-
AuthorSearch Results
-
February 3, 2021 at 2:30 am #17950
In reply to: የፖለቲካ ፓርቲዎች ድምጽ (ኢትዮጵያ ውስጥ የሚነቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች)
AnonymousInactiveየጥላቻና ዘር ፍጅት ቅስቀሳ በውጤት ደረጃ ሀገርና ሕዝብን የህልውና አደጋ ላይ ይጥላል
ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የተሰጠ መግለጫ!ድርጅታችን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ በሀገራችን ውስጥ እስካሁን የተካደው ኢትዮጵያዊ ዜግነት ተገቢውን እውቅና እንዲያገኝ፣ ዜግነት የፖለቲካችን ማዕከል እንዲሆን የሚያስችል መሠረታዊ የትርክት ለውጥና የመዋቅር ክለሳ እንዲደረግ በርካታ ጥሪዎችን ሲያደርግ ቆይቷል። ለሀገራችችን የፖለቲካ ምስቅልቅል (crisis) መነሻ የሆነው የጥላቻ ትርክት በሕገ-መንግሥትና በመዋቅሮች መስረፅ ምክንያት መሆናቸውን በመገንዘብ፥ ሕዝባችን ከባድ መስዋዕትነትን የጠየቀ የለውጥ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ቆይቷል። በዚህም ቀላል የማይባሉ እመርታዎችን ያስመዘገበ ቢሆንም፥ በዋናነት የአፋኙ ሥርዓት አካልና ወራሽ የሆነ ስብስብ የሕዝባችንን ቅን ልቦና ባጎደፈ መልኩ የጽንፈኝነት ባህሪውን ለጊዜው ደብቆና ስሙን ብቻ ቀይሮ የሕዝባችንን የለውጥ ሂደት አግቶት ይገኛል።
የአማራ ሕዝብና የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በትሕነግ ላይ የነበረው አቋም የተፈተሸ፣ የጠራና የነጠረ ስለመሆኑ አስረጅ አያስፈልገውም። አብን ከሁለት ዓመታት በፊት ትሕነግ ሽብርተኛ ድርጅት መሆኑን በመጥቀስ ከሰላማዊ የፖለቲካ ፖርቲዎች ዝርዝር እንዲሰረዝና ጉዳዩ በሕግ የበላይነት ማዕቀፍ እንዲታይ ማሳሰቡ ይታወሳል። በወቅቱ መንግሥት ከትሕነግ ጋር አብሮ በአንድ ጥምረት ውስጥ ሆኖ የሚሠራበት ነበር። አብዛኛው የሀገራችን የፖለቲካ ኃይሎች በአብን መግለጫ ቢያንስ ተደናግጠው እንደነበር የሚታወስ ሃቅ ነው።
አብን የአማራ ሕዝብ ሁለንተናዊ ንቅናቄ አካል እንደመሆኑ መጠን ዝቅተኛው የፖለቲካ ስምሪቱ ሀገራችን በጽንፈኛ ኃይሎች ቅንጅት እጅ ዳግም እንዳትወድቅ መከላከል ነው። የኮሮናቫይረስ (COVID-19) ወረርሽኝ ስጋትን ተከትሎ በሀገራዊ የምርጫ መርኃግብር ላይ በታየው የፖለቲካ ችግር ወቅት የወሰድነው አቋም አብን ኢትዮጵያን በተመለከተ ላለው የማያወላዳ አቋም ዓይነተኛ ጠቋሚ መሆኑ አያከራክርም።
ድርጅታችን አብን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግር ሊፈታ የሚችለው መሠረታዊ ለውጦችን በማድረግ እንጅ በስምና በቅብ ለውጥ ሊሆን እንደማይችል በመረዳት ሀገራችን በሽግግር መንግሥት ምሥረታ ሳይሆን በሽግግር ጊዜ ምዕራፍ ማለፍ እንዳለባት አሳውቆ ነበር። በተያያዘ ሁኔታ በሽግግር ጊዜ ውስጥ ዘላቂ እልባት ማስገኘት የሚችሉ አንኳር የለውጥ ተግባራት መፈፀም እንዳለባቸው ገልፆ ጥሪ ማስተላለፉም ይታወሳል። ነገር ግን በጥሬ የስልጣን ግብግብና በጥላቻ ባሕል የተቃኘው የሀገራችን አጠቃላይ የፖለቲካ ስምሪት ዘላቂ ተግዳሮት ሆኖ በመቀጠሉ፥ ተፈላጊው ለውጥ እውን ሊሆን ካለመቻሉም በላይ በሕዝባችን ላይ ተከታታይ የዘር ማጥፋትና የዘር ማፅዳት ጥቃቶች ተፈፅመዋል። የዜሮ ድምር የፖለቲካ ዘይቤን የቀጠለ ሲሆን በሀገራዊ መግባባትና ትብበር መሠራት ያለባቸውን ጉዳዮች በፉክክርና በጥላቻ ለመፍታት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ሊገቱ ባለመቻላቸው ምክንያት የሕዝባችን ትግል ገና ተቀናጅቶና ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተገንዝበናል።
በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያዊነትን እና የኢትዮጵያዊነትን ትሩፋቶች በብቸኝነት ለመበየንና ለማከፋፈል የቋመጡ ጽንፈኛ መንግሥታዊ አካላት ሀገራችንን ተፈትሾ በወደቀው የሴራ ፖለቲካቸው አዙሪት ውስጥ ለማቆየት ከፍተኛ ርብርብ እያደረጉ ይገኛሉ። በርካታው የሀገራችን ክፍል የደህንነት ስጋት ያንዣበበት ሲሆን፥ የሕዝብ በሰላም የመንቀሳቀስም ይሁን በሕይወት የመኖር መብት በመደበኛነት አደጋ ውስጥ ይገኛል።
አብን በዚህ ዓመት በሚካሄደው ሀገራዊ ምርጫ ለመሳተፍ ሲወስን የጥላቻና የሴራ ፖለቲካ ግንባር ቀደም ተጠቂ ድርጅት በሆነበት አግባብ ነው። የምርጫ ትርጉም በአንድ ቀን ውስጥ ተከፍቶ በሚዘጋ ሳጥን ውስጥ በሚጨመሩ ካርዶች የታጠረ እንዳልሆነም ይገነዘባል። በሀገራችን ውስጥ ያለው የቅድመ ምርጫ መደላድል ያለበት ሁኔታ ለሕዝባችን የተሰወረ አይደለም። በተለይም የአማራን ሕዝብ ማገት የፖለቲካ ስልት ሆኖ የቀጠለ እውነታ ነው፤ አብን የአማራ ሕዝብ ሀቀኛና የማያወላዳ እንዲሁም ጸረ-ጭቆናና ጸረ-ዘረኝነት የትግል እንቅስቃሴ በቀጥታ የወለደው ድርጅት በመሆኑ አማራን የሚፈርጁና የሚያጠቁ ጽንፈኞች ዓይናቸውን ለአፍታ እንኳን ዘወር እንደማያደርጉለት ይታወቃል።
ከአማራ ክልል ውጭ በተለይም በኦሮሚያና በቤኒሻንጎል ክልል ውስጥ ባሉት የአብን መዋቅሮችና አመራሮች ላይ የተለያዩ ጥቃቶች ሲፈፀሙም ቆይተዋል፤ አሁንም ቀጥለዋል። በተለይም የክልሎቹ ባለስልጣናት በሆኑ የብልፅግና ፖርቲ አባላት የሚፈፀሙ ችግሮች መሆናቸውን መነሻ በማድረግ፥ ከፖርቲው ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመነጋገር ለመፍታት ጥረት ሲያደርግ ቆይቶ ባለመሳካቱ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማመልከቻ አቅርቦ በምርመራ ላይ ይገኛል።
ጉዳዮቹ በዚህ አግባብ በሚገኙበት ሁኔታ ጭምር “የኦሮሞ ብልፅግና” ከፍተኛ አመራሮች በማኅበራዊ ድረ-ገፅ በአብን፣ በአመራሮቻችን፣ አባላቶቻችን፣ ደጋፊዎቻችን እና በአጠቃላይ በአማራ ሕዝብ ድርጅቶችና አመራሮች ላይ የሀሰት፣ የአፍራሽና የጥቃት ጥሪዎችን በተደጋጋሚ እያስተላለፉ ይገኛሉ። የብልፅግና ፖርቲ እንደተቋም በሚፈፀሙ ጥሰቶች ላይ ምንም ዓይነት ተጨባጭ እርምት ለማድረግ ባለመፈለግ በቀጥታ የተቀበላቸውና የአማራን ሕዝብ በተመለከተ ያለውን አቋም በምግባር፣ በድርጊትና በቸልታ አረጋግጧል።
ጥር 25 ቀንም በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች በተደረጉ ሰልፎች በዋናነት አብንን የሚያጠለሹና የሚያወግዙ እንዲሁም በሕዝባችን ላይ ቀጣይ ስጋትን የጋረጡ ድምፆች ከፍ ብለው ሲስተጋቡ ተሰምተዋል። አብንን “ከኦነግ ሸኔ” ጋር የሚያመሳስሉ መፍክሮች ተሰምተዋል።
ስለሆነም፦
1/ በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ እየተፈፀመ ያለውን ገደብ የለሽ የፖለቲካ ነውረኝነትና የዘረኝነት እንቅስቃሴ ለመቃወም በባልደራስ ፓርቲ ተጠርቶ የነበረውን ሕዝባዊ ሰልፍ በማንአለብኝነት የከለከለ መንግሥት ለፖርቲ ፍጆታ ሲሆን ሰልፍ መጥራቱና መፍቀዱ፤
2/ በሰልፉ ላይ (ጥር 25 ቀን 2013 ዓ.ም. የተደረገው የብልፅግና ፓርቲ ሰልፍ) የጥላቻና የጥቃት ጥሪዎችን ሲመሩ የነበሩት በስምና በኃላፊነት የሚታወቁ የመንግሥትና የብልፅግና ፖርቲ አመራሮች መሆናቸው፤
3/ ጥር 25 ቀን 2013 ዓ.ም. በተደረገው የብልፅግና ፓርቲ ሰልፍ ላይ ጎልተው የተሰሙት ድምፆች የክልሉ አመራሮች በማኅበራዊ ድህረ-ገጽ ሲፅፏቸው የነበሩ ኃሳቦች ቀጥተኛ ግልባጭ መሆናቸው፤
4/ በዚህም በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በአጠቃላይ ያለውን የፖለቲካ አፈና ወደተሟላ እርከን ለማሸጋገር በማሰብ አብን በክልሉ ውስጥ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ለመግታትና በክልሉ የሚኖረውን የአማራ ሕዝብና ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ በጭቆና ቀንበር ስር የማቆየት ዓላማ ያነገበ ተግባር መሆኑ፤
5/ በተለይም ጥር 25 ቀን 2013 ዓ.ም. በተደረገው የብልፅግና ፓርቲ ሰልፍ ላይ በአማራ ሕዝብ ላይ በተደጋጋሚ የዘር ፍጅት ለመፈፀም ጽንፈኛ ኃይሎች መንደርደሪያ አድርገው የሚጠቀሙበት “ነፍጠኛ” የሚለው ቃል በሰፊው ሲገለፅ የነበረና በግልፅም “ነፍጠኛ ይውጣ” የሚል ሀሳብ ሲሰማ የነበረ መሆኑ፣
6/ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ ኃላፊነት የጎደላቸው ጽንፈኛ አመራሮች በአማራ ሕዝብ ላይ እየደረሰ ላለው ጥቃት ሽፋን በመስጠትና በቀጥታ በመሳተፍ እንደሚያስፈፅሙ የተረጋገጠ ጉዳይ ሆኖ እያለ፥ በታየው ደረጃ የተላለፈውን የጥላቻና የጥቃት ጥሪ የመንግሥት ሚዲያዎች መዘገባቸው እና የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትርም እርምት መስጠት እየተገባቸው፥ ‘ቡራኬ’ መስጠታቸው እጅግ አሳዛኝ የሆነና በቀጣዩ የሀገራችን የፖለቲካ ሂደት ላይም ከፍተኛ ስጋትን እንደሚፈጥር መረዳት ይቻላል።
በአጠቃላይ የሀገራችንን የፖለቲካ እንቅስቃሴ የተለየ ፖለቲካዊ እይታ የማስተናገድ ዝንባሌና ቀጣዩን ምርጫ በተመለከተ በመንግሥት በኩል እየታየ ያለው አቋምና አፍራሽ እንቅስቃሴ በአስቸኳይ እንዲቆም እየጠየቅን፥ የአብን የብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ጉዳዩን በቀጥታ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድና በግልባጭ ለሚመለከታቸው አካላት በደብዳቤ አሳውቋል።
በመጨረሻም መላው ኢትዮጵያውያን፥ በተለይም የአማራ ሕዝብ፥ የብልፅግና ፓርቲ ሰልፍ ላይ የተስተጋባው የጥላቻና ዘር ፍጅት ቅስቀሳ በውጤት ደረጃ ሀገርና ሕዝብን ለህልውና አደጋ የሚጥል መሆኑን በመረዳት የተፈፀመውን አስነዋሪ ድርጊት በጽኑ እንዲያወግዝና አብን ከሚያደርጋቸው የፍትህ፣ እኩልነትና ነፃነት ትግሎች ጎን እንዲሰለፍ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
የሴራ ፖለቲካ ምዕራፍ የሚዘጋበት፣ የጥላቻና የፍረጃ ፖለቲካ ላንቃ የሚዘጋበት ጊዜው አሁን ነው!
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)
ጥር 25 ቀን 2013 ዓ.ም.
አዲስ አበባ፤ ሸዋ፤ ኢትዮጵያ!January 20, 2021 at 2:55 am #17545AnonymousInactiveከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰጠ መግለጫ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለ6ተኛው ሀገራዊ ምርጫ የሚያደርገውን ዝግጅት አስመልክቶ የጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱ፥ እንዲሁም የተለያዩ ተግባራትን ለማከናውን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ እየሠራ እንደሚገኝ ይታወቃል። ከዚህም መካከል የምርጫ ጸጥታን ማረጋገጥ እንዲሁም የምርጫ ክልል እና የዞን ቢሮዎችን ለመክፈት መሥራት ይገኙበታል። በዚህም መሠረት ቦርዱ በተለያዩ ወቅቶች ከክልል መስተዳድር ኃላፊዎች ጋር ውይይቶችን ያከናወነ ሲሆን፥ በእነዚህ ውይይቶች ላይ የምርጫ ኦፕሬሽን መዋቅር እና የክልል መስተዳድሮች የሚጠበቁ ሚናዎችን በዝርዝር አቅርቧል። በውይይቶቹ በተደረሰው ስምምነት መሠረት ቦርዱ የሚከተሉትን ዋና ዋና ትብብሮች ከክልል መንግሥታት የጠየቀ ሲሆን እነሱም በዋናነት፦
- የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር – 33 የምርጫ ክልል ቢሮዎች እና 3 የዞን ማስተባበሪያ ቢሮዎች እና የስልጠና ቦታዎች
- የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብሔራዊ ክልል መንግሥት – 22 የምርጫ ክልል ቢሮዎች እና 3 የዞን ማስተባበሪያ ቢሮዎች እና የስልጠና ቦታዎች
- ድሬደዋ ከተማ መስተዳድር – 47 የምርጫ ክልል ቢሮዎች እና 1 የዞን ማስተባበሪያ ቢሮዎች እና የስልጠና ቦታዎች
- ሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት –72 የምርጫ ክልል ቢሮዎች እና 11 የዞን ማስተባበሪያ ቢሮዎች እና የስልጠና ቦታዎች
- ጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት – 14 የምርጫ ክልል ቢሮዎች እና 3 የዞን ማስተባበሪያ ቢሮዎች እና የስልጠና ቦታዎች
- ደ/ብ/ብ/ህ ክልላዊ መንግሥት – 113 የምርጫ ክልል ቢሮዎች እና 16 የዞን ማስተባበሪያ ቢሮዎች እና የስልጠና ቦታዎች
- ሃረሪ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት – 3 የምርጫ ክልል ቢሮዎች እና 1 የዞን ማስተባበሪያ ቢሮዎች እና የስልጠና ቦታዎች
- አፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት –32 የምርጫ ክልል ቢሮዎች እና 5 የዞን ማስተባበሪያ ቢሮዎች እና የስልጠና ቦታዎች
- አማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት – 138 የምርጫ ክልል ቢሮዎች እና 12 የዞን ማስተባበሪያ ቢሮዎች እና የስልጠና ቦታዎች
- ሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት –19 የምርጫ ክልል ቢሮዎች እና 1 ዞን ማስተባበሪያ ቢሮ እና የስልጠና ቦታዎች
- ኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት – 179 የምርጫ ክልል ቢሮዎች እና 20 የዞን ማስተባበሪያ ቢሮዎች እና የስልጠና ቦታዎች
ናቸው። ቦርዱም በጥያቄው ለክልሎች ለዕቅድ እና ለአፈፃፀም ያመቻቸው ዘንድ የምርጫ ክልሎች ዝርዝር እና ቢሯቸው የሚቋቋምባቸው ከተሞች ዝርዝር፣ የዞን ማስተባበሪዎች ዝርዝር እና ቢሯቸው የሚቋቋምባቸው ከተሞች ዝርዝር እንዲሁም ቦርዱ ያወጣውን ረቂቅ የምርጫ ሰሌዳ ቅጂ (copy) አብሮ አቅርቧል።
ይሁንና ለክልሎች ይህንኑ ለቢሮ መከፈት የሚያስፈልግ ዝግጅት በደብዳቤ በመጠየቅ ለጥር 10 ቀን 2013 ዓ.ም. እንዲያሳውቁ ጥያቄ ያቀረበ ቢሆንም፥ እስከአሁን ድረስ ይህንን ዝግጅት አስመልክቶ ምላሽ ያቀረበ የክልል መስተዳድር የለም። በመሆኑም በደብዳቤ የተገለጹት አስፈላጊ የምርጫ ክልል ቢሮዎችን ለመክፈት የሚያስፈልጉ ትብብሮች ለምርጫው ሂደት አስፈላጊነታቸውን በመገንዘብ ክልሎች ትብብራቸውን እንዲፋጥኑ እንዲሁም በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ 1162/2011 አንቀጽ 161 የተቀመጠውን የመተባበር ግዴታቸውን እንዲወጡ እናሳስባለን።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
ጥር 10 ቀን 2013 ዓ.ም.January 2, 2021 at 12:56 am #17232In reply to: የሰብዓዊ መብቶች እና ተያያዥ ጉዳዮች ― ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
AnonymousInactiveየኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) መግለጫ
ኦሮሚያ ክልል ― የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል ተከስቷል፤ አጥፊዎቹ ሕግ ፊት መቅረብ አለባቸውየኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል ልዩ ልዩ አካባቢዎች በተከሰተ የፀጥታ መደፍረስ የተሳተፉ ሰዎችና ቡድኖች በሲቪል ሰዎች ላይ ያደረሷቸው ጥቃቶች በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል ባህርያትን የሚያሟሉ መሆናቸውን በምርመራ ሪፖርቱ አመለከተ።
ኢሰመኮ ከሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ በነበሩ ሦስት ተከታታይ ቀናት በኦሮሚያ ክልል የተከሰተውን የፀጥታ መደፍረስና የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት የባለሙያ ቡድኖቹን ወደ 40 የክልሉ አካባቢዎች የላከ ሲሆን፥ የምርመራውን ግኝቶች ታኅሣሥ 23 ቀን 2013 ዓ.ም. ይፋ አድርጓል።
በ59 ገጽ ሪፖርቱ እንደተመለከተው፥ በዚህ መጠነ ሰፊ ጥቃት የተሳተፉት ብዙ ቁጥር ያላቸው እና ከቦታ ቦታ በቡድን ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሰዎች ሲሆኑ፤ በጩቤ፣ በድንጋይ፣ በእሳት፣ በኤሌክትሪክ ገመድ፣ በዱላ፣ በዶማ፣ በገጀራ እና በመጥረቢያ ተጠቅመው ሰዎችን ደብድበዋል፤ የአካል ጉዳት አድርሰዋል፤ ፍጹም ግፍና ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ በማሰቃየት እና በማረድ ጭምር ሰዎችን ገድለዋል። በጥቃቶቹ የ123 ሰዎች ሕይወት አልፏል፤ 500 ሰዎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተፈናቅለዋል።
በአብዛኛው በቡድን የተደራጁ ሰዎች ከቦታ ቦታ እየተንቀሳቀሱ፣ በብሔርና በሀይማኖታቸው ተለይተው የተመረጡ ሲቪል ሰዎችን፣ ቢያንስ በ40 የተለያዩ ቦታዎች በተስፋፋና ለሦስት ቀናት በቆየ ሁከት ማጥቃታቸው፣ በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል እንደሚያደርገው የኮሚሽኑ ግኝቶች ያመላክታሉ።
ምንም እንኳን የፀጥታ ኃይሉ በየቦታው የገጠመውን መጠነ ሰፊ የፀጥታ መደፍረስ ችግር እና የፀጥታ አባሎቹንም የሕይወት መስዋዕትነት በሚጠይቅ ሁኔታ በመሰማራታቸው ኃላፊነታቸው እጅግ ፈታኝ የነበረ መሆኑን መገንዘብ ቢቻልም፤ በተወሰኑ ቦታዎች የኃይል አጠቃቀም ተመጣጣኝነት ከፍተኛ ጥያቄ የሚያስነሳ መሆኑን ሪፖርቱ አክሎ ገልጿል። በአንዳንድ አካባቢዎች የፀጥታ ኃይሉ በወሰደው ያልተመጣጠነ እርምጃ፥ ሰልፍ ውስጥ ያልነበሩ፥ በመንገድ ወይም በቤታቸው በር ላይ የተገደሉ፣ ለማሸማገል ጣልቃ የገቡ የአገር ሽማግሌዎችን እና የአዕምሮ ህመምተኛ ጭምር እንዲሞቱ ምክንያት ሆኗል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ‘በኢትዮጵያ የሚታየው የግፍና የጭካኔ ወንጀሎች መደጋገም፣ የችግሩን ስር መሠረት ለመፍታት የሚያስችል የተሟላ ብሔራዊ የግፍና ጭካኔ ወንጀል መከላከያ ስትራቴጂ ነድፎ በአፋጣኝ በሥራ ላይ ማዋል እንደሚገባ የሚያሳይ መሆኑን’ ገልጸዋል።
ሙሉ ሪፖርቱ “መንግስት ያለ አይመስልም ነበር፡ የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በተከሰተው የፀጥታ መደፍረስ ምክንያት የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ምርመራ ሪፖርት” በሚል ርዕስ እዚህ ጋር በመጫን ያገኙታል።
December 26, 2020 at 3:11 am #17118In reply to: የፖለቲካ ፓርቲዎች ድምጽ (ኢትዮጵያ ውስጥ የሚነቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች)
AnonymousInactiveኦህዴድ/ ብልጽግና አዲስ አበባን የኦሮሞ ንብረት ለማድረግ የጀመረውን ዘመቻ ያቁም!
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲኦህዴድ/ ብልጽግና ቤተ-መንግሥት ከገባ ጀምሮ የመላ ኢትዮጵያውያን ብሎም የአፍሪካ መዲና የሆነችውን አዲስ አበባን በኦሮማዊነት መንፈስ ለመቆጣጠር እንቅስቃሴዎችን እያደረገ ይገኛል።
ከሰሞኑ ከተማዋን የኦሮሞ ብቻ መዲና ለማድረግ እና ኦሮማዊ ሥነ-ልቦናን ለማላበስ ኦሕዴድ/ ብልጽግና የሕንፃዎች ግንባታ ዘመቻን ጀምሯል። የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በ1.8 ቢሊዮን ብር ወጭ የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሕንፃን፣ በ1.5 ቢሊዮን ብር ወጭ የኦሮሚያ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት ሕንፃን፣ በአንድ ቢሊዮን ብር የኦሮሞ ታጋዮች ፋውንዴሽን ሕንፃን እንዲሁም በሰባት መቶ ሚሊዮን ብር ወጭ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ሕንፃን በአዲስ አበባ ለመገንባት ሥራዎች ጀምሯል። ይህ እንቅስቃሴ ህወሓት ሲያደርግ እንደ ነበርው የሕዝብ ሀብት እየተዘረፈ ለነገድ የፖለቲካ ድርጅቶች እና ለሚመሯቸው የፖለቲካ ኤሊቶች ጥቅም ማስገኛ እንደሚሆን ሳይታለም የተፈታ እውነታ ነው። በሕገ-መንግሥቱ የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማ አዲስ አበባ እንደሆነች ባልተፈቀደበት ሁኔታ ይህ የተወሰደው እርምጃ አዲስ አበባን በኦሮሞ ሥነ-ልቦና ለመሥራት በሚል ሽፋን የኦሮሞ የነገድ ፓለቲካ ኤሊቶች ጥቅም ማጋበሻ እንዲሆኑ የታለሙ መሆናቸውን ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) ያምናል። ይህም በ16 እና በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመናት ተቋርጦ የነበረውን የገዳ ሥርዓት ወረራ ለማስቀጠል እየተደረገ ያለ እንቅስቃሴም አካል ነው።
አቶ ሽመልስ አብዲሳ እንዳሉት ይህ ወረራ አዲስ አበባን ሙሉ በሙሉ ለመዋጥ ወይም ለማጥፋት ያለመ ነው። ‹በረራ› በመባል ትታወቅ የነበረችው ጥንታዊቷ አዲስ አበባ ዳግማዊ ምኒልክ እንደ ገና የዛሬዋን አዲስ አበባ እስከቆረቆሩበት ጊዜ ድረስ ፈርሳ የቆየችው በገዳ ወረራ እንደሆነ ታሪክ ያስረዳል። በ16ኛው እና በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመናት በተካሄደው የገዳ ሥርዓት ወረራ ከ28 በላይ ነባር የኢትዮጵያ ነገዶች መጥፋታቸው በታሪክ የተመዘገበ ነው።
በመሆኑም በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚኖሩ ከመላ ኢትዮጵያ የተሰበሰቡ ነዋሪዎች ከሚገብሩት ግብር ለክልሎች ፈሰስ ከሚደረገው ድጎማ የኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናት ለነገድ የፖለቲካ ማራመጃነት እና ለግል ጥቅም ማካበቻ በማን አለብኝነት የሚያባክኑት የሀገር ሀብት ተጠያቂ የሚሆኑበት ሥርዓት እንዲፈጠር መላው የከተማዋ ነዋሪ በሰላማዊ ትግል አድሏዊ ከሆነ የኪራይ ሰብሳቢ አካሄድ እንቅስቃሴያቸው እንዲታቀቡ ባልደራስ በአፅንኦት ያሳስባል።
ታኅሣሥ 14 ቀን 2013 ዓ.ም.
አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ
ድል ለዲሞክራሲ!
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲDecember 25, 2020 at 4:20 pm #17110In reply to: የፖለቲካ ፓርቲዎች ድምጽ (ኢትዮጵያ ውስጥ የሚነቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች)
AnonymousInactiveበመተከል በአማራ ሕዝብ ላይ የቀጠለውን የዘር ፍጅት አስመልክቶ ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የተሰጠ መግለጫ
የአማራ ሕዝብ እና ሀገራችን ከገጠሟቸው ፈተናዎች ለመውጣት ዘላቂው መፍትሄ ሁሉንም ሕዝብ እና አካላት ባለቤት የሚያደርግ፣ ሀገራዊ መከራንም በጋራ መቀልበስ የሚያስችል ሥርዓትና ስሪት ማቆም መሆኑን ሳናሰልስ ተናግረናል፤ አስገንዝበናል፤ ወትውተናል።
የፍትህና እኩልነት ሥርዓት ስለማቆም ሳያሰልሱ መወትወትና መታገሉ በመሠረታዊነት አንዳችም ስህተት የሌለበት ቢሆንም ሀገራዊ ፕሮጀክቱ አማራውን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት ከሚሠሩ የጥላቻ ኃይሎች ጋር በመሆን ማሳካት እንደማይቻል ግለፅ እየሆነ የመጣ እውነታ ሆኗል።
ሁሉን አቀፍ በጎ ውጥኖች በተግባር እስኪተረጎሙና የጥፋት ኃይሎችም ልቦና ገዝተው በባለቤትነት ስሜት ጭምር የየራሳቸውን አዎንታዊ አበርክቶ መወጣት ሊጀምሩ ይችላሉ ከሚለው እሳቤ በፊት የሕዝባችን ህልውና የሚቀድም መሆኑን በመረዳት አሳዳጅና ገዳዮቻችን ክላሽ፣ ሜንጫና ቀስታቸውን ጥለው እስኪመጡ ድረስ ለሽግግር የሚሆን የተቀናጀ እርምጃ እንዲወሰድ ዛሬም ለማሳሰብ እንወዳለን።
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የመላው አማራ ሕዝብ ወኪል መሆኑን ማረጋገጥ ያለበት ወቅት መሆኑን በመረዳት በትሕነግ ላይ የወሰደውን ዓይነት ህልውናን የማስከበር ታሪካዊ ቁርጥ ውሳኔ በማሳለፍ በመተከል እየተፈፀመ ያለውን የዘር ፍጅት ለማስቆም ተግባራዊ ምላሽ ሊሰጥ ይገባል። በዚህ ረገድ አብን ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ለማድረግ ያለንን ቁርጠኝነትም መግለጽ እንወዳለን።
የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግሥት በዜጎቻችን ላይ ለሚፈፀመው ጭፍጨፋ ቀዳሚ ተጠያቂ ከመሆኑም በላይ በጭፍጨፋው የተሳተፉ ከክልል እስከ ቀበሌ የሚገኙ አመራሮችን በቸልታ በማለፍ የጥቃቱ ተባባሪ ሆኖ ይገኛል።
የፌደራል መንግሥትም ኦሮሚያንና ቤንሻንጉል ጉሙዝን ጨምሮ በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈፀመውን ሰፊ የዘር ማጥፋት ወንጀል ማስቆም ካለመቻሉም በላይ ወንጀሉን በስሙ ባለመጥራት በዜጎቻችን ላይ ለሚፈፀመው ጅምላ ፍጅት ተባባሪ በመሆኑ ከተጠያቂነት እያመልጥም።
በአማራ ሕዝብ ላይ እየተፈፀመ ያለውን የማያባራ የዘር ፍጅት መላው ኢትዮጵያውያን እንድታወግዙና የአማራ ሕዝብ ህልውናውን ለማስቀጠል ከሚያደርገው ትግል ጎን እንድትቆሙም ንቅናቄያችን በአክብሮት ይጠይቃል። ንቅናቄያችን በመተከል በአማራ ወገኖቻችን ላይ የሚፈፀመውን የማያባራ የዘር ፍጅት በጽኑ እያወገዘ፤ ለዘር ፍጅት ሰለባ ቤተሰቦችና ለመላው የአማራ ሕዝብም መጽናናትን ይመኛል።
አንድ አማራ ለሁሉም አማራ፥ ሁሉም አማራ ለአንድ አማራ!
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)
ታኅሣሥ 15 ቀን 2013 ዓ.ም
አዲስ አበባ፣ ሸዋ፥ ኢትዮጵያ!November 17, 2020 at 2:16 am #16724In reply to: የሰብዓዊ መብቶች እና ተያያዥ ጉዳዮች ― ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
AnonymousInactiveየኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጋዜጣዊ መግለጫ
ኦሮሚያ ክልል፡ የዋስትና መብትን በተቀላጠፈ መንገድ ስለማረጋገጥየኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበታ ልዩ ችሎት ለአራት ወራት ያህል በእስር በቆዩት በአቶ ለሚ ቤኛ እና በአቶ ዳዊት አብደታ ጉዳይ የዋስትና መብታቸውን በማረጋገጥ የሰጠውን ትክክለኛ ውሳኔ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እውቅና እየሰጠ፣ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ሥራ አስፈጻሚና የፍትሕ አካላት በተመሳሳይ መልኩ የሌሎችንም ተጠርጣሪዎች የዋስትና መብት መከበሩን እንዲያረጋግጡ ጥሪ ያቀርባል።
ኢሰመኮ መስከረም 12 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፥ በፍርድ ቤት የዋስትና መብት ተፈቅዶላቸውና የዋስትና ሁኔታውን አሟልተው ከእስር እንዲለቀቁ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ የሰጠላቸው ሰዎች በእስር እንዲቆዩ መደረጉ ፍትህን የሚያጓድልና ሰብአዊ መብቶችን የሚጥስ ተግባር መሆኑን በመግለጽ፥ በፍርድ ቤት የዋስትና መብት ተከብሮላቸዉ በእስር ላይ የነበሩ ሰዎች በአስቸኳይ ከእስር እንዲፈቱ ማሳሰቡ ይታወሳል።
በዚሁ መሠረት ኮሚሽኑ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ፖሊስ ጣቢያዎች በእስር ስለሚገኙ ሰዎች ሁኔታ ሊወሰድ የሚገባውን እርምጃ ለሚመለከታቸው የክልሉ ኃላፊዎች በማሳወቅ ክትትሉን የቀጠለ ሲሆን፤ በተለያዩ ቦታዎች አበረታች አርምጃዎች የተወሰዱ ቢሆንም አሁንም ድረስ በተለይ የዋስትና መብት ተፈቅዶላቸው በእስር የሚገኙ ሰዎች አሉ። ከእነዚህ መካከል የአቶ ልደቱ አያሌው እና የዶ/ር ሁሴን ከድር ጉዳይ አፋጣኝ እልባት የሚሻ መሆኑን ኮሚሽኑ ያሳስባል።
ከሐምሌ 18 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ በቢሾፍቱ ከተማ በእስር ላይ ለሚገኙት አቶ ልደቱ አያሌው ፍርድ ቤት በዋስትና እንዲፈቱ ተደጋጋሚ ትዕዛዝ ቢሰጥም፤ ውሳኔው ተግባራዊ ሳይሆን ቀርቶ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተጨማሪ ክስ የተመሠረተባቸው ሲሆን፤ አሁንም በድጋሚ ያቀረቡት የዋስትና መብት ጥያቄ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለኅዳር 18 ቀን 2013 ዓ.ም. ቀጠሮ መሰጠቱ ይታወቃል። በኢሰመኮ ምርመራ መሠረት በአቶ ልደቱ ላይ የቀረቡት ክሶች የዋስትና መብት የማያስከለክሉ ከመሆኑም በተጨማሪ፣ ኢሰመኮ የተመለከተው የጤንነታቸው ሁኔታ ማስረጃዎች የዋስትና መብት ጥያቄውን በአፋጣኝ ተግባራዊ ማድረግን አስፈላጊነት ያስረዳል። ስለሆነም የአቶ ልደቱ አያሌው የዋስትና መብት በአስቸኳይ ሊፈቀድ የሚገባ ነው።
በሌላ በኩል ከሐምሌ 4 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ በእስር ላይ የሚገኙት ዶ/ር ሁሴን ከድር የአጋርፋ ወረዳ ፍርድ ቤት ጥቅምት 11 ቀን 2013 ዓ.ም. የዋስትና መብት ፈቅዶላቸዉ ከእስር እንዲለቀቁ ትዕዛዝ ከመስጠቱም በተጨማሪ፥ የፌደራል ዐቃቤ ሕግ ጥቅምት 13 ቀን 2013 ዓ.ም. ከፖሊስ በቀረበለት የተጠርጣሪው የምርመራ መዝገብ ላይ በሰጠው ውሳኔ ክስ ለማቅረብ የሚያበቃ ማስረጃ አለማግኘቱን ጠቅሶ የምርመራ መዝገቡን ዘግቷል። ይሁንና ውሳኔው ተግባራዊ ሳይሆን ቀርቶ ፖሊስ ለኮሚሽኑ እንዳሳወቀው በተጨማሪ ወንጀል በመጠርጠራቸው አሁንም በእስር ላይ ናቸው፡፡ ዶ/ር ሁሴን ከድር አብዛኛውን የእስር ጊዜ የቆዩት በአጋርፋ እስር ቤት ሲሆን፤ ጥቅምት 27 ቀን 2013 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ ከተማ ተወስደው አሁንም በኦሮሚያ ፖሊስ ቁጥጥር ስር እንደሚገኙ ኢሰመኮ የተረዳ ቢሆንም፤ ወደ አዲስ አበባ ከመጡ ወዲህ ከቤተሰቦቻቸው አለመገናኘታቸው ኮሚሽኑን አሳስቦታል። ስለሆነም ዶ/ር ሁሴን ከድር በአስቸኳይ በቤተሰባቸው ሊጎበኙ የሚገባ ከመሆኑም በተጨማሪ፤ ሊያስከስስ የሚችል አሳማኝ ክስ ካለ በአፋጣኝ ሊቀርብ፣ አሊያም ከእስር ሊለቀቁ ወይም የዋስትና መብታቸው በአስቸኳይ ሊከበር ይገባል። የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ እንደገለጹት “የዋስትና መብት በሕገ መንግሥቱና ኢትዮጵያ በተቀበለቻቸው የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች የተረጋገጠ መሠረታዊ መብት እንደመሆኑ፥ በሕግ በግልጽ ከተመለከቱ ሁኔታዎች በስተቀር የዋስትና መብት በተቀላጠፈ አሠራር ተግባራዊ ሊደረግ የሚገባው ነው።” አክለውም “በዚህ ረገድ ፍርድ ቤቶች የተከሳሾችን የዋስትና መብት የሚያረጋግጡ ውሳኔዎችን እየወሰኑ መሆናቸው የሚበረታታ ተግባር ነው” ብለዋል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን
November 7, 2020 at 1:18 am #16662In reply to: ከመንግሥታዊ ተቋማት የሚወጡ ሰሞነኛ ዜናዎችና መግለጫዎች
SemonegnaKeymasterበወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ዙሪያ ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ
አዲስአበባ
ጥቅምት 27 ቀን 2013 ዓ.ምበሀገር አቀፍ ደረጃ የተደረገውን ለውጥ ተከትሎ መንግሥት ባደረገላቸው ጥሪ መሠረት የተለያዩ የፖለካ አካላት ወደ ሀገር መግባታቸው፣ በተሰማሩበት ቦታ ሁሉ ችግሮች እንዳያጋጥማቸውና ደህንነታቸውን በመጠበቅና የፈለጉትን ሀሳብ እንዲገልጹ በቂ ክትትል ሲደረግላቸው መቆየቱን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄነራል እንዳሻው ጣሰው በመግለጫቸው አስታውሰዋል።
በፌደራልና በክልል የሚገኙ የፖለቲካ እስረኞች መንግሥት ባደረገላቸው ምኅረትና ይቅርታ እንዲፈቱ መደረጋቸውን እንደ ትልቅ ሥራ መወሰድ አለበት ያሉት ኮሚሽነር ጄነራሉ፥ ሚዲያዎችም የተለያየ ሀሳብ ለሕብረተሰቡ ተደራሽ እንዲያደርጉና ከሕብረተሰቡ የሚነሱ ጉዳዮችን ለመንግሥት እንዲያደርሱ ነፃነታቸውን በመጠበቅ በኩል በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን ተናግረዋል።
ከሕዳሴ ግድብ ጀምሮ በመላ ሀገሪቱ ተቀዛቅዞ የነበረ የትላልቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ በተጠናከረ መልኩ እንዲቀጥልና የተጀመረ የልማት ሥራ እንዲቋጭ የተለያዩ ሥራዎች ተሠርተዋል ያሉት ኮሚሽነር ጄነራሉ፥ በፖሊስ፣ በሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ በብሔራዊ መረጃና ደህንነትና በሌሎች የጸጥታ አካላት የተከናወኑ ሰፋፊ የሪፎርም ሥራዎችን በበጎ የሚወሰዱ ተግባራት መሆናቸውን ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ግን በሰላማዊ መንገድ ጥሪ ከተደረገላቸው አካላት መካከል ሰላማዊ መንገዱን በመተው ወደ ትጥቅ ትግል የገቡ አካላት እንዳሉ የገለጹት ኮሚሽነር ጄነራሉ፥ በተለይ የኦኔግ ሸኔ ቡድን በምዕራብ ወለጋና በሌሎች አካባቢዎች እንቅስቃሴ በማድረግ ሕብረተሰቡን በመግደል፣ በማገት፣ ንብረት በማውደምና ሌሎች የተለያዩ ሕገ-ወጥ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን ጠቁመዋል።
በተማሪዎች ጠለፋ ላይም በመሰማራት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ በደቡብ ክልል ጉራ ፈርዳና በቅርቡ ደግሞ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ አካባቢ የኦኔግ ሸኔ አባላትና ህወሓት በተቀናጀ መንገድ የሕዝብ ግዲያ በመፈጸም የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውኑ እንደነበር ለማየት ተችሏል ብለዋል ኮሚሽነር ጄነራሉ።
ኮሚሽነር ጄነራሉ አያይዘውም የህወሓት ጽንፈኛው ኃይል ከእነዚህ ከፍተኛ ጥፋቶች ኋላ ተሰማርቶ ሲሠራ እንደነበረ በተለያዩ ጊዜ ባደረግናቸው ምርመራዎች ለማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል።
የህወሓት ጽንፈኛ ኃይል ከፌደራል መንግሥት ጋር ለመሥራት ያለመፈለግ፣ ሕገ-ወጥ ምርጫ ማከናወን፣ የሠራዊት አባላትን ለውጊያ በሚመጥን መንገድ ማዘጋጀት፣ የፌደራል መንግሥትን ሕገ-ወጥ ነው በማለት ባገኘው ሚዲያ በሙሉ ማሰራጨትና ሌሎች ለጸጥታ ሥራ ስጋት የሆኑ ጉዳዮችን ሲያከናውን መቆየቱንም ኮሚሽነር ጄነራሉ ገልጸዋል።
በአጠቃላይ የህወሓት ጽንፈኛ ቡድንና የኦኔግ ሸኔ ታጣቂው ኃይል በተደራጀ መንገድ ከውጭና ከሀገር ውስጥ የሚደረግላቸውን የፋይናንስ ድጋፍ በመጠቀም ለሁለት ዓመታት የተለያዩ የሀገሪቱን ክፍል ሲያተራምሱ መቆየታቸውን ለማረጋገጥ እንደተቻለም ኮሚሽነር ጄነራል እንዳሻው ተናግረዋል።
በሁሉም አካባቢ የተፈጸሙ የጸጥታ ችግሮች ሲያደራጁና ሲመሩ የነበሩ መሆናቸውን ምርመራዎቻችንና የተለያዩ መረጃዎቻችን አረጋግጧል ያሉት ኮሚሽነር ጄነራሉ፥ የተለያዩ ፍንዳታዎችን በመፈጸም፣ የግድያ ሙከራዎችን ማከናወን፣ ንብረት ማውደም፣ ሕዝብን ከሕዝብ ማጋጨትና በቤተ-እምነቶች መካከል ግጭት እንዲፈጠር ለማድረግ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እንደነበራቸውም ኮሚሽነር ጄነራሉ በመግለጫቸው ጠቁመዋል።
አሁንም በትግራይ ክልል ጦርነት ከፍተው ባሉበት ወቅት በሀገራችን የተለያዩ ክፍሎችና ትላልቅ ከተሞች ላይ ጥቃት ለማድረስ ያሰማሩት ኃይል እንዳለ ተደርሶበታል ያሉት ኮሚሽነር ጄነራሉ፥ ይሄ ኃይል ፖሊስና ሌሎች የጸጥታ አካላት ባደረጉት ስምሪት ግማሹ የተያዘ ሲሆን ግማሹ ደግሞ በቅርብ ቀን ከተደበቀበት በማውጣት በቁጥጥር ስር የማዋል ሥራ በተጠናከረ መልኩ እንደሚከናወን ተነግሯል።
የፌደራል ፖሊስ ባለው ሕገ-መንግሥታዊ ተልዕኮ መሠረት በሀገሪቱ በሁሉም አካባቢ በመሰማራት የሕብረተሰቡን ሰላምና ጸጥታን የሚጠብቅ ኃይል መሆኑን በመግለጽ በትግራይ ክልልም በ22 ትልልቅ ተቋማት ላይ በመሰማራት አገልግሎት ሲሰጥ የነበረ ተቋም ነው ብለዋል።
የፌደራል ፖሊስ አባላት ኤርፖርቶችን፣ ዲፖዎችን፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ጣቢያዎችን፣ ቴሌኮምን፣ ቤተ መንግሥትን፣ ትላልቅ ግድቦችንና ኬላዎችን ጨምሮ ሌሎች የሕዝብና የመንግሥት ተቋማትን በመጠበቅ ተገቢውን አገልግሎት ለሕብረተሰቡ ሲሰጡ መቆየታቸውንና በትግራይ ውስጥ ለሚሰሩ የልማት ሥራዎችን ከሕብረተሰቡ ጎን በመሰለፍ በገንዘባቸው፣ በእውቀታቸውና በጉልበታቸው ከፍተኛ አስተዋፅኦ ሲያደርጉ እንደነበር ተገልጿል።
የፌደራል ፖሊስ ኃይል ሕብረተሰቡን ሲያግዝ በነበረበት ወቅት ህወሓት ከፍተኛ ኃይል በመመደብ ጥቃት እንደሰነዘረባቸውና የንብረት ዝርፊያ መፈጸሙን የተናገሩት ኮሚሽነር ጄነራሉ፥ በአንዳንድ አካባቢ የፌደራል ፖሊስ ሠራዊትና የትግራይ ሕዝብ አንድ ላይ ሆነው ሊወረው የመጣውን ኃይል ተከላክሏል ብለዋል።
መውጫና መግቢያ መንገዶችን ለሠራዊቱ በማሳየት የትግራይ ሕዝብ ሊያጠቃው የመጣውን አካል መከላከል መቻሉና ከሰሜን እዝ ጋር በመሆን ጽንፈኛውን ተዋጊ ኃይል በመመከትና በመምታት የራሱን ድርሻ እየተጫወተ ይገኛል ተብሏል።
ጽንፈኛው የህወሓት ቡድን የፈፀመው ይሄ አስነዋሪ ድርጊት ታሪክ፣ ሕግና ህሊና ይቅርታ የማይሰጠው ጉዳይ ነው ያሉት ኮሽነር ጄነራል እንዳሻው ጣሰው፥ ሠራዊቱንና ሕዝቡን የደፈሩበት ሂደት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋልም ብለዋል።
ለውጊያ ሳይሆን ለጥበቃ ሥራ የተሰማራ የፌደራል ፖሊስ ኃይል በታጠቀና ለውጊያ በተዘጋጀ ኃይል ተከቦ እንደዚህ ዓይነት እርምጃ መውሰድ አጅግ አሳፋሪ መሆን በመግለጽ ሕግ የማስከበር ሂደታችን በድል በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ የፌደራልና የክልል ፖሊስ እንዲሁም ሕዝባዊ አደረጃጀት ያላቸው የሚኒሻ አባላት በጋራ በመደራጀት አካባቢያቸውን በአግባቡ መጠበቅ እንዳለባቸው ጠቁመዋል፤ ለተለያየ እኩይ ተግባር የተሰማሩ ሃይሎችን በየአካባቢው በቂ ጥናት በማድረግ በቁጥጥር ስር ማዋል እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
በአማራ ክልል ጎንደር ከተማ፣ በአፋር፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላና በሌሎች አካባቢዎች የነበሩ የጥፋት ሙከራዎችን በቁጥጥር ስር በማዋል ሠራዊቱ በአንድ ረድፍ በመሰለፍ ይህንን ችግር ለመከላከል ላሳየው ከፍተኛ ጽናት አድናቆታቸውን በመግለጽ አሁንም ከኢንቨስትመንት ጀምሮ ለትልልቅ የኢንዱስትሪ መንደሮች ተረባርበን አስፈላጊውን ጥበቃ በማድረግ ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮችን መከላከል አለብን ብለዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት በሚሰጠው መመሪያ መሠረት መፈጸም ከሠራዊቱ አባላት የሚጠበቅ ተግባር መሆኑን የገለጹት ኮሚሽነር ጄነራሉ ሕብረተሰቡ በዲጂታል ወያኔ የሚሠራጩ የሐሰት ፕሮፓጋንዳዎችን በጋራ መከላከል እንዳለበትና በየቀኑ ከመንግሥት የሚሰጠውን መግለጫ ብቻ መከታተል እንዳለበት አስገንዝበዋል።
መንግሥት ለሚያቀርበው ጥሪ ሕብረተሰቡ በቂ ዝግጅት በማድረግ እኩይ ተግባር ለመፈጸም የተሰማራ ኃይል በመከታተል መጠቆምና ማጋለጥ እንዳለበትም ኮሚሽነር ጄነራሉ ጥሪ አቅርበዋል።
በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በተሰጡ አድራሻዎች መሠረት በዚህ በሁለት ቀናት ውስጥ ብቻ ከ1,500 በላይ የሚደርሱ ጥቆማዎች መድረሳቸውንና በዚህም ውጤታማ ሥራዎች መከናወናቸውን የተናገሩት ኮሚሽነር ጄነራሉ በሌሎችም መሰል ሥራዎች መሠራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
የተጀመረው ጸረ-ሰላም ኃይልን የማጥራት ሂደት በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ፊታችንን ሙሉ በሙሉ ለሰላም፣ ለልማትና ለዲሞክራሲ ግንባታ በማዞር ጥረት የምናደርግበት ጊዜ እንዲሆንም የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄነራል እንዳሻው ጣሰው ተመኝተዋል።
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን
November 3, 2020 at 11:22 pm #16627In reply to: ነፃ አስተያየት (ስለኢትዮጵያ በኢትዮጵያውያን)
AnonymousInactiveበህወሓትና በውጭ ኃይሎች የተቃጣውን የእብሪት ጦርነት በጋር ከመመከት ውጭ ሌላ አማራጭ የለም
ነአምን ዘለቀበሀገራችን አንድነትና በኢትዮጵያ ሕዝብ ደህንነት ላይ በህወሓትና በውጭ ኃይሎች የተቃጣውን የእብሪት ጦርነት በጋር ከመመከት ውጭ ሌላ አማራጭ የለም።
ሀገራችን ኢትዮጵያ ከባድ የህልውና አደጋ፣ ከባድ ፈተና ውስጥ እየገባች ነው። በእብሪት፣ በበታችነት፣ በዘረኝነት በሽታ የተለከፈው፣ በኢትዮጵያ ላይ የነበረውን ሁለንተናዊ የበላይነት ያጣው የመሰሪው የህወሓት መሪዎች ትግራይ ወስጥ በሚገኘው የሰሜን እዝ የመከላከያ ካምፕ ላይ የኃይል እርምጃ በውሰድ ሀገሪቱን ወደ ጦርነት ለመውሰድ የመጀመሪያ እርምጃቸውን እንደወሰዱ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት የተላለፈው መልዕክት ያሳያል።
1ኛ) የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር በጋራ ከመቆም ሌላ አማራጭ የለም። በልዩ ልዩ የህገሪቱ ችግሮች ከመንግሥት ጋር የሚገኙ ልዩነቶች ሁሉ ወደ ጎን ማድረግ አማራጭ የለውም።
2ኛ) በሀገራችን አንድነትና በሕዝብ አብሮነት ላይ የተቃጣውን የህወሓት እብሪት በጋር ከመመከት ውጭ ሌላ አማራጭ የለም።
3ኛ) የህወሓቶች ዒላማ የፌደራሉ መንግሥት ብቻ አይደለም፤ ይህ ጥቃት የተቃጣው በኢትዮጵያ ህልውና፣ በሕዝባችን ሰላም፣ ደህነትና አብሮነት ላይ ነው።
4ኛ) የህወሓቶች ጥቃት በመከላከያ ሠራዊት፣ በብልጽግና ፓርቲና እና በመንግሥት ላይ ብቻ አይደለም፤ የህወሓቶች እብሪትና ጠብ አጫሪነት እነሱ ያልገዟት ኢትዮጵያ እንድትፈርስ፣ ብሎም እነሱ የሚያስታጥቁትና የሚደግፉዋቸው ኃይሎች በቤኒሻንጉል፣ በወለጋ እንደተደረጉት እጅግ ዘግናኝና አረመኔያዊ ግድያዎች በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች እንዲደደገሙ በማድረግ ኢትዮጵያን ማፍረስ ነው። ይህን በጋራ ህልውናችውን ላይ የተቃጣ ከባድ አደጋ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በጋራ ሆነን መመከት አለብን።
5ኛ) ሕወሓት፣ ኦነግ ሸኔ፣ ግብጽ፣ እና በዲያስፓራም በሀገር ውስጥ የሚገኙ ቅጥረኖቻቸው ኢትዮጵያን ለማተራመስ ከቻሉ ማዕከላዊ መንግሥቱን ዳግም ለመቆጣጠር፥ ካልቻሉም ደግሞ ህወሓት አባይ ትግራይን ይመሠርታል፤ ግብጽም የአባይን ግድብ ህልውና እና አገልግሎት ለማምከን ትችላለች፤ ኦነግ ሸኔም የኦሮሚያ ሪፑብሊክ ይመሠርታል። አነዚህን ዋና ዒላማቸው አድርገው በጋራ እየተንቀሳቀሱ መሆኑ ግልጽ ነው። ከዚያ ስለሚከተለው ምድራዊ ሲኦል ህወሓትና የኦነግ ሽኔ የሞራልና የስብዕና ድኩማኖች ፈጽሞ ሊረዱ የሚችሉት አይደለም።
ኢትዮጵያውያን ሁሉ፥ በዲያስፓራ የምንገኝ ሀገር ወዳዶች ሁሉ፥ በሀገር ውስጥም ወጣቱ፥ ጀግናው የቀድሞ ሠራዊት አባላት ሁሉ ከዳር አስከ ዳር በጋራ ሆነን፣ በጋራ ቆመን ከማዕከላዊ መንግሥትና ከመከላከያ ሠራዊቱ ጀርባ በመሰለፍ፣ አሰፈላጊውን ድጋፍና መስዋዕትነት መክፈል አለብን። የሀገራችንን ህልውና፣ የሕዝብን ሰላምና ደህነት፥ የጥፋት፣ የዘረኝነት፣ የእብሪት ክምችት ከሆነው ከህወሓትና ግብረ-አበሮቹ ለመታደግ በጋራ መቆም፣ በጋራ መሰለፍ የወቅቱ [ዋና ተግባራችን መሆን አለበት።]
ይህን የማያደርግ የታሪክ ተወቃሽ ብቻ ሳይሆን የራሱንም፣ የቤተሰቡንም ዕጣ ፈንታ ለህወሓቶች ዳግማዊ የክረፋው ዘረኝነት፣ ጭካኔና ባርነት መዳረግ ይሆናል፤ ከዚያም ሲያልፍ ሀገር-አልባ መሆንም ይከተላል።
ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድም ሆነ ከብልጽግና ጋር ያለ ማናቸውም ልዩነት ወደ ጎን አድርገን የመጣብንን የህልወና አደጋ በጋራ መመከት የወቅቱ አብይ ተግባር ነው!!
ነአምን ዘለቀ (ከአሜሪካ)
ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረ–ገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forums) ላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።
November 2, 2020 at 11:42 pm #16613In reply to: የፖለቲካ ፓርቲዎች ድምጽ (ኢትዮጵያ ውስጥ የሚነቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች)
AnonymousInactiveበአማራ ሕዝብ ላይ እየተፈፀመ ባለው የዘር ማጥፋት ወንጀል መራሹ የኦህዴድ ብልጽግና መንግሥት ግንባር ቀደም ተጠያቂ ነው!!!
የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) በጥቅምት 22 ቀን 2013 ዓ.ም ምሽት ላይ በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ ጋዋ ጋንቃ ቀበሌ ከ200 በላይ አማሮች በማንነታቸው ብቻ ተለይተው በጅምላ በተፈፀመባቸው የዘር ማጥፋት ድርጊት የተሰማውን መሪር ሀዘን ይገልፃል።
ላለፉት ሰላሳ ዓመታት በሀገሪቱ ውስጥ በአማራ ሕዝብ ላይ ማንነትን መሠረት ያደረገ የጅምላ ጭፍጨፋና የዘር የማፅዳት ወንጀል እየተፈፀመ ይገኛል። በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በአማራው ሕዝብ ላይ የሚደርሰውን ሰቆቃ ማስቆም የሚችል የመንግሥት ኃይል አለመኖሩ ደግሞ ችግሩን እያባባሰው መጥቶ ዛሬ ላይ የአማራ ሕዝብ ከፍተኛ የህልውና አደጋ ተጋርጦበት ይገኛል።
በዚህም ምክንያት በእነዚህ በርካታ ዓመታት በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈፀመው የዘር ማጥፋት ወንጀል ተባብሶ ቀጥሏል። መንግሥትም በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈፀመውን ተደጋጋሚ የዘር ማጥፋት ወንጀል በስሙ ከመጥራት እና ብሔራዊ የደኅንነት ስጋት አድርጎ ጥቃቱን ከማስቆምና የችግሩን ፈጣሪዎች በቅጡ ለይቶ የሚመጥን ርምጃ በወቅቱ ከመውሰድና የሕዝቡን ደህንነት ከመጠበቅ ይልቅ እሹሩሩ በማለትና ወንጀሉን በማድበስበስ የወንጀሉ ቀንደኛ ተባባሪ ሆኖ ይገኛል።
በተለያዩ የኦሮሚያ ዞኖች የሚንቀሳቀሰው ታጣቂው የኦነግ ሸኔ ኃይል ከኤርትራ ሙሉ ትጥቅ ይዞ እንዲገባ በማድረግ በየቦታው ካሉ አማራጠል ፅንፈኛ ኃይሎች ጋር በቅንጅት አማራዉን ማኅበራዊ ረፍት ለመንሳትና በጅምላ ለመጨፍጨፍ እንዲችሉ ፍቃድ የሰጣቸው የፌደራል መንግሥቱ ነው።
በኦህዴድ መራሹ የብልጽግና መንግሥት የስልጣን መዋቅር ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ አፍቃሬ ኦነግ የኦህዴድ ባለስልጣናት በአካባቢው የነበረውን የኦሮሚያ ልዩ ኃይል በማስወጣትና ድርጊቱ ሲፈፀም እየሠሙና እያወቁ እንዳላዩ ማለፋቸው የዚህ የወንጀል ድርጊት ተሳታፊ እንደሆኑ ይቆጠራል። በአጠቃላይ የአማራ ሕዝብ የዘር ማጥፋት ታውጆበት እያለ የማዕከላዊ መንግሥቱ ዝምታና እንዳላየ ማለፉ እጅግ አሳፋሪ ተግባር ነው።
የአማራው ሕዝብ በመንግሥት ድጋፍ እየተፈፀመበት ያለውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ተደራጅቶ እና ተዘጋጅቶ እንዲመክት የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ጥሪውን እያቀረበ በአሸባሪው የኦነግ ሽኔ ሽፍታ ቡድን ህይወታቸን ላጡ ወገኖቻችን ቤተሰቦች መፅናናትን እንዲሰጥልን እንመኛለን።
የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)
ጥቅምት 22 ቀን 2013 ዓ.ምNovember 2, 2020 at 11:11 pm #16609In reply to: የፖለቲካ ፓርቲዎች ድምጽ (ኢትዮጵያ ውስጥ የሚነቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች)
AnonymousInactiveምዕራብ ኦሮሚያ የተፈጸመውን ግድያ በጽኑ እናወግዛለን
የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)ከትላንት በስትያ ህዳር 1 ቀን 2020 [ጥቅምት 22 ቀን 2013 ዓ.ም] ምዕራብ ኦሮሚያ ውስጥ በዜጎች ላይ ግድያ መፈጸሙን ከመገናኛ ብዙሃን የሰማን ሲሆን፥ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ይህንን የግድያ ተግባር በጽኑ እያወገዘ፤ የተሰማውን ጥልቅ ሀዘንም ይገልጻል።
መንግሥት ነኝ የሚለው አካል ከአሁን ቀደም እንደለመደው ይህንን ግድያ የፈጸሙት ህወሓት እና ኦነግ-ሸኔ ናቸው በሚል ገልጿል። ኦነግ-ሸኔ በሚል የሚታወቅም ይሁን በዚህ ስም እራሱን የሚጠራ ድርጅት ግን አላገኘንም። ለኢትዮጵያ ሕዝቦችም ይሁን ለዓለም ማኅበረሰብ በዚህ ስም የሚከሰሰው ድርጅት ማንነት ግልጽ አይደለም።
ይህ የግድያ ድርጊት እና ሌሎች መሰል ድርጊቶች ሁሉም ነጻና ተዓማኒነት ባለው ገለልተኛ አካል በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጣርተው ለተጎጂዎችና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች፥ እንዲሁም ለዓለም ማኅበረሰብ ግልጽ እንዲሆኑ እንጠይቃለን። ከዚህ ባሻገር ሁሉም አካላት ሕዝቦችን የሚያጋጩና በብሔሮች መካከል መጠራጠርን የሚፈጥሩ ማናቸውንም ዓይነት መረጃ ከማሰራጨት እንዲቆጠቡ መልዕክታችንን እናስተላልፋለን።
በመጨረሻም ዜጎችን ለከፋ አደጋ እያጋለጠ ያለው ቀውስና የደህንነት ችግር ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት መፍትሄ ካልተበጀለት፥ ይበልጥ እየተባባሰ እንደሚሄድ ኦነግ በመግለጫው ሲያሳስብ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፤ አሁን እያየን ያለነውን አደጋ ለማስቀረት እና ኦሮሚያና ዜጎችን ከባሰ ቀውስ ለመታደግ ያለው ብቸኛው መፍትሄ የኦሮሚያ ሽግግር መንግሥት ማቋቋም በመሆኑ ሁሉም ዜጋ ድርሻውን እንዲወጣ ጥሪያችንን በድጋሚ እናድሳለን።
በድጋሚ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) በምዕራብ ኦሮሚያ በዜጎች ላይ የተፈጸመውንና ካሁን ቀደምም በተመሳሳይ መልኩ የተፈጸሙ ግድያዎችን ሁሉ በጥቅብ እንደሚያወግዝ እያሳሰበ፥ ለሟች ቤተሰቦችና ዘመዶች እንዲሁም ሰላም ወዳዶች ሁሉ መጽናናትን ይመኛል።
ድል ለሰፊው ሕዝብ!
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)
ህዳር 3 ቀን 2020 ዓ.ም- በአማራ ሕዝብ ላይ በየቦታው እየተፈፀመ ላለው የዘር ማጥፋት ወንጀል ሙሉ ኃላፊነቱን መንግሥት ይወስዳል ― አብን
- ንጹሃን ዜጎችን በማንነታቸዉ በጅምላ ማጥቃት የሽብር እንጂ የፖለቲካ ትግል ሊሆን አይችልም ― ብልጽግና ፓርቲ
- የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን በምዕራብ ወለጋ ዞን በተፈጸመው ጥቃት ህይወታቸው ያለፉ ሰዎች ቁጥር 32 እንደሆነ ገለጸ
- የምንገኝበት የፖለቲካ ቀውስ፣ ፈጣን ፖለቲካዊ መፍትሔ ይፈልጋል! – ከኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ሥራ አስፈፃሚ የተሰጠ መግለጫ
- ሰላማችንን በማስጠበቅ እና ቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ ላይ በንቃት በመሳተፍ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠረት እንጣል! ― ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የተሰጠ መግለጫ
November 2, 2020 at 1:48 pm #16584In reply to: በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ውስጥ እየደረሰ ያለው የሰላማዊ ሰዎች ጥቃት
AnonymousInactiveየኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን በምዕራብ ወለጋ ዞን በተፈጸመው ጥቃት ህይወታቸው ያለፉ ሰዎች ቁጥር 32 እንደሆነ ገለጸ
- የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መልዕክት
- የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን መልዕክት
- የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ጋዜጣዊ መግለጫ
- የብልጽግና ፓርቲ ጋዜጣዊ መግለጫ
- የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) መልዕክት
- የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) መግለጫ
- የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) መግለጫ
የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ ጋዋ ቃንቃ ቀበሌ በተፈጸመው ጥቃት ህይወታቸው ያለፉ ሰዎች ቁጥር 32 እንደሆነ ገለጸ።
የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል አራርሳ መርዳሳ ጥቅምት 23 ቀን 2013 ዓ.ም. ማምሻውን ለኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) እንዳሉት፥ በጥቃቱ የተነሳ የተፈናቀሉ 200 ያህል አባወራዎችን የማረጋጋትና ሥራ እየተሠራ ነው።
በተፈጸመው ጥቃት 23 ወንድ እና 9 ሴቶች በድምሩ 32 ሰዎች ህይወታቸው ማለፉን የገለጹት ኮሚሽነር ጄኔራሉ፥ 10 ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸው ሕክምና እየተከታተሉ እንደሚገኙ አመልክተዋል።
በጥቃቱ የመኖሪያ ቤቶችና አንድ ትምህርት ቤት እንደተቃጠለ ተናግረው፥ ከአካባቢው ሕብረተሰብ ጋር በመተባበር መልሶ የማቋቋም ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል።
የጥቃት ድርጊቱን የፈጸመው አካል ኦነግ ሸኔ መሆኑን ገልጸው፥ ከጀርባ በመሆን የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) እየደገፈው እንደሚገኝ ተናግረዋል። በተለይም ቡድኑ የታጠቃቸው እንደ ስናይፐርና ብሬል ያሉ የጦር መሳሪያዎች ህወሓት ያስታጠቀው እንደሆነ ገልጸዋል። ከኦነግ ጀርባ በመሆን ህወሓት በህብረተሰቡ ላይ ጥፋት እያደረሰ እንደሆነም አክለዋል።
ጥቃት የተፈጸመበት ቀበሌ ከወረዳ ከተማ በ75 ኪሎ ሜትር የሚርቅ መሆኑን ገልጸው፥ ህወሓት በብሔሮች መካከል ግጭት ለመፍጠር በስሌት የፈጸመው ተግባር ስለመሆኑ ተናግረዋል።
ከድርጊቱ ፈጻሚዎች መካከል የተወሰኑት መያዛቸውን ተናግረው ቀሪዎቹን ለመያዝ እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸው፥ ተመሳሳይ ጥቃት እንዳይፈጸም ከሕብረተሰቡ ጋር እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
- የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መልዕክት
በተያያዘ ዜና፥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ኢትዮጵያውያን ላይ እየተፈጸመ ባለው ማንነትን መሠረት ያደረገ ጥቃት ከምንጩ ለማድረቅ መንግስት የሚወስደውን ርምጃ በመደገፍ ሕዝቡ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የጸጥታ አካላት ምሁራንና ሌሎችም የሚጠበቅባቸውን እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ያሰፈሩት መልዕክት እንደሚከተለው ይነበባል።
“በኢትዮጵያውያን ላይ እየተፈጸመ ባለው ማንነትን መሠረት ባደረገው ጥቃት እጅግ ማዘኔን እገልፃለሁ።
የኢትዮጵያ ጠላቶች፤ “ወይ እኛ እንገዛለን፤ ወይ ሀገር አትኖርም” ብለው ተነሥተዋል። ለዚህም የጥፋት አቅማቸውን ሁሉ እየተጠቀሙ ነው። አንደኛው ዒላማቸውም የሕዝባችንን ቅስም መስበር ነው።
ለዚህ እየተጠቀሙበት ያለው ስልት ግራ ቀኝ የማያውቁ ሰዎችን እየሰበሰቡ በማሠልጠንና በማስታጠቅ በየአካባቢው ማንነትን መሠረት ያደረገ አረመኔያዊ ጥቃት ማድረስ ነው። ይህ ተግባር ሕዝቡ እንዲደናገጥ፣ እንዲፈራና በስሜት ያልተገባ ርምጃ እንዲወስድ የታለመ ነው።
መንግሥት በተለያዩ ቦታዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ ያላቸውን ጥፋቶች በቅድሚያ መረጃ ሰብስቦ ርምጃ በመውሰድ ሲያከሽፍ ቆይቷል። ነገር ግን ያለፈው ሥርዓት ያወረሰንን ቀዳዳዎች ሁሉ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ደፍኖ መጨረስ አልተቻለም።
የጥፋት ኃይሎች ከውጭ ላኪዎቻቸውና በመንግሥት መዋቅር ውስጥ በሚገኙ ባልጠሩ አድር ባዮች ትብብር በሕዝባችን ላይ አሳዛኝ ጥቃት እያደረሱ ነው። ሁኔታው እንደ መሪም እንደ ዜጋም ልብ ይሰብራል።
ይህ ግን ከመንገዳችን ወደኋላ፣ ከግባችን ወደ ሌላ አያደርገንም። ተስፋ ቆርጠን እንድናቆም፣ ተሸንፈን እንድናፈገፍግ አያደርገንም። ከምንጊዜውም በላይ ኃይላችንን አሰባስበን እንድንነሣ ያደርገናል እንጂ።
መንግሥት ሁሉንም ዓይነት አማራጮች ተጠቅሞ የችግሩን ሰንኮፍ ይነቅለዋል። የጸጥታ አካላት ጥቃቱ ወደተፈጸመበት አካባቢ ተሠማርተዋል። ርምጃም እየወሰዱ ነው። በቀጣይም የሕዝባችንን ደኅንነት ለማስጠበቅ መንግሥት የመንግሥትነቱን ሥራ በቁርጥና በጽናት ይሠራል።
ሕዝቡ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የጸጥታ አካላት፣ ምሁራንና ሌሎችም፧ መንግሥት ችግሩን ከምንጩ ለማድረቅ የሚወስደውን ርምጃ በመደገፍ የሚጠበቅባቸውን እንዲያደርጉ ጥሪ አቀርባለሁ።”
- የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን መልዕክት
የኢፌዲሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ በንፁኃን ዜጎች ላይ የተፈፀመውን አሰቃቂ ጭፍጨፋ በማስመልከት መልዕክት አስተላልፈዋል። አቶ ደመቀ መኮንን ባስተላለፉት መልዕክት የሚከተለውን ብለዋል።
“በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ በንፁሃን ዜጎች ላይ የተፈፀመው አሰቃቂ ጭፍጨፋ የተሰማኝን ሀዘን እየገለፅኩ፥ ለሟች ቤተሰቦች መፅናናትን እመኛለሁ።
በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ቀደም ሲል ብሔርን፣ ሀይማኖትን እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት የማድረስ ዓላማ ያላቸው ጥቃቶችና ጭፍጨፋዎች ተካሂደዋል። በተመሳሳይ በምዕራብ ወለጋ ዞን በንፁሃን ዜጎች ላይ አሰቃቂ ጭፍጨፋ ተፈፅሟል።
በተለይ የአማራን ማኅበረሰብ ትኩረት ያደረገና በንፁሃን ዜጎች ላይ የሚካሄደው ጭፍጨፋ ፍፁም አረመኔያዊና በፍጥነት መቆም ያለበት እኩይ ድርጊት ነው። ድርጊቱ አስቀድሞ መዋቅራዊ በሆነ መልኩ ሲዘራ የቆየ በመሆኑ፥ ችግሩን የሚመጥን መፍትሄ በዘላቂነት ለማበጀት አስፈላጊው ሁሉ ይደረጋል። ከዚህ አኳያ የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ እንዲሁም ከሁሉም አቅጣጫ የሚቃጡ ጥቃቶችን ለመመከት የመንግሥትና ሕዝብ ቅንጅታዊ ርብርብ ተጠናክሮ ይቀጥላል።”
- የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ጋዜጣዊ መግለጫ
ይህንን ጥቃት ተከትሎ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ባወጣው መግለጫ በአማራ ሕዝብ ላይ በየቦታው እየተፈፀመ ላለው የዘር ማጥፉት ወንጀል ሙሉ ኃላፊነቱን መንግሥት ይወስዳል ብሏል። ሙሉ መግለጫውን እዚህ ጋር በመጫን ያንብቡ።
- የብልጽግና ፓርቲ ጋዜጣዊ መግለጫ
የብልጽግና ፓርቲ በበኩሉ፥ ንጹሃን ዜጎችን በማንነታቸው በጅምላ ማጥቃት የሽብር እንጂ የፖለቲካ ትግል ሊሆን እንደማይችል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል። ሙሉ መግለጫውን እዚህ ጋር በመጫን ያገኙታል።
- የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) መልዕክት
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) “በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ በዜጎች ላይ ማንነትን መሠረት ባደረገ ጥቃት በተገደሉት እና ጉዳት በደረሰባቸው ኢትዮጵያውያን የተሰማንን ሀዘን እንገልፃለን” በማለት የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ክፍል መልዕክቱን አስተላልፏል።
ፓርቲው በዚሁ መልዕክቱ፥ ኢትዮጵያውያን በዚህ አስቸጋሪ ወቅት በአንድነት በመቆም የዘውግ ፖለቲካ ያመጣብንን በሕይወት የመኖር እና እንደ ሀገር የመቀጠል አደጋ ልንታገለው እንደሚገባና፤ ኢዜማ አጠቃላይ የሀገራችንን ሁኔታ አስመልክቶ በቀጣይ ቀናት መግለጫ እንደሚሰጥ አመላክቷል።
በማስከተልም፥ በምዕራብ ወለጋ ጉሊሶ ወረዳ ማንነትን መሰረት አድርጎ የተፈፀመው ጥቃት የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ሐዘን ሲሆን፤ የጥቃቱ ዓላማም ሀገርን የማፍረስ መሆኑን ተረድተን ሀዘናችንን በጋራ በመግለፅ በአንድነት እንድንቆም እንጠይቃለን ሲል መልዕክቱን ቋጭቷል።
- የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) መግለጫ
የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) በሰላማዊ ሰዎች ላይ የደረሰውን ጥቃት ካወገዘ በኋላ፥ መንግሥት ጥቃቱን ያደረሱት ህወሓትና ኦነግ ሸኔ ናቸው ማለቱን በከፊል በማስተባበል፤ ይልቁንስ ኦነግ ሸኔ የሚባል ቡድን በአካል እንደሌለ ገልጿል። የኦነግን ሙሉ መግለጫ እዚህ ጋር በመጫን ያገኙታል።
- የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) መግለጫ
የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ደግሞ በሰጠው መግለጫ፥ በአማራ ሕዝብ ላይ እየደረሰ ላለው ዘር-ተኮር ጥቃት የፌደራል መንግሥቱን የሚመራው ብልጽግና ፓርቲ ግንባር ቀደም ተጠያቂ እንደሆነ አትቷል። ሙሉ መግለጫውን እዚህ ጋር ያገኙታል።
October 31, 2020 at 11:28 pm #16572In reply to: የፖለቲካ ፓርቲዎች ድምጽ (ኢትዮጵያ ውስጥ የሚነቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች)
AnonymousInactiveከዓመቱ የትምህርት ፕሮግራም መጀመር ጋር ለተማሪዎች ደህንነትም አስፈላጊው ቅድመ ጥንቃቄ መደረግ አለበት
ከኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) የተሰጠ መግለጫበኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት የመማር-ማስተማሩ ሂደት ከተስተጓጎለ ከስድስት ወራት በላይ ሆኖታል። መንግሥት የተቋረጠውን የትምህርት ፕሮግራም መልሶ ለማስጀመርና የወረርሽኙን ጥቃት ለመቆጣጠር በሚያስችል ሁኔታ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ ከሕዝብ ዜና ማሰራጫዎች እየሰማን እንገኛለን። በእርግጥም የትምህርት ፕሮግራሙን መልሶ ማስጀመር የግድ እንደሆነ ብንረዳም፤ ከዚሁ ጋርም ስለወጣት ተማሪዎቹ ደህንነትም መታሰብ እንዳለበት ለማስገንዘብ ይህንን መግለጫ አወጥተናል።
ከኮሮና ወረርሽኝ ስጋት በተጓዳኝ የሀገራችን የፖለቲካ ቀውስ እና በየቦታው እየተነሱ የሕዝቦቻችንን ደህንነት የሚያውኩ ግልገል አምባገነኖች የሚፈጽሙት እኩይ ተግባራት ተጨማሪ ስጋት ሊሆን እንደሚችል ግምት አለን። ጠባብ ዓላማ ያነገቡ የተለያዩ ኃይሎች በሚፈጥሩት ግጭቶች፣ መንግሥት የሚመድባቸው ባለሥልጣናት የማስፈጸም አቅም ውስንነት እና አንዳንዶች ደግሞ ከሕዝባዊ ወገናዊነት ማነስ የተነሳ ለትምህርት ፕሮግራሙ ስኬት የሚጠበቅባቸውን ግደታ በትክክል ሳይወጡ ሲቀሩ፥ ለጋ ወጣት ተማሪዎች አደጋ ላይ ይወድቃሉ፤ ደርሶም ታይቷል። በዚህን ጊዜ ቁጥራቸውን መግለፅ አስፈላጊ ባይሆንም፥ በ2012 ዓ.ም የአንደኛ ሴሚስተር ጊዜ ውስጥ ከደረሰባቸው የሕይወትና ንብረት መጎዳት የተነሳ የኦሮሚያ ክልል ወጣት ተማሪዎች ወደ ሌሎች ክልሎች የትምህርት ተቋማት ሄደው ለመማር የሚያሳዩት ፍላጎት እያነሰ በመሄድ ላይ እንደሚገኝና በክልላቸው ለመማር እንዲችሉ ሁኔታዎች እንዲመቻችላቸው ጥያቄ እያቀረቡ እንደሆነ ተረድተናል።
-
- የትምህርት መጀመር ሁኔታን አስመልክቶ በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ የተላለፈ መልዕክት
- የትምህርት መጀመር ሁኔታን አስመልክቶ በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ የተላለፈ መልዕክት
በተጠቀሰው ጊዜ በየትም ክልል ይሁን በተማሪዎቹ ላይ ወንጀል የፈጸሙ ኃይሎች ላይ ስለተወሰደ ሕጋዊ እርምጃ የተሰማ ነገር ባይኖርም፤ አሁንም በማንኛውም ክልል የሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለማንኛውም ወጣት ተማሪ ምክር እየተለገሳቸው ራሳቸውን ብሎም ሀገርን ማስተዳደር የሚችሉበት ሁኔታ መፍጠሪያ ቦታና ተቋማቱ ደግሞ ከቤት ውጭ ቤት ሆነው አገልግሎት መስጠት እንዳለባቸው እንገነዘባለን። ይህ ይሆን ዘንድ ማረጋገጫ መስጠት የሚችለው ማንም ሳይሆን መንግሥት ነው። ይህ ሳይሆን ቀርቶ እንደከዚህ ቀደሙ የወጣት ተማሪዎችን ሕይወት የሚቀጥፍ ሁኔታ ከተፈጠረ በሀገራችን ሌላ ተጨማሪና ሊያባራ የማይችል ቀውስ እንዳይፈጥር እንሰጋለን።
ስለሆነም፥ የተቋረጠውን የትምህርት ፕሮግራም መልሶ ለማስጀመር ዝግጅት በሚደረግበት ጊዜ ለኮሮና ወረርሽኝ መከላከል ብቻ ሳይሆን ለመማር ማስተማሩ ሥራ አመቺ የሆነና በአንፃራዊነትም ከግጭት ነፃ የሆነ ከባቢ ለመፍጠር አስፈላጊው እንዲደረግ ለመንግሥትና ለሁሉም የፌዴራሉ ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ከአደራ ጭምር እናሳስባለን።
የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ)
ፊንፊኔ፤ ጥቅምት 2013 ዓ.ም.October 26, 2020 at 12:12 am #16485In reply to: የፖለቲካ ፓርቲዎች ድምጽ (ኢትዮጵያ ውስጥ የሚነቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች)
AnonymousInactiveየአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በአማራ ክልል ከተሞች እና በአዲስ አበባ ታላልቅ ሰለማዊ ሰልፎችን ለማድረግ ጥሪ አደረገ
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በአማራ ክልል ከተሞች እና በአዲስ አበባ ታላልቅ ሰለማዊ ሰልፎች እንደሚደረጉ አስታውቋል። አብን ስለሰላማዊ ሰልፎቹ እና በአጠቃላይ በአማራ ሕዝብ ላይ ከዕለት ወደ ዕለት ያልተቋረጠ በደል እየደረሰበት መሆኑን ያመላከተበት ትንታኔ የሚከተለውን ይመስላል።
ለመላው የአማራ ሕዝብ፣
ለንቅናቄያችን አባላትና ደጋፊዎች፣
ለመላው ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በሙሉ !የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) መንግሥታዊና ሥርዓታዊ ጭቆና እና የዘር ጥቃት ያንዣበበትን የአማራን ሕዝብ ከህልውና ስጋት ለመታደግና በነፃነት፣ በእኩልነት፣ በፍትህና በወንድማማችነት የሚኖርባት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት የቆመ ድርጅት ነው።
አብን ባለፉት ሁለት ከመንፈቅ ዓመታት ሕዝባችን በከፍተኛ መስዋዕትነት ያስገኘው የለውጥ ተስፋ እንዳይመክን፣ በትግላችን የተንበረከኩ አማራ-ጠል ኃይሎች ዳግም እንዳያንሰራሩና የሀገር እና የሕዝብ ህልውና በድጋሚ አደጋ ላይ እንዳይወድቅ እልህ አስጨራሽ ትግል አድርጓል። የአማራ ብሔርተኝነት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ አዎንታዊ የመረጋጋት፣ የመቻቻልና የግንባታ ሚና እንዲኖረው ያልተቆጠበ ጥረት አድርጓል።
ይሁን እንጂ ተስፋ የተጣለበት “ለውጥ” እያደር መስመሩን በመሳቱ አዲሱ አገዛዝ የአምባገነንነትና የአንድ ቡድን ፍላጎት አስፈፃሚነት አዝማሚያ ማሳየቱ ገሃድ ወጥቷል። በተለይም በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈፀመው የዘር ጥቃት እየተባባሰና አድማሱን እያሰፋ በቅርቡ እንኳን በኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና በደቡብ ጉራ ፈርዳ ተከታታይ ለሆኑ የጅምላ ጭፍጨፋዎች፣ የዘር ማጽዳትና የማፈናቀል ጥቃቶች ሰለባ ሆኗል።
አብን በሕዝባችን ላይ ስልታዊ፣ የተደራጀ፣ ሰፊ የመገናኛ ብዙኃን ቅስቀሳ የተደረገበት ዘመቻና በመንግሥት መዋቅር ጭምር የተደገፈ የዘር ማጥፋት እየተፈፀመበት መሆኑን በመግለጽ መንግሥት ችግሩን እንዲያስቆም በተደጋጋሚ ወትውቷል። እንደ ሕዝብም መቻቻልና ሀገር ወዳድነት ትርጉም እስኪያጡ ድረስ ታግሰናል። ነገር ግን ብልፅግና-መራሹ መንግሥት የሕዝባችንን ሆደ-ሰፊነትና አስተዋይነት እንደ ዓይነተኛ ድክመት በመቁጠር፥ ንቅናቄያችን ለሀገር ህልውና ሲባል የሰጠውን ይሁንታ በሰፊው በማጓደል ዛሬም አማራው መንግሥት-አልባ ሕዝብ መሆኑን አረጋግጦልናል።
አብን በሕዝባችን ላይ ለሚደርሰው ጥቃት ቀንደኛው ተጠያቂ ማዕከላዊ መንግሥት መሆኑን ያምናል። መንግሥት ‹‹የወንጀሎች ሁሉ ወንጀል›› የሚባለውን የዘር ማጥፋትን በመከላከል፣ በማስቆምና ዘላቂ መፍትሄ በመፈለግ ረገድ የረባ ሚና አልተጫወተም። እንዲያውም የዘር ጥቃቶችን “ግጭት” እያለ ለማድበስበስ፣ መረጃዎችን ለማፈንና ሰለባዎችን ጭምር ለመወንጀል ተደጋጋሚ ጥረቶችን ሲያደርግ ተስተውሏል። መንግሥት በአማራ ላይ የተፈፀሙ የዘር ጥቃቶች ልዩ ጠባሳ የሆነውን የጉራ ፈርዳ ጥቃት መሪ አቀናባሪ የነበረውን ግለሰብ ለዳግም ሹመት የመምረጡን አንድምታ እንረዳለን፤ አሁን የሚፈፀመውን ካለፈው የሚያስተሳስር ረጅም ክር አለው።
በሁለተኛ በአማራ ሕዝብ ላይ የዘር ፍጅት በተፈፀመባቸው ክልሎች ያሉ መንግሥታት በተለያየ ደረጃ ኃላፊነታቸውን ካለመወጣት አልፈው፥ በቀጥታና በተዘዋዋሪ በሕግ፣ በመዋቅር፣ በመሣሪያና በገንዘብ ጥቃቶችን መደገፋቸውና ማቀናበራቸው በገሃድ ይታወቃል። ከጥቃቱም በኋላ የየክልሎቹ የብልፅግና ፖርቲ አመራሮች በሕዝባችን ላይ በየፊናቸው በማንአለብኝነት የሚያደርጉት ዛቻና ማስፈራሪያ በድርጊቱ አለመጸጸታቸውንና ችግሩን ለማረም ፈቃደኝነት እንደሌላቸውም ያረጋግጣል።
ሦስተኛው ተጠያቂ “የአማራ ብልፅግና” የሚባለው ነው። ለአማራ ሕዝብ ብልፅግናውን ቀርቶ ህልውናውንም ሊያስጠብቅለት አልቻለም። ቀድሞ ከነበረው አጠቃላይ አቋም መሻሻል አላሳየም። ንቅናቄያችን አማራው እንደ ሕዝብ በአንድነት እንዲቆም ለማስቻል ለሁለት ዓመታት ያክል “የአማራ – ብልፅግናን” ለማግባባት ያደረገው ሰፊ እና ያላሰለሰ ጥረት ፍሬ አላፈራም። የአማራ ሕዝብንም፣ አብንንም በተደጋጋሚ ያሳዘነ ሲሆን፤ ከታሪክ ተጠያቂነትም አያመልጥም።
አብን በማዕከልም ሆነ በክልል ያሉ መንግሥታት የተጫወቱት አፍራሽ ሚና ውጤቱ በአማራው ሕዝብ ተገድቦ እንደማይቀር በውል እንዲጤን ይሻል። መንግሥት መሠረታዊ መብቶቹን የማያስጠብቅለትን ሕዝብ ማናቸውንም የሞራልም ሆነ የሕግ ግዴታ ሊጥልበት አይቻለውም። በሕዝብና በመንግሥት መካከል ያለው ማኅበራዊ ውልም ክፉኛ ይናጋል።
አብን በአማራው ላይ የሚደረገው የዘር ማጥፋት ድርጊት ዞሮ ኢትዮጵያን እንደሀገር ዋጋ እንደሚያስከፍልም ይገነዘባል። ንቅናቄያችን እስካሁን የአማራ ሕዝብ በኢትዮጵያዊነት ተስፋ እንዲቆርጥና ወደ አመፅ እንዲያመራ የሚደረገውን አሉታዊ ጥረት ሲታገል ቆይቷል። ሆኖም ከእንግዲህ ወዲያ የሕዝባችን ህልውና በምንም መልኩ ለድርድር እንደማይቀርብ ለማረጋገጥ ይወዳል።
አብን የአማራ ሕዝብ ሆደ ሰፊና አስተዋይ በመሆኑ ተፈጥሯዊ መብቱንና ነፃነቱን በልቅሶና በልመና ሳይሆን በተደራጀ ትግል እንደሚያስከብር ይተማመናል። ይህን ታላቅ ታሪካዊ ኃላፊነት በመምራት ከግብ ለማድረስ ድርጅታችን ቁርጠኝነቱን ያረጋግጣል።
አብን መንግሥት ችግሩን በአስቸኳይ ከማስቆም በተጨማሪ ጥቃቱን እንዲያምንና በስሙ እንዲጠራ፣ ጉዳዩን የሚያጣራ ገለልተኛ አካል በፍጥነት እንዲሰይም፣ ወንጀለኞችን አጣርቶ ለፍርድ እንዲያቀርብና ለተጎጂዎችም ተገቢውን ካሳ እንዲከፍል በጥብቅ ይጠይቃል። ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት መሠረታዊ ምንጭ የሆነው አማራ-ጠል ሕገ-መንግሥት የሚሻሻልበትን አግባብ በአስቸኳይ እንዲያመቻች ይጠይቃል።
አብን መንግሥት የሀገሪቱን ሰላምና ደህንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ማስከበር አለመቻሉንና በተደጋጋሚ የአማራ ተማሪዎችን ደህንነት ለመጠበቅ ችላ ማለቱን በማጤን ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ያደረገው የትምህርት መጀመር ጥሪም ያሳስበዋል። ብዙ ሽህ የአማራ ተማሪዎች በፅንፈኞች ጥቃት ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው ሲፈናቀሉ፣ ሲገደሉ፣ ሲደበደቡና ሲታገቱ በአሳፋሪ ሁኔታ አልታደጋቸውም። አሁንም ለተማሪዎች አስተማማኝ ጥበቃ እንዲያደርግ በጥብቅ እንጠይቃለን።
የአብን ብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በጥቅምት 14 እና 15 ቀን 2013 ዓ.ም ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ በወሰነው መሠረት በሀገራችንና በሕዝባችን ላይ ያንዣበበውን ከፍተኛ የደህንነት ስጋት በመቀልበስ፤ የሕዝባችንን ህልውና ለማረጋገጥ የሚያደርጋቸውን ሰላማዊና ሕጋዊ የትግል ጥረቶችና ስልቶች ለሕዝባችን ለማሳወቅ የፊታችን ረቡዕ ጥቅምት 18 በአማራ ክልል ከተሞች፤ እሁድ ጥቅምት 22 በአዲስ አበባ ታላላቅ ሕዝባዊ ትዕይንቶች ይደረጋሉ።
በእነዚህ ሰልፎች ላይ መላው የአማራ ሕዝብ ማናቸውም ልዩነት ሳይገድበው እንዲሳተፍ፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የአማራ የፖለቲካ ኃይሎች፣ የተለያዩ የአማራ የሲቪክ አደረጃጀቶች በወገናችሁ ላይ የሚደርሰውን ግፍና በደል እንድትቃወሙ ጥሪ እናደርጋለን።
አብን በአማራ ክልልና በአዲስ አበባ የተጠሩት የተቃውሞ ሰልፎች ፍፁም ሰላማዊ እንዲሆኑና ሊከተሉ የሚችሉ አላስፈላጊ ረብሻዎችንና ጥቃቶችን ለማስቀረት ሕዝቡ የራሱን ደህንነት በንቃት እንዲጠብቅ ያሳስባል።
ሰልፉን በተመለከተ ዝርዝር ጉዳዮች፣ በሰልፉ ላይ የሚተላለፉ መልዕክቶችና መፈክሮች በማዕከል ተዘጋጅተው በፓርቲያችን ይፋዊ ገፅ የሚለጠፉትና ለየአካባቢው የሚላኩት ናቸው።
ጉዳዩ የሕዝብ ህልውና ጥያቄና የራሱ ሰልፍ በመሆኑ የሀገር መከላከያና አጠቃላይ የደህንነት ኃይሉ የሕዝቡ ሰልፍ የተሳካ እንዲሆን ተገቢውን የፀጥታ ሥራ እንዲያከናውን ጥሪ እናደርጋለን።
በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ አማሮች እሁድ ጥቅምት 22 ቀን 2013 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከሚደረገው ሰልፍ ጋር በተለያዩ ክፍለ ዓለማት ድምፃችሁን እንድታሰሙ አብን ጥሪውን ያቀርባል።
ሰልፉ ለኮቪድ-19 ወረርሽኝ በማያጋልጥ መልኩ በጥንቃቄ እንዲካሄድ እያሳሰበ፥ ሕዝባችን በየአካባቢውና በየቤተሰቡ በገጠመን ፅኑ ወቅታዊ ችግር ላይ ውይይት እንዲያካሂድ፤ በቀጣይም ዘላቂ መፍትሄ ለማፈላለግ አብን ዓለምአቀፍ የመላው አማራ ሕዝባዊ ውይይት መድረኮችን እንደሚያመቻች መግለጽ ይወዳል።
በአዲስ አበባም ሆነ በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈፀመው የማናለብኝነትና የተረኝነት አካሄድ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ጉዳት በመሆኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ በወንድሙ በአማራው ሕዝብ ላይ የሚፈፀመውን ግፍና በደል በመቃወም አብሮ እንዲሰለፍ አብን ጥሪውን ያቀርባል።
አብን ከእንግዲህ ጉዳዩ የማያዳግም እልባት እስከሚያገኝ ድረስ ማናቸውንም የሰላማዊ ትግልና የሕዝባዊ እምቢተኝነት ስልቶችን በየደረጃው የሚተገብር በመሆኑ ሕዝባችን ከወዲሁ እንዲያውቀውና ወትሮ ዝግጁ እንዲሆን ጥሪያችንን እናቀርባለን።
አንድ አማራ ለሁሉም አማራ ፥ ሁሉም አማራ ለአንድ አማራ!
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)
ጥቅምት 16 ቀን 2013 ዓ.ም
ሸዋ፥ አዲስ አበባ፥ ኢትዮጵያ!October 19, 2020 at 2:36 pm #16408In reply to: የፖለቲካ ፓርቲዎች ድምጽ (ኢትዮጵያ ውስጥ የሚነቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች)
AnonymousInactiveከኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) በወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታዎች ላይ የተሰጠ የአቋም መግለጫ
የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ሀገራዊ ምክር ቤት አንደኛ ዓመት ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባዉን ከመስከረም 29 ቀን እስከ ጥቅምት 1 ቀን 2013 ዓ.ም ሲያካሂድ በወቅታዊ የኢትዮጵ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የሰላም መደፍረስ ጉዳዮች ላይ በስፋትና በጥልቀት መክሯል፤ ፓርቲው የሚተገብራቸውን የተለያዩ መመሪያዎች፣ እንዲሁም የ2013-2017 ዓ.ም የፓርቲዉን የአምስት ዓመት ስልታዊ ዕቅድና የ2013 ዓ.ም የአንድ ዓመት ዕቅድ በስፋት እና በጥልቀት በመመርመር ወደተግባር እንዲገቡ በሙሉ ድምጽ ዉሳኔ ካሳለፈ በኋላ የሚከተሉትን የአቋም መግለጫዎች አዉጥቷል።
- ሁሉንም ተግባራት ማከናወን የሚቻለዉ በሀገሪቱ አራቱም ማዕዘኖች ሰላም ሲኖርና የሕግ የበይላነት ሲከበር መሆኑ ለሁሉም ግልጽ ነዉ፤ ነገር ግን በመላ ኢትዮጵያ ሀገሪቱን ለ27 ዓመታት ሲዘርፍና የዜጎችን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በመንፈግ እንደፈለገ ሲያስር ሲገድልና ሲያኮላሽ የነበረዉ ዘረኛዉ ህወሓት ከጠቅላይ አምባገነንቱ ተባሮ መቀሌ ከመሸገበት እና በዶ/ር ዐቢይ አህመድየሚመራዉ “የለዉጡ ቡድን” መንግሥታዊ ስልጣን ከተቆናጠጠበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ ሁነቶች ተከስተዋል። በሀገራችን ኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታ እጅግ ዘግናኝ ግድያዎችና የዘር ማጥፋት ወንጀሎች ነፍስ ባላወቁ እምቡጥ ሕፃናት ሳይቀር በጽንፈኛ ብሔርተኞችና እነሱ በሚደግፏቸዉ ታጣቂ ቡድኖች፤ በኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ (በተለይ በመተከል በተደጋጋሚ) እንዲሁም በደቡብ ክልሎች እስካሁን ድረስ እየተፈጸሙ ነዉ። ዜጎች በገዛ ሀገራቸዉ እንደሁለተኛ ዜጋ እየታዩ ሀብት ንብረታቸዉ እየተዘረፈና እየወደመ፣ ከመኖሪያ ቀያቸዉ እየተፈናቀሉ ነዉ። ኢሕአፓ ከዚህ በፊት ባወጣቸዉ ተደጋጋሚ አቋሞቹ እንደገለጸዉ፥ መንግሥት የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ያሳየዉ ቸልተኝነትና መዘግየት እነዚህ ሁሉ ዘግናኝ ድርጊቶች እንዲፈጸሙ በር እንደከፈተ ያምናል። ስለዚህ ሉዓላዊነታችንንና የሕግ የበላይነትን የማስከበር፣ ሀገራዊ ሰላምን የማረጋገጥ እና የዜጎችን ደህንነነት የመጠበቅ ኃላፊነት ያለባቸዉን የተለያዩ የጸጥታ መዋቅሮች የሚመራዉ መንግሥት ስለሆነ፥ አሁን የጀመረዉን ሕግ የማስከበር ሥራ አጠናክሮ እንዲቀጥል፣ በአጥፊዎችም ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወስድ፣ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በተለይም በቤኒሻንጉልና በኦሮሚያ መሽገው የዜጎችን ህይወት የሚቀጥፉ ሕገ-ወጥ ታጣቂ ቡድኖች ላይ ትጥቅ የማስፈታት እና ወደሕግ የማቅረብ፤ በወንጀል ድርጊት ያልተሳተፉትን አጣርቶ ወደ ሰላማዊ ኑሯቸዉ እንዲመለሱ የማድረግ የማያዳግም እርምጃ እንዲወስድ ይጠይቃል፤ ፓርቲያችን ኢህአፓም ጸረ-ሰላም ኃይሎችን በጽናት ይታገላል።
- በሀገራችን ኢትዮጵያ ላለፉት በርካታ ዓመታት የሚፈጸሙት ዘግናኝ የሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች መጣስ መንስዔው በዋነናት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግሥት ስለመሆኑ በተደጋጋሚ ተገልጧል። ከሁለት ዓመታት በፊት፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አስተዳደርም ሕገ-መንግሥቱን ለማሻሻል በተደጋጋሚ ቃል ገብቶ እንደነበረ ይታወቃል። ነገር ግን ያ ሁሉ ቃል-ኪዳንና ያ ሁሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ወደጎን ተትቶ፥ በፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድርና ውይይት ወቅት ይታያል ተብሎ የነበረው ሕገ-መንግሥት ምንም ዓይነት ማሻሻያም ሆነ ማስተካከያ ሳይደረግበት ከሃያ አምስት ዓመታት በላይ ለሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ሁሉ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ዋነኛው መንስዔ እንደሆነ አለ። ኢሕአፓ ኢትዮጵያ ውስጥ በገዢው ፓርቲና በአጋሮቹ ለሚፈጸሙት ግፎች ሁሉ የመጀመሪያው ተጠያቂ ይህ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግሥትና ይዘቱ ስለሆነ አስቸኳይ ማሻሻያ እንዲደረግበት መንግሥትን ይጠይቃል።
- በተጨማሪም፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር በተደጋጋሚ ይደረጋል እያለ ቃል ሲገባ የነበረው የብሔራዊ ዕርቅና የሀገራዊ መግባባት አጀንዳ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ አጀንዳ እንደሆነ ኢሕአፓ ጽኑ እምነት አለው። በኢትዮጵያ የሚገኙት ሕጋዊና ሰላማዊ የሆኑት የፖለቲካ ኃይሎች በሙሉ የሚሳተፉበት፣ ሀገራዊ መግባባትን ትኩረቱ ያደረገ የፓርቲዎችና የሲቪክ ማኅበራት የጋራ መድረክ አስፈላጊነት ሳይታለም የተፈታ በመሆኑ፥ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መንግሥት ለዚህ አጀንዳ ቅድሚያ ሰጥቶ የውይይትና የድርድር መድረኩ በአፋጣኝ እንዲካሄድ ኢሕአፓ ጥሪውን ያስተላልፋል።
- በያዝነው የ2013 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ይካሄዳል የተባለውና የሚጠበቀው 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ሕጋዊና ሰላማዊ ሆኖ እንዲተገበር ኢሕአፓ ከፍተኛ የሆነ ፍላጎት አለው። በመሆኑም፥ ምርጫ የአንድ ቀን ተግባር ሳይሆን የብዙ ወራትን የመደራጀትና የማደራጀት ተግባራት ከእያንዳንዱ የፖለቲካና የሲቪክ ማኅበር የሚጠይቅ ክንውን መሆኑ ግልጽ ነው። ሆኖም ግን ከ5ኛው ሀገራዊ ምርጫ ማግስት ጀምሮ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መንግሥት ሰላምንና ጸጥታን ማስከበር ተስኖት በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ውስጥ ሁከትና ብጥብጥ እየተከሰተ ይገኛል። በዚህ ያለመረጋጋትና የሰላም እጦት ውስጥ ሆኖ ምርጫን የሚያክል ከፍተኛ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማድረግም አጅግ አዳጋች ነው። በመሆኑም መንግሥት ሁሉም ዜጎች በሕግ ፊት እኩል የሚሆኑበትንና የሚዳኙበትን የፖለቲካ-ኢኮኖሚ ምህዳር አስፍቶ የዜጎችን በሕግ የበላይነት ሥር ብቻ የመምረጥና መመረጥ መብታቸውን እንዲያከናውኑ የማድረግ ኃላፊነቱን በተግባር እንዲወጣ ኢሕአፓ ጥሪውን ያስተላልፋል።
- በየጊዜዉ እያሻቀበ ያለዉ የዋጋ ግሽበትና በኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰት ምክንያት በከፍተኛ ደረጃ ቁጥሩ የጨመረዉ ሥራ አጥነት የዜጎችን የእለት ተእለት ኑሮ በሰቆቃ የተሞላ አድረጓል፤ ከዚህ በተጨማሪ ባሳለፍነዉ 2012 ዓ.ም በተከሰቱ ሰው-ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችም ለከፋ የርሀብ አደጋ ተጋላጭ ሆነዋል። በመሆኑም ኢሕአፓ መንግሥት በረዥም ጊዜ ለዜጎች በተለይም ለወጣቶች በርካታ የሥራ ዕድል መፍጠር የሚችሉ ሀገር በቀል ኢንቨስትመንቶችን እንዲያስፋፋ፣ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ እና ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርን በመቆጣጠር የዋጋ ግሽበቱን ከ2 ዲጂት በታች የሚወርድበትን የኢኮኖሚ አማራጭ እንዲተገበር፣ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸዉም ተገቢዉን ድጋፍ በወቅቱ እንዲያቀርብ በአጽንኦት ይጠይቃል።
- ከደንቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ወደ ትዉልድ ቀያቸዉ ሲመለሱ ታፍነዉ ተወስደዉ እስካሁን ድረስ ደብዛቸዉ የጠፋዉ ተማሪዎች ጉዳይ አሁንም ድረስ የኢሕአፓ የእግር እሳት ነዉ፤ ስለዚህ መንግሥት ልዩ ተኩረት ሰጥቶ ተማሪዎቹ እዉነት በህይወት ካሉ የማስመለስ ሥራ እንዲሠራ፥ አለያም እዉነቱን ለቤተሰቦቻቸዉ፣ ለኢትዮጵያና ለዓለም ሕዝብ እንዲያሳውቅ ኢሕአፓ የዘወትር ጥያቄዉን ዛሬም ያቀርባል።
- ኢሕአፓ ሕብረ-ብሔራዊ ፓርቲ እንደመሆኑ በኢትዮጵያ አንድነትና ሉአላዊነት፣ በሕዝቧ ዉህድ ማንንነት የማይጠራጠሩ፣ በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ትግል ለሚያምኑና በሕጋዊ መንግድ ለተደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሁሉ ኑ! ሀገራችን ከገባችበት ጽንፈኛ የጎሳ እና የጥላቻ ፖለቲካ ቅርቃር በጋራ እንታደጋት፤ ሀገራዊ ብሔራዊ መግባባትን በመፍጠርና የፖቲካ ቁርሾን በማስወገድ ዘላቂ ሰለማና እድገት የሰፈነባት ሀገር እናድርጋት፤ የሚል የአክብሮት ጥሪዉን ያስተላልፋል።
- በሀገር ቤትና በዉጪ ሀገር ለምትገኙ ቀደምት የኢሕአፓ አባላትና መሥራቾች ዘላለማዊ ከሆነዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ህላዌ ጋር በየጊዜዉ እየታደሰ የሚዘልቅ ዘመን ተሸጋሪ ሀሳብ ያነገበዉ ኢሕአፓ ከዉጪ ሀገር ወደ ሀርቤት ከገባ ጊዜ ጀምሮ በሀገሩ ምድር ላይ ትግሉን በጽናትና ቁርጠኝነት እያካሄደ መሆኑን ተገንዝባችሁ ፓርቲያችን ኢሕአፓን በተለያየ መንገድ በመደገፍና በማጠናከር የትግላችሁን ፍሬ ማፍራት እውን ታደርጉ ዘንድ ጥሪዉን ያስተላልፋል።
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!
ኢሕአፓ ለተሻለ ነገ!የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)
ጥቅምት 5 ቀን 2013 ዓ.ም
አዲስ አበባOctober 13, 2020 at 5:14 pm #16337In reply to: የፖለቲካ ፓርቲዎች ድምጽ (ኢትዮጵያ ውስጥ የሚነቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች)
AnonymousInactiveየምንገኝበት የፖለቲካ ቀውስ፣ ፈጣን ፖለቲካዊ መፍትሔ ይፈልጋል!
ከኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ሥራ አስፈፃሚ የተሰጠ መግለጫበኢትዮጵያ ሕዝብ የረዥም ጊዜ መራራ ትግል 2010 ዓ.ም ላይ የመጣው ለውጥ ሕዝቡ ከነበረው ተስፋ በተቃራኒ የመክሸፍ አደጋ አጋጥሞታል።
ከእንግዲህ በሀገራችን እውነተኛ ዴሞክራሲ እውን እንዲሆን፣ የዜጎች ሰብዓዊና ፖለቲካዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን፥ በእርግጠኝነት ደጋግሞ ቃል በመግባት ከፍተኛ የሕዝብ ድጋፍ አግኝቶ የነበረው የዶ/ር ዐቢይ አህመድ መንግሥት ለሕዝብ የገባቸውን ቃሎች ሁሉ በማጠፍ የለየለት አምባገነናዊ መንግሥት መሆን ጀምሯል።
በዚህም ምክንያት የሀገራችንን ሰላምና መረጋጋት ክፉኛ የሚፈታተንና የሀገሪቱን አጠቃላይ ህልውና አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል ከፍተኛ የፖለቲካ ውጥረትና ቀውስ በሀገራችን ተከስቷል። በብዙ ዜጎች ከፍተኛ መስዋዕትነት የተገኘው ለውጥ መክሸፉና ሀገሪቱ ተመልሳ በሌላ አምባገነናዊ ሥርዓት ስር መውደቋ እጅግ ልብ የሚሰብር አሳዛኝ ክስተት ቢሆንም፥ የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ሀገራችንን ከውድቀት ለማዳን ዛሬም ዕድሉ በእጃችን ነው ብሎ ያምናል።
ይህ ከውድቀት የመዳን እድል እውን ሊሆን የሚችለውም በአንድ ገዥ ፓርቲ የበላይነትና ፈላጭ ቆራጭነት፣ ወይንም ባለፉት 27 ዓመታት ያየነው ዓይነት ውጤቱ አስቀድሞ የሚታወቅ የይስሙላ ምርጫ በማካሄድ አይደለም።
በኢዴፓ እምነት ከዚህ አሳሳቢ የህልውና አደጋ ወጥተን ወደ ተሻለ ሁኔታ ለመሸጋገር ቢያንስ የሚከተሉት አራት ተጨባጭ እርምጃዎች ሊወሰዱ ይገባል ብለን እናምናለን፤
- በሀገራችን የሕግ የበላይነት የመጥፋት ችግር እጅግ አሳሳቢ ወደ ሆነ የከፋ ደረጃ እየተሸጋገረ ነው። በኢዴፓ አመራር በአቶ ልደቱ አያሌው እና በሌሎችም የፖለቲካ ሰዎች ላይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሲሆን እንደታየው ሰዎች በፈጠራ ክስ ያለአግባብ የሚንገላቱበትና የፍርድ ቤቶች ውሳኔና ትዕዛዝ የማይከበርበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ያለ ፍርድ ቤት ነፃነት በአንድ ሀገር ላይ የሕግ የበላይነት ሊከበር ስለማይችል ፍርድ ቤቶችን ለፖለቲካ ጉዳይ ለመጠቀም፤ እና የፍርድ ቤቶችን ውሳኔ በመጣስ እየተፈፀመ ያለው ሕገ-ወጥ ድርጊት በአስቸኳይ መቆም አለበት።
- በአሁኑ ወቅት የኢዴፓ/አብሮነት፣ የኦፌኮ፣ የኦነግና የባልደራስ ከፍተኛ ዓመራሮች፣ እንዲሁም በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች /በተለይም በኦሮሚያ ክልል/ ከፖለቲካ ጋር በተያያዘ በእስር ላይ ስለሚገኙ በሀገራችን ከፍተኛ የፖለቲካ ውጥረት ነግሷል። ይህ አሳሳቢ ውጥረት ወደ ሌላ አሳሳቢ ደረጃ ከመሸጋገሩ በፊት ሁሉም ከፖለቲካ ጉዳይ ጋር በተያያዘ በእስር ላይ የሚገኙ ዜጎች ያለምንም ቅድመ-ሁኔታ በአስቸኳይ መፈታት አለባቸው።
- ሀገራችን በዚህ ዓይነት የፖለቲካ ውጥረት ውስጥ ሆና በፍፁም ሀገራዊ ምርጫ ለማካሄድ መታሰብ የለበትም። ከአሁን ጀምሮ እስከሚቀጥለው ሀገራዊ ምርጫ ድረስ ሀገሪቱ እንዴት ትተዳደር? ምርጫው ከመካሄዱ በፊት በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ ምን ዓይነት ውይይት እና ድርድር ይካሄድ? ከክልልነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ በደቡቡ የሀገራችን ክፍል ያለው የፖለቲካ ውጥረት እንዴት ይርገብ? ሀገሪቱ ቋሚ መንግሥት እስከሚኖራት ድረስ የኢኮኖሚ ደህንነቷን የሚያስጠብቅ ምን ዓይነት እርምጃ ሊወሰድ ይገባል? ያልለየለትን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭት በተመለከተ ምን ልናደርግ ይገባል? በሚሉትና በመሳሰሉ መሠረታዊ ጥያቄዎች ዙሪያ መፍትሄ ማመንጨት የሚያስችል አንድ ሁሉን አቀፍ የውይይትና የድርድር ሂደት /national dialogue / በአስቸኳይ መጀመር አለበት።
- በአሁኑ ወቅት በፌደራሉ መንግሥትና በትግራይ ክልል መካከል እየታየ ያለው ተገቢ ያልሆነና አሳሳቢ ፍጥጫ በአስቸኳይ መቆም አለበት። ጉዳዩ ከሀገሪቱ ሰላምና አንድነት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ እንደምታ ያለው እጅግ አሳሳቢ ጉዳይ በመሆኑ ያለምንም ቅድመ-ሁኔታ በውይይትና በድርድር መፈታት አለበት።
በአጠቃላይ እነዚህ መሠረታዊ ጥያቄዎች በአግባቡ መመለስ ሳይችሉ ከቀሩና በሀገሪቱ ላይ የሚታየው ውጥረት የበለጠ ተባብሶ በዜጎችና በሀገር ላይ ለሚደርሰው ለማንኛውም የከፋ ጉዳት ዋናው ተጠያቂ ብልፅግና ፓርቲ መሆኑን እንገልፃለን። ከማንም በላይ የጉዳዩ እና የሀገሪቱ ባለቤት ሕዝቡ ነውና ከፍ ሲል የዘረዘርናቸው ጥያቄዎች በአስቸኳይ ተገቢ ምላሽ አግኝተው ሀገራችን ከውድቀት እንድትድን ሁሉም ሀገር ወዳድ ዜጋ በብልፅግና ፓርቲ ላይ ሕጋዊ እና ሰላማዊ ተፅዕኖ እንዲያደርግ ኢዴፓ ጥሪውን ያቀርባል።
የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ
ጥቅምት 3 ቀን 2013 ዓ.ም
አዲስ አበባ -
AuthorSearch Results