-
Search Results
-
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ያካሄደውን አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ በሊቀመንበርነት ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔን በአቶ በለጠ ሞላ ጌታሁን በመተካት፣ ዘጠኝ የሥራ አስፈፃሚ አመራሮችን እና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን በመምረጥ ተጠናቀቀ።
ደብረ ብርሃን (አብን) – የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ የካቲት 14 እና 15 ቀን 2012 ዓ.ም. አንደኛ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔውን የምርጫ ቦርድ ታዛቢ በተገኘበት በደብረ ብርሃን ከተማ አካሂዷል።
ጉባዔውን በንግግር የከፈቱት የንቅናቄው ሊቀመንበር ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ አብን የአማራን ሕዝብ ጥያቄ መመለሥ በሚያስችለውና ወቅቱ በሚፈልገው ልክ ይገኝ ዘንድ ላለፉት ጊዜያት የመጣበትን መንገድ መርምሮ በጥናት ላይ የተመሠረተ መዋቅራዊ ማሻሽያ መዘጋጀቱን ገለፀው በዚህ ላይ ጠቅላላ ጉባዔው በደንብ ተወያይቶ አቋም እንዲይዝበት ጠይቀዋል።
ጉባዔው በመጀመረያ ቀን ውሎው የአብን መዋቅራዊ ማሻሽያ (reform) አስፈላጊነትና አላማ፣ የንቅናቄው ጥቅል የሥራ ክንውን ሪፖርት፣ የፋይናንስ ኦዲትና ኢንስፔክሽን ሪፖርት፣ የብሔራዊ ምክር ቤቱ ሪፖርት፣ የተሻሻለው የንቅናቄው መተዳደሪያ ደንብና ቀርቦ በጠቅላላ ጉባዔው አባላት ሰፊ ውይይት ካደረገ በኃላ አፅድቋል።
ጠቅላላ ጉባዔው 5 ተለዋጭ አባላት ያሉት 45 የንቅናቄውን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን በሚስጥር ድምፅ አሰጣጥም መርጦ ያፀደቀ ሲሆን የተመረጡት አባላትም የድርጅቱን ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር መርጠዋል። በተጨማሪም በሊቀመንበሩ የቀረቡለትን ብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚዎችን አፅድቋል። በዚህም መሠረት 9ኙ የአብን ሥራ አስፈፃሚ አመራሮች፦
- አቶ በለጠ ሞላ ጌታሁን – ሊቀመንበር፣
- አቶ የሱፍ ኢብራሂም – ምክትል ሊቀመንበር፣
- አቶ አዲስ ኃረገወይን – የፖሊሲ ስትራቴጂ ኃላፊ፣
- አቶ ጣሂር ሞሐመድ – የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ፣
- ዶ/ር ቴዎድሮስ ኃ/ማርያም – የውጭ ጉዳይ እና ዓለማቀፍ ግንኙነት
- አቶ ጋሻው መርሻ – የአደረጃጀት ጉዳይ ኃላፊ፣
- አቶ መልካሙ ፀጋዬ – የፅሕፈት ቤት ኃላፊ፣
- አቶ ጥበበ ሰይፈ – የሕግ እና ሥነ-ምግባር ኃላፊ፣ እና
- አቶ ክርስቲያን ታደለ – የፓለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ ናቸው።
ምንጭ፦ አብን/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
—–
ተመሳሳይ ዜናዎች፦
- የህወሓት አመራሮችና አባላት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸውን ተከትሎ ህወሓት የሰጠው መግለጫ
- ዶክተር መሐሪ ታደሰ ወልደጊዮርጊስ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሆነው ተሾሙ
- ኢህአዴግ ሙሉ ለሙሉ መፍርሱን እና ብልጽግና ፓርቲ ከህወሓት ጋር ንብረት እንዲከፋፈል ምርጫ ቦርድ አጸደቀ
- በኢትዮጵያ መንግሥት እየተፈጸመ ያለዉ የሰብዓዊ መብት ረገጣ በነፃ እና ገለልተኛ አካል ምርመራ ሊደረግበት ይገባል ― ኦነግ
- በየትኛውም ወገን የሚፈፀም፣ ሥርዓት አልበኝነት በቃ ለማለት ጊዜው አሁን ነው! የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ
ምርጫ የሚደረግበት የመጨረሻ ቀን ወደፊት ይገለጣል፤ ጊዚያዊ የምርጫ ቅስቀሳ ማድረግ አይቻልም
አዲስ አበባ (ዶይቸ ቬለ አማርኛ) – ኢትዮጵያ ዉስጥ ምርጫ የሚደረግበት የመጨረሻ ጊዜ ወደፊት ይፋ እንደሚያደርግ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ አስታወቀ። ቦርዱ ነሐሴ 10 ቀን 2012 ዓ.ም.ን ጊያዊ የምርጫ ቀን ማድረጉን በቅርቡ አስታዉቆ ነበር። የቦርዱ ቃል አቀባይ ወ/ት ሶሊያና ሽመልስ ጥር 13 ቀን 2012 ዓ.ም. እንዳስታወቁት ግን የመጨረሻዉ የምርጫ ቀን ከፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችና “የሕብረተሰብ ክፍል” ካሏቸዉ ወገኖች ጋር ቦርዱ ከተወያየ በኋላ ይወሰናል። ቦርዱ ያስቀመጠዉ ጊዜያዊ የምርጫ ቅስቀሳ ጊዜ ሳይጀመር የምረጡኝ ቅስቀሳ በሚያደርጉት ፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ በመመርመር ላይ እንደሆነም የቦርዱ ቃል አቃባይ ወ/ት ሶሊያና ሽመልስ ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ የዘንድሮዉ ምርጫና ዝግጅቱ የሚደረግበት ጊዜያዊ የጊዜ ሰሌዳ በቅርቡ ይፋ አድርጓል። በጊዜ ሰሌዳዉ መሠረት ካለዉ ታህሳስ 22 ቀን ጀምሮ የምርጫ ክልል ቢሮዎችን እያደራጀ ነዉ። የቦርዱ የተረጋገጠ ውጤት ማሳወቂያ ጊዜን ነሐሴ 20 ቀን 2012 ዓ.ም. ለማድረግ ጊዚያዊ ቀጠሮ መያዙንም ነው ይፋ የተደረገው የጊዜ ሰሌዳ የሚያለክተው።
የምርጫ ቦርዱ ጊዜያዊ የጊዜ ሰሌዳን ሕጋዊ እና ትክክለኛ በማለት ስምምነታቸውን የገለጹ የመኖራቸውን ያህል ምርጫዉ በከባዱ የክረምት ወቅት ይደረጋል መባሉ፣ በመንገድ መሠረተ ልማት እና የወንዞች ሙላት ምርጫው ያለ ችግር ስለመከናወኑ ጥርጣሬ የገባቸው እንዳሉም ታይቷል።
የምርጫ ቦርድ በበኩሉ የመጨረሻ በሚለው የምርጫ ማስፈጸሚያ የጊዜ ሰሌዳ ለማውጣት እየሠራ መሆኑን አስታውቋል። ቀደም ሲል ለመነሻነት ይፋ ያደረገው የጊዜ ሰሌዳ ላይ አስተያየት እያሰባሰበበት ስለመሆኑም ነው የቦርዱ ቃል አቀባይ ወ/ሪት ሶሊያና ሽመልስ ለዶይቸ ቬለ የተናገሩት።
በኢትዮጵያ በየአምስት ዓመቱ ሀገራዊ ምርጫ መካሔድ እንዳለበት በሕገ መንግሥቱ ተደንግጓል። በዚሁ በሥራ ላይ ያለው ሕገ- መንግሥት ሥራ ላይ ከዋለ ለስድስተኛ ጊዜ ሊካሄድ በጊዜያዊነት የተያዘለት ቀነ-ቀጠሮ ውዝግብ ማስነሳቱ ከሕግ አንጻር እንዴት ይታይ ይሆን?
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህሩ ዶ/ር ጌታቸው አሰፋ እንደሚሉት የምርጫ ቦርዱ በሕግ የተሰጠውን ስልጣን ተጠቅሞ ከአሠራሩ ጋር በሚያመቸው መልኩ የጊዜ ሰሌዳ ማዘጋጀት ይችላል በማለት ይናገራሉ። ቦርዱ ሕግን የሚተላለፍ ተግባር እስካልፈጸመ ድረስ በየትኛውም የአየር ጠባይ ውስጥ ቀጠሮውን የመያዝ ስልጣን ቢኖረውም ሁሉን ሊያስማማ ወደ ሚችል የውይይት መድረክ ቢያመራ የተሻለ ውጤት ሊገኝበት እንደሚችል እምነታቸው መሆኑን ያስረዳሉ።
ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ በጊዜያዊነት ይፋ ያደረገው የየምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ተግባራዊ መደረግ ባልጀመረበት አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ቅስቀሳ እና ሕዝባዊ ስብሰባዎችን እያደረጉ መሆናቸው ቦርዱ የፖለቲካ ፓርቲዎቹን በሕግ ማዕቀፍ ውስጥ እንዲንቀሳቀሱ ተገቢውን ቁጥጥር አላደረገም የሚል ወቀሳ እና ትችት ሲሰነዘር ይሰማል።
የምርጫ ቦርድ ቃል አቃባይ ወ/ሪት ሶሊያና ሽመልስ እንደሚሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች ከተሰጣቸው ሕጋዊ የመንቀሳቀሻ መንገድ ወጥተው በሚገኙት ላይ ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ በቅድሚያ ተፈጸሙ የተባሉ የሕግ ጥሰቶች መመርመር አለበት ይላሉ።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ከተዘጋጀላቸው የሕግ ማዕቀፍ ወጥተው ሲገኙ ይህንኑ ለማስተዳደር በወጣው ሕግ ሊዳኙ እንደሚገባ የሚያሳስቡት ደግሞ ዶ/ር ጌታቸው አሰፋ ናቸው። ከሰሞኑ ጀምሮ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያደርጌቸው ጊዜያቸውን ያልጠበቁ የምርጫ ቅስቀሳዎች ወይም የቅስቀሳ ይዘት ያላቸው ሕዝባዊ ስብሰባዎች ሕጋዊ መንገድን ሊከተሉ እንደሚገባም ነው የሚያሳስቡት።
የብሔራዊ የምርጫ ቦርድ የ2012 ምርጫ ቀነ-ቀጠሮን ቁርጥ ባያደርግም የአዳዲስ ተወዳዳሪ ፓርቲዎችን ግን መመዝገቡን ቀጥሏል። ቦርዱ ጥር 13 ቀን 2012 ዓ.ም. እንዳስታወቀው ለአራት ፓርቲዎች የእውቅና ምስክር ወረቀትና ጊዜያዊ የምዝገባ ፈቃድ ሰጥቷል። የእውቅና ምስክር ወረቀትና ጊዜያዊ የምዝገባ ፈቃድ የተሰጣቸው አራቱ ፓርቲዎች ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ፣ አንድ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ አማራ ጊዮናዊ ንቅናቄ እና እናት ፓርቲ ናቸው።
ምንጭ፦ ዶይቸ ቬለ አማርኛ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ ጊዜያዊ ውጤትን አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
ህዳር 13 ቀን 2012 ዓ.ም
ሀዋሳየደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት ኅዳር 12 ቀን 2011 ዓ.ም. ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት የሲዳማ ዞን በክልልነት የመደራጀት ጥያቄ ሕዝብ ውሳኔ ኅዳር 10 ቀን 2012 ዓ.ም. ተካሂዷል።
የሕዝበ ወሳኔው አፈፃፀም ተአማኒ፣ ሰላማዊ እና ፍትሃዊ አንዲሆን ለማድረግ ቦርዱ እስከ ሕዝብ ውሳኔው ድምጽ መስጫ ዕለት ድረስ በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል። ቦርዱ የሕዝበ ውሳኔውን ጥያቄ የማስፈፀም ኃላፊነቱን መወጣት የጀመረው ሂደቱ ፍትሃዊ፣ ሰላማዊ እና ተአማኒ እንዲሆን እንዲሁም በሲዳማ ዞን እና በሀዋሳ ከተማ የሚኖሩ ዜጎች ያለ አድልዎ ፍላጎታቸውን የሚገልፁበት አሠራር ለመዘርጋት የሚያስችል የሲዳማ ሕዝብ ውሳኔ አፈፃፀም መመሪያ በማጽደቅ ነው።
ከዚህ በተጓዳኝ የሕዝብ ወሳኔውን የአፈፃፀም የጊዜ ሰሌዳ በማዘጋጀት ለሚመለከታቸው የክልሉ እና የዞን መስተዳደር አካላት እንዲደርስ ለሕዝብም ይፋ እንዲሆን ተደርጓል። ቦርዱ በሕዝብ ውሳኔው እቅድ አፈፃፀም ከክልሉና የዞኑ መስተዳደር አካላት ጋር በርካታ ውይይት እና ስምምነቶችን አድርጓል። በዚህም መሠረት ለሕዝብ ውሳኔ ማስፈፀሚያ የሚያስፈለገውን በጀት በክልሉ መንግሥት እንዲፈቀድ ተደርጓል። ሕዝብ ውሳኔው በሰላማዊ ሁኔታ ለማስፈፀም አስፈላጊ ሁኔታዎችን የክልሉ ምክር ቤት አስቀድሞ እንዲፈጽም በጠየቀው መሠረት የሕዝቡ ውሳኔ የሲዳማ ዞን በክልልነት እንዲደራጅ የሚል ከሆነ በዞኑ ውስጥ የሚኖሩ ሌሎች ብሔረሰቦች መብት ጥበቃንና አዲስ በሚፈጠረው እና ነባሩ ክልል መሃከል የሚኖረውን የሃብት ክፍፍል የሚወሰንበት አስተዳደርና በሕግ ማእቀፍ አውጥቶ አቅርቧል።
በቅድመ ሕዝበ ውሳኔ ዝግጅት በቦርዱ ባለሞያዎች የመስክ ጥናት አካሂደው የድምፅ መስጫ ጣቢያዎችን መረጃ አደራጅተዋል። በዚህም መሠረት ለሕዝበ ውሳኔው ማስፈጸሚያ 1692 ምርጫ ጣቢያዎች የተቋቋሙ ሲሆን ከድምጽ ሰጪዎች ምዝገባ በኋላ ተጨማሪ 169 የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች ተደራጅተዋል። የሕዝብ ወሳኔው አፈፃፀም ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ እንዲያስችል የክልሉ፣ ከዞኑ፣ ከሀዋሳ ከተማ እንዲሁም የፌደራል የጸጥታ ተቋማት እና አስተዳደር ተቋማት የሕዝበ ውሳኔው ፀጥታ ዕቅድ አዘጋጅተው አቅርበዋል። የዕቅዱንም አፈጻጸም ቦርዱ በጋራ ሲከታተል ቆይቷል። ከቅድመ ሕዝበ ውሳኔ ዝግጅት እስከ ድኅረ ሕዝበ ውሳኔ የነበረው የፀጥታና ደኅንነት ሁኔታ በዚህ ዕቅድ መሠረት በጋራ ኮሚቴ በየጊዜው እየታየ ሰላማዊ ሕዝበ ውሳኔ ለማካሄድ ተችሏል።
ሕዝበ ውሳኔውን በገለልተኝነትና በሕግ መሠረት የሚያስፈፅሙ 6843 አስፈፃሚዎችን ከአዲስ አበባ ከተማ እና ኦሮሚያ ክልል አከባቢዎች በመመልመል በዞኑ ያሰማራ ሲሆን ሁሉም አስፈጻሚዎች ሕዝበ ውሳኔውን እንዴት እንደሚያስፈጽሙ ስልጠና ተሰጥቷቸዋል። ስልጠናውም ቀድመው የአሰልጣኞች ስልጠና በወሰዱ 20 አሰልጣኞች ለ5 ቀናት የተከናወነ ሲሆን ሁሉም አስፈጻሚዎች የታተመ የማስፈጸሚያ መመሪያ (manual) እንዲኖራቸው ተደርጓል።
የመራጮች ምዝገባ በዞኑ እና በሀዋሳ ከተማ መስተዳድር ለሚኖሩ ማንኛውም ሕጋዊ መስፈርቱን ለሚያሟሉ ዜጎች ክፍት ሆኖ ከጥቅምት 27 እስከ ህዳር 06 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ምዝገባው ተካሂዶ 2,280,147 ድምጽ ሰጪዎች ተመዝግበዋል።
የድምጽ ሰጪዎች ሕዝበ ውሳኔው ድምጻቸውን ለመስጠት እንዲመዘገቡ ለመቀስቀስ በሬዲዮና በቴሌቪዥን የተለያዩ የምዝገባ መስፈርቶችን የሚገልጹ እንዲሁም ስለድምጽ አሰጣጡ የሚያብራሩ መልእክቶች ተላልፈዋል። በድምጽ ሰጪዎች ምዝገባና ድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ የዜጎች መብት እንዳይገደብ እና የሂደቱን ሰላማዊነት ለማረጋገጥ የሚያግዙ የተለያዩ ተግባራት ተከናውነዋል። ከነዚህም መካከል የመጀመሪያው የቦርዱ አመራር አባላት በሀዋሳ፣ በይርጋለም፣ በወንዶ ገነት፣ በበሌላ፣ በመዘዋወር የድምጽ ሰጪዎች ምዝገባና ድምጽ ሰጪዎች ድምጽ አሰጣጥ ሂደት ክትትል በማድረግ የታዩ ጉድለቶች እና የአሠራር ዝንፈቶች እንዲስተካከሉ ያደረጉ ሲሆን፣ በተጨማሪም ዜጎች በድምጽ ሰጪዎች ምዝገባ እንዲሁም በድምጽ መስጠት ሂደቱ የታዘቧቸውን ግድፈቶች በቀጥታ ለቦርዱ ለማሳወቅ እንዲችሉ የቀጥታ የስልክ መስመሮች ተዘጋጅተው ለመገናኛ ብዙኃን እና ማኅበራዊ ሚዲያ ይፋ ተደርጓል። በደረሱት ጥቆማዎችም መሠረት የተለያዩ የማስተካከያ እርምጃዎች እንዲሁም መረጃዎች ሲሰጡ ቆይተዋል።
በቦርዱ አባላት በተደረጉ ጉብኝቶች እና ቀደም ብሎ ከዞኑ እና ከክልል መስተዳድር ተቋማት ጋር በተደረጉ ተከታታይ ግንኙነቶች በሕዝበ ውሳኔው ሂደት በርካታ ማስተካከያዎች የተደረጉ ሲሆን ከነዚህም ጥቂቶቹ፦
- የአካባቢ ሚሊሻ አባላት የምርጫ ጣቢያዎችን ጸጥታ አጠባበቅ ምንም አይነት ሚና እንዳይኖራቸው ተደርጓል፤
- በሕዝበ ውሳኔው አፈጻጸም ያልተገባ ጣልቃ ገብነት የፈጸሙ ሰዎች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል፤
- በሕዝበ ውሳኔው መራጮች ምዝገባ እና ድምጽ መስጠት ሂደት ሁለቱም አማራጮችን የሚወክሉ ወኪሎች አንዲገኙ ጥረት ተደርጓል፤
- የተጓደሉ የሕዝበ ውሳኔ ማስፈጸሚያ ቁሳቁሶች በፍጥነት እንዲሟሉ ተደርጓል።
የሕዝበ ውሳኔውን ሂደት ሰላማዊ ፣ ፍትሃዊነት እና ግልጽነቱን ለማረጋገጥ፣ እንዲሁም ለወደፊት መሻሻል ላለባቸው አሠራሮች ትምህርት ለመውሰድ ለ128 የሲቪል ማኅበራት ታዛቢዎች እና 74 የአገር ውስጥና የውጪ ሚዲያ ጋዜጠኞች ሂደቱን እንዲታዘቡና እንዲዘግቡ የሚያስችል እውቅና ተሰጥቷል። በተጨማሪም ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጋር በመነጋገር የኮሚሽኑ 20 ታዛቢዎች ሕዝበ ውሳኔውን እንዲታዘቡ ተደርጓል። በኢትዮጵያ መንግሥት ሕዝበ ውሳኔውን እንዲታዘቡ ፍቃድ የተሰጣቸው የአሜሪካን መንግሥት ወኪሎችና ዲፕሎማቶች ሕዝበ ውሳኔን እንዲታዘቡ አስፈላጊው ድጋፍ ተደርጓል።
የድምጽ ሰጪዎች ምዝገባ ከተጠናቀቀበት እስከ ድምጽ መስጫው ቀን ባሉት ጥቂት ቀናት ቦርዱ የድምጽ መስጫ ቁሳቁሶችን ያሰራጨ ሲሆን በዚህም ሂደት 3000 የድምጽ መስጫ ሳጥኖች እና 2.5 ሚሊዮን በላይ (መጠባበቂያን ጨምሮ) የድምጽ መስጫ ወረቀቶች እንዲሁም የተለያዩ ቅጾችና ቁሳቁሶች ስርጭት ተከናውኗል።
በሕዝበ ውሳኔው ሂደት ጸጥታ እና ደኅንነት አስመልክቶ ቦርዱ ሂደቱን በሚመራበት ወቅት የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም መረጃ በመሰብሰብ፣ በሀዋሳ ከተማ እንዲሁም በሌሎች ወረዳዎች የሚገኙ ምርጫ ጣቢያዎች የመስክ ጉብኝት አድርጓል። ከአስተዳደር ወሰን ጋር በተያያዘ እና ቀድሞ ግጭት በነበረባቸው የተወሰኑ ቀበሌዎች ከማኅበረሰብ ክፍሎች የቀረቡ አቤቱታዎችን በማዳመጥ የቦርድ አመራር አባላት በቦታው በመገኘት የመስክ ቅኝቶችን አድርገው ከቀበሌ አስተዳደሮች ጋርም ውይይት አድርገዋል። ከውይይቱም በተጨማሪ የሲዳማ ዞን እና የደቡብ ክልል የጸጥታ አካላት፣ የፌደራል ፓሊስ እንዲሁም የመከላከያ ሰራዊትን ያካተተ የፀጥታ ችግሮችን በጋራ የሚያይ መድረክ በማቋቋም ሂደቱ ሰላማዊ እንዲሆን ተደርጓል።
ኅዳር 10 ቀን 2012 ዓ.ም. የተከናወነው የድምጽ መስጠት ሂደት ሰላማዊ እና ጉልህ የሎጄስቲክስ ችግር ያልታያበት ሲሆን አንዳንድ ቦታዎች ላይ የመራጮች ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ ሰልፎች ከመኖራቸው በስተቀር በታቀደበት ሁኔታ ተጠናቋል። በዕለቱ የቦርድ አመራር አባላት የመስክ ጉብኝቶችን ያካሄዱ ሲሆን የምርጫ ቆጠራውም በዕለቱ ተጠናቆ በየምርጫ ጣቢያዎቹ ተለጥፏል። በዕለቱ ከመራጮች የሚመጡ ጥቆማዎችንም መሠረት በማድረግ የተለያዩ እርምት እርምጃዎች ሲከናወኑ ውለዋል።
በዚህም መሠረት በአጠቃላይ ከተመዘገበው 2,280,147 መራጭ 2,277,063 ሰው ድምጹን ሰጥቷል። ይህም የምርጫ ቀን የድምጽ መስጠት ተሳትፎ (voter turnout) 99.86 በመቶ መሆኑን ያሳያል። ሲዳማ በነባሩ ክልል ውስጥ እንዲደራጅ ጎጆ ምልክትን የመረጠ ሰው ብዛት 33,463 ሲሆን የሲዳማ በክልልነት መደራጀትን ሻፌታን የመረጠ ሰው ብዛት 2,225,249 ነው። በውጤቱም ሻፌታ የመረጠው 98.51 % ሲሆን ጎጆን የመረጠው 1.48 % ነው። ። በሂደቱ የዋጋ አልባ ድምጽ ቁጥር 18,351(0.01%) ነው። የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 47/2/ እና /3/ ማንኛውም ብሄር ብሄረሰብ ወይም ሕዝብ የራሱ ክልል የመቋቋም መብት አለው በማለት በሚደነግገው መሠረት፥ የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ ሕጋዊና ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ ተፈጽሟል። የዞኑ ነዋሪዎች በነፃ ፈቃዳቸው በሰጡት ውሣኔ መሠረት ሲዳማ ክልል ሆኖ መደራጀት የሚያስችለውን ድምፅም በዚህ ውሳኔ አግኝቷል።
የሕዝበ ውሳኔው ሂደት ሰላማዊና ተአማኒ እንዲሁም ከፍተኛ የሕዝብ ተሳትፎ የታየበት ነው። ሕዝበ ውሳኔው ዜጎች መብታቸውን በሰላማዊ መንገድ ተግባራዊ ያደረጉበት እና በሀገራችን የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ አንድ እርምጃ ነው ብሎ ቦርዱ ያምናል። በውጤቱ መሠረትም በሕገ-መንግስቱ አንቀጽ 47/3/መ ላይ እንደተጠቀሰው የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት እና በሲዳማ ዞን አስተዳደር የሕዝቡን ድምጽ ባከበረ፣ ሰላማዊ እና ግልጽ በሆነ መልኩ እንዲሁም ሽግግሩን ጊዜን በጠበቀ ሁኔታ በማከናወን የስልጣን ርክክቡን በአግባቡ አከናውነው ይህንን ሕዝበ ውሳኔ ውጤት እንደሚያስፈጽሙ ቦርዱ የጸና እምነት አለው።
ያጋጠሙ ተግዳሮቶች
የሕዝበ ውሳኔው አፈፃፀም ሰላማዊና ሕጋዊ መሆኑ በዚህ ሂደት የተገኘ በጎ ውጤት ሲሆን፥ ለዝግጅት ከነበረው አጭር ጊዜም አንጻር የቦርዱ አፈጻጸም የተሳካ ነው ብሎ ያምናል። የአፈፃፀም ሂደቱ ጠቃሚ ትምህርት የተገኘበት መሆኑን ያህል ተግዳሮቶች የነበሩበት በመሆኑ ለቀጣይ ትምህርት ይሆን ዘንድ የሚከተሉትን ማንሳት ተገቢ ይሆናል፤- የሕግ ማዕቀፍ እንዲወጣ (የአነስተኛ ቡድኖች መብት ጥበቃ፤ የሀብት ክፍፍል) በቦርዱ የቀረበው ጥያቄ በክልሉ ምክር ቤት የተሰጠው ምላሽ መዘግየት፤
- የሕዝበ ውሳኔው ቅስቀሳ ሂደት የአንድን ወገን አማራጭ ብቻ የቀረበበት መሆኑ እና የሕዝበ ውሳኔውን ሂደት እንዲታዘቡ የክልሉ መንግሥት ወኪሎች እንዲመድብ በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢቀርብለትም አለመመደቡ፤
- የድምጽ መስጫ ጣቢያዎችን ለመወሰን የሚያስፈልገው የሕዝብ ቁጥር የተሟላ መረጃ አለመኖር፤
- በተወሰኑ የሀዋሳ ከተማን የገጠር አካባቢ ድምፅ መስጫ ጣቢያዎች የማይመለከታቸው ሰዎች መገኘት፣ በድምፅ ሰጪዎች ላይ በአንዳንድ ጣቢያዎች ተፅእኖ የማሳደር ሁኔታ መታየት፤
- በአንዳንድ ቦታዎች በድምፅ ሰጪዎች ብዛት ምክንያት የድምጽ መስጫ ጣቢያዎች መጨናነቅ መከሰቱ፤
- በሕዝበ ውሳኔው ውጤት አገላለጽ ላይ ከሀዋሳ ከተማና ከዞኑ መስተዳድር ተቋማት ኃላፊዎች በቦርዱ ይፋዊ መግለጫ ከመሰጠቱ በፊት አስቀድሞ የመገመት (projection) እና የመግለጽ ችግር መታየቱ፤
- በአንዳንድ የድምጽ መስጫ ጣቢያዎች በሕግ የተቀመጠን የምርጫ ጣቢያ መክፈቻ እና መዝጊያ ሰዓት አለመጠበቅ እንደዋና ተግዳሮት የሚጠቀሱ ሲሆን (ማለትም የክልሉ የጸጥታ ተቋማት፣ የደቡብ እዝ የአገር መከላከያ ሠራዊት) የሕዝበ ውሳኔ ቁሳቁስ ማጓጓዝ፣ የአካባቢ ጸጥታ እና ደኅንነትን በመጠበቅ፣ የአስፈጻሚዎች ስምሪትን እንዲሁም ድምጽ የተሰጠባቸውን ሰነዶችን ጥበቃ በማድረግ እጅግ የሚመሰገን ድጋፍ ማድረጋቸው እና በሕዝበ ውሳኔው ሂደት ከፍተኛ ቅንጅት መኖሩ እንደትልቅ ስኬት የሚነሳ ነው።
ምስጋና
በሲዳማ የክልልነት የመደራጀት ሕዝበ ውሳኔ እስካሁን በአገራችን ከነበረው ልምድ የተለየ እና መጀመሪያው ቢሆንም ሰላማዊ እና ሕጋዊ በሆነ ሁኔታ ሊፈጸም ችሏል። ይህንን ሕዝበ ውሳኔ ስኬታማ ለማድረግ ቦርዱ ከተለያዩ አካላት፣ ተቋማት እና ግለሰቦች ድጋፍ አግኝቷል። በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለሚከተሉት ተቋማትና ግለሰቦች ምስጋናውን ያቀርባል።- በሕዝበ ውሳኔው በሰላማዊ እና ሥነ ሥርዓት ባለው ሁኔታ ለተሳተፉት የሲዳማ ዞን ነዋሪዎች በሙሉ፣
- ከመኖሪያ አካባቢያቸው ርቀው በመሄድ ባልተሟላ አንዳንዴም በአስቸጋሪ ሁኔታ ሕዝበ ውሳኔውን ላስፈጻሙ የሕዝበ ውሳኔው አስፈጻሚዎች እና ሥራውን በማስተባበር ለደከሙ የቦርዱ ሠራተኞች፣
- ለሕዝበ ውሳኔው አስፈጻሚዎች ምልመላ ድጋፍ ያደረጉልን፣ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ከንቲባ ፣ ለአዲስ አበባ ሴቶችና ሕጻናት ቢሮ፣ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ፣ የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ፣ ለኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ፣
- ለደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት፣ ለደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስዳድር እና የርዕሰ መስተዳድሩ ሕህፈት ቤት፣
- ለሲዳማ ዞን ምክር ቤት፣
- ለሲዳማ ዞን አስተዳደር፣
- ለሀዋሳ ከተማ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት፣
- ለኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሃገር መከላከያ ሠራዊትና ለአገር መከላከያ ሠራዊት ደቡብ እዝ፣
- ለፌደራል ፓሊስ፣
- ለደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ፓሊስ ኮሚሽን፣
- ለሲዳማ ዞን ፓሊስ፣
- ለሀዋሳ ከተማ ፓሊስ፣
- ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣
- ሕዝበ ውሳኔውን ለመታዘብ ለተሳተፉ ሲቪል ማኅበራት፣
- የተለያዩ እገዛዎችንን ላደረጉልን የአሜሪካን የልማት ድርጅት (USAID/IFES) እና የተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት (UNDP)፣
- ለአዲስ ፓርክ
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) – ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የ2019 የሰላም የኖቤል ሽልማት አሸናፊ ሆኑ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የሰላም የኖቤል ሽልማት ለመቀበል የበቁት ከኤርትራ ጋር ለ20 ዓመታት የዘለቀው አለመግባባት በሰላም በመቋጨታቸውና በአፍሪካ ቀንድ ሰላም እንዲሰፍን ባበረከቱት አስተዋጽኦ መሆኑ ሽልማቱን የሚሰጠው ኮሚቴ ገልጿል።
በሐምሌ 2010 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ኤርትራ ያደረጉት ጉብኝት ዓለምን ያስገረመና ምንም ዓይነት ቅድመ ሁኔታ ያልተቀመጠለት የቅርብ ወዳጅ ዘመድ ጥየቃ ዓይነት ቃና የነበረው ነው። የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጉብኝት ተከትሎ ሁለት ዓይነት ሀሳቦች ቢስተናገዱም ሚዛን የሚደፋው ጉብኝቱ ሰላምን ለማምጣት መሠረት የተደረገ መሆኑ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በአገር ውስጥና በአጎራባች አገሮች እያመጡ ያለውን ጉልህ ለውጥ ተከትሎ ‘ሽልማቱ ይገባቸዋል’ የሚሉ ድምጾች አሸናፊነታቸውን ቀድመው እንዳወጁላቸው ያመለክታል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአጠቃላይ በጎረቤት አገሮች መካከል ሰላምንና አብሮነት ለማስረጽ ባደረጉት ጥረት የዘንድሮው የሰላም ኖቤል አሸናፊ ሆነው ተመርጠዋል።
ኖርዌይ ላይ አሸናፊው ይፋ ሲደረግ በኮሚቴው እንደተገለጸው፥ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥረት እውቅናና ማበረታቻ ያስፈልገዋል።
በእንግሊዝ ኪል ዩኒቨርሲቲ (Keele University) የህግ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ኢትዮጵያዊው አወሎ አሎ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሁለቱ አገሮች መካከል የነበረው ገጭት እንዲያበቃ በማድረጋቸው ሽልማቱ ይገባቸዋል” ማለት ግጭቱ በሁለቱ አገሮች ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ኪሳራ እንዳስከተለና የማይተካውን ብዙ ህይወት እንደቀጠፈም ተናግረዋል።”
ከኤርትራ ጋር የወረደው ሰላም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍ ያለ ሙገሳ ያስገኘላቸው ሲሆን ለሁለቱ አገሮች ወንድማማች ህዝቦች ደግሞ ትርጉሙ ከዚህ የላቀ ነበር። በተለይ ተለያይተው የነበሩ ቤተሶች ሲገናኙ ያፈሰሱት የደስታ እምባ ሰላም ምን ያህል ዋጋ እንዳላት በተጨባጭ የመሰከረ ነው።
- ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በአገር ውስጥ የጀመሯቸው የለውጥ ማሻሻያዎች የፖለቲካ እስረኞችንና ጋዜጠኞችን በመልቀቅ ተጀምሮ ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ አሸባሪ ተብለው የተፈረጁ ግለሰቦችንና ድርጅቶችን እንኳን ደህና መጣችሁ ብለው አስከመቀበል የዘለቀ ነው።
- ኢትዮጵያና ኤርትራ በሐምሌ ወር 2010 ዓ.ም. የተፈራረሙት የሰላም ስምምነት በሁለቱ አገሮች መካከል የነበረውን አለመግባባት በመፍታት በቀጠናው የሰላም አየር እንዲነፍስ መሠረት ጥሏል።
- በሱዳን የተነሳውን የለውጥ ፍላጎት ከዳር ለማድረስ የተጀመረው ተቃውሞ በሰላም እንዲጠናቀቅና ተቃዋሚዎች ከወታደራዊ ቡድኑ ጋር ሰላም እንዲያወርዱ ያደረጉት አስተዋጽኦ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በሱዳናውያን ልብ ውስጥ ትልቅ ቦታ እንዲያገኙ አድርጓቸዋል። በተለይ በሰኔ 2011 ዓ.ም ወደ ሱዳን በማቅናት ሁለቱን አገሮችለማስማማት የጀመሩትን ጥረት ሳዑዲ አረቢያና የተባበሩት አረብ ኢምሬት እንዲደግፉት በማድረግ ለውጤት እንዲበቃ አድርገዋል።
- ከዚህ ባለፈ ኤርትራና ጂቡቲ ጀርባ የተሰጣጡበትን አለመግባባቶች በሰላም እንዲቋጩና ለጋራ እድገት በጋራ እንዲነሱ የማይተካ ሚና ተጫውተዋል።
- በደቡብ ሱዳን የሰላም ድርድር በአፍሪካ ቀንድአገሮች መካከል የኢኮኖሚ ህብረት እንዲኖር ያደረጉት ጥረት ለሰላምና ወንድማማችነት ያላቸውን ክፍት ልብ ያሳየ ነው።
- ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአገሪቱ የተጀመረውን ለውጥ ከግብ ለማድረስና ሁሉንም ያማከለ እንዲሆን የማይደፈረውን ደፈረው ተንቀሳቅሰዋል።
- በዚህም ከዚህ በፊት በተቃዋሚነት ተፈርጀው ለእስር የተዳረጉትን አቶ ዳንኤል በቀለን የአገሪቱ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አድርገው የሾሟቸው ሲሆን ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳን ደግሞ የምርጫ ቦርድ ሊቀመንበር አድርገዋቸዋል።
- በተጨማሪም ከተቃዋሚ ፖለቲከኞች ጋር ፊት ለፊት በመገናኘት በአገሪቱ መፃኢ ዕድል ላይ ውይይት ማድረጋቸው ሌላው ስኬታቸው ነው። በውጭ አገር ተቀምጠው የአገሪቱን ፖለቲካ ለመዘወር ሲጥሩ ከነበሩት ተቃዋሚዎች ጋርም ሰላም በማውረድ አገራቸው ገብተው እንዲታገሉ ሜዳውን ከፍተውላቸዋል።
- የደህንነቱንና የፍትህ ዘርፉንም ተአማኒ ለማድረግ በሩን ክፍት በማድረግ ተቋማዊ ለውጥ እንዲያመጡ እያገዙ ነው።
- በአገሪቱ ወደ ኋላ የቀረውን የሴቶች ተሳትፎ ከነበረበት አዘቅት በማውጣት ሴቶች በአመራርነት ቦታ ላይ ተመጣጣኝ ውክልና እንዲኖራቸውም አድርገዋል።
- በአንድ ጀንበር 200 ሚሊዮን ችግኝ በመትከል ለአየር ንብረት ለውጥ መስተካከል ያላቸውን ቁርጠኝነት አሳይተዋል። በዚህም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አብሮነቱንና ዕውቅናውን ሰጥቷቸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የኖቤል ሽልማት 100ኛው አሸናፊ ናቸው። የኖቤል የሰላም ሽልማትን የሚያሸንፉ ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች 900 ሺ ዶላር የሚሰጣቸው ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በመጪው ታህሳስ ወር በኦስሎ ሽልማታቸውን ይወስዳሉ።
በአጠቃላይ 301 ዕጩዎች ለዚህ ታላቅ ክብር ታጭተው የነበረ ሲሆን ከነዚህ መካከል 223 ግለሰቦችና 78 ድርጅቶች ይገኙበታል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
‘በሕገ-ረቂቁ እንዲካተቱ ያቀረብናቸው ማሻሻያዎች አልተካተቱም፤ ሃሳቦቻችንና አስተያየቶቻችን ያልተካተቱበትን ሰነድ ለመቀበል እንቸገራለን’ በማለት የተወሰኑ የተፎካካሪ ፓርቲ ተወካዮች መድረኩን ረግጠው መውጣታቸውን የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታውቋል።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኢትዮጵያ ምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ሕገ-ረቂቅ አዋጅ ዙሪያ ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ከተለያዩ ማኅበራት ተወካዮች ጋር ተወያይቷል።
‘በሕገ-ረቂቁ እንዲካተቱ ያቀረብናቸው ማሻሻያዎች አልተካተቱም፤ ሃሳቦቻችንና አስተያየቶቻችን ያልተካተቱበትን ሰነድ ለመቀበል እንቸገራለን’ በማለት የተወሰኑ የተፎካካሪ ፓርቲ ተወካዮች መድረኩን ረግጠው መውጣታቸውን የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታውቋል።
እንዲካተቱ ያቀረብናቸው ማሻሻያዎች ሳይካተቱ ሕገ-ረቂቁ እንዳይጸድቅ ሲሉ የተፎካካሪ ፓርቲ ተወካዮቹ ቋሚ ኮሚቴውን አሳስበዋል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ የሺእመቤት ነጋሽ በበኩላቸው መሠረታዊ ማሻሻያዎች የተደረገባቸው አሥራ ሦስት ነጥቦች በሕገ-ረቂቁ መካተታቸውን ገልጸው፣ የብዙሃኑን የተፎካካሪ ፓርቲ ሃሳብና አስተያየት አካተናል ብለዋል።
ማሻሻያዎቻችን አልተካተቱም ያሉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች እስከ ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ ለቋሚ ኮሚቴው በጽሑፍ ማቅረብ እንደሚችሉም ወይዘሮ የሺእመቤት አሳውቀዋል።
በውይይቱ ላይ የመንግሥት ሠራተኞች ለምርጫ በዕጩነት ከተመዘገቡበት ጊዜ ጀምሮ የምርጫ ሂደቱ እስኪጠናቀቅ ድረስ ከሥራ ገበታቸው በጊዜያዊነት እንደሚለቁና ደመወዝና ጥቅማ-ጥቅማቸውም እንደማይከር በሚዘረዝረው ረቂቅ-ሕግ አንቀጽ 33 ላይ ሰፋ ያለ ውይይት ተደርጎበታል።
በደመወዙ ኑሮውን መደጎም ያልቻለን የመንግሥት ሠራተኛ ለምርጫ በዕጩነት ከተመዘገበበት ጊዜ ጀምሮ ደመወዙና ጥቅማ-ጥቅሙ አይከበርም ማለት ወደ ምርጫ አትግቡ ከማለት ለይተን አናየውም ብለዋል የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮቹ።
የመንግሥት ሠራተኞች በሥራ ኃላፊነት ያገኙትን ስልጣን፣ የመንግሥትንና የሕዝብን ሃብትና ንብረት ለምርጫው አገልግሎት እንዳያውሉት ለማስቻል እንደሆነ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ ተናግረዋል።
ረቂቅ ሕጉ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ምሥረታ ጀምሮ እስከ የመሥራች ቁጥር አባላት ድረስ አዳዲስ አሠራሮችን እንዳካተተም ተገልጿል።
አንድ ሃገር-አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲ ለመመሥረት ቢያንስ አስር ሺህ እንዲሁም አንድ የክልል ፓርቲ ለመመሥረት ደግሞ ቢያንስ አራት ሺህ አባላት እንደሚያስፈልጉ በረቂቅ ሕጉ ተጠቅሷል።
ሃገር አቀፍም ሆነ የክልል ፓርቲ ለመመሥረት ሃገሪቱ ያለችበት ተጨባጭ ሁኔታ የተጠቀሰውን የመሥራች ቁጥር አባላት ለማሟላት እንደሚቸገሩ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎቹ ተናግረዋል።
መቶ ሚሊዮን ሕዝብ ባለበት ሃገር የተጠቀሰውን የመሥራች ቁጥር አባል ማሟላት አስቸጋሪ እንደማይሆን ወይዘሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ አብራርተዋል።
በግንቦት ወር 2011 ዓ.ም. 107 የነበሩ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ቁጥር አሁን ላይ 137 እንደደረሰ ወይዘሪት ብርቱካን ገልጸዋል።
ምንጭ፦ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
[caption id="attachment_11503" align="aligncenter" width="600"] የተፎካካሪ ፓርቲ ተወካዮች[/caption]