-
Search Results
-
የወላይታ ዞን ምክር ቤት 4ተኛ ዙር 7ተኛ ዓመት 2ኛ አስቸኳይ ጉባኤ በጠራው ስብሰባ ላይ ያወጣው የአቋም መግለጫ
የወላይታ ሕዝብ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢፌዴሪ) ሕገ-መንግሥት መሠረት አድርጎ ራስን በራስ የማስተዳደርና ክልል የመመሥረት መብት ተግባራዊ ለማድረግ ተደጋጋሚ ጥያቄ ሲያቀርብ እንደነበረ ይታወቃል። ጥያቄው የቀረበለት የክልል ምክር ቤት ጥያቄው በደረሰው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለጠየቀው ወላይታ ብሔር ሕዝበ ውሳኔ ማደራጀት እንደሚገባው ሕገ-መንግሥቱ በግልጽ ቢደነግግም የክልሉ ምክር ቤት የወላይታን ክልል የመመሥረት ጥያቄን ለምክር ቤት እንደ አጀንዳ ላለማቅረብ በማሰብ መደበኛ ስብሰባዎችን በተደጋጋሚ ሆን ብሎ እየዘለለ ቆይቷል።
ከዚህም ባሻገር የክልሉ ምክር ቤት መደበኛ የምክር ቤት ጉባዔ ጊዜ ካሳለፈ በኋላ ባካሄዳቸዉ አስቸኳይ ጉባዔዎች የወላይታ ሕዝብ ጥያቄ ለጉባዔው እንዳይቀርብ የተደረገ ሲሆን የወላይታ ሕዝብ ተወካዮች በምክር ቤቱ አጀንዳ ለማስያዝ ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም ታፍነዉ ዕድል እንዳይሰጣቸዉ ተደርገዋል።
ይህንን ኢፍትሐዊ አሠራር መነሻ በማድረግ የወላይታ ዞን ምክር ቤት ሰኔ 15 ቀን 2012 ዓ.ም. አስቸኳይ ጉባኤ የጠራ ሲሆን፥ በዚህ አስቸኳይ ጉባዔ በዋናነት የዞኑ መስተደድር የሕዝቡን ክልል የመመሥረት ጥያቄን የመራበት ሂደት በጥልቀት የተመለከተ ሲሆን፥ እስካሁን ያለው ሂደት አመርቂ መሆኑንም ገምግሟል።
በዚህም መሠረት ምክር ቤቱ በስፋትና በጥልቀት ከተወያየ በኋላ የሚከተለዉን ባለሰባት ነጥብ የአቋም መግለጫ አዉጥቷል፤
- የወላይታ ሕዝብ በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 47 (3) መሠረት የጠየቀዉ የራሱን ክልል የመመሥረት መብት ተግባራዊ ለማድረግ ሲሆን የሚመሠረተዉ ክልል ስያሜው የወላይታ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት፣ የሥራ ቋንቋ ወላይትኛ (Wolaittatto Doona)፣ የክልሉ ርዕሰ-ከተማ ‹‹ወላይታ ሶዶ›› ይሆናል። ስለሆነም መንግሥት ሕገ-መንግሥታዊ ለሆነ ሕዝብ ጥያቄ ሕገ–መንግሥትን በተከተለ መንገድ አስቸኳይ ምላሽ እንዲሰጥ የወላይታ ብሔር ምክር ቤት አጥብቆ ይጠይቃል።በተጨማሪም ይሄ ጥያቄ በጊዜ ባለመመለሱ የተነሳ በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ቁጣ የቀሰቀሰ፣ የዞኑ መንግሥት ሙሉ ጊዜውን በልማት ሥራ እንዳያውል እንቅፋት እየሆነ የሚገኝ በመሆኑ ሂደቱም ወደ ፀጥታ ችግር ሳይሸጋገር የፈደራል መንግሥት ኃላፊነት ወስዶ ምላሽ እንዲሰጥ ምክርቤቱ ጠይቋል።
- የወላይታ ብሔርን ወክለዉ በክልል ምክር ቤት ሲሳተፉ የነበሩ የወላይታ ሕዝብ ተወካዮች በቀን ሰኔ 11 ቀን 2012 ዓ.ም. የክልሉ ምክር ቤት ባካሄደዉ 5ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ አስቸኳይ ጉባዔ ላይ ላለመሳተፍ ራሳቸዉን ከምክር ቤት አባልነት ማግለላቸዉ ለሁሉም ኢትዮጵያ ሕዝብ ግልጽ ነዉ። ይህንን ያደረጉበት ምክንያት የክልሉ ምክር ቤት ለወላይታ ሕዝብ ጥያቄ ተገቢ ምላሽ ባለመስጠቱ ነዉ። ይህ የወላይታ ብሔር ተወካዮች ውሣኔ ለወላይታ ብሔር ያላቸዉን ክብር የሚያሳይ ስለሆነ ምክር ቤቱ በአድናቆት ተመልክቷል። ነገር ግን እነዚህን ተወካዮች የክልሉ አስተዳደርና የክልሉ ምክር ቤት ጠርተዉ ማወያየት ሲገባዉ እስካሁን ድረስ ዝም ማለቱ መላዉን የወላይታ ሕዝብ አለማክበሩን ያሳያል። የሕዝብ ውክልና የያዘ አካል ለክልሉ ምክር ቤት ያለዉን ቅሬታ ለማሳየት መልቀቂያ ቢያስገባ የዚህን ሕዝብ ተወካዮች ጠርቶ አለማወያየትና ተገቢ ትኩረት አለመስጠት ኃላፊነት የጎደለው ተግባር መሆኑን እንገነዘባለን። የወላይታ ሕዝብ በሀገሪቱ ለመጣዉ ለዉጥ ትልቅ ዋጋ የከፈለ ታሪክ ያለዉ ሕዝብ ነዉ። ስለዚህም የፌዴራል መንግሥት እነዚህን የወላይታ ሕዝብ ተወካዮችን ጠርቶ እንዲያነጋግር የዞኑ ምክር ቤት አጥብቆ ይጠይቃል።
- የደቡብ ክልል ምክር ቤት የሚወስናቸው ወላይታን የሚመለከት ማንኛውም ውሳኔ ተግባራዊ ከመሆናቸው አስቀድሞ በወላይታ ዞን ምክር ቤት ይሁንታ ማግኘት እንዳለበት ወስኗል። በተጨማሪም በክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት የሚወስኑ የወላይታ ሕዝብ ጥቅም የሚጎዱ ማነኛውም ውሳኔ ተግባራዊ እንዳይሆን ምክር ቤቱ ወስኗል።
- የደቡብ ክልል ፀጥታ መዋቅር የሚመሩ አካላት ላይ እምነት ስሌለንና ገለልተኛ ባለመሆናቸው እንዲሁም የክልሉ ፀጥታ ሥራ በኮማንድ ፓስት (Command Post) የሚመራ በመሆኑ የወላይታ ዞን ፀጥታ ሥራ በሕዝቡ እና በዞኑ ፀጥታ መዋቅር ጋር በትብብር መፈፀም እንዳለበት እና ድጋፍ በሚያስፈልግበት ጊዜ ከፈደራል ፀጥታ መዋቅር በትብብር መሠራት እንዳለበትም ተወስኗል።
- ወደፊት የሚመሠረተው የወላይታ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚዊ እና ፓለቲካዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ሕጎችን፣ ደንቦችን፣ አዋጆችንና መመሪያዎችን እንዲያዘጋጅ ሰክራቴሪያት ፅ/ቤት እንዲቋቋም ተወስኗል። በተጨማሪም የዞኑ መንግሥት እንደየአስፈላጊነቱ ለወላይታ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምሥረታ የሚያግዙ ተቋማትንና ግብረ ኃይሎችን በማቋቋም ሂደቱን በበላይነት እንዲመራም ተወስኗል።
- ቀጣይ ሕዝባዊ ጥያቄ ሰላማዊ፣ ሕጋዊና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እንዲመራ ተወስኗል።
- የወላይታና አጎራባች ሕዝቦች ትስስር ለዘመናት የቆየና በቀጣይ አብሮ የሚኖርና የሕዝቦች ትስስር ከመዋቅር በላይ በመሆኑ ግንኙነቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም የዞኑ ምክር ቤት ወስኗል።
ለመላዉ የወላይታ ሕዝብ የራሱን ክልል የመመሥረት ሕገ–መንግሥታዊ መብት በሚመለከተው ፌዴራል መንግሥት አካል ለጥያቄዉ ተገቢ ምላሽ እስኪሰጥ ድረስ እንደተለመደው ሁሉ ሰላማዊ ትግሉን አጠናክሮ እንዲቀጥል የወላይታ ዞን ምክር ቤት ጥሪ አቅርቧል።
“የኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥትና ዓለማቀፍ ሕግ ያጎናጸፈዉ የወላይታ ሕዝብ ክልል የመመሥረት መብት ጥያቄ በሰላማዊ ሕዝብ ትግል እውን ይሆናል!”
ሰላም ለሀገራችን
የወላይታ ዞን ምክር ቤት
ወላይታ ሶዶ፣ ኢትዮጵያ
ሰኔ 15 ቀን 2012 ዓ.ም.2ተኛው አረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር በይፋ ተጀመረ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – ሁለተኛው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ኡመር ሁሴን፣ የደቡብ ብ/ብ/ሕ/ክልላዊ መንግሥት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው፣ ሌሎች ሚኒስትሮች፣ ሚኒስትር ዴኤታዎች እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የፌደራልና የክልል አመራሮች፣ የአካባቢው ማኅበረሰብ ተወካዮች በተገኙበት የ2012 ዓ.ም የ5 ቢሊዮን የኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ አርብ ግንቦት 28 ቀን 2012 ዓ.ም. በሀዋሳ ከተማ በታቦር ተራራ በይፋ ተጀምሯል።
የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) ባስጀመሩበት ወቅት ኢትዮጵያ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት 20 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል አቅዳ እየሠራች እንደሆነ ገልፀዋል።
ባለፈው ዓመት የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር 84 በመቶ መፅደቁን አስታውሰው፥ ዘንድሮ የታቀደውን 5 ቢሊዮን ችግኝ ተከላ ግቡን ለማሳካት ለኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ (ኮቪድ-19) አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ ግቡን ማሳካት ከእያንዳንዱ ዜጋ እንደሚጠበቅ አሳስበዋል።
በዘንድሮ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በደቡብ ክልል በ227 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ 1.5 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል የታቀደ ሲሆን፥ ወይራ፣ ዋንዛ፣ ዝግባ እና የአበሻ ፅድ የመሳሰሉት ሃገር በቀል ችግኞች የሚተከሉ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።
በዓለም ለ47ተኛ ጊዜ በሀገራችን ለ27ተኛ ጊዜ የሚከበረው የአለም የአካባቢ ቀንም (World Environment Day) “አካባቢን መጠበቅ የብዝሃ-ህይወትን በመጠበቅ ነው” በሚል መሪ-ቃል ከ2012 ዓ.ም አገር አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር ጋር እየተከበረ ይገኛል። በዓለም አቀፍ ደረጃ የዘንድሮው መሪ ቃል “ለተፈጥሮ ጊዜ እንስጥ” (‘Time for Nature’) የሚል ነው።
ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት “40 ዛፍ በነፍስ ወከፍ” በሚል መሪ ቃል ሀምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም 200 ሚሊዮን ችግኞችን በአንድ ጀምበር ለመትከል አቅዳ 353 ሚሊዮን 633 ሺህ 660 ችግኞች ተተክሎ የዓለም ክብረ ወሰን መያዟ የሚታወስ ነው።
አምና 4 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ በአጠቃላይ 4.7 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መትከል የተቻለ ሲሆን 23 ሚሊዮን ሕዝብ መሳተፉም ይታወሳል። በቀጣም የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ በየዓመቱ የሚካሄድ ይሆናል ተብሏል።
ምንጭ፦ የግብርና ሚኒስቴር/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
የሀገሪቱ ንግድና ኢንዱስትሪ ዘርፍ ሁነኛ ደጋፊ የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የ2019 የግሎባል ቢዝነስ አውትሉክ ሽልማት አሸናፊ ሆነ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የ2019 የግሎባል ቢዝነስ አውትሉክ ሽልማት አሸናፊ ሆነ። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሸናፊ የሆነው “በምርጥ የንግድ ባንክ” ምድብ ነው።
ባንኩ በተለያዩ ዘርፎች ከቀረቡ ባንኮች ጋር ተወዳድሮ ነው “ምርጥ ንግድ ባንክ” /Best Commercial Bank/ ሽልማት አሸናፊ መሆን የቻለው። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከዚህ ቀደም በአፍሪካ ምርጥ ባንኮች ደረጃ እያገኘ የመጣ ሲሆን ለዚህ ዓለም አቀፍ ሽልማት ሲበቃ ይህ የመጀመሪያው ነው።
ሽልማቱ ግሎባል ቢዝነስ አውትሉክ በሚያወጣቸው መስፈርቶች ተመሥርቶ የሚካሄድ ሲሆን፥ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለዚህ ሽልማት አሸናፊ ለመሆን ካስቻሉት መስፈርቶች መካከል ለበርካታ ዓመታት በትርፋማነት መቀጠሉ፣ ተደራሽነቱ በፍጥነት እያደገ መሄዱ፣ የደንበኞች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ መጨመሩ፣ ለልማት ሥራዎች የሚያስፈልግ የፋይናንስ አቅርቦት ማሳደጉ፣ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን በሚገባ መወጣቱና ሌሎች የባንክ አገልግሎቶችን በተሟላ ሁኔታ መስጠት መቻሉ እንደሆነም ተጠቅሷል።
ባንኩ የአገሪቱን ቁልፍ የልማት ሥራዎች እየደገፈና ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ በሚያደርጉ የጤና፣ ትምህርት፣ አካባቢ ጥበቃና ሌሎችም ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች በግንባር ቀደምትነት ለመደገፍና በመሳተፍ ለአገራችን ልማት አጋር መሆኑን በተጨባጭ ያስመሰከረ መሆኑ ዓለም አቀፍ ሽልማቱን በቀዳሚነት እንዲያገኝ እንዳስቻለው ነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንትና ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ባጫ ጊና የገለፁት።
በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ከሆኑ ሥራዎች መካከል የሀገሪቱን የኃይል አቅርቦት ማሳደግ የሚያስችሉ ግዙፍ ኘሮጀክቶችን ፋይናንስ በማድረግ ባለፉት ዓመታት በርካታ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች እንዲከናወኑ አድርጓል። ለኃይል ማመንጫ ኘሮጀክቶች በርካታ ገንዘብ በማቅረብ ግንባታዎች እንዲከናወኑ በማድረግ ላይ መሆኑም ነው የተገለፀው።
የሀገሪቱ ንግድና ኢንዱስትሪ ዘርፍ ዋና ደጋፊ ከሆኑ ድርጅቶች መካከል ቀዳሚ የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፥ በየዓመቱ ለግብርና ግብዓቶች አቅርቦት፣ ለክልሎች ፋይናንስ ማቅረቡ፣ ለሀገር ውስጥ ከሚያቀርበው ከፍተኛ መጠን ካለው ብድር በተጨማሪ ለህብረተሰቡ እጅግ አስፈላጊ የሆኑ የመድኃኒት፣ የምግብ ዘይት፣ ስንዴ፣ ስኳርና ቅባት ሌሎች የፍጆታ እቃዎችና የፋብሪካ ግብአቶች ከውጪ እንዲገቡ በማገዝ እየሠራ መሆኑም ለአሸናፊነቱ አስተዋፅኦ ማበርከቱ ተገልጿል። አቶ ባጫ ጊና አክለውም ሽልማቱ ባንኩ በቀጣይ ያለውን አገልግሎት ለማሳደግና በሌሎች ዘርፎችም ተሸላሚ ለመሆን የሚያነሳሳ መሆኑን ገልፀዋል።
ግሎባል ቢዝነስ አውትሉክ በ2019 ካዘጋጃቸው የውድድር ምድቦች መካከል፦
- Best Commercial Bank – የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣
- Best Islamic Bank – የአፍጋኒስታኑ Islamic Bank of Afghanistan፣
- Best Innovative Bank – የአርመኑ InecoBank፣
- Best Digital Bank – የቦትስዋናው FNB Botswana፣
- Best Customer Service Bank – የባህሬኑ BBK፣
- Best Retail Bank – የግብጹ National Bank of Egypt፣
ከአሸናፊ ምርጥ ዝርዝሮች መካከል ይጠቀሳሉ። በተለያዩ ዘርፎች ያሸነፉ የባንኮችን ዝርዝር ለማየት እዚህ ጋር ይጫኑ። ከዚህ ቀደም የግሎባል ቢዝነስ አውትሉክ ሽልማት አሸናፊ ከነበሩ ሀገራት መካከል ካናዳ፣ ሩስያ፣ ቻይና፣ ፖርቹጋል፣ ህንድ፣ ኢንዶኒዥያ፣ ደቡብ አፍሪካና ናይጀሪያ ይጠቀሳሉ።
ግሎባል ቢዝነስ አውትሉክ መቀመጫነቱ ለንደን ከተማ (እንግሊዝ) የሆነ ንግድና ኢንዱስትሪ ዘገባዎች ላይ ትኩረት ያደረገ የህትመት ድርጅት ነው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ) ሕጋዊ ሰውነት ማጣትን በተመለከተ ውሳኔ ሰጠ። ይህንንም ተከትሎ አዲሱ ብልጽግና ፓርቲ እና ራሱን ያገለለው ህወሓት ንብረት እንዲከፋፈሉ ቦርዱ ወስኗል።
አዲስ አበባ (የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ) – የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) በሊቀመንበሩ በኩል ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በላከው ደብዳቤ ግንባሩ መፍረሱን ለቦርዱ ያሳወቀ ሲሆን፥ በሌላ በኩል ደግሞ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በሊቀመንበሩ በኩል በተጻፈ ደብዳቤ ግንባሩ በመፍረሱ የንብረት ክፍፍልን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ (ቦርዱ) ውሳኔ እንዲሰጥበት ጥያቄ አቅርበዋል።
የግንባርን (የጥምረት ፓርቲን) መፍረስ የመወሰን ስልጣን የቦርዱ በመሆኑ፥ ግንባሩም ሆነ ህወሓት ግንባሩ መፍረሱን መጥቀሳቸው የማይገባ ቢሆንም ቦርዱ ሁለቱ ሊቃነመናብርት ያቀረቧቸውን የጽሁፍ ጥያቄዎች መሠረት በማድረግ “ግንባሩ መፍረስ አለበት ወይ? ከፈረሰስ ውጤቱ ምን ይሆናል?” በሚል ቦርዱ መርምሮ ውሳኔ ሰጥቷል።
በመሆኑም ቦርዱ የግንባሩ አባል ሦስት ፓርቲዎች ከግንባሩ ወጥተው አዲስ ውህድ ፓርቲ መመሥረታቸውን የብልጽግና ፓርቲን አመሠራረት ከሚያሳየው መዝገብ ተረድቷል። በመሆኑም ግንባሩ በተግባር መፍረሱን ቦርዱ በሙሉ ድምጽ ወስኗል። የግንባሩ መፍረስ ተከትሎ ቦርዱ የኢህአዴግን ንብረት አስመልክቶ ውሳኔ መስጠት እንደሚያስፈልግም ተረድቷል።
በመሆኑም የኢህአዴግ አባል ድርጅት የነበሩት ሦስቱ ፓርቲዎች (ማለትምየአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /አዴፓ/፣ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /ኦዴፓ/ እና ደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ደኢህዴን/) “ብልጽግና ፓርቲ” የሚባል አዲስ ፓርቲ መመሥረታቸው፣ በሌላ በኩል ደግሞ ህወሃት ህልውናውን ጠብቆ የቆየ ፓርቲ በመሆኑ በሕጉ መሠረት በብልጽግና እና በህወሃት መካከል የኢህአዴግን ንብረት ክፍፍል ማድረግ እንደሚገባ ቦርዱ ተገንዝቧል። በመሆኑም ቦርዱ የኢህአዴግን ንብረት አስመልክቶ የሚከተሉትን ውሳኔዎች ወስኗል።
- ብልጽግና እና ህወሃት የኢህአዴግ ንብረት እና ሂሳብ የሚያጣራ አጣሪ በጋራ እንዲሰይሙ፣
- በኢህአዴግ ስም (የተመዘገበ) ያለ ማናቸውም እዳ ተጣርቶ እንዲከፈል፣
- ከእዳ ክፍያ ቀሪ የሆነ ሃብት ሦስት ሩብ ያህሉ (¾ ተኛው) ለብልጽግና ፓርቲ (የሦስቱ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ውህደት በመሆኑ) ሩብ ያህሉ (¼ተኛ) ደግሞ ለህወሃት ድርሻ መሆኑ ታውቆ በዚያ መሠረት ክፍፍል እንዲያጠናቅቁ፣
- ከላይ የተጠቀሱትን ተግባራት በሕጉ መሠረት በ6 ወር ውስጥ ለቦርዱ እንዲያሳውቁ ተወስኗል። (ውሳኔው በጽሁፍ የሚደርሳቸው ይሆናል)
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
ጥር 26 ቀን 2012 ዓ.ም.
አዲስ አበባዓለምን እጅግ ያሰጋው የኖቬል ኮሮና ቫይረስ የተጠቂዎች ቁጥር እጅግ አሻቅቧል፤ ቻይና ውስጥ በአንድ ቀን ብቻ 57 በበሽታው የተጠቁ ሰዎች ሞተዋል። የተለያዩ ሀገራት ዜጎቻቸውን ከዉሃን ከተማ ማስወጣት ጀምረዋል።
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የዓለም ጤና ድርጅት የኖቭል ኖቬል ኮሮና ቫይረስ በሽታ ከታሕሳስ 21, 2012 ዓ.ም. ጀምሮ በቻይና ዉሃን (Wuhan) ግዛት የተከሰተ መሆኑን ካሳወቀ ጀምሮ ይህ ዜና እስከተጠናከረበት ሰዓት ደረስ (በኢትዮጵያ ቀንና ሰዓት አቆጣጠር እስከ ጥር 25 ቀን 2012 ዓ.ም. ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ድረስ) በአጠቃላይ 17,488 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን፥ ከእነዚህ ውስጥ 2,298 (13%) ታማሚዎች በሽታው ክፉኛ የጸናባቸው (in critical conditions) ናቸው። እስካሁን ድረስ በሽታው የተገኘባቸው የሀገራc ቁጥር ቻይናን ጨምሮ 24 የደረሰ ሲሆን፣ በበሽታው የሞቱት ሰዎች ቁጥር 362 ደርሷል (361 የሞቱደርሷል ቻይና ውስጥ ሲሆን፣ አንዱ ብቻ ፊሊፒንስ ውስጥ ነው)። ሰኞ ጥር 25 ቀን 2012 ዓ.ም. ብቻ 57 በበሽታው የተጠቁ ሰዎች ቻይና ውስጥ ሞተዋል።
በሀገረ ቻይና እንዲሁ ቫይረሱ ለመጀመሪያ ጊዜ በተስፋፋባቸው ግዛቶች ምንም ዓይነት የመግባትና የመውጣት አንቅስቃሴ እንዳይደረግ ቢታገድም የስርጭቱ መጠን ከሚታሰበው ባላይ አሳሳቢ አየሆነ እንደመጣ ለማወቅ ተችሏል።
ይህ መላ ዓለምን እጅግ በሚያሰጋ ሁኔታ እየተስፋፋ እየተሰጨና፣ ብሎም ቻይና ውስጥ በበሽታው የሚሞቱት ሰዎች ቁጥር እያሻቀበ ያለው ኖቬል ኮሮና ቫይረስ ወደ ቻይና የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን (በተለይም የ አየር በረራዎችን) መቆጣጠር ጀምሯል። ከችግሩ አሳሳቢነት አንፃር ብዙ ጎረቤት ሀገራት ከቻይና ጋር የሚያዋስናቸውን ድንበር ለመዝጋት የተገደዱ ሲሆን፤ ሌሎች ሃገራትም ወደቻይና የሚደረጉ ማንኛውም በረራዎችን ለማቆም እንደተገደዱ ነው። ለምሳሌ የጀርመኑ ግዙፍ አየርመንገድ ሉፍታንዛ ወደ ቻይና የሚያደርጋቸውን በረራዎች (ቢያንስ እስከ የካቲት 1 ቀን 2012 ዓ.ም.) ሙሉ ለሙሉ አቁሟል። የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች (UAE) ወደ ዋና ከተማ ቤጂንግ ከሚደረጉ በረራዎች በስተቀር ሌሎች ወደ ቻይና የሚደረጉ ሁሉንም በረራዎች እንደምትሰርዝ አስታውቃለች። ካናዳ በበኩሏ ዜግቿን ኖቬል ኮሮና ቫይረስ ለመጀመሪያ ጊዜ ከተነሳባት ሁቤይ (Hubei) ግዛት ከምትገኘው ዉሃን (Wuhan) ከተማ ማስወጣት ጀምራለ፤ ሌሎች ሀገራትም ተመሳሳይ እርምጃ ለመውሰድ እንቅስቃሴ ጀምረዋል።
ቫይረሱ በሀገራቸው በሚኖሩ ዜጎች ላይ መታያቱን ያረጋገጡት የጂ-7 (G-7) ሀገራትም (ካናዳ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣልያን፣ ጃፓን፣ እንግሊዝ እና አሜሪካ) በችግሩ ላይ በትብብር በመሥራት ምላሽ ለመስጠት መዘጋጀታቸውን የጀርመን የጤና ሚኒስቴር ጄንስ ፋህን በትላንትናው ጥር 24 ቀን 2012 ዓ.ም. ተናግረዋል።
ወደ ሀገራችን ስንመለስ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር እና ሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን ለኖቬል ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ዝግጅት በማድረግ ላይ መሆኑን ሰኞ ጥር 25 ቀን 2012 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል። እንደመግለጫው እየተወሰዱ ካሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ውስጥ ብሔራዊ ታስክ ፎርስ እና በኢንስቲትዩቱ ለኮሮና ቫይረስ ድንገተኛ አደጋዎች ምላሽ የሚሰጠው ማዕከል ሥራ ጀምረዋል። ከኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ፣ ከኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ፣ ከቦሌ አየር መንገድ፣ ከግልና ከመንግስት ጤና ተቋማት ለተውጣጡ ተሳታፊዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ተሰጥቷል። በተመሳሳይ ጥር 25 ቀን 2012 ዓ.ም. ለ200 የሚሆኑ የሆስፒታል አመራሮች እና ባለሞያዎች በጤና ሚኒስተር አማካኝነት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጥቷል። በቦሌ ኢንተርናሽናል ኤርፖርት እና 27 የተለያዩ የድምበር መግቢያ እና መውጫ ኬላዎች ላይ የሚደረገው የማጣራት ምርመራ በተጠናከረ ሁኔታ እየቀጠለ ይገኛል። የማጣራት ምርመራው ከፍተኛ የሙቀት መጠን ያላቸውን ተጓዦች የሚለይ ሲሆን ይሄም የቫይረሱ የበሽታ ምልክት የሚያሳዩትን ለመለየት ይረዳል።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ አራት ሰዎች (አንድ ቻይናዊ እና ሦስት ኢትዮጵያውያን) በኖቬል ኮሮና ቫይረስ በሽታ ተጠርጥረው፥ አንድ በአክሱም እና ሦስት በቦሌ ጨፌ በለይቶ ማቆያ ክትትል እየተደረገላቸው ሲሆን፥ ናሙናቸው ተወስዶ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመላክ ዝግጅት ተጠናቋል።
የኖቬል ኮሮና ቫይረስ አስካሁን ድረስ ምንም አይነት ፈዋሽ መድኃኒት ወይም ክትባት ያልተገኘለት ሲሆን በዋናነት የመተንፈሻ አካላትን በማጥቃት ሰዎችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለሞት የሚዳርግ በሽታ ነው። የኖቬል ኮሮና ቫይረስ እንደአውሮፓውያኑ በ2003 በቻይና ከተከሰተው “ሳርስ” በሽታ ጋር የመተንፈሻ አካልን በማጥቃት በኩል ተመሳሳይ ቢመስልም፤ የስርጭት መጠኑ እና የሚያደርሰው ጉዳት ግን እጅግ ከፍተኛ መሆኑ የሚለየው ጉዳይ ነው።