Forum Replies Created
-
AuthorPosts
-
SemonegnaKeymaster
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በቅድመና ድኅረ ምረቃ መርሃ ግብሮች ያሠለጠናቸውን ተማሪዎች ለ35ኛ ጊዜ አስመረቀ
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያና በ2ኛ ዲግሪ መርሃ ግብሮች በመደበኛ፣ በማታ፣ በክረምት፣ በሳምንት መጨረሻ እና በተከታታይና ርቀት፣ እንዲሁም በ3ኛ ዲግሪ በመደበኛ መርሃ ግብር ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ 2,561 ተማሪዎችን ሰኔ 25 ቀን፥ 2014 ዓ.ም አስመርቋል፡፡ ከተመራቂዎቹ መካከል 662ቱ ሴቶች ናቸው፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ የኢትዮጵያን እድገትና ክብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በሀገሪቱ የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማኅበረሰብና ምሩቃን ድርሻቸው የጎላ መሆኑን ጠቅሰው ተመራቂዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የሀገር ሰላምን ለማደፍረስ የሚሰራጩ እኩይ ተልዕኮዎችን ሳያስተናግዱ በስኬት አጠናቀው ለምረቃ በመብቃታቸው አድናቆትና ምስጋና አቅርበዋል፡፡ ይህን መልካም ሥነ ምግባር በማስቀጠል በሚሄዱበት የሀገራችን አካባቢዎች ሁሉ ለሰላም፣ ልማትና ዲሞክራሲ ቅድሚያ ሰጥተው የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉም አደራ ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በ6 ካምፓሶች በ75 የመጀመሪያ፣ በ114 የ2ኛ እና በ26 የ3ኛ ዲግሪ በአጠቃላይ ከ25 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በመደበኛና መደበኛ ባልሆኑ መርሃ ግብሮች በማስተማር ላይ ሲሆን የዛሬዎቹን ተመራቂዎች ጨምሮ ዩኒቨርሲቲው ከ72 ሺህ በላይ ምሩቃንን ማፍራቱን ፕሬዝደንቱ ገልጸዋል፡፡
የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ዳይሬክተር ጄኔራል፣ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ አባልና የእለቱ የክብር እንግዳ አቶ ፈጠነ ተሾመ ለተመራቂዎች ባስተላለፉት መልዕክት ትምህርት ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ እድገት ቁልፍ መሣሪያ እንዲሁም የማይከስር ሀብት መሆኑን በመገንዘብ እንዲሁም የሀገራችንን ሁለንተናዊ ለውጥ ለማረጋገጥ ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸው በመረዳት ተመራቂዎች በትምህርት ቆይታቸው በንድፈ ሃሳብና በተግባር ያገኙትን ዕውቀት በሚሰማሩበት ዘርፍ ሁሉ ለዘላቂ እድገትና ሽግግር እንዲጠቀሙበት አሳስበዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው የቀድሞ ምሩቃን /አልሙናይ/ ማኅበር ፕሬዝደንት አቶ ኤርሚያስ ዓለሙ ተመራቂዎች በትምህርት ያገኙትን ዕውቀት በተግባር ውጤታማ ለማድረግ ብዙ የሚጠበቅባቸው መሆኑን ተናግረው በቀጣይ ራሳቸውን ለማሻሻል እንዲሁም ያስተማራቸውን ቤተሰብ፣ ማኅበረሰብና ሀገር ለማገልገል በታማኝነትና በትጋት እንዲሠሩ እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው የቀድሞ ምሩቃን አባል በመሆን ለአካባቢው ማኅበረሰብና ለዓለም መልካም አስተዋጽኦዎችን እንዲያበረክቱ ጠይቀዋል፡፡
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ዳይሬክተር ጄኔራልና የዩኒቨርሲቲው ሥራ አመራር ቦርድ አባል፣ የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ፣ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮችና ተጋባዥ እንግዶች የተገኙ ሲሆን የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ዓለማየሁ ጩፋሞ እጩ ምሩቃንን ለምረቃ በማቅረብ አስመርቀዋል፡፡
July 4, 2022 at 2:05 am in reply to: ምርጫ በኢትዮጵያ ― የኢትዮጵያ ብሔራዊ እና ክልላዊ ምርጫዎች ― ሰሞነኛ ዜናዎችና መረጃዎች #48240SemonegnaKeymasterፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የኢዜማ መሪ ሆነው ስለተመረጡ እንኳን ደስ ያለዎት!
አቶ አንዱዓለም አራጌከተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች አያሌ ኪሎ ሜትሮች አቆራርጣችሁ ለሁለት ቀናት በዚህ ታላቅ ጉባዔ ላይ የታደማችሁ፣ የተከበራችሁና የተወደዳችሁ የጉባዔ አባለት፥ አንደኛ መደበኛ ጉባዔያችንን በአማረና በተሳካ ሁኔታ ማጠናቀቅ በመቻላችን እንኳንም ደስ አላችሁ! እንኳን ደስ ያለን ለማለት እወዳለሁ።
ኢዜማ ለሀገራችን እንግዳ የሆነዉን የዴሞክራሲ ባህል ናሙና በጓዳዉ ሲጠነስስ ጀምሮ የፓርቲያችንን መፈረካከስ የሚሹ፣ ፓርቲያችንን የሚደግፉና የፓርቲያችን አባላት ሳይቀሩ ተመሳሳይ ድምፀት ያለዉ ሀሳብ ሲያስተላልፉ ሰምተናል፤ ኢዜማ ይፈረካከሳል የሚል። ይህ ታላቅ ጉባዔ በአካሄደዉ ጥብብ የተሞላ ዉይይት ኢዜማ ከመሰነጣጠቅ ይልቅ ተጠናክሮና ፈርጥሞ እንዲወጣ ለማድረግ በመቻሉ በድጋሚ እንኳን ያላችሁ ለማለት እወዳለሁ።
ዴሞክራሲን አምጣ ለመዉለድ ባልቻለችዉ ሀገራችን ማህፀን የተፈጠረዉ ኢዜማ በራሱ ጓዳ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በማድረግ እዉነተኛዉንና መሠረታዊዉን የዴሞክራሲ ችግኝ በመትከል ታሪክ ሠርቷል። ይህ በኢዜማ ጓዳ ዉስጥ የተፈላዉ የዴሞራሲ ችግኝ ነገ አባጣ ጎርብጣዉን የሀገራችንን የፖለቲካ መልክዐ-ምድር በመሸፈን፣ ሀገራችንን ለዘመናት እያቆረቆዛት የመጣዉን ዘመን ጠገብ የፖለቲካ ስብራት ለመፈወስ የመሠረት ድንጋይ እንዳስቀምጥን አማናለሁ።
የተወደዳችሁና የተከበራችሁ የዚህ ጉባዔ አባለት፥ አንድ ከዚህ ወጣ ወደ አለ ጉዳይ ልዉስዳችሁ። ይህን ሰሞን የምርጫ ቅስቀሳ አድርጌ ስመለስ ልጆቼ አንድ ቀልድ ይቀልዱብኝ ነበር፤ ልክ እዚህ መድረክ ላይ የተገኙ በማስመሰል የምርጫዉን ዉጤት በድራማ መልክ ያሳዩኝ ነበር –እንዲህ እያሉ “እባካችሁ ከሦስት ተወዳዳሪዎች አራተኛ ለወጣዉ ለአንዱዓለም አራጌ ሞቅ ያለ ጭብጨባ አድርጉለት” በማለት ሲቀልዱብኝ ነዉ የሰነበቱት። ዛሬ ሟርታቸዉ ሰምሮ በምርጫዉ በመሸነፌ ጥሩ አለንጋ ገዝቼ ወደ ቤት በመግባት ብስጭቴን እንደምወጣባቸዉ ቤቱ እንዲያዉቅልኝ እፈልጋለሁ። ዛሬ እነርሱን አያድርገኝ!
ወደ ፍሬ ሀሳባችን ልመልሳችሁ፤ ኢዜማ ሲጠነስስ ሀሳብ ነበር። ባለፉት ሦስት ዓመታት ደግሞ ድርጅታዊ ዉቅሩን አስቀምጠናል። ከዚህ አንደኛ መደበኛ ጉባዔያችን ቀጥሎ ደግሞ መሬት የቆነጠጠና፣ ሰንጥቆ መዉጣት የሚችል ድርጅት እንዲሆን ስጋ የማልበስ ሥራችንን እንቀጥላለን። ግዙፉን መዋቅራችንን አስፈላጊ የሆኑ አካላዊና ርዕዮታዊ ትጥቆችን በጥንቃቄ ካስታጠቅነዉ ከፊታችን በሚመጡ ዓመታት ለኢትዮጵያችን ፖለቲካዊ ተዓምራቶችን መሥራት የሚችል ድርጅት ይሆናል ብዬ አምናለሁ። አብዛኛዎቻችን በመርከብ ተጉዘን የምናዉቅ አይመስለንም ይሆናል። ነገር ግን መለስተኛ ከተማን የሚያክል መርከብ፣ በባህር ላይ ሲንሳፈፍ ብዙዎቻችን በቴሌቪዥን መስኮት [ሳናይ] አንቀርም። ብዙዎቻችን ይህንን ግዙፍ አካል አንድ ካፒቴን ሺህ ማይሎችን እንዴት ሊያንሳፍፈዉ እንደቻለ እያሰብን እንደመም ይሆናል፤ ነገር ግን መርከቡ ሁለንተናዊ ጤንነቱ ተጠብቆ እንዲንሳፈፍ የሚያስችሉትን አያሌ ቴክኒሽያኖች እንዘነጋለን። በአንድ ቴክኒሽያን ስህተት አንድ ኤሌክራቲካል ወይንም ሜካኒካል ክፍሉ ቢበላሽ ካፒቴኑ ምንም መፈየድ እንደማይችል የምናስተዉል ስንቶቻችን እንሆን?
ኢዜማን የሚያክል ግዙፍ ድርጅትም ያስመዘገባቸዉን በጎ ዉጤቶች ሁሉ ያስመዘገበዉ ሁለንተናቸሁን ለትግሉ ሰጥታችሁ በየአከባቢያችን ኢዜማን ባቆማችሁ ያልተዘመራለቸሁ ጀግኖች ትልቀ ተጋድሎ ጭምር እንጅ በጥቂት አመራሮች ብቻ አልመሆኑን በአንክሮ እገነዘባለሁ። እናንተን ከመሰሉ ጀግኖች ፊት ስቆም ከአክብሮት በላይ ከልቤም ዝቅ የምለዉ ለተጋድሏችሁ ካለኝ ክብር የተነሳ ነዉ። የምርጫዉንም ዉጤት የምቀበለዉ ለእናንተ ካለኝ ትልቅ አክብሮትና ከፍ ያለ ትህትና ጋር ነዉ። ከአንድ ደሃ የገበሬ ቤተሰብ ብገኝም ሁልጊዜም የነፃነትና እኩልነት ጉዳይ ሕይወቴ የሚሾርበት ምህዋር ነዉ። ዴሞክራሲ ስንል አሸንፎ መደሰት ብቻ ሳይሆን ሽንፈትን በፀጋ መቀበልንም ያካትታል። በሂደቱ ግን ከምንም በላይ ድርጅታችን አሸናፊ አድርገናል። በቅስቀሳ ወቅት ቃል እንደገባሁላችሁ ቃሌን እጠብቃለሁ። በማያሻማ ቋንቋ ፕ/ር ብርሃኑ ለሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት እንዲመሯችሁ መርጣችኋቸዋል፤ ምርጫችሁን ተቀብያለሁ። ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ከዚህ ሰዓት ጀምሮ የመርጣችኋቸዉ የእናንተ ብቻ ሳይሆኑ የተፎኮካርኳቸዉ እኔና እኔን የመረጡ የጉባዔ አባላትም መሪ መሆናቸዉን ለመግለፅ እወዳለሀ! በዚህ አጋጣሚ ፕ/ር ብርሃኑን እንኳን ደስ ያለዎት እያልኩ፥ መልካም የሥራ ዘመን እንዲሆንላቸዉ ከልብ እመኛለሁ!!
የምርጫ ዘመቻ ቡድኔን፣ በገንዘብና በምክር የረዳችሁኝ ዜጎች ሁሉ ከልብ እያመሰገንኩ፥ ለሽንፈታችን ተጠያቂዉ እኔና እኔ ብቻ እንደሆኑኩ ለመግለፅ እወዳለሁ!
ዘመኑ የፈተና ነዉ፤ ዘመኑ የትግል ነዉ። በድል የሚወጣዉ ደግሞ በጠንካራ መሠረት ላይ የቆመና አንድነቱን በብርቱ የሚያስጠብቅ ድርጅት ነዉ። ሁላችንም ከዚህ ሰዓት ጀምሮ እጅ ለእጅ በመያያዝ ትግላችንን እንድንቀጥል አደራ እላለሁ!
ፍትህ እንደ ቀጥር ፀሐይ፣ ፍቅር እንደ ኃይለኛ ጅረት፣ ወንድማማችነት እንደ አበባ ጉንጉን በኢትዮጵያ ላይ ለዘላለም ይንገስ!!
[caption id="attachment_48242" align="aligncenter" width="600"] ፕሮፈሰር ብርሃኑ ነጋ እና አቶ አንዱዓለም አራጌ[/caption]
SemonegnaKeymasterዳሸን ባንክ ዘመናዊ የመረጃ ማዕከል አስመረቀ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – ኢትዮጵያ የባንክ አገልግሎት ታሪክ ውስጥ የአዲስ ዘመን ጅማሮ ተደርጎ ሊወሰዱ የሚችሉትን የኤሌክትሮኒክ ክፍያ እና የሞባይል ካርድ አገልግሎቶች በማስተዋወቅ ረገድ ፈር ቀዳጅ የሆነው ዳሸን ባንክ፣ ዘመናዊና በግል የፋይናንስ ተቋም ደረጃ የመጀመሪያ የሆነውን Tier III የውሂብ/የመረጃ ማዕክል (data center) አስመረቀ።
ዳሸን ባንክ ያለውን የመረጃ ቴክኖሎጂ (information technology /IT/) ለማሳደግ በከፍተኛ ደረጃ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነና፤ ለመረጃ ቴክኖሎጂ (IT) መሠረተ ልማትና ግንባታ ብቻ በ2014 በጀት ዓመት አንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር በጀት በመመደብ እየሠራ መሆኑን የባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አስፋው ዓለሙ ለኢትዮጵያ ሪፖርተር ጋዜጣ አብራርተዋል። አሁን የተመረቀውን የውሂብ/የመረጃ ማዕከል (data center) ለመገንባት ባንኩ በአጠቃላይ 230 ሚሊዮን ብር ማውጣቱን አቶ አስፋው ጨምረው ገልጸዋል።
የመረጃ ማዕከሉ ከፍተኛ ኃይል ያላቸውን ከ1,000 ያላነሱ ሰርቨሮችና ሌሎች ተያያዥ የኔትወርክ መሣሪያዎችን የማስተናገድ አቅም ያለው ነው። በጥገና ወቅትም መደበኛ የባንኩን ሥራ ሳያቋርጥ ዓመቱን ሙሉ አገልግሎት መስጠት የሚችል ነው።
የመረጃ ማዕከሉ በአካባቢው የሚስተዋሉ የተለያዩ ክስተቶችን በመለየት ለማዕከሉ ዋና የመቆጣጠሪያ ክፍል መረጃ ማስተላለፍ የሚችል ሲሆን፣ ችግር ሲከሰትም ችግሩን በመለየት ስጋቶችን ለማስቀረት በሚችል ዓለማቀፋዊ ደረጃውን የጠበቀ ቴክኖሎጂ የተሟላ ነው።
ይህ የመረጃ ማዕከል ዘመናዊ የባንክ አገልግሎትን ከየትኛውም ቦታ ማግኘት የሚያስችልና ባንኩ የተለያዩ አዳዲስ አገልግሎቶችን ያለምንም ችግር ወደ ሥራ ለማስገባት የሚያግዘው ይሆናል። በተጨማሪም ባንኩ በዲጂታል ዘርፍ አዳዲስ አገልግሎቶችን በማስተዋወቅና የአገልግሎቱንም ደህንነትና ጥራት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግ ሁነኛ ሚና ይኖረዋል።
ይህ ማዕከል የዳሸን ባንክን ፍላጎት ከማሟላት ባሻገር በሥራ ላይ ለሚገኙ እና ወደ አገሪቱ የባንክ ኢንዱስትሪ ለሚቀላቀሉ የአገር ዉስጥም ሆነ የዉጭ ባንኮች እንዲሁም ለሌሎች ተቋማት አገልግሎት መስጠት የሚችል አቅም ያለዉ ነዉ።
በመረጃ ማዕከሉ ምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ የብሔራዊ ባንክ ገዢ ዶ/ር ይናገር ደሴ፣ የባንኮች ሥራ አስፈፃሚዎች፣ የተለያዩ ድርጅት ኃላፊዎች፣ የባንኩ የሥራ አመራር ቦርድ አባላት፣ የባንኩ የበላይ አመራሮች፣ ተገኝተዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉት ቀደምት እና እጅግ አትራፊ ከሆኑት የግል ባንኮች አንዱ የሆነው ዳሸን ባንክ በአሁኑ ሰዓት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ከ450 በላይ ቅርንጫፎች ያሉት ሲሆን፥ በባለፈው (2013) የበጀት ዓመት ከግብር በፊት 2.4 ቢሊየን ብር ትርፍ አስመዝግቧል። ባንኩ ከሦስት ሚሊዮን በላይ ደንበኞች ሲኖሩት፤ የአሞሌ (በስልክ የባንክ አገልግሎት) ተጠቃሚቾ ቁጥርም ከ2.4 ሚሊየን በላይ ነው። የባንኩ አጠቃላይ ሀብት ደግሞ ከ94 ቢሊዮን ብር በላይ ነው።
SemonegnaKeymasterየአማራን ሕዝብ ሰቆቃ እያየ እንዳለየ፣ እየሰማ እንዳልሰማ…
ጋዜጠኛ አበበ ገላውየአማራ ሕዝብ በደለኝ የሚል ካለ ማስረጃውን ይዞ ይቅረብ። አንድም ሰው አይገኝም። የኦሮሞም ይሁን የትግራይ፣ የአፋርም ሕዝብ ይሁን የሲዳማ፣ የጋምቤላም ይሁን የሶማሌ፣ የጉራጌም ይሁን የወላይታ ሕዝብ… ፈጽሞ ማንንም በድለው አያውቁም። የትኛውም ሕዝብ በጅምላ ግለሰቦችንም ይሁን ቡድኖችን ሊበድል ፈጽሞ አይችልም። ስለዚህም ነው በዓለማችን ላይ እጅግ አሰቃቂው ግፍ በተፈጸመበት አውሮፓ ናዚዎች ለፈጸሙት ወንጀል ተጠያቂ አድርጎ ጀርመኖችን እያደነ የሚገድልና የሚያፈናቅል ቡድን ኖሮ አያውቅም። በእኛም ሀገር ሞሶሎኒ በመርዝ ጋዝ ሳይቀር ለፈጸመው ግፍ ንጹኃን የጣሊያን ዜጎችን አሳደንም ይሁን ጨፍጭፈን አናውቅም። እንዲህ ዓይነቱን አስነዋሪ ወንጀል ብንሞክረውም ግፍ እንጂ ፍትሃዊ ሊሆን ፈጽሞ አይችልም።
በእኛ ሀገር በክፋት ህወሓት በዋነኛነት ከፋፍሎ ለመግዛት እንዲያመቸው መዋቅርና ቅርጽ የሰጠውን ተረት በማንገብ በጥንታዊ ነገሥታትና መንግሥታት ለተፈጸሙ በደሎች መላውን የአማራ ሕዝብ በነፍጠኛነት ፈርጆ ከምንም የሌሉበትን ምሲኪን ድሆች በጅምላ መግደል፣ ማሳደድ፣ ማፈናቀል፣ አፍኖ መውሰድ፣ አካላዊና ስለልቦናዊ ጥቃት መሰንዘር የተለመደ ክስተት ከሆነ አርባ አመታት ተቆጥረዋል። አብዛኛው የአማራ ተወላጅ ሀገሩ እንዳይፈርስ፣ ሕዝብ ለበቀል እንዳይነሳ እና ማለቂያ የሌለው እልቂትና ውድመት እንዳይደርስ በሚል የአስተዋይነት መንፈስና ባህል የሆዱን በሆዱ ይዞ በትዕግስት ህመሙን እና ሀዘኑን አፍኖ በኢትዮጵያዊነት ጨዋነት ከየትኛውም ኢትዮጵያዊ ወገኑ ጋር ተቻችሎና ተከባብሮ ለመኖር የሚቻለውን ሁሉ አድርጓል።
ይሁንና አሳዛኙ ሃቅ የሕዝቡን ትዕግስት እንደ ፍርሃት የቆጠሩ እኩይ ኃይሎች የአማራን ሕዝብ በጅምላ ዘውትር ከማሸማቀቅ አልፈው የጅምላ ጭፍጨፋ፣ ግፍና ማፈናቀል ያለማቋረጥ እየፈጸሙበት ይገኛሉ። የሕዝቡን ሰላምና ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነትን የተረከበው “የለውጥ” ኃይልና መንግሥትም ከእነ መለስ ዜናዊ ባልተለየ ሁኔታ የአማራን ሕዝብ ሰቆቃ እያየ እንዳለየ፣ እየሰማ እንዳልሰማ… ሕዝቡ በገፍ እያለቀና እየተሰቃየ ባለስልጣናቱ ሌላው ቀርቶ የረባ የሀዘን መግለጫ፣ ማጽናኛም ይሁን የአንዲት ሰከንድ የህሊና ጸሎት ነፍገውታል።
የዚህ ታጋሽ ሕዝብ ትግስት አልቋል። መንግሥት የሕዝብን ደህንነትና ሰላም በአግባቡ መጠበቅ ካልቻለና የዜጎቹ የጅምላ ሞት፣ ሰቆቃ መፈናቀል፣ የደም ጎርፍና እንባ ግድ የማይለው ከሆነ ሕዝቡ ሰላሙን፣ ደህነንቱና ዜግነታዊ መብቱን ሙሉ በሙሉ የሚያከብርለትና እኩልነትና አንድነትን የሚያረጋግጥለት መንግሥት እንዲመጣ አምርሮ ከመታገል ውጭ አማራጭ እንደማይኖረው ሊታወቅ ይገባል።
ጋዜጠኛ አበበ ገላው (facebook.com/agellaw)
[caption id="attachment_41752" align="aligncenter" width="600"] በጀርመን የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ሰላማዊ ሰልፍ ላይ[/caption]
February 28, 2021 at 2:57 am in reply to: ምርጫ በኢትዮጵያ ― የኢትዮጵያ ብሔራዊ እና ክልላዊ ምርጫዎች ― ሰሞነኛ ዜናዎችና መረጃዎች #18367SemonegnaKeymasterየምርጫ ክርክር ለማዘጋጀት ፍላጎት ላላቸው የሲቪል ማኅበራት እና ሚዲያዎች የተደረገ ጥሪ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 6ተኛው ጠቅላላ ምርጫ ተግባራትን እያከናወነ እንደሆነ ይታወቃል፤ በዚህም መሠረት የተወሰኑ ተቋማት በተወዳዳሪዎች መካከል የምርጫ ክርክር ለማከናወን ከቦርዱ ፍቃድና አቅጣጫ ለማግኘት ጥያቄዎችን አቅርበዋል።
ይህንን፥ እንዲሁም ሌሎች ልምዶችን መሠረት በማድረግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የእጩዎች ምዝገባ ተጠናቆ ተወዳዳሪ ፓርቲዎች ከታወቁ በኋላ ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ክርክር ሂደትን ለማስተባበር ይፈልጋል። በመሆኑም ከዚህ በፊት ጥያቄ/ ማብራሪያ ያስገባችሁም ሆነ በዚሁ ጉዳይ ላይ ፍላጎት ያላችሁ መንግሥታዊ ያልሆናችሁ ተቋማት እና ሚዲያዎች በተናጠል ወይም በጋራ የምርጫ ክርክር ዝርዝር የፍላጎት መግለጫ ወረቀት (expression of interest) ለቦርዱ እንድታቀርቡ ጥሪ ያቀርባል።
የፍላጎት መግለጫ ማካተት የሚገባቸው ዋና ዋና ሃሳቦች
ማንኛውም የምርጫ ክርክር ለማከናወን የሚያስብ ተቋም የሚመለከቱትን ዋና ዋና ነገሮችን ያሟላ የፍላጎት መግለጫ ሊያቀርብ ይገባል።
- ሊያከናውኑት ያቀዱት የምርጫ ክርክር ግልጽ ዓላማ፣
- ሊያከናውኑት ያቀዱት ክርክሩ የሚከናወንበት መንገድ (mode of engagement)፣
- ሊያከናውኑት ያቀዱት የክርክሩ ሥነ-ምግባር ደንብ (code of conduct)፣
- የክርክሩ ቁጥር ብዛት፣ የተሳታፊዎች ሁኔታ፣ ለሕዝብ የሚቀርብበት ሁኔታ፣
- የአከራካሪ አመራረጥ ሂደት፣ መስፈርት እና መመዘኛ፣
- ክርክሩ ለሕዝብ የሚቀርብበት መንገድ፣
- በጀት እና የገንዘብ ምንጭ፣
- ክርክሩን የሚከናወንባቸው ቋንቋዎች እና የመሳሰሉት፣
ከላይ ከተጠቀሱት ዋና ዋና ጉዳዮች በተጨማሪ ምክረ-ሃሳብ የሚያስገቡ ተቋማት አስፈላጊ ነው የሚሉትን ዝርዝር ዕቅድ በምክረ-ሃሳባቸው ውስጥ አካተው ማቅረብ ይችላሉ። ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ክርክሩን በማመቻቸት ብሔራዊ ክርክር መከናወንን ከማመቻቸት በተጨማሪ ለክርክር ዝግጅት የሚሆን የፋይናንስ ድጋፍ አያደርግም።
የፍላጎት መግለጫ ወረቀት እስከ የካቲት 26 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ (በአምስት የሥራ ቀናት ውስጥ) በቦርዱ ዋና መሥሪያ ቤት በግንባር ወይም በ media@nebe.org.et ኢ-ሜይል አድራሻ ሊቀርብ እንደሚችል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።
ከምርጫ ቦርድ መግለጫ ሳንወጣ፥ ቦርዱ ለ6ተኛው አጠቃላይ ምርጫ የእጩዎች ምዝገባን እያከናወነ ባለበት በአሁኑ ወቅት የመጀመሪያ ዙር የእጩ ምዝገባ የሚከናውንባቸው ክልሎች እና የከተማ መስተዳድሮች ማለትም፦
- የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር
- የድሬደዋ ከተማ መስተዳድር
- የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል
- የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብሔራዊ ክልል
- የጋምቤላ ብሔራዊ ክልል
- ሃሪሪ ብሔራዊ ክልል ለእጩዎች ምዝገባ የተቀመጠው የጊዜ ገደብ መሠረት የካቲት 08- 21 ድረስ እንደሚከናወን ማሳወቁ ይታወቃል።
ቦርዱ የእጩዎች ምዝገባ ሂደትን በመገምገም የምርጫ ክልል ቢሮዎች ለመከፈት በመዘግየታቸው፥ የትራንስፓርት መጓተት የተወሰኑ የምርጫ ክልሎች ላይ የምዝገባ ቀንን በማራዘሙ እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለያዩ ምክንያቶች እጩዎችን ለመመዝገብ ችግር ስላጋጠመን ይራዘምልን ብለው ጠይቀዋል። በመሆኑም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከላይ የተጠቀሱትን አሳማኝ ምክንያቶች በማየት የመጀመሪያ ዙር ምዝገባ በጀመሩት ከላይ በተጠቀሱት ክልሎች/የከተማ መስተዳድሮች ላይ የሚካሄደው የእጩዎች ምዝገባ ለ4 ቀናት ያህል እስከ የካቲት 25 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ መራዘሙን አስታወቋል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
SemonegnaKeymasterበወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ዙሪያ ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ
አዲስአበባ
ጥቅምት 27 ቀን 2013 ዓ.ምበሀገር አቀፍ ደረጃ የተደረገውን ለውጥ ተከትሎ መንግሥት ባደረገላቸው ጥሪ መሠረት የተለያዩ የፖለካ አካላት ወደ ሀገር መግባታቸው፣ በተሰማሩበት ቦታ ሁሉ ችግሮች እንዳያጋጥማቸውና ደህንነታቸውን በመጠበቅና የፈለጉትን ሀሳብ እንዲገልጹ በቂ ክትትል ሲደረግላቸው መቆየቱን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄነራል እንዳሻው ጣሰው በመግለጫቸው አስታውሰዋል።
በፌደራልና በክልል የሚገኙ የፖለቲካ እስረኞች መንግሥት ባደረገላቸው ምኅረትና ይቅርታ እንዲፈቱ መደረጋቸውን እንደ ትልቅ ሥራ መወሰድ አለበት ያሉት ኮሚሽነር ጄነራሉ፥ ሚዲያዎችም የተለያየ ሀሳብ ለሕብረተሰቡ ተደራሽ እንዲያደርጉና ከሕብረተሰቡ የሚነሱ ጉዳዮችን ለመንግሥት እንዲያደርሱ ነፃነታቸውን በመጠበቅ በኩል በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን ተናግረዋል።
ከሕዳሴ ግድብ ጀምሮ በመላ ሀገሪቱ ተቀዛቅዞ የነበረ የትላልቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ በተጠናከረ መልኩ እንዲቀጥልና የተጀመረ የልማት ሥራ እንዲቋጭ የተለያዩ ሥራዎች ተሠርተዋል ያሉት ኮሚሽነር ጄነራሉ፥ በፖሊስ፣ በሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ በብሔራዊ መረጃና ደህንነትና በሌሎች የጸጥታ አካላት የተከናወኑ ሰፋፊ የሪፎርም ሥራዎችን በበጎ የሚወሰዱ ተግባራት መሆናቸውን ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ግን በሰላማዊ መንገድ ጥሪ ከተደረገላቸው አካላት መካከል ሰላማዊ መንገዱን በመተው ወደ ትጥቅ ትግል የገቡ አካላት እንዳሉ የገለጹት ኮሚሽነር ጄነራሉ፥ በተለይ የኦኔግ ሸኔ ቡድን በምዕራብ ወለጋና በሌሎች አካባቢዎች እንቅስቃሴ በማድረግ ሕብረተሰቡን በመግደል፣ በማገት፣ ንብረት በማውደምና ሌሎች የተለያዩ ሕገ-ወጥ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን ጠቁመዋል።
በተማሪዎች ጠለፋ ላይም በመሰማራት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ በደቡብ ክልል ጉራ ፈርዳና በቅርቡ ደግሞ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ አካባቢ የኦኔግ ሸኔ አባላትና ህወሓት በተቀናጀ መንገድ የሕዝብ ግዲያ በመፈጸም የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውኑ እንደነበር ለማየት ተችሏል ብለዋል ኮሚሽነር ጄነራሉ።
ኮሚሽነር ጄነራሉ አያይዘውም የህወሓት ጽንፈኛው ኃይል ከእነዚህ ከፍተኛ ጥፋቶች ኋላ ተሰማርቶ ሲሠራ እንደነበረ በተለያዩ ጊዜ ባደረግናቸው ምርመራዎች ለማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል።
የህወሓት ጽንፈኛ ኃይል ከፌደራል መንግሥት ጋር ለመሥራት ያለመፈለግ፣ ሕገ-ወጥ ምርጫ ማከናወን፣ የሠራዊት አባላትን ለውጊያ በሚመጥን መንገድ ማዘጋጀት፣ የፌደራል መንግሥትን ሕገ-ወጥ ነው በማለት ባገኘው ሚዲያ በሙሉ ማሰራጨትና ሌሎች ለጸጥታ ሥራ ስጋት የሆኑ ጉዳዮችን ሲያከናውን መቆየቱንም ኮሚሽነር ጄነራሉ ገልጸዋል።
በአጠቃላይ የህወሓት ጽንፈኛ ቡድንና የኦኔግ ሸኔ ታጣቂው ኃይል በተደራጀ መንገድ ከውጭና ከሀገር ውስጥ የሚደረግላቸውን የፋይናንስ ድጋፍ በመጠቀም ለሁለት ዓመታት የተለያዩ የሀገሪቱን ክፍል ሲያተራምሱ መቆየታቸውን ለማረጋገጥ እንደተቻለም ኮሚሽነር ጄነራል እንዳሻው ተናግረዋል።
በሁሉም አካባቢ የተፈጸሙ የጸጥታ ችግሮች ሲያደራጁና ሲመሩ የነበሩ መሆናቸውን ምርመራዎቻችንና የተለያዩ መረጃዎቻችን አረጋግጧል ያሉት ኮሚሽነር ጄነራሉ፥ የተለያዩ ፍንዳታዎችን በመፈጸም፣ የግድያ ሙከራዎችን ማከናወን፣ ንብረት ማውደም፣ ሕዝብን ከሕዝብ ማጋጨትና በቤተ-እምነቶች መካከል ግጭት እንዲፈጠር ለማድረግ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እንደነበራቸውም ኮሚሽነር ጄነራሉ በመግለጫቸው ጠቁመዋል።
አሁንም በትግራይ ክልል ጦርነት ከፍተው ባሉበት ወቅት በሀገራችን የተለያዩ ክፍሎችና ትላልቅ ከተሞች ላይ ጥቃት ለማድረስ ያሰማሩት ኃይል እንዳለ ተደርሶበታል ያሉት ኮሚሽነር ጄነራሉ፥ ይሄ ኃይል ፖሊስና ሌሎች የጸጥታ አካላት ባደረጉት ስምሪት ግማሹ የተያዘ ሲሆን ግማሹ ደግሞ በቅርብ ቀን ከተደበቀበት በማውጣት በቁጥጥር ስር የማዋል ሥራ በተጠናከረ መልኩ እንደሚከናወን ተነግሯል።
የፌደራል ፖሊስ ባለው ሕገ-መንግሥታዊ ተልዕኮ መሠረት በሀገሪቱ በሁሉም አካባቢ በመሰማራት የሕብረተሰቡን ሰላምና ጸጥታን የሚጠብቅ ኃይል መሆኑን በመግለጽ በትግራይ ክልልም በ22 ትልልቅ ተቋማት ላይ በመሰማራት አገልግሎት ሲሰጥ የነበረ ተቋም ነው ብለዋል።
የፌደራል ፖሊስ አባላት ኤርፖርቶችን፣ ዲፖዎችን፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ጣቢያዎችን፣ ቴሌኮምን፣ ቤተ መንግሥትን፣ ትላልቅ ግድቦችንና ኬላዎችን ጨምሮ ሌሎች የሕዝብና የመንግሥት ተቋማትን በመጠበቅ ተገቢውን አገልግሎት ለሕብረተሰቡ ሲሰጡ መቆየታቸውንና በትግራይ ውስጥ ለሚሰሩ የልማት ሥራዎችን ከሕብረተሰቡ ጎን በመሰለፍ በገንዘባቸው፣ በእውቀታቸውና በጉልበታቸው ከፍተኛ አስተዋፅኦ ሲያደርጉ እንደነበር ተገልጿል።
የፌደራል ፖሊስ ኃይል ሕብረተሰቡን ሲያግዝ በነበረበት ወቅት ህወሓት ከፍተኛ ኃይል በመመደብ ጥቃት እንደሰነዘረባቸውና የንብረት ዝርፊያ መፈጸሙን የተናገሩት ኮሚሽነር ጄነራሉ፥ በአንዳንድ አካባቢ የፌደራል ፖሊስ ሠራዊትና የትግራይ ሕዝብ አንድ ላይ ሆነው ሊወረው የመጣውን ኃይል ተከላክሏል ብለዋል።
መውጫና መግቢያ መንገዶችን ለሠራዊቱ በማሳየት የትግራይ ሕዝብ ሊያጠቃው የመጣውን አካል መከላከል መቻሉና ከሰሜን እዝ ጋር በመሆን ጽንፈኛውን ተዋጊ ኃይል በመመከትና በመምታት የራሱን ድርሻ እየተጫወተ ይገኛል ተብሏል።
ጽንፈኛው የህወሓት ቡድን የፈፀመው ይሄ አስነዋሪ ድርጊት ታሪክ፣ ሕግና ህሊና ይቅርታ የማይሰጠው ጉዳይ ነው ያሉት ኮሽነር ጄነራል እንዳሻው ጣሰው፥ ሠራዊቱንና ሕዝቡን የደፈሩበት ሂደት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋልም ብለዋል።
ለውጊያ ሳይሆን ለጥበቃ ሥራ የተሰማራ የፌደራል ፖሊስ ኃይል በታጠቀና ለውጊያ በተዘጋጀ ኃይል ተከቦ እንደዚህ ዓይነት እርምጃ መውሰድ አጅግ አሳፋሪ መሆን በመግለጽ ሕግ የማስከበር ሂደታችን በድል በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ የፌደራልና የክልል ፖሊስ እንዲሁም ሕዝባዊ አደረጃጀት ያላቸው የሚኒሻ አባላት በጋራ በመደራጀት አካባቢያቸውን በአግባቡ መጠበቅ እንዳለባቸው ጠቁመዋል፤ ለተለያየ እኩይ ተግባር የተሰማሩ ሃይሎችን በየአካባቢው በቂ ጥናት በማድረግ በቁጥጥር ስር ማዋል እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
በአማራ ክልል ጎንደር ከተማ፣ በአፋር፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላና በሌሎች አካባቢዎች የነበሩ የጥፋት ሙከራዎችን በቁጥጥር ስር በማዋል ሠራዊቱ በአንድ ረድፍ በመሰለፍ ይህንን ችግር ለመከላከል ላሳየው ከፍተኛ ጽናት አድናቆታቸውን በመግለጽ አሁንም ከኢንቨስትመንት ጀምሮ ለትልልቅ የኢንዱስትሪ መንደሮች ተረባርበን አስፈላጊውን ጥበቃ በማድረግ ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮችን መከላከል አለብን ብለዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት በሚሰጠው መመሪያ መሠረት መፈጸም ከሠራዊቱ አባላት የሚጠበቅ ተግባር መሆኑን የገለጹት ኮሚሽነር ጄነራሉ ሕብረተሰቡ በዲጂታል ወያኔ የሚሠራጩ የሐሰት ፕሮፓጋንዳዎችን በጋራ መከላከል እንዳለበትና በየቀኑ ከመንግሥት የሚሰጠውን መግለጫ ብቻ መከታተል እንዳለበት አስገንዝበዋል።
መንግሥት ለሚያቀርበው ጥሪ ሕብረተሰቡ በቂ ዝግጅት በማድረግ እኩይ ተግባር ለመፈጸም የተሰማራ ኃይል በመከታተል መጠቆምና ማጋለጥ እንዳለበትም ኮሚሽነር ጄነራሉ ጥሪ አቅርበዋል።
በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በተሰጡ አድራሻዎች መሠረት በዚህ በሁለት ቀናት ውስጥ ብቻ ከ1,500 በላይ የሚደርሱ ጥቆማዎች መድረሳቸውንና በዚህም ውጤታማ ሥራዎች መከናወናቸውን የተናገሩት ኮሚሽነር ጄነራሉ በሌሎችም መሰል ሥራዎች መሠራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
የተጀመረው ጸረ-ሰላም ኃይልን የማጥራት ሂደት በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ፊታችንን ሙሉ በሙሉ ለሰላም፣ ለልማትና ለዲሞክራሲ ግንባታ በማዞር ጥረት የምናደርግበት ጊዜ እንዲሆንም የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄነራል እንዳሻው ጣሰው ተመኝተዋል።
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን
SemonegnaKeymasterበኢትዮጵያ ስምንት ዩኒቨርሲቲዎች የምርምር ልህቀት ማዕከል ተብለው ተለዩ
ጎንደር (ኢዜአ) – በኢትዮጵያ ስምንት የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የምርምር ልህቀት ማዕከል (Center of Excellence) በመባል መለየታቸውን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በተመረጡ ትምህርት ቤቶች በትምህርት ጥራት ዙሪያ ያካሄደውን የምርምር ግኝቶች ላይ መስከረም 29 ቀን 2013 ዓም ከባለድርሻዎች ጋር ተወያይቷል።
የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከፍተኛ አማካሪ ዶ/ር ወርቁ ነጋሽ በወቅቱ እንደገለጹት፥ በሀገሪቱ የሚገኙ 46 ዩኒቨርሲቲዎች በምርምር፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም በአጠቃላይ ትምህርት በሚል በሦስት ደረጃዎች ተለይተዋል።
ባለፉት ዓመታት በርካታ ችግር ፈቺ የምርምር ውጤቶችን ሲያበረክቱ የቆዩና ወደፊትም አስተዋጽዖ ይኖራቸዋል የተባሉ ስምንት ዩኒቨርሲቲዎች በምርምር ዘርፍ የልህቀት ማዕከል እንዲሆኑ መለየታቸውን ተናግረዋል።
“ጎንደር፣ አዲስ አበባ፣ ባህር ዳር፣ መቀሌ፣ ጅማ፣ ሀዋሳ፣ አርባ ምንጭ እና ሐረማያ ዩኒቨርሲቲዎች የምርምር ልህቀት ማዕከል እንዲሆኑ ተለይተዋል” ብለዋል ዶ/ር ወርቁ።
ለአንድ ሀገር ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ችግር ፈቺ ምርምር ቁልፍ ሚና እንዳለው የገለጹት ዶ/ር ወርቁ፥ “ያደጉ ሀገሮች የእድገት ምስጢርም ከዚህ የመነጨ ነው” ብለዋል። የምርምር (Research) ዩኒቨርሲቲዎቹ በዓለምአቀፍ ደረጃ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር አቻ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ አቅማቸውን ለመገንባት በትኩረት እንደሚሠራ አመላክተዋል።
ሌሎች 15 የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ደግሞ በሳይንስና ቴክኖሎጂ (Science and Technology) ዘርፍ ትምህርትና ስልጠና እንዲሰጡ መለየታቸውን ተናግረዋል። ዩኒቨርሲቲዎቹ በቂ እውቀትና ክህሎት ያዳበረ ዜጋ ማፍራት እንዲችሉ ተከታታይ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው አመላክተዋል።
ቀሪዎቹ 23 ዩኒቨርሲቲዎች ደግሞ አጠቃላይ ትምህርትና ስልጠና እንዲሰጡ የተለዩ መሆኑን ዶ/ር ወርቁ አስታውቀዋል።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር መርሻ ጫኔ ዩኒቨርሲቲው በርካታ ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምር በማካሄድ ለማህበረሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረጉን ተናግረዋል።
ላለፉት ሶስት አመታት ጎንደር ከተማን ጨምሮ በሰሜን፣ በማእከላዊና በምዕራብ ጎንደር ዞኖች በተመረጡ 1,343 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ በትምህርት ጥራት ዙሪያ ጥናትና ምርምር መካሄዱን ገልጸዋል። በምርምር ውጤቶቹ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይትና ምክክር እየተካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል።
“በዩኒቨርሲቲው የሥነ-ትምህርት ኮሌጅ መምህራን የተዘጋጀው የምርምር ውጤት ለፖሊሲ አውጪዎች ጠቃሚ ግብዓት ሆኖ የሚያገለግል ነው” ያሉት ደግሞ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አሥራት አጸደወይን ናቸው።
ባለፈው ዓመት ዩኒቨርሲቲው ከ200 በላይ የምርምር ሥራዎችን ማካሄዱን ዶ/ር አሥራት አስታውሰዋል፤ ዘንድሮም በተለያዩ ዘርፎች ምርምር ለማካሄድ የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት እያካሄደ እንደሚገኝ ፕሬዝዳንቱ ማሳወቃቸውን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ዘግቧል።
ለአንድ ቀን በተካሄደው ውይይት የዩኒቨርሲቲው መምህራንና የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም ከጎንደር ከተማ አስተዳደር የተውጣጡ መምህራንና የትምህርት አመራሮች ተሳትፈዋል።
ምንጭ፦ ኢዜአ
SemonegnaKeymasterኢዜማ በአባላቱ ላይ እየደረሰ ስላለው እስር እና እንግልት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በደብዳቤ አቤቱታውን አቀረበ
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ማክሰኞ፥ መስከረም 19 ቀን 2013 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ በተለያዩ ክልሎች በአባላቱና በደጋፊዎቹ ላይ እየተፈፀሙ ስላሉ እስር እና እንግልቶች ውይይት ካደረገ በኋላ የጉዳዩን አሳሳቢነት በመረዳት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ድብዳቤ እንዲፃፍ ውሳኔ ማስተላለፉን ተከትሎ ደብዳቤው እንደተፃፈና ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንደተላከ የኢዜማ ድርጅት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ዋሲሁን ተስፋዬ ለዜጎች መድረክ ገለፁ።
ኃላፊው፥ ኢዜማ ምሥረታውን ካደረገበት ጊዜ አንስቶ እዚህም፣ እዚያም ግጭቶች ይከሰቱ እንደነበርና አብዛኛዎቹ ቦታዎች ላይም የጸጥታ ችግር እንደነበር አስታውሰዋል። ፓርቲያቸው በእነዚህ ችግሮች ውስጥ በማለፍ አባላቶቹን በማደራጀት መዋቅሮቹን ሲዘረጋ እንደነበር አውስተዋል። “በማደራጀት ሂደት ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች የጸጥታ ችግር ይገጥመን ነበር” ያሉት አቶ ዋሲሁን ተስፋዬ፥ የተለያዩ ኢ-መደበኛ የሆኑ አደረጃጀቶች መዋቅሮቻችንን እንዳንዘረጋ የተለያየ ጫና ያሳድሩብን ነበር ብለዋል።
“የተለያዩ ፈተናዎች ነበሩ፤ በእነዚህ ፈተናዎች ውስጥ ታልፎ ነው እዚህ ደረጃ የተደረሰው። ለዚህም በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ አባሎቻችን ብዙ ዋጋ ከፍለዋል›› ያሉት ድርጅት ጉዳይ ኃላፊው፥ በአባላቶቻቸውና በደጋፊዎቻቸው ላይ የሚደርሰው እንግልት፣ እስር እና ጫና ከመቀነስ ይልቅ እየተባባሰ በመምጣቱ የተነሳ ለሚመለከተው አካል ማሳወቅ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ጉዳዩን እንዲመረምርና ችግሩ በአፋጣኝ መፍትሔ እንዲያገኝ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ደብዳቤ መፃፍ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን አስረድተዋል።
“አባላቶቻችሁ ሲታሰሩ አልያም እንግልት ሲደርስባቸው ብዙም ስትሉ አይደመጥም አሁን ምን ተፈጥሮ ነው ደብዳቤ ለመፃፍ የወሰናችሁት?” በሚል ከዜጎች መድረክ (በኢዜማ ሕዝብ ግንኙነት የሚዘጋጅ ሳምንታዊ ጋዜጣ) ለተነሳላቸው ጥያቄ ኃላፊው ሲመልሱ፥ “የተለያዩ ፈተናዎች ሲገጥሙን ችግሩን ወደ አደባባይ በማውጣት ችግሩ ይፈታል የሚል እምነት የለንም። አሁንም ቢሆን ችግሩን ከመፍታት አንጻር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ቁጭ ብሎ በመነጋገር እንዲፈታ እንፈልጋለን። ከፖለቲካ አተያይ አንጻርም አባሌ ታስሯል እያሉ አባል ለማፍራት አይቻልም። እኛ ሰላማዊ የሆነ ምህዳር ተፈጥሮ ማንኛውም አካል ሳይፈራና ሳይሸማቀቅ በነፃ አባል እንዲሆን ነው የምንሻው። እዚህ ጋር አባሌ እንዲህ ሆኗል፤ እዚህ ጋር አባሌ ታስሯል እያሉ አባል ማፍራት ያሰቸግራል” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
“በብዙ ፈተናዎች ውስጥ አልፈን ነው እዚህ ደረጃ የደረስነው” ያሉት ድርጅት ጉዳይ ኃላፊው፥ ፓርቲያቸው በአሁኑ ሰዓት በመላው ኢትዮጵያ 280 ቢሮዎች እንዳሉትና 435 የምርጫ ወረዳ ላይ አደረጃጀቱን መዘርጋቱን ጠቁመዋል። ፓርቲያቸው ይህንን ሊያሳካ የቻለውም ችግሮች ሲከሰቱ ከመካሰስ ይልቅ በችግሮቹ ውስጥ መውጫን በመፈለግ ላይ በማተኮሩ የተነሳ መሆኑን ተናግረዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በተለያዩ ክልሎች ላይ በሚገኙ አባላትና ደጋፊዎቻቸው ላይ የሚደርሰው እስራትና እንግልት እያየለ በመምጣቱ የተነሳ በደብዳቤ ለሚመለከተው አካል ማሳወቅ አስፈላጊ ሆኖ ስላገኙት ለሚመለከተው አካል አቤቱታቸውን ማስገባታቸውን ኃላፊው አስረድተዋል።
በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ የኢዜማ አባላትና ደጋፊዎች ላይ እየደረሰ ያለው እስር እና እንግልት እየጨመረ መምጣቱን የሚያነሱት የኢዜማ ድርጅት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ዋሲሁን ተስፋዬ፥ በቤንች ማጂ ዞን፣ ቴፒና ጋምቤላ ብቻ ከ30 በላይ አባላቶቻቸው ታስረው እንደሚገኙባቸው ገልፀዋል።
ምንጭ፦ ኢዜማ
SemonegnaKeymasterመንግሥት የሰዎችን በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደህነነትና ነጻነት የመጠበቅ እና ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብት ይጠብቅ!
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ – ኢሰመጉ-
መንግሥት በቤንሻንጉል ክልል የሰዎችን በሕይወት የመኖርና የአካል ደህንነት መብት ይጠብቅ
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 14 ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ በመሆኑ የማይደፈርና የማይገሰስ በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደህንነትና ነጻነት መብት እንዳለው በግልጽ ይደግጋል። ይሁንና፥ በቤኒሻንጉል-ጉሙዝ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት፥ መተከል ዞን፥ ጉባ፣ ዲባጢ፣ ቡለን እና ወንበራ ወረዳዎች ውስጥ ከባለፈው ጳጉሜ ወር ጀምሮ ማንነቸታው ባልታወቁ አካላት ሲደርስ የነበረው ጥቃት፤ መስከረም 14 ቀን 2013 ዓ.ም በዳንጉር ወረዳ፣ በንገዝ ቀበሌ ዳግም ተከስቶ የበርካታ ንጹኃን ሰዎች ሕይወት መጥፋቱን፣ እንዲሁም የአካል ጉዳት መድረሱን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) ከቦታው ካሉ እማኞች ለመረዳት ችሏል። ጥቃቱ እየደረሰባቸው ያሉ ወረዳዎች በኢ.ፌ.ዲ.ሪ መከላከያ ሠራዊት ኮማንድ ፖስት ስር ተይዘው የጸጥታ ማስከበር እርምጃዎች እየተሠሩ ያሉ ቢሆንም፤ አሁንም ግን ተጨባጭ ስጋቶች እንዳሉ ኢሰመጉ ለማወቅ ችሏል።
በመሆኑም፥ ኢሰመጉ መስከረም 9 ቀን 2013 ዓ.ም ባወጣው አስቸኳይ ጋዜጣዊ መግለጫ ይህ መሰሉ ጥቃት ዳግም እንዳይከሰት መንግሥት አስፈላጊና ሕጋዊ የሆኑ የአጭር እና የረዥም ጊዜ እርምጃዎችን በአስቸኳይ እንዲወስድ ማሳሰቡ አይዘነጋም። ስለሆነም፥ በእነዚህ አካባቢዎች ላይ በተደጋጋሚ በንጹኃን ሰዎች ላይ የሚደርሰውን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች መንግሥት በከፍተኛ ትኩረት በመመልከት የሰዎችን በሕይወት እና በሰላም የመኖር፣ የአካል ደህነነትና ነጻነት የመጠበቅ ሰብዓዊ መብት በምልዓት እንዲያረጋግጥ ኢሰመጉ ዳግም ጥሪውን ያቀርባል። የችግሩ ስፋት ተባብሶ ከዚህም የባሱ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ከመድረሱ በፊት፥ የፌደራል እና የክልሉ መንግሥት፣ የአዋሳኝ ክልሎች መንግሥታት፣ የሲቪክ ማኅበራት፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሀይማኖት አባቶች በአካባቢው ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በትኩረት እንዲሠሩ ኢሰመጉ ያሳስባል።
በተጨማሪም፥ መንግሥት በእስካሁኑ ሕገ-ወጥ ድርጊት የተሳተፉ አጥፊዎችን ለሕግ እንዲያቀርብ፣ ለተጎጂዎች ተገቢውን ካሳ እንዲሰጥ እና የአካባቢውን ሰላም በማስጠበቅ የደረሰውን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት መጣራት የሚቻልበት ሁኔታ እንዲያመቻች ኢሰመጉ በጥብቅ ያሳስባል።
-
መንግሥት የዜጎችን ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ ነጻነት ይጠብቅ
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግሥት አንቀፅ 32 (1) ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በመረጠው የሀገሪቱ አካባቢ የመዘዋወር መብት እንዳለው በግልጽ ያስቀመጠ ቢሆንም፤ ዜጎች ለሥራ፣ ለትምህርት፣ ለንግድና ለተለያዩ ጉዳዮች ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብታቸው ግልጽ ባልሆነ ሁኔታ ተገድቧል። ከመስከረም 11 እስከ መስከረም 14 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ ባሉት ቀናት መነሻቸውን ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች አድርገው ወደ አዲስ አበባ ከተማ ሲጓዙ የነበሩ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብሶች ሰበታ፣ ሱሉልታ፣ ጫንጮ እና ገብረ ጉራቻ ከተሞች ላይ ሲደርሱ በኦሮሚያ ክልል ፖሊስ እና ጸጥታ ኃይሎች ታግደው ወደ አዲስ አበባ እንዳይገቡ መደረጋቸውን ኢሰመጉ በየአካባቢዎቹ ከሚገኙ ከመረጃ ምንጮቹ ለመረዳት ችሏል። በእነዚህ ቀናት በነበረው እንቅስቃሴ ወደ አዲስ አበባ ሲጓዙ ከነበሩ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብሶች መካከል አብዛኛዎቹ በአቅራቢያ ወዳሉ ከተሞች ተመልሰው ለማደር በመገደዳቸው፤ ዜጎች ለከፍተኛ እንግልትና ወጪዎች መዳረጋቸውን ኢሰመጉ ለማረጋገጥ ችሏል።
ይህን መሰሉ ድርጊት፥ ከአሁን ቀደምም ተከስቶ ጥቅምት 01 ቀን 2012 ዓ.ም መነሻቸውን ከተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች ያደረጉ ከ80 በላይ የሆኑ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡሶች ‹‹ወደ አዲስ አበባ መግባት አትችሉም›› በማለት ወደ ደጀንና ባህር ዳር ከተሞች እንዲመለሱ መደረጋቸው ይታወሳል። ይህን አስመለክቶም፥ ኢሰመጉ በወቅቱ ጥቅምት 07 ቀን 2012 ዓ.ም ዜጎች ለከፍተኛ እንግልት እንየተዳረጉና ከቦታ ቦታ በነጻነት የመንቀሳቀስ መብታቸው አላግባብ እየተጣሰ መሆኑን የሚገልጽ አስቸኳይ ጋዜጣዊ መግለጫ አውጥቶ ነበር። ስለሆነም፤ ከዚህ በኋላ ተመሳሳይ ዓይነት የመብት ጥሰቶች እንዳይከሰቱ፤ ተጨባጭ የጸጥታ እና ደህንነት ጉዳዮች በሚኖሩ ጊዜ አስቀድሞ ለማኅበረሰቡ በግልጽ በማሳወቅ አስፈላጊና ሕጋዊ የሆኑ እርምጃዎችን ከሕብረተሰቡ ጋር በትብብር በመሥራት ሊፈቱ እንደሚገባ ኢሰመጉ ያምናል።
ከዚህም በተጨማሪ፥ በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች በልዩ ልዩ ምክንያቶች የዜጎችን ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብት አላግባብ የሚገድቡ የመንገድ መዝጋት እንቅስቃሴዎችን እና እርምጃዎችን በየደረጃው ያሉ የመንግሥት አካላት በትኩረት ተመልክተው ሕጋዊ እርምጃዎችን እንዲወስዱ ኢሰመጉ ይጠይቃል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ – ኢሰመጉ
መስከረም 18 ቀን 2013 ዓ.ምየኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) በአፍሪካ የሕዝቦችና የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የታዛቢነት ቦታ አለው፤ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ፌዴሬሽን (FIDH) አባል፣ የዓለም አቀፍ ጸረ-ሥቃይ ድርጅት (OMCT) አባል፣ የምሥራቅና የአፍሪካ ቀንድ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ጥበቃ ኅብረት (Defend Defenders) መሥራች አባል ነው።
SemonegnaKeymasterትምህርት እንደሚጀመር ከሁለቱ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች የተሰጡ ማብራሪያዎች
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ትምህርት ሚኒስቴር በሦስት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ትምህርት እንደሚጀመር ሲያሳውቅ፤ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ደግሞ ዩኒቨርሲቲዎች እና የቴክኒክና ሙያ ተቋማት የተቋረጠውን ትምህርት የሚያስቀጥሉበት አቅጣጫን አስቀምጧል።
ከሁለቱም የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች መቼ እና እንዴት ትምህርት እንደሚጀመር የተሰጡት መረጃዎች የሚከተሉት ናቸው።
ትምህርት ሚኒስቴር
የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎችን በሦስት ሳምንታት ውስጥ ያሟሉ ትምህርት ቤቶች ትምህርት እንዲጀምሩ ተወስኗል።
የዓለም የጤና ድርጅትና የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጤና ሚኒስቴር ወረርሽኙን ለመከላከል ባስቀመጡት ቅድመ ሁኔታ መሠረት ትምህርት ቤቶች ከመከፈታቸው በፊት በመድኃኒት ማጽዳት፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብልና የእጅ ማጽጃ ማሟላት እንዲሁም አካላዊ ርቀትን ማስተግበር ይጠበቅባቸዋል፡፡
ለሌላ አገልግሎት (ለምሳሌ፥ ለለይቶ ማቆያነት) ውለው የነበሩ ትምህርት ቤቶችም አስፈላጊውን የማስተካከያ ሥራ ሊሠራላቸው እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡
እንደየ ትምህርት ቤቶቹ ነባራዊ ሁኔታ ትምህርት በፈረቃ እና አንድ ቀን በመዝለል ተራ ሊያስተምሩም ይችላሉ፡፡
ትምህርት ሚኒስቴር ባስቀመጠው መስፈርት መሠረት በአንድ ክፍል ውስጥ ከ20 እስከ 25 ተማሪ ማስተማር የሚችሉ መሆንም ይጠበቅባቸዋል ተብሏል፡፡
የተቀመጠው መስፈርት እንዳለ ሆኖ፡-
- በገጠር ወረዳና ቀበሌ ከተሞች የሚገኙ ትምህርት ቤቶች በመጀመሪያው ዙር ጥቅምት 9 ቀን 2013 ዓ.ም፤
- በሁሉም የዞንና የክልል ከተሞች የሚገኙ ትምህርት ቤቶች በ2ኛ ዙር ጥቅምት 16 ቀን 2013 ዓ.ም፤
- በአዲስ አበባና አዲስ አበባ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ደግሞ በሦስተኛ ዙር ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም
ትምህርት እንዲጀምሩ የውሳኔ ምክረ ሀሳብ መቅረቡ ይታዋሳል፡፡
በዚህ መሠረት የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል በሦስት ሳምንታት ውስጥ አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታ ያሟሉ ትምህርት ቤቶች በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ትምህርት መጀመር ይችላሉ ተብሏል፡፡
የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር
መስከረም 14 ቀን 2013 ዓ.ም የኮቪድ-19 ወረርሽኝን እየተከላከልን የዩኒቨርሲቲዎችን እና የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠናን ከተቋረጠበት ለማስቀጠል በመሪዎች ደረጃ በተካሄደው ስብሰባ አቅጣጫ ተቀምጧል።
በዚህም መሠረት፥ በዓለም የጤና ድርጅት መስፈርትና በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጤና ሚኒስቴር የየኮቪድ-19 መከላከያ መመሪያ መነሻ፣ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የትምህርትና ሥልጠና ዘርፍ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት የማስተማርና የማሰልጠን ተግባራት ዝርዝር መመሪያ እንዲያዘጋጅና ተገቢውን ውይይት ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በማድረግና ግንዛቤ በማሳደግ፣ የተቋማትን ዝግጁነት በማረጋገጥ፣ አግባብነት ያለውን የትምህርትና ሥልጠና መርሀግብር በማዘጋጀት ተማሪና ሰልጣኝ መቀበል የሚችሉ መሆኑን፤ ለዚህም ተቋማት ቀሪ የመስከረም ወር ቀናትንና የጥቅምት ወር የመጀመሪያ ሳምንትን የዝግጅት ምዕራፍ ሥራዎችን ለማከናወን እንዲጠቀሙ ስምምነት ላይ ተደርሷል።
ስለሆነም፥ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እስከ ጥቅምት ወር የመጀመሪያ ሳምንት መጨረሻ የተቋማትን የዝግጅት ምዕራፍ አፈፃፀም በአካል እየተገኘ ገምግሞ በቂ የኮቪድ-19 መከላከያ ዝግጅት ላደረጉት የመንግሥትና የግል ዪኒቨርሲቲዎች እንዲሁም የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ተማሪና ሰልጣኝ እንዲቀበሉ የሚፈቅድ ይሆናል። በቂ ዝግጅት ያላደረጉ ተቋማት፣ ዝግጅታቸውን እስከሚያጠናቅቁ ድረስ ክትትል ይደረጋል። ያለ በቂ ዝግጅትና ያለሚኒስቴሩ የመስክ ምልከታና ፈቃድ ተማሪዎችን ወይም ሰልጣኞችን ተቀብሎ መገኘት አግባብነት አይኖረውም።
ስለሆነም፥ የ2012 ዓ.ም ተመራቂ ተማሪዎችና የስልጠና አጠናቃቂዎች እንዲሁም በሌሎች የትምህርትና ሥልጠና እርከን የሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎች በቀጣይ በሚዲያ በሚታወጀው የተማሪና ሰልጣኝ ቅበላ መርሀግብር መሠረት በየተቋሞቻቸው ጥሪ የሚደርግላቸው መሆኑን፤ እስከዚያው ድረስ አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረጉ እንዲቆዩ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ ገልጸዋል። አያይዘውም ትምህርት/ስልጠና በሚጀመርበት ጊዜ የተጣበበ የትምህርትና ስልጠና ጊዜ የሚኖር በመሆኑ፥ ተማሪዎች/ሰልጣኞች ቀጣይ ጊዜያቸውን ለንባብና ለተያያዥ ዝግጅቶች እንዲጠቀሙበት አሳስበዋል።
ወቅቱ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በመሆኑ፥ ሁሉን አቀፍ ጥንቃቄ እየተደረገ የትምህርትና ስልጠና ተግባራትን በጋራ ሆነን እንወጣዋለን በማለት ዶ/ር ሳሙኤል መግለጫቸውን ቋጭተዋል።
SemonegnaKeymasterየተባበረችና የተከበረች ኢትዮጵያን ለመገንባት ወደፊት!
ከባልደራስ – መኢአድ ቅንጅት የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫኢትዮጵያ ሀገራችን ከገባችበት ምስቅልቅል ፓለቲካዊ ችገሮች ለማውጣት በቅንጅት መሥራት አስፈላጊነቱን የተረዱት የመላው ኢትዮጽያ አንድነት ድርጅት /መኢአድ/ እና ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ /ባልደራስ/ የካቲት 29 ቀን 2012 ዓ.ም በመኢአድ ጽሕፈት ቤት ባደረጉት ስብሰባ ሁለቱ ፓርቲዎች በቅንጅት ለመሥራት ያደረጉትን ስምምነት ለሕዝብ ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።
የባልደራስ – መኢአድ ቅንጅት ተመሥርቶ ለሕዝብ ይፋ በተደረገ በቀናት ውስጥ ዓለም-አቀፍ ወረርሽኝ የሆነው የኮሮና ቫይረስ /COVID-19/ ወደ ሀገራችን መግባቱን ተከትሎ የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከ4 ሰው በላይ መሰብሰብ በመከልከሉ 20 አባላት ያሉት የቅንጅቱ ምክር ቤት ስብሰባዎችን ለማድረግ ተቸግሮ ቆይቷል::
የሁለቱ ፓርቲዎቸ ቅንጅት አላማ በሀገራችን ኢትዮጵያ ያለውን ሰፊ የፖለቲካና የልሂቃን ክፍፍል በማጥበብ፥ ብሎም በሚመጣው ምርጫ ላይ ተቀናጅቶ በመወዳደር አብላጫውን የሕዝብ ድምጽ ይዞ መንግሥት በመመሥረት ሀገራችን ኢትዮጵያ አንድነቷና ሕብረቷ ተጠብቆ እንዲኖር ለማድረግ ብሎም ከፍተኛ የሆኑ ሀገራዊና መዋቅራዊ ችግሮችን በመፍታት ኢትዮጵያችን በሰላምና በልማት ጎዳና ላይ ከፍ ብላ እንድትራመድ ለማድረግ ነው።
የባልደራስ – መኢአድ የጋራው ምክር ቤት መስከረም 9 ቀን 2013 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ የቅንጅቱን ፕሬዝደንት፣ ምክትል ፕሬዝደንት እና ሥራ አስፈፃሚውን በሙሉ ድምፅ መርጧል።
በሀገራችን ኢትዮጵያ ለሦስት አስርት ዓመታት በተደረገው መራራ ትግል ውስጥ አቶ እስክንድር ነጋ አድልዎንና ኢፍትሃዊነትን በብዕራቸው በመታገል የሚታወቁት ናቸው። ነገር ግን ዛሬም እንደገና ለእስር የተዳረጉ ሲሆን ይህ ውንጀላና እስር በፖለቲካ አመለካከታቸው ብቻ እንደሆነ የሚያምነው የባልደራስ – መኢአድ ከፍተኛው ምክር ቤት ጥልቅ ውይይት ካካሄደ በኋላ ክቡር አቶ እስክንድር ነጋ በእስር ቤት ሆነውም ቢሆን የባልደራስ – መኢአድ ፕሬዚዳንት እንዲሆኑ በሙሉ ድምጽ ወስኗል። እኚህን የሕዝብ ልጅና መሪ መንግሥት በፍጥነት ከእስር እንዲለቅም ምክር ቤቱ በጽኑ አሳስቧል።
በሌላ በኩል ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ ሰፊ ተሳትፎ የነበራቸውና በተደጋጋሚ ለእስር የተዳርጉትን የነፃነት ታጋዩን አቶ ማሙሸት አማረን በምክትል ፕሬዚዳንትነት የመረጠ ሲሆን፥ አቶ ማሙሸት አማረ ለሕግ የበላይነት ለዴሞከራሲ ሥርዓት ግንባታ የከፈሉትን ወደር የሌለው መስዋዕትነትና ቁርጠኝነት የቅንጅቱ ምክር ቤት ያደነቀ ሲሆን፥ በቀጣይነት ትግሉን በመምራት ቅንጅቱ በአሸናፊነት እንዲወጣ ያላሰለሰ ጥረት እንደሚያደርጉ ምክር ቤቱ እምነቱን ገልጿል።
ምክር ቤቱ ለሌሎች ፓርቲዎችም ጥሪ ያቀረበ ሲሆን፥ ከባልደራስ – መኢአድ ጋር አብሮ ለመሥራት የጠየቁትን ፓርቲዎች በቅርቡ አብሮ ለመሥራት የሚያስችሉ ሥራዎችን እንደሚጀምር የገለጸ ሲሆን፥ ሌሎች ከቅንጅቱ ጋር ለመሥራት ፍላጎት ያላቸውን ፓርቲዎች የሀገራችንን ተጨባጭ ሁኔታ ከግምት በማስገባት ቅንጅቱን እንድትቀላቅሉ ሲል ጥሪውን አቅርቡዋል። መላው የኢትዮጵያ ሕዝብም ከቅንጅቱ ጎን በመሆን ያልተቆጠበ ድጋፉን እንዲሰጥ በታላቅ ትህትና ጥሪውን አቅርቧል።
ምክር ቤቱ በመጨረሻም በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የመከረ ሲሆን፥ በቅርቡ በቤኒሻንጉል-ጉሙዝ ክልል በንጹሃን አርሶ አደር ወገኖቻችን ላይ ማንነትን መሠረት ባደረገው ጭፍጨፋ ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖቻችን የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን እየገለጸ፥ የቅርብ ቤተሰቦቻቸውን ላጡ እና ለመላው ሕዝባችን አምላክ መጽናናትን እንዲሰጥልን እንመኛለን ሲል ተጎጅዎችን ያጽናናል። ምክር ቤቱ ይህንን ማንነትን መሠረት ያደረገ ጭፍጨፋ እያወገዝ፥ መንግሥት ሙሉ ኃላፊንቱን ይወስዳል ሲል አሳስቧል። በወልጋ፣ በሚዛን ቴፒ፣ በሐረር፣ በደራና በሌሎችም አካባቢዎች በተደራጁ ቡድኖች አማካኝነት በዜጎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ ሲሆን፥ በቀጣይም አስከፊ ጉዳት ከመድረሱ በፊት የመከላከል እርምጃዎች እንዲወሰዱ ምክር ቤቱ ያሳስባል።
በሌላ በኩል በጎርፍ መጥለቅለቅ በአዋሽ ተፋሰስ አካባቢዎች በተለይም በመተሃራ፣ አፋር፣ ጋምቤላ እንዲሁም በጣና ዙሪያ ባሉ ጉማራና ርብ ወንዞች መሙላት በተከሰተው የጎርፍ መጥለቅለቅ ህይወታቸውንና ንብረታቸው ላጡ ወገኖቻችንም ከልብ ማዘናችንን እየገለጽን፥ መላው ሕዝባችን ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች በአኩሪ ኢትዮጵያዊ የመደጋገፍ ባህላችን በመደገፍ ኃላፊነታችንን እንድንወጣ ምክር ቤቱ ጥሪውን ያቀርባል።
ዓለም-አቀፍ የሆነውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ /COVID-19/ ወደ ሀገራች መግባቱን ተከትሎ የበሽታውን ወረርሽኝ ለመግታት መላው ሕዝባችን ሳይዘናጋ ራሱን ከወረርሽኙ እንዲጠብቅ ምክር ቤቱ ጥሪውን አቅርቧል።
በመጨረሻም የሀገራችንን ኢትዮጵያ መፃዒ ዕጣ-ፈንታ የተሻለ ለማድረግ በምናደርገው ወሳኝ ትግል ውስጥ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር የምትኖሩ የቅንጅቱ ደጋፊዎች የሚጠበቅባችሁን ትግል እንድታደርጉልን ጥሪያችንን እናቀርባለን።
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
መስከረም 11 ቀን 2013 ዓ.ም
የባልደራስ – መኢአድ ቅንጅትSemonegnaKeymasterቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ 70 አዳዲስ የድኅረ-ምረቃ ትምህርት ክፍሎችን ሊከፍት ነው
ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ በአዲሱ የትምህርት ዘመን በሁለተኛ እና ሦስተኛ ድግሪ 70 አዳዲስ ትምህርት ዓይነቶችን ለመክፈት መዘጋጀቱን አስታወቀ። ይህም ዩኒቨርሲቲው በሁለተኛ እና ሦስተኛ ዲግሪ የሚሰጣቸውን የትምህርት ዓይነቶች 101 እንደሚያደርሰው ተጠቁሟል።
የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ታምሩ አኖሌ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እንዳሉት በ2013 የትምህርት ዘመን በዩኒቨርሲቲው አዲስ ከሚከፈቱት 19 የሦስተኛ ዲግሪ መርሀግብሮች ውስጥ የገዳ እና የአስተዳደር ጥናት አንዱ ነው።
ቀሪዎቹ የተለያዩ የሁለተኛ ዲግሪ መርሀግብሮች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ይህም ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ በሦስተኛ ዲግሪ ይሰጥ የነበረውን አንድ መርሀግብር ወደ 20 ከፍ ሲያደርገው የሁለተኛ ዲግሪውን ደግሞ ከ30 ወደ 81 የትምህርት ክፍሎች እንደሚያሳድገው ዶ/ር ታምሩ አመላክተዋል። የትምህርት ክፍሎችን ፍላጎት ከመለየት አንስቶ የየሥርዓተ ትምህርት (curriculum) ቀረጻና ትችት እንዲሁም የሰው ኃይልና ግብዓት የማሟላት ሥራዎች በጥንቃቄ መከናወናቸውንም በማከል አስረድተዋል።
የመማር ማስተማር ሂደቱን ውጤታማ ለማድረግ የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ከሀገር ውስጥና ከውጭ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ስምምነት ሰነድ መፈራረሙንም ዶ/ር ታምሩ ገልጸዋል። የመምህራን እጥረት እንዳይከሰት ረዳት ፕሮፈሰርና ከዚያ በላይ የትምህርት ደረጃ ያላቸው 73 የውጭና 43 የሀገር ውስጥ መምህራን ቅጥር መፈጸሙንም አስታውቀዋል።
ለመማር ማስተማር ሂደት አጋዥ የሆኑ በተለይ ለኢንጅነሪግና ለተፈጥሮ ሳይንስ ቤተ-ሙከራና ቤተ-መጽሐፍት ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ በማድረግ መደራጀቱን ገልጸዋል። ይህም ጥራቱን የጠበቀ ትምህርት ለማድረስ እገዛ ከማድረግ ባለፈ ከዚህ ቀደም ዩኒቨርሲቲው ለተለያዩ የተግባር ትምህርቶች ወደ ሌሎች አካባቢዎች ተማሪዎችን በመውሰድ የሚያወጣውን ውጭ እንደሚያስቀር አስረድተዋል።
ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የልህቀት ማዕከል (Center of Excellence) አቋቁሞ ከኢትዮጵያ ምርጥ አምስት እንዲሁም ከአፍሪካ ምርጥ 10 ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ አንዱ ለመሆን እየሠራ እንደሚገኝ የተናገሩት ደግሞ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ጫላ ዋታ ናቸው።
በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ የገዳ ሥርዓት እንዲካተት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ግንባር ቀደሚ ሚናውን ከመወጣት ባለፈ በዩኒቨርሲቲው ከኮመን ኮርስ (common course) እስከ ሦስተኛ ዲግሪ ድረስ የገዳ ሥርዓት ትምህርት እየተሰጠ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
“ዩኒቨርሲቲው በስሩ ባሉት ስምንት ኮሌጆችና በአንድ ኢንስትቲዩት ከ17 ሺህ በላይ ተማሪዎችን እያስተማረ ይገኛል” ብለዋል ዶ/ር ጫላ።
ምንም እንኳን በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭት ምክንያት መደበኛ የመማር ማስተማር ሂደቱ ለጊዜው ቢቆምም በቀጣይ ዓመታት የተማሪዎችን ቁጥር በእጥፍ ለማሳደግ እየተሠራ እንደሚገኝ ከፕሬዝዳንቱ ገለፃ ለማወቅ ተችሏል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን
SemonegnaKeymasterሸገር ፓርክ በትልቅ ሥነ-ሥርዓት ተመርቋል
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የአዲስ አበባን ከተማ የቀይራል ተብሎ የሚጠበቀው ሸገር ፓርክ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት በአዲስ ዓመት ዋዜማ ጳጉሜን 5 ቀን 2012 ዓ.ም. ባለስልጣናት እና ጥሪ የተደረገላቸው የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር እንግዶች በተገኙበት ተካሂዷል።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች፣ ዲፕሎማቶች እና የተለያዩ የሃይማኖት አባቶችና ሌሎችም በተገኙበት ተካሂዷል።
ሸገር ፓርክ የኢትዮጵያን ሕብረ ብሔራዊነት በሚያሳይ መልኩ የተገነባ ሲሆን፥ በውስጡ የተፈጥሮ እጽዋትንም ያካተተ ነው። ፓርኩ የኢትዮጵያን ቀደምት ታሪክ በማሳየት የወደፊት ብሩህ ተስፋን የሚያሳይ የወዳጅነት ፓርክ እንደሆነ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ዘግቧል።
ግንባታው ከአንድ ዓመት በፊት የተጀመረው ሸገር ፓርክ በቻይና ግዙፉ የግንባታ ሥራ ተቋራጭ ኩባንያ “China Communications Construction Company (CCCC)” የተገነባ ነው።
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በፓርኩ ግንባታ አስተዋጽኦ ላደረጉ የቻይና የተለያዩ ኩባንያዎች ትልቁን የወዳጅነት ሽልማት አበርክተዋል። በግንባታው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ ኢትዮጵያዊያንም እውቅናና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በሸገር ፓርክ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ ካደረጉት ንግግር የተወሰዱ ነጥቦች፡-
- አዲስ አበባ ይህን ፓርክ ማግኘቷ ስሟንና ደረጃዋን ከፍ ያደርገዋል፤
- ይህ እና ሌሎች ፓርኮች የከተማይቱንና የሀገራችንን ገፅታ ያስውቡታል፤
- ፓርኩ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል፤
- ፓርኩ ተባብሮ መሥራት የሚያስገኘውን ውጤት ማሳያ ነው፤
- ሸገር ፓርክ ከመሃል ሀገር ሳንወጣ ሩቅ ቦታ የተጓዝን የሚያስመስለን ፓርክ ነው፤
- ከተለምዶው የተለየ ነገር ማየት አድማሳችንን ያሰፋዋል፤
- [በግሌ] ይህ ፓርክ በዚህ ፍጥነት ለምረቃ ይበቃል ብዬ አላሰብኩም ነበር፤
- በፓርኩ በሚገኘው የአበባ ማፍያ ስፍራ ከዓይናችን ጠፍተው የቆዩ አበቦችን ሳይቀር ማስተዋል ችያለሁ፤
- ውበትን መሻት ካለንበት ሀኔታ ጋር አይፃረርም፤
- አገራችንን የማስዋብ ጥረታችንን ከሌሎች የልማት ጥረቶቻችን ጋር ጎን ለጎን ካስኬድነው በአጭር ጊዜ የአገራችንን ገፅታ መቀየር እንችላለን፤
- በፕሮጀክቱ የተሳተፉ ሁሉም አካላት የላቀ ምስጋና ይገባቸዋል።
SemonegnaKeymasterሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ በተለያየ የትምህርት ዘርፎች ያስተማራቸውን 659 ተማሪዎችን አስመረቀ
ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች በቅድመ- እና ድኅረ- ምረቃ መርሀግብሮች ያሰለጠናቸውን 659 ተማሪዎችን ጳጉሜን 3 ቀን 2012 ዓ.ም አስመረቀ። ዩኒቨርሲቲው ለ12ኛ ዙር ለምረቃ ካበቃቸው ተማሪዎች መካከል 515 ወንዶች ሲሆኑ 144 ደግሞ ሴቶች ናቸው።
ዩኒቨርሲቲው በእጽዋት ሳይንስ፣ በእንስሳት ሳይንስ፣ በተፈጥሮ ሀብት አጠባበቅ፣ በኢኮኖሚክስ፣ በሥራ አመራር (Management)፣ እንዲሁም በጂኦግራፊና አካባቢ-ነክ ጥናቶች (Environmental Studies) በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ አስተምሮ አስመርቋል።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አህመድ ሙስጠፋ እንደገለጹት፥ ዩኒቨርሲቲው ከተቋቋመበት ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ የመማር ማስተማር፣ የምርምር እና የማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራዎችን ተግባራዊ ሲያደርግ ቆይቷል። እንደ ዶ/ር አህመድ ገለጻ፥ ዩኒቨርሲቲው ከዚህ ቀደም ከ15 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በማስመረቅ ለውጤት አብቅቷል።
እንደ ተጠባባቂ ፕሬዝደንቱ ገለጻ፥ ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ በተያዘው ዓመት በ46 የመጀመሪያ ዲግሪና በ23 የሁለተኛኛ ዲግሪ ፕሮግራሞች ከ17ሺ በላይ ተማሪዎችን በማስተማር ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
በጥናትና ምርምር ሥራዎች በሀገር አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ጭብጦች 18 የምርምር ንድፈ ሀሳቦች የቀረቡ ሲሆን፥ ከእነዚህ ውስጥ 15ቱ ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል ብለዋል – ዶ/ር አህመድ። የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከልም ከ3 ሺህ ሊትር በላይ የንጽህና መጠበቂያ ፈሳሽ (ሳኒታይዘር) በማምረት አገልግሎት ላይ እንዲውል ተደርጓልሲሉ አስረድተዋል።
የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ እና የዩኒቨርሲቲው ምክትል የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ፍቅሬ አማን በክብር እንግድነት ተገኝተው ባስተላለት መልዕክት፥ እንዳሉት የዘንድሮው የምረቃ በዓል ለዓለማችን፣ ብሎም ለሀገራችን ህዝቦች የኮርና ቫይረስ ወረርሽኝ ፈታኝ በሆነበት በዚህ ወቅት ተመራቂዎች የጥናትና ምርምር ሥራዎችን በማጠናቀቅ ለውጤት በመብቃታቸው የተሰማቸውን ልባዊ ደስታ ገልጸዋል።
ሀገራችን በመደመር ፍልስፍና ከነበረችበት ችግር ወጥታ ወደ ብልጽግና ጎዳና እየተጓዘች ባለችበት በዚህ የይቅርታና የምኅረት ወር በሆነችው በጳጉሜ ወር ተማሪዎች ለምረቃ በመብቃታቸው እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል።
ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞውን ሚዛን ተፈሪ ግብርና ኮሌጅ መሠረት አድርጎ በደቡብ ክልል ሚዛን ተፈሪ እና ቴፒ ከተሞች በ1999 ዓ.ም የተቋቋመ ዩኒቨርሲቲ ነው።
SemonegnaKeymasterቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ እና አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በአጠቃላይ ከ3 ሺህ በላይ ተማሪዎችን አስመረቁ
ዲላ/አርባ ምንጭ (ኢዜአ/አ.ም.ዩ) – ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መረሃ ግብሮች ያሰለጠናቸውን 1,043 ተማሪዎችን ነሐሴ 30 ቀን 2012 ዓ.ም. አስመረቀ።
በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጫላ ዋታ እንደገለጹት ከተመራቂዎቹ መካከል 283 በመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን የተከታተሉ ናቸው። ቀሪዎቹ በምስክር ወረቀት የተመረቁ መሆኑን አስረድተዋል።
ተመራቂዎቹ ትምህርታቸውን በበይነ መረብ ቴክኖሎጂ አማካኝነት ሲከታተሉ እንደቆዩ አመልክተው፥ በተለይ የሁለተኛ ዲግሪ ተመራቂዎች የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከመከሰቱ በፊት የክፍል ትምህርታቸውን ማጠናቀቃቸውን አስታውቀዋል።
ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ሥራው በተጓዳኝ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን መከላከልን ጨምሮ በተለያዩ የማኅበረሰብ አገልግሎቶች ውጤታማ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝም ዶ/ር ጫላ ገልጸዋል።
የዩኒቨርሲቲው የቦርድ አባል አቶ ኡዴሳ ክዮላ በበኩላቸው፥ ተመራቂዎቹ በቀጣይ በሚሰማሩበተ የሥራ መስክ ሀገርና ሕዝብ የሚጠብቅባቸውን ኃላፊነት በታማኝነትና ታታሪነት እንዲወጡ አሳስበዋል።
ከተመራቂዎቹ መካከል በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ትምህርቱን የተከታተለው ቅዱስ ይገረሙ በሰጠው አስተያየት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ያሳደረውን ተጽዕኖ ተቋቁሞ ትምህርቱን በማጠናቀቅ ለምረቃ በመብቃቱ መደሰቱን ገልጿል። በሰለጠነበት በ“ሶፍትዌር ዲዛይን” ዘርፍ በመሰማራት እራሱንና ሀገሩን ለመጥቀም እንደሚሠራ ተናግሯል።
በሁለተኛ ዲግሪ ማኔጅመንት የትምህርት ዘርፍ የተመረቀው ዋቆ ጥላሁን በበኩሉ በትምህርት ቆይታው ያገኘውን እውቀት በመጠቀም ውጤታማ ሥራ ለማከናወን እንደሚጥር ገልጿል።
የሦስተኛ ትውልድ ዩኒቨርሲቲ የሆነው ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መረሃ ግብሮች የሚያስተምራቸው ከ17 ሺህ በላይ ተማሪዎች እንዳሉት በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ወቅት ተገልጿል።
ከተማሪዎች ምርቃት ጋር በተያያዘ፥ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ መርሃ ግብር ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ለ33ኛ ጊዜ አስመርቋል።
ዩኒቨርሲቲው በ2012 ዓ.ም በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ መርሃ ግብር በመደበኛ፣ በክረምት፣ በሳምንት መጨረሻ እና በተከታታይና ርቀት ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ 2,326 ተማሪዎች ቅዳሜ ነሐሴ 30/2012 ዓ/ም በተመሳሳይ ዕለት አስመርቋል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንደገለጹት፥ ዩኒቨርሲቲው በስድስት የተለያዩ ካምፓሶች በ76 የመጀመሪያ ዲግሪ፣ በ99 የ2ኛ ዲግሪ እና በ21 የ3ኛ ዲግሪ መርሀግብሮች በአጠቃላይ ከ36 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በመደበኛና መደበኛ ባልሆኑ መርሀግብሮች በማስተማር ላይ ይገኛል። ተቋሙ ባለፉት 33 ዓመታት በልዩ ልዩ የምህንድስና፣ የሕክምናና የጤና፣ የግብርና፣ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ፣ የማኅበራዊ እንዲሁም የተፈጥሮና ቀመር ሳይንስ ዘርፎች 56,958 ምሩቃንን በማፍራት ለሀገሪቱ የሰው ሀብት ልማት ጉልህ አስተዋፅዖ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
አክለውም በ2012 የትምህርት ዘመን በ2ኛው አጋማሽ ላይ በዓለም ላይ በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በሁሉም ደረጃዎች በመማሪያ ክፍል ሆኖ የመማር ማስተማር ሂደት የተቋረጠ ቢሆንም፥ ዩኒቨርሲቲዎች ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመሆን ባደረጉት ከፍተኛ ጥረት ቴክኖሎጂን በመጠቀም የጥናትና ምርምር ሥራቸውን ሲሠሩ የቆዩ ተማሪዎች አስፈላጊውን የምረቃ መስፈርት በማጠናቀቅ ለምረቃ መብቃታቸውን ተናግረዋል። በቀጣይ ዓመታት በተከፈቱ የ2ኛ እና የ3ኛ ዲግሪ መርሀግብሮች ላይ የማጠናከር ሥራ የሚሠራ ሲሆን፥ ዩኒቨርሲቲው በ2013 የትምህርት ዘመን በዩኒቨርሲቲው ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በ3ኛ ዲግሪ የሚያስመርቅ መሆኑን ባቀረቡት ሪፖርት ጠቁመዋል።
የዕለቱ የክብር እንግዳ የጋሞ ዞን አስተዳዳሪና የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ እንደተናገሩት፥ የመማር ግቡ ከግለሰብ ህይወት እስከ ሀገር ድረስ ያሉ የተለያዩ ችግሮችን በመፍታት ምቹና ተስማሚ አኗኗርን ለመፍጠር የለውጥና የዕድገት ጎዳናን መከተል ነው። በመሆኑም የዕለቱ ተመራቂዎች ሀገራችን ኢትዮጵያ ወደ ብልፅግና ማማ እንድትደርስ የበኩላችሁን ድርሻ እንድትወጡ ሲሉ አሳስበዋል። በተጨማሪም ወደ ሥራ ዓለም ሲቀላቀሉ በተሰማሩበት መስክ ሁሉ ሀገራቸውንና ሕዝባቸውን በታማኝነት እንዲያገለግሉ ጠይቀዋል። ሀገሪቱ በበርካታ ፈተናዎች ውስጥ እየተሻገረች የምትገኝ እንደመሆኗ መጠን ፈተናዎቹን በብቃት መክተን ወደ መልካም ዕድል መቀየር ይጠበቅብናል ብለዋል።
በመጨረሻም የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ እና የሬጂስትራርና አልሙናይ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር በለጠ ይልማ የእጩ ምሩቃን መግለጫ በመስጠት አስመርቀዋል።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የጋሞ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የዩኒቨርሲቲው ሥራ አመራር ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ በክብር እንግድነት፣ የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት እንዲሁም የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮችና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።
ምንጮች፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እና አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ (አ.ም.ዩ)
-
AuthorPosts