Search Results for 'አማራ ክልል'

Home Forums Search Search Results for 'አማራ ክልል'

Viewing 15 results - 1 through 15 (of 120 total)
  • Author
    Search Results
  • Semonegna
    Keymaster

    የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የሠጠው መግለጫ

    የአማራ ሕዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ወንድምና እህት ሕዝቦች ጋር በመሆን የኢትዮጵያን ሕልውና ለማስጠበቅ ያልከፈለው ዋጋ የለም፡፡

    የኢትዮጵያዊ አንድነትን ለማጽናትም ሲል ከመክፈል የሚሰስተው ዋጋ የለም፡፡ በመሆኑም የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትም ሆነ መላው የክልሉ ሕዝብ በሀገር ሕልውና እና በኢትዮጵያ አንድነት ጉዳይ ላይ ያለው አቋም የጊዜ እና የሁኔታዎች መፈራረቅን ተከትሎ የማይለዋወጥ ጽኑ ሀቅ ስለመሆኑ በታሪክና በዜጎች ህሊና እንዳይፋቅ ሆኖ የተከተበ እውነታ ነው፡፡

    ስለሆነም የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በክልላችን ውስጥ የሚተለሙም ሆነ የሚፈጸሙ ማንኛውም ዓይነት ተግባራት ከዚህ ብሔራዊ መዳረሻ አንጻር የሚቃኙ መሆናቸውን መገንዘብ ያስፈልጋል። ማንኛውም ዓይነት ተቋማዊ መዋቅሮች የሚደራጁበትም አልፋ እና ኦሜጋዊ አመክንዮ ይኸው ነው፡፡

    ከሰሞኑ በሀገር አቀፍ ደረጃ ዋና አጀንዳ ከሆኑት ብሔራዊ ጉዳዮች መካከል አንዱ የሆነውና በሁሉም ክልሎች የሚገኙ የልዩ ኃይል አደረጃጀቶችን መልሶ የማደራጀት ተግባር ዋነኛ እና ብቸኛ ምክንያትም ዓላማው የኢትዮጵያን ሕልውናን የበለጠ የማበርታት የጋራ ግብን ያነገበ፣ በተሟላ ሀገራዊ ጥናት ላይ የተመሠረተ፣ የሕዝቦችን አንድነትንና ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የተተለመ እንዲሁም የጋራ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታን እውን ለማድረግ በሁሉም ክልሎች ታምኖበት የተገባበት ወሳኝ ተግባር ነው።

    የአማራ ክልል ልዩ ኃይል በክልሉ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ከሀገር መከላከያ ሠራዊትና ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በጋራ በመሆን የአማራ ክልልን ሕዝብ ሠላም እና ጸጥታን ለማስከበር በቅንነትና በቆራጥነት አገልግሏል፡፡

    ከክልል አቀፍ ውለታው ባሻገር በኢትዮጵያ ሕልውና ላይ ተጋርጦ የነበረን ከፍተኛ አደጋ ለመቀልበስ ሲል ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ወንድምና እህት ሕዝቦች ጋር በመሆን በኢትዮጵያዊነት የላቀ ሥነ-ልቦናዊ ከፍታ ሁሉንም ዓይነት መስዋዕትነት ከፍሎ ኢትዮጵያና አትዮጵያዊነት ላይ የተቃጣን አደጋ በታማኝነት አምክኗል፡፡ ይህ አኩሪ ገድልና ውለታ ሁልጊዜም በታሪክና በትውልድ ልቦና ውስጥ እየተዘከረና ጽንቶ የሚኖር ታላቅ ተግባር ነው፡፡

    ይህን መሰሉን ብሔራዊ ውለታ የበለጠ ለማጎልበትና ለማስፋት የሚቻልበትን ሁኔታ ለማመቻቸት አማራ ክልል ጨምሮ በሁሉም ክልላዊ መንግሥታት ውስጥ የሚገኙ የልዩ ኃይል አደረጃጀቶችን ያሰባሰበ በጥናት ላይ የተመሠረተ መልሶ የማደራጀት ሥራ በሁሉም ክልሎች በየደረጃው ካለው የፀጥታ አመራር፣ የመንግሥት አመራር፣ የልዩ ኃይል አመራርና አባላት፣ በጉዳዩ ዙሪያ ውይይት የተደረገበትና እየተደረገበት ያለ በሂደት ላይ የሚገኝ የጋራ ሀገራዊ ተግባር ነው።

    ይህ የልዩ ኃይል ፖሊስ አደረጃጀቶችን መልሶ የማደረጃት ወይም የሪፎርም ሥራ በሁሉም የፌደራልና ክልላዊ መንግሥታት መሪዎች የጋራ ስምምነትና እንደ አንድ ሀገር አንድ ጠንካራ የፌደራልና የክልል የፀጥታ መዋቅር እንዲኖረን ታስቦ የተለያዩ አማራጮች ለልዩ ኃይል አባላቶቻችን ያቀረበ እና ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን በኩር ያደረገ ሀገር አቀፍ ታሪካዊ ተግባር ነው፡፡ ተግባሩም ለሁሉም ክልል የልዩ ኃይል አደረጃጀቶች የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የፌደራልና የክልል መደበኛ ፖሊስ፣ የፌደራልና የክልል የማረሚያ ቤቶችን ፖሊስ አባል እንዲሆኑ አማራጮች ያቀረበ ብሔራዊ ተግባር ነው።

    በቅርቡ በመንግሥት የተጀመረው የልዩ ኃይል ፖሊሶች የሪፎርም ተግባር እውነታዉ ከላይ በተቀመጡት አማራጮች ለሁሉም ክልሎች የልዩ ኃይል አባላት እንደየፍላጎታቸው በቀረቡት አማራጮች እንዲካተቱ ታሳቢ ያደረገ የፌደራልና የክልል የፀጥታ አካላትን የማጠናከር በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተከናወነ የሚገኝ ብሔራዊ ተግባር ነው።

    ይሁን እንጂ እውነታዉ ይሄ ሆኖ ሳለ አንዳንድ አካላት የአማራ ክልል ልዩ ኃይልን አየር ላይ እንዲበተን እየተደረገ ነው የሚል ከእውነት የራቀ ፍፁም በተሳሳተ መንገድ ሀሰተኛ መረጃዎችን በማሰራጨት የአማራን ሕዝብ ውስጣዊ ሰላምና አንድነት የሚያደፈርስ፣ የልዩ ኃይሉን አንድነት የሚረብሽ፣ ባልተገባ መንገድ ጥርጣሬ ውስጥ እንዲገባ የሚያደርጉ እንቅስቃሴ ላይ ተጠምደው ይገኛሉ። ድርጊቱም ሕዝባችንና የልዩ ኃይል አባሎቻችንን በተጨባጭ እየረበሸ ይገኛል።

    ስለሆነም መላው የልዩ ኃይል አባላትና መላው የክልሉ ሕዝብ እንዲገነዘቡት የምንፈልገው መንግሥት ይህንን የመልሶ ማደራጀት ሥራ የሚከውነው የልዩ ኃይላችንን የሰው ኃይል ለበለጠ ፋይዳ ላለው ተልዕኮ መልሶ የማደራጀትና ብቁ የማድረግ ሀገራዊና ክልላዊ ፋይዳ የማዘጋጀት ተግባር እንጅ በመልሶ ማደራጀቱ ሂደት ምንም ዓይነት የሚበተንም ኃይል የሌለ መሆኑን ግንዛቤ ሊያዝበት ይገባል።

    ስለሆነም መላው የአማራ ሕዝብ በአንዳንድ አፍራሽ የሚዲያ ቡድኖች በሚነዛው አሉቧልታ ሳይታለልና ሳይደናገር እንደ አንድ ሕዝብ ያለውን ታሪኩን እና ሥነ ልቦናውን በሚመጥነው የኢትዮጵያዊነት ላዕላዊ ማእቀፍ ጥላ ስር በመሰባሰብ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊ አንድነትን የማጽናት ሂደትን እንዲደግፍ ጥሪ እናቀርባለን፡፡

    የተከበራችሁ የክልላችን ሕዝቦች፥ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የክልሉን ሕዝብ መብትና ጥቅም የሚጋፋ የትኛውንም ዓይነት ውሳኔ ተግባራዊ እንደማያደርግ ሕዝባችን ሊያውቀው ይገባል።

    የተከበራችሁ የክልላችን የልዩ ኃይል ፖሊስ አባላት እንዲሁም መላው ሕዝባችን፥ ለራሳቸው ጥቅምና ፖለቲካዊ ዓላማ ሲሉ ክልላችንን የትርምስ ቀጠና ለማድረግ ከሚሠሩ አካላት ራሳችሁን በመጠበቅ የክልላችን የፀጥታ ኃይል ብቁ ዘቦች ሁናችሁ ሰላምና ፀጥታን በማስጠበቅ ሥራችሁ እንድትተጉ እያሳሰብን የተጀመረውን ልዩ ኃይሉን መልሶ የማደራጀት ሥራ መላው ሕዝባችንንና ልዩ ኃይላችንን በማወያየት እና በመተማመን የሚፈፀም በመሆኑ በየካምፓችሁ ወይም በየተመደባችሁበት የሥራ ቦታ ተረጋግታችሁ በትግስት እንድትጠብቁ የክልሉ መንግሥት ጥሪውን ያስተላልፋል።

    የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት
    መጋቢት 29/2015 ዓም
    ባሕር ዳር፥ ኢትዮጵያ

    ምንጭ፦ የክልሉ ሕዝብ ግንኙነት

    Amhara Regional State የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት

    Semonegna
    Keymaster

    “ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ በሚቀጥሉት አስር ዓመታትም የሚቀጥል ነው – አቶ መላኩ አለበል የኢንዱስትሪ ሚኒስትር

    አዲስ አበባ (ኢፕድ) – “ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ በሚቀጥሉት አስር ዓመታትም ተጠናክሮ የሚቀጥልና ራሱን የቻለ ፕሮጀክት ቢሮ ተቋቁሞለት በጥብቅ ዲስፕሊን እየተመራ እንደሚገኝ ተገለጸ፡፡

    የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል በተለይም ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት (ኢፕድ) እንደገለፁት፥ “ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ እሳቤው በጣም ሰፊ እና በሚቀጥሉት አስር ዓመታትም ተጠናክሮ ይቀጥላል።

    እንደሀገር ለኢትዮጵያ የማምረት ጉዳይ የህልውና ጉዳይ ነው፤ ኢትዮጵያ ማምረት አለባት ያሉት ሚኒስትሩ፥ የለመድነውና ደጋግመን የምንለው መሪ ሀሣብ አለን። ይህም “ኢትዮጵያ ለዘላላም ትኑር” እንላለን፡፡ ኢትዮጵያ ዘላለም መኖር የምትችለው ማምረት ስትችል ነው ብለዋል።

    ‘የምንፈልጋት ጠንካራ ኢትዮጵያ እንድትኖር ለማድረግ ማምረት አለብን፤ ሁሉም ዘርፎችም ማምረት አለባቸው’ ያሉት ሚኒስትሩ፥ “ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ በሚጀምርበት ወቅት የማምረቻ (manufacturing) ኢንዱስትሪ ላይ ያሉትን ነባራዊ ሁኔታዎች ከግምት ውስጥ በማስገባት በሀገር ምርትና ምርታማነት በማተኮር የመነጨ የአንድ ተቋም ሳይሆን የሀገር ሉዓላዊነት አጀንዳም ጭምር መሆኑን አመልክተዋል።

    ለመልፋት፣ ለመድከምና በኢኮኖሚ ጠንካራ ለመሆን መሥራት ያለብንን ባለመሥራታችን ምክንያት ወደ ኋላ ቀርተናል፤ በመሆኑም “ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ የሉዓላዊነት፣ የመኖርና የህልውና እሳቤ ነው። “ኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ ከማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ጋር የተያያዘ ፖለቲካውንም፣ ኢኮኖሚውንም ማኅበራዊ ጉዳይንም የሚነካ ነው። በመሆኑም ለጠላት ያልተንበረከከ ጉልበት ለስንዴ መንበርከክና እጁን መዘርጋት እንደሌለበት አስገንዝበዋል።

    “ያለፉትን 6 ወራት የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አፈፃፀም ከፌደራልና ክልል የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት ጋር በአፍሪካ ሕብረት አዳራሽ ዛሬ [ኅዳር 9 ቀን፥ 2015 ዓ.ም] ገምግመናል። በተገኙ አበረታች ውጤቶችና ቀጣይ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ላይም ተግባብተናል።” የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው

    “ኢትዮጵያ ታምርት” የንቅናቄ አጀንዳ ሆኖ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስጀምረውት እስከ ታች ወረዳ ድረስ አምራቾች ማግኘት የሚገባቸውን ድጋፍ ማግኘት አለባቸው በሚል መነሻ የመጣ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፥ ከዚህ አኳያ አንዱ የተሳካው ግብ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ አጀንዳ እንዲሆን ማድረግ እንደነበር ተናግረዋል።

    በተጨማሪም አምራቾች ከእያንዳንዱ የመንግሥት አካልም ማግኘት ያለባቸውን ድጋፍ ማግኘት አለባቸው የሚለው እሳቤ ስኬታማ እየሆነ ነው፤ አጀንዳም ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት።

    “በየትኛውም ሀገር ላይ ኢንዱስትሪዎች ጠንካራ የፖሊሲ ድጋፍ የሚያደርጉ መንግሥታት ውጤት ናቸው” ያሉት አቶ መላኩ አለበል፥ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች ኢንዱስትሪዎች የገጠሟቸው ማነቆዎች እንዲፈቱ በማድረግ ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክተዋል። በዚህም የቆሙ ኢንዱስትሪዎች ችግራቸው ተፈትቶ ወደ ሥራ ተመልሰዋል፤ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች ወደ ዘርፉ ገብተዋል፤ ያለአግባቡ የባከኑ መንግሥትና የሕዝብ ሀብቶች እንዲመለሱ ማስቻሉን አብራርተዋል።

    በኢትዮጵያ ትልቁ ሀብት መሬት ነው። ያለአግባብ መሬት ከያዙት በመቀበል ለአልሚዎች ተላልፏል። ችግሮችን በመለየት እስከታችኛው መዋቅር ድረስ ችግሮቻቸውን ለመፍታት አቅም ሰጥቷል፤ የአደረጃጀት ችግሮችም ተፈትተዋል። በመሆኑም “ኢትዮጵያ ታምርት” የሚለው ንቅናቄ ትልቅ ውጤት አስገኝቷል። ይህም የአንድ ዓመት ዘመቻ ሳይሆን በዘላቂነት የሚሠራ ነው። የፖሊሲ ማሻሻያዎችን በማድረግ፥ ያለውን ፖሊሲ በመተግበርና አማራጮችን በመመልከት የሚስተካከሉ ጉዳዮች መኖራቸውንም አስገንዝበዋል።

    ባለፈው ዓመት (የ2014 በጀት ዓመት) የአስር ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርቱን ለኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበበት ጊዜ፥ በበጀት ዓመቱ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ውጤት ማምጣቱን ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገልጾ ነበር

    ምንጭ፦ ኢፕድ

    ኢትዮጵያ ታምርት

    Semonegna
    Keymaster

    ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ የተግባር ምክር ቤት የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

    ሀገራችን ኢትዮጵያ ተገዳ የገባችበትን የህልውና ጦርነት በጋራ ለመመከት በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊን ከሕዝባቸው ጎን በቆራጥነት በመቆም የሀገርን ሉአላዊነት ለማስከበር በሚደረገው ዘመቻ የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

    ይህ የህልውና ጦርነት በውጭ ሀገር የምንገኘውን ኢትዮጵያውያን እንቅልፍ የነሳና ሀገራችን እንደ ሀገር እንዳትቀጥል በወያኔ ጁንታ ቡድን፣ በአልሸባብ፣ እና በሸኔ እንዲሁም በውጭ ሀገር የሚገኙ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች በቅንጅት የከፈቱብን ጦርነት ብሔራዊ ክብራችንና የሚነካ የሀገራችንን ሰላም የሚያውክ በመሆኑ በእጅጉ አሳስቦናል።

    ስለዚህ መንግሥት በሆደ ሰፊነት ቀደም ሲል የወሰዳቸውን ቁርጠኛ የሰላም ፍላጎቶቹን በማድነቅ የሰላም ድርድሩ ውጤታማ እንዲሆን ሙሉ ድጋፍ ስንሰጥ መቆየታችን እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በአሸባሪነት የተፈረጀቱ ፀረ-ሰላም ኃይሎች ከሰላም ይልቅ ጦርነትንና እልቂትን መርጠው የከፈቱብንን የአጥፍቶ መጥፋት ጦርነትን በጥብቅ አውግዘን መንግሥት እየወሰደ ያለውን እርምጃ እንደግፋለን።

    የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የተግባር ምክር ቤት የአሸባሪውን ጁንታ ቡድን እንዲሁም አልሸባብና ሸኔን ማውገዝ ብቻ ሳይሆን ለሀገር ሕልውናና ለሕዝባችን ሰላምና ጥቅም ስንል ከመንግሥትና እንዲሁም ከመከለከያ ሠራዊታች ጎን በመቆም የዜግነት ድርሻችንን ለመወጣት የትግባር ምክር ቤቱ ዝግጁ መሆናችንን እናረጋግጣለን።

    በእርግጥ ዲያስፖራው ዛሬም ነገም ለሀገሩ ለወገኑ ድጋፉን አጠናክሮ እንደቀጠለ ቢሆንም በሀገራችን ውስጥ በተፈጠረው ሀገር የማዳን ዘመቻ በዘር፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ እምነት ሳንከፋፈል ከስሜታዊነትና ከኩሪፊያ በመውጣት ለነገዋ ኢትዮጵያ የተሻለ ነገር ለማምጣት፣ የተሻለችውን ኢትዮጵያ ለማየት ትግሉን የሚጠይቀውን ማንኛውንም ድጋፉ እንድናደርግ ምክር ቤታችን በድጋሚ በመላው ዓለም ለሚገኙ የኢትዮጵያዊያንና ለኢትዮጵያ ወዳጆች ሁሉ ጥሪ ያቀርባል።

    መንግሥት ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ከፍታ ለማድረስ፣ ችግሮችን በውይይት በመፍታት፣ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት፣ የሀገራችንን ፖለቲካ ለማዘመን፣ ውስጣዊ ችግሮቻችን በተገቢው መንገድ ለመፍታት ግጭቶችና የጦርነትን ውድመት እንዳይቀጥል በቁርጠኝነት ተነሳስቶ ለሀገረ መንግሥት ግንባታው መሠረት ለመጣል ፖለቲካዊ ችግሮችን በአግባቡ ፈትሾ ሁሉን አቀፍ ውይይትና ድርድር ማድረግ፤ በሀገሪቱ ምክር ቤት በአሸባሪነት የተፈረጁትን ቡድኖች ወደ ዘላቂ ሰላም የጠረንጴዛ ድርድር እንዲቀመጡ ወስዶት የነበረውን የሰላም ጥረት አሁንም ወደፊትም እንዲቀጥል ምክር ቤታችን መደገፉን ይቀጥላል።

    ነገር ግን ከጦርነት በተሻለ ሰላምን መምረጥ ትርፋማነቱ ቢያዋጣም አሸባሪውና ጎጠኛው የጁንታው ቡድን የአማራና አፋርን ሕዝብ በመውረር የትግራይን ሕዝብ አግተው በሰላማዊ ሕዝብና በመሠረተዊ የልማት ተቋማት ላይ ያደረሱትን መጠነ ሰፊ ውድመት መልሰን ለማቋቋም እርብርብ በምናደርግበት ወቅት የሀገርን ሉአላዊነት አደጋ ላይ ለመጣል ለሦስተኛ ዙር የተከፈተብን ታሪክ ይቅር የማይለው ጦርነት በእጅጉ አስቆጥቶናል። ስለዚህ፦

    1ኛ የአማራና የአፋር ክልልን በመውረር ሲዋጉና አመራር ሲሰጡ የነበሩትን እንዲሁም እድሚያቸው ለውትድርና ሞያ ያልደረሱ የትግራይ ህፃናትን በመመልመል ለጦርነት ያሰልፉትን የወያኔ ጁንታ አመራሮች ተለይተው በጦር ወንጀለኝነትና በሀገር ክህደት ክስ ተመሥርቶባቸው በአስቸኳይ ለፍርድ እንዲቀርቡ መንግሥትን እንጠይቃለን።

    2ኛ ሀገራችን በገጠማት የሰላም ማጣት ችግርና ተገዳ ከገባችበት የህልውና ጦርነት በተጨማሪ የሕዝብ ሞትና የሥነ ልቦና ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ የሐሀት ቅስቀሳና የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ በሚያደርጉ ቅጥረኛ ሚዲያዎች፣ አለአግባብ ለመበልፀግ የኢኮኖሚ አሻጥር በሚፈፅሙ ነጋዴዎች፣ በተለይ የመንግሥት ሙሰኞችና ሌቦች ላይ ያለምንምንም ይቅርታ ጠንካራ እርምጃ መንግሥት እንዲወስድ እናሳስባለን።

    3ኛ መንግሥት የሚቻለው ሁሉ ጥረት በማድረግ ለሀገር ጠቀሜታ ሲል ዘላቂ መፍትሔ የሚያመጡ አካሄዶችና አዳዲስ ስልቶችን (strategies) መንደፍ አለበት። በተለይ ከዲያስፖራው ማኅበረሰብ ጋር እጅ ለእጅ ተያይዞ በጋራ የዓለም አቀፉን ሕብረተሰብ በተሳሳተ ፕሮፖጋንዳ የሚያውኩትን የሚዲያ ተቋማትን ተጠያቂ ለማድረግ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለድፕሎማቶቹን ጥብቅ መመሪያ እንዲሰጥና ለተግባራዊነቱም ልዩ ክትትል እንዲያደርግ በጥብቅ እናሳስባለን።

    በመጨረሻም ምክር ቤቱ ወደፊት ከሚያደርጋቸው የድጅታል ዲፕሎማሲ ትግል በተጨማሪ ጦርነቱን በአጭር ጊዜ ለመጨረስ በሚደረገው የህልውና ጦርነት የዘማቹ ሠራዊት ደጀን በመሆን ጠንካራ ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ መሆናችንን ለኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት እናረጋግጣለን።

    የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የተግባር ምክር ቤት (ኢዳተም)

    Semonegna
    Keymaster

    “በኢዜማ እምነት አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት ባለበት እስከቀጠለ ድረስ እንኳን ዴሞክራሲያዊ ኢትዮጵያን መገንባት ይቅርና እንደ ሀገር የመቀጠል ህልውናችንም ቢሆን አደጋ ላይ የወደቀ ነው!!”
    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)

    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ሀገራችን ላይ እውን እንዲሆኑ ከሚታገልላቸው የፖለቲካ መሠረቶች አንዱ እና ዋነኛው የዜጎች እውነተኛ የስልጣን ባለቤትነትንና ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ነው!!

    ፌደራሊዝም “የፖለቲካ ስልጣን ምንጭ ሕዝብ ነው” የሚለውን ትልቅ የዴሞክራሲ መርህ ሰፋ ያለ ትርጉም በመስጠት፥ “ሕዝብ በሚኖርበት አከባቢ ራሱን በራሱ ማስተዳደር አለበት” የሚለውን መርህ ተግባራዊ የሚያደርግ የአስተዳደር መዋቅር ነው።

    ፓርቲያችን ኢዜማ ኢትዮጵያ ካላት ሰፊ የቆዳ ስፋት፣ ከአንድ ቦታ ሁሉን ማስተዳደር የማይመች መልከአ ምድር፣ በተለያየ ደረጃ ያለ ኢኮኖሚ በየአካባቢው ባለበት፣ ብዝኀ ማንነት ማለትም ብዙ ዘውግ፣ ቋንቋ፣ ባህልና ሃይማኖት አንፃር ያልተማከለ ሥርዓት ያስፈልጋል ብሎ ያምናል። ካልተማከሉ የፖለቲካ ሥርዓቶች ውስጥ ደግሞ የመጀመርያው ምርጫ ፌደራሊዝም ነው።

    እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገሮች ፌደራሊዝም ተመራጭ የሚሆነው በሁለት ዋነኛ ምክንያቶች ነው። አንደኛው ሕዝብ በአካባቢው ራሱን በራሱ ማስተዳደር እንዲችል ሙሉ መብትና ስልጣን የሚሰጥ የመንግሥት ሥርዓት ስለሆነ ሲሆን፤ ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ፌደራሊዝም ከአሐዳዊ መንግሥት በተሻለ ብዝኀነትን ማስተናገድ መቻሉ ነው።

    ኢትዮጵያ ባለፉት 30 ዓመታት የተከተለችው የፌደራሊዝም ሥርዓት፤ ፌደራል ሥርዓቱን የፈጠረው ሕገ መንግሥት ሥራ ላይ ከመዋሉ አስቀድሞ በነበሩ ሂደቶች ብዙኃኑን ያላሣተፈ መሆኑ ዴሞክራሲያዊነቱን አሳጥቶታል። ከዚያ በተጨማሪ የፌደራሊዝም ዋና ጥቅም ለሕዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት በመስጠትና በዘውግና በቋንቋ ልዩነቶች ላይ ተመስርተው የሚነሱ ግጭቶችን ማስወገድ ሆኖ እያለ፤ የኢትዮጵያ ፌደራሊዝም ግን ራሱ የተመሠረተው በዘርና በቋንቋ ልዩነቶች ላይ ስለሆነ ማስወገድ የሚገባውን ችግር ጭራሹኑ አባብሶታል። በተለይ የፌደራል ሥርዓቱ ማንነትንና የመሬት ባለቤትነት በሕገ መንግሥት ደረጃ እንዲያያዝ በማደረጉ ከዚህ ቀደም በመካከላቸው የሚለያያቸው ወሰን ባልነበረ ኩታ ገጠም በሆኑ ወረዳዎች በሚኖሩ የዘውግ ማኅበረሰቦች መካከል ደም ያፋሰሱ በርካታ ግጭቶች እንዲካሄዱ ምክንያት ሆኗል። አሁንም መሆኑን ቀጥሏል።

    በኢዜማ እምነት አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥት ባለበት እስከቀጠለ ድረስ እንኳን ዴሞክራሲያዊ ኢትዮጵያን መገንባት ይቅርና እንደ ሀገር የመቀጠል ህልውናችንም ቢሆን አደጋ ላይ የወደቀ ነው ብሎ ያምናል።

    ይህንን አደጋ ለማስወገድ የፌደራል ሥርዓቱ እንዴት መመሥረት አለበት? ክልሎች እንዴት መዋቀር አለባቸው? በክልሎችና በፌደራል መንግስቱ መካከል ያለው ግንኙነት ምን መምሰል አለበት? የሚሉና ከፌደራል መንግሥትና ከክልል መንግሥታት ማን የበለጠ ስልጣን ይኑረው? ለሚሉት ጥያቄዎች እና ሌሎች ሀገሪቱን አደጋ ላይ ጥለዋታል የሚባሉ የሕገ መንግሥቱ ክፍሎችን አንድ በአንድ ነቅሶ በማውጣት ከፊታችን ሀገራችን ታደርገዋለች ተብሎ በሚጠበቀው ሀገራዊ ምክክር ላይ ማቅረብ የግዴታ አስፈላጊ ነው ብለን እናምናለን።

    ኢዜማ ለዚህ ምክክር ጠንካራ አማራጭ ሀሣቦችን ይዞ ለመቅረብ ሀገራዊ ምክክሩ ላይ ብቻ ትኩረትን ሰጥቶ የሚሠራ ኮሚቴ በማዋቀር እየሠራ ሲሆን ዝግጅቱንም አጠናቆ የመድረኩን መጀመር እየተጠባበቀ ይገኛል።

    ባለፉት ጥቂት ዓመታት በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የ “ክልል ወይንም ዞን እንሁን” የሚሉ ጥያቄዎች በስፋት እየተደመጡ ነው። ይህንንም ተከትሎ ሁለት ሕዝበ-ውሳኔዎች ተደርገው ሕገ መንግሥቱ ሲጸድቅ ከነበሩት ዘጠኝ ክልሎች ሁለት ተጨምረው የክልሎች ቁጥር ወደ 11 ከፍ ብሏል።

    አንዳንዶቹ የክልልነት ጥያቄዎች የሚቀርቡት ሕዝብ በወከላቸው እንደራሴዎች ሳይሆን ስልጣን ላይ ባሉ አካላት የግል የፖለቲካ እና ሌሎች ጥቅሞችን የማግበስበስ ፍላጎት መነሻነት መሆኑን ፓርቲያችን በተደጋጋሚ ገልጾ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም ጥሪ አስተላልፏል። አሁንም በዚህ ተግባር የተጠመዱ ስልጣን ላይ ያሉ አካላት ከዚህ ተግባር እንዲቆጠቡ እናሳስባለን።

    ማኅበረሰቡም ለእነዚህ ጥቅመኛ ግለሰቦች የግል ፍላጎት ማስፈጸሚያ መሣርያ ከመሆን ይልቅ ከታችኛው የአስተዳደር መዋቅር ጀምሮ ያጋጠሙትን አስተዳደራዊ በደሎች ለመፍታት በቅርብ ጊዜ ውስጥ ይደረጋል ተብሎ በሚታመነው የአካባቢ፣ የቀበሌ እና የወረዳ ምርጫ በንቃት በመሣተፍ በአግባቡ ሊያስተዳድሩት የሚችሉ ግለሰቦችን እንዲመርጥ ጥሪ እያስተላለፍን፤ የሀገራዊ ምክክሩንም ሂደት በተመሣሣይ እንዲሁ በአንክሮ እንዲከታተል እንጠይቃለን።

    ከዚህ በተጨማሪ መንግሥት የፌደራል ሥርዓቱ ያሉበት እንከኖች ሳያንስ ያለ ሕዝብ ፈቃድ እና ይሁንታ እንዲሁም አማራጭ ሐሣቦችን ሣይመለከት “የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልላዊ መንግስትን በክላስተር ለማዋቀር” ብቸኛው አማራጭ አድርጎ ይዞ መምጣቱ ፈጽሞ ትክክል አለመሆኑን እና ሀገራዊ ምክክሩ ላይ አጀንዳ ሆኖ ይቀርባል ተብለው ከሚታመንባቸው አንዱ የሆነውን የፌደራል አወቃቀር ከወዲሁ በመነካካት ሀገራዊ ምክክሩ ላይ እምነት እንድናጣ ከማድረግ ሊቆጠብ ይገባል።

    ኢዜማ ፌደራሊዝም ራስን በራስ ከማስተዳደር ጋር የተያያዘ በመሆኑ፤ በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ሕዝቡ ራሱን ለማስተዳደር መፈለጉ በራሱ ችግር አለመሆኑን ይገነዘባል፡፡

    የዞን እና ክልል የመሆን ጥያቄ ያላቸው ማኅበረሰቦች ምንም እንኳ አሁን ሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥት አንቀጽ 47(2) መሠረት ጥያቄዎችን የማንሳት ሕገ መንግሥታዊ መብት ቢኖራቸውም፤ ክልል የመሆን ጥያቄዎች ከዘውግ ይልቅ ዜግነትን መሠረት ያደረገ እና ሁሉንም ማህበረሰብ ባቀፈ መልኩ መቅረብ እንዳለባቸው ኢዜማ ማስገንዘብ ይወዳል፡፡ ይህም ለጋራ የወደፊት ዘላቂ ሰላም እና ልማታችን  ቁልፍ መሆኑን ያምናል፡፡

    ኢዜማ በአራቱም አቅጣጫ ላለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘላቂ ሰላም እና ልማት የሚጠቅመው በጥናት ላይ የተመሰረተ እንዲሁም የህዝብን ከታች እስከ ላይ ባሉ መዋቅሮች ራስን በቀጥታ የማስተዳደር መብት የሚያጎናጽፈው እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ፌደራሊዝም መሆኑን ያምናል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ በሀገሪቱ ከፍተኛ በጀት ፈሰስ ተደርጎበት በአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን የተጠናው የአስተዳደር ክልሎች እንዴት ይዋቀሩ የሚለው የጥናት ውጤት ለሀገራዊ ምክክሩ እንደ ግብአት ሆኖ እንዲቀርብ እንጠይቃለን።

    የዞን እና ክልል የመሆን ጥያቄ ያላቸው አካላት ቀጣይ ሀገራችን ታካሂደዋለች ተብሎ የሚጠበቀው ሀገራዊ ምክክር ላይ ተነስተው መፍትሄ ያገኛሉ ተብለው የሚጠበቁ ጉዳዮች ላይ ከወዲሁ ውሳኔ እንዲሰጥባቸው ማድረግ ምክክሩ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳርፍ መሆኑን ተረድተው ከጊዚያዊ አካባቢያዊ ጥቅም ይልቅ የትልቋን ኢትዮጵያ ምስል በማየት ለነገ የጋራ ጥቅማችን አስቦ አጀንዳውን በማሳደር፤ በሀገራዊ ምክክሩ ላይ በሰከነ እና የሀገሪቱን አጠቃላይ ሁኔታ በተረዳ መልኩ ከተለያዩ አካላት የሚቀርቡ ሀሳቦችን ከመመዘን እስከ ሕዝባዊ ውሳኔዎች ላይ ከፍተኛ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጥሪ እናቀርባለን።

    ሀምሌ 28 ቀን፥ 2014 ዓ.ም
    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)
    አዲስ አበባ፥ ኢትዮጵያ

    ኢዜማ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግን ማብራሪያ ጠየቀ

    Semonegna
    Keymaster

    ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ሁለተኛውን የምገባ ማዕከል ለማቋቋም የስምምነት ሰነድ ተፈራረመ

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ከአዲስ አበባ ሴቶች ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ጋር ለድርጅቱ ሁለተኛውን የምገባ ማዕክል (ተስፋ ብርሀን አሙዲ ቁጥር 2) ለማቋቋም የስምምነት ሰነድ ሰኔ 8 ቀን 2014 ዓ.ም. ተፈራርሟል።

    በከተማዋ የሚገኙ በቀን አንድ ጊዜ መመገብ ለማይችሉ ዜጎች ጤናውን የጠበቀ ምግብ እንዲያገኙ ስድስት የምገባ ማዕከላት መገንባታቸውን ከተማ አስተዳደሩን በመወከል የስምመነት ሰነድ የተፈራረሙት የአዲስ አበባ ሴቶች ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ሀና የሺንጉስ ተናግረዋል።

    መንግሥት ከድርጅቶችና ግለሰቦች ጋር በመተባበር ስራዎች እያከናወነ መሆኑን የተናገሩት ኃላፊዋ ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ከዳሽን ባንክ ኃ.የተ.የግ.ማ. ጋር በመተባበር ለከተማችን ሰባተኛ ለድርጅቱ ደግሞ ሁለተኛ የሆነ የምገባ ማዕከል ለማቋቋም አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን ገልጸዋል፤ ለዚህ የሚውል የ40 ሚልየን ብር ወጪ ለማድረግ የስምምነት ሰነድ መፈራረሙንም አስረድተዋል።

    በሚድሮክ ኢቨስትመንት ግሩፕ የኮርፖሬት ማኅበራዊ ኃላፊነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር የሆኑት አምባሳደር አሊ ሱለይማን በበኩላቸው ሀገራችን እያስተናገደችው ያለው ማኅበራዊ ችግር በሀገሪቷ ብሎም በከተማዋ ድጋፍ የሚሹ ዜጎችን ቁጥር ከፍ አድርጎታል ብለዋል። ለዚህም ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ባለፈው ዓመት “ተስፋ ብርሀን አሙዲ” የተሰኘ የምገባ ማዕከል በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ አቋቁሞ እየሠራ መሆኑን አስታውሰዋል።

    በዚህ ሰዓትም ቁጥር ሁለት ተስፋ ብርሀን አሙዲ የምገባ ማዕከልን በልደታ ክፍለ ከተማ በመገንባት ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ስራ መጀመሩን ገልፀዋል።

    በስምነት ሰነዱም ቢሮው የመገንቢያ ቦታ የማመቻቸት፣ ከቦታው ጋር ተያይዘው ለሚነሱ የሦስተኛ ወገን የመብት ጥያቄ ኃላፊነት ወስዶ ለማመቻቸት እና የተመጋቢ ምልመላና መረጣ የመሳሰሉ የከተማ አስተዳደሩ ኃላፊነቶችን እንደሚወጣ ተገልጿል።

    ሚድሮክ የኢንቨስትመንት ግሩፕ ከዳሽን ባንክ ኃ.የተ.የግ.ማ. ጋር በመተባበር በሚገነቡበት ቦታ ላይ የሚገኙና በዝቅተኛ ኑሮ ለሚኖሩ ስምንት አባወራዎች ስምንት የመኖሪያ ቤቶች ለመገንባት እንዲሁም ባሉበት የልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችላቸውን 16 የሱቅ ቤቶች በመገንባት ለማስረከብ እንደሚሠራምዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

    ከዚህም በተጨማሪ በምገባ ማዕከሉ ቅጥር ግቢ ያለውን ክፍት ቦታ በከተማ ግብርና ለማልማትና የልማቱን ውጤትም ለተመጋቢዎች በምግነት እንዲጠቀሙ ለማድረግ እንደሚሠራ በሚድሮክ በኩል ስምምነቱን የፈረሙት አምባሳደር አሊ አረጋግጠዋል።

    በተያያዘ ዜና፥ ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ (ኢትዮ አግሪ ሴፍት ኃላ/የተ/የግል ማኅበር) እና በላይነህ ክንዴ ግሩፕ (ፊቤላ ኢንዱስትሪስ ኃላ/የተ/የግል ማኅበር) በጥምረት በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን ውስጥ በምትገኘው ማንኩሳ ከተማ ያስገነቡት ዘመናዊ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመርቆ ሥራውን ጀምሯል

    ማንኩሳ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፥ ግንባታው ብቻ 43 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎበታል፤ የወጪው 75 በመቶ በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ተሸፍኗል፤ ትምህርት ቤቱን ገንብቶ ለመጨረስ የወሰድው ጊዜ ስምንት ወራትን ብቻ ሲሆን፥ ትምህርት ቤቱ 36 የመማሪያ ክፍሎች፣ ዘመናዊና የተሟሉ የአስተዳደር ህንጻዎች፣ ቤተ-መጽሐፍት፣ የተሟላ ቤተ-ሙከራ፣ የመረጃና ግንኙነት ቴክኖሎጂ (ICT)፣ ንጹህ የሴትና የወንድ መፀዳጃ ቤት ህንጻዎች እና ሌሎችም የትምህርት ግብዓቶች ተሟልተውለታል።

    ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ

    Anonymous
    Inactive

    የአማራ ብልፅግና ፓርቲ መግለጫ

    አሸባሪው ህወሓት (ትህነግ) የአማራና የአፋር ክልል መሬቶች መውረሩንና በሀገር ላይ እያደረሰ ያለውን ሁለንተናዊ ጥፋትና ሽብር ተከትሎ፥ የአማራ ብልፅግና ፓርቲ የሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ይህንን ይመስላል።

    እምቢ ለባርነት፤ ክተት ለነጻነት!!
    የአማራ ብልፅግና ፓርቲ መግለጫ

    በሁሉም የክልላችን ዞኖች፣ በበርካታ ከተሞች እና ወረዳዎች የህልውና ዘመቻውን ተከትሎ እየተካሄዱ ያሉ መሠረታዊ የውትድርና ስልጠናዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል። ሕዝባችን ህልውናውንና ኢትዮጵያን በደምና በአጥንቱ እንደሚጠብቅ የአባቶቹን ቃል-ኪዳን በማደስ ላይ ይገኛል። በዚህም የወገን ጦር ከፍተኛ መነቃቃት ሲያሳይ በአንጻሩ በቅርብም ሆነ በርቀት ያለው ጠላት በፍርሃት እየተናጠ ይገኛል። አሁን መላ የኢትዮጵያ ብሔር ብሄረሰቦች ለህልውናቸውና ለሉአላዊነታቸው ሲሉ ወታደር መሆን መርጠዋል። የዘመቻው ድጋፍ ይህን ሀቅ ያስረግጣል። በታሪክ ስናየው የኖረው እውነታ ኢትዮጵያ ሊቀብሯት የተነሱትን የውጭና የሀገር ውስጥ ፋሽስቶች ሁሉ በመቅበር ስታሳፍራቸው ኑሯለች።

    አሸባሪው ትህነግ፣ ከታሪክ የመማር አንዳች ፍላጎት የለውም። በለመደ የባንዳ ታሪኩ ከጀርባው የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶችን ተማምኖ ወክየዋለሁ የሚለውን ሕዝብ ጥይት ማብረጃ ማድረጉን ተያይዞታል። ለባዕድ ሥርዓት የመታመን ልማድ ያለውና የኢትዮጵያ ካንሰር የሆነው ትህነግ አማራን ሊያጠፋ፤ ኢትዮጵያን ሊበትን ቆርጦ መነሳቱን ተከትሎ በአጸፋው የኢትዮጵያ ብሔር ብሄረሰቦችን በቁጭት ስሜት ከዳር እስከ ዳር አነቃንቋል።

    በክልላችን የታወጀውን የክተት ጥሪ ተከትሎ የታየው አስደማሚ ሕዝባዊ ንቅናቄም ጥሪውን ተቀብሎ የመፋለም ጉዳይ “አማራን እና ኢትዮጵያን የመታደግ ጉዳይ ነው” በሚል እምነት ስለመሆኑ በተግባር እየተረጋገጠ ነው። በሁሉም የንቃናቄ መድረኮች የተሰማው ሕዝባዊ ድምጽ አንድና አንድ ነው። “ጦርነቱ የህልውናና ሀገር ማዳን ዘመቻ ነው” ፤ “በአሸባሪው ትህነግ መቃብር ላይ በጠንካራ ወንድማማችንት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እንገነባለን!” የሚል ነው።

    ምንም እንኳ አሸባሪው ትህነግ ዕድሜው ከ12 ዓመት ህፃን እስከ 70 ዓመት አዛውንት ሴት፣ ወንድ ሳይለይ ኢትዮጵያን ለመውጋት ያሰለፈና የተነሳ ቢሆንም፥ የዚህ ጦርነት ተደማሪ ግብ የትህነግ አስተሳሰብ ቁራኛ የሆነውን የትግራይ ሕዝብን ነጻ ማውጣትን ይጨምራል። በተለይም ኑሮውን በደሳሳ ጎጆ እየኖረ በድንጋይ ስር አፈር እየገፋ የሚኖረው ጭቁኑ የትግራይ አርሶ አደር፥ አሸባሪውን ትህነግ “ልጆቻችንን የት ጣላችኋቸው ?” ብሎ መጠየቅ የሚጀምርበት ጊዜ ሩቅ አይደለም።

    ጦርነት በባህሪው ከሚፈጥረው የኢኮኖሚ ድቀት በላይ ማኅበዊ ቀውሱ ተሻጋሪ ዕዳ እንደሚያመጣ ከትግራይ አርሶ አደሮች በላይ እውነታውን የሚረዳ የለም። ይህ ጦርነት በግብ የኢትዮጵያ ካንሰር የሆነውን ትህነግ ወደመቃብር ማውረድ ቢሆንም በውጤቱ የወላድ መካን የሆነችው የትግራይ እናትም ነጻ ትወጣበታለች። የኢትዮጵያ የግዛት አንድነት በመንደር ወንበዴዎችና ግልገል ሽብርተኞች አደጋ ላይ እንዲወድቅ የኢትዮጵያ ብሔር ብሄረሰቦች እንደማይፈቅዱ በተግባር እያሳዩ ይገኛል።

    የዚሁ ተግባራዊ ዐቢይ ምዕራፍ አካል የሆነው የክልላችን የህልውና ዘመቻ ዝግጅትና አፈጻጸም በስኬት መጓዙን ቀጥሏል። የክተት ጥሪውና የንቅናቄ መድረኩ ወደመሬት ስራ ወርዷል። የወቅቱ ተልዕኳችንም ከአደባባይ ንቅናቄ ወደግንባር መሰለፍ ሁኗል። የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የልዩ ኃይል ምልመላዎች በመካሄድ ላይ ናቸው። አሁንም የነገ ባለአራት ኮከብ ጀኔራሎች የሚገኙት ዛሬ መከላከያ ሠራዊቱን በመቀላቀል ላይ ከሚገኙት ወጣቶች ነውና ምዝገባው ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል። በተመሳሳይ የአማራ ልዩ ኃይል በሰው ኃይል፣ በአደረጃጃት እና በወታደራዊ ዲሲፕሊን የማጠናከሩ እና የማዘመኑ ተልዕኮ የክተት ጥሪውን በተቀበሉ ጀኔራል መኮንኖቻችን በመካሄድ ላይ ነው። ከወታደራዊ መረጃ አኳያ ቁጥሩን በይፋ ለመግለጽ ባይቻልም የልዩ ኃይላችን፣ የሚሊሻችን በጥቅሉ የአማራ ሕዝባዊ ሠራዊታችን አቅም በፍጠነት እያደገ ነው። በተመሳሳይ ተልዕኮ በሁሉም ማዕከላት ተጠባባቂ ኃይል የማፍራት ስራው የህልውና አጀንዳው አካል ሁኗል።

    ይህም ሁኖ ሰብዓዊነቱን ክዶ ለመጣው ጠላት ከዚህም በላይ ዝግጅት ሊካሄድ ይገባል። ከአንድ ወር ወዲህ ያለውን የጠላት ዝግጅት ብንመለከት፡- በትግራይ በሁሉም ወረዳወች በብዙ ሽህዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላ (conscription) ኮታ ተጥሎበታል። ይህ የፌዴራል መንግሥቱ የተናጠል የተኩስ አቁም ካወጀ በኋላ ትህነግ በአማራና አፋር ክልሎች ላይ የከፈተውን ወረራ ተከትሎ የተጣለ ግዳጅ ነው። ከዚህ ግዳጅ በፊት የነበረው ሰልጥኖ የታጠቀው ኃይል አብዛኛው ወደመቃብር የወረደ ሲሆን፤ ይህንኑ የሰው ኃይል ክፍተቱን ለመሙላት በዚህ ወር ብቻ በብዙ ሺህዎች የሚገመት የሳምንታት ስልጠና የወሰዱ ታዳጊዎችን ለወረራ አሰልፏል። ይህ ኃይል ከኢትዮጵያዊነት እሴት የራቀ በመሆኑ እንደአንበጣ በየደረሰበት ያገኘውን የሚወር፣ የሚዘርፍ፣ ሴቶችንና እናቶችን የሚደፍር፣ መሠረተ ልማቶችንም የሚያወድም በጥቅሉ ሰብዓዊነቱን የካደ፤ በአማራና በኢትዮጵያ ጥላቻ ያበደ በመሆኑ በፍጥነት ሊደመመስ ይገባል። እረፍትም ጊዜም ሊሰጠው አይገባም።

    ስለሆነም የህልውና ዘመቻው በጊዜ የለንም መንፈስ ተጠናክሮ ይቀጥላል። መሽቶ በነጋ ቁጥር አሸባሪው ኃይል ወደመቀመቅ የሚወርድበት ጉድጓድ ጥልቀት ይጨምራል። ጠላት በተግባርም ሆነ በአስተሳሰብ ሊቀበር ይገባል።

    ይህ የሽብር ቡድን በተመሳሳይ ሰዓት ከአማራም፣ ከአፋርም እንዲሁም ከጎረቤት ኤርትራ ጋር በአንድ ጊዜ ወደግጭት መግባት ያስፈለገው ግጭት ብቸኛ የዕድሜ ማስቀጠያው እንደሆነ በማመኑ ነው። ባለፉት ሠላሳ ዓመታት በተግባሩም ሆነ በአስተሳሰቡ ለኢትዮጵያ ካንሰር ስለመሆኑ በበቂ ሀገራዊ ኪሳራ ተገምግሟልና አሁን ላይ ለወረራ የተሰለፈባቸው የአማራና የአፋር መሬቶች የአሸባሪው ትሕነግ መቀበሪያ መሆናቸው ይቀጥላል።

    እምቢ ለባርነት፤ ክተት ለነጻነት!!
    የአማራ ብልፅግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት
    ሐምሌ 30 ቀን፥ 2013 ዓ.ም.
    ባህር ዳር፥ ኢትዮጵያ

    የአማራ ብልፅግና ፓርቲ መግለጫ

    Anonymous
    Inactive

    የኢፌዴሪ ባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር በ2013 በጀት ዓመት በባህል ኢንዱስትሪ ልማት ዋና ዋና ክንውኖች
    ሐምሌ 2013 ዓ.ም.
    አዲስ አበባ

    • በባህል ፖሊሲ፣ በቋንቋ ፖሊሲ በባህል እሴቶችና ሀገር በቀል ዕውቀቶች፣ በዕደ ጥበብ ማበልፀግና የገበያ ትስስር ስትራቴጂዎችና አዘገጃጀት ሂደት እና አተገባበር ላይ ከ10 ክልሎች እና ከ2 የከተማ መስተዳድር ለተውጣጡ 53 የባህል ዘርፍ ሙያተኞች እና አስፈጻሚዎች ስልጠና ተሰጥቷል።
    • ከኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ ጋር በመተባበር ለባህል ተቋማት በሲኒማ ቤት፣ በቴአትር ቤት እና ቤተ መፃሕፍት ላይ የደረጃ ሰነድ (standard) ተዘጋጅቷል።
    • በኪነጥበብ እና በሥነ ጥበብ ተቋማት ዘርፍ ላይ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ግለሰቦች የማበረታቻ ሽልማት የሚሰጥበትን አሰራር ሥርዓት በመዘርጋት የመጀመሪያው ሀገር አቀፍ የሽልማትና ዕውቅና መርሃ ግብር በሙዚቃ፣ በቴአትር፣ በድርሰት፣ በሰርከስ፣ በስዕልና ቅርፃ ቅርፅ፣ በፋሽን ዲዛይን፣ በውዝዋዜ እና በፊልም 2013ዓ.ም የሽልማትና ዕውቅና ለመስጠት ሥራዎች ተሠርተዋል።
    • ኢትዮጵያ ያላትን ሀብትና የተፈጥሮ ፀጋ ለማስተዋወቅ እንዲሁም ወደ ኢንቨስትመንት አማራጭ ለመለወጥ ያለመ “የኢትዮጵያ ሳምንት” በወዳጅነት አደባባይ ተካሂዷል። ክልሎች ልዩ መገለጫችን ነው ያሉትን ባህላቸውን በተለያዩ ቅርፃ ቅርፆች፣ በተንቀሳቃሽ ምስሎች እንዲሁም ልዩ ልዩ ጭፈራዎችን በማቅረብ ተከብሯል።
    • የባህል ኢንዱስትሪ መረጃዎችን ለማዘመንና ወጥነት ያላቸው እንዲሆኑ ለማስቻል ከኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽንና ቴክኖሎጂ ጋር በጋራ በመሆን የመረጃ ቋት (ዳታቤዝ) በማዘጋጀት የ2013 ዓ.ም የባህል ኢንዱስትሪ ተቋማትና ሙያተኞች መረጃ ተደራጅተዋል።
    • በባህል ዘርፍ (በባህል፣ በፊልም፣ በቋንቋ ፖሊሲዎችና በእደ ጥበብ ልማት በሀገር በቀል እውቀቶች)፣ በጎጂና መጤ ባህላዊ ድርጊቶች እና ባህል ዘርፍ ተቋማት አከፋፈት የኮቪድ 19 ጥንቃቄና ደህንነት መመሪያን ማስተዋወቅ ሥራ ለ7 ክልሎችና ከሁለት ከተማ አስተዳደር ለተውጣጡ ለ52 አሰልጣኞች የማስተዋወቅ ሥራ ተሠርቷል።
    • ከሙያ ማኅበራት ጋር በመተባበር በኮቪድ ወቅት ጥንቃቄና ደህንነትን መሠረት ባደረገ ሁኔታ የወረርሽኙን አስከፊነት የጥንቃቄ ትኩረትን የሚያስገነዝብና ከ100 በላይ ማስታወቂያዎች (ስፖት) በተለያዩ ሚዲያዎች ተለቋል።
    • የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከል የባህል ዘርፍ አገልግሎት ተቋማትን ሥራ ለማስጀመር እንዲቻል ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የአሠራር መመሪያ ተዘጋጅቷል።
    • ለክልሎችና ከተማ መስተዳድሮች እንዲሁም የባህል ጥበባት ዘርፍ ለባለድርሻ አካላት በሁለት ዙር መድረክ ሥልጠና ተሰጥቷል።
    • በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ የተመለከቱት ሥዕል ኤግዚቪሽን ለሶሰት ቀናት ለሕዝብ ዕይታ ቀርቧል።
    • በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ትምህርት ቤቶች በተዘጉ ወቅት በቤት ተቀምጠው የነበሩ ተማሪዎች እና ሕፃናት የተሳተፉበት የኪነ ጥበብ ፈጠራ ውድድር ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የአንድ ወር የቴሌቪዥን ፕሮግም ተሠርቷል።
    • ኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከል በተደረገ ዘመቻ ለተሳተፉ አካላትና መመሪያውን ተግባራዊ ላደረጉ ለሁለት ክልልና ለአንድ ከተማ መስተዳድር በድምሩ ለ25 ተቋማት እውቅና የመሥጠት ሥራዎች ተከናውነዋል።
    • የባህል ኢንዱስትሪ ዘርፍ በተመለከተ 6 የአሰራር ሥርዓት ሰነዶችና መመሪያዎች ተዘጋጅተዋል።
    • ከዩኔስኮ በተገኘው ዓለም አቀፋዊና ሀገራዊ ኤክስፐርቶቸች ድጋፍ በመታገዝ የቴክኒክ ኮሚቴ ተቋቁሞ የፈልም ፖሊሲ ማስተገበሪያ (የተቋም ማቃቋሚያ ሰነድ እና የፈልም ፖሊሲ ማስፈጸሚያ ስትራተጂ) ፕሮጀክት እየተከናወነ ነው።
    • የ2005 የዩኔስኮ ኮንቬንሽን ስምምነት መሠረት የ2020 (2012 ዓ.ም.) የሚቀርበውን በየአራት ዓመታቱ የሚዘጋጀውን ሪፖርት ለማጠናቀቅ እንዲቻል ሀገራዊ ኮሚቴውን በማስተባበር በወቅቱ ገቢ ለማድረግ ተችሏል።

    ምንጭ፦ የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር

    የኢፌዴሪ ባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር

    Anonymous
    Inactive

    “የሕዝባችንን ህልውና ከጠላት ጥቃት የምንታደግበት የታሪክ መድረክ ላይ ስለምንገኝ ከመቼውም ጊዜ በላይ ልዩነታችንን ወደጎን በመተው የሕዝባችንን አንድነት ጠብቀን በጋራ እንድንረባረብ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ጥሪውን ያቀርባል።”

    የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ የሰጠው መግለጫ
    “አንድነታችንን ጠብቀን ያጋጠመንን የህልውና አደጋ በትግላችን እንቀለብሰዋለን”

    የኢትዮጵያና የአማራ ሕዝብ ጠላት የሆነው ትህነግ ወያኔ እንደሀገር ባደረሰብን ህልቆ መሳፍርት የሌለው ግፍና በደል እንዲሁም ለፈጸመብን ሀገራዊና ሕዝባዊ ክህደት የሀገራችንን የግዛት አንድነት በመሸርሸር ሉአላዊነቷ የማይከበር፣ ራሷን ችላ መቆም የማትችልና በሁሉም መስክ ተንበርካኪ ሀገር ባለቤቶች እንድንሆን በርካታ ደባ ፈጽሞብናል። በዓለም አደባባይ የምንኮራበት ሀገራዊና ሕዝባዊ የጋራ ታሪክ ባህልና እሴት እንዳይኖረን አንድነታችንንና አብሮነታችንን በፈጠራ ታሪክ እየቦረቦረ እርቃናችንን እንድንቀር፣ አንዳችን ለሌላችን ጋሻና መከታ መሆን ሲገባን እርስ በእርስ በመጠራጠር አውሎ ነፋስ ወዲያና ወዲህ እንድንላጋና በጠላትነት እንድንፈራረጅ ከሰማይ በታች ያልፈጸመብን ግፍ የለም።

    ከሁሉም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ጋር ተባብረንና ተፈቃቅደን የጸረ ጭቆና ትግሉን አንድ ብለን ስንጀምር በጋራ ያነሳነው የፍትህና የእኩል ተጠቃሚነት ጥያቄ በትህነግ መንደር የቱን ያህል መራር የሆነ የመደፈር ስሜት እንደፈጠረ የቅርብ ጊዜ ክስተት ነው። አሸባሪው ትህነግ ከመንበረ ስልጣኑ ተምዘግዝጎ ሲወድቅና መቀሌ ሲከትም የነበረው ብቸኛ ምክንያት ዓይናችሁን ጨፍኑና ላሞኛችሁ የሚል ፖለቲካዊ ቁማር እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም። በውህድ ፓርቲ ደረጃ የተፈጠረውን አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ አደረጃጀት የአሃዳውያን ውጤት አድርጎ ያበሻቀጠው ፍላጎቱ በለመደው የአድራጊ ፈጣሪና የአዛዥነት ሚና ያልተሳተፈበትን መዋቅር ለማጣጣል ከማለም ባሻገር፥ ለኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች እኩል ተጠቃሚነት ባለው ከፍ ያለ ንቀትና ጥላቻ ምክንያት መሆኑ ለሁሉም ግልጽ ነው።

    ይህንን ተከትሎ በትግራይ ክልል የሰሜን ዕዝ እንዳይንቀሳቀስ በተደጋጋሚ ያደረገው ሙከራ የልብ ልብ ሰጥቶት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ውድ ልጆችን በግፍ ያለርህራሄ አሰቃቂ ግድያ ከፈጸመባቸው በኋላ የዕዙን ጠቅላላ ንብረት በመውረስ በመላው ኢትዮጵያውያን ላይ ጦርነት ማወጁ ይታወቃል። የአማራ ክልልን ወሰን ጥሶ በማለፍ ጥቃት ለመፈጸም ያደረገው ጥረት ባይሳካለትም በማይካድራ ንጹሀን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ላይ የፈጸመው አረመኔያዊ የጅምላ ጭፍጨፋ የሚዘነጋ አይደለም። ይህንን ተከትሎም መንግሥት በየደረጃው የሕግ የበላይነት ለማስከበር ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን አከናውኗል። በሂደቱም በርካታ ውጤቶች መመዝገባቸው የሚዘነጋ አይደለም። ይሁን እንጂ ይህ አረመኔና አሸባሪ ቡድን ዓይኑን በጨው አጥቦ ጥቃት የተፈጸመበት በማስመሰል ዓለምአቀፉን ማኅበረሰብ በተደጋጋሚ በማጭበርበር ላይ ይገኛል።

    የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት በአንድ ወገን የወሰደውን የተኩስ አቁም ውሳኔ እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም በኢትዮጵያና በአማራ ክልል ሕዝብ ላይ መሠረተ ሰፊ የሆነ ወረራና ጥቃት ማድረግ ጀምሯል። ይህ አሸባሪ ቡድን የጀመረብንን ግልጽ ወረራ ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሚያወግዘውና የምንጊዜም አጋርነቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ፍጹም ጥርጣሬ የለንም። በዚህ አጋጣሚ የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ በግልጽ እንደሚያውቀው የአማራ ክልልና ሕዝብ የዚህ አሸባሪ ቡድን ቀጥተኛና የቅርብ ተጠቂ መሆኑን ነው። ስለሆነም ትግላችን ለሕዝባችን ህልውናና ለሀገር ሉአላዊነት መሆኑ ግንዛቤ ውስጥ ገብቶ የጋራ ጠላታችንን በጋራ እንድንፋለመው የአጋርነት ጥሪያችንን እናቀርባለን።

    አሸባሪው የትህነግ ቡድን ከአማራ ክልል ጋር በሚያዋስኑት ሁሉም አቅጣጫዎች መጠነ ሰፊ ወረራና ጥቃት እየፈጸመ የሚገኝ አረመኔና ጨካኝ ቡድን መሆኑ እንዲታወቅና ሁሉም የአማራ ክልል ሕዝብ ጉዳዩን ከህልውናው ጋር በማስተሳሰር እንዲመለከተውና ከዚህ ጨካኝና አረመኔ ቡድን ጋር ቀጣይ የምናደርገው ሁሉ አቀፍ ትግል የህልውና ትግል መሆኑን አውቆ በገንዘብ፣ በጉልበትና በህይወት መስዋዕትነት አስፈላጊውን አበርክቶ ለማድረግ ራሱን እንዲያዘጋጅና የመንግሥትን ጥሪ እንዲጠባበቅ የክልሉ መንግሥት ጥሪውን ያቀርባል።

    አሸባሪው ትህነግ የትግራይን ሕዝብ ከህጻን እስከአዋቂ በማንቀሳቀስ ዓለም አቀፍ የጦርነት ሕግጋትን በመቃረን ሕጻናትንና ሴቶችን በጅምላ ጦርነት እየማገደና ያለ የሌለውን አቅሙን ተጠቅሞ ክልላችን ላይ ወረራ የፈጸመ ሲሆን፥ በተለይም ለዘመናት የአማራ ሕዝብ የማንነትና የወሰን ጥያቄ እያነሳ ሲታገልባቸው የቆዩ የራያ፣ አላማጣና ኮረም አካባቢዎችን ዳግም በመውረር እንዲሁም ወልቃይት ጠገዴ ሴቲት ሁመራ በኃይል ለመያዝ በተለይም ጠለምትና አካባቢውን ለመያዝ አሁናዊ ሙከራ የጀመረ መሆኑ በአካባቢው የሚኖሩ አማራዎችንና የአማራ ክልል ተወላጆችን ፈጽሞ የማጥፋት ህልሙን እውን ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። ስለሆነም ይህንን አረመኔያዊ ድርጊትና ዳግም ወረራ የክልሉ መንግሥት በፍጹም የማይቀበለውና በጀመርነው የህልውና ትግል ተፈጥሯዊና ታሪካዊ መብታችንን የምናረጋግጥ መሆኑን አበክረን እንገልጻለን።

    ስለሆነም፡-

    1ኛ. በየግንባሩ የምትገኙ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት፣ የክልላችን ልዩ ኃይልና የሚሊሻ አባላት፣ ሕዝባዊ ፖሊስና ሰላም አስከባሪ አባላት እንዲሁም ሀገርና ሕዝብን ለማዳን የተግባር እንቅስቃሴ እያደረጋችሁ የምትገኙ የየክልሉ የጸጥታ አካላት፥ በዚህ ታሪካዊ መድረክ ከጠላት ጋር ፊት ለፊት በመግጠም ለሀገራችሁ ሉአላዊነትና ለሕዝባችሁ ህልውና የምትከፍሉትን ክቡር መስዋዕትነት ታሪክ ምንጊዜም ሲያስታውሰው ይኖራል። በቀጣይም የተሰጣችሁን ሕዝባዊና ሀገራዊ ተልዕኮ በጽናትና በቁርጠኝነት እንደምትወጡ እምነታችን የጸና ነው። ስለሆነም፥ መላው የኢትዮጵያና የአማራ ሕዝብ ከጎናችሁ መሆኑን አውቃችሁ በጀግንነት ታሪካዊ ጠላታችንን በመደምሰስ ለሀገራችሁ ዳግም የኩራት ምንጭ እንድትሆኑ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

    2ኛ. መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በትህነግ ወያኔ ላይ የተጀመረው ሕግን የማስከበር ትግል ተጠናክሮ እንዲቀጥል አስፈላጊውን እርብርብ ሁሉ ማድረግ አለበት ብለን እናምናለን። አሸባሪው ትህነግ ሀገር ከማፍረስ እኩይ ተልዕኮው ሊታቀብ የሚችለው የሀገራችንን ሉአላዊነትና የግዛት አንድነት በጽናትና በአላማ ቁርጠኝነት በጋራ መጠበቅ ስንችል ስለሆነ በዚህ ታሪካዊ መድረክ ላይ በጋራ እንድንቆም የአክብሮት ጥሪያችንን እናቀርባለን።

    3ኛ. በየትኛውም ዘመን ሰልጥናችሁ፣ የሀገርና የሕዝብ ሉአላዊነት ለማስከበር በማንኛውም የመንግሥት ጸጥታ መዋቅር ውስጥ ተሰልፋችሁ ስታገለግሉ የቆያችሁና በታሪክ አጋጣሚ የሙያ ዘርፍ የቀየራችሁ የክልላችን ነዋሪዎች፥ ለህልውናችን የምናደርገውን የትግል ጥሪ ተቀብላችሁ በክልሉ ጸጥታ መዋቅር ውስጥ እንድትቀላቀሉ ጥሪያችንን እያቀረብን ከዛሬ ጀምሮ በየአካባቢያችሁ ሰላምና ደህንነት ጽሕፈት ቤት በአካል ተገኝታችሁ በፈቃደኝነት እንድትመዘገቡ ለማሳሰብ እንወዳለን።

    4ኛ. መላው የክልላችን ወጣቶች፥ ከፊት ለፊታችን የተደቀነብንን የህልውና አደጋ ያለበቂ ዝግጅትና ደረጃውን ከጠበቀ ስልጠና ውጭ የምንጋፈጠው አይደለም። ስለሆነም ከማንኛውም ግብታዊ እንቅስቃሴ ታቅባችሁ በየደረጃው ለሚኖረው ምልመላና ስልጠና በመሳተፍ በቂ ዝግጅት አድርጋችሁ የመንግሥትን ጥሪ እንድትጠባበቁ እናሳስባለን።

    5ኛ. መላው የክልላችን ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሲቪክና የሙያ ማህበራት፣ ማኅበራዊ አንቂዎችና የሚዲያ ባለሙያዎች፥ የጀመርነው የህልውና ትግል የሁላችንንም አንድነት፣ ኅብረትና ተቀራርቦ መሥራት የሚጠይቅ ነው። በሩቅ ሆኖ ስህተት በመፈለግና እርስ በእርስ በመነቋቆር ከጠላት መንጋጋ ፈልቅቀን የምንታደገው አንዳችም ህልውና የለንም። በቂ መረጃ ባገኘንበትም፣ ባላገኘንበትም ጉዳይ ላይ ተሳፍረን በተለያዩ አቅጣጫዎች መክነፍ ለጠላቶቻችን ተጨማሪ ጉልበት ከመሆን ባለፈ ለሕዝባችን የሚሰጠው ጥቅም የለም። ስለሆነም የጋራ ዕጣ ፋንታችንን በጋራ ጥረት የምናስከብርበትና አደጋ የተጋረጠበትን የሕዝባችንን ህልውና ከጠላት ጥቃት የምንታደግበት የታሪክ መድረክ ላይ ስለምንገኝ ከመቼውም ጊዜ በላይ ልዩነታችንን ወደጎን በመተው የሕዝባችንን አንድነት ጠብቀን በጋራ እንድንረባረብ የክልሉ መንግሥት ጥሪውን ያቀርባል።

    6ኛ. መላው የክልላችን ሕዝብ፣ በከተማና በገጠር የምትኖሩ የክልላችን ነዋሪዎች፣ በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ የምትገኙ ምሁራንና የክልላችን ተወላጆች፣ በተለያየ ሙያ ተሰማርታችሁ ሀገርና ሕዝብ በማገልገል ላይ የምትገኙ የክልላችን ነዋሪዎችና ባለሀብቶች፥ የጀመርነውን የህልውና ትግል በማገዝ የትግል ሂደት አዎንታዊ ሚናችሁን እንድትወጡ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

    በመጨረሻም የጀመርነው ትግል እልህ አስጨራሽ በጣም መራርና ረዥም ጊዜ የሚጠይቅ እንደሚሆን ይጠበቃል። የፈጀውን ጊዜ ይፍጅ የእኛ አንድ መሆንና ለጋራ ግብ በጋራ መተባበር በመድረኩ አሸናፊ ሆነን እንደምንወጣ ያለምንም ጥርጥር ልናረጋግጥልችሁ እንወዳለን። ሁልጊዜም ቢሆን የአማራ ክልል ሕዝብ ትግል ከኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የጋራ ተጠቃሚነት ውጭ እንደማይሳካ ጠንቅቀን እናውቃለን። የምናደርገው ትግል ለሀገራችን ሉአላዊነት መከበርና የጭቁን ሕዝባችን የህልውና ትግል እንጂ እላፊ ጥቅም ለማግኘት የምናደርው ትግል በፍጹም አይደለም።

    የአማራ ሕዝብ ከፉክክር ይልቅ ትብብርን ከእብሪት ይልቅ ድርድርን የሚያስቀድም፣ ‘በፍትህ ከሄደች በቅሎየ፥ ያለፍትህ ያጣኋት ጭብጦየ’ ትቆረቁረኛለች ብሎ የሚያምን ሕዝብ ነው። ስለሆነም ዛሬ የምናደርገው ትግል ለልጅ ልጆቻችን የምናወርሰው የኩራትና የክብር ምንጭ እንደሚሆን አንጠራጠርም። የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት የወሰደው ተናጠላዊ የተኩስ አቁም ውሳኔን ተከትሎ የጠላት ኃይል ሀገርና ሕዝብ ለማዋረድ የሚያደርገውን እብሪተኛ እንቅስቃሴ መሠረት በማድረግ በጠላት ላይ የማያዳግም እርምጃ እንዲወስድ በአጽንኦት እናሳስባለን።

    ትግላችን ለህልውናችን !
    ሐምሌ 6 ቀን 2013 ዓ.ም.
    የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት

    የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት

    Anonymous
    Inactive

     ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የምርጫ ውጤት

    ሰኔ 14 ቀን፥ 2013 ዓ.ም. የተካሄደው የስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውጤት ይፋ ተደረገ። ይህ ውጤት የሚገለፀው ባገኙት ወንበር ልክ ሲሆን በዚህም መሠረት፦

    • የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር
      – መስተዳድሩ ያለው የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ: 23
      – ሰኔ 14 ቀን ምርጫ የተከናወነበት የተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ክልል ብዛት: 23
      □ ብልፅግና ፓርቲ ያገኘው መቀመጫ: 22
      □ የግል ተወዳዳሪ ያገኘው መቀመጫ: 1
    • የአፋር ብሔራዊ ክልል
      – ክልሉ ያለው የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ: 8
      – ሰኔ 14 ቀን ምርጫ የተከናወነበት የተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ክልል ብዛት: 6
      □ ብልፅግና ፓርቲ ያገኘው መቀመጫ: 6
    • የአማራ ብሔራዊ ክልል
      – ብሔራዊ ክልሉ ያለው የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ: 138
      – ሰኔ ቀን ምርጫ የተከናወነበት የተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ክልል ብዛት: 125
      □ ብልፅግና ፓርቲ ያገኘው መቀመጫ: 114
      □ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ፓርቲ ያገኘው መቀመጫ: 5
      – ድጋሚ ቆጠራ የሚከናወንበት ምርጫ ክልል ብዛት: 1
      – ድጋሚ ምርጫ የሚከናወንበት ምርጫ ክልል ብዛት: 5
    • የቤኒሻንጉል-ጉሙዝ ብሔራዊ ክልል
      – ብሔራዊ ክልሉ ያለው የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ: 9
      – ሰኔ 14 ቀን ምርጫ የተከናወነበት የተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ክልል ብዛት: 3
      □ ብልፅግና ፓርቲ ያገኘው መቀመጫ: 3
      – ድጋሚ ምርጫ የሚከናወንበት ምርጫ ክልል ብዛት: 2
    • የድሬዳዋ ከተማ መስተዳድር
      – መስተዳድሩ ያለው የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ: 2
      – ሰኔ 14 ቀን ምርጫ የተከናወነበት የተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ክልል ብዛት: 2
      □ ብልፅግና ፓርቲ ያገኘው መቀመጫ: 1
      – ድጋሚ ቆጠራ የሚከናወንበት ምርጫ ክልል ብዛት: 1
    • የጋምቤላ ብሔራዊ ክልል
      – ብሔራዊ ክልሉ ያለው የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ: 3
      – ሰኔ 14 ቀን ምርጫ የተከናወነበት የተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ክልል ብዛት: 3
      □ ብልፅግና ፓርቲ ያገኘው መቀመጫ: 3
    • የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል
      – ብሔራዊ ክልሉ ያለው የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ: 178
      – ሰኔ 14 ቀን ምርጫ የተከናወነበት የተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ክልል ብዛት: 170
      □ ብልፅግና ፓርቲ ያገኘው መቀመጫ: 167
      □ የግል ተወዳዳሪዎች ያገኙት መቀመጫ: 3
    • የሲዳማ ብሔራዊ ክልል
      – ብሔራዊ ክልሉ ያለው የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ: 19
      – ሰኔ 14 ቀን ምርጫ የተከናወነበት የተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ክልል ብዛት: 19
      □ ብልፅግና ፓርቲ ያገኘው መቀመጫ: 19
    • የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ብሔራዊ ክልል
      – ብሔራዊ ክልሉ ያለው የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ: 104
      – ሰኔ 14 ቀን ምርጫ የተከናወነበት የተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ክልል ብዛት: 85
      □ ብልፅግና ፓርቲ ያገኘው መቀመጫ: 75
      □ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ ያገኘው መቀመጫ: 4
      □ የጌዴኦ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት: 2
      – ድጋሚ ቆጠራ የሚከናወንበት ምርጫ ክልል ብዛት: 1
      – ድጋሚ ምርጫ የሚከናወንበት ምርጫ ክልል ብዛት: 3

    በዚህ ሐምሌ 3 ቀን፥ 2013 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ባደረገው የምርጫ ውጤት መሠረት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመቀመጫ ብዛት በአጠቃላይ 484 ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ በስልጣን ላይ የሚገኘው ብልፅግና ፓርቲ 410 መቀመጫ አሸንፏል። ይህም ውጤት ፓርቲውን መንግሥት ለመመሥረት ያስችለዋል።

    ይህን የምርጫ ውጤት እና የፓርቲያቸው ማሸነፍን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ያስተላለፉትን መልዕክት ለማንበብ እዚህ ጋር ይጫኑ

    የምርጫ ክርክር የምርጫ ውጤት

    Anonymous
    Inactive

    ህወሓት ጠቡ ከኢትዮጵያ እና ከኢትዮጵያዊነት ጋር ነው

    በአቶ ዮሐንስ መኮንን

    “ከማዕከላዊው የመንግሥት የሥልጣን ማማ ተገፍቼያለ” ብሎ ያኮረፈው የህወሓት ቡድን ከሦስት ዓመታት በፊት የጦርነት ዳርዳርታ በጀመረ ሰሞን መገዳደል ማንንም አትራፊ ስለማያደርግ የጦርነት ጉሰማውን እንዲተው በሀገር ሽማግሌዎች፣ በልኂቃንም ሆነ በተራ ዜጎች ሳይቀር ተለምኖ ነበር። የህወሓት ሰዎች ግን “ጦርነት ባህላዊ ጨዋታችን ነው” እያሉ ያፌዙ እንደነበር ኢትዮጵያውያን ሁላችንም የምናስታውሰው የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።

    የጦርነት ጉሰማው ድንበሩን አልፎ “የ45 ደቂቃ መብረቃዊ ጥቃት” ሲሉ በራሳቸው አንደበት በነገሩን አረመኔያዊ የክህደት እርምጃ ወገናቸው በሆነው የሀገር መከላከያ ላይ የፈጸሙት ጥቃት እና በማይ ካድራ ንጹሐን ላይ የፈጸሙት ጭፍጨፋ ለህወሓት ሰዎች እና ደጋፊዎቻቸው ዛሬ ላይ “ጀብድ” ይምሰላቸው እንጂ የፈጸሙት ተግር በታሪክ ፊት አንገታቸውን የሚያሰደፋ የነውር ጥግ ነበር።

    ይህንኑ የህወሓት አረመኔያዊ ተግባ ተከትሎ የመከላከያ ሠራዊታችን በወሰደው የአጸፋ እርምጃ ዋንኛው ዓላማ ህወሓትን ከነመዋቅሯ መደምሰስ ቢሆንም ጦርነቱ በንጹሓን ዜጎች ይልቁኑም በሴቶች እና በሕጻናት ላይ ያደረሰው ጉዳት የሚያሳዝነን እና የሚያሳፍረን ክስተት ነበር።

    ዛሬ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት በውጪ መንግሥታት ተጽእኖም ይሁን በጦርነቱ አክሳሪነት የተነሳ “የጽሙና ጊዜ ለመስጠት” የተናጥል የተኩስ አቁም ውሳኔ አሳልፎ ከክልሉ ሠራዊታችን ማስወጣቱ ተገቢ እርምጃ ነው። ይህ ማለት ግን “ትግራይን የራሱ ሉዓላዊት ሀገር አካል መሆኗ አበቃ” ማለት አይደለም። በግልጽ ቋንቋ ለመግለጥ “ህወሓት ይሻለናል” ለሚሉ አባላቶቿ ደጋፊዎቿ “ዕድል ለመስጠት ያለመ” መሆኑን እገነዘባለሁ።

    ይሁን እንጂ መንግሥት ተገፍቶ ሕግ ወደማስከበር ጦርነት ሲገባም ሆነ አሁን ትግራይን ለቅቆ ሲወጣ ጉዳዩን ያየዘበት መንገድ ሌላ ዘላቂ ሀገራዊ ችግር ተክሎብን እንዳያልፍ ሊጠነቀቅባቸው የሚገቡ ጉዳዮች እንዳሉ ይሰማኛል። በምክንያት ላስረዳ፡

    ህወሓት ያኮረፈውም ሆነ የተጣላው ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር እንጂ ከአንድ ሕዝብ ጋር እንዳልነበረ የሚስተው ያለ አይመስለኝም። ጦርነቱ እንደተጀመረ ተደራጅቶ በቅርብ ርቀት ላይ ገኝ የነበረው የአማራ ልዩ ኃይል ቀድሞ የህወሓትን ተስፋፊ ጦር መመከቱ የሚያስመሰግነው ተግባር መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በሂደት ግን በዓለም ዓቀፉ ማኅበረሰብም ሆነ በአንዳንድ “ልኂቃን” ጭምር የህወሓት ጠብ “ከአማራ ልዩ ኃይል” ጋር አስመስለው መግለጻቸው ተገቢ ካለመሆኑም በላይ የአንድን ጠባብ ቡድን የእብሪት ጦርነት በሁለት ሕዝቦች መካከል የተደረገ ጦርነት አስመስሎ ማቅረቡ ጉዳቱ ውሎ አድሮ የሚያመረቅዝ ቁስል እንዳተርፈን ያሳስበኛል። በእርግጥ የመከላከያ ሠራዊታችን ከሁሉም ብሔሮች የተውጣጣ ጦር መሆኑ እየታወቀ ተደጋግሞ “አማራ ልዩ ኃይል” የጦርነቱ ፊት አውራሪ ተደርጎ መሳሉ የህወሓት ጠብ ከአንድ ሕዝብ ጋር አስመስሎታል።

    በቀደም እለት ጠቅላይ ሚንስትሩ በፓርላማ ባደረጉት ንግግርም “የአማራ ሕዝብ ለህወሓት አይንበረከክም” የሚለው ንግገራቸው ምንም እኳን ሕዝቡን ለማጀገን እንደተጠቀሙበት ብረዳውም የአማራ ልዩ ኃይል ለሀገር አንድነት የከፈለውን መስዋእትነት ክልሉን ለመከላከል እንደተከፈለ መስዋእትነት አሳንሶ ወደማየት እንዳይተረጎም ያሳስበኛል።

    ዛሬ ደግሞ የጀርመኑ ዶቼቬሌ ሂውማን ራይት ዎችን ጠቅሶ እንደዘገበው ህወሓት “በአማራ ክልል ልዩ ኃይሎች ተይዘውብኛል” የሚላቸውን አካባቢዎች መልሶ ለመንጠቅ በርካታ ታጣቂዎቹን እያንቀሳቀሰ መሆኑን ሰምተናል። እንደዘገባው ከመጠለያ ካምፖች ሳይቀር ወጣቶችን በገፍ እየመለመለች ነው። (ህወሓት ሰንአፌ በረሃ አርቅቃ ኢትዮጵያ ላይ የጫነችውን “ሕገመንግሥት” ሳይቀር በተቃረነ መንገድ የአማራ ገበሬዎችን በማፈናቀል በወረራ የቀማቻቸውን ወልቃይት እና ሁመራን የመሳሰሉ ለም መሬቶች በግፍ መንጠቋ ይታወሳል)

    የህወሓትን ትፍራፊ ጦር እንደ አመጣጡ ለመመለስ የአማራ ልዩ ኃይል የሚያንስ ባይሆንም ትንኮሳውን ማስቆም ያለበት ዋንኛው ፊትአውራሪ ጦር ግን የሀገር መከላከያ ኃይል ነው ብዬ በጽኑ አምናለሁ። የልዩ ኃይል ተሳፎ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም የአማራ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ክልሎች ልዩ ኃይሎች በመከላከያ ሠራዊት ሥር ታቅፈው ስምሪት ሊሰጣቸው ይገባል።

    “ኢትዮጵያን ሳላፈርስ እንቅልፍ አይወስደኝም” ብሎ የማለውን የህወሓት ትርፍራፊ ጦር መመከት እና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም መደምስ የሁሉም ኢትዮጵያውያን የቅድሚያ ቅድሚያ ኃላፊነት ነው። ምክንያቱም የህወሓት ጸብ ከኢትዮጵያ እና ከኢትዮጵያዊነት ጋር ነው!

    በአቶ ዮሐንስ መኮንን

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forums) ላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።

    ህወሓት ጠቡ ከኢትዮጵያ እና ከኢትዮጵያዊነት ጋር ነው

    Anonymous
    Inactive

    ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

    ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን ) የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ
    ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣
    ለሁሉም የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሉች፤
    የኢትዮጵያ ጉዳይ ለሚያሳስባችሁ አፍሪካውያን ወንድሞቻችንና ዓለምአቀፍ አጋሮቻችን፤
    በመላው ዓለም ለምትገኙ ሰላም ወዳድ ኃይሎች በሙሉ !

    የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በሰኔ 26 እና 27 ቀን 2013 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ጥልቅና ዙሪያ መለስ ውይይት በማድረግና፤

    • የሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ፖለቲካ መሠረት ለመጣልና በሕዝብ ይሁንታ ብቻ ሥልጣን የሚይዝ ሥርዓት ለመፍጠር የተደረገውን 6ኛውን ሀገራዊ የምርጫ ሂደት በመገምገም፤
    • የታላቁን የአባይ ግድብን በማጠናቀቅና እንደ ሀገር የተፈጥሮ ፀጋችንን ተጠቅመን የመልማት መብታችንን ለማረጋገጥ በተያያዝነው ጥረት ረገድ የተጋረጡብንን ተግዳሮቶች በመገንዘብ፤
    • ሕዝባችን በሰላምና ደህንነት እጦት፣ በኮቪድ-19 ወረርሽኝና መረን በለቀቀ የኑሮ ውድነት እየደረሰበት ያለውን ምጣኔ ሀብታዊ ድቀት ግምት ውስጥ በማስገባት፤
    • ከሁሉም በላይ ሀገራችን ከውስጥ በከሃዲያንና እኩያን ኃይሎች ቅንጅት፣ ከውጭ በታሪካዊ ጠላቶቻችንና ዓለምአቀፍ አጋሮቻቸው አይዞህ ባይነትና ድጋፍ የተደቀነባትን የህልውና ስጋት ተቀዳሚ ትኩረት በመስጠት፤

    የፓርቲው ሥራ አስፈፃሚ የደረሰባቸውን አቋሞች ለተከበረው ሕዝባችን፣ ለአፍሪካውያን ወንድሞቻችንና በአጠቃላይም ለዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ለማሳወቅ ይወዳል።

    1. ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ በተመለከተ

    አብን እንደ ድርጅት የመጀመሪያው አብይ የፖለቲካ ተመክሮው በሆነው በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ውስጥ ለመሳተፍ ሲያቅድ፥ ገና ከመነሻው ሀገራችን የምትገኝበትን የፖለቲካ አውድ በመገምገም በምርጫው የመሳተፉን ውሳኔ ያደረገው በዋነኝነት ከድርጅታዊ ፋይዳዎች ይልቅ ለሀገራዊ ፖለቲካው መረጋጋትና ለዴሞክራሲያዊ ተመክሮ ግንባታ ከሚኖረው ፋይዳ አንፃር እንደሆነ በይፋ አሳውቋል።

    አብን ሀገራዊ ፓርቲ እንደመሆኑ መጠን የምርጫ ዘመቻውን ስትራቴጂክ ግቦችና ማስፈፀሚያ ስልቶችን በዝርዝር በመንደፍ፣ አማራጭ ፖሊሲዎቹን በማኒፌስቶ በመሰነድና ሙሉ ድርጅታዊ ኃይሉን በማንቀሳቀስ በምርጫ በሚሳተፍባቸው በአማራና ሌሎችም የሀገሪቱ ክፍሎች 510 እጩዎችን በማቅረብ ሰፊውን መራጭ ሕዝብ ለመድረስ ያልተቆጠበ ጥረት አድርጓል።

    በዚህም መሠረት የምርጫ ዘመቻው ከነተግዳሮቶቹ ተጠናቅቆ፣ በሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ፓርቲያችን በሚወዳደርባቸው ክልሎች ድምፅ ተሰጥቶና በከፊል ጊዜያዊ ውጤት ተገልጾ በድኅረ ምርጫ ሂደት ላይ እንገኛለን።

    ፓርቲያችን በመላ ሀገሪቱ በተወዳደረባቸው አካባቢዎች በምርጫው ሂደት የተፈፀሙትን አበይት ጥሰቶች በማሰባሰብና በዝርዝር ቅሬታዎችን በመሰነድ በህግ አግባብ ለብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አቅርቧል። የምርጫ ቦርድ ከተጣለበት ታላቅ ሀገራዊ ኃላፊነት አኳያ ከሰው፣ ከፋይናንስ፣ ከተመክሮና ከሎጂስቲክ አቅም ውሱንነት ቢታይበትም በአጠቃላይ ከቅድመ ምርጫው ጀምሮ አንፃራዊ አዎንታዊነት እንዳሳየ እናምናለን። በቦርዱ የበላይ አመራር የታየው ገለልተኝነት፣ ግልፅነትና ፍትሃዊነት መንፈስ እንደ ተቋም የሚፈተንበት ወቅት እንደሆነም እንገነዘባለን።

    የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ ሕዝባችን ይህንን ሁሉ ጫና ተቋቁሞ በምርጫው ሂደት ውስጥ በመሳተፍ ላሳየው ፅናት ልባዊ አድናቆቱን በመግለፅ፣ የመራጩ ድምፅ እንዲከበር ተገቢውን ሰላማዊና ህጋዊ ጥረት እንደሚያደርግና የሕዝባችንንም ሀቀኛ ውሳኔ ያለማወላወል እንደሚቀበል ለማሳወቅ ይወዳል።

    በሌላ በኩል 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ የሥርዓቱን እውነተኛ ባህርይ በተግባር መፈተንና ማጋለጥ መቻሉን ትልቁ ውጤት አድርጎ መውሰድ ይቻላል። በምርጫው ሂደት የታየው ጎዶሎነትና ክፍተት ከምርጫ ውጤት አኳያ የምንመዝነው ከሆነ የሀገራችንን ተጨባጭ ሁኔታና የሃሳብ ብዝሃነት የማያመለክት መሆኑን መናገር ይቻላል።

    አብን እንደ ድርጅት በምርጫ በመሳተፉ ምን አገኘ፣ አሳካ የሚለውን ስንገመግም አንዳንድ ተስፋ ሰጭ ነገሮች እንዳሉ መካድ አይቻልም። ከሁሉም በላይ የሕዝባችን እውነተኛ ወኪል ስለመሆናችን ሕዝባችን የነበሩትን ጫናዎች ተቋቁሞ በሰጠን የመተማመኛ ድምፅ በቂ ማረጋገጫ አግኝተናል። ይህም የመጪው ዘመን ፓርቲ መሆናችንን ይመሰክራል። በሐገር አቀፍ ድረጃ በተሻለ ሕዝብን የማስተባበር አቅም እንዳለንና ጠንካራ ተገዳዳሪ የፖለቲካ ኃይል መሆናችንን በማያሻማ ሁኔታ አረጋግጠናል።

    የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ የምርጫው ሂደት አጠቃላይ ድርጅታዊ ቁመናውን የሚፈትሽበት መልካም አጋጣሚ መሆኑንም ይገነዘባል። በቀጣይም ከሂደቱ ያገኛቸውን ተመክሮዎችና ትምህርቶች በማካተትና ሁለገብ የማሻሻያ እርምጃዎች በመውሰድ ለብሔራዊ ፖለቲካችን ሁነኛ ሚና መጫወቱን እንደሚቀጥል አያጠራጥርም።

    1. ብሔራዊ ደህንነትን በተመለከተ

    የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ በተለይ በሀገር ሉዓላዊነትና አንድነት፣ በሕዝብ ጥቅምና ክብር፣ በሀገረ መንግሥቱ ቀጣይነት ረገድ ግልፅና የማያሻማ አቋም ያራምዳል። በገዥው ፓርቲ ግልፅ ፍረጃ፣ ወከባና ጥቃት እየደረሰበትም ቢሆን የፖለቲካ ማዕከሉ እንዲረጋጋና በአፍሪካ ረዥሙንና ደም አፋሳሹን የእርስ በርስ ጦርነት ያደረገች ሀገር ተመልሳ ወደ ቀውስ እንዳትገባ ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል።

    አብን ወቅታዊው የሀገራችን ብሔራዊ ደህንነት ከጊዜ ጊዜ እየከፋና እጅግ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ይገነዘባል። የውጭ ወራሪዎችና የውስጥ ቦርቧሪዎች ከተቻለ ኢትዮጵያን ለየዘውጉ አምበሎች በታትኖ ከዓለም ካርታ ለማጥፋት፤ ካልሆነ ደግሞ ውስጣዊ አንድነት የሌላት፣ ደካማና ፍላጎታቸውን ያለማንገራገር የምትቀበል አድርገው ለማሽመድመድ እየተረባረቡ ይገኛሉ።

    ከዚህ አንፃር የብልጽግና አገዛዝ የሀገሪቱን፣ የዜጎችና የመንግሥቱን ሰላምና ደህንነት፣ ጥቅምና ክብር በማስጠበቅ ረገድ ጉልህ ክፍተቶች እየተስተዋለበት ነው። በአሁኑ ወቅት መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ባደረገው ከፍተኛ ተጋድሎ ከአፈናና ጭቆና መንበሩ የተባረረውና በሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ በአማራ እና አፋር ልዩ ኃይልና ሕዝባዊ ሚሊሺያ ድባቅ የተመታው የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር (ትህነግ) ተመልሶ በማንሰራራት በብሔራዊ ደህንነታችን ላይ ተቀዳሚ አደጋ ሊሆን በቅቷል።

    አብን ማዕከላዊ መንግሥትና በየደረጃው ያሉ መንግሥታዊ አካላት ሀገሪቱ ከተደቀነባት የህልውና አደጋ ለመታደግ በሚደረገው ርብርብ የራሳቸውን ሚና በግልፅ ከመወሰን አንስቶ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያካተተ የብሔራዊ ደህንነት እርምጃ እንዲወስዱ ጥሪ ያቀርባል።

    መንግሥት ልዩ የደህንነት ስጋት ያለባቸው አካባቢዎች ላይ ትኩረት እንዲያደርግ፤ በተለይም አሸባሪው የትህነግ ቡድን መልሶ በተቆጣጠረው በትግራይ የተማሪዎችንና የሲቪል ዜጎችን፤ በአጠቃላይም የትግራይን ሕዝብ ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ይጠይቃል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በትግራይ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ተመድበው ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙ ተማሪዎች ሁኔታ አብንን በእጅጉ ያሳስበዋል። የትግራይ ሕዝብ በመካከሉ ለሚገኙ ተማሪ ልጆቹ አስፈላጊውን ጥበቃና ክብካቤ እንዲያደርግ ጥሪ እናደርጋለን።

    አብን መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ሀገር ወዳድ ዜጎችና በተለይም ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል ሀገራችን ስለገጠማት የብሔራዊ ደህንነት አደጋ ግልፅ ግንዛቤ እንዲኖራቸውና ኢትዮጵያን ለመታደግ በአንድነት እንዲሰለፉ ጥሪ ያደርጋል።

    በወታደራዊ ኃይል የሚገኘው ድል ዳግም በዲፕሎማሲው አውድማ እንዳይነጠቅ መላው ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን የሀገራቸው አምባሳደር በመሆን በዓለምአቀፍ የዲፕሎማሲ ትግል እንዲሳተፉ ጥሪ ያቀርባል።

    በተለይም ደግሞ በፀረ – ኢትዮጵያው ጎራ በጠላትነት ተፈርጆ ዘርፈ ብዙ ጥቃት የተሰነዘረበት የአማራ ሕዝብ የሚገኝበትን ወቅታዊ የስጋት ደረጃ በውል ተገንዝቦ የበኩሉን ጥንቃቄና ዝግጅት እንዲያደርግ፣ የአማራ ዲያስፖራ በሕዝባችንና በሀገራችን ላይ የተቃጣውን አደጋ ለመቀልበስ ሁለገብ የሃሳብ፣ የፋይናንስ፣ የዲፕሎማሲ ተሳትፎውን አጠንክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ያቀርባል።

    አብን አፍሪካውያን ወንድሞቻችን፣ መላው የኢትዮጵያ ወዳጆችና አጋሮች የጥንታዊ ሥልጣኔ፣ አኩሪ የነፃነት ታሪክ ያላት ሀገር በእኩያን ኃይሎች የተከፈተባትን ወታደራዊ፣ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ጥቃት ለመመከት ከጎናችን እንዲሰለፉ ጥሪ ያደርጋል። በዚህ ረገድ በአካባቢው ጉዳይ ትኩረት አድርገው የሚንቀሳቀሱ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ዓለምአቀፍ ተቋማት በአፍራሽ የሀሰት ፕሮፓጋንዳ እንዳይደለሉና የችግሩን ዙሪያ ገብ በፍትሃዊነት በመገምገም እንዲንቀሳቀሱ ጥሪ ያቀርባል።

    የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ በሀገራችን ላይ የተደቀነውን ፅኑ የብሔራዊ ደህንነት ስጋት ለመመከትና ከምንም በላይ የቆመለትን የሀገር አንድነትና ሉዓላዊነት፣ የሕዝብ ጥቅምና ክብር እንዲሁም የሀገረ መንግሥቱን ቀጣይነት ለማረጋገጥ የሚጠበቅበትን ሁሉ ድርጅታዊ አስተዋፅኦ ለማድረግ ቁርጠኝነቱን በአፅንኦት ለመግለፅ ይወዳል።

    የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)
    አዲስ አበባ፣ ሸዋ፣ ኢትዮጵያ
    ሰኔ 28 ቀን 2013 ዓ.ም

    ምንጭ፦ አብን

    የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ

    Anonymous
    Inactive

    ሚያዝያ 11 ቀን፥ 2013 ዓ.ም.
    አቶ ልደቱ አያሌው
    ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን
    አዲስ አበባ

    ጉዳዩ:- በድጋሚ አቤቱታ ማቅረብን ይመለከታል

    በቅድሚያ በእኔ በአመልካቹ ላይ በተደጋጋሚ እየደረሰ የሚገኘውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፍትሄ እንዲያገኝ መሥሪያ ቤታችሁ እያደረገ ስላለው ያልተቋረጠ ጥረት ልባዊ ምስጋናየን አቀርባለሁ። ሆኖም በእኔ ላይ እየተፈፀመ የሚገኘው የሰብዓዊ መብት ጥሰት አሁንም ያልተቋረጠና ለሕይወቴ አስጊ በሆነ ደረጃ ተጠናክሮ የቀጠለ በመሆኑ፥ ይሄንን አቤቱታ በድጋሚ ለማቅረብ ተገድጃለሁ።

    የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በሀገሪቱ የተፈጠረውን የፖለቲካ ቀውስ ሰበብ በማድረግ በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንድውል ከተደረገበት ከሐምሌ 17 ቀን፥ 2012 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገሪቱ ሕግና የሕግ የበላይነት የለም ሊያስብል በሚባል ደረጃ በርካታና ተከታታይ የሰብዓዊ መብት መብት ጥሰት በእኔ ላይ እየተፈፀመ ይገኛል። ለማስታወስ ያህል…

    1. ሕጋዊ ነዋሪነቴ ተመዝግቦ የሚገኘው በአዲስ አበባ ከተማ ሆኖ እያለ፥ እንድታሰር የተደረገው ግን ያለ አግባብ በኦሮሚያ ክልል ነው።
    2. በስልክ ተጠርቼና ለፌደራሉ ፖሊስ ኮሚሽን በእራሴ ፈቃድ እጄን ሰጥቼ በቁጥጥር ስር ከዋልኩ በኋላም በሕጉ መሠረት በ48 ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት እንድቀርብ አልተደረገም።
    3. በቁጥጥር ስር ከዋልኩ በኋላ ያለምንም ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በስልክና በኢንተርኔት አማካይነት ያደረኳቸው የግል የመልዕክት ልውውጦች በሕገ-ወጥ መንገድ እንዲበረበሩና በሲዲ እንዲቀዱ ተደርገዋል። የግል ማስታወሻወቼና ረቂቅ የፅሁፍ ሰነዶቸ ሳይቀሩ በፖሊስ ተወስደዋል።
    4. በቁጥጥር ውስጥ ውዬ ገና ክስ እንኳ ባልተመሠረተብኝ ወቅት የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኛ ነን የሚሉ ሰዎች ወንጀለኛ እንደሆንኩ አድርገው ሰፊ የስም ማጥፋት ዘመቻ እንዲያካሂዱብኝ ተደርጓል።
    5. በምርመራ ወቅትና የምርመራ ፋይሌ ከተዘጋ በኋላም የዋስ መብት ተከልክዬና ክስ ሳይመሠረትብኝ በጊዜ ቀጠሮ ሰበብ ከሁለት ወራት በላይ ለሆነ ጊዜ በሕገ-ወጥ መንገድ በእስር ቤት እንድቆይ ተደርጓል።
    6. በፍርድ ሂደቱ ወቅት በግልፅ እንደታየው፥ በቢሾፍቱ ከተማ አመፅ አስነስተሀል፤ ሕገ-ወጥ መሣሪያ ታጥቀህ ተገኝተሀል፤ መንግሥትን በሕገ-ወጥ መንገድ አፍርሰሀል የሚሉ የፈጠራ ክሶች እንዲቀርቡብኝ ተደርጓል።
    7. “መንግሥትን በሕገ-ወጥ መንገድ አፍርሰሀል” በሚል የተከሰስኩበት ወንጀል አዲስ አበባ በሚገኝ የፌደራሉ ፍርድ ቤት መታየት ሲገባው ያለ አግባብ በአዳማ ከተማ የሚገኘው የኦሮሚያ ክልል ጥቅላይ ፍርድ ቤት በውክልና እንዲያየው ተደርጓል። ይህም መሆኑ የፍርድ ሂደቱ በማልናገረው ቋንቋ እንዲካሄድና ብዙ ውጣ ውረድ እንዲደርስብኝ አድርጓል።
    8. በፍርድ ሂደቱ ወቅት ለሁለት ጊዜ ያህል የዋስ መብት በፍርድ ቤት ቢፈቀድልኝም ፖሊስ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ በመጣስ ለሁለት ወራት ያህል በእስር አቆይቶኛል። ከዋስትና መብቴ ጋር በተያያዘም ፍርድ ቤት ለአምስት ጊዜ የሰጣቸው የተለያዩ ትዕዛዞች በፖሊስ እምቢተኝነት ሳይፈፀሙ ቀርተዋል።
    9. ለሕይወት አስጊ የሆነ ከፍተኛ የልብ ህመም ያለብኝ ሰው መሆኔ እየታወቀም የኮቪድ ወረረሽኝ ተጠቂ ከሆኑ ሰዎች ጋር በአንድ ጠባብ ግቢ ውስጥ ታስሬ ለረጅም ጊዜ እንድቆይ ተደርጓል።
    10. ከአምስት ወራት መታሰር በኋላ የዋስ መብቴ ተጠብቆ ከተፈታሁ ከጥቂት ቀናት በኋላም እኔንና የትግል ጓደኞቼን ከሀገሪቱ የፖለቲካ ሂደት ለማግለል ሲባል አባል የሆንኩበት የፖለቲካ ፓርቲ በሕገ-ወጥ መንገድ እንዲሰረዝና ህልውናውን እንዲያጣ ተደርጓል።
    11. ከእስር ቤት ወጥቸ አስቸኳይ የቀዶ ጥገና የሕክምና እርዳታ ለማግኘት ወደ ውጭ ሀገር ለመጓዝ ለሁለት ጊዜ ያደረኩት ሙከራም ምንም አይነት የፍርድ ቤት እገዳ ባልተጣለብኝና እንዲያውም ጉዳዩን ይመለከት የነበረው ፍርድ ቤት ወደ ውጭ ሀገር ሄጀ የመታከሜን አስፈላጊነት በማመን ረዥም ቀጠሮ ሰጥቶኝ እያለ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት መሥሪያ ቤት በሕግ ባልተሰጠው ሥልጣን ባደረገብኝ ሕገ-ወጥ ክልከላ ምክንያት ከሀገር የመውጣት ሕገ- መንግሥታዊ መብቴ ተጥሷል።
    12. ይህ የተጣለብኝ ሕገ-ወጥ እገዳ እንዲነሳልኝ ለማድረግ የተለያዩ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን የመንግሥት ባለ ስልጣናት ቀጠሮ ይዤ ለማነጋገር በተደጋጋሚ ብሞክርም ባለስልጣናቱ ሊያናግሩኝ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ሙከራዬ ሳይሳካ ቀርቷል።
    13. መሥሪያ ቤታችሁ ባደረገው ጥረት ምክንያት የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት መሥሪያ ቤት በእኔ ላይ ምንም ዓይነት የጉዞ ክልከላ እንዳላደረገ የሚክድ ደብዳቤ ለመሥሪያ ቤታችሁ ከፃፈ በኋላም ለሦስተኛ ጊዜ ከሀገር ለመውጣት ያደረኩት ሙከራ የኢሚግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ክልከላ ስላደረገብኝ ጉዞዬ ሳይሳካ ቀርቷል። የጉዞ ፓስፖርቴም በመሥሪያ ቤቱ ባልደረቦቼ ተወስዶብኛል።
    14. የኢሚግሬሽን መሥሪያ ቤት ለምን የጉዞ ክልከላ እንዳደረገብኝና እንደቀማኝ በማግስቱ ዋናው መሥሪያ ቤት ድረስ ሄጄ ለመጠየቅ ባደረኩት ሙከራ የፌዴራሉ ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ክፍል ባቀረበው ጥያቄ መሠረት በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውዬ ምርመራ እስከሚካሄድብኝ ድረስ የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የአራዳ ምድብ አንደኛ ችሎት የካቲት 4 ቀን፥ 2013 ዓ.ም. በዋለው ችሎት ወደ ውጭ እንዳልጓዝ እገዳ የጣለብኝ ስለመሆኑ ተነግሮኛል።

    ከእነዚህ ከዚህ በላይ ከተዘረዘሩት ተደጋጋሚ የመብት ጥሰቶች በግልፅ መረዳት እንደሚቻለውና በእኔ በኩል እንደምገነዘበውም መንግሥት በእኔ ላይ ይህን ሁሉ የመብት ጥሰት እየፈፀመ የሚገኘው የፈፀምኩት ወንጀል ስላለ ሳይሆን መብቴን በሕገ-ወጥ መንገድ በመጣስና በመገደብ ከፖለቲካ ተሳትፎ ውጭ እንድሆን ስለፈለገ ነው።

    እኔ አመልካቹ የአለፈ ታሪኬ እንደሚያሳየው ለሃያ ስምንት ዓመታት በሀገሪቱ ፖለቲካ በነበረኝ ተሳትፎ ስድስት ጊዜ በሕገ-ወጥ መንገድ በፈጠራ ክስ የታሰርኩ ቢሆንም አንድም ጊዜ በወንጀለኝነት ተፈርዶብኝ አያውቅም። የኢትዮጵያ ህዝብ በግልፅ እንደሚያውቀው በዚህ የረጅም ጊዜ የፖለቲካ ተሳትፎዬ ስታገል የኖርኩት በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም፣ እርቅና የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን ሲሆን፤ በአንፃሩም ሕገ-ወጥነትን፣ አመጽንና የኃይል አማራጭን በግልፅና በድፍረት በማውገዝ የምታወቅ ሰላማዊ የፖለቲካ ሰው ነኝ። ሆኖም መንግሥት ከላይ በተገለፀው ሁኔታ በፈጠረብኝ ተከታታይ ሕገ-ወጥ ጫና ምክንያት በአሁኑ ወቅት ከፖለቲካ ተሳትፎዬ ሙሉ በሙሉ ለመገለል የተገደድኩ ሲሆን ከዚያም በላይ ያለብኝን ከፍተኛ የልብ ህመም ወደ ውጭ ሀገር ሄጀ መታከም ባለመቻሌ ምክንያት በህይወት የመኖር ዕድሌ ከፍተኛ አደጋ ላይ ወድቋል። በአጠቃላይም እየደረሰብኝ ባለው ተደጋጋሚ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ምክንያት ለከፍተኛ የጤና መታወክ፣ የሞራል ውድቀት፣ የገንዘብና የጊዜ ብክነት ተዳርጊያለው።

    ይህ ሁሉ በተደጋጋሚ የተፈጸመብኝ በደል አልበቃ ብሎም እኔ አመልካቹ ፈጽሞ ባልተነገረኝና በማላውቀው ሁኔታ፣ ምንም ዓይነት ጥያቄ ባልቀረበልኝና ምርመራ ባልተካሄደበት ሁኔታ፣ ከዚያም በላይ ተፈልጌ የጠፋሁ ወንጀለኛ የሆንኩ በሚያስመስል ሁኔታ የጉዞ እገዳ የተጣለብኝ ስለመሆኑ የአራዳ ፍርድ ቤት ሰጠ የተባለው ትዕዛዝ አሁንም በእኔ ላይ የፈጠራ ክስ እንደገና በመመሥረት እንድታሰርና ሕይወቴ አደጋ ውስጥ እንዲወድቅ እየታሰበና ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ነው።

    በአንድ ሰው የደረሰ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በሁሉም ሰው ላይ እንደደረሰ ጥሰት የሚቆጠር መሆኑን ታሳቢ በማድረግና በእኔ ላይ እየተፈፀመ ያለው ተደጋጋሚ መቋጫ ያጣ የሰብዓዊ መብት ጥሰትም የፖለቲካና ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ ሕገ-መንግሥታዊ መብቴን ከመጣስም በላይ በሕይወት ለመኖር ያለኝን የማይገሰስ ሰብዓዊ መብቴን አደጋ ላይ የጣለ መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት፥ መሥሪያ ቤታችሁ በጉዳዩ ልዩ ትኩረት በመስጠት ምርመራ እንዲያካሂድልኝና አስቸኳይ መፍትሔ እንዳገኝ እንዲያግዘኝ በድጋሚ በአክብሮት እጠይቃለሁ።

    ከሰላምታ ጋር!
    ልደቱ አያሌው

    ግልባጭ፦
    ለመገናኛ ብዙሀን

    አቶ ልደቱ አያሌው ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የጻፉት ደብዳቤ

    Anonymous
    Inactive

    ሕዝባችን ከመቼውም ጊዜ በላይ የተጋረጠበትን መንግሥታዊ ሽብር በተደራጀ አግባብ እንዲከላከል ጥሪ እናቀርባለን!
    የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)

    ድርጅታችን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በአንድ በኩል በሕዝባችን ላይ ለበርካታ አስርተ ዓመታት የቀጠለውን ሕግና መዋቅር ሠራሽ የፖለቲካ ሸፍጥ በዘላቂነት ለመቅረፍ፣ በሌላ በኩል ሕዝባችንና ሀገራችን ከተጋረጠባቸው የኅልውና አደጋዎች ለመታደግ በሚደረገው ሀገራዊ የበጎ ኃይሎች ጥምረት አካል በመሆንና በትጋት በመሥራት ላይ የሚገኝ መሆኑን በሀቅ የሚፈርድ ሁሉ የሚረዳው እውነታ ነው።

    ምንም እንኳን ትጋታችን ለማንም አካል በመታያነት የቀረበ ባይሆንም፥ እጅግ ፈታኝ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ እንኳ ሆነን “የተሻለ ነገ” ሊመጣ ይችላል የሚል እሳቤን አንግበን እዚህ ደርሰናል።

    ቀደም ሲል በተደጋጋሚ ለመንግሥት እንዳሳሰብነው መሠረታዊ የሆኑ የለውጥ ሀሳቦችን መሬት ለማስረገጥና የተሳሳተውን የማደራጃ ትርክት፣ የተዛነፈውን መዋቅራዊና ሥርዓታዊ ማእቀፍ በማስተካከል ሕዝብን ለዘላቂ ሰላምና ሥልጣን ለማብቃት የበኩላችንን ያልተቋረጠ ጥረት ከማድረግ ጎን ለጎን በተለይ ሀገራችንና ማዕከላዊ ሥርዓቱ እንዳይፈርሱ ለማድረግ በተደረጉ ጥረቶች ሁሉ አብንና የአማራ ሕዝብ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል።

    ሆኖም፦

    1/ መንግሥታዊ ሽብሩን በማባባስ፣ በመደገፍ እና ትእዛዝ በመስጠት ጭምር የሚሳተፉት የሀገራችን ጠቅላይ ሚንስቴርና የሚመሩት የኦሮሞ ብልጽግና ክፍል መንግሥታዊ መዋቅርንና የሀገር ሀብትን በመጠቀም የአማራን ሕዝብ የማሸበር ተግባር አጠናክረው ቀጥለዋል። ሕዝባችንን ለማሸበር የተከፈተው መጠነ-ሰፊ የዘር ፍጅት በመንግሥት መዋቅር በቀጥታ የሚደገፍና የሚመራ መሆኑን አብን ያምናል። ለዚህም የሚከተሉትን ነጥቦች በጉልህ ማሳያነት ማቅረብ ይቻላል።

    ሀ/ በአማራ ሕዝብ ላይ የተቀናጁ የጅምላ ፍጅት ጥቃቶችን የከፈተው በተለምዶ “ኦነግ ሸኔ” ተብሎ በጠቅላይ ሚንስትሩ የሚጠራው አካል ከመነሻው ከነትጥቁ ወደ ሀገር ቤት የገባበትን አሻጥር፤

    ለ/ ከዚያ ቀደም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጭምር እንደገለጹት ከተጠቀሰው ድርጅት ጋር የነበራቸው መረጃን የመለዋወጥ ድብቅ ግንኙነት የሚታወቅ በመሆኑ ከልጅነት እስከ እውቀት አጋር የሆናቸውን ድርጅት አሁንም በልዩ ስልት የማደራጀት፣ የመደገፍ እና የመንከባከብ ሚናቸውን እየተጫወቱ እንደሆነ ንቅናቄያችን በጽኑ ያምናል።

    ሐ/ የ“ኦነግ ሸኔ” ኮር ስትራቴጂክ አመራር በመሀል አዲስ አበባ ውስጥ ተቀምጦ እየመራ ባንኮችን ጭምር በጠራራ ፀሐይ በመዝረፍ ኃይል እንዲያጎለብት የተፈቀደበትና የተመቻቸበት አግባብ መኖሩ፤

    መ/ በአማራ ሕዝብ ላይ እየተፈፀመ ያለውን ተደጋጋሚ የዘር ጥቃት ማስቆም ይቅርና ጅምላ ፍጅቱ በሀገር ደረጃ ለሀዘን መግለጫ እንኳ እንዳይበቃ የተደረገ ከመሆኑም በላይ በሀዘን ድንኳናችን ላይ ቀይ ምንጣፍ አንጥፈው ሕንፃ እና አበባ የሚመርቁበት አስደንጋጭ ማኅበራዊ ስላቅ ሳይቋረጥ መቀጠሉ፤

    ሠ/ በአማራ ሕዝብ ላይ የተከፈተው ዘር-ተኮር ጥቃት የታቀደና የተቀናጀ ሲሆን፥ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጭምር የዘር ማጥፍት ወንጀል ለማስፈጸም አመላካች የሆኑ የመግቢያ ንግግሮችን በይፋ ሲያሰሙ መቆይታቸውና ለዚህም ምንም ዓይነት አስተዳደራዊም ይሁን ፖለቲካዊ እርምት አለመሰጠቱ፤

    ጠቅላይ ሚንስትሩና የሚመሩት መንግሥት በዚህ የአማራን ሕዝብ የማሸበርና የዘር ፍጅት እንቅስቃሴ ውስጥ ሚና አላቸው ብሎ ንቅናቄያችን ለማመን ተገዷል።

    2/ የአማራ ክልል መንግሥት ከተፈጥሯዊውና መደበኛው የታዛዥነት መንፈስ አለመውጣቱ፣ ደንታ ቢስነቱና አቅመ ቢስነቱም እየበረቱበት መሆኑ ሕዝባችንን አቻ ለማይገኝለት ማኅበራዊ ውርደት ያበቃ በመሆኑ፤

    አብን የአማራ ሕዝብ ትግል ከተለመደው አካሄድ ተላቆ ኅልውናውን የመታደግና የማስከበር የተቀናጀና የተጠናከረ የትግል ምእራፍ ውስጥ መግባት አለበት የሚል ድምዳሜ ደርሷል። ትግሉንም ለመምራት ንቅናቄያችን ከፊት ይሰለፋል።

    መላው የአማራ ሕዝብም የተከፈተበትን አጠቃላይ የኅልውና አደጋ በመገንዘብ እና ለደኅንነቱ የሚያስብለት መንግሥት እንደሌለው በመረዳት ራሱን የመከላከል ተፈጥሯዊ መብቱን እንዲሠራበት አብን በአጽንዖት ያሳስባል። ሕዝባችንም በዚህ ፈታኝ ወቅትም ወዳጅ መስለው በጠላትነት በቆሙ ቡድኖችና ግለሰቦች ግፊት ፈተና ላይ እንዲወድቅ የሚፈለገውን አንድነቱን አጠናክሮ እንዲጠብቅ እናሳስባለን።

    በሀገር ውስጥም ይሁን በውጭ ሀገራት የምትገኙ ወገን ወዳድ ኢትዮጵያውያን፥ በመሠረቱ ያንዣበበው አደጋ በአማራ ሕዝብ ላይ ብቻ ተወስኖ የሚቆም አለመሆኑን በመገንዘብ በአማራ ሕዝብ ላይ በተቀናጀ ሁኔታ እየተፈፀመ ያለውን የዘር ፍጅት ጥቃት እንድታወግዙና የመልሶ ማቋቋም ሥራዎችን እንድታግዙ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።

    በተለያዩ ስምሪቶች በቅንነት ሀገራችሁን የደገፋችሁ መስሏችሁ ለሥርዓቱ እገዛ የምታደርጉ ወገኖች ሂደቱን በመገምገም ጥያቄ እንድታነሱና ከተገፉ ወገኖች ጎን እንደትሰለፉ ጥሪ እናቀርባለን።

    በሀገር ውስጥም ይሁን በውጭ ሀገራት የምትኖሩ የአማራ ተወላጆች በእያንዳንዱ ቀን የአማራ ሕዝብ ደም እንደጅረት የሚፈስበት ሀገር መሆኑን በመረዳት፥ አማራው ለአጠቃላይ የኅልውና አደጋ የተጋለጠ መሆኑን በመቀበልና መሠረተ-ቢስና መናኛ ከሆኑና የሞራልና የታሪክ ተጠያቂነት ከሚያስከትሉ ልማዳዊ የፖለቲካ ዘይቤዎች በአስቸኳይ በመላቀቅ ሰብዓዊ፣ ወገናዊና ሀቀኛ የሆነ የፖለቲካ አቋም በመውሰድ ሕዝብ የመታደግ ድርሻችሁን እንድትወጡ የሚል ታሪካዊ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።

    ኅልውናችንን በትግላችን እናስከበራለን!
    እጣፋንታችንን በራሳችን እጆች እንጽፋለን!
    የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)

    የፖለቲካ ፓርቲዎች ድምጽ (ኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች)

    ሕዝባችን ከመቼውም ጊዜ በላይ የተጋረጠበትን መንግሥታዊ ሽብር በተደራጀ አግባብ እንዲከላከል ጥሪ እናቀርባለን

    Anonymous
    Inactive

    ከኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር በሀገራችን ወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታ የተሰጠ መግለጫ

    በአንዳንድ የሀገራችን አከባቢዎች ሕዝብን ከሕዝብ በማጋጨት በንጹሃን ዜጎች ላይ የህይወት እና ንብረት አደጋ ባደረሱ የጥፋት ቡድኖች ላይ እርምጃ መወሰድ ተጀምሯል።

    የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊታችን በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ትግራይ ክልል ውጤታማ ሕግ የማስከበር ተልእኮውን በጀግንነት በመፈጸም ላይ በሚገኝበት በአሁኑ ወቅት፣ በአንዳንድ የሀገራችን አከባቢዎች የጸጥታ ችግሮች እየተስተዋሉ ይገኛሉ።

    እነዚህ ሆን ተብሎ የሠራዊታችንን ሕገ-መንግሥታዊ ተልእኮ ለማስተጓጎል ታስበው የተሠሩ የጥፋት ሴራዎች፣ በሰላም ወዳዱ ሕዝባችን እና በመከላከያ ሠራዊታችን የተቀናጀ ሥራ ሊከሽፉ ችለዋል።

    አንደኛ በመተማ መስመር ለዘመናት አብረው በኖሩ የቅማንት እና የአማራ ተወላጆች መካከል የተፈጠሩ የጸጥታ ችግሮችን የፈዴራል እና የክልል የጸጥታ ኃይሎች ከኅብረተሰቡ እና ከአካባቢው የሀገር ሽማግሌዎች ጋር የተቀናጀ ሥራ በመሥራት የተከሰቱ የጸጥታ ችግሮን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ከፍተኛ ሥራ እየተሠራ ይገኛል ።

    ሁለተኛ፥ በወለጋ ቡሬ መስመር፣ በጊዳ አያና፣ አንገር ጉቴ አዋሳኝ አከባቢዎች ለረዥም ጊዜ አብሮ በኖሩ የአማራ እና የኦሮሚያ ክልል ነዋሪዎችን ሆን ብሎ ለማጋጨት ታስቦ የተደረገው ሙከራ በአከባቢው ኅብረተሰብ ትብብር ወደ ሰላማዊ ሁኔታ ለመመለስ ተችሏል።

    ሦስተኛ፥ የሀገራችንን የገቢ እና ወጪ የንግድ እንቅስቃሴን ለመገደብ በማሰብ፣ በሱማሌ እና የአፋር ኢሳ ሕዝቦችን ለማጋጨት የተሴረው ሴራ በሰላም ወዳዱ ሕዝባችን የተቀናጀ ተሳትፎ በቁጥጥር ስር ለመዋል ችሏል።

    አራተኛ፥ ሰሞኑን በሰሜን ሸዋ እና በደቡብ ወሎ የኦሮሞ ልዩ ዞን ወረዳዎች በተለይም በዚህ ሁለት ሶስት ቀን በአጣዬ ከተማ እና በአከባቢው በታጠቁ ኃይሎች በሰው ህይወት እና ንብረት ላይ በደረሰው ውድመት፣ የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን እየገለጸ፥ በዚህ አደጋ ለተጎዱ ወገኖች መጽናናትን ይመኛል።

    በዚህ የጸጥታ ችግር ተሳታፊ የሆኑ ወንጀለኞችን በቁጥጥር ስር የማዋል እና መሣርያ ይዘው በጸጥታ አካላት ላይ ተኩስ የከፈቱ፣ የሠራዊቱን እንቅስቃሴ የገደቡ ጸረ-ሰላም ኃይሎች ላይ ሠራዊታችን እርምጃ መውሰድ መጀመሩን እየገለጽን፤ መንገድ መዝጋትን ጨምሮ የኅብረሰተሰቡን ሰላም በማወክ ላይ የተሰማሩ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር በጥብቅ ለማሳሰብ ይወዳል።

    በዚህም መሠረት፥ በሰሜን ሸዋ እና በደቡብ ወሎ የኦሮሞ ልዩ ዞን ወረዳዎች ከተከሰተው የጸጥታ ችግር ጋር ተያይዞ ከክልል እና ከፌዴራል የጸጥታ ተቋማት ጨምሮ ሶስቱንም ዞኖች ያካተተ ኮማንድ ፖስት ተቋቁሟል። ኮማንድ ፖስቱ የአካባቢውን ጸጥታ በማደፍረስ ሥራ ላይ በተሰማሩ የጥፋት ቡድኖች ላይ እርምጃ በመውሰድ የሕግ የበላይነት የማረጋገጥ ሥራን ይሠራል።

    በዚህም መሠረት የአከባቢውን ሰላም ወደ ነበረበት ለመመለስ ሲባል የሚከተሉት ክልከላዎች የተደረጉ መሆኑን ኮማንድ ፖስቱ ይገልጻል።

    1ኛ ከደብረ ሲና እስከ ኮምቦልቻ አዋሳኝ ወረዳዎች መንገድ ላይ፣ ከመንገዱ ግራ እና ቀኝ እስከ 20 ኪሎ ሜትር ውስጥ የጦር መሣሪያ ይዞ መንቀሳቀስ በጥብቅ የተከለከለ ነው።

    2ኛ መንገድ መዝጋትን ጨምሮ አብያተ ክርስቲያናትን እና የመንግሥት ተቋማትን፣ የግለሰብ መኖሪያ ቤትን እና ንብረት ማውደም ወይም ለዚህ ተግባር በተናጠልም ይሁን በቡድን መንቀሳቀስ በጥብቅ የተከለከለ ነው።

    ከላይ የተዘረዘሩትን እና ቀጣይ በኮማንድ ፖስቱ ለኅብረተሰቡ የሚገለጹ ክልከላዎችን ተላልፎ የተገኘ የፖለቲካ ድርጅት፣ የመንግሥት መዋቅር እና በድኖች ላይ ሕጋዊ እርምጃ የሚወሰድበት መሆኑ መታወቅ አለበት።

    በመጨረሻም መላው ኅብረተሰባችን እንደ ወትሮው ሁሉ ከጸጥታ ተቋማት ጎን በመሰለፍ ለገሀራችን ሰላም እና ደህንነት የበኩሉን ገንቢ ሚና እንዲጫወት ጥሪያችንን እናቀርባለን።

    የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር
    ሚያዝያ 10፥ ቀን 2013 ዓ.ም.

    ከመንግሥታዊ ተቋማት የሚወጡ ሰሞነኛ ዜናዎችና መግለጫዎች

    Anonymous
    Inactive

    ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) ማኒፌስቶውን ይፋ አደረገ

    ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) የምርጫ ማኒፌስቶ ይፋ ማድረጊያ መርሀ ግብር
    የፓርቲው ሊቀመንበር ዶ/ር አብዱልቃድር አደም ያስተላለፉትን መልእክት ሙሉ ቃል

    የተከበራችሁ የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ አባላት እና አመራሮች፣
    የተከበራችሁ ጥሪ የተደረገላችሁ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች፣
    የተወደዳችሁ የሚዲያ ተቋማት ተወካዮች፣

    ክቡራት እና ክቡራን፥

    ሀገራችን ኢትዮጵያ እጅግ ፈታኝ እና አስጨናቂ በሆነ የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ በማለፍ ላይ ትገኛለች። ያልተቋጨው የሀገር ግንባታ ፕሮጀክት የወለዳቸው ታላላቅ ተቃርኖዎች፣ ለግማሽ ምዕተ-ዓመት በሀገራችን የናኘው የግራ ፖለቲካ፣ በሥርዓት ያልተመራው የሪፎርም ሂደት ስር ከሰደደው ድህነት ጋር ተደርቦ የሕዝባችንን ህይወት በሰቆቃ እና በስጋት የተሞላ አድርጎታል።

    ሀገራችን በዘርፈ ብዙ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና አስተዳደራዊ ችግሮች ውስጥ ተዘፍቃ በርካታ ዘመን አልፏል። የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መጨፍለቅ፣ ሙስና እና አድልዎ፣ የፍትህ መዛባት፣ የመልካም አስተዳደር እጦት፣ የማኅበራዊ አገልግሎቶች መጓደል፣ ሥራ-አጥነት፣ የግጭቶች መበራከት፣ የሰላምና መረጋጋት መጥፋት የሀገራችን መለያ ምልክቶች ሆነዋል። በታሪክ የወረስናቸው ዜጎችን “አንደኛ እና ሁለተኛ” አድርገው የከፈሉ ግልጽ እና ስውር መንግሥታዊ አሰራሮች እና ልማዶች፤ ነጻነት፣ እኩልነት እና ፍትህ የሰፈነበት የመንግሥት ሥርዓት የመመስረት ሀገራዊ ትልማችን እውን እንዳይሆን እንቅፋት ሆነው ቆይተዋል።

    ለበርካታ ኢትዮጵያውያን የእለት ጉርስ የዓመት ልብስ ማግኘት የቀን ህልም ነው። የንጹህ የመጠጥ ውሀ፣ ዳቦ፣ መብራት እና ትራንስፖርት የመሳሰሉ መሠረታዊ አገልግሎቶች ለአብዛኛው የሀገራችን ሕዝብ እንደ ሰማይ የራቁ ናቸው። ሕዝባችን ይህ ሳያንሰው ከቤት በሰላም ወጥቶ መመለስ እጅግ አሳሳቢ ሆኖበታል። በሀገራችን ዜጎች ሀሳባቸውን በነጻነት መግለጽ ብዙ ዋጋ የሚያስከፍል ሆኖ የቆየ ሲሆን፣ ሰፊው የማኅበረሰብ ክፍል ሀሳቡን በነጻነት የመግለጽ መብቱ ተገፎ በርካታ ትውልድ አልፏል።

    መላ የሀገራችን ሕዝቦች ሰላም እና መረጋጋትን የሚያረጋግጥ የፖለቲካ ሥርዓት፣ የዜጎችን ሰብአዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚያስከብር ሕገ-መንግሥታዊ ዋስትና፣ ከአስከፊ ድህነት እና የኑሮ ውድነት የሚያላቅቅ፣ ለዜጎች በተለይም ለወጣቶች በቂ የሥራ ዕድል የሚያስገኝ የኢኮኖሚ ፖሊሲ፣ ዜጎች ራስን በራስ የማስተዳደር መብታቸውን በተግባር የሚያረጋግጥ ጠንካራ እና እውነተኛ የፌደራል ሥርዓት፣ ከጎረቤት ሀገራት እና ከመላው የዓለም ሕዝቦች ጋር ሰላም እና የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ፣ ሕግ እና ሥርዓትን የሚያስከብር፣ በዜጎች ላይ የሚደርስን ጥቃት መመከት የሚችሉ የመከላከያ እና የደህንነት ተቋማት ይሻሉ።

    ዘርፈ ብዙ ታሪካዊ እና ወቅታዊ ችግሮቻችንን አስወግደን ነጻነት፣ እኩልነት፣ ፍትህ፣ ልማት ለማረጋገጥ እና ኅብረ-ብሔራዊ አንድነታችንን ለማጠናከር በሕዝብ የተመረጠ፣ ሕዝብን የሚያገለግል እና ለሕዝብ ተጠያቂ የሆነ መንግሥት ያስፈልጋል።

    የተከበራችሁ ተሳታፊዎች፥

    በሀገራችን ታሪክ ነጻ እና ፍትሀዊ ምርጫ ተካሂዶ አያውቅም – በፍጹም። ባለፉት 25 ዓመታት የተካሄዱት ምርጫዎች ለዚህ ጥሩ ማሳያ ናቸው። የምርጫ ሂደት እና ውጤት ኢዴሞክራሲያዊ የነበሩ፣ የዜጎችን ነጻነት እና የስልጣን ባለቤትነት በግልጽ የካዱና ያዋረዱ፣ አማራጭ ሀሳቦች እንዳይሰሙ የታፈኑበት፣ በግጭት የተሞሉና በርካታ ንጹሀን ዜጎችን ለሞት እና ለአካል ጉዳት የዳረጉ ነበሩ።

    ጠንካራ እና ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳይፈጠሩ ተቋማዊ እና መዋቅራዊ መሰናክሎችን በመፍጠር እውነተኛ የመድብለ-ፓርቲ ሥርዓት እንዳይፈጠር ተደርጓል። በሀገራችን የተካሄዱ ምርጫዎች በሙሉ አንድ ፓርቲ ከራሱ ጋር ተወዳድሮ የሚያሸንፍበት፣ ከውጭ ኃይላት ድጋፍ ለማግኘት ሲባል የሚካሄድ ትርኢት ነበር።

    6ኛው ሀገር አቅፍ ምርጫ የሚካሄደው በዚህ መራር ታሪካዊ ሀቅ ውስጥ ሆነን ነው።

    የመምረጥ እና መመረጥ መብት ከዴሞክራሲያዊ መብቶች አንዱ እና ዋነኛው ነው። ቀደምት ኢትዮጵያውያን ይህንን መብት ለማግኘት ከፍተኛ መስዋእትነት ከፍለዋል። ከሕዝባችን የዴሞክራሲ ፍላጎት በተቃራኒ የቆሙ ገዥ መደቦች ዜጎች የመምረጥ እና የመመረጥ መብታቸውን በነጻነት እንዳይጠቀሙ ሰፊ የአፈና መዋቅር አደራጅተው መብቱን ነፍገውት ቆይተዋል።

    ባለፉት በርካታ አስርት ዓመታት መላ የሀገራችን ሕዝቦች የብሄር፣ የኃይማኖት እና የፖለቲካ ልዩነታቸውን ወደ ጎን ትተው በጋራ በከፈሉት ከባድ መስዋእትነት ብልጭ ያለው የለውጥ ብርሀን ዘላቂ ይሆን ዘንድ በሕዝብ ይሁንታ ያገኘ መንግሥት ሀገርን ሊያስተዳድር ይገባል።

    ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ታሪካዊ አጋጣሚ ነው ብለን እናምናለን። በመሆኑም መላው የሀገራችን ሕዝቦች በዚህ ታሪካዊ ምርጫ በንቃት በመሳተፍ በሀገራችን የነጻነት፣ የእኩልነት እና የፍትህ ዘመን እውን ይሆን ዘንድ የድርሻችንን ልንወጣ ይገባል።

    ደካማ እና አሳፋሪ የምርጫ ታሪካችን በምርጫ ላይ ያለን እምነት እጅጉን እንዲሸረሸር አድርጎታል። ይህ ስሜት ሀገራችን ውስጥ ያለው አሳሳቢ የሰላም እና መረጋጋት ስጋት ታክሎበት 6ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ “ነጻ፣ ፍትሀዊ እና ሰላማዊ” ላይሆን ይችላል የሚል ስጋት በበርካታ ወገኖች ዘንድ እንዲፈጠር አድርጓል። ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ይህ ስጋት ምክንያታዊ እንደሆነ ይረዳል።

    ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ “ታሪካዊም ሆኑ ወቅታዊ ችግሮቻችንን ለመፍታት ከሚረዱ የፖለቲካ መሣሪያዎች አንዱ ምርጫ ነው።” ብሎ በጽኑ ያምናል። ምርጫ ዜጎች ሉአላዊ የስልጣን ባለቤት መሆናቸውን የሚያረጋግጡበት፣ የፖለቲካ ስልጣን ከሕዝብ የሚመነጭ መሆኑ በተግባር የሚረጋገጥበት ሥርዓት ነው።

    በመሆኑም ይህን የዜግነት መብት አስቸጋሪ በሆነ የፖለቲካ አውድ ውስጥ በሚካሄደው 6ኛው ጠቅላላ ምርጫ ልንጠቀምበት የሚገባ እና በፍጹም ልናሳልፈው የማይገባ የዜግነት መብት መሆኑን ሕዝባችን እንዲገነዘብ እንወዳለን።

    የመምረጥ መብታችንን በተግባር ለማረጋገጥ በአሁኑ ሰአት በመካሄድ ላይ ባለው የመራጮች ምዝገባ ዜጎች በንቃት መሳተፍ፣ በመራጭነት በመመዝገብ የመራጭነት መታወቂያችንን መያዝ ያስፈልጋል። ፈጠነን በመመዝገብ እና ሌሎች እንዲመዘገቡ በማድረግ ታሪካዊ እና ሀገራዊ ኃላፊነታችንን ልንወታ ይገባል።

    ክቡራት እና ክቡራን፥

    ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) ለምርጫው ካደረጋቸው ዝግጅቶች አንዱ ብቁ እና ተወዳዳሪ እጩዎችን ማቅረብ ነው። በዚህም ከ600 መቶ በላይ እጩዎችን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ለክልል ምክር ቤቶች በማቅረብ ለ6ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ከፍተኛ እጩ ካቀረቡ ፓርቲዎች አንዱ ለመሆን ችሏል። ይህ የእጩዎች ቁጥር ነእፓ ከተመሠረተ ጀመሮ ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በሕዝብ ዘንድ ያተረፈውን ከፍተኛ ተቀባይነት እና የፓርቲውን አደረጃጀት በመላ ሀገራችን ለመዘርጋት የተሰራውን ከፍተኛ እና ውጤታማ ሥራ ያሳያል።

    ፓርቲያችን ለምርጫው ካደረጋቸው ዝግጅቶች ውስጥ ሌላው የፓርቲውን የምርጫ ማኒፌስቶ ማዘጋጀት ሲሆን ይህንኑ ከፍተኛ የምርጫ ሰነድ በከፍተኛ ጥንቃቄ እና ትጋት አጠናቀን በዛሬው እለት ለሕዝባቸን ይፋ እናደርጋለን። የነእፓ የምርጫ ማኒፌስቶ ፓርቲያችን በምርጫው የሚያገኘው ውጤት ተንተርሶ በቀጣይ 5 ዓመት ሊሰራቸው ያቀዳቸውን ምጣኔ ሀብታዊ፣ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ አካባቢያዊ እና የዓለማቀፍ ግንኙነት ዓላማዎች እና ግቦች በዝርዝር ይዟል።

    የነእፓ የምርጫ ማኒፌስቶ ሲያዘጋጅ ብሔራዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ሰነዶችን፣ ግቦችን እና ስትራቴጂዎችን በሚገባ ለመከለስ ሞክሯል። በመሆኑም በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የሀገራችን ማኅበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ እድገት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተቀመጡ ግቦች ጋር የተናበበ እንዲሆን ተደርጓል። የአፍሪካ እና ዓለም አቀፍ የፖለቲካ እና ኢኮኖሚያዊ የለውጥ እመርታ ታሳቢ የተደረገ ሲሆን ከፍተኛ፣ የተረጋጋ እና አካታች የኢኮኖሚ እድገት እውን ማድረግን ያለመ ነው።

    ማኒፊስቶው ሲዘጋጅ የሰው ኃይል/ሀብት ልማት፣ አህጉራዊ ተወዳዳሪነት፣ ፈጣን የመረጃና የተግባቦት ቴክኖሎጂ እድገት፣ የአካባቢ ጥበቃ እና ዘላቂ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም ከግንዛቤ ውስጥ ገብተዋል። የመንግሥት እና የግል ባለሀብቶች የተቀናጀ ተሳትፎ ይበልጥ በማጠናከር መዋቅራዊ ለውጥ ማረጋገጥ እና ከፍ ወዳለ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ የእድገት ደረጃ ሽግግር ማካሄድ፣ የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ማሻሻል፣ የሀገራችንን ሰላም እና መረጋጋት ማስጠበቅ፣ የዜጎችን ሞት እና መፈናቀል ማስቆም የማኔፌስቶው ቁልፍ ጉዳዮች ናቸው።

    በውጭ ግንኙነታችን ኢትዮጵያ በአካባቢ እና አህጉራዊ ጉዳዮች ያላትን ቦታ እና ተሰሚነት ከፍ ማድረግ፣ በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ደህነነት፣ ከጎረቤት ሀገሮች እንዲሁም ከሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች ሕዝቦች እና መንግሥታት ጋር በሰላም እና በጋራ ጥቅሞች ላይ በትብብር መሥራት የማኒፊስቶው ወሳኝ የትኩረት አቅጣጫዎች ተደርገው ተወስደዋል።

    ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ ምርጫ አሸንፎ ሀገር የማስተዳደር ኃላፊነት ከተረከበ ማኒፌስቶውን ለመፈጸም የሚረዱ ዓመታዊ እቅዶች እና ዝርዝር የአፈጻጸም ስትራቴጂዎች የሚዘጋጁ ሲሆን ጠንካራ የቁጥጥር እና ክትትል ሥርዓት ይዘረጋል።

    ክቡራት እና ክቡራን፥

    6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ካለፉት ስህተቶች የጸዳ እንዲሆን ከምርጫ በፊት፣ በምርጫ ወቅት እና ድህረ-ምርጫ ነጻ፣ ፍትሀዊ እና ሰላማዊ እንዲሆን መላ የሀገራችን ሕዝቦች በምርጫው ሂደት በንቃት በመሳተፍ የዜግነት ግዴታችንን ልንወጣ ይገባል። ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ 6ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ ሰላማዊ፣ ሂደቱ እና ውጤቱ በመራጩ ሕዝብ፣ በተፎካካሪ ፓርቲዎች እና በታዛቢዎች ተቀባይነት ያለው እንዲሆን አቅሙ የሚፈቅደለትን ሁሉ ያደርጋል።

    መላው የፓርቲያችን አባላት እና ደጋፊዎች የፓርቲያችንን የምርጫ ስነ-ምግባር ደንብ እና አግባብነት ያላቸውን የሀገሪቱን ህጎች ጠብቀን ለምርጫው ሰላማዊነት የበኩላችንን አስተዋጾ እንድናበረክት አደራዬ ከፍ ያለ ነው።

    በመጨረሻም፥

    ይህ ማኒፌስቶ ሲዘጋጅ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ኤክስፐርቶች ተካፍለዋል። በመንግሥት እና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች፣ በአለም-ዓቀፍ ተቋማት፣ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እና በግል አማካሪነት በመሥራት ላይ የሚገኙት እኚህ ኤክስፐርቶች በየሙያ ዘርፋቸው ለማኒፌስቶው ዝግጅት መነሻ ጥናታዊ ጽሁፎችን አቅርበዋል። በመላው የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ አመራር እና አባላት ስም ላደረጉት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ምስጋና አቀርባለሁ።

    የተከበራችሁ የሀገራችን ወጣቶች፣ ሴቶች፣ አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች፣ የንግዱ ማኅበረስብ አባላት፣ ተማሪዎች፣ አካል ጉዳተኞች፣ አረጋውያን፣ ህጻናት እንዲሁም ልዩ እንክብካቤ የሚያስፈልጋችሁ ዜጎች ነእፓ ለሁላችሁም የሚሆን አማራጭ ፖሊሲዎችን እና ፕሮግራሞችን “በሚዛናዊነት” እና “አብሮ ማሸነፍ” የትግል ዘይቤ ይዞ ይቀርቧል።

    ነጻነት፣ እኩልነት እና ፍትህ በተግባር እንዲረጋገጥ፣ በታማኝነት እና በእውነተኛ የሀገር ፍቅር ስሜት መላውን የሀገራችን ሕዝቦች ለማገልገል ነእፓ ከፍተኛ ዝግጅት በማድረግ አድርጓል።

    በመሆኑም ድምጽዎን ለቅን ልቦች እና ለታማኝ እጆች ይስጡ፣ ነእፓን ይምረጡ፣ ብእርን ይምረጡ።

    “እኩልነት በተግባር”
    አመሰግናለሁ

    ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ

Viewing 15 results - 1 through 15 (of 120 total)