Search Results for 'ኦነግ'

Home Forums Search Search Results for 'ኦነግ'

Viewing 15 results - 1 through 15 (of 27 total)
  • Author
    Search Results
  • Anonymous
    Inactive

    ሕዝባችን ከመቼውም ጊዜ በላይ የተጋረጠበትን መንግሥታዊ ሽብር በተደራጀ አግባብ እንዲከላከል ጥሪ እናቀርባለን!
    የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)

    ድርጅታችን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በአንድ በኩል በሕዝባችን ላይ ለበርካታ አስርተ ዓመታት የቀጠለውን ሕግና መዋቅር ሠራሽ የፖለቲካ ሸፍጥ በዘላቂነት ለመቅረፍ፣ በሌላ በኩል ሕዝባችንና ሀገራችን ከተጋረጠባቸው የኅልውና አደጋዎች ለመታደግ በሚደረገው ሀገራዊ የበጎ ኃይሎች ጥምረት አካል በመሆንና በትጋት በመሥራት ላይ የሚገኝ መሆኑን በሀቅ የሚፈርድ ሁሉ የሚረዳው እውነታ ነው።

    ምንም እንኳን ትጋታችን ለማንም አካል በመታያነት የቀረበ ባይሆንም፥ እጅግ ፈታኝ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ እንኳ ሆነን “የተሻለ ነገ” ሊመጣ ይችላል የሚል እሳቤን አንግበን እዚህ ደርሰናል።

    ቀደም ሲል በተደጋጋሚ ለመንግሥት እንዳሳሰብነው መሠረታዊ የሆኑ የለውጥ ሀሳቦችን መሬት ለማስረገጥና የተሳሳተውን የማደራጃ ትርክት፣ የተዛነፈውን መዋቅራዊና ሥርዓታዊ ማእቀፍ በማስተካከል ሕዝብን ለዘላቂ ሰላምና ሥልጣን ለማብቃት የበኩላችንን ያልተቋረጠ ጥረት ከማድረግ ጎን ለጎን በተለይ ሀገራችንና ማዕከላዊ ሥርዓቱ እንዳይፈርሱ ለማድረግ በተደረጉ ጥረቶች ሁሉ አብንና የአማራ ሕዝብ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል።

    ሆኖም፦

    1/ መንግሥታዊ ሽብሩን በማባባስ፣ በመደገፍ እና ትእዛዝ በመስጠት ጭምር የሚሳተፉት የሀገራችን ጠቅላይ ሚንስቴርና የሚመሩት የኦሮሞ ብልጽግና ክፍል መንግሥታዊ መዋቅርንና የሀገር ሀብትን በመጠቀም የአማራን ሕዝብ የማሸበር ተግባር አጠናክረው ቀጥለዋል። ሕዝባችንን ለማሸበር የተከፈተው መጠነ-ሰፊ የዘር ፍጅት በመንግሥት መዋቅር በቀጥታ የሚደገፍና የሚመራ መሆኑን አብን ያምናል። ለዚህም የሚከተሉትን ነጥቦች በጉልህ ማሳያነት ማቅረብ ይቻላል።

    ሀ/ በአማራ ሕዝብ ላይ የተቀናጁ የጅምላ ፍጅት ጥቃቶችን የከፈተው በተለምዶ “ኦነግ ሸኔ” ተብሎ በጠቅላይ ሚንስትሩ የሚጠራው አካል ከመነሻው ከነትጥቁ ወደ ሀገር ቤት የገባበትን አሻጥር፤

    ለ/ ከዚያ ቀደም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጭምር እንደገለጹት ከተጠቀሰው ድርጅት ጋር የነበራቸው መረጃን የመለዋወጥ ድብቅ ግንኙነት የሚታወቅ በመሆኑ ከልጅነት እስከ እውቀት አጋር የሆናቸውን ድርጅት አሁንም በልዩ ስልት የማደራጀት፣ የመደገፍ እና የመንከባከብ ሚናቸውን እየተጫወቱ እንደሆነ ንቅናቄያችን በጽኑ ያምናል።

    ሐ/ የ“ኦነግ ሸኔ” ኮር ስትራቴጂክ አመራር በመሀል አዲስ አበባ ውስጥ ተቀምጦ እየመራ ባንኮችን ጭምር በጠራራ ፀሐይ በመዝረፍ ኃይል እንዲያጎለብት የተፈቀደበትና የተመቻቸበት አግባብ መኖሩ፤

    መ/ በአማራ ሕዝብ ላይ እየተፈፀመ ያለውን ተደጋጋሚ የዘር ጥቃት ማስቆም ይቅርና ጅምላ ፍጅቱ በሀገር ደረጃ ለሀዘን መግለጫ እንኳ እንዳይበቃ የተደረገ ከመሆኑም በላይ በሀዘን ድንኳናችን ላይ ቀይ ምንጣፍ አንጥፈው ሕንፃ እና አበባ የሚመርቁበት አስደንጋጭ ማኅበራዊ ስላቅ ሳይቋረጥ መቀጠሉ፤

    ሠ/ በአማራ ሕዝብ ላይ የተከፈተው ዘር-ተኮር ጥቃት የታቀደና የተቀናጀ ሲሆን፥ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጭምር የዘር ማጥፍት ወንጀል ለማስፈጸም አመላካች የሆኑ የመግቢያ ንግግሮችን በይፋ ሲያሰሙ መቆይታቸውና ለዚህም ምንም ዓይነት አስተዳደራዊም ይሁን ፖለቲካዊ እርምት አለመሰጠቱ፤

    ጠቅላይ ሚንስትሩና የሚመሩት መንግሥት በዚህ የአማራን ሕዝብ የማሸበርና የዘር ፍጅት እንቅስቃሴ ውስጥ ሚና አላቸው ብሎ ንቅናቄያችን ለማመን ተገዷል።

    2/ የአማራ ክልል መንግሥት ከተፈጥሯዊውና መደበኛው የታዛዥነት መንፈስ አለመውጣቱ፣ ደንታ ቢስነቱና አቅመ ቢስነቱም እየበረቱበት መሆኑ ሕዝባችንን አቻ ለማይገኝለት ማኅበራዊ ውርደት ያበቃ በመሆኑ፤

    አብን የአማራ ሕዝብ ትግል ከተለመደው አካሄድ ተላቆ ኅልውናውን የመታደግና የማስከበር የተቀናጀና የተጠናከረ የትግል ምእራፍ ውስጥ መግባት አለበት የሚል ድምዳሜ ደርሷል። ትግሉንም ለመምራት ንቅናቄያችን ከፊት ይሰለፋል።

    መላው የአማራ ሕዝብም የተከፈተበትን አጠቃላይ የኅልውና አደጋ በመገንዘብ እና ለደኅንነቱ የሚያስብለት መንግሥት እንደሌለው በመረዳት ራሱን የመከላከል ተፈጥሯዊ መብቱን እንዲሠራበት አብን በአጽንዖት ያሳስባል። ሕዝባችንም በዚህ ፈታኝ ወቅትም ወዳጅ መስለው በጠላትነት በቆሙ ቡድኖችና ግለሰቦች ግፊት ፈተና ላይ እንዲወድቅ የሚፈለገውን አንድነቱን አጠናክሮ እንዲጠብቅ እናሳስባለን።

    በሀገር ውስጥም ይሁን በውጭ ሀገራት የምትገኙ ወገን ወዳድ ኢትዮጵያውያን፥ በመሠረቱ ያንዣበበው አደጋ በአማራ ሕዝብ ላይ ብቻ ተወስኖ የሚቆም አለመሆኑን በመገንዘብ በአማራ ሕዝብ ላይ በተቀናጀ ሁኔታ እየተፈፀመ ያለውን የዘር ፍጅት ጥቃት እንድታወግዙና የመልሶ ማቋቋም ሥራዎችን እንድታግዙ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።

    በተለያዩ ስምሪቶች በቅንነት ሀገራችሁን የደገፋችሁ መስሏችሁ ለሥርዓቱ እገዛ የምታደርጉ ወገኖች ሂደቱን በመገምገም ጥያቄ እንድታነሱና ከተገፉ ወገኖች ጎን እንደትሰለፉ ጥሪ እናቀርባለን።

    በሀገር ውስጥም ይሁን በውጭ ሀገራት የምትኖሩ የአማራ ተወላጆች በእያንዳንዱ ቀን የአማራ ሕዝብ ደም እንደጅረት የሚፈስበት ሀገር መሆኑን በመረዳት፥ አማራው ለአጠቃላይ የኅልውና አደጋ የተጋለጠ መሆኑን በመቀበልና መሠረተ-ቢስና መናኛ ከሆኑና የሞራልና የታሪክ ተጠያቂነት ከሚያስከትሉ ልማዳዊ የፖለቲካ ዘይቤዎች በአስቸኳይ በመላቀቅ ሰብዓዊ፣ ወገናዊና ሀቀኛ የሆነ የፖለቲካ አቋም በመውሰድ ሕዝብ የመታደግ ድርሻችሁን እንድትወጡ የሚል ታሪካዊ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።

    ኅልውናችንን በትግላችን እናስከበራለን!
    እጣፋንታችንን በራሳችን እጆች እንጽፋለን!
    የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)

    የፖለቲካ ፓርቲዎች ድምጽ (ኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች)

    ሕዝባችን ከመቼውም ጊዜ በላይ የተጋረጠበትን መንግሥታዊ ሽብር በተደራጀ አግባብ እንዲከላከል ጥሪ እናቀርባለን

    Anonymous
    Inactive

    ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የተሰጠ ወቅታዊ መግለጫ

    የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንና ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር አዲስ አበባ ከተማን ከማንኛውም የፀጥታ ስጋት የፀዳች ለማድረግ ባካሄደው የአንድ ሳምንት የተቀናጀ የጋራ የፀጥታ ኦፕሬሽን ውጤት ማስመዝገቡን ገለፀ።

    ኮሚሽኑ የፀጥታ ሥራውን በብቃት ለማከናወን የሚያስችል ዕቅድ አዘጋጅቶ የጋራ በማድረግ በተግባር ምዕራፉ የመጀመሪያ ሳምንት ባካሄደው ሁለንተናዊ ሰላምና ደህንነትን የማረጋገጥ ሂደት ባከናወናቸው ጠንካራ የወንጀል መከላከል ተግባራት

    1. በተደራጀ መንገድ ታቅደው የሚፈፀሙ የዘረፋና የግድያ ወንጀሎች፣
    2. የግል ትራንስፖርት አሽከርካሪዎች ላይ የሚፈፀም አፈና እና ግድያ፣
    3. የተሽከርካሪ ስርቆት፣
    4. ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ እና ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ወንጀሎችን መቀነስ መቻሉን ገልጿል።

    ኮሚሽኑ እንደገለፀው በእነዚህ ወንጀሎች የተጠረጠሩ 359 ተጠረጣሪዎች ተከታትሎ በሕግ ቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝና ከዚህ ውስጥ

    ትግራይ ላይ በተፈፀመው የጁንታው ጥቃት የተሳተፉና በተለያየ መንገድ አምልጠው ወደ አዲስ አበባ ከተማ በመግባት በተለያየ የወንጀል ተገባር ሲሳተፉ በተገኘ የሕዝብ ጥቆማ 135 ተጠርጣሪዎች እንዲሁም ከዚሁ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ሰባት የኦነግ ሸኔ አባላት በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ በማጣራት ላይ መሆኑን ኮሚሽኑ ገልጿል።

    ኮሚሽኑ ኅብረተሰቡን ከጎኑ በማሰለፍ በተቀናጀ የጋራ ኦፕሬሽን በተለያዩ በወንጀል የተጠረጠሩ የነፍስ ወከፍና የቡድን ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያዎች፣ የሀገር ውስጥ ሀሰተኛ ገንዘብ እና የተለያዩ የውጭ ሀገራት ገንዘቦች፣ በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ ገብተዋል ተብለው የተጠረጠሩ ተሽከርካሪዎች፣ በዘረፋና በግድያ ከተወሰዱ 10 ራይድ ተሽከርካሪዎች ስምንቱ እንደተያዙና የሁለቱ አካላቸው እንደተፈታ ፖሊስ ደርሶበት በቁጥጥር ስር አውሎ በዚህ ወንጀል የተጠረጠሩ 11 ግለሰቦችን ይዞ ምርመራ እየተጣራባቸው መሆኑን አመልክቷል።

    ኮሚሽኑ ባካሄደው የጋራ ኦፕሬሽን የኑሮ ውድነት ለማባባስ እና የንግድ ስር-ዓቱን ለማዛባት የሚንቀሳቀሱ አካላትን በዚህ ኦፕሬሽን በቀጥጥር ስር አውሎ ከእነሱም ብዛት ያላቸው ሸቀጦችና ቁሳቁሶችን በቁጥጥር ስር አውሏል።

    በሌላ በኩል ኮሚሽኑ ባካሄደው በዚህ የጋራ ኦፕሬሽን በቁጥጥር ስር ካዋላቸው ንብረቶች መካከል በዝርፊያ የተወሰደ አንድ ሲኖ-ትራክ ከባድ መኪናንና ከግለሰቦች የተነጠቁና ከድርጅቶች የተዘረፉ ባርካታ ተንቀሳቃሽ ስልኮችን በመያዝ ለባለ ንብረቶቹ ተመላሽ ማድረግ የተቻለ ሲሆን ሐሰተኛ መታወቂያ በመቀያየርና በመጠቀም በተለያዩ የተሽከርካሪ መሸጫ ድርጅቶች እየተቀጠሩ ተሽከርካሪዎችን በሌሎች በማሰረቅ የተጠረጠሩ አራት ግለሰቦች መያዛቸውንም ጨምሮ ገልጿል።

    በመጨረሻም ኮሚሽኑ ይህ ከጅምሩ ውጤት ያስመዘገበ የተቀናጀ የጋራ የፀጥታ ኦፕሬሽን ወደ ፊትም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ገልፆ የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ደህንነት አስተማማኝና ዘላቂ ይሆን ዘንድ የሰላሙ ባለቤት የሆነው መላው የከተማው ህዝብ ለሁከትና ብጥብጥ የሚያነሳሱ መረጃዎችን ባለመቀበልና ሀሰተኛ መረጃዎችንም ባለመጋራት እንዲሁም ለፖሊስ ዓይንና ጆሮ ሆኖ ለፀጥታ ስጋት የሆኑ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙት በፍጥነት እንደተለመደው መረጃ በመስጠት እንዲተባበር እየጠየቀ ለዚህ ኦፕሬሽን መሳካት የከተማው ህዝብ ላደረገው ከፍተኛ አሰተዋጽኦ ኮሚሽኑ ሌሎች የፀጥታ ሀይሎችንም በመወከል የላቀ ምስጋና ያቀርባል።

    የኢፌዲሪ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን
    መጋቢት 18 ቀን 2013 ዓ.ም

    የኢፌዲሪ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን

    Anonymous
    Inactive

    በብልፅግና ሰልፎች ላይ ፓርቲዎች የሚመሩባቸው ሥነ ምግባሮች ተጥሰዋል
    ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰጠ መግለጫ

    ጥር 25 ቀን 2013 ዓ.ም. በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች ለብልፅግና ፓርቲ ድጋፍ ለማሳየት የተለያዩ ሰልፎች መካሄዳቸው ይታወቃል። እነዚህን ሰልፎች ተከትሎ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) “ፓርቲያችን ያለአግባብ ተወንጅሏል፤ ይህም ፓርቲዎች የፈረሙትን የጋራ የሥነ ምግባር ደንብ የጣሰ ነው” ሲል አቤቱታውን ለቦርዱ አቅርቧል። ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም ከአቤቱታው በተጨማሪ በዕለቱ የተደረጉ የተለያዩ ሰልፎችን በሚዲያ ክትትል ክፍሉ አማካኝነት ክትትል በማድረግ በአሜሪካ ድምጽ፣ በዋልታ፣ በፋና፣ በኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ እንዲሁም በእነዚሁ ሚዲያዎች የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች በቀጥታ የተላለፉ መልእክቶችን በማየት፦

    • ሠልፎቹ በዋልታ ቴሌቪዥን እና በኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ በቀጥታ መተላለፋቸውን እንዲሁም የመንግሥት አመራር አካላት፣ የብልፅግና ፓርቲ አመራሮች እና ደጋፊዎች መሳተፋቸውን ተረድቷል፤
    • ከሚዲያዎቹ በቀጥታ ከመተላለፉም በተጨማሪ የተለያዩ የመንግሥት አመራር አባላት በሰልፎቹ ላይ ያደረጓቸውን ንግግሮች ተመልክቷል፤
    • በሰልፎቹ የተለያዩ መፈክሮች፣ በተወሰኑ የመንግሥት የዞን፣ የከተማ አስተዳድር አመራር አካላት እና ብልፅግናና ፓርቲ ኃላፊዎች ንግግሮች በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተመዘገቡ እና የምርጫ ምልክቶቻቸውን የመረጡ ፓርቲዎች በአሉታዊ መልኩ መነሳታቸውን ተገንዝቧል።

    እነዚህ ሰልፎች ላይ የተነሱ ንግግሮች እና መፈክሮች በሕጋዊነት ተመዝግበው፣ በፖለቲካ ፓርቲነት የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎችን ማለትም አማራ ብሔራዊ ንቅናቄባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ እና የኦሮሞ ነጻነት ግንባር በአመፃ ተግባር በመሳተፍ ከምርጫ ቦርድ ከተሰረዘው ጁንታ በማለት ከሚጠሩ ህወሓት ፓርቲ ጋር አንድ በማድረግ፣ የኢትዮጵያ ጠላት ናቸው ብሎ በመፈረጅ እና ሕገ ወጥ ናቸው በማለት የምርጫ፣ ፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና ሥነ ምግባር ሕግ 1162/2011 ላይ ያሉ ድንጋጌዎችን ጥሰዋል።

    ቦርዱ ሰልፎቹ ላይ የተንጸባረቁት ንግግሮች እና መፈክሮች በአዋጁ አንቀጽ 132 ንዑስ 2(ሀ) ላይ የተጠቀሰውን ስም የሚያጠፋ ንግግርን ክልከላ ድንጋጌ አንዲሁም በዚሁ ሕግ አንቀጽ 143 (2) ላይ የተጠቀሰውን ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ሀሳባቸውን በነጻነት እንዳያሰራጩ ስጋት እና ፍርሀት የመፍጠር የሥነ ምግባር ጥሰት ፈጽሞ አግኝቶታል። ከዚህም በተጨማሪ ከላይ ስማቸው የተጠቀሱት የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ገዥው ፓርቲ በጋራ ተስማምተው በፈረሙት የቃልኪዳን ሰነድ አንቀጽ 8 ንዑስ አንቀጽ 1 ላይ የተጠቀሰውን “የሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በየትኛውም ጉዳይ ላይ ሊኖር የሚችል የዓላማ፣ የሃሳብ ወይም የዘር ልዩነትን፣ ወይም ሌላ ምክንያት መሠረት በማድረግ የሌሎች ፓርቲዎችን መብቶች የሚፃረሩ ወይም የሚያጣብቡ ድርጊቶችን ከመፈፀም የመቆጠብ ግዴታ አለባቸው” የሚለውን አንቀጽ የሚጥስ ተግባር ነው።

    ይህ ተግባር በተለይ ቦርዱ የመጨረሻ የጊዜ ሰሌዳ አውጥቶ የምርጫ ተግባራት በይፋ መፈጸም ከጀመረ በኋላ በምንገኝበት የምርጫ ወቅት መከሰቱ በምርጫ ውድድር ላይ ፓርቲዎች በእኩልነት የመወዳደር መብታቸውን ችግር ላይ የሚጥል በመሆኑ ቦርዱን በእጅጉ አሳስቦታል። በመሆኑም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በየደረጃው ያሉ የገዥው ፓርቲ አመራሮች እና በየአስተዳደር እርከኑ ያሉ የመንግሥት ኃላፊዎች በተመሳሳይ ተግባራት ከመሳተፍ እንዲቆጠቡ ያሳውቃል።

    ለወደፊትም በተመሳሳይ በምርጫ፣ ፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና ሥነ ምግባር ሕግ 1162/2011 እና ተያያዥ መመሪያዎች መሠረት የፓርቲዎች የቅስቀሳ የንግግር እና ሌሎች ለሕዝብ የሚያሰራጯቸውን መልዕክቶች ላይ ክትትል በማድረግ አስፈላጊውን እስከእጩ መሠረዝ የሚደርስ አስተዳደራዊ እርምጃ ሊወስድ እንደሚችል ያሳውቃል።

    የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
    ጥር 26 ቀን 2013 ዓ.ም.

    በብልፅግና ሰልፎች ላይ ፓርቲዎች የሚመሩባቸው ሥነ ምግባሮች ተጥሰዋል ― ምርጫ ቦርድ

    Anonymous
    Inactive

    የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የአመራሮች ክፍፍልን አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰጠ መግለጫ

    የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በተቋቋመበት አዋጅ 1133/2011 በምርጫ በፖለቲካ ፓርቲዎች እና በሥነ ምግባር አዋጅ 1162/2011 በተሰጠው ስልጣን መሠረት ፖለቲካ ፓርቲዎች ድጋፍ እና ቁጥጥር የሚያደርግ ተቋም ነው። በዚህም መሠረት በኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ፓርቲ አመራሮች መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት ሕጋዊ እና ተደጋጋሚ ጥረቶችን ሲያደርግ እንደነበር ይታወሳል።

    በዚህም መሠረት፦

    1. የፓርቲው የተወሰኑ የሥራ አስፈጻሚ አባላት ነሐሴ 01 ቀን 2012 ዓ.ም. በተጻፈ እና በድርጅቱ ምክትል ሊቀ-መንበር በተፈረመ ደብዳቤ የድርጅቱን ሊቀ-መንበር መታገዳቸውን ለቦርዱ አሳውቀው እንደነበር፤ ከዚህም በተጨማሪ የድርጅቱ አመራር ላይ ተከታታይ አቤቱታዎች አስገብተው እንደነበር ይታወሳል። በሌላ በኩል የድርጅቱ ሊቀ-መንበር መስከረም 02 ቀን 2013 ዓ.ም. ድርጅቱ ብሔራዊ ምክር ቤት ስብሰባ አድርጎ የፓርቲውን ምክትል ሊቀ-መንበር፣ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላትን እንዲሁም የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት እስከሚቀጥለው የድርጅቱ ጠቅላላ ጉባዔ ድረስ ከኃላፊነታቸው ታግደው እንዲቆዩ እንደወሰነ ለቦርዱ አሳውቀዋል።
    2. ፖለቲካ ፓርቲ አባላት መካከል አለመግባባት ሲከሰት እና ለቦርዱ አቤቱታ ሲቀርብለት በአዋጅ ቁጥር 1162/11 አንቀፅ 74 ንዑስ አንቀፅ 6 መሠረት ጉዳዩን ተመልክቶ የውሳኔ ሃሳብ የሚያቀርብ የባለሙያዎች ጉባዔ ለማቋቋም በተሰጠው ስልጣን መሠረት በማድረግ የሁለቱንም ቡድኖች ደብዳቤዎች እና አቤቱታዎች፣ እንዲሁም የውስጥ ሕጎች የሚያይ የባለሞያዎች ኮሚቴ ለማቋቋም ውሳኔ አሳልፎ እንደነበርም ይታወሳል። በዚህም መሠረት በእነ አቶ አራርሶ በኩል ባለሞያ ቢመድቡም፥ በእነ አቶ ዳውድ በኩል ባለሞያ ለመመደብ ፍቃደኛ ካለመሆናቸውም በላይ የፓርቲው የውስጥ ደንብ መሠረት መጠናቀቅ ያለበት ጉዳይ ነው በማለት መልስ በመስጠታቸው የባለሙያዎች ጉባዔ ማቋቋም ሳይሳካ ቀርቷል።
    3. በኦነግ አመራር መካከል የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት የተደረገው የመጀመሪያው የቦርዱ ጥረት ባለመሳካቱ ጉዳዩን ከባለሞያዎች ጉባዔ ይልቅ በራሱ ሊያየው ተገድዷል። በዚህም መሠረት ከሁለቱም ወገን የገቡትን እገዳዎች በማየት እና የገቡ ሰነዶችን በመመርመር፥ እንዲሁም ከሁለቱም ቡድን አመራሮች ጋር እንዲሁም ከሥነ ሥርዓት እና ቁጥጥር ኮሚቴ አመራር አባላት ጋር ሰፊ ውይይት አድርጓል። በውይይቱም ወቅት ፓርቲው አመራር ቀውስ ውስጥ እንደገባ፣ ለአባላቱ አመራር መስጠት የሚችልበት ሁኔታ ላይ እንዳልሆነ፣ በተለይም ደግሞ ሁለቱም ቡድኖች ያቀረቧቸው እገዳዎች ሕጋዊ እንዳልሆኑ ቦርዱ ወስኗል። በዚህም መሠረት የሁለቱም ወገን እገዳ የቀረበባቸው አባላት በነበራችው ሕጋዊ ኃላፊነት ላይ እንደሚቆዩ ወሰነ።

    በተጨማሪም ሁለቱም አካላት ሕጋዊ ሂደቱ የተሟላ ሰነድ ባለማቅረባቸው፣ ፓርቲው ያለበት የአመራር ቀውስ ለመፍታት አለመቻላቸውን በመረዳት ቦርዱ የአመራር መከፋፈሉን  ጠቅላላ ጉባዔ በማከናወን የፓርቲው አባላት መሪዎቻቸውን እንዲመርጡ ታኅሣሥ 08 ቀን 2013 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ ከመወሰኑም በተጨማሪ፥ የጠቅላላ ጉባዔውን ለማመቻቸት ኃላፊነቱንም እንደሚወስድ አሳውቆ እንደነበር ይታወሳል።

    1. ከላይ በተጠቀሰው ውሳኔ መሠረት ለሁለቱም አመራር ቡድኖች ቦርዱ ውሳኔ በደብዳቤ ደርሷቸው የመጀመሪያውን ውይይት በቦርዱ አመቻችነት በጋራ ለማከናወን የመጀመሪያውን የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ አባላት ጥሪ ቢደረግላቸውም በድርጅቱ ምክትል ሊቀመንበር አቶ አራርሶ የሚመራው የሥራ አስፈጻሚ ቡድን ቦርዱ በጠራው ስብሰባ ላይ ሲገኝ፥ በአቶ ዳውድ የሚመራው ቡድን ግን “ቦርዱ ይህንን የማመቻቸት ሕጋዊ ሚና የለውም” በማለት በውይይቱ ላይ አልገኝም በማለታቸው በቦርዱ የተደረገው ጥረት አሁንም ሊሳካ አልቻለም።
    2. ይህ ሂደት በዚህ ላይ እንዳለ ሁለቱም ወገኖች የተለያዩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን ሚመለከቱ ማመልከቻዎችን ለቦርዱ ማቅረባቸውን ቀጥለዋል።
    3. የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጥር 19 ቀን 2013 ዓ.ም. ባደረገው የቦርድ አመራር አባላት ስብሰባ በኦነግ ሥራ አስፈጻሚ መከፈልን አስመልክቶ እስከአሁን የተደረጉ ጥረቶችን እና ለመፍታት የወሰዳቸውን እርምጃዎች በዝርዝር መርምሯል። በዚህም መሠረት ቦርዱ እጁ ላይ ባሉት የሕግ እና የአስተዳደር መሣሪያዎች በመጠቀም ሊያግዝ የሚችልበት ተጨማሪ አሠራር አለመኖሩን ተረድቷል።
    4. በዚህም መሠረት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር አባላት፣ የተለያዩ የድርጅቱ መዋቅሮች እና አመራሮች ለችግሩ መፍቻ ሊሆን የሚችለውን ጠቅላላ ጉባዔ እንዲያደርጉ ቦርዱ ማሳሰብ እንደሚገባው ወስኗል። በመሆኑም ፓርቲው በመሀከሉ ያለውን አለመግባባት በሥራ አስፈጻሚ አመራሮቹ ሊፈታ ባለመቻሉ የተለያዩ የድርጅቱ መዋቅሮች እና አባላት አውቀው ጠቅላላ ጉባዔ እነዲከናወን የሚያደርጉባቸውን ማንኛውንም መንገዶች እንዲጠቀሙ ቦርዱ በጥብቅ ያሳስባል።

    የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
    ጥር 27 ቀን 2013 ዓ.ም.

    የኦሮሞ ነፃነት ግንባር የአመራሮች ክፍፍልን አስመልክቶ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰጠ መግለጫ

    Anonymous
    Inactive

    የጥላቻና ዘር ፍጅት ቅስቀሳ በውጤት ደረጃ ሀገርና ሕዝብን የህልውና አደጋ ላይ ይጥላል
    ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የተሰጠ መግለጫ!

    ድርጅታችን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ በሀገራችን ውስጥ እስካሁን የተካደው ኢትዮጵያዊ ዜግነት ተገቢውን እውቅና እንዲያገኝ፣ ዜግነት የፖለቲካችን ማዕከል እንዲሆን የሚያስችል መሠረታዊ የትርክት ለውጥና የመዋቅር ክለሳ እንዲደረግ በርካታ ጥሪዎችን ሲያደርግ ቆይቷል። ለሀገራችችን የፖለቲካ ምስቅልቅል (crisis) መነሻ የሆነው የጥላቻ ትርክት በሕገ-መንግሥትና በመዋቅሮች መስረፅ ምክንያት መሆናቸውን በመገንዘብ፥ ሕዝባችን ከባድ መስዋዕትነትን የጠየቀ የለውጥ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ቆይቷል። በዚህም ቀላል የማይባሉ እመርታዎችን ያስመዘገበ ቢሆንም፥ በዋናነት የአፋኙ ሥርዓት አካልና ወራሽ የሆነ ስብስብ የሕዝባችንን ቅን ልቦና ባጎደፈ መልኩ የጽንፈኝነት ባህሪውን ለጊዜው ደብቆና ስሙን ብቻ ቀይሮ የሕዝባችንን የለውጥ ሂደት አግቶት ይገኛል።

    የአማራ ሕዝብና የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በትሕነግ ላይ የነበረው አቋም የተፈተሸ፣ የጠራና የነጠረ ስለመሆኑ አስረጅ አያስፈልገውም። አብን ከሁለት ዓመታት በፊት ትሕነግ ሽብርተኛ ድርጅት መሆኑን በመጥቀስ ከሰላማዊ የፖለቲካ ፖርቲዎች ዝርዝር እንዲሰረዝና ጉዳዩ በሕግ የበላይነት ማዕቀፍ እንዲታይ ማሳሰቡ ይታወሳል።  በወቅቱ መንግሥት ከትሕነግ ጋር አብሮ በአንድ ጥምረት ውስጥ ሆኖ የሚሠራበት ነበር። አብዛኛው የሀገራችን የፖለቲካ ኃይሎች በአብን መግለጫ ቢያንስ ተደናግጠው እንደነበር የሚታወስ ሃቅ ነው።

    አብን የአማራ ሕዝብ ሁለንተናዊ ንቅናቄ አካል እንደመሆኑ መጠን ዝቅተኛው የፖለቲካ ስምሪቱ ሀገራችን በጽንፈኛ ኃይሎች ቅንጅት እጅ ዳግም እንዳትወድቅ መከላከል ነው። የኮሮናቫይረስ (COVID-19) ወረርሽኝ ስጋትን ተከትሎ በሀገራዊ የምርጫ መርኃግብር ላይ በታየው የፖለቲካ ችግር ወቅት የወሰድነው አቋም አብን ኢትዮጵያን በተመለከተ ላለው የማያወላዳ አቋም ዓይነተኛ ጠቋሚ መሆኑ አያከራክርም።

    ድርጅታችን አብን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግር ሊፈታ የሚችለው መሠረታዊ ለውጦችን በማድረግ እንጅ በስምና በቅብ ለውጥ ሊሆን እንደማይችል በመረዳት ሀገራችን በሽግግር መንግሥት ምሥረታ ሳይሆን በሽግግር ጊዜ ምዕራፍ ማለፍ እንዳለባት አሳውቆ ነበር። በተያያዘ ሁኔታ በሽግግር ጊዜ ውስጥ ዘላቂ እልባት ማስገኘት የሚችሉ አንኳር የለውጥ ተግባራት መፈፀም እንዳለባቸው ገልፆ ጥሪ ማስተላለፉም ይታወሳል። ነገር ግን በጥሬ የስልጣን ግብግብና በጥላቻ ባሕል የተቃኘው የሀገራችን አጠቃላይ የፖለቲካ ስምሪት ዘላቂ ተግዳሮት ሆኖ በመቀጠሉ፥ ተፈላጊው ለውጥ እውን ሊሆን ካለመቻሉም በላይ በሕዝባችን ላይ ተከታታይ የዘር ማጥፋትና የዘር ማፅዳት ጥቃቶች ተፈፅመዋል። የዜሮ ድምር የፖለቲካ ዘይቤን የቀጠለ ሲሆን በሀገራዊ መግባባትና ትብበር መሠራት ያለባቸውን ጉዳዮች በፉክክርና በጥላቻ ለመፍታት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ሊገቱ ባለመቻላቸው ምክንያት የሕዝባችን ትግል ገና ተቀናጅቶና ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተገንዝበናል።

    በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያዊነትን እና የኢትዮጵያዊነትን ትሩፋቶች በብቸኝነት ለመበየንና ለማከፋፈል የቋመጡ ጽንፈኛ መንግሥታዊ አካላት ሀገራችንን ተፈትሾ በወደቀው የሴራ ፖለቲካቸው አዙሪት ውስጥ ለማቆየት ከፍተኛ ርብርብ እያደረጉ ይገኛሉ። በርካታው የሀገራችን ክፍል የደህንነት ስጋት ያንዣበበት ሲሆን፥ የሕዝብ በሰላም የመንቀሳቀስም ይሁን በሕይወት የመኖር መብት በመደበኛነት አደጋ ውስጥ ይገኛል።

    አብን በዚህ ዓመት በሚካሄደው ሀገራዊ ምርጫ ለመሳተፍ ሲወስን የጥላቻና የሴራ ፖለቲካ ግንባር ቀደም ተጠቂ ድርጅት በሆነበት አግባብ ነው። የምርጫ ትርጉም በአንድ ቀን ውስጥ ተከፍቶ በሚዘጋ ሳጥን ውስጥ በሚጨመሩ ካርዶች የታጠረ እንዳልሆነም ይገነዘባል። በሀገራችን ውስጥ ያለው የቅድመ ምርጫ መደላድል ያለበት ሁኔታ ለሕዝባችን የተሰወረ አይደለም። በተለይም የአማራን ሕዝብ ማገት የፖለቲካ ስልት ሆኖ የቀጠለ እውነታ ነው፤ አብን የአማራ ሕዝብ ሀቀኛና የማያወላዳ እንዲሁም ጸረ-ጭቆናና ጸረ-ዘረኝነት የትግል እንቅስቃሴ በቀጥታ የወለደው ድርጅት በመሆኑ አማራን የሚፈርጁና የሚያጠቁ ጽንፈኞች ዓይናቸውን ለአፍታ እንኳን ዘወር እንደማያደርጉለት ይታወቃል።

    ከአማራ ክልል ውጭ በተለይም በኦሮሚያና በቤኒሻንጎል ክልል ውስጥ ባሉት የአብን መዋቅሮችና አመራሮች ላይ የተለያዩ ጥቃቶች ሲፈፀሙም ቆይተዋል፤ አሁንም ቀጥለዋል። በተለይም የክልሎቹ ባለስልጣናት በሆኑ የብልፅግና ፖርቲ አባላት የሚፈፀሙ ችግሮች መሆናቸውን መነሻ በማድረግ፥ ከፖርቲው ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመነጋገር ለመፍታት ጥረት ሲያደርግ ቆይቶ ባለመሳካቱ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማመልከቻ አቅርቦ በምርመራ ላይ ይገኛል።

    ጉዳዮቹ በዚህ አግባብ በሚገኙበት ሁኔታ ጭምር “የኦሮሞ ብልፅግና” ከፍተኛ አመራሮች በማኅበራዊ ድረ-ገፅ በአብን፣ በአመራሮቻችን፣ አባላቶቻችን፣ ደጋፊዎቻችን እና በአጠቃላይ በአማራ ሕዝብ ድርጅቶችና አመራሮች ላይ የሀሰት፣ የአፍራሽና የጥቃት ጥሪዎችን በተደጋጋሚ እያስተላለፉ ይገኛሉ። የብልፅግና ፖርቲ እንደተቋም በሚፈፀሙ ጥሰቶች ላይ ምንም ዓይነት ተጨባጭ እርምት ለማድረግ ባለመፈለግ በቀጥታ የተቀበላቸውና የአማራን ሕዝብ በተመለከተ ያለውን አቋም በምግባር፣ በድርጊትና በቸልታ አረጋግጧል።

    ጥር 25 ቀንም በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች በተደረጉ ሰልፎች በዋናነት አብንን የሚያጠለሹና የሚያወግዙ እንዲሁም በሕዝባችን ላይ ቀጣይ ስጋትን የጋረጡ ድምፆች ከፍ ብለው ሲስተጋቡ ተሰምተዋል። አብንን “ከኦነግ ሸኔ” ጋር የሚያመሳስሉ መፍክሮች ተሰምተዋል።

    ስለሆነም፦

    1/ በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ እየተፈፀመ ያለውን ገደብ የለሽ የፖለቲካ ነውረኝነትና የዘረኝነት እንቅስቃሴ ለመቃወም በባልደራስ ፓርቲ ተጠርቶ የነበረውን ሕዝባዊ ሰልፍ በማንአለብኝነት የከለከለ መንግሥት ለፖርቲ ፍጆታ ሲሆን ሰልፍ መጥራቱና መፍቀዱ፤

    2/ በሰልፉ ላይ (ጥር 25 ቀን 2013 ዓ.ም. የተደረገው የብልፅግና ፓርቲ ሰልፍ) የጥላቻና የጥቃት ጥሪዎችን ሲመሩ የነበሩት በስምና በኃላፊነት የሚታወቁ የመንግሥትና የብልፅግና ፖርቲ አመራሮች መሆናቸው፤

    3/ ጥር 25 ቀን 2013 ዓ.ም. በተደረገው የብልፅግና ፓርቲ ሰልፍ ላይ ጎልተው የተሰሙት ድምፆች የክልሉ አመራሮች በማኅበራዊ ድህረ-ገጽ ሲፅፏቸው የነበሩ ኃሳቦች ቀጥተኛ ግልባጭ መሆናቸው፤

    4/ በዚህም በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በአጠቃላይ ያለውን የፖለቲካ አፈና ወደተሟላ እርከን ለማሸጋገር በማሰብ አብን በክልሉ ውስጥ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ለመግታትና በክልሉ የሚኖረውን የአማራ ሕዝብና ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ በጭቆና ቀንበር ስር የማቆየት ዓላማ ያነገበ ተግባር መሆኑ፤

    5/ በተለይም ጥር 25 ቀን 2013 ዓ.ም. በተደረገው የብልፅግና ፓርቲ ሰልፍ ላይ በአማራ ሕዝብ ላይ በተደጋጋሚ የዘር ፍጅት ለመፈፀም ጽንፈኛ ኃይሎች መንደርደሪያ አድርገው የሚጠቀሙበት “ነፍጠኛ” የሚለው ቃል በሰፊው ሲገለፅ የነበረና በግልፅም “ነፍጠኛ ይውጣ” የሚል ሀሳብ ሲሰማ የነበረ መሆኑ፣

    6/ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ ኃላፊነት የጎደላቸው ጽንፈኛ አመራሮች በአማራ ሕዝብ ላይ እየደረሰ ላለው ጥቃት ሽፋን በመስጠትና በቀጥታ በመሳተፍ እንደሚያስፈፅሙ የተረጋገጠ ጉዳይ ሆኖ እያለ፥ በታየው ደረጃ የተላለፈውን የጥላቻና የጥቃት ጥሪ የመንግሥት ሚዲያዎች መዘገባቸው እና የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትርም እርምት መስጠት እየተገባቸው፥ ‘ቡራኬ’ መስጠታቸው እጅግ አሳዛኝ የሆነና በቀጣዩ የሀገራችን የፖለቲካ ሂደት ላይም ከፍተኛ ስጋትን እንደሚፈጥር መረዳት ይቻላል።

    በአጠቃላይ የሀገራችንን የፖለቲካ እንቅስቃሴ የተለየ ፖለቲካዊ እይታ የማስተናገድ ዝንባሌና ቀጣዩን ምርጫ በተመለከተ በመንግሥት በኩል እየታየ ያለው አቋምና አፍራሽ እንቅስቃሴ በአስቸኳይ እንዲቆም እየጠየቅን፥ የአብን የብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ጉዳዩን በቀጥታ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድና በግልባጭ ለሚመለከታቸው አካላት በደብዳቤ አሳውቋል።

    በመጨረሻም መላው ኢትዮጵያውያን፥ በተለይም የአማራ ሕዝብ፥ የብልፅግና ፓርቲ ሰልፍ ላይ የተስተጋባው የጥላቻና ዘር ፍጅት ቅስቀሳ በውጤት ደረጃ ሀገርና ሕዝብን ለህልውና አደጋ የሚጥል መሆኑን በመረዳት የተፈፀመውን አስነዋሪ ድርጊት በጽኑ እንዲያወግዝና አብን ከሚያደርጋቸው የፍትህ፣ እኩልነትና ነፃነት ትግሎች ጎን እንዲሰለፍ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

    የሴራ ፖለቲካ ምዕራፍ የሚዘጋበት፣ የጥላቻና የፍረጃ ፖለቲካ ላንቃ የሚዘጋበት ጊዜው አሁን ነው!

    የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)
    ጥር 25 ቀን 2013 ዓ.ም.
    አዲስ አበባ፤ ሸዋ፤ ኢትዮጵያ!

    የጥላቻና ዘር ፍጅት ቅስቀሳ በውጤት ደረጃ ሀገርና ሕዝብን የህልውና አደጋ ላይ ይጥላል

    Anonymous
    Inactive

    መቆሚያ ያጣው በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል (መተከል ዞን) ያሉ ሰዎች እልቂት!
    አስቸኳይ ጋዜጣዊ መግለጫ (ኢሰመጉ)

    የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) በቤንሻንጉል ጉሙዝ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት፣ መተከል ዞን፣ በቡለን፣ ድባጤ፣ እና ዳንጉር ወረዳዎች ላይ በንጹኃን ሰዎች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት አሁንም ተባብሶ መቀጠሉ እጅግ አሳስቦታል።

    ኢሰመጉ ታህሳስ 15 ቀን 2013 ዓ.ም ባወጣው አስቸኳይ ጋዜጣዊ መግለጫ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል (መተከል ዞን)፣ ቡለን ወረዳ፣ በኩጂ ቀበሌ ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት ከ100 በላይ ንጹኃን ሰዎች መገደላቸውን፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መፈናቀላቸውን እና ለከፍተኛ ችግር የተጋለጡ መሆናቸውን አውግዞ፤ መንግሥት በአካባቢው በተደጋጋሚ ጊዜ የሚከሰተውን የንጹኃን ሰዎች ሰቆቃ ለማስቆም የሚያስችል ፈጣን፣ ተጨባጭ እና ዘላቂ መፍትሔ እንዲያበጅ ማሳሰቡ አይዘነጋም።

    ሆኖም፤ ከሰሞኑ ይኸው ችግር ዳግም ተከስቶ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን ተጎጂዎች እና የተጎጂ ቤተሰቦች ለኢሰመጉ ተናግራዋል። ታህሳስ 25 ቀን 2013 ዓ.ም ከቻግኒ ወደ ግልገል በለስ የሚሄድ መኪና ውስጥ የነበሩ ተጓዦች ማንዱራ ከተማ ላይ በታጣቂዎች እንዲወርዱ ተደርጎ አንድ ሰው መገደሉን እና ሁለት ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን ለማወቅ ተችሏል።

    ከጥር 2 እስከ ጥር 3 ቀን 2013 ዓ.ም. በቡለን እና ጉባ ወረዳዎች፣ ኦሜድላ እና አይነሸምስ በተባሉ ቀበሌዎች ላይ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት ከ50 በላይ ሰዎች መገደላቸውን እና መኖሪያ ቤቶችም መቃጠላቸውን ኢሰመጉ መረጃዎች ደርሰውታል።

    በሌላ በኩል፤ ‹‹በድባጤ ወረዳ፣ ቆርቃ ቀበሌ፣ ዳሌቲ በተባለች መንደር ትላንት ጥር 4 ቀን 2013 ዓ.ም ከሌሊቱ 11፡30 ጀምሮ የኦነግ ሸኔ እና የቤኒን ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት ሰዎች መገደላቸውን፣ እስከአሁን ድረስ እኔ ራሴ ባለሁበት የ82 ሰዎች አስከሬን በፍለጋ መገኘቱን እና የቀብር ቦታዎች እየተዘጋጁ መሆኑን አይቻለሁ›› ሲሉ አንድ የዓይን እማኝ ለኢሰመጉ ተናግረዋል።

    ኢሰመጉ በትላንትናው (ጥር 4 ቀን) ጥቃት ሰለባ የሆኑ ሰዎች ቁጥር ከ100 ሊበለጥ እንደሚችል፣ በአብዛኛው ሴቶችና ህጻናት መሆናቸውን እና ከ24 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ቆስለው በጋሊሳ ጤና ጣቢያ እና ቡለን ሆስፒታል ውስጥ ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑን ከአካባቢው ካሰባሰባቸው መረጃዎች ለማወቅ ችሏል።

    በመሆኑም፥ መንግሥት ድርጊቱን የሚፈጽሙ አካላትን በአግባቡ አጣርቶ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወስድ፤ ለዚህ ተደጋጋሚ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ፈጣን፣ ተጨባጭ እና ዘላቂ መፍትሔ ማፈላለጉ ላይ በብርቱ እንዲሠራ ኢሰመጉ ያሳስባል። ኢሰመጉ ይህ ጉዳይ እልባት እንዲያገኝ ሁሉም ግለሰቦች፣ የማኅበረሰብ አንቂዎች፣ መገናኛ ብዙኃን፣ የሲቪል ማኅበራት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የሀይማኖት ተቋማት እና የሀገር ሽማግሌዎች በመንግሥት ላይ ውትወታ እንዲያደርጉ ጥሪውን ያቀርባል።

    የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ)
    ጥር 5 ቀን፥ 2013 ዓ.ም.
    አዲስ አበባ፥ ኢትዮጵያ

    መቆሚያ ያጣው በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል (መተከል ዞን) ያሉ ሰዎች እልቂት

    Anonymous
    Inactive

    የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ለሀቀኛ የፌዴራሊዝም ሥርዓት ካልታገለ እንደ ብልጽግና መቆም አይችልም!

    የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ወቅታዊ አቋም
    ኅዳር 27 ቀን 2013 ዓ.ም.
    ባህር ዳር

    ስናጠፋ የሚገስጸን፣ ስናለማ የሚያግዘን ሕዝብ እንዳለን እናምናለን። በሕዝባችን ስብራት ላይ ተደማሪ ስብራት መሆን ስለማንፈልግ ከሀቀኛ የፌዴራሊዝም ሥርዓት በመነጨ ቅን ልቦናና ፍላጎት የሕዝባችንን ድምጽ ለማክበርና ለማስከበር ተዘጋጅተናል። የብልጽግና ፓርቲ ሲመሠረት የአብዮታዊ ዴሞክራሲን ማቅ እና ድሪት አውልቆ የሕዝብን ሀቀኛ ፍላጎትና እውነተኛ መሻት የሆነውን መካከለኛ አማራጭና የወሳኝ ኩነቶች ወሳኝነት ለሕዝብ ተጠቃሚነት የሚበጀውን የፕራግማቲዝም (pragmatism) ድርና ማግ ተጎናጽፎ ነው። በብልጽግና እምነት ቋሚና የማይለወጥ እውነት የለም፤ ሁሉም ነገር ቋሚ ሊሆን አይችልም። በብልጽግና እምነት የማይለወጥ መሠረታዊና ቁሳዊ የሆነ ነገርም አይኖርም። ከብልጽግና ርዕዮተዓለማዊ እምነት አኳያ ቋሚና የማይለወጥ ነገር አለ ከተባለ እሱም ኅብረብሔራዊ ፌዴራሊዝምና ኢትዮጵያዊነት ብቻ ነው።

    መደመርን መንገዳችን፣ ብልጽግናን መዳረሻችን አድርገን ስንነሳ መደመር የሚፈልጉ ዜጎቻችንን ልንቀንሳቸው አንችልም። ዛሬ በማይካድራ፣ በዳንሻ፣ በዓላማጣ፣ በጥሙጋና በዋጃ ባጠቃላይ በራያ ዋጃ ዓላማጣና ኮረም እንዲሁም በወልቃይት ጠገዴ ሴቲት ሁመራ በተደረገው ሕዝባዊ ሰልፍ ያሰማችሁትን የ‘አማራ ነን’ ድምጽ በአክብሮት የምንቀበለውና በጽናት የታገልንለት ወደፊትም የምንታገልለት የመደመር ኅብረብሔራዊ ፌዴራላዊ ትርጉም ያለው የቆየ ግን በእብሪት የተገፋና መልስ የተነፈገው የዜጎች ጥያቄ ነው።

    ሁሉም የብልጽግና ቤተሰቦችና በሀገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባኛል የሚሉ ኃይሎች እንዲረዱት የምንፈልገው ቁምነገር አለ።

    በግፍ ተወረርን እንጂ ማንንም አልወረርንም።

    ክልላዊ ወሰናችንንና ፌዴራላዊ መብታችንን በመጋፋት በግፍ ተጠቃን እንጂ ማንንም አላጠቃንም።

    በጭካኔና ያለርህራሄ የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈጸመብን እንጂ በማንም ላይ የግፍ አጸፋ አልመለስንም። በደም ፍላት ስሜት ተገፍትረው ግፍ ለመፈጸም የቃጡና የሚቃጡ በውስጣችን ያሉ ስሁታንንም ያለርህራሄ ታግለናል፤ እየታገልንም እንገኛለን።

    ከልክ በላይ በተወጠረ እብሪት በትምክህተኝነት ስሜትና በተስፋፊነት ልክፍት ተወጥረው ሕዝባችንን፣ መሬታችንን፣ ታሪካችንን፣ መልካም ስማችንን፣ የ30 ዓመት ሁሉአቀፍ ክልላዊ እድገታችንን፣ እድሜያችንንና ሥነ-ልቦናችንን በግፍ ተዘረፍን እንጂ የማንንም ቅንጣት አልዘረፍንም።

    የወሰን፣ የማንነትና የፍትሀዊ ተጠቃሚነት ጥያቂያችንን በሕግና በሥርዓት አቀረብን እንጂ እንደ ትሕነግ በማን አለብኝነት ‘ዘራፍ’ አላልንም።

    የተገፋን፣ የተበደልንና የተጨፈጨፍን ቢሆንም ለፌዴራል መንግሥቱም ሆነ ለሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ አደጋ አልፈጠርንም።

    የሀገር መከላከያ ሠራዊትንና የሀገር ሉአላዊነትን ጠብቆ ለማስጠበቅ እስከ አሁኗ ሰዓት ድረስ ቁርጠኛ አጋርነታችንን በክቡር መስዋዕትነት አረጋገጥን እንጂ ሀገራችንና ሕዝባችንን በመካድ አልወጋንም። ሀገርና ሕዝብ ክደው በወገን ላይ የጭካኔ አፈሙዝ ያዞሩትንም የታሪክ ማፈርያዎች እንደሆኑ እንረዳለን።

    በሰላማዊ መንገድ እጅ የሰጡና የተማረኩ የትሕነግ ተዋጊ ኃይሎችን በወንድማማች መንፈስ ቁስላቸውን ጠረግን፣ እንዲያገግሙ በፍቅር ተንከባከብን እንጂ እንደጠላት አልገፋናቸውም። በተለመደው አማራዊ የእንግዳ አቀባበል ሥርዓት እልፍኛችንን ለቀን፣ ከአልጋችን ወርደን የምርኮኛነት ስሜት እንዳይሰማቸው አስተናገድናቸው እንጂ በግፍ አላሸማቀቅናቸውም።

    እብሪተኛው የአፓርታይድ ቡድን በፈጸመብን ሴራ እስከአሁኗ ሰዓት ድረስ በተለያዩ የሀገሪቷ አካባቢዎች በስጋትና በጭንቀት የሚኖረው የአማራ ሕዝብ ነው። በ10ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቻችን አሁንም በስደት ላይ ይገኛሉ። በቤንሻንጉል ክልል በመተከል ዞን የሚፈሰው የአማራ ደም ዛሬም አልቆመም። በሌሎችም አካባቢዎች የስጋት ጅረት አልተገደበም። በማይካድራና በሁመራ በየቦታው የተጣሉ አስከሬኖች ‘በክብር ቅበሩኝ’ ጥሪ ቢያስተጋቡም የንጹሃኑ በድኖች ግን ዛሬም ድረስ ተለቅመው አላለቁም።

    ይሁን እንጂ የአማራ ሕዝብ ጥንተ ጠላት የሆነው ትሕነግና ጽንፈኛ ወዳጆቻቸው ከትክክለኛው ወቅታዊ አውድ ፍጹም የሚቃረን ሙግትና ትንታኔ ሲሰጡ ልማዳቸው መሆኑን ብናውቅም ለአንድ አንድ የትግል አጋሮቻችንና ደጋፊዎቻችንን ግልጽ መልዕክት ማስተላለፍ እንፈልጋለን።

    1. ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. አረመኔውና የአፓርታይድ ሥርዓት አቀንቃኙ ትሕነግ በሰሜን ዕዝ ላይ የተጠናና የተደራጀ ሁሉ-አቀፍ ጥቃት ሲፈጽም የወራሪነት፣ የተስፋፊነትና የጨፍጫፊነት አድማሱን በማስፋት በ24 ሰዓት ውስጥ በምሥራቅና በምዕራብ የአማራ ክልል አቅጣጫዎች ጎንደርንና ወልድያን የመቆጣጠር ግብ አስቀምጦ ነው። ይህንን እኩይ ዓላማውን ለማሳካት ከ3 ዓመት ያላነሰ ወታደራዊ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል። ትሕነግ ያስቀመጠውን የወራሪነት ግብ በመቀልበስ ሀገርና ሕዝብን ለመታደግ በወትሮ ዝግጁነት መፈጸሙ የአማራን ሕዝብ ሊያስመሰግነው ሲገባ፥ በጥርጣሬ እንድንታይ የሚያደርግ በፍጹም አይሆንም። የተከፈተብንን የግፍ ጦርነት ተከላክለንም፣ አጥቅተንም ጦርነቱን መቀልበሳችንና በግፍ ተነጥቀን የነበረውን ተፈጥሯዊ መብታችንን በእጃችን ማስገባታችን (repossession right) የተፈጥሮን ሕግ የሚቃረን ሳይሆን በእብሪተኞች የማይታረቅ ተቃርኖ መቃብር ላይ የተረጋገጠ ድል ነው። ስለሆነም እርስት ለማስመለስ ያልታገለን ይልቁንም ላለፉት 30 ዓመታት ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ጥያቄ ሲያቀርብ የቆየን ሕዝብና መንግሥት እርስት ለማስመለስ እንደተዋጋ አድርጎ ኢ-ሕገ መንግሥታዊና አመክንዮ የጎደለው ድምጽ ማሰማት ነውር ነው እንላለን። በእርግጥ እርስት ማስመለስ የሚለው ትችት ለባለእርስቶች የተወረወረ የበላ-ልበልሀ ክርክር መሆኑ የአማራ ሕዝብን ጥያቄ ፍትሀዊነት ያረጋገጠ ሀቅ በመሆኑ ሀሳቡን ደጋግማችሁ ለተጠቀማችሁ ሁሉ ምስጋና እናቀርብላችኋለን።
    2. እንደ ብልጽግና ፓርቲ የአማራ ሕዝብ ሀቅ ይታወቃል። የአማራ ሕዝብ ሀቅ ዛሬም በአደባባይ በሕዝባዊ ሰልፍ በይፋ እንደሚታየው የማንነት፣ የወሰን፣ በህይወት የመኖርና የአካል ደህንነት ፍትሀዊ ጥያቄ ነበር። ከ500ሺ ሕዝብ በላይ የተፈናቀለባቸው፣ በ10ሺዎች የሚቆጠር ሕዝብ የተገደለባቸው፣ በ10ሺዎች የሚቆጠር ሕዝብ የተሰወረባቸው እነዚህ አካባቢዎች ዛሬም የተረጋገጠ የጅምላ መቃብር የተገኘባቸውና የአፓርታይድ ሥርዓት በተጨባጭ የተፈጸመባቸው የትሕነግ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ጭካኔ ማረጋገጫ የግፉአን መቀበርያ አጽመ እርስቶች ናቸው።

    በግፍ የተጨፈጨፉ የንጹሀን ወገኖቻችን አስከሬኖች ተለቅመው በክብር ባላረፉበት በዚህ ወቅት የባለቤትነት ጥያቄ ማንሳት የወንበዴውን ቡድን ወንጀል ለመደበቅና ለማድበስበስ እየተፈጸመ የሚገኝ ሌላኛው የትሕነግ ሸፍጥ ማምለጫ መንገድ ሲሆን፥ የአካባቢውን ነባራዊ ሀቅ በመረዳትም ሆነ ባለመረዳት የሚራመዱ የተሳሳቱ ሀሳቦች የሞራል ጥያቄ የሚነሳባቸው ናቸው።

    ስለሆነም የሕግ የበላይነት ለማስከበር፣ የሀገር ሉአላዊነት ለማጽናት በተደረገ ሁሉ አቀፍ የትግል ጀብዱ በታሪክ አጋጣሚ ወደባለእርስቱ የገቡ አካባቢዎች (repossessed lands) ላይ የሚነሳውን ማንኛውንም ጥያቄ በሥርዓቱና በአግባቡ በቀጣይ ማየት ይቻላል የሚል እምነት አለን። ግን ደግሞ የትሕነግን የአፓርታይድነት የወንጀል ፈለግ (criminal scene) መፈተሽና መመርመር፣ ለትግራይና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ማጋለጥ ከመቸውም ጊዜ በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል የሚል እምነት አለን። ስለሆነም:-

      • ላለፉት 50 ዓመታት የዜጎች ማጎርያና ማሰቃያ የሆኑ ከመሬት በታች የተሰሩ ዋሻዎች (underground torching caves) ለሕዝብ ይፋ መደረግ አለባቸው።
      • ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የጅምላ መቃብሮች ታስሰው ላለፉት 50 ዓመታት እንደ ሕዝብ የተፈጸመብንን ግፍና ጭካኔ ዓለም እንዲያውቀው ማድረግ ታሪካዊ ኃላፊነት እንደሆነ እናምናለን።
    1. በአጠቃላይ የብልጽግና ፓርቲ ተልዕኮ ግፈኛና ግፍን ነቅሎ በአዲስና በተረኛ ግፈኛና ግፈኝነትን ማጽናት አይደለም። ወትሮም ቢሆን የኢትዮጵያ ችግር ከግፈኞች አልነበረም። እንደሀገር ግፈኞችን መቅበር የተለመደ እንጂ አዲስ ነገር አይደለም። በየታሪክ ምዕራፉ ግፈኞችን መቅበር የምትችል ሀገር ግፍን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማስወገድ ግን አልቻለችም። ስለሆነም የብልጽግና ፓርቲ ግፈኝነትን በጽናት በሚታገልበት በዚህ ታሪካዊ መድረክ የየበኩላችንን ድርሻ እንድንወጣ እየጠየቅን፥ በእኛ በኩል እብሪተኝነትም ሆነ ግፈኝነት የሕዝባችንን ክብር ዝቅ ስለሚያደርገው በጽናትና በታማኝነት የምንታገለው መሆኑን አበክረን እንገልጻለን።
    2. በሁሉም የክልላችን አካባቢዎች አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን የሕግ የበላይነት የምናስከብር መሆኑን እያረጋገጥን፤ በቤንሻንጉል ክልል በሕዝባችን ላይ ተደጋጋሚ ግፍ የሚፈፅሙ የእብሪተኞች ቅሪት ዓላማና ፍላጎት በድል እንደሚቋጭ ሳንጠራጠር የተጀመረውን ሕግ የማስበር ሥራ አጠናክረን መቀጠል ይኖርብናል። ጎን ለጎንም የተፈናቃይ ወገኖቻችንን መሠረታዊና ወቅታዊ ፍላጎት እንዲሟላ ከማድረግ ባሻገር የሕዝባችንን እንቅፋት በሕግ አግባብ ተጠራርጎ መጥፋቱ ከተረጋገጠ በኋላ ዜጎቻችንን ተመልሰው በቀያቸው ላይ እንዲሰፍሩ የሚደረግ መሆኑን በድጋሚ እናረጋግጣለን።

    በመጨረሻም በትሕነግ መራሹ እብሪተኛ አፓርታይድ እርምጃ ዘግናኝ ግፍ የተፈጸመባችሁ ውድ የመከላከያ ሠራዊት አባላትና የማይካድራና የሁመራ ሰማዕታት ሁልጊዜም በሕዝባችን ልብ ውስጥ ዘላለማዊ ክብር አላችሁ።

    የሕግ የበላይነት ለማስከበር በተፈጸመው እልህ አስጨራሽ ግብ ግብ ክቡር መስዋዕትነት የፈጸማችሁ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት፣ የአማራ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ፣ የአፋር ልዩ ኃይልና ሚሊሻ የአባቶቻችን ልጆች ስለሆናችሁ ኮርተንባችኋል፤ ለዘላለምም እንኮራባችኋለን።

    የኦነግ ሽኔንና የጉሙዝ አማጺ ቡድንን ለመደምሰስ በሁሉም የአገሪቷ አካባቢዎች ስምሪት ወስዳችሁ ታሪካዊ መስዋዕትነት በመክፈል ላይ የምትገኙ የፌዴራል የጸጥታ ኃይሎች፣ የኦሮምያና የቤንሻንጉል ክልል ሀቀኛ የልዩ ኃይልና የሚሊሻ አባላት ጀግንነታችሁን ስንዘክር በአማራ ሕዝብ አክብሮትና ትህትና ነው።

    ድል ከኢትዮጵያና ከአማራ ሕዝብ አብራክ ለተገኙ ታሪካዊ ጀግኖቻችን!!!
    ውርደት በእብሪትና በትዕቢት ተወጥረው ሀገራችንንና ሕዝባችንን ለሚወጉ ጠላቶቻችን!!!
    ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ፈጣሪ አብዝቶ ይጠብቅ!!!
    የአማራ ብልጽግና ፓርቲ

    የአማራ ብልጽግና ፓርቲ

    Semonegna
    Keymaster

    በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ዙሪያ ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

    አዲስአበባ
    ጥቅምት 27 ቀን 2013 ዓ.ም

    በሀገር አቀፍ ደረጃ የተደረገውን ለውጥ ተከትሎ መንግሥት ባደረገላቸው ጥሪ መሠረት የተለያዩ የፖለካ አካላት ወደ ሀገር መግባታቸው፣ በተሰማሩበት ቦታ ሁሉ ችግሮች እንዳያጋጥማቸውና ደህንነታቸውን በመጠበቅና የፈለጉትን ሀሳብ እንዲገልጹ በቂ ክትትል ሲደረግላቸው መቆየቱን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄነራል እንዳሻው ጣሰው በመግለጫቸው አስታውሰዋል።

    በፌደራልና በክልል የሚገኙ የፖለቲካ እስረኞች መንግሥት ባደረገላቸው ምኅረትና ይቅርታ እንዲፈቱ መደረጋቸውን እንደ ትልቅ ሥራ መወሰድ አለበት ያሉት ኮሚሽነር ጄነራሉ፥ ሚዲያዎችም የተለያየ ሀሳብ ለሕብረተሰቡ ተደራሽ እንዲያደርጉና ከሕብረተሰቡ የሚነሱ ጉዳዮችን ለመንግሥት እንዲያደርሱ ነፃነታቸውን በመጠበቅ በኩል በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን ተናግረዋል።

    ከሕዳሴ ግድብ ጀምሮ በመላ ሀገሪቱ ተቀዛቅዞ የነበረ የትላልቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ በተጠናከረ መልኩ እንዲቀጥልና የተጀመረ የልማት ሥራ እንዲቋጭ የተለያዩ ሥራዎች ተሠርተዋል ያሉት ኮሚሽነር ጄነራሉ፥ በፖሊስ፣ በሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ በብሔራዊ መረጃና ደህንነትና በሌሎች የጸጥታ አካላት የተከናወኑ ሰፋፊ የሪፎርም ሥራዎችን በበጎ የሚወሰዱ ተግባራት መሆናቸውን ገልጸዋል።

    በሌላ በኩል ግን በሰላማዊ መንገድ ጥሪ ከተደረገላቸው አካላት መካከል ሰላማዊ መንገዱን በመተው ወደ ትጥቅ ትግል የገቡ አካላት እንዳሉ የገለጹት ኮሚሽነር ጄነራሉ፥ በተለይ የኦኔግ ሸኔ ቡድን በምዕራብ ወለጋና በሌሎች አካባቢዎች እንቅስቃሴ በማድረግ ሕብረተሰቡን በመግደል፣ በማገት፣ ንብረት በማውደምና ሌሎች የተለያዩ ሕገ-ወጥ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን ጠቁመዋል።

    በተማሪዎች ጠለፋ ላይም በመሰማራት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ በደቡብ ክልል ጉራ ፈርዳና በቅርቡ ደግሞ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ አካባቢ የኦኔግ ሸኔ አባላትና ህወሓት በተቀናጀ መንገድ የሕዝብ ግዲያ በመፈጸም የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውኑ እንደነበር ለማየት ተችሏል ብለዋል ኮሚሽነር ጄነራሉ።

    ኮሚሽነር ጄነራሉ አያይዘውም የህወሓት ጽንፈኛው ኃይል ከእነዚህ ከፍተኛ ጥፋቶች ኋላ ተሰማርቶ ሲሠራ እንደነበረ በተለያዩ ጊዜ ባደረግናቸው ምርመራዎች ለማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል።

    የህወሓት ጽንፈኛ ኃይል ከፌደራል መንግሥት ጋር ለመሥራት ያለመፈለግ፣ ሕገ-ወጥ ምርጫ ማከናወን፣ የሠራዊት አባላትን ለውጊያ በሚመጥን መንገድ ማዘጋጀት፣ የፌደራል መንግሥትን ሕገ-ወጥ ነው በማለት ባገኘው ሚዲያ በሙሉ ማሰራጨትና ሌሎች ለጸጥታ ሥራ ስጋት የሆኑ ጉዳዮችን ሲያከናውን መቆየቱንም ኮሚሽነር ጄነራሉ ገልጸዋል።

    በአጠቃላይ የህወሓት ጽንፈኛ ቡድንና የኦኔግ ሸኔ ታጣቂው ኃይል በተደራጀ መንገድ ከውጭና ከሀገር ውስጥ የሚደረግላቸውን የፋይናንስ ድጋፍ በመጠቀም ለሁለት ዓመታት የተለያዩ የሀገሪቱን ክፍል ሲያተራምሱ መቆየታቸውን ለማረጋገጥ እንደተቻለም ኮሚሽነር ጄነራል እንዳሻው ተናግረዋል።

    በሁሉም አካባቢ የተፈጸሙ የጸጥታ ችግሮች ሲያደራጁና ሲመሩ የነበሩ መሆናቸውን ምርመራዎቻችንና የተለያዩ መረጃዎቻችን አረጋግጧል ያሉት ኮሚሽነር ጄነራሉ፥ የተለያዩ ፍንዳታዎችን በመፈጸም፣ የግድያ ሙከራዎችን ማከናወን፣ ንብረት ማውደም፣ ሕዝብን ከሕዝብ ማጋጨትና በቤተ-እምነቶች መካከል ግጭት እንዲፈጠር ለማድረግ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እንደነበራቸውም ኮሚሽነር ጄነራሉ በመግለጫቸው ጠቁመዋል።

    አሁንም በትግራይ ክልል ጦርነት ከፍተው ባሉበት ወቅት በሀገራችን የተለያዩ ክፍሎችና ትላልቅ ከተሞች ላይ ጥቃት ለማድረስ ያሰማሩት ኃይል እንዳለ ተደርሶበታል ያሉት ኮሚሽነር ጄነራሉ፥ ይሄ ኃይል ፖሊስና ሌሎች የጸጥታ አካላት ባደረጉት ስምሪት ግማሹ የተያዘ ሲሆን ግማሹ ደግሞ በቅርብ ቀን ከተደበቀበት በማውጣት በቁጥጥር ስር የማዋል ሥራ በተጠናከረ መልኩ እንደሚከናወን ተነግሯል።

    የፌደራል ፖሊስ ባለው ሕገ-መንግሥታዊ ተልዕኮ መሠረት በሀገሪቱ በሁሉም አካባቢ በመሰማራት የሕብረተሰቡን ሰላምና ጸጥታን የሚጠብቅ ኃይል መሆኑን በመግለጽ በትግራይ ክልልም በ22 ትልልቅ ተቋማት ላይ በመሰማራት አገልግሎት ሲሰጥ የነበረ ተቋም ነው ብለዋል።

    የፌደራል ፖሊስ አባላት ኤርፖርቶችን፣ ዲፖዎችን፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ጣቢያዎችን፣ ቴሌኮምን፣ ቤተ መንግሥትን፣ ትላልቅ ግድቦችንና ኬላዎችን ጨምሮ ሌሎች የሕዝብና የመንግሥት ተቋማትን በመጠበቅ ተገቢውን አገልግሎት ለሕብረተሰቡ ሲሰጡ መቆየታቸውንና በትግራይ ውስጥ ለሚሰሩ የልማት ሥራዎችን ከሕብረተሰቡ ጎን በመሰለፍ በገንዘባቸው፣ በእውቀታቸውና በጉልበታቸው ከፍተኛ አስተዋፅኦ ሲያደርጉ እንደነበር ተገልጿል።

    የፌደራል ፖሊስ ኃይል ሕብረተሰቡን ሲያግዝ በነበረበት ወቅት ህወሓት ከፍተኛ ኃይል በመመደብ ጥቃት እንደሰነዘረባቸውና የንብረት ዝርፊያ መፈጸሙን የተናገሩት ኮሚሽነር ጄነራሉ፥ በአንዳንድ አካባቢ የፌደራል ፖሊስ ሠራዊትና የትግራይ ሕዝብ አንድ ላይ ሆነው ሊወረው የመጣውን ኃይል ተከላክሏል ብለዋል።

    መውጫና መግቢያ መንገዶችን ለሠራዊቱ በማሳየት የትግራይ ሕዝብ ሊያጠቃው የመጣውን አካል መከላከል መቻሉና ከሰሜን እዝ ጋር በመሆን ጽንፈኛውን ተዋጊ ኃይል በመመከትና በመምታት የራሱን ድርሻ እየተጫወተ ይገኛል ተብሏል።

    ጽንፈኛው የህወሓት ቡድን የፈፀመው ይሄ አስነዋሪ ድርጊት ታሪክ፣ ሕግና ህሊና ይቅርታ የማይሰጠው ጉዳይ ነው ያሉት ኮሽነር ጄነራል እንዳሻው ጣሰው፥ ሠራዊቱንና ሕዝቡን የደፈሩበት ሂደት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋልም ብለዋል።

    ለውጊያ ሳይሆን ለጥበቃ ሥራ የተሰማራ የፌደራል ፖሊስ ኃይል በታጠቀና ለውጊያ በተዘጋጀ ኃይል ተከቦ እንደዚህ ዓይነት እርምጃ መውሰድ አጅግ አሳፋሪ መሆን በመግለጽ ሕግ የማስከበር ሂደታችን በድል በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ የፌደራልና የክልል ፖሊስ እንዲሁም ሕዝባዊ አደረጃጀት ያላቸው የሚኒሻ አባላት በጋራ በመደራጀት አካባቢያቸውን በአግባቡ መጠበቅ እንዳለባቸው ጠቁመዋል፤ ለተለያየ እኩይ ተግባር የተሰማሩ ሃይሎችን በየአካባቢው በቂ ጥናት በማድረግ በቁጥጥር ስር ማዋል እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

    በአማራ ክልል ጎንደር ከተማ፣ በአፋር፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላና በሌሎች አካባቢዎች የነበሩ የጥፋት ሙከራዎችን በቁጥጥር ስር በማዋል ሠራዊቱ በአንድ ረድፍ በመሰለፍ ይህንን ችግር ለመከላከል ላሳየው ከፍተኛ ጽናት አድናቆታቸውን በመግለጽ አሁንም ከኢንቨስትመንት ጀምሮ ለትልልቅ የኢንዱስትሪ መንደሮች ተረባርበን አስፈላጊውን ጥበቃ በማድረግ ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮችን መከላከል አለብን ብለዋል።

    በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት በሚሰጠው መመሪያ መሠረት መፈጸም ከሠራዊቱ አባላት የሚጠበቅ ተግባር መሆኑን የገለጹት ኮሚሽነር ጄነራሉ ሕብረተሰቡ በዲጂታል ወያኔ የሚሠራጩ የሐሰት ፕሮፓጋንዳዎችን በጋራ መከላከል እንዳለበትና በየቀኑ ከመንግሥት የሚሰጠውን መግለጫ ብቻ መከታተል እንዳለበት አስገንዝበዋል።

    መንግሥት ለሚያቀርበው ጥሪ ሕብረተሰቡ በቂ ዝግጅት በማድረግ እኩይ ተግባር ለመፈጸም የተሰማራ ኃይል በመከታተል መጠቆምና ማጋለጥ እንዳለበትም ኮሚሽነር ጄነራሉ ጥሪ አቅርበዋል።

    በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በተሰጡ አድራሻዎች መሠረት በዚህ በሁለት ቀናት ውስጥ ብቻ ከ1,500 በላይ የሚደርሱ ጥቆማዎች መድረሳቸውንና በዚህም ውጤታማ ሥራዎች መከናወናቸውን የተናገሩት ኮሚሽነር ጄነራሉ በሌሎችም መሰል ሥራዎች መሠራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

    የተጀመረው ጸረ-ሰላም ኃይልን የማጥራት ሂደት በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ፊታችንን ሙሉ በሙሉ ለሰላም፣ ለልማትና ለዲሞክራሲ ግንባታ በማዞር ጥረት የምናደርግበት ጊዜ እንዲሆንም የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄነራል እንዳሻው ጣሰው ተመኝተዋል።

    የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን

    የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን

    Anonymous
    Inactive

    ከባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ (ባልደራስ) ፓርቲ የተሰጠ ወቅታዊ መግለጫ!

    በቅርቡ በወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ፣ ባለፈው ሳምንት በጉራፈርዳ በአማራ ዜጎቻችን ላይ የተካሄደው ዘግናኝ የዘር ጭፍጨፋ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ በጽኑ እንደሚያወግዝ ይገልጻል። እንዲሁም ይህንን ዘግናኝ የዘር ጭፍጨፋ የፈጸሙና ያስፈጸሙ ኃይሎች ለሕግ እንዲቀርቡ ፓርቲያችን አበክሮ ይጠይቃል።

    ይህ የዘር ፍጅት እየተባባሰ በመምጣቱ እና ማቆሚያው ባለመታወቁ መንስ ዔውም የአስፈጻሚው የመንግሥት አካል ዳተኝነት መሆኑን የተገነዘበው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለዚህ የዘር ፍጅት አስፈጻሚው የመንግሥት አካልን ተጠያቂ ማድረጉ ይታወቃል።

    የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ መንግሥት በፓርላማው የተነሳበትን ተጠያቂነት መሠረት በማድረግ እና ህወሓት በሰሜኑ እዝ ላይ በከፈተው ጥቃት በህወሓት ላይ ጦርነት አውጇል

    የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በጠየቁት መሠረት እና ከጦርነቱ ጎን ለጎን ህወሓት በሽብርተኝነት እንዲፈረጅ እና አስቸኳይ እርምጃ ሊወሰድበት እንደሚገባ ፓርቲያችን በጽኑ ያምናል።

    ልክ በህወሓት ላይ እንደሚካሄደው ጦርነት የዘር ፍጅት እየፈጸመ በሚገኘው በኦነግ ሸኔ እና በኦሮሞ ጽንፈኞች እና ተመሳሳይ ተግባር በተለያዩ አካባቢዎች ላይ በሚፈጽሙት ሁሉ ላይ መደረግ ያለበት የዘገየ እርምጃ እንደሆነ የባልደራስ እምነት ነው። ይህም በሽብርተኝነት የመፈረጁ እርምጃ በዘር ፍጅት ላይ በማስፈጸም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የተሳተፉትን ማጠቃለል ይኖርበታል።

    ሀገራችንን ለዚህ ሁሉ የዘር ፍጅትና ትርምስ ውስጥ የከተታት ህወሓት እና ኦነግ ያዘጋጁት ሕገ-መንግሥት ለሀገር አንድነት እና ስጋት ምንጭ ስለሆነ ሊታገድ ይገባል። ከጦርነቱ በኋላ መንግሥት ሕገ-መንግሥቱ የሚታገድበትን እና ሁሉም ኢትዮጵያውያን የሚስማሙበት አዲስ ሕገ-መንግሥት እንዲዘጋጅ ሁኔታዎችን ሊያመቻች እንደሚገባ ፓርቲያችን በጽኑ ያምናል።

    በመጨረሻም፥ አሁን በሀገራችን በህወሓት ላይ የሚደረገው ጦርነት ተገቢ እንደሆነ ፓርቲያችን በጽኑ ያምናል። ዳሩ ግን ወንድም በሆነው በትግራይ ሕዝብ ላይ እልቂት እንዳይፈጸም ፓርቲያችን ማሳሰብ ይወዳል። በጦርነቱ ላይ ለሚሳተፉት የመከላከያ ሠራዊትም ሆነ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል ፓርቲያችን ልዩ ክብር አለው። ጦርነቱንም የሚመሩ ባለስልጣናት ከእልህ እና ከቂም በቀል በራቀ ሕግን በማስከበር ብቻ እንዲመሩ ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ጥሪውን እያቀረበ፤ በሂደቱ መስዋዕትነት እየከፈሉ ለሚገኙ የመከላከያ ሠራዊታችን እና ለአማራ ልዩ ኃይል አክብሮት እና እድናቆቱን ዳግም እየገለጸ፥ ሌሎችን ሀገራዊ ጉዳዮችን ከጦርነት ጎን ለጎን የሚፈቱበትን አማራጭ ላይ ሁሉም ስለኢትዮጵያ ያገባኛል የሚል ኃይል እንዲሳተፍ ያሳስባል።

    ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ)
    ጥቅምት 25 ቀን 2013 ዓ.ም

    ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ

    Anonymous
    Inactive

    በህወሓትና በውጭ ኃይሎች የተቃጣውን የእብሪት ጦርነት በጋር ከመመከት ውጭ ሌላ አማራጭ የለም
    ነአምን ዘለቀ

    በሀገራችን አንድነትና በኢትዮጵያ ሕዝብ ደህንነት ላይ በህወሓትና በውጭ ኃይሎች የተቃጣውን የእብሪት ጦርነት በጋር ከመመከት ውጭ ሌላ አማራጭ የለም።

    ሀገራችን ኢትዮጵያ ከባድ የህልውና አደጋ፣ ከባድ ፈተና ውስጥ እየገባች ነው። በእብሪት፣ በበታችነት፣ በዘረኝነት በሽታ የተለከፈው፣ በኢትዮጵያ ላይ የነበረውን ሁለንተናዊ የበላይነት ያጣው የመሰሪው የህወሓት መሪዎች ትግራይ ወስጥ በሚገኘው የሰሜን እዝ የመከላከያ ካምፕ ላይ የኃይል እርምጃ በውሰድ ሀገሪቱን ወደ ጦርነት ለመውሰድ የመጀመሪያ እርምጃቸውን እንደወሰዱ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት የተላለፈው መልዕክት ያሳያል።

    1ኛ) የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር በጋራ ከመቆም ሌላ አማራጭ የለም። በልዩ ልዩ የህገሪቱ ችግሮች ከመንግሥት ጋር የሚገኙ ልዩነቶች ሁሉ ወደ ጎን ማድረግ አማራጭ የለውም።

    2ኛ) በሀገራችን አንድነትና በሕዝብ አብሮነት ላይ የተቃጣውን የህወሓት እብሪት በጋር ከመመከት ውጭ ሌላ አማራጭ የለም።

    3ኛ) የህወሓቶች ዒላማ የፌደራሉ መንግሥት ብቻ አይደለም፤ ይህ ጥቃት የተቃጣው በኢትዮጵያ ህልውና፣ በሕዝባችን ሰላም፣ ደህነትና አብሮነት ላይ ነው።

    4ኛ) የህወሓቶች ጥቃት በመከላከያ ሠራዊትበብልጽግና ፓርቲና እና በመንግሥት ላይ ብቻ አይደለም፤ የህወሓቶች እብሪትና ጠብ አጫሪነት እነሱ ያልገዟት ኢትዮጵያ እንድትፈርስ፣ ብሎም እነሱ የሚያስታጥቁትና የሚደግፉዋቸው ኃይሎች በቤኒሻንጉል፣ በወለጋ እንደተደረጉት እጅግ ዘግናኝና አረመኔያዊ ግድያዎች በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች እንዲደደገሙ በማድረግ ኢትዮጵያን ማፍረስ ነው። ይህን በጋራ ህልውናችውን ላይ የተቃጣ ከባድ አደጋ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በጋራ ሆነን መመከት አለብን።

    5ኛ) ሕወሓት፣ ኦነግ ሸኔ፣ ግብጽ፣ እና በዲያስፓራም በሀገር ውስጥ የሚገኙ ቅጥረኖቻቸው ኢትዮጵያን ለማተራመስ ከቻሉ ማዕከላዊ መንግሥቱን ዳግም ለመቆጣጠር፥ ካልቻሉም ደግሞ ህወሓት አባይ ትግራይን ይመሠርታል፤ ግብጽም የአባይን ግድብ ህልውና እና አገልግሎት ለማምከን ትችላለች፤ ኦነግ ሸኔም የኦሮሚያ ሪፑብሊክ ይመሠርታል። አነዚህን ዋና ዒላማቸው አድርገው በጋራ እየተንቀሳቀሱ መሆኑ ግልጽ ነው። ከዚያ ስለሚከተለው ምድራዊ ሲኦል ህወሓትና የኦነግ ሽኔ የሞራልና የስብዕና ድኩማኖች ፈጽሞ ሊረዱ የሚችሉት አይደለም።

    ኢትዮጵያውያን ሁሉ፥ በዲያስፓራ የምንገኝ ሀገር ወዳዶች ሁሉ፥ በሀገር ውስጥም ወጣቱ፥ ጀግናው የቀድሞ ሠራዊት አባላት ሁሉ ከዳር አስከ ዳር በጋራ ሆነን፣ በጋራ ቆመን ከማዕከላዊ መንግሥትና ከመከላከያ ሠራዊቱ ጀርባ በመሰለፍ፣ አሰፈላጊውን ድጋፍና መስዋዕትነት መክፈል አለብን። የሀገራችንን ህልውና፣ የሕዝብን ሰላምና ደህነት፥ የጥፋት፣ የዘረኝነት፣ የእብሪት ክምችት ከሆነው ከህወሓትና ግብረ-አበሮቹ ለመታደግ በጋራ መቆም፣ በጋራ መሰለፍ የወቅቱ [ዋና ተግባራችን መሆን አለበት።]

    ይህን የማያደርግ የታሪክ ተወቃሽ ብቻ ሳይሆን የራሱንም፣ የቤተሰቡንም ዕጣ ፈንታ ለህወሓቶች ዳግማዊ የክረፋው ዘረኝነት፣ ጭካኔና ባርነት መዳረግ ይሆናል፤ ከዚያም ሲያልፍ ሀገር-አልባ መሆንም ይከተላል።

    ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድም ሆነ ከብልጽግና ጋር ያለ ማናቸውም ልዩነት ወደ ጎን አድርገን የመጣብንን የህልወና አደጋ በጋራ መመከት የወቅቱ አብይ ተግባር ነው!!

    ነአምን ዘለቀ (ከአሜሪካ)

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forums) ላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።

    በህወሓት የተቃጣው የእብሪት ጦርነት

    Anonymous
    Inactive

    በአማራ ሕዝብ ላይ እየተፈፀመ ባለው የዘር ማጥፋት ወንጀል መራሹ የኦህዴድ ብልጽግና መንግሥት ግንባር ቀደም ተጠያቂ ነው!!!
    የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)

    የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) በጥቅምት 22 ቀን 2013 ዓ.ም ምሽት ላይ በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ ጋዋ ጋንቃ ቀበሌ ከ200 በላይ አማሮች በማንነታቸው ብቻ ተለይተው በጅምላ በተፈፀመባቸው የዘር ማጥፋት ድርጊት የተሰማውን መሪር ሀዘን ይገልፃል።

    ላለፉት ሰላሳ ዓመታት በሀገሪቱ ውስጥ በአማራ ሕዝብ ላይ ማንነትን መሠረት ያደረገ የጅምላ ጭፍጨፋና የዘር የማፅዳት ወንጀል እየተፈፀመ ይገኛል። በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በአማራው ሕዝብ ላይ የሚደርሰውን ሰቆቃ ማስቆም የሚችል የመንግሥት ኃይል አለመኖሩ ደግሞ ችግሩን እያባባሰው መጥቶ ዛሬ ላይ የአማራ ሕዝብ ከፍተኛ የህልውና አደጋ ተጋርጦበት ይገኛል።

    በዚህም ምክንያት በእነዚህ በርካታ ዓመታት በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈፀመው የዘር ማጥፋት ወንጀል ተባብሶ ቀጥሏል። መንግሥትም በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈፀመውን ተደጋጋሚ የዘር ማጥፋት ወንጀል በስሙ ከመጥራት እና ብሔራዊ የደኅንነት ስጋት አድርጎ ጥቃቱን ከማስቆምና የችግሩን ፈጣሪዎች በቅጡ ለይቶ የሚመጥን ርምጃ በወቅቱ ከመውሰድና የሕዝቡን ደህንነት ከመጠበቅ ይልቅ እሹሩሩ በማለትና ወንጀሉን በማድበስበስ የወንጀሉ ቀንደኛ ተባባሪ ሆኖ ይገኛል።

    በተለያዩ የኦሮሚያ ዞኖች የሚንቀሳቀሰው ታጣቂው የኦነግ ሸኔ ኃይል ከኤርትራ ሙሉ ትጥቅ ይዞ እንዲገባ በማድረግ በየቦታው ካሉ አማራጠል ፅንፈኛ ኃይሎች ጋር በቅንጅት አማራዉን ማኅበራዊ ረፍት ለመንሳትና በጅምላ ለመጨፍጨፍ እንዲችሉ ፍቃድ የሰጣቸው የፌደራል መንግሥቱ ነው።

    በኦህዴድ መራሹ የብልጽግና መንግሥት የስልጣን መዋቅር ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ አፍቃሬ ኦነግ የኦህዴድ ባለስልጣናት በአካባቢው የነበረውን የኦሮሚያ ልዩ ኃይል በማስወጣትና ድርጊቱ ሲፈፀም እየሠሙና እያወቁ እንዳላዩ ማለፋቸው የዚህ የወንጀል ድርጊት ተሳታፊ እንደሆኑ ይቆጠራል። በአጠቃላይ የአማራ ሕዝብ የዘር ማጥፋት ታውጆበት እያለ የማዕከላዊ መንግሥቱ ዝምታና እንዳላየ ማለፉ እጅግ አሳፋሪ ተግባር ነው።

    የአማራው ሕዝብ በመንግሥት ድጋፍ እየተፈፀመበት ያለውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ተደራጅቶ እና ተዘጋጅቶ እንዲመክት የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ጥሪውን እያቀረበ በአሸባሪው የኦነግ ሽኔ ሽፍታ ቡድን ህይወታቸን ላጡ ወገኖቻችን ቤተሰቦች መፅናናትን እንዲሰጥልን እንመኛለን።

    የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)
    ጥቅምት 22 ቀን 2013 ዓ.ም

    በአማራ ሕዝብ ላይ እየተፈፀመ ባለው የዘር ማጥፋት መንግሥት ተጠያቂ ነው

    Anonymous
    Inactive

    ምዕራብ ኦሮሚያ የተፈጸመውን ግድያ በጽኑ እናወግዛለን
    የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)

    ከትላንት በስትያ ህዳር 1 ቀን 2020 [ጥቅምት 22 ቀን 2013 ዓ.ም] ምዕራብ ኦሮሚያ ውስጥ በዜጎች ላይ ግድያ መፈጸሙን ከመገናኛ ብዙሃን የሰማን ሲሆን፥ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ይህንን የግድያ ተግባር በጽኑ እያወገዘ፤ የተሰማውን ጥልቅ ሀዘንም ይገልጻል።

    መንግሥት ነኝ የሚለው አካል ከአሁን ቀደም እንደለመደው ይህንን ግድያ የፈጸሙት ህወሓት እና ኦነግ-ሸኔ ናቸው በሚል ገልጿል። ኦነግ-ሸኔ በሚል የሚታወቅም ይሁን በዚህ ስም እራሱን የሚጠራ ድርጅት ግን አላገኘንም። ለኢትዮጵያ ሕዝቦችም ይሁን ለዓለም ማኅበረሰብ በዚህ ስም የሚከሰሰው ድርጅት ማንነት ግልጽ አይደለም።

    ይህ የግድያ ድርጊት እና ሌሎች መሰል ድርጊቶች ሁሉም ነጻና ተዓማኒነት ባለው ገለልተኛ አካል በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጣርተው ለተጎጂዎችና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች፥ እንዲሁም ለዓለም ማኅበረሰብ ግልጽ እንዲሆኑ እንጠይቃለን። ከዚህ ባሻገር ሁሉም አካላት ሕዝቦችን የሚያጋጩና በብሔሮች መካከል መጠራጠርን የሚፈጥሩ ማናቸውንም ዓይነት መረጃ ከማሰራጨት እንዲቆጠቡ መልዕክታችንን እናስተላልፋለን።

    በመጨረሻም ዜጎችን ለከፋ አደጋ እያጋለጠ ያለው ቀውስና የደህንነት ችግር ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት መፍትሄ ካልተበጀለት፥ ይበልጥ እየተባባሰ እንደሚሄድ ኦነግ በመግለጫው ሲያሳስብ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፤ አሁን እያየን ያለነውን አደጋ ለማስቀረት እና ኦሮሚያና ዜጎችን ከባሰ ቀውስ ለመታደግ ያለው ብቸኛው መፍትሄ የኦሮሚያ ሽግግር መንግሥት ማቋቋም በመሆኑ ሁሉም ዜጋ ድርሻውን እንዲወጣ ጥሪያችንን በድጋሚ እናድሳለን።

    በድጋሚ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) በምዕራብ ኦሮሚያ በዜጎች ላይ የተፈጸመውንና ካሁን ቀደምም በተመሳሳይ መልኩ የተፈጸሙ ግድያዎችን ሁሉ በጥቅብ እንደሚያወግዝ እያሳሰበ፥ ለሟች ቤተሰቦችና ዘመዶች እንዲሁም ሰላም ወዳዶች ሁሉ መጽናናትን ይመኛል።

    ድል ለሰፊው ሕዝብ!
    የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)
    ህዳር 3 ቀን 2020 ዓ.ም

    ምዕራብ ኦሮሚያ የተፈጸመው ግድያ

    Anonymous
    Inactive

    ንጹሃን ዜጎችን በማንነታቸዉ በጅምላ ማጥቃት የሽብር እንጂ የፖለቲካ ትግል ሊሆን አይችልም
    ብልጽግና ፓርቲ

    ባለፉት ሁለት ዓመታት ተኩል በሀገራችን እዉነተኛ የዲሞክራሲ ሥርዓት ሽግግር ለማደረግ የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋትን ጨምሮ በርካታ ተግባራዊ እርምጃዎች ሲወሰዱ መቆየታቸዉ ይታወሳል።

    በዚህም በሀገራችን ሕዝቦች ዘንድ ትልቅ ተስፋና መነቃቃት መታየት የጀመረ ሲሆን ሀገራችን በሰላማዊ፣በሰለጠነና በሰከነ የፖለቲካ አስተሳሰብ በሚመራ ነጻ፣ፍትሃዊና ገለልተኛ ምርጫ ወደ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ልትሸጋገር እንደምትችን የተስፋ ብርሃን የታየበት የፖለቲካ ሪፎርም ሲካሄድ መቆየቱ አይዘነጋም።

    ይሁን እንጂ ሰላማዊና የሰለጠነ የፖለቲካ ስርዓት የማይዋጥላቸዉና ግድያን፣ ማፈናቀልን፣ ንብረት ማዉደምንና ንጹሃን ዜጎችን ማሸማቀቅን እንደ ዋነኛ የስልጣን ምንጭ አድርገዉ የሚንቀሳቀሱ የኢትዮጵያን መረጋጋትና የዜጎቿን ሰላም የማይፈልጉ ሃይሎች ቅንጅት በመፍጠር ምንም ዓይነት የፖለቲካ ወገንተኝነት የሌላቸዉን ንጹሃን ዜጎች በማንነታቸዉ ብቻ ኢላማ በማድረግ ጥቃት በማደረስ ላይ ይገኛሉ።

    በዚህ እኩይና ጭካኔ የተሞላበት አረመኔያዊ የጥፋት ተግባራቸዉ ባለፉት አመታት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የዜጎች ህይወት እንዲጠፋ፣ አካል እንዲጎድል፣ ንብረት እንዲወድምና ዜጎች የሰላም ስሜት እንዳይሰማቸዉ ሲደረግ ቆይቷል።

    በተለይም ሰሞኑን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል ዞን እና በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በቤንች ሸኮ ዞን በጉራ ፈርዳ ወረዳ የበርካታ ንጹሃንን ህይወት የቀጠፈ ጨካኝ የሽብር ተግባር ተፈጽሟል።

    የንጹንን ደም በማፍሰስ ስልጣን መያዝን ካልሆነም አገርን መበታተንን ዋነኛ ዓላማቸዉ አድርገዉ ከሚነቀሳቀሱ ቡድኖች መካከል አንዱ የሆነዉ ኦነግ ሸኔ የተባለዉ አሸባሪ ቡድን በሀይል ወደ ስልጣን ለመመለስ ከሚፈልጉ ካልተሳካላቸዉም ኢትዮጵያን ለመበታተን ሌት ተቀን ከሚሰሩ ተቀናጅተዉና በትጥቅ ተደግፈዉ በትናንትናዉ ዕለት ማታ [ጥቅምት 22 ቀን 2013 ዓ.ም] በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ ጋዋ ጋንቃ በተባለዉ ቀበሌ ባደረሱት ጥቃት የዜጎች ህይወት ያለፈ ሲሆን በርካታ የአካል ጉዳትም ደርሷል።

    ይህ የሽብር ጥቃት ፍጹም ሰላማዊ በሆኑ ንጹሃን ዜጎች ላይ የተቃጣ መሆኑ አጥፊ ቡድኑ የሚከተለዉ መንገድ ምን ያህል ያልሰለጠነ፣ ኋላ ቀርና ጭካኔ የተሞላበት መሆኑን ለአለም ሕዝብ ያጋለጠበት ነዉ።

    በዚህ አረመኔዊ ተግባር ህይወታቸዉን ላጡ ዜጎቻችን የተሰማንን ጥልቅ ሃዘን እየገለጽን ለተጎጂዎች ቤተሰቦችና ወዳጅ ዘመዶች እንዲሁም ለመላዉ ኢትዮጵያዊያን መጽናናትን እንመኛለን።

    መንግሥት እነዚህን ነብሰ ገዳዮች ከያሉበት አድኖ ሕጋዊ እርምጃ የሚወስድ መሆኑን እያረጋገጥን የፓርቲያችን አመራሮች፣ አባላት፣ ደጋፊዎችና መላዉ የሀገራችን ሕዝቦች የንጹሃን ዜጎችን ህይወት ያጠፉና አካል ያጎደሉ ሽብርተኛ ቡድኖችን አድነን እርምጃ በመዉሰድ የህግ የበላይነትን ለማስከበርና ህብረ-ብሄራዊ ፌዴራላዊ አንድነታችንን ለማስቀጠል በምናደርገዉ እርምጃ ዉስጥ ከጎናችን በመሆን አስፈላጊዉን ትብብርና ድጋፍ እንድታደርጉልን ጥሪያችንን እናቀርባለን።

    ብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽ/ቤት
    ጥቅምት 23 ቀን 2013 ዓ.ም

    ንጹሃን ዜጎችን በማንነታቸዉ በጅምላ ማጥቃት

    Anonymous
    Inactive

    በአማራ ሕዝብ ላይ በየቦታው እየተፈፀመ ላለው የዘር ማጥፋት ወንጀል ሙሉ ኃላፊነቱን መንግሥት ይወስዳል
    የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)

    የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በትላንትናው ዕለት ማታ [ጥቅምት 22 ቀን 2013 ዓ.ም] በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ ጋዋ ጋንቃ ቀበሌ ከ200 በላይ አማሮች በማንነታቸው ብቻ ተለይተው በጅምላ በተፈፀመባቸው የዘር ማጥፋት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ይገልፃል።

    በሀገሪቱ ውስጥ ለበርካታ አስርት ዓመታት በአማራ ሕዝብ ላይ ማንነትን መሠረት ያደረገ የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈፅሟል፤ እየተፈፀመም ይገኛል። ጥቃቶቹ ሊደርስ እንደሚችሉ በተደጋጋሚ ያሳወቅን ቢሆንም ተጨባጭ መፍትኼ ሊገኝ አልቻለም።

    የጥቃቱ ምንጭ ውስብስብ እንደሆነ እንረዳለን፤ የአረመኔዎች ቅንጅት ሕዝባችን በደም ጎርፍ እንዲታጠብ አድርጓል። በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈፀመው የዘር ማጥፋት ወንጀል ተባብሶ ቀጥሏል።

    መንግሥትም በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈፀመውን ተደጋጋሚ የዘር ማጥፋት ወንጀል በስሙ ከመጥራትና ብሔራዊ የደህንነት ስጋት አድርጎ ጥቃቱን ከማስቆምና የችግሩን ፈጣሪዎች በቅጡ ለይቶ የሚመጥን እርምጃ በወቅቱ ከመውሰድና የሕዝቡን ደኅንነት ከመጠበቅ ይልቅ እሹሩሩ በማለትና ወንጀሉን በማድበስበስ የወንጀሉ ተባባሪ ሆኖ ይገኛል።

    በተለይም የኦነግ ሸኔ ኃይል ከኤርትራ ሙሉ ትጥቅ ይዞ እንዲገባ በማድረግ በየቦታው ካሉ አማራ-ጠል ፅንፈኛ ኃይሎች ጋር በቅንጅት አማራዉን ማኅበራዊ ረፍት ለመንሳትና በጅምላ ለመጨፍጨፍ እንዲችሉ ፍቃድ የሰጣቸው የፌደራል መንግሥቱ ነው።

    በአማራ ሕዝብ ላይ በየቦታው እየተፈፀመ ያለውን የዘር ማጥፋት ለማውገዝ የተጠራውን ሰልፍ አማራ ማዘን እንኳን አይችልም በሚል እርቃን በወጣ አምባገነንነት የከለከለ መንግሥት ሕዝባችን ላይ የሚደርስን ቀጣይነት ያለው ጥቃት ለማስቆም ፍላጎት ማጣቱ ጥቃቱን እንደሚፈልገው አብይ ማሳያ ነው።

    ሕዝባችን የዘር ማጥፋት ታውጆበትና መንግሥትም የጥቃቱ ተባባሪ ሆኖ ከገዳዮቹ ጋር በአንድ ሀገር ለመቀጠል የሚቸገር በመሆኑ ሁሉም የሀገሪቱ ጉዳይ ይመለከተኛል የሚል አካል ተገቢውን እንቅስቃሴ እንዲያደርግ አብን ጥሪ ያስተላልፋል።

    ሕዝባችንም በየቦታው የሚፈፀምበትን የዘር ማጥፋት ወንጀል ተደራጅቶ እንዲመክት አብን ጥሪውን ያቀርባል።

    ውድ አማራዉያን፥ አሁን ሐዘናችንንና ቁጭታችንን በቅጡ ለመግለፅ እንኳ አቅም ማጣታችን ግልፅ ነው። ከሂደቶች የምንገነዘበው ተጨማሪ ጥቃቶች ሊከፈቱ እንደሚችሉ ነው። ፈጣን ምክክር በማድረግ የኅልውና አደጋዉን በዘላቂ ሁኔታ ለመቀልበስ በቂ ዝግጅት ማድረግ አለብን።

    ይህ ጉዳይ በመደበኛ እንቅስቃሴ ሊመከት አልቻለም። የአማራ ሕዝብ የሀገራዊ ፖለቲካው ሽኩቻ ሁሉ ብቸኛና ቋሚ ማስያዥያ ሆኖ ቀጥሏል። አሁን የሕግ የበላይነት ቦታ አጥቷል። መንግሥት ሕግ የማስከበርና የሕዝብን ደኅንነት የመጠበቅ ኃላፊነቱን መወጣት አለመፈለጉና አለመቻሉ ተረጋግጧል። ቀሪው ነገር የአማራ ሕዝብ ተደራጅቶ ራሱን ይከላከል የሚለው ነው።

    አብን ከሕዝቡ ጎን ተሰልፎ የድርሻውን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ያረጋግጣል። አብን የተደራጁ የትግል ስልቶችን ነድፎ ለሕዝባችን ይፋ እንደሚያደርግም ለመጠቆም ይወዳል።

    በድጋሚ ነፍስ ይማር።

    የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)

    በአማራ ሕዝብ ላይ እየተፈፀመ ላለው የዘር ማጥፉት ወንጀል ኃላፊነቱን መንግሥት ይወስዳል

    Anonymous
    Inactive

    የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን በምዕራብ ወለጋ ዞን በተፈጸመው ጥቃት ህይወታቸው ያለፉ ሰዎች ቁጥር 32 እንደሆነ ገለጸ

    • የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መልዕክት
    • የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን መልዕክት
    • የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ጋዜጣዊ መግለጫ
    • የብልጽግና ፓርቲ ጋዜጣዊ መግለጫ
    • የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) መልዕክት
    • የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) መግለጫ
    • የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) መግለጫ

    የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ ጋዋ ቃንቃ ቀበሌ በተፈጸመው ጥቃት ህይወታቸው ያለፉ ሰዎች ቁጥር 32 እንደሆነ ገለጸ።

    የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል አራርሳ መርዳሳ ጥቅምት 23 ቀን 2013 ዓ.ም. ማምሻውን ለኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) እንዳሉት፥ በጥቃቱ የተነሳ የተፈናቀሉ 200 ያህል አባወራዎችን የማረጋጋትና ሥራ እየተሠራ ነው።

    በተፈጸመው ጥቃት 23 ወንድ እና 9 ሴቶች በድምሩ 32 ሰዎች ህይወታቸው ማለፉን የገለጹት ኮሚሽነር ጄኔራሉ፥ 10 ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸው ሕክምና እየተከታተሉ እንደሚገኙ አመልክተዋል።

    በጥቃቱ የመኖሪያ ቤቶችና አንድ ትምህርት ቤት እንደተቃጠለ ተናግረው፥ ከአካባቢው ሕብረተሰብ ጋር በመተባበር መልሶ የማቋቋም ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል።

    የጥቃት ድርጊቱን የፈጸመው አካል ኦነግ ሸኔ መሆኑን ገልጸው፥ ከጀርባ በመሆን የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) እየደገፈው እንደሚገኝ ተናግረዋል። በተለይም ቡድኑ የታጠቃቸው እንደ ስናይፐርና ብሬል ያሉ የጦር መሳሪያዎች ህወሓት ያስታጠቀው እንደሆነ ገልጸዋል። ከኦነግ ጀርባ በመሆን ህወሓት በህብረተሰቡ ላይ ጥፋት እያደረሰ እንደሆነም አክለዋል።

    ጥቃት የተፈጸመበት ቀበሌ ከወረዳ ከተማ በ75 ኪሎ ሜትር የሚርቅ መሆኑን ገልጸው፥ ህወሓት በብሔሮች መካከል ግጭት ለመፍጠር በስሌት የፈጸመው ተግባር ስለመሆኑ ተናግረዋል።

    ከድርጊቱ ፈጻሚዎች መካከል የተወሰኑት መያዛቸውን ተናግረው ቀሪዎቹን ለመያዝ እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸው፥ ተመሳሳይ ጥቃት እንዳይፈጸም ከሕብረተሰቡ ጋር እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

    • የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መልዕክት

    በተያያዘ ዜና፥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ኢትዮጵያውያን ላይ እየተፈጸመ ባለው ማንነትን መሠረት ያደረገ ጥቃት ከምንጩ ለማድረቅ መንግስት የሚወስደውን ርምጃ በመደገፍ ሕዝቡ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የጸጥታ አካላት ምሁራንና ሌሎችም የሚጠበቅባቸውን እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ያሰፈሩት መልዕክት እንደሚከተለው ይነበባል።

    “በኢትዮጵያውያን ላይ እየተፈጸመ ባለው ማንነትን መሠረት ባደረገው ጥቃት እጅግ ማዘኔን እገልፃለሁ።

    የኢትዮጵያ ጠላቶች፤ “ወይ እኛ እንገዛለን፤ ወይ ሀገር አትኖርም” ብለው ተነሥተዋል። ለዚህም የጥፋት አቅማቸውን ሁሉ እየተጠቀሙ ነው። አንደኛው ዒላማቸውም የሕዝባችንን ቅስም መስበር ነው።

    ለዚህ እየተጠቀሙበት ያለው ስልት ግራ ቀኝ የማያውቁ ሰዎችን እየሰበሰቡ በማሠልጠንና በማስታጠቅ በየአካባቢው ማንነትን መሠረት ያደረገ አረመኔያዊ ጥቃት ማድረስ ነው። ይህ ተግባር ሕዝቡ እንዲደናገጥ፣ እንዲፈራና በስሜት ያልተገባ ርምጃ እንዲወስድ የታለመ ነው።

    መንግሥት በተለያዩ ቦታዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ ያላቸውን ጥፋቶች በቅድሚያ መረጃ ሰብስቦ ርምጃ በመውሰድ ሲያከሽፍ ቆይቷል። ነገር ግን ያለፈው ሥርዓት ያወረሰንን ቀዳዳዎች ሁሉ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ደፍኖ መጨረስ አልተቻለም።

    የጥፋት ኃይሎች ከውጭ ላኪዎቻቸውና በመንግሥት መዋቅር ውስጥ በሚገኙ ባልጠሩ አድር ባዮች ትብብር በሕዝባችን ላይ አሳዛኝ ጥቃት እያደረሱ ነው። ሁኔታው እንደ መሪም እንደ ዜጋም ልብ ይሰብራል።

    ይህ ግን ከመንገዳችን ወደኋላ፣ ከግባችን ወደ ሌላ አያደርገንም። ተስፋ ቆርጠን እንድናቆም፣ ተሸንፈን እንድናፈገፍግ አያደርገንም። ከምንጊዜውም በላይ ኃይላችንን አሰባስበን እንድንነሣ ያደርገናል እንጂ።

    መንግሥት ሁሉንም ዓይነት አማራጮች ተጠቅሞ የችግሩን ሰንኮፍ ይነቅለዋል። የጸጥታ አካላት ጥቃቱ ወደተፈጸመበት አካባቢ ተሠማርተዋል። ርምጃም እየወሰዱ ነው። በቀጣይም የሕዝባችንን ደኅንነት ለማስጠበቅ መንግሥት የመንግሥትነቱን ሥራ በቁርጥና በጽናት ይሠራል።

    ሕዝቡ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የጸጥታ አካላት፣ ምሁራንና ሌሎችም፧ መንግሥት ችግሩን ከምንጩ ለማድረቅ የሚወስደውን ርምጃ በመደገፍ የሚጠበቅባቸውን እንዲያደርጉ ጥሪ አቀርባለሁ።”

    • የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን መልዕክት

    የኢፌዲሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ በንፁኃን ዜጎች ላይ የተፈፀመውን አሰቃቂ ጭፍጨፋ በማስመልከት መልዕክት አስተላልፈዋል። አቶ ደመቀ መኮንን ባስተላለፉት መልዕክት የሚከተለውን ብለዋል።

    “በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ በንፁሃን ዜጎች ላይ የተፈፀመው አሰቃቂ ጭፍጨፋ የተሰማኝን ሀዘን እየገለፅኩ፥ ለሟች ቤተሰቦች መፅናናትን እመኛለሁ።

    በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ቀደም ሲል ብሔርን፣ ሀይማኖትን እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት የማድረስ ዓላማ ያላቸው ጥቃቶችና ጭፍጨፋዎች ተካሂደዋል። በተመሳሳይ በምዕራብ ወለጋ ዞን በንፁሃን ዜጎች ላይ አሰቃቂ ጭፍጨፋ ተፈፅሟል።

    በተለይ የአማራን ማኅበረሰብ ትኩረት ያደረገና በንፁሃን ዜጎች ላይ የሚካሄደው ጭፍጨፋ ፍፁም አረመኔያዊና በፍጥነት መቆም ያለበት እኩይ ድርጊት ነው። ድርጊቱ አስቀድሞ መዋቅራዊ በሆነ መልኩ ሲዘራ የቆየ በመሆኑ፥ ችግሩን የሚመጥን መፍትሄ በዘላቂነት ለማበጀት አስፈላጊው ሁሉ ይደረጋል። ከዚህ አኳያ የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ እንዲሁም ከሁሉም አቅጣጫ የሚቃጡ ጥቃቶችን ለመመከት የመንግሥትና ሕዝብ ቅንጅታዊ ርብርብ ተጠናክሮ ይቀጥላል።”

    • የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ጋዜጣዊ መግለጫ

    ይህንን ጥቃት ተከትሎ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ባወጣው መግለጫ በአማራ ሕዝብ ላይ በየቦታው እየተፈፀመ ላለው የዘር ማጥፉት ወንጀል ሙሉ ኃላፊነቱን መንግሥት ይወስዳል ብሏል። ሙሉ መግለጫውን እዚህ ጋር በመጫን ያንብቡ።

    • የብልጽግና ፓርቲ ጋዜጣዊ መግለጫ

    የብልጽግና ፓርቲ በበኩሉ፥ ንጹሃን ዜጎችን በማንነታቸው በጅምላ ማጥቃት የሽብር እንጂ የፖለቲካ ትግል ሊሆን እንደማይችል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል። ሙሉ መግለጫውን እዚህ ጋር በመጫን ያገኙታል።

    • የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) መልዕክት

    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) “በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ በዜጎች ላይ ማንነትን መሠረት ባደረገ ጥቃት በተገደሉት እና ጉዳት በደረሰባቸው ኢትዮጵያውያን የተሰማንን ሀዘን እንገልፃለን” በማለት የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ክፍል መልዕክቱን አስተላልፏል።

    ፓርቲው በዚሁ መልዕክቱ፥ ኢትዮጵያውያን በዚህ አስቸጋሪ ወቅት በአንድነት በመቆም የዘውግ ፖለቲካ ያመጣብንን በሕይወት የመኖር እና እንደ ሀገር የመቀጠል አደጋ ልንታገለው እንደሚገባና፤ ኢዜማ አጠቃላይ የሀገራችንን ሁኔታ አስመልክቶ በቀጣይ ቀናት መግለጫ እንደሚሰጥ አመላክቷል።

    በማስከተልም፥ በምዕራብ ወለጋ ጉሊሶ ወረዳ ማንነትን መሰረት አድርጎ የተፈፀመው ጥቃት የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ሐዘን ሲሆን፤ የጥቃቱ ዓላማም ሀገርን የማፍረስ መሆኑን ተረድተን ሀዘናችንን በጋራ በመግለፅ በአንድነት እንድንቆም እንጠይቃለን ሲል መልዕክቱን ቋጭቷል።

    • የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) መግለጫ

    የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) በሰላማዊ ሰዎች ላይ የደረሰውን ጥቃት ካወገዘ በኋላ፥ መንግሥት ጥቃቱን ያደረሱት ህወሓትና ኦነግ ሸኔ ናቸው ማለቱን በከፊል በማስተባበል፤ ይልቁንስ ኦነግ ሸኔ የሚባል ቡድን በአካል እንደሌለ ገልጿል። የኦነግን ሙሉ መግለጫ እዚህ ጋር በመጫን ያገኙታል።

    • የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) መግለጫ

    የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ደግሞ በሰጠው መግለጫ፥ በአማራ ሕዝብ ላይ እየደረሰ ላለው ዘር-ተኮር ጥቃት የፌደራል መንግሥቱን የሚመራው ብልጽግና ፓርቲ  ግንባር ቀደም ተጠያቂ እንደሆነ አትቷል። ሙሉ መግለጫውን እዚህ ጋር ያገኙታል።

    በምዕራብ ወለጋ ዞን በተፈጸመው ጥቃት ህይወታቸው ያለፉ ሰዎች ቁጥር

Viewing 15 results - 1 through 15 (of 27 total)