Search Results for 'ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ'

Home Forums Search Search Results for 'ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ'

Viewing 15 results - 16 through 30 (of 65 total)
  • Author
    Search Results
  • Anonymous
    Inactive

    የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በአማራ ክልል ከተሞች እና በአዲስ አበባ ታላልቅ ሰለማዊ ሰልፎችን ለማድረግ ጥሪ አደረገ

    የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በአማራ ክልል ከተሞች እና በአዲስ አበባ ታላልቅ ሰለማዊ ሰልፎች እንደሚደረጉ አስታውቋል። አብን ስለሰላማዊ ሰልፎቹ እና በአጠቃላይ በአማራ ሕዝብ ላይ ከዕለት ወደ ዕለት ያልተቋረጠ በደል እየደረሰበት መሆኑን ያመላከተበት ትንታኔ የሚከተለውን ይመስላል።

    ለመላው የአማራ ሕዝብ፣
    ለንቅናቄያችን አባላትና ደጋፊዎች፣
    ለመላው ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በሙሉ !

    የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) መንግሥታዊና ሥርዓታዊ ጭቆና እና የዘር ጥቃት ያንዣበበትን የአማራን ሕዝብ ከህልውና ስጋት ለመታደግና በነፃነት፣ በእኩልነት፣ በፍትህና በወንድማማችነት የሚኖርባት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት የቆመ ድርጅት ነው።

    አብን ባለፉት ሁለት ከመንፈቅ ዓመታት ሕዝባችን በከፍተኛ መስዋዕትነት ያስገኘው የለውጥ ተስፋ እንዳይመክን፣ በትግላችን የተንበረከኩ አማራ-ጠል ኃይሎች ዳግም እንዳያንሰራሩና የሀገር እና የሕዝብ ህልውና በድጋሚ አደጋ ላይ እንዳይወድቅ እልህ አስጨራሽ ትግል አድርጓል። የአማራ ብሔርተኝነት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ አዎንታዊ የመረጋጋት፣ የመቻቻልና የግንባታ ሚና እንዲኖረው ያልተቆጠበ ጥረት አድርጓል።

    ይሁን እንጂ ተስፋ የተጣለበት “ለውጥ” እያደር መስመሩን በመሳቱ አዲሱ አገዛዝ የአምባገነንነትና የአንድ ቡድን ፍላጎት አስፈፃሚነት አዝማሚያ ማሳየቱ ገሃድ ወጥቷል። በተለይም በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈፀመው የዘር ጥቃት እየተባባሰና አድማሱን እያሰፋ በቅርቡ እንኳን በኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና በደቡብ ጉራ ፈርዳ ተከታታይ ለሆኑ የጅምላ ጭፍጨፋዎች፣ የዘር ማጽዳትና የማፈናቀል ጥቃቶች ሰለባ ሆኗል።

    አብን በሕዝባችን ላይ ስልታዊ፣ የተደራጀ፣ ሰፊ የመገናኛ ብዙኃን ቅስቀሳ የተደረገበት ዘመቻና በመንግሥት መዋቅር ጭምር የተደገፈ የዘር ማጥፋት እየተፈፀመበት መሆኑን በመግለጽ መንግሥት ችግሩን እንዲያስቆም በተደጋጋሚ ወትውቷል። እንደ ሕዝብም መቻቻልና ሀገር ወዳድነት ትርጉም እስኪያጡ ድረስ ታግሰናል። ነገር ግን ብልፅግና-መራሹ መንግሥት የሕዝባችንን ሆደ-ሰፊነትና አስተዋይነት እንደ ዓይነተኛ ድክመት በመቁጠር፥ ንቅናቄያችን ለሀገር ህልውና ሲባል የሰጠውን ይሁንታ በሰፊው በማጓደል ዛሬም አማራው መንግሥት-አልባ ሕዝብ መሆኑን አረጋግጦልናል።

    አብን በሕዝባችን ላይ ለሚደርሰው ጥቃት ቀንደኛው ተጠያቂ ማዕከላዊ መንግሥት መሆኑን ያምናል። መንግሥት ‹‹የወንጀሎች ሁሉ ወንጀል›› የሚባለውን የዘር ማጥፋትን በመከላከል፣ በማስቆምና ዘላቂ መፍትሄ በመፈለግ ረገድ የረባ ሚና አልተጫወተም። እንዲያውም የዘር ጥቃቶችን “ግጭት” እያለ ለማድበስበስ፣ መረጃዎችን ለማፈንና ሰለባዎችን ጭምር ለመወንጀል ተደጋጋሚ ጥረቶችን ሲያደርግ ተስተውሏል። መንግሥት በአማራ ላይ የተፈፀሙ የዘር ጥቃቶች ልዩ ጠባሳ የሆነውን የጉራ ፈርዳ ጥቃት መሪ አቀናባሪ የነበረውን ግለሰብ ለዳግም ሹመት የመምረጡን አንድምታ እንረዳለን፤ አሁን የሚፈፀመውን ካለፈው የሚያስተሳስር ረጅም ክር አለው።

    በሁለተኛ በአማራ ሕዝብ ላይ የዘር ፍጅት በተፈፀመባቸው ክልሎች ያሉ መንግሥታት በተለያየ ደረጃ ኃላፊነታቸውን ካለመወጣት አልፈው፥ በቀጥታና በተዘዋዋሪ በሕግ፣ በመዋቅር፣ በመሣሪያና በገንዘብ ጥቃቶችን መደገፋቸውና ማቀናበራቸው በገሃድ ይታወቃል። ከጥቃቱም በኋላ የየክልሎቹ የብልፅግና ፖርቲ አመራሮች በሕዝባችን ላይ በየፊናቸው በማንአለብኝነት የሚያደርጉት ዛቻና ማስፈራሪያ በድርጊቱ አለመጸጸታቸውንና ችግሩን ለማረም ፈቃደኝነት እንደሌላቸውም ያረጋግጣል።

    ሦስተኛው ተጠያቂ “የአማራ ብልፅግና” የሚባለው ነው። ለአማራ ሕዝብ ብልፅግናውን ቀርቶ ህልውናውንም ሊያስጠብቅለት አልቻለም። ቀድሞ ከነበረው አጠቃላይ አቋም መሻሻል አላሳየም። ንቅናቄያችን አማራው እንደ ሕዝብ በአንድነት እንዲቆም ለማስቻል ለሁለት ዓመታት ያክል “የአማራ – ብልፅግናን” ለማግባባት ያደረገው ሰፊ እና ያላሰለሰ ጥረት ፍሬ አላፈራም። የአማራ ሕዝብንም፣ አብንንም በተደጋጋሚ ያሳዘነ ሲሆን፤ ከታሪክ ተጠያቂነትም አያመልጥም።

    አብን በማዕከልም ሆነ በክልል ያሉ መንግሥታት የተጫወቱት አፍራሽ ሚና ውጤቱ በአማራው ሕዝብ ተገድቦ እንደማይቀር በውል እንዲጤን ይሻል። መንግሥት መሠረታዊ መብቶቹን የማያስጠብቅለትን ሕዝብ ማናቸውንም የሞራልም ሆነ የሕግ ግዴታ ሊጥልበት አይቻለውም። በሕዝብና በመንግሥት መካከል ያለው ማኅበራዊ ውልም ክፉኛ ይናጋል።

    አብን በአማራው ላይ የሚደረገው የዘር ማጥፋት ድርጊት ዞሮ ኢትዮጵያን እንደሀገር ዋጋ እንደሚያስከፍልም ይገነዘባል። ንቅናቄያችን እስካሁን የአማራ ሕዝብ በኢትዮጵያዊነት ተስፋ እንዲቆርጥና ወደ አመፅ እንዲያመራ የሚደረገውን አሉታዊ ጥረት ሲታገል ቆይቷል። ሆኖም ከእንግዲህ ወዲያ የሕዝባችን ህልውና በምንም መልኩ ለድርድር እንደማይቀርብ ለማረጋገጥ ይወዳል።

    አብን የአማራ ሕዝብ ሆደ ሰፊና አስተዋይ በመሆኑ ተፈጥሯዊ መብቱንና ነፃነቱን በልቅሶና በልመና ሳይሆን በተደራጀ ትግል እንደሚያስከብር ይተማመናል። ይህን ታላቅ ታሪካዊ ኃላፊነት በመምራት ከግብ ለማድረስ ድርጅታችን ቁርጠኝነቱን ያረጋግጣል።

    አብን መንግሥት ችግሩን በአስቸኳይ ከማስቆም በተጨማሪ ጥቃቱን እንዲያምንና በስሙ እንዲጠራ፣ ጉዳዩን የሚያጣራ ገለልተኛ አካል በፍጥነት እንዲሰይም፣ ወንጀለኞችን አጣርቶ ለፍርድ እንዲያቀርብና ለተጎጂዎችም ተገቢውን ካሳ እንዲከፍል በጥብቅ ይጠይቃል። ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት መሠረታዊ ምንጭ የሆነው አማራ-ጠል ሕገ-መንግሥት የሚሻሻልበትን አግባብ በአስቸኳይ እንዲያመቻች ይጠይቃል።

    አብን መንግሥት የሀገሪቱን ሰላምና ደህንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ማስከበር አለመቻሉንና በተደጋጋሚ የአማራ ተማሪዎችን ደህንነት ለመጠበቅ ችላ ማለቱን በማጤን ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ያደረገው የትምህርት መጀመር ጥሪም ያሳስበዋል። ብዙ ሽህ የአማራ ተማሪዎች በፅንፈኞች ጥቃት ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው ሲፈናቀሉ፣ ሲገደሉ፣ ሲደበደቡና ሲታገቱ በአሳፋሪ ሁኔታ አልታደጋቸውም። አሁንም ለተማሪዎች አስተማማኝ ጥበቃ እንዲያደርግ በጥብቅ እንጠይቃለን።

    የአብን ብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በጥቅምት 14 እና 15 ቀን 2013 ዓ.ም ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ በወሰነው መሠረት በሀገራችንና በሕዝባችን ላይ ያንዣበበውን ከፍተኛ የደህንነት ስጋት በመቀልበስ፤ የሕዝባችንን ህልውና ለማረጋገጥ የሚያደርጋቸውን ሰላማዊና ሕጋዊ የትግል ጥረቶችና ስልቶች ለሕዝባችን ለማሳወቅ የፊታችን ረቡዕ ጥቅምት 18 በአማራ ክልል ከተሞች፤ እሁድ ጥቅምት 22 በአዲስ አበባ ታላላቅ ሕዝባዊ ትዕይንቶች ይደረጋሉ።

    በእነዚህ ሰልፎች ላይ መላው የአማራ ሕዝብ ማናቸውም ልዩነት ሳይገድበው እንዲሳተፍ፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የአማራ የፖለቲካ ኃይሎች፣ የተለያዩ የአማራ የሲቪክ አደረጃጀቶች በወገናችሁ ላይ የሚደርሰውን ግፍና በደል እንድትቃወሙ ጥሪ እናደርጋለን።

    አብን በአማራ ክልልና በአዲስ አበባ የተጠሩት የተቃውሞ ሰልፎች ፍፁም ሰላማዊ እንዲሆኑና ሊከተሉ የሚችሉ አላስፈላጊ ረብሻዎችንና ጥቃቶችን ለማስቀረት ሕዝቡ የራሱን ደህንነት በንቃት እንዲጠብቅ ያሳስባል።

    ሰልፉን በተመለከተ ዝርዝር ጉዳዮች፣ በሰልፉ ላይ የሚተላለፉ መልዕክቶችና መፈክሮች በማዕከል ተዘጋጅተው በፓርቲያችን ይፋዊ ገፅ የሚለጠፉትና ለየአካባቢው የሚላኩት ናቸው።

    ጉዳዩ የሕዝብ ህልውና ጥያቄና የራሱ ሰልፍ በመሆኑ የሀገር መከላከያና አጠቃላይ የደህንነት ኃይሉ የሕዝቡ ሰልፍ የተሳካ እንዲሆን ተገቢውን የፀጥታ ሥራ እንዲያከናውን ጥሪ እናደርጋለን።

    በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ አማሮች እሁድ ጥቅምት 22 ቀን 2013 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከሚደረገው ሰልፍ ጋር በተለያዩ ክፍለ ዓለማት ድምፃችሁን እንድታሰሙ አብን ጥሪውን ያቀርባል።

    ሰልፉ ለኮቪድ-19 ወረርሽኝ በማያጋልጥ መልኩ በጥንቃቄ እንዲካሄድ እያሳሰበ፥ ሕዝባችን በየአካባቢውና በየቤተሰቡ በገጠመን ፅኑ ወቅታዊ ችግር ላይ ውይይት እንዲያካሂድ፤ በቀጣይም ዘላቂ መፍትሄ ለማፈላለግ አብን ዓለምአቀፍ የመላው አማራ ሕዝባዊ ውይይት መድረኮችን እንደሚያመቻች መግለጽ ይወዳል።

    በአዲስ አበባም ሆነ በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈፀመው የማናለብኝነትና የተረኝነት አካሄድ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ጉዳት በመሆኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ በወንድሙ በአማራው ሕዝብ ላይ የሚፈፀመውን ግፍና በደል በመቃወም አብሮ እንዲሰለፍ አብን ጥሪውን ያቀርባል።

    አብን ከእንግዲህ ጉዳዩ የማያዳግም እልባት እስከሚያገኝ ድረስ ማናቸውንም የሰላማዊ ትግልና የሕዝባዊ እምቢተኝነት ስልቶችን በየደረጃው የሚተገብር በመሆኑ ሕዝባችን ከወዲሁ እንዲያውቀውና ወትሮ ዝግጁ እንዲሆን ጥሪያችንን እናቀርባለን።

    አንድ አማራ ለሁሉም አማራ ፥ ሁሉም አማራ ለአንድ አማራ!
    የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)
    ጥቅምት 16 ቀን 2013 ዓ.ም
    ሸዋ፥ አዲስ አበባ፥ ኢትዮጵያ!

    የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)

    Anonymous
    Inactive

    በእነ እስክንድር ነጋ ኢ-ፍትሃዊ እስር ላይ የተሰጠ መግለጫ

    የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ጥቅምት 12 ቀን 2013 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ የእነ እስክንድር ነጋ የክስ ሂደትን አጀንዳ በማድረግ አስቸኳይ ስብሰባ አካሂዷል። ፓርቲው እስክንድር ነጋ (ሊቀ መንበር)፣ ስንታየሁ ቸኮል፣ ቀለብ ስዩም እና አስካለ ደምሌ በምንም ዓይነት የሚያስከስስ ወንጀል ጉዳይ እንዳልተሳተፉ እና ንጹሃን መሆናቸውን ከዚህ በፊት መግለጹ ይታወቃል፤ ይልቁንም የፍትህ ሥርዓቱን መጠቀሚያ በማድረግ በቀጣዩ [ሀገራዊ] ምርጫ ጠንካራ ተፎካካሪ የሚሆኗቸውን እነ እስክንድር ነጋ እና ፓርቲያቸውን ለማጥቃት ታስቦ እንደሆነ ገልጸናል። ይህንን አቋማችንን የበለጠ የሚያጠናክርልን ሁለት ነገሮች ደግሞ በጥቅምት 12 ቀን  የችሎት ውሎ ታዝበናል፦

    1ኛ. ዐቃቤ ሕግ ከዚህ በፊት ያሰማውን የምስክሮች ቃል በመተው እንደገና 21 (ሀያ አንድ) ምስክሮች ማንነታቸው ሳይገለጽ ከመጋራጃ ጀርባ እንዲሰሙ እና በዝግ ችሎት እንዲደመጡ ጥያቄ ማቅረቡ ላይ እየተደረገ ያለው የፍትህ አሰጣጡን የሚያዛባ እና የሚያጓትት ሂደት፤

    2ኛ. የሚሰጡ ቀጠሮዎች (በተለይም አዳዲስ ዳኞች እንደተሾሙ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ በፓርላማም ከተናገሩ በኋላ) ረጅም መሆናቸው ሂደቱን በማጓተት እነ እስክንድር ነጋ ሳይፈረድባቸው በእስር እንዲቀጡ የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ በዚህ ዓመት በሚደረገው ምርጫ ከክሱ ነጻ ቢባሉ እንኳን እንዳይሳተፉ የሚያደርግ ሆኖ አግኝተነዋል።

    እነዚህ እና መሰል ጉዳዩች በክስ ሂደቱ ላይ የአስፈጻሚው አካል ረጅም እጆች እንዳሉበት የሚያስረዱ ሆነው አግኝተናቸዋል። ከዚህም በመነሳት ፓርቲያችን መሪዎቻችን ትክክለኛ ፍትህ፣ ሳይዘገይ ያገኛሉ የሚል እምነት እንዳይኖረን አድርጎናል። ስለሆነው ፓርቲያችን የኦህዴድ/ብልጽግና ፖለቲካ ዓላማ ለማሳካት በማሰብ በሀሰት በተቀነባበረ ክስ የተያዙ አመራሮቻችንን ለማስፈታት ከዚህ በፊት ሲያደርገው ከነበረው ትግል በተለየ እና በበለጠ ሁኔታ ውጤታማ የሚያደርጉ የትግል መንገዶችን ነድፎ በሥራ ላይ ያውላል። መላው የፓርቲያችን አባላት እና ፍትህ ወዳጅ ሕዝባችን በቀጣይ ይፋ ለምናደርጋቸው የትግል እንቅስቃሴዎች እንደከዚህ ቀደሙ እራሱን እንዲያዘጋጅ እና ለነጻነት በሚደረገው ትግል ንቁ ተሳታፉ እንዲሆን ጥሪያችንን እናቀርባለን።

    ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ)
    አዲስ አበባ
    ጥቅምት 13 ቀን 2013 ዓ.ም

    ምንጭ፦ ባልደራስ
    ——
    ሌሎች ተመሳሳይ ዜናዎች፦

    በእነ እስክንድር ነጋ ኢ-ፍትሃዊ እስር ላይ የተሰጠ መግለጫ

    Anonymous
    Inactive

    ከኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) በወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታዎች ላይ የተሰጠ የአቋም መግለጫ

    የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ሀገራዊ ምክር ቤት አንደኛ ዓመት ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባዉን ከመስከረም 29 ቀን እስከ ጥቅምት 1 ቀን  2013 ዓ.ም ሲያካሂድ በወቅታዊ የኢትዮጵ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የሰላም መደፍረስ ጉዳዮች ላይ በስፋትና በጥልቀት መክሯል፤ ፓርቲው የሚተገብራቸውን የተለያዩ መመሪያዎች፣ እንዲሁም የ2013-2017 ዓ.ም የፓርቲዉን የአምስት ዓመት ስልታዊ ዕቅድና የ2013 ዓ.ም የአንድ ዓመት ዕቅድ በስፋት እና በጥልቀት በመመርመር ወደተግባር እንዲገቡ በሙሉ ድምጽ ዉሳኔ ካሳለፈ በኋላ የሚከተሉትን የአቋም መግለጫዎች አዉጥቷል።

    1. ሁሉንም ተግባራት ማከናወን የሚቻለዉ በሀገሪቱ አራቱም ማዕዘኖች ሰላም ሲኖርና የሕግ የበይላነት ሲከበር መሆኑ ለሁሉም ግልጽ ነዉ፤ ነገር ግን በመላ ኢትዮጵያ ሀገሪቱን ለ27 ዓመታት ሲዘርፍና የዜጎችን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በመንፈግ እንደፈለገ ሲያስር ሲገድልና ሲያኮላሽ የነበረዉ ዘረኛዉ ህወሓት ከጠቅላይ አምባገነንቱ ተባሮ መቀሌ ከመሸገበት እና በዶ/ር ዐቢይ አህመድየሚመራዉ “የለዉጡ ቡድን” መንግሥታዊ ስልጣን ከተቆናጠጠበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ ሁነቶች ተከስተዋል። በሀገራችን ኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታ እጅግ ዘግናኝ ግድያዎችና የዘር ማጥፋት ወንጀሎች ነፍስ ባላወቁ እምቡጥ ሕፃናት ሳይቀር በጽንፈኛ ብሔርተኞችና እነሱ በሚደግፏቸዉ ታጣቂ ቡድኖች፤ በኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ (በተለይ በመተከል በተደጋጋሚ) እንዲሁም በደቡብ ክልሎች እስካሁን ድረስ እየተፈጸሙ ነዉ። ዜጎች በገዛ ሀገራቸዉ እንደሁለተኛ ዜጋ እየታዩ ሀብት ንብረታቸዉ እየተዘረፈና እየወደመ፣ ከመኖሪያ ቀያቸዉ እየተፈናቀሉ ነዉ። ኢሕአፓ ከዚህ በፊት ባወጣቸዉ ተደጋጋሚ አቋሞቹ እንደገለጸዉ፥ መንግሥት የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ያሳየዉ ቸልተኝነትና መዘግየት እነዚህ ሁሉ ዘግናኝ ድርጊቶች እንዲፈጸሙ በር እንደከፈተ ያምናል። ስለዚህ ሉዓላዊነታችንንና የሕግ የበላይነትን የማስከበር፣ ሀገራዊ ሰላምን የማረጋገጥ እና የዜጎችን ደህንነነት የመጠበቅ ኃላፊነት ያለባቸዉን የተለያዩ የጸጥታ መዋቅሮች የሚመራዉ መንግሥት ስለሆነ፥ አሁን የጀመረዉን ሕግ የማስከበር ሥራ አጠናክሮ እንዲቀጥል፣ በአጥፊዎችም ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወስድ፣ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በተለይም በቤኒሻንጉልና በኦሮሚያ መሽገው የዜጎችን ህይወት የሚቀጥፉ ሕገ-ወጥ ታጣቂ ቡድኖች ላይ ትጥቅ የማስፈታት እና ወደሕግ የማቅረብ፤ በወንጀል ድርጊት ያልተሳተፉትን አጣርቶ ወደ ሰላማዊ ኑሯቸዉ እንዲመለሱ የማድረግ የማያዳግም እርምጃ እንዲወስድ ይጠይቃል፤ ፓርቲያችን ኢህአፓም ጸረ-ሰላም ኃይሎችን በጽናት ይታገላል።
    2. በሀገራችን ኢትዮጵያ ላለፉት በርካታ ዓመታት የሚፈጸሙት ዘግናኝ የሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች መጣስ መንስዔው በዋነናት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግሥት ስለመሆኑ በተደጋጋሚ ተገልጧል። ከሁለት ዓመታት በፊት፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አስተዳደርም ሕገ-መንግሥቱን ለማሻሻል በተደጋጋሚ ቃል ገብቶ እንደነበረ ይታወቃል። ነገር ግን ያ ሁሉ ቃል-ኪዳንና ያ ሁሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ወደጎን ተትቶ፥ በፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድርና ውይይት ወቅት ይታያል ተብሎ የነበረው ሕገ-መንግሥት ምንም ዓይነት ማሻሻያም ሆነ ማስተካከያ ሳይደረግበት ከሃያ አምስት ዓመታት በላይ ለሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ሁሉ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ዋነኛው መንስዔ እንደሆነ አለ። ኢሕአፓ ኢትዮጵያ ውስጥ በገዢው ፓርቲና በአጋሮቹ ለሚፈጸሙት ግፎች ሁሉ የመጀመሪያው ተጠያቂ ይህ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግሥትና ይዘቱ ስለሆነ አስቸኳይ ማሻሻያ እንዲደረግበት መንግሥትን ይጠይቃል።
    3. በተጨማሪም፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር በተደጋጋሚ ይደረጋል እያለ ቃል ሲገባ የነበረው የብሔራዊ ዕርቅና የሀገራዊ መግባባት አጀንዳ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ አጀንዳ እንደሆነ ኢሕአፓ ጽኑ እምነት አለው። በኢትዮጵያ የሚገኙት ሕጋዊና ሰላማዊ የሆኑት የፖለቲካ ኃይሎች በሙሉ የሚሳተፉበት፣ ሀገራዊ መግባባትን ትኩረቱ ያደረገ የፓርቲዎችና የሲቪክ ማኅበራት የጋራ መድረክ አስፈላጊነት ሳይታለም የተፈታ በመሆኑ፥ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መንግሥት ለዚህ አጀንዳ ቅድሚያ ሰጥቶ የውይይትና የድርድር መድረኩ በአፋጣኝ እንዲካሄድ ኢሕአፓ ጥሪውን ያስተላልፋል።
    4. በያዝነው የ2013 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ይካሄዳል የተባለውና የሚጠበቀው 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ሕጋዊና ሰላማዊ ሆኖ እንዲተገበር ኢሕአፓ ከፍተኛ የሆነ ፍላጎት አለው። በመሆኑም፥ ምርጫ የአንድ ቀን ተግባር ሳይሆን የብዙ ወራትን የመደራጀትና የማደራጀት ተግባራት ከእያንዳንዱ የፖለቲካና የሲቪክ ማኅበር የሚጠይቅ ክንውን መሆኑ ግልጽ ነው። ሆኖም ግን ከ5ኛው ሀገራዊ ምርጫ ማግስት ጀምሮ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መንግሥት ሰላምንና ጸጥታን ማስከበር ተስኖት በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ውስጥ ሁከትና ብጥብጥ እየተከሰተ ይገኛል። በዚህ ያለመረጋጋትና የሰላም እጦት ውስጥ ሆኖ ምርጫን የሚያክል ከፍተኛ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማድረግም አጅግ አዳጋች ነው። በመሆኑም መንግሥት ሁሉም ዜጎች በሕግ ፊት እኩል የሚሆኑበትንና የሚዳኙበትን የፖለቲካ-ኢኮኖሚ ምህዳር አስፍቶ የዜጎችን በሕግ የበላይነት ሥር ብቻ የመምረጥና መመረጥ መብታቸውን እንዲያከናውኑ የማድረግ ኃላፊነቱን በተግባር እንዲወጣ ኢሕአፓ ጥሪውን ያስተላልፋል።
    5. በየጊዜዉ እያሻቀበ ያለዉ የዋጋ ግሽበትና በኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰት ምክንያት በከፍተኛ ደረጃ ቁጥሩ የጨመረዉ ሥራ አጥነት የዜጎችን የእለት ተእለት ኑሮ በሰቆቃ የተሞላ አድረጓል፤ ከዚህ በተጨማሪ ባሳለፍነዉ 2012 ዓ.ም በተከሰቱ ሰው-ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችም ለከፋ የርሀብ አደጋ ተጋላጭ ሆነዋል። በመሆኑም ኢሕአፓ መንግሥት በረዥም ጊዜ ለዜጎች በተለይም ለወጣቶች በርካታ የሥራ ዕድል መፍጠር የሚችሉ ሀገር በቀል ኢንቨስትመንቶችን እንዲያስፋፋ፣ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ እና ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርን በመቆጣጠር የዋጋ ግሽበቱን ከ2 ዲጂት በታች የሚወርድበትን የኢኮኖሚ አማራጭ እንዲተገበር፣ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸዉም ተገቢዉን ድጋፍ በወቅቱ እንዲያቀርብ በአጽንኦት ይጠይቃል።
    6. ከደንቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ወደ ትዉልድ ቀያቸዉ ሲመለሱ ታፍነዉ ተወስደዉ እስካሁን ድረስ ደብዛቸዉ የጠፋዉ ተማሪዎች ጉዳይ አሁንም ድረስ የኢሕአፓ የእግር እሳት ነዉ፤ ስለዚህ መንግሥት ልዩ ተኩረት ሰጥቶ ተማሪዎቹ እዉነት በህይወት ካሉ የማስመለስ ሥራ እንዲሠራ፥ አለያም እዉነቱን ለቤተሰቦቻቸዉ፣ ለኢትዮጵያና ለዓለም ሕዝብ እንዲያሳውቅ ኢሕአፓ የዘወትር ጥያቄዉን ዛሬም ያቀርባል።
    7. ኢሕአፓ ሕብረ-ብሔራዊ ፓርቲ እንደመሆኑ በኢትዮጵያ አንድነትና ሉአላዊነት፣ በሕዝቧ ዉህድ ማንንነት የማይጠራጠሩ፣ በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ትግል ለሚያምኑና በሕጋዊ መንግድ ለተደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሁሉ ኑ! ሀገራችን ከገባችበት ጽንፈኛ የጎሳ እና የጥላቻ ፖለቲካ ቅርቃር በጋራ እንታደጋት፤ ሀገራዊ ብሔራዊ መግባባትን በመፍጠርና የፖቲካ ቁርሾን በማስወገድ ዘላቂ ሰለማና እድገት የሰፈነባት ሀገር እናድርጋት፤ የሚል የአክብሮት ጥሪዉን ያስተላልፋል።
    8. በሀገር ቤትና በዉጪ ሀገር ለምትገኙ ቀደምት የኢሕአፓ አባላትና መሥራቾች ዘላለማዊ ከሆነዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ህላዌ ጋር በየጊዜዉ እየታደሰ የሚዘልቅ ዘመን ተሸጋሪ ሀሳብ ያነገበዉ ኢሕአፓ ከዉጪ ሀገር ወደ ሀርቤት ከገባ ጊዜ ጀምሮ በሀገሩ ምድር ላይ ትግሉን በጽናትና ቁርጠኝነት እያካሄደ መሆኑን ተገንዝባችሁ ፓርቲያችን ኢሕአፓን በተለያየ መንገድ በመደገፍና በማጠናከር የትግላችሁን ፍሬ ማፍራት እውን ታደርጉ ዘንድ ጥሪዉን ያስተላልፋል።

    ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!
    ኢሕአፓ ለተሻለ ነገ!

    የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)
    ጥቅምት 5 ቀን 2013 ዓ.ም
    አዲስ አበባ

    የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)

    Anonymous
    Inactive

    የሰላም ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል ሃሳብ ሊደገፍ የሚገባው ነው
    የሺዋስ አሠፋ

    ወ/ሮ ሙፈሪሃት የፌደራል መንግሥቱን (ብልፅግና) እና የትግራይ ክልል አስተዳደርን (ህወሓት) መካረር በተመለከተ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የገለፁትን አይቼ በግሌ ጥሩ ጅምር ነው – ይበርቱ ብያለሁ። ስድብ፣ ፉከራ እና ይዋጣልን ሀገርን እና ሕዝብን ምስቅልቅል ውስጥ ከመክተት ውጭ ምንም ፋይዳ የለውም። “እልህ ምላጭ ያስውጣል” እንዲሉ ለራሳችሁም ቢሆን ውስጣችሁን የሚቆራርጥ ከሚሆን በስተቀር አይጠቅምም። የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አቋራጭ መንገድ የለውም፣ ውይይት/ድርድር ብቻ! በጉልበት/በጠመንጃ የሚሆን ቢሆን ኢትዮጵያን የሚቀድም ባልነበረም ነበር። ልብ በሉ ለውይይት አሻፈረኝ የሚሉ ወገኖች በስተመጨረሻ ቢፈልጉ አያገኙትም፤ ምክንያቱም አይበለው እንጂ ጦርነትም ቢሆን መቋጫው ውይይት/ድርድር ነው።

    በ2009 ዓ.ም ራሳቸው ወ/ሮ ሙፈሪሃት የነበሩበትን የፓርቲዎች ውይይት/ድርድር (ስያሜው ራሱ አወዛጋቢ ነበር) ባስታውሳቸው ጠቃሚ የሚሆን ይመስለኛል። ሙከራው የተቀጨው ከጅምሩ ነበር። የቀድሞ ገዢ ፓርቲን ጨምሮ 22 ሀገር አቀፍ ፓርቲዎች ለሚያደርጉት ውይይት/ድርድር የመሀል ዳኛ (mediators) ያስፈልጋሉ/አያስፈልጉም በሚለው የጦፈ ክርክር ተደርጎ ኢህአዴግ እና ሌላ አሁን ስሙን የማላስታውሰው አንድ ፓርቲ አያስፈልግም ሲሉ 20 ፓርቲዎች ያስፈልጋል ብለን በከፍተኛ ቁጥር አሸነፍን፣ mediators ሊሆኑ የሚችሉትን ወገኖች የሥራ ልምድና የትምህርት ደረጃ መግለጫ (ማለትም፥ CV) እና ዝርዝር ማዘጋጀት ጀመርን።

    በዚህ የተናደዱት የሂደቱ ፊትአውራሪ የነበሩት የተከበሩ አቶ አስመላሽ ወልደሥላሴ [የህወሓት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል] ለሳምንት እንደገና እንየው ብለው በተኑት። በሳምንቱ ራሳቸው አጀንዳውን አንስተው mediators ያስፈልጋሉ/አያስፈልጉም እጅ አውጡ ሲሉ ጠየቁ። ከመድረክና ሰማያዊ ፓርቲ ውጭ ሁሉም አያስፈልጉም አሉ። በሳምንት ልዩነት 20 ለ 2 ውጤቱ ሲገለበጥ ወ/ሮ ሙፈሪሃት እጃቸውን በአፋቸው ጭነው ይታዘቡ ነበር።  እኔም በጣም ተበሳጭቼ “የተከበሩ አቶ አስመላሽ! ሳምንቱን ሙሉ ሲደልሉና ሲያስፈራሩ ሰንብተው ውጤቱን በጉልበት አስቀየሩት! ይሄ ጉልበት ግን አይቀጥልም፤ ነገ በሌላ ጉልበት ይሰበራል!” ብዬ ትቻቸው ወጣሁ። ሂደቱም ተጨናግፎ ቀረ (በወቅቱ ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 ሬድዮ ዘግቦታል)። ከ3 ዓመታት በኋላ እነአቶ አስመላሽን ወክለው አቶ አዲስዓለም ባሌማ ሁሉን አካታች ውይይት/ድርድር እናድርግ ብለው ሲጠይቁም፣ ያልተገባ ምላሽ ሲሰጣቸውም በተራዬ በትዝብት ተመለከትኩ።

    ዛሬ የመንግሥት አካል ከሆነው የሰላም ሚኒስትር መፍትሄው ውይይት/ድርድር ነው የሚል ተነሳሽነት ሲመጣ አያስፈልግም ብሎ መታበይም ሆነ ተለመንኩ ብሎ ማጣጣል አይገባም። ሚኒስትሯ እንዳሉት፥ ከስሜት ወጥቶ፣ ሰከን ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል። በእኔ እምነት ይሄ ትልቅ እርምጃ ነው፤ ቀጣዩን ታሪክ ለመሥራት መሽቀዳደም ለኢትዮጵያ ውለታ ነውና ማን ይሆን ፈጥኖ ወደ መቀሌ ከተማ ወይም ወደ ወለጋ ጫካዎች ነጭ ባንዲራ ይዞ የሚዘምተው? (የኬንያው Building Bridges Initiative (BBI) ጥሩ መማሪያ ይሆነናል) ወይም ወደአዱ ገነት የሚመጣው? የወጣቶቻችንን ህይወት ከመቀጠፍ፣ የእናቶቻችንን እንባ ከመፍሰስ የሚታደገው? ከፌደሬሽን ምክር ቤት? ከሰላም ሚኒስትር? ከሀይማኖት አባቶች? ከእርቀ-ሰላም ኮሚሽን? ከሀገር ሽማግሌዎች? ከግብረ ሰናይ ድርጅቶች? ከአባ ገዳዎች? ከጋሞ አባቶች? እናቶች? ከወጣቶች? ከህፃናት?… ማን ይሆን በሞራል ልዕልና እና በመንፈስ ከፍታ ቆሞ ከኢትዮጵያ ሰማይ ሥር የሚጥመለመለውን የጥላቻ አውሎ ነፋስ ገስፆ የሚያስቆመው? እስኪ “እኔ አለሁ” በሉ! (እኔ እንዳልሞክር ፓርቲ ውስጥ መሆን ይሄን ነፃነት አይሰጥም) ግን ኢትዮጵያ የሰው ድሃ አይደለችምና ፍጠኑ። ሰላም!

    የሺዋስ አሠፋ

    አቶ የሺዋስ አሠፋ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)  ሊቀ መንበር ሲሆኑ፤ ከዚያ በፊት ደግሞ የቀድሞው ሰማያዊ ፓርቲ ሊቀ መንበር ነበሩ።

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forums) ላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።

    አቶ የሺዋስ አሠፋ

    Anonymous
    Inactive

    የምንገኝበት የፖለቲካ ቀውስ፣ ፈጣን ፖለቲካዊ መፍትሔ ይፈልጋል!
    ከኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ሥራ አስፈፃሚ የተሰጠ መግለጫ

    በኢትዮጵያ ሕዝብ የረዥም ጊዜ መራራ ትግል 2010 ዓ.ም ላይ የመጣው ለውጥ ሕዝቡ ከነበረው ተስፋ በተቃራኒ የመክሸፍ አደጋ አጋጥሞታል።

    ከእንግዲህ በሀገራችን እውነተኛ ዴሞክራሲ እውን እንዲሆን፣ የዜጎች ሰብዓዊና ፖለቲካዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን፥ በእርግጠኝነት ደጋግሞ ቃል በመግባት ከፍተኛ የሕዝብ ድጋፍ አግኝቶ የነበረው የዶ/ር ዐቢይ አህመድ መንግሥት ለሕዝብ የገባቸውን ቃሎች ሁሉ በማጠፍ የለየለት አምባገነናዊ መንግሥት መሆን ጀምሯል።

    በዚህም ምክንያት የሀገራችንን ሰላምና መረጋጋት ክፉኛ የሚፈታተንና የሀገሪቱን አጠቃላይ ህልውና አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል ከፍተኛ የፖለቲካ ውጥረትና ቀውስ በሀገራችን ተከስቷል። በብዙ ዜጎች ከፍተኛ መስዋዕትነት የተገኘው ለውጥ መክሸፉና ሀገሪቱ ተመልሳ በሌላ አምባገነናዊ ሥርዓት ስር መውደቋ እጅግ ልብ የሚሰብር አሳዛኝ ክስተት ቢሆንም፥ የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ሀገራችንን ከውድቀት ለማዳን ዛሬም ዕድሉ በእጃችን ነው ብሎ ያምናል።

    ይህ ከውድቀት የመዳን እድል እውን ሊሆን የሚችለውም በአንድ ገዥ ፓርቲ የበላይነትና ፈላጭ ቆራጭነት፣ ወይንም ባለፉት 27 ዓመታት ያየነው ዓይነት ውጤቱ አስቀድሞ የሚታወቅ የይስሙላ ምርጫ በማካሄድ አይደለም።

    በኢዴፓ እምነት ከዚህ አሳሳቢ የህልውና አደጋ ወጥተን ወደ ተሻለ ሁኔታ ለመሸጋገር ቢያንስ የሚከተሉት አራት ተጨባጭ እርምጃዎች ሊወሰዱ ይገባል ብለን እናምናለን፤

    1. በሀገራችን የሕግ የበላይነት የመጥፋት ችግር እጅግ አሳሳቢ ወደ ሆነ የከፋ ደረጃ እየተሸጋገረ ነው። በኢዴፓ አመራር በአቶ ልደቱ አያሌው እና በሌሎችም የፖለቲካ ሰዎች ላይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሲሆን እንደታየው ሰዎች በፈጠራ ክስ ያለአግባብ የሚንገላቱበትና የፍርድ ቤቶች ውሳኔና ትዕዛዝ የማይከበርበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ያለ ፍርድ ቤት ነፃነት በአንድ ሀገር ላይ የሕግ የበላይነት ሊከበር ስለማይችል ፍርድ ቤቶችን ለፖለቲካ ጉዳይ ለመጠቀም፤ እና የፍርድ ቤቶችን ውሳኔ በመጣስ እየተፈፀመ ያለው ሕገ-ወጥ ድርጊት በአስቸኳይ መቆም አለበት።
    2. በአሁኑ ወቅት የኢዴፓ/አብሮነት፣ የኦፌኮ፣ የኦነግና የባልደራስ ከፍተኛ ዓመራሮች፣ እንዲሁም በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች /በተለይም በኦሮሚያ ክልል/ ከፖለቲካ ጋር በተያያዘ በእስር ላይ ስለሚገኙ በሀገራችን ከፍተኛ የፖለቲካ ውጥረት ነግሷል። ይህ አሳሳቢ ውጥረት ወደ ሌላ አሳሳቢ ደረጃ ከመሸጋገሩ በፊት ሁሉም ከፖለቲካ ጉዳይ ጋር በተያያዘ በእስር ላይ የሚገኙ ዜጎች ያለምንም ቅድመ-ሁኔታ በአስቸኳይ መፈታት አለባቸው።
    3. ሀገራችን በዚህ ዓይነት የፖለቲካ ውጥረት ውስጥ ሆና በፍፁም ሀገራዊ ምርጫ ለማካሄድ መታሰብ የለበትም። ከአሁን ጀምሮ እስከሚቀጥለው ሀገራዊ ምርጫ ድረስ ሀገሪቱ እንዴት ትተዳደር? ምርጫው ከመካሄዱ በፊት በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ ምን ዓይነት ውይይት እና ድርድር ይካሄድ? ከክልልነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ በደቡቡ የሀገራችን ክፍል ያለው የፖለቲካ ውጥረት እንዴት ይርገብ? ሀገሪቱ ቋሚ መንግሥት እስከሚኖራት ድረስ የኢኮኖሚ ደህንነቷን የሚያስጠብቅ ምን ዓይነት እርምጃ ሊወሰድ ይገባል? ያልለየለትን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭት በተመለከተ ምን ልናደርግ ይገባል? በሚሉትና በመሳሰሉ መሠረታዊ ጥያቄዎች ዙሪያ መፍትሄ ማመንጨት የሚያስችል አንድ ሁሉን አቀፍ የውይይትና የድርድር ሂደት /national dialogue / በአስቸኳይ መጀመር አለበት።
    4. በአሁኑ ወቅት በፌደራሉ መንግሥትና በትግራይ ክልል መካከል እየታየ ያለው ተገቢ ያልሆነና አሳሳቢ ፍጥጫ በአስቸኳይ መቆም አለበት። ጉዳዩ ከሀገሪቱ ሰላምና አንድነት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ እንደምታ ያለው እጅግ አሳሳቢ ጉዳይ በመሆኑ ያለምንም ቅድመ-ሁኔታ በውይይትና በድርድር መፈታት አለበት።

    በአጠቃላይ እነዚህ መሠረታዊ ጥያቄዎች በአግባቡ መመለስ ሳይችሉ ከቀሩና በሀገሪቱ ላይ የሚታየው ውጥረት የበለጠ ተባብሶ በዜጎችና በሀገር ላይ ለሚደርሰው ለማንኛውም የከፋ ጉዳት ዋናው ተጠያቂ ብልፅግና ፓርቲ መሆኑን እንገልፃለን። ከማንም በላይ የጉዳዩ እና የሀገሪቱ ባለቤት ሕዝቡ ነውና ከፍ ሲል የዘረዘርናቸው ጥያቄዎች በአስቸኳይ ተገቢ ምላሽ አግኝተው ሀገራችን ከውድቀት እንድትድን ሁሉም ሀገር ወዳድ ዜጋ በብልፅግና ፓርቲ ላይ ሕጋዊ እና ሰላማዊ ተፅዕኖ እንዲያደርግ ኢዴፓ ጥሪውን ያቀርባል።

    የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ
    ጥቅምት 3 ቀን 2013 ዓ.ም
    አዲስ አበባ

    የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ)

    Anonymous
    Inactive

    ሰላማችንን በማስጠበቅ እና ቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ ላይ በንቃት በመሳተፍ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠረት እንጣል!
    ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የተሰጠ መግለጫ

    ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ሊካሄድ የግዜ ሰሌዳ ወጥቶለት ሁሉም ባለድርሻ አካላት እንቅስቃሴ ከጀመሩ በኋላ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመታወጁ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያወጣውን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ እንዲሰርዝ መገደዱ ይታወሳል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በታወጀበት እና የምርጫ ሰሌዳው በተሰረዘበት ወቅት ወረርሽኙ በሌሎች የዓለማችን ሀገራት የጤና ሥርዓት ላይ ያስከተለውን ከፍተኛ ጫና እና በሰው ሕይወት ላይ ሲያደርስ የነበረውን ጉዳት በተጨባጭ በማየት የተለያዩ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ገደብ መደረጉ እና በዚህ ምክንያት ምርጫው መራዘሙ ተገቢ ነበር ብለን አምነናል።

    ምርጫው አለመካሄዱን ተከትሎ የመንግሥት ቀጣይነትን ለማረጋገጥ በተለያዩ ወገኖች የተለያዩ አማራጮች መቅረባቸው የሚታወስ ነው። የተለያዩ ፖለቲካ ፖርቲዎችም ከሕገ-መንግሥት ውጪ ያሉ አማራጮችን አቅርበው ነበር። ኢዜማ የመንግሥት ቀጣይነትን በሕጋዊ ማዕቀፍ ውስጥ መፍታት እንደሚቻል ጠቅሶ፥ አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ-መንግሥት ከሚሰጣቸው የመፍትሄ አማራጮች ውስጥ ደግሞ የመንግሥትን የሥልጣን ጊዜ እና ምርጫ የሚደረግበትን ጊዜ የሚደነግገውን የሕገ-መንግሥት አንቀጽ ከአቅም በላይ እና በድንገተኛ ምክንያት ምርጫ ማድረግ የማይቻልበት ሁኔታ ሲፈጠር የመንግሥትን ሥልጣን ከአንድ ዓመት ላልበለጠ ጊዜ ማራዘም እንዲያስችል አድርጎ ማሻሻል የተሻለ አማራጭ እንደሆነ ማቅረቡ ይታወሳል። ማሻሻያው ሥልጣን ላይ የሚቆየው መንግሥት የሥልጣን ጊዜ ገደብ ያስቀመጠ እና ውሳኔ የሚሰጥባቸው ጉዳዮች በቀጣይ ምርጫ አሸንፎ ሥልጣን የሚይዘው መንግሥት ላይ ግዴታ የማይጥሉ መሆናቸውን ባረጋገጠ መልኩ መሆን እንዳለበትም ምክረ-ሀሳብ አቅርበን ነበር።

    የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ክፍተቱን በሕገ-መንግሥት ትርጉም ለመሙላት ወስኖ የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ባቀረበው የውሳኔ ሀሳብ እና በፌደሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ምርጫውን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስጋት አለመሆኑ በጤና ሚኒስቴር እና የኅብረተሰብ ጤና ተቋም እስኪረጋገጥ ድረስ አራዝሞ የፌደራል እና የክልል መንግሥታት እና ምክር ቤቶችን የሥራ ጊዜ ያለገደብ እንዲቀጥል መወሰኑ ይታወሳል።

    ይህን ውሳኔ ተከትሎ ኢዜማ የጊዜ እና ውሳኔ የሚያሳልፍባቸው ጉዳዮች ላይ ወሰን ሳይደረግ ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት የሥራ ዘመን መራዘሙ ላይ ያለውን ተቃውሞ ገልፆ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለሕገ-መንግሥት አጣሪ ጉባዔ በገለጸው መሠረት አስፈላጊው ጥንቃቄ ተደርጎ ምርጫው መደረግ በሚችልበት ቅርብ ጊዜ እንዲደረግ ጠይቋል።

    በቅርቡ የጤና ሚኒስትር አስፈላጊው ጥንቃቄ እየተደረገ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ እንደሚቻል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባሳወቀው መሠረት ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ በያዝነው ዓመት እንዲካሄድ ውሳኔ ተላልፏል።

    ይህ በእንዲህ እያለ፥ “ሥልጣን ለማራዘም የተሄደበት መንገድ ሕገ-መንግሥታዊ አይደለም፤ በዚህም ምክንያት ከመስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም በኋላ መንግሥት የለም፤ ሕዝብ እና የመንግሥት መዋቅር ለፌደራል እና የክልል መንግሥታት ሊታዘዙ አይገባም» በሚል ቅስቀሳ ሲደረግ መቆየቱን እና አሁንም እየተደረገ እንደሚገኝ ለማስተዋል ችለናል

    ይህ ቅስቀሳ የሀገራችንን ሰላም እና መረጋጋት ከማወክ እና የዜጎችን ሕይወት አደጋ ላይ ከመጣል በዘለለ ፋይዳ እንደሌለው የኢትዮጵያ ሕዝብ በደንብ እንደሚገነዘብ እናውቃለን። ይህንን ቅስቀሳ እያደረጉ ያሉ አካላትም ከዚህ ተግባራቸው ተቆጥበው የጋራ ሀገራችን ሰላም እና የዜጎች ደህንነት ተጠብቆ በሰላማዊ መንገድ ችግሮቻችንን መፍታት ወደምንችልበት የውይይት መድረክ ከመምጣት ውጪ በሁከት እና በጉልበት ወደሥልጣን ለመውጣት የሚደረግ ማንኛውም እንቅስቃሴ ለራሳቸውም ቢሆን የማይጠቅም አደገኛ መንገድ መሆኑን ሊረዱ ይገባል። መንግሥትም እነዚህን ቅስቀሳዎች በንቃት እየተከታተለ አደጋ ከመድረሱ በፊት የመከላከል እና አደጋ ለማድረስ የሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ ሕጋዊ እርምጃ በመውሰድ የሀገር ሰላምን እና የዜጎችን ደህንነት የማስከበር ኃላፊነቱን እንዲወጣ እናሳስባለን።

    ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ዘንድሮ እንዲካሄድ የተወሰነውን ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ነፃ እና ፍትሃዊ ማድረግን ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባው እና ምርጫው እስከሚካሄድ እና የሕዝብ ድምፅ ያገኘው ተለይቶ እስከሚታወቅ ድረስ የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ፣ የሀገር ሉዓላዊነትን ማስከበር እና ምርጫውን ነፃ እና ፍትሃዊ ከማድረግ ጋር በቀጥታ ግንኙነት የሌላቸውን በተለይም በምርጫው የሚወዳደሩ ፓርቲዎች የተለያየ ፖሊሲ አቅርበው የሕዝብን ቅቡልነት ለማግኘት በሚወዳደሩባቸው ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ከማሳለፍ እና ከመተግበር እንዲቆጠብ እናሳስባለን።

    እኛንም ጨምሮ በሀገራችን የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሙሉ በነፃነት ተንቀሳቅሰው ሃሳባቸውን መግለፅ እንዲችሉ ከዚህ ቀደም በተስማማንበት የፖለቲካ ፓርቲዎች የቃል ኪዳን ሰነድ መሠረት የምናደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ሰላማዊ፣ ሕጋዊ እና የሌሎችን መብት ያከበረ መሆኑን እያረጋገጥን ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ነፃ እና ፍትሃዊ እንዲሆን የሚጠበቅብንን ሁሉ እንድናደርግ እንጠይቃለን። በሀገራችን የምትንቀሳቀሱ የሲቪክ ተቋማትም የፖለቲካ ፓርቲዎች የተስማሙበትን የቃልኪዳን ሰነድ እንዲያከብሩ ግፊት እንድታደርጉ እና በጋራ ሊሠሯቸው እና ሊስማሙባቸው በሚገቡ ተጨማሪ ጉዳዮች ላይ ውይይት ማድረግ የሚችሉበት መድረክ እንድታዘጋጁ የአደራ ጥሪያችንን እያስተላለፍን፥ በመድረኮቹ ላይ በንቃት ለመሳተፍ ያለንን ፍላጎት ከወዲሁ ለመግለጽ እንወዳለን።

    መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ በሀገራችን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ለምንገነባው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መደላድል የምንጥልበት ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑን በመገንዘብ የምርጫውን ሂደት ከአሁን ጀምሮ በንቃት እንዲከታተል እና ምርጫው ሰላማዊ፣ ነፃ እና ፍትሃዊ መሆኑን ለማረጋገጥ የሚጠበቅባችሁን ሁሉ እንድታደርጉ የአደራ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።

    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)
    መስከረም 26 ቀን 2013 ዓ.ም

    ሀገራዊ ምርጫ

    Anonymous
    Inactive

    የሞኝ ለቅሶ መልሶ መላልሶ! ኦሪት ዘህወሓት!
    (ታዬ ዳንደአ)

    የግራ አስተሳሰብ ሁሌ ግራ ተጋብቶ ግራ ያጋባል። ህወሓት የግራ ጁንታ መሆኑ ይታወቃል። የግራ ፖለቲካ ደግሞ ውሸት ሲደጋገም እውነት እንደሚሆን ያምናል። “መስከረም 25/30” የሚደጋገመዉ ለዚህ ይመስላል። ህወሓት ከፈረሶቹ ጋር ብቅ ጥልቅ እያለ ይፎክራል። በሕገ-መንግሥት እና በፌዴራሊዝም ስም ያለቃቅሳል። ከመስከረም 25/30 በኋላ መንግሥት ስለማይኖር “ባለአደራ መንግሥት ከሰማይ ይዉረድልኝ” ይላል። ኢትዮጵያን ወደ ሊቢያ ለመቀየር አቅዶ በሙሉ ኃይሉ ይንደፋደፋል! በእርግጥ ዋነኛ እቅዱ ሰኔ 2012 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ተሞክሮ በኢትዮጵያዊያን የተባበረ ክንድ ከሽፏል! አሁን ቅዠትን እዉነት ለማድረግ በህወሓት አሻንጉሊቶች በከንቱ ዳንኪራ ይመታል። ይህ በአማርኛ ‘የሞኝ ለቅሶ መልሶ መላልሶ’ ይባላል!

    የህወሓት ህልም ሩቅ ኖሯል። ኢትዮጵያዊያንን ከፋፍሎ እየገዛ ለመቶ ዓመታት ኢትዮጵያን የመጋጥ ግልፅ ዕቅድ እንደነበረዉ ይታወቃል። በዚሁ አግባብ ለ27 ዓመታት በኢትዮጵያዊያን ሰቆቃ ውስኪ እየተራጬ ሲንደላቀቅ ኖሯል። ያ ሁኔታ መጋቢት 2010 ዓ.ም. ላይ አክትሟል። በኢትዮጵያ ሕዝብ የዘመናት ትግልና በለውጥ አመራሩ ቆራጥ ውሳኔ የህወሓት ጉልበት ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ተንኮታኩቷል፤ ነገር ግን እዉነታዉ አልዋጥ ብሎታል። የቀን ቅዠት እዉን እየመሰለዉ አስቸግሮታል! ሁሌ ድምፂ ወያኔ ላይ ወጥቶ “ከመስከረም በኋላ ከኔ ውጭ ሌላ የለም” ይላል። “የለም! የለም!” እያለ ግልፅና ተጨባጭ እዉነታን መሰረዝ ይፈልጋል። መቼስ ከዚህ በላይ የሚገርም በዓለም ላይ ምን ይኖራል? ህወሓት ከነሙሉ ጥርሱና ጥፍሩ በነበረበት ወቅት ታግሎት ያቃተዉን ለዉጥ ከሬሳ ሳጥን ደጃፍ ሆኖ “የለም!” በማለት ብቻ ለመቀልበስ ይሞክራል!

    ዘንድሮ ‘ሰይጣን ለተንኮሉ ቅዱሳን መጽሐፍትን ይጠቅሳል’ የሚባለዉ በግልፅ መታየት ጀምሯል። ህወሓት በምክንያት የኢሬቻ 2013 ዋነኛ አቀንቃኝ ሆኖ ብቅ ብሏል። በኢሬቻ አስታኮ አዲስ አበባ ላይ ተጀምሮ አዲስ አበባ ላይ እንዲያልቅ ታቅዶ የከሸፈዉን ጦርነት ዳግም ለማወጅ ፈልጓል! ፍላጎቱን ለማሳካት ደግሞ በኦሮሞ ስም የሚነግዱ አሉላ የሚቀልባቸዉን ፈረሶች አዘጋጅቷል! በፈረሶቹ በኩል የኦሮሞ ወጣት ኢሬቻን አሳቦ በነቂስ በመዉጣት ሸገር ላይ እንዲረብሽ ይቀሰቅሳል። በዲጂታል ወያኔ ደግሞ “ኢሬቻ የሰይጠን አምልኮ ነዉ” እያለ በአማራ ስም ያሰራጫል። የኦሮሞን ሕዝብ ‘ጋኔን’ ያለዉ ህወሓት መሆኑ ግን ይታወቃል። በተጨማሪም “ኢሬቻ አዲስ አበባ ላይ መከበር የለበትም!” እያለ በሌላዉ አሻንጉሊቱ በኩል የሸገር ወጣቶችን ይቀሰቅሳል። ኢሬቻ 2009ን የዘነጋነዉ መስሎታል። ያኔ ቢሾፍቱ ላይ በአንድ ቀን ብቻ ከ700 በላይ የኢሬቻ ታዳሚ ኦሮሞዎች በወያኔ አግዓዚ ገደል ውስጥ ተጥለዉ ሞቷል። በዚያ ወሳኝ ወቅት “የኦሮሞ ደም ደሜ ነዉ” ያሉትን የጎንደር ወጣቶች ታሪክ መዝግቧል። ኢሬቻን መደገፍ እና ማሞገስ ከቁርጥ ቀን ወገኖች ያምራል! ዛሬ ወያኔ በግራና በቀኝ የሚያጫውታቸዉን አሻንጉሊቶች ማን ይሰማል?

    ታዲያ በመጨረሻ ምን ይሆናል? ውሾቹ እየጮሁ ግመሉ ይጓዛል! ባቡሩ ፍጥነቱን እና አቅጣጫዉን ጠብቆ ወደፊት ይገሰግሳል። ኢትዮጵያዊያን ለዘመናት በከፈሉት ውድ ዋጋ የመጣዉ ለውጥ ከመስከረም 25/30 በኋላም ተጠናክሮ ይቀጥላል! የተቋማት ግንባታ እና ብሔራዊ ውይይት መሠረት ይይዛል። በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት ይፈጠራል። ህወሓት ሲያበላሸዉ የነበረዉ ብሔራዊ ምርጫም በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ግልፅ፣ አሳታፊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ ይከወናል። የማይኖረዉ ህወሓት እና ተፅዕኖዉ ብቻ ይሆናል። ጓድ ህወሓት ቀስ እያለ ወደ መቃብሩ ጠጋ ጠጋ ይላል! በትግራይ ላይ ጠባሳ ሳይጥል፤ ማንም ሳይነካዉ ራሱን ችሎ ይሞታታል! የትግራይ ሕዝብም እንደወገኖች የነፃነትን አየር ይተነፍሳል! አሉላ ፈረሶቹን የሚቀልብበት መኖ ያጣል። በዚያዉ ጋብቻዉ ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ ይፈርሳል። አሻንጉሊትም አስታዋሽና አጫዋች ያጣል! የሴራና የሸር ሥራ ብኩን ይሆናል። የሌብነት፣ የውሸት፣ የፅንፈኝነት እና የክፋት ዘመን ያበቃል! እዉነት እና ዕዉቀት መርህና መመሪያ ይሆናል! የኢትዮጵያ ኅብረ-ብሔራዊ አንድነት እና ብልጽግና ደግሞ እየጎለበተ ይሄዳል! የኢትዮጵያ ሕዝብ ወንድማማችነትን መሠረታዊ መርሁ አድርጎ በድል ላይ ድል ይጎናጸፋል! ይህ ቃል ነዉ! ቃል ይነቅላል! ቃል ይተክላል! አሜን!!

    ታዬ ዳንደአ

    አቶ ታዬ ዳንደአ የኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲ ቃል አቀባይ ናቸው።

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forums) ላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።

    አቶ ታዬ ዳንደአ

    Anonymous
    Inactive

    ግልፅ ደብዳቤ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ለክብርት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ
    ነጋችንን እንዳንፈራ ሕግ ተርጓሚው ይፈራ!

    ክብርት ፕሬዝደንት፥ እንደሚያውቁት የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ባለፉት 20 ዓመታት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በጭፍን ከመደገፍ እና ከመቃወም ወጥቶ በምክንያት መቃወም እና መደገፍ የፖለቲካ ባህል፣ አስተሳሰብ እንዲገነባ የራሱን ሚና ሲጫወት የቆየ ፓርቲ ነው። ይሄ ስልጡን የፖለቲካ ባህል እንደምንፈልገው ፍሬ ባያፈራም ቀላል የማይባል የፖለቲካ ባህል ለውጥ ጭላንጭል አይተናል ብለን እናስባለን። ይህን አዲስ ባህል የፈጠረ ፓርቲ ግን ለሱ የሚመጥነውን ያህል ክብር ሊሰጠው ቀርቶ በየዘመኑ የመጡ ገዥዎች አና ጽንፈኛ ፖለቲከኞች በሴራ አላላውስ ብለውታል።

    ኢዴፓ ከለውጡ በፊት ባሉት ሁለት ዓመታት እና ከለውጡ ማግስት ባሉ ሁለት ዓመታት የተቀነባበረ በሚመስል ደረጃ ፓርቲያችንን የማዳከም እና ከፖለቲካው መድረክ እንዲገለል የማድረግ ከፍተኛ ደባ እየተሠራበት ይገኛል። ይህን በፓርቲው ህልውና ላይ የተቃጣውን መሠረተ ሰፊ የማፍረስ እርምጃ በተለያዩ መድረኮች እያሸነፍን እዚህ ብንደርስም፥ አሁንም ድረስ በግፍ የተነጠቅነውን የፓርቲውን ቢሮዎች፣ ንብረቶች ገንዘቦች እና ሰነዶች ለማስመለስ በፍትህ አደባባይ እየታገልን ነው። አሁንም በቢሮክራሲ ውጣ ውረድ እየተንገላታን ነው፤ ባለፉት አራት ዓመታት በፓርቲያችን ህልውና ላይ እየደረሰ ያለውን ፈተና እየታገልን ባለንበት ሁኔታ ይባስ ብሎ የአርቲስት ሃጫሉን ሞት ተከትሎ ሌላ የፖለቲካ ጫና እየደረሰብን ይገኛል። ይኸውም የፓርቲያችን ብሔራዊ ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ልደቱ አያሌው ያለጥፋታቸው የፖለቲካ ጥቃት ሰለባ እንዲሆኑ ተፈርዶባቸዋልል። አቶ ልደቱ በወንጀል ድርጊት ውስጥ መሳተፋቸው በተጨባጭ ማስረጃ እስከተረጋገጠባቸው ድረስ አይያዙ አንልም፤ ለሕግ የበላይነት ሲታገል የኖረ ፓርቲ በዚህ ረገድ ምንም ብዥታ የለበትም። ነገም ከነገ ወዲያም ማንም በፖለቲካ ፓርቲ አመራርነትና አባልነት ስም ከሕግ ማምለጥ አለበት ብለን አናምንም፤ ነገር ግን ፖሊስ እርቸውን አስሮ ማስረጃ ሲፈልግ ሲታይ፣ ማስረጃ ማቅረብ ተስኖት ፍርድ ቤት ልቀቅ ብሎ ሲወስን እምቢኝ ካለ የታሰረው ወንጀል ሠርቶ ሳይሆን ለምን የተለየ አሰብክ ተብሎ እንደሆነ ድርጊቱ ያሳብቃል። ከዚህ በተጨማሪ አቶ ልደቱ መንግሥት ላይ የሰላ ትችት በማቅረባቸውና በመቃወማቸው ብቻ እንደታሰሩ በፍትህ ሂደቱ ላይ የታዩትን ህጸጾች ስለታዘብኩ ነው ለእርስዎ አቤት ማለቴ። አቶ ልደቱ የሃጫሉን ሞት ተከትሎ ሁከት በተቀሰቀሰበት ሰዓት የፌዴራል ፖሊስ ለህይወትህ ያሰጋሃል ብሎ አጅቦ ከቢሾፍቱ ወደ አዲስ አበባ አምጥቷቸዋል። ይሄ ሆኖ ሳለ በፖሊስ የተከሰሱበት እና የተጠረጠሩበት ወንጀል የቢሾፍቱ ከተማ ወጣቶችን አደራጅተሃል፣ በገንዘብ ረድተሃል እና አስተባብረሃል ቢሆንም ተጨባጭ ማስረጃ ፖሊስ ለፍርድ ቤት ሊያቀርብ አልቻለም። በኋላም የተሰጠውን የምርመራ ግዜ በመጨረሱና አቃቢ ሕግም ተጨማሪ የምርመራ ግዜ ባለመጠየቁ ፍርድ ቤቱ በነፃ አሰናብቷቸዋል። ነገር ግን ይህንን የፍርድ ቤት ውሳኔ ሰምቶ ፖሊስ መልቀቅ ሲገባው፥ ከ17ቀናት በላይ በሕገ-ወጥ መንገድ አስሮ ሲያሰቃያቸው ቆይቷል። እኛም በፍትህ ሂደቱ ተስፋ ቆርጠን፣ አቶ ልደቱም ጠበቆቻቸውን አሰናብተው ፌደራል ላይ አካልን ነፃ የማውጣት ክስ ልንመሠርት ስንዘጋጅ ደግሞ ሌላ ክስ አዳማ ላይ ተከፈተባቸው።

    ይሄ ክስ በመጀመሪያው የቢሾፍቱ ከተማ የክስ መዝገብ ላይ ሕገ-ወጥ ሽጉጥ ተገኝቶባቸዋል ተብሎ ማስረጃ ቀርቦበት ውድቅ የተደረገ የክስ ጭብጥ ነው። የሆነው ሆኖ በሕገ-ወጥ መሣሪያ በመያዝ በሚል ምሥራቅ ሸዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቢከሰሱም ፍርድ ቤቱ የአቃቢ ሕግንና የጠበቆቻችንን የሕግ ክርከር መርምሮ አቶ ልደቱን በ100,000 (አንድ መቶ ሺህ) ብር ዋስትና ውጭ ሆነው እንዲከራከሩ ወሰነ። እኛም 100,000 (አንድ መቶ ሺህ) ብር አስይዘን ማስፈቻ ትዕዛዝ ለፖሊስ ብንወስድም አሁንም ፖሊስ ትዕዛዙን አልፈፅምም አለ። እኛም ትዕዛዙን ለሰጠው ፍርድ ቤት አቤት ብለን መልስ ሊነገረን ለበነጋታው ቀጠሮ ይዘን መጣን። ነገር ግን ማታ የአቶ ልደቱ ዋስትና እንደታገደ በመገናኛ ብዙኃን ሰማን። በዚህ ሁኔታ አቶ ልደቱ ከልብ ህመም ጋር ተያይዞ የልብ ቀዶ ጥገና ባደረጉበት አሜሪካ ቀጠሮአቸው እንዲያልፍ ተደርጎ፥ ከዚህ በተጨማሪ ካለባቸው የአስም ህመም የተነሳ ለኮሮና ተጋላጭ መሆናቸው በሐኪሞችም በፍርድ ቤቶቹም ታምኖበት ጭምር ውጭ ሆነው እንዲከራከሩ የተደረገው ጥረት በፖሊስ እምቢተኝነት ህይወታቸው አደጋ ውስጥ እንዲወድቅ ተደርጓል። በሂደቱ ሁሉ አቶ ልደቱ እያቀረቡት ያለው ቅሬታ ሁሉ ተቀባይነት እያጣ፣ የፍርድ ቤት ውሳኔ እየተሻረ የፖለቲካ ውሳኔ አሸናፊ እየሆነ ይገኛል። አሁንም እንደቀጠለ ነው። እና በፍትህ አደባባይ አቶ ልደቱ ደግመው ደጋግመው ነፃ ቢሆኑም ፖሊስ አለቅም ማለቱን ሳይ ነው የአቶ ልደቱ እስር ሕግ ጥሰው ሳይሆን በፖለቲካ እስር ነው ብዬ በእርግጠኝነት መናገሬ፤ እንጂማ ሁለቴ ያሸነፈ አይደለም አንድ ግዜም ያሸነፈ ቤቱ እስር ቤት አይሆንም ነበር። ይሄ የሚያሳየው የፍትህ ሥርዓቱ ላይ የበዛ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት መኖሩን ነው።

    ክብርት ፕሬዝደንት፥ የፍትህ ተቋሙ በእርስዎ መመራት ሲጀምር በፍትህ መጓደል ላለፉት 27 ዓመታት ፍዳውን ሲያይ የነበረው ዜጋ እፎይ ይላል ብዬ በግሌ ተስፋ አድርጌ ነበር፤ ሕግ ተርጓሚው ከሕግ አስፈፃሚው ተፅዕኖ ወጥቶ የሚገባውን ክብር እና የሚወስነውም ውሳኔ በአስፈጻሚው አካል ሳይሸራረፍ ተፈፃሚ ይሆናል ብዬም ነበር። ፍትህ እና ርትዕ በእርስዎ አመራር ይሰፍናል ብዬ በእርስዎ የቀደመ ልምድ ፍፁም ተማምኜ የነበረ ቢሆንም እየሆነ ያለው የተገላቢጦሽ ነው። ፍትህ ከቀደመው ጊዜ በባሰ ችግር ውስጥ መውደቁን እኔ በግሌ በዚች ሁለት ወር በተግባር ባየሁት ነገር አረጋግጫለሁ። እርስዎ የተሰጠዎትን ኃላፊነት ያለምንም ፍርሃት እና ይሉኝታ ለመወጣት ከሞከሩ የፍትህ ሥርዓቱ ወደ መስመር ውስጥ መግባቱ አይቀርም፤ ግን ክብርት ፕሬዝደንት ለተቋማዊ ለውጥና ከታሪክ ተጠያቂነት ለመዳንም የበኩልዎን ይወጡ።

    ክብርት ፕሬዝደንት፥ ዜጋ በፍትህ ሥርዓቱ ተስፋ ሲቆርጥ ለሥርዓት አልበኝነት መንገድ ይከፈታል፤ የሞራል ልዕልና ቦታ አጥቶ ፍትህ በየአደባባዩ ትረገጣለች፤ ዜጋ በራሱ መንገድ ፍትህን ይፈልጋል፤ ፍትህን በራሱ ህሊና ተመርቶ ለመስጠት ይገደዳል። ያኔ እንደ ሀገር ዜጋው ወጥቶ የመግባት፣ ሠርቶ ሀብት ንብረት የማፍራት መብቱ አደጋ ውስጥ ይወድቃል። ስለዚህ እርስዎ የሚመሩት ተቋም ክብርና ሞገሱን ካጣ የሀገር ክብር እና ሞገስ ጠፍቶ እንደ ሀገር የመኖር ህልውናችንም አደጋ ውስጥ ይወድቃል። የመንግሥት መኖር ምልክት የሆነው ሕግና ሥርዓት ጠፍቶ ባለፈው እንዳየነው በየአካባቢው የደቦ ፍርድ ይነግሳል። አቶ ልደቱስ በፖለቲካው ባላቸው ተደማጭነት እና ተሰሚነት ድምፅ የሚሆናቸው ብዙ ነው። በዚህ ሁኔታ ተራው ዜጋ ምን ያህል በፍትህ ሥርዓቱ ፍዳውን ሊያይ እንደሚችል ተገንዝበውታል? ለእርስዎ ተቋም ክብር የሚመጥን የፍትህ ሥርዓት አለ ብለው ያምናሉ? አይመስለኝም ፍትህ እና ርትዕ እንዲሰፍን፣ እንዳይጓደል የበለጠ ሥራ በመሥራት የዳኞችን ክብር ያስመልሱ። ዳኞች የሚፈርዱት ፍርድ በአስፈፃሚው አካል ሲደፈጠጥ ማየት ያሳፍራል፣ ያሸማቅቃል ነገን እንድፈራ ያደርጋል። ነጋችንን እንዳንፈራ ሕግ ተርጓሚው ይፈራ! ስለዚህ ክብርት ፕሬዝደንት፥ ጉዳዩ የአቶ ልደቱን ጉዳይ የፍትህ መጓደል ብቻ አድርገው አይቁጠሩት። በህይወት የመኖር እና ያለመኖር የመብት ጥያቄ ነው እያቀረበ ያለው። በፍርድ ቤት ውሳኔ ሳይሆን በአስፈፃሚው ጡንቻ በህይወቱ ላይ አንድ ነገር ቢደርስስ ማን ነው ተጠያቂው? በተለይ የሃጫሉን ሞት ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል የታዘብኩት ዜጎች ወደ ፍትህ ሳይቀርቡ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ እየተጉላሉ መሆኑን ነው። በየማጎሪያው እየተሰቃዩ ነው፤ የፍትህ ያለ እያሉ ነው። አሁንም እደግመዋለሁ ወንጀል የፈፀመ አይታሰር አልልም፤ ግን ከሕገ-መንግሥቱ ድንጋጌ ውጭ ዜጎች መጉላላት የለባቸውም፤ የተፋጠነ ፍትህ ይሰጣቸው፤ ሰብዓዊ መብታቸው ይጠበቅላቸው። ይህን በሁለት ወር ውስጥ የታዘብኩት ነው። ይህ የሚያሳየው የፍትህ መጓደል በሌሎች ክልሎች ላይም ቀላል በማይባል ደረጃ ችግሩ መኖሩን ነው። በቢሾፍቱና አዳማ ዋስትና ተፈቅዶላቸው ከወር በላይ ፖሊስ አለቅም በማለቱ በእስር የሚማቅቁ ብዙ ዜጎች እንዳሉ ያገኘኋቸው የሕግ ባለሙያዎች አጫውተውኛል። ፍትህ ተጠምተው በየእስር ቤቱ የሚሰቃዩ ብዙዎች ናቸው። ለፍትህ መከበር ሁሉም ሊጮህ ይገባል። ፍትህ በጉልበተኞች ጫማ ሲደፈጠጥ ሥርዓት አልበኝነት ይነግሳልና!

    ክብርት ፕሬዝደንት መዓዛ፥ ይህችን ግልፅ አቤቱታዬን ሰምተው በፍትህ ሥርዓቱ ላይ ነፍስ ይዘሩበታል፤ በየማጎሪያ ካምፑ ያሉ የብዙ ዜጎችን እንባ ያብሳሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። አመሰግናለሁ።

    ከከበረ ሰላምታ ጋር!
    አዳነ ታደሰ
    የኢዴፓ ፕሬዝደንት

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forums) ላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።

    የጠቅላይ ፍርድ ቤት ክብርት ፕሬዝደንት መዓዛ አሸናፊ

    Anonymous
    Inactive

    በብሔራዊ መግባባት ዙሪያ ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) ጥናታዊ ጽሁፍ አቀረበ

    አዲስ አበባ (ነእፓ) – በኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አስተባባሪነት በሀገራችን ብሔራዊ መግባባት በመፍጠር ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም ዴሞክራሲያዊ ሽግግር እውን ለማድረግ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የመጀመሪያ ዙር ውይይት ነሐሴ 16 ቀን 2012 ዓ.ም መካሄዱ ይታወሳል። የዚሁ መድረክ ሁለተኛ ዙር ውይይት ነሐሴ 30 2012 ዓ.ም በአዲስ አበባ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ECA) ተካሂዷል።

    በውይይቱ ላይ በከፍተኛ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች አራት የተለያዩ ጽሁፎች የቀረቡ ሲሆን፥ የነጻነትና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ) ሊቀመንበር ዶ/ር አብዱልቃድ አደም “ብሔራዊ መግባባት በኢትዮጵያ፡ ዘላቂ ሰላም፣ ሀገራዊ አንድነት እና ዴሞክራሲያዊ ሽግግር” በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሁፍ አቅርበዋል።

    ዶ/ር አብዱልቃድር የብሔራዊ መግባባት ምንነት፣ አጠቃላይ ማዕቀፍ፣ አደረጃጀት፣ ዓለም አቀፍ ተሞክሮ እና ሌሎች ከብሔራዊ መግባባት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በዝርዝር ያቀረቡ ሲሆን ብሔራዊ መግባባትን አስመልክቶ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ግልጽ እና ተቀራራቢ አቋም እንዲኖራቸው ለማድረግ እንዲሁም ብሔራዊ መግባባትን አስመልክቱ የተሳሳቱ ግንዛቤዎችን ለማስተካካል ጥናታዊ ጽሁፉ ከፍተኛ ፋይዳ እንደነበረው በውይይቱ የተሳተፉ የፖለተካ ፓርቲዎች ገልጸዋል።

    የቀረበው ወረቀት (ጥናታዊ ጽሑፍ) በሀገራችን በቅርቡ ይጀመራል ተብሎ በሚጠበቀው ሁሉን አቀፍ የብሔራዊ መግባባት ሂደት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንደሚኖረው ይታመናል።

    ነእፓ ቀደም ሲል በሀገራችን በብሔራዊ መግባባት ዙሪያ የመነሻ ጽሁፍ  በማዘጋጀት ሀሳቡን ለመንግስት፣ ለፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ለሲቪክ ማኅበራትና በኢትዮጵያ ለሚገኙ የውጪ ሀገር የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ ማሰራጨቱ ይታወሳል።

    ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ በሀገራችን ሰላም፣ መረጋጋትና አንድነት እንዲሰፍን፣ ቀጣዩ ምርጫ ነጻ ፍትሀዊ እና ቅቡል እንዲሆን ሁሉን አቀፍ የብሔራዊ መግባባት ሂደት በአፋጣኝ መካሄድ እንዳለበት በጽኑ ያምናል። ይህንኑ እውን ለማድረግ ፓርቲው የጀመረውን ጥረት ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን አጠናክሮ ይቀጥላል።

    በመድረኩ የቀረበውን ጽሁፍ እዚህ ሊንክ ላይ በመጫን ማግኘት ይቻላል።

    ምንጭ፦ ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ (ነእፓ)

    ተመሳሳይ ዜናዎች

    ነጻነትና እኩልነት ፓርቲ

    Anonymous
    Inactive

    የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) መግለጫ
    መስከረም 13፥ 2020

    የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ለኢትዮጵያ ውስብስብ የፖለቲካ ችግሮች አስተማማኝና ዘላቂ መፍትሄ ሊገኝ የሚችለው ሁሉን በሚያካትት ዴሞክራሲና በሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ተሳትፎ ብቻ ነው የሚል ቅን እምነት አለው። ይህንንም ለማድረግ ኦነግ ሀገሪቱን የማስተዳደር ስልጣን ያላቸውን እና የተቃዋሚ ቡድኖችን ጨምሮ ከተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች ጋር በመሆን በኢትዮጵያ የፖለቲካ ቀውሶችን ለመፍታት የጋር ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር ሲሠራ ቆይቷል። ኦነግ ከፍተኛ አመራሩን ወደ ሀገር ካዛወረ እ.ኤ.አ. ከመስከረም 15 ቀን 2018 ወዲህ ወደ ሁሉን አቀፍ እውነተኛ ዴሞክራሲ የሚያመራውን የሰላም ሂደት ስኬታማ ለማድረግ በሐቀኝነትና በታማኝነት ለመሥራት ወሰነ።

    ምንም እንኳን ከመጀመሪያው ጀምሮ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሽግግር አያያዝ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መንግሥት እንዴት እንደተከናወነ አስመልክቶ ኦነግ ደስተኛ ባይሆንም፣ ይሻሻላል ብለን ተስፋ በማድረግ ሁኔታዎችን በትዕግስት ተቋቁመናል፤ ያለ ዋጋ ግን አይደለም።

    ሆኖም እ.ኤ.አ. በ2018 የተጀመረው የፖለቲካ ለውጥ ከውስጥ ከገዢው ፓርቲ እንዲሁም ከውጭ ከተቃዋሚ ቡድኖች ግዙፍ ተግዳሮቶች አጋጠመው። ሁኔታዎቹ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሱ በመሄድ በአሁኑ ወቅት ሁሉም ነገር ከቁጥጥር ውጭ ወደሆነበት ደረጃ በመድረስ መንግሥትን ወደ ውድቀት እያመራው ይገኛል። አሁን በሀገሪቱ ውስጥ በጣም እጅግ አሳሳቢ አለመረጋጋትና የተሰበረ ፖለቲካ ተስፋ ይስተዋላል፤ ሕዝቡ ከገዢው ፓርቲ ተስፋና እምነት አጥቷል። በሀገሪቱ ውስጥ ግልጽ “የሕገ-መንግሥታዊ ቀውስ” የተመለከትን ሲሆን፥ በስልጣን ላይ ያለው ፓርቲ መጀመሪያ ከገባቸው ቃላት ማሽቆለቆሉና ሕገ-መንግሥቱን የማስጠበቅ ኃላፊነት ያለባቸውን የመንግሥት አካላት ለራሱ የፖለቲካ ጥቅም ሲገለገልባቸው ቆይቷል።

    የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮችንና አባላትን ማሰርና ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የዕለት ተዕለት ሥራ ናቸው። ምንም እንኳን የጭካኔ ድርጊቶች ቢኖሩም፤ ኦነግ እና ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለውጡን በተናጥል እንዲሁም በጋራ ለመደገፍ ያላቸውን ፍላጎት መግለፃቸውን ቀጥለዋል።

    በተናጠል ካለው የመፍትሄ ሀሳብ በተጨማሪ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ዴሞክራሲያዊ ሽግግሩን ለመደገፍ በተለያዩ የተቃዋሚ ፓርቲዎች መድረክ ላይ ተሳትፏል። ከመድረኮቹ መካከል ለሽግግሩ እና ለዴሞክራሲያዊ ሂደቱ የጋራ ድጋፍ ለመስጠት ያለመው ትብብር ለሕብረ-ብሔር ዴሞክራሲያዊ ፌዴራሊዝም (ትብብር) አንዱ ነበር። እ.ኤ.አ. በሚያዝያ 2020 ይህ ትብብር በሽግግር ሂደት ላይ ለመንግሥት ሁሉን አቀፍ የመፍትሔ ምክረ-ሀሳቦችን አቅርቧል። የመፍትሄ ምክረ-ሀሳቦቹ በመግባባት ላይ ለተመርኮዘ የፖለቲካ እልባት በለውጡ እንዴት መቀጠል እንደሚቻልና የተረጋጋ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር እንዴት በደረጃ-በደረጃ ሂደት ሊመሠረት እንደሚችል በግልጽ አስቀምጧል።

    የመፍትሄ ሀሳቦቹ በኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት ማዕቀፍ ውስጥ የተቀረፁ ሲሆን የለውጡ ሂደት ስህተቶችና የገዢው ፓርቲ ባህሪይ፣ አሁን ያሉ የአለመረጋጋትና የፀጥታ ጉዳዮች፣ እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ግምት ውስጥ ያስገባ ነው። በአጠቃላይ የለውጥ ሥርዓቱን ተግዳሮቶች በሁለቱም አቅጣጫዎች (ገዢው ፓርቲ እና ተቃዋሚዎች) በመተንተን በገዢው ፓርቲና በተቃዋሚ ቡድኖች በጋራ የሚተገበር ተግባራዊ የመፍትሔ ምክረ-ሀሳብ አቅርበናል።

    የቀረቡት ሀሳቦች ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሳተፉ የሚያስችላቸው አስገዳጅ የፖለቲካ ኮንቬንሽን እንዲኖርና እውነተኛ ዴሞክራሲን ለመገንባትና በሀገሪቱ ውስጥ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ለማድረግ የለውጡ ሂደት ትክክለኛ ቁጥጥርን ለማረጋገጥና ትብብሩና አባል ድርጅቶች እንዲሁም ሌሎች ኃይሎች ሁሉ የበኩላቸውን ሚና የሚጫወቱበትን የዜጎች ኑሮ መሻሻልን ያረጋግጣል።

    የታሰበው አስገዳጅ የፖለቲካ ኮንቬንሽን የሚከተሉትን ያካትታል፦

    1. የውጭ ግንኙነት ምክር ቤት፦ የሀገር ውስጥ አመኔታን ለማነሳሳት እና ዓለምአቀፍ ተቀባይነት እንዲያገኝ ለማድረግ
    2. የተቀናጀ ብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት፦ በክልሎች ውስጥ የፀጥታ አደረጃጀቶችን ትግበራ ለመከታተል
    3. የዴሞክራሲ ግንባታ ተቋም፦ አስፈፃሚዎችን ተጠያቂ ሊያደርጉ የሚችሉ ገለልተኛ የፍትህ አካላት፣ የምርጫ ቦርድና ነጻ ሚዲያ ራስን ማስተዳደርና ስልጣንን ለመጠበቅ
    4. ከፍተኛ የፖለቲካ ችግሮችን ለመፍታት ብሔራዊ የጋራ መግባባት እንዲፈጠር መንግሥት ግንባታና በሀገር ግንባታ መካከል ያሉ አለመግባባቶችንና ልዩነቶችን የሚፈታ አካል
    5. ማንኛውንም ለምርጫው የሚደረግ ሌላ የጊዜ ማራዘሚያ ጥያቄን ለመገደብና አመቺውን የምርጫ ቀን ለማስቀመጥ የኮንቬንሽኑን አፈፃፀም የሚከታተል አካል

    በተጨማሪም እነዚህ አካላት የሚሠሩበትን የኃላፊነት፣ የሥርዓትና የአሠራር ዘዴ ዝርዝርን ጨምሮ የመፍትሔ ምክረ-ሀሳቦቹን ተግባራዊነት አመልክተናል። እነዚህን የመፍትሔ ሀሳቦች ተግባራዊ ማድረጉ ዴሞክራሲን ለመገንባትና በሀገሪቱ ውስጥ ዘላቂ ሰላም ለመፍጠር ይረዳል ብለን እናምናለን። ከዚህም ሌላ በክልላዊ መንግሥታት መካከል ያለውን የፀጥታ ጉዳዮች እንዲሁም በመንግሥትና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል እና በተቃዋሚዎች እርስ በርሳቸው መካከል ያሉ ልዩነቶችን እንዲሁም “በመንግሥት ግንባታ” እና “በሀገር ግንባታ” ላይ ተቃራኒ አቋም ላላቸው ጉዳዮችም መፍትሄ ያቀርባል።

    ስለሆነም በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የተስፋፉ ቀውሶችን ይፈታል ብለን ስለምናምን የኢትዮጵያ መንግሥት እነዚህን የመፍትሄ ምክረ-ሀሳቦች እንደገና እንዲያጤን በጥብቅ እናሳስባለን። እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን የሚወጡ ከሆነ በእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሂደት ውስጥ የበኩላችንን ለመወጣት ፈቃደኛ መሆናችንን በድጋሚ ለመግለጽ እንወዳለን።

    በዚህ አጋጣሚ ዓለምአቀፍ ማኅበረሰብ ኢትዮጵያን ከሕገ-መንግሥታዊ ቀውሶች እና ከጠቅላላው ትርምስ ለመታደግ ጠንካራ እርምጃ እንዲወስድ ጥሪ እናቀርባለን።

    በተለይም የአፍሪካ ሕብረትየተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አካላት፣ የአውሮፓ ሕብረት እና ሌሎችም ዓለምአቀፍ ማኅበረሰብ የኢትዮጵያ መንግሥት ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ድርድር እንዲያደርግ እና ነፃና ፍትሃዊ ምርጫን የሚያዘጋጅና ተግባራዊ የሚያደርግ በሥልጣን መጋሪያ የሽግግር መንግሥት አማካይነት ሁሉን አካታች የዴሞክራሲ ፍኖተ-ካርታ በጋራ እንዲያስቀምጥ እንዲያሳስቡ አጥብቀን እንጠይቃለን።

    የአፍሪካን ሰላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ በብዙ የአፍሪካ አገራት ግጭትን ለመከላከል እና መፍትሄ ለማምጣት ውይይትን ማዕከል ያደረገ አቀራረብን በመምራት እና በማስተዋወቅ የአፍሪካ ሕብረት እየተጫወተ ያለውን ሚና እናደንቃለን። አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ቀውስ ከማንኛውም አካል የበለጠ የአፍሪካ ሕብረትን የላቀ ትኩረት ይጠይቃል ብለን እናምናለን። በአፍሪካ ሕብረት አዋጅ አንቀጽ 4 (ሸ) መሠረት ህብረቱ ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለመከላከል በአባል ሀገር ውስጥ ጣልቃ የመግባት መብት አለው።

    ብሔራዊ እና ዓለምአቀፉ ማስረጃዎች የኢትዮጵያ ሥርዓት ቀጣይነት ያለው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ላለፉት 27 ዓመታት በሀገሪቱ ዜጎች ላይ መፈጸሙንና ባለፉት ሁለት ዓመታትም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ እንደተፈፀመ በግልጽ ያሳያሉ። በተጨማሪም በአብዛኛዎቹ የክልል መንግሥታት አጠቃላይ አስተዳደርን አደጋ ላይ የሚጥሉና በመላ ሀገሪቱ የፀጥታ ቀውስ የሚያመጡ የተደራጁ እና ጠንካራ የታጠቁ ኃይሎች አሉ። አሁን ካሉት ቀውሶች እና በፍጥነት ከሚጓዙ እምቅ ግጭቶች እና ስጋቶች አንጻር የአፍሪካ ሕብረት በአፋጣኝ ጣልቃ ገብቶ ኃላፊነቱን መወጣት አለበት።

    አሁን በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ በአፍሪካ ሁለተኛዋን ትልቅ ሀገር መበታተን ብቻ ሳይሆን “ሰላማዊና የተረጋጋች አፍሪካን” የሚመኝ አጀንዳ 2063 የተባለውን የአፍሪካ ሕብረት ምኞት 4 (Aspiration 4) ለማሳካት ካሉ ዋና እንቅፋቶች መካከል አንዱ መሆኑን ማሳሰብ እንወዳለን። በተጨማሪም ፊንፊኔ (አዲስ አበባ) የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መቀመጫ፣ የኦሮሚያ ዋና ከተማና የአፍሪካ ሕብረት ዋና መሥሪያ ቤት በመሆኗ የአፍሪካ ሕብረት ጽሕፈት ቤትና እዚያ የሚሠሩ ከ2000 በላይ ሠራተኞች ደህንነት አሁን በኢትዮጵያ በተለይም በኦሮሚያ ካለው የሰላም የአለመረጋጋት ጉዳዮች ጋር ከግምት ውስጥ መግባት አለበት።

    የተባበሩት መንግሥታት በዓለም ላይ የሚከሰቱ ቀውሶችን በማስወገድ ረገድ የተጫወተውን ሚና የምንገነዘብ ሲሆን፥ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት (UNSC)፣ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (UNHRC) እና ሌሎችም በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የሚከሰቱ ቀውሶችን ለማስወገድ የድርሻቸውን እንዲወጡ እንጠይቃለን። በተለይም በዓለምአቀፍ ደረጃ ሰላምንና ፀጥታን ለማስጠበቅ በተባበሩት መንግሥታት ቻርተር መሠረት ቀዳሚ ኃላፊነት ያለው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በአፍሪካ ካሉ ትልልቅ ሀገሮች ሁለተኛ የሆነችዋ ኢትዮጵያ የፖለቲካ፣ ማኅበራዊ፣ ሰብዓዊ መብቶች እና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች ሲያጋጥሟትና ወደ ውድቀት ስታመራ ጆሮ ዳባ ብሎ ማለፍ የለበትም።

    የአውሮፓ ሕብረት ብሔራዊ የለውጥ አጀንዳውን ለመደገፍና ከኢትዮጵያ ጋር ልዩ ልዩ የልማት ትብብሮችን በመፍጠር በኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ውህደት፣ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን እየተጫወተ ያለውን የመሪነት ሚና እናደንቃለን። ሆኖም እ.ኤ.አ. በ2018 የተጀመረው የፖለቲካ ለውጥ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በአግባቡ ባለመመራቱ ግዙፍ ፈተናዎች ገጥሞት ወድቋል። ይህም የአውሮፓ ሕብረት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን አጋርነትና ሕብረት ለኢትዮጵያ ያለውን ሁሉንም ምኞት ይገታል። ስለዚህ የአውሮፓ ሕብረት በቀጠናው ያሉ ቁልፍ አጋሮቹ ያጋጠማቸውን የፖለቲካ ቀውሶችን ለማስቀረት ባለው አቅም ጣልቃ እንደሚገባ እናምናለን።

    ስለሆነም፦

    1. በአፍሪካ ሕብረት በአንቀጽ 4 (ሸ) /Article 4(h)/ እና በሌሎች የሕብረቱ ደጋፊ አንቀጾች ላይ በተቀመጠው መብቱ ላይ በመመሥረት በኢትዮጵያ ቀውሶች ውስጥ ጣልቃ እንዲገባ ጥሪ እናቀርባለን።
    2. በኢትዮጵያ የሰላምና ደህንነት አደጋዎች በግልጽ የሚታዩ በመሆናቸው የጸጥታው ምክር ቤት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አንቀፅ 39 እና 41 ላይ በተመለከቱት ግዴታዎች መሠረት ተገቢ እርምጃዎችን እንዲወስድ ጥሪ እናስተላልፋለን። የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔም (UNHRC) በኢትዮጵያ የተፈጸሙ ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለመቅረፍ በዚሁ መሠረት እርምጃ እንዲወስድ እንጠይቃለን።
    3. ይህ የመቶ ዓ መት ግዙፍ ግጭትና በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት ላይ የጎላ ጉዳት ስለሚያስከትልና የአውሮፓ ሀገራትና የኢትዮጵያን ዲፕሎማሲያዊ እና የልማት አጋርነት የሚነካ በመሆኑ የአውሮፓ ሕብረት በኢትዮጵያ በተለይም በኦሮሚያ ለተፈጠረው አለመረጋጋት ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጥ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
    4. በኢትዮጵያ ያሉ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ያቀረብነውን የመፍትሄ ሀሳብ በቁም ነገር በመመልከት እየተቃረበ ያለውን አስከፊ ቀውስ ለማስቀረት ከእኛ ጋር እንዲሠሩ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።

    ገለልተኛ የኦሮሞ የፖለቲካ ኃይሎችና መላው ኦሮሞ ሕዝብ ማንኛውንም ዓይነት የፖለቲካና የፀጥታ ችግር ለማስወገድ ለኦሮሚያ የሽግግር መንግሥት እንዲዘጋጁ ጥሪ እያቀረበ፥ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር በዚህ አቋም ላይ ባለድርሻ አካላትን በሁለቱም የመንግሥት ደረጃዎች ማማከሩ እንደሚቀጥል ያሳውቃል።

    ድል ለሰፊው ሕዝብ!
    የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)
    ፊንፊኔ
    መስከረም 13፥ 2020

    የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)

    Anonymous
    Inactive

    ግልፅ ደብዳቤ ለኢንጂነር ታከለ ኡማ (ቢደርስም ባይደርስም)
    ወንድማገኘሁ አዲስ

    ሰላምታዬንና አክብሮቴን በማስቀደም የተከበሩ ሚኒስትር ኢንጂነር ታከለ ኡማ፥ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በጥናት ደረስኩበት ብሎ ይፋ ላደረገው ሰነድ በሰጡት መልስ የተገነዘብኩት እንደ አንድ ተራ ዜጋ ላቀርብልዎት እወዳለሁ።

    ሲጀመር የሰጡት ርዕስ ራሱ ችግር እንዳለበት ይሰማኛል። ማስረጃ አጠናቅሬያለሁ ያለ ድርጅት መግለጫ ከማውጣቱ ሰነዱን ለሚመለከታቸው አቅርቦ ይመሩት የነበረው ፅሕፈት ቤት መልስ ስላልሰጠ። ኢዜማ ከዚህ ቢሮ መልስ አግኝቶ ቢሆን ኖሮ አንደኛ መልሱን ሪፖርቱ ላይ ያካትት ነበር፤ አሳማኝ የሆኑ ጉዳዮች ከቀረቡም ፓርቲው ከሪፖርቱ ላይ የተወሰኑትን እንዲያርም ወይም እንዲያሻሽል ዕድሉ ክፍት ይሆን ነበር ብዬ አምናለሁ።

    በመቀጠልም ምላሽ ለመስጠት ተገቢው ቦታ ባልገኝም ሲሉ ተገቢው ቦታ ለመሆኑ የቱ ነው? ሰነዱ በቀጥታ ከሚመለከታቸው ግለሰቦች አካላት እርስዎና እርስዎ ይመሩት የነበረው ተቋም በመሆናቸው መልስ እንዳይሰጡ ቦታ ምክንያት ይሆናል ብዬ አላስብም ።

    በመቀጠልም የመሬት ወረራን በተመለከተ ስልጣን ላይ ከወጣንበት የመጀመሪያ ቀን ጀምሮ እስከ መጨረሻዋ ቀን ድረስ ጠንካራ እርምጃዎች ስንወስድበት የነበረ ጉዳይ ነው ብለዋል።  ለእርስዎ አድልተን ያሉትን ብንቀበል እንኳን “የመሬት ወረራውን አስቆሙት ወይ? የኮንዶሚኒየሙን አድሎአዊ እደላ አስወገዱት ወይ ነው?” ጥያቄው በራስዎ አንደበት የሀይማኖት ተቋማት ሳይቀሩ በኢ-መደበኛ አደረጃጀቶች ሲወረሩና በመንግሥት አካላት ሲፈርሱ በተነሳብዎት ተቃውሞ ምክንያት እርስዎ ራስዎ ይቅርታ አልጠየቁም ወይ? ከፍተኛ የሆነ የመሬት ወረራ እንዳለ በይፋ አልተናገሩም ወይ? ባለፉበት ባገደሙበት ሁሉ የከተማዋን መሬት ለግለሰቦችና ለተቋማት ሲያድሉ አልነበር ወይ?

    ሌላው ክቡር ኢንጂነር ታከለ ኡማ፥ የተፈናቀሉትን አርሶ አደሮች በመታከክ እንደ ህወሀቶቹ የቀን ጅቦች ብሄርዎን ዋሻ ለማድረግ የሄዱበት መንገድ በጣም ከእርስዎ በጭራሽ ያልጠኩት ነበር። ለመሆኑ የትኛው የኢዜማ የመግለጫው ክፍል ላይ ነው “የተፈናቀሉት ገበሬዎች የመኖሪያ ቤት ተጠቃሚ አይሆኑ” የሚለው። ማነው በቃለ መጠይቁስ ላይ “ለተፈናቀሉት ቤት አይሰጥ” ያለው? በእርስዎ የስልጣን ዘመን በገፍ ቤት የታደላቸው በሺዎች የሚቆጠሩት የኦሮሚያ ባለስልጣናት የተፈናቀሉ አርሶ አደሮች ነበሩ ወይ? እስከ ልጅ ልጅ የሚሰጠው መሬት ፍትሀዊ ነበር ወይ? ለስፖርት ክለቦች የታደለውስ? ይህ ሁሉ እየሆነ ያለው እኮ “በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ድሆች ከዛሬ ነገ አንገታችንን ማስገቢያ፣ ልጆቻችንን ማሳረፊያ ቤት ልናገኝ ነው” በማለት ቤትን የህልውናቸውና የተስፋቸው ጥግ አርገው እየጠበቁ ሳለ ነው።

    “እኛ ሕጋዊ እርምጃ ስንወስድ የዛሬ ተችዎቻችን የሰብዓዊ መብት ተነካ፤ ዜጎች ተፈናቀሉ ብለው ዘመቻ የከፈቱብን አካላት ናቸው” ብለዋል። በመጀመሪያ ደረጃ እርምጃ ሲወሰድ የሰብዓዊ መብት መከበር አለበት የሚለው ዓለም-አቀፋዊ መርህ እንደተጠበቀ ሆኖ ‘ዘመቻ’ ላሉት ቃል ግን ይቅርታ ያድርጉልኝና ማፈር ይኖርብዎታል። ለእርስዎም ሆነ ለመንግሥትዎ የኢዜማን ያክል ዕድል የሰጠ አንድም ድርጅት የለም። መወቀስ ካለበትም በሰጣችሁ ሰፊ ዕድልና በታገሳችሁ ልክ መሆን አለበት፤ ምንም እንኳን ሁለቱም ምክንያታዊ ናቸው ብዬ ባምንም።

    ሌላው እጅግ አስገራሚ የሆነው ደሞ “አንድም ቀን ለተናቀሉት የመቆርቆር ስሜት አሳይቶ የማያውቅ ድርጅት” ሲሉ የጠቀሱት ለመሆኑ ኢዜማ የጠቀሷቸው ዜጎች ሲፈናቀሉ ህልው ፓርቲ ነበር ወይ? ያፈናቀላቸው እኮ የራስዎ ድርጅት የዛሬው የኦሮሚያ ብልጽግና የትናንቱ ኦህዴድ ነበር! ተረሳ ክቡር ሚኒስትር? አርበኞች ግንቦት 7 (አግ7) እንዲሁም ከስመው ኢዜማን የመሠረቱት እኔ የማቃቸው ፓርቲዎች እና ግለሰቦች ሁሉ እናንተ ስታፈናቅሉ እነሱ ከተፈናቃዮች ጎን ሆነው ድምፃቸውን ሲያሰሙ የነበሩ መሆናቸውን አስረግጬ መናገር እችላለሁ። እንደ አንድ ለወገኑ እንደሚቆረቆር ኢትዮጲያዊ እኔም ከእነሱ ባለሁበት ያቅሜን ስጮህ ነበር። ለምን ይዋሻል ኢንጂነር?!

    “የአርሶ አደሮችን ጉዳይ ለተቀባይነት ማግኛ” በማለት የፃፉት እና “መጀመሪያ ላይ በሀሰተኛ መረጃ ሀገር ማፍረስ እንጂ አይገነባም” ላሉት ደሞ ትንሽ ማለት አለብኝ። ለመሆኑ ኢዜማ እርስዎ ባሉት መልኩ ተቀባይነት ማግኘት እንደሚቻል ጠፍቶት ነው በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ደጋፊዎቹን ያጣው? ሌላው ቢቀር በእናት ድርጅትዎ መዋቅር በአብዛኛው ኦሮሚያና እርስዎ ሲያስተዳድሯት በነበረችው በአዲስ አበባ ከተማ በፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች ላይ ሲደርሱ የነበሩት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በማስጮህ ብቻ ተከታይን ማፍራት አይቻልም ብለው ያስባሉ? ይልቅስ ከላይ እንደጠቀስኩት የተፈናቃዮችን ልብ በፀረ-ኢዜማ ትርክት ለማነፅና ጭፍን ተከታይ ለማፍራት የኳተኑት እርስዎ ራስዎ ነዎት። በነገራችን ላይ፥ ለሀገር ሰላምና መረጋጋት ዕድል መስጠት ከመንግሥታዊ ኢ-ሕገመንግሥታዊ ተግባራት ጋር ማበር አይደለም።

    ክቡር ኢንጂነር፥ አሁን ላይ በደንብ የገባኝ ከስልጣን ሲወርዱ፣ በሀሳብ መሟገት ሲያቅታቸውና ፖለቲካ ፊት ስትነሳቸው “ብሔርን መደበቂያ ዋሻ” ማድረግ በስፋት እየተዛመተ ያለ አስፈሪ ፖለቲካዊ ባህል መሆኑን ነው። እርስዎም ይሄን መንገድ በመከተል የእነ ሀይለመስቀል ሸኚን ፣ የእነ አቦይ ስብሀትን የእነ ልደቱ አያሌውን ዱካ እንደተከተሉ ተረድቻለሁ።

    የአሿሿምዎ ሂደት አጠያያቂነት እንደተጠበቀ ሆኖ ክቡር ሚኒስትር፥ እርስዎ የታላቋ አዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ነበሩ። ሲያስተዳድሯት የነበረችው አዲስ አበባ ማለት የ AU፣ የ ECA እና የመሳሰሉት ታላላቅ ዓለም-አቀፋዊ ድርጅቶች መቀመጫና በዓለም ላይ 3ኛዋ ወይም 4ኛዋ የዲሎማሲና የፖለቲካ ከተማ እንደሆነች ዓለም የሚያውቀው ሀቅ ነው። አሁንም ቢሆን ሚኒስትር እንጂ እንደኔ አክቲቪስት አይደሉም። ቢሆን ደስ የሚለኝ ‘ቀረበ’ የተባለውን ሰነድ በሚገባ ፈትሸው ተመጣጣኝ በሆነ አግባብ መልስ ቢሰጡ ነበር። ሰነዱን በሙሉም ሆነ በከፊል ወይም በተወሰነ ደረጃ ተቀብለው፥ ያም ካልሆነ ተቃውመው የነበሩበትንና ያሉበትን ወንበር የሚመጥን አጸፋ ይሰጣሉ ብዬ ጠብቄ ነበር። በእኔ በኩል ያደረጓቸውን በጎ ተግባራት በዜሮ የማጣፋ ሰው አይደለሁም። የዛሬው መልስዎ ስሜቴን በእጅጉ ቢበርዘውም ለበጎ ለበጎዎቹ ሥራዎችዎ ዛሬም ክብር እሰጣለሁ። ይሁን እንጂ በቀረበብዎ ክስ እና በሰጡት መልስ ምክንያት የተደበቀውን “ኢንጂነር ታከለ ኡማን” ማየቴን ደሞ አልሸሽግዎትም። አሁን ለደረስኩበት ግንዛቤ ትልቁ ግብአቴ ደግሞ እርስዎ ራስዎ የነገሩንን ጭምር በመካድዎ ነው። ይሄ ሁሉ ሆኖም የነበሩበትንና ያሉበትን ደረጃ የሚመጥን መልስ ካለ ለመስማት አሁንም ፍቃደኛ ነኝ።

    ክቡር ሚኒስትር፥ ስንብቴን አስቀድሜ እያቀረብኩ ደብዳቤዬን ከማጠናቀቄ በፊት እርስዎ ወይም ይመሩት የነበረው አስተዳደር ስለተሞገታችሁ ብቻ ሀገር እንደማትፈርስ በርግጠኝነት ልነግርዎ እወዳለሁ። ይልቅስ ሀገር የሚያፈርሰው የዜጎችን ድምፅ ለማፈን ይመሩት የነበረው ተቋም እየወሰደ ያለው ኢ-ሕገመንግሳታዊና ኢ-ዴሞክራሲያዊ እርምጃ ነው። የኢዜማ መግለጫዎች መታገድ የከንቲባ አዳነች አቤቤ ሳይሆን የእስዎ የሁለት ዓመታት የከንቲባነት ዘመን ውጤት ነው። የክብርት ከንቲባዋን ውጤት ደሞ ሰነባብተን እናየዋለን።

    አክባሪዎ ወንድማገኘሁ አዲስ

    ተያያዥ ጉዳዮች፦

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forums) ላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።

    ግልፅ ደብዳቤ ለኢንጂነር ታከለ ኡማ

    Anonymous
    Inactive

    እውነታውን በማድበስበስ ከተጠያቂነት ማምለጥ አይቻልም! ― የኢዜማ ሕዝብ ግንኙነት

    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በአዲስ አበባ ከተማ መሬት ወረራን እና የጋራ መኖሪያ ቤቶች ኢ-ፍትሃዊ ዕደላን በተመለከተ የሚደርሱትን ጥቆማዎች በመቀበል ጉዳዩን የሚመረምር ከብሔራዊ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት የተወጣጣ ኮሚቴ አቋቁሞ ጥናት ሲያደርግ ቆይቷል። የጥናቱን ውጤት ለሕዝብ እና ለመገናኛ ብዙኃን ይፋ ለማድረግ ዛሬ አርብ ነሐሴ 22 ቀን 2012 ዓ.ም ጋዜጣዊ መግለጫ ተዘጋጅቶ ነበር።

    ይህ ጋዜጣዊ መግለጫ ሲዘጋጅ ከዚህ ቀደም ጋዜጣዊ መግለጫ ስንሰጥ እንደምናደርገው ሁሉ ጋዜጣዊ መግለጫው ለሚደረግበት ራስ ሆቴል እንዲሁም በደብዳቤ ቁጥር ኢዜማ/695/12 ለኢፌዴሪ ሰላም ሚኒስቴር አስቀድመን አሳውቀናል።

    ፓርቲያችን ሊሰጥ የነበረውን መግለጫ ለመከታተል እና ለሕዝብ ለማድረስ የተጠሩ ጋዜጠኞች ከተባሉት ሰዓት ቀድመው በአዳራሹ ውስጥ የተገኙ ሲሆን፥ ብዙዎቹም የቀረጻ መሣሪዎቻቸውን አሰናድተው  የመግለጫውን መሰጠት በመጠባበቅ ላይ እያሉ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አባል መሆናቸውን የገለፁ የፖሊስ አባላት መግለጫው መሰጠት እንደማይቻል በማሳወቅ፥ ጋዜጠኞቹ አዳራሹን ለቀው እንዲወጡ አድርገዋል። ፖሊሶቹ ጋዜጣዊ መግለጫውን ለማስቆም የሰጡት ምክንያት ጋዜጣዊ መግለጫው እንዲካሄድ ትዕዛዝ አልተሰጠንም የሚል ነበር።

    በስፍራው የተገኙት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) አመራሮች ሙሉ ትብብር ያደረጉ ሲሆን፥ ስለመግለጫው ለሰላም ሚኒስቴር በደብዳቤ ማሳወቃቸውን ለፖሊስ አባላቱ አስረድተዋል። ወደ ሰላም ሚኒስቴር በመደውልም የተፈጠረውን ለሚንስትር መሥሪያ ቤቱ ያሳወቁ ሲሆን፥ የፖሊስ አባላቱን ከሰላም ሚኒስቴር ጋርም በስልክ የማገናኘት ሥራ ተሠርቷል። ነገር ግን የፖሊስ አባላቱ መልሰው “የሰላም ሚኒስቴር ሊፈቅድ የሚችለው ስብሰባዎችን እንጂ ጋዜጣዊ መግለጫዎችን አይደለም። የመግለጫ ጉዳይ የሚመለከተው ፖሊስን ነው።” በሚል መግለጫውን በመከልከል ጸንተዋል። ይህንንም ተከትሎ የኢዜማ በአዲስ አበባ ከተማ እየተፈፀመ ያለውን የመሬት ወረራ እና የጋራ መኖሪያ ቤቶች ኢ-ፍትሃዊ ዕደላን አስመልክቶ የሠራውን ጥናት ውጤት ለሕዝብ ለማሳወቅ ያዘጋጀው ጋዜጣዊ መግለጫ ተስተጓጉሏል።

    ትላንት የአዲስ አበባ መሬት በሕገ-ወጥ መንገድ እየታጠረ ሲወረር እና ሲዘረፍ ማቆም ያልቻሉ የሕግ አስከባሪዎች፥ በሕጋዊ መንገድ የተጠራ ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳይሰጥ አጥር ሆነዋል። የሕዝብ የሥልጣን ባለቤትነትን እና የሕግ የበላይነትን የሚያረጋግጥ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ውስጥ እንደዛሬው ዓይነት እክል ትላንትናም አላስቆመንም፤ ዛሬም አያስቆመንም! የተፈጸመ ስህተት ካለ አዳምጦ ለማረም ከመዘጋጀት ይልቅ የዜጎችን እና የፖለቲካ ፓርቲዎችን ሀሳብን የመግለጽ ነፃነት በማፈን እና እውነቱን በማድበስበስ ከተጠያቂነት ለመራቅ መሞከር ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንቅፋት እንደሆነ ግልጽ ሊሆን ይገባል። ዛሬ በተከሰተው መግለጫውን የማስተጓጎል ተግባር እውነታውን ማድበስበስ እና ከተጠያቂነት ማምለጥ አይቻልም።

    ከዚህ ቀደም የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት፣ የመሬት ልማት ቢሮ እና የቤቶች ልማት ኤጀንሲ በጥናታችን የደረስንበትን ውጤት አያይዘን የእነሱን ምልከታ በጥናት ውጤታችን ውስጥ ለማካተት ምላሽ እንዲሰጡን ጠይቀን የነበረ ቢሆንም፥ ሁሉም ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ካለመሆናቸው በተጨማሪ የመሬት ልማት ቢሮ እና የቤቶች ልማት ኤጀንሲ የላክንላቸውን ደብዳቤም ለመቀበል ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

    ኢዜማ በጥናቱ የደረሰበትን ሕገ-ወጥነት እና ኢፍትሃዊነት ሰኞ ነሐሴ 25 ቀን 2012 ዓ.ም ከሰዓት 8 ሰዓት ለሕዝብ ይፋ ያደርጋል። ሀሳባችንን የመግለጽ ሕገ-መንግሥታዊ መብታችንን ለማስከበር ወደኋላ እንደማንል እና ያገኘነውን ውጤት ሕዝብ ጋር እንደምናደርስ እንዲያውቁት በድጋሚ ለኢፌዴሪ ሰላም ሚኒስትር እና ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ደብዳቤ ልከናል።

    የኢዜማ ሕዝብ ግንኙነት

    የኢዜማ ሕዝብ ግንኙነት

    Semonegna
    Keymaster

    አቶ ልደቱ አያሌው ለፍርድ ቤት ያቀረበው የሕግ መከራከሪያ ነጥብና የፍትህ ሥርዓቱን ውድቀት ያሳየበት ልብ የሚነካ ንግግር*

    ክቡር ፍርድ ቤት፥

    ለመጀመሪያ ቀን በዚህ ችሎት ላይ ስገኝ ከችሎቱ ጀርባ የተፃፈውንና “ተልዕኳችን የሕግ የበላይነትን በማስከበር አርዓያ መሆን ነው” የሚለውን ሳነብ እና ከአሁን ቀደም በተመሳሳይ ሁኔታ ተከስሼ ነፃ ያወጡኝ ፍርድ ቤቶች በመሆናቸው እውነተኛ ፍትህ ከዚህ ችሎት አገኛለሁ ብዬ ተስፋ አድርጌ ነበር። ዛሬ ግን በዚህ ችሎት ፊት የተገኘሁት ሕጋዊ ግዴታዬን ለመወጣትና ለችሎቱ ያለኝን አክብሮት ለመግለፅ እንጂ፥ ፍትህ አገኛለሁ ብዬ ተስፋ በማድረግ አይደለም። ክቡር ፍርድ ቤት፥ ይህንን ማለት የተገደድኩት በሚከተሉት ምክንያቶች ነው።

    1ኛ. ለፖሊስ ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ የሚሰጠው በምርመራ ሂደቱ ላይ ያሉት ለውጦች በዳኞች እየተመዘኑ ቢሆንም፥ እስካሁን በቀረብኩባቸው አራት ችሎቶች ጉዳዩን ያዩት አራት የተለያዩ ዳኞች በመሆናቸው ምንም ዓይነት የምርመራ ውጤት ለውጥ በሌለበት ሁኔታ ተከታታይ የጊዜ ቀጠሮ እየተሰጠብኝ ያለው ከሕጉ መንፈስ ውጭ በመሆኑ፤

    2ኛ. ለከፍተኛ ሕክምና ወደ ውጭ አገር ለመሄድ ቀጠሮ እንዳለኝ፣ በአሁኑ ወቅትም ከፍተኛ የልብ ህመም ታማሚ እንደሆንኩ፣ ከህመሜ ጋር በተያያዘም በኮቪድ-19 ቫይረስ ብጠቃ ህይወቴ አደጋ ውስጥ ሊወድቅ እንደሚችል የሕክምና መረጃ አቅርቤ እያለና በፖሊስ የቀረበብኝ ክስ የዋስትና መብት የማያስከለክል ሆኖ እያለ ያለ አግባብ የዋስ መብት ተከልክያለሁ። ክቡር ፍርድ ቤት፥ ከምገኝበት አሳሳቢ የጤና ችግር በእስር ላይ ከምገኝበት ለኮሮና እጅግ ተጋላጭ የሆነ እስር ቤት አንፃር የተከለከልኩት የዋስትና መብት ሳይሆን የሰው ልጅ መሠረታዊ መብት የሆነውን በህይወት የመኖር መብቴን ነው። ይህም የሚያሳየው ገና ወንጀለኛ ተብዬ ሳይፈረድብኝ የሞት ፍርድ የተፈረደብኝ መሆኔን ነው፤

    3ኛ. በዚህ በተከበረው ፍርድ ቤት ፊት አሁን እየተከራከርን ያለነው አንድ መንግሥት እና አንድ ዜጋ አይደለንም። በሕጉ መሠረት ከሳሽና ተከሳሽ ነን። ክቡር ፍርድ ቤቱ ለከሳሽና ለተከሳሽ መብት መከበር እኩል መቆም ሲገባው ሁል ጊዜ የከሳሽን ምክንያታዊ ያልሆነ ጥያቄ እየተቀበለ፥ በተቃራኒው ደግሞ የእኔን በመረጃ የተደገፈ ጥያቄ ውድቅ እያደረገ አድሏዊነት እየፈፀመብኝ በመሆኑ፤

    4ኛ. በአጠቃላይ በሀገር ደረጃ ያለውን ሁኔታ ስናይም፥ ፍትህ እየተሰጠ ያለው ከችሎት አደባባይ ሳይሆን ከአራት ኪሎ ቤተ-መንግሥት መሆኑን እያየን ነው። በወቅቱ የፖለቲካ ቀውስ ምክንያት በእስር ላይ የምንገኘው ዜጎች በብዙ ሺዎች የምንቆጠር ሆኖ እያለ፥ ልክ ሁላችንም አንድ ዓይነት ወንጀል እንደሠራንና ጉዳያችን በአንድ ዳኛና ችሎት ብቻ እየታየ እንደሆነ ሁላችንም የዋስ መብት ተነፍገን በተደራራቢ የጊዜ ቀጠሮ መብታችን በጅምላ እየተጣሰ ነው።

    ክቡር ፍርድ ቤት፥ እኛ ፍትህ የምንጠብቀው ከፍርድ ቤት እንጂ ከሳሻችን ከሆነው የአራት ኪሎ መንግሥት አይደለም። የአራት ኪሎ መንግሥት ኃላፊነት ሕግ ማስፈፀም ነው እንጂ ሕግ መተርጎም አይደለም። ክቡር ፍርድ ቤት፥ በአጠቃላይ እነዚህ ከላይ የጠቀስኳቸው አራት ነጥቦች የሚያሳዩት የሕግ ሳይሆን የፖለቲካ እስረኞች መሆናችንን ነው። አሁን በመጨረሻ ፖሊስ “የሽግግር መንግሥት ጥያቄ በማቅረብ መንግሥትን የመገልበጥ ሙከራ አድርጓል” በሚል ክስ ሲያቀርብብኝ መታየቱ ይህንን የሚያረጋግጥ ነው።

    በዚህ ሁኔታ እውነተኛ ፍትህ ይገኛል ብዬ ስለማልጠብቅ በጊዜ ቀጠሮ እየተመላለስኩ እኔና ጠበቃዬ አጉል ከምንጉላላ፥ ውድ የሆነው የፖሊስ እና የፍርድ ቤት ጊዜም ያለ አግባብ ከሚባክን- መቋጫ የሌለው የፖሊስ የጊዜ ቀጠሮ ጥያቄ እንዲቋረጥና ጉዳዩ የፖለቲካ ውሳኔ ሲሰጠውና ፖሊስ “ምርመራዬን ጨርሻለው” ባለ ጊዜ ከእስር ቤት ወደ ችሎት እንድቀርብ እንዲወሰን በታላቅ አክብሮት እጠይቃለሁ።

    ምንጭ፦ ሀብታሙ አያሌው

    * አቶ ልደቱ አያሌው የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ምክር ቤት ሲሆኑ፥ ሐምሌ 17 ቀን 2012 ዓ.ም. ፓርቲው በፕሬዝደንቱ አቶ አዳነ ታደሰ በኩል፥ አቶ ልደቱ አያሌው የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ በቁጥጥር ስር እንዳዋላቸውና ቢሾፍቱ (ደብረ ዘይት) ከተማ በሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ እንደታሰሩ ገልጾ ነበር። ይህንንም አስመልክቶ ፓርቲው ሐምሌ 21 ቀን 2012 ዓ.ም. ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቶ ነበር።

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forums) ላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።

    አቶ ልደቱ አያሌው

    Anonymous
    Inactive

    በኢትዮጵያ የሀገረ-መንግሥት ግንባታ የታሪክ ዳራ፥ በእኩልነት ላይ የተመሠረተች ሀገር ለመፍጠር የተደረጉ ሙከራዎች፣
    ያጋጠሙን የታሪክ ፈተናዎችና ያመለጡን ዕድሎች በብሔራዊ መግባባት መነፅር ሲታይ

    መረራ ጉዲና (ፕሮፌሰር)
    ለብሔራዊ መግባባት ውይይት የቀረበ ጥናት
    ነሐሴ 2012

    አብዛኛዎቹ የሀገራችን የታሪክ ምሁራን የኢትዮጵያ ታሪክ ከክርስቶስ ልደት በፊት፣ በአስረኛው ምዕተ ዓመት የንግስት ሳባ እና የንጉሥ ሰለሞን ግንኙነት በሚባለው ጊዜ ይጀምራል ይላሉ። ይህ ለአንዳንዶቹ የሚታመን ታሪክ ተደርጎ የሚወሰደው፤ ለሌሎች ደግሞ ተረት እንደነበረ የሚነገረው ክስተት የማስመሰያ ትርክቱ የእስራኤል አምላክ የቀባቸው ገዥዎች ተብሎ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት ንጉሦቹ ቅቡልነትን አግኝተውበታል። በትርክቱም ሀገሪቷን እስከ 1966 ሕዝባዊ አብዮት ድረስ ያለ ብዙ ጭንቀት ገዝተውበታል።

    የዛሬይቱ ሰፊዋ ኢትዮጵያ እንደ ሕብረ ብሔራዊ የነገሥታት መንግሥት (multi-ethnic empire state) የተፈጠረችው በ2ኛው የ19ኛው ክፍለ ዘመን ግማሽ፤ የዘመነ መሳፍንት ከሚባለው ዘመን በኋላ ስለሆነና ዛሬም በጣም ሰፊ ቀውስ ውስጥ የከተተን ታሪካዊ ዳራም ከዚሁ ጊዜ ጀምሮ ስለሆነ፥ ጽሑፌም ከዘመናዊ ኢትዮጵያ መፈጠር ጋር በተፈጠሩ ችግሮች ላይ ያተኩራል።

    የዘመነ መሳፍንትን ክስተት በመለወጥ የተጀመረው የዛሬዋን ሰሜናዊ ኢትዮጵያን አንድ የማድረግ ሕልም በግማሽ ምዕተ ዓመት ውስጥ ከሦስት እጥፍ በላይ የሰፋች ኢትዮጵያን መፍጠር ችሎዋል። ይህ የታሪክ ክስተት የሦስት ምኞቶች ዉጤት ነበር። እነዚህም፡-

    1ኛ/ ተበታትና የነበረችውን የዛሬዋን ሰሜናዊ ኢትዮጵያ ሕዝቦችን ለማሰባሰብ የታለመ ምኞት፣
    2ኛ/ የኦሮሞና የሶማሌ ሕዝቦችን ጨምሮ ሰፊውን የደቡብ ክፍል የማስገበር ምኞት፣
    3ኛ/ አፍሪካን ለመቀራመት የመጡትን የአውሮፓ ሀገሮች ጋር የመፎካከር ምኞት ነበሩ።

    እነዚህን ሦስት ምኞቶች ለማሳካት የመጀመሪያ የሆነውን ሙከራ የጀመሩት እንደምታውቁት አፄ ቴዎድሮስ ነበሩ። ቴዎድሮስ ሕልሞቹን ለማሳካት ጠንካራና ሰፊ ሠራዊት ማደራጀት ነበረባቸው፤ ለዚህም ሰፊ መሬት የያዙትን ቄሶች መሬት መቀማትና ዘመናዊ መሣሪያን ከክርስቲያን አውሮፓ ለማግኘት ጥረት ማድረግ ነበር። የአዉሮፓ መሪዎችን ማሳመን ሲያቅታቸው ደግሞ ሙያው የሌላቸውን አውሮፓዊያንን ሳይቀር በቤተ መንግሥታቸው ሰብስበው ከባድ የጦር መሣሪያ ውለዱ እስከማለት ደርሰዋል። ይህም ምኞታቸዉ ይሳካ ዘንድ በነበራቸዉ የጦር መሣሪያ የአካባቢ ገዥዎችንም ለማንበርከክ ተንቀሳቅሰዋል።

    ቄሶችን ለመግፋት ያደረጉት ሙከራ እግዚአብሔርን የካዱ ንጉሥ ተብሎ ተሰባከባቸዉ። የአውሮፓውያንን ዘመናዊ መሣሪያ ለማግኘት ገደብ ያለፈ ጉጉታቸው ከእንግሊዘኞች ጋር ያለጊዜ አላተማቸው። የየአከባቢውን ገዥዎች በጉልበት ለማንበርከክ እጅና አንገት በመቁረጥ የገፉበት ሙከራ ከእንግሊዞች ጋር ለመዋጋት የቁርጥ ቀን ሲመጣ፥ የትግራይ፣ የወሎ፤ የጎጃም፣ የሸዋ፣ የጎንደር ገዥዎች ሁሉም በሚባልበት ደረጃ ካዷቸው። በአጭሩ የየአከባቢዉ ገዥዎች በእንግሊዞች እጅ መሞታቸውን ሲሰሙ ከማዘን ይልቅ ተገላገልን ያሉ ይመስላል። ለዚህም ይመስለኛል ዕውቁ የታሪክ ምሁር ፕሮፌሴር ባህሩ ዘውዴ የቴዎድሮስን ሚና በተሻለ የታሪክ ሚዛን ላይ ለማስቀመጥ ሲሞክር፥ “የተወናበዱ የለዉጥ ነቢይ” (“confused prophet of change”) ያላቸዉ።

    በዚህ የቴዎድሮስ የታሪክ ሚና ላይ ብዙ ሰው ልብ የማያደርገውን የታሪክ ማስታወሻ አስቀምጬ ልለፍ። ይኼውም ቴዎድሮስ በጊዜው ለነበሩ የአውሮፓ ኃያላን መንግሥታት በፃፉት ደብዳቤ ውስጥ፥ “አባቶቼ በሠሩት ኃጢአት ምክንያት እግዚአብሔር “ጋሎችን” በሀገሬ ላይ ለቆ፣ እነሱ ጌቶች ሆነው፣ እኛ የእስራኤል ልጆች የነሱ አሽከሮች ሆነን እንኖር ነበር። አሁን እግዚአብሔር ከትቢያ አንስቶኝ የኢትዮጵያ ንጉሥ አድርጎኛል። እናንተ ከረዳችሁኝ በጋራ እየሩሳሌምንም ነፃ ልናወጣ እንችላለን” ማለታቸዉ ነዉ (ትርጉም የኔ ነው)። እዚህ ላይ ሁለት ነገሮችን ልበል፦

    1) “ጋሎቹ” የሚባሉት በዘመነ መሳፍንት የጎንደርን ቤተ መንግሥት በበላይነት ሲቆጣጠሩ የነበሩ የየጁ ኦሮሞዎች መሆናቸውና እየሩሳሌም በጊዜው በእስላሞች እጅ የነበረች መሆንዋን ነው።
    2) ከዚህ አንጻር ማስታወስ የሚያስፈልገው ትልቁ ጉዳይ አፄ ቴዎድሮስ የብሔረሰብ (የዘር) ፖለቲካን በግልፅ የተናገሩ የመጀመሪያዉ የኢትዮጵያ መሪ መሆናቸው ነው።

    ከቴዎድሮስ ሞት በኋላ ለሦስት ዓመታት በተክለጊዮርጊስ እና ካሣ (አማቾች የነበሩ ይመስለኛል) ከተካሄደው የሥልጣን ትግል በኋላ በአሸናፊነት የወጡት አፄ ዮሐንስ (ካሣ ምርጫ) ነበሩ። አፄ ዮሐንስ ከሀገር ውስጥ ከወሎ፣ ከጎጃም፣ ከጎንደር፣ ከሸዋ ገዢዎች ጋር እየተጋጩ፥ ከውጭ ደግሞ ከጣሊያኖች፣ ከግብፆችና ከሱዳን መሐዲስቶች (ደርቡሾች ) ጋር ሲዋጉ በመጨረሻ በመሐዲስቶች እጅ ወድቋዋል።

    በአጭሩ ዮሐንስ ለትግራይ ሊሂቃን የኢትዮጵያ ማዕከል ነበርን፤ የአክሱም ሀቀኛ ወራሾች እኛ ነን የሚለውን የፖለቲካ ስሜት መፍጠር ቢችሉም፥ በኢትዮጵያ የሀገረ-መንግሥት ግንባታ ታሪክ ውስጥ የተለየ ሚና መጫወት አልቻሉም።

    በማያሻማ ቋንቋ፥ የዛሬዋ ኢትዮጵያ በዋናነት የተፈጠረችውና የዛሬው የታሪክ ጣጣችንም በዋናነት የተፈጠረው በአፄ ምኒልክ ነው። ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ዮሐንስን የሱዳን መሐዲስቶች እስኪገድሉላቸው ድረስ ከአውሮፓ መንግሥታት፥ በተለይም ከጣሊያን በገፍ ባገኙት የጦር መሣሪያ እነራስ ጎበና የመሳሰሉ የኦሮሞ የጦር መሪዎችን በመጠቀም በጊዜው ጠንካራ የሚባል ግዙፍ ሠራዊት መገንበት ችለዋል። ይህንን ግዙፍ ሠራዊትን ከዮሐንስ ጋር በመዋጋት ከማድከም ይልቅ፥ በአንድ በኩል ዮሐንስን እየገበሩ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ያኔ የነበረችውን ኢትዮጵያ ሦስት እጅ እጥፍ የሆነ ሰፊ ግዛት መፍጠር ችሎዋል። በዚህም መጀመሪያ ሳይጠቀለሉ የቀሩትን የሸዋ ኦሮሞዎችን ጠቅልለው ያዙ። ከዚያ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር (እ.አ.አ) በ1876 ጉራጌን ብዙ ሕይወት ከጠየቀ ጦርነት በኋላ አስገበሩ። ብዙ ዝርዝር ውስጥ ሳይገባ የምኒልክን የመስፋፋት ጦርነቶች እንደሚከተለው ማጠቃለል ይቻላል። ይኸውም በምኒልክና ጀኔራሎቹ ብዙ የግዛት መስፋፋት ጦርነቶችን ቢወጉም ሦስቱ ወሳኝ ጦርነቶች ነበሩ።

    አንደኛው በምዕራብ በኩል በእማባቦ (ዛሬ ሆሮ ጉዱሩ በሚባለው ላይ በጎበና መሪነት እ.አ.አ በ1882 የተዋጉት ጦርነት ነበር። ይህ ጦርነት ኦሮሞን ጨምሮ የምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦችን ዕድልና የጎጃም መሪዎች ከሸዋ ጋር የነበራቸውን ፉክክር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የወሰነና የሸዋንም የበላይነት ያረጋገጠ ነበር።

    ሌላው የምኒልክ ጦርነት በአርሲ ላይ እ.አ.አ በ1886 የተደመደመዉ ነው። አርሲዎች ከሌሎች የኦሮሞ አካባቢዎች በተለየ መንገድ ለአምስት ዓመታት በጀግንነት ተዋግተዋል። በመጨረሻም በራሳቸው በምኒልክ በተመራ ጦር የአውሮፓ መሣሪያ በፈጠረው ልዩነት ሊሸንፉ ችለዋል። ተመሳሳይ የመከላከል ጦርነት እንዳይገጥማቸው ይመስላል ምኒልክ ዛሬ አለ፣ የለም የሚባለውን የአኖሌ ዓይነት የጭካኔ በትር በአርሲዎች ላይ አሳርፈዋል። እዚህ ላይ ዛሬ እየተነጋገርንበት ላለው የብሔራዊ መግባባት መሳካት፥ የለም ከሚለው አጉል ክርክር ወጥተን የትናንትናውን የታሪክ ቁስላችንን በሚያክም መልኩ እንድናስተካክል መምከርን እወዳለሁ።

    ሦስተኛው የምኒልክ ትልቁ ጦርነት አሁንም በእሳቸው የተመራውና እ.አ.አ በ1887 የተካሄደው የጨለንቆ ጦርነት ነበር። የዚህ ጦርነት ውጤት በጊዜው የሀብታሟ የሐረር ከተማ መንግሥት (the Harari city-state) ጨምሮ ምስራቅ ኢትዮጵያ ያለ ደረሰኝ ምኒልክ እጅ የገባበት ሁኔታን ፈጥሯል። ከዚህም በኋላ ከፋን፣ ወላይታን፣ ወዘተ ለመያዝ ብዙ ደም የፈሰሰባቸው ጦርነቶች ነበሩ። እንደሚባለው በእንግሊዝ ተስፋፊዎችና በምኒልክ ኢትዮጵያ መካከል የመምረጥ ዕድል የገጠማቸው የቦረና ኦሮሞዎች፥ ‘ማንን ትመርጣላችሁ?’ ሲባሉ፥ የፊታወራሪ ሀብተጊዮርጊስ ፊትን አይተው፥ የእኛኑ ፊት የሚመስለው ይሻላል ብለው በሪፈረንደም (referendum) እየሰፋ በመጣው የኢትዮጵያ መንግሥታዊ ግዛት ውስጥ የተቀላቀሉበት ሁኔታም እንዳለ ይነገራል።

    እ.አ.አ በ1889 አፄ ዮሐንስ በመሐዲስቶች ሲገደሉ፥ ኦሮሞን ጨምሮ አብዛኛው ደቡብን የተቆጣጠሩት ምኒልክ ለሰሜኑ ወንድም መሪዎች ፈረንጆች እንደሚሉት “ካሮትና ዱላን ማስመረጥ” (carrot-and-stick approach) ብቻ በቂ ነበር። የሰሜኑ መሪዎች ምርጫም በማያሻማ መንገድ ካሮት ነበር። ስለካሮቱም በግልፅ ቋንቋ ለማስቀመጥ፥ የኦሮሞ አከባቢዎችን ጨምሮ በደቡብ የተገኘውን እጅግ በጣም ሰፊ ግዛት ዉስጥ በታናሽ ወንድምነት ሹማቶችን መቀራመት ነበር።

    በብሔራዊ መግባባታችን ውይይት አንፃር በምኒልክ በተፈጠረው ሰፊ አፄያዊ ግዛት ጋር የተፈጠሩ ችግሮችን ወደ ማንሳቱ ልለፍ። አንደኛው ችግር ከላይ እንዳነሳሁት፥ በጉልበት የግዛት ፈጠራ ላይ አኖሌን የመሳሰሉ የታሪክ ጠባሳዎች መፈጠራቸው። ሁለተኛውና ዋናው ነገር ግን ከማቅናቱ ጋር የተፈጠረው የፖለቲካል ኤኮኖሚው ነው። ይህም በነፍጥ ላይ የተመሠረተዉ የፖለቲካ ኤኮኖሚ ዛሬም እያወዛገበን ያለው የነፍጠኛ ሥርዓት በሚባለው ላይ የተመሠረተዉ ነዉ። ለማቅናት የተሰማራው የፊውዳሉ ሥርዓት ሠራዊት የገባር ሕዝቦችን ነፃነት ቀምተዋል፤ መሬታቸዉን ዘርፈዋል፤ ሕዝቦችን በገዛ መሬታቸው ላይ ጭሰኛና አሽከር አድርገዋል፤ ቋንቋቸውን አፍነው በ’ስማ በለው’ ገዝቷቸዋል። በአጭሩ፥ እጅግ በጣም ዘግናኝና ጨካኝ የሆነ የፖለቲካ ሥርዓት ጭነውባቸዋል። አንዳንዱ ነፍጠኛ በሃያ ሺዎች የሚቆጠር ጋሻ መሬትም ነበረው። ወረ-ገኑ የመሳሰሉ የቤተ መንግሥት መሬቶች እጅግ በጣም ብዙ ነበሩ። እዚህ ላይ ማስታወስ የሚያስፈልገው የሰሜንና የደቡብ ኢትዮጵያ የመሬት ይዞታም በፍጹም የተለያዩ መሆናቸው ነው። አነሰም በዛ የሰሜኑ ገበሬ የዘር ግንዱን ቆጥሮ መሬት ያገኛል። መሬት አያያዙም የወል ነበር። ሌላው ቢቀር የሚገዛውም በራሱ ቋንቋ ነበር። በደቡቡ ያለው ግን የመሬት ሥርዓቱ የግል ሆኖ፥ ጭሰኝነት እጅግ የተንሠራፋበት ነበር። ሲሶ ለነጋሽ፣ ሲሶ ለቀዳሽ፣ ሲሶ ለአራሽ የሚባለው የኢትዮጵያ ነገሥታት የመሬት ፖሊሲ እጅግ በጣም ዘግናኝ በሆነ ሁኔታ ሥራ ላይ የዋለው በደቡቡ የሀገራችን ክፍል ላይ ነው።

    በ1960ዎቹ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ዘመን “መሬት ላራሹ” እና “የብሔረሰቦች እኩልነት” የተባሉ ሕዝባዊ መፈክሮች የተወለዱት ከዚሁ ጨቋኝ ሥርዓት ነበር። ዛሬ የታሪክ ክለሳ ውስጥ ብንገባም፥ በእውነቱ ከሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብራክ የወጡ ወጣቶች፥ እንዲያውም በወቅቱ ‘አማራ’ ከሚባለው ክፍል የሚበዙ ይመስለኛል፤ መፈክሮቹን በጋራ አስተጋብተዋል።

    ለማንኛውም ከብሔራዊ መግባባታችን አንፃር አንድ ነገር ግልፅ ላድርግ። ‘ነፍጠኛ’ የሚባለው ሥርዓት ገዝፎ የነበረ ሥርዓት መሆኑና፥ ይህም ሥርዓት ከደቡቡ አርሶ አደር የተሻለ ኑሮ የማይኖሩትን፥ ቢፈልጉ እንኳን የደቡቡን ገበሬ ለመዝረፍ አቅሙም ሆነ ዕድሉን ያልነበራቸውን የአማራ አርሶ አደርን አይጨምርም፤ መጨመሩም ጩቡ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ዛሬ አንዳንድ የአማራ ሊሂቃን “እኔም ነፍጠኛ ነኝ” የሚለውን መፈክር ሲያሰሙ፥ ጥቅሙ ኦሮሞን ጨምሮ የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦችን ከአማራ ሕዝብ ጋር ከማጋጨት የዘለለ የፖለቲካ ትርፍ የሚኖረው አይመስለኝም። ስለሆነም የምንችለውን ያክል ሁላችንም ከሁለቱም ጩቡዎች እንጠንቀቅ ዘንድ አደራ እላለሁ።

    ወደ ሌሎች ነጥቦች ከማለፌ በፊት በዋናናት በምኒልክ የተፈጠረችዉ ኢትዮጵያን ለማስተካከል ያቃታቸዉና መሪዎች ማለፍ ያልቻሉት የታሪክ ፈተና ምንድን ነው? የሚለውን ጥያቄ በንጽጽር እንደ ታሪክ ቁጭት ማንሳትን እወዳለሁ። አፄ ቴዎድሮስ የሞቱት እ.አ.አ በ1868 ነበር። ጃፓንን ከታላላቅ የዓለም መንግሥታት ተርታ ያሰለፏት መጅ (Meiji) የሚባሉ የንጉሣውያን ቤተሰብ ወደ ሥልጣን የተመለሱት (The Meiji Restoration) በዚሁ ዓመተ ምኅረት ነበር። የጃፓን ንጉሣዊ ቤተሰቦች በሰላሳ ዓመታት ውስጥ በኢኮኖሚ የበለፀገች ታላቋ ጃፓንን ፈጠሩ። የጃፓኖች የሀገር ፍቅር ግንባታቻውም ባዶ አልነበረም። ትዝ እስከሚለኝ ድረስ አንድ የጃፓን ወታደር ንጉሤ የጃፓንን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት መሸነፍ አልነገሩኝም ብሎ ከሃምሳ ዓመታት በኋላ በፊሊፕንስ ይሁን፤ በኢንዲኔዢያ ጫካ ውስጥ ተገኝቷል። ለሀገር ፍቅር ሲባል እራስን በራስ ማጥፋት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በትናንሽ አይሮፕላኖችን የአሜሪካን መርከቦች ውሰጥ እየጠለቁ አጥፍቶ መጥፋትን የጀመሩት የጃፓን ካሚከዞች (Kamikaze) የሚበሉ ነበሩ። የኢትዮጵያ መሪዎች ግን በተመሳሳይ ጊዜ (እ.አ.አ 1868-1900) ድረስ ሀገሪቷን ከዓለም ጭራነት አላላቀቋትም። በነገራችን ላይ ጃፓንና ኢትዮጵያ በ1868 ላይ ተመሳሳይ የዕድገት ደረጃ ላይ ነበሩ።

    ሌላው ንጽጽሬና የታሪክ ቁጭታችን መሆን ያለበት፥ ታላቋ ጀርመንን የፈጠሩት ቢስማርክ (Otto von Bismarck) እና ምኒልክ የአንድ ዘመን ሰዎች ነበሩ። ምንም ይሁን ምን እነ ቢስማርክ ዓለምን ሁለት ጊዜ ጦርነት ውስጥ መክተት የቻለች ኃያሏን ጀርመን ሲፈጥሩ፥ የኢትዮጵያ ገዥዎች ግን ኋላቀር ኢትዮጵያን ትተውልን ሄደዋል። በነገራችን ላይ ሀገር ትፈርሳለች ተብሎ ስለተሰጋ፥ የምኒልክ ሞት ለሕዝብ ይፋ የሆነው ከዓመታት በኋላ ነበር ይበላል።

    በአጠቃላይ ከብሔራዊ መግባባት ፈጠራችን አንፃር መረሳት የሌለበት ቁመነገር፥ በምኒልክና ጣይቱ የተመራው የአድዋው የጋራ ድል እንኳ ያልፈቱት የሚጋጩ ሦስት አመለካከቶች ዛሬም ከእኛ ጋር መኖራቸዉ ነዉ።

    አንደኛው፥ የሀገራችን ሀገረ-መንግሥት ግንባታ አንድ የነበሩና የተበታተኑ ሕዝቦችን አንድ ላይ መልሶ ያመጣ ነዉ የሚላዉ አመላካከት (reunification)፤
    ሁለተኛው፥ በአንድ ላይ ያልነበሩ ሕዝቦችን ወደ አንድ ማምጣት ነዉ የሚለዉ አመላካከት (unification and/or expansion)፤
    ሦስተኛው፥ ነፃ ሕዝቦችን ጨፍልቆ በኃይል ማቅናት ነዉ የሚላዉ አመላካከት (colonial thesis) ናቸው። የበለጠ ግልፅ ለማድረግ፥ የኢትዮጵያ አንድነት አጥባቂዎች ነን የሚሉ በዋናነት የምኒልክን ኃጢአቶች አይቀበሉም። እንደሚሉት እምዬ ምኒልክ በዓለም ከተደረጉት የሀገር ግንባታዎች ምን የተለየ ነገር ሠራ የሚለውን ሐሳብ ያራምዳሉ። ከዚያም አልፈዉ ምኒልክ የሠራዉ ሥራ ተለያይተዉ የነበሩትን የኢትዮጵያ ግዛቶችን መመለሰ ነበር ይላሉ። በአንፃሩ የኢትዮጵያ አንድነትን የማያጠብቁ ብሔረተኞች ደግሞ የአቶ ሌንጮ ለታን አባባል ለመጠቀም (አሁን አቋማቸዉ ያ መሆኑን አላዉቅም)፥ ሲያንስ “ኢትዮጵያዊ ለመሆን እንደራደራለን ሲበዛ ደግሞ ነፃ መንግሥታትን እስከ መፍጠር ድረስ እንሄደለን” የሚሉ ናቸው። በጥቅሉ እነዚህ አመለካከቶች በፖለቲካችን ለሚጋጩ ሕልሞቻችን መሠረት የሆኑና ካልተገደቡ የሥልጣን ሕልሞች ጋር ተደምሮ የብሔራዊ መግባባት ጥረታችንን የሚያወሳስቡ አመለካከቶች መሆናቸውን በውል መገንዘብ ያስፈልጋል።

    በእነምኒልክ የተፈጠረችዉን ኢትዮጵያን ለማስተካከል የተደረጉ ሙከራዎችና ያመለጡን ዕድሎች፡-

    1) የልጅ ኢያሱ ሙከራ

    ልጅ ኢያሱ የምኒልክ ልጅ ልጅ ሲሆን፥ በእኩልነት ላይ የተመሠረተች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ልዩ ዕድል የነበረውና ያንንም ልዩ ዕድል አውቆ ለመጠቀም ሲሞክር በወጣትነት ዕድሜው ላይ የተቀጨ መሪ ነበር። በብሔር ግንዱ ኦሮሞና አማራ የነበረ፣ በሃይማኖት ጀርባዉ ክርስቲያንና ሙስሊም የነበረ ሰዉ ነዉ። ከወሎም በመወለዱ፣ ትግራይንና ሸዋን ለማገናኘት የተሻለ ድልድይ ለመሆን ይችል ነበር። የሚገርመው ግን፥ የልጅ ኢያሱ ወንጀሎች የሚመነጩት እነዚህኑ አዎንታዊ እሴቶችን ለሀገረ-መንግሥት ግንባታ ለመጠቀም መሞከሩ ነበር። ለምሳሌ አንዳንድ የታሪክ ማስታወሻዎች እንደሚያስረዱት፥ አርሲዎች እንደልጃቸው ይመለከቱት ነበር ይባላል። ከሱማሌዎችና ከአፋሮች ጋር ጥብቅ ግንኙነት እንደነበረው በቂ የሆነ የታሪክ ማስረጃ አለ። ከጎጃሙ ራስ ኃይሉና ከወለጋው ደጃዝማች ጆቴ ቱሉ ጋር የጋብቻ ዝምድና እንደነበረው ይታወቃል። ቤተ ክርስቲያንን ለማሠራት የሚጥረውን ያክል (ለምሳሌ የቀጨኔውን መድሃኔዓለምን እሱ ነው ያሠራው ይባላል) መስግዶችን ያሠራ ነበር። ከሥልጣን ላወረዱት የሸዋ ሊሂቃን ግን፤ አንዱና ትልቁ የልጅ ኢያሱ ወንጀል መስጊዶችን ማሠራቱ ነበር። የመጨረሻው ትልቁ ወንጀል ደግሞ ኢትዮጵያን ለመቀራመት ያንዣበቡ የቅኝ ገዥ ኃይሎች ከሰሜንና ምስራቅ ጣሊያን፣ በምዕራብ፣ በደቡብና በምስራቅ እንግሊዝ፣ በምስራቅ ፈረንሳይ የሦስትዮሽ ስምምነት (tripartite treaty) የሚባለውን እ.አ.አ በ1903 ፈርሞ የምኒልክን ሞት ይጠብቁ ከነበሩት መራቅና በአንደኛው የዓለም ጦርነት በአከባቢያችን ግዛት ካልነበራቸው ከነጀርመንና ቱርክ ጋር ለመደጋገፍ መሞከሩ ነበር።

    በጥቅሉ ከሁሉም በላይ ወንጀሎቹ ሰፊዋን ኢትዮጵያን የፈጠርን እኛ ነን የሚሉትን የሸዋ ልሂቃንን መጋፋቱ ነበር። በግልፅ ቋንቋ ለማስቀመጥ፥ የኢያሱ ወንጀሎች የሸዋ ልጅ አለመሆኑ (የኢያሱ አባት ወሎ ነው)፣ ሐቀኛ የክርስቲያን ልጅ አለመሆኑ (አባቱ የግድ ክርስቲያን ከመሆናቸው በፊት መሐመድ ዓሊ ነበሩና) እንዲሁም የአውሮፓ የቅኝ ገዥ ኃይሎችን ማስቀየሙ ናቸው።

    እ.አ.አ በ1916 በመስቀል ቀን ኢያሱን ለማውረድ ሁሉም መሣሪያዎቻቸውን ይዘው ተሰለፉ። ቄሶቹ ኢያሱ ሐቀኛ የክርስቲያን ልጅ አይደለም በማለት በማውገዝ፣ የሸዋ ሊሂቃን ሠራዊታቸውን በመሳለፍ፣ የአውሮፓዊያኑ መንግሥታት ምክርና ጥበባቸውን ይዘው ተሰለፉ። የአውሮፓዊያኑ ጥበብ የሚገርም ነበር፤ ኢያሱ በኢትዮጵያ ባንዲራ ላይ የእስልምና ምልክት የሆነውን ግማሽ ጨረቃ ለጥፎ ለቱርኮች ዲፕሎማት ሲሰጥ የሚያሳይ ፎቶ ሾፕ የሆነ ሥዕል (ፎቶ ሾፕም፣ የባንድራ ፖለቲካም በልጅ ኢያሱ ዘመንም ነበር) መፈንቅለ መንግሥት እንድያከሄዱ የሸዋ ሊሂቃንን መርዳት ነበር። እዚህ ላይ ለታሪክ ትዝብት አንድ ነገር ልብ በሉልኝ። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ሳስተምር፥ የሀገረ-መንግሥት ግንባታ ችግሮቻችንን በሚመለከት ፈተናም ፈትኜበታለሁ፤ የሸዋው ጦር መሪ የነበሩት ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ የመፈንቅለ መንግሥቱም መሪ ነበሩ፤ ልጅ ኢያሱን ሲያወርዱ ባስተላለፉት መልዕክት ውስጥ የሚከተለው ይገኝበታል።

    “He claims that he eats flesh of cattle slain by Muslims in order to extend frontiers and to win hearts. But these Somali and Muslims have already been brought to heel [and do not need such diplomacy]”

    በጥሬው ሲተረጎም፥ ግዛትን ለማስፋፋትና ልቦችን ለመሳብ ብዬ በሙስሊም የታረደውን የከብት ሥጋ እባላለሁ ይላል። ነገር ግን እነዚህን ሱማሌዎችና ሙስሊሞችን ቀድሞውኑ ስላንበረከክን እንዲህ ዓይነቱ ዲፕሎማሲ አያስፈልጋቸውም።

    ይህንን የሀብተጊዮርጊስን ንግግር በሚመለከት ሰፊውን ትንተና ለናንተ ትቼ፥ በዚህ ዓይነት የተዛባ አመለካከት ላይ የተገነባችውን ኢትዮጵያን አስተካክሎ በሰፊ መሠረት ላይ የተገነባችውን ኢትዮጵያን ለመፍጠር የተደረገው የመጀመሪያ ሙከራ፥ ልጅ ኢያሱን ለሥልጣን ተብሎ በተጠነሰሰው ሤራ መውረዱን እንዳትረሱት አደራ ማለት እፈልጋለሁ። ያመለጠንን ዕድል ትርጉም ግን ለታሪክ መተውን አመርጣለሁ።

    2) ኢያሱን በወሳኝነት የተኩት ንጉሥ ኃይለ ሥላሴ

    የሀገራችንን ሀገረ-መንግሥት ግንባታን በተሻለ መሠረት ላይ ለመገንባት ረጅም ጊዜ (ለ60 ዓመታት ገደማ አገሪቷን መርተዋል) በልጅነታቸው የተሻለ የፈረንጅ ዕውቀት የቀመሱና ከማንም የበለጠ ተደጋጋሚ ዕድል ያገኙ ነበሩ። ነገር ግን በእኔ ግምት ታሪክ የሰጣቸዉን ዕድል አልተጠቃሙበትም። ንጉሥ ኃይለ ሥላሴን የተለያዩ ሰዎች በተለያዩ የታሪክ ሚዛን ላይ ቢያስቀጣቸውምና እኔም ቢሆን በዘመናዊ ትምህርትና በመሳሰሉት ላይ የነበራቸውን አሻራ ቀላል ነው ብዬ ባላስብም፥ ንጉሡ ሕይወት ዘመናቸውን በሙሉ የግል ዝናንና ሥልጣንን ማዕከል ማድረጋቸው ኢትዮጵያዉያንን የ20ኛው ክፍለ ዘመን ሕዝቦች ማድረግ አልተቻላቸውም። ስለዘር ግንዳቸው ሀሜቱ እንዳለ ሆኖ፥ ከኢያሱ በተሻለ ደረጃ ኦሮሞም፣ ጉራጌም አማራም ነበሩ። ይህንን ስረ ግንድ አልተጠቀሙም። በተለይ ኦሮሞ ከሚባል ሕዝብ ሲሸሹ እንደኖሩ ብዙ ማስረጃዎች አሉ። ለማንኛዉም፤ አንድንድ ወሳኝ ነገሮችን እንመልከት።

    አምቦ 2ኛ ደረጃ ተማሪ በነበርኩበት ጊዜ የሰማሁት ይመስለኛል፤ አንድ ጋዜጠኛ ካነበቡት መጽሐፍት ዉስጥ የትኛውን እንደሚያደንቁ ሲጠይቃቸው፥ ቀልባቸውን በጣም የሳበውና ብዙ ጊዜ ደጋግመው ያነበቡት በኒኮሎ ማኪያቬሊ (Niccolò Machiavelli) የተፃፈውን “The Prince” የተባለውን እንደነበረ ትዝ ይለኛል። ንጉሡ አብዘኛዉን የሕይወት ዘመናቸዉን የተመሩት በማኪያቬሊ ምክር ነበር ብዬ እጠረጥራለሁ። በማክያቬሊ ትምህርት በመመራትም የሥልጣን ተቀናቃኞቻቸውን አንድ በአንድ አስወግደው ከአስራ አራት ዓመታት በኋላ እ.አ.አ በ1930 ጥቁር ማክያቬሊ ፈላጭ ቆራጭ ንጉሥ ሆነው ወጡ።

    እንደ ሀብተጊዮርጊስ ዓይነቱን እግዚአብሔር በጊዜ ሲገላገልላቸው፣ እንደ ጎንደሩ ራስ ጉግሳና ባለቤታቸው ንግስት ዘዉድቱን ያስወገዱበት የፖለቲካ ጥበብ፣ በጊዜው በርግጥም አስደናቂ ነበር። ይህ የንጉሡ ጥበብ፤ አርባ ዓመታትን ቆጥራ የአድዋን ሽንፈት ለመበቀል የመጣቸውን ጣሊያንን ለመከላከል አልረዳም። መንግሥታቸዉንም፤ ሀገሪቷንም ለክፉ ቀን አላዘጋጁም።

    አድዋ ላይ ታሪካዊ ድል ያስገኙ ጀግኖችም የሉም። አንድ ለታሪክ የተረፉት ደጀዝማች ባልቻ ሣፎም በንጉሡ ዉሰኔ እስር ቤት ነበሩ። እዚህም ላይ አንድ የታሪክ ትዝብት አስቀምጬ ማለፍ እፈልጋለሁ። ኃይለ ሥላሴ ለሥልጣናቸዉ ብሎ የገፏቸው ብዙ የአከባቢ መሪዎች፥ ከትግራዩ ደጃዝማች ኃይለሥላሴ ጉግሳ ጀምሮ የጎንደር፣ የጎጃም፣ የሸዋ፣ የጅማ፣ የወለጋ ገዥዎች የጣሊያን ባንዳ ሆኑ። ከሚታወቁት ውስጥ ለታሪክ ‘ተፈሪ ሌላ፣ ሀገር ሌላ’ ብለው ሲዋጉ የሞቱት ደጃዝማች ባልቻ ብቻ ነበሩ። በንጉሡ ስህተት ሀገሪቷ ውድ ዋጋ ከፍላለች። ለዚህ ነው ጠቅላይ ሚኒስቴሩን ጨምሮ የብልጽግና ፓርቲ ባለሥልጣናት ጠዋትና ማታ ባንዳ፣ ባንዳ ሲሉ፥ ግብፅ ሱዳንን ይዛ የምር ከመጣች ሰው ያላሰበውን አሳስበው ለኪሳራ እንዳይዳርጉን የሚፈራው።

    ያም ሆነ ይህ፥ ኃይለ ሥላሴ ለጦርነት ያላዘጋጇትን ሀገር በክፉ ቀን ጥለው ሸሹ። ሐረርጌ ላይም የጂቡቲን ባቡር ሲሳፈሩ ከጦር ሜዳ መሸሻቸውን ለመሸፈን፥ ‘የት ይሄደሉ?’ ብሎ ለጠያቀቸዉ የፈንሳይ ጋዜጠኛ፡ “Je ne suis pas né soldat” (“ወታደር አይደለሁም”) ብለው ያለፉት። ለሳቸዉም ፍትሃዊ ለመሆን፥ የአውሮፓ ዲፕሎማቶች ቢክዷቸውም በዓለም መንግሥታት ማኅበር ላይ የሚያስመካ ሥራ ሠርተዋል። ሆኖም ከጦር ሜዳ የመሸሻቸው ጉዳይ እስከ መንግሥታቸው ፍፃሜ ድረስ እንደ ጥቁር ነጥብ ስትከታላቸዉ ኖራለች። የአርበኞችም ሆነ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ዋናው የተቃውሞ መፈክርም ይህች የሽሸት ጉዳይ ነበረች። ከጣሊያን ወረራ በኋላም ንጉሥ ኃይለ ሥላሴ በሁለት መሠረታዊ ነገሮች ምክንያት፥ ጋዜጣቸውን “አዲስ ዘመን” ብለው እንደሰየሙ፥ በእርግጥም አዲስ ዘመን፤ ለአዲስቷ ኢትዮጵያ ይፈጠራሉ ብሎ የጠበቁ ብዙ መሆናቸውን ብሎ መገመት አስቸጋሪ አይመስለኝም።

    ለአምስት ዓመታት በእንግሊዝ ሀገር በስደት ሲኖሩ ስለራሳቸው ስህተትም ሆነ የሰለጠነው ዓለም ንጉሦች እንዴት ሕዝቦቻቸውን እንደሚመሩና በዚያም ምክንያት በሕዝቦቻቸው ዘንድ ተከብረው እንዴት እንደሚኖሩ ተምረዋል ብሎ መጠበቅ ይቻል ነበር። ከሁሉም በላይ በጣሊያን ወረራ ምክንያት እሳቸውንም ሆነ ሀገራቸውን ከገጠመው ውርደትና ኪሳራ ይማራሉ ተብሎ ይጠበቅም ነበር። ከሁሉም አልተማሩም። በባሰ ሁኔታና ፍጥነት ወደ ድሮአቸው ተመለሱ። ለዓቢይነት፥ አስተዳደራቸውን የተቃወሙ የራያ ገበሬዎችን (ቀዳማይ ወያኔ የሚባለዉ ነዉ) ከየመን በመጡ የእንግሊዝ አይሮፕላኖች አስደበደቡ። የሪፐብሊካን አስተሳሰብ ነበራቸው የሚባሉትን አርበኛ ደጃዝማች ታከለን (ደጃዝማች ታከለ ወልደሀዋርያት) አሰሩ። እኚህ ሰው ከተደጋጋሚ እስር በኋላ በመጨረሻም ሊይዟቸው ከተላኩ የንጉሡ ወታደሮች ጋር ሲዋጉ ሞቱ። ሌላው ስመጥር አርበኛ የነበሩ በላይ ዘለቀንም ያለርህራሄ ሰቀሉ።

    የአምባሳደር ብርሃኑ ድንቄ ግልፅ ደብዳቤ እንኳን (አምባሳደር ብርሃኑ፤ በአሜሪካ አምባሳደር የነበሩና ንጉሡ የገፉበት መንገድ ዉሎ አድሮ ንጉሡንም ሆነ ሀገሪቷን ለዉርደት እንደሚያበቃ የመጀመሪያ የማስጠንቃቂያ ደወል በአደባባይ የሰጡ ባለስልጣን ነበሩ) አሠራራቸውን አላስለወጧቸውም።

    በፖለቲካ ሥርዓታቸው ላይ በተከታታይ ቦንቦች ፈነዱ። የመጀመሪያዉ ትልቁ ቦንብ በራሳቸው ቤተ መንግሥት ውስጥ የፈነዳው የነመንግሥቱ ንዋይ ያውም የእሳቸውን ክብርና ሞገስ ለመጠበቅ ከፈጠሩት የክብር ዘበኛ ጦር ነበር። ንጉሡ ከክስተቱ ከመማር ይልቅ ጀኔራል መንግሥቱ ንዋይን በሞት ቀጡ፤ የታናሽ ወንድማቸውን ሬሳ እኔን ያየህ ተቀጣ በሚመስል መንገድ በስቅላት ቀጡ። የበሉበትን [ወጭት] ሰባሪዎች ናቸው ብለውም በአዝማሪ አዘለፏቸው።

    ማን እንደመከራቸው ባይታወቅም ትልቁን የመንግሥታቸውን የዲፕሎማሲ ውጤትን ያበላሸውና ለትልቅ ኪሳራ ያበቃንን የኤርትራን ፌዴሬሽንን አፈረሱ። ውጤቱም ሁላችንም እንደምናውቀው የኤርትራ ነፃ አውጪ ግንባር መፈጠር ሆነ። ትንሽ ቆይቶ ደግሞ ኦሮሞዎች የሜጫና ቱለማ ልማት ማኅበር በመፍጠራቸው ጠገቡ ተብሎ መሪዎቹ እነ መቶ አለቃ ማሞ መዘምር ተሰቀሉ፤ ኃይለማርያም ገመዳ እስር ቤት ውስጥ በተፈፀመበት ድብዳባ ሞተ። ጀኔራል ታደሰ ብሩ ሞት ተፈርዶባቸው በአማላጅ ወደ ሐረርጌ በግዞት ተላኩ። እኔ እስከ ማውቀው ድረስ ሁሉም በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ጥያቄ አልነበራቸውም። ውጤቱ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)ን መፍጠር ሆነ። በነገራችን ላይ በእነ ኤሌሞ ቅልጡ በኦነግ ስም የመጀመሪያዋ ጥይት የተተኮሰችው ጀኔራል ታደሰ ብሩ የታሰሩበት ሥፍራ ሐራርጌ ዉስጥ ነበር። በዚሁ ጊዜ ሰፋፊ ማኅበራዊ ፍትህን የሚጠይቁ ተከታታይ ጥያቄዎችም መቅረብ ጀመሩ። እ.አ.አ በ1965 የንጉሡ ፊውዳላዊ ሥርዓት የተመሠረተበት ላይ በመሬት ላራሹ ሰልፍ ድንገተኛ የፖለቲካ ቦንብ ፈነዳ። ከአራት ዓመት በኋላ ደግሞ እስከዛሬ ኢትዮጵያን እያመሰ ያለው በእነ ዋለልኝ መኮንን የብሔረሰቦች ጥያቄ ታወጀ። ይህችኛውን ንጉሡና ሥርዓቱ በቀላሉ የተመለከቷት አይመስልም። ንጉሡ የቀ.ኃ.ሥ ዩኒቨርሲቲ፥ የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ማኅበር ፕሬዝደንት የነበረውን ጥላሁን ግዛዉን በማሰገደል “ልጆቼ” ከሚሏቸው ተማሪዎች ጋር ደም መቃባት ዉስጥ ገቡ። በዚህም የታሪክ ጎማው ወደፊት እንዳይሽከረከር ጣሩ።

    አሳዛኙ ጉዳይ መካሪዎቻቸውም ሆኑ እሳቸው አስተዳደራቸው ለሃያኛዉ ክፍለ ዘመን የማይመጥን መሆኑን፣ በጣም እወዳታለሁ የሚሏትም ኢትዮጵያ በታሪክ ፍራሽ ላይ ተኝታ የምትሸሞነሞን ሀገር መሆኗን አልተረዱም። የኤርትራ ግንባሮች ጥይትም ከረጅም ዘመን እንቅልፋቸው አላነቋቸውም። የባሌና የጎጃም ሕዝብ አመፅም አልቀሰቀሳቸውም። ለዓመታት የቆየው የተማሪዎች ንቅናቄ ጩኸትም አላነቃቸውም። ከኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ በቀጥታ የወጡ የመኢሶንና የኢህአፓ የሶሻሊስት አብዮት ደወልም አላነቃቸውም። በመጨረሻም በመቶ ሺዎች የሚቆጠረው የወሎ ሕዝብ እልቂት እንኳን ከእንቅልፋቸዉ አላበነናቸውም።

    በነገራችን ላይ፥ ብልጡ ደርግ በጠዋቱ ሊያወርዳቸው፣ ማታ ያሳየው የወሎ ሕዝብ እልቂት፥ በአንድ በኩል የንጉሡ ውሻ በጮማ ሥጋ ሲጫወት፣ በሌላ በኩል ደግሞ በረሃብ በተረፈረፈ ሕዝብ ውስጥ ሕፃን ልጅ የሞተች እናቷን ጡት ስታጠባ የሚያሳየዉን የጆናታን ዲምበልቢ (Jonathan Dimbleby, “The Unknown Famine”) ፊልም ነበር። ያንን ፊልም ደርግ በቅድሚያ ንጉሡና የኢትዮጵያ ሕዝብን እንዲያዩ ስለጋበዘ ቴሌቪዥን ያልነበረን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በስድስት ኪሎና አራት ኪሎ አካባቢዎች ያሉትን ቡና ቤቶችን አጣብበን ስንመለከት ነበር። የንጉሡ ደጋፊዎች እንኳ ጃኖሆይ እንዲህ ጨካኝ ነበሩ እንዴ? የሚሉትን ይዘን ወደ ዶርማችን እንደገባን ትዝ ይለኛል። ምናልባት ከእንቅልፋቸው የነቁት በማግስቱ የደርግ አባላቱ በኩምቢ ቮልስዋገን ከቤተ መንግሥታቸው ወደ አራተኛ ክፍለ ጦር ሲወስዷቸው በሠሩባቸው ድራማ ይመስለኛል። ብልጣብልጦቹ ደርጎች የተጠቀሙት ቮልስ መጀመሪያ መስኮቷ ዝግ ነበር ይባላል።

    ንጉሡ ከውጭ ብዙ ሰው ሲጮህ ተመልክተው፥ “እናንተ ልጆች የሚወደን ሕዝባችን ንጉሤን የት እየወሰዳችሁ ነው እያለ ነዉ” ሲሉ፥ ብልጦቹ ደርጎችም መስኮቱን ከፍተው የሕዝቡን ድምፅ ሲያሰሟቸው ጩኼቱ “ተፈሪ ሌባ፤ ተፈሪ ሌባ” የሚለውን ሰምተው፥ “አይ ኢትዮጵያ ይኼን ያክል በድዬሻለሁ እንዴ?” አሉ ይባላል። በዚህ ሽኝታቸው ድሮ ቤተ ክርስቲያን ሲሄዱ ዳቦ የሚጥሉላት ለማኝ ዳቦዋን ስትጠብቅ፥ ‘ንጉሡ ወረዱ፤ ንጉሡ ወረዱ’ ሲባል ሰምታ፥ ‘ለዚህ ያበቃኸኝ አንተ ነህ!’ ብላ በቮልሷ አቅጣጫ የወረወረችው ዳቦ ብቻ ነበር ይባላል። የንጉሡ ሬሳም ከ17 ዓመታት በኋላ ከመንግሥቱ ኃይለማርያም ሽንት ቤት ሥር ተቆፍሮ እንደተገኘ ይታወቃል። እዚህ ላይ ልብ አድርገን ማለፍ ያለብን የፖለቲካ ቁም ነገር ለ60 ዓመታት ገደማ (የአምስት ዓመቱ የጣሊያን ወረራ እንዳለ ሆኖ) በፈላጭ ቆራጭነት ኢትዮጵያን ሲገዙ የሀገረ መንግሥታቸው ግንባታ ፕሮጀክት በአጉል ምክርም ይሁን በራሳቸው ገታራ አቋም ከሽፎ ሽኝታቸው በለማኟ ዳቦ፣ ቀብራቸው ደግሞ በአሳደጓቸው ወታደሮች ሽንት ቤት ሥር መሆኑ ነው።

    3) አብዮቱ እና የደርግ የሀገረ-መንግሥት ግንባታ ሙከራ

    አዲስቷን ኢትዮጵያን ለመፍጠር ሕዝባዊ አብዮቱ ልዩ ዕድል ፈጥሮ ነበር። አብዮቱ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ማኅበረሰቦች የመጡ የአዲሱ ትዉልድ ምሁራን ድጋፍና ተሳትፎ ነበረው። እንደ አብዮቱ መሪ ወደፊት የመጣውን መንግሥቱ ኃይለማርያምም ‘ቪቫ መንግሥቱ፣ ቪቫ መንግሥቱ!’ ብለን ተቀብለን ነበር።

    የኢትዮጵያ አብዮትን አብዮት ያደረገው የጭሰኝነት ሥርዓትን ያስወገደውና የደርግ እርምጃ (ውለታው የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ቢሆንም) እስከዛሬ በኢትዮጵያ የሕዝቦች የትግል ታሪክ ውስጥ ልዩ ሥፍራ አለው ብዬ ባምንም፥ ነገሮችን በቶሎ የሚያዩ ወጣቶች “ተፈሪ ማረኝ፤ የደርጉ ነገር አላማረኝ ” ማለት የጀመሩት ብዙዉም ሳይቆዩ ነበር። በአጭሩ ለማስቀመጥ፥ የደርግ የሥልጣን ፍቅር፣ የመኢሶንና የኢህአፓ አሳዛኝ ክፍፍል፣ የኤርትራ ግንባሮችና የህወሓት የተናጠል የፖለቲካ ፕሮጀክቶች በአብዮቱ መፈንዳት የተፈጠረውን ልዩ ታሪካዊ ዕድል አምክኖታል።

    ደርግ መሃይምነትና የሥልጣን ፍቅር ስለተደባለቀበት፥ የሶሻሊስት አብዮቱን እንደሰው ማሰርና መግደል ወሰደው። በዚህ ሶቭዬት ህብረት ድረስ ሄዶ የሌኒን ሐውልት አይተው የመጡት ባለሥልጣኖቹ ስለሶሻሊዝም የተማርነው ከበሰበሰ ከቡርዧ ቤተ መፃሕፍት ሳይሆን ከምንጩ ከሌኒን ሀገር ነው እያሉ ተዘባበቱ። ካደሬዎቻቸው ድንቅ የሶሻሊስት ዕውቀታቸውን ከፍተኛነት ለማሰየት በሚመስል መንገድ የስታሊን ቀይ በትር ሥራ ላይ ይዋል አሉ። ደርግ የሱማሌ ወረራን፣ የኤርትራ ግንባሮችና የህወሓት እንቅስቃሴዎች በኢትዮጵያ አንድነት እንዲነግድ ልዩ ሁኔታ ስለፈጠሩለት “አብዮታዊት እናት ሀገር፥ ወይም ሞት!” አለ።

    ከኤርትራ ግንባሮች እስከ ኢህአፓ እና መኢሶን (ኢጭአት/ ኦነግን ጨምሮ ሌሎች ድርጅቶች እዚህ መሃል ናቸው) የኢትዮጵያ ሕዝቦች የአንድነትና የአብዮት ጠላቶች ሆነው ልዩ ልዩ ስሞች ተለጣፈበቸው። በአጭሩ የኢህአፓና መኢሶን መከፋፈልም ደርግን ብቻኛ የሀገር አንድነትና የአብዮት ተወካይ አደረገው። ሌሎች ዝርዝሮችን ትቼ ለኢትዮጵያ አንድነትና አብዮት ግንባታ ወሳኝ የሆኑ እርምጃዎችን ላንሳ።

    የደርግ የመጀመሪያው ሊቀ መንበር አማን አንዶም የሚባሉ ኤርትራዊ ጀኔራል ነበሩ። የደርግ ሊቀ መንበር ተብሎ ከደርግ ውጭ የተመረጠትም ለኢትዮጵያ አንድነት ብሎ እስከ ሞቃዲሾ ድረስ ሄዶ ካልተዋጋሁ ብሎ ንጉሡን ያስቸገሩ መኮንን ስለነበሩ ነዉ። በወታደሮቹ ዘንድም ተወዳጅ ስለነበረ በራሳቸው በደርግ አባሎቹ ጥያቄ መጀመሪያ መከላከያ ሚኒስቴር፣ ከዚያም ከደርግ ውጭ የደርግ ሊቀ መንበር የሆነው የተመረጡትና በአደባባይ እስከሚታወቀውም በኢትዮጵያ አንደነት ላይም (መቼም በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ልዩ ፍቅር አለን የሚሉ ብዙ ቢኖሩም፥ ፍቅራቸውን የሚለካልን መሣሪያ በሜዲካል ሳይንስ እስካሁን አልተፈጠረልንም) ምንም ዓይነት ጥያቄ ያልነበራቸውና የኤርትራን ችግር በሰላም ለመፍታት አሥመራ ድረስ ሄዶ ሕዝቡን ያወያዩ ነበሩ። ለኢትዮጵያ ልዩ ፍቅር አለኝ የሚሉ እነሻለቃ መንግሥቱ ኃይለማርያም ግን ጠረጠሯቸዉ፤ በታንክ እቤታቸው ውስጥ ገደሉት። በእኔ ግምት ውጤቱ የኤርትራና የኢትዮጵያን አንድነት መግደል ነበር። በዚህም ኤርትራ የደም ምድር ሆነች። ዛሬ እንዲህ ልንሆን የፈሰሰው የሰው ደም ዋጋም ሆነ ለጠፋው ሀብትና ንብረት ሂሳብ ለፈረደበት ታሪክ መተው ይመረጣል።

    የብሔራዊ አንድነት መንግሥትን ልታመጡብኝ ብሎ መንግሥቱ ኃይለማርያም ሁለተኛውን የደርግ ሊቀ መንበር የነበሩትን ጀኔራል ተፈሪ በንቲን ከደጋፊዎቻቸው የደርግ አባላት ጋር ረሸናቸው።

    ኮሎኔል አጥናፉ አባተንም ቅይጥ ኢኮኖሚ ልታመጣብን ነው ብሎ መንግሥቱ ኃይለማርያም በፀረ-አብዮታዊነት ረሸነዉ። በነገራችን ላይ የመጨረሻ ጭንቅ ሲመጣ መንግሥቱ ኃይለማርያም የአጥናፉን ቅይጥ ኢኮኖሚ ላይ ለመንጠላጠል ሞክሮ ነበር።

    በዛሬው የኦሮሞ ፖለቲካ ውስጥ ልዩ ሥፍራ ያላቸው ጀኔራል ታደሰ ብሩ ለሁለተኛ ጊዜ ሞት ተፈርዶባቸው ተረሸኑ። እኔ መከታተል እስከቻልኩ ድረስ ታደሰ ብሩ በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ፍጹም ጥያቄ ያልነበራቸው፤ ለኢትዮጵያ ብሎ ከሰላሌ ጫካ እሰካ ሞቃዲሾ ድረስ ተወስደው የታሰሩ እንግሊዞች ኢትዮጵያን ነፃ እናወጣለን ብለው ሲመጡ ከነሱ ጋር እየተዋጉ የመጡ አርበኛ ነበሩ። ከተራ ወታደርነት እስከ ጀኔራል ማዕረግ ድረስ ሀገራቸውን ያገለገሉም ነበሩ። እግር ጥሏቸው አብዮቱ ውስጥ የገቡት መንግሥቱ ኃይለማርያም ያላርህራሄ ገደሏቸዉ። በነገራችን ላይ ከጀኔራል ታደሰ ብሩ ጋር በፀረ አንድነት ክስ የተገደለ፣ ብዙ ሰው የማያስታውሰው መለስ ተክሌ የሚባል በቀ.ኃ.ሥ ዩኒቨርሲቲ ከተማሪ መሪዎች አንዱ የሆነ የትግራይ ተወላጅ ነበር (በጊዜዉ ከነበረዉ አቋም ተነስቼ፥ ይህ ሰው ቢቆይ ኖሮ የትኛው ድርጅት ውስጥ ሊገባ እንደሚችል ዶክተር አረጋዊን ደግሜ መጠየቄን አስታውሳለሁ)። ይህ ሰዉ ሌላ ተከታይ ቢያጣ ለሩብ ምዕተ ዓመት አከባቢ የምኒልክ ቤተ መንግሥትን ተቆጣጥሮ በፈላጭ ቆራጭነት ሀገሪቷን የገዛው ለገሠ ዜናዊ ስሙን አንስቶ ትግራይ በረሃ ገብቷል። ይህም ደርግ በኢትዮጵያ አንድነት ስም ያመጣብን የታሪክ ዕዳ ነው።

    በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ምንም ዓይነት ጥያቄ እንዳልነበራቸው በተሻለ የማውቃቸውን የመኢሶን መሪዎችን ላንሳ። ለሥልጣን ተብሎ በደርግና ብዙ የፖለቲካ ተቀናቃኞቹ ዘንድ እንደ ኦሮሞ ድርጅት፥ በኦሮሞ ደግሞ እንደነፍጠኛ ድርጅት የሚታየው መኢሶን በዘመኑ በየትኛውም ሚዛን የተሻለ ትምህርት የነበራቸው መሪዎች ነበሩት፤ በስብጥራቸውም ኤርትራዊ የዘር ግንድ አላቸው ከሚባሉት ኅሩይ ተድላ እና አበራ የማነአብ እስከ ሲዳማው እሼቱ አራርሶ የነበሩበት ነው። ሽኩሪ የሚባል አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አብረን የነበርነው ልጅ በስተቀር ሰፊ ተሳትፎ እንደልነበራቸዉ የማዉቀዉ የሱማሌ ምሁራንን ብቻ ነበር።

    የመጀመሪያዉ የመኢሶን ሊቀ መንበር የሰሜን ሸዋ አማራ ከሚባለው የተወለዱ፥ ዶ/ር ወርቁ ፈረደ፣ ሁለተኛው ኃይሌ ፊዳ፣ ሦስተኛው የወሎ አማራ ከሚባለው የመጡ ዶ/ር ከበደ መንገሻ ነበሩ። ሕብረ ብሔር ነን፤ ለሀገረ- መንግሥት ግንባታው የተሻለ ግንዛቤም እዉቀትም አለን ለሚሉ የመኢሶን ምሁራንም ደርጎች ርህራሄ አላደረጉም። በተለይ የመጀመሪያው የኦሮሞ የምሁር ትዉልድ የሚባሉት ኃይሌ ፊዳን ጨምሮ አብዱላህ ዩሱፍ፣ ዶ/ር ከድር መሀመድ፣ ዶ/ር ተረፈ ወልደፃዲቅ፣ ዶ/ር መኮንን ጆቴ የመሳሰሉት ሕበረ ብሔር በሚባለው መኢሶን ውስጥ አልቀዋል። በእኔ እምነት ብዙዎች ሊቀየሙኝ ቢችሉም፥ እንደስማቸው በኢትዮጵያ ምድር ሕብረ ብሔር የነበሩ ድርጅቶች መኢሶንና ኢህአፓ ብቻ ነበሩ። አላስፈላጊ ክርክር ዉስጥ ሳልገባ፥ እኔ እስከ ማምነው ድረስ ኢሠፓ የወታደሮች ፓርቲ ነበር። የኢህአዴግን ምንነት ለብልጽግና አበላት እተዋለሁ። የብልጽግናን ምንነት ደግሞ የታሪክ ፈተናዉን ሲያልፍ ብንነጋገርበት የተሻለ ይመስለኛል።

    ደርግ ሕበረ ብሔር ድርጅቶችን በቀላሉ አንድ በአንድ ቀርጥፎ በላቸው። ኢህአፓን ቁርስ አደረገ፤ መኢሶንን ምሳ አደረገ:: ብሔር ሆኖ ለመውጣት ገና ዳዴ የሚሉትን ወዝሊግንና ማሌሪድን እራት አደረጋቸው። ከደርግ ዱላ የተረፉት በደርግ አስተዋጽኦ ጭምር በተሸለ ሁኔታ ኃይል ሆነዉ የወጡት የብሔር ንቅናቄዎች ናቸው። ኢጭአት (የኢትዮጵያ ጭቁኖች አብዮታዊ ትግል) ወደ ኦነግ ተጠቃልሎ ገብቶ ዛሬ የምናውቀው ኦነግን ፈጠረ። የሱማሌ ድርጅቶች ኦብነግ ዓይነትን ፈጠሩ። የሲዳማ አርነት ንቅናቄ ቢያንስ ዋናው ክንፍ ዛሬ ሲአን (የሲዳማ አርነት ንቅናቄ) የሚለው ሆነ። አፋሮችም የአፋር ግራ ክንፍ አርዱፍ እያሉ በሕይወት ያሉ ድርጅቶች አሏቸው። በጣም የተሳካላቸው የብሔር ንቅናቄዎች በኢትዮጵያና ኤርትራ ላይ ደርግን ለሁለት ቀብረው መንግሥታት ሆኑ።

    የደረግ ዘመንን ስናጠቃልል መረሳት የሌለባቸው ሦስት ዋና ዋና ጉዳዮች፥ ለሥልጣን ብሎ ደረግ ባካሄዳቸው ጦርነቶች፡-

    የሀገረ-መንግሥት ግንባታውን የበለጠ አወሳስቦ መሄዱን፣
    ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ በፃፉት መጽሐፍ በትክክል እንዳስቀመጡት፥ ደርግ ትቶት የሄደው በደም እምባ የታጠበች ሀገር መሆንዋን፣
    በሀገር አንድነት ስም ባካሄደው ትርጉም-የለሽ ጦርነት የባከነው የሀገር ሀብት ብቻ ሳይሆን በዓለም ትልቋ ወደብ-አልባ ሀገር ኢትዮጵያን ትቶ መሄዱን ነዉ።

    ደርግ ለ17 ዓመታት የተጫወተዉ የአጥፍቶ መጥፋት ፖለቲካን እንደ ኑዛዜም፣ እንደ ቁጭትም የደርግ ከፍተኛ ባለሥልጣን የነበሩት ኮሎኔል ፍስሃ ደስታ (ኮ/ል መንግሥቱ ኃይለማርምም ሆነ ሻምበል ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ እድፋቸውን ከታጠቡበት በጣም ይሻላል) በፃፉት መጽሐፍ ልዝጋ።

    የኢህአፓ ወጣቶችን የትግል ስሜት፣ የመኢሶን መሪዎች ዕውቀትና የእኛን የወታደሮቹን የሀገር ወዳድነት ብንጠቀምበት ኖሮ ሀገራችን እንዲህ አትሆንም ማለታቸውን እስር ቤት ሆኜ ማንበቤ ትዝ ይለኛል። ምክራቸው ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይም የሚሆን ይመስለኛል። በነገራችን ላይ በታሪክ አጋጣሚ ወደ አስር ወሮች ገደማ በኢህአዴግ እስር ቤት የተኛሁበት አልጋ ኮ/ል ፍስሃ ደስታ ይተኙበት እንደነበረ ሰምቻለሁ።

    4) የኢህአዴግ ዘመን የሀገረ-መንግሥት ግንባታ

    ለአራተኛ ጊዜ የሀገራችን ፖለቲካን ማሰልጠንና የተሻለ የሀገረ-መንግሥት ግንባታ ዕድል ያመለጠን የኢህአዴጉ ዘመን ነው (ይህ የመለስ እና የኃይለማርያም ዘመንን ይጨምራል)። የኢህአዴግ ዘመን ሌላው ቢቀር የብሔረሰቦች ጥያቄን ለሁሉም ሕዝቦች ተቀባይነት ባለው መንገድ ይመልሳል ብሎ (እኔን ጨምሮ) የጠበቁ ብዙ ናቸው። ይህም ለሀገረ-መንግሥት ግንባታ የተሻለ ዕድል ይፈጠራል ተብሎም ተገምቶ ነበር።

    ገና የሽግግር መንግሥቱ ሲመሠረት፥ የኢህአዴግ ባለሥልጣናት እንደግል ሠርጋቸው የፈለጉትን ጠርተው፣ ያልፈለጉትን በመተው የሠሩት የፖለቲካ ቲያትር ጫካ ሆነው ስደግፋቸው ከነበሩት የኢህአዴግ መሪዎች ተለየሁ። እኔም ብቻ ሳልሆን ብዙ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ጓደኞቼ በዚህ ጊዜ የተለዩዋቸዉ ይመስለኛል። ኢህአዴግ መጀመሪያ በጦርኛነት፤ ቀጥሎ ደግሞ በዘመኑ ቋንቋ የሽብርተኝነት ታርጋ እየለጠፈ ለ27 ዓመታት ሕዝብና ሀገርን አመሰ። ዝርዝር ነገሮች ውስጥ ሳልገባ፥ በኦሮሚያ እና በሱማሌ ክልሎች፤ በሲዳማ፣ በሀዲያ፤ በወላይታ፣ በጋምቤላ፣ በአፋር፣ ቁጥራቸውን የኢህአዴግ ባለሥልጣናት እንኳ የማያውቁት ሕይወት ጠፋ። የአፍሪካ መዲና የምትባለው አዲስ አበባ/ፊንፊኔም ሆነች የኢህአፓን ጠበል በቀመሱ ብአዴኖች የሚመራው የአማራ ክልልም ውሎ አድሮ ከኢህአዴግ ዱላ አልተረፉም።

    በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም (ነገርየው መሬት ላይ ሲፈተሽ፥ የአብዮታዊነትም የዴሞክራሲያዊነትም ባህርይ አልነበረውም) የተተበተበው የሞግዚት አስተዳደር እውነተኛ የፌዴራል ሥርዓት ሊሆን አልቻለም። የሕዝቦችን እራስን በራስ ማስተዳደር ጋር ምንም ግንኙነት ያልነበረው፥ ጆርጅ ኦርዌል የእንስሳት እርሻ (George Orwell, “Animal Farm”) በሚለዉ መጽሐፉ ላይ፥ ሁሉም እንስሶች እኩል ናቸው፤ አንዳንድ እንስሶች የበለጠ እኩል ናቸው “All animals are equal, but some are more equal than others” ከሚለው ያለፈ የፖለቲካ ፋይዳ አልነበረውም። ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ተብዬዎቹም ከ97ቱ በስተቀር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መፍጠር ይቅርና ቅርጫ እንኳ ሊ ሆኑ አልቻሉም። ዉጤቱም ዴሞክራሲያዊ የሀገረ-መንግሥት ግንባታ ዕድል መጨናገፉ ብቻም ሳይሆን ለ27 ዓመታት ውድ የሕይወት ዋጋ ጭምር ሲያስከፍለን ኖሯል። በዚህም ምክንያት የታሪክ ጣጣችንን አስተካክለን በእኩልነት ላይ የተመሠረተ ዴሞክራሲያዊ ፌዴራሊዝም የመፍጠር ተስፋችን ሕልም ሆኖ ቀርቷል።

    5) በማምለጥ ላይ ያለ አዲስ የሀገረ-መንግሥት ግንባታ ሙከራ

    አሁን እየገጠመን ያለውን የታሪክ ፈተናን ለማለፍ፥ ጨክነን በቁርጠኝኘት ብሔራዊ መግባባት ውስጥ መግባት ወይም ኢትዮጵያን እንደ ሀገረ-መንግሥት የምታበቃበት የሚጨምር ቀውስ ውስጥ መግባት ይመስለኛል። እዚህ ላይ የሌሎች ሀገሮችን ፖለቲካ በድኅረ ቅኝ ግዛት ዘመን ብቻ እንኳን በመቀኛት ብጀምር፥ ችግሮቻቸውን ለመፍታት በቁርጠኝነት የሠሩት ተሳክቶላቸዋል። ያንን ያልቻሉት ወይ ፈርሰዋል ወይም አሁንም በቀውስ ውስጥ እየዳከሩ ነዉ። ቅኝታችንን በላቲን አሜሪካ ብንጀምር፥ ቀዉስ ገጥሟቸዉ አነ አርጀንቲና፣ ቺሌ፣ ፔሩ፣ ኒካራጓ፣ ኮሎምቢያ የመሰሰሉ ሀገሮች በተለያየ ደረጃ ፖለቲካቸውን ያስተካከሉ ሀገሮች ናቸው። ከ60 ዓመታት በላይ ለልዕለ ኃያሏ አሜሪካ ሳትበገር በአሜሪካ አፍንጫ ሥር የኖረችው አስደናቂዋ ሶሻሊስት ኩባና በአሜሪካ ጣልቃ ገብነት ምክንያት አሁን በሁለት ፕሬዝዳንቶች የምትገዛዋ ሶሻሊስት ቬኔዙዌላም በዚሁ ክፍለ ዓለም ይገኛሉ። በአውሮፓ ፖርቹጋል፣ ስፓኝ፣ ግሪክ፣ ፖለቲካቸዉን ማስተካከል ችለዋል። ዩጎዚላቪያ ውድ ዋጋ ብትከፍልም ከመፍረስ አልደነችም። ሶቭዬት ህበረትና (ግማሽ አውሮፓ ነች) ቼኮዝላቫኪያ በሰላማዊ መንገድ ፈርሰዋል። በኤዥያ፥ ኔፓል የፓለቲካ ችግርዋን በብሔራዊ መግባባት ስትፈታ፥ፓኪስታን፣ ቬየትናም፣ ካምቦዲያና ላኦስ ደግሞ ችግሮቻቸውን በጦርነት ፈተዋል። አፍጋኒስታን፣ ኢራቅ፣ ሶሪያና የመን አሁንም እየቀወሱ ነው። ወደ አፍሪካችን ስንመጣ፥ ደቡብ አፍሪካና ጋና ከመሳሰሉት በስተቀር አብዘኛዎቹ በይስሙላ ምርጫ ላይ የተመሠረቱ አምባገነን መንግሥታት ሲሆኑ፥ የአፍሪካ ሕብረትም የዲክታተሮች ማኅበር (trade union of dictators) ከመሆን አላለፈም (በኢህአዴግ ጊዜ የተከሰስኩበት አንዱ ወንጀሌ የአፍሪካ መሪዎችን ተሰደብክ የሚል ነበር)። ሱማሊያና ሊቢያ ፈረንጆች የወደቁ መንግሥታት (failed states) የሚሏቸው ሲሆኑ፤ ሩዋንዳ ጊዜውን ጠብቆ የሚፈነዳ ሌላ ቦንብ የምትጠብቅ ይመስለኛል።

    በዚህ የአፍሪካ ፖለቲካ ምስቅልቅል ጉዞ ውስጥ አንዱ የሚገርመኝ ላለፉት 60 ዓመታት ፖለቲካቸውን ማስተካከል አቅቷቸው በቀውስ ሲናጡ የኖሩ ሁለት ሀገሮች፥ በተፈጥሮ ፀጋ እጅግ ሀብታሟ የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፑቢሊክና የሦስት ሺህ ዓመታት ዕድሜ አለኝ የምትለዋ ድሃዋ ኢትዮጵያ መሆናቸው ነው።  ከንጉሡ ዘመን ጀምሮ ይህንኑ የሀገራችንን የፖለቲካ እንቆቅልሾችን የተከታተለ፣ ያጠና፣ ያስተማረና ብዙ ጽሑፎችን የፃፈበት ጆን ማርካከስ (John Markakis) የሚባል ፈረንጅ፥ የታሪክና ፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሴር “Ethiopia: The Last Two Frontiers” (የኢትዮጵያ፥ የመጨረሻዎቹ ሁለት ድንበሮች) ብሎ ፅፏል። ምሳ ጋብዞኝ መፅሐፉን ለዶ/ር ዓቢይ ስጥልኝ ብሎኝ፥ ዶ/ር ዓቢይ ያንብበው አያንብበው ባላውቅም፥ እሳቸውን ማግኘት ለሚችል ለኦፒድኦ ባለሥልጣን ልኬላቸው እንደነበርም አሰታዉሰለሁ። መፅሐፉ በአጭሩ የኢትዮጵያ መሪዎች የሀገረ-መንግሥት ግንባታ የንጉሦቹ ሞዴል (the Imperial model) ፣ የደርግ የሶሻሊስት ሞዴልና የኢህአዴጉ ፌዴራሊስት ሞዴል በሙሉ ከሽፈዋል ይላል። የከሸፉበትም ዋናዉ ምክንያት የባለጊዜ ገዥዎችን ሥልጣን ለማሳካት የተገፋበት መንገድ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን እኩልነት ያላጎናፀፈና የልማት ጥማታቸውንም ያላረካ በመሆኑ ነው ይላል።

    ይህ የፈረንጅ ምሁር እንዳለው፥ ፖለቲካችንን ማሰልጠን ባለመቻላችን ሚሊየኖች ሕይወታቸውን አጥተዋል፤ ሚሊዮኖች ከቀዬያቸው ተፈናቅለዋል፤ ሚሊዮኖችም ተሰደዋል። እኔም ከላይ ባነሳሁት ከዚሁ ምሑር ዕይታ ተነስቼ ሀገራችን ስለገባችበት የፖለቲካ ቅርቃርና በብሔራዊ መግባባት አንፃር ከቅርቃሩ ለማውጣት በሌኒን ቋንቋ ምን መደረግ አለበት (What is to be done?) የሚለውን መሠረታዊ ጥያቄ የሀገራችን ፖለቲካ እስከገባኝ ድረስ ልመልስ።

    1. መሠረታዊ ችግራችን በታሪክ አጋጣሚ ሥልጣን ላይ የወጡ መሪዎቻችን ሀገርን የመምራት ሕልማቸው፤ ሥልጣንን ጨምድዶ ከመቆየት ሕልማቸው ጋር ሁሌ ስለሚጋጭባቸው ነው። ለሕዝብ አለን ከሚሉት ፍቅር የሥልጣን ፍቅራቸው ስለሚበልጥባቸው ነው። ለዚህ ነው ንጉሥ ኃይለ ሥላሴ የሚወደንና (ሕዝቡ ምን ያከል እንደሚወደቸዉ እንዴት እነዳወቁ ባናዉቅም) የምንወደው ሕዝባችን ሲሉ ኖረው ለ60 ዓመታት ገደማ የገዟትን ኢትዮጵያ ለ20ኛዉ ክፍለ ዘመን ሳያበቁ ከዓለም ሀገሮች ጭራ ደረጃ ትተዋት የሄዱት። የሕዝብ ፍቅራቸውንም ደረጃ በረሃብ በመቶ ሺህዎች ያለቀው የወሎ ሕዝብ ይመሰክራል። ይህን የመሳሰሉ የመሪዎቻችን ባዶ የሕዝብና የሀገር ፍቅር፥ የንጉሡ ሕይወቴና የኢትዮጵያ እርምጃ፣ የመንግሥቱ ኃይለማርያም አብዮታዊት እናት ሀገር ወይም ሞት የመለስ ዜናዊ በቀን ሦስት ጊዜ የሚመገቡ ዜጎችን እፈጠራለሁ ወ.ዘ.ተ መሸፈን አይችልም። ለዚህ አሁን ያሉ መሪዎቻችንም ሆኑ ተስፈኛ መሪዎች ይህንን የታሪክ እውነታ በውል እንዲገነዘቡት እፈልጋለሁ።
    2. የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችና የተቀሩት ልሂቃን በተለያየ ደረጃ የሚጋጩ ሕልሞቻቸውን ይዘው መጓዛቸው ነው። ከመኢሶንና ኢህአፓ ዘመን እስከዛሬ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶቻችንና መሪዎቻቸው ይህንን እውነታ በውል መገንዘብ ይኖርባቸዋል። የሕልሟን ጉዳይ በፈንጆቹ አባባል ከዜሮ ድምር ፖለቲካ (zero-sum game politics) የመውጣቱን ጉዳይና የፖለቲካ ፍላጎቶቻቸዉን በገደብ የማድረጉን ነገር በጥብቅ እንዲያስቡበት እመክራለሁ። ዋና ጉዳያችን ሥልጣን ሆኖ ከፊንፊኔ እስከ መቀሌ ባንዳ፣ ባንዳ እየተባባሉ መካሰሱ ሕዝባችንን ከማደናገር በላይ ብዙ የፖለቲካ ትርፍ የለውም። ዛሬ በአሜሪካና በአውሮፓ በሚደረጉ ሰልፎች ላይ በአንድ እጅ እስክንድር ነጋ ይፈታ፣ በሌላ እጅ ጃዋር ሽብርተኛ ነው የሚሉት መፈክር ዓይነቶቹ ለሀገረ-መንግሥት ግንባታችንም ሆነ ለብሔራዊ መግባባት ሥራችን ብዙ የሚጠቅሙ አይመስሉኝም። በእኔ በኩል እንዲህ ዓይነቱ ጉዳይ ስላስቸገረኝ ነበር በ2008 በፃፍኩት መፅሐፍ ላይ ለቡዳ ፖለቲካችን መላ እንፈልግ ብቻ ሳይሆን የሚጋጩ ሕልሞች ሊታረቁ ወይስ ኢትዮጵያን ሊያፈርሱ በሚል ግልፅ ጥያቄ የደመደምኩኝ። ለእኔ መፍትኼው ለአዲስቷ ኢትዮጵያ ፈጠራ የሚሆን አዲስ ማኅበራዊ ውል (new social contract) ከመፈራረም ውጭ የተሻለ የማጂክ ፎርሙላ ያለን አይመስለኝም። ይህንን እውነታ የምኒልክ ቤተ መንግሥት ያሉ የብልጽግና ወንድሞቻችንም ሆኑ ከአዲስ አበባ/ፍንፍኔም እስከ አውሮፓና አሜሪካ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ግፋ በለው የሚሉ ሁሉ እንዲረዱልኝ አደራ እላለሁ። በቅርብ ጊዜ በተፈጠረው ቀውስ በሁሉም በኩል ላለቁትም የተሻለ የሐዘን መግለጫ የሚሆነውና ዕንባቸውን የሚያብሰው የችግሮቻችን ምንጭ አዉቀን ዘለቂ መፍትኼ ስንፈልግ ይመስለኛል።
    1. ከላይ ካነሳኋቸው ሁለት ነጥቦች ጋር ተያይዞ ሺህ ጊዜ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ እየተባለ በሕዝብ ላይ የሚሠራዉ የፖለቲካ ትያትር መቆም አለበት።
      የንጉሡ ዘመን የምርጫ ትያትሮች፣ የደርግ ዘመን የምርጫ ትያትሮች፣ የኢህአዴግ ዘመን የምርጫ ትያትሮች በግልፅ ቋንቋ ለማስቀመጥ፥ ሲያንሱ በዴሞክራሲ ስም የተቀለዱ  ቀልዶች፣ ሲበዙ ደግሞ በኢትዮጵያ ሕዝቦች ላይ የተሠሩና ታሪክ ይቅር የማይላቸው ወንጀሎች ነበሩ። በሰለጠነው ዓለም የሕዝብን ድምፅ ከመስረቅ በላይ ወንጀል የለም። እዚህ ላይ ሁለት ነገሮችን አስታውሼ ልለፈው። በ“ኢህአዴግ-1” ዘመን አቶ በረከት፥ “ኢህአዴግ ከስድስት ሚሊዮን በላይ አባላት አሉትና በዝረራ ያሸንፋል” ብሎ ሲያስቸግረኝ፤ አቶ በረከት፥ “ኢህአዴግ ሁለት ምርኩዞች አሉት፤ አንደኛው ምርጫ ቦርድ ነው። ሁለተኛው ጠመንጃችሁ ነው። ሁለቱን ምርኩዞቻችሁን አስቀምጣችሁ ተቃዋሚዎችን ካሸነፋችሁ፥ እኔ በግሌ እናንተ የምትሉትን 20 ና 30 ዓመታት ብቻ ሳይሆን ለሃምሳ ዓመታት እንድትገዙን እፈርምልሀለሁ” እንዳልኩት አሰታዉሰለሁ። በ“ኢህአዴግ-2” ጊዜ ደግሞ ዶ/ር ዓቢይ በጠሩት ድንገተኛ ስብሰባ ላይ ገለልተኛ የሆነው ጠቋሚ ኮሚቴ ስምንት ሰዎች አጣርቶ ስላቀረበ አራት ሰዎች መመረጥ ስላለባቸው በተጠቆሙት ሰዎች ላይ አስተያየት ስጡ አሉን። ሌሎች ስብሰባው ላይ የተገኙ የየድርጅት መሪዎች ያሉትን ብለዋል፤ እኔ ጨዋታው ስላላማረኝ፥ “አብዛኛዎቹን ዕጩዎች ብዙዎቻችን አናዉቃቸውምና ከየት እንደመጡ እንኳ ለማወቅ የ24 ሰዓት ጊዜ ስጡኝ” ብዬ አጥብቄ ጠየኩኝ። ዶ/ር አቢይ ‘አይቻልም’ አሉ። ነገ የምናገረው እንዳይጠፋኝና ለታሪክም ቢሆን ተአቅቦ (reservation) መዝግቡልኝ ማለቴ ትዝ ይለኛል። ምስክሮችም አሉኝ። የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መጥቶ የምርጫ ቦርድ ኃላፊዎች የምርጫ ጊዜውን ሰሌዳ ለማስተላለፍ በጠሩት የምክክር ስብሰባ ላይ እንደተናገርኩኝ፥ መለኮታዊ ጣልቃ ገብነት (divine intervention) ነው እንዳልኩኝ ምርጫው ባይተላለፍ ኖሮ የአዲሱ ምርጫ ቦርድ አካሄድ ሌላ ከበድ ቀውስ ሊያስከትል ይችል እንደነበረ ዛሬ ላይ ሆኜ በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ። ይህንኑ ደግም ብዙ ጊዜ በታጋይነቷ ለምናውቃት ክብርት ብርቱካንም ጭምር መናገሬን አስታውሳለሁ።

    ስለሆነም የሚመጣውን ምርጫ አዲስቷን ዴሞክራትክ ኢትዮጵያ እንድትወለድበት ካላደረግን፥ የንጉሥ የማክያቬሊ ምክር፣ የመንግሥቱ ኃይለማርያም፣ የጆሴፍ ስታሊን ቀይ በትር፣ የመለስ ዜናዊ፣ የሊቀ መንበር ማኦ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ውሰት፣ ኢትዮጵያን ለመለወጥ የታሪክ ፈተናውን ለማለፍ እንዳላስቻላቸዉ፥ የዶ/ር ዓቢይም የመደመር የፖለቲካ ቀመር አዛውንቱ የፈረንጅ ምሁር የሚለውን የኢትዮጵያ ፖለቲካ የመጨረሻ ሁለት ድንበሮችን የሚያሻግረን አይመስለኝም። እሱን ካልተሻገርን ደግሞ ሁሌም እንደምለው ለሁላችንም የምትሆን ዴሞክራትክ ኢትዮጵያ የምትፈጠር አይመሰልኝም።

    ከማጠቃለሌ በፊት የብሔረታዊ መግባባቱ የፖለቲካ ጥረታችን ይሳካ ዘንድ መፍትሄ የሚሹ ቁልፍ ጉዳዮች ላስቀምጥ፦

    1. ያለ ሀገራዊ ስምምነት በዋናነት በአንድ ቡድን ሕልምና ፍላጎት (በተለይ የአንድ ቡድን ፍኖተ-ካርታ /road map/) የመመረቱ ጉዳይ ለዉጡን አጣብቂኝ ዉስጥ ማስገበቱን የማወቅ ጉዳይ፤
    2. ለውጡን ለማምጣት በዋናነት የላቀ አስተዋጽኦ ያላቸው ኃይሎች (ለምሳሌ እንደ ኦሮሞ ቄሮ ዓይነቶቹ) ወደ ዳር የመገፋታቸው ጉደይ፤
    3. ለውጡን እየመራ ያለው ከራሱ ከኢህአዴግ የወጣ ቡድን ቢሆንም፥ በለውጡ ምንነት፣ ፍጥነት፣ ስፋትና ጥልቀት ላይ የተለያዩ የኢህአዴግ ክንፎች ስምምነት ማጣታቸውና በዚህም ምክንያት እያመጣ ያለው አደገኛ ሁኔታ፤
    4. በሚጋጩ ሕልሞቻችን ምክንያት ላለፉት 50 ዓመታት መፍትሄ ያላገኘንለት የመከፋፈል ፖለቲካችን (political polarization) ጉዳይ፤
    5. ዴሞክራሲያዊ ለውጡ ለአብዛኛዉ የኢትዮጵያ ሕዝቦችና የፓለቲካ ኃይሎች ተቀባይነት ያለዉ፣ ሰላማዊና የተሳካ እንዲሆን የጋራ ፍኖተ-ካርታ (roadmap) የመቀየስ አስፈላጊነት ጉዳይና፤ የተቀየሰዉን በጋራ ሥራ ላይ የማዋል ጉደይ፤
    6. ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ማለት በእርግጥም በሕዝቦች ይሁንታ ላይ የተመሠረተ የፓለቲካ ጨዋታ መሆኑን የመረዳት ጉዳይ፤
    7. ሀገራችን እዉነተኛ ዲሞክራሲያዊ የፈድራል ሥርዓት ያስልጋታል ስንል፥ ከሕልሞቻችን በሻገር በሕዝቦቻችን ፍላጎት ላይ የተመሠረተ የፖሊቲካ ሥርዓት መሆኑን የማረጋገጥ ጉዳይ፤
    8. ብሔራዊ መግባባቱ በተሻለ መንገድ የሚሳካው፥ በደቡብ አፍሪካ እና ኮሎምቢያ በመሰሰሉት ሀገሮች እንዳየነው የፖለቲካ እስረኞችንና የጫካ አማፅያንን መጨመርን የማስፈለጉ ጉዳይ፤
    9. የተሳካ ብሔራዊ እርቅን ለመምጣት ከሥልጣን በሻገር የምር የፖለቲካ ቁረጠኝነት (political will) የማስፈለጉ ጉዳይ፤
    10. ስለኢትዮጵያ አንድነት ያለን ግንዘቤ ከፊታዉራሪ ሀብተጊዮርጊስ እይታ የሰፋና ለሀገሪቷ ያለን ፍቅርም ገደብ የማድረጉ ጉደይ ናቸዉ።

    በመደምደሚያዬም፥ እዚህ ያደረሰንን የሀገራችንን ፖለቲካ ጉዞ ታሪክ ወደኋላ እያየሁ፥ የወደፊቱን የሀገራችንን ዕጣ ፈንታንም እያማተርኩ ለጠቅላይ ሚኒስትሩም፣ ለሁላችንም የታሪክ የግርጌ ማስታወሻ ልተዉ።

    በቅርብ ቀን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‘ኢትዮጵያ አትፈርስም፤ ኢትዮጵያን የሚያፈርሷት እኛን ቀድሞ ሲያፈርሱ ነው፤ ኢትዮጵያን ለማፍረስ አይፈቀድላቸውም’ ሲሉ አዳምጫለሁ። ሀገርን ለመፍረስ የሚፈልጉ ኃይሎች መጀመሪያኑ ፈቃድ ይጠይቃሉ፤ አይጠይቁም የሚለዉን ክርክር ውስጥ ሳልገባ፥ በጨዋ ቋንቋ ንግግራቸውን አልወደድኩላቸውም። ንግግራቸውንም ተከትሎ የኢሳት ቴሌቪዥን የፖለቲካ ተንታኞች የሚታወቁ የአዛውንት ምሁርን በመጥቀስ (ይህኑን ምሁር መንግሥቱ ሀይለማርያምም ያዉቃል ብለን ስለተሠሩ የንጉሡ ባለስልጣኖች ምክር ጠይቀነዉ፥ ጠመንጃዉ በእናንተ እጅ ነዉ፤ የምን ምክር ትጠይቁናላችሁ ብሎኛል ማለቱን አንብቤአለሁ) ዶ/ር ዓቢይ ጥሩ ይዘዋል፤ ሕጉንም ሰይፉንም እየተጠቀሙ ነው ያሉት የበለጠ ሥጋት ፈጥሮብኛል። እዚህ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ሁላችንም ደጋግመን ማሰብ ያለብን ጨዋታው ከተበላሸ አብዛኛው ዓለምን በሰዓታት ውስጥ ወደ አመድነት የሚለወጥ ወይም ሕይወት-አልባ ሊያደርግ የሚችል የኒዩክሊየርር መሣርያ የታጠቀ፣ ነፍሷን ይማርና የሶቭዬት ህብረት ሠራዊት ዓይኑ እያየ ሀገራቸው መበቷን ነው። የሀገራችንን ፖለቲካ በጋራ አስተካክለን ሁላችንንም በእኩልነት የምታስተናግድ ዴሞክራቲክ ኢትዮጵያን ለመፍጠር እግዚአብሔር ይርዳን እላለሁ።

    ዋቢ መፃሕፍት:

    1. Bahiru Zewde (1991) A History of Modern Ethiopia, 1885 -1991.
    2. Gebru Tareke (1996) Ethiopia: Power and Protest, Peasant Revolts in the Twentieth Century.
    3. John Markakis, (2011) Ethiopia: The Last Two Frontiers.
    4. Merera Gudina, (2002) Ethiopia: Competing Ethnic Nationalisms and the Quest for Democracy, 1960-2000.
    5. Teshale Tibebu, (1995), The Making of Modern Ethiopia, 1896-1974.

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forumsላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።

    በኢትዮጵያ የሀገረ-መንግሥት ግንባታ የታሪክ ዳራ… መረራ ጉዲና (ፕሮፌሰር)

    Semonegna
    Keymaster

    በደቡብ ክልል ወላይታ ዞን የክልልነት ጥያቄ በማንሳት የሚንቀሳቀሰው የዞኑ አመራርና ሕዝብ
    በሕገ-መንግሥቱ ድንጋጌ መሠረት ተገቢ መልስ በሰላማዊ አግባብ ሊሰጠው ይገባል!
    የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ)

    ከኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) የተሰጠ መግለጫ

    የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ራስን በራስ የማስተዳደርና ክልላዊ መንግሥት የማቋቋም መብት እንዳላቸው በሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ 47(2) ላይ ተደንግጓል። ይህን ሕገ-መንግሥታዊ መብት ለማስከበር ከአስር በላይ የሆኑ የደቡብ ብሔራዊ ክልል ዞኖች፣ በየዞናቸው ምክር ቤት በማስወሰን ለክልሉ ምክር ቤት ጥያቄዎቻቸውን ማቅረባቸውንና ውሳኔ እንዲሰጣቸው በመጠየቅ ላይ መሆናቸውን ከተለያዩ ምንጮች ስንሰማ ቆይተናል።

    እስከ አሁን ጥያቄያቸውን ካቀረቡት ዞኖች መካካል በሕገ-መንግሥቱ መሠረት ሕዝበ-ውሳኔ ተካሂዶ በክልልነት የመደራጀት መብት የተከበረለት የሲዳማ ዞን ብቻ ሲሆን፥ የሌሎች ዞኖችን በተመለከተ በአሁኑ ወቅት የተለያዩ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን በቡድን /በክላስተር/cluster/ በማሰባሰብ ከአንድ በላይ በሚሆኑ ክልሎች ለማደራጀት በመንግሥት እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑ ይታወቃል። ይህ እየሆነ ባለበት ሁኔታ በመንግሥት እየተደረገ ያለውን በክላስተር የማደራጀትን አማራጭ የሚቃወሙ እንቅስቃሴዎች በአንዳንድ ዞኖች እየታዩ ናቸው። በመሆኑም ከሚመለከተው አካል ፈጣን ምላሽ አልተሰጠንም ከሚል ተስፋ መቁረጥ ተነስቶ፥ ሕዝቡ ወደ ግጭት እንዳይገባ የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ከዚህ ቀደም ባወጣው መግለጫ ሥጋቱን ገልጿል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ፥ የተፈራው ስጋት እውን ሁኖ የወላይታ ዞን አመራር የመንግሥትን የመፍትሄ አቅጣጫ በመቃወም የምክክር ስብሰባ እያደረገ ባለበት ወቅት መንግሥት በወሰደው እርምጃ በቁጥጥር ስር እንዳዋላቸው ተሰምቷል። በዚህ መነሻነትም ሕዝቡ ተቃውሞ እያሰማ እንደሆነና ከፀጥታ አስከባሪ ኃይሎች ጋር በሚፈጠሩ ግጭቾች የሰው ሕይወት እስከ መጥፋት እየደረሰ መሆኑም በእጅጉ አሳስቦናል።

    ስለሆነም፥ መንግሥት የጉዳዩን ሰፊ እንደምታ በጥልቀት በመመልከት፣ በዞኑ ለተነሳው ሕገ-መንግሥታዊ ጥያቄ ተገቢ ምላሽ በመስጠት፣ ጥያቄውን በማንገብ ምላሽ ለመሻት የተንቀሳቀሱትን የወላይታ ዞን አመራር አካላትን እና በጉዳዩ ሳቢያ የታሰሩትን ሁሉ በመፍታት፣ ለተከሰተው ችግር ሰላማዊ መፍትሄ በአስቸኳይ እንዲፈልግ ኢሶዴፓ ያሳስባል። አስተዋዩ ሰፊ የወላይታ ሕዝባችንም ጉዳዩን በወትሮ ጥበቡ በትዕግስት በመያዝ፣ የሰላማዊ መፍትሄ አካል እንዲሆን ኢሶዴፓ በአክብሮት ጥሪ ያደርጋል!!

    የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ)
    ነሐሴ 6 ቀን 2012 ዓ.ም.
    አዲስ አበባ

    *የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) በሀገራችን ኢትዮጵያ ሕዝባዊ፣ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት በመመሥረት ለመሠረታዊ ችግሮች መፍትሔ ለመስጠት ርዕዮተ-ዓለሙ ማኅበረ-ዴሞክራሲ (social democracy) ሆኖ ኢኮኖሚያዊና ማኅብራዊ ፍትህን በሀገሪቱ እውን ለማረግ የሚንቅሳቅስ ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲ ነው።

    የፖለቲካ ፓርቲዎች ድምጽ (ኢትዮጵያ ውስጥ የሚነቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች)

    የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ

Viewing 15 results - 16 through 30 (of 65 total)