Search Results for 'ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ'

Home Forums Search Search Results for 'ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ'

Viewing 15 results - 1 through 15 (of 18 total)
  • Author
    Search Results
  • Semonegna
    Keymaster

    በ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ፈተና ግማሽ (50%) እና ከዚያ በላይ ውጤት ያስመዘገቡ
    እና የማጠናከሪያ መርሐ ግብር የሚከታተሉ ተማሪዎች ወደ ከፍተኛ ትምህርት እንደሚገቡ ተገለፀ

    አዲስ አበባ (ትምህርት ሚኒስቴር) – የትምህርት ሚኒስቴር የ2014 ዓ.ም 12ኛ ክፍል ፈተና የዉጤት ትንታኔ፣ ወደ ከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ውጤትና ተያያዥ ጉዳዮች አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።

    መግለጫውን የሰጡት የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የተገኘው የፈተና ውጤት ከስርቆትና ከኩረጃ በፀዳ መልኩ በትክክል የተመዘገበ መሆኑን ገልጸዋል።

    በ2014 ዓ.ም ለተሰጠው ፈተና በጠቅላላ የተመዘገቡት ተፈታኞች ቁጥር 985,354 ሲሆኑ፤ ከእነዚህ ውስጥ 92 ከመቶ የሚሆኑት ፈተናውን ወስደዋል። 20,170 ተማሪዎች በፈተናው ከተገኙ በኋላ በተለያዩ የደንብ ጥሰቶች ምክንያት ተባረዋል።

    ከፍተኛ ውጤት የተበመገበበት የትምህርት መስክ — በተፈጥሮ ሳይንስ 666 ከ700 ከፍተኛ ውጤት ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን በማህበራዊ ሳይንስ ደግሞ 524 ከ600 ከፍተኛ ውጤት ሆኖ ተመዝግቧል። በሀገር አቀፍ ደረጃ ፈተናውን ካስፈተኑ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ሰባት ትምህርት ቤቶች ያስፈተኑትን ተማሪዎች 100% አሳልፈዋል ተብሏል።

    በጾታ ደረጃ የወንዶች አማካይ ውጤት 30.2 ከመቶ ሲሆን፤ የሴቶች አማካይ ውጤት ደግሞ 28.1 ከመቶ እንደሆነ፥ ይህም በወንዶች እና በሴቶች መካከል በአሐዛዊ ምልከታ (statistically) የጎልላ ልዩነት እንዳለና፤ ወንዶች ከሴቶች አሐዛዊ ብልጫ (statistically higher) ውጤት እንዳስመዘገቡ አስረድተዋል።

    በክልሎች ደረጃ በዉጤት ደረጃ የጎላ ልዩነት እንደሌለ ገልፀው፤ አዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም የሐረሪ ክልል አሐዛዊ የተሻለ (statistically significantly higher) ውጤት ያስመዘገቡ መሆኑን ፕሮፌሰር ብርሃኑ አብራርተዋል።

    በ2014 ዓ.ም በተሰጠው የ12ኛ ክፍል ፈተና ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሊያስገባ የሚችል ወጤት፥ ማለትም ግማሽ (50%) እና ከዚያ በላይ ያስመዘገቡት ተማሪዎች ቁጥር ሲታይ፥ የተፈጥሮ ሳይንስ ፈተና ከወሰዱት አጠቃላይ 339,642 ተማሪዎች መካከል 22,936 (6.8%) ተማሪዎች፣ የማኅበራዊ ሳይንስ ፈተና ከወሰዱት አጠቃላይ 556,878 ተማሪዎች መካከል 6,973 (1.3%) ተማሪዎች ግማሽ (50%) እና ከዚያ በላይ አስመዝግበዋል።  የሁለቱም የትምህርት መስኮች በድምር ሲታይ፥ ፈተናውን ከወሰዱት 896,520 ተማሪዎች ውስጥ 29,909 (3%) የሚሆኑት ተማሪዎች 50% እና ከዚያ በላይ ያስመዘገቡ መሆናቸውን ገልፀዋል።

    ከተፈጥሮ ሳይንስ ተፈታኞች የተገኘው አማካይ ውጤት 31.6 ከመቶ ሲሆን፤ ከማኅበራዊ ሳይንስ ተፈታኞች የተገኘው አማካይ ውጤት ደግሞ 27.8 ከመቶ ነው። በሁሉም የትምህርት ዓይነቶች የተፈጥሮ ሳይንስ ተፈታኞች አማካይ ውጤት ከማኅበራዊ ሳይንስ ተፈታኞች አማካይ ውጤት አሐዛዊ ጉልህ (statistically significant) ብልጫ እንዳላቸው ሚኒስትሩ አመላክተዋል።

    በአጠቃላይ ከፍተኛ ውጤት፥ በመላው ሀገሪቱ በማኅበራዊ ሳይንስ  ከ500 በላይ (ከሙሉ 600 ነጥብ) ያስመዘገቡ 10 (አስር) ተማሪዎች ብቻ ሲሆኑ፤ በተፈጥሮ ሳይንስ ከ600 በላይ (ከሙሉ 700 ነጥብ) ያስመዘገቡ ደግሞ 263 (ሁለት መቶ ስድሳ ሦስት) ተማሪዎች ናቸው። ወደፊት ጊዜው ሲደርስ እነዚህን እጅግ ከፍተኛ (great distinction) ላመጡ ተማሪዎች ትምህርት ሚኒስቴር ልዩ እውቅና እንደሚሰጣቸው ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ አስታውቀዋል።

    ፈተናውን ከወሰዱ አጠቃላይ 485,393 ወንድ ተማሪዎች መካከል ግማሽ (50%) እና ከዚያ በላይ ያገኙት 20,343 (4.2 በመቶ) ወንድ ተፈታኞች ሲሆኑ፤ ከተፈተኑት አጠቃላይ 411,127 ሴት ተማሪዎች መካከል ግማሽ (50%) እና ከዚያ በላይ ያገኙት 9,566 (2.3 በመቶ) ሴት ተፈታኞች ናቸው።

    ወደ ዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ያላመጡ ተማሪዎች በማጠናከሪያ መርሐግብር (remedial program) እንደ ዩኒቨርሲቲዎቹ የመቀበል አቅም ተማሪዎችን ውጤት መሠረት አድርጎ በሚጸም የምልመላ መስፈርት ለዚህ ዓመት ብቻ ወደ ዩኒቨርሲቲዎች ገብተው በልዩ ሁኔታ በደከሙባቸው የትምህርት ዓይነቶች የተሻለ ዉጤት እንዲያስመዘግቡ የሚያስችል ድጋፍ ተደርጎላቸዉ ፈተና ተፈትነው የሚያልፉ ተማሪዎች የከፍተኛ ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ይደረጋል ብለዋል። በዚህ የማጠናከሪያ መርሐግብር መሠረት፥ ዩኒቨርሲቲ ከሚቀላቀሉት እና መደበኛ ትምህርት (regular course) ከሚጀምሩ 29,909 ተማሪዎች ውጭ ያሉ ሌሎች ከ100 ሺህ የሚልቁ ተማሪዎች በውጤታቸው ተለይተው እንደ ዩኒቨርሲቲዎች የመቀበል አቅም እየታየ ለአንድ ዓመት የማሻሻያ ትምህርት ወስደው በድጋሚ እንዲፈተኑ ይደረጋል ብለዋል።

    የዚህ ዓመት የ12ኛ ክፍል ፈተና አንድምታ ለዓመታት ሲንከባለል የቆ የበርካታ ችግሮች መገለጫ እና ተሸፋፍኖ የቆየውን እውነተኛ የትምህርት ሥርዓታችን ያለበትን ደረጃ ያመላከተ መሆኑን የሚያሳይ ሲሆን ለዚህም ሁሉም የትምህርት ባለድርሻ አካላት በጋር የሚወስዱት ኃላፊነት በመሆኑ ለቀጣይ ሥራ መረባረብ ይገባል ብለዋል።

    ከዚሁ ጋር በተያያዘ የትምህርት ሚኒስትሩ ከተገኘው የፈተናና የተፈታኞች ውጤት ባሻገር፥ አጠቃላይ ስለ አዲሱ የትምህርት እና ምዘና ሥርዓት አንዳንድ ማብራሪያዎችን ሰጥተዋል። ከዚህ በፊት የነበረው የትምህርት እና ምዘና ሥርዓት በርካታ ብልሹ አሠራሮች እንደነበሩበት ያነሱት ሚንስትሩ፤ የአሁኑ የፈተና ሥርዓት ይህን ብልሹ አሠራር ለማረም የተወሰደ የመጀመሪያ እርምጃ ነው ብለዋል።

    የዚህ ዓመት ውጤት አንድምታ ሲታይ፥ ለዓመታት ከትውልድ ትውልድ ሲንከባለል የተሻገረውን እና ተሸፋፍኖ የቆየውን የትምህርት ሥርዓት ብልሽት የሚያሳይ ነው ብለዋል ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በመግለጫቸው።

    ለዚህም መንግሥት የትምህርት ሥርዓቱን ባለማሻሻል፣ ወላጆች ልጆቻቸውን ባለመከታተልና በሥነ ምግባር ባለመቅረፅ፣ ትምህርት ቤቶች እና ባለሀብቶች በጋራ የወድቀቱ ተጠያቂ ናቸው ብለዋል። ከላይ የተጠቀሱ አካላት ቀጣይ መፍትሄዎች ላይ የአንበሳውን ድርሻ በመውሰድ ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

    በ2014 ዓ.ም ከተሰጠው ፈተና እና ተፈታኞች የተገኘው ውጤትአስደንጋጭ እንደሆነ እንረዳለን ያሉት ሚኒስትሩ፥ ነገ የተሻለ ትውልድ ለመፍጠር በዚህ ውስጥ ልናልፍ ግድ ይለናል፤ ይህ የማንቂያ ደወል ሊሆን ይገባል ብለዋል። በበጎ ጎን ከተነሱጥ ነጥቦች መካከል፥ ፈተናው ሙሉ ለሙሉ ከስሮቆት የፀዳ እንደነበረም ተነስቷል።

    የፈተናው አሰጣጥ በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ያለፈ እንደሆነ አንስተው፤ በስኬት ለመጠናቀቁ አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።

    ምንጭ፦ ትምህርት ሚኒስቴር/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የ12ኛ ክፍል ፈተና ውጤት መግለጫ ከትምህርት ሚኒስቴር

    Semonegna
    Keymaster

    ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ በተለያየ የትምህርት ዘርፎች ያስተማራቸውን 659 ተማሪዎችን አስመረቀ

    ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች በቅድመ- እና ድኅረ- ምረቃ መርሀግብሮች ያሰለጠናቸውን 659 ተማሪዎችን ጳጉሜን 3 ቀን 2012 ዓ.ም አስመረቀ። ዩኒቨርሲቲው ለ12ኛ ዙር ለምረቃ ካበቃቸው ተማሪዎች መካከል 515 ወንዶች ሲሆኑ 144 ደግሞ ሴቶች ናቸው።

    ዩኒቨርሲቲው በእጽዋት ሳይንስ፣ በእንስሳት ሳይንስ፣ በተፈጥሮ ሀብት አጠባበቅ፣ በኢኮኖሚክስ፣ በሥራ አመራር (Management)፣ እንዲሁም በጂኦግራፊና አካባቢ-ነክ ጥናቶች (Environmental Studies) በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ አስተምሮ አስመርቋል።

    በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አህመድ ሙስጠፋ እንደገለጹት፥ ዩኒቨርሲቲው ከተቋቋመበት ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ የመማር ማስተማር፣ የምርምር እና የማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራዎችን ተግባራዊ ሲያደርግ ቆይቷል። እንደ ዶ/ር አህመድ ገለጻ፥ ዩኒቨርሲቲው ከዚህ ቀደም ከ15 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በማስመረቅ ለውጤት አብቅቷል።

    እንደ ተጠባባቂ ፕሬዝደንቱ ገለጻ፥ ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ በተያዘው ዓመት በ46 የመጀመሪያ ዲግሪና በ23 የሁለተኛኛ ዲግሪ ፕሮግራሞች ከ17ሺ በላይ ተማሪዎችን በማስተማር ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

    በጥናትና ምርምር ሥራዎች በሀገር አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ጭብጦች 18 የምርምር ንድፈ ሀሳቦች የቀረቡ ሲሆን፥ ከእነዚህ ውስጥ 15ቱ ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል ብለዋል – ዶ/ር አህመድ። የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከልም ከ3 ሺህ ሊትር በላይ የንጽህና መጠበቂያ ፈሳሽ (ሳኒታይዘር) በማምረት አገልግሎት ላይ እንዲውል ተደርጓልሲሉ አስረድተዋል።

    የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ እና የዩኒቨርሲቲው ምክትል የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ፍቅሬ አማን በክብር እንግድነት ተገኝተው ባስተላለት መልዕክት፥ እንዳሉት የዘንድሮው የምረቃ በዓል ለዓለማችን፣ ብሎም ለሀገራችን ህዝቦች የኮርና ቫይረስ ወረርሽኝ ፈታኝ በሆነበት በዚህ ወቅት ተመራቂዎች የጥናትና ምርምር ሥራዎችን በማጠናቀቅ ለውጤት በመብቃታቸው የተሰማቸውን ልባዊ ደስታ ገልጸዋል።

    ሀገራችን በመደመር ፍልስፍና ከነበረችበት ችግር ወጥታ ወደ ብልጽግና ጎዳና እየተጓዘች ባለችበት በዚህ የይቅርታና የምኅረት ወር በሆነችው በጳጉሜ ወር ተማሪዎች ለምረቃ በመብቃታቸው እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል።

    ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞውን ሚዛን ተፈሪ ግብርና ኮሌጅ መሠረት አድርጎ በደቡብ ክልል ሚዛን ተፈሪ እና ቴፒ ከተሞች በ1999 ዓ.ም የተቋቋመ ዩኒቨርሲቲ ነው።

    ተመሳሳይ ዜናዎች፦

    ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ

    Semonegna
    Keymaster

    ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ እና አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በአጠቃላይ ከ3 ሺህ በላይ ተማሪዎችን አስመረቁ

    ዲላ/አርባ ምንጭ (ኢዜአ/አ.ም.ዩ) – ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መረሃ ግብሮች ያሰለጠናቸውን 1,043 ተማሪዎችን ነሐሴ 30 ቀን 2012 ዓ.ም. አስመረቀ።

    በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጫላ ዋታ እንደገለጹት ከተመራቂዎቹ መካከል 283 በመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን የተከታተሉ ናቸው። ቀሪዎቹ በምስክር ወረቀት የተመረቁ መሆኑን አስረድተዋል።

    ተመራቂዎቹ ትምህርታቸውን በበይነ መረብ ቴክኖሎጂ አማካኝነት ሲከታተሉ እንደቆዩ አመልክተው፥ በተለይ የሁለተኛ ዲግሪ ተመራቂዎች የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከመከሰቱ በፊት የክፍል ትምህርታቸውን ማጠናቀቃቸውን አስታውቀዋል።

    ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ሥራው በተጓዳኝ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን መከላከልን ጨምሮ በተለያዩ የማኅበረሰብ አገልግሎቶች ውጤታማ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝም ዶ/ር ጫላ ገልጸዋል።

    የዩኒቨርሲቲው የቦርድ አባል አቶ ኡዴሳ ክዮላ በበኩላቸው፥ ተመራቂዎቹ በቀጣይ በሚሰማሩበተ የሥራ መስክ ሀገርና ሕዝብ የሚጠብቅባቸውን ኃላፊነት በታማኝነትና ታታሪነት እንዲወጡ አሳስበዋል።

    ከተመራቂዎቹ መካከል በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ትምህርቱን የተከታተለው ቅዱስ ይገረሙ በሰጠው አስተያየት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ያሳደረውን ተጽዕኖ ተቋቁሞ ትምህርቱን በማጠናቀቅ ለምረቃ በመብቃቱ መደሰቱን ገልጿል። በሰለጠነበት በ“ሶፍትዌር ዲዛይን” ዘርፍ በመሰማራት እራሱንና ሀገሩን ለመጥቀም እንደሚሠራ ተናግሯል።

    በሁለተኛ ዲግሪ ማኔጅመንት የትምህርት ዘርፍ የተመረቀው ዋቆ ጥላሁን በበኩሉ በትምህርት ቆይታው ያገኘውን እውቀት በመጠቀም ውጤታማ ሥራ ለማከናወን እንደሚጥር ገልጿል።

    የሦስተኛ ትውልድ ዩኒቨርሲቲ የሆነው ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መረሃ ግብሮች የሚያስተምራቸው ከ17 ሺህ በላይ ተማሪዎች እንዳሉት በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ወቅት ተገልጿል።

    ከተማሪዎች ምርቃት ጋር በተያያዘ፥ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ መርሃ ግብር ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ለ33ኛ ጊዜ አስመርቋል።

    ዩኒቨርሲቲው በ2012 ዓ.ም በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ መርሃ ግብር በመደበኛ፣ በክረምት፣ በሳምንት መጨረሻ እና በተከታታይና ርቀት ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ 2,326 ተማሪዎች ቅዳሜ ነሐሴ 30/2012 ዓ/ም በተመሳሳይ ዕለት አስመርቋል።

    የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንደገለጹት፥ ዩኒቨርሲቲው በስድስት የተለያዩ ካምፓሶች በ76 የመጀመሪያ ዲግሪ፣ በ99 የ2ኛ ዲግሪ እና በ21 የ3ኛ ዲግሪ መርሀግብሮች በአጠቃላይ ከ36 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በመደበኛና መደበኛ ባልሆኑ መርሀግብሮች በማስተማር ላይ ይገኛል። ተቋሙ ባለፉት 33 ዓመታት በልዩ ልዩ የምህንድስና፣ የሕክምናና የጤና፣ የግብርና፣ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ፣ የማኅበራዊ እንዲሁም የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ዘርፎች 56,958 ምሩቃንን በማፍራት ለሀገሪቱ የሰው ሀብት ልማት ጉልህ አስተዋፅዖ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

    አክለውም በ2012 የትምህርት ዘመን በ2ኛው አጋማሽ ላይ በዓለም ላይ በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በሁሉም ደረጃዎች በመማሪያ ክፍል ሆኖ የመማር ማስተማር ሂደት የተቋረጠ ቢሆንም፥ ዩኒቨርሲቲዎች ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመሆን ባደረጉት ከፍተኛ ጥረት ቴክኖሎጂን በመጠቀም የጥናትና ምርምር ሥራቸውን ሲሠሩ የቆዩ ተማሪዎች አስፈላጊውን የምረቃ መስፈርት በማጠናቀቅ ለምረቃ መብቃታቸውን ተናግረዋል። በቀጣይ ዓመታት በተከፈቱ የ2ኛ እና የ3ኛ ዲግሪ መርሀግብሮች ላይ የማጠናከር ሥራ የሚሠራ ሲሆን፥ ዩኒቨርሲቲው በ2013 የትምህርት ዘመን በዩኒቨርሲቲው ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በ3ኛ ዲግሪ የሚያስመርቅ መሆኑን ባቀረቡት ሪፖርት ጠቁመዋል።

    የዕለቱ የክብር እንግዳ የጋሞ ዞን አስተዳዳሪና የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ እንደተናገሩት፥ የመማር ግቡ ከግለሰብ ህይወት እስከ ሀገር ድረስ ያሉ የተለያዩ ችግሮችን በመፍታት ምቹና ተስማሚ አኗኗርን ለመፍጠር የለውጥና የዕድገት ጎዳናን መከተል ነው። በመሆኑም የዕለቱ ተመራቂዎች ሀገራችን ኢትዮጵያ ወደ ብልፅግና ማማ እንድትደርስ የበኩላችሁን ድርሻ እንድትወጡ ሲሉ አሳስበዋል። በተጨማሪም ወደ ሥራ ዓለም ሲቀላቀሉ በተሰማሩበት መስክ ሁሉ ሀገራቸውንና ሕዝባቸውን በታማኝነት እንዲያገለግሉ ጠይቀዋል። ሀገሪቱ በበርካታ ፈተናዎች ውስጥ እየተሻገረች የምትገኝ እንደመሆኗ መጠን ፈተናዎቹን በብቃት መክተን ወደ መልካም ዕድል መቀየር ይጠበቅብናል ብለዋል።

    በመጨረሻም የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ እና የሬጂስትራርና አልሙናይ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር በለጠ ይልማ የእጩ ምሩቃን መግለጫ በመስጠት አስመርቀዋል።

    በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የጋሞ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የዩኒቨርሲቲው ሥራ አመራር ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ በክብር እንግድነት፣ የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት እንዲሁም የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮችና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።

    ምንጮች፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እና አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ (አ.ም.ዩ)

    ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ እና አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን አስመረቁ

    Anonymous
    Inactive

    ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ መርሀግብሮች ያስተማራቸውን ከ900 በላይ ተማሪዎችን አስመረቀ

    ወልቂጤ (ሰሞነኛ) – የሦስተኛ ትውልድ ዩኒቨርሲቲ የሆነው ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ መርሀግብሮች ያስተማራቸውን 929 ተማሪዎች ነሐሴ 30 ቀን 2012 ዓ.ም ለሰባተኛ ጊዜ ባካሄደው የምረቃ ሥነ ሥርዓት አስመርቋል።

    በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ በክብር እንግድነት ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሙሉ ነጋ እንዳሉት፥ እውቀትና ብቃት ያለው የሰለጠነ የሰው ኃይል ለአንድ ሀገር እድገትና ቀጣይነት የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው። በዚህ ረገድ ጥራትና አግባብነት ያለው ትምህርት በተለይ ደግሞ ከፍተኛ ትምህርት ማስፋፋት ወሳኝ ነው ብለዋል።

    ዶ/ር ሙሉ አክለውም፥ መንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሀገራችንን ሕዝብ ህይወት ቀላልና ዘመናዊ በማድረግ ወደተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር ቁልፍ ሚና እንዳላቸው በማመን በየዓመቱ ከፍተኛውን የሀገሪቱን በጀት ለትምህርት መድቦ እየሠራ ይገኛል ብለዋል።

    ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የለውጥ ሃሳቦችን በማፍለቅና በመተግበር መልካም አርአያ የሚሆኑ ዜጎችን ማፍሪያ፣ የዲሞክራሲያዊ አስተሳሰቦችና ቴክኖሎጂዎች መፍለቂያ፣ የባህላዊ እሴቶቻችን መጎልበቻ፣ የሕዝቦች የመተሳሰብ፣ የመቻቻልና የአብሮነት ባህል የሚቀመርባቸው ማዕከላት እንዲሆኑ ማድረግ አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው ብለዋል – ዶ/ር ሙሉ።

    ሚኒስትር ዴኤታው ሰላም በምንም ነገር የማይተካ መሆኑን ገልጸው፥ ተመራቂዎች የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት እንዲደግፉና በህይወት ጎዳናቸው ከጽዩፍ አስተሳሰብና እና ድርጊት ተጠብቀው በተሰማሩበት መስክ የችግሮች መፍትሄ በመሆን ሀገራቸውን እንዲያገለግሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

    ዶ/ር ሙሉ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸው፤ ተመራቂዎች ሀገራችሁንና ሕዝባችሁን በሚጠቅሙ ሥራዎች ላይ በመሰማራት ታታሪ፣ የሀገራችሁን ሁለንተናዊ እድገት እና ብልጽግና የምታረጋግጡ ሰላም ወዳድ እንድትሆኑ አደራ እላለሁ ብለዋል።

    የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፋሪስ ደሊል በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በአዋጅ የተሰጠውን ተልዕኮ ለማሳካት በምርምር፣ በማኅበረሰብ-አቀፍ አገልግሎት (community-based service) እና መማር-ማስተማር መስክ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ገልጸው፤ በተለይም ኮቪድ-19 ከመጣ በኋላ የዩኒቨርሲቲው ሠራተኞች የአንድ ወር ደመወዛቸውን በማዋጣት አቅመ ደካሞችን መርዳታቸውን ገልጸዋል። ዩኒቨርሲቲው ከ3,000 ሊትር በላይ ሳኒታይዘር፣ 4,000 የፊት ጭንብል (face-mask)፣ 1800 ብሊች (bleach) የማምረት ሥራዎችን ሠርቶ በጉራጌ ዞን ለሚገኙና በሥራ ጸባያቸው ለቫይረሱ ተጋላጭ ለሆኑ ተቋማት ማበርከቱን ጠቁመዋል። ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የለይቶ ማቆያ ማዕከል (quarantine center) ሆኖ በማገልገል ላይም ይገኛል ብለዋል።

    በምርምር ረገድም ድርቅን በመቋቋም የሚታወቀውን ቆጮን ጨምሮ በተለያየ መልኩ ለምግብነት የሚውለውን እና የአከባቢው ማኅበረሰብ የኑሮ አለኝታ የሆነውን የእንሰት ተክል እንዳይጠፋ፣ እንዲሁም ዝርያው እንዲጠበቅና እንዲሻሻል የእንሰት ማዕከል በማደራጀት ዝርያዎችን የማሰባሰብ ሥራዎችን እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

    ዶ/ር ፋሪስ ባስተላለፉት መልዕክት ተመራቂ ተማሪዎች ሥራ ወዳድና ታታሪ፣ በሕግ የበላይነት ላይ የማትደራደሩ፣ የጥላቻን ዘር የማትዘሩ በጥላቻ ሳይሆን የተዘራውን ክፉ አረም በፍቅርና አብሮነት የምትነቅሉ በሥነ-ምግባር የታነጻችሁ ሀገር ተረካቢ ብቻ ሳትሆኑ አሻጋሪ ናችሁ ብለዋል።

    በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የዛሬው ምረቃ ሥነ ሥርዓት የተሳተፉት በክረምትና በማታ መርሀግብሮች በአምስት ኮሌጆች ስር በሚገኙ 15 ትምህርት ክፍሎች ከዓለምአቀፉ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ (ኮቪድ-19) በፊት ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ወንድ 597፣ ሴት 143፤ በድምሩ 840 የቅድመ ምረቃ ተማሪዎች እና በቢዝነስና ኢኮኖሚክስ እንዲሁም በግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጆች ስር በሚገኙ አራት ትምህርት ክፍሎች ከወረርሽኙ በኋላም በቴክኖሎጂ አማራጮች ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ በመደበኛና በማታው የድኅረ ምረቃ መርሀግብሮች ወንድ 81፣ ሴት 8፤ በድምሩ 89 ምሩቃን ናቸው።

    በ2004 ዓ.ም በ13 የትምህርት መስኮች 595 መደበኛ ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር የጀመረው ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በአሁኑ ጊዜ በስምንት ኮሌጆችና አንድ ትምህርት ቤት በቅድመ ምረቃ 50 መርሀግብሮች እንዲሁም ሁለተኛ ዲግሪ እና 12 ፕሮግራሞች በጠቅላላው ከ14 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በመደበኛ፣ በማታና በክረምት መርሃ ግብሮች እያስተማረ ይገኛል።

    ምንጭ፦ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር

    ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ

    Anonymous
    Inactive

    ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን 4,700 ተማሪዎችን ዛሬ አስመረቀ

    ሐዋሳ (ኢዜአ/HU) – ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ በበይነ-መረብ (virtual) ትምህርታቸውን እንዲጨርሱ ያስቻለቸውን የድኅረ ምረቃ (ሁለተኛ እና ሦስተኛ ዲግሪ) ተማሪዎች እንዲሁም ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት በፊት በእንስሳት ሕክምና እና በሌሎች መርሀ-ግብሮች ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ የመጀመሪያ ዲግሪ 4,780 ተማሪዎችን ነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም አስመረቀ።

    ዩኒቨርሲቲው ለ21ኛ ጊዜ ካስመረቃቸው መካከል 2,866 በመጀመሪያ፣ 1,900 በሁለተኛ እና 12 ደግሞ በሦስተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸው መሆናቸውን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር አያኖ በራሶ ገልጸዋል።

    ተማሪቂዎችና ቤተሰቦቻቸው በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ (ኮቪድ-19) ምክንያት የተፈጠረውን አስቸጋሪ ሁኔታ ተቋቁመው ለመመረቅ በመብቃታቸው እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል። ዩኒቨርሲቲው ወረርሽኙን ከመከላከሉ ሥራ በተጓዳኝ ችግር ፈቺ የምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ሥራዎች ላይ ትኩረት በመስጠት እና የመንግሥትን የልማት እንቅስቃሴ በጥናት ለመደገፍ ጥረት እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት ወረርሽኙን እየተከላከሉ መደበኛ የትምህርት ሥራቸውን ለመጀመር እየተዘጋጁ መሆኑን ገልጸዋል።

    ዶ/ር አያኖ በአዲሱ ፍኖተ-ካርታ መሠረት የምርምር ዩኒቨርሲቲ (Research University) ለመሆን ከሚጠበቁት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መካከል ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ በቀዳሚነት ለማሰለፍ በቁርጠኝነት እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።

    የዩኒቨርሲቲው ምክትል ቦርድ ሰብሳቢና የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ጥራቱ በየነ በበኩላቸው ተመራቂዎች የቀሰሙትን ዕውቀት በተግባር በማዋል የሀገሪቱን ዕድገት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል። ተቋሙ በተደራረበ ጫና ውስጥ እያለ ተማሪዎችን ማስመረቁ፥ ምርምርና የማኅበረሰብ አገልግሎቶችን አጠናክሮ መቀጠሉ የአመራሩንና የሠራተኞችን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ብለዋል።

    በእንስሳት ሕክምና ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ የተመረቀው ዶ/ር ግርማ በዳዳ በሰጠው አስተያየት፥ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ጫና በመቋቋምና ጥናቱ ላይ በመትጋት ለምርቃ መብቃቱን ተናግሯል። ለዚህም ዩኒቨርሲቲውን አመሰግኗል።

    ሌላዋ በሶሻል ሣይኮሎጂ የሁለተኛ ዲግሪ ተመራቂ ማርታ ማጋ በበኩሏ፥ ወረርሽኙ ከመከሰቱ በፊት የክፍል ትምህርት ማጠናቀቃቸውን ጠቅሳ፤ የምርምር ሥራዋን ከዩኒቨርሲቲው ውጭ በማካሄድ ለመመረቅ እንደበቃች ገልጻለች።

    ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ በመደበኛና ተከታታይ የትምህርት መርሀ-ግብር የሚያስተምራቸው ከ43,000 በላይ ተማሪዎች እንዳሉት ከዩኒቨርሲቲው ድረ-ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። ዩኒቨርሲቲው በአጠቃላይ ከ7,000 በላይ ሠራተኞች (staff)፣ ሰባት ካምፓሶች፣ ስምንት ኮሌጆችና ሁለት ተቋማት (institutes)፣ እና ከ200 በላይ የትምህርት መርሀ ግብራት (programs) እንዳሉት ድረ-ገጹ ያሳያል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)/ ዩኒቨርሲቲው (HU)

    ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ

    Semonegna
    Keymaster

    ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ መርሀ ግብሮች ያሰለጠናቸውን 7520 ተማሪዎች በበይነ-መረብ አስመረቀ

    (ባሕር ዳር) – ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በድኅረ ምርቃ መርሀ-ግብር በሁለተኛ ዲግሪ በመደበኛውና በተከታታይ መርሀ-ግብር 2254 ተማሪዎች፣ በሦስተኛ ዲግሪ መርሀ-ግብር 40 ተማሪዎች፣ እንዲሁም በስፔሻሊቲ መርሀ-ግብር 41 ተማሪዎች፣ በምስክር ወረቀት መርሀ-ግብር 642 ተማሪዎች በድምሩ 7520 ተማሪዎችን በበይነ-መረብ በመታገዝ ነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም አስመርቋል። ከተመራቂ ተማሪዎቸ መካከል 2345 ሴቶች ሲሆኑ፤ ከእነዚህ ሴት ተመራቂ ተማሪዎች መካከል አምስቱ የሦስተኛ ዲግሪ ተመራቂ ተማሪዎች መሆናቸው ታውቋል።

    በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ድኤታና የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ አባል ወ/ሮ ሰሀረላ አብዱላሂ፣ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ዋና ዳሬክተርና የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ አባል ፕ/ር ማስረሻ ፈጠነ፣ እንዲሁም የአማራ መልሶ ማቋቋም ልማት ድርጅት /አመልድ/ ዋና ዳሬክተርና የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ አባል ዶ/ር አለማየሁ ዋሴ፣ የዩኒቨርሲቲው የሴኔት አባላት፣ ዲኖችና ዳይሬክተሮች እና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።

    በሥነ-ሥርዓቱ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ ለተመራቂ ተማሪዎችና ለተመራቂ ቤተሰቦች የእንኳን ደስ ያላችሁ መልክዕት አስተላልፈዋል። በመልዕክታቸውም ዓለምን ባስጨነቀው የኮሮና ወረርሽኝ ተግዳሮት ሳይደናቀፉ የሚጠበቅባቸውን አሟልተው ለተመረቁ ተማሪዎች አድናቆታቸውን ገልፀው ወደ ቀደምት ትልቅነታችን እና ጥበብ ለመመለስ እና አሁን የጀመርናቸውን የአባይ ግድብን ጨምሮ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ለማሳካት የጋራ መድኃኒት ስለሚያስፈልገን ሁላችንም ለሀገራችን ሰላም በጋራ መሥራት እንደሚገባን አሳስበዋል።

    የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን (ኮቪድ-19) ለመከላከል እና ለመቆጣጠር እየተደረገ ባለው እንቅስቃሴ ዩኒቨርስቲዎች ሕይወትን ለመታደግ የእውቀት እና የሕዝብ ተቋምነታቸውን ማስመስከራቸውን ጠቅሰው ለዚህም ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያስችሉ ቁሳቁሶችን በማምረት እና በርካታ የፈጠራ ሥራዎችን በማበርከት ሕበረተሰቡን ከወረርሽኙ እየታደገ መሆኑን ዶ/ር ፍሬው ገልፀዋል። በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት ተማሪዎች በኮቪድ-19 ምክንያት ሙሉ በሙሉ ከትምህርት እንዳይለዩ በዩኒቨርሲቲው የICT ባለሙያዎች የበለፀገ የትምህርት አስተዳደር ሥርዓት (learning management system) ለአማራ ክልለዊ መንግሥት ትምህርት ቢሮ ማበርከቱን አውስተዋል።

    በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚንስትርና የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ እንዳሉት መማር ትርጉም የሚኖረው የሕበረሰተቡን ኑሮ ማሻሻልና ለችግሮቹ መፍቻ የሚሆን አዳዲስ አሠራሮችንና ሀሳቦችን መፍጠር ሲቻል መሆኑን ጠቁመው የሀገራችን ችግር የሚፈታው የችግሮችን ስፋትና ጥልቀት በሚረዱ ምሁራን በመሆኑ የምንግዜም ጠላታችን የሆነውን ድህነትን ለማስወገድ ተመራቂ ተማሪዎች በተመረቁበት መስክ ትኩረት ሰጥተው ለመሥራት ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

    አክለውም፥ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የልሕቀት ማዕከል ለመሆን የሚያደርገውን ትጋት አድንቀው፤ በእምቦጭ ዙሪያ ብዙ ሥራ መሥራት የሚያስችል በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው ትኩረት ሰጥቶ በስፋት እንዲሠራ ጥሪ አቅርበዋል። ከአባይ ፏፏቴ ጀምሮ እስከ ሰሜን ብሔራዊ ፓርክ ድረስ ትኩረት በመስጠት የቱሪዝም ኮሪደር ለማድረግ የሚቻልበትን ምርምር በመሥራት መሻሻል የሚገባቸውን ጉዳዮች ማሳየትም ከዩኒቨርሲቲው እንደሚጠበቅ ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ ተናግረዋል።

    የምረቃ ሥነ-ሥርዓቱን ጥቂት ተማሪዎች አዳራሽ ውስጥ በአካል በመገኘት፥ አብዛኛዎቹ ተመራቂ ተማሪዎች ደግሞ በየቤታቸው ሆነው በአማራ ቴሌቪዥን ከጥበብ ህንፃ የመሰብሰቢያ አዳራሽ በቀጥታ ስርጭት፣ በፌስቡክ (Facebook) እና ዩቲዩብ (YouTube) የተላለፈውን ታድመዋል።

    ምንጭ፦ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ

    ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ

     

    Anonymous
    Inactive

    ለመጪው የትምህርት ዘመን ትምህርት ቤቶች ከነሐሴ 20 ጀምሮ ምዝገባ እንደሚጀምሩ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)፦ የ2013 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን ምዝገባ ከነሐሴ 20 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ እንደሚጀመር ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ። ሚኒስቴሩ ትምህርት ቤቶች የቀጣይ ዓመት የትምህርት ምዝገባን ከነሐሴ 20 ጀምረው ማካሄድ ይችላሉ ብሏል።

    የትምህርት ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ወ/ሮ ሀረጓ ማሞ፥ ትምህርት ቤቶች ምዝገባውን ሲያካሂዱ ኮሮና ቫይረስን (ኮቪድ 19) ለመከላከል በዓለም የጤና ድርጅት እና በኢፌዲሪ ጤና ሚኒስቴር የተቀመጡ ቅድመ ዝግጅቶችንና መከላከያ መንገዶችን በሚገባ በመተግበር መሆን እንዳለበት አሳስቧል።

    ትምህርት የሚጀመርበት ቀን በቀጣይ እንደሚወሰንና ይፋ እንደሚደረግም የገለፁት ዳይሬክተሯ፥ የቀጣዩ ዓመት የትምህርት ሂደት ስኬታማ እንዲሆንም ተማሪዎች፣ መምህራን፣ ወላጆችና መላው የትምህርት ማኅበረሰብ ይህን አስቸጋሪ ወቅት ለማለፍ የሚተላለፉትን ገዢና አስፈላጊ መልዕክቶች ብቻ በመከታተልና ቫይረሱ ሊተላለፍ የሚችልባቸውን መንገዶች ከውዲሁ በማስወገድ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል።

    አካላዊ ርቀትን ጠብቆ ለማስተማር፣ የንፅህና መጠበቂያዎችን ከማዘጋጀትና መሰል የኮሮና ቫይረስን  የመከላከያ መንገዶችን ተግባራዊ ለማድረግ በሚያስችል መልኩ ቀድመው ዝግጅት የሚደረግባቸው ተግባራትም እንደሆኑ አክለው ገልጸዋል።

    በምን ዓይነት መልኩ ትምህርት መጀመር እንዳለበት የተለያዩ አማራጮችን ለማመላከት ሰፊ ውይይት እየተደረገባቸው ሲሆን፥ ውሳኔዎች ላይ ሲደረሱ በቀጣይ ይፋ ይደረጋሉ።

    የ8ኛና የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ጊዜን በተመለከተ ትምህርት ሚኒስቴር በቅርብ የሚያሳውቅ ሲሆን ተማሪዎች ራሳቸውን እያዘጋጁ እንዲቆዩ ሚኒስቴሩ አሳስቧል።

    በመጪው የትምህርት ዘመን ተማሪዎች ለኮሮና ተጋላጭ እንዳይሆኑ ትምህርት ሚኒስቴር ምን ዓይነት ዝግጅት እያደረገ ነው?

    በ2013 የትምህርት ዘመን ተማሪዎች ለኮሮና ተጋላጭ እንዳይሆኑ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ትምህርት ሚኒስቴር ነሐሴ 19 ቀን 2012 ዓ.ም. አስታወቋል።

    የትምህርት ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢ/ር ጌታሁን መኩሪያ እንደገለጹት፥ የቀጣዩ ዓመት ትምህርት ምዝገባ ከነገ ነሐሴ 20 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በመንግሥት እና በግል ትምህርት ቤቶች እንደሚጀመር እና ትምህርት ቤቶች የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ቅደመ ዝግጅቶችንና  ተግባራትን በተገቢው መንገድ በመተግበር ምዝገባ እንዲያከናውኑ አሳስበዋል።

    የበሽታው ሁኔታ እየተስፈፋ ቢሆንም የትምህርት ዝግጅት እና እንቅስቃሴ መጀመር አስፈላጊ ሆኑ መገኘቱን ነው ሚኒስትሩ የተናገሩት።

    ወደ መማር ማስተማር ተግባር በሚገባበት ወቅት ለተማሪዎች ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር እንደሚሠራ ገልጸው፥ የፊት መሸፈኛ ጭንብል (face mask)፣ የእጅ ማፅጃ (sanitizer) እና መሰል አቅርቦቶችን ከባላድርሻ አካላት ጋር በመሆን ለማቅረብ በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

    በግልም ሆነ በመንግሥት ትምህርት ቤቶች የኮሮና ቫይረስ ስርጭት እንዳይከሰት ተማሪዎች የፊት መሸፈኛ ጭንብል በማድረግ፣ አካላዊ ርቀትን በመጠበቅ እና እጅን በተደጋጋሚ በመታጠብ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚኖርባቸው ሚኒስትሩ አሳስበዋል።

    ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ እስከ 12ኛ ክፍል ላሉት ተማሪዎች በ2012 የትምህርት ዘመን በ2ኛ ሴሚስተር ያለፋቸውን ትምህርቶች ማካካሻ ለመስጠት መታሰቡንም ዶ/ር ኢ/ር ጌታሁን ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮሮፖሬሽን (EBC) ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል።

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    በመጪው የትምህርት ዘመን ተማሪዎች

    Anonymous
    Inactive

    ድሬዳዋ፣ መዳ ወላቡ እና ሰመራ ዩኒቨርሲቲዎች ከ460 በላይ ተማሪዎችን አስመረቁ

    ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የሙያ መስኮች በድኅረ ምረቃና በቅድመ መደበኛ መርሃ ግብር ያሰለጠናቸውን 118 ተማሪዎች አስመረቀ። ከተመራቂዎች መካከል 56ቱ የድኅረ ምረቃ ተማሪዎች ሲሆኑ፥ 23 ተማሪዎች ደግሞ በጤና ሳይንስ ኮሌጅ የሰለጠኑ የሕክምና ዶክተሮች እንዲሁም በቴክኖሎጂ ኢኒስቲቲዩት 39 ተማሪዎች በኪነ ህንፃ በመጀመሪያ ዲግሪ ያሰለጠናቸው ናቸው።

    የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፈጡም ሙስጠፋ ተመራቂዎች ሃገራችን በኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ ውስጥ ሆና የተመረቁ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ በተለይም የሕክምና ተመራቂዎች የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል በተጀመረው ጥረት ውስጥ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

    ሌሎችም በተመረቁበት ሙያ የሀገሪቱን እድገት በማረጋገጥ ረገድ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል።

    የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ኡባህ አደም በበኩላቸው፥ ዩኒቨርሲቲው በምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት በመሰማራት በ2012 በጀት ዓመት 38 የምርምር ሥራዎች ፀድቀው ወደ ሥራ መግባታቸውንና ሃያ ሰባቱ መጠናቀቃቸውን ተናግረዋል።

    ከዩኒቨርሲቲው ጋር በተያያዘ፥ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሙሉ ነጋ እና ሌሎች የሥራ ኃላፊዎች የድሬደዋ ዩኒቨርሲቲን የሥራ እንቅስቃሴ ጎብኝተዋል።

    በጉብኝቱ የዩኒቨርሲቲው ሪፈራል ሆስፒታል ያለበትን የግንባታ ደረጃና የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ በዩኒቨርስቲው እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችንና የSTEM ማዕከሉን ጎብኝተዋል።

    ከተማሪዎች ምረቃ ዜና ሳንወጣ፥ መዳ ወላቡ እና ሰመራ ዩኒቨርሲቲዎች በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ያሰለጠናቸውን 345 ተማሪዎች ነሐሴ 16 ቀን 2012 አስመርቀዋል።

    የመዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አህመድ ከሊል በምረቃው ሥነ-ሥርዓት እንደተናገሩት፥ ተቋሙ በየዓመቱ በርካታ ተማሪዎችን አሰልጥኖ ቢያስመርቅም ዘንድሮ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከፍተኛ ጫና አሳድሯል። ሆኖም እንደ “ኦንላይን” ያሉ የተለያዩ አማራጭ በመጠቀም ምሩቃን ተማሪዎች የሚጠበቅባቸውን እንዲያሟሉ ማድረጉንም ገልጸዋል።

    መዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ በዕለቱ በሁለተኛ ዲግሪ መርሃ ግብር ያስመረቃቸው 208 ተማሪዎች አምስተኛው ዙር ሲሆኑ፥ በተፈጥሮ ሳይንስ፣ ቋንቋና ሥነ ጽሁፍ፣ ሕክምናና ጤና ሳይንስ፣ ማኅበራዊ ሳይንስ፣ የተፈጥሮ ቀመር፣ ቢዝነስና ምህንድስና የተማሩ ናቸው።

    ዶክተር አህመድ እንደገለጹት፥ ዩኒቨርሲቲው የአካባቢውን ማኅበረሰብ ከኮሮና ቫይረስ ለመጠበቅ ግንዛቤ ከማስጨበጡ በተጓዳኝ ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን የመደገፍና ተመርምረው ራሳቸውን እንዲያውቁ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል። ተመራቂዎች በትምህርት ቆይታቸው የቀሰሙትን ዕውቀት ወደ ተግባር ቀይረው ሀገራቸውንና ሕዝባቸውን እንዲያገለግሉና ኮሮናን በመከላከሉም የድርሻቸውን እንዲወጡ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

    ከተመራቂዎች መካከል መሐመድ አህመድ በሰጠው አስተያየት፥ ኮሮና ቫይረስ በትምህርቱ ዘርፍ ጫና ቢያሳድርም በቴክኖሎጂ ታግዘው ለምርቃት በመብቃቱ መደሰቱን ገልጾ፥ በሰለጠነበት ሙያ ሕብረተሰቡን ለማገልገል ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል። ሌላው የእለቱ ተመራቂ ጣህር መሐመድ በበኩሉ በሙያው ሕዝቡን በማገልገል የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ገልጿል።

    በ1999 ዓ.ም 742 ተማሪዎች ተቀብሎ ሥራ የጀመረው መዳ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ አሁን ላይ ከ24ሺህ የሚበልጡ ተማሪዎች እንዳሉት ተመልክቷል።

    በተመሳሳይ ሰመራ ዩኒቨርሲቲ በመደበኛ፣ ርቀትና ተከታታይ የትምህርት መረሃ ግብር ያሰለጠናቸው 137 ተማሪዎች አስመርቋል።

    የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር አደም ቦሪ በምረቃው ሥነ-ሥርዓት እንደገለጹት፥ ያስመረቋቸው ተማሪዎች ኮሮና ቫይረስ ጫና ቢፈጥርባቸውም አማራጭ የመገናኛ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ናቸው።

    ከተመራቂዎቹ መካከል 107 ተማሪዎች በሁለተኛ ዲግሪ በተለያዩ የትምህርት መስኮች የሰለጠኑ ሲሆኑ፥ ቀሪዎቹ በመጀመሪያ ዲግሪ መደበኛ፣ ርቀትና ተከታታይ ትምህርት የተከታተሉ መሆኑ ተመልክቷል።

    ተመራቂዎች ወደ ሥራ ሲገቡ በሰለጠኑበት ሙያ ሀገራቸውንና ሕዝባቸውን በቅንነትና ፍትሃዊነት ማገልገል እንዳለባቸው ፕሬዚዳንቱ ዶ/ር አደም ቦሪ አሳስበዋል።

    ከተመራቂዎች መካከል በሁለተኛ ዲግሪ አካውንቲንግና ፋይናንስ የትምህርት መስክ አራት ነጥብ በማምጣት የተመረቀው መሃመድ አሊ በሰጠው አስተያየት፥ ከ17 ዓመታት በኋላ ወደ ትምህርት ተመልሶ የቤተሰብ ኃላፊነትና የሥራ ጫና ተቋቁሞ ለዚህ ውጤት በመብቃቱ መደሰቱን ገልጿል። በቀጣይም እራሱን የበለጠ በማብቃት በተሰማራበት ሙያ በቅንነትና በትጋት ሀገሩን ለማገልገል እንደሚሠራ ተናግሯል።

    ድሬዳዋ፣ መዳ ወላቡ እና ሰመራ ዩኒቨርሲቲዎች ከ460 በላይ ተማሪዎችን አስመረቁ

    Anonymous
    Inactive

    በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በተፈጠረው የሰላም እጦት ጋር በተያያዘ ከ640 በላይ ተማሪዎች፣ 40 መምህራን እና ከ240 በላይ የአስተዳደር ራተኞች ላይ የተለያዩ እርምጃዎች መወሰዳቸው ተገለጸ

    አዲስ አበባ (ኢብኮ) – ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ተፈጥሮ የነበረው የጸጥታ ችግር ለማረጋጋት በ22 ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በነበሩ ከ640 በላይ ተማሪዎች፣ 40 መምህራን እና ከ240 በላይ የአስተዳደር ሠራተኞች ላይ የተለያዩ እርምጃዎች እንደተወሰደ የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ገልጿል።

    በዩኒቨርሲቲዎች በተፈጠረ የሰላም እጦት 35 ሺህ ተማሪዎች ትምህርት ጥለው መውጣታቸውን የገለጸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ፥ እነዚህን ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው ለመመለስ እየተሠራ መሆኑን አስታውቋል። የተማሪዎችን አደረጃጀት በኅብረ ብሔር ለማሰባጠር መታሰቡንም ሚኒስቴሩ ገልጿል።

    የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ዩኒቨርሲቲዎች ሰላም ባጡባቸው ጉዳዮች ላይ ከተለያዩ አካላት ጋር ግምገማ እና ምክክር እያደረገ ይገኛል።

    በ22 ዩኒቨርሲቲዎች ተፈጥሮ የነበረውን የጸጥታ ችግር ለማጣራት የተዋቀረው ኮሚቴ ባደረገው የመስክ ምልከታ ያዘጋጀው ሪፖርት በመድረኩ ላይ ቀርቧል። በቀረበው ሪፖርትም የዩኒቨርሲቲዎች የሰላም መታወክ የፖለቲካ አመራሮች ትልቅ ሚና እየተጫወቱ እንዳለ ተገልጿል።

    በተለያዩ ክልሎች ባሉ የተለያዩ የፖለቲካ አመራሮች የሚወጡ መግለጫዎች እና ከግቢ ውጭ ተማሪዎችን ሰብስቦ ተልእኮ የመስጠት ሥራዎች ለመማር ማስተማሩ መታወክ እንደ አንድ ምክንያት ተጠቁሟል። ተልእኮ የተቀበሉ ተማሪዎች መማር የሚፈልጉ ተማሪዎች ላይ የሥነ ልቦና፣ አካላዊ፣ የሕይወት እና ንብረት ጉዳት በማድረስ ግጭት እንደሚያነሳሱም ተጠቁሟል። በሚዲያዎች፣ በሶሻል ሚዲያዎች እና በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን የተጋነኑ እና የተዛቡ መረጃዎች መሰራጨት፣ የዩኒቨርሲቲ አመራሮች ችግሮችን ውጫዊ ማድረግ ወይም ቸልተኝነትም ሌላው ለዩኒቨርሲቲዎች የሰላም እጦት የተነሣ ተግዳሮት ነው። በዩኒቨርሲቲዎች ያለው በቤተ ዘመድ የተሳሳበ የሠራተኛ አደረጃጀት እንዲሁ እንደ አንድ ችግር ተጠቅሷል።

    ችግር የፈጠሩ እና ምንም ዓይነት የሕግ እርምጃ ሳይወሰድባቸው በነፃ የሚለቀቁ እና እንዲማሩ የሚፈቀድላቸው ተማሪዎችም በዩኒቨርሲቲዎች ለሚታየው የሰላም እጦት ሌላው ምክንያት መሆናቸው ተጠቁሟል።

    በዩኒቨርሲቲ አመራሩ በኩል ውጫዊ ማስፈራሪያዎችን በመፍራት ውሳኔ ሰጭነት ላይ የሚታየውን ማፈግፈግ እንዲሻሻል እና ጠንካራ አስተዳደራዊ እርምጃ እንደሚወሰድም ተገልጿል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢብኮ) / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በዩኒቨርሲቲዎች የሰላም እጦት

    Semonegna
    Keymaster

    ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ጥፋት ፈፅመው በተገኙ 77 ተማሪዎች ተማሪዎች ላይ ዛሬ እርምጃ ወሰደ

    ሐረማያ (ሰሞነኛ) – ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተወሰኑት የአገራችን ዩኒቨርሲቲዎች ሰላማዊ መማር ማስተማርን ለማረጋገጥ አስቸጋሪ ችግሮች እንደጋጠማቸው ይታወቃል። በተለይ በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ያለምንም ምክንያት ውድ የሆነው የሰው ሕይወት በሚያሳዝን ሁኔታ ጠፍቷል።

    ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ይህ እንዳይሆን ጠንካራ እና ሁሉን አቀፍ ቅንጅት በማድረግ ሲሠራ በመቆየቱ የሰው ሕይወት ባያልፍም የጥፋት አላማን አንግበው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ጥቂት ተማሪዎች ግን ሰላማዊ መማር ማስተማር እንዲታወክ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ የዩኒቨርሲቲውን አጠቃላይ ህልውናን ጭምር አደጋ ውስጥ በመክተት የጥፋት ተልዕኮአቸውን ሲያከናውኑ ቆይተዋል። እነዚህ ለጥፋት የተሰማሩ ተማሪዎች ከጥፋታቸው እንዲመለሱና እንዲታረሙ ተደጋጋሚ ምክርና ጊዜ የተሰጣቸው ቢሆንም ከጥፋታቸው ሊታረሙ አልቻሉም።

    በመሆኑም የዩኒቨርሲቲውን ሰላማዊ መማር ማስተማርን ለማስቀጠል እንዲቻል በተለያዩ ጊዜያት በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማር ሥራው እንዲስተጓጎል ምክንያት በሆኑ 77 ተማሪዎች ላይ እርምጃ የተወሰደባቸው ሲሆን ለእርምጃው መወሰድ ምክንያቶች በዋናነት የሚከተሉትን ያካትታል፦

    • በዩኒቨርሲቲው ሰላማዊ መማር ማስተማር እንዳይኖር በተደራጀ ሁኔታ ሰላማዊ ተማሪ ላይ ጥቃት በማድረስ፣ ሕገ-ወጥ ሰልፍ በማደራጀት እና መማር ማስተማር እንዳይካሄድ የተለያዩ እንቅፋቶችን በመፍጠር፣
    • በቡድን ተደራጅተው በማንነት ላይ የተመሠረተ ጥቃት ማድረስ ፣ የማሸማቀቅ እና የማስፈራራት ተግባርን በመፈፀም፣
    • በሕገ-ወጥ ሰልፍ በዩኒቨርሲቲው ንብረት ላይ ውድመት ማድረስ፥ ለምሳሌ፡- ታህሳስ 30 ቀን 2012 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ በዩኒቨርሲቲው የቴክኖሎጂ ተቋም 3 (ሦስት) ተሸከርካሪዎችን አውድመዋል፤ የባንክ ኤቲኤም (ATM) ማሽን ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጪ አድርገዋል፤ ዩኒቨርሲቲው ላይም ከፍተኛ ውድመት እንዲከሰት እሳት አቀጣጥለዋል።
    • የብሔር ግጭት የሚቀሠቅሱ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸውን ንግግሮችን በማጉላት በተማሪዎች መሀከል የስጋት ድባብ እንዲነግስ ማድረግ እና ብሔርን መሠረት አድርጎ ተማሪን በመከፋፈል ትምህርት አቋርጠው እንዲበተኑ ማድረግ ይጠቀሳል።

    በዚሁ መሠረት ሰላማዊ ተማሪዎችን ሕይወት ለመጠበቅና ሰላማዊ የመማር ማስተማሩን ሥራ ለማስቀጠል ሲባል እርምጃ ከተወሰደባቸው አጥፊ ተማሪዎች መካከል 2 (ሁለቱ) ሙሉ ለሙሉ እንዲሰናበቱ የተደረገ ሲሆን 75 ተማሪዎች ደግሞ ለ2 (ሁለት) ዓመት ከትምህርት ገበታቸው እንዲታገዱ ተወስኗል።

    በተጨማሪም ሁለት መምህራን ተማሪዎችን በማስኮብለል ድርጊት ላይ ተሳትፈው በመገኘታቸው በደመወዝ ቅጣትና የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ እንዲደርሳቸው ተደርጓል።

    ዩኒቨርሲቲው ድብቅ ዓላማን አንግበው በተለያዩ ማደነጋገሪያ ሽፋኖች የሚንቀሣቀሱ እና ተቋሙ የጥፋት ዓላማዎች ማራመጃ ሜዳ እንዲሆን ሁኔታዎችን ለማመቻቸት የሚሠሩ ተማሪዎች፣ መምህራን እና የአስተዳደር ሠራተኞች ላይ በቀጣይ የማጣራት ሥራ የሚሠራ ሲሆን፥ እንደጥፋታቸው ደረጃ እና ጥልቀት ሕጋዊ እና ተቋሟዊ እርምጃ ለመውሰድ በቁርጠኝነት እንደሚሠራ እያሳወቅን፥ ዩኒቨርሲቲው የሚያደርገው ጥረት ስኬታማ እንዲሆን ሁሉም ጉዳዩ የሚመለከታቸው እና የሀገራቸው እና የዩኒቨርሲቲያቸው ሰላም የሚያሳስባቸው የአስተዳደር፣ ፀጥታ እና ማኅበረሰብ አካላት እንደተለመደው ከዩኒቨርሲቲው ጐን እንዲቆሙ በአክብሮት እንጠይቃለን። በተጨማሪም የተማሪ ቤተሰቦች ልጆቻችሁን በመምከር እንድታግዙን ዩኒቨርሲቲው ጠይቋል።

    ምንጭ፦ ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ


    Anonymous
    Inactive
    • ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በዩኒቨርሲቲው የጸጥታ ችግር የተሳተፉ ተማሪዎች ላይ እርምጃ ወሰደ
    • ወሎ ዩኒቨርሲቲ በ335 ተማሪዎች፣ ሁለት የአስተዳደር ሠራተኞች እና አንድ መምህር ላይ እርምጃ ወሰደ
    • የጋምቤላ፣ ቦንጋ እና አርባምንጭ ዩኒቨርሲቲዎች የተማሪዎች ጥያቄዎች በተለያዩ ሀይሎች ሴራ እንዳይጠመዘዝ አስቀድመው በመሥራታቸው የመማር ማስተማር ሂደቱ በሰላማዊ ሁኔታ መቀጠሉን አስታወቁ

    የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ሴኔት ታህሳስ 27 ቀን 2012 ዓ.ም. ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ በ2012 ዓ.ም. በተደጋጋሚ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር የተለያየ ተሳትፎ በነበራቸው ተማሪዎች ላይ የሚከተሉትን ውሳኔዎች ወስኗል።

    1. ሁለት (2) ተማሪዎች ሙሉ በሙሉ ከትምህርት ገበታቸው እንዲሰናበቱ፣
    2. ሰባት (7) ተማሪዎች እያንዳንዳቸው ለሦስት (3) ዓመት ከትምህርት ገበታቸው እንዲታገዱ፣
    3. ስምንት (8) ተማሪዎች እያንዳንዳቸው ለሁለት (2) ዓመት ከትምህርት ገበታቸው እንዲታገዱ፣
    4. አንድ (1) ተባሮ የነበረ (በወቅቱ የዩኒቨርሲቲው ተማሪ ያልነበረ) ነገር ግን በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ውስጥ ተሳታፊ የነበረ ዩኒቨርሲቲው ክስ መስርቶ ግለሰቡን በሕግ ተጠያቂ እንዲያደርግ፤

    በመጨረሻም በወቅቱ ለሴኔቱ ውሳኔ ለቀረበ ተጨማሪ ስልሳ ዘጠኝ (69) ተማሪዎች ዲሲፕሊን ጉዳይ ላይ ተወያይቶ ጥፋታቸው በሂደት ተጣርቶ ወደ ፊት እርምጃ እንደሚወሰድባቸው እንዲሁም በቀጣይ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር በተለያየ መልኩ ተሳታፊ የነበሩ የዩኒቨርሲቲው ሠራተኞች ላይ እንደየጥፋታቸው እርምጃ እንደሚወሰድ አቅጣጫ ተቀምጧል።

    በተያያዘ ዜና የጋምቤላ፣ ቦንጋ እና አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲዎች የተማሪዎች ጥያቄዎች በተለያዩ ሀይሎች ሴራ እንዳይጠመዘዝ አስቀድመው በመሥራታቸው የመማር ማስተማር ሂደቱ በሰላማዊ ሁኔታ መቀጠሉን አስታወቁ።

    ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሃይማኖትና የብሄር ተኮር ግጭቶች ማዕከል ሆነው እና የጸጥታ ችግር ተጋርጦባቸው ጥቂት የማይባሉ ዩኒቨርሲቲዎችም በተደጋጋሚ ትምህርት ለማቆም ተገደዋል፤ በተማሪዎች ላይም ጉዳት አጋጥሟል። የግጭት መንስኤዎች የተለያዩ ሲሆን አንዳንዶቹ ከአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች ጋር የተያያዙ ናቸው።

    ወሎ ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማር ሥራውን አውከዋል ያላቸውን 332 ተማሪዎች፣ ሁለት የአስተዳደር ሠራተኞች እና አንድ መምህር ላይ እርምጃ መውሰዱን አስታወቋል።

    ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር በመሆን ባለፉት ሁለት ወራት ችግር ፈጣሪዎችን ለመለየት በተከናወነው ጠንካራ የሕግ ማስከበር ሥራ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሥራው እንዳይቀጥል ፍላጎት ባላቸው 332 ተማሪዎች፣ ሁለት የአስተዳደር ሠራተኞች እና አንድ መምህር ላይ እርምጃ መወሰዱን ዩኒቨርስቲው አስታውቋል።

    የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር አባተ ጌታሁን ለ ኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እንደገለጹት፥ ዩኒቨርሲቲው በሰላማዊ የመማር ማስተማር ሥራ ተመራጭ እና ተምሳሌት ሆኖ ቆይቷል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በብሔር እና በሀይማኖት ሽፋን በተፈጠረ አለመረጋጋት የመማር ማስተማር ሥራው ባለፉት ወራት ውስጥ ለሦስት ጊዜ መቋረጡን አውስተዋል።

    በዚህም የሁለት ተማሪዎች ሕይወት ማለፉንና በተወሰኑት ላይ ደግሞ የአካል ጉዳት መድረሱን ጠቅሰው፣ ይህም ከአንድ የእውቀት ምንጭ ተቋም የማይጠበቅ አሳፋሪ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።

    የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጴጥሮስ ወልደጊዮርጊስ ግን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ የሚታዩት የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች ለግድያ የሚያደርሱ እንዳልሆኑ ይናገራሉ። አብዛኛዎቹ ተማሪዎች ሰላም ወዳድ መሆናቸውን የሚገልጸው ዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማሩን ለማወክ የሞከሩ ጥቂት ተማሪዎች እንዳልተሳካላቸው የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ገልፀዋል።

    ከ4 ሺህ በላይ ተማሪዎችን እያስተናገደ የሚገኘው ጋምቤላ ዩኒቨርሲቲም ሁነኛ የጸጥታ ችግር ሳያጋጥመው የመማር ማስተማሩ ሂደት በሰላማዊ ሁኔታ ከቀጠለባቸው ዩኒቨርሲቲዎች መካከል ተጠቃሹ ነው። ዩኒቨርሲቲው ባወጣው መርሃ ግብር መሠረት የአንደኛ መንፈቅ ዓመት ትምህርትን ወደማገባደድ መቃረቡን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ኡጁሉ ኦካክ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።

    የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛም የመማር ማስተማር ሂደቱ በሰላማዊ ሁኔታ መቀጠሉን አንስተዋል። ዩኒቨርሲቲዎቹ በተለይም ተማሪዎች በተደጋጋሚ የሚያነሷቸውን የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመቅረፍ ካልተቻለም ለማሻሻል ጥረት ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።

    ተማሪዎችን ተቀብለው ማስተናገድ ከጀመሩ በኋላ የሚነሱ ቅሬታዎችን በአጭሩ ለመፍታትም ከተማሪዎች ጋር የሰከነ እና የሰለጠነ ውይይት ማድረጋቸውን የአርባምንጭ እና ጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች ገልፀዋል። ለዚህም ተማሪዎች እያንዳንዱ ጥያቄ በሂደት እንደሚፈታ ማመናቸውና አርቆ ተመልካችነታቸው ሰላማዊ ሁኔታው እንዲቀጥል ትልቁን ድርሻ እንደተወጣም ተጠቁሟል።

    የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገኙባቸው አካባቢዎች የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት መሪዎች እና ወጣቶች በሰላማዊ የመማር ማስተማሩ ሂደት ላይ የራሳቸውን ሚና እንዲወጡ መደረጉንም ዩኒቨርሲቲዎቹ የገለጹት።

    የዩኒቨርሲቲዎቹ ባለቤት የሆነው ማኅበረሰብ ተማሪዎቹን እንደ ራሱ ልጆች ተመልክቶ እንዲጠብቃቸው የተሰራው ሥራም ውጤታማ እንደነበር ነው ፕሬዚዳንቶቹ የገለጹት።

    ተማሪዎችም በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች የታዩ አሰቃቂ ተግባራት እንዳይደገሙ በጋራ መሥራት አለባቸው፤ ከስሜታዊ ድርጊትም ሊታቀቡ ይገባልም ነው ያሉት። የብዙሃኑን ሰላም ለመጠበቅ ጥቂት በጥባጮችን አደብ ማስገዛት ይገባል ብለዋል በመልዕክታቸው።

    ምንጮች፦ ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ / የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    በዩኒቨርሲቲዎች የጸጥታ ችግር

    Semonegna
    Keymaster

    የሳይንስና ክፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ዶ/ር ጀማል አባፊጣ ከሚያዚያ 11 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ አዲሱ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ሆነዉ እንዲያገለግሉ መርጧቸዋል። ዶ/ር ጀማል ዩኒቨርሲቲው ውስጥ እ.ኤ.አ ከ2003 ጀምሮ በተለያዩ የሥራ ቦታዎች አገልግለዋል።

    ጅማ (ሰሞነኛ) – ጅማ ዩኒቨርሲቲ ለፕሬዝዳንትነት ቦታ ብቃቱና ፍላጎት ያላቸዉ አመልካቾች እንዲወዳደሩ ጥር 24 ቀን 2011 ዓ.ም. በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ባወጣዉ ግልጽ ማስታወቂያ መሠረት አመልካቾች መረጃቸዉን በማስገባት በተለያዩ ደረጃዎች ዉድድር ሲካሄድ መቆየቱ ይታወሳል::

    በምርጫ ሂደቱም ከ250 በላይ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ ተወካዮች በተገኙበት የዩቨርሲቲዉ ሴኔት እና የሥራ አመራር ቦርድ መጋቢት 7 ቀን 2011 ዓ.ም. የቃለ-መጠይቅ ፓናል በማካሄድ ለዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንትነት የተወዳደሩና ማጣሪያዎችን አልፈው የደረሱ 9 ዕጩዎችን በመገምገም 5 ዕጩዎችን ለዩኒቨሲቲዉ የሥራ አመራር ቦርድ አስተላልፏል።

    የዉድድሩ ሂደት የተመራዉ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ባወጣዉ መስፈርት ሲሆን፤ ሂደቱን ለመምራት አምስት ሰዎችን የያዘ ኮሚቴ ተቋቁሞ በየደረጃዉ ግምገማ ሲያካሄድ ቆይቷል። ኮሚቴዉ ከቦርድ አባላት፣ ከሴኔት አባላት፣ ከተማሪ፣ ከመምህራን እና ከአስተዳደር ሠራተኞች ተወካይ የተዉጣጣ ሲሆን የዉድድር ማስታወቂያ ከማዉጣት ጀምሮ ለዩኒቨርሲቲዉ የሥራ አመራር ቦርድ ጉባዔ የሂደቱን ዉጤት እስከ ማሳወቅ ድረስ በትጋት ሲሠራ ቆይቷል።

    በዚሁ መሠረት የዩኒቨርሲቲዉ የሥራ አመራር ቦርድ ሚያዚያ 02 ቀን 2011 ዓ.ም. ባካሔደው ልዩ ጉባዔ 3 ዕጩዎችን (ዶ/ር ጀማል አባፊጣ፣ ፕሮፌሰር አርጋዉ አምበሉ እና ዶ/ር ናቃቸዉ ባሹን) በዕጩነት ለሳይንስና ክፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አቅርቧል:: የሳይንስና ክፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴርም ዶ/ር ጀማል አባፊጣን ከሚያዚያ 11 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ አዲሱ የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ሆነዉ እንዲያገለግሉ መርጧቸዋል።

    ዶ/ር ጀማል አባፊጣ የዩኒቨርሲቲዉ ነባር መምህር እና ተመራማሪ ሲሆኑ በተለያዩ ደረጃዎች በዩኒቨርሲቲውና ከዩኒቨርሲቲው ውጭ በሃላፊነት ያገለገሉና በአሁኑም ወቅት የማኅበረሰብ አገልግሎት ቢሮ ዳይሬክተር ሆነዉ እያገለገሉ ይገኛሉ። ዶ/ር ጀማል አባፊጣ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በስታቲስቲክስ (BSc in Statistics)፣ የሁለተኛ ዲግሪያቸውንም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ (MA in Economics)፣ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ደግሞ በደቡብ ኮርያ ቻንችኦን ከተማ ከሚገኘው ካንግዎን ናሽናል ዩኒቨርሲቲ (Kangwon National University; Chuncheon, South Korea) በግብርና ግብዓቶች ምጣኔ ሀብት (Agricultural Resources Economics) አግኝተዋል።

    ስለ ዶ/ር ጀማል አባፊጣ የትምህርት ዝግጅትና የሥራ ልምድ ይህን ማስፈንጠርያ በመጫን ሙሉ መረጃ ማግኘት ይችላሉ።

    ምንጭ፦ ጅማ ዩኒቨርሲቲ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
    ——
    ሌሎች ዜናዎች፦

    ጀማል አባፊጣ


    Semonegna
    Keymaster

    እ.ኤ.አ በ2011 የተመሠረተው ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ዶክተሮችን ሲያስመርቅ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ጊዜ እንደሆነ ተገልጿል። ዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ወቅት ስድስት ኮሌጆች፣ አንድ ትምህርት ቤት እና አንድ ተቋም (ኢንስቲትዩት) አለው። 

    ዓዲግራት (ሰሞነኛ)– ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ለመጀመርያ ግዜ ሰባት ሴቶች 25 ወንዶች በድምሩ 32 የሕክምና ዶክተሮችን (medical doctors) እንዲሁም በድኅረ መሠረታዊ መርሃግብር (post basic program) 30 ተማሪዎችን አስተምሮ መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም. አስመርቋል። በዕለቱ የክብር እንግዳ የነበሩ የትግራይ ክልል ም/ር/መስተዳደር ክቡር ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል ባስተላለፉት መልዕክት፥ በሃገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ከፍተኛ የጤና ባለሙያዎች እጥረት እንዳለና ችግሮቻችን በማቃለል አንዳንዱን በመፍታት ልዩነት የሚያመጣ ድርሻ እንደሚኖራችሁ ባለ ሙሉ ተስፋ ነኝ ብለው መልእክታቸው አስተላልፍዋል።

    በዕለቱ የምርቃት ሥነ ስርዓት ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሚኒስትር ድኤታ ወ/ሮ ስሃረላ ኣብዲላሂ በበኩላቸው የጤና ባለሙያ ማለት የግል ምቾትን እንደ መስዋዕትነት በመክፈል እንብካቤ ለሚያስፈልጋቸው እንክብካቤ መስጠት መሆኑን በማወቅ በየተኛውም የሃገሪቱ ክፍል ሄዳችሁ ያስተማራችሁን ህብረተሰብ ለማገልገል ዝግጁ እንድትሆኑ በማለት ለዕለቱ ተመራቂዎች መልዕክታቸውን አስተላለፈዋል። ዩኒቨርሲቲው የነበሩበትን ፈተናዎች ኣልፈው ለመመረቅ መብቃታችው በጣም የሚያኮራ ታሪክ መሆኑ የዩኒቨርሲቲው ግዝያዊ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ገ/መስቀል ገልፀዋል።

    ኬር ኢትዮጵያ በ7 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር ወጭ ያስገነባውን የምርምርና የስልጠና ማዕከል ለሐረማያ ዩኒቨርሲቲ አስረከበ

    ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ዶክተሮችን ሲያስመርቅ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሆነ ተገልጿል። ዩኒቨርሲቲው የተመሠረተው እ.ኤ.አ በ2011 ሲሆን፥ በአሁኑ ወቅት ስድስት ኮሌጆች፣ አንድ ትምህርት ቤት እና አንድ ተቋም (ኢንስቲትዩት) አለው። ከሁለት ዓመታት በፊት ዩኒቨርሲቲው ባወጣው የአሃዝ ዘገባ በአጠቃላይ ከ16,000 በላይ ተማሪዎች በመደበኛው፣ እንዲሁም ከ6,000 በላይ ተማሪዎች በተከታታይ (continuing education) መርሀ ግብር እያስተማረ ይገኛል።

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
    ——
    ተመሳሳይ ዜናዎች፦

    ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ


    Semonegna
    Keymaster

    በድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ እና በሞናኮ ኢንስቲትዩት (Institut de Paléontologie Humaine, Fondation Prince Albert Ier de Monaco) መካከል በጋራ ለመሥራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈረመ።
    —–

    ስምምነቱን የድሬዳዋ ከንቲባና የድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ ምክትል ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ኢብራሂም ኡስማን እና የኢንስቲትዩቱ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ሄነሪ ዲ ሉምሌይ (Henry de Lumley) ፈርመዋል ።

    ስምምነቱ ለዩኒቨርስቲው መምህራንና ተማሪዎች የሁለተኛና የሦስተኛ ዲግሪ የትምህርት ዕድልና አጫጭር ስልጠናዎችን የሚያስገኝ ነው ተብሏል።

    በተጨማሪም ስምምነቱ የምርምር ሥራዎችን በጋራ ለመሥራት ዕድል የሚፈጥር ሲሆን በዋናነት በጂኦሎጂና በቅድመ ታሪክ ጥናት ላይ ያተኮረ እንደሚሆን በስምምነቱ ወቅት ተገልጿል ።

    ከንቲባ ኢብራሂም ኡስማን የስምምነቱ መፈረም በድሬዳዋና በአካባቢው ቅድመ ታሪክ ላይ ጥናትና ምርምር ለማድረግ እድል ከመፍጠሩም ባሻገር ዩኒቨርሲቲውን በሰው ሀይል ለማጠናከር ትልቅ እገዛ ይኖረዋል ሲሉ በፊርማ ስነስርአቱ ወቅት ተናግረዋል።

    ምንጭ፦ የድሬዳዋ ከተማ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት

    Semonegna
    Keymaster

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – STEMpower የተሰኘ መቀመጫውን USA (ሳሌም፥ ማሳቹሴትስ፣ አሜሪካ) ያደረገ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ምህንድስና እና ሒሳብ ትምህርቶችን በዩኒቨርሲቲዎች እየረዳ የሚገኝ ሲሆን በአገራችን 13 ማዕከላትን ከፍቶ በትብብር እየሠራና እየረዳ ይገኛል።

    ድርጅቱ የድጋፍ አድማሱን በማስፋት በኢትዮጵያ ተጨማሪ 10 ማዕከላትን (ሰባት ማዕከላትን በመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች፣ ሶስቱን በተለያዩ ከተሞች እ.አ.አ. በ2019) ለመክፈት ከኢፌዴሪ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እንዲሁም ከሰባቱ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የትብብር ስምምነት የካቲት 14 ቀን 2011ዓ.ም. ተፈራርመዋል።

    የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ሂሩት ወልደማርያም (ፕ/ር) STEMpower ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ትምህርቶችን ለማበልጸግ እያደረገ ያለውን ትብብር በማመስገን፥ ዩኒቨርሲቲዎችም ዕድሉን በመጠቀም በአግባቡ ማዕከላቱን ማሳለጥ እንደሚጠበቅባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።

    አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማስተማሪያ ክፍሎቹ ውስጥ ዲጂታል ሰሌዳዎችን መጠቀም ጀመረ።

    የሳንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አፈወርቅ ካሱ (ፕ/ር) በበኩላቸው ለሰባቱ ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች (አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲአዲግራት ዩኒቨርሲቲአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲጅማ ዩኒቨርሲቲ እና ወሎ ዩኒቨርሲቲ) ማዕከሉን በመጠቀም በአካባቢዎቻቸው ያሉትን የማኅበረሰብ ችግሮች መፍታት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

    የSTEMpower አስተባባሪ ዳይሬክተርና ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ቅድስት ገብረአምላክ፥ “STEMpower ከየት ወዴት?” በሚል ርዕስ ከድርጅቱ አመሠራረት ጀምሮ ዓላማውን፣ አሁን ያለበት ሁኔታ እና የወደፊት ዕቅድ አጭር ማብራሪያ ለተሳታፊዎቹ አቅርበዋል። ለወደፊትም ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጋር በስፋት እንደሚሠሩ ፣ በ2040 የበለጸገች ኢትዮጵያን ማየት እንደሆነ ገልጸዋል።

    አገራችን ኢትዮጵያ የራሷን የሆነ ጥንታዊ ታሪክና ባህል ያላት አገር እንደመሆኗ ድርጅቱ በማኅበራዊ ሳይንስ ላይም ትኩረት እንዲያደርግ ከተሳታፊዎቹ አስተያየት ተሰንዝሯል።

    የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) ባደረጉት የመዝጊያ ንግግር ማዕከሎቹ በከፍተኛ ትምህርት እና በሳይንስ ትምህርቶች አከባቢ የሚስተዋሉትን ችግሮች በመቅረፍ የአገሪቱን ብልጽግና ከማረጋገጥ ረገድ መልካም ሁኔታ እንደሚፈጥሩ ገልጸዋል።

    ምንጭ፦ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
    ——
    ሌሎች ዜናዎች፦

    STEMpower


Viewing 15 results - 1 through 15 (of 18 total)