-
Search Results
-
የፌደራል የሥነ ምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ሀብታቸውን ለማስመዝገብ ፈቃደኛ ያልሆኑ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ተጠያቂ አደረገ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የፌደራል የሥነ ምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ሀብታቸውን ለማስመዝገብ ፈቃደኛ ያልሆኑ 184 የሚሆኑ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጉዳያቸው በምርመራ እንዲጣራ እና ክስ እንዲመሠረት ነሐሴ 20 ቀን 2012 ዓ.ም ስም ዝርዝራቸውን ለኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እና ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን መላኩን አስታወቀ።
ኮሚሽኑ ሀብትና ንብረት የማስመዝገብ ግዴታ ያለባቸውን ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት ሀብታቸውን እንዲያስመዘግቡ በተለያየ ጊዜ በቴሌቪዥን፣ በሬድዮ እና በደብዳቤ ጥሪ ባስተላለፈው መሠረት አብዛኞቹ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት ሀብትና ንብረታቸውን አስመዝግበዋል።
ይሁን እንጂ በፌደራልና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደረጃ 184 የሚሆኑ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት ኮሚሽኑ ባስቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ሀብትና ንብረታቸውን ለማስመዝገብ ፈቃደኛ ሆነው አልተገኙም። ሀብትን ከማስመዝገብ ግዴታ ጋር ተያይዞ ፈቃደኛ ሆኖ ያልተገኙ አካላት በኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠባቂነት ሙስናን እና ብልሹ አሠራርን ለመከላከል በወጣው የሀብት ማሳወቅና ማስመዝገብ አዋጅ ቁጥር 668/2002 መሠረት ተጠያቂ እንደሚሆኑ ተደንግጓል።
በዚሁ መሠረት ኮሚሽኑ የሀብት ምዝገባ ሥራን በማካሄድ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ የመንግሥት የሥራ ኃላፊነትና የግል ጥቅም ሳይቀላቀሉ በየራሳቸው መንገድ የሚመሩበትን ግልጽ ሥርዓት እንዲኖር እያደረገ ባለው ሂደት ሀብታቸውን ለማስመዝገብ ፈቃደኛ ያልሆኑ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ተጠያቂ እንዲሆኑ እያደረገ ሲሆን፥ በቀጣይም ሀብታቸውን ለማስመዝገብ ፈቃደኛ በማይሆኑ የመንግሥት ተሿሚዎችና ሠራተኞች ላይ በሕጉ መሠረት ተመሳሳይ እርምጃ ለመውሰድ የሚገደድ መሆኑን ያሳውቃል።
ከባለስልጣናት ሀብት ምዝገባ ጋር በተያያዘ፥ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔና ምክትል አፈ-ጉባዔን ጨምሮ የምክር ቤቱ አባላት ነሐሴ 18 ቀን 2012 ዓ.ም የሀብት ምዝገባ እድሳት አካሂደዋል።
በሀብት ምዝገባ እድሳቱ ላይ የተገኙት የምክር ቤቱ አፈ-ጉባዔ የተከበሩ አቶ ታገሰ ጫፎ እንደተናገሩት፥ የፌደራል የሥነ ምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ሙስናና ብልሹ አሠራሮችን ለመከላከል እየሠራቸው ካሉት በርካታ ሥራዎች መካከል የሀብት ምዝገባ ሥራ አንዱ ነው። የሀብት ምዝገባ ሥራ ሙስናን ለመከላከል ዓይነተኛ መሣሪያ እንደመሆኑ መጠን ሊደገፍና ሊጠናከር ይገባል ሲሉ አፈ-ጉባዔው አክለው ገልጸዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሁሉም አካላት ሀብታቸውን በማስመዝገብ ሙስናና ብልሹ አሠራሮችን ለመከከላከል የሚደረገውን ጥረት መደገፍ እንደሚገባቸው አፈ-ጉባዔው አሳስበዋል።
አፈ-ጉባዔዎቹን ጨምሮ የሀብት ምዝገባ እድሳት ያካሄዱ የምክር ቤቱ አባላት ሀብታቸውን ያሳደሱበትን ሰነዶች ለፌደራል የሥነ ምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ክቡር አቶ ፀጋ አራጌ አስረክበዋል።
ምንጭ፦ የፌደራል የሥነ ምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሸን ጋዜጣዊ መግለጫ
አዲስ አበባ፥ ጥቅምት 13 ቀን 2012 ዓ.ም.
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ዋና ኮሚሸነር የእስረኞች ጉብኝት በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን።የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሸን ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ በፌዴራል ፖሊስ ተይዘው በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሸን ስር በአደራ ቁጥጥር ስር የሚገኙ ተጠርጣሪ ታሳሪዎችን ጥቅምት 10 ቀን 2012 ዓ.ም. ጐብኝተዋል።
ዋና ኮሚሸነሩ በዚህ ጉብኝታቸው ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. በባህር ዳር እና በአዲስ አበባ ከተማ ከተከሰተው የፖለቲካ ግድያ ጋር በተያያዘ እና በሌሎችም ተዛማጅ ጉዳዮች በቁጥጥር ስር ከሚገኙ እስረኞች ውስጥ፥ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አመራር እና አባሎች ውስጥ እነ አቶ ክርስቲያን ታደለ፣ አቶ በለጠ ካሳን፤ ከባልደራስ ባለአደራ ምክር ቤት ንቅናቄ አባሎች ውስጥ እነ አቶ ኤልያስ ገብሩ፣ አቶ ስንታየሁ ቸኰል እና አቶ መርከብ ኃይሌን፤ ከኢትዮጵስ ጋዜጣ ባልደረቦች አቶ ምሥጋና ጌታቸው እና አቶ አዳሙ ሁጁራን (አቶ አዳሙ በተጨማሪም የባልደራስ ባለአደራ ም/ቤት ንቅናቄም አባል ናቸው)፤ እንዲሁም «የተጠለፈው ትግል›› ከሚለው መጽሐፍ ሕትመት ጋር በተያያዘም በእስር የሚገኙትን አቶ ፍሬው በቀለ፣ አቶ ሳሙኤል በቀለ፣ አቶ መለሰ ማሩ፣ አቶ ጋዲሳ ዳንኤል እና አቶ አማረ ተፈራን፤ በተጨማሪም የሟች ብ/ጄኔራል አሳምነው ጽጌን ባለቤት ወ/ሮ ደስታ አሰፋንና ሌሎች በርካታ ታሳሪዎችን በማነጋገር ጉዳያቸው ያለበትን ደረጃ እና የእስር ሆኔታቸውንም ተመልክተዋል።
ዋና ኮሚሸነሩ ‹‹የሴቶች እስር ክፍሉ በአንፃራዊነት የተሻለ እና የጽዳት ደረጃው የተጠበቀ ሲሆን በሌላ በኩል ከ300 በላይ ታሳሪዎችን የያዘው የወንዶች እስር ቦታ እጅግ የተጨናነቀ፣ በውሃ መቋራረጥ እና በታሳሪው ብዛትም የጽዳት ደረጃው ዝቅተኛ ነው» ያሉ ሲሆን ታሳሪዎቹ በየእለቱ ከቤተሰብ፣ ወዳጅ እና የሕግ አማካሪዎቻቸው ጋር ለመገናኘት እንደሚችሉም ለማወቅ ችለዋል።
በሌላ በኩል “ታሳሪዎቹ ከ 3–4 ወር ያህል የፖሊስ ምርመራን ለማጠናቀቅ በሚል በእስር የቆዩና በአሁኑ ወቅት በሕግ የሚፈቀደው የተጨማሪ ምርመራ ጊዜ በአብዛኛው የተጠናቀቀ እና ቀሪውም በመጠናቀቅ ላይ ያለ በመሆኑ ከዚህ በላይ ታሳሪዎቹ በእስር ሊቆዩ ስለማይገባ እንደየአግባቡ በዋስ ወይም ያለዋስትና ከእስር እንዲለቀቁ ወይም ተዓማኒ የሆነ ክስ በመደበኛው የወንጀል ሕግ መሰርት ሊቀርብ ይገባል” በማለት ዋና ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።
“ከአንድ መጽሐፍ ሕትመት ጋር በተያያዘ የመጽሐፉ ፀሐፊ ነው ተብሎ ከተጠረጠረ ግለሰብ አንስቶ፣ የማታሚያ ቤቱ ባለቤት፣ የመጽሐፉ የፊት ገጽ ዲዛይን የሰራ ግለሰብ፣ የመጽሐፉ አከፋፋይ እና የመጽሐፉ የጐዳና ላይ ቸርቻሪ ሻጭ ሳይቀር እንዲሆም ሌሎች ታሳሪዎች ፍርድ ቤት በሚቀርቡበት ጌዜ ፎቶ አንስተሃል በሚል የተያዘ ጋዜጠኛ ጭምር ለዚህን ያህል ጊዜ በእስር መቆየታቸው አሳሳቢ ሁኔታ በመሆኑ አፋጣኝ እልባት እና የዋስትና መብት መከበር ያስፈልገዋል” በማለት ዋና ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።
ክቡር ዋና ኮሚሽነሩ በተጨማሪም ለጉዳዮቹ ሁሉ ሕጋዊ እልባት ለማግኘት ከሚመለከታቸው የስራ ክፍሎች ጋር በመነጋገር ኮሚሽኑ ክትትሉን እየቀጠለ መሆኑን አሳውቀዋል።
ጉብኝቱ በዓለም ዓቀፍ የእስር ቤቶች ጉብኝት ደረጃ መሠረት ያለ ቅድሚያ ማስታወቂያ የተደረገ ሲሆን የፖሊስ ኮሚሸኑ አመራሮች እና የጥበቃ ክፍል ኃላፊዎች ለዋና ኮሚሸነሩ ጉብኝቱ በማመቻቸት ኃላፊነታቸውን በመወጣታቸው ዋና ኮሚሸነሩ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ምንጭ፦ የኮሚሽኑ ፌስቡክ ገጽ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
ባህር ዳር (አብመድ)፦ ሰኞ ሐምሌ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ሹመታቸው የጸደቀላቸው የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ለምክር ቤት አባላትና ለሕዝቡ መልዕክት አስተላልፈዋል።
እንደ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝደንትነት ለመጀመሪያ ጊዜያቸው ንግግር ያደረጉት አቶ ተመስገን በመልዕክታቸው የወሰንና የማንነት ጥያቄዎች ለግጭት ምክንያት ሳይሆኑ በሕግ እንዲመለሱ እንደሚሠሩ ገልጸዋል።
በተጨማሪም የኢኮኖሚ ዕድገቱም ትኩረት ይሰጠዋል ብለዋል። ከዚህ ጋር በተያያዘም ለሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ለመኖሪያ ቤቶች ግንባታ እና ለኢንቨስትመንት ዕድገትም አትኩሮት እንደሚሰጥ አስገንዝበዋል።
አቶ ተመስገን ጥሩነህ አስከትለውም “የሕግ የበላይነትን ማስፈንም ለነገ የምንለው ጉዳይ አይሆንም” ብለዋል ለአማራ ክልል ሕዝብ ባስተላለፉት መልዕክት።
ለመሆኑ አቶ ተመስገን ጥሩነህ ድንቁ ማን ናቸው?
አቶ ተመስገን ጥሩነህ ምሥራቅ ጎጃም ዞን ብቸና ወረዳ ወይራ ቀበሌ ነው የተወለዱት። ከታችኛው የመንግሥት መዋቅር እስከ ፌዴራል ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎችም አገልግለዋል።
በትምህርት ደረጃ የ1ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በትውልድ ቀያቸው በጎተራ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል፤ የመለስተኛና 2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በብቸና በሚገኘው የበላይ ዘለቀ ትምህርት ቤት ነው ያጠናቀቁት። የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከማይክሮሊንክ ኮሌጅ በሶፍትዌር ዘርፍ እና የሁለተኛ ዲግሪቸያውን ደግሞ እንግሊዝ ሀገር ከሚገኘው ግሪንዊች ዩኒቨርሲቲ (University of Greenwich) በለውጥ አመራርና አስተዳደር ተከታትለዋል።
ርዕሰ መስተዳድር ተመስገን ጥሩነህ ድንቁ በ አማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት እና በፌደራል መንግስት ደረጃ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች አገልግለዋል።
በአማራ ክልል የርዕሰ መስተዳድሩ የፀጥታ እና ቴክኖሎጂ አማካሪ፣ የአማራ ገጠር መንገዶች ባለስልጣን ምክትል ሥራ አስኪያጅ፣ የአማራ ገጠር መንገዶች ኮንስትራክሽን ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የምሥራቅ ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ፣ የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር በመሆን ሠርተዋል።
ፌደራል መንግስት ደረጃ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (Information Network Security Agency) ዋና ዳይሬክተር እና የኢትዮ-ቴሌኮም ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ በመሆንም አገልግለዋል።
አቶ ተመስገን የሀገር መከላከያ ሠራዊት መረጃ ዋና መምሪያ፣ የኤሌክትሮኒክስ እና የቴክኒካል መረጃ መምሪያ ኃላፊ በመሆንም አገልግለዋል። በመከላከያ ሠራዊት ውስጥም እስከ ሻለቃነት ማዕረግ ደርሰዋል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ መሥራች ከመሆን ባለፈ በዚሁ መሥሪያ ቤት ከመምሪያ ኃላፊነት እስከ ዋና ዳይሬክተርነትም አገልግለዋል። እስከ ዛሬ ድረስ ደግሞ በሚኒስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ በመሆን ሲያገለግሉ ቆይተዋል።
ምንጭ፦ የአማራ መገናኛ ብዙሀን ድርጅት (አብመድ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
የገቢዎች ሚኒስቴር የተጠናከረ የጉምሩክ ስርዓት እና የተጠናከረ ኬላ ፍተሻ ቁጥጥር ስርዓት መዘርጋቱን ተከትሎ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚያዙ ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያዎችና የተለያዩ አገራት ገንዘቦችም (የገንዘብ ኖቶችም) ጨምረዋል
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – ለሕገ-ወጥ የገንዘብ እና የጦር መሣሪያ ዝውውር ስጋት ናቸው የተባሉ ቦታዎችን በመለየት ተጨማሪ 36 አዳዲስ የጉምሩክ ኬላዎች መቋቋማቸውን የኢፌዴሪ የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ።
አዳዲስ ኬላዎችን በመክፈት እንዲሁም ቦታቸው ትክክል ያልነበሩ ነባር ኬላዎችን ወደ ትክክለኛ ቦታ በመቀየር ሕገ-ወጥ የገንዘብና የጦር መሣሪያ ዝውውርን ለመከላከል ከምንጊዜውም በላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን የገቢዎች ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አዲሱ ይርጋ ለኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) ተናግረዋል።
ችግሩን ለመከላከል በተደረው ጥናት በኬላዎች ላይ 1 ሺህ 400 የፖሊስ ኃይል እንደሚያስፈልግ በተጨማሪ ተገልጿል።
ጥናቱን ተከትሎ ተጠሪነቱ ለፌደራል ፖሊስ፣ ስምሪቱ በጉምሩክ ኮሚሽን የሆነ ጥሩ ሥነ ምግባር የተላበሰ፣ ለቦታው የሚመጥን የጉምሩክ ተቆጣጣሪ ፖሊስ እንዲቋቋምና ወደ ሥራ እንዲገባ መደረጉን ዳይሬክተሩ አቶ አዲሱ ይርጋ ገልጸዋል።
የተጠናከረ የጉምሩክ ስርዓት እና የተጠናከረ ኬላ ፍተሻ ቁጥጥር ስርዓት መዘርጋቱን ተከትሎ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚያዙ ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያዎችና ገንዘቦችም ጨምረዋል ነው የተባለው።
የፌዴራል ፖሊስ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ጀላል አብዲ በበኩላቸው ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያ የራሳቸውን ገንዘብ ለማግኘት በሚንቀሳቀሱ ሕገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች ከተለያዩ አገራት (በተለይም ከጎረቤት አገራት) ወደ አገር ውስጥ ይገባል ብለዋል።
የጦር መሣሪያዎቹን መዳረሻ ለማወቅ ጥናት የሚጠይቅ ቢሆንም ከሁኔታ ግምገማ በመነሳት በአገር ውስጥ ጸጥታና የደህንነት ስጋት ያለ በመሆኑ ማንኛውም ሰው ራሱን እና ንብረቱን ለመጠበቅ የጦር መሣሪያ ፍላጎት እንደ አንድ ምክንያት ሊወሰድ ይችላል ብለዋል። በሌላ በኩል ደግሞ የተለያየ ዓላማና ግብ ያላቸው የታጠቁ ቡድኖችም የጦር መሣሪያ መዳረሻ ሊሆኑ እንደሚችሉም ጠቁመዋል ዳይሬክተሩ።
የዘርፉን ችግር ለመቅረፍ የጦር መሣሪያ ቁጥጥር ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ውይይት እየተደረገበት መሆኑ ይታዋሳል።
ምንጭ፦ ኢቢሲ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
——
ሌሎች ዜናዎች፦- በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አማካኝነት የተሠራው ባለሞተር ማረሻ ተመረቀ
- አለርት ሆስፒታል ውስጥ ዘመናዊ የሕፃናት ሆስፒታል እና የአደጋ ሕክምና ማዕከል ይገነባሉ
- ዩኒቨርሲቲዎች በሦስት መስኮች ተደልድለው እንዲያስተምሩ የሚያስችል ጥናት እየተጠናቀቀ ነው
- የወልድያ ዩኒቨርሲቲ እና ጎተንበርግ ዩኒቨርሲቲ በትብብር የቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ የትምህርት መስክ ሊጀምሩ ነው
- ሀገር በቀል የመድኃኒት አምራቾች መሠረታዊ ችግሮች በጥናት ሊለዩ ይገባል ― የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ