-
Search Results
-
ከኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር የተሰጠ መግለጫ
(የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ተልዕኮን በተመለከተ)
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት በኢትዮጵያ ፌዴራዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 87 በተደነገጉ ግልጽ መርሆዎች መከላከያ ሠራዊት አዋጅ ቁጥር 1100/2011 በተሰጡት ግዳጆች መሠረት ዝርዝር ተልዕኮዎችን ለማስፈጸም የሚያስችሉ ደንቦች እና መመሪያዎችን በማውጣት፥ በሀገራችን ላይ የተቃጡ የውጭና የውስጥ ጥቃቶችን በመመከት የሀገራችንን ሉዓላዊነት አስከብሯል። የሕዝብንም ሰላም በማስጠበቅ ላይ ይገኛል።
መከላከያ ሠራዊቱ የአፍሪካውያን ወንድሞቻችን ሰላም የእኛም ሰላም ነው በሚል መርህ በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ላይ ተሰማርቶ ዛሬም ግዳጁን በአስደናቂ ሁኔታ በመወጣት ላይ ይገኛል።
ከሁሉም በላይ የዓለም ሕዝቦችና የቀጠናችን ብሎም የሀገራችን ዋነኛ ጠላት የሆነውን አሸባሪነት ለመዋጋት በጎረቤት ሀገር ሶማሊያ የመሸገውን የአልሸባብ አሸባሪ ቡድን በመመከት ቀጠናችን ሰላም የሰፈነበትና የተረጋጋ እንዲሆን መስዋዕትነት በመክፈል ላይ ነው።
በሀገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች የሚነሱ አለመረጋጋቶችን ከሌሎች የሀገራችን የፀጥታ ኃይሎች፣ ከክልል መስተዳድሮች፣ ከሀይማኖት አባቶች፣ ከሀገር ሽማግሌዎችና በዋነኝነት ከሕዝባችን ጋር በመተባባር ችግሩን ለመቅረፍ ዘለቄታዊ መፍትሄ እንዲመጣ ሠርቷል፤ አሁንም በመሥራት ላይ ይገኛል። በዚህ ተግባሩ ሠራዊታችን በደረሰበት ቦታ ሁሉ ሕዝብ ከፍተኛ የሰላም አየር የሚተነፍስ እና እፎይታ የሚሰማው መሆኑን የኢትዮጵያ ሕዝቦች ህያው ምስክር ናቸው።
ከእነዚህ የሠራዊቱ አኩሪ ድሎች የምንረዳው ነገር ቢኖር፥ ሠራዊታችን ደከመኝ፣ ሰለቸኝ ሳይል በአንድ ጊዜ ግዳጆችን መወጣት የሚችል፣ ለፈተናዎች የማይበገር፣ ለሀገር ሉዓላዊነት እና ለሕዝቦች ሰላም ሲል ማንኛውንም መስዋዕትነት ከመክፈል ወደኋላ የማይል ሕዝባችን የሚመካበት ሠራዊት መሆኑን ነው።
የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ሕዝቦች፥
የመከላከያ ሠራዊታችን የተጋድሎና የአሸናፊነት ገድሉ በወታደራዊ ስምሪት እና የግዳጅ አፈጻጸም ላይ ብቻ ሳይገደብ የሕዝብ ችግር ችግሬ ነው የሚል የሕዝቦች ደህንነትና ኋላ ቀርነት የሚያንገበግበውና የሚቆጨው ያለውን ሁሉ ለመስጠት ወደኋላ የማይል፣ የሕዝባችን አለኝታ የሆነ የልማትና የሰላም ሠራዊት ነው።
የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የአንድነትና የጥንካሬ መለያ የሆነውን ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ገንብቶ ለማጠናቀቅ በሚደረገው ጥረት ሠራዊቱ ግድቡ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ለግድቡ ግንባታ ከወር ደመወዙ በማዋጣት በቢሊየን የሚቆጠር ገንዘብ አስተዋጽኦ ከማበርከት አልፎ፤ በግድቡ ላይ ሊሰነዘር የሚችል ማንኛውንም ዓይነት ጥቃት ለመመከት ሌት ተቀን ዘብ ቆሞ በመጠበቅ ላይ ይገኛል።
መከላከያ ሠራዊታችን ከራሱ በፊት ለሕዝቡና ለሀገር የሚለውን እሴት መሠረት በማድረግ የሀገራችን ሕዝቦች ለገጠማቸው ሰው-ሠራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች ግንባር ቀደም ተዋናይ በመሆን አብነት የሚሆን ተግባር እየፈጸመ ይገኛል።
በጎርፍ አደጋ ዜጎች የሚደርስባቸውን አደጋ ለመቀነስ፣ በደም ልገሳ መርሃ ግብር ላይ በመሳተፍ፣ በአርሶ አደሮች ማሳ ላይ ተሰማርቶ በማገዝ፣ በተፈጥሮ ጥበቃ ላይ ጉልህ ተሳትፎ በማድረግ፣ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ የሆነውን ኮቪድ-19 በሽታን ለመከላከል፣ ከደመወዙ ቀንሶ ለአቅመ ደካሞች ድጋፍ በማድረግ፣ ገበታ ለሀገር ፕሮጀከት እውን እንዲሆን የወር ደመወዙን በማዋጣት እና በሀገራችን በተለያዩ ጊዜያት የሚከሰተውን የአንበጣ ወረርሽኝ ከሕዝቡ ጋር በመሆን በመከላከል ከፍተኛ ጥረት ያደረገና በማድረግ ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ ይህ ሕዝባዊነቱን ያስመሰከረ ተግባሩን ከመጀመሪያውኑ ሠራዊቱ የታነጸበት መሠረታዊ ባህሪው መሆኑን የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠንቅቆ የሚያውቀው ሃቅ ነው።
መከላከያ ሠራዊታችን ሀገራዊ ግዳጆቹን ሲወጣና ሕዝባዊ ተግባራቱን ሲያከናውን የሚገጥሙትን ችግሮች ሁሉ በመቋቋም ፈተናዎችን በጽናት ተጋፍጦ በማለፍና ውድ ህይወቱን መስዋዕት በማድረግም ጭምር መሆኑ በሕዝባችን የሚታወቅ ሃቅ ነው።
ይሁን እንጂ ሠራዊቱ የሀገሪቱን ሉዓላዊነትና የሕዝቦችን ሰላም የማረጋገጥ ሕገ-መንግሥታዊ ተልዕኮውን በጀግንነትና በቁርጠኝነት እየተወጣ ባለበት በዚህ ሰዓት የሀገራችንን ሰላምና ደህንነት የማይፈልጉ ቡድናዊና ፖለቲካዊ ፍላጎት ያላቸው ኃይሎች የተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም የሠራዊቱን ስምና ዝና በማጠልሸት በመርህና በሕግ ላይ ያልተመሠረተ የትችት ናዳ በማውረድ ላይ የሚገኙ ቢሆንም፥ ሠራዊቱ ይህን የፀረ-ሰላም ኃይሎች አጀንዳ በውል በመገንዘብ ትኩረቱን ግዳጁ ላይ ብቻ በማድረግ እየሰራ ይገኛል።
የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ሕዝቦች፥
ሰሞኑን በተለያዩ የትግራይ መገናኛ ብዙሃን ወቅታዊ የአቋም መግለጫ በሚል ርዕስ ስር መግለጫ ያወጣው አካል ሠራዊቱን የሚመለከቱ ጉዳዮች የተካተቱበት ባለ ሰባት ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥቶ አሰራጭቷል።
በዚህ መግለጫ 1ኛ ተራ ቁጥር ላይ በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 87(5) ድንጋጌ መሠረት የመከላከያ ሠራዊቱ ተግባር ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ በሆነ አኳኋን እንደሚያከናውን የተደነገገውን መርህ በሚጥስ መልኩ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች ተወያይተው ከሚሰጡት መፍትሄ ውጭ መከላከያ የአደረጃጃት፣ የስምሪትና የቁጥጥር ተግባሩን መፈጸም አይችልም በማለት መከላከያ በተቋማዊ ዕቅዱ እንዲሁም ወቅታዊና ሀገራዊ የደህንነት ስጋቶችን መነሻ አድርጎ ግዳጁን እንዳይፈጽም በሚገድብ አኳኋን የተዛባ ይዘት ያለው መግለጫ አውጥቷል።
በዚህ መግለጫ ተራ ቁጥር 5 ላይ ደግሞ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የሀገር ሉዓላዊነትና የሕዝብ ደህንነት አደጋ ላይ የወደቀ በዝምታ እንዳለፈና የሕገ-ወጥ የፖለቲካ ኃይሎች ጥቅም አስጠባቂ ኃይል መሆኑን የሚገልጽ መልዕክት በመግለጫ ላይ ተካቷል።
እውነታው የመከላከያ ሠራዊታችን የዜጎችን ህይወት ለመታደግ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ተሰማርቶ አስፈላጊ ተገቢና ሕጋዊ እርምጃ በመውሰድ ላይ የሚገኝ ቢሆንም ይህንን በተጻረረ መልኩ ሠራዊቱ ሕዝብን እየጨፈጨፈ ነው በማለት የመከላከያ ኃይሉን የማይመጥን፣ ተቋሙ ለሀገርና ለሕዝብ የከፈለውን እና እየከፈለ ያለውን ክብር መስዋዕትነት የሚያንኳስስ ሀገራዊ ተልዕኮውን እና አኩሪ ታሪኩን የሚያጠልሽ መልዕክት ይህ አካል ባወጣው መግለጫ ተስተጋብቷል።
ይህንኑ መግለጫ ተከትሎ አንዳንድ ግለሰቦች እና ባለስልጣናት በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ይህ አካል መከላከያን በሚመለከት ያወጣውን መግለጫ በማስተጋባት ፍጹም የሠራዊቱን ሕገ-መንግሥታዊ ተልዕኮ በማራከስ ተግባር ላይ ተጠምደው ይገኛሉ።
ይህ ተግባር መከላከያ ሠራዊቱ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች እና በትግራይ ክልል የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል ከክልሉ ሕዝብ ጋር ከፍተኛ ጥረት በሚያደርግበት የክልሉ ሕዝብ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያደርገውን ጥረት ትርጉም ባለው ደረጃ ሕዝባዊ ወገንተኝነቱን እያስመሰከረ ባለበት እና አጠቃላይ በክልሉ ያለውን ስምሪት የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር ዓላማ አድርጎ ግዳጁን ለመወጣት ዝግጁነቱን ባረጋገጠበት ወቅት የሠራዊቱን ተልዕኮ የሚገድብ መግለጫ ማውጣቱ አግባብነት የጎደለው ተግባር ሆኖ አግኝተነዋል።
ይህ መግለጫ የሠራዊቱን ተልዕኮ ያላገናዘበ፣ ግዳጁንም ተንቀሳቅሶ እንዳይፈጽም የሚያስተጓጉል ሀገራዊና ክልላዊ ተግባሮቹንም በአግባቡ እንዳይወጣ የሚያደናቅፍ ኃላፊነት የጎደለው መግለጫ ነው።
ከዚህ በፊትም እነዚህ አካላት ተመሳሳይ ይዘት ያላቸውን መልዕክቶች በማስተላለፍ ላይ የነበሩ ቢሆንም ለሕዝቦች ክብር እና ጥቅም ሲባል በከፍተኛ ኃላፊነት መንፈስ ለማለፍ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል። መላው የሀገራችን ሕዝቦች እንደሚገነዘቡት የመከላከያ ሠራዊታችን የማንም ፖለቲካ ኃይል፣ ክልል ወይንም ቡድን ጉዳይ አስፈጻሚ ሳይሆን የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሉዓላዊነታቸውን እንዲያስከብርላቸው፣ ሰላምና ደህንነታቸውን እንዲያረጋግጥላቸው የገነቡት ጠንካራ፣ ብሔራዊና ሀገራዊ ተቋም ነው።
ስለሆነም የሠራዊቱን አደረጃጀት፣ ስምሪትና የግዳጅ አፈጻጸም የሚመለከቱ ጉዳዮችን ሠራዊቱ በሕገ-መንግሥቱ የተቀመጠለትን መርህና በአዋጅ የተሰጠውና ግዳጅና ተልዕኮ መሠረት በማድረግ ተግባራቱን በራሱ የሚወስን እንጅ የሠራዊቱን አጠቃላይ ተልዕኮ እኔ ነኝ የምወስንልህ በሚል አግባብ ይህ አካል የሰጠው መግለጫ የሠራዊቱን ገለልተኝነት የሚጋፋ ግልጽ የሆነ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት መግለጫ ሆኖ አግኝተነዋል።
ይህ ወቅት የሀገራችን ሕዝቦች እንደ ሀገር የገጠማቸውን ሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ ችግሮች በመመከት ሰላማቸውን ለማረጋገጥና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ እድገት ለማስመዝገብ ደፋ ቀና በሚሉበት ወቅት የሀገራችንን እድገት የማይፈልጉ አካላት በተለይ ከሕዳሴ ግድባችን ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በግልጽ በሚጻረር መልኩ በእጅ አዙር እና በቀጥታ ጥቃት የሚፈጽሙበትና አንዳንድ ፀረ-ሰላም ኃይሎች ሀገራችንን ወደለየለት ትርምስ ለማስገባት ዓላማ አድርገው በሀገራችን የተለያዩ ክፍሎች በዜጎች ላይ አሰቃቂ ግድያ እና የማፈናቀል ወንጀል በመፈጸም ላይ የሚገኙ መሆኑ ይታወቃል።
መከላከያ ሠራዊት ከሕዳሴ ግድብ ጋር የተያያዙ የደህንነት ስጋቶችን ለመመከት የሚያስችል ከፍተኛ ዝግጅት እያደረገ ባለበት እና በሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች የተከሰቱ ግድያዎች እና መፈናቀሎችን ለማስቆም አስቸጋሪ የአየር ፀባይ እና መልክዓ ምድራዊ ቦታዎች ዘልቆ ሰፊ ስምሪት በማድረግ፣ ክቡር መስዋዕትነትን በመክፈል የሕዝቡን ሰላም ለማረጋገጥ ጥረት በሚያደርግበት በዚህ ወቅት መግለጫውን ያወጣው አካል የሠራዊቱን ወርቃማ ዕድል በሚያጎድፍ መልኩ ሠራዊቱን በሚመለከት ያሰራጨው መልዕክት ፍጹም ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን።
ጉዳዩ ከሕገ-መንግሥቱ ጋር በቀጥታ የሚቃረን፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ስምሪት እና ተልዕኮ በምንም መልኩ በአንድ አካል ወይም ቡድን ስር የማይወድቅ ሕጋዊና ሕገ-መንግሥታዊ በሆነ አግባብ ብቻ የሚመራ መሆኑን እያስታወቅን፤ መግለጫውን ያወጣው አካል ስህተቱን በይፋ እንዲያርም አጥብቀን እንጠይቃለን። ማንኛውም አካል የሠራዊቱን ተልዕኮ በሚያደናቅፍ አግባብ መግለጫ ከመስጠት እና አላስፈላጊ መልዕክት ከማስተላለፍ እንዲቆጠብም እናሳስባለን።
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ሀገርና ሕዝብ የሰጠንን ሕገ-መንግሥታዊ ተልዕኮ በገባነው ቃልኪዳን መሠረት ከማንኛውም የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ነጻ በመሆን፣ ክቡር የሆነውን ህይወታችንን በመክፈል ጭምር የሀገራችንን ሉዓላዊነትና የሕዝባችንን ሰላም ለማስጠበቅ ከመቼውም ጊዜ በላይ በአስተማማኝ ቁመና ላይ የምንገኝ መሆኑን ለመላው ሕዝባችን እያረጋግጥን የኢትዮጵያ ሕዝብ አሁንም እንደወትሮው ሁሉ ከጎናችን ሆኖ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረጉን እንዲቀጥል ጥሪያችንን እናቀርባለን።
መላው የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት አባላት፥
እኛ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት በተጋድሎና በድል የደመቀ አንፀባራቂ ታሪክ ያለን ሠራዊት ነን። በከፍተኛ ሕዝባዊ ወገንተኝነትና ፅናት ምድራዊ ፈተና ተቋቁመን እና ጥሰን በማለፍም ለሀገራችን እና ለሕዝባችን ሰላም፣ ደህንነትና ልማት ስንል ሁሉንም ዓይነት መስዋዕትነት እየከፈልን አልፈናል። በቀጣይም ከዚህ ጉዟችን ሊያደናቅፉን የሚጥሩ፣ ከተልዕኳችን ሊገድቡን ከሚሞክሩና አንድነታችንን ሊሸረሽሩ በሚታክቱ ማንኛውም ዓይነት ኃይሎች ሴራ ሳንገታ ደማቅ ታሪክ መሥራታችንን እንቀጥላለን።
የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር
ጥቅምት 20 ቀን 2013 ዓ.ም
አዲስ አበባ፥ ኢትዮጵያበተባበረ ሀገራዊ አቅም የእንቦጭ አረምን ከጣና ሐይቅ ላይ ለማስወገድ የሚስችል ዘመቻ ሊጀመር ነው
የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴርአዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – በተባበረ ሀገራዊ አቅም የእንቦጭ አረምን ከጣና ሐይቅ ላይ ለማስወገድ የሚስችል ዘመቻ ሊጀመር ነው፤ ዘመቻውን አስመልክቶ የኢፌዲሪ የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር መስከረም 29 ቀን 2013 ዓ.ም ውይይት አካሂዷል። በውይይት መድረኩም ላይ የአማራ ክልላዊ መንግሥት አመራሮችን ጨምሮ የዩንቨርሲቲ ምሁራንና ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።
በዘመቻው እንቦጭን ከጣና ሐይቅ ላይ ለማስወገድ ሁሉንም ክልሎች፣ የከተማ አስተዳደሮች እና የፌደራል እና የክልል ተቋማት እንዲሁም መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ለማስቻል የተዘጋጀ ዕቅድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
በውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተፋሰስ ልማት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር አዳነች ያሬድ የሚደረገውን ዘመቻ ዕቅድ ባቀረቡበት ወቅት፥ እንደገለጹት እንቦጭ በጣና ሐይቅና በአባይ ተፋሰስ የውሃ አካላት ላይ እጅግ በሰፊው ተንሠራፍቶ እንደሚገኝ አሳውቀው፤ እንቦጭ የተንሠራፋበትን ይህንን የውሃ አካል ለማጽዳት ሁሉም ክልሎች፣ የከተማ አስተዳደሮች እና የፌደራል እና የክልል ተቋማት እንዲሁም መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት እንቦጭ የተንሠራፋበትን የሐይቁን አካል በመከፋፈል በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ የሚስወግዱት ይሆናል። አረሙን ከውሃው ላይ ማስወገድ፣ መንቀል፣ በአንድ ቦታ ማከማቸትና ማቃጠል ወይንም መቅበር በዘመቻው የሚሠራበት መፍትሄ ነው።
የውሃ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢነጂነር ስለሺ በቀለ ለአንድ ወር በሚካሄደው በዚህ ዘመቻ ላይ ሁሉም ክልሎች፣ የከተማ አስተዳደሮች፣ ተቋማትና ሁሉም ኢትዮጵያውያን በዘመቻው በንቃት እነዲሳተፍበት ጥሪ አቅርበዋል።
በተለይ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው ተቋማት ለዘመቻው ስኬታማነት ከተለመደው አሠራር ባሻገር ማቀድና ስራውን መፈጸም ይጠበቅብናል ብለዋል። ከክልል እስከ ቀበሌ ያለውን መዋቅርም በከፍተኛ ንቅናቄ መምራት ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።
በዚሁ መድረክ ላይ የተገኙት የአማራ ክልላዊ መንግሥት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ፋንታሁን ማንደፍሮ ይህ እቅድ በአግባቡ የምንተገብረው ከሆነ እንቦጭ የሚስከትለውን ጉዳት መቀነስ እንችላለን በማለት ሀሳባቸውን ገልጸዋል። በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለሚካሄደው ለዚህ ዘመቻ 92 ሚሊዮን ብር የሚያስፈልግ እንደሆነም ተመላክቷል። ለዘመቻውም እስከ 10 ሺህ የሚጠጉ ሰዎችን ለማሳተፍ ታቅዷል።
የእንቦጭ አረም በተፋሰሱ በሚገኙ 30 ቀበሌዎች በሚያዋስኑት የሐይቁ አካል ላይ ተንሠራፍቶ ይገኛል።
ምንጭ፦ የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ