክትትል እንዲያደርግ በጥብቅ እናሳስባለን።
በመጨረሻም ምክር ቤቱ ወደፊት ከሚያደርጋቸው የድጅታል ዲፕሎማሲ ትግል በተጨማሪ ጦርነቱን በአጭር ጊዜ ለመጨረስ በሚደረገው የህልውና ጦርነት የዘማቹ ሠራዊት ደጀን በመሆን ጠንካራ ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ መሆናችንን ለኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት እናረጋግጣለን።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የተግባር ምክር ቤት (ኢዳተም)
July 5, 2022 at 1:48 am #48292In reply to: የፖለቲካ ፓርቲዎች ድምጽ (ኢትዮጵያ ውስጥ የሚነቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች)
SemonegnaKeymasterድርድሩ የሚደገፍ ቢሆንም በሁለቱ ፓርቲዎች መካከል የሚደረግ እንዳይሆን ጥንቃቄ ይደረግ!
በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከእናት ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ
እናት ፓርቲበሰሜን ኢትዮጵያ የተቀሰቀሰውና ሁለት ዓመት ሊሞላው ጥቂት ወራት የቀረው ጦርነት ምን አልባት ኢትዮጵያ በታሪኳ ካጋጠሟት ጥፋቶችና ውድመቶች ሁሉ ከቀዳሚዎቹ ሊቆጠር የሚችል ነው። ሰዋዊ፣ ቁሳዊ፣ ሥነ ልቡናዊና ድፕሎማሲያዊ ጉዟችንን ለብዙ አስርት ዓመታት ወደኋላ መልሷልና! ፓርቲያችን ይህ ጦርነት ሊያመጣ የሚችለው ምስቅልቅልና ዳፋ አሳስቦት በእርቅና ሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ሽማግሌዎችን ከማፈላለግ ጀምሮ የተለያዩ ጥረቶች ሲያደርግ ቆይቷል። አሁንም ያ ውድመትና ‘ውረድ እንውረድ’ ዳግም እንዳይከሰት ጦርነቱን በድርድር ለመፍታት የታየው መነሳሳት ፓርቲያችን በደስታ የሚመለከተው ኩነት ነው። በእርግጥ ብንታደል በመጀመሪያ ችግሩ እንዳይከሰት ብንከላከለው፥ ከተከሰተም በኋላ የውጭ አካል ገብቶ በድርድር መልክ ከሚፈታ ይልቅ በሀገሬው ባህል በእርቅና ይቅርታ ቢፈታ በውደድን።
ይህ ድርድር ብዙ ውስብስብ ጉዳዮችን ተሸክሞ የሚደረግ ነው፤፡ ስለሆነም ሂደቱ ከቅድመ ድርድር ጀምሮ ዘለቄታዊ መፍትሔ በሚያመጣ መልኩ ታቅዶ ካልተፈጸመ እና የውጭ ኃይሎችን “አላስፈላጊ” ጣልቃ ገብነት መከላከል ካልተቻለ “ጅብ ፈርቸ ዛፍ ብወጣ፣ ነብር ቆየኝ” ዓይነት መሆኑ አይቀሬ ነው። በማዕከላዊ መንግሥት በኩል ከአሁኑ የአካሄድ መጣረስ /procedural fallacy/ እየታየ ነው። አዎ፤ ችግሩን የፈጠረው የህወሓትና ብልጽግና የስልጣን ሽኩቻ ነው፤ የተዋጋውና ዳፋው የተረፈው ግን ሕዝብና መንግሥት በመሆኑ ወደአንድ ፓርቲ ለመጎተት የሚደረገው ጥረት አዋጭ እንዳልሆነ ግንዛቤ ውስጥ ሊገባ ይገባል። ወዲህም ፓርላማው ህወሓትን አሸባሪ በሚል ፈርጇል። ምንም እንኳን እንዳለመታደል ሆኖ የአንድ ፓርቲ ውቅርም ቢሆን ድርድሩን መፍቀድ፣ ከሽብርተኝነት መሰረዝ፣ የድርድር ነጥቦችን ማውጣት፣ ብቁና ወካይ ተደራዳሪዎችን መሰየም፣ ሂደቱን በየጊዜው መከታተል፣ ውጤቱንም ማጽደቅ ያለበት ፓርላማው ሆኖ ሳለ የፓርቲ ውሳኔ እንደመንግሥት ውሳኔ ተቆጥሮ ዘሎ የማለፍ አዝማሚያ አደገኛ ውጤት ያለው ነው ብለን እናምናለን። ስለሆነም ፓርቲያችን ለድርድሩ ውጤታማነት ቀጥሎ ያሉ ነጥቦችን ከግንዛቤ እንዲገቡ ያሳስባል።
- በፌደራል መንግሥት ከሚወከሉት በተጨማሪ የጦርነቱ ግንባር ቀደም ገፈት ቀማሽ የነበሩት የአፋር እና የአማራ ክልሎች ተወካዮች የድርድር ቡድኑ አባላት መሆን እንደሚገባቸው አጽንዖት በመስጠት እናሳስባለን። በዚህ አጋጣሚ የትግራይ ሕዝብንም ስሜት በትክክል የሚያንጸባርቁ አካላት እንዲወክሉት ጥሪያችንን እናቀርባለን።
- የእኛን የኢትዮጵውያንን ችግር ከእኛ የተሻለ ማንም የሚረዳው እንደማይኖር በመገንዘብ በገለልተኛ አካላት (ሲቪክ ተቋማት፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦች እና ምሁራን) አማካኝነት ተደራዳሪዎች በሚስማሙበት ቦታ እንዲካሄድ፤ ይህ ካልሆነ ድርድሩ በአፍሪካ ኅብረት አመካኝነት እንዲካሄድ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
- አጠቃላይ ድርድሩ እንደመንግሥት እንዲመራና ፓርላማው ሙሉ ሂደቱን እንዲመራው፤ ውጤቱም ተግባራዊ የሚሆነው በፓርላማው ሲጸድቅ ብቻ እንዲሆን፤ ተደራዳሪዎችም የአንድ ፓርቲ ተወካዮች ብቻ ሳይሆኑ በዕውቀታቸው፣ ልምዳቸው፣ በሀገራቸው ጥቅምና ሉዓላዊነት የማይደራደሩና የፓርቲ ውክልና የሌላቸው አካላት ጭምር እንዲካተቱበት አበክረን እንጠቃይለን።
- ለድርድሩ ስኬታማነት ከመንግሥት ጥረት ጎን ለጎን ሕዝብ፣ ፓርቲዎች፣ መገናኛ ብዙኃን አዎንታዊ አስተዋጽዖ በማድረግ በተለይ ከሁለቱም ወገን አላስፈላጊ የአደባባይና የውስጥ እንካ ስላንትያዎች እንዲቆሙ ጥሪያችንን እናስተላለፍለን።
- ድርድሩ ሕዝብን የሚያቀራርብ፣ ቂምና ቁርሾን የሚሽር፣ ግልጽና ጥፋተኛን በውል የሚቀጣ፣ ከሴራና እልኸኝነት የራቀ ለሕዝብ በየጊዜው ይፋ የሚደረግ እንዲሆን እንጠይቃለን።
- በአጠቃላይ ወደ ድርድር የምንገባው ከጦርነት ተላቀን እንደሀገር ብዙ ለማትረፍ እንጂ ለበለጠ ኪሣራ አይደለምና ሂደቱ የኢትዮጵያን አንድነትና ሉዓላዊነት በምንም መልኩ ለድርድር የማያቀርብ እንዲሆን አበክረን እናሳስባለን።
በመጨረሻም ድርድርና እርቅ የሚወደድ ተግባር ነው። የምንደራደረው ግን ከ“ህወሓት” ጋር በመሆኑ የጸጥታ ኃይሉ ከመዘናጋት ይልቅ ከመቸውም ጊዜ በላይ በመናበብ፣ ከፍ ባለ ዝግጅት እና በተጠንቀቅ እንዲቆም አበክረን ማሳሰብ እንወዳለን።
ፈጣሪ ሀገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ
እናት ፓርቲ (ENAT Party)
ሰኔ 27 ቀን 2014 ዓ.ም
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያJune 28, 2022 at 12:20 am #41750In reply to: ነፃ አስተያየት (ስለኢትዮጵያ በኢትዮጵያውያን)
SemonegnaKeymasterየአማራን ሕዝብ ሰቆቃ እያየ እንዳለየ፣ እየሰማ እንዳልሰማ…
ጋዜጠኛ አበበ ገላውየአማራ ሕዝብ በደለኝ የሚል ካለ ማስረጃውን ይዞ ይቅረብ። አንድም ሰው አይገኝም። የኦሮሞም ይሁን የትግራይ፣ የአፋርም ሕዝብ ይሁን የሲዳማ፣ የጋምቤላም ይሁን የሶማሌ፣ የጉራጌም ይሁን የወላይታ ሕዝብ… ፈጽሞ ማንንም በድለው አያውቁም። የትኛውም ሕዝብ በጅምላ ግለሰቦችንም ይሁን ቡድኖችን ሊበድል ፈጽሞ አይችልም። ስለዚህም ነው በዓለማችን ላይ እጅግ አሰቃቂው ግፍ በተፈጸመበት አውሮፓ ናዚዎች ለፈጸሙት ወንጀል ተጠያቂ አድርጎ ጀርመኖችን እያደነ የሚገድልና የሚያፈናቅል ቡድን ኖሮ አያውቅም። በእኛም ሀገር ሞሶሎኒ በመርዝ ጋዝ ሳይቀር ለፈጸመው ግፍ ንጹኃን የጣሊያን ዜጎችን አሳደንም ይሁን ጨፍጭፈን አናውቅም። እንዲህ ዓይነቱን አስነዋሪ ወንጀል ብንሞክረውም ግፍ እንጂ ፍትሃዊ ሊሆን ፈጽሞ አይችልም።
በእኛ ሀገር በክፋት ህወሓት በዋነኛነት ከፋፍሎ ለመግዛት እንዲያመቸው መዋቅርና ቅርጽ የሰጠውን ተረት በማንገብ በጥንታዊ ነገሥታትና መንግሥታት ለተፈጸሙ በደሎች መላውን የአማራ ሕዝብ በነፍጠኛነት ፈርጆ ከምንም የሌሉበትን ምሲኪን ድሆች በጅምላ መግደል፣ ማሳደድ፣ ማፈናቀል፣ አፍኖ መውሰድ፣ አካላዊና ስለልቦናዊ ጥቃት መሰንዘር የተለመደ ክስተት ከሆነ አርባ አመታት ተቆጥረዋል። አብዛኛው የአማራ ተወላጅ ሀገሩ እንዳይፈርስ፣ ሕዝብ ለበቀል እንዳይነሳ እና ማለቂያ የሌለው እልቂትና ውድመት እንዳይደርስ በሚል የአስተዋይነት መንፈስና ባህል የሆዱን በሆዱ ይዞ በትዕግስት ህመሙን እና ሀዘኑን አፍኖ በኢትዮጵያዊነት ጨዋነት ከየትኛውም ኢትዮጵያዊ ወገኑ ጋር ተቻችሎና ተከባብሮ ለመኖር የሚቻለውን ሁሉ አድርጓል።
ይሁንና አሳዛኙ ሃቅ የሕዝቡን ትዕግስት እንደ ፍርሃት የቆጠሩ እኩይ ኃይሎች የአማራን ሕዝብ በጅምላ ዘውትር ከማሸማቀቅ አልፈው የጅምላ ጭፍጨፋ፣ ግፍና ማፈናቀል ያለማቋረጥ እየፈጸሙበት ይገኛሉ። የሕዝቡን ሰላምና ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነትን የተረከበው “የለውጥ” ኃይልና መንግሥትም ከእነ መለስ ዜናዊ ባልተለየ ሁኔታ የአማራን ሕዝብ ሰቆቃ እያየ እንዳለየ፣ እየሰማ እንዳልሰማ… ሕዝቡ በገፍ እያለቀና እየተሰቃየ ባለስልጣናቱ ሌላው ቀርቶ የረባ የሀዘን መግለጫ፣ ማጽናኛም ይሁን የአንዲት ሰከንድ የህሊና ጸሎት ነፍገውታል።
የዚህ ታጋሽ ሕዝብ ትግስት አልቋል። መንግሥት የሕዝብን ደህንነትና ሰላም በአግባቡ መጠበቅ ካልቻለና የዜጎቹ የጅምላ ሞት፣ ሰቆቃ መፈናቀል፣ የደም ጎርፍና እንባ ግድ የማይለው ከሆነ ሕዝቡ ሰላሙን፣ ደህነንቱና ዜግነታዊ መብቱን ሙሉ በሙሉ የሚያከብርለትና እኩልነትና አንድነትን የሚያረጋግጥለት መንግሥት እንዲመጣ አምርሮ ከመታገል ውጭ አማራጭ እንደማይኖረው ሊታወቅ ይገባል።
ጋዜጠኛ አበበ ገላው (facebook.com/agellaw)
[caption id="attachment_41752" align="aligncenter" width="600"] በጀርመን የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ሰላማዊ ሰልፍ ላይ[/caption]
August 9, 2021 at 3:20 am #20165In reply to: የፖለቲካ ፓርቲዎች ድምጽ (ኢትዮጵያ ውስጥ የሚነቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች)
AnonymousInactiveየአማራ ብልፅግና ፓርቲ መግለጫ
አሸባሪው ህወሓት (ትህነግ) የአማራና የአፋር ክልል መሬቶች መውረሩንና በሀገር ላይ እያደረሰ ያለውን ሁለንተናዊ ጥፋትና ሽብር ተከትሎ፥ የአማራ ብልፅግና ፓርቲ የሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ይህንን ይመስላል።
እምቢ ለባርነት፤ ክተት ለነጻነት!!
የአማራ ብልፅግና ፓርቲ መግለጫበሁሉም የክልላችን ዞኖች፣ በበርካታ ከተሞች እና ወረዳዎች የህልውና ዘመቻውን ተከትሎ እየተካሄዱ ያሉ መሠረታዊ የውትድርና ስልጠናዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል። ሕዝባችን ህልውናውንና ኢትዮጵያን በደምና በአጥንቱ እንደሚጠብቅ የአባቶቹን ቃል-ኪዳን በማደስ ላይ ይገኛል። በዚህም የወገን ጦር ከፍተኛ መነቃቃት ሲያሳይ በአንጻሩ በቅርብም ሆነ በርቀት ያለው ጠላት በፍርሃት እየተናጠ ይገኛል። አሁን መላ የኢትዮጵያ ብሔር ብሄረሰቦች ለህልውናቸውና ለሉአላዊነታቸው ሲሉ ወታደር መሆን መርጠዋል። የዘመቻው ድጋፍ ይህን ሀቅ ያስረግጣል። በታሪክ ስናየው የኖረው እውነታ ኢትዮጵያ ሊቀብሯት የተነሱትን የውጭና የሀገር ውስጥ ፋሽስቶች ሁሉ በመቅበር ስታሳፍራቸው ኑሯለች።
አሸባሪው ትህነግ፣ ከታሪክ የመማር አንዳች ፍላጎት የለውም። በለመደ የባንዳ ታሪኩ ከጀርባው የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶችን ተማምኖ ወክየዋለሁ የሚለውን ሕዝብ ጥይት ማብረጃ ማድረጉን ተያይዞታል። ለባዕድ ሥርዓት የመታመን ልማድ ያለውና የኢትዮጵያ ካንሰር የሆነው ትህነግ አማራን ሊያጠፋ፤ ኢትዮጵያን ሊበትን ቆርጦ መነሳቱን ተከትሎ በአጸፋው የኢትዮጵያ ብሔር ብሄረሰቦችን በቁጭት ስሜት ከዳር እስከ ዳር አነቃንቋል።
በክልላችን የታወጀውን የክተት ጥሪ ተከትሎ የታየው አስደማሚ ሕዝባዊ ንቅናቄም ጥሪውን ተቀብሎ የመፋለም ጉዳይ “አማራን እና ኢትዮጵያን የመታደግ ጉዳይ ነው” በሚል እምነት ስለመሆኑ በተግባር እየተረጋገጠ ነው። በሁሉም የንቃናቄ መድረኮች የተሰማው ሕዝባዊ ድምጽ አንድና አንድ ነው። “ጦርነቱ የህልውናና ሀገር ማዳን ዘመቻ ነው” ፤ “በአሸባሪው ትህነግ መቃብር ላይ በጠንካራ ወንድማማችንት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እንገነባለን!” የሚል ነው።
ምንም እንኳ አሸባሪው ትህነግ ዕድሜው ከ12 ዓመት ህፃን እስከ 70 ዓመት አዛውንት ሴት፣ ወንድ ሳይለይ ኢትዮጵያን ለመውጋት ያሰለፈና የተነሳ ቢሆንም፥ የዚህ ጦርነት ተደማሪ ግብ የትህነግ አስተሳሰብ ቁራኛ የሆነውን የትግራይ ሕዝብን ነጻ ማውጣትን ይጨምራል። በተለይም ኑሮውን በደሳሳ ጎጆ እየኖረ በድንጋይ ስር አፈር እየገፋ የሚኖረው ጭቁኑ የትግራይ አርሶ አደር፥ አሸባሪውን ትህነግ “ልጆቻችንን የት ጣላችኋቸው ?” ብሎ መጠየቅ የሚጀምርበት ጊዜ ሩቅ አይደለም።
ጦርነት በባህሪው ከሚፈጥረው የኢኮኖሚ ድቀት በላይ ማኅበዊ ቀውሱ ተሻጋሪ ዕዳ እንደሚያመጣ ከትግራይ አርሶ አደሮች በላይ እውነታውን የሚረዳ የለም። ይህ ጦርነት በግብ የኢትዮጵያ ካንሰር የሆነውን ትህነግ ወደመቃብር ማውረድ ቢሆንም በውጤቱ የወላድ መካን የሆነችው የትግራይ እናትም ነጻ ትወጣበታለች። የኢትዮጵያ የግዛት አንድነት በመንደር ወንበዴዎችና ግልገል ሽብርተኞች አደጋ ላይ እንዲወድቅ የኢትዮጵያ ብሔር ብሄረሰቦች እንደማይፈቅዱ በተግባር እያሳዩ ይገኛል።
የዚሁ ተግባራዊ ዐቢይ ምዕራፍ አካል የሆነው የክልላችን የህልውና ዘመቻ ዝግጅትና አፈጻጸም በስኬት መጓዙን ቀጥሏል። የክተት ጥሪውና የንቅናቄ መድረኩ ወደመሬት ስራ ወርዷል። የወቅቱ ተልዕኳችንም ከአደባባይ ንቅናቄ ወደግንባር መሰለፍ ሁኗል። የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የልዩ ኃይል ምልመላዎች በመካሄድ ላይ ናቸው። አሁንም የነገ ባለአራት ኮከብ ጀኔራሎች የሚገኙት ዛሬ መከላከያ ሠራዊቱን በመቀላቀል ላይ ከሚገኙት ወጣቶች ነውና ምዝገባው ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል። በተመሳሳይ የአማራ ልዩ ኃይል በሰው ኃይል፣ በአደረጃጃት እና በወታደራዊ ዲሲፕሊን የማጠናከሩ እና የማዘመኑ ተልዕኮ የክተት ጥሪውን በተቀበሉ ጀኔራል መኮንኖቻችን በመካሄድ ላይ ነው። ከወታደራዊ መረጃ አኳያ ቁጥሩን በይፋ ለመግለጽ ባይቻልም የልዩ ኃይላችን፣ የሚሊሻችን በጥቅሉ የአማራ ሕዝባዊ ሠራዊታችን አቅም በፍጠነት እያደገ ነው። በተመሳሳይ ተልዕኮ በሁሉም ማዕከላት ተጠባባቂ ኃይል የማፍራት ስራው የህልውና አጀንዳው አካል ሁኗል።
ይህም ሁኖ ሰብዓዊነቱን ክዶ ለመጣው ጠላት ከዚህም በላይ ዝግጅት ሊካሄድ ይገባል። ከአንድ ወር ወዲህ ያለውን የጠላት ዝግጅት ብንመለከት፡- በትግራይ በሁሉም ወረዳወች በብዙ ሽህዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላ (conscription) ኮታ ተጥሎበታል። ይህ የፌዴራል መንግሥቱ የተናጠል የተኩስ አቁም ካወጀ በኋላ ትህነግ በአማራና አፋር ክልሎች ላይ የከፈተውን ወረራ ተከትሎ የተጣለ ግዳጅ ነው። ከዚህ ግዳጅ በፊት የነበረው ሰልጥኖ የታጠቀው ኃይል አብዛኛው ወደመቃብር የወረደ ሲሆን፤ ይህንኑ የሰው ኃይል ክፍተቱን ለመሙላት በዚህ ወር ብቻ በብዙ ሺህዎች የሚገመት የሳምንታት ስልጠና የወሰዱ ታዳጊዎችን ለወረራ አሰልፏል። ይህ ኃይል ከኢትዮጵያዊነት እሴት የራቀ በመሆኑ እንደአንበጣ በየደረሰበት ያገኘውን የሚወር፣ የሚዘርፍ፣ ሴቶችንና እናቶችን የሚደፍር፣ መሠረተ ልማቶችንም የሚያወድም በጥቅሉ ሰብዓዊነቱን የካደ፤ በአማራና በኢትዮጵያ ጥላቻ ያበደ በመሆኑ በፍጥነት ሊደመመስ ይገባል። እረፍትም ጊዜም ሊሰጠው አይገባም።
ስለሆነም የህልውና ዘመቻው በጊዜ የለንም መንፈስ ተጠናክሮ ይቀጥላል። መሽቶ በነጋ ቁጥር አሸባሪው ኃይል ወደመቀመቅ የሚወርድበት ጉድጓድ ጥልቀት ይጨምራል። ጠላት በተግባርም ሆነ በአስተሳሰብ ሊቀበር ይገባል።
ይህ የሽብር ቡድን በተመሳሳይ ሰዓት ከአማራም፣ ከአፋርም እንዲሁም ከጎረቤት ኤርትራ ጋር በአንድ ጊዜ ወደግጭት መግባት ያስፈለገው ግጭት ብቸኛ የዕድሜ ማስቀጠያው እንደሆነ በማመኑ ነው። ባለፉት ሠላሳ ዓመታት በተግባሩም ሆነ በአስተሳሰቡ ለኢትዮጵያ ካንሰር ስለመሆኑ በበቂ ሀገራዊ ኪሳራ ተገምግሟልና አሁን ላይ ለወረራ የተሰለፈባቸው የአማራና የአፋር መሬቶች የአሸባሪው ትሕነግ መቀበሪያ መሆናቸው ይቀጥላል።
እምቢ ለባርነት፤ ክተት ለነጻነት!!
የአማራ ብልፅግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት
ሐምሌ 30 ቀን፥ 2013 ዓ.ም.
ባህር ዳር፥ ኢትዮጵያJuly 19, 2021 at 3:37 am #19950In reply to: የፖለቲካ ፓርቲዎች ድምጽ (ኢትዮጵያ ውስጥ የሚነቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች)
AnonymousInactiveበሀገር አንድነት እና ሰላም ላይ የተደቀነውን አደጋ የመመከት ኃላፊነት በዋነኛነት የፌደራል መንግሥቱ ነው!
ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የተሰጠ መግለጫመንግሥት በትግራይ ያለው ግጭት ቆሞ ለሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረስ የተሻለ ሁኔታ ለመፍጠር እና ሌሎች ምክንያቶችን ጠቅሶ የተናጥል ተኩስ አቁም ማወጁን ተከትሎ ሰኔ 26 ቀን 2013 ዓ.ም የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ባወጣው የ‘ቢሆንስ’ ትንተና ሊሆን ይችላል ብለን ያስቀመጥነው ሁለተኛው ቢሆንስ (scenario) መንግሥት በትግራይ ክልል የተናጠል ተኩስ አቁም ካወጀ በኋላ የትግራይ አማጺዎች ግጭቱን ለማስፋት የሚያደርጉት ሙከራ ቀጥሎ ግልፅ አሸናፊ የማይኖርበት ሁኔታ ይከሰታል የሚል ነበር። ይህም ከቀጠለ በክልሉ ሕግና ሥርዓትን ማስከበር አዳጋች መሆኑ የሚፈጥረውን አጋጣሚ በመጠቀም ዘረፋዎች ሊበራከቱ እንደሚችሉ፣ የዕለት እርዳታ የሚያስፈልጋቸው የክልሉ ነዋሪዎች በሚፈለገው ደረጃ እርዳታ ሳያገኙ ቀርተው ለከፍተኛ አደጋ ሊጋለጡ እንደሚችሉ፣ መሰረታዊ ለኑሮ የሚያስፈልጉ አገልግሎቶች እና ግብዓቶች (የውሃ፣ የመብራት፣ ህክምና) ማግኘት የማይቻልበት ሁኔታ ሊፈጠር የሚችልበት ዕድል ከፍተኛ በመሆኑ የክልሉ ሕዝብ ለከፍተኛ ችግር የሚጋለጥበት ሁኔታ ሊበራክት እና ለረጅም ጊዜ ምንም ዓይነት አስተዳደራዊ አገልግሎት ሊያገኝ የማይችልበት ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል እና የዚህ ዓይነት የማያቋርጥ ግጭት ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ብዙ ችግሮችን ስቦ በማምጣት (ኢንቬስትመንት ይቀንሳል፤ ቱሪዝም ይቀንሳል፤ በዚህም የሥራ አጥ ቁጥር ይጨምራል) በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎችም አለመረጋጋትን ሊያስከትል ይችላል የሚል ትንተና አስቀምጠን ነበር። በትንተናችን ውስጥ ይህ ቢሆንስ (scenario) የመሆን ዕድሉ ከሌሎቹ የበለጠ መሆኑን ጠቅሰን በክልሉና ባጠቃላይ በሀገራችን ከብሔር ፖለቲካ ጋር ተያይዞ የመጣውን አደጋ በዘላቂነት የማይፈታ፣ ሀገሪቱን ቀስ እያለ ውስጧን እንደሚበላ በሽታ ከመግደሉ በፊት መፍትሄ የሚፈልግ እንደሆነ ገልፀን ነበር። በተጨማሪም በዚህ ሁኔታ ውስጥ መረጋጋትን ማስፈን ስለማይቻል የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ወደ ከፍተኛ ግጭት ማምራቱ እንደማይቀር በትንታኔያችን ውስጥ አስቀምጠን ነበር።
የፌደራል መንግሥቱ የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት በይዞታው ስር የነበሩ ቦታዎችን ለቆ ከወጣ በኋላ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ያስተዋልነው እንቅስቃሴ በቢሆንስ (scenario) ትንተናችን ውስጥ ከሁሉም የተሻለ የመከሰት ዕድል አለው ብለን ያስቀመጥነው ሁለተኛው ቢሆንስ (scenario) እውን እየሆነ እንደሆነ የሚያመላክት ነው።
በእርግጥ ከላይ በጠቀስነው ትንተናችን ውስጥ ህወሓት የሚያደርሳቸውን ትንኮሳዎች በኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት እየተመከቱ እና እየከሸፉ ሊሄዱ ይችላሉ የሚል ግምታችንን ብናስቀምጥም በተግባር ያየነው ግን የፌደራል መንግሥት ህወሓት ግጭቱን ለመቀጠል የወሰዳቸውን እርምጃዎች በግንባር ቀደምነት አመራር እየሰጠ ለማክሸፍ ከመሞከር ይልቅ ግጭቱን በክልሎች መካከል ያለ ግጭት እስኪመስል የወሰደው ግልፅ ያልሆነ አቋም እጅግ አስደንጋጭ ሆኖ አግኝተነዋል።
ከዚህም በላይ ግጭቱን በተመለከተ በፌደራል መንግሥቱ በኩል የሚወሰዱ እርምጃዎች የተጣደፉ እና በቅጡ ያልታሰበባቸው መምሰላቸው በአጭር ጊዜ ከህወሓት የተደቀነውን አደጋ በማንኛውም መንገድ ከማክሸፍ ባለፈ እርምጃዎቹ ለሀገራችን ሰላም እና አንድነት በዘላቂነት የሚኖራቸውን አንድምታን ያልገመገሙ ስለመሆናቸው አመላካች ሆነው አግኝተናቸዋል።
መንግሥት የሚወስዳቸው እርምጃዎችን በተመለከተ ጊዜውን የጠበቀ እና ትክክለኛ መረጃ ለሕዝብ ባለማድረሱ በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ መደናገጥ ከመፍጠሩም ባለፈ በመንግሥት ላይ ያለው እምነት እንዲሸረሸር ምክንያት ሆኗል። በተጨማሪም ህወሓት ያደረሳቸውን ወንጀሎች እና የሚፈጽማቸውን ኢሰብዓዊ ድርጊቶች ከተራ ክስ ባለፈ በተጨባጭ ማስረጃዎች አስደግፎ ለዜጎች እና ለዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ እንዲደርስ ማድረግ ላይ ከፍተኛ ክፍተት እየተስተዋለ ይገኛል። እነዚህ ክፍተቶች በጊዜ መፍትሄ ካልተበጀላቸው ችግሩን የበለጠ እያባባሱት እንደሚሄዱ እናምናለን።
መንግሥት በተጨባጭ ማስረጃዎች ላይ ተመስርቶ ለህወሓት የሚደረግ ማንኛውንም ዓይነት ድጋፍ ለማስቆም እና ተጠያቂነትን ለማስፈን ያለበትን ኃላፊነት ሙሉ በሙሉ የምንደግፍ ቢሆንም በሌሎች የሀገራችን አካባቢዎች ህወሓትን ትደግፋላችሁ በሚል ምክንያት የሚወሰዱ እርምጃዎች ማስረጃ ላይ የተመሰረቱ ከመሆን ይልቅ እንዲሁ በጅምላ የሚወሰዱ መሆናቸው የዜጎችን ሰብዓዊ መብት የሚጋፉ እና በትግራይ ያለውን ችግር የበለጠ የሚያወሳስቡ ድርጊቶች ናቸው። ለአብነት በአዲስ አበባ ከተማ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ብቻ በተመሳሳይ ወቅት ቢያንስ 60 የንግድ ተቋማት/ሱቆች ከግጭቱ ጋር በተያያዙ ምክንያቶች ታሽገው ላለፉት ሁለት ሳምንታት ተዘግተው ቆይተዋል። ከግጭቱ ጋር በተያያዘ ሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚደርስ እንግልት፣ ከሕግ አግባብ ውጪ የሆነ እስር እና ጥቃት በአፋጣኝ መቆም እንደሚገባው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ሐምሌ 8 ቀን 2013 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ መጠየቁ ይታወሳል።
ከላይ የተጠቀሱትን መሰረት በማድረግ የሚከተሉት ምክረ ሀሳቦች ተግባራዊ እንዲደረጉ እንጠይቃለን፥
- በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች የሚገኙ የፀጥታ አስከባሪዎች ህወሓት የደቀነው አደጋን ለማክሸፍ እያደረጉ ያሉትን መረባረብ በከፍተኛ አክብሮት እናደንቃለን። ህወሓት የፌደራል መንግሥቱን በበላይነት ይቆጣጠር በነበረበት ጊዜ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊያን ላይ በሙሉ ግፍ ሲፈጽም እንደነበረ ሁሉ አሁንም የደቀነው አደጋ በሀገር አንድነት እና ሰላም ላይ እንጂ በአንድ ወይንም በጥቂት ክልሎች ላይ ብቻ ያነጣጠረ እንዳልሆነ በመረዳት አደጋውን ለመከላከል የሚወሰደው እርምጃ አንድ ወጥ የዕዝ ሰንሰለት ኖሮት በፌደራል መንግሥት እና በኢፌደሪ መከላከያ ሠራዊት አመራር ሰጪነት ብቻ እንዲወሰድ፤
- በትግራይ ክልል ያለውን ችግር አሁን ከፊታችን ህወሓት ከደቀነው አደጋ እንፃር ብቻ በማየት ህወሓትን ማሸነፍን ብቻ ዓላማ ያደረገ የአጭር ጊዜ ስልት ይዞ ከመንቀሳቀስ ባለፈ በዘላቂነት ክልሉ ወደተረጋጋ ሰላም እና ዜጎች ወደ መደበኛ ሕይወታቸው ሊመለሱ የሚችሉበት እንዲሁም ግጭቱ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ተቋጭቶ የሀገር ህልውና እና አንድነትን በዘላቂነት ማረጋገጥ የሚቻልበት ስልት የአካባቢውን ተወላጆች በማሳተፍ እንዲነደፍ እና ተግባራዊ እንዲደረግ፤
- አሁን ያለው ግጭት ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲያበቃ እና ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ በትግራይ ክልልም ሆነ በሌሎች የሀገራችን አካባቢዎች የምትገኙ የሀገር ሽማግሌዎች እና ሌሎች ልሂቃን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የምታስፈልጉበት ወቅት ላይ መሆናችሁን ተረድታችሁ የሚጠበቅባችሁን ኃላፊነት እንድትወጡ፤
- የሰብዓዊ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ድጋፍ እንዲደርሳቸው የሚደረገው ጥረት አሁን ከምን ጊዜውም በላይ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እና መንግሥት የሰብዓዊ እርዳታ በክልሉ ለሚኖሩ ዜጎች እንዲዳረስ የሚያደርገውን ጥረት በግልፅ እንዲያሳውቅ፤ እንዲሁም በዚህ ተግባር የሚሳተፉ የሰብዓዊ ድርጅቶች በግልፅነት እንዲንቀሳቀሱ ተገቢው ክትትል እንዲደረግ፤
- የተለመዱ መንግሥትን የሚያሞግሱ የፕሮፖጋንዳ ሥራዎችን እየደጋገሙ ሕዝብን ከማሰልቸት ይልቅ መንግሥት የወሰዳቸውን እርምጃዎች በተመለከተ ትክክለኛ እና ወቅታዊ መረጃ ለሕዝብ እንዲደርስ እንዲደረግ እና ህወሓት የሚፈፅማቸውን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች እና ታዳጊዎችን በወታደርነት መመልመል እና በጦርነት ማሳተፍን የመሳሰሉ ወንጀሎችን በተገቢው ፍጥነት በተጨባጭ ማስረጃዎች እያስደገፉ ይፋ የማድረግ ሥራ ተገቢውን ትኩረት ተሰጥቶት እንዲሠራ፤
- ዜጎች ለህወሓት የሚደረግ ማንኛውም የሞራልም ሆነ ቁሳዊ ድጋፍ በሕዝብ ሠላም፣ በሀገር ደህንነት እና ሕይወቱን ለመሰዋዕትነት አዘጋጅቶ በተሰለፈው የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ላይ የሚደረግ ክህደት መሆኑን በመረዳት ከተመሳሳይ ድርጊቶች እንዲታቀቡ፤
- ህወሓትን ደግፋቹኻል በሚል በጅምላ የሚወሰዱ እርምጃዎች ባስቸኳይ እንዲቆሙ እና እስካሁንም በዚህ መልኩ የተወሰዱ እርምጃዎች አፋጣኝ ማጣራት ተደርጎ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ እንዲሁም አሁን ያለውን ሁኔታ እንደ አጋጣሚ በመጠቀም የግል ጥቅም ለማግኘት ዜጎች ላይ እንግልት የሚፈፅሙ የመንግሥት እና የፀጥታ ሠራተኞች ላይ አስፈላጊው ማጣራት በአስቸኳይ ተደርጎ የማያዳግም ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ፤
በመጨረሻም የሀገራችን ሰላም እና አንድነት በዘላቂነት ተረጋግጦ የሁሉም ዜጎች መብት እኩል የሚከበርበት እና እኩል ዕድል የሚሰጥበት እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት ሁላችንም የምንችለውን ሁሉ የምናዋጣበት አሳሳቢ ወቅት ላይ እንዳለን እያስታወስን ሁላችንም ኃላፊነታችንን ከምር ወስደን እንድንወጣ እናሳስባለን።
ሐምሌ 10 ቀን 2013 ዓ.ም.
አዲስ አበባ፥ ኢትዮጵያJuly 18, 2021 at 4:23 am #19942In reply to: ነፃ አስተያየት (ስለኢትዮጵያ በኢትዮጵያውያን)
AnonymousInactiveይድረስ ለትግራይ ወገኖቼ!
በአቶ ክርስቲያን ታደለ ጸጋዬ
የትግራይ ሕዝብ ከባለጌ ልጆቹ በላይ ሀገሩን የሚመርጥበት ጊዜ ደርሷል። በተለይም የትግራይ እናቶች እና አባቶች በራሳቸው ልጆች እኩይ ስምሪት ቀደምቶቻቸው ለአንድነቷ ሰማዕትነትን የተቀበሉላት ኢትዮጵያችን ክብሯ እንዲጎድፍ በዝምታ መተባበራቸውን ይበቃል ለማለት ትክክለኛው ወቅት አሁን መሆኑን ልብ ሊሉ ይገባል።
የዘመን ተጋሪዬ ለሆናችሁ የትግራይ ወጣቶችም “ጅብም ብሆን የወንዝህ ጅብ ስለሆንሁ፤ ልበላህ መብት አለኝ” የሚሉ ሀገር አጥፊዎችን በመተው ከሀገራችን ኢትዮጵያ እና ወንድሞቻችሁ ጎን እንድትቆሙ ወንድማዊ ጥሪዬን አቀርብላችኋለሁ።
የሀይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ጨዋው የትግራይ ሕዝብ በሀገር አፍራሽ፣ ዘር አጥፊና ዘራፊ ብኩኖች በኩል ዘላቂ መብቶቹ፣ ጥቅሞቹና ፍላጎቶቹ እንደማይከበሩለት አውቃችሁ፤ ሁለንተናው ከኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ጋር የተሸመነውን የትግራይ ሕዝብ ታሪክ፣ ክብርና የወደፊት በጎ ተስፋ በሚመጥን ስምሪት እንድትገኙ ዝቅ ብዬ እለምናችኋለሁ።
ታላቁ የትግራይ ሕዝብ በሌባ አይወከልም! ከዘፍጥረት ጀምሮ እስካሁን ድረስም እናት ኢትዮጵያም ሆነች ወንድሙ የአማራ ሕዝብ ለትግራይ ሕዝብ የክብሩ ምንጭ የደኅንነቱ ደጀኖች እንጂ የስጋቱ ምንጮቹኘች ሆነው አያውቁም፤ አይሆኑምም። እንዴት ሀገር ገንቢው ትግራይ በሀገር አፍራሽ ይወከላል?
ትግራይ የምታሸንፈው ኢትዮጵያ ስታሸንፍ ብቻ ነው፤ ትግራይ አንገት ደፍታ ኢትዮጵያ አትቃናም። በትግራይ ለቅሶ ፈገግታው የሚደምቅ አንድም ኢትዮጵያዊ አይኖርምም። ሌባና ዘራፊ፤ ባንዳና ሀገር አጥፊ ግን ከየትም ይሁን የትም የጋራ ጠላታችን ነውና በጋራ ልንደመስሰው ይገባናል። በባንዳ ሞት ደረት የሚደቃና ፊት የሚነጭ ሊኖር አይገባም።
እናም ለተከበራችሁ የትግራይ አባቶቼና እናቶቼ፣ ወንድሞቼና እህቶቼ፥ ስለደማቁ የትናንት ትናንታችን ብቻ ሳይሆን ስለብሩህ ነጋችንም ብላችሁ ለኢትዮጵያችን ኅልውና እንዲሁም ለሕዝባችን ፍትሕ፣ እኩልነትና ነፃነት መረጋገጥ በአንድነት እንድንቆም ስል ጥሪዬን ደግሜ ላቀርብላችሁ እወዳለሁ።
ሁሉም ችግሮች ከጋራ አቅማችን በታች ናቸው። ስንደማመጥ፣ ስንከባበርና ስንተማመን ከባዱ ቀላል ይሆናል። ኢትዮጵያ ስታሸንፍ ሁላችንም እናሸንፋለን!
አቶ ክርስቲያን ታደለ ጸጋዬ
አቶ ክርስቲያን ታደለ ጸጋዬ በፌደራል የጤና ሚኒስቴር፥ የማኅበረሰብ ጤና ኤክስፐርት (public health expert) ሲሆኑ፤ በፖለቲካ እንቅስቃሴአቸው ደግሞ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ናቸው። እርሳቸውን በፌስቡክ ገጻቸው ወይንም በትዊተር ሃንድላቸው ሊያገኟቸው ይችላሉ።
ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረ–ገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forums) ላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።
July 18, 2021 at 2:53 am #19938In reply to: የፖለቲካ ፓርቲዎች ድምጽ (ኢትዮጵያ ውስጥ የሚነቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች)
AnonymousInactiveየኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታ ላይ የሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ
የኦሮሚያ ክልል ሕዝብና መንግሥት ኢትዮጵያን በመገንባት ዉስጥ የሚመጥነዉን አስተዋፅኦ ሲያበረክት ቆይቷል። የሀገርና የሕዝብ ሉአላዊነትና ነፃነትን ለማስከበር በሚከፈለዉ መስዋዕትነት ላይ እራሱን ቆጥቦ አያውቅም። በዉጪ ወረራና በታሪክ አጋጣሚ የባንዳነትን ተግባር ሲፈጽሙ በነበሩት ኃይሎች ላይ በየታሪክ ምዕራፉ ራሱን ሰጥቶ ኢትዮጵያን የገጠሟትን ችግሮች ለማክሸፍ መስዋዕትነትን ከፍሏል። እንደሀገር ስናስመዘግብ በቆየናቸው ድሎች ዉስጥ ተወራራሽ ታሪክ አስመዝግቧል።
ዛሬም እንደ ትናንቱ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የክልሉን ሕዝብ በማቀናጀት በወንድሞቻችን አብሮነት በኢትዮጵያ ላይ የሚቃጣውን የውስጥና የውጪ ትንኮሳ ለማክሸፍ ዝግጁነቱን ይገልፃል።
የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የፌደራል መንግሥቱ የወሰደውን የአንድ ወገን ተኩስ የማቆም እርምጃ ለሕዝብ ጥሩ የጥሞና ጊዜ የፈጠረ መሆኑን አምኖ ሲደግፍ ቆይቷል። ይሁን እንጂ ከአፈጣጠሩ የተጣመመው ህወሓት ለሕዝብ ጥቅም ተብሎ ለተደረገው ጥሪ ቦታ እንደሌለዉ በግልፅ አሳይቷል። ዛሬም እንደ ትናንቱ በአሮጌ የፖለቲካ እይታ ተሞልቶ የጦርነት ነጋሪት እየጎሰመ ይገኛል።
የህወሓት የፖለቲካ ፅንሰ-ሐሳብ ሕዝብን እንደ ጠላት በመፈረጅ ላይ ያተኮረ ነው። የግጭት መነሻ የአንድነት ፀርና ለሀገራዊ ብሔርተኝነት መውደቅ ምክንያት ሆኗል።
የህወሓት ፀረ አንድነት ፈንጂ በየቀኑ እየፈነዳ ለዜጎች ሞትና ስቃይ ምክንያት በመሆን ዓመታትን አስቆጥሯል። የድህነትና የኋላ ቀርነትን እሽክርክሪት ዘመን አራዝሞብናል። ለእድገታችንና የብልፅግና ጉዞ እንቅፋት በመሆን እንድንሸማቀቅ አርጎናል። በዚህ ሁኔታ ዉስጥ ሀገርና ሕዝብ በቀዳሚነት እየተጎዱ ነው።
አሸባሪው ህወሓት ‘እታገልላቸዋለሁ’ ብሎ የሚናገረውና በስማቸው እየኖረ ያለውን የትግራዋይ ሕዝብን ጨምሮ አስቦላቸው ወይም ተቆርቁሮላቸው አያውቅም። ይህ ቡድን ትናንት የሓውዜን ሕዝብ በሚገበያይበት ቦታ ላይ ቦምብ በማዝነብ የጅምላ ጭፍጨፋ ሲፈፅም ለፕሮፖጋንዳ ግብአትነት እንጂ ለሉአላዊነት ትግል አልነበረም። ሕዝብን በመጨፍጨፍ ሕዝብን ነፃ ማውጣት በየትኛውም መስፈርት የሚታረቅ አስተሳሰብ አይደለም።
ዛሬም ቢሆን በተባበሩት መንግሥታት የወጣውን የሕፃናት መብት ድንጋጌ በመጣስ ጨቅላ ሕፃናትን ለጦርነት ከፊት አሰልፈው በመማገድ ላይ ይገኛል። አዛውንቶችን፣ እናቶችን እና የሀይማኖት አባቶችን እንደ ጋሻ ከፊት በማሰለፍ በእልቂታቸው የጀግንነት አክሊል ለመድፋት ይሞክራል። አሁንም ቢሆን አሸባሪው ህወሓት የፌደራል መንግሥት ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን ካሳየው ፍላጎት በተቃራኒ በመሄድ ላይ ይገኛል። በፌደራል መንግሥት የታወጀው የተናጠል የተኩስ አቁም ስምምነት አርሶአደሩ በክረምት ወቅት ተረጋግቶ እንዲያርስ፣ ለዜጎች እርዳታ እንዲደርስና ግጭት እንዳይባባስ ቢሆንም፥ ህወሓት የተፈጠረበትን የጥፋት ስሜትና እጅ መቆጣጠር አልቻለም።
የ1967ቱ ህወሓት ማኒፌስቶ ሕዝብና ሕዝብን በማጋጨት ሰላምና መረጋጋትን ለመንፈግ የተወጠነ ነበር። ለኢትዮጵያ ግንባታ ቋሚና ማገር በመሆን ለዛሬ ያደረሳትን ሕዝብ ለመበታተን ያለመ ነው።
አሸባሪው ህወሓት ላለፉት 27 ዓመታት ሀገር ሲመራ በነበረበት ወቅት በሕዝብ ውስጥ ትቶት ያለፈው ሰቆቃ ሳያንስ፥ ዛሬም በሀገር ላይ የጭካኔ ተግባራትን እየፈፀመ ነው። ሕወሓት በማይካድራ የፈፀመው የዘር ማጥፋት ተግባር በብሔር ላይ ያተኮረ የሕዝብ ጠላትነት ላይ የተመሠረተ እኩይ ተግባር ነው። አሁንም በተደጋጋሚ ተመሳሳይ ድርጊት ለመፈፀም ሲቅበዘበዝ ይታያል።
የሕወሓት ኃይል የሕዝብና የሀገር ጥቅምን አሳልፎ ከመስጠት አይመለስም። እድገታችንንና ልማታችንን ለመግታት ከሚታገሉ የውስጥና ውጪ ጠላቶች ጋር በማበር የጥፋትና የማፍረስ ሴራዎችን በዋና ተዋናይነት ሲፈፅም እንደነበረ በገሀድ ታይቷል። አሸባሪው ህወሓት ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከማስተጓጎል ጀምሮ ከነአካቴው እስከ ማደናቀፍ ድረስ የተላላኪነት እና የባንዳነት ትወና ድርሻውን ተወጥቷል።
የአሸባሪው ህወሓት ክህደት በሕዝብ ንቀት ብቻ የተገታ አልነበረም፤ የሀገር ሉዓላዊነትን ጭምር ጥያቄ ውስጥ እስኪገባ አስነዋሪ ተግባር ፈጽሟል። ኢትዮጵያ ብትፈርስም፣ በውጪ ወራሪ ብትወረርም ደንታ እንደሌለው እስከ መግለፅ ደርሷል።
ስለሆነም ህወሓት ለአንዱ የሚያስብ፣ ሌላውን የሚነፍግ ሳይሆን በጅምላ የመጨፍጨፍ እና የማፈራረስ አቅጣጫን ይከተላል። ከእሱ ተወልዶ፣ ከእጁ በልቶ ላደገዉ ሕዝብ የማይራራ፣ ሌላ ዘመድ ሊኖረውም ሆነ ሊያፈቅር አይችልም። “ጅግራ ዘመድ መስሎ ወፊቱን በላት” እንደሚባለው ሁሉ፥ ለአንዱ አዝኖ፣ ሌላውን አኩርፎ፣ ሌሎችን ደግሞ የተጸየፈ መስሎ የሚቀርበውን ፕሮፖጋንዳ አምኖ መቀበል ሞኝነት ነው።
የአሸባሪው ህወሓት ኃይል ተሸንፏል፤ በፖለቲካ ሜዳው አሸናፊ ሀሳብ ማቅረብ ተስኖት ለቆ ስደትን መርጧል። በማግስቱ የጦርነት ነጋሪትን መጎሰም ጀመረ። ውሎ ሳያድር በዜጎቻ ላብ የተገዛውን የሀገር ሉዓላዊነት የሚጠበቅበት መሣርያ በመዝረፍ ኢትዮጵያን ለማንበርከክ ዛተ። በከሀዲዎችና የውጪ ኃይሎች ማበረታቻ የሰከረው ሕወሓት በመከላከያ ሠራዊቱ ለይ የጥቃት እርምጃ ወሰደ። ከትግራይ ሕዝብ ጋር ከ20 ዓመታት በላይ የኖረውን የመከላከያ ሠራዊት በከባድ የጭነት መኪናዎች ከመጨፍለቅ ጀምሮ እጅግ አስነዋሪ እርምጃዎችን ወስዷል።
የክልልና የሀገራችን ሕዝብ በመከላከያ ሠራዊታችን ላይ የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ መከላከያ ሠራዊቱን ለመደገፍ ሁሉ አቀፍ ድርሻውን ተወጥቷል። ዛሬም ቢሆን የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትና ሕዝብ የሀገር ሉዓላዊነት ጋሻ ከሆነው የመከላከያ ሠራዊታችን ጎን በመሆን ማናቸዉንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነው። መንግሥትም የሕዝብ ተሳትፎን በማቀናጀት ሁለንተናዊ ስኬት ለማስመዝገብ ያላሰለሰ ጥረት ያደርጋል።
ትናንት በችግር ውስጥ የመንግሥትን ጥሪን በመስማት ሁለንተናዊ ድርሻችሁን የተወጣችሁና የአሸባሪዎች የጥፋት መርዝ እንዲደፋ ያደረጋችሁ የክልላችን የኅብረተሰብ ክፍሎች ዛሬም እንደ ትናንቱ የጎላ ተሳትፎአችሁን እንድታበረክቱ መንግሥት ጥሪውን ያቀርባል።
በሕዝባችን የተባበረ ክንድ ዘላቂ ሉዓላዊነታችን ይረጋገጣል!!
የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት
ሐምሌ 2013
ፊንፊኔJuly 14, 2021 at 3:48 am #19914In reply to: የፖለቲካ ፓርቲዎች ድምጽ (ኢትዮጵያ ውስጥ የሚነቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች)
AnonymousInactive“የሕዝባችንን ህልውና ከጠላት ጥቃት የምንታደግበት የታሪክ መድረክ ላይ ስለምንገኝ ከመቼውም ጊዜ በላይ ልዩነታችንን ወደጎን በመተው የሕዝባችንን አንድነት ጠብቀን በጋራ እንድንረባረብ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ጥሪውን ያቀርባል።”
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ የሰጠው መግለጫ
“አንድነታችንን ጠብቀን ያጋጠመንን የህልውና አደጋ በትግላችን እንቀለብሰዋለን”የኢትዮጵያና የአማራ ሕዝብ ጠላት የሆነው ትህነግ ወያኔ እንደሀገር ባደረሰብን ህልቆ መሳፍርት የሌለው ግፍና በደል እንዲሁም ለፈጸመብን ሀገራዊና ሕዝባዊ ክህደት የሀገራችንን የግዛት አንድነት በመሸርሸር ሉአላዊነቷ የማይከበር፣ ራሷን ችላ መቆም የማትችልና በሁሉም መስክ ተንበርካኪ ሀገር ባለቤቶች እንድንሆን በርካታ ደባ ፈጽሞብናል። በዓለም አደባባይ የምንኮራበት ሀገራዊና ሕዝባዊ የጋራ ታሪክ ባህልና እሴት እንዳይኖረን አንድነታችንንና አብሮነታችንን በፈጠራ ታሪክ እየቦረቦረ እርቃናችንን እንድንቀር፣ አንዳችን ለሌላችን ጋሻና መከታ መሆን ሲገባን እርስ በእርስ በመጠራጠር አውሎ ነፋስ ወዲያና ወዲህ እንድንላጋና በጠላትነት እንድንፈራረጅ ከሰማይ በታች ያልፈጸመብን ግፍ የለም።
ከሁሉም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ጋር ተባብረንና ተፈቃቅደን የጸረ ጭቆና ትግሉን አንድ ብለን ስንጀምር በጋራ ያነሳነው የፍትህና የእኩል ተጠቃሚነት ጥያቄ በትህነግ መንደር የቱን ያህል መራር የሆነ የመደፈር ስሜት እንደፈጠረ የቅርብ ጊዜ ክስተት ነው። አሸባሪው ትህነግ ከመንበረ ስልጣኑ ተምዘግዝጎ ሲወድቅና መቀሌ ሲከትም የነበረው ብቸኛ ምክንያት ዓይናችሁን ጨፍኑና ላሞኛችሁ የሚል ፖለቲካዊ ቁማር እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም። በውህድ ፓርቲ ደረጃ የተፈጠረውን አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ አደረጃጀት የአሃዳውያን ውጤት አድርጎ ያበሻቀጠው ፍላጎቱ በለመደው የአድራጊ ፈጣሪና የአዛዥነት ሚና ያልተሳተፈበትን መዋቅር ለማጣጣል ከማለም ባሻገር፥ ለኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች እኩል ተጠቃሚነት ባለው ከፍ ያለ ንቀትና ጥላቻ ምክንያት መሆኑ ለሁሉም ግልጽ ነው።
ይህንን ተከትሎ በትግራይ ክልል የሰሜን ዕዝ እንዳይንቀሳቀስ በተደጋጋሚ ያደረገው ሙከራ የልብ ልብ ሰጥቶት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ውድ ልጆችን በግፍ ያለርህራሄ አሰቃቂ ግድያ ከፈጸመባቸው በኋላ የዕዙን ጠቅላላ ንብረት በመውረስ በመላው ኢትዮጵያውያን ላይ ጦርነት ማወጁ ይታወቃል። የአማራ ክልልን ወሰን ጥሶ በማለፍ ጥቃት ለመፈጸም ያደረገው ጥረት ባይሳካለትም በማይካድራ ንጹሀን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ላይ የፈጸመው አረመኔያዊ የጅምላ ጭፍጨፋ የሚዘነጋ አይደለም። ይህንን ተከትሎም መንግሥት በየደረጃው የሕግ የበላይነት ለማስከበር ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን አከናውኗል። በሂደቱም በርካታ ውጤቶች መመዝገባቸው የሚዘነጋ አይደለም። ይሁን እንጂ ይህ አረመኔና አሸባሪ ቡድን ዓይኑን በጨው አጥቦ ጥቃት የተፈጸመበት በማስመሰል ዓለምአቀፉን ማኅበረሰብ በተደጋጋሚ በማጭበርበር ላይ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት በአንድ ወገን የወሰደውን የተኩስ አቁም ውሳኔ እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም በኢትዮጵያና በአማራ ክልል ሕዝብ ላይ መሠረተ ሰፊ የሆነ ወረራና ጥቃት ማድረግ ጀምሯል። ይህ አሸባሪ ቡድን የጀመረብንን ግልጽ ወረራ ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሚያወግዘውና የምንጊዜም አጋርነቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ፍጹም ጥርጣሬ የለንም። በዚህ አጋጣሚ የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ በግልጽ እንደሚያውቀው የአማራ ክልልና ሕዝብ የዚህ አሸባሪ ቡድን ቀጥተኛና የቅርብ ተጠቂ መሆኑን ነው። ስለሆነም ትግላችን ለሕዝባችን ህልውናና ለሀገር ሉአላዊነት መሆኑ ግንዛቤ ውስጥ ገብቶ የጋራ ጠላታችንን በጋራ እንድንፋለመው የአጋርነት ጥሪያችንን እናቀርባለን።
አሸባሪው የትህነግ ቡድን ከአማራ ክልል ጋር በሚያዋስኑት ሁሉም አቅጣጫዎች መጠነ ሰፊ ወረራና ጥቃት እየፈጸመ የሚገኝ አረመኔና ጨካኝ ቡድን መሆኑ እንዲታወቅና ሁሉም የአማራ ክልል ሕዝብ ጉዳዩን ከህልውናው ጋር በማስተሳሰር እንዲመለከተውና ከዚህ ጨካኝና አረመኔ ቡድን ጋር ቀጣይ የምናደርገው ሁሉ አቀፍ ትግል የህልውና ትግል መሆኑን አውቆ በገንዘብ፣ በጉልበትና በህይወት መስዋዕትነት አስፈላጊውን አበርክቶ ለማድረግ ራሱን እንዲያዘጋጅና የመንግሥትን ጥሪ እንዲጠባበቅ የክልሉ መንግሥት ጥሪውን ያቀርባል።
አሸባሪው ትህነግ የትግራይን ሕዝብ ከህጻን እስከአዋቂ በማንቀሳቀስ ዓለም አቀፍ የጦርነት ሕግጋትን በመቃረን ሕጻናትንና ሴቶችን በጅምላ ጦርነት እየማገደና ያለ የሌለውን አቅሙን ተጠቅሞ ክልላችን ላይ ወረራ የፈጸመ ሲሆን፥ በተለይም ለዘመናት የአማራ ሕዝብ የማንነትና የወሰን ጥያቄ እያነሳ ሲታገልባቸው የቆዩ የራያ፣ አላማጣና ኮረም አካባቢዎችን ዳግም በመውረር እንዲሁም ወልቃይት ጠገዴ ሴቲት ሁመራ በኃይል ለመያዝ በተለይም ጠለምትና አካባቢውን ለመያዝ አሁናዊ ሙከራ የጀመረ መሆኑ በአካባቢው የሚኖሩ አማራዎችንና የአማራ ክልል ተወላጆችን ፈጽሞ የማጥፋት ህልሙን እውን ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። ስለሆነም ይህንን አረመኔያዊ ድርጊትና ዳግም ወረራ የክልሉ መንግሥት በፍጹም የማይቀበለውና በጀመርነው የህልውና ትግል ተፈጥሯዊና ታሪካዊ መብታችንን የምናረጋግጥ መሆኑን አበክረን እንገልጻለን።
ስለሆነም፡-
1ኛ. በየግንባሩ የምትገኙ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት፣ የክልላችን ልዩ ኃይልና የሚሊሻ አባላት፣ ሕዝባዊ ፖሊስና ሰላም አስከባሪ አባላት እንዲሁም ሀገርና ሕዝብን ለማዳን የተግባር እንቅስቃሴ እያደረጋችሁ የምትገኙ የየክልሉ የጸጥታ አካላት፥ በዚህ ታሪካዊ መድረክ ከጠላት ጋር ፊት ለፊት በመግጠም ለሀገራችሁ ሉአላዊነትና ለሕዝባችሁ ህልውና የምትከፍሉትን ክቡር መስዋዕትነት ታሪክ ምንጊዜም ሲያስታውሰው ይኖራል። በቀጣይም የተሰጣችሁን ሕዝባዊና ሀገራዊ ተልዕኮ በጽናትና በቁርጠኝነት እንደምትወጡ እምነታችን የጸና ነው። ስለሆነም፥ መላው የኢትዮጵያና የአማራ ሕዝብ ከጎናችሁ መሆኑን አውቃችሁ በጀግንነት ታሪካዊ ጠላታችንን በመደምሰስ ለሀገራችሁ ዳግም የኩራት ምንጭ እንድትሆኑ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
2ኛ. መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በትህነግ ወያኔ ላይ የተጀመረው ሕግን የማስከበር ትግል ተጠናክሮ እንዲቀጥል አስፈላጊውን እርብርብ ሁሉ ማድረግ አለበት ብለን እናምናለን። አሸባሪው ትህነግ ሀገር ከማፍረስ እኩይ ተልዕኮው ሊታቀብ የሚችለው የሀገራችንን ሉአላዊነትና የግዛት አንድነት በጽናትና በአላማ ቁርጠኝነት በጋራ መጠበቅ ስንችል ስለሆነ በዚህ ታሪካዊ መድረክ ላይ በጋራ እንድንቆም የአክብሮት ጥሪያችንን እናቀርባለን።
3ኛ. በየትኛውም ዘመን ሰልጥናችሁ፣ የሀገርና የሕዝብ ሉአላዊነት ለማስከበር በማንኛውም የመንግሥት ጸጥታ መዋቅር ውስጥ ተሰልፋችሁ ስታገለግሉ የቆያችሁና በታሪክ አጋጣሚ የሙያ ዘርፍ የቀየራችሁ የክልላችን ነዋሪዎች፥ ለህልውናችን የምናደርገውን የትግል ጥሪ ተቀብላችሁ በክልሉ ጸጥታ መዋቅር ውስጥ እንድትቀላቀሉ ጥሪያችንን እያቀረብን ከዛሬ ጀምሮ በየአካባቢያችሁ ሰላምና ደህንነት ጽሕፈት ቤት በአካል ተገኝታችሁ በፈቃደኝነት እንድትመዘገቡ ለማሳሰብ እንወዳለን።
4ኛ. መላው የክልላችን ወጣቶች፥ ከፊት ለፊታችን የተደቀነብንን የህልውና አደጋ ያለበቂ ዝግጅትና ደረጃውን ከጠበቀ ስልጠና ውጭ የምንጋፈጠው አይደለም። ስለሆነም ከማንኛውም ግብታዊ እንቅስቃሴ ታቅባችሁ በየደረጃው ለሚኖረው ምልመላና ስልጠና በመሳተፍ በቂ ዝግጅት አድርጋችሁ የመንግሥትን ጥሪ እንድትጠባበቁ እናሳስባለን።
5ኛ. መላው የክልላችን ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሲቪክና የሙያ ማህበራት፣ ማኅበራዊ አንቂዎችና የሚዲያ ባለሙያዎች፥ የጀመርነው የህልውና ትግል የሁላችንንም አንድነት፣ ኅብረትና ተቀራርቦ መሥራት የሚጠይቅ ነው። በሩቅ ሆኖ ስህተት በመፈለግና እርስ በእርስ በመነቋቆር ከጠላት መንጋጋ ፈልቅቀን የምንታደገው አንዳችም ህልውና የለንም። በቂ መረጃ ባገኘንበትም፣ ባላገኘንበትም ጉዳይ ላይ ተሳፍረን በተለያዩ አቅጣጫዎች መክነፍ ለጠላቶቻችን ተጨማሪ ጉልበት ከመሆን ባለፈ ለሕዝባችን የሚሰጠው ጥቅም የለም። ስለሆነም የጋራ ዕጣ ፋንታችንን በጋራ ጥረት የምናስከብርበትና አደጋ የተጋረጠበትን የሕዝባችንን ህልውና ከጠላት ጥቃት የምንታደግበት የታሪክ መድረክ ላይ ስለምንገኝ ከመቼውም ጊዜ በላይ ልዩነታችንን ወደጎን በመተው የሕዝባችንን አንድነት ጠብቀን በጋራ እንድንረባረብ የክልሉ መንግሥት ጥሪውን ያቀርባል።
6ኛ. መላው የክልላችን ሕዝብ፣ በከተማና በገጠር የምትኖሩ የክልላችን ነዋሪዎች፣ በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ የምትገኙ ምሁራንና የክልላችን ተወላጆች፣ በተለያየ ሙያ ተሰማርታችሁ ሀገርና ሕዝብ በማገልገል ላይ የምትገኙ የክልላችን ነዋሪዎችና ባለሀብቶች፥ የጀመርነውን የህልውና ትግል በማገዝ የትግል ሂደት አዎንታዊ ሚናችሁን እንድትወጡ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
በመጨረሻም የጀመርነው ትግል እልህ አስጨራሽ በጣም መራርና ረዥም ጊዜ የሚጠይቅ እንደሚሆን ይጠበቃል። የፈጀውን ጊዜ ይፍጅ የእኛ አንድ መሆንና ለጋራ ግብ በጋራ መተባበር በመድረኩ አሸናፊ ሆነን እንደምንወጣ ያለምንም ጥርጥር ልናረጋግጥልችሁ እንወዳለን። ሁልጊዜም ቢሆን የአማራ ክልል ሕዝብ ትግል ከኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የጋራ ተጠቃሚነት ውጭ እንደማይሳካ ጠንቅቀን እናውቃለን። የምናደርገው ትግል ለሀገራችን ሉአላዊነት መከበርና የጭቁን ሕዝባችን የህልውና ትግል እንጂ እላፊ ጥቅም ለማግኘት የምናደርው ትግል በፍጹም አይደለም።
የአማራ ሕዝብ ከፉክክር ይልቅ ትብብርን ከእብሪት ይልቅ ድርድርን የሚያስቀድም፣ ‘በፍትህ ከሄደች በቅሎየ፥ ያለፍትህ ያጣኋት ጭብጦየ’ ትቆረቁረኛለች ብሎ የሚያምን ሕዝብ ነው። ስለሆነም ዛሬ የምናደርገው ትግል ለልጅ ልጆቻችን የምናወርሰው የኩራትና የክብር ምንጭ እንደሚሆን አንጠራጠርም። የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት የወሰደው ተናጠላዊ የተኩስ አቁም ውሳኔን ተከትሎ የጠላት ኃይል ሀገርና ሕዝብ ለማዋረድ የሚያደርገውን እብሪተኛ እንቅስቃሴ መሠረት በማድረግ በጠላት ላይ የማያዳግም እርምጃ እንዲወስድ በአጽንኦት እናሳስባለን።
ትግላችን ለህልውናችን !
ሐምሌ 6 ቀን 2013 ዓ.ም.
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትJuly 10, 2021 at 5:19 pm #19894AnonymousInactive“በዚህ ሀገራዊ ምርጫ የፈጠርነው አሸናፊና ተሸናፊን ሳይሆን፣ ጠያቂና ተጠያቂ ያላበት የዲሞክራሲ ሥርዓትን ነው። በዚህ ደግሞ ያሸነፉት በምርጫው የተሳተፉት ሁሉም አካላት ናቸው።” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ስድስተኛው የስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ውጤትን ያስተላለፉት መልዕክት
የተከበራችሁ ኢትዮጵያውያን እና ኢትዮጵያውያት፥
ላለፈው ግማሽ ክፍለ ዘመናት፣ የሀገራችን ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ በነጻ ፈቃዱ የመረጠው መንግሥት እንዲኖረው ብዙ ሙከራዎች ሲደረጉ ቢቆዩም፤ በተለያዩ ምክንያቶች ሲሰናከሉ ነበር። በሂደቱ አያሌ ተማሪዎችና ወጣቶች፣ ገበሬዎችና የቤት እመቤቶች፣ ምሁራንና መለዮ ለባሾች፣ መላው የሀገራችን ሕዝብ ከፍተኛ ዋጋ ከፍሏል። ካለፈ ልምዳችንና ባልተሳኩ ጉዞዎች ጠባሳ ሰበብ፣ የአሁኑም ምርጫ ዴሞክራሲያዊነቱ ተጠብቆ ባይጠናቀቅስ በሚል ስጋት፣ ያለፉትን ወራት እንደ ሀገር በፍርሃት ተወጥረን መክረማችን ሊካድ አይችልም። ኢትጵያውያን ግን ጨዋ ብቻ ሳይሆኑ አርቆ አሳቢ መሆናቸውን ዛሬም አስመስክረዋል። የተሰጋውን ሳይሆን የሚፈልጉትን ማድረግ እንደሚችሉ በግብር አሳይተዋል። ዝናብና ፀሐይ ሳይገድባቸው፣ በረጃጅም ሰልፎች ሳይሰለቹ፣ እስከ እኩለ ሌሊት ታግሰው ፍላጎታቸውን በካርዳቸው ገልጸዋል። እንደ እኛ እምነትም በዚህ ምርጫ አሸናፊ የሆነው ሕዝባችን ነው። ከሕዝባችን በመቀጠል፣ በብዙ ውሱንነቶች ውስጥ አልፈው በዲሞክራሲና በሕዝብ ድምፅ ላይ ባላቸው ጽኑ እምነት፣ ሀሳብና ፖሊሲያቸውን ለሕዝብ አቅርበው ብርቱ ውድድር ያደረጉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የዴሞክራሲያዊ ሂደቱ ድል አድራጊዎች ናቸው።
ይህንን ምርጫ ልዩና ታሪካዊ የሚያደርጉት ብዙ ጉዳዮች አሉ። በታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ ከተጽዕኖዎች በተላቀቀ የምርጫ ቦርድ ዳኝነት ያደረግነው ምርጫ መሆኑ አንደኛው ነው። የምርጫ ቦርድ ዳኝነት እንዲሳካ ደግሞ ቁጥራቸው የበዙ የግልና የመንግሥት ሚዲያዎች፣ የሲቪል ተቋማት፣ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን፣ ፍርድ ቤቶችና ሌሎችም ተቋማት በግልጽ የተከታተሉት መሆኑ ሂደቱን ከመቼም ጊዜ በላይ ተአማኒና ዲሞክራሲያዊነቱ የተጠበቀ ምርጫ ያደርገዋል። ምርጫው ዴሞክራሲን የመትከል ግባችንን አንድ እርምጃ ያስኬደ በመሆኑ፣ ፓርቲያችን ከምንም በላይ ቀዳሚ ድሉ አድርጎ ይቆጥረዋል። በታሪካዊው ምርጫ ተሳታፊ መሆን በራሱ የሚፈጥረው ደስታ እንዳለ ሆኖ፣ ፓርቲያችን በሕዝብ ይሁንታ አግኝቶ ሀገር ለማስተዳደር መመረጡ አስደስቶናል። በውጤቱም ከአሸናፊነት ይልቅ ኃላፊነት፣ ከድል አድራጊነት ይልቅ ታላቅ የሆነ ሀገራዊ አደራ እንዲያድርብን አድርጎናል።
መንግሥት የሚመሠረተው በሕዝብ በተመረጡ ፓርቲዎች ቢሆንም ሀገርን መምራትና ማስተዳደር ግን ለተመረጡ ፓርቲዎችና መሪዎች ብቻ የሚተው አይደለም። ተፎካካሪ ፓርቲዎችና መሪዎቻቸውም እስከሚቀጥለው ምርጫ በመንግስት አስተዳድርና ሕዝብን በማገልገል ሂደት ውስጥ ሚናቸው ሰፊ ሊሆን እንደሚገባ ለማስታወስ እወዳለሁ። በቀጣይ ወራት ብልጽግና በሚመሠርተው መንግሥት ውስጥ በአስፈጻሚው አካልም ሆነ በፍርድ ቤቶች፣ በሌሎችም የፌደራልና የክልል ተቋማት ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው፣ በዘንድሮው ምርጫ በኃላፊነትና በብቃት የተወዳደሩ የሕዝብ አለኝቶችን ከዚህ በፊት ካደረግነው በእጅጉ ከፍ ባለና አዎንታዊ ለውጥ በሚፈጥር መልኩ እንደምናካትታቸው ለመግለጽ እወዳለሁ። በተጨማሪም እስከሚቀጥለው ምርጫ የበለጠ ተጠናክረውና ተቋማዊ አቅማቸው ደርጅቶ ብርቱ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ ከማድረግ ወደ ኋላ አንልም። በዚህ ምርጫ የፈጠርነው አሸናፊና ተሸናፊን ሳይሆን፣ ጠያቂና ተጠያቂ ያላበት የዲሞክራሲ ሥርዓትን ነው። በዚህ ደግሞ ያሸነፉት በምርጫው የተሳተፉት ሁሉም አካላት ናቸው።
ውድ የኢትዮጵያ ልጆች፥
በምርጫ ካርዳችሁ ስትመርጡን በዕቅድና በፖሊሲ የያዝናቸውን የብልጽግና ግቦች እንድናሳካ የድፍረትና የጥንካሬ ስንቅ እንደሚያቀብለን ሁሉ፣ እኛና እናንተን ያስተሳሰረው ቃል ኪዳን ተጠብቆ እንዲቆይ ነገሮች አልጋ በአልጋ እንደማይሆኑን እንገነዘባለን። ቢሆንም ግን ከመቼውም ጊዜ በላይ ትከሻችንን አስፍተን፣ ኢትዮጵያን ከሚወዱ አካላት ጋር ሁሉ በትብብር ዐቅማችን አማጥጠን ለመሥራት ቆርጠን እንደተነሣን ሳበስራችሁ ደስ እያለኝ ነው። በቀጣይ ዓመታት ሀገራችን በእውነትም በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ከፍ የምትልበት ዘመን ይሆናል። ይህ እንዲሳካ የሐሳብና የሞራል ስንቅ እንደምታቀብሉን፣ መንገድ ስንስት እንደምትመልሱን፣ ስናጠፋም እንደምታርሙን ተስፋ በማድረግ ነው።
በሀገራችን ሁለንተናዊ ብልጽግና እውን እንዲሆን በቀጣዩ አምስት ዓመት ፈር ጠራጊ እንሆናለን የምንለው፣ በዙሪያችን ባሉና ብልጽግና በሚቀላጠፍባቸው አራት ማዕዘኖች መሐል ቆመን ነው። የመጀመሪያው ማዕዘናችን የመሠረተ ልማት ግንባታ ሲሆን፥ ሀገራችን እንድትበለጽግ በኢኮኖሚውም ሆነ በማኅበራዊና ፖለቲካ ዘርፎች ዘላቂ መሠረት የሚሆኑ፣ በፍጥነት የሚጠናቀቁ፣ ጥራታቸው የተጠበቁ፣ ከብክነት ነጻ የሆኑ እና የምንፈጥራቸውን ተቋማት መሸከም የሚችሉ ትውልድ ተሻጋሪ መሠረተ ልማቶችን መገንባታችንን እንቀጥላለን። ጥቂትም ቢሆኑ ባለፉት 3 ዓመታት አመርቂ ሥራዎችን ለመሥራታችን ምስክሮቹ እናንተው ናችሁ።
ሁለተኛው ማዕዘናችን የተቋማት ግንባታ ሲሆን፣ በጥቂት ግለሰቦችና ነጠላ ተቋማት ላይ ከማተኮር ባለፈ ሀገራችንን በጽኑ መሠረት ላይ የሚያቆሙ ጠንካራ ተቋማት ያስፈልጉናል። ዘመን ተሻጋሪ ሥርዓት ለማጽናት የሚስችሉ ገለልተኛና ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ዜጋ የሚያገለግሉ ተቋማትን መገንባት ላይ ትኩረት ይደረጋል። ይሄ ማሕቀፍ ከፌደራል እስከ ክልል የሚገኙ ተቋማትን የሚያካትት ይሆናል።
በሦስተኛ ደረጃ እንደ ሀገር የሚያስተሳስሩን የጋራ አመለካከቶችና የጋራ ትርክቶች ላይ ትኩረት ሰጥተን ልንሠራባቸው ይገባል። እርስ በእርስ የሚቃረኑና የሚጠፋፉ ትርክቶች ምን ያህል ለጠላቶቻችን ተመችቷቸው እኛን ደካማ እንዳደረገን ያሳለፍናቸው ዓመታት ሕያው ምስክሮች ናቸው። ስለዚህ ክፍተቶቻችንን በሚደፍን መልኩ ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገር አጠንክረው በሚያቆሙን እሴቶች ላይ የተመሰረተ፣ ገዢና ሁላችንንም አሸናፊ የሚያደርግ ትርክት ለመገንባት ጠንክረን እንሠራለን።
በአራተኛ ደረጃ የሞራል ልዕልናና ግብረገባዊነት ተመጣጣኝ ትኩረት አግኝተው እስካልተሠራባቸው ድረስ በሀገራችን ኃላፊነት የሚሰማቸው ዜጎች ቁጥር እየቀነሰ፣ በተቃራኒው ኢ-ሞራላዊ ድርጊቶች እየተስፋፉ እንዲመጡ በር ይከፍታል። ይኼንን ችግር የመቅረፍ ኃላፊነት መንግሥትና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ላይ ብቻ የሚጣል ሳይሆን፣ ከግልና ከቤተሰብ ጀምሮ የሚሠራ ሥራ ነው። ሁሉም አካላት ተረባርቦ ሀገርና ትውልዱን እያቆሸሹ ያሉ መጥፎ ተግባሮችን ጠርጎ ሊጥላቸው ይገባል። በቀጣይ ዓመታት በሞራል ንጽህና የተገነቡ ተቋማትንና መሪዎችን አንጥረን የምናወጣበት እንዲሆን ተስፋ አደርጋለሁ።
ውድ የሀገሬ ዜጎች፥
ባለፉት ሦስት ዓመታት በከፍተኛ ጥንቃቄ የቀረጽነው የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ ለተግባራዊነቱ በጋራ ከተጋን ያለ ጥርጥር ቀጣዩቹ ዓመታት ለሀገራችን ብልጽግና እንደ ወሳኝ የመታጠፊያ ኩርባ ይሆናል። ዕምቅ ዐቅሞቻችን ምንድን ናቸው? ምን ዓይነት የመበልጸግ ዕድል እጃችን ላይ አለ? ምን ብናደርግ ኢኮኖሚያችን መዋቅራዊ ለውጥ ያመጣል? የሚሉትን በሚገባ ፈትሸን ያረቀቅነው ዕቅድ ነው።
በሀገራችን ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ለነገ የማይባል ጉዳይ ነው። በፍጥነት የምግብ ፍላጎታችንን በማሟላት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከውጭ የምግብ ድጎማ መላቀቅ አለብን። ምግብ ለእኛ ቅንጦት መሆን አይገባም። ጠግቦ መብላት ቅንጦት የሆነበት ሕዝባችንን መርጦ መብላት እንዲጀምር ለማድረግ ቆርጠን መነሳት አለብን። በብዝኃ ዕጽዋትና በብዝኃ እንስሳት የምትታወቅ ሀገራችን የእንስሳት ተዋጽዖና ፍራፍሬዎች ለገበታችን ከቅንጦትነት ወደ አዘቦትነት መለወጥ አለባቸው። ዶሮና ዕንቁላል፣ ወተትና ቅቤ፣ ተርፎን ለገበያ የምናቀርባቸው እንጂ ለዓመት በዓል አይተናቸው የሚሰወሩ የሩቅ እንግዳ መሆናቸው ሊያከትም ይገባል።
እዚህ ጋር አንድ መታወቅ ያለበት ሀቅ አለ። መንግስትና ሕዝብ እጅና ጓንት ሆነው እስካልሠሩ ድረስ ሕልማችን ይሳካል ማለት ዘበት ነው። በቀጣይ 5 ዓመታት ተባብረን በተለይ በግብርናው ዘርፍ ምርታማነት ለማሳደግ ጠንክረን መስራት አለብን። ከዚህ ቀደም ጀምረናቸው ውጤት እያመጡ ያሉ ተግባራት አሉ። የበጋ ሰብሎችና ፍራፍሬዎች ላይ ለውጥ ለማምጣት ከተጀመሩ አነስተኛ መስኖዎች ባለፈ፣ ዝናብ አጠርነት ለመዋጋት በቴክኖሎጂ አማካኝነት ደመናን ወደ ዝናብ የመቀየር ልምምዳችን እያደገ ይገኛል። በቅርቡም ምርትን የሚያሳድጉ ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅመን ችግሮቻችንን ወደ ዕድል መቀየር ጀምረናል።
አየር ንብረታችንን የሚያስተካክለውና የብዝኃ ዕጽዋትና የብዝኃ እንስሳት ሀብታችንን በእጅጉ ያሳድጋል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብራችን እንዲሁ ተጠቃሽ ነው። በቁጥር ግንባር ቀደም ያደረጉን የቀንድ ከብቶቻችን ከመቀንጨር ወጥተው ምርታማ እንዲሆኑ ያደርጋል። ወደየጎረቤት ሀገሩ የሸሹ የዱር አራዊትም ተመልሰው፣ ከታሪካዊና ባህላዊ መስህቦች ጋር የተዋደደ ተፈጥሮአዊ መስህብ በመሆን የቱሪስት ፍስትን እንዲጨምርና ኢኮኖሚያችን መስፈንጠር እንዲችል መደላድል ይሆናል ብዬ አምናለሁ።
የሀገራችን ሕዝብ ሆይ፥
ባለፉት ጥቂት ዓመታት ትኩረታችንን ሰቅዘው ከያዙት ጉዳዮች መካከል ሌላኛው የሕዳሴ ግድብን የተመለከተ ጉዳይ ነው። የዴሞክራሲ ጥያቄን አንድ ምዕራፍ ለማሳደግ የምርጫችን መሳካት ወሳኝ እንደነበረው ሁሉ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ችግራችንን ለመቅረፍና ለዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች መቀላጠፍ ጉልህ አስተዋጽዖ ከሚያበረክቱ ፕሮጀክቶቻችን መካከል አንዱና ወሳኙ የሕዳሴ ግድብ ግንባታችን እንደሆነ ይታወቃል።
የሕዳሴ ግድብ አጀንዳ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ከግድብም፣ ከኤሌክትሪክ ኃይል ምንጭነትም በላይ ነው። ከኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ባለፈ ዳግም የመነሣታችን ተምሳሌት ነው። በራስ ዐቅም የመቆም፣ በራስ ፍላጎት የመመራት፣ የሉዓላዊነታችን ምልክት፤ የሀገራዊ አንድነታችን ገመድ ነው። በሕዳሴ ጉዳይ ብዙ አይተናል፣ ብዙ ተፈትነንበታል። በራሳችን ዐቅም መቆማችን የሚያስደነግጣቸው፣ በፍላጎታችን መመራት መጀመራችን የሚቆጫቸው ብዙ ጋሬጣዎችን ሲጥሉብን ነበር። “ሚስማር አናቱን ሲመቱት ይበልጥ ይጠብቃል” እንዲሉ ሆኖ፤ በዓባይ ጉዳይ በገፉን ቁጥር እየቆምን፣ በተጫኑን ቁጥር እየበረታን፣ ባዋከቡን ቁጥር ይበልጥ እየጸናን አሁን የደረስንበት ቦታ ላይ ቆመናል። በቅርቡ ሁለተኛውን ዙር የውኃ ሙሌት አድርገን፣ በምርጫው ስኬት የተደሰትነውን ያህል፣ በሕዳሴያችንም ሐሴት እንደምናደርግ አልጠራጠርም።
በሕዳሴ ግድብ ላይ ፍትሐዊ ተጠቃሚነታችን እንዲጠበቅልን እንጂ መቼም ቢሆን ሌሎች ሀገራትን የመጉዳት ፍላጎት ኖሮን አያውቅም። አሁንም ለታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ደግመን ማረጋገጥ የምንፈልገው ሐቅ፣ የዓባይ ወንዝ እንደሚያስተሳስራቸው ወንድም ሕዝቦች በእናንተ ላይ ምንም ዓይነት አሉታዊ ተጽዕኖ የመፍጠር ፍላጎት የለንም። ዛሬም ሆነ ወደፊት በጋራ ተጠቃሚነት ዙሪያ ለመመካከር በራችን ክፍት ነው። እኛንም ሆነ እናንተን ነጥሎ ተጎጂ ወይም ተጠቃሚ በሚያደርጉ አካሄዶች ላይ እንድንሳተፍ ኢትዮጵያዊ ማንነታችን አይፈቅም።
ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያለንም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከዚህ ኢትዮጵያዊ ማንነታችን የሚቀዳ ነው። በጋራ ተጠቃሚነት ዙሪያ ለመሥራት ሁሌም ዝግጁዎች ነን። የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ሰላሙ እንዲጠበቅ፣ የጋራ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ማኅበረሰብ እንዲፈጠር፣ በትብብርና በመግባባት እንድናድግ ኢትዮጵያ ትፈልጋለች፤ ጥሪም ታቀርባለች።
የተከበራችሁ ተፎካካሪ ፓርቲዎች፥
የሀገራችን መጻኢ ጊዜ ብሩህ ለማድረግ በተገቢው መወጣት ከሚገቡን የቤት ሥራዎች መካከል አንዱና ዋነኛው ፖለቲካዊ ጉዳዮቻችንን በሠለጠነ መንገድ መምራት ነው። ከላይ በመግቢያዬ እንደገለጽኩት ይኼ ኃላፊነት በመንግሥትና በተመረጠው ፓርቲ ላይ ብቻ የሚጣል አይደለም፤ አንድ አካል ልሥራው ብሎ ቢነሣ እንኳን በአግባቡ የሚወጣው ጉዳይ እንዳልሆነ በተደጋጋሚ አይተናል። እንኳንስ የሠለጠነ የፖለቲካ ሥርዓት መገንባትን የሚያህል ነገር ይቅርና፣ አንድ ዙር ምርጫን ዴሞክራሲያዊ አድርጎ ለማጠነቀቅ ብዙ አካላት መረባረብ እንዳለባቸው ካለፍናቸው ምርጫዎች በሚገባ ተረድተናል። የዘንድሮውንም ምርጫ ካለ እናንተ ድጋፍና ትብብር ፍትሐዊና ዴሞራሲያዊ በሆነ መንገድ ማከናወን ባልተቻለ ነበር።
በቀጣይም ዓመታት የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሂደታችን መሬት እንዲረግጥ የተለመደ ትብብራችሁና በየምዕራፉ ያላሰለሰ ድጋፋችሁ እንደሚያሻን ከወዲሁ ለመግለጽ እወዳለሁ። በሀገራችን የብልጽግና ጉዞ ውስጥ የሚኖራችሁ ድርሻ ወሳኝ እንደሆነ እናምናለን።
የፖለቲካ ልዩነቶቻችን እንዳሉ ሆነው፣ ለሀገርና ለሕዝባችን በሚጠቅሙ ማናቸውም የፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ አጀንዳዎች ላይ ከእናንተ ጋር በመግባባት ለመሥራት ዝግጁዎች ነን።
ምርጫውን ስኬታማ ያደረጋችሁ ውድ የተቋማት አመራሮችና ሠራተኞች፣
ይህ ምርጫ የተሳካ እንዲሆን የምርጫ ቦርድ አመራሮችና ሠራተኞች፣ እንዲሁም የምርጫ አስፈጻሚዎችና ታዛቢዎች ሁሉ ከደም መሥዋዕትነት በመለስ ያለ ከፍተኛ ዋጋ ከፍላችኋል። ከግራ ከቀኝ የሚመጡትን ጫናዎች ተቋቁማችሁ በውጣ ውረዶች ሳትበገሩ ለሀገራችን የማይደበዝዝ የዴሞክራሲ አሻራ አትማችኋል፤ በዚህም ታሪክ ስማችሁን አድምቆ ይጽፈዋል።
የጸጥታ አካላት፤ ምርጫው ሰላማዊ እንደሆን ጉልህ ሚና ተጫውታችኋል፤ እናንተ ዕንቅልፍ አጥታችሁ ሥጋቶቻችን ሁሉ እንደ ጉም እንዲተንኑ ስላደረጋችሁ ክብር ይገባችኋል። በተመሳሳይ፣ ፈጣንና ሚዛናዊ መረጃን ወደ ሕዝቡ በማድረስ በኩል የግልና የመንግስት ሚዲያዎች፤ እንዲሁም አጭር የጽሑፍ መልዕልት ስርጭት በኩል የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ሠራተኞች፣ ላበረከታችሁት አስተዋጽዖ ኢትዮጵያ ታመሰግናችኋለች።
ውድ የፓርቲያችን አመራሮችና አባላት፥
በዚህ ምርጫ ሕዝቡ ያስተላለፈውን መልእክት በሚገባ መረዳት የወደፊቱን መንገዳችንን ቀና እንደሚያደርገው እናምናለን። ሕዝቡ በአብላጫ ድምጽ እኛን የመረጠው ፓርቲያችን እንከኖች ስለሌሉበት አይደለም፤ ከነስሕቶቻችንን ዕድል ሰጠን እንጂ ድል አላደረግንም። ሕዝብ የመረጠን በአንድ በኩል ያጠፋናቸውን እንድናርም፣ በሌላ በኩል መልካም ጅማሮዎቻችንን እንድናስቀጥል፣ ከሀገር ግንባታ አንጻር በወሳኝ ደረጃ ላይ ያሉ የለውጥ ሥራዎችን በቀጣይ ጊዜያት ፈጽመን እንድናሰረክብ ነው። ሕዝባችን ጉድለቶቻችንን በሚገባ ያውቃል። ከስርቆት ዓመል ያልተላቀቁ፣ ለሰው ነፍስ ግድ የሌላቸው፣ ሕግን የማያከብሩ፣ ኃላፊነታቸውን የማይወጡ አመራሮች በመካከላችን መኖራቸውን ጠንቅቆ ያውቃል። ድምፁን ሲሰጠን ታረሙ፣ ውስጣችሁን አጥሩ እያለን ጭምር ነው። እኛም በተግባር ሆነን ማሳየት አለብን። ይኼን ማድረግ ካልቻልን ከአምስት ዓመት በኋላ በካርዱ እንደሚቀጣን እናውቃለን።
በአሁኑ ምርጫ መምረጥ ያልቻላሁ ወገኖቻችን በሙሉ፥
በልዩ ልዩ የጸጥታና የደኅንነት ምክንያቶች፣ እንዲሁም በሎጅስቲክና በተለያዩ ውሱንነቶች ምርጫው በተያዘለት ክፍለ ጊዜ መሠረት ከተቀረው ሕዝብ ጋር አብራቸሁ ድምፅ ባለመስጠታችሁ ታላቅ የሆነ ቅሬታ ፈጥሮብናል። ይኼ የሆነው ባልተጠበቁ ምክንያቶች እንደሆነ ግንዛቤ ትወስዳላችሁ የሚል ግምት አለን። ሁኔታዎች ተስተካክለው የምርጫ ቦርድ በወሰነው ቀን ምርጫው እንደሚደረግ እምነቴ ነው።
ትግራይን በተመለከተ የትግራይ ሕዝብ በሚፈልገው መንገድ ከተደራራቢ ችግር የሚወጣበትን፣ ተያያዥ ሀገራዊ ችግሮች የሚፈቱበትን እና ሰላምና ደኅንነት የሚረጋገጥበትን የመፍትሔ አቅጣጫ እንከተላለን።
በመጨረሻም፣ ከለውጡ ጊዜ አንሥቶ እስከ ዛሬ ድረስ ስለ ሀገር አንድነትና ስለ ሕዝባችን ተጠቃሚነት ቀና ቀናውን በማሰብ በመንገዳችን ሁሉ ድጋፍ ሲያደርጉልን የነበሩ አካላትን ከልብ ሳላመሰግን አላልፍም። ኢትዮጵያ በታሪክ ለውጥ ላይ ናት። በዚህ የለውጥ ሂደት ተሳፍረን የተሻለች ሀገር እንገነባለን። በዚህ ምርጫ ኢትዮጵያችን አሸናፊ ስለሆነች በድጋሚ ለመግለጽ እወዳለሁ። ቀጣይ ዘመናችንን ብሩህ ያድርግልን፤ ሁላችንም እንኳን ደስ አለን።
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ሐምሌ፣ 2013 ዓ.ም- በስድስተኛ ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ብልጽግና ፓርቲ 410 መቀመጫዎችን ማሸነፉን የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሐምሌ 3 ቀን 2013 ዓ.ም. አስታውቋል። ዝርዝሩን ለማንበብ እዚህ ጋር ይጫኑ።
- የስድስተኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ ውጤት መታወቅን ተከትሎ የኢፌዴሪ ፕሬዝደንት ወ/ሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ “ኢትዮጵያ ሀገራችን ተከብራ የምትኖረው ስንቻቻል፣ ስንደማመጥና የሌላውን ሃሳብ ስንቀበል ብቻ ነው” በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
- ይህ ሀገራዊ ምርጫ በተሳካ ሁኔታ እንዲካሄድ ትልቁን ሚና የተጫወተውን የብሔራዊ ምርጫ ቦርድን የሚመሩት ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ “ሀገራዊ ምርጫው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ገለልተኝነት በይፋ የታየበት ነው” ብለዋል።
July 7, 2021 at 2:08 am #19856In reply to: ነፃ አስተያየት (ስለኢትዮጵያ በኢትዮጵያውያን)
AnonymousInactiveህወሓት ጠቡ ከኢትዮጵያ እና ከኢትዮጵያዊነት ጋር ነው
በአቶ ዮሐንስ መኮንን
“ከማዕከላዊው የመንግሥት የሥልጣን ማማ ተገፍቼያለ” ብሎ ያኮረፈው የህወሓት ቡድን ከሦስት ዓመታት በፊት የጦርነት ዳርዳርታ በጀመረ ሰሞን መገዳደል ማንንም አትራፊ ስለማያደርግ የጦርነት ጉሰማውን እንዲተው በሀገር ሽማግሌዎች፣ በልኂቃንም ሆነ በተራ ዜጎች ሳይቀር ተለምኖ ነበር። የህወሓት ሰዎች ግን “ጦርነት ባህላዊ ጨዋታችን ነው” እያሉ ያፌዙ እንደነበር ኢትዮጵያውያን ሁላችንም የምናስታውሰው የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።
የጦርነት ጉሰማው ድንበሩን አልፎ “የ45 ደቂቃ መብረቃዊ ጥቃት” ሲሉ በራሳቸው አንደበት በነገሩን አረመኔያዊ የክህደት እርምጃ ወገናቸው በሆነው የሀገር መከላከያ ላይ የፈጸሙት ጥቃት እና በማይ ካድራ ንጹሐን ላይ የፈጸሙት ጭፍጨፋ ለህወሓት ሰዎች እና ደጋፊዎቻቸው ዛሬ ላይ “ጀብድ” ይምሰላቸው እንጂ የፈጸሙት ተግር በታሪክ ፊት አንገታቸውን የሚያሰደፋ የነውር ጥግ ነበር።
ይህንኑ የህወሓት አረመኔያዊ ተግባ ተከትሎ የመከላከያ ሠራዊታችን በወሰደው የአጸፋ እርምጃ ዋንኛው ዓላማ ህወሓትን ከነመዋቅሯ መደምሰስ ቢሆንም ጦርነቱ በንጹሓን ዜጎች ይልቁኑም በሴቶች እና በሕጻናት ላይ ያደረሰው ጉዳት የሚያሳዝነን እና የሚያሳፍረን ክስተት ነበር።
ዛሬ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት በውጪ መንግሥታት ተጽእኖም ይሁን በጦርነቱ አክሳሪነት የተነሳ “የጽሙና ጊዜ ለመስጠት” የተናጥል የተኩስ አቁም ውሳኔ አሳልፎ ከክልሉ ሠራዊታችን ማስወጣቱ ተገቢ እርምጃ ነው። ይህ ማለት ግን “ትግራይን የራሱ ሉዓላዊት ሀገር አካል መሆኗ አበቃ” ማለት አይደለም። በግልጽ ቋንቋ ለመግለጥ “ህወሓት ይሻለናል” ለሚሉ አባላቶቿ ደጋፊዎቿ “ዕድል ለመስጠት ያለመ” መሆኑን እገነዘባለሁ።
ይሁን እንጂ መንግሥት ተገፍቶ ሕግ ወደማስከበር ጦርነት ሲገባም ሆነ አሁን ትግራይን ለቅቆ ሲወጣ ጉዳዩን ያየዘበት መንገድ ሌላ ዘላቂ ሀገራዊ ችግር ተክሎብን እንዳያልፍ ሊጠነቀቅባቸው የሚገቡ ጉዳዮች እንዳሉ ይሰማኛል። በምክንያት ላስረዳ፡
ህወሓት ያኮረፈውም ሆነ የተጣላው ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር እንጂ ከአንድ ሕዝብ ጋር እንዳልነበረ የሚስተው ያለ አይመስለኝም። ጦርነቱ እንደተጀመረ ተደራጅቶ በቅርብ ርቀት ላይ ገኝ የነበረው የአማራ ልዩ ኃይል ቀድሞ የህወሓትን ተስፋፊ ጦር መመከቱ የሚያስመሰግነው ተግባር መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በሂደት ግን በዓለም ዓቀፉ ማኅበረሰብም ሆነ በአንዳንድ “ልኂቃን” ጭምር የህወሓት ጠብ “ከአማራ ልዩ ኃይል” ጋር አስመስለው መግለጻቸው ተገቢ ካለመሆኑም በላይ የአንድን ጠባብ ቡድን የእብሪት ጦርነት በሁለት ሕዝቦች መካከል የተደረገ ጦርነት አስመስሎ ማቅረቡ ጉዳቱ ውሎ አድሮ የሚያመረቅዝ ቁስል እንዳተርፈን ያሳስበኛል። በእርግጥ የመከላከያ ሠራዊታችን ከሁሉም ብሔሮች የተውጣጣ ጦር መሆኑ እየታወቀ ተደጋግሞ “አማራ ልዩ ኃይል” የጦርነቱ ፊት አውራሪ ተደርጎ መሳሉ የህወሓት ጠብ ከአንድ ሕዝብ ጋር አስመስሎታል።
በቀደም እለት ጠቅላይ ሚንስትሩ በፓርላማ ባደረጉት ንግግርም “የአማራ ሕዝብ ለህወሓት አይንበረከክም” የሚለው ንግገራቸው ምንም እኳን ሕዝቡን ለማጀገን እንደተጠቀሙበት ብረዳውም የአማራ ልዩ ኃይል ለሀገር አንድነት የከፈለውን መስዋእትነት ክልሉን ለመከላከል እንደተከፈለ መስዋእትነት አሳንሶ ወደማየት እንዳይተረጎም ያሳስበኛል።
ዛሬ ደግሞ የጀርመኑ ዶቼቬሌ ሂውማን ራይት ዎችን ጠቅሶ እንደዘገበው ህወሓት “በአማራ ክልል ልዩ ኃይሎች ተይዘውብኛል” የሚላቸውን አካባቢዎች መልሶ ለመንጠቅ በርካታ ታጣቂዎቹን እያንቀሳቀሰ መሆኑን ሰምተናል። እንደዘገባው ከመጠለያ ካምፖች ሳይቀር ወጣቶችን በገፍ እየመለመለች ነው። (ህወሓት ሰንአፌ በረሃ አርቅቃ ኢትዮጵያ ላይ የጫነችውን “ሕገመንግሥት” ሳይቀር በተቃረነ መንገድ የአማራ ገበሬዎችን በማፈናቀል በወረራ የቀማቻቸውን ወልቃይት እና ሁመራን የመሳሰሉ ለም መሬቶች በግፍ መንጠቋ ይታወሳል)
የህወሓትን ትፍራፊ ጦር እንደ አመጣጡ ለመመለስ የአማራ ልዩ ኃይል የሚያንስ ባይሆንም ትንኮሳውን ማስቆም ያለበት ዋንኛው ፊትአውራሪ ጦር ግን የሀገር መከላከያ ኃይል ነው ብዬ በጽኑ አምናለሁ። የልዩ ኃይል ተሳፎ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም የአማራ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ክልሎች ልዩ ኃይሎች በመከላከያ ሠራዊት ሥር ታቅፈው ስምሪት ሊሰጣቸው ይገባል።
“ኢትዮጵያን ሳላፈርስ እንቅልፍ አይወስደኝም” ብሎ የማለውን የህወሓት ትርፍራፊ ጦር መመከት እና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም መደምስ የሁሉም ኢትዮጵያውያን የቅድሚያ ቅድሚያ ኃላፊነት ነው። ምክንያቱም የህወሓት ጸብ ከኢትዮጵያ እና ከኢትዮጵያዊነት ጋር ነው!
ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረ–ገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forums) ላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።
July 6, 2021 at 3:24 am #19830In reply to: የፖለቲካ ፓርቲዎች ድምጽ (ኢትዮጵያ ውስጥ የሚነቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች)
AnonymousInactiveከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ
ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን ) የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ
ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣
ለሁሉም የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሉች፤
የኢትዮጵያ ጉዳይ ለሚያሳስባችሁ አፍሪካውያን ወንድሞቻችንና ዓለምአቀፍ አጋሮቻችን፤
በመላው ዓለም ለምትገኙ ሰላም ወዳድ ኃይሎች በሙሉ !የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በሰኔ 26 እና 27 ቀን 2013 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ጥልቅና ዙሪያ መለስ ውይይት በማድረግና፤
- የሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ፖለቲካ መሠረት ለመጣልና በሕዝብ ይሁንታ ብቻ ሥልጣን የሚይዝ ሥርዓት ለመፍጠር የተደረገውን 6ኛውን ሀገራዊ የምርጫ ሂደት በመገምገም፤
- የታላቁን የአባይ ግድብን በማጠናቀቅና እንደ ሀገር የተፈጥሮ ፀጋችንን ተጠቅመን የመልማት መብታችንን ለማረጋገጥ በተያያዝነው ጥረት ረገድ የተጋረጡብንን ተግዳሮቶች በመገንዘብ፤
- ሕዝባችን በሰላምና ደህንነት እጦት፣ በኮቪድ-19 ወረርሽኝና መረን በለቀቀ የኑሮ ውድነት እየደረሰበት ያለውን ምጣኔ ሀብታዊ ድቀት ግምት ውስጥ በማስገባት፤
- ከሁሉም በላይ ሀገራችን ከውስጥ በከሃዲያንና እኩያን ኃይሎች ቅንጅት፣ ከውጭ በታሪካዊ ጠላቶቻችንና ዓለምአቀፍ አጋሮቻቸው አይዞህ ባይነትና ድጋፍ የተደቀነባትን የህልውና ስጋት ተቀዳሚ ትኩረት በመስጠት፤
የፓርቲው ሥራ አስፈፃሚ የደረሰባቸውን አቋሞች ለተከበረው ሕዝባችን፣ ለአፍሪካውያን ወንድሞቻችንና በአጠቃላይም ለዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ለማሳወቅ ይወዳል።
- ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ በተመለከተ
አብን እንደ ድርጅት የመጀመሪያው አብይ የፖለቲካ ተመክሮው በሆነው በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ውስጥ ለመሳተፍ ሲያቅድ፥ ገና ከመነሻው ሀገራችን የምትገኝበትን የፖለቲካ አውድ በመገምገም በምርጫው የመሳተፉን ውሳኔ ያደረገው በዋነኝነት ከድርጅታዊ ፋይዳዎች ይልቅ ለሀገራዊ ፖለቲካው መረጋጋትና ለዴሞክራሲያዊ ተመክሮ ግንባታ ከሚኖረው ፋይዳ አንፃር እንደሆነ በይፋ አሳውቋል።
አብን ሀገራዊ ፓርቲ እንደመሆኑ መጠን የምርጫ ዘመቻውን ስትራቴጂክ ግቦችና ማስፈፀሚያ ስልቶችን በዝርዝር በመንደፍ፣ አማራጭ ፖሊሲዎቹን በማኒፌስቶ በመሰነድና ሙሉ ድርጅታዊ ኃይሉን በማንቀሳቀስ በምርጫ በሚሳተፍባቸው በአማራና ሌሎችም የሀገሪቱ ክፍሎች 510 እጩዎችን በማቅረብ ሰፊውን መራጭ ሕዝብ ለመድረስ ያልተቆጠበ ጥረት አድርጓል።
በዚህም መሠረት የምርጫ ዘመቻው ከነተግዳሮቶቹ ተጠናቅቆ፣ በሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ፓርቲያችን በሚወዳደርባቸው ክልሎች ድምፅ ተሰጥቶና በከፊል ጊዜያዊ ውጤት ተገልጾ በድኅረ ምርጫ ሂደት ላይ እንገኛለን።
ፓርቲያችን በመላ ሀገሪቱ በተወዳደረባቸው አካባቢዎች በምርጫው ሂደት የተፈፀሙትን አበይት ጥሰቶች በማሰባሰብና በዝርዝር ቅሬታዎችን በመሰነድ በህግ አግባብ ለብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አቅርቧል። የምርጫ ቦርድ ከተጣለበት ታላቅ ሀገራዊ ኃላፊነት አኳያ ከሰው፣ ከፋይናንስ፣ ከተመክሮና ከሎጂስቲክ አቅም ውሱንነት ቢታይበትም በአጠቃላይ ከቅድመ ምርጫው ጀምሮ አንፃራዊ አዎንታዊነት እንዳሳየ እናምናለን። በቦርዱ የበላይ አመራር የታየው ገለልተኝነት፣ ግልፅነትና ፍትሃዊነት መንፈስ እንደ ተቋም የሚፈተንበት ወቅት እንደሆነም እንገነዘባለን።
የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ ሕዝባችን ይህንን ሁሉ ጫና ተቋቁሞ በምርጫው ሂደት ውስጥ በመሳተፍ ላሳየው ፅናት ልባዊ አድናቆቱን በመግለፅ፣ የመራጩ ድምፅ እንዲከበር ተገቢውን ሰላማዊና ህጋዊ ጥረት እንደሚያደርግና የሕዝባችንንም ሀቀኛ ውሳኔ ያለማወላወል እንደሚቀበል ለማሳወቅ ይወዳል።
በሌላ በኩል 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ የሥርዓቱን እውነተኛ ባህርይ በተግባር መፈተንና ማጋለጥ መቻሉን ትልቁ ውጤት አድርጎ መውሰድ ይቻላል። በምርጫው ሂደት የታየው ጎዶሎነትና ክፍተት ከምርጫ ውጤት አኳያ የምንመዝነው ከሆነ የሀገራችንን ተጨባጭ ሁኔታና የሃሳብ ብዝሃነት የማያመለክት መሆኑን መናገር ይቻላል።
አብን እንደ ድርጅት በምርጫ በመሳተፉ ምን አገኘ፣ አሳካ የሚለውን ስንገመግም አንዳንድ ተስፋ ሰጭ ነገሮች እንዳሉ መካድ አይቻልም። ከሁሉም በላይ የሕዝባችን እውነተኛ ወኪል ስለመሆናችን ሕዝባችን የነበሩትን ጫናዎች ተቋቁሞ በሰጠን የመተማመኛ ድምፅ በቂ ማረጋገጫ አግኝተናል። ይህም የመጪው ዘመን ፓርቲ መሆናችንን ይመሰክራል። በሐገር አቀፍ ድረጃ በተሻለ ሕዝብን የማስተባበር አቅም እንዳለንና ጠንካራ ተገዳዳሪ የፖለቲካ ኃይል መሆናችንን በማያሻማ ሁኔታ አረጋግጠናል።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ የምርጫው ሂደት አጠቃላይ ድርጅታዊ ቁመናውን የሚፈትሽበት መልካም አጋጣሚ መሆኑንም ይገነዘባል። በቀጣይም ከሂደቱ ያገኛቸውን ተመክሮዎችና ትምህርቶች በማካተትና ሁለገብ የማሻሻያ እርምጃዎች በመውሰድ ለብሔራዊ ፖለቲካችን ሁነኛ ሚና መጫወቱን እንደሚቀጥል አያጠራጥርም።
- ብሔራዊ ደህንነትን በተመለከተ
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ በተለይ በሀገር ሉዓላዊነትና አንድነት፣ በሕዝብ ጥቅምና ክብር፣ በሀገረ መንግሥቱ ቀጣይነት ረገድ ግልፅና የማያሻማ አቋም ያራምዳል። በገዥው ፓርቲ ግልፅ ፍረጃ፣ ወከባና ጥቃት እየደረሰበትም ቢሆን የፖለቲካ ማዕከሉ እንዲረጋጋና በአፍሪካ ረዥሙንና ደም አፋሳሹን የእርስ በርስ ጦርነት ያደረገች ሀገር ተመልሳ ወደ ቀውስ እንዳትገባ ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል።
አብን ወቅታዊው የሀገራችን ብሔራዊ ደህንነት ከጊዜ ጊዜ እየከፋና እጅግ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ይገነዘባል። የውጭ ወራሪዎችና የውስጥ ቦርቧሪዎች ከተቻለ ኢትዮጵያን ለየዘውጉ አምበሎች በታትኖ ከዓለም ካርታ ለማጥፋት፤ ካልሆነ ደግሞ ውስጣዊ አንድነት የሌላት፣ ደካማና ፍላጎታቸውን ያለማንገራገር የምትቀበል አድርገው ለማሽመድመድ እየተረባረቡ ይገኛሉ።
ከዚህ አንፃር የብልጽግና አገዛዝ የሀገሪቱን፣ የዜጎችና የመንግሥቱን ሰላምና ደህንነት፣ ጥቅምና ክብር በማስጠበቅ ረገድ ጉልህ ክፍተቶች እየተስተዋለበት ነው። በአሁኑ ወቅት መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ባደረገው ከፍተኛ ተጋድሎ ከአፈናና ጭቆና መንበሩ የተባረረውና በሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ በአማራ እና አፋር ልዩ ኃይልና ሕዝባዊ ሚሊሺያ ድባቅ የተመታው የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር (ትህነግ) ተመልሶ በማንሰራራት በብሔራዊ ደህንነታችን ላይ ተቀዳሚ አደጋ ሊሆን በቅቷል።
አብን ማዕከላዊ መንግሥትና በየደረጃው ያሉ መንግሥታዊ አካላት ሀገሪቱ ከተደቀነባት የህልውና አደጋ ለመታደግ በሚደረገው ርብርብ የራሳቸውን ሚና በግልፅ ከመወሰን አንስቶ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያካተተ የብሔራዊ ደህንነት እርምጃ እንዲወስዱ ጥሪ ያቀርባል።
መንግሥት ልዩ የደህንነት ስጋት ያለባቸው አካባቢዎች ላይ ትኩረት እንዲያደርግ፤ በተለይም አሸባሪው የትህነግ ቡድን መልሶ በተቆጣጠረው በትግራይ የተማሪዎችንና የሲቪል ዜጎችን፤ በአጠቃላይም የትግራይን ሕዝብ ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ይጠይቃል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በትግራይ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ተመድበው ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙ ተማሪዎች ሁኔታ አብንን በእጅጉ ያሳስበዋል። የትግራይ ሕዝብ በመካከሉ ለሚገኙ ተማሪ ልጆቹ አስፈላጊውን ጥበቃና ክብካቤ እንዲያደርግ ጥሪ እናደርጋለን።
አብን መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ሀገር ወዳድ ዜጎችና በተለይም ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል ሀገራችን ስለገጠማት የብሔራዊ ደህንነት አደጋ ግልፅ ግንዛቤ እንዲኖራቸውና ኢትዮጵያን ለመታደግ በአንድነት እንዲሰለፉ ጥሪ ያደርጋል።
በወታደራዊ ኃይል የሚገኘው ድል ዳግም በዲፕሎማሲው አውድማ እንዳይነጠቅ መላው ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን የሀገራቸው አምባሳደር በመሆን በዓለምአቀፍ የዲፕሎማሲ ትግል እንዲሳተፉ ጥሪ ያቀርባል።
በተለይም ደግሞ በፀረ – ኢትዮጵያው ጎራ በጠላትነት ተፈርጆ ዘርፈ ብዙ ጥቃት የተሰነዘረበት የአማራ ሕዝብ የሚገኝበትን ወቅታዊ የስጋት ደረጃ በውል ተገንዝቦ የበኩሉን ጥንቃቄና ዝግጅት እንዲያደርግ፣ የአማራ ዲያስፖራ በሕዝባችንና በሀገራችን ላይ የተቃጣውን አደጋ ለመቀልበስ ሁለገብ የሃሳብ፣ የፋይናንስ፣ የዲፕሎማሲ ተሳትፎውን አጠንክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ያቀርባል።
አብን አፍሪካውያን ወንድሞቻችን፣ መላው የኢትዮጵያ ወዳጆችና አጋሮች የጥንታዊ ሥልጣኔ፣ አኩሪ የነፃነት ታሪክ ያላት ሀገር በእኩያን ኃይሎች የተከፈተባትን ወታደራዊ፣ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ጥቃት ለመመከት ከጎናችን እንዲሰለፉ ጥሪ ያደርጋል። በዚህ ረገድ በአካባቢው ጉዳይ ትኩረት አድርገው የሚንቀሳቀሱ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ዓለምአቀፍ ተቋማት በአፍራሽ የሀሰት ፕሮፓጋንዳ እንዳይደለሉና የችግሩን ዙሪያ ገብ በፍትሃዊነት በመገምገም እንዲንቀሳቀሱ ጥሪ ያቀርባል።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ በሀገራችን ላይ የተደቀነውን ፅኑ የብሔራዊ ደህንነት ስጋት ለመመከትና ከምንም በላይ የቆመለትን የሀገር አንድነትና ሉዓላዊነት፣ የሕዝብ ጥቅምና ክብር እንዲሁም የሀገረ መንግሥቱን ቀጣይነት ለማረጋገጥ የሚጠበቅበትን ሁሉ ድርጅታዊ አስተዋፅኦ ለማድረግ ቁርጠኝነቱን በአፅንኦት ለመግለፅ ይወዳል።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)
አዲስ አበባ፣ ሸዋ፣ ኢትዮጵያ
ሰኔ 28 ቀን 2013 ዓ.ምምንጭ፦ አብን
July 3, 2021 at 11:06 pm #19816In reply to: የሰብዓዊ መብቶች እና ተያያዥ ጉዳዮች ― ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
AnonymousInactiveትግራይ ክልል – የሲቪል ሰዎችን ሁኔታ ለማሻሻል አፋጣኝ እርምጃዎች ሊወሰዱ ይገባል
አዲስ አበባ (ኢሰመኮ) – የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ሰኔ 21 ቀን፥ 2013 ዓ.ም. የፌዴራል መንግሥት በትግራይ ክልል የተኩስ አቁም ማወጁን ተከትሎ የግንኙነት መሰመሮች በመቋረጣቸው፣ በክልሉ ነዋሪዎች የሚገኙበት ሁኔታ እንደሚያሳስበውና መንግሥት የነዋሪዎችን ደኅንነት ለማስጠበቅ የሚረዱ እርምጃዎች በአፋጣኝ ሊወስድ እንደሚገባ ገለጸ። በክልሉ የተቋረጡ መሠረታዊ አገልግሎቶችን መመለስና በትግራይ ክልል ስላለው ተጨባጭ የፀጥታ ሁኔታና የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት በቂ መረጃ መስጠት፣ በዚህ ረገድ ያሉ ክፍተቶችን ለማረምና የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ትብብር ለመፍጠር ቀዳሚ እርምጃዎች ናቸው።
ለግጭቱ ሰላማዊ መፍትሔ ለማፈላለግ የሚደረገው ጥረት አስፈላጊነት እንደተጠበቀና በክልሉ ለሚደረጉ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦቶች ጥበቃና ለተደራሽነቱ ትብብር እንደሚቀጥል መገለጹ የሚበረታታ ሆኖ፣ የሲቪል ሰዎች ደኅንነትና ሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል። በአሁኑ ወቅት በአብዛኛዎቹ የትግራይ አከባቢዎች የመብራት፣ የስልክ እና የውሃ አገልግሎት በመቋረጡ በክልሉ ነዋሪዎች ላይ ከባድ የኑሮ ጫና እያስከተለ ይገኛል። የባንክ አገልግሎት መቋረጥና የጤና አገልግሎት አቅርቦትና ተደራሽነት ውሱንነት ችግሩን አባብሶታል።
በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሱ ሀገራዊና ዓለምአቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች የኤሌክትሪክ እና የስልክ አገልግሎት መቋረጥን ጨምሮ የሌሎች አቅርቦቶች እጥረት የሰብዓዊ ድጋፉን በከፍተኛ ደረጃ እንደጎዳውና በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ ነዋሪዎች፣ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና ስደተኞች ስለሚገኙበት ሁኔታ ማወቅ አስቸጋሪ እንዳደረገው ይገልጻሉ።
በአዲስ አበባ ከተማ የትግራይ ክልል ተወላጅ የሆኑ ነዋሪዎችና የሚዲያ ሰዎችን ጨምሮ፣ ሌሎች ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል ተጠርጥረው የታሰሩ ሰዎችን ሁኔታ ኮሚሽኑ በመከታተል ላይ ይገኛል። ይህም በነዋሪዎች ላይ ማንነትን በመለየት ለጥርጣሬ እና መድልዎ የሚያጋልጥ ተግባር እንዳይሆን ስጋት የሚያሳድር ነው።
በተጨማሪም፥ በክልሉ ዩኒቨርሲቲዎች የሚማሩ ወጣቶች ወላጆችና ቤተሰቦች ተማሪዎቹ በአሁኑ ወቅት ስለሚገኙበት ሁኔታ ተገቢው ምላሽ እና ማብራሪያ እንዲሰጣቸው የሚመለከታቸውን የመንግሥት አካላት በመጠየቅ ላይ ይገኛሉ።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ የነዋሪዎችን ደኅንነት ማረጋገጥ ቀዳሚው የመንግሥት ግዴታ መሆኑን አስታውሰው፥ “በክልሉ የሚገኙ ነዋሪዎች ስላሉበት ሁኔታ የተገቢው መረጃ ማነስ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ከሚደመጡ ዘገባዎችና ንግግሮች ጋር ተዳምሮ ነዋሪዎችን ስጋት ላይ የሚጥል ነው። የተኩስ አቁሙ በሁሉም በግጭቱ ተሳታፊ በነበሩ ወገኖች ሁሉ በቁርጠኝነት መከበር እና የመሠረታዊ አገልግሎቶች በአፋጣኝ መመለስ፣ አጠቃላይ ሁኔታውን ለማሻሻል፣ በትግራይ ክልል ለተፈጠረው ችግር ዘላቂ መፍትሔ ለማፈላለግ፣ እንዲሁም ሰብዓዊ አቅርቦቱ እንዳይቋረጥ የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ነው። በተጨማሪም ማንኛውም አይነት እስር ሁልጊዜም ሕጋዊ ሥርዓትን የተከተለ ሊሆን ይገባል” ብለዋል። ዋና ኮሚሽነሩ አክለውም በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል የሚገኙ የመንግሥት እና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት ሁሉ ሁኔታውን የሚያባብሱ፣ በሕዝቦች መካከል ጥላቻና ጥርጣሬን ሊፈጥሩ ከሚችሉ ንግግሮች እንዲቆጠቡ ጥሪ አቅርበዋል።
ምንጭ፦ ኢሰመኮ
June 26, 2021 at 3:01 pm #19782In reply to: የሰብዓዊ መብቶች እና ተያያዥ ጉዳዮች ― ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
AnonymousInactiveበ2013 ዓ.ም. ሀገራዊ ምርጫ ድምጽ መስጫ ቀን የተደረገ የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ክትትል (ቀዳሚ ሪፖርት)
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)በ2013 ዓ.ም. ሀገራዊ ምርጫ የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ላይ የታዩ ክፍተቶች በተገቢው የሕግ እና የአሠራር ማሻሻያ ሊታረሙ ይገባል
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከሰኔ 12 እስከ ሰኔ 16 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ ምርጫ በተካሄደባቸው በሁሉም ክልሎች በሚገኙ የተመረጡ አካባቢዎች ተንቀሳቃሽ የክትትል ቡድን በማሰማራት ያጠናቀረውን የሰብዓዊ መብቶች ክትትል ሪፖርት ይፋ ሲያደርግ፤ ክትትሉ በተከናወነባቸው የተወሰኑ የምርጫ ጣቢያዎችና አካባቢዎች የተመለከታቸው ክፍተቶች ተገቢው ትኩረት እንዲያገኙና አስፈላጊውን የሕግና የአተገባበር መፍትሔ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ገለጸ።
ኮሚሽኑ ለሀገራዊ ምርጫ 2013 ዓ.ም. ባለ6 ነጥብ የሰብዓዊ መብቶች አጀንዳ ይፋ በማድረግና ለሰብዓዊ መብቶች ትኩረት እንዲሰጥ ከመወትወት በተጨማሪ፥ በቅድመ ምርጫውና በምርጫው ቀን የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ክትትል ሲያከናውን ቆይቷል። በተለይም ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ፣ የመዘዋወር፣ የመሰብሰብ እና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብቶችን በተመለከተና የሴቶችን ተሳትፎ ማሳደግ፣ እንዲሁም ምርጫው የአካል ጉዳተኞችን እና የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ያሳተፈና ለእነሱ ተደራሽ የሆነ በማድረግ ረገድ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ክትትል ሲያደርግ ቆይቷል።
በዚህም መሠረት 94 ባለሞያዎችን ያካተተው ቡድን በአጠቃላይ በአዲስ አበባ፣ በድሬዳዋ ከተሞችና በሁሉም ምርጫ በተካሄደባቸው ክልሎች በሚገኙ 99 የምርጫ ክልሎችና 404 የምርጫ ጣቢያዎች ተዘዋውሮ፥ የአካባቢውን አስተዳደር፣ ነዋሪዎችን፣ የፀጥታ ኃይሎችን እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮችን፣ እጩዎችንና አባላት እንዲሁም የምርጫ አስፈጻሚ አካላትና ሌሎች ባለድርሻዎችን አነጋግሯል። በዋና ጽሕፈት ቤቱ በተመደቡ ባለሞያዎች አማካኝነት በ7037 የስልክ ቁጥሩ ጥቆማዎችንና አቤቱታዎችን ተቀብሎ አስተናግዷል።
ምርጫው የተካሄደበት አውድ በሀገር ውስጥ የተደራረቡ ችግሮች የገጠሙበት እና በትግራይ ክልል የተከሰተውን ግጭት ጨምሮ በሌሎችም አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶች ባሉበት፥ በተወሰኑ አካባቢዎች በጸጥታ ችግር ምርጫው እንዲተላለፍ አስገዳጅ በሆነበት፣ የተወሰኑ የፖለቲካ ቡድኖች እራሳቸውን ከምርጫው ሂደት ባገለሉበት፣ ሌሎች የፖለቲካ ቡድን አመራሮች በቀረበባቸው የወንጀል ክስ ምክንያት በእስር በሚገኙበት ወቅት መሆኑ የማይዘነጋ መሆኑንና ከግምት ውስጥ ማስገባት እንደሚገባ ኮሚሽኑ ገልጿል። ይህ ተግዳሮት እንዳለ ሆኖ፤ ኢሰመኮ በምርጫው መዳረሻ ቀናት እና በምርጫው ዕለት ክትትል ባደረገባቸው አካባቢዎች የተወሰኑ የሰብዓዊ መብቶች አጠባበቅ ክፍተት የታየ ቢሆንም፤ በአብዛኛዎቹ ቦታዎች የጎላ ወይም የተስፋፋ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት እንዳልታየ ገልጾ፤ ክትትል ባደረገባቸው በአብዛኛዎቹ አካባቢዎች የምርጫው ዕለት ሂደት ያለ የጎላ ችግር በሰላም ተጀምሮ የተጠናቀቀና በሰብዓዊ መብቶች አጠባበቅ ረገድ በብዙ መልኩ የተሳካ የድምጽ አሰጣጥ ሂደት እንደነበር አሳውቋል። በተጨማሪም በምርጫው ሂደት በሕጋዊና ሰላማዊ መንገድ ለተሳተፉና አስተዋጽኦ ላደረጉ ወገኖች ሁሉ እውቅና ሰጥቶ፤ በቀሪው ሂደትም በሕጋዊና ሰብዓዊ መብቶችን ባከበረ መንገድ እንዲቀጥሉ ጥሪውን በድጋሚ አቅርቧል።
እነዚህን አዎንታዊና አበረታች እርምጃዎች እንደተጠበቁ ሆነው፥ በተወሰኑ የምርጫ ክልሎች እና ጣቢያዎች ከምርጫው ዕለት ጥቂት ቀናት በፊት፣ በምርጫው ዕለትና ከምርጫው ቀን በኋላ የደረሰ የሰው ሕይወት መጥፋትና የአካል ጉዳት፣ ተገቢ ያልሆነ እስር፣ በመራጮች ላይ የደረሰ ማስፈራራት፣ በምርጫ ታዛቢዎችና ጋዜጠኞች ላይ ስለደረሰ መጉላላትና ማዋከብ፣ የምርጫው ሂደት ለአካል ጉዳተኛ ሰዎች ያለው ተደራሽነትና የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን የተሳትፎ መጠን በሚመለከት ባወጣው የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት አስረድቶ፤ ሊወሰዱ ስለሚገባቸው እርምጃዎች ምክረ ሃሳብ ሰጥቷል።
በተጨማሪም ጥፋተኛ በሆኑ ሰዎች ላይ በአፋጣኝ ምርመራ በማድረግ ተጠያቂነታቸው እንዲረጋገጥ እና ኮሚሽኑ በሕግ የተሰጠውን በምርጫ ወቅት የሰብዓዊ መብቶች ክትትል የማድረግ ኃላፊነቱንና ተግባሩን በአግባቡ እንዳይወጣ የሚያግዱ፣ የሚገድቡ ወይም የሚያሰናክሉ ሁኔታዎች በተለይም የምርጫ ጣቢዎችን ያለ እንቅፋት የመጎብኘት አስፈላጊነት እና የእስር ቦታዎችን ያለ ቅድሚያ ማስታወቂያ የመጎብኘት አስፈላጊነት በሚመለከት ለወደፊቱ ማናቸውም ዓይነት እንቅፋት እንዳይከሰት ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ተገቢውን እርምጃ እንዲወስዱና ሁሉም ሰዎችና ተቋማት ለኮሚሽኑ ሥራ የመተባበር ግዴታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ አሳስቧል።
ኢሰመኮ ያወጣውን ሪፖርት እዚህ ጋር በመጫን ያግኙ።
ምንጭ፦ ኢሰመኮ
June 12, 2021 at 7:41 pm #19647In reply to: ነፃ አስተያየት (ስለኢትዮጵያ በኢትዮጵያውያን)
AnonymousInactiveየሰሞኑ “ቃል በተግባር” የተሰኘው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ዘጋቢ /ገላጭ/ ፊልም በሁለት ኢትዮጵያውያን አተያይ
[ቃል በተግባር ― በዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ እና በአቶ ያሬድ ኃይለማርያም አተያይ]- ቃል በተግባር ― ኢትዮጵያን ሀገር ሆና አየኋት
[በድሉ ዋቅጅራ (ዶ/ር)]
ኢትዮጵያን እንደሀገር ያገለገልኳት፣ ያፈቀርኳት በ1970ዎቹ መጨረሻ (1976-79) ባለው ጊዜ ነበር፤ በመጀመሪያው ዙር የብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት ዘመኔ። ከትምህርት ቤት በግዴታ ታፍሼ የገባሁበት የብሔራዊ ውትድርና ከሀገሬ ጋር ልብ ለልብ አስተዋወቀኝ፤ አፈቀርኳት።
ግዳጄን ፈጽሜ፣ ዩኒቨርሲቲ ተምሬ፣ በ1983 አ.ም. ወደ ሥራ ስሰማራ ኢትዮጵያን አጣኋት። በብሔር ፖለቲካ ሴራ የተካኑ፣ ስሟን መጥራ የሚዘገንናቸው መሪዎች እጅ ወድቃለች። ለጎሳና ቋንቋ ድንበር ከልላ፣ ባንዲራ [ሰንደቅ ዓላማ] ሰቅላ እሷ ፈዝዛለች።… ለብሔረሰቦችና ለቋንቋዎች እኩልነትና ለሰብዓዊ መብት መከበር ዝም ብዬ አላውቅም፤ እሟገታለሁ። ባንዲራቸው ሲከልላት፣ የምትተነፍሰው አየር ሲያጥራት፣ ኢትዮጵያን ሲረሷት ግን አዝናለሁ፤ ያመኛል።
ከረዥም ጊዜ በኋላ በትላንትናው ዘጋቢ ፊልም ውስጥ ኢትዮጵያን ሀገር ሆና አየኋት። ዘመንን መስላ፣ ተስፋ አዝላ አነበብኳት። በሦስት ዓመት፣ ያለጥላቻና ግጭት ዜና ነግቶ በማይመሽበት ሀገር፣ ‘የእኔ ሀሳብ ካልሆነ ሀገሬ ትበተን’ በሚል ጽንፍ ረገጥ ፖለቲካዊ መርገምት ውስጥ፣ እንኳን በልዕልና መሥራት፥ በትክክል ማሰብስ ይቻላል ወይ? ያውም ይህ ሁሉ ኃላፊነት ለተጫነበት መሪ?!
የእያንዳንዳችን አመለካከትና እይታ የሚመነጨው ከቆምንበት ቦታ ነው!
አዎ፣ ሀገራችን የብሔር ፖለቲካው ካጣባት ደዌ አልተፈወሰችም። አዎ አሜሪካ ማእቀብ ጥላብናለች። አዎ ሱዳን ድንበራችንን ተሻግራ መሬታችንን ይዛለች። አዎ የትግራይ ወገኞቻችን በከፍተኛ ሰብዓዊ ችግር ላይ ናቸው። አዎ የኤርትራ ወታደሮች ከሀገራችን ጨርሶ አልወጡም። አዎ ሸኔና የጁንታው ርዝራዦች በሚሰነዝሩት ጥቃት አሁንም ዜጎች ህይወታቸውን እያጡ ነው። አዎ የኑሮ ውድነት ጣራ ነክቷል።… ሀገራችን ውስጥ በርካታ ችግሮች፣ በርካታ ያልተመለሱ ጥያቄዎች አሉ።
እነዚህ ሁሉ ችግሮች እያሉ እነዚህ አስደናቂ ፕሮጀክቶች መሠራታቸው አግባብ አይደለም በማለት ሰዎች ለጥላቻቸው የሰበብ ድር ያዳውራሉ። እኔን የሚገርመኝ በዚህ ሁሉ ችግር ውስጥ መሠራት መቻላቸው ነው።
መሠራት የነበረበት ያልተሠራ አለ። ካልተሠራው የበለጠ የተሠራው የወደፊት መንገዳችንን ያሳያል። ጠቅላይ ሚንስትሩ ከሀገሪቱ ባጀት ሳይነካ፣ የተሸለመውን የግል ገንዘብ ሳይሰስት፣ ወዳጆቹን ለምኖ በሦስት ዓመት፣ ጥላቻና ዘለፋን ቁብ ሳይል ይህንን ሠራ። ባለቤቱ ቀዳማዊ እመቤት ዝናሽ ታያቸው እንዲሁ ከሀያ በላይ ትምህርት ቤቶችን በገጠር ቀበሌዎች ገነባች። ለመሆኑ እነዚህን ሰዎች የማናደንቀው ከእነማን ጋር እያወዳደርናቸው ነው? እንኳን በሦስት ዓመት፣ በሦስት አስርታት ውስጥ የዚህን ግማሽ የሠራ መሪ ኖሮን ያውቃል?
እንደመሪ እነሱ ይህን ሠሩ፤ ያልመለሷቸው ችግሮችም አሉ። እኛስ! እንደ ዜጋ ባለፉት ሦስት ዓመታት ምን ሠራን? እኛ እንደዜጋ ያለነው የት ነው? የሠሩት በጎ ተግባር ወይስ ያልመለሷቸው ችግሮች አካል ነን? በዋናነት የእያንዳንዳችን አመለካከትና እይታ የሚመነጨው ከቆምንበት ቦታ ነው። ሀገራችን በውስጥና ውጭ ችግር ተተብትባለች፤ ፈተና ላይ እንደሆነችም እናውቃለን። ዋናው፣ እያንዳንዳችን ማወቅ ያለብን ጉዳይ ግን ሀገራችንን የተበተባት ችግር፣ የተጋረጠባት ፈተና አካል አለመሆናችንን ነው። እና እንጠይቅ! እንደዜጋ የቆምነው የት ነው?!
ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ ደራሲና ገጣሚ ሲሆኑ፥ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የሂዩማኒቲስ፤ የቋንቋዎች ጥናት የጆርናሊዝምና የኮሚኒኬሽን ኮሌጅ ውስጥ ደግሞ መምህር ናቸው። ከዚህ ቀደም ለህትመት ከበቁላቸው ሥራዎች ውስጥ የማይፃፍ ገድል፣ የራስ ምስል፣ ያልተከፈለ ስለት፣ የወይራ ስር ጸሎት፣ የማይጻፍ ገድል፣ የተስፋ ክትባት፣ እና ፍካት ናፋቂዎች የጠቀሳሉ። በተጨማሪም በብሔራዊ ቲያትር ቀርቦ በተመልካች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነትን ያገኘው “ደብተራው” የተሰኘው የሁለት ገጸባሕርያት ቲያትር (two-handler theater) ደራሲ ናቸው።
- ቃል በተግባር ― እያደነቅን ስጋታችንንም እንገልጻለን፤ አቧራው መሬት ላይ ያለ ግፍ፤ ሃሜቱም ሃቅ ነው
[አቶ ያሬድ ኃይለማርያም]
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በአዲስ አበባ የሠሯቸውን እና እየሠሯቸው ያሉ ድንቅ ነገሮችን አደንቃለሁ። ለዚህ ሥራቸው ሊመሰገኑ ይገባል። ከሠሯቸው ሥራዎቹ አንዱ የሆነውን የእንጦጦ ፖርክን የመጎብኘት ዕድል ገጥሞኛል። የሚያስደምም ድንቅ ሥራ ነው።
ከትላንት መግለጫቸውም ሁለት ነገር መረዳት ይቻላል። አንደኛው ሀገር ለማልማት ብዙ እቅድ እና ህልም እንዳላቸው ነው። ሁለተኛው ደግሞ ይህን ህልማቸውን እውን ለማድረግ አንባገነን እሰከመሆን የሚሄዱ መሆናቸውን ነው። አገሪቱ አሁን ያለችበትን ውጥንቅጥ እና አሳሳቢ ችግር፣ የተቃዋሚዎቻቸውን ቅሬታ እና በመንግሥታቸው ላይ የሚሰነዘሩ ቅሬታዎችን ‘አቧራ’ በሚል ገልጸውታል። “ሀሜት አቧራ እንጂ አሻራ መሆን አይችልም። አቧራውን ንቀን አሻራ ማኖራችንን እንቀጥላለን” የምትለዋ ንግግራቸው አለቃቸው የነበሩትን መለስን [የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን] አስታወሱኝ። ባጭሩ የመለስን የመታበይ ንግግር ነው የደገሙት። መለስ ‘ውሾቹ ይጮኻሉ፤ ግመሎቹም ጉዟቸውን ይቀጥላሉ’ ነበር ያሉት?
ታቃዋሚዎቻቸውን ውሻ አድርገው እና ተቋውሟቸውንም እንደ ውሻ ጩኸት ቆጥረው እሳቸው ከጉዟቸው ምንም አይነት ምድራዊ ኃይል እንደማያስቆማቸው ሊያውም በፓርላማ ፎክረው ነበር። የመሠረት ድንጋይ ጥለው ያስጀመሩትን የሕዳሴ ግድብ መጨረሻ ለማየትና ሪባን ለመቁረጥ ግን አልታደሉም። ግመሎቹስ ዛሬ ወዴት አሉ? አብይም ያች በሽታ እየታየችበት ነው። ሀገሪቱ ውስጥ ያለውን ያፈጠጠ እና አሳሳቢ ችግር እንደ አቧራ መቁጠር መጥፎ መታበይ ነው። አቧራው እንዲሰክን የሚቀርቡ ምክርና ወቀሳዎችንም እንደ ሀሜት መቁጠር ሌላው አሳሳቢ የክሽፈት ምልክት ነው።
ሕዝብ እየተራበ ነው፤ የኑሮ ውድነት ሌላ የቀውስ ምንጭ ነው፤ ያልተረጋጋ ፖለቲካም የልማት ጸር ነው፤ ጦርነትም አውዳሚ ነው፤ የመብት ጥሰቶች መበራከት የአፈና ሥርዓት መሳለጫ ነው። እነዚህ ችግሮች አቧራ አይደሉም። በእነዚህ ጉዳዮች ዙሪያ የሚቀርብብዎት ወቀሳና ነቀፌታዎች ሀሜት አይደለም። ልማቱን ግፉበት፤ መታበይዎን አቁመው ለዲሞክራሲ፣ ለሕግ የበላይነት፣ ለሰብዓዊ መብቶች እና ለፍትህ ቀናዕይ በመሆን እንደ ልማቱ አፋጣኝ መልስ ይስጡ። ካልሆነ ግን መካር እንደሌለው ንጉሥ… ይሆናሉ።
አቶ ያሬድ ኃይለማርያም መቀመጫውን ጄኔቭ ከተማ፥ ስዊዘርላንድ ያደረገ ስብስብ ለሰብዓዊ መብቶች በኢትዮጵያ (Association for Human Rights in Ethiopia) የተባለ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ናቸው።
ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረ–ገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forums) ላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።
-
AuthorSearch Results