-
Search Results
-
2ተኛው አረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር በይፋ ተጀመረ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – ሁለተኛው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ኡመር ሁሴን፣ የደቡብ ብ/ብ/ሕ/ክልላዊ መንግሥት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው፣ ሌሎች ሚኒስትሮች፣ ሚኒስትር ዴኤታዎች እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የፌደራልና የክልል አመራሮች፣ የአካባቢው ማኅበረሰብ ተወካዮች በተገኙበት የ2012 ዓ.ም የ5 ቢሊዮን የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ አርብ ግንቦት 28 ቀን 2012 ዓ.ም. በሀዋሳ ከተማ በታቦር ተራራ በይፋ ተጀምሯል።
የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ባስጀመሩበት ወቅት ኢትዮጵያ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት 20 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል አቅዳ እየሠራች እንደሆነ ገልፀዋል።
ባለፈው ዓመት የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር 84 በመቶ መፅደቁን አስታውሰው፥ ዘንድሮ የታቀደውን 5 ቢሊዮን ችግኝ ተከላ ግቡን ለማሳካት ለኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ (ኮቪድ-19) አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ግቡን ማሳካት ከእያንዳንዱ ዜጋ እንደሚጠበቅ አሳስበዋል።
በዘንድሮ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በደቡብ ክልል በ227 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ 1.5 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል የታቀደ ሲሆን፥ ወይራ፣ ዋንዛ፣ ዝግባ እና የአበሻ ፅድ የመሳሰሉት ሃገር በቀል ችግኞች የሚተከሉ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።
በዓለም ለ47ተኛ ጊዜ በሀገራችን ለ27ተኛ ጊዜ የሚከበረው የአለም የአካባቢ ቀንም (World Environment Day) “አካባቢን መጠበቅ የብዝሃ-ህይወትን በመጠበቅ ነው” በሚል መሪ-ቃል ከ2012 ዓ.ም አገር አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር ጋር እየተከበረ ይገኛል። በዓለም አቀፍ ደረጃ የዘንድሮው መሪ ቃል “ለተፈጥሮ ጊዜ እንስጥ” (‘Time for Nature’) የሚል ነው።
ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት “40 ዛፍ በነፍስ ወከፍ” በሚል መሪ ቃል ሀምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም 200 ሚሊዮን ችግኞችን በአንድ ጀምበር ለመትከል አቅዳ 353 ሚሊዮን 633 ሺህ 660 ችግኞች ተተክሎ የዓለም ክብረ ወሰን መያዟ የሚታወስ ነው።
አምና 4 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ በአጠቃላይ 4.7 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መትከል የተቻለ ሲሆን 23 ሚሊዮን ሕዝብ መሳተፉም ይታወሳል። በቀጣም የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ በየዓመቱ የሚካሄድ ይሆናል ተብሏል።
ምንጭ፦ የግብርና ሚኒስቴር/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሞታ በተገኘችው ተማሪ (ሃይማኖት በዳዳ) የተጠረጠረው ግለሰብ በቁጥጥር መዋሉን ፖሊስ አስታወቀ
አዲስ አበባ (ኢፕድ) – ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ውስጥ የተገደለችው የወጣት ሃይማኖት በዳዳ ተጠርጣሪ ገዳይ በቁጥጥር ስር መዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ። የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በቁጥጥር ስር ያዋለው የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪ የሆነውና በ20ዎቹ እድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ ደግነት ወርቁ የተባለ ወጣት ሲሆን፥ ወጣት ደግነት ወርቁን ፖሊስ የ27 ዓመቷን ሃይማኖት በዳዳ ሕይወት በማጥፋት ጠርጥሮት በቁጥጥር ስር አውሎታል።
ግንቦት 20 ቀን 2012 ዓ.ም. ከምሽቱ አንድ ሰዓት ላይ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት ባካሄደው ክትትል ነው ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ስር የዋለው። ቀን ከሌሊት በተካሄደው በዚህ ክትትል የተያዘው ወጣቱ ደግነት ወርቁ ከሟች ጋር ምንም ዓይነት ትውውቅ እንዳልነበራቸው በቁጥጥር ስር በኋላ ለሰዓታት በተደረገ ምርመራ የወንጀሉን ዝርዝር ለፖሊስ አስርድቷል።
ግለሰቡ የ12ኛ ክፍል ተማሪ እንደነበርና የኤች አይ ቪ ኤድስ መድኃኒት ለማግኘት ምርምር ላይ ስለሆንኩ የጥቁር አንበሳ ሐኪሞች ይርዱኝ በማለት ወደ ግቢው በተለያዩ ጊዜያት ይመላለስ እንደነበር ዘርዝሯል። ከዚያም በግንቦት 17 ቀን 2012 ዓ.ም. እንደልማዱ ለዚሁ ጉዳይ እንደመጣ ገንዘብ እንደተቸገረና ቢላዋ ይዞ በግቢው ውስጥ ከሚገኙ ቢሮዎች በአንዱ ላፕቶፕ ወይም ሞባይል ካገኘ ሰርቆ ሽጦ ለመጠቀም ሲዟዟር የሟች ክፍል ክፍት በመሆኑ መግባቱን አስረድቷል። ሟች ሃይማኖት በዳዳ ሞባይሏን እንድትሰጠው ጠይቋት እምቢ ስትለው መታገላቸውንና ከዚያም በያዘው ስለት ወግቷት ንብረቱን ይዞ መውጣቱን ተናግሯል።
ፖሊስ ከሟች ጋር የቅርብ ግንኙነት የነበራቸው 12 ተጠርጣሪዎችን ይዞ ተጨማሪ ምርመራ ማድረጉን የግድያ ወንጀሎች ምርመራ ዳይሬክቶሬት ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን (ኢቲቪ) ገልጿል። ለፖሊስ ምርመራ ትልቅ አቅም የሆነው የሟች ወላጅ አባት ከሳምንት በፊት ለልጃቸው የሰጧት የ5 ሺ ብር ቼክ ነው።
ገዳዩ በወቅቱ የሟችን ላፕቶፕና ሞባይል ፓስፖርት መታወቂያና ይህንን ቼክ ወስዶ ስለነበር ቼኩን የካ አካባቢ በአንድ ባጃጅ ተሳፍሮ አሽከርካሪውን መታወቂያ ስላልያዝኩ በአንተ መታወቂያ ይህንን ብር አውጣልኝ ብሎት የባጃጁ ሹፌርም (አቶ እንዳለማው ታረቀኝ) መልኩን አስተውሎ ስለነበር ምርመራው ከዚህ እንደጀመረ ፖሊስ ገልጿል፡
ኮሚሽኑ በወቅቱ የሆስፒታሉ የደኅንነት (security) ካሜራ ከአገልግሎት ውጪ መሆኑን (‘update’ እንዳልተደረገ) እና የጥበቃ ሠራተኞችም ቢላዋ ተይዞ እስከሚገባ ፍተሻቸው አጋላጭ መሆኑንም ጠቁሟል ሲል የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) ዘግቧል።
ሃይማኖት በዳዳ ማነች?
ወጣት ሃይማኖት በዳዳ ተወልዳ ያደገችው መተሃራ ከተማ ሲሆን፥ ወላጆች በአሁኑ ወቅት በአዳማ ከተማ ጎሮ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ይኖራሉ። በ2009 ዓ.ም. ከሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ በ’ክሊኒካል ፋርማሲ’ የመጀመሪያ ዲግሪዋን በማዕረግ ያገኘች ሲሆን፥ በዚያው በተማረችበት ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት ስታገለግል ነበር። ከዚያም በ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የጤና ሳይንስ ኮሌጅ የሁለተኛ ዲግሪዋን በመከታተል ላይ እንደነበረች አባቷ አቶ በዳዳ ፈይሳ ተናግረዋል።
የሃይማኖት አባት አቶ በዳዳ ፈይሳ ልጃቸው 2009 ዓ.ም ከሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ በ’ክሊኒካል ፋርማሲስት’ በማዕረግ ተመርቃ በዩኒቨርስቲው በመምህርነት ስታገለግል መቆየቷን ያስታውሳሉ። ከዚያም ሁለተኛ ዲግሪዋን ለመማር ወደ ጥቁር አንበሳ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ተልካ ትምህርቷን በመከታተል ላይ እንደነበረች ይናገራሉ።
ምንጮች፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት (ኢፕድ) እና ቢቢሲ አማርኛ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – ከነሐሴ ወር 2010 ዓ.ም. ጀምሮ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሆነው ያገለገሉት ዶ/ር አብርሃም በላይ በጥር ወር 2012 ዓ.ም. የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ሆነው መሾማቸውን ተከትሎ በምትካቸው አቶ አሸብር ባልቻ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው ተሹመዋል።
በጥር ወር 2012 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሆነው ከነሐሴ ወር 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ያገለገሉት ዶ/ር አብርሃም በላይ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ሆነው መሾማቸውን ተከትሎ አቶ አሸብር ባልቻ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው ተሹመዋል።
በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን አምቦ ከተማ በ1973 ዓ.ም. የተወለዱት አቶ አሸብር የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በዚያው በአምቦ አዲስ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በአምቦ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል።
የከፍተኛ ትምህርታቸውን ደግሞ በቀድሞ የአርባ ምንጭ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት፤ በአሁኑ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተከታትለው 1995 ዓ.ም. ላይ በሜካኒካል ኢንጂነሪንግ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ተቀብለዋል። ከግሪንዊች ዩኒቨርሲቲ (Greenwich University) በዓለምአቀፍ ቢዝነስ የማስተርስ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል። ከስዊዲን ሀገር ኬ. ቲ. ኤች ሮያል ኢንስቲትዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ (KTH Royal Institute of Technology) በዘላቂ ኢነርጂ ምህንድስና ዘርፍ ተጨማሪ ኮርሶችን ወስደዋል።
አቶ አሸብር በሜካኒካል ምህንድስና ከተመረቁ በኋላ በበደሌ ቢራ ፋብሪካ ጀማሪ ሜካኒካል ኢንጂነር የሥራ መደብ ላይ ለ7 ወራት አገልግለዋል። ከነሐሴ 1996 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ተቀጥረው በጊምቢ–መንዲ–አሶሳ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክት ሥራቸውን ጀምረዋል። በተከዜ የውሃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ከጥር ወር 1997 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ግንቦት ወር 2003 ዓ.ም. ድረስ መሪ መካኒካል ኢንጂነር ሆነው የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎችን በመቆጣጠር ተቋሙን አገልግለዋል።
ከግንቦት 2003 ዓ.ም. እስከ መስከረም ወር 2012 ዓ.ም. ድረስ የገባ የውሃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ በመሆን ካገለገሉ በኋላ ከጥቅምት ወር 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ይህን ኃላፊነት እስከተቀበሉበት ቀን ድረስ የኃይል ማመንጫዎች ግንባታ ሥራ አስፈፃሚ ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተዋል።
አቶ አሸብር ባልቻ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልን በተለያዩ የሥራ መደቦች በባለሙያነትና በኃላፊነት ለ16 ዓመታት አገልግለው ከየካቲት 09 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ተቋሙን በዋና ሥራ አስፈፃሚነት እንዲመሩ በተቋሙ የሥራ አመራር ቦርድ ተሹመዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ዶ/ር አብርሃም በላይ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሥራ አመራር ቦርድን እንዲመሩ ተጨማሪ ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል።
ዶ/ር አብርሃም እስካሁን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ወደትክክለኛው መስመር እንዲመጣና እንዲፋጠን ከፍተኛ ክትትልና ድጋፍ ሲያደርጉ ቆይተዋል። በተለይም በኢፌዲሪ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ሜቴክ ተይዘው የነበሩ ሥራዎች ልምድ ላላቸው ዓለም አቀፍ ተቋራጮች እንዲሰጥና ተቋራጮቹም በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ እንዲሰሩ በማድረግ በኩል ጉልህ የአመራር ሚና ነበራቸው። የገናሌ ዳዋ 3 የውሃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የካሳ ጥያቄ እልባት አግኝቶ ለምርቃት እንዲበቃም ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።
ቢተገበሩ ወጪ ከማውጣት ባለፈ ውጤታማ የማይሆኑ ረዥም ዓመታት የወሰዱ ፕሮጀክቶች በህጋዊ መንገድ እንዲቋረጡ በማድረግ ተቋሙንና መንግስትን ከተጨማሪ ወጪ ማዳን ችለዋል። በተጨማሪም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጤናማ የፋይናንስ አቅም እንዲኖረው በማድረግና በተቋሙ የአሰራር ስርዓቶችን በማሻሻል ተጨባጭ አምጥተዋል።
የተቋሙን የዕዳ ጫና በተመለከተ ተቋሙ የሚመለከተውን ብድር ብቻ እንዲሸከምና ሌሎች ብድሮች ግን ወደ ብድሩ ባለቤቶች እንዲተላለፉ የሚያስችል ቁርጠኛ አቋም በመያዝ የብድር ጫናው እንዲቀንስ አድርገዋል።
በመሆኑም በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የተጀመረው ለውጥ እንዲቀጥል በማሰብ እና በተቋሙ ላከናወኑት ሥራ እውቅና ለመስጠት ተቋሙን በሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢነት እንዲመሩ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ተጨማሪ ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል።
ዶ/ር አብርሃም ባሳዩት ውጤት በተቋሙ አመራር እና ሰራተኞች ዘንድ ተወዳጅ የነበሩና የለውጥ መሪ ተምሳሌት ተደርገው የሚወሰዱ ነበር። የተቋሙ አመራርና ሠራተኞችም ዶ/ር አብርሃም በሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢነት ዳግም ወደተቋሙ በመምጣታቸው ደስታቸውን ገልፀዋል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
በየትኛውም ወገን የሚፈፀም፣ ሥርዓት አልበኝነት በቃ ለማለት ጊዜው አሁን ነው!
ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫየኢትዮጵያውያን የፍትህ የእኩልነትና የዴሞክራሲ ጥያቄ በርካታ አስርት ዓመታትን ያስቆጠረ ብቻ ሳይሆን የአያሌ ዜጎችን ሁለንተናዊ መስዋዕትነት የወሰደ ረጅም ጉዞ ነው። በተለይ ባለፉት አምስት ዓመታት የሁሉንም ተሳትፎ ያማከለና አገዛዙ ከሚቋቋመው በላይ የሆነ ንቅናቄ የታየበት ትግል ተደርጓል። ውጤቱም የዛሬዋን ሁኔታ ወልዷል።
ከበርካታ የዓለም ሀገራት ተሞክሮ እንዳየነው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ማዋለድ ከባድ ምጥ ያለበት የጭንቅ ጊዜ ማሳለፍ የግድ መሆኑን ነው። በኢትዮጵያችንም እያየን ያለነው ይህንኑ ነው። በእንደዚህ ዓይነት አስጨናቂ ወቅት ይህን ሂደት እንደአንድ ከባድ ታሪካዊ ኃላፊነት ወስደው የሚሠሩ የመኖራቸውን ያህል ግርግር ፈጥረውና የራሳቸውን ፍላጎት በኃይል ለመጫን የሚፍጨረጨሩ ቡድኖችና ግለሰቦች መኖራቸውን በየእለቱ በየቦታው የምናየው አሳዛኝ ክስተት ሆኗል።
ፓርቲያችን ከተመሠረተ ጀምሮ ለሀገር ሠላምና ለሕዘብ መረጋጋት የራሱን ያልተቆጠበ አሥተዋፅዖ እያበረከተ ይገኛል። በእኛ ዕምነት የተያዘው የሽግግር ሂደት ለአንድ ወገን የማይተውና የሁሉንም ተሳትፎ የሚጠይቅ እንደሆነ እናምናለን። ያም ሆኖ በዚህ ፈታኝ ወቅት የመንግሥት ሚና ትልቅና ከፍተኛ እንደሚሆን እንገነዘባለን።
ፓርቲያችን በሀገር አቀፍ ደረጃ የተከሠቱ ፈታኝ ሁኔታዎችንና የመንግሥትን ምላሽ በመገምገም በሚከተሉት ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያለውን አቋም ይገልፃል።
- የየትኛውም በኢትዮጵያ ሀገረ-መንግሥት ግዛት ውስጥ የሚንቀሳቀስ ቡድንም ሆነ ግለሰብ ተግባር የሀገራችን ሕጎ እና ሀገራችን ያፀደቀቻቸውንና የተቀበለቻቸውን ድንጋጌዎች ባከበረ መልኩ ብቻ እንዲሆን ማድረግ የሚገባን ዛሬ ነው። ዜጎች በሕግ ጥበቃ እንደሚደረግላቸው ካልተረጋገጠላቸው እና ከሕግ በታች መሆናቸውን ካልተረዱ ማንም እየተነሳ የፈለገውን አድርጎ “አልጠየቅም” የሚል ማንአለብኝነት ከሠፈነ መቼም ማቆሚያ ወደማይኖረው የሁከት ዓለም ጅው ብሎ እንዳይገባ ያሠጋል።
- የሁሉም የፖለቲካ አስተሳሰቦችን በነፃነት እና በሠለጠነ መንገድ መግለፅ፣ በሥልጣን ላይ ያለውንም ሆነ ሌሎች ፓርቲዎችን መተቸት፣ ማጋለጥ አልፎም በምርጫ ከሥልጣን ማውረድ የተለመደና ተገቢም ሊሆን ይችላል። ሀገርን የሚያዋርድ ተግባር መፈፀም ግን ለማንም ያልተፈቀደ የሀገር ከህደት ወንጀል መሆኑ በግልፅ ሊታወቅ ይገባል። በሕዝብ፣ በሃይማኖቶች፣ በብሔረሰቦች፣ በሰንደቅ ዓለማና በመሳሰሉት የአገር መገለጫዎች ላይ የሚፈፀም ማንኛውም የነውር ተግባር አስተማሪ የሆነ ቅጣት የሚያስከትል መሆን አለበት።
- ለዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የሚሠጠው ትኩረት ከዚህ በፊት ከነበረው የተለየና ከወቅቱ የፖለቲካ ትኩሳት የሚጠብቃቸው መሆን እደሚገባው እናምናለን። በሁሉም የሀገራችን ክፍሎች ባሉ ዩኒቨርስቲ ግቢዎች የተከሠቱ ችግሮች የሕዝባችንን ልብ ሰብረው ያለፉ ክስተቶች ናቸው። ከሁሉም በላይ በደንቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ይማሩ የነበሩ ተማሪዎች ላይ የተደረገው እገታ ውሉ የጠፋና የመንግሥትን የተማሪዎችን ህይወት የመጠበቅ ኃላፊነት አለመወጣት ያጋለጠ ነው። ከዚህ ቀደም መንግሥት ስለለተማሪዎቹ እገታ ወቅቱን የጠበቀ እና ትክክለኛ መረጃ ለተማሪዎቹ ቤተሰቦች እና ለሕዝብ እንዲሰጥ ኢዜማ መጠየቁ ይታወሳል። ሆኖም መንግሥት ትክክለኛ እና ወቅታዊ መረጃ የመስጠት ከፍተኛ ክፍተት ታይቶበታል። ከዚህ አንጻር መንግሥት ተማሪዎቹን ከእገታ የማስለቀቁን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጣ እና የሕዝብን ልብ እንዲያሳርፍ አበክረን እንጠይቃለን።
- “በየትኛውም አካባቢ የሚፈጸም ግፍ ለየትኛውም አካባቢ ለሚገኝ ሰላም ጠንቅ ነው” እንዲሉ፥ ለተማሪዎቻችን የመቆም ጉዳይ የአንድ ወገን ወይም የአንድ ክልል ጉዳይ ሊሆን አይገባውም። የሁላችንንም ተናብቦ መሥራት ግድ ይላል። ከዚህ አንጻር የታገቱ ልጆቻችንን በሰላም ለማስለቀቅ ሕግ እና ሥርዓትን በተከተለ መልኩ በሀገራችን በሁሉም አካባቢዎች በሕዝባችን የሚደረጉ ሀቀኛ ጥረቶችን እንደግፋለን።
- ሀገርን እና ሕዝብን የማወክ አንድ አካል የሆነው የሞጣ መስጂዶችን የማቃጠል ድርጊት በአጥፊዎቹ ላይ አስተማሪ ርምጃ ተወስዶ ለሕዝብ ይፋ እንዲደረግ፤ መስጂዶቹን አድሶና ምዕመናኑን ክሶ ወደቀድሞው ሰላማዊ አገልግሎት ለመመለስ የሚደረጉትን የአብሮነት እንቅስቃሴዎችን እንደግፋለን።
- በቅርቡ የጥምቀት በዓል አከባበር ወቅት በተወሰኑት አካባቢዎች በተለይም በአቦምሳ የከተራ በዓል ሳይከበር የቀረበትን ሁኔታ ታዝበናል። የጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊ ይዘቱን ጠብቆ እንዳይከበር እንቅፋት የሆኑ አካላትም ለሕግ እንዲቀርቡና ተገቢ ቅጣት እንዲያገኙ እንጠይቃለን።
- ኢዜማ የምርጫ ወረዳዎችን አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች እንደዚሁም ሕዝባዊ ውይይቶች በሚያካሄድበት ጊዜ ጥቂት ሥርዓት አልበኞች የሚፈጥሩት ግርግር ሕዝብን የሚወክል እንዳልሆነ ብንረዳም በአጠቃላይ የፖለቲካ ድባቡ ላይ የሚፈጠረው የስሜት መሻከር ያሳስበናል። በተለይም ወደምርጫ ለመግባት ዝግጅት እያደረግን ነው በሚባልበት በዚህ ወቅት ሕዝቡ ሕገመንግሥታዊ የሆነውን የመሰብሰብ መብቱን መጠቀም የማይችልበት ሁኔታ ይታያል። ባሳለፍነው ሳምንት በተከሠቱ በተለይ የጎንደር እና የሸዋሮቢት ድርጊቶችን ተከታትሎ አጥፊዎችን እንዲቀጣ አቤቱታችንን ለመንግሥት አቅርበናል። ኢዜማ ላይ የሚከሠቱ ችግሮች ሁለት ገጽ አላቸው አንደኛው ከመንግስት መዋቅር የሚመጣ ሲሆን ሁለተኛው ከዚያ ውጭ የሆኑ ሥርዓት አልበኞች የሚፈጥሩት ነው። “ባለጌና ጨዋ በተጣሉ ጊዜ ለጊዜውም ቢሆን ባለጌ ያሸነፈ ይመስላል” የሚል የቆየ የሀገራችን ብሂል አለ። ይህም ጨዋው በሕግ ስለሚያምንና የሕግ አስከባሪ ባለጌውን ይቀጣል፤ ብሎ በማመን ነው። በእኛ መዋቅርም የሚታየው ይሄው ሕግን የማክበር ጉዳይ ነው፤ ይህም ቢሆን ልክ አለው፤ ከገደብ ያለፈ ነውር ሲፈፀም አመራሩም፣ አባሉም፣ ደጋፊውም ራሱን፣ ፓርቲውንና ሀገሩን የመጠበቅ ተፈጥሯዊ መብት አለው። ኢዜማ ሀገርንና ሕዝብን ለድርድር አያቀርብም። ይህንንም ደግመን ደጋግመን ተናግረናል! መንግሥት በራሱ ውስጥም ሆነ ከራሱ ውጭ ያሉትን ሥርዓት አልበኞች በሕግ ሊቀጣ ይገባል። ይህ ካልሆነ ግን ሕዝቡ ራሱን ወደመከላከልና ሰላሙን ወደ ማስጠበቅ ሊገፋ ይችላል። ይህም በየትኛውም መመዘኛ ስህተት ሊሆን አይችልም።
በመጨረሻም የዴሞክራሲ ግንባታ ሂደቱን መጠበቅ ለሁላችንም የሚጠቅም ሀገር እና ሕዝብን የሚታደግ ብቸኛው መንገድ መሆኑን አውቀን እንድንጓዝበት መልዕክታችንን እያስተላለፍን ሥርዓት አልበኝነትን በጋራ በቃ የምንልበት ጊዜው ዛሬ መሆኑን በአፅንኦት እንገልፃለን።
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)
ጥር 22 ቀን 2012 ዓ.ም
አዲስ አበባ