Search Results for 'ህወሓት'

Home Forums Search Search Results for 'ህወሓት'

Viewing 15 results - 1 through 15 (of 61 total)
  • Author
    Search Results
  • Semonegna
    Keymaster

    የግሸን ደብረ ከርቤ በዓል በሰላምና በድምቀት ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ ነው – አስተዳደሩ

    ደሴ (ኢዜአ) – የግሸን ደብረ ከርቤ የንግሥ በዓልን በሰላምና በድምቀት ለማክበር አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የደቡብ ወሎ ዞን አስተዳደር አስታወቀ።

    ኢትዮጵያ ካሏት የቱሪዝም መስህቦች መካከል በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች የሚታደሙበት ባህላዊና ሀይማኖታዊ የንግሥ በዓላት ዋነኞቹ ናቸው።

    የመስቀል/ ደመራ በዓል፣ የጥምቀት በዓል፣ እሬቻና ፍቼ ጨምበላላን የመሳሰሉት በዓላት ደግሞ አገሪቷ ለዓለም ቅርስነት በማስመዝገብ የቱርስቶችን ዓይን መማረክ የቻሉ ባህላዊና ሀይማኖታዊ በዓላት ናቸው።

    በደቡብ ወሎ ዞን አምባሰል ወረዳ በየዓመቱ መስከረም 21 የሚከበረው ግሸን ደብረ ከርቤ የንግሥ በዓልም ሰላሙን በማረጋገጥ ሀይማኖታዊና ታሪካዊ ይዘቱን ጠብቆ በማክበር እስከ ዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ ሰፊ ሥራዎች መሠራት ይገባቸዋል።።

    የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱ ሁሴን እንደገለጹት፥ በዓሉን በሰላምና በድምቀት ለማክበር ቅድመ ዝግጅቶች እየተካሄዱ ናቸው።

    በኮሮና ቫይረስ እና አሸባሪው ህወሓት በከፈተው ጦርነት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሚፈለገው መልኩ አለመከበሩን ጠቁመው ዘንድሮ በርካታ ምዕምናን በተገኙበት በልዩ ሁኔታ በድምቀት እንደሚከበር ገልጸዋል።

    በዓሉ ያለ ምንም የጸጥታ ችግርና በሰላም እንዲከበር የፀጥታ ኮሚቴ እስከ ታች ድረስ በማዋቀር እየተሠራ መሆኑን ጠቁመው የመሠረተ ልማት ሥራዎችም እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።

    የደቡብ ወሎ ዞን ባህል ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ መስፍን መኮነን በበኩላቸው በዓሉን በድምቀት በማክበር አካባቢውን የቱሪስት መዳረሻ ጭምር በማድረግ ለገቢ ምንጭነት እንዲውል እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

    ዓለም አቀፍ የቱሪዝም ቀንና የመስቀል በዓልን በግሸን ለማክበርም ቅደመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ ግማደ መስቀሉ በሚገኝበት ቦታ ሁሉም ሰው ተገኝቶ የበዓሉ ታዳሚ እንዲሆን ጥሪ አስተልፈዋል።

    “ሁሉንም በዓላት ታሳቢ ያደረገ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው” ያሉት ኃላፊው በተለይም የመንገድ፣ የውሃ፣ የመብራትና የቴሌ መሠረተ ልማቶችን የማስተካከል ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል፡፡

    በዓሉን ለማክበርም ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ምዕመንና ጎብኚዎች በቦታው በመገኘት ይሳተፋል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን የትራንስፖርት ችግር እንዳይከሰትም ከአጎራባች ዞኖችና ከተሞች ጋር እየሰሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

    የግሸን ደብረ ከርቤ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ መምህር አባ ለይኩን ወንድይፈራው በዓሉ ሀይማኖታዊ ይዘቱን ጠብቆ በሰላምና በደስታ እንዲከበር ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

    በዓሉ ከመስከረም 16 ጀምሮ እስከ መስከረም 22 በተለያዩ ሁነቶች እንደሚከበር ጠቁመው አካባቢው ፍጹም ሰላማዊ በመሆኑ በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ሁሉ የበዓሉ ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።፡

    ግሸን ደብረ ከርቤ በደቡብ ወሎ ዞን አምባሰል ወረዳ ግማደ መስቀሉ ያረፈበት ቦታ በመሆኑ በየዓመቱ መስከረም 21 በድምቀት ይከበራል፡፡

    ምንጭ፦ ኢዜአ

    የግሸን ደብረ ከርቤ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን

    Semonegna
    Keymaster

    ድርድሩ የሚደገፍ ቢሆንም በሁለቱ ፓርቲዎች መካከል የሚደረግ እንዳይሆን ጥንቃቄ ይደረግ!
    በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከእናት ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ
    እናት ፓርቲ

    በሰሜን ኢትዮጵያ የተቀሰቀሰውና ሁለት ዓመት ሊሞላው ጥቂት ወራት የቀረው ጦርነት ምን አልባት ኢትዮጵያ በታሪኳ ካጋጠሟት ጥፋቶችና ውድመቶች ሁሉ ከቀዳሚዎቹ ሊቆጠር የሚችል ነው። ሰዋዊ፣ ቁሳዊ፣ ሥነ ልቡናዊና ድፕሎማሲያዊ ጉዟችንን ለብዙ አስርት ዓመታት ወደኋላ መልሷልና! ፓርቲያችን ይህ ጦርነት ሊያመጣ የሚችለው ምስቅልቅልና ዳፋ አሳስቦት በእርቅና ሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ሽማግሌዎችን ከማፈላለግ ጀምሮ የተለያዩ ጥረቶች ሲያደርግ ቆይቷል። አሁንም ያ ውድመትና ‘ውረድ እንውረድ’ ዳግም እንዳይከሰት ጦርነቱን በድርድር ለመፍታት የታየው መነሳሳት ፓርቲያችን በደስታ የሚመለከተው ኩነት ነው። በእርግጥ ብንታደል በመጀመሪያ ችግሩ እንዳይከሰት ብንከላከለው፥ ከተከሰተም በኋላ የውጭ አካል ገብቶ በድርድር መልክ ከሚፈታ ይልቅ በሀገሬው ባህል በእርቅና ይቅርታ ቢፈታ በውደድን።

    ይህ ድርድር ብዙ ውስብስብ ጉዳዮችን ተሸክሞ የሚደረግ ነው፤፡ ስለሆነም ሂደቱ ከቅድመ ድርድር ጀምሮ ዘለቄታዊ መፍትሔ በሚያመጣ መልኩ ታቅዶ ካልተፈጸመ እና የውጭ ኃይሎችን “አላስፈላጊ” ጣልቃ ገብነት መከላከል ካልተቻለ “ጅብ ፈርቸ ዛፍ ብወጣ፣ ነብር ቆየኝ” ዓይነት መሆኑ አይቀሬ ነው። በማዕከላዊ መንግሥት በኩል ከአሁኑ የአካሄድ መጣረስ /procedural fallacy/ እየታየ ነው። አዎ፤ ችግሩን የፈጠረው የህወሓትና ብልጽግና የስልጣን ሽኩቻ ነው፤ የተዋጋውና ዳፋው የተረፈው ግን ሕዝብና መንግሥት በመሆኑ ወደአንድ ፓርቲ ለመጎተት የሚደረገው ጥረት አዋጭ እንዳልሆነ ግንዛቤ ውስጥ ሊገባ ይገባል። ወዲህም ፓርላማው ህወሓትን አሸባሪ በሚል ፈርጇል። ምንም እንኳን እንዳለመታደል ሆኖ የአንድ ፓርቲ ውቅርም ቢሆን ድርድሩን መፍቀድ፣ ከሽብርተኝነት መሰረዝ፣ የድርድር ነጥቦችን ማውጣት፣ ብቁና ወካይ ተደራዳሪዎችን መሰየም፣ ሂደቱን በየጊዜው መከታተል፣ ውጤቱንም ማጽደቅ ያለበት ፓርላማው ሆኖ ሳለ የፓርቲ ውሳኔ እንደመንግሥት ውሳኔ ተቆጥሮ ዘሎ የማለፍ አዝማሚያ አደገኛ ውጤት ያለው ነው ብለን እናምናለን። ስለሆነም ፓርቲያችን ለድርድሩ ውጤታማነት ቀጥሎ ያሉ ነጥቦችን ከግንዛቤ እንዲገቡ ያሳስባል።

    1. በፌደራል መንግሥት ከሚወከሉት በተጨማሪ የጦርነቱ ግንባር ቀደም ገፈት ቀማሽ የነበሩት የአፋር እና የአማራ ክልሎች ተወካዮች የድርድር ቡድኑ አባላት መሆን እንደሚገባቸው አጽንዖት በመስጠት እናሳስባለን። በዚህ አጋጣሚ የትግራይ ሕዝብንም ስሜት በትክክል የሚያንጸባርቁ አካላት እንዲወክሉት ጥሪያችንን እናቀርባለን።
    2. የእኛን የኢትዮጵውያንን ችግር ከእኛ የተሻለ ማንም የሚረዳው እንደማይኖር በመገንዘብ በገለልተኛ አካላት (ሲቪክ ተቋማት፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦች እና ምሁራን) አማካኝነት ተደራዳሪዎች በሚስማሙበት ቦታ እንዲካሄድ፤ ይህ ካልሆነ ድርድሩ በአፍሪካ ኅብረት አመካኝነት እንዲካሄድ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
    3. አጠቃላይ ድርድሩ እንደመንግሥት እንዲመራና ፓርላማው ሙሉ ሂደቱን እንዲመራው፤ ውጤቱም ተግባራዊ የሚሆነው በፓርላማው ሲጸድቅ ብቻ እንዲሆን፤ ተደራዳሪዎችም የአንድ ፓርቲ ተወካዮች ብቻ ሳይሆኑ በዕውቀታቸው፣ ልምዳቸው፣ በሀገራቸው ጥቅምና ሉዓላዊነት የማይደራደሩና የፓርቲ ውክልና የሌላቸው አካላት ጭምር እንዲካተቱበት አበክረን እንጠቃይለን።
    4. ለድርድሩ ስኬታማነት ከመንግሥት ጥረት ጎን ለጎን ሕዝብ፣ ፓርቲዎች፣ መገናኛ ብዙኃን አዎንታዊ አስተዋጽዖ በማድረግ በተለይ ከሁለቱም ወገን አላስፈላጊ የአደባባይና የውስጥ እንካ ስላንትያዎች እንዲቆሙ ጥሪያችንን እናስተላለፍለን።
    5. ድርድሩ ሕዝብን የሚያቀራርብ፣ ቂምና ቁርሾን የሚሽር፣ ግልጽና ጥፋተኛን በውል የሚቀጣ፣ ከሴራና እልኸኝነት የራቀ ለሕዝብ በየጊዜው ይፋ የሚደረግ እንዲሆን እንጠይቃለን።
    6. በአጠቃላይ ወደ ድርድር የምንገባው ከጦርነት ተላቀን እንደሀገር ብዙ ለማትረፍ እንጂ ለበለጠ ኪሣራ አይደለምና ሂደቱ የኢትዮጵያን አንድነትና ሉዓላዊነት በምንም መልኩ ለድርድር የማያቀርብ እንዲሆን አበክረን እናሳስባለን።

    በመጨረሻም ድርድርና እርቅ የሚወደድ ተግባር ነው። የምንደራደረው ግን ከ“ህወሓት” ጋር በመሆኑ የጸጥታ ኃይሉ ከመዘናጋት ይልቅ ከመቸውም ጊዜ በላይ በመናበብ፣ ከፍ ባለ ዝግጅት እና በተጠንቀቅ እንዲቆም አበክረን ማሳሰብ እንወዳለን።

    ፈጣሪ ሀገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ
    እናት ፓርቲ (ENAT Party)
    ሰኔ 27 ቀን 2014 ዓ.ም
    አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

    እናት ፓርቲ

    Semonegna
    Keymaster

    የአማራን ሕዝብ ሰቆቃ እያየ እንዳለየ፣ እየሰማ እንዳልሰማ…
    ጋዜጠኛ አበበ ገላው

    የአማራ ሕዝብ በደለኝ የሚል ካለ ማስረጃውን ይዞ ይቅረብ። አንድም ሰው አይገኝም። የኦሮሞም ይሁን የትግራይ፣ የአፋርም ሕዝብ ይሁን የሲዳማ፣ የጋምቤላም ይሁን የሶማሌ፣ የጉራጌም ይሁን የወላይታ ሕዝብ… ፈጽሞ ማንንም በድለው አያውቁም። የትኛውም ሕዝብ በጅምላ ግለሰቦችንም ይሁን ቡድኖችን ሊበድል ፈጽሞ አይችልም። ስለዚህም ነው በዓለማችን ላይ እጅግ አሰቃቂው ግፍ በተፈጸመበት አውሮፓ ናዚዎች ለፈጸሙት ወንጀል ተጠያቂ አድርጎ ጀርመኖችን እያደነ የሚገድልና የሚያፈናቅል ቡድን ኖሮ አያውቅም። በእኛም ሀገር ሞሶሎኒ በመርዝ ጋዝ ሳይቀር ለፈጸመው ግፍ ንጹኃን የጣሊያን ዜጎችን አሳደንም ይሁን ጨፍጭፈን አናውቅም። እንዲህ ዓይነቱን አስነዋሪ ወንጀል ብንሞክረውም ግፍ እንጂ ፍትሃዊ ሊሆን ፈጽሞ አይችልም።

    በእኛ ሀገር በክፋት ህወሓት በዋነኛነት ከፋፍሎ ለመግዛት እንዲያመቸው መዋቅርና ቅርጽ የሰጠውን ተረት በማንገብ በጥንታዊ ነገሥታትና መንግሥታት ለተፈጸሙ በደሎች መላውን የአማራ ሕዝብ በነፍጠኛነት ፈርጆ ከምንም የሌሉበትን ምሲኪን ድሆች በጅምላ መግደል፣ ማሳደድ፣ ማፈናቀል፣ አፍኖ መውሰድ፣ አካላዊና ስለልቦናዊ ጥቃት መሰንዘር የተለመደ ክስተት ከሆነ አርባ አመታት ተቆጥረዋል። አብዛኛው የአማራ ተወላጅ ሀገሩ እንዳይፈርስ፣ ሕዝብ ለበቀል እንዳይነሳ እና ማለቂያ የሌለው እልቂትና ውድመት እንዳይደርስ በሚል የአስተዋይነት መንፈስና ባህል የሆዱን በሆዱ ይዞ በትዕግስት ህመሙን እና ሀዘኑን አፍኖ በኢትዮጵያዊነት ጨዋነት ከየትኛውም ኢትዮጵያዊ ወገኑ ጋር ተቻችሎና ተከባብሮ ለመኖር የሚቻለውን ሁሉ አድርጓል።

    ይሁንና አሳዛኙ ሃቅ የሕዝቡን ትዕግስት እንደ ፍርሃት የቆጠሩ እኩይ ኃይሎች የአማራን ሕዝብ በጅምላ ዘውትር ከማሸማቀቅ አልፈው የጅምላ ጭፍጨፋ፣ ግፍና ማፈናቀል ያለማቋረጥ እየፈጸሙበት ይገኛሉ። የሕዝቡን ሰላምና ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነትን የተረከበው “የለውጥ” ኃይልና መንግሥትም ከእነ መለስ ዜናዊ ባልተለየ ሁኔታ የአማራን ሕዝብ ሰቆቃ እያየ እንዳለየ፣ እየሰማ እንዳልሰማ… ሕዝቡ በገፍ እያለቀና እየተሰቃየ ባለስልጣናቱ ሌላው ቀርቶ የረባ የሀዘን መግለጫ፣ ማጽናኛም ይሁን የአንዲት ሰከንድ የህሊና ጸሎት ነፍገውታል።

    የዚህ ታጋሽ ሕዝብ ትግስት አልቋል። መንግሥት የሕዝብን ደህንነትና ሰላም በአግባቡ መጠበቅ ካልቻለና የዜጎቹ የጅምላ ሞት፣ ሰቆቃ መፈናቀል፣ የደም ጎርፍና እንባ ግድ የማይለው ከሆነ ሕዝቡ ሰላሙን፣ ደህነንቱና ዜግነታዊ መብቱን ሙሉ በሙሉ የሚያከብርለትና እኩልነትና አንድነትን የሚያረጋግጥለት መንግሥት እንዲመጣ አምርሮ ከመታገል ውጭ አማራጭ እንደማይኖረው ሊታወቅ ይገባል።

    ጋዜጠኛ አበበ ገላው (facebook.com/agellaw)

    [caption id="attachment_41752" align="aligncenter" width="600"] በጀርመን የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ሰላማዊ ሰልፍ ላይ[/caption]

    Anonymous
    Inactive

    የአማራ ብልፅግና ፓርቲ መግለጫ

    አሸባሪው ህወሓት (ትህነግ) የአማራና የአፋር ክልል መሬቶች መውረሩንና በሀገር ላይ እያደረሰ ያለውን ሁለንተናዊ ጥፋትና ሽብር ተከትሎ፥ የአማራ ብልፅግና ፓርቲ የሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ይህንን ይመስላል።

    እምቢ ለባርነት፤ ክተት ለነጻነት!!
    የአማራ ብልፅግና ፓርቲ መግለጫ

    በሁሉም የክልላችን ዞኖች፣ በበርካታ ከተሞች እና ወረዳዎች የህልውና ዘመቻውን ተከትሎ እየተካሄዱ ያሉ መሠረታዊ የውትድርና ስልጠናዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል። ሕዝባችን ህልውናውንና ኢትዮጵያን በደምና በአጥንቱ እንደሚጠብቅ የአባቶቹን ቃል-ኪዳን በማደስ ላይ ይገኛል። በዚህም የወገን ጦር ከፍተኛ መነቃቃት ሲያሳይ በአንጻሩ በቅርብም ሆነ በርቀት ያለው ጠላት በፍርሃት እየተናጠ ይገኛል። አሁን መላ የኢትዮጵያ ብሔር ብሄረሰቦች ለህልውናቸውና ለሉአላዊነታቸው ሲሉ ወታደር መሆን መርጠዋል። የዘመቻው ድጋፍ ይህን ሀቅ ያስረግጣል። በታሪክ ስናየው የኖረው እውነታ ኢትዮጵያ ሊቀብሯት የተነሱትን የውጭና የሀገር ውስጥ ፋሽስቶች ሁሉ በመቅበር ስታሳፍራቸው ኑሯለች።

    አሸባሪው ትህነግ፣ ከታሪክ የመማር አንዳች ፍላጎት የለውም። በለመደ የባንዳ ታሪኩ ከጀርባው የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶችን ተማምኖ ወክየዋለሁ የሚለውን ሕዝብ ጥይት ማብረጃ ማድረጉን ተያይዞታል። ለባዕድ ሥርዓት የመታመን ልማድ ያለውና የኢትዮጵያ ካንሰር የሆነው ትህነግ አማራን ሊያጠፋ፤ ኢትዮጵያን ሊበትን ቆርጦ መነሳቱን ተከትሎ በአጸፋው የኢትዮጵያ ብሔር ብሄረሰቦችን በቁጭት ስሜት ከዳር እስከ ዳር አነቃንቋል።

    በክልላችን የታወጀውን የክተት ጥሪ ተከትሎ የታየው አስደማሚ ሕዝባዊ ንቅናቄም ጥሪውን ተቀብሎ የመፋለም ጉዳይ “አማራን እና ኢትዮጵያን የመታደግ ጉዳይ ነው” በሚል እምነት ስለመሆኑ በተግባር እየተረጋገጠ ነው። በሁሉም የንቃናቄ መድረኮች የተሰማው ሕዝባዊ ድምጽ አንድና አንድ ነው። “ጦርነቱ የህልውናና ሀገር ማዳን ዘመቻ ነው” ፤ “በአሸባሪው ትህነግ መቃብር ላይ በጠንካራ ወንድማማችንት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን እንገነባለን!” የሚል ነው።

    ምንም እንኳ አሸባሪው ትህነግ ዕድሜው ከ12 ዓመት ህፃን እስከ 70 ዓመት አዛውንት ሴት፣ ወንድ ሳይለይ ኢትዮጵያን ለመውጋት ያሰለፈና የተነሳ ቢሆንም፥ የዚህ ጦርነት ተደማሪ ግብ የትህነግ አስተሳሰብ ቁራኛ የሆነውን የትግራይ ሕዝብን ነጻ ማውጣትን ይጨምራል። በተለይም ኑሮውን በደሳሳ ጎጆ እየኖረ በድንጋይ ስር አፈር እየገፋ የሚኖረው ጭቁኑ የትግራይ አርሶ አደር፥ አሸባሪውን ትህነግ “ልጆቻችንን የት ጣላችኋቸው ?” ብሎ መጠየቅ የሚጀምርበት ጊዜ ሩቅ አይደለም።

    ጦርነት በባህሪው ከሚፈጥረው የኢኮኖሚ ድቀት በላይ ማኅበዊ ቀውሱ ተሻጋሪ ዕዳ እንደሚያመጣ ከትግራይ አርሶ አደሮች በላይ እውነታውን የሚረዳ የለም። ይህ ጦርነት በግብ የኢትዮጵያ ካንሰር የሆነውን ትህነግ ወደመቃብር ማውረድ ቢሆንም በውጤቱ የወላድ መካን የሆነችው የትግራይ እናትም ነጻ ትወጣበታለች። የኢትዮጵያ የግዛት አንድነት በመንደር ወንበዴዎችና ግልገል ሽብርተኞች አደጋ ላይ እንዲወድቅ የኢትዮጵያ ብሔር ብሄረሰቦች እንደማይፈቅዱ በተግባር እያሳዩ ይገኛል።

    የዚሁ ተግባራዊ ዐቢይ ምዕራፍ አካል የሆነው የክልላችን የህልውና ዘመቻ ዝግጅትና አፈጻጸም በስኬት መጓዙን ቀጥሏል። የክተት ጥሪውና የንቅናቄ መድረኩ ወደመሬት ስራ ወርዷል። የወቅቱ ተልዕኳችንም ከአደባባይ ንቅናቄ ወደግንባር መሰለፍ ሁኗል። የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የልዩ ኃይል ምልመላዎች በመካሄድ ላይ ናቸው። አሁንም የነገ ባለአራት ኮከብ ጀኔራሎች የሚገኙት ዛሬ መከላከያ ሠራዊቱን በመቀላቀል ላይ ከሚገኙት ወጣቶች ነውና ምዝገባው ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል። በተመሳሳይ የአማራ ልዩ ኃይል በሰው ኃይል፣ በአደረጃጃት እና በወታደራዊ ዲሲፕሊን የማጠናከሩ እና የማዘመኑ ተልዕኮ የክተት ጥሪውን በተቀበሉ ጀኔራል መኮንኖቻችን በመካሄድ ላይ ነው። ከወታደራዊ መረጃ አኳያ ቁጥሩን በይፋ ለመግለጽ ባይቻልም የልዩ ኃይላችን፣ የሚሊሻችን በጥቅሉ የአማራ ሕዝባዊ ሠራዊታችን አቅም በፍጠነት እያደገ ነው። በተመሳሳይ ተልዕኮ በሁሉም ማዕከላት ተጠባባቂ ኃይል የማፍራት ስራው የህልውና አጀንዳው አካል ሁኗል።

    ይህም ሁኖ ሰብዓዊነቱን ክዶ ለመጣው ጠላት ከዚህም በላይ ዝግጅት ሊካሄድ ይገባል። ከአንድ ወር ወዲህ ያለውን የጠላት ዝግጅት ብንመለከት፡- በትግራይ በሁሉም ወረዳወች በብዙ ሽህዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላ (conscription) ኮታ ተጥሎበታል። ይህ የፌዴራል መንግሥቱ የተናጠል የተኩስ አቁም ካወጀ በኋላ ትህነግ በአማራና አፋር ክልሎች ላይ የከፈተውን ወረራ ተከትሎ የተጣለ ግዳጅ ነው። ከዚህ ግዳጅ በፊት የነበረው ሰልጥኖ የታጠቀው ኃይል አብዛኛው ወደመቃብር የወረደ ሲሆን፤ ይህንኑ የሰው ኃይል ክፍተቱን ለመሙላት በዚህ ወር ብቻ በብዙ ሺህዎች የሚገመት የሳምንታት ስልጠና የወሰዱ ታዳጊዎችን ለወረራ አሰልፏል። ይህ ኃይል ከኢትዮጵያዊነት እሴት የራቀ በመሆኑ እንደአንበጣ በየደረሰበት ያገኘውን የሚወር፣ የሚዘርፍ፣ ሴቶችንና እናቶችን የሚደፍር፣ መሠረተ ልማቶችንም የሚያወድም በጥቅሉ ሰብዓዊነቱን የካደ፤ በአማራና በኢትዮጵያ ጥላቻ ያበደ በመሆኑ በፍጥነት ሊደመመስ ይገባል። እረፍትም ጊዜም ሊሰጠው አይገባም።

    ስለሆነም የህልውና ዘመቻው በጊዜ የለንም መንፈስ ተጠናክሮ ይቀጥላል። መሽቶ በነጋ ቁጥር አሸባሪው ኃይል ወደመቀመቅ የሚወርድበት ጉድጓድ ጥልቀት ይጨምራል። ጠላት በተግባርም ሆነ በአስተሳሰብ ሊቀበር ይገባል።

    ይህ የሽብር ቡድን በተመሳሳይ ሰዓት ከአማራም፣ ከአፋርም እንዲሁም ከጎረቤት ኤርትራ ጋር በአንድ ጊዜ ወደግጭት መግባት ያስፈለገው ግጭት ብቸኛ የዕድሜ ማስቀጠያው እንደሆነ በማመኑ ነው። ባለፉት ሠላሳ ዓመታት በተግባሩም ሆነ በአስተሳሰቡ ለኢትዮጵያ ካንሰር ስለመሆኑ በበቂ ሀገራዊ ኪሳራ ተገምግሟልና አሁን ላይ ለወረራ የተሰለፈባቸው የአማራና የአፋር መሬቶች የአሸባሪው ትሕነግ መቀበሪያ መሆናቸው ይቀጥላል።

    እምቢ ለባርነት፤ ክተት ለነጻነት!!
    የአማራ ብልፅግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት
    ሐምሌ 30 ቀን፥ 2013 ዓ.ም.
    ባህር ዳር፥ ኢትዮጵያ

    የአማራ ብልፅግና ፓርቲ መግለጫ

    Anonymous
    Inactive

    በሀገር አንድነት እና ሰላም ላይ የተደቀነውን አደጋ የመመከት ኃላፊነት በዋነኛነት የፌደራል መንግሥቱ ነው!
    ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የተሰጠ መግለጫ

    መንግሥት በትግራይ ያለው ግጭት ቆሞ ለሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረስ የተሻለ ሁኔታ ለመፍጠር እና ሌሎች ምክንያቶችን ጠቅሶ የተናጥል ተኩስ አቁም ማወጁን ተከትሎ ሰኔ 26 ቀን 2013 ዓ.ም የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ባወጣው የ‘ቢሆንስ’ ትንተና ሊሆን ይችላል ብለን ያስቀመጥነው ሁለተኛው ቢሆንስ (scenario) መንግሥት በትግራይ ክልል የተናጠል ተኩስ አቁም ካወጀ በኋላ የትግራይ አማጺዎች ግጭቱን ለማስፋት የሚያደርጉት ሙከራ ቀጥሎ ግልፅ አሸናፊ የማይኖርበት ሁኔታ ይከሰታል የሚል ነበር። ይህም ከቀጠለ በክልሉ ሕግና ሥርዓትን ማስከበር አዳጋች መሆኑ የሚፈጥረውን አጋጣሚ በመጠቀም ዘረፋዎች ሊበራከቱ እንደሚችሉ፣ የዕለት እርዳታ የሚያስፈልጋቸው የክልሉ ነዋሪዎች በሚፈለገው ደረጃ እርዳታ ሳያገኙ ቀርተው ለከፍተኛ አደጋ ሊጋለጡ እንደሚችሉ፣ መሰረታዊ ለኑሮ የሚያስፈልጉ አገልግሎቶች እና ግብዓቶች (የውሃ፣ የመብራት፣ ህክምና) ማግኘት የማይቻልበት ሁኔታ ሊፈጠር የሚችልበት ዕድል ከፍተኛ በመሆኑ የክልሉ ሕዝብ ለከፍተኛ ችግር የሚጋለጥበት ሁኔታ ሊበራክት እና ለረጅም ጊዜ ምንም ዓይነት አስተዳደራዊ አገልግሎት ሊያገኝ የማይችልበት ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል እና የዚህ ዓይነት የማያቋርጥ ግጭት ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ብዙ ችግሮችን ስቦ በማምጣት (ኢንቬስትመንት ይቀንሳል፤ ቱሪዝም ይቀንሳል፤ በዚህም የሥራ አጥ ቁጥር ይጨምራል) በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎችም አለመረጋጋትን ሊያስከትል ይችላል የሚል ትንተና አስቀምጠን ነበር። በትንተናችን ውስጥ ይህ ቢሆንስ (scenario) የመሆን ዕድሉ ከሌሎቹ የበለጠ መሆኑን ጠቅሰን በክልሉና ባጠቃላይ በሀገራችን ከብሔር ፖለቲካ ጋር ተያይዞ የመጣውን አደጋ በዘላቂነት የማይፈታ፣ ሀገሪቱን ቀስ እያለ ውስጧን እንደሚበላ በሽታ ከመግደሉ በፊት መፍትሄ የሚፈልግ እንደሆነ ገልፀን ነበር። በተጨማሪም በዚህ ሁኔታ ውስጥ መረጋጋትን ማስፈን ስለማይቻል የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ወደ ከፍተኛ ግጭት ማምራቱ እንደማይቀር በትንታኔያችን ውስጥ አስቀምጠን ነበር።

    የፌደራል መንግሥቱ የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት በይዞታው ስር የነበሩ ቦታዎችን ለቆ ከወጣ በኋላ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ያስተዋልነው እንቅስቃሴ በቢሆንስ (scenario) ትንተናችን ውስጥ ከሁሉም የተሻለ የመከሰት ዕድል አለው ብለን ያስቀመጥነው ሁለተኛው ቢሆንስ (scenario) እውን እየሆነ እንደሆነ የሚያመላክት ነው።

    በእርግጥ ከላይ በጠቀስነው ትንተናችን ውስጥ ህወሓት የሚያደርሳቸውን ትንኮሳዎች በኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት እየተመከቱ እና እየከሸፉ ሊሄዱ ይችላሉ የሚል ግምታችንን ብናስቀምጥም በተግባር ያየነው ግን የፌደራል መንግሥት ህወሓት ግጭቱን ለመቀጠል የወሰዳቸውን እርምጃዎች በግንባር ቀደምነት አመራር እየሰጠ ለማክሸፍ ከመሞከር ይልቅ ግጭቱን በክልሎች መካከል ያለ ግጭት እስኪመስል የወሰደው ግልፅ ያልሆነ አቋም እጅግ አስደንጋጭ ሆኖ አግኝተነዋል።

    ከዚህም በላይ ግጭቱን በተመለከተ በፌደራል መንግሥቱ በኩል የሚወሰዱ እርምጃዎች የተጣደፉ እና በቅጡ ያልታሰበባቸው መምሰላቸው በአጭር ጊዜ ከህወሓት የተደቀነውን አደጋ በማንኛውም መንገድ ከማክሸፍ ባለፈ እርምጃዎቹ ለሀገራችን ሰላም እና አንድነት በዘላቂነት የሚኖራቸውን አንድምታን ያልገመገሙ ስለመሆናቸው አመላካች ሆነው አግኝተናቸዋል።

    መንግሥት የሚወስዳቸው እርምጃዎችን በተመለከተ ጊዜውን የጠበቀ እና ትክክለኛ መረጃ ለሕዝብ ባለማድረሱ በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ መደናገጥ ከመፍጠሩም ባለፈ በመንግሥት ላይ ያለው እምነት እንዲሸረሸር ምክንያት ሆኗል። በተጨማሪም ህወሓት ያደረሳቸውን ወንጀሎች እና የሚፈጽማቸውን ኢሰብዓዊ ድርጊቶች ከተራ ክስ ባለፈ በተጨባጭ ማስረጃዎች አስደግፎ ለዜጎች እና ለዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ እንዲደርስ ማድረግ ላይ ከፍተኛ ክፍተት እየተስተዋለ ይገኛል። እነዚህ ክፍተቶች በጊዜ መፍትሄ ካልተበጀላቸው ችግሩን የበለጠ እያባባሱት እንደሚሄዱ እናምናለን።

    መንግሥት በተጨባጭ ማስረጃዎች ላይ ተመስርቶ ለህወሓት የሚደረግ ማንኛውንም ዓይነት ድጋፍ ለማስቆም እና ተጠያቂነትን ለማስፈን ያለበትን ኃላፊነት ሙሉ በሙሉ የምንደግፍ ቢሆንም በሌሎች የሀገራችን አካባቢዎች ህወሓትን ትደግፋላችሁ በሚል ምክንያት የሚወሰዱ እርምጃዎች ማስረጃ ላይ የተመሰረቱ ከመሆን ይልቅ እንዲሁ በጅምላ የሚወሰዱ መሆናቸው የዜጎችን ሰብዓዊ መብት የሚጋፉ እና በትግራይ ያለውን ችግር የበለጠ የሚያወሳስቡ ድርጊቶች ናቸው። ለአብነት በአዲስ አበባ ከተማ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ብቻ በተመሳሳይ ወቅት ቢያንስ 60 የንግድ ተቋማት/ሱቆች ከግጭቱ ጋር በተያያዙ ምክንያቶች ታሽገው ላለፉት ሁለት ሳምንታት ተዘግተው ቆይተዋል። ከግጭቱ ጋር በተያያዘ ሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚደርስ እንግልት፣ ከሕግ አግባብ ውጪ የሆነ እስር እና ጥቃት በአፋጣኝ መቆም እንደሚገባው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ሐምሌ 8 ቀን 2013 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ መጠየቁ ይታወሳል።

    ከላይ የተጠቀሱትን መሰረት በማድረግ የሚከተሉት ምክረ ሀሳቦች ተግባራዊ እንዲደረጉ እንጠይቃለን፥

    1. በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች የሚገኙ የፀጥታ አስከባሪዎች ህወሓት የደቀነው አደጋን ለማክሸፍ እያደረጉ ያሉትን መረባረብ በከፍተኛ አክብሮት እናደንቃለን። ህወሓት የፌደራል መንግሥቱን በበላይነት ይቆጣጠር በነበረበት ጊዜ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊያን ላይ በሙሉ ግፍ ሲፈጽም እንደነበረ ሁሉ አሁንም የደቀነው አደጋ በሀገር አንድነት እና ሰላም ላይ እንጂ በአንድ ወይንም በጥቂት ክልሎች ላይ ብቻ ያነጣጠረ እንዳልሆነ በመረዳት አደጋውን ለመከላከል የሚወሰደው እርምጃ አንድ ወጥ የዕዝ ሰንሰለት ኖሮት በፌደራል መንግሥት እና በኢፌደሪ መከላከያ ሠራዊት አመራር ሰጪነት ብቻ እንዲወሰድ፤
    2. በትግራይ ክልል ያለውን ችግር አሁን ከፊታችን ህወሓት ከደቀነው አደጋ እንፃር ብቻ በማየት ህወሓትን ማሸነፍን ብቻ ዓላማ ያደረገ የአጭር ጊዜ ስልት ይዞ ከመንቀሳቀስ ባለፈ በዘላቂነት ክልሉ ወደተረጋጋ ሰላም እና ዜጎች ወደ መደበኛ ሕይወታቸው ሊመለሱ የሚችሉበት እንዲሁም ግጭቱ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ተቋጭቶ የሀገር ህልውና እና አንድነትን በዘላቂነት ማረጋገጥ የሚቻልበት ስልት የአካባቢውን ተወላጆች በማሳተፍ እንዲነደፍ እና ተግባራዊ እንዲደረግ፤
    3. አሁን ያለው ግጭት ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲያበቃ እና ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ በትግራይ ክልልም ሆነ በሌሎች የሀገራችን አካባቢዎች የምትገኙ የሀገር ሽማግሌዎች እና ሌሎች ልሂቃን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የምታስፈልጉበት ወቅት ላይ መሆናችሁን ተረድታችሁ የሚጠበቅባችሁን ኃላፊነት እንድትወጡ፤
    4. የሰብዓዊ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ድጋፍ እንዲደርሳቸው የሚደረገው ጥረት አሁን ከምን ጊዜውም በላይ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እና መንግሥት የሰብዓዊ እርዳታ በክልሉ ለሚኖሩ ዜጎች እንዲዳረስ የሚያደርገውን ጥረት በግልፅ እንዲያሳውቅ፤ እንዲሁም በዚህ ተግባር የሚሳተፉ የሰብዓዊ ድርጅቶች በግልፅነት እንዲንቀሳቀሱ ተገቢው ክትትል እንዲደረግ፤
    5. የተለመዱ መንግሥትን የሚያሞግሱ የፕሮፖጋንዳ ሥራዎችን እየደጋገሙ ሕዝብን ከማሰልቸት ይልቅ መንግሥት የወሰዳቸውን እርምጃዎች በተመለከተ ትክክለኛ እና ወቅታዊ መረጃ ለሕዝብ እንዲደርስ እንዲደረግ እና ህወሓት የሚፈፅማቸውን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች እና ታዳጊዎችን በወታደርነት መመልመል እና በጦርነት ማሳተፍን የመሳሰሉ ወንጀሎችን በተገቢው ፍጥነት በተጨባጭ ማስረጃዎች እያስደገፉ ይፋ የማድረግ ሥራ ተገቢውን ትኩረት ተሰጥቶት እንዲሠራ፤
    6. ዜጎች ለህወሓት የሚደረግ ማንኛውም የሞራልም ሆነ ቁሳዊ ድጋፍ በሕዝብ ሠላም፣ በሀገር ደህንነት እና ሕይወቱን ለመሰዋዕትነት አዘጋጅቶ በተሰለፈው የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ላይ የሚደረግ ክህደት መሆኑን በመረዳት ከተመሳሳይ ድርጊቶች እንዲታቀቡ፤
    7. ህወሓትን ደግፋቹኻል በሚል በጅምላ የሚወሰዱ እርምጃዎች ባስቸኳይ እንዲቆሙ እና እስካሁንም በዚህ መልኩ የተወሰዱ እርምጃዎች አፋጣኝ ማጣራት ተደርጎ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ እንዲሁም አሁን ያለውን ሁኔታ እንደ አጋጣሚ በመጠቀም የግል ጥቅም ለማግኘት ዜጎች ላይ እንግልት የሚፈፅሙ የመንግሥት እና የፀጥታ ሠራተኞች ላይ አስፈላጊው ማጣራት በአስቸኳይ ተደርጎ የማያዳግም ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ፤

    በመጨረሻም የሀገራችን ሰላም እና አንድነት በዘላቂነት ተረጋግጦ የሁሉም ዜጎች መብት እኩል የሚከበርበት እና እኩል ዕድል የሚሰጥበት እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት ሁላችንም የምንችለውን ሁሉ የምናዋጣበት አሳሳቢ ወቅት ላይ እንዳለን እያስታወስን ሁላችንም ኃላፊነታችንን ከምር ወስደን እንድንወጣ እናሳስባለን።

    ሐምሌ 10 ቀን 2013 ዓ.ም.
    አዲስ አበባ፥ ኢትዮጵያ

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ

    የፌደራል መንግሥቱ

    Anonymous
    Inactive

    ይድረስ ለትግራይ ወገኖቼ!
    በአቶ ክርስቲያን ታደለ ጸጋዬ

    የትግራይ ሕዝብ ከባለጌ ልጆቹ በላይ ሀገሩን የሚመርጥበት ጊዜ ደርሷል። በተለይም የትግራይ እናቶች እና አባቶች በራሳቸው ልጆች እኩይ ስምሪት ቀደምቶቻቸው ለአንድነቷ ሰማዕትነትን የተቀበሉላት ኢትዮጵያችን ክብሯ እንዲጎድፍ በዝምታ መተባበራቸውን ይበቃል ለማለት ትክክለኛው ወቅት አሁን መሆኑን ልብ ሊሉ ይገባል።

    የዘመን ተጋሪዬ ለሆናችሁ የትግራይ ወጣቶችም “ጅብም ብሆን የወንዝህ ጅብ ስለሆንሁ፤ ልበላህ መብት አለኝ” የሚሉ ሀገር አጥፊዎችን በመተው ከሀገራችን ኢትዮጵያ እና ወንድሞቻችሁ ጎን እንድትቆሙ ወንድማዊ ጥሪዬን አቀርብላችኋለሁ።

    የሀይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ጨዋው የትግራይ ሕዝብ በሀገር አፍራሽ፣ ዘር አጥፊና ዘራፊ ብኩኖች በኩል ዘላቂ መብቶቹ፣ ጥቅሞቹና ፍላጎቶቹ እንደማይከበሩለት አውቃችሁ፤ ሁለንተናው ከኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ጋር የተሸመነውን የትግራይ ሕዝብ ታሪክ፣ ክብርና የወደፊት በጎ ተስፋ በሚመጥን ስምሪት እንድትገኙ ዝቅ ብዬ እለምናችኋለሁ።

    ታላቁ የትግራይ ሕዝብ በሌባ አይወከልም! ከዘፍጥረት ጀምሮ እስካሁን ድረስም እናት ኢትዮጵያም ሆነች ወንድሙ የአማራ ሕዝብ ለትግራይ ሕዝብ የክብሩ ምንጭ የደኅንነቱ ደጀኖች እንጂ የስጋቱ ምንጮቹኘች ሆነው አያውቁም፤ አይሆኑምም። እንዴት ሀገር ገንቢው ትግራይ በሀገር አፍራሽ ይወከላል?

    ትግራይ የምታሸንፈው ኢትዮጵያ ስታሸንፍ ብቻ ነው፤ ትግራይ አንገት ደፍታ ኢትዮጵያ አትቃናም። በትግራይ ለቅሶ ፈገግታው የሚደምቅ አንድም ኢትዮጵያዊ አይኖርምም። ሌባና ዘራፊ፤ ባንዳና ሀገር አጥፊ ግን ከየትም ይሁን የትም የጋራ ጠላታችን ነውና በጋራ ልንደመስሰው ይገባናል። በባንዳ ሞት ደረት የሚደቃና ፊት የሚነጭ ሊኖር አይገባም።

    እናም ለተከበራችሁ የትግራይ አባቶቼና እናቶቼ፣ ወንድሞቼና እህቶቼ፥ ስለደማቁ የትናንት ትናንታችን ብቻ ሳይሆን ስለብሩህ ነጋችንም ብላችሁ ለኢትዮጵያችን ኅልውና እንዲሁም ለሕዝባችን ፍትሕ፣ እኩልነትና ነፃነት መረጋገጥ በአንድነት እንድንቆም ስል ጥሪዬን ደግሜ ላቀርብላችሁ እወዳለሁ።

    ሁሉም ችግሮች ከጋራ አቅማችን በታች ናቸው። ስንደማመጥ፣ ስንከባበርና ስንተማመን ከባዱ ቀላል ይሆናል። ኢትዮጵያ ስታሸንፍ ሁላችንም እናሸንፋለን!

    አቶ ክርስቲያን ታደለ ጸጋዬ

    አቶ ክርስቲያን ታደለ ጸጋዬ በፌደራል የጤና ሚኒስቴር፥ የማኅበረሰብ ጤና ኤክስፐርት (public health expert) ሲሆኑ፤ በፖለቲካ እንቅስቃሴአቸው ደግሞ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ናቸው። እርሳቸውን በፌስቡክ ገጻቸው ወይንም በትዊተር ሃንድላቸው ሊያገኟቸው ይችላሉ።

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forums) ላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።

    አቶ ክርስቲያን ታደለ

    Anonymous
    Inactive

    የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታ ላይ የሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ

    የኦሮሚያ ክልል ሕዝብና መንግሥት ኢትዮጵያን በመገንባት ዉስጥ የሚመጥነዉን አስተዋፅኦ ሲያበረክት ቆይቷል። የሀገርና የሕዝብ ሉአላዊነትና ነፃነትን ለማስከበር በሚከፈለዉ መስዋዕትነት ላይ እራሱን ቆጥቦ አያውቅም። በዉጪ ወረራና በታሪክ አጋጣሚ የባንዳነትን ተግባር ሲፈጽሙ በነበሩት ኃይሎች ላይ በየታሪክ ምዕራፉ ራሱን ሰጥቶ ኢትዮጵያን የገጠሟትን ችግሮች ለማክሸፍ መስዋዕትነትን ከፍሏል። እንደሀገር ስናስመዘግብ በቆየናቸው ድሎች ዉስጥ ተወራራሽ ታሪክ አስመዝግቧል።

    ዛሬም እንደ ትናንቱ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የክልሉን ሕዝብ በማቀናጀት በወንድሞቻችን አብሮነት በኢትዮጵያ ላይ የሚቃጣውን የውስጥና የውጪ ትንኮሳ ለማክሸፍ ዝግጁነቱን ይገልፃል።

    የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የፌደራል መንግሥቱ የወሰደውን የአንድ ወገን ተኩስ የማቆም እርምጃ ለሕዝብ ጥሩ የጥሞና ጊዜ የፈጠረ መሆኑን አምኖ ሲደግፍ ቆይቷል። ይሁን እንጂ ከአፈጣጠሩ የተጣመመው ህወሓት ለሕዝብ ጥቅም ተብሎ ለተደረገው ጥሪ ቦታ እንደሌለዉ በግልፅ አሳይቷል። ዛሬም እንደ ትናንቱ በአሮጌ የፖለቲካ እይታ ተሞልቶ የጦርነት ነጋሪት እየጎሰመ ይገኛል።

    የህወሓት የፖለቲካ ፅንሰ-ሐሳብ ሕዝብን እንደ ጠላት በመፈረጅ ላይ ያተኮረ ነው። የግጭት መነሻ የአንድነት ፀርና ለሀገራዊ ብሔርተኝነት መውደቅ ምክንያት ሆኗል።

    የህወሓት ፀረ አንድነት ፈንጂ በየቀኑ እየፈነዳ ለዜጎች ሞትና ስቃይ ምክንያት በመሆን ዓመታትን አስቆጥሯል። የድህነትና የኋላ ቀርነትን እሽክርክሪት ዘመን አራዝሞብናል። ለእድገታችንና የብልፅግና ጉዞ እንቅፋት በመሆን እንድንሸማቀቅ አርጎናል። በዚህ ሁኔታ ዉስጥ ሀገርና ሕዝብ በቀዳሚነት እየተጎዱ ነው።

    አሸባሪው ህወሓት ‘እታገልላቸዋለሁ’ ብሎ የሚናገረውና በስማቸው እየኖረ ያለውን የትግራዋይ ሕዝብን ጨምሮ አስቦላቸው ወይም ተቆርቁሮላቸው አያውቅም። ይህ ቡድን ትናንት የሓውዜን ሕዝብ በሚገበያይበት ቦታ ላይ ቦምብ በማዝነብ የጅምላ ጭፍጨፋ ሲፈፅም ለፕሮፖጋንዳ ግብአትነት እንጂ ለሉአላዊነት ትግል አልነበረም። ሕዝብን በመጨፍጨፍ ሕዝብን ነፃ ማውጣት በየትኛውም መስፈርት የሚታረቅ አስተሳሰብ አይደለም።

    ዛሬም ቢሆን በተባበሩት መንግሥታት የወጣውን የሕፃናት መብት ድንጋጌ በመጣስ ጨቅላ ሕፃናትን ለጦርነት ከፊት አሰልፈው በመማገድ ላይ ይገኛል። አዛውንቶችን፣ እናቶችን እና የሀይማኖት አባቶችን እንደ ጋሻ ከፊት በማሰለፍ በእልቂታቸው የጀግንነት አክሊል ለመድፋት ይሞክራል። አሁንም ቢሆን አሸባሪው ህወሓት የፌደራል መንግሥት ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን ካሳየው ፍላጎት በተቃራኒ በመሄድ ላይ ይገኛል። በፌደራል መንግሥት የታወጀው የተናጠል የተኩስ አቁም ስምምነት አርሶአደሩ በክረምት ወቅት ተረጋግቶ እንዲያርስ፣ ለዜጎች እርዳታ እንዲደርስና ግጭት እንዳይባባስ ቢሆንም፥ ህወሓት የተፈጠረበትን የጥፋት ስሜትና እጅ መቆጣጠር አልቻለም።

    የ1967ቱ ህወሓት ማኒፌስቶ ሕዝብና ሕዝብን በማጋጨት ሰላምና መረጋጋትን ለመንፈግ የተወጠነ ነበር። ለኢትዮጵያ ግንባታ ቋሚና ማገር በመሆን ለዛሬ ያደረሳትን ሕዝብ ለመበታተን ያለመ ነው።

    አሸባሪው ህወሓት ላለፉት 27 ዓመታት ሀገር ሲመራ በነበረበት ወቅት በሕዝብ ውስጥ ትቶት ያለፈው ሰቆቃ ሳያንስ፥ ዛሬም በሀገር ላይ የጭካኔ ተግባራትን እየፈፀመ ነው። ሕወሓት በማይካድራ የፈፀመው የዘር ማጥፋት ተግባር በብሔር ላይ ያተኮረ የሕዝብ ጠላትነት ላይ የተመሠረተ እኩይ ተግባር ነው። አሁንም በተደጋጋሚ ተመሳሳይ ድርጊት ለመፈፀም ሲቅበዘበዝ ይታያል።

    የሕወሓት ኃይል የሕዝብና የሀገር ጥቅምን አሳልፎ ከመስጠት አይመለስም። እድገታችንንና ልማታችንን ለመግታት ከሚታገሉ የውስጥና ውጪ ጠላቶች ጋር በማበር የጥፋትና የማፍረስ ሴራዎችን በዋና ተዋናይነት ሲፈፅም እንደነበረ በገሀድ ታይቷል። አሸባሪው ህወሓት ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከማስተጓጎል ጀምሮ ከነአካቴው እስከ ማደናቀፍ ድረስ የተላላኪነት እና የባንዳነት ትወና ድርሻውን ተወጥቷል።

    የአሸባሪው ህወሓት ክህደት በሕዝብ ንቀት ብቻ የተገታ አልነበረም፤ የሀገር ሉዓላዊነትን ጭምር ጥያቄ ውስጥ እስኪገባ አስነዋሪ ተግባር ፈጽሟል። ኢትዮጵያ ብትፈርስም፣ በውጪ ወራሪ ብትወረርም ደንታ እንደሌለው እስከ መግለፅ ደርሷል።

    ስለሆነም ህወሓት ለአንዱ የሚያስብ፣ ሌላውን የሚነፍግ ሳይሆን በጅምላ የመጨፍጨፍ እና የማፈራረስ አቅጣጫን ይከተላል። ከእሱ ተወልዶ፣ ከእጁ በልቶ ላደገዉ ሕዝብ የማይራራ፣ ሌላ ዘመድ ሊኖረውም ሆነ ሊያፈቅር አይችልም። “ጅግራ ዘመድ መስሎ ወፊቱን በላት” እንደሚባለው ሁሉ፥ ለአንዱ አዝኖ፣ ሌላውን አኩርፎ፣ ሌሎችን ደግሞ የተጸየፈ መስሎ የሚቀርበውን ፕሮፖጋንዳ አምኖ መቀበል ሞኝነት ነው።

    የአሸባሪው ህወሓት ኃይል ተሸንፏል፤ በፖለቲካ ሜዳው አሸናፊ ሀሳብ ማቅረብ ተስኖት ለቆ ስደትን መርጧል። በማግስቱ የጦርነት ነጋሪትን መጎሰም ጀመረ። ውሎ ሳያድር በዜጎቻ ላብ የተገዛውን የሀገር ሉዓላዊነት የሚጠበቅበት መሣርያ በመዝረፍ ኢትዮጵያን ለማንበርከክ ዛተ። በከሀዲዎችና የውጪ ኃይሎች ማበረታቻ የሰከረው ሕወሓት በመከላከያ ሠራዊቱ ለይ የጥቃት እርምጃ ወሰደ። ከትግራይ ሕዝብ ጋር ከ20 ዓመታት በላይ የኖረውን የመከላከያ ሠራዊት በከባድ የጭነት መኪናዎች ከመጨፍለቅ ጀምሮ እጅግ አስነዋሪ እርምጃዎችን ወስዷል።

    የክልልና የሀገራችን ሕዝብ በመከላከያ ሠራዊታችን ላይ የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ መከላከያ ሠራዊቱን ለመደገፍ ሁሉ አቀፍ ድርሻውን ተወጥቷል። ዛሬም ቢሆን የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትና ሕዝብ የሀገር ሉዓላዊነት ጋሻ ከሆነው የመከላከያ ሠራዊታችን ጎን በመሆን ማናቸዉንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነው። መንግሥትም የሕዝብ ተሳትፎን በማቀናጀት ሁለንተናዊ ስኬት ለማስመዝገብ ያላሰለሰ ጥረት ያደርጋል።

    ትናንት በችግር ውስጥ የመንግሥትን ጥሪን በመስማት ሁለንተናዊ ድርሻችሁን የተወጣችሁና የአሸባሪዎች የጥፋት መርዝ እንዲደፋ ያደረጋችሁ የክልላችን የኅብረተሰብ ክፍሎች ዛሬም እንደ ትናንቱ የጎላ ተሳትፎአችሁን እንድታበረክቱ መንግሥት ጥሪውን ያቀርባል።

    በሕዝባችን የተባበረ ክንድ ዘላቂ ሉዓላዊነታችን ይረጋገጣል!!
    የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት
    ሐምሌ 2013
    ፊንፊኔ

    የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት

    Anonymous
    Inactive

    ህወሓት ጠቡ ከኢትዮጵያ እና ከኢትዮጵያዊነት ጋር ነው

    በአቶ ዮሐንስ መኮንን

    “ከማዕከላዊው የመንግሥት የሥልጣን ማማ ተገፍቼያለ” ብሎ ያኮረፈው የህወሓት ቡድን ከሦስት ዓመታት በፊት የጦርነት ዳርዳርታ በጀመረ ሰሞን መገዳደል ማንንም አትራፊ ስለማያደርግ የጦርነት ጉሰማውን እንዲተው በሀገር ሽማግሌዎች፣ በልኂቃንም ሆነ በተራ ዜጎች ሳይቀር ተለምኖ ነበር። የህወሓት ሰዎች ግን “ጦርነት ባህላዊ ጨዋታችን ነው” እያሉ ያፌዙ እንደነበር ኢትዮጵያውያን ሁላችንም የምናስታውሰው የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።

    የጦርነት ጉሰማው ድንበሩን አልፎ “የ45 ደቂቃ መብረቃዊ ጥቃት” ሲሉ በራሳቸው አንደበት በነገሩን አረመኔያዊ የክህደት እርምጃ ወገናቸው በሆነው የሀገር መከላከያ ላይ የፈጸሙት ጥቃት እና በማይ ካድራ ንጹሐን ላይ የፈጸሙት ጭፍጨፋ ለህወሓት ሰዎች እና ደጋፊዎቻቸው ዛሬ ላይ “ጀብድ” ይምሰላቸው እንጂ የፈጸሙት ተግር በታሪክ ፊት አንገታቸውን የሚያሰደፋ የነውር ጥግ ነበር።

    ይህንኑ የህወሓት አረመኔያዊ ተግባ ተከትሎ የመከላከያ ሠራዊታችን በወሰደው የአጸፋ እርምጃ ዋንኛው ዓላማ ህወሓትን ከነመዋቅሯ መደምሰስ ቢሆንም ጦርነቱ በንጹሓን ዜጎች ይልቁኑም በሴቶች እና በሕጻናት ላይ ያደረሰው ጉዳት የሚያሳዝነን እና የሚያሳፍረን ክስተት ነበር።

    ዛሬ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት በውጪ መንግሥታት ተጽእኖም ይሁን በጦርነቱ አክሳሪነት የተነሳ “የጽሙና ጊዜ ለመስጠት” የተናጥል የተኩስ አቁም ውሳኔ አሳልፎ ከክልሉ ሠራዊታችን ማስወጣቱ ተገቢ እርምጃ ነው። ይህ ማለት ግን “ትግራይን የራሱ ሉዓላዊት ሀገር አካል መሆኗ አበቃ” ማለት አይደለም። በግልጽ ቋንቋ ለመግለጥ “ህወሓት ይሻለናል” ለሚሉ አባላቶቿ ደጋፊዎቿ “ዕድል ለመስጠት ያለመ” መሆኑን እገነዘባለሁ።

    ይሁን እንጂ መንግሥት ተገፍቶ ሕግ ወደማስከበር ጦርነት ሲገባም ሆነ አሁን ትግራይን ለቅቆ ሲወጣ ጉዳዩን ያየዘበት መንገድ ሌላ ዘላቂ ሀገራዊ ችግር ተክሎብን እንዳያልፍ ሊጠነቀቅባቸው የሚገቡ ጉዳዮች እንዳሉ ይሰማኛል። በምክንያት ላስረዳ፡

    ህወሓት ያኮረፈውም ሆነ የተጣላው ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር እንጂ ከአንድ ሕዝብ ጋር እንዳልነበረ የሚስተው ያለ አይመስለኝም። ጦርነቱ እንደተጀመረ ተደራጅቶ በቅርብ ርቀት ላይ ገኝ የነበረው የአማራ ልዩ ኃይል ቀድሞ የህወሓትን ተስፋፊ ጦር መመከቱ የሚያስመሰግነው ተግባር መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በሂደት ግን በዓለም ዓቀፉ ማኅበረሰብም ሆነ በአንዳንድ “ልኂቃን” ጭምር የህወሓት ጠብ “ከአማራ ልዩ ኃይል” ጋር አስመስለው መግለጻቸው ተገቢ ካለመሆኑም በላይ የአንድን ጠባብ ቡድን የእብሪት ጦርነት በሁለት ሕዝቦች መካከል የተደረገ ጦርነት አስመስሎ ማቅረቡ ጉዳቱ ውሎ አድሮ የሚያመረቅዝ ቁስል እንዳተርፈን ያሳስበኛል። በእርግጥ የመከላከያ ሠራዊታችን ከሁሉም ብሔሮች የተውጣጣ ጦር መሆኑ እየታወቀ ተደጋግሞ “አማራ ልዩ ኃይል” የጦርነቱ ፊት አውራሪ ተደርጎ መሳሉ የህወሓት ጠብ ከአንድ ሕዝብ ጋር አስመስሎታል።

    በቀደም እለት ጠቅላይ ሚንስትሩ በፓርላማ ባደረጉት ንግግርም “የአማራ ሕዝብ ለህወሓት አይንበረከክም” የሚለው ንግገራቸው ምንም እኳን ሕዝቡን ለማጀገን እንደተጠቀሙበት ብረዳውም የአማራ ልዩ ኃይል ለሀገር አንድነት የከፈለውን መስዋእትነት ክልሉን ለመከላከል እንደተከፈለ መስዋእትነት አሳንሶ ወደማየት እንዳይተረጎም ያሳስበኛል።

    ዛሬ ደግሞ የጀርመኑ ዶቼቬሌ ሂውማን ራይት ዎችን ጠቅሶ እንደዘገበው ህወሓት “በአማራ ክልል ልዩ ኃይሎች ተይዘውብኛል” የሚላቸውን አካባቢዎች መልሶ ለመንጠቅ በርካታ ታጣቂዎቹን እያንቀሳቀሰ መሆኑን ሰምተናል። እንደዘገባው ከመጠለያ ካምፖች ሳይቀር ወጣቶችን በገፍ እየመለመለች ነው። (ህወሓት ሰንአፌ በረሃ አርቅቃ ኢትዮጵያ ላይ የጫነችውን “ሕገመንግሥት” ሳይቀር በተቃረነ መንገድ የአማራ ገበሬዎችን በማፈናቀል በወረራ የቀማቻቸውን ወልቃይት እና ሁመራን የመሳሰሉ ለም መሬቶች በግፍ መንጠቋ ይታወሳል)

    የህወሓትን ትፍራፊ ጦር እንደ አመጣጡ ለመመለስ የአማራ ልዩ ኃይል የሚያንስ ባይሆንም ትንኮሳውን ማስቆም ያለበት ዋንኛው ፊትአውራሪ ጦር ግን የሀገር መከላከያ ኃይል ነው ብዬ በጽኑ አምናለሁ። የልዩ ኃይል ተሳፎ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም የአማራ ብቻ ሳይሆን የሁሉም ክልሎች ልዩ ኃይሎች በመከላከያ ሠራዊት ሥር ታቅፈው ስምሪት ሊሰጣቸው ይገባል።

    “ኢትዮጵያን ሳላፈርስ እንቅልፍ አይወስደኝም” ብሎ የማለውን የህወሓት ትርፍራፊ ጦር መመከት እና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም መደምስ የሁሉም ኢትዮጵያውያን የቅድሚያ ቅድሚያ ኃላፊነት ነው። ምክንያቱም የህወሓት ጸብ ከኢትዮጵያ እና ከኢትዮጵያዊነት ጋር ነው!

    በአቶ ዮሐንስ መኮንን

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forums) ላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።

    ህወሓት ጠቡ ከኢትዮጵያ እና ከኢትዮጵያዊነት ጋር ነው

    Anonymous
    Inactive

    ከባልደራስ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ
    ኢትዮጵያ መቼ ይሆን ነፃ፣ ፍትሀዊና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ የሚኖራት?!

    ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ከተመሠረተ ጊዜ ጀምሮ ፍትህ እንዲሰፍን ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ፣ አድሎአዊነትና ዘረኝነት እንዲወገድ፣ ሕዝብ ከመፈናቀልና ከድህነት እንዲላቀቀቅ፣ አዲስ አበባ የራስ ገዝ አስተዳደር እንድትሆን እና ሌሎችም ዲሞክራሲያዊ መብቶች እንዲሰፍኑ የሚያስችል ሥርዓት ለማምጣት ጠንክሮ ሠርቷል፤ እየሠራም ነው። የሀገሪቱ መሪ “ከባልደራስ ጋር ግልጽ ጦርነት እንከፍታለን” እያሉ በተናገሩበት ወቅት እንኳን ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ከመታገል ቁርጠኛ አቋሙ ወደ ኋላ አላለም።

    ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) በ6ኛው ሀገር አቀፍ ቅድመ ምርጫ ሂደት (pre-election process) ላይ በተለያዩ ጊዜያት ሳይንሳዊ ጥናቶች አካሂዶ ዝቅተኛውን ዓለም አቀፍ የምርጫ መስፈርት የማያሟላ መሆኑን አረጋግጧል። የምርጫ ሂደቱ የተበላሸ ከሆነ ውጤቱም በተመሳሳይ መንገድ ሊሆን እንደሚችል የሚጠበቅ ቢሆንም ባልደራስ በኢትዮጵያ ሰላም ለማስፈን የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማበርከት ሲል በምርጫው የተሳተፈ መሆኑን ለማሳወቅ እንወዳለን።

    ፓርቲያችን ከአራት ወራት በፊት ጀምሮ ባካሄዳቸው ከፍተኛ የምርጫ እንቅስቃሴዎች ወቅት ሕዝብ ከጎኑ መሆኑን በተለያዩ መንገዶች አረጋግጧል። አዲስ አበቤ ለድርጅታችን ባሳየው ደጀንነትም ፓርቲያችን እጅጉን ኮርቷል። ያነሳነውን አዲስ አበባን ራስ ገዝ የማድረግ ጉዞ ሕዝባችን ከጎናችን በመሆን ስለሰጠን ድጋፍ ከልብ እናመሰግናለን። ለሰጣችሁንም ድምፅ ምስጋናችን ከፍ ያለ ነው። ይህንኑ ወደ ፊትም አጠናክረን እንደምንሄድ በዚሁ አጋጣሚ እንገልፃለን ።

    ዓላማችንን ከግብ ለማድረስ ደከመኝ፣ ሰለቸኝ ሳትሉ፥ ዕውቀታችሁን፣ ጊዜያችሁን፣ ገንዘባችሁንና ልዩ ልዩ ቁሳቁሶችን ጭምር የለገሳችሁ የፓርቲው አመራሮች፣ የሕዝብ ተወካዮችና የአዲስ አበባ ምክር ቤቶች እጩዎች፣ የምርጫው የቅስቀሳና የሎጂስቲክስ አካላት፣ የባልደራስ የዴሞክራሲ ማዕዘን በመሆን የምርጫውን ሂደት ከሁለት ቀንና ሌሊት በላይ የተከታተላችሁ ወኪሎቻችን እና በተለያዩ እንቅስቃሴዎቻችን ላይ የተሳተፋችሁ ሁሉ የላቀ ምስጋና የምናቀርብላችሁ በታላቅ ደስታ ነው። በሰሜን አሜሪካ፣ በአውሮፓ እና በሌሎችም ዓለማት የምትኖሩ የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የድጋፍ ሰጭ ኮሚቴ እና የአማካሪ ቦርድ አባላት ላደረጋችሁት ሁሉን አቀፍ ድጋፍ፣ ምክር እና አስተዋፆኦ ምስጋናችን እጅጉን ከፍ ያለ ነው።

    “አዲስ አበባን ማዳን ኢትዮጵያን ማዳን ነው” በሚል ዓላማ የጀመርነውን ጉዞ ገዥው ፓርቲ መሪዎቻችንን በማሰር ለማሰናከል ጥረት አድርጓል። ነገር ግን ትግሉ የተነሳበትን ዓላማ ይበልጥ ከፍ አድርጎ በመቀጠሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች የሚገዙት ሃሳብ ሆኗል። በሀገር ውስጥ ያላችሁ አባላት እና በውጭ ሀገር የምትኖሩ ድጋፍ ሰጭዎች የተሸረበውን ሴራ በጣጥሳችሁ በመውጣት፣ በሰላማዊ ትግሉ ፋና ወጊ የሆኑ መሪዎችን ቀንዲል ከፍ ብሎ እንዲታይ ያደረጋችሁ ናችሁና በድጋሚ የባልደራስ አመራር በእናንተ ደስታና ኩራት እንደሚሰማው ይገልጻል ።

    በባልደራስ ፓርቲ ቅድመ ምርጫ ሂደት ጥናት እንደተረጋገጠው በብዙ ውጥንቅጥ ውስጥ የታጀበው ዝቅተኛውን የምርጫ መመዘኛ ደረጃዎች ያላሟላው የሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ምርጫ የመጣውን ውጤት ማሳየት ችሏል። እንደሌሎቹ ጊዜዎች ሁሉ የዘንድሮውንም ምርጫ ነፃ፣ ፍትሃዊ እና ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ ከመንግሥት በኩል ምንም ቁርጠኝነት አለመኖሩን ፓርቲያችን ተገንዝቧል።

    ከምርጫው ቀን ዋዜማ ጀምሮ በአዲስ አበባ ነዋሪ ላይ የፍርሃት ድባብ ለመፍጠር በከፍተኛ ደረጃ የታጠቁ የፓሊስ እና የመከላከያ አባላት የጦር መሣሪያቸውን ወድረው በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር የሥነ ልቦና ጫና ሲፈጥሩ ሰንብተዋል። ይህም “ሊበሏት ያሰቧትን አሞራ ይሏታል ጅግራ” እንደሚባለው በምርጫው ሰሞን ከነበሩ ኢ-ዲሞክራሲያዊ ትዕይንቶች አንዱ ነበር።

    ምርጫውን ነፃ፣ ፍትሃዊ እና ዴሞክራሲያዊ ማድረግ ጠቀሜታው በሥልጣን ላይ ላለው መንግሥት እና ተወዳድረው ለማሸነፍ ለሚፎካከሩት ፓርቲዎች ብቻ ሳይሆን ለሚወክሉት ሕዝብ ጭምር መሆኑ ይታወቃል። ምርጫው ነፃ፣ ፍትሃዊ እና ዴሞክራሲያዊ ሳይሆን ሲቀር የሕዝብ ነፃነት ይገፈፋል፤ ሥርዓት አልበኝነት ይነግሣል። በዜጐች መካከል የደረጃ ልዩነት እና መሰል ችግሮች ተፈጥረው ሕዝብ በፍርሃት አረንቋ ውስጥ ይወድቃል። እነዚህን ችግሮችን ለማስወገድ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ከፍተኛ ኃላፊነት ያለበት መሆኑ ይታወቃል።

    በ6ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ የተከሰቱ ችግሮችን ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ በጥልቀት እየመረመረው ይገኛል። እስካሁን በደረሰበት ሁኔታ ምርጫው ነፃ፣ ፍትሃዊ እና ዴሞክራሲያዊ አልነበረም የሚል መደምደሚያ ላይ የሚያደርሱ ተግባራት መኖራቸውን ፓርቲያችን ያምናል። ለአብነትም፡-

    1. ድምፅ አሰጣጥን በተመለከተ ግንዛቤ ለመስጠት የተሰየሙት የምርጫ አስፈፃሚዎች የገዢው ፓርቲ እንዲመረጥ የሚረዳ ገለጻ ሲያካሂዱ የፓርቲዎች ወኪሎች እርምት እንዲያደርጉ ቢያስገነዝቡም አስፈፃሚዎች ብልሹ አሠራራቸውን አለማስተካከላቸው በችግርነት የታየ ጉዳይ ነው፤
    2. በመራጮች ምዝገባ ወቅት ያልነበሩ አዳዲስ ንዑስ የምርጫ ጣቢያዎችን ከመክፈት በተጨማሪ ማንነታቸው የማይታወቁ የምርጫ ጣቢያዎች ተከፍተው በድምፅ መስጫ ቀን ድምፅ ሲሰጡባቸው መቆየታቸው፣
    3. አቅመ ደካሞችን፣ በእድሜ የገፉትን እና የአካል ጉዳተኞችን የመንግሥት ካድሬዎች ከምርጫ ሕጉ ውጭ በማገዝ ስም በሚስጥር ድምፅ በሚሰጥባቸው ክፍሎች ይዘዋቸው በመግባት ጫና እየፈጠሩ የሚፈልጉትን ማስመረጣቸው፣
    4. በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች የባልደራስን የምርጫ ውጤት ቁጥሮች እየቀነሱ እንዲጻፉ መደረጋቸው፣
    5. ባልደራስ የተመረጠባቸውን ወረቀቶች በስልት ከጥቅም ውጭ እንዲሆኑ ወይም የባከኑ ውጤቶች እንዲሆኑ መደረጋቸው፣
    6. በእያንዳንዱ የምርጫ ጣቢያ ያለው የመራጩ ቁጥር ቀድሞ የሚታወቅ ሆኖ እያለ በብዙ የምርጫ ጣቢያዎች የመራጮች ድምፅ መስጫ ወረቀቶች ከመራጮች ቁጥር እንዲያንስ መደረጉና ወረቀቱ እስኪመጣ መራጮች በፀሐይ፣ በዝናብና በብርድ በርካታ ሰዓታት እንዲቆዩ መሆናቸው የተወሰኑት ሳይመርጡ ወደ የቤታቸው እንዲሄዱ አስገድዷቸዋል።
    7. ለአዲስ አበባ ምክር ቤት ለውድድር የቀረቡ ፓርቲዎች በርካታ በመሆናቸውና በምርጫ ወረቀቱ ላይ በምርጫ አስፈፃሚዎች በቂ እና ግልጽ ማብራሪያ ባለመሰጠቱ የምርጫ ወረቀቱ በውስጡ ምን ያህል እጩዎች እንደያዘ አለመታወቁ ለመራጮች አስቸጋሪ ሁኔታን የሚፈጥር ሆኗል። ይህም መራጩ በግልጽ ድምፅ የመስጠት ነፃነት እንዳይኖረው አድርጓል።በዚህም የድምፅ መስጫ ወረቀቶች እንዲባክኑ ወይም መራጩ ላልፈለገው ድምፅ እንዲሰጥ ሆኗል። ከላይ የተጠቀሱት በምሳሌነት ከሚነሱት ችግሮች እጅግ በጣም ጥቂቶቹ ናቸው።

    የገዥው ፓርቲ በምርጫ ወቅት ለችግረኛ ሰዎች የተለያዩ መደለያዎች በመስጠት የሕዝብን ገንዘብ ለሥልጣን መሸመቻ ማድረጉ በምድር ቀርቶ በፈጣሪ ዘንድ ይቅር የማያሰኝ ተግባር ነው። በሌሎች ጊዜዎች የድሆችን ችግር ለማስወገድ ትኩረት የማይሰጠው ገዥው ፓርቲ በምርጫ ሰዓት ብቻ ማባበያ ይዞ መቅረቡ ነዋሪውን ለመደገፍ ሳይሆን ሥልጣኑን ለማቆየት የተጠቀመበት ዘዴ መሆኑ ግልጽ ነው።

    ከምርጫ 97 ወዲህ የምርጫ ጣቢያዎች እንዲበዙ የተደረገባቸው ምክንያቶች ኗሪዎች በረጃጅም ሰልፎች ላይ በመቆየት እንዳይንገላቱ ለማድረግ መሆኑ ይታወቃል። ነገር ግን ዛሬ ምርጫ ጣቢያዎች እንደአሸን እንዲፈሉ በተደረገበት ወቅት መራጮችን ለማሰላቸትና ለማስመረር ይሁን ተብሎ የተከናወኑት ማጓተቶች ድምፅ ሰጭዎች እንዲንገላቱ ማድረጉ የሚያስተዛዝብ ሁኔታን ፈጥሯል። ቀን በፀሐይና በዝናብ፣ በምሽት እና በሌሊት ደግሞ በብርድ እንዲንገላታ የተደረገበትን ደባ ተቋቁሞ የተሰለፈው አዲስ አበቤ ድምፁን ለማን እንደሰጠ ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ጠንቅቆ ያውቃል ።

    በገዥው ፓርቲና በምርጫ ቦርድ ለማሰላቸት ሆን ተብሎ በተፈጠረው ተስፋ የማስቆረጥ ሂደት ሳትመርጡ ለቀራችሁ፣ ሆን ተብሎ በተሠራ ደባ ካርድ እንዳታወጡ የተደረጋችሁ እና መምረጥ ያልቻላችሁ፣ ጊዜ በማጣት ካርድ ላልወሰዳችሁ፣ እንዲሁም በሀገራችን ሁኔታ ተስፋ በመቁረጥ የዜግነት ግዴታ መወጣት ያልቻላችሁ የእናንተ ድምፅ ሀገራችን ከገባችበት ውጥንቅጥ ችግሮች መውጫ ከፍተኛ ሚና የሚጫወት ሆኖ ሳለ በመቅረቱ በእጅጉ ያስቆጫል።

    የአሁኑ የኦህዴድ/ብልጽግና አባት የሆነው ህወሓት/ኢህአዴግ በምርጫ 2007 የ100% የአሸነፍኩ ጉዞ ከ2 ዓመት በላይ በሥልጣን መቆየት እንዳልቻለ የ3 ዓመት ትውስታችን ነው። በሕዝብ ያልተመረጠ መንግሥት ራሱን ይሸነግል ይሆናል እንጂ ረጅም ርቀት እንደማይጓዝ ከዚሁ ከሀገራችን ታሪክ መረዳት ይቻላል። ለነፃ፣ ፍትሀዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ዳኝነት የሚሰጠው ሕዝብ ነውና።

    6ኛውን ሀገር አቀፍ ምርጫ “ነፃ፣ ፍትሃዊ እና ዴሞክራሲያዊ አደርጋለሁ” ይል የነበረው ኦህዴድ/ብልጽግና በምርጫው ዙሪያ እየተፈጸሙ ያሉት ድርጊቶች የማያልቅ ሀሰቱ ማሳያዎች ሆነዋል። ዜጎች እየተገደሉ፣ ሰብዓዊ መብታቸው እየተጣሰ፣ ንብረታቸው እየወደመ፣ እየተራቡ እና እየተደፈሩ፣ የውጭ ወራሪ ኃይሎች ድንበር ጥሰው ሀገራችን ውስጥ ገብተው እንደፈለጉ እየሆኑ “ኢትዮጵያ አሸንፋለች፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም ሰፍኗል።…” የተሰኙት አባባሎች ዓይናችሁን ጨፍኑ ላሞኛችሁ ከማለት ያለፈ ትርጉም የላቸውም።

    የአዲስ አበባ ሕዝብ ለሰጠን ታላቅ ድጋፍና ፍቅር፣ ክብርና ሞገስ አሁንም ደግመን እናመሰግነዋለን። የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ አመራሮች እና አባላት በሕዝብ ፊት በተግባር ጭምር እየተፈተንን የሰላማዊ ትግል አርበኞች መሆናችንን አስመስክረናል።

    የዴሞክራሲ ኃይሎች ትንንሽ ልዩነቶችን ወደ ጎን በመተው ለማይቀረው የሰላማዊ ትግል ተደጋግፈን ሕዝብን በማስተባበር እንድንታገል ዛሬም እንደቀድሞው ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ጥሪውን ያቀርባል።

    ብሔራዊ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. የተካሄደወን የምርጫ ውጤት ይፋ ካደረገ በኋላ ከምርጫው ጋር በተያያዘ በዝርዝር ጉዳዮች ላይ ባልደራስ መግለጫ የሚሰጥ መሆኑን በአክብሮት ይገልጻል።

    የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ
    ድል ለእውነተኛ ዴሞክራሲ!!!
    ሰኔ 18 ቀን 2013 ዓ.ም.

    ምንጭ፦ ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ

    ነፃ፣ ፍትሀዊና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ

    Anonymous
    Inactive

    እብለት የሌለበት ምስክርነቴ – ለዶ/ር ብርሀኑ ነጋ

    (የትነበርክ ታደለ /ጋዜጠኛ/*)

    በሀገራችን የዲሞክራሲ ትግል ውስጥ ትልቁ ፈተና ኢ-ዴሞክራሲያዊና አምባገነን መንግሥታት ብቻ አይደሉም፤ የሴራ ምሁራንም ጭምር እንጂ። በገዛ ራሳችን ምሳሌ “ቀና ቀና ያለች ማሽላ አንድም ለወፍ፥ አንድም ለወንጭፍ” እንደ ተባለው የሀገራችን የሴራ ምሁራን ከመካከላቸው ቀና ያለውን በማጥቃት ብዙ ፍሬ ያዘሉ ሰብሎቻችንን አምክነው ኖረዋል። በዚህ ድርጊታቸው ከአምባገነን መንግሥታት በላይ ሀገራችንን መከራ ውስጥ ጨምረዋል። ብርሀኑ ነጋ ለእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የመፍትሄ ምንጭ እንጂ ጸረ-ኢትዮጵያዊ ወይም ጸረ-ኢትዮጵያ ተብሎ ለተከታታይ ዓመታት በአደባባይ የሚዘመትበት ሰው አልነበረም!!

    ብርሀኑ…

    ከጽንፈኛ ብሔርተኞችና ከአክራሪ ሀይማኖተኞች በሚወረወርበት ሾተል ጀርባው እየደማ የዜግነት ፖለቲካን የሙጥኝ ያለው ‘በኔ ጉዳት ኢትዮጵያ ትዳን’ ብሎ እንጂ ኢትዮጵያን ስለሚጠላ አይደለም!

    እንዲህም ተባለ እንዲያ ዛሬ ያ መገፋቱ ፍሬ አፍርቶ እነሆ ከሦስት የጭለማ ዓመታት በኋላ ሀገር ኖራ፣ ምርጫም ኖሮ፣ ወደ ፊት ልንሻገር ነው ብለን የምናስብበት የተስፋ ጭላንጭል ላይ ደርሰናል።

    ‘ምርጫ አለ’ ያልነው ብርሀኑ ስላለ ነው! ኢትዮጵያ ያንን ሁሉ መከራ አልፋ ለምርጫ የደረሰችው ብርሀኑ ነጋ በፖለቲካ ስም ሀገር የመናድ የገመድ ጉተታው አካል ስላልነበረ ነው!

    ዶላርና የጥይት አረር ታቅፈው ከውጭ የገቡ ተቃዋሚዎችና ሚሳኤል የታጠቀች ህወሓት “ሕገ-መንግሥቱን ትነኩትና” እያሉ በሚያስፈራሩበት በዚያ የሦስት ዓመት ጭለማ ክረምት ውስጥ ሕዝብ ብርሀኑን ሰምቶ “እውነት ነው፤ ጊዜው የሕገ መንግሥት ጥያቄ ማንሻ አይደለም” ብሎ ጋብ ባይል ኖሮ፤ “ይህ የምንፈልገው ሥርዓት አይደለም፣ ይሁን እንጂ ለሀገራችን ስንል እንደግፈው፣ ከችግሮቹ ይልቅ ጠንካራ ጎኖቹን እያሳየን ወደ ፊት እንግፋው” ብሎ ከመንግሥት ጎን ቆሞ “አለሁ!” ባይል ኖሮ የዛሬው የምርጫ ክርክር ቅንጦት በሆነ ነበር።

    በእውቀቱ ልክ እያሰበ በሀገር ፍላጎት ልክ እየወሰነ ባይራመድ ኖሮ “በለው! በለው! ፍለጠው! ቁረጠው!” ባዮች ጋር በስሜት ጋልቦ ቢሆን ኖሮ… እንኳን አንግቦት የተነሳውን የዜግነት ፖለቲካ ለአካለ ምርጫ ማድረስ ይቅርና፥ ለሀገራችንም ጦስ በሆነ ነበር።

    ይህ ሁሉ ለሕዝብ ግልጽ የሆነ ሀገራዊ አበርክቶው በሴራ ምሁራን ትንታኔ እየታጀለ ቀን ከሌት መዶስኮሩ ሰውዬው በእርግጥም ፍሬ ያዘለ ሰብል መሆኑን ከማሳየቱ በቀር እንደሚሉት ጥላቻ በልቦናው የተሸከመ ጸረ-ሕዝብና ጸረ-ሀገር መሆኑን ፈጽሞ አይመሰክርም!!

    ― ይድረስ ለብርሀኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) ―

    የመጨረሻ ውጤቱ፣ ጥራቱና መጠኑ ምንም ይሁን ምን፣ ዴሞክራሲን አዋልደሀል!! ጨቅላውን ዴሞክራሲ አንስቶ መሳም፣ አቅፎ ማሳደግ የኛ ድርሻ ይሆናል! ለዘመናት የተጫነብንን የዘር ፖለቲካ የምናራግፍበትን አንድ ዘዴ የሆነውን የዜጋ ተኮር ፖለቲካ አስተምረህ፣ አዋቅረህ፣ ከምርጫው ኮሮጆ አድርሰህልናል – ያለፈውን ጥፋት ላለመድገምና እንደ ቀሪው ዓለም በሀሳብ ላይ መሠረት ያደረገ ፖለቲካን መምረጥ የኛ ፋንታ ይሆናል። በብዙ መከራዎች መካከል ባለች ሀገር ውስጥ የሰከነ የተቃውሞ ፖለቲካን በማራመድ ሀገርና መንግሥት በፈለጉን ጊዜ አቤት እያልን በቀረው ደግሞ እየተቃወምንና እየተቸን መጓዝ የምንችልበትን የሰለጠን አስተሳሰብ አሳይተኸናል። ይህን መንገድ ተከትሎ ያለጩኸት እና ያለ ወከባ መንግሥት መቀያየርን መልመድ የኛ ተግባር ይሆናል።… በቀረው ደግሞ ምርጫው በሰላም ተጠናቆ ቢሆን በፓርላማው፣ ከዚያም ሲያልፍ በመንግሥት ስልጣን ላይ ሆነህ ቀሪ ህይወትህን ለዚህች ደሀ ሀገራችን የበለጠ እንድትሠራ መልካም ውጤት እመኝልሀለሁ! በቀረው ግን ውለታህ አለብን እንጂ ግዴታችን የሌለብህ ከሚጠበቅብህ በላይ ያገለገልከን ታላቅ ዜጋ ነህና እናከብርሀለን!!!

    * አቶ የትነበርክ ታደለ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የሚጽፍ ጋዜጠኛ ሲሆን፥ በፌስቡክ ገጹ ሊያገኙትና ጽሁፎቹን ሊከታተሉ ይችላሉ።

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forums) ላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።

    ዶ/ር ብርሀኑ ነጋ

    Anonymous
    Inactive

    ሀገራችን ኢትዮጵያ ያለችበት የሕልውና አደጋ በአቶ ልደቱ አያሌው እይታ

    ስንብት፥ ለመሰንበት
    ልደቱ አያሌው
    የካቲት 29 ቀን 2013 ዓ.ም.

    ሀገራችን ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የሕልውና አደጋ ውስጥ ትገኛለች። ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ የሆነ የዕውቀት፣ የአቅምና የቅንነት ድክመት ያለበት በመሆኑ ሀገሪቱ የገጠማትን ችግር ከማቃለልና ከመፍታት ይልቅ፥ የበለጠ እያባባሰውና እያወሳሰበው ይገኛል። በዚህም ምክንያት ሀገራችን ሕልውናዋን የሚፈታተን አሳሳቢ የእርስ በርስ ግጭት ውስጥ ከመግባቷም በላይ፥ ከኤርትራና ከሱዳን መንግሥታት ግልጽ ወረራ ተፈጽሞባታል። ከታሪኳና ከማንነቷ በተቃራኒም ይህንን ግልጽ ወረራ  ለመቀልበስ የሚያስችል አቅምና ወኔ ያጣች ደካማ ሀገር ሆናለች። ይህ ክስተት ሀገሪቱ ምን ያህል በሂደት ውስጣዊ አንድነቷ እየተዳከመ እንደመጣና ወደ መበታተን አደጋ ውስጥ እየገባች ስለመሆኑ አንድ ማሳያ ነው።

    ብልጽግና ፓርቲ እያራመደ በሚገኘው የተሳሳተ የውጭ ግንኙነት ምክንያትም ሀገራችን ለከፍተኛ የዲፕሎማሲ ጫና ተጋላጭ በመሆን ብሔራዊ ጥቅሞቿንና ሉዓላዊነቷን በአግባቡ ማስከበር የማትችልበት ሁኔታ ውስጥ ገብታለች። ‘በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ’ እንዲሉም ሀገራዊ ሕልውናችንን በሚፈታተን መጠን ኢኮኖሚያችን ወደ ጥልቅ ቀውስና ኪሣራ ውስጥ እየገባ ይገኛል።

    ይህ ሁሉ እየሆነ ያለው በብዙ የሕይወት መሥዋዕትነት የተገኘውና የዛሬ ሦስት ዓመት ገደማ ተጀምሮ የነበረው የለውጥ ሂደት በአመራር ድክመትና በአምባገነናዊ ባህርይ ምክንያት እንዲከሽፍ በመደረጉ ነው። በሥልጣን ላይ የሚገኘው ብልጽግና ፓርቲ ለለውጡ መምጣት ምክንያት የሆኑትን ፖለቲካዊ ችግሮች ሕጋዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ በሆነ አግባብ ከመፍታት ይልቅ አማራጭ ሀሳቦችን በማፈን፣ በፖለቲካ ተቀናቃኞቹ ላይ የስም ማጥፋት ዘመቻ በማካሄድና የፈጠራ ክስ በመመሥረት፣ በሕገ-ወጥ መንገድ ተቀናቃኞቹን በማሰርና ‘ለሕልውናዬ ስጋት ናቸው’ ብሎ የሚፈራቸውን የፖለቲካ ድርጅቶች ሕጋዊ ዕውቅና በመሠረዝ ጭምር ካለፈው የ27 ዓመቱ የኢሕአዴግ ሥርዓት የባሰ እንጂ የተሻለ አለመሆኑን በተግባር አሳይቷል። ባጭሩ፥ ሀገራችን ከእንግዲህ በብልጽግና ፓርቲ ወይም በዶ/ር ዐቢይ አሕመድ እየተመራች ከአንድ ቀውስ ወደ ሌላ የባሰ ቀውስ የመሸጋገር እንጂ ወደ በጎና የተሻለ ሥርዓታዊ ለውጥ የመሸጋገር ዕድል እንደሌላት በማያሻማ ሁኔታ ግልጽ ሆኗል።

    እኔም ሆንኩ አባል የሆንኩበት ፓርቲ፥ በአንድ በኩል የተጀመረው የለውጥ ሂደት ስኬታማ እንዲሆን ከተፈለገ ምን ዓይነት መዋቅራዊ ለውጦች በቅደም ተከተል መካሄድ እንዳለባቸው፤ በሌላ በኩል ደግሞ በአመራር ብቃት ማነስ ምክንያት የተጀመረው የለውጥ ሂደት ከከሸፈ በሀገራችን አጠቃላይ ሕልውና ላይ ሊያስከትል የሚችለው አደጋ ምን ያህል ከባድና አደገኛ እንደሚሆን የሚያሳስብ የሀሳብ ትግል ላለፉት ሦስት ዓመታት ስናካሂድ ቆይተናል።

    ነገር ግን የወቅቱ የሀገራችን ፖለቲካ በዕውቀት፣ በምክንያታዊነትና በሐቀኝነት የሚካሄድ ሳይሆን ብሔርተኝነት፣ ጽንፈኝነት፣ ሤረኝነት፣ ጥላቻና ውሸት የነገሠበት በመሆኑ ጩኸታችን የቁራ ጩኸት ሆኖ ቀርቷል። ሆኖም ቀደም ብለን ስናቀርበው የነበረው ስጋት ከተራ ሟርተኝነት ሳይሆን፥ ከተጨባጭ የፖለቲካ ግምገማ፣ ግንዛቤና ትንታኔ የመነጨ ስለነበር እንደፈራነው የለውጥ ሂደቱ ከሽፎ አሁን ሀገሪቱ ወደባሰና ውስብስብ የሕልውና አደጋ ውስጥ ገብታለች።

    የለውጥ ሂደቱን መክሸፍ ተከትሎ ሀገራችን ወደ ከፍተኛ የእርስ በርስ ጦርነት የገባችና በውጭ ኃይሎች ወረራ ሥር የወደቀች ቢሆንም፥ ግብዞቹ የብልጽግና አመራሮችና የእነርሱ የፕሮፓጋንዳ ሰለባ የሆኑ ተከታዮቻቸው ግን ዛሬም ጭምር ሀገሪቱ ወደላቀ የብልጽግና ጎዳና እየገሰገሰች እንደሆነ ሊነግሩን ሲደፍሩ እያየን ነው። ብልጽግና ፓርቲ የከሸፈን የለውጥ ሂደት ተከትሎ የሚካሄድ ሀገራዊ ምርጫ፥ የተጨማሪ ቀውስ ምንጭ ከመሆን ባለፈ ለሀገሪቱ መዋቅራዊ የፖለቲካ ችግሮች የሚያስገኘው ምንም ዓይነት አዎንታዊ ፋይዳ የሌለ መሆኑን መገንዘብ ተስኖት የሥልጣን ቅቡልነት ልባስ ለመደረብ ሲል ብቻ ትርጉም የለሽ ምርጫ ለማካሄድ እየተጣደፈ ይገኛል። ይህም ሀገሪቱ ወደባሰና ከቁጥጥር ውጭ ወደሆነ የፖለቲካ ቀውስ ልትገባ ትችላለች የሚል ተጨማሪና ምክንያታዊ ስጋት ፈጥሯል።

    በእኛ በኩል ውጤታማ ሽግግር ባልተካሄደበትና አንጻራዊ ሰላምና መረጋጋት ባልተፈጠረበት ሁኔታ በችኮላ ወደ ምርጫ ውስጥ መግባት አደገኛና ኃላፊነት የጎደለው ውሳኔ ነው የሚል የጠነከረ አቋም ያለን ቢሆንም፥ ምርጫው መካሔዱ የማይቀር ከሆነ ግን ቢያንስ በምርጫው ሂደት ሊፈጠር የሚችልን አደጋ ለመቀነስ በሚያስችል አግባብ በምርጫው ተሳታፊ ለመሆን በዝግጅት በማድረግ ላይ ነበርን።

    ነገር ግን ከሁሉም ነገር በላይ ሀሳብን አብዝቶ የሚፈራውና ከሀገሪቱ ደኅንነት በላይ ለራሱ የሥልጣን የበላይነት ሰፍሳፋ የሆነው የወቅቱ መንግሥት በመጭው ምርጫም ሆነ በቀጣዩ የትግል ሂደት ተሳትፎ እንዳይኖረን ስለፈለገና ስለወሰነ በሕገ-ወጥ መንገድ ፓርቲያችን እንዲሰረዝና ከትግሉ ሜዳ እንዲወገድ አድርጓል።

    በእኔ ላይም በባለቤትነት በሚቆጣጠራቸውና ለልዩ ተልዕኮ ባቋቋማቸው የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ቅጥረኞቹን አሰማርቶ ሰፊ የስም ማጥፋት ዘመቻ በማካሄድ፣ የዛቻና ማስፈራራት ድርጊት በመፈጸም፣ የፈጠራ ክስ በመመሥረትና በሕገ-ወጥ መንገድ በማሰር የትግል ተሳትፎዬን ለመገደብ ሞክሯል። ይህም አልበቃ ብሎት በፖለቲካ መድረኩ ላይ ብቻ ሳይሆን በሕይወትም እንዳልኖር ስለፈለገ፥ ያለምንም ሕጋዊ ድጋፍ ያለብኝን ከፍተኛ የልብ ሕመም ወደውጭ ሀገር ሄጄ እንዳልታከም እገዳ ጥሎብኛል። ይህ ሕገ-ወጥ እገዳ እንዲነሳልኝ የተለያዩ የመንግሥት ተቋማትንና ባለሥልጣናትን ለማነጋገርና ለመማጸን ያደረግኩት ጥረትም ስኬታማ ሳይሆን ቀርቷል። በዚህም ምክንያት ከፍተኛ የልብ ቀዶ ጥገና ሕክምና ለማድረግ የነበረኝ ቀጠሮ በመስተጓጎሉ በእያንዳንዱ ሰዓትና ዕለት ሕይወቴ ለዕልፈት ሊጋለጥ በሚችልበት አደጋ ውስጥ እገኛለሁ። በዚህ ድርጊቱም የወቅቱ መንግሥት አምባገነናዊ ብቻ ሳይሆን ምን ያህል ኢ-ሰብአዊ መሆኑን በተግባር አሳይቷል። በርግጥም ሥርዓቱ ከግለሰብ ግድያ ጀምሮ እስከ የሕዝብ ጅምላ ጭፍጨፋ ከሚደርስ ቀውስ የፖለቲካ ትርፍ ለመቃረም የሚጥር ኃይል በመሆኑ በእኔ ላይ ይህንን ማድረጉ እምብዛም አያስደንቅም።

    ሰሞኑን የምገኝበትን አሳሳቢ የጤና ሁኔታ በተመለከተ ከሐኪም ጋር ባደረግሁት ምክክርም ለሕመሜ አስተማማኝ ሕክምና እስካገኝ ድረስ በአካሌም ሆነ በአዕምሮዬ ላይ ምንም ዓይነት ጫናና ውጥረት የሚፈጥር ሥራ እንዳልሠራና በቂ ረፍት እንዲኖረኝ ከባድ ማስጠንቀቂያና ምክር ተሰጥቶኛል። ጤናዬ ከሚገኝበት አሳሳቢ ደረጃ (risk) አኳያ በሕይወት ለመሰንበት የምፈልግ ከሆነ፥ ለጊዜው ያለኝ ብቸኛ አማራጭ ይህንን ማድረግ እንደሆነ ተነግሮኛል።

    ሀገራችን የምትገኝበትን እጅግ አሳሳቢ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት በእኔ በኩል አስቸኳይ የሕክምና እርዳታ አግኝቼና ጤናዬ ተስተካክሎ በትግሉ ሂደት የጎላ ተሳትፎ እንዲኖረኝ ከፍተኛ ፍላጎት የነበረኝና አሁንም ያለኝ ቢሆንም የሕክምና እርዳታ እንዳላገኝ ራሳቸውን በፈጣሪ ቦታ ሊተኩ በሚፈልጉ ገዥዎች በመከልከሌ ምክንያት ይህንን ምኞቴን ማሳካት የማልችልበት እንቅፋት ገጥሞኛል። ስለሆነም ተገቢውን የሕክምና እርዳታ አግኝቼ ጤናዬ እስኪመለስ ድረስ በሕይወት የመሰንበት ዕድሌን ለመሞከር ስል ከማንኛውም ዓይነት የትግል እንቅስቃሴ (ገንዘብ ወይም ምክር ከማዋጣት ባለፈ) ራሴን ለጊዜው ለማቀብ የተገደድኩ ስለመሆኑ በከፍተኛ ቁጭትና ሐዘን እገልጻለሁ።

    በዚህ ጉዳይ ላይ የሚሰማኝ ቁጭትና ሐዘን ልብን የሚሰብር የሆነብኝ ያለምክንያት ሳይሆን፥ ሀገራችን ከመቼውም ጊዜ በላይ የሕልውና አደጋ ውስጥ በገባችበትና ዋጋ የሚከፍልላት ዜጋ በሚያስፈልጋት በአሁኑ ወቅት ከአቅሜ በላይ በሆነ የጤና ችግር ምክንያት ራሴን ከትግሉ ሜዳ ለማግለል መገደዴ ያልጠበቅሁትና ከፍላጎቴ ውጭ የሆነ መጥፎ ገጠመኝ ስለሆነ ነው።

    የሆነው ሆኖ ይህንን መጥፎ አጋጣሚ እንደ አንድ ጊዜያዊ ስንብት ልቁጠረውና ስለ ዛሬዋ ኢትዮጵያ ሕዝቡ ግንዛቤ ሊወስድ ይገባዋል ብዬ በማምንባቸው በሚከተሉት ስምንት ነጥቦች ዙሪያ የሚሰማኝን በመግለጽ ለመሰናበት ልሞክር።

    1. ከእንግዲህ በብልጽግና ፓርቲ የሚባባስ እንጂ የሚፈታ ችግር የለንም

    በአሁኑ ወቅት ሀገራችን ለገጠማት የሕልውና አደጋ በአስተሳሰብና በመዋቅር ደረጃ ዋናዎቹ ተጠያቂ ምክንያቶች የጽንፈኝነት ፖለቲካ፣ ብሔርተኝነትና የፖለቲካ አመራር ድክመቶች ናቸው። ስለሆነም ለወቅቱ የለውጥ ሂደት መክሸፍ ዋናው ተጠያቂ የእነዚህ መዋቅራዊ ድክመቶች ሰለባ የሆነው የቀድሞው ኢሕአዴግ፣ የአሁኑ ብልጽግና ፓርቲ ነው።

    ብልጽግና ፓርቲ በእጁ የገባውን ወርቃማ የለውጥ ዕድል በአግባቡ መጠቀም ሳይችል የቀረበት ተጨማሪ ምክንያትም ፓርቲው ከሀገሪቱ ጥቅምና ደኅንነት በላይ ለራሱ የፖለቲካ ሥልጣን የበላይነት ቅድሚያ በመስጠት ውስጣዊ አንድነቱን በማዳከሙና ወደ የእርስ በርስ የሥልጣን ሽኩቻ ውስጥ በመግባቱ ነው። የፓርቲው ውስጣዊ ክፍፍል በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች እየተፈጠሩ ላሉ የእርስ በርስ ግጭቶችና በትግራይ ክልል ለተከሰተው ጦርነት ዋናው ምክንያት ሲሆን፥ ውስጣዊ ችግሩ አሁንም የተሻለ ትኩረት አግኝቶ ካልተፈታ በስተቀር ሀገሪቱን ለባሰ ቀውስና ጦርነት የሚዳርጋት ይሆናል። የራሱን ውስጣዊ ችግር መፍታት ያልቻለና ከራሱ የፖለቲካ ሥልጣን በላይ የሀገሪቱን ጥቅም ማስቀደም የተሳነው ደካማ ገዥ ፓርቲ የለውጥ ሂደቱን ስኬታማ ሊያደርግም ሆነ ሀገሪቱን ከጥፋት ሊታደጋት አይችልም።

    ቀደም ሲል ብልጽግና ፓርቲ ይህንን መሠረታዊ ድክመቱን አምኖ በመቀበልና በማረም ራሱንም ሆነ ሀገሪቱን ከጥፋት ሊታደጋት ይችላል የሚል ግምት (ምናልባትም የሞኝነት) የነበረን ቢሆንም ግምታችን ስህተት እንደነበር ያለፉት ሦስት ዓመታት ሂደት በተግባር አሳይቶናል። በዚህም ምክንያት ብልጽግና ፓርቲ እንደ ፈጣሪውና አሳዳጊው ህወሓት ሁሉ፥ ከመሞት መዳን ያለመቻል መዋቅራዊ ችግር ያለበት ግትርና ጀብደኛ ድርጅት እንደሆነ መገንዘብ ችለናል። ምክንያቱም ብልጽግና ፓርቲ አምባገነን የሆነው አምባገነን እንዲሆን ያስገደዱት ነባራዊ ሁኔታዎች ስላሉ ሳይሆን በራሱ ፍላጎትና ውሳኔ አምባገነን መሆንን የመረጠ ድርጅት ስለሆነ ነው።

    ከይቅርታ ጋር፥ እዚህ ላይ በከፍተኛ ድፍረትና ርግጠኛነት ልናገር የምችለው፥ የ21ኛዋን ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያን በ16ኛው ክፍለ ዘመን የማክያቬሊ የፖለቲካ ሤራ ስልት (conspiracy theory) እና የንግርት አምልኮት ለመግዛት እየሞከረ ያለው ብልጽግና ፓርቲ አሁን በያዘው አቅጣጫ መጓዝ ከቀጠለ ራሱንም ሆነ ሀገሪቱን የማፍረስ እንጂ ወደ ዘላቂ ለውጥ የማሸጋገር ሚና ከቶውንም ሊኖረው አይችልም። በአሁኑ ወቅት ትግራይ ውስጥ የገባንበትን ከባድ ጦርነት፣ በኤርትራናና በሱዳን መንግሥት የተፈጸመብንን ወረራ፣ በሕዳሴ ግድብ ምክንያት ከግብጽና ከሱዳን ጋር የገባንበትን ፍጥጫ፣ በተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች እየተፈጸመ የሚገኘውን የሕዝብ መፈናቀልና የጅምላ ጭፍጨፋ፣ በገዥው ፓርቲና በበርካታ ተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል የሚታየውን ፍጥጫ፣ ከዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ እየደረሰብን ያለውን ከባድ ተጽዕኖ፣ የኮሮና ወረርሽኝ እያስከተለብን ያለውን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውስ፣ ከፊታችን እየመጣ ያለውን ሁለንተናዊ ኢኮኖሚያዊ ውድቀትና ሌሎች ተመሳሳይ ፈተናዎቻችንን በጥቅሉ ደምረን ስናያቸው እንኳንስ ብልጽግና ፓርቲ ብቻውን ሆኖ ሁላችንም ተባብረን በአንድነት ብንቆም የወቅቱን የሀገሪቱን ፈተና በቀላሉ መወጣት አዳጋች ነው። ስለሆነም የውስጥ ችግራችንን ፈተን በአንድነት እስካልቆምን ድረስ በብልጽግና ፓርቲ የተናጠል ጥረት ችግራችን ፍጹም ሊፈታ እንደማይችል መገንዘብ ያስፈልጋል።

    1. ወቅቱ ኢትዮጵያውያን በአስተሳሰብና በሞራል ዝቅታ ላይ የምንገኝበት ነው

    የምንገኝበት ወቅት ኢትዮጵያውያን ከመቼውም ጊዜ በላይ ጭካኔን፣ ጅምላ ግድያን፣ የሤራ ፖለቲካን፣ የጥላቻ ንግግርን፣ ውሸትንና የግለሰብ አምልኮትን እየተለማመድን የምንገኝበት ነው። እነዚህን እኩይ ተግባራት በፊት አውራሪነት እያለማመደን የሚገኘው መንግሥት ሲሆን፥ ጋሻጃግሬዎቹ ደግሞ ሀይማኖተኛ፣ ብሔርተኛና ምሁራን ነን ባይ “ልሂቃን” መሆናቸውን እያየን ነው።

    በርግጥም ወቅቱ የ“ዝቅታችን” ወቅት ነው። ለአንድ “ህወሓት” የተባለ አምባገነናዊ የሆነና በሕዝብ ትግል ከሥልጣን ለተወገደ ኃይል ባለን ገደብ የለሽ ጥላቻ ምክንያት ዓይነልቦናችን ታውሮ የዛሬ ገዥዎቻችን በሕዝብና በሀገር ላይ እየፈጸሙት ያለን የዛሬ ግፍና በደል ፈጽሞ ማየትና መረዳት ተስኖናል። የወቅቱ ገዥዎቻችን ለራሳቸው የሥልጣን የበላይነት ሲሉ በሀሰትና በአስመሳይነት በጥብጠው የሚግቱንን ሥልታዊ ፕሮፓጋንዳ፣ በሀገር ጥቅምና በሕግ ማስከበር ሰበብ እየፈጸሙት ያለን በውጤቱ ሀገር በታኝ የሆነ የሤራና የበቀል ተግባር መገንዘብ ተስኖን እንደ ሕዝብ የአዲስ አምባገነናዊ ኃይል አዋላጅና ወላጅ ሆነናል። እወደድ ባይና ደካማ በሆነው የብልጽግና ፓርቲ አመራርና ተከታዮቹ በሆኑት የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል ያለው የጋራ አጀንዳ፥ በዋናነት ህወሓትን በመጥላትና በመበቀል ዙሪያ የተቃኘ ቢሆንም፥ ዋናውና የጋራ መገለጫቸው የሆነው ባሕርያቸውና ግብራቸው ግን የህወሓት አውዳሚ አመለካከትና ውርስ (legacy) አራማጅና አስቀጣይ መሆን ነው። እነዚህ ግብዝ ኃይሎች በህወሓት መንገድ መጓዝ ህወሓት በከፋፋይ አጀንዳው ያዳከማትን ሀገር ለይቶላት እንድትፈርስ ከማድረግ ያለፈ ውጤት እንደማያመጣ መገንዘብ ተስኗቸዋል። ይህም በራሱ ኢትዮጵያውያን ከሌሎችም ሆነ ከራሳችን ያለፈ ስህተትና ውድቀት የመማር አቅማችን እጅግ አናሳ መሆኑን ያሳያል።

    በአጠቃላይም ወቅቱ ኢትዮጵያውያን በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በራሳችን ታሪክ፣ አንድነት፣ ሉዓላዊነት፣ ሰላም፣ የወደፊት ዕድገትና ጥቅም ላይ ራሳችን ጦርነት ያወጅንበት ወቅት ነው ማለት ይቻላል። በአጭሩ የራሱን ፍላጎትና ዘለቄታዊ ጥቅም የማያውቅ ግብዝ ሕዝብ ሆነናል። ከገባንበት ዝቅጠት ጥልቀትና ስፋት አኳያም አንዳንዶች “ኢትዮጵያውያን እርስ በርስ ተጨራርሰን ከምንጠፋ በስምምነት ተለያይተን መኖር የምንችልበት ዕድል ይኖር ይሆን?” ብለው ራሳቸውን ለመጠየቅ የተገደዱበት ወቅት ላይ ደርሰናል። ኢትዮጵያውያን እንደ “ሕዝብ” በዚህ ዓይነት የአስተሳሰብና የሞራል ዝቅታ ላይ እንደምንገኝ ተገንዝበን ስክነትና ብስለት ወደተላበሰ የፖለቲካ አቅጣጫ በፍጥነት ካልገባን በስተቀር ሀገራችንን ከገጠማት የመፈራረስ አደጋ ልንታደጋት አንችልም። እጅግ አማላይና መሠሪ በሆነው የሥርዓቱ የፕሮፓጋንዳ ስልት ሰለባ በመሆን፣ ወይም በአድር ባይነት፣ ወይም በጥቅመኝነትም ሆነ በማንኛውም ሌላ ምክንያት የወቅቱን ሥርዓት እየደገፍን የምንገኝ ዜጎች በታሪክና በትውልድ ፊት የየራሳችን የተጠያቂነት ድርሻ እንደሚኖርብን ተገንዝበን፥ ሥርዓቱን መቃወምና መታገል ቢያቅተን እንኳን ቢያንስ ዝም በማለት የሀገሪቱ ጥፋትና ውድቀት ቀጥተኛ ተጋሪ ከመሆን ልንቆጠብ ይገባል።

    1. በይስሙላ ምርጫ የሚፈታ ችግር የለንም

    ነጻና ፍትሐዊ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል ውጤታማ የሽግግር ሂደት ባላካሄድንበት ሁኔታ የሚካሄደው የዘንድሮው ሀገራዊ ምርጫ ሂደትም ሆነ ውጤት የሀገሪቱን የፖለቲካ ቀውስ የበለጠ የማባባስ እንጂ የመፍታት አንደምታ አይኖረውም። ምርጫው ሳይጀመር ያለቀና ውጤቱም ሀገሪቱን ወደ ባሰ ቀውስ ማስገባት ወይም አምባገነናዊነትን ማጽናት መሆኑ አስቀድሞ የታወቀ ነው። ይህ ምርጫ ብልጽግና ፓርቲ በማንኛውም መንገድ አሸናፊ ሆኖ በሥልጣን ላይ ለመቀጠል ወስኖና ተዘጋጅቶ የገባበት ምርጫ ስለሆነ፥ የዚችን ደሃ ሀገር በጀት ከማባከን ያለፈ ፋይዳ አይኖረውም። በአጭሩ መጭው ምርጫ ነጻና ፍትሐዊ እንደማይሆን ሳይሆን እንዳልሆነ የቅድመ ምርጫው ሂደት በማያሻማ ሁኔታ አሳይቷል። የወቅቱ የፖለቲካ ችግር በዘላቂነት ሊፈታ የሚችለው በአንጻራዊነት ነጻ፣ ገለልተኛና ጠንካራ የዴሞክራሲ ተቋማትን ለመገንባት፣ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በነጻነትና በእኩልነት ምርጫ የሚወዳደሩበትን ሁኔታ ለማመቻቸት፣ ብሔራዊ መግባባትና ዕርቅን ለማስፈን፣ ብሎም ሕገ-መንግሥታዊ ማሻሻያ ለማድረግ በሚያስችል ሁሉን አቀፍ በሆነ የሽግግርና የሀሳብ ግብይት ሂደት (national dialogue) ነው እንጂ በተለመደው ዓይነት የታይታ የምርጫ ግርግር አይደለም።

    ወደ መዋቅራዊና ዘላቂ ለውጥ ለመግባት ከተፈለገ መፍትሔው የችኮላ ምርጫ ማካሄድ ሳይሆን በቅድሚያ ከፖለቲካ ጉዳይ ጋር በተያያዘ በመላው ሀገሪቱ የታሠሩ የፖለቲከኛ እስረኞችን መፍታት፣ ዜጎች ላይ የሚደረግ አፈናና ግድያን ማስቆም፣ የሀገሪቱ ሕግጋትና ተቋማት ሀገር ጠቀም በሆነ አግባብ እንዲሻሻሉ ማድረግና ቢያንስ ዶ/ር ዐቢይ ወደ ሥልጣን በመጡባቸው በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ሳምንታት የታየው ዓይነት የዕርቅና የመቻቻል መንፈስ በሀገሪቱ እንዲሰፍን ማድረግ ያስፈልጋል።

    1. ልዩ ትኩረት አዲስ አበባ ከተማን ለማሸነፍ

    በተግባር እየተፈጸመ ከሚገኘው ግልጽ ድርጊት እንደምንረዳው ብልጽግና ፓርቲ ነጻና ፍትሐዊ በሆነ ምርጫ ተወዳድሮ በማሸነፍ ሳይሆን በአፈናና በኃይል በሥልጣን ላይ ለመቀጠል የወሰነ አምባገነን ኃይል ነው። ገዥው ፓርቲ የሚጠላቸውንና የሚፈራቸውን የፖለቲካ ፓርቲዎች ከፖለቲካ መድረኩ በማስወገድና የፓርቲ አመራሮችን በማሰር በወሰደው እርምጃ መጭው ምርጫ ነጻና ፍትሐዊ እንዳልሆነ ከወዲሁ በተግባር አረጋግጧል። ሆኖም ምርጫው በታሰበበት ጊዜ የሚካሄድ ከሆነ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ራሳቸውን ከሂደቱ ከማግለል ይልቅ አቅማቸውና ሁኔታው በፈቀደላቸው መጠን በምርጫው ተሳታፊ ቢሆኑ የተሻለ ይሆናል እላለሁ።

    ነገር ግን በቂ ዝግጅት አድርገውና የገዥውን ፓርቲ ሁለንተናዊ ተጽዕኖ በብቃት ተቋቁመው በሀገር ደረጃ መንግሥት ለመሆን በሚያስችል መጠን ምርጫውን ለማሸነፍ የሚኖራቸው ዕድል እጅግ ጠባብ መሆኑን በመገንዘብ ሙሉ ትኩረታቸውን አዲስ አበባ ከተማን ለማሸነፍ ማድረግ ይኖርባቸዋል። አዲስ አበባ ከተማን አሸንፎ ለመረከብም አንድነት ተኮር የሆኑ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የመተባበር ጉዳይ ምንም ዓይነት ቅድመ ሁኔታ ሊቀርብበት የማይገባና ምትክ የለሽ እርምጃ መሆኑን መገንዘብ አለባቸው። ግለሰብን በመጥላት የሀገርን ጥቅም ጥያቄ ውስጥ ማስገባት ከማንኛውም ኃላፊነት ከሚሰማው ፓርቲ የማይጠበቅ ተግባር ቢሆንም ምናልባት የእኔ ለጊዜውም ቢሆን ከምርጫውና ከትግሉ ሂደት ገለል ማለት ለተቃዋሚው ጎራ መተባበር አንድ ጥሩ አጋጣሚ ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ።

    የአንድነት ኃይሉ ምንም ዓይነት ድምጽ ሊባክን በማይችልበት ሁኔታ እርስ በርስ ላለመፎካከር አስቀድሞ ካልተስማማ በስተቀር፥ ብልጽግና ፓርቲና አጋሮቹ (በፓርቲም ሆነ በግል የሚወዳደሩ) አዲስ አበባን የማሸነፍ ዕድል እንደሚኖራቸው መገንዘብ ያስፈልጋል። ብልጽግና ፓርቲና አጋሮቹ አዲስ አበባን የማሸነፍ ዕድል ካገኙም የአዲስ አበባ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ ጥቅምና ሕልውና አደጋ ውስጥ እንደሚገባ መገንዘብ ያስፈልጋል። በተጨማሪም በምርጫ 97 ሲሆን እንደታየው “ምርጫው ስለተጭበረበረ ያሸነፍነውን ወንበር ወይም ምክር ቤት አንረከብም” በሚል የተሠራው ታሪካዊ ስህተት በዘንድሮውም ምርጫ እንዳይደገም ፓርቲዎች ከወዲሁ በጉዳዩ ላይ መተማመንና መወሰን ይኖርባቸዋል።

    1. መፍትሔው ሁሉን አቀፍ የሆነ የሽግግር ሂደት መፍጠር ነው

    በአሁኑ ወቅት ሀገራችን በሁለት የጎረቤት ሀገራት (በኤርትራና ሱዳን) ሉዐላዊነቷ ተደፍሮ የግዛት ወረራ ተፈጽሞባታል። ይህ ወረራ ከማንኛውም ውስጣዊ ችግሮቻችን በላይ ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጠውና በአስቸኳይ ሊቀለበስ የሚገባው ነው። ይህንን ማድረግ ሳንችል ኢትዮጵያውያን እንደ ሀገርና ሕዝብ የነጻነት ታሪክም ሆነ ሉዐላዊ ሕልውና አለን ብለን መናገር አስቸጋሪ ይሆናል። የወቅቱ መንግሥት በሀገር ውስጥ እየተፈጸመ ያለውን ብሔር ተኮር ጭፍጨፋ ማስቆምም ሆነ የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ማስከበር ስላለመቻሉ የሚያቀርበው ማንኛውም ምክንያትም ተቀባይነት ሊኖረው አይገባም። የወቅቱ መንግሥትም ሆነ መንግሥትን በዋናነት የሚመሩት ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ እነዚህን ሁለት ቁልፍና መሠረታዊ የአንድ መንግሥት ኃላፊነቶች በአግባቡ መወጣት ስላልቻሉ ከእንግዲህ የሚኖራቸው ብቸኛ አማራጭ ችግሩን ለመፍታት የሚያስችል ሀገራዊ የሀሳብ ግብይት ሂደት (national dialogue) መጀመርና ሁሉን ዐቀፍ የሆነ የሽግግር ሂደት ማካሄድ ነው።

    የወቅቱ መንግሥት ቀደም ሲል በኢሕአዴግ ስም፣ አሁን ደግሞ በብልጽግና ፓርቲ ስም ሕዝባዊ ይሁንታ ሳይኖረው ለ30 ዓመታት በሥልጣን ላይ ያለ ኃይል ነው። ይህ መንግሥት የሀገሪቱን መሠረታዊ ፖለቲካዊ ችግሮች መፍታት ካለመቻሉም በላይ ይበልጥ እያባባሰውና እያወሳሰበው ይገኛል። ስለሆነም የወቅቱ ብልጽግና ፓርቲ በአንድ በኩል የሀገሪቱን አንድነትና ሉዓላዊነት ማስከበር ባልቻለበት ሁኔታ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ነጻና ፍትሐዊ ምርጫ አካሒዶ የሕዝብ እውነተኛ ውክልና ለማግኘት በሐቅ ባልተዘጋጀበት ሁኔታ የሀገሪቱን የፖለቲካ ሥልጣን በቋሚ ርስትነት ይዞ ሊቀጥል አይገባውም።

    ገዥው ብልጽግና ፓርቲ ከግለሰብ በላይ የሆነ ሚና አለኝ ብሎ የሚያምንና ድክመቱ የኔ ሳይሆን የመሪዎቼ ወይም የመሪዬ ነው ብሎ የሚያስብ ከሆነም ሀገሪቱ ለይቶላት ከመፍረሷ በፊት መሪዎቹን ወይም መሪውን የመቀየር ርምጃ ሊወስድ ይገባዋል። ይህንን ማድረግ ካልቻለ ግን ለሀገሪቱ ውድቀት ፓርቲውም እንደ ድርጅት ተጠያቂ ይሆናል።

    ከዚህ ውጭ በአንድ ሀገር የዘር ጭፍጨፋን ማስቆምና የውጭ ወረራን መከላከል ያልቻለ ማንኛውም መንግሥት በሥልጣን ላይ መቀጠል የሚችልበት ሕጋዊ፣ ፖለቲካዊም ሆነ ሞራላዊ ምክንያት የለም። ከዚህ በተጻራሪ የዘር ጭፍጨፋን ማስቆምና ሀገሪቱን ከውጭ ወራሪ መከላከል ያልቻለ መንግሥት፥ “ሌላ አማራጭ የለንም” በሚል ሰበብ በሥልጣን ላይ ሊቀጥል የሚችለው ኢትዮጵያ ሕልውናዋን ከጥፋት አድኖ የሚያስቀጥላት ትውልድና ዜጋ ያልፈጠረች መካን ሀገር መሆኗን አምነን ከተቀበልን ብቻ ይሆናል።

    በተጨማሪም በቅርቡ ትግራይ ክልል ውስጥ የገባንበት ጦርነት የሀገሪቱን አንድነት ከፍተኛ ጥያቄ ውስጥ የሚጥልና ከኛ ዘመንም አልፎ ምናልባትም ለልጅ ልጆቻችን የሚተርፍ ጣጣ የሚያስከትል አሳሳቢ ክስተት ነው። ስለሆነም ይህ ችግር በዘላቂነት በጦርነት ሊፈታ እንደማይችል በመገንዘብ ከሥልጣን ጥያቄ፣ ከበቀል፣ ከስሜትና ከጀብደኝነት በራቀ አተያይ ለችግሩ አስቸኳይ ሰላማዊና ፖለቲካዊ መፍትሔ መፈለግ ይኖርበታል።

    1. ሀገሪቱን ከሕልውና አደጋ መታደግ የሚችል ጠንካራ ፓርቲ መፈጠር አለበት

    ኢትዮጵያውያን ሁልጊዜም በሀገሪቱ በጎ የፖለቲካ ለውጥ እንዲመጣ የምንመኝና የምንፈልግ ቢሆንም ይህንን የሁልጊዜ ምኞታችንን ዕውን ለማድረግ የሚያስችል ጠንካራና ለመርህ ታማኝ የሆነ ፓርቲ መፍጠር እስካሁን አልቻልንም። ዛሬም እንደ ትናንቱ የሥርዓቱን ድክመቶችና ጥፋቶች ስንቆጥር የምንውል የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች፣ ምሁራን፣ ጋዜጠኞችና አክቲቪስቶች ብንኖርም ያለጠንካራ ፓርቲ መኖር ሀገሪቱን ከጥፋት መታደግም ሆነ ዘላቂ ለውጥ ማምጣት እንደማይቻል መገንዘብ የቻልን አይመስልም። በምሬት፣ በጩኸትና በውግዘት ብቻ ሊመጣ የሚችል ዘላቂ ለውጥ እንደማይኖር ተገንዝበን ለመጭው ትርጉም የለሽ ምርጫ ከምንሰጠው ትኩረት በላይ ለሀገሪቱ ችግሮች የሚመጥን ጠንካራና ታማኝ ፓርቲ በመፍጠር ሥራ ላይ ማተኮር አለብን። በተለይም አንድነት ተኮር የሆነው የፖለቲካ ኃይል ከመቼውም ጊዜ በላይ በተዳከመበትና በተበታተነበት ሁኔታ ኢትዮጵያን ከጥፋት ለመታደግ የሚያስችል አስተማማኝ ለውጥ ማምጣት እንደማይቻል በመገንዘብ አዲሱ ትውልድ ዋና ተዋናይ የሚሆንበት ጠንካራና ታማኝ ፓርቲ መፍጠር ቀዳሚና ለነገ የማይባል አጀንዳችን መሆን ይገባዋል እላለሁ። ይህንን ማድረግ ካልቻልን “አማራጭ የለም” በሚል ሰበብ አምባገነኖችና የሀገርን ሕልውና አደጋ ላይ የሚጥሉ ፓርቲዎች ወይም መሪዎች ሁልጊዜም በሥልጣን ላይ የሚቀጥሉበትን ዕድል እንፈጥራለን።

    1. የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረት ለሰላም

    የወቅቱ የሀገራችን ፖለቲካዊ ሁኔታ በብዙ ውጥረቶች የተሞላና በቀላሉ ተሰባሪ ነው። በዚህ ምክንያት ውጤታማ በሆነ የሽግግር ሂደት ሳይታለፍ የሚካሄደው መጪው ምርጫ ሀገራችንን ወደ ባሰ ግጭትና ትርምስ ሊያስገባ የሚችልበት ሰፊ ዕድል አለ። ይህ ስጋት በቂ መነሻ ምክንያት ያለው መሆኑን በመረዳት ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች የምርጫ ሂደቱ ወደ ግጭትና ብጥብጥ እንዳያመራ የማድረግ የጋራ ኃላፊነት አለባቸው። ይህንን በመገንዘብ ከፍተኛ ጥንቃቄ የተሞላበትና የሰከነ ሰላማዊ የምርጫ ቅስቀሳ ሊያካሒዱ ይገባል። አሁን ከምንገኝበት እጅግ ከባድና ውስብስ የፖለቲካ ሁኔታ አንጻር የሰላም እጦት የሀገሪቱን ሕልውና የሚፈታተን አደጋ ይዞብን ሊመጣ ስለሚችል፥ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምርጫውን አሸናፊ ለመሆን ከመሥራት በላይ ለሰላም መኖር የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረት መስጠት ይኖርባቸዋል።

    በአግባቡ ካልተጠቀምንበትም በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋ ያለው ማኅበራዊ ሚዲያ የብሔራዊ ደኅንነታችን ዋና የአደጋ ምንጭ ሊሆን ይችላል። ይህንን እውነታ በመገንዘብ ማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ የሆኑ ዜጎቻችን በምርጫው ወቅት የሚኖራቸው ሚና ለሰላም ቅድሚያ በሚሰጥ የኃላፊነት ስሜት ሊካሄድ ይገባዋል። በአጠቃላይ ሀገራችን በአሁኑ ወቅት በውስጥም በውጭም ከፍተኛና አሳሳቢ ውጥረት ውስጥ የምትገኝ መሆኑን በመገንዘብ ለሰላም መኖር የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረት መስጠት ግዴታችን መሆኑን መገንዘብ ያስፈልገናል።

    1. ሕገ-መንግሥቱ ሳይሻሻል የፖለቲካ ችግራችን አይፈታም

    የወቅቱ የሀገራችን የፖለቲካ ችግር የሀገራዊ ብሔርተኞችንና የንዑስ ብሔር ብሔርተኞችን የተካረረ የፖለቲካ ቅራኔ በአንጻራዊነት በሚያቻችል አግባብ የወቅቱን ሕገ-መንግሥት ከማሻሻል ባነሰ ሌላ የመፍትሔ ርምጃ ሊፈታ አይችልም። ሕገ-መንግሥቱ እስካልተሻሻለ ድረስ ከማንነት ጋር በተያያዘ በአሁኑ ወቅት የተነሱትም ሆነ ወደ ፊት ባልተቋረጠ ሁኔታ ሊነሱ የሚችሉ ጥያቄዎች የሀገሪቱን ሰላምና ሕልውና እያወኩ መቀጠላቸው አይቀርም። ይህ ችግር ዘላቂ መፍትሔ እስካላገኘ ድረስም የሀገሪቱ ሰላም፣ አንድነት፣ ሕልውናና የኢኮኖሚ እጥረት በዘላቂነት መፍትሔ ሊያገኝ አይችልም።

    ከዚህ ግንዛቤ ጋር በተያያዘ በኔ በኩል ለውይይት መነሻ የሚሆን የሕገ-መንግሥት አማራጭ ረቂቅ ሰነድ በመጽሐፍ መልክ በማሳተም ላይ እገኛለሁ። የሕገ-መንግሥቱ መሻሻል ለሀገሪቱ የፖለቲካ ችግሮች መፈታት የሚኖረውን ምትክ የለሽ አዎንታዊ አስተዋዕፆ የምትገነዘቡ መገናኛ ብዙኃን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ምሁራንና ዜጎች በረቂቅ ሰነዱ ላይ ውይይት በማድረግ ትችት እንድታቀርቡበትና እንድታዳብሩት፣ ከተቻለም ሰነዱን በመጭው ምርጫም ሆነ በቀጣዩ የትግል ሂደት የጋራ የትግል አጀንዳ አድርጋችሁ እንድትጠቀሙበት በዚህ አጋጣሚ ጥሪዬን አቀርባለሁ።

    በመጨረሻም ከአቅም በላይ በሆነ የጤና ምክንያት ቢሆንም ሀገራችን ከመቼውም ጊዜ በላይ ዋጋ የሚከፍልላት ዜጋ በሚያስፈልጋት በአሁኑ ወቅት ለጊዜውም ቢሆን ከትግል ተሳትፎዬ ለመታቀብ በመገደዴ፥ የትግል አጋሮቼንና የዐላማ ደጋፊዎቼን ሁሉ ከልብ ይቅርታ እጠይቃለሁ። ይህንን የምለው ከእኔ ብዙ እንደምትጠብቁና ለእኔ ለራሴ እንደሆነብኝ ሁሉ ለእናንተም ይህ ክስተት ድንገተኛ መርዶ እንደሚሆንባችሁ ስለምገነዘብ ነው። ወደፊት የጤና ሁኔታዬ ተሻሽሎ እስከመጨረሻው በፖለቲካ ሂደቱ ለመቀጠል ለራሴ የገባሁትን ቃል ለመፈጸም ፈጣሪ ዕድል እንደሚሰጠኝ ተስፋ እያደረግኹ ሀገራችን ኢትዮጵያ መልካሙ ሁሉ እንዲገጥማት ያለኝን ልባዊ ምኞት በዚህ አጋጣሚ እገልጻለሁ።

    ልደቱ አያሌው

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forums) ላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።

    ሀገራችን ኢትዮጵያ ያለችበት የህልውና አደጋ በአቶ ልደቱ አያሌው እይታ

    Anonymous
    Inactive

    ሱዳን በኢትዮጵያ ላይ ያደረገችውን ወረራ አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) የተሰጠ መግለጫ

    “ከድንበሩ ቆሞ ጌታ ካልመለሰው፥
    መሬትም ይሄዳል እግር አለው እንደ ሰው።”

    የሀገራችን ዳር ድንበር በአባቶቻችንና በእናቶቻችን ደምና አጥንት ተለስኖ የተሠራ የማይነቃነቅ አምድ እንጂ፥ እንደ ሰንበሌጥ አጥር ማንም በፈለገው ጊዜ እየጣሰው የሚገባ ድንበር አይደለም። ሀገሩንና ድንበሩን የማያስከብር ሕዝብ ለባርነት እንደተዘጋጀ ይቆጠራል። ለአንድ ዜጋ ሀገርና ድንበር የክብሩ ከፍተኛ መገለጫው ነውና።

    ኢትዮጵያ ሀገራችን በትግራይ ከአሸባሪው የህወሓት ቡድን እንዲሁም በመተከል በኦሮሚያ ክልል ጽንፈኞችን ለማጽዳት ከፍተኛ ግብግብ በምታደርግበት ወቅት፣ ሱዳን ድንበራችንን ተሻግራ ጦሯን ማስፈሯንና በአካባቢው በነበሩ ኢትዮጵያውን ገበሬዎች ላይ ጥቃት መፈጸሟን የተለያዩ የዜና አውታሮች የዘገቡት ሃቅ ነው። አሁን በቅርቡ ደግሞ በምዕራብ አርማጭሆ በደለሎ የገበሬዎችን የእርሻ ምርት ማቃጠሏን በከፍተኛ ቁጭት ሰምተናል። ይህ የሱዳን ድፍረት ማንኛውንም ኢትዮጵያጵያዊ ዜጋ እጅግ የሚያስቆጣ እርምጃ በመሆኑ ሁላችንንም እንቅልፍ የሚነሳ ድፍረት ነው ይላል ኢሕአፓ።

    የድንበር ውዝግቡ ለረዥም ጊዜ እልባት ሳያገኝ የቆየ መሆኑ ቢታወቅም፥ ኢትዮጵያ አንድም ጊዜ ድንበሯን አልፋ አንድ ጋት መሬት ከሱዳን ፈልጋ አታውቅም። ሱዳን ግን አጋጣሚ እየጠበቀች በተደጋጋሚ ከመተንኮስ ቦዝና አታውቅም። በሰላማዊ ጊዜም ከብቶቿን ወደ ኢትዮጵያ መሬት አሻግራ እንዲግጡ በመድረግ፣ ለእጣን የሚሆን ሙጫ በመሰብሰብ፣ ለቤትና ለማገዶ የሚሆን እንጨት እየቆረጠች በመውሰድ የምትፈጽማቸውን ድርጊቶች ኢትዮጵያውያን ገበሬዎች በመቃወማቸው በተደጋጋሚ ስትጋጭ ኖራልች። ኢሕአፓ በአካባቢው በሚንቀሳቀስበት ጊዜም ይህን ለማስቆም ለሱዳን መንግሥት ገበሬዎቻቸው ድንበራችንን እየተሻገሩ የሚያደርጉትን የጥሬ ሀብት ስብሰባና የከብት ግጦሽ እንዲያስቆሙ በተደጋጋሚ ጠይቆ አሻፈረኝ ስላሉ፤ የአካባቢውን የምዕራብ በጌምድርን (መተማ፣ ቋራ፣ ጫቆ) ሕዝብ አስተባብሮ የሱዳንን ጦር በመውጋት ድል አድርጎ የኢትዮጵያን ድንበር አስከብሮ አንደነበረ የሚታወቅ ነው። በዚህም ምክንያት ሱዳን የነበሩ የድርጅቱ አባሎች ለእስርና እንግልት ተዳርገዋል፤ የተወሰኑትንም ለህወሓት በማስረከብ ለሰቆቃ/ግርፋትና እስር እንዲዳረጉ አድርገዋል። ገዳሪፍ የነበረውን የድርጅቱን ጽሕፈት ቤት በርብረው የድርጅቱን ንብረቶች ወስደዋል። ከህወሓት ጋር በመተባበር ኢሕአፓን ከበው ወግተዋል። ህወሓትንም አጅበው አዲስ አበባ አስገብተው ተመልሰዋል።

    ህወሓት እና የሱዳን መንግሥት ከመጀመሪያ ጀምረው የጠበቀ ወዳኝነት እንደነበራቸው ይታወቃል። በደርግ ዘመን ህወሓት ጉልበት ያገኘውና የኢትዮጵያን ጦር አሸነፍኩ ያለው ሱዳን ከፍተኛ መከታና ደጀን ሆና ስለረዳቻቸው ጭምር ነው። ለዚህ ውለታ ሱዳኖች ድንበራችን ጥሰው በደለሎ በኩል ገብተው ኢትዮጵያውያን ገበሬዎችን አፈናቆለው ለረዥም ዓመታት ሲያርሱ ኖረዋል። የአካባቢው ገበሬዎች ድርጊቱን በመቃወም ሲከላከሉ፣ የህወሓት ካድሬዎች “መንግሥትና መንግሥት ይነጋገራል እንጂ ገበሬውን አያገባውም” በማለት ኢትዮጵያውያንን ገበሬዎችን ያስሩና ያንገላቱ ነበር። እውነታው ግን ሱዳን እንደፈለገች የኢትዮጵያን መሬት እንድትጠቀም በነአባይ ፀሐዬ የተሸረበ ሤራ መሆኑ ነው። የገበያ ግርግር ለሌባ ያመቻል እንዲሉ፥ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የህወሓትን አሸባሪ ቡድን ለማፅዳት ጦርነት እያደረገ በነበረበት ወቅት ሱዳን ድንበራችንን ተሻግራ ኢትዮጵያውያን ገበሬዎችን ከማሳቸው ያፈናቀለችው የወዳጇ የህወሓት መመታት ስለከነከናትና በአጋጣሚውም የረጅም ጊዜ ምኞቷን ለማሳካት የወሰደችው እርምጃ ነው።

    ሱዳን ድንበራችንን የጣሰችበት ሌላው ምክንያት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሥራ ለማደናቀፍ እንዲቻል ከሱዳን ጀርባ ተጫማሪ ገፊ ኃይል ሊኖር እንደሚችል መገመት አይቸግርም። ከዚህ በተጨማሪ ህወሓትና የውጭ ደጋፊዎቻቸው ትግራይ ውስጥ የሚደረገውን የሀገር አፍራሹን ቡድን የማጽዳት ዘመቻ ቀጣናዊ መልክ ለማስያዝ የሚጥሩትን እውን ለሜድረግ ሱዳን የጦስ ዶሮ ሆና መቅረቧ አጠራጣሪ አይደለም እንላለን።

    በጦርነቱ ሳቢያ በትግራይ ውስጥ የተጎዳው ሕዝባችን አስፈላጊው እርዳታ እንዲደርሰው መንግሥት እስካሁን እያደረገ ያለው ድጋፍ በተጠናከረ መልክ እንዲቀጥልና የዓለምአቀፍ የሰብዓዊ ድርጅቶችም እርዳታና ድጋፋቸውን በመንግሥት በኩል ለሕዝቡ የሚደርስበትን መንገድ እንዲያመቻች እናሳስባለን።

    የኢትዮጵያ መንግሥት ሱዳን መሬታችንን ለቃ እስክትወጣ ድረስ የሱዳንን ትንኮሳ ጥንቃቄ በተሞላበት በሰላማዊና ዲፕሎማሲያዊ መንገድ በመያዝ ከፍጻሜ ለማድረስ ከፍተኛ ትግል ማድረግ ይኖርበታል። ድንበራችን በቋሚነት የሚከለልበትንም መንገድ እንዲያመቻች እናሳስባለን።

    የኢትዮጵያ ሕዝብ የሀገሩን ዳር ድንበር ለማስከበርና የሀገሩን አንድነት ለማስጠበቅ ሊፋለም እንደሚችል ግልጽ መሆን አለበት። ሕዝባችን በተደጋጋሚ እንዳስመሰከረው ሱዳን ከሀገራችን ክልል እስክትወጣ ድረስ አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ በመሆን፥ ከመከላከያ ሠራዊታችን ጎን እንደሚቆም አንጠራጠርም። ኢሕአፓም በማንኛውም መንገድ ከሕዝባችን ጎን ዘብ ለመቆም ዝግጁ መሆኑን ያረጋግጣል። አባቶቻችን ስለሀገርና ድንበር ሲነሳ እንደ እግር እሳት ሲያንግበግባቸው፦

    “ከደንበሩ ቆሞ ጌታ ካልመለሰው፥
    መሬትም ይሄዳል እግር አለው እንደ ሰው”

    ይሉ ነበር።

    ኢትዮጵያ በልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘለዓለም ትኖራለች!
    የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)
    ጥር 29 ቀን፥ 2013 ዓ. ም.

    ሱዳን ያደረገችውን ወረራ

    Anonymous
    Inactive

    በብልፅግና ሰልፎች ላይ ፓርቲዎች የሚመሩባቸው ሥነ ምግባሮች ተጥሰዋል
    ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰጠ መግለጫ

    ጥር 25 ቀን 2013 ዓ.ም. በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች ለብልፅግና ፓርቲ ድጋፍ ለማሳየት የተለያዩ ሰልፎች መካሄዳቸው ይታወቃል። እነዚህን ሰልፎች ተከትሎ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) “ፓርቲያችን ያለአግባብ ተወንጅሏል፤ ይህም ፓርቲዎች የፈረሙትን የጋራ የሥነ ምግባር ደንብ የጣሰ ነው” ሲል አቤቱታውን ለቦርዱ አቅርቧል። ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም ከአቤቱታው በተጨማሪ በዕለቱ የተደረጉ የተለያዩ ሰልፎችን በሚዲያ ክትትል ክፍሉ አማካኝነት ክትትል በማድረግ በአሜሪካ ድምጽ፣ በዋልታ፣ በፋና፣ በኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ እንዲሁም በእነዚሁ ሚዲያዎች የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች በቀጥታ የተላለፉ መልእክቶችን በማየት፦

    • ሠልፎቹ በዋልታ ቴሌቪዥን እና በኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ በቀጥታ መተላለፋቸውን እንዲሁም የመንግሥት አመራር አካላት፣ የብልፅግና ፓርቲ አመራሮች እና ደጋፊዎች መሳተፋቸውን ተረድቷል፤
    • ከሚዲያዎቹ በቀጥታ ከመተላለፉም በተጨማሪ የተለያዩ የመንግሥት አመራር አባላት በሰልፎቹ ላይ ያደረጓቸውን ንግግሮች ተመልክቷል፤
    • በሰልፎቹ የተለያዩ መፈክሮች፣ በተወሰኑ የመንግሥት የዞን፣ የከተማ አስተዳድር አመራር አካላት እና ብልፅግናና ፓርቲ ኃላፊዎች ንግግሮች በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተመዘገቡ እና የምርጫ ምልክቶቻቸውን የመረጡ ፓርቲዎች በአሉታዊ መልኩ መነሳታቸውን ተገንዝቧል።

    እነዚህ ሰልፎች ላይ የተነሱ ንግግሮች እና መፈክሮች በሕጋዊነት ተመዝግበው፣ በፖለቲካ ፓርቲነት የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎችን ማለትም አማራ ብሔራዊ ንቅናቄባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ እና የኦሮሞ ነጻነት ግንባር በአመፃ ተግባር በመሳተፍ ከምርጫ ቦርድ ከተሰረዘው ጁንታ በማለት ከሚጠሩ ህወሓት ፓርቲ ጋር አንድ በማድረግ፣ የኢትዮጵያ ጠላት ናቸው ብሎ በመፈረጅ እና ሕገ ወጥ ናቸው በማለት የምርጫ፣ ፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና ሥነ ምግባር ሕግ 1162/2011 ላይ ያሉ ድንጋጌዎችን ጥሰዋል።

    ቦርዱ ሰልፎቹ ላይ የተንጸባረቁት ንግግሮች እና መፈክሮች በአዋጁ አንቀጽ 132 ንዑስ 2(ሀ) ላይ የተጠቀሰውን ስም የሚያጠፋ ንግግርን ክልከላ ድንጋጌ አንዲሁም በዚሁ ሕግ አንቀጽ 143 (2) ላይ የተጠቀሰውን ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ሀሳባቸውን በነጻነት እንዳያሰራጩ ስጋት እና ፍርሀት የመፍጠር የሥነ ምግባር ጥሰት ፈጽሞ አግኝቶታል። ከዚህም በተጨማሪ ከላይ ስማቸው የተጠቀሱት የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ገዥው ፓርቲ በጋራ ተስማምተው በፈረሙት የቃልኪዳን ሰነድ አንቀጽ 8 ንዑስ አንቀጽ 1 ላይ የተጠቀሰውን “የሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በየትኛውም ጉዳይ ላይ ሊኖር የሚችል የዓላማ፣ የሃሳብ ወይም የዘር ልዩነትን፣ ወይም ሌላ ምክንያት መሠረት በማድረግ የሌሎች ፓርቲዎችን መብቶች የሚፃረሩ ወይም የሚያጣብቡ ድርጊቶችን ከመፈፀም የመቆጠብ ግዴታ አለባቸው” የሚለውን አንቀጽ የሚጥስ ተግባር ነው።

    ይህ ተግባር በተለይ ቦርዱ የመጨረሻ የጊዜ ሰሌዳ አውጥቶ የምርጫ ተግባራት በይፋ መፈጸም ከጀመረ በኋላ በምንገኝበት የምርጫ ወቅት መከሰቱ በምርጫ ውድድር ላይ ፓርቲዎች በእኩልነት የመወዳደር መብታቸውን ችግር ላይ የሚጥል በመሆኑ ቦርዱን በእጅጉ አሳስቦታል። በመሆኑም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በየደረጃው ያሉ የገዥው ፓርቲ አመራሮች እና በየአስተዳደር እርከኑ ያሉ የመንግሥት ኃላፊዎች በተመሳሳይ ተግባራት ከመሳተፍ እንዲቆጠቡ ያሳውቃል።

    ለወደፊትም በተመሳሳይ በምርጫ፣ ፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና ሥነ ምግባር ሕግ 1162/2011 እና ተያያዥ መመሪያዎች መሠረት የፓርቲዎች የቅስቀሳ የንግግር እና ሌሎች ለሕዝብ የሚያሰራጯቸውን መልዕክቶች ላይ ክትትል በማድረግ አስፈላጊውን እስከእጩ መሠረዝ የሚደርስ አስተዳደራዊ እርምጃ ሊወስድ እንደሚችል ያሳውቃል።

    የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
    ጥር 26 ቀን 2013 ዓ.ም.

    በብልፅግና ሰልፎች ላይ ፓርቲዎች የሚመሩባቸው ሥነ ምግባሮች ተጥሰዋል ― ምርጫ ቦርድ

    Anonymous
    Inactive

    የብልፅግናው ታዬ ደንደዓ … ስለማያወቀው ታሪክ የሚጽፈው ነገርስ ምን ይሉታል?
    (ጋዜጠኛ ፋሲል የኔዓለም)

    ለታላቋ ኢትዮጵያ ተብሎ ዝም ቢባል አሁንስ በዛ። ታዬ ደንደዓ፣ የብልፅግናው ባለስልጣን፣ ስለማያውቀው ታሪክ እየጻፈ የአብይ አህመድን መንግሥት አጣብቂኝ ውስጥ እየከተተው ነው። አብይ አህመድ ህወሓት የቀደዳትን ኢትዮጵያን እንቅልፉን አጥቶ ለመስፋት ይሞከራል፤ ታዬ ደንደዓ እና መሰሎቹ ደግሞ በጎን ይተረትራሉ።

    አብይ አህመድን ለማመስገን የኢትዮጵያን ታሪክ ማጠልሸት አይስፈልግም። አብይ በተደጋጋሚ እንዳለው ነው፤ ኢትዮጵያ ከሱ በፊት በነበሩ መሪዎች እየተገነባች እዚህ የደረሰች አገር ናት።

    ታዬ ደንደዓ ስለ ቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሀብተወልድ የተሳሳተ ታሪክ ጻፈ። በዚህ ስህተቱ ሳያፍር ቀጥሎ ደግሞ የዛግዌንና የዶ/ር አብይን መንግሥት አወዳድሮ ሌላ የማይሆን ታሪክ ጫረ። “ሞኝ ባያፍር፣ የሞኝ ዘመድ ያፍር” ነው ነገሩ።

    ታዬ ከዛገዌ መጨረሻ እስከ አፄ ኃይለሥላሴ ዘመን የነበረውን የነገሥታቱን ዘመን ምንም ሥራ እንዳልሠራ አድርጎ ረገመው። በአጭሩ የደርግን ፕሮፓጋንዳ ደገመው። ዓላማው እነሱ የአማራ መንግሥት የሚሉት የሰሎሞናዊው መንግሥት ምንም እንዳልሠራ በማሳየት አማራን መወረፍ ነው።

    አላዋቂነት የወለደው ድፍረትና ስልጣን የወለደው ትዕቢት ታዬን እያቅበዘበዘው ነው።

    ከዛገዌ በኋላ ሸዋ ላይ የተመሠረተው ታላቅ ስልጣኔ በማን እንደፈረሰ ታዬ የሚያውቅ አይመስልም። አክሱም፣ ዛግዌና የሰሎሞናዊው ስርወ-መንግሥት ስልጣኔዎች የማይነጣጠሉ፣ ተያያዥነትና ተደጋጋፊነት ያላቸው የኢትዮጵያ ታሪኮች መሆናቸውን ለማወቅ የልብ ብርሃን ያስፈልጋል።

    ደግሞ የታሪክ ሒሳብ ማወራረድ ውስጥ ከተገባ በማን እንደሚከፋ ታዬና ቢጤዎቹ ያወቁትም ያሰቡበትም አይመስልም። ደርግ እንዳስወራውና ታዬ እንደደገመው ሳይሆን፥ የኢትዮጵያ ነገሥታት ለእደ ጥበብ ሰዎች አክብሮት ነበራቸው። በሄዱበት ሁሉ ይዘዋቸው ከሚዞሩ ሰዎች መካከል የእደ ጥበብ ባለሙያዎች ይገኙበት ነበር። የኢትዮጵያ ነገሥትታና የሙስሊም ነጋዴዎች ቁርኝት በታሪክ ተመዝግቦ የሚገኝ ነው። ይህ ሲባል እንከን አልነበረም ማለት አይደለም፤ እንኳንስ ትናንት ዛሬም ብዙ እንከኖች አሉ።

    የመካከለኛው ዘመን ነገሥታት የሠሩትን ሥራ ለማወቅ እኮ የዛሬዋን አዲስ አበባ ቆፈር ቆፈር ማድረግ ነው። አንቶን ዲ አባዲ የተባለው ፈረንሳዊው አሳሽ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የቆመበት ቦታ ላይ የነበረውን በመካከለኛው ዘመን የተሠራውን የቤተ ክርስቲያን ፍርስራሽ ዓይቶ አግራሞቱን እንዲህ ሲል ገልጾ እንደነበር Abba Emile Foucher እንዲህ ሲል ጽፏል፦

    Who could have been the architect of such a building? … People who constructed such a building with well-cut stone, linked with mere clay, must have been of another type of civilizations.

    የረርን፣ በራራን፣ ፈጠጋርን፣ ጋሞን፣ ጉራጌን በአጠቃላይ የሸዋን የጥንት ታሪክ ያጠና ሰው፣ የኢትዮጵያ ነገሥታት የኢትዮጵያን ሕዝብ አንድነት ለማጥናት እየዘመቱ፣ በጎን ደግሞ ታላቅ ስልጣኔ ገንብተው እንደነበር ይረዳል። ያው እነዚህ ስልጣኔዎች እንዴት እና በእነማን እንደፈረሱ ዝርዝር ውስጥ አልገባም። ታሪካችን ስለሆነ ከመቀበልና ወደፊት ከመጓዝ ውጭ በታሪክ ‘እኘኘ…’ ስንል አንገኝም። እንደ ታዬ ደንደዓ ዓይነት አምቦጫራቂዎች ከበዙ ግን እውነቱን ከመናገር ወደ ኋላ አንልም።

    ታዬ የዛግዌ መንግሥትን ከአብይ አህመድ መንግሥት ጋር ሲያነጻጻር በተዘዋዋሪ መንገድ የአብይን መንግሥት የኦሮሞ መንግሥት አድርገን እንድንቀበለው እየነገረን ነው። አብይን የሚደግፈው አብዛኛው ሰው የአብይን መንግሥት የኢትዮጵያ መንግሥት እንጅ የኦሮሞ መንግሥት አድርጎ አያየውም። ከተሳሳትኩ እታረማለሁ። እንዲህ ከሆነማ አንዳንዶች “ተረኝነት አለ!” የሚሉት ትክክል ነው ማለት ነው።

    አብይ አህመድ የራሱን መንግሥት የኢትዮጵያ መንግሥት እንጂ የኦሮሞ መንግሥት ብሎ ሲጠራው ወይም ተራው የኦሮሞ ነው በሚል አስተሳሰብ ስልጣን እንደያዘ ሲናገር ሰምቼ አላውቅም። አብይን የደገፉት ሰዎች ሁሉ አብይን በኢትዮጵያዊነት እንጂ በኦሮሞነት የሚስሉትም አይመስለኝም። አብይ ከኦሮሞ ነገድ ቢወጣም፥ ስልጣን የያዘው በኢትዮጵያዊነቱ እንጂ የስልጣን ተራው የኦሮሞ ስለሆነ አይደለም። ስልጣን በብሔር ተራ ተከፋፍሎ ከሆነማ ኦሮሞ በየትኛው የዕጣ ድልድል ነው ከሶማሌ፣ ከአፋር፣ ከጋምቤላ፣ ከአማራ ወይም ከጉራጌ ቀድሞ ስልጣን የያዘው? እስኪ ዕጣው መቼ እንደወጣና እንዴት እንደወጣ ንገሩን?

    የእነ ታዬ ደንደዓ አመለካከት በጣም አደገኛ የሚሆነው በምርጫ ቢሸነፉ፣ እንደ ህወሓቶች ሁሉ፣ “ኦሮሞ መሪ ካልሆነ ወይም በእጅ አዙር ካልገዛ ስልጣን አንለቅም” የሚሉ መሆናቸው ነው። ስልጣንን በብሔር መንጽር ማየት ኢትዮጵያዊነትን ማዳከም ብቻ ሳይሆን፣ የብሔር አምባገነንነትም ይፈጥራል። ዋ!

    የታዬ አስተሳሰብ ያላቸው ብዙ የኦሮሞ ብሔርተኞች መንግሥት ውስጥ እንዳሉ ይታወቃል። ዶ/ር አብይ አህመድ ከእነዚህ በብሔር ከሚያስቡ ሰዎች በላይ ከፍ ብሎ የሚበር ስልጡን ሰው እንደሆነ በግሌ አስባለሁ። ስለኢትዮጵያ ታሪክ ያለው አመለካከትም ከብዙዎቹ የተለየና በእውቀት ላይ የተመሠረተ ነው። አብይ እንደነ ታዬ ደንደዓ በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ አያላግጥም። በአላዋቂነት ድፍረትም ሆነ በስልጣን ግብዝነት የማያውቀውን ታሪክ ሲዘባርቅ ሰምቼው አላውቅም። አብይ ንባብ ከአላዋቂነት ድፍረት ነጻ ያወጣው ሰው ነው።

    የኦሮሞ ብልፅግና ውስጥ እንደ አብይ አህመድ ንባብ ነጻ ያወጣቸው አርቀው የሚያዩ ስንት ሰዎች አሉ? ስለአንድ አብይ ብለን የኦሮሞ ብልፅግናን ሁሉ ይቅር እንበለው ወይስ ስለኦሮሞ ብልፅግና ብለን አንድ አብይ አህመድን እንርገመው የሚለውን ጥያቄ መመለሱ ከባድ እየሆነ ነው።

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forums) ላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።

    የብልፅግናው ታዬ ደንደዓ

    Anonymous
    Inactive

    ከባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) የአዲስ አበባ እና ድሬድዋ ከተማ አስተዳድሮች ድምጽ መስጫ ቀንን በተመለከተ የተሰጠ መግለጫ

    ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ6ኛው ሀገር አቀፍ የመጨረሻ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ በአዲስ አበባ እና ድሬድዋ ከተማ አስተዳድሮች ምክር ቤቶች እና ለፌደራል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ድምጽ መስጫ ቀን በሳምንት ወደፊት መገፋቱን በተመለከተ የፓርቲያችንን ቅሬታ በጽሁፍ ለቦርዱ አስገብተናል።

    ቦርዱ በደብዳቤ ላስገባነው ቅሬታ ተገቢውን ምላሽ ሳይሰጥ፥ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማጽደቁን በማኅበራዊ ሚዲያ ገፁ ታኅሣሥ 30 ቀን፥ 2013 ዓ.ም.  (January 8, 2021 G.C.) አሳውቋል። ፓርቲያችን ቦርዱ የድምጽ መስጫውን ቀን በአዲስ አበባ እና ድሬድዋ ብቻ ከሀገሪቱ የምርጫ ቀን በሳምንት ዘግይቶ እንዲደረግ ስለመወሰኑ የሰጣቸውን አስተዳደራዊ ምክንያቶች ፓርቲያችን መርምሯል። ቦርዱ ያቀረባቸውን የሚከተሉትን ምክንያቶች ፓርቲያችን ባልደራስ አሳማኝ ሁነው አላገኛቸውም።

    ቦርዱ የሰጣቸው ምክንያቶች የሚከተሉት ናቸው፡-

    1. የምርጫ አስፈፃሚዎች በአንድ ጊዜ የአንድ ምርጫ አካባቢ የምርጫ ውጤትን ወደ ማዕከሉ መላክ ይችላሉ፤ ከዚህ በላይ ከሆነ ግን ስህተት ሊፈፀም ይችላል፤
    2. መራጮች ካለምርጫ ካርድ ሊመርጡ ይችላሉ፤
    3. ወደ ሌሎች አካባቢዎች የተሰማሩ የምርጫ ቦርድ አስፈፃሚዎች እና የፓርቲዎች የምርጫ ታዛቢዎች ውጤቱን አጠናቅረው ወደ አዲስ አበባ እና ድሬድዋ አስኪመለሱ ድረስ ጊዜ ይፈጅባቸዋል።

    [1ኛ] የምርጫ አስፈፃሚዎች በሁሉም የምርጫ አካባቢዎች በበቂ መጠን እንዲሰማሩ ማድረግ የምርጫ ቦርድ ተግባር ነው። የምርጫ የአስፈፃሚዎች ቁጥር ከምርጫ አካባቢዎች ጋር ተመጣጣኝ እንዲሆን ማድረግ እየተቻለ፥ በአንድ ጊዜ ከአንድ በላይ የምርጫ አካባቢ ውጤትን ወደ ማዕከል መላክ አይቻልም የሚል ምክንያት ውሃ አይቋጥርም።

    [2ኛ] ‘መራጮች ካለምርጫ ካርድ ሊመርጡ ይችላሉ’ የሚለው የቦርዱ አባባል ምንም ስሜት የማይሰጥ እና አሳፋሪ ነው። የምርጫ ቦርድ አስፈፃሚዎች እና የምርጫ ታዛቢዎች የምርጫ ድንጋጌዎች ተግባራዊ መሆናቸውን መከታተል ካልሆነ ሌላ ምን ሊሠሩ ነው?

    [3ኛ] ሌሎች አካባቢዎች የተሰማሩ የቦርድ የምርጫ አስፈፃሚዎች እና የፓርቲዎች የምርጫ ታዛቢዎች ወደ አዲስ አበባ እስኪመለሱ ጊዜ ይወስድባቸዋል በሚል የቀረበው ምክንያትም በኢትዮጵያ ውስጥ የሰው ኃይል እጥረት ያለ የሚያስመስል ነው። ሲጀመር ለሁሉም አካባቢ በቂ ቁጥር ያላቸው የምርጫ አስፈፃሚዎችን እና የምርጫ ታዛቢዎችን ለማሰማራት ምን የሚያስቸግር ነገር አለ?

    አሁንም ፓርቲያችን በተለይ በሁለት ዋነኛ ምክንያቶች የአዲስ አበባ እና የድሬደዋ አስተዳደሮች ድምጽ መስጫ ቀን ከፌደራል ድምጽ መስጫ ቀን የተለየ እንዲሆን መደረጉ (ማለትም ከግንቦት 28 ቀን 2013 ወደ ሰኔ 5/2013 እንዲዛወር መደረጉ) የገዥውን ፓርቲ ፍላጎት ብቻ ከግምት ውስጥ ያስገባ ነው። ሕዝቡ ነፃ ፍላጎቱን ያለ ተፅዕኖ እንዲገልፅ የሚያደርግ አይደለም።

    በባልደራስ በኩል የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ከተሞች ምርጫ ከሌላው ሀገራዊ ምርጫ በአንድ ሳምንት መገፋቱ፣

    1ኛ. በሕገ ወጥ መንገድ ኦህዴድ/ብልፅግና ከከተማው ነዋሪ ውጪ መታወቂያ ካርድ የሰጣቸው ግለሰቦች ግንቦት 28 ባሉበት አካባቢ ከመረጡ በኋላ በሳምንቱ ሰኔ 5/2013 ካሉበት ቦታ ወደ አዲስ አበባ ተመልሰው በአዲስ አበባ መታወቂያቸው ዳግም ምርጫ ማድረግ እንዲችሉ የታቀደ እንደሆነ፣

    2ኛ. ከሳምንት በኋላ በሚደረገው ምርጫ ተቃዋሚዎችን ሊመርጥ የሚችለውን መራጭ ሕዝብ በብሔራዊ ምርጫው ውጤት ተስፋ ቆርጦ በሳምንቱ በሚካሄደው የከተሞች ምርጫ እንዳይሳተፍ የሥነ ልቦና ተፅዕኖ ውስጥ እንዲገባ እና ለመምረጥ እንዳይተጋ ለማድረግ የተመረጠ ዘዴ እንደሆነ እናምናለን።

    ቦርዱ ባልደራስ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ፓርቲዎች ላስገቡት ቅሬታ መልስ ሳይሰጥ ታኅሣሥ 30 ቀን፥ 2013 ዓ.ም.  (January 8, 2021 G.C.) የምርጫ ሰሌዳው የመጨረሻ ተብሎ ለሕዝብ ይፋ ማድረጉ ፓርቲያችንን በእጅጉ ያሳዘነ ጉዳይ ነው። ቦርዱ የፓርቲያችንን ፍትሃዊ ስጋት ወደ ጎን በማለት በምርጫው ላይ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ በሀገራችን የዴሞክራሲ ሥርዓትን ለማዋለድ ለሚደረገው ትግል የማይጠቅም መሆኑን ፓርቲያችን ከልብ ያምናል። ስለሆነም በዚህ ጉዳይ ላይ ያቀረብነው ፍትሃዊ ጥያቄ ምላሽ አግኝቶ አዲስ አበባ እና ድሬድዋ ከተሞች የድምጽ መስጫ ቀን በተመሳሳይ ቀን፥ ማለትም ግንቦት 28 ቀን 2013 ዓ.ም. እንዲሆን በድጋሚ እንጠይቃለን። ቦርዱ አሳማኝ ባልሆኑ ምክንያቶች የደረሰበትን ውሳኔ እንደ ገና በማጤን እንዲያሻሽለው ፓርቲያችን ጥሪውን ያቀርባል። ቦርዱ ይህን የፓርቲያችንን ፍትሃዊ ጥያቄ ገፍቶ ቢያልፈው ግን ቀጣዩ ምርጫ እና እሱን ተከትሎ ሊፈጠር ለሚችለው የተቀባይነት ችግር ቦርዱ ከወዲሁ ኃላፊነቱን የሚወስድ መሆኑን ያሳውቃል።

    እንዲሁም፥ ከምርጫው ጋር በተያያዘ አዲስ አበባ ላይ ለምርጫ አስፈፃሚነት ቦርዱ ካቀረባቸው 64 ግለሰቦች ውስጥ 47ቱ የሕዝብ አመኔታ ከሌላው ብቻ ሳይሆን ባለፉት 27 ዓመታት ከህወሓት ትዕዛዝ እየተቀበለ የአማራውን ሕዝብ ቁጥር በመቀነስ ለፅንፈኛ ሥርዓቱ በታማኝነት ሲያገለግል ከነበረው የ“ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጄንሲ” እና 15ቱ ደግሞ “ሥራ ፈላጊ ኮሚሽን” ተብሎ ከሚታወቀው የካድሬዎች መጠራቀሚያ ተቋም መሆናቸውን በተመለከተ ለቦርዱ በፅሁፍ ቅሬታችንን ያስገባን መሆኑን እየገለፅን፤ ይህን ጉዳይ በተመለከተ ፓርቲያችን በተከታታይ በሚያወጣው መግለጫ የተቃውሞውን ዝርዝር ይፋ የሚያደርግ መሆኑን ይገልፃል።

    የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ

    አዲስ አበባ እና ድሬድዋ

Viewing 15 results - 1 through 15 (of 61 total)