Search Results for 'ምርጫ'

Home Forums Search Search Results for 'ምርጫ'

Viewing 15 results - 31 through 45 (of 116 total)
  • Author
    Search Results
  • Anonymous
    Inactive

    ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰጠ መግለጫ

    የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለ6ተኛው ሀገራዊ ምርጫ የሚያደርገውን ዝግጅት አስመልክቶ የጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱ፥ እንዲሁም የተለያዩ ተግባራትን ለማከናውን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ እየሠራ እንደሚገኝ ይታወቃል። ከዚህም መካከል የምርጫ ጸጥታን ማረጋገጥ እንዲሁም የምርጫ ክልል እና የዞን ቢሮዎችን ለመክፈት መሥራት ይገኙበታል። በዚህም መሠረት ቦርዱ በተለያዩ ወቅቶች ከክልል መስተዳድር ኃላፊዎች ጋር ውይይቶችን ያከናወነ ሲሆን፥ በእነዚህ ውይይቶች ላይ የምርጫ ኦፕሬሽን መዋቅር እና የክልል መስተዳድሮች የሚጠበቁ ሚናዎችን በዝርዝር አቅርቧል። በውይይቶቹ በተደረሰው ስምምነት መሠረት ቦርዱ የሚከተሉትን ዋና ዋና ትብብሮች ከክልል መንግሥታት የጠየቀ ሲሆን እነሱም በዋናነት፦

    1. የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር – 33 የምርጫ ክልል ቢሮዎች እና 3 የዞን ማስተባበሪያ ቢሮዎች እና የስልጠና ቦታዎች
    2. የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብሔራዊ ክልል መንግሥት – 22 የምርጫ ክልል ቢሮዎች እና 3 የዞን ማስተባበሪያ ቢሮዎች እና የስልጠና ቦታዎች
    3. ድሬደዋ ከተማ መስተዳድር – 47 የምርጫ ክልል ቢሮዎች እና 1 የዞን ማስተባበሪያ ቢሮዎች እና የስልጠና ቦታዎች
    4. ሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት –72 የምርጫ ክልል ቢሮዎች እና 11 የዞን ማስተባበሪያ ቢሮዎች እና የስልጠና ቦታዎች
    5. ጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት – 14 የምርጫ ክልል ቢሮዎች እና 3 የዞን ማስተባበሪያ ቢሮዎች እና የስልጠና ቦታዎች
    6. ደ/ብ/ብ/ህ ክልላዊ መንግሥት – 113 የምርጫ ክልል ቢሮዎች እና 16 የዞን ማስተባበሪያ ቢሮዎች እና የስልጠና ቦታዎች
    7. ሃረሪ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት – 3 የምርጫ ክልል ቢሮዎች እና 1 የዞን ማስተባበሪያ ቢሮዎች እና የስልጠና ቦታዎች
    8. አፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት –32 የምርጫ ክልል ቢሮዎች እና 5 የዞን ማስተባበሪያ ቢሮዎች እና የስልጠና ቦታዎች
    9. አማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት – 138 የምርጫ ክልል ቢሮዎች እና 12 የዞን ማስተባበሪያ ቢሮዎች እና የስልጠና ቦታዎች
    10. ሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት –19 የምርጫ ክልል ቢሮዎች እና 1 ዞን ማስተባበሪያ ቢሮ እና የስልጠና ቦታዎች
    11. ኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት – 179 የምርጫ ክልል ቢሮዎች እና 20 የዞን ማስተባበሪያ ቢሮዎች እና የስልጠና ቦታዎች

    ናቸው። ቦርዱም በጥያቄው ለክልሎች ለዕቅድ እና ለአፈፃፀም ያመቻቸው ዘንድ የምርጫ ክልሎች ዝርዝር እና ቢሯቸው የሚቋቋምባቸው ከተሞች ዝርዝር፣ የዞን ማስተባበሪዎች ዝርዝር እና ቢሯቸው የሚቋቋምባቸው ከተሞች ዝርዝር እንዲሁም ቦርዱ ያወጣውን ረቂቅ የምርጫ ሰሌዳ ቅጂ (copy) አብሮ አቅርቧል።

    ይሁንና ለክልሎች ይህንኑ ለቢሮ መከፈት የሚያስፈልግ ዝግጅት በደብዳቤ በመጠየቅ ለጥር 10 ቀን 2013 ዓ.ም. እንዲያሳውቁ ጥያቄ ያቀረበ ቢሆንም፥ እስከአሁን ድረስ ይህንን ዝግጅት አስመልክቶ ምላሽ ያቀረበ የክልል መስተዳድር የለም። በመሆኑም በደብዳቤ የተገለጹት አስፈላጊ የምርጫ ክልል ቢሮዎችን ለመክፈት የሚያስፈልጉ ትብብሮች ለምርጫው ሂደት አስፈላጊነታቸውን በመገንዘብ ክልሎች ትብብራቸውን እንዲፋጥኑ እንዲሁም በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ 1162/2011 አንቀጽ 161 የተቀመጠውን የመተባበር ግዴታቸውን እንዲወጡ እናሳስባለን።

    የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
    ጥር 10 ቀን 2013 ዓ.ም.

    ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰጠ መግለጫ

    Anonymous
    Inactive

    የህወሓቶች እብሪት ― የህወሓቶች ውድቀት ― እንደሀገር፣ እንደዜጋ የሚያስተምረን ትምህርት
    (አቶ ነአምን ዘለቀ)

    ጆርጅ ሳንታያና (George Santayana) የተባለው ፈላስፋ “ታሪክን የማያስተውሱ ታሪክን በመድገም ይረገማሉ” (‘Those who cannot remember the past are condemned to repeat it.’) እንዳለው፥ አምባገነኖች ከሂትለት እሰከ ሳዳም ሁሴን – ካለፈው መማር ሳይችሉ ያንኑ ሲደጋግሙ ኖሩ። የህወሓቶች እብሪት፣ ትእቢት፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የነበራቸው ንቀት የዚሁ እብሪተኞች ካለፈው ለመማር አለመቻልና የፍትህን ማዕከላዊነት ጥሎ ልከኝነት ረግጦ የመራመድ ቅጥያ ውጤት ነው።

    ለ27 ዓመታት ፍጹም ሊባል በሚችል የበላይነት የመንግሥት፣ የኢኮኖሚ፣ የወታደራዊና የደህንነት ቦታዎች ላይ የአንበሳ ድርሻውን ይዞ የነበረው ህወሓት፥ ከ2018ቱ (እንደ አውሮፓውያን አቆጣጥር) ለውጥ በኋላ በእኩልነት ለመኖር የተሰጠውን ዕድል መቀበል እንዳልቻለ ግልጽ የነበረው የዛሬ ሁለት ወር ተኩል ገደማ በትግራይ በሚገኘው የሰሜን እዝ ሠራዊት አባላት ላይ ያደረሰው መብረቃዊ ጥቃትና ጭካኔያዊ እርምጃ ያን ተከተሎ በተደረገው ሕግን የማስከበር ወታደራዊ ዘመቻ የተጀመረ ሳይሆን ከሁለት ዓመት ተኩል ጀምሮ አንደ ነበር ግልጽ ነው ።

    ያ የነበረውን ሁለንተናዊ የበላይነት ሲያጣ የሞት ሞት ሆነበትና እንዴት ያድርገው!? መላ ቅጡ ጠፋው። ከጅምሩም የያዙትን ስልጣን ለፍትህ፣ በልከኝነት፣ ለሕዝብና ለሀገር ጥቅም ለማስከበር ሳይሆን በሀገርና በሕዝብ ኪሳራ የራሳቸውን፥ አለፍ ሲልም የአንድ ብሔር ሊሂቃን የበላይነት ለማረጋገጥ የተቀሙበት የዘረፋ፣ የዘረኝነትና የመንግሥታዊ ሽብር መሣሪያቸው ነበር። ህወሓቶች ስለራሳቸው ልዩ መሆን፣ ከሌላው ኢትዮጵያዊ የተለየ ጀግንነት፣ ብቃትና ክህሎት ራሳቸው በፈጠሩት የሀሰት ትርክት በእብሪትና በትእቢት የተወጠረው አእምሮአቸው አዲሱን የኢትዮጵያ የለውጥ መንገድ እንዲሁም ከለውጡ ጋር ተከትሎ የመጣውን ነባራዊ እውነታ ሊቀበሉ አልቻሉም።

    እነ ስዩም መስፍን ኢትዮጵያን “ሶርያና የመን እናደርጋታለን” ብለው በአደባባይ አወጁ። እነ ጌታቸው ረዳ “ትግራይ ሀገር መንግሥት መሆን እንዳለባትና እና በቀጣይም ከኢትዮጵያ ጋር ሶማሌላንድ ከሞቃድሾ ጋር እንዳላት ግንኙነት ነው የምንፈልገው” በማለት በድፍረት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ነገሩ። “ተራራን ያንቀጠቀጥን”፣ “የደርግን ሠራዊት የደመሰስን”፣ “ከወርቅ ሕዝብ የተገኘን”፣ “ኢትዮጵያን እንደ አዲስ የሠራን”፣ “የብሔር ብሔረሰቦችን መብት ያረጋገጥን”፣… ብለው ለአስርት ዓመታት የሰበኩት ህወሓቶች የሀሰት ትርክቶቻቸውንም አብጠው አብጠው በአምሮአቸው ውስጥም ተገንብተው፣ ጠጥረውና ደድረው እውነታን ለማየት የማያስችል ግርዶሽ ሆነው ቆዩ። በርካታ የትግራይን ወጣቶችንም በዚሁ ትርክት እወናበዱ። መሬት ላይ ካለው ከነባራዊው እውነታ ጋር ፍጹም በተቃራኑ ቆሙ። እውነታውን ተቀብለው ለመሄድም በትዕቢት፣ በእብሪት፣ በዘረኝነት የተተበተበው ልቦናቸውና ህሊናቸው ፈጽሞ አልፈቅድላቸው አለ።

    በመሆኑም ህወሓቶች ማድባትና መዘጋጀት ጀመሩ። ለሁለት ዓመታት ሲደራጁ፣ ሲዘጋጁ ቆይተው ማዕከላዊ መንግሥቱን ዳግም ለመቆጣጠር፥ ይህ ካልሆነም ኢትዮጵያን አተራምሰውና በታትነው “የትግራይን ሀገር መንግሥት” ለመመሥረት “በመብረቃዊ ጥቃት” በሰሜን እዝ ላይ ክህደትና ጭካኔ የተሞላበት ግፍ ፈጸሙ። በስልጣን ዘመናቸውም ግፍና መከራ ለሕዝብ ሲሰፍሩ ኖሩ። በሰፈሩት ቁና መስፈር አይቀርምና የሚሊዮኖች እምባ፣ የብዙ ሺዎች ደም፣ ዋይታና ሰቆቃ፣ በህወሓቶች ግፍ የተሰደዱ የአስር ሺዎች ኢትዮጵያውያውን መከራ ፈጽሞ ይሆናል ብለው ባልጠበቁትና ባልተዘጋጁበት የበስተርጅና እድሜያቸው፣ በመጦሪያ ዘመናቸው እጅግ የመረረ ዋጋ ጠየቃቸው። በመጨረሻም መራሩን ውድቀትና ውርደት አከናነባቸው። የኢትዮጵያ ሕዝብም ‘አክ እንትፍ!’ እንዳላቸው ሊከሰትላቸው ፈጽሞ ሳይችል ቀርቶ በስተርጅና እድሜያቸው ለውድቀትና ለውርደት፣ ገሚሶቹ ደግሞ በመደምሰስ ፍጻሜያቸው ባጁ።

    የኢትዮጵያ አምላክም በእነዚህ ግፈኞች ላይ መብረቃዊ ጥቃት ያደረሰ ይመስለኛል። ስልጣንና ሀብት ደደብና ደነዝ አድርጎ ለውርደት ከዳረጋቸው ከህወሓቶችና ካለፉ አምባገነኖች ታሪክ ለመማር ያልቻሉ፥ አሁንም በያዙት ስልጣን መከታ በማድረግ በሕዝብ ጫንቃ ለመናጠጥ የሚሞክሩ፣ ፍትህን፣ ሰላምን፣ ለሀገር የሚበጀውን፣ የዜጎችን ህይወት የሚለውጥ ተግባር ላይ ከማተኮርና ከመትጋት ይልቅ ሕዝብን ከሕዝብ የሚከፋፍሉ፣ የብሔር ካርድ ለስልጣን ማጠናከሪያ የሚመዙ፣ የሕዝብ ሰላም የሚያውኩና ሀገሪቱ እንዳትረጋጋ የሚደነፉ፣ በየመድረኩም የሚፎክሩ አፍራሽ በየብሔሩ ስም የተደራጁ ኃይሎችና ቡድኖች በገዢው ፓሪቲ የሚገኙ እንዳንድ መሪ ካድሬዎች ከዚህ ታሪክ ይማሩ ይሆን?

    ከስልጣን ጋር በሚመጣ እብጠትና ማን አለብኝነት ብዙ ርቀት የማያስኬድ መሆኑን ማጤን ትልቅ አስተውሎ ነው። ከፋፋይና ሕዝብን በጭንቀት ውስጥ እንዲኖር ከሚያደርጉ የማኅበራዊ ሚዲያዎችና በየሚዲያው ከሚሰነዘሩ መርዛማና ከፋፋይ አሰተያየቶች ለመሰንዘር ከመሽቀዳደም በጎ በጎውን፣ ለሀገር የሚበጀውን፣ ለሕዝብ ተስፋ የሚሆንውን፣ ለሥራ-አጡ ሥራ የሚፈጥረው፣ ኢትዮጵያን የሚያለማውን፣ ሕዝብ ከሕዝብ የሚያቀራርቡ ተግባራት ላይ ማተኮርና መትጋት በኃላፊነት ላይ ለሚገኙ እነዚህ የገዥው ፓርቲ መሪ ካድሬዎች ቅድሚያ ሊሰጡት ይገባል።

    የሕዝብን ጥቅም ማስቀደም፣ የሕግ የበላይነትና ፍትህን ያማከለ ብሎም ለእያንዳዱ ዜጋ በየትኛውም ክልልና ቦታ ለሚኖር ኢትዮጵያዊ/ት የደህንነት ዋስትናው የሚጠበቅበት፣ ሠርቶ ለፍቶ በሰላም መኖሩ የሚረጋገጥበት፣ የዜጎችን ህይወት የሚቀይሩ እንቅስቃሴዎች ላይ በማተኮር ሕዝብን የሚጠቅም ሥራ ሠርቶ ጊዜው ሲደርስ ስልጣን ማስተላለፍ መሆን ይገባዋል። ስልጣንን ለማቆየት የብሔር ካርድ በየዕለቱ መምዘና ህወሓቶች እንዳደረጉት የሕዝብም አብሮነት የሚሸረሽሩ፣ ብሔር ለብሔር የሚያጋጩ ተግባራት ላይ መጠመድ ዋና ሥራ ሆኖ መቀጠል የለበትም። ከሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት ከሙስጠፋ ኦማርና ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እና ከሌሎችም ሊማሩ ይገባል።

    ሕዝብ በአግባቡና በቅጡ ማገልገል ቅድሚያ መስጠቱ በህወሓቶች ውድቀትና ውርደት ዋዜማ ትልቁ ትምህርት ይህ እንደሆነ መቀበል ብልህነት ነው ። ለሀገርና ለሕዝብም ብቸኛው መንገድ የሕዝብን ሰላም፣ ደህንነት፣ ፍትህ፣ መብቶችና ጥቅሞች እንዲሁም አስከፊውን ድህነት ለማስወገድ አካታችና ዘላቂ ልማትን ማስቀደም መሆን አለባቸው። የህወሓቶች ውድቀት ዋዜማ እንደ ሀገር ምን እንማራለን ለሚለው አንዱ አስተምሮና አስተውሎ ይህ ይመስለኛል።

    አቶ ነአምን ዘለቀ

    የህወሓቶች እብሪት ― የህወሓቶች ውድቀት

    Anonymous
    Inactive

    ቀጣዩን ሀገር-አቀፍ ምርጫ ባሰብን ጊዜ…
    (የብሔር ፖለቲካ እና መጪው የኢትዮጵያ ምርጫ)
    ጌታሁን ሄራሞ (ኢ/ር)

    በሀገራችን በምርጫ ዲሞክራሲ ሂደት ብሔርን መሠረት ያደረጉ ፓርቲዎችን ተከትሎ ከሚከሰቱ ተቃርኖዎች (paradoxes) ውስጥ አንዱም፥ ተወዳዳሪዎቹ መነሻ ላይ ብሔራቸውን ብቻ ወክለው ካሸነፉ በኋላ በድኅረ-ምርጫው 82 ብሔሮች የሚኖሩባትን ሀገርን ለመምራት መብቃታቸው ነው። ጅምር ላይ የአንድ ብሔር ውክልና ብቻ ያለው ተወዳዳሪ በምን አመክንዮ ነው 82 ወይም ከዚያም በላይ ብሔሮች የሚኖሩባትን ሀገር መምራት የሚችለው?

    ናይጄሪያ ውስጥ የብሔር ፓርቲዎች እንደ አሸን በፈሉበት ወቅት ከላይ የጠቀስኩት ግራ አጋቢ ውክልና አወዛጋቢ በመሆኑ በሂደት ሁለት ቅድመ ሁኔታዎች በፖሊሲ አውጪዎቹ ተቀመጡ። የመጀመሪያው “የትኛውም የብሔር ፓርቲ ሀገራዊ ስሜትን (national sense) የሚያንፀባርቁ አንቀፆችን በፕሮግራሙ ውስጥ በግልፅ ማስቀመጥ አለበት” የሚል ነበር። እናም ፕሮግራሙ ውስጥ የራሱን ጎጥ ጥቅምና ጥያቄ ብቻ የጠቀጠቀ የብሔር ፓርቲ ሀገርን መምራት አይችልም፤ በምርጫ ቦርዱም የመመዝገብ ዕድሉ የለውም። ሁለተኛው ቅድመ ሁኔታ ደግሞ… አንዳንድ የብሔር ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች የመጨረሻ ህልማቸው ትልቋን ናይጄሪያን መምራት ከሆነ በምርጫ ወቅት ከራሳቸው ክልል በዘለለ ሌሎች ብሔሮች በሚኖሩበት ክልሎችም ጭምር እንዲወዳደሩ የሚያስገድድ ነበር። በነገራችን ላይ ናይጄሪያ ብሔርን ከፖለቲካ ለማፋታት የተጠቀመችበት ዘዴ “positive banning” ተብሎ ይጠራል። ሂድ አትበለው ግን እንዲሄድ ግን አድርገው ዓይነት… (ብሔርን ከፖለቲካ ማፋታት ማለት የብሔር ብሔረሰቦች መብት ባህልና ታረክን አለማክበር ማለት እንዳልሆነ እዚህ ጋር ይሰመርልኝ፤ ብዙ ሀገሮች ጎጥ፣ ጎሳና ብሔር ወደ ፖለቲካ ሰፈር ድርሽ ሳይሉ የዜጎቻቸውን ባህልንና ራስን በራስ የማስተዳደር መብትን በአማራጭ የፌዴራል ዲዛይን ተግብረዋል።)

    በምርጫ ወቅት ብሔሩን ወክሎ የማታ ማታ ለሀገር መሪነት የሚበቃ መሪ፦

    1. በሥልጣን ወንበሩ ላይ እንደተቀመጠ ሀገራዊ ስሜትን አንፃባርቆ ሁሉንም ብሔሮች በእኩልነት መምራት ሲጀምር ቀደም ሲል ውክልናውን በሰጠው በገዛ ብሔሩ ዘንድ እንደ ከሀዲ ይቆጠራል።
    2. ሌሎች ብሔሮችን በእኩልነት ከመምራት ይልቅ በመንግሥታዊ ተቋማት ምሥረታና በሌሎች ሲቪክ መሥሪያ ቤቶች መዋቅር ውስጥ የብሔሩን ተወላጆች ብቻ እየመረጠ የሚሾም ከሆነ ደግሞ በሌሎች ብሔሮች ዘንድ “ተረኝነት”ን እንደሚተገብር፣ ወገንተኛና ኢ-ዲሞክራሲያዊ መሪ ሆኖ ይከሰሳል።

    ይህ የብሔር ፓርቲ የሚያስከትለው አዙሪት የፖለቲካ ሳይንትስቶችንም የሚያወዛግብ ነው፤ በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ የአንፃራዊ ፖለቲካ (comparative politics) ሳይንትስት የሆነው ፕሮፈሰር አረንድ ሊፓርት (Arend Lijphart) በብሔር ፖለቲካ የምትመራ ሀገር ካለች በመሪነቱ ሂደት ልዩ ልዩ ሀሳቦችን የሚያንፀባርቁ ልሂቃን በ“grand coalition” አጋዥነት ተሳባስበው በአመራሩ መሳተፍ አለባቸው ያለው ከላይ ያነሳሁትን ተቃርኖ ለመቀነስ በማቀድ ነው፤ እንዲሁም የብሔር ፖለቲካን የሚያራምዱ ሀገራት በየትኛውም መስፈርት መተርጎም ያለባቸው ተመጣጣኝ ውክልናን መሠረት ያደረገ የምርጫን ሥርዓት ነው ያለውም ከዚሁ ተነስቶ ነው። በተመጣጣኝ የውክልና ምርጫ መርህ ቢያንስ ሌሎች ተፎካከሪ ፓርቲዎች ወደ ፓርላማ በመግባት ሚዛኑን ሊያስጠብቁ ይችላሉ።

    ከፕሮፈሰር ሊፓርት በተጨማሪ የሕግና የፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፈሰሩ ዶናልድ ሆሮውዝም (Donald Horowitz) (በብሔር ግጭቶች ጥናት ጥርሱን የነቀለ ሳይንትስት ነው) የብሔር ፓርቲ መዘዝ የሚያመጣውን የአመራር ሳንካ ለመቀነስ “centripetal” ዲሞክራሲን መተግበርን በቅድመ ሁኔታነት ያስቀምጣል። ከላይ ናይጄሪያዎች ጥቅም ላይ እንዳዋሉት ያስቀመጥኩት ጽንሰ-ሀሰብ ባለቤትነቱ የፕሮፈሰር ሆሮውዝ ነው… የአንድ ብሔር ተወካይ የሆነው የምርጫ ተወዳዳሪ ሕልሙ ሁሉም ብሔሮች የሚኖሩባትን ሀገር መምራት ከሆነ መወዳደር ያለበት ከራሱ ቀዬ ባለፈ በሌሎችም ክልሎችም ነው… የሚለው መርህ የሆሮውዝ ነው።

    ከላይ ያነሳሁትን የብሔር ፓርቲን መዘዝ እኛ ኢትዮጵያዊያን ለፖለቲካ ሳይንሱ ባይተዋር ብንሆን እንኳ መሬት ላይ ወርዶ ያየነው እውነት ነው። ህወሓት በቀዬዋ ለምርጫ ተወዳድራ አመሻሽ ላይ ለሀገር መሪነት ስትበቃ የሀገሪቷን ተቋማት ያስወረረችው በራሷ ሰዎች ነበር፤ ሌላው ቀርቶ ክልሎችም ይመሩ የነበሩት በሞግዚትነት በራሷ ተወካዮች ነበር። ለዚህም ነበር በሀገሪቱ የፖለቲካ መዋቅር ውስጥ የ“አንድ ብሔር በላይነት” ስለመስተዋሉ ብዙዎች እሪታቸውን ሲያስደምጡን የነበረው!! የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑት ዶ/ር አብይም በብሔር ፖለቲካ ባቡር ተሳፍረው ወደ ሥልጣን ከመጡበት ማግስት ጀምሮ ብዙዎች ስለ “ተረኝነት” ስጋት ተሰምቷቸው ድምፃቸውን ማሰማታቸው የአንድ ብሔር ውክልና ከፈጠረው ድባብ የተነሳ ነው። በብሔር ፖለቲካ ቦይ ፈስሶ ለሥልጣን መብቃት ፈተናው ለተሿሚውም ቢሆን ብዙ ነው።

    በነገራችን ላይ አሁን የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ ሀገራችን እየተመራች ያለችው የብሔር ፖለቲካ ውልዶች በሆኑ የፖለቲካ ሰዎች ነው። ምናልባትም በቀጣዩ ምርጫ አሸናፊዎቹ በቦሌም ይሁን በባሌ እነሱ ሊሆኑ ይችላሉ። ሀገራችን ብሔርን ብቻ መንደርደሪያ ካደረገው የፖለቲካ ሥርዓት በተለየ ሌላ ዓይነት የፌዴራል የአስተዳደር መዋቅር እስከሚያጋጥማት ድረስ ገዥው የብልፅግና ፓርቲ ከሀገራችን የፖለቲካ አውድ በሚስማማ መልኩ የነአረንድ ሊፓርትንና የዶናልድ ሆሮውዝን ጽንሰ-ሀሰቦችን ቢያጤን መልካም ነው። የብሔር ፖለቲካ ያመጣብን መዘዝ ሀገር በቀል በሆኑ እሳቤዎች ብቻ እልባት የሚያገኝ አይደለም። ሐኪሞች በሀገር ውስጥ ለማከም የሚያዳግታቸውን በሽታ ከአቅማችን በላይ ነው በማለት እልባት ያገኝ ዘንድ ወደ ውጭ ሀገር “refer” ያደርጉ የለ? እዚህ ጋር ያስቀመጥኳቸው ምስሎች የሚያመለክቱት የኔዜርላንድና የአሜሪካ ጥምር ዜግነት ያለው ፕሮፈሰር ሊፓርት /Lijphart/ ከአራት ዓመታት በፊት ለካናዳ የምርጫ ኮሚቴ ስለ ተመጣጣኝ ምርጫና ስለ ዲሞክራሲ መርሆች ከራሱ ንድፈ ሐሳቦች ጋር በማገናኘት የቪዲዮ ኮንፍረንስ ላይ ሀሳቡን ሲሰጥ ነው። ካናዳዎቹ ለመፍትሔዎቻቸው “ሀገር-በቀል” መፍትሔ ብቻ ያስፈልጋል በሚል ግትር አቋም ሳይወሰኑ ጠቃሚ እስከሆነላቸው ድረስ በዘርፉ ጥናት ካደረጉ ምሁራን ለመማር ያላቸው ተነሳሽነት የቱን ያህል እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል። እንዲያው ለነገሩ እንጂ እኛስ ብንሆን የብሔር ፖለቲካውን የቀዳነው ከቀድሞዋ ሶቪዬት መሪዎች ከአምባገነኑና ጨፍጫፊው ጆሴፍ ስታሊን (Joseph Stalin)ና ሌኒን (Vladimir Lenin) አይደል? የጨፍጫፊውን የስታሊንን እሳቤ ለመቅዳት ያላፈርን የሌሎች የውጭ ሀገራት ምሁራንን ሳይንሳዊ ምክርን ከመስማት ለምን እንታቀባለን? ከሁሉም በላይ እኛ በስታሊናዊ የብሔር ፖለቲካ አንቀፆች ተጣብቀን ቀርተን በተቃራኒው የእሳቤው ምንጭ የነበሩ እነራሺያ የስታሊንን እሳቤ በሀገር በታኝነት ፈርጀው አሽንቀጥረው ከጣሉ ዓመታት እንዳለፉ ገና መረጃው አልደረሰንም ማለት ነው? የብሔር ፖለቲካ የታሪክ ምዕራፉ እስከሚዘጋ የብልፅግና ፓርቲ ቢያንስ የእነ ሊፓርትና የእነ ዶናልድ ሆሮውዝን ምክሮችን በድኅረ ምርጫውም ቢሆን ከሀገራዊ አውድ ጋር አመሳክሮ ተግባራዊ ለማድረግ ፈቃደኝነቱን ማሳየት ይጠበቅበታል… ከ“grand coalition” እስከ ተመጣጣኝ የውክልና ምርጫ ተግባራዊ እስከማድረግ ጭምር!

    ጌታሁን ሄራሞ (ኢ/ር)

    የብሔር ፖለቲካ እና መጪው የኢትዮጵያ ምርጫ

    Anonymous
    Inactive

    የብሔር ልዩነታችን ላይ መሠረት ባደረገ ፖለቲካዊ የአስተዳደር ሥርዓት የዜጎችን መሠረታዊ ሰብዓዊ መብቶች ማረጋገጥ አይቻልም
    ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ
    ጋዜጣዊ መግለጫ

    በሀገራችን ኢትዮጵያ በንጹሃን ዜጎች ላይ እየደረሰ ያለ አሰቃቂ ግድያ፣ የአካል መጉደል፣ ለዘመናት ከኖሩበት ስፍራ መፈናቀል፣ እንዲሁም ያፈሩትን ሀብትና ጥሪት በአንድ ጀንበር አጥተው ለተረጅነት መዳረግ በየጊዜው የሚያጋጥም የተለመደ አሳዛኝ ክስተት ሆኗል።

    ይህንን በዜጎች እየደረሰ ያለውን አሰቃቂ ግድያ፣ የአካል መጉደል፣ መፈናቀልና  ሀብትና ንብረታቸውን ማጣት እንዲቆም ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማትና ግለሰቦች ደግመው ደጋግመው ቢያወግዙም በተቃራኒው ችግሩ ከጊዜ ወደጊዜ እየተባባሰ ይገኛል።

    እኛ ኢትዮጵያውያን እምነት፤ ባህል፣ ሥነ ልቦና፣ ጋብቻ፣ ሥራ፣ ጉርብትና ሌሎችም መስተጋብሮች ላንለያይ አስተሳስረውን ጠንካራ የአብሮነት ባህል የነበረን ሕዝቦች ነን። ይህ የአብሮነት መስተጋብር በብዙ አጋጣሚዎች ፈተና ላይ የወደቀ ቢሆንም እስከዛሬዋ ቀን ድረስ አብረን እንድንጓዝ አድርጎናል።

    መሠረታዊ የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶች ሳይሸራረፉ በማክበር የሁላችንም መኖሪያ የሆነችውን ሀገር አንድነት በማስጠበቅ፣ በመንግሥት አስተዳደር ሥርዓት ውስጥ ብዝኃነታችንን የሚያስተናግዱ የተለያዩ ፖሊሲዎችንና የሕግ ማእቀፎችን በማዘጋጀት ለጋራ ጥቅም በማዋል፣ እስከዛሬ የነበሩንን ጠንካራ ልምዶች ይበልጥ በማጠናከር ከድክመቶቻችን እና ስህተቶቻችን በመማር ብሎም በማሻሻል በአብሮነት ሁሉም አሸናፊና ተጠቃሚ የሚሆንበት ሥርዓት መዘርጋት ይቻላል ብለን እናምናለን።

    በእኛም ሀገር ይሁን በሌሎች ሀገራት ላይ ለሚከሰቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩም በአሁኑ ጊዜ የቆየ አብሮ የመኖር እሴቶቻችንን በመፈታተን በሀገራችን እየተከሰቱ ለምንመለከታቸው ከፍተኛ የንጹሃን ህይወት መቀጠፍ፣ መፈናቀልና የንብረት ውድመት የመብት ጥሰቶች ዋነኛው መንስዔ የሀሰት ትርክት (false narrative) የወለደው ብሔር ተኮር የጥላቻ ፖለቲካ መሆኑ ጥርጥር የሌለው አሳዛኝ ሐቅ ነው።

    አሁንም መንግሥትም ሆነ ሌሎች የሚመለከታቸው የፖለቲካ ባለድርሻ አካላት በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት፣ ሀገራዊ ፍቅርና ቁርጠኝነት የዓለም አቀፍ ሕግጋትን መሠረት ባደረገ መልኩ፥ ያለንበትን 21ኛውን ክ/ዘመን በሚመጥን፣ በሰከነ ስሜት በቅንነት በመነጋገር፥ መሬት ላይ ያለውን ብዙኃኑን ምስኪን የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚመስል የፖለቲካ አስተዳደር ሥርዓት ለመዘርጋት እስካልወሰኑ ድረስ በሁሉም የሀገራችን ወሰን ውስጥ ያሉ ዜጎቻችንን መሠረታዊ የሰብዓዊ መብቶች በዘላቂነት ማስከበር ከቶውንም አይቻልም።

    ሰብዓዊ መብቶች ባልተከበሩበት፣ የሕግ የበላይነት ባልተረጋገጠበት፣ ሰላም ባልሰፈነበት ሁኔታ የሀገርን እድገትና ለውጥ እውን ለማድረግ ማሰብ እጅግ አዳጋች ነው።

    በአሁኑ ጊዜ እየተስተዋለ ያለው የጥላቻ፣ የመናናቅ፣ ልዩነትን መሠረት ያደረገ የብሔር ፖለቲካ፣ የጨቋኝ ተጨቋኝና የመጤ ሰፋሪ ትርክት ምንአልባትም ከእስካሁኑም ወደከፋ የግጭት አረንቋ ቢከተን ነው እንጂ የዜጎችን ሰው በመሆናቸው ብቻ እና በዜግነታቸው ማግኘት ያለባቸውን መብቶች ማስከበር ፈጽሞ አይቻልም። ችግሩን በፈጠርንበት አስተሳሰብ፣ ችግሩን በፈጠሩት የፓለቲካና የታሪክ ስሁት ትርክቶችን ሳናስተካከል መፍትሔ ማምጣትም ከባድ ነው።

    በሀገራችን በየትኛውም ዘመን እንደሕዝብ ተለይቶ የደላው ወይ ሌላውን የጨቆነ የለም። ይህንንም የተለያዩ የመንግሥት እና የፖለቲካ ድርጅቶች አመራሮች በተደጋጋሚ አስረግጠው የተናገሩት እውነታ ቢሆንም በተቃራኒው በተዛባ የታሪክ አረዳድ ሆን ብለውም ይሁን በስህተት የፖለቲካ አጀንዳ ባደረጉ አካላት ምክንያት የተነሳ ምንም የማያውቁ ንጹሀን ወገኖቻችን ደም እንደጎርፍ እየፈሰሰ ንብረታቸው እየወደመ ይገኛል። ይህም የሀገር ህልውናን አደጋ ላይ በመጣል ወደ ከፍተኛ ግጭት፣ ሞት፣ መፈናቀልና ስደት፣ ብሎም ለውጭ ኃይሎች ወረራና ጥቃት ሊያጋልጠን ይችላል።

    ከአባይ ግድብ ጋር በተገናኘም ሆነ በቀጠናችን ካለ የሽብርተኝነት እንቅስቃሴ ይህ የማይሆንበት ሁኔታ ይኖራል ብለን አንገምትም። ስለሆነም በቅርቡ በእርስ በርስ ግጭት ሕዝባቸውን ለስደትና ሞት ከዳረጉ ሀገራት በመማር ከምን ጊዜውም በላይ ሀገራዊ እና ሕዝባዊ አንድነታችንን ማጠናከር የሚገባን ጊዜ ላይ እንገኛለን።

    መንግሥት ሕግና ሥርዓት እያለ እንኳ በተገቢው መልኩ ማስቀረት ያልቻለውን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት በጦርነትና በስደት መካከል ደግሞ ምን ያህል የከፋ ሊሆን እንደሚችልና ለውርደት እንደሚዳርገን ማስተዋል ያስፈልጋል።

    ይህ ፖለቲካው የወለደው የዜጎች ማንነትን መሠረት ያደረገ ጥቃት አይነቱን እየቀያየረ አንድ ጊዜ ሀይማኖትን ሌላም ጊዜ ብሔርን ወይንም አመለካከትንና አቋምን ሰበብ በማድረግ ይብዛም ይነስም ያልደረሰበትና ያልነካው የሕብረተሰብ ክፍል የለም ማለት ይቻላል። የችግሩ ምንጭም የቅርብ ሳይሆን አስርት አመታትን የቆየና አሁን እየባሰ የመጣ ነው።

    በሀገራችን ይህ ሁሉ ቢሆንም እንደ ሕዝብ የሚገድልና እንደሕዝብ የሚያፈናቅል አላየንም። ለዚህም ጥቃት በሚደርስባቸው አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎች ተጠቂዎችን ለማዳን፤ ለማሸሽ እና ለመደበቅ ያደረጉት ወገናዊና ሞራላዊ መልካም ሥራ ማስረጃ ነው።

    የፖለቲካው በቅንነት በመተማመን እና በአንድ ሀገራዊ ስሜት አለመመራት ሁሉንም የሀገሪቱ ዜጎች በየትኛውም ስፍራ በእኩል ዓይን በማየት ለሰብዓዊ እና የዜግነት መብቶቻቸውን በሚያከብር እና በሚያስከብር መልኩ ባለመመራቱ የተነሳ ችግሩን ከማቅለል ይልቅ በማወሳሰብ፡-

    • እጅግ ብዙ ንፁሐን ወገኖቻችን ሕፃናትን፡ ነፍሰጡሮችን፡ አቅመ ደካሞችን ጨምሮ ያለአግባብ በአሰቃቂ ሁኔታ ሕይወታቸው እንዲያልፍ ሆኗል፤
    • የሀገሪቱን የቀድሞ ኤታ ማዦር ሹም ጨምሮ የክልል ከፍተኛ አመራሮችን አጥተናል፤
    • ኢማሞችን እና ቀሳውስትን ጨምሮ የቤተ እምነት አገልጋዮችን ውድ ሕይወት አጥተናል፤
    • በዩንቨርሲቲዎቻችን ለትምህርት የሄዱ ብዙ ወጣቶችን ትርጉም በሌለው ምክንያት ተቀጥፈውብናል፤
    • ለትምህር የሄዱ ሴት ተማሪዎችና የጤና ረዳት ሰራተኞች ታግተው ለስቃይ ተዳርገዋል፤
    • በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች መሠረታዊ አቅርቦቶች ለምሳሌ እንደ ትራንስፖርት፤ መንገድ መዘጋት፤ ምግብ፤ ባንክ፤ ቴሌኮሚኒኬሽን አገልግሎት፣ መድሀኒት ወዘተ አቅርቦት በተደጋጋሚ ረዘም ላሉ ጊዜያት በመቆራረጥ ሰላማዊ ዜጎች ለከፍተኛ ችግር እንዲዳረጉ ሆኗል፤
    • ግምቱ ከፍተኛ የሆነ የሀገር እና የሕዝብ ንብረትና ሀብት እንዲወድም ሆኗል፤
    • ከዚህ ሁሉ በላይ በሰሜን እዝ የመከላከያ ሰራዊት ላይ የደረሰው ጥቃት ችግራችን የደረሰበትን የአሳሳቢነት ደረጃ ፍንትው አድርጎ የሚያሰይ ነው። ለዚህ ጥቃት ዋንኛ መንስኤ ከሀገርና ከሰው ይልቅ ብሔርን ያስቀደመ የማንነት ፖለቲካ ውጤት ሁኖ እናገኘዋለን።

    ይህ አሳዛኝ ሁኔታ ዳግም እንደማይፈጠርስ ምን ማስተማመኛ አለን? ከብሔር፤ ከሀይማኖትና ከፖለቲካ ነጻ የሆነውን የመከላከያ ሠራዊት ከውስጡ የወጡ የራሱ ወገኖች ያጠቁት የብሔር ፖለቲካው ውጤት ነው።

    ይህም በቶሎ በታላቅ መስዋዕትነት በቁጥጥር ባይውል ኖሮ የሀገራችንን ሉዓላዊነትን የሚገዳደርና ከዚህ የከፋ ቀውስ የሚያስከትል እንደነበረ መረዳት አያዳግትም።

    ችግሩ ላይ ብቻ ሳይሆን የችግሩ መንስዔ ላይ አተኩረን ለመሥራት እና ለማስተካከል ከዚህ በላይ ምን ምክንያትና ምቹ ጊዜ እየጠበቅን ነው? ምንስ እስኪፈጠር ነው ለውሳኔ የምንዘገየው?

    በየቀኑ ክቡር የሰው ነፍስ በአሰቃቂ ሁኔታ እየተቀጠፈ እያለ የሞተው ወይም ገዳይ ከኛ ነው ከነሱ ነው እያሉ የፖለቲካ ቁማር ከመጫወት ሁላችንንም እንደሀገር ከሰውነት ከፍታ ያወረደንን የጥላቻ ፖለቲካ በመመካከርና በማሻሻል የተሻለ ሥርዓትን ለትውልድ እናቆይ።

    ለፌደራልና ለክልል መንግሥታት አመራሮች፦

    ልዩነታችን ላይ መሠረት ባደረገ የፖለቲካ አስተዳደር ሥርዓት የዜጎችን መሠረታዊ የሰብዓዊ መብቶች ማረጋገጥ አይቻልም።

    የፖለቲካ ባለድርሻ አካላት በከፍተኛ ታሪካዊ ሀገራዊ ስሜት በመሞላት በቁርጠኝነት የዓለም አቀፍ ሕግጋትን መሠረት ባደረገ፤ ያለንበትን 21ኛውን ክ/ዘመን በሚመጥን በሰከነ ስሜትና በቅንነት በመነጋገር፤ መሬት ላይ ያለውን በደምና በእምነት ተሳስሮ በሀዘንም በደስታ አብሮ የሚኖረውን ብዙኃኑን ምስኪን የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚመስል የፖለቲካ አስተዳደር ሥርዓት ለመዘርጋት እስካልወሰናችሁ ድረስ በሁሉም የሀገራችን ወሰን ውስጥ ያሉ ዜጎቻችንን መሠረታዊ የሰብዓዊ መብቶች በዘላቂነት ማስከበር ከቶውንም አትችሉም።

    ሰብዓዊ መብቶች፤ ሰላምና ሕግ ባልተከበረበት ሁኔታ ደግሞ እድገትንና ለውጥን ማሰብ እጅግ አዳጋች ነው። ይህ አካሔድ ደግሞ ለናንተም አይጠቅምም። ከእስካሁኑ ተግዳሮት በጊዜ ትምህር መውሰድ መልካም ነው።

    ችግሩን ለመፍታት እንደሚታሰበውም ቀላል እንዳልሆነ ብንረዳም እንደሚፈራውም ከባድ እንዳልሆነ እናምናለን።

    ከባድ ቢሆንም ደግሞ የእውነትን የአንድነትን የእኩልነትን ሰብዓዊ መብቶች የሚከበሩበትን፤ ለትውልድ ጥላቻን ሳይሆን ፍቅርን የምናወርስበትን መንገድን መርጠን የሚጠይቀውን መስዋዕትነት መክፈል የተሻለ ነው። ተቋማትም እስኪገነቡም ቢሆን የሰው ልጆች ወጥተው መግባት ዜጎች በህይወት የመኖር መብት አላቸው።

    መንግሥት የዜጎቹን ደህንነት ከማረጋገጥ የቀደመ ምን አይነት አጀንዳ ሊኖረው ፈጽሞ አይገባም።

    በመሆኑም፦

    1. መንግሥት ችግሩን ከምንጩ ለአንዴና ለመጨረሻ ለማድረቅ ቁርጠኛ ውሳኔ በመወሰን ጊዜ ባለመስጠት ውይይትና ምክክር ከላይ እስከታች እንዲጀመር እስከዚያውም በከፍተኛ ርብርብ ሕግ የማስከበር ሥራውን እንዲያስፈፅም እንጠይቃለን፤
    2. እስከዛሬም ድረስ በሁሉም የሀገራችን ክፍሎች የተፈጠሩትን ዘግናኝ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ገለልተኛ ወገን እንዲያጣራ በማድረግ አጥፊዎችና ተባባሪዎች እንደ ተሳትፎዋቸው መጠን ከፍተኛውን ቅጣት እንዲያገኙ ተጎጂዎችም ተመጣጣኝ ካሳ እንዲያገኙ እንዲደረግ እንጠይቃለን፤
    3. እስከዛሬም ድረስ በተፈጠሩ ችግሮች ምክንያት ከሚኖሩበት አካባቢ የተፈናቀሉ ዜጎች ተገቢው ድጋፍ ተደርጎላቸው ወደነበሩበት እንዲመለሱና መደበኛ ኑሯቸውን እንዲጀምሩ በመንግሥት ያለተገደበ ድጋፍ እንዲደረግላቸው እንጠይቃለን።

    ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ፦

    እስከዛሬ ድረስ በፖለቲካው ምክንያት በተፈጠሩ ችግሮች ብዙ ዋጋ እየከፈለ እና መሠረታዊ ሰብዓዊ መብቱን እየተገፈፈ ያለው ንጹህ የሆነው እና አብሮ በሰላም እየኖረ ያለው በሁሉም የሀገራችን ክፍሎች የሚኖረው ሕዝባችን እንደሆነ ይታወቃል። ያለንን አብሮነት አሁንም በማጠናከር እንደሕዝብም እንደግለሰብም አብረን በመቆም ለልጆቻችን የተሻለች ሀገር እናቆይ።

    ከጥላቻና ከብሔር ወይም ከማናቸውም የማንነት ልዩነት በመውጣት ለፖለቲካ ቁማር የማንመች እንሁን። ካለበለዚያ ከእስካሁኑ በባሰ የመጨረሻ ተጎጂዎች እኛው ነን።

    ምንም እንኳን የተለያየ አመለካከት ቢኖረንም በሰው ልጆች ሰብዓዊ መብቶች እና በሀገር አንድነት ጉዳይ የማንደራደር እንሁን። ሁላችንንም ስደተኞች ረሀብተኞችና ጠፊዎች ያደርገናል እንጂ ሀገር ለአንድ ብሔር፤ ለአንድ ክልል፤ለአንድ ቡድን ወይ ለአንድ ፓርቲ ብቻ ተለይታ አትፈርስም። ለተወሰነ ባለስልጣን ወይ አክቲቪስት ፈርሳ ለሌሎቻችን አትቆምም።

    ከሰሜን እስከደቡብ ከምሥራቅ እስከምእራብ አብረን ስንቆም ችግሮቻችን ከኛ በታች ይሆናሉ። ጥላቻና መጋደል በሕግም ፊት ወንጀል በሞራልም ነውር በእምነቶቻችንም ኃጥያት ነውና በሰከነ መንፈስ ሰብዓዊነትን በማስቀደም ሀገራችንን በማስከበር በብዝኃነት መኖር እንደለመድነው ቃልኪዳናችንን እናድስ።

    ውስጣዊ አንድነታችን በተዳከመ ቁጥር የውጭ ጠላቶቻችን ይደፍሩናል ያጠቁናል የዚያን ጊዜ ብሔር መርጠው አይወጉንም፤ ሁላችንንም ጨለማ ይወርሰናል። ምርጫው በእጃችን ነውና ሳይዘገይብን በይቅርታ መንፈስ እንነሳ።

    ሰው መሆናችን ትልቁ አንድነታችን መሆኑን እናስተውል።የነበሩንን እና ያሉንን መልካም አብሮ የመኖር እሴቶች በማጠናከር ችግሮቻችንን በእርጋታ እየፈታን እንጓዝ። የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በማንም ይፈጠሩ፤ ማንም ተጎጂ ይሁን ሰው ነውና ወገን ነውና በአንድነት በማውገዝ በአንድነት ፍትህን በመጠየቅ ለሚለያዩን የማንመች እንሁን። ለልጆቻችን ፍቅርን ተስፋን መከባበርንና የሥራ ባህልንና ማውረስ አለብን።

    እናቶች፣ አባቶች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ ምሁራን፣ የጥበብ ሰዎች፣ የሚድያ አካላት በአጠቃላይ ሁላችሁ ኢትዮጵያውያን በሀገር ውስጥም ይሁን በውጭ ያላችሁ በሙሉ ይህን ከባድ ጊዜ ተያይዘን እንድናልፈው የበኩላችንን አስተዋጽዖ እንድናደርግና የዜጎች ሰብዓዊ መብቶች ሳይሸራረፉ የሚከበሩበት፡ በሕግና በሥርዓት ብቻ ፍትህ የሚጠየቅበትና የሚገኝበት ማንኛውም አካል ከዜጎችና ከሀገር ደህንነት በታች የሚሆንበት መዋቅራዊ የሥርዓት መሻሻል እንዲመጣ በሰላማዊ መንገድ አብረን ጥሪያችንን እንድናሰማ ስንል በታላቅ አክብሮት እንማፀናችኋለን።

    ቅድሚያ ለሰብዓዊነት!
    ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ
    ታህሳስ 22 / 2013
    ​አዲስ አበባ፥ ኢትዮጵያ

    የዜጎችን መሠረታዊ ሰብዓዊ መብቶች ማረጋገጥ

    Anonymous
    Inactive

    የፌዴሬሽን ምክር ቤት በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም ወሰነ

    የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕገ-መንግሥቱና በአዋጅ ቁጥር 359/1995 በተሰጠው ስልጣን መሠረት በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋምና ሌሎች ተያያዥነት ያላቸው ውሳኔዎችን ወሰነ።

    ሕገ-ወጡ የትግራይ ክልል መንግሥት ወደ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱ እንዲመለስ የተሰጠውን በቂ ዕድል መጠቀም ባለመቻሉ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥቅምት 28 ቀን 2013 ዓ.ም ባካሄደው አስቸኳይ ጉባዔ በሕገ-መንግሥቱና በአዋጅ ቁጥር 359/1995 በተሰጠው ስልጣን መሠረት ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋምና ሌሎች ተያያዥነት ያላቸው ውሳኔዎችን ወስኗል።

    ሕገ-ወጡ የትግራይ ክልል መንግሥት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ምሽት ላይ በክልሉ በሚገኘው ጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ አስነዋሪ ጥቃት ፈጽሟል። በተጨማሪም በአማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ላይ ጥቃት በመፈፀም በንፁሃን ዜጎችና ንብረት ላይ ጉዳት አድርሷል።

    የፌዴራል መንግሥት በክልል ጣልቃ የሚገባበትን ሥርዓት ለመደንገግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 359/95 አንቀጽ 12 በአንድ የክልል መንግሥት ተሳትፎ ወይም ዕውቅና ሕገ-መንግሥቱን ወይም ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን ባለማክበር የሚደረግ እንቅስቃሴ ወይም ድርጊት በተለይም፡

    (1) በትጥቅ የተደገፈ የአመጽ እንቅስቃሴ ማድረግ፤

    (2) ከሌላ ክልል ወይም ከሌላ ክልል ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ጋር የተፈጠሩ ችግሮችን ሰላማዊ ባልሆነ መንገድ መፍታት፤

    (3) የፌዴራሉን ሰላምና ጸጥታ ማናጋት ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ እንቅስቃሴ ወይም ድርጊት እንደሆነ እንደሚቆጠር ተደንግጓል። ከዚህ ድንጋጌ አንጻር ሕገ-ወጡ የትግራይ ክልል መንግሥት የፈጸመው እና እየፈጸመ ያለው ድርጊት ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ ተጨማሪ እንቅስቃሴ ወይም ድርጊት እንደሆነ ተረጋግጧል።

    በዚሁ መሠረት የኢፌዲሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 62 (9) ማንኛውም ክልል ሕገ-መንግሥቱን በመጣስ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ እንደሆነ የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ የማዘዝ ስልጣን እንዳለው የተደነገገ በመሆኑ፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ስልጣንና ተግባር ለመዘርዘር በወጣው አዋጅ ቁጥር 251/93 አንቀጽ 36 (1) የፌዴሬሽን ምክር ቤት በአንድ ክልል ውስጥ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ ወድቋል ብሎ ሲያምን የፌዴራሉ መንግሥት ተገቢና ተመጣጣኝ እርምጃ እንዲወስድ ማዘዝ እንደሚችል እንዲሁም በአዋጅ ቁጥር 359/95 አንቀጽ 13 (4) ምክር ቤቱ የፌዴራል መንግሥቱ ጣልቃ መግባት አስፈላጊ ሆኖ ያገኘው እንደሆነ ጣልቃ እንዲገባ ሊያዝ እንደሚችል በመደንገጉ ሕገ-ወጡ የትግራይ ክልል መንግሥት ሕገ-መንግሥታዊ እና የፌዴራል ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ድርጊት በመፈጸም የፌዴሬሽኑን ህልውና አደጋ ላይ የጣለ ስለሆነ ይህንን ድርጊት ማስቆም ተገቢ ሆኖ ተገኝቷል። በመሆኑም የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕገ-መንግሥቱና በአዋጆቹ የተሰጠውን ስልጣንና ኃላፊነት በመጠቀም ሕገ-መንግሥታዊ መፍትሔ መስጠት ያለበት ሆኖ በመገኘቱ፥ ጥቅምት 28 ቀን ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ የሚከተሉትንን ውሳኔዎች አሳልፏል።

    1. ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለውን ድርጊት ለማስቆም የፌዴራል መንግሥቱ ጣልቃ እንዲገባ ትዕዛዝ ሰጥቷል፤ እንዲሁም ሊወሰዱ የሚገባቸውን እርምጃዎች በተመለከተ በአዋጅ ቁጥር 359/95 አንቀጽ 14 (2) መሠረት ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተጣጣመ መልኩ አደጋውን ለማስወገድ እንዲቻል የፌደራል ፖሊስን ወይም የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ወይንም ሁለቱንም በክልሉ እንዲያሰማራ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፤
    2. ሕገ-ወጡን የክልሉ ምክር ቤት እና የክልሉ ከፍተኛ የሕግ አስፈጻሚ አካል ታግዶ ለፌደራል መንግሥቱ ተጠሪ የሆነና በአዋጅ 359/1995 አንቀጽ 15 ላይ የተቀመጡት ስልጣንና ተግባራት የሚኖሩት ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም ወስኗል። በዚሁ መሠረት የሚቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር ከሌሎች አግባብነት ካላቸው መንግሥታዊ አካላት ጋር በመተባበር ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለውን ሁኔታ ለማስወገድ የሚያስችሉ እርምጃዎችን ይወስዳል። በተጨማሪም ለክልሉ ከፍተኛ የሕግ አስፈፃሚ አካል የተሰጡትን ተግባሮች ይኖሩታል። በተለይም ጊዜያዊ አስተዳደሩ፤

    ሀ) አስፈፃሚ አካሉን ይመራል፣ ያስተባብራል፤

    ለ) የጊዜያዊ አስተዳደሩን ኃላፊዎች ይመድባል፤

    ሐ) ሕግና ሥርዓት መገበሩን ያረጋግጣል፤

    መ) አግባብ ባለው ህግ መሠረት በክልሉ ምርጫ የሚከናወንበትን ሁኔታ ያመቻቻል፤

    ሠ) የክልሉን እቅድና በጀት ያፀድቃል፤

    ረ) በፌዴራል መንግሥቱ ሚሰጡ ሌሎች ተግባሮችን ያከናውናል።

    1. ከፍ ብሎ የተጠቀሱትን የምክር ቤቱ ውሳኔዎች አፈጻጸምና ክልሉ ስለሚገኝበት ሁኔታ በተመለከተ ክቡር የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደ አስፈላጊነቱ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በየሦስት ወሩ ሪፖርት እንዲያቀርብ በማለት ወስኗል።

    በመጨረሻም፥ መላው የትግራይ ሕዝብና የሀገራችን ሕዝቦች ሕገ-ወጡ ቡድን የፈፀመውን ኢ-ሕገ መንግሥታዊና አስነዋሪ ድርጊት በማውገዝ የሀገርን ሉዓላዊ ክብር ለማስጠበቅ ከራስ በፊት ለሕዝብና ለሀገር በሚል መርህ እስከ ህይወት መስዋዕትነት እየከፈለ ካለውና የኩራታችን ምንጭ ከሆነው ጀግናው የመከላከያ ሠራዊት ጨምሮ ከፌደራሉ መንግሥት እና ከሚቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር ጎን እንዲቆም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥሪውን ያቀርባል። በተጨማሪም መላው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በመተሳሰብ፣ አንዱ ለሌላው ጠበቃና ዋስትና በመሆን እኩይ ዓላማ ይዘው እርስ በርሳችንን በማጋጨት ሀገራችንን ለመበታተን ሌትተቀን የሚሠሩ ኃይሎችን ነቅተን በመጠበቅና ሕብረ-ብሔራዊ አንድነታችንን በማጠናከር ረገድ ሁሉም ዘብ እንዲቆም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥሪውን ያቀርባል።

    የፌዴሬሽን ምክር ቤት

    የፌዴሬሽን ምክር ቤት

    Semonegna
    Keymaster

    በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ዙሪያ ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

    አዲስአበባ
    ጥቅምት 27 ቀን 2013 ዓ.ም

    በሀገር አቀፍ ደረጃ የተደረገውን ለውጥ ተከትሎ መንግሥት ባደረገላቸው ጥሪ መሠረት የተለያዩ የፖለካ አካላት ወደ ሀገር መግባታቸው፣ በተሰማሩበት ቦታ ሁሉ ችግሮች እንዳያጋጥማቸውና ደህንነታቸውን በመጠበቅና የፈለጉትን ሀሳብ እንዲገልጹ በቂ ክትትል ሲደረግላቸው መቆየቱን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄነራል እንዳሻው ጣሰው በመግለጫቸው አስታውሰዋል።

    በፌደራልና በክልል የሚገኙ የፖለቲካ እስረኞች መንግሥት ባደረገላቸው ምኅረትና ይቅርታ እንዲፈቱ መደረጋቸውን እንደ ትልቅ ሥራ መወሰድ አለበት ያሉት ኮሚሽነር ጄነራሉ፥ ሚዲያዎችም የተለያየ ሀሳብ ለሕብረተሰቡ ተደራሽ እንዲያደርጉና ከሕብረተሰቡ የሚነሱ ጉዳዮችን ለመንግሥት እንዲያደርሱ ነፃነታቸውን በመጠበቅ በኩል በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን ተናግረዋል።

    ከሕዳሴ ግድብ ጀምሮ በመላ ሀገሪቱ ተቀዛቅዞ የነበረ የትላልቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ በተጠናከረ መልኩ እንዲቀጥልና የተጀመረ የልማት ሥራ እንዲቋጭ የተለያዩ ሥራዎች ተሠርተዋል ያሉት ኮሚሽነር ጄነራሉ፥ በፖሊስ፣ በሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ በብሔራዊ መረጃና ደህንነትና በሌሎች የጸጥታ አካላት የተከናወኑ ሰፋፊ የሪፎርም ሥራዎችን በበጎ የሚወሰዱ ተግባራት መሆናቸውን ገልጸዋል።

    በሌላ በኩል ግን በሰላማዊ መንገድ ጥሪ ከተደረገላቸው አካላት መካከል ሰላማዊ መንገዱን በመተው ወደ ትጥቅ ትግል የገቡ አካላት እንዳሉ የገለጹት ኮሚሽነር ጄነራሉ፥ በተለይ የኦኔግ ሸኔ ቡድን በምዕራብ ወለጋና በሌሎች አካባቢዎች እንቅስቃሴ በማድረግ ሕብረተሰቡን በመግደል፣ በማገት፣ ንብረት በማውደምና ሌሎች የተለያዩ ሕገ-ወጥ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን ጠቁመዋል።

    በተማሪዎች ጠለፋ ላይም በመሰማራት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ በደቡብ ክልል ጉራ ፈርዳና በቅርቡ ደግሞ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ አካባቢ የኦኔግ ሸኔ አባላትና ህወሓት በተቀናጀ መንገድ የሕዝብ ግዲያ በመፈጸም የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውኑ እንደነበር ለማየት ተችሏል ብለዋል ኮሚሽነር ጄነራሉ።

    ኮሚሽነር ጄነራሉ አያይዘውም የህወሓት ጽንፈኛው ኃይል ከእነዚህ ከፍተኛ ጥፋቶች ኋላ ተሰማርቶ ሲሠራ እንደነበረ በተለያዩ ጊዜ ባደረግናቸው ምርመራዎች ለማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል።

    የህወሓት ጽንፈኛ ኃይል ከፌደራል መንግሥት ጋር ለመሥራት ያለመፈለግ፣ ሕገ-ወጥ ምርጫ ማከናወን፣ የሠራዊት አባላትን ለውጊያ በሚመጥን መንገድ ማዘጋጀት፣ የፌደራል መንግሥትን ሕገ-ወጥ ነው በማለት ባገኘው ሚዲያ በሙሉ ማሰራጨትና ሌሎች ለጸጥታ ሥራ ስጋት የሆኑ ጉዳዮችን ሲያከናውን መቆየቱንም ኮሚሽነር ጄነራሉ ገልጸዋል።

    በአጠቃላይ የህወሓት ጽንፈኛ ቡድንና የኦኔግ ሸኔ ታጣቂው ኃይል በተደራጀ መንገድ ከውጭና ከሀገር ውስጥ የሚደረግላቸውን የፋይናንስ ድጋፍ በመጠቀም ለሁለት ዓመታት የተለያዩ የሀገሪቱን ክፍል ሲያተራምሱ መቆየታቸውን ለማረጋገጥ እንደተቻለም ኮሚሽነር ጄነራል እንዳሻው ተናግረዋል።

    በሁሉም አካባቢ የተፈጸሙ የጸጥታ ችግሮች ሲያደራጁና ሲመሩ የነበሩ መሆናቸውን ምርመራዎቻችንና የተለያዩ መረጃዎቻችን አረጋግጧል ያሉት ኮሚሽነር ጄነራሉ፥ የተለያዩ ፍንዳታዎችን በመፈጸም፣ የግድያ ሙከራዎችን ማከናወን፣ ንብረት ማውደም፣ ሕዝብን ከሕዝብ ማጋጨትና በቤተ-እምነቶች መካከል ግጭት እንዲፈጠር ለማድረግ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እንደነበራቸውም ኮሚሽነር ጄነራሉ በመግለጫቸው ጠቁመዋል።

    አሁንም በትግራይ ክልል ጦርነት ከፍተው ባሉበት ወቅት በሀገራችን የተለያዩ ክፍሎችና ትላልቅ ከተሞች ላይ ጥቃት ለማድረስ ያሰማሩት ኃይል እንዳለ ተደርሶበታል ያሉት ኮሚሽነር ጄነራሉ፥ ይሄ ኃይል ፖሊስና ሌሎች የጸጥታ አካላት ባደረጉት ስምሪት ግማሹ የተያዘ ሲሆን ግማሹ ደግሞ በቅርብ ቀን ከተደበቀበት በማውጣት በቁጥጥር ስር የማዋል ሥራ በተጠናከረ መልኩ እንደሚከናወን ተነግሯል።

    የፌደራል ፖሊስ ባለው ሕገ-መንግሥታዊ ተልዕኮ መሠረት በሀገሪቱ በሁሉም አካባቢ በመሰማራት የሕብረተሰቡን ሰላምና ጸጥታን የሚጠብቅ ኃይል መሆኑን በመግለጽ በትግራይ ክልልም በ22 ትልልቅ ተቋማት ላይ በመሰማራት አገልግሎት ሲሰጥ የነበረ ተቋም ነው ብለዋል።

    የፌደራል ፖሊስ አባላት ኤርፖርቶችን፣ ዲፖዎችን፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ጣቢያዎችን፣ ቴሌኮምን፣ ቤተ መንግሥትን፣ ትላልቅ ግድቦችንና ኬላዎችን ጨምሮ ሌሎች የሕዝብና የመንግሥት ተቋማትን በመጠበቅ ተገቢውን አገልግሎት ለሕብረተሰቡ ሲሰጡ መቆየታቸውንና በትግራይ ውስጥ ለሚሰሩ የልማት ሥራዎችን ከሕብረተሰቡ ጎን በመሰለፍ በገንዘባቸው፣ በእውቀታቸውና በጉልበታቸው ከፍተኛ አስተዋፅኦ ሲያደርጉ እንደነበር ተገልጿል።

    የፌደራል ፖሊስ ኃይል ሕብረተሰቡን ሲያግዝ በነበረበት ወቅት ህወሓት ከፍተኛ ኃይል በመመደብ ጥቃት እንደሰነዘረባቸውና የንብረት ዝርፊያ መፈጸሙን የተናገሩት ኮሚሽነር ጄነራሉ፥ በአንዳንድ አካባቢ የፌደራል ፖሊስ ሠራዊትና የትግራይ ሕዝብ አንድ ላይ ሆነው ሊወረው የመጣውን ኃይል ተከላክሏል ብለዋል።

    መውጫና መግቢያ መንገዶችን ለሠራዊቱ በማሳየት የትግራይ ሕዝብ ሊያጠቃው የመጣውን አካል መከላከል መቻሉና ከሰሜን እዝ ጋር በመሆን ጽንፈኛውን ተዋጊ ኃይል በመመከትና በመምታት የራሱን ድርሻ እየተጫወተ ይገኛል ተብሏል።

    ጽንፈኛው የህወሓት ቡድን የፈፀመው ይሄ አስነዋሪ ድርጊት ታሪክ፣ ሕግና ህሊና ይቅርታ የማይሰጠው ጉዳይ ነው ያሉት ኮሽነር ጄነራል እንዳሻው ጣሰው፥ ሠራዊቱንና ሕዝቡን የደፈሩበት ሂደት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋልም ብለዋል።

    ለውጊያ ሳይሆን ለጥበቃ ሥራ የተሰማራ የፌደራል ፖሊስ ኃይል በታጠቀና ለውጊያ በተዘጋጀ ኃይል ተከቦ እንደዚህ ዓይነት እርምጃ መውሰድ አጅግ አሳፋሪ መሆን በመግለጽ ሕግ የማስከበር ሂደታችን በድል በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ የፌደራልና የክልል ፖሊስ እንዲሁም ሕዝባዊ አደረጃጀት ያላቸው የሚኒሻ አባላት በጋራ በመደራጀት አካባቢያቸውን በአግባቡ መጠበቅ እንዳለባቸው ጠቁመዋል፤ ለተለያየ እኩይ ተግባር የተሰማሩ ሃይሎችን በየአካባቢው በቂ ጥናት በማድረግ በቁጥጥር ስር ማዋል እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

    በአማራ ክልል ጎንደር ከተማ፣ በአፋር፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላና በሌሎች አካባቢዎች የነበሩ የጥፋት ሙከራዎችን በቁጥጥር ስር በማዋል ሠራዊቱ በአንድ ረድፍ በመሰለፍ ይህንን ችግር ለመከላከል ላሳየው ከፍተኛ ጽናት አድናቆታቸውን በመግለጽ አሁንም ከኢንቨስትመንት ጀምሮ ለትልልቅ የኢንዱስትሪ መንደሮች ተረባርበን አስፈላጊውን ጥበቃ በማድረግ ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮችን መከላከል አለብን ብለዋል።

    በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት በሚሰጠው መመሪያ መሠረት መፈጸም ከሠራዊቱ አባላት የሚጠበቅ ተግባር መሆኑን የገለጹት ኮሚሽነር ጄነራሉ ሕብረተሰቡ በዲጂታል ወያኔ የሚሠራጩ የሐሰት ፕሮፓጋንዳዎችን በጋራ መከላከል እንዳለበትና በየቀኑ ከመንግሥት የሚሰጠውን መግለጫ ብቻ መከታተል እንዳለበት አስገንዝበዋል።

    መንግሥት ለሚያቀርበው ጥሪ ሕብረተሰቡ በቂ ዝግጅት በማድረግ እኩይ ተግባር ለመፈጸም የተሰማራ ኃይል በመከታተል መጠቆምና ማጋለጥ እንዳለበትም ኮሚሽነር ጄነራሉ ጥሪ አቅርበዋል።

    በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በተሰጡ አድራሻዎች መሠረት በዚህ በሁለት ቀናት ውስጥ ብቻ ከ1,500 በላይ የሚደርሱ ጥቆማዎች መድረሳቸውንና በዚህም ውጤታማ ሥራዎች መከናወናቸውን የተናገሩት ኮሚሽነር ጄነራሉ በሌሎችም መሰል ሥራዎች መሠራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

    የተጀመረው ጸረ-ሰላም ኃይልን የማጥራት ሂደት በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ፊታችንን ሙሉ በሙሉ ለሰላም፣ ለልማትና ለዲሞክራሲ ግንባታ በማዞር ጥረት የምናደርግበት ጊዜ እንዲሆንም የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄነራል እንዳሻው ጣሰው ተመኝተዋል።

    የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን

    የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን

    Anonymous
    Inactive

    የሀገር ሰላም እና አንድነትን ለማረጋገጥ የሚወሰደው እርምጃ በፍጥነት ተጠናቆ ሙሉ ትኩረታችንን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት ላይ እናድርግ!
    ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የተሰጠ መግለጫ

    በሀገራችን ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ መንግሥታዊ ድጋፍ አግኝቶ በተግባር ላይ የቆየው ማንነትን መሠረት ያደረገ ፖለቲካ በዜጎች እና ማኅበረሰቦች መካከል የጥላቻ እና ያለመተማመን ስሜት እንዲሰፍን ማድረጉ የሚታወቅ ነው። በወቅቱ ስልጣን ላይ የነበረው አገዛዝ በስልጣን ላይ ለመቆየት የጥላቻ እና አለመተማመን መስፈኑን እንደአንድ መሣሪያ ሲጠቀመው ቆይቷል። ይህን ለረጅም ጊዜ በመንግሥት መዋቅር ጭምር እየተደገፈ የተሠራው ማንነትንን መሠረት ያደረገ መከፋፈል፣ የጥላቻ እና የእርስ በርስ አለመተማመን አሁንም ድረስ በየአካባቢው ተንሰራፍቶ፤ ዜጎች በሀገራቸው በየትኛውም ቦታ ተንቀሳቅሰው ደህንነታቸው ተጠብቆ የመኖር፣ የመሥራት እና ሀብት የማፍራት ሕገ-መንግሥታዊ እውቅና ያለውን ሰብዓዊ መብታቸውን እየገፈፈ ነው።

    ይህ መከፋፈል፣ የእርስ በርስ ጥላቻ እና አለመተማመን ከሕጋዊ እና ሰላማዊ መንገድ ውጪ የፖለቲካ አመለካከታቸውን በኃይል ለመጫን የሚፈልጉ ኃይሎች ዓላማቸውን ለማሳካት እንደአጋጣሚ ወስደው እየተጠቀሙበት እንደሆነ ግልፅ ነው። አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግሥት መዋቅርም ሙሉ በሙሉ ከዚህ ችግር ያልጸዳ ብቻ ሳይሆን አደጋ በደረሰባቸው ቦታዎች የመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ ሰዎች ከአጥፊዎች ጋር በትብብር እየሠሩ ከአደጋ መጠበቅ የሚገባቸውን የንፁሃን ዜጎች ሕይወት አደጋ ላይ እየጣሉ ይገኛል።

    የዜጎችን ደህንነት የመጠበቅ እና የሀገር ሰላም እንዲሁም አንድነትን የማስከበር ኃላፊነት ያለባቸው የደህንነት መዋቅሮች የደህንነት ስጋት ያለባቸው ቦታዎችን በአግባቡ ተንትኖ ደረጃቸውን መለየት እና በዚያም ልክ ተዘጋጅቶ የንፁሃን ዜጎችን ሕይወት እና የሀገርን ሰላም ማስጠበቅ ላይ በተደጋጋሚ ክፍተት እንዳለባቸው አይተናል። የንፁሃንን ሕይወት የቀጠፉ እና ከፍተኛ ጉዳት ያደረሱ ጥቃቶች መደጋገማቸው ከተፈፀሙ በኋላ የሚወሰዱ የእርምት እርምጃዎችም አጥጋቢ እንዳልሆኑ በግልፅ የሚያሳዩ ናቸው። እነዚህን ጉድለቶችን ሙሉ ለሙሉ ማረም እና አስተማማኝ የሆነ የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ እና ተጠያቂነትን ለማስፈን የረጅም ጊዜ ከባድ ሥራ የሚጠይቅ ቢሆንም፥ ክፍተቱ እያስከተለ ያለው የንፁሃን ዜጎች ሕይወት ጥፋት የማስተካከያ እርምጃዎች ከማንኛውም ጊዜ በላይ በከፍተኛ ትኩረት ቅድሚያ ተሰጥቶዋቸው እንዲሠሩ የሚያስገድድ ነው።

    ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በስልጣን ላይ የቆየው ኢሕአዴግ አባል የነበሩ ሰዎች በሀገር እና ዜጎች ላይ ላደረሱት ጥፋት ሁሉ ይቅርታ ጠይቀው፤ አብዛኛው ኢትዮጵያዊያንም ተቀብሎት፤ ሀገር አቀፍ ለውጥ ሂደት ጅማሮ ውስጥ መግባታችን ይታወቃል። የነበረውን ስልጣን የበላይነት ያጣው ህወሓት በተለያየ ጊዜ የወሰዳቸው እርምጃዎች ከአጠቃላይ የለውጡ መንፈስ ውጪ ከመሆን አልፈው፤ የሀገር ሰላም እና አንድነትን በተደጋጋሚ አደጋ ላይ የሚጥሉ ነበሩ። የተወሰኑትን ለመጥቀስ ያክል የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ የፌደራሉን መንግሥትና የምርጫ ቦርድ ውሳኔን በቀጥታ በመቃወም ራሱ አስመራጭ፣ ተመራጭ፣ ታዛቢ እና ቆጣሪ የነበረበት ሕገ-ወጥ የክልል ምርጫ አድርጓል። በዚህም የተነሳ የፈደራል መንግሥት ከክልሉ ጋር ያለዉን ቀጥተኛ ግንኙነት ማቋረጡን እናስታውሳለን። “ከመስከረም 25 በኋላ መንግሥት የለም!” የሚል አደገኛ ቅስቀሳ በማድረግ በሀገራችን ውስጥ ፍፁም ሥርዓት አለበኝነት እንዲነግሥ በባለስልጣናቱ እና በሚቆጣጠራቸው መገናኛ ብዙኃን ተደጋጋሚ ጥሪ ሲያደርግ ቆይቷል። በሀገሪቱ በተለያየ አካባቢ የሚንቀሳቀሱ የጥፋት ቡድኖችን ቢያንስ በእርግጠኝነት የምናውቀውን የሚዲያ እና የሞራል ድጋፍ በማድረግ የብዙ ንጹሀን ሕይወት እንዲቀጠፍ ተባባሪ ሆኗል።

    በሀገራችን የመከላከያ ሠራዊት ላይም በተደጋጋሚ ሥራዉን የማደናቀፍ እና የሚገባዉን ክብር የመንፈግ ድርጊቶች ፈጽሟል። የሠራዊቱ የተለያዩ ክፍሎች ከቦታ ቦታ ሲዘዋወሩ መንገድ በመዝጋት እና በማዘጋት እንዲሁም በመከላከያ ሕግ እና ደንብ መሠረት የሚፈጸሙ የከፍተኛ የጦር ኃይል አመራር ሹመቶችን ባለመቀበል አስተጓጎሏል። ህወሓት የፖለቲካ ዓላማውን ለማሳካት በሰላማዊ መንገድ ከመንቀሳቀስ እና ችግሮችን በውይይት ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ የትግራይን ሕዝብ እንደከለላ በመውሰድ እና ያከማቸውን ገንዘብ እና የኃይል አቅም በመጠቀም በማንአለብኝነት የፈፀማቸው ድርጊቶች እያደር የብዙ ዜጎችን ሕይወት እንዲሁም የሀገር ሰላም እና አንድነት የበለጠ አደጋ ውስጥ እየከተቱ መጥተው መንግሥት ያለውን ኃይልን ተጠቅሞ የዜጎችን ደህንነት የመጠበቅ እና የሀገር ሰላም እና አንድነት የማስጠበቅ ኃላፊነቱን ተግባራዊ ለማድረግ የተገደደበት ደረጃ ላይ መድረሱን እንገነዘባለን።

    ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት እራሱን ለመከላከል እና ለሀገር አንድነትና ሰላም ከፍተኛ እና ተደጋጋሚ ስጋት ሲደቅን የነበረው ህወሓት ላይ መውሰድ የጀመረው እርምጃ በሌሎች የሀገራችን አካባቢዎችም ኃይልን ተጠቅመው የዜጎችን ደህንነት እንዲሁም የሀገር ሰላም እና አንድነት ላይ አደጋ በመጣል የፖለቲካ ዓላማቸውን ለማሳካት የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን በሙሉ ሥርዓት የሚያሲዝ እና ከአሁን በኋላ የፖለቲካ ዓላማን ለማሳካት ከሰላማዊ እና ሕጋዊ መንገድ ውጪ ለመንቀሳቀስ ያሉ አማራጮችን በሙሉ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚዘጋ መሆን ይኖርበታል።

    በሁሉም አካባቢዎች ችግር ሲያጋጥም አሰስፈላጊውን መስዕዋትነት እየከፈለ የሚጠብቀን የሀገር መከላከያ ሠራዊታችን በዚህ ወቅት ከውጭ ጠላቶች ሀገርን የመከላከል እና ከሀገር ውስጥ የጥፋት ኃይሎች ሀገርን የመታደግ ድርብርብ ከባድ ኃላፊነቶችን እንደተሸከመ እንረዳለን። ምንም እንኳን ተደራራቢ እና አስቸጋሪ ኃላፊነት ቢሆንም የተቋቋመበት ኃላፊነት እና የተሰጠው ሕገ-መንግሥታዊ ግዳጅ በመሆኑ እንደሚወጣው እናምናለን። በዚህ አጋጣሚ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የሀገርን አንድነት እና ሰላምን ለማስከበር የሚወስዳቸው እርምጃዎች የኢዜማ አባላት እና አመራር ሙሉ በሙሉ ከጎኑ እንደሚቆም ለማረጋገጥ እንወዳለን።

    በመሆኑም፦

    1. መከላከያ ሠራዊቱ እና ሌሎች የመንግሥት የፀጥታ ተቋማት የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የሚወስዷቸው እርምጃዎች የሁሉንም ዜጎች ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ያከበረ እንዲሁም ሰላማዊ ዜጎች በተለይም ሕፃናት፣ ሴቶች እና በዕድሜ የገፉ አረጋውያን ማንኛውም ጉዳት እንዳይደርስባቸው አስፈላጊው ጥንቃቄ ሁሉ እንዲደረግ ልናሳስብ እንወዳለን። የዜጎችን ደህንነት እንዲሁም የሀገር ሰላምን እና አንድነትን ለማስከበር የሚወሰደው እርምጃ በተቻለው አቅም በአጭር ጊዜ ተጠናቆ በሁሉም አካባቢዎች መደበኛ የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ የሚቀጥልበት ሁኔታም ሊመቻች ይገባል።
    2. የትግራይ ሕዝብ አሁን እየተወሰደ ያለው እርምጃ የሀገር ሰላም እና አንድነትን የማረጋገጥ እርምጃ መሆኑ በማወቅ ለረጅም ጊዜ የስጋት ድባብ በመፍጠር እንደሽፋን እየተጠቀመ ሲበዘብዘው እና በስሙ ሲነግድ የነበረው ህወሓትን በፍፁም ሳይተባበር ከአብራኩ ከወጣው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ጎን በመቆም ለሀገር ሰላም እና አንድነት ከአባት እና እናቶቹ የወረሰውን ቁርጠኝነት በተግባር እንዲያረጋግጥ የአደራ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
    3. የትግራይ ክልል ፖሊስ እና ልዩ ኃይል አባላት ህወሓት የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት እንዲደርስ በማድረግ በኢትዮጵያ አንድነት እና ሉዓላዊነት ላይ መዳከም እንዲፈጠር በሚያደረገው ሀገርን የማፍረስ ዘመቻ ላይ እንዳይሳተፉ ጥሪያችንን እናቀርባለን። የትግራይ ክልል ፖሊስ እና ልዩ ኃይል በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ጎን በመቆምም ሕዝቡን ከስጋት እና ከአደጋ እንዲጠብቅ እንጠይቃለን።
    4. መላው የኢትዮጵያ ሕዝብም የሚወሰደው እርምጃ የዜጎችን ደህንነት እና የሀገር ሰላም እና አንድነት ለማረጋገጥ መሆኑን በመረዳት አብሮነታችንን አደጋ ላይ የሚጥሉ እና ለሰላም እና ደህንነት እንቅፋት የሚሆኑ ማንኛውንም እንቅስቃሴዎች ከማድረግ እንዲቆጠብ፣ በሁሉም አካባቢ ስጋት የገባቸውን ሰላማዊ ዜጎች ከለላ እና ማበረታቻ በመስጠት እንዲሁም አካባቢውን በንቃት እየጠበቀ ለሰላም እና ደህንነት መከበር ከፀጥታ አስከባሪዎች ጋር ትብብር እንዲያደርግ የአደራ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
    5. አሁን እንደ ሀገር የተደቀነብን አደጋ ማንንም ከማንም የማይመርጥ የህልውና አደጋ መሆኑን በመገንዘብ ይህንን አደጋ የሚመጥን መፍትሄ በማፈላለግ ረገድ የተማረው ማኅበረሰብ ሚና ትልቅ እንደሆነ እሙን ነው። የተማረው የኅብረተሰብ ክፍል ከዳር ቆሞ አስተያየት ሰጪና ተቺ ከመሆን ወጥቶ ወደመሀል በመግባት ሊመጡ የሚችሉ የፖለቲካ መፍትሄዎችን በመጠቆም፤ እንዲሁም በቀጥታ ድጋፉን የሀገር አንድነትን እና ሰላምን ከሚፈልጉ ኃይሎች ጎን በማሰለፍ ያለበትን ማኅበረሰባዊ ኃላፊነት እንዲወጣ በዚህም በታሪክ ከሚመጣበት ወቀሳ እንዲድን ጥሪያችንን እናቀርባለን።
    6. አሁን እየተተገበረ ላለው ሀገራዊ ግዳጅ ጥሪ ተደርጎላችሁ የምትሳተፉ ኃይሎች የሀገር መከላከያ ሠራዊት ትዕዛዝ ስር ብቻ ተልኮውን እንድትፈፅሙ እና በተሰጣችሁ ሀገራዊ ግዳጅ ላይ ብቻ እንድታተኩሩ እናሳስባን። ኢዜማ ለሀገራዊው ጥሪ በፍጥነት ለሕይወታችሁ ሳትሳሱ ምላሽ ለሰጣችሁ ሁሉ ምስጋናውን እያቀረበ በዚህ ሂደት ውስጥ ምንም ዓይነት በይፋ ከመንግሥት ከተሰጠ ተልዕኮ ወጪ የሆነ ለሀገር ሰላም እና አንድነት የበለጠ እንቅፋት የሚሆን ተግባር እንዳትፈፅሙ ስንል እናሳስባለን። በተለይም ኢ-መደበኛ በሆነ አደረጃጀት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች የገባንበትን ችግር የበለጠ የሚያወሳስብ እጅግ አደገኛ ተግባር እንደሆነ ልናሳስብ እንወዳለን። ስለዚህም አሁን የዜጎችን ደህንነት እንዲሁም የሀገር ሰላም እና አንድነትን ለማስከበር የተገባው በሀገራዊ ግዳጅ ላይ ብቻ አተኩረን በመንቀሳቀስ በፍጥነት የሕዝብን ጭንቀት በመቋጨት ሌሎች የዴሞክራሲ እና የይገባኛል ጥያቄዎች በሰላማዊ እና ሕጋዊ መንገዶች ወደፊት የሚፈቱበት መንገድን እንድናመቻች በአፅንዖት እናሳስባለን።
    7. ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ተፅእኖ ያላገገመው የኢኮኖሚ እንቀውሰቃሴ የአንበጣ መንጋ ጥቃት ተጨምሮበት ኅብረተሰባችን ምን ያህል ጉዳት ውስጥ እንደሚገኝ ለመገመት የሚከበድ አይደለም። በዚህ አስቻጋሪ ሁኔታ የተቀሰቀሰው ግጭት ሊፈጥር የሚችለውን ሰብዓዊ ቀውስ ከግምት ውስጥ በመክተት ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት፣ የእርዳታ ድርጅቶችና ታዋቂ ግለሰቦች ዜጎች ድጋፍ ሊያገኙ የሚችሉበትን መንገድ ከወዲሁ ታሳቢ በማድረግ እንዲንቀሳቀሱ ለማሳሰብ እንወዳለን።
    8. በተደጋጋሚ እንደገለፅነው የዜጎችን ደህንነትና ያለስጋት የመኖር መብት የማስከበር ቀዳሚ ኃላፊነት የመንግሥት ነው። መንግሥት በተደጋጋሚ ይህን ኃላፊነቱን መወጣት ሳይችል በመቅረቱ ዜጎች ውድ የሆነውን ሕይወታቸውን ሲያጡ ቆይተዋል። በሀገር ውስጥ የሚፈፀሙ በተለይም ማንነትን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች በማንም ይፈፀሙ በማን የማስቆም እና የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነት የመንግሥት በመሆኑ መንግሥት ከተጠያቂነት ነፃ ሊሆን አይችልም። ጠመንጃ ደግነው ጥይት ተኩሰው ሰው ከሚገድሉት ነብሰበላዎች እኩል እነዚህን ኃይሎች በተለያየ መንገድ የሚያበረታቱ ከጎናችሁ ነን የሚሉ በተለይም በተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያዎች እና በመደበኛ መገናኛ ብዙኃን ጭምር ንፁሃን ላይ ለሚደርስ ጥቃት ድጋፍ ሲሰጡ የሚታዩ ኃይሎች ላይ መንግሥት አስተማሪ የእርምት እርምጃ በመውሰድ እንዲያስቆም እናሳስባለን። ምንም እንኳን ሰላምን የማረጋገጥ ኃላፊነት በዋናነት የመንግሥት ቢሆንም መንግሥት ብቻውን የሚፈፅመው አይደለም። ማኅበረሰቡን ያላስተባበረ እና ያላካተተ የሕግ ማስከበር እርምጃ ውጤታማ እንደማይሆን በተደጋጋሚ ታይቷል። ስለሆነም መንግሥት የሚወስደው እርምጃ ውጤታማ እንዲሆን መላውን ማኅበረተሰብ ባሳተፈ መልኩ ከፖለቲካ ወገንተኝነት የፀዳ በየቀበሌው የፀጥታና አካባቢ ጥበቃ ሥርዓት እንዲዘረጋ ለማሳሰብ እንወዳለን። በተለይም መንግሥት በተደጋጋሚ በመግለጫ ጭምር የችግሩ አካል እንደሆኑ የሚገልፃቸው የመንግሥት ስልጣን ላይ ያሉ ግለሰቦችን ወደ ተጠያቂነት በማምጣት ራሱን እንዲያጠራ አፅንኦት ሰጥተን እናሳስባለን። ለዚህም ኅብረተሰቡን የመፍትሄው አካል ማድረግ ወሳኝ ነው። መንግሥት በቅርብ ጥቃት የተፈፀመባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ወደመደበኛ ሕይወታቸው የሚመለሱበት ሁኔታን በአፋጣኝ እንዲያመቻች እንዲሁም ሌላ ተጨማሪ ጥቃት እንዳይደርስ አስፈላጊውን ጥበቃ ማድረግ እንዳለበት ለማስታወስ እንወዳለን። ተመሳሳይ ማንነት ላይ ያተኮሩ ጥቃቶች ሊፈጸሙ የሚችሉባቸው ቦታዎችን አስቀድሞ በመለየት በልዩ ትኩረት ጥበቃ እንዲደረግም እናሳስባለን። በተለይም የክልል አስተዳደሮች በክልሉ ውስጥ የሚኖሩ ዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ የመጀመሪያ ኃላፊነት እንዳለባቸው ተገንዝበው አስፈላጊውን ዝግጅት እንዲያደርጉ እንጠይቃለን።
    9. ኢዜማ በክልል የተደራጀው ልዩ ኃይል በምንም መስፈርት ሕጋዊ ነው ብሎ እንደማያምን እና ለዴሞከራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ከፍተኛ ተግዳሮት እንደሚሆን በተደጋጋሚ መግለጹ ይታወሳል። ይህ አደረጃጀት በሀገር አንድነት ላይ ሊያስከትለው የሚችለው ተጨባጭ አደጋ ማሳያ በትግራይ ክልል ሰሞኑን የተከሰተው ክስተት አንዱ እና ዋነኛው ነው። በዘውግ ላይ የተመሠረተው የሀገራችን ፖለቲካ አንዱን የዘውግ ማንነት ከሌላው ለመከላከል ወይም ሌላውን ለማጥቃት በሚዋቀረው የልዩ ኃይል እየተደገፈ የሀገራችንን ሕዝብ ወደበለጠ ስቃይ እና የጭንቅ እየከተታት ይገኛል። ሕዝቡም እርስ በእርሱ በጠላትነት እንዲተያይ የሚያደርግ እኩይ አደረጃጀትም መሆኑን በተደጋጋሚ በተግባር ለማየት ችለናል። ስልዚህም በየክልሉ በስፋት የተደራጀውን ልዩ ኃይል ወደ ክልል መደበኛ ፖሊስ፣ የፌደራል ፖሊስ ወይንም የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የሚቀላቀልበትን አሠራር እንዲዘረጋ እንጠይቃለን።
    10. በሁሉም አካባቢ የምትገኙ የኢዜማ አባላት እና ደጋፊዎች በተለመደው ሥነ-ምግባር በየአካባቢያቹ ሰላም እና ደህንነትን ለማስከበር በንቃት ማኅበረሰቡን በማስተባበር እና ከፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር እንድትሠሩ እናሳስባለን።

    በመጨረሻም የሀገራችን ሰላም እና አንድነት በዘላቂነት የሚጠበቀው የሁሉም ዜጎች እኩል መብት የሚከበርበት እና ለሁሉም ዜጎች እኩል ዕድል የሚሰጥ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሲመሠረት እንደሆነ በፅኑ እናምናለን። የሀገራችን አንድነት እና ሰላም ተጠብቆ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲመሠረት ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሀገር አንድነት እና ሰላም ተባብረው ለመሥራት ፈቃደኛ እና ቁርጠኛ መሆን አለባቸው። ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የሀገር አንድነት እና ሰላም ላይ ተቀራርበው እንዲሠሩ የሚያስችል ከምር የሚወሰድ የውይይት መድረክ መዘጋጀት አለበት። ይህ ውይይት ላይ የሚሳተፉ የፖለቲካ ኃይሎች ግን ሁሉም የሕግ የበላይነትን እና የፖለቲካ ፓርቲዎች የፈረሙትን የቃልኪዳን ሰነድ የሚያከብሩ መሆን አለባቸው። የደህንነት እና የፍትህ ተቋማት ኃላፊነታቸውን በሚገባ መወጣት መቻላቸው በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሚደረገው ውይይት ውጤታማ እንዲሆን የማይተካ ሚና ይኖረዋል። በመሆኑም መንግሥት ኃይልን የመጠቀም ብቸኛ ስልጣኑን አረጋግጦ እውነተኛ እና ለውጥ ማምጣት የሚችል ውይይት እንዲጀመር መንገድ የመጥረግ ሥራውን በአፋጣኝ አጠናቆ ሁላችንም ትኩረታችንን ወደዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እንድናዞር አበክረን ጥሪ እናደርጋለን።

    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)
    ጥቅምት 26 ቀን 2013 ዓ.ም

    የሀገር ሰላምና አንድነትን ለማረጋገጥ የሚወሰደው እርምጃ በፍጥነት ተጠናቆ ትኩረታችንን ዴሞክራሲ ግንባታ ላይ እናድርግ!

    Anonymous
    Inactive

    ምዕራብ ኦሮሚያ የተፈጸመውን ግድያ በጽኑ እናወግዛለን
    የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)

    ከትላንት በስትያ ህዳር 1 ቀን 2020 [ጥቅምት 22 ቀን 2013 ዓ.ም] ምዕራብ ኦሮሚያ ውስጥ በዜጎች ላይ ግድያ መፈጸሙን ከመገናኛ ብዙሃን የሰማን ሲሆን፥ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ይህንን የግድያ ተግባር በጽኑ እያወገዘ፤ የተሰማውን ጥልቅ ሀዘንም ይገልጻል።

    መንግሥት ነኝ የሚለው አካል ከአሁን ቀደም እንደለመደው ይህንን ግድያ የፈጸሙት ህወሓት እና ኦነግ-ሸኔ ናቸው በሚል ገልጿል። ኦነግ-ሸኔ በሚል የሚታወቅም ይሁን በዚህ ስም እራሱን የሚጠራ ድርጅት ግን አላገኘንም። ለኢትዮጵያ ሕዝቦችም ይሁን ለዓለም ማኅበረሰብ በዚህ ስም የሚከሰሰው ድርጅት ማንነት ግልጽ አይደለም።

    ይህ የግድያ ድርጊት እና ሌሎች መሰል ድርጊቶች ሁሉም ነጻና ተዓማኒነት ባለው ገለልተኛ አካል በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጣርተው ለተጎጂዎችና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች፥ እንዲሁም ለዓለም ማኅበረሰብ ግልጽ እንዲሆኑ እንጠይቃለን። ከዚህ ባሻገር ሁሉም አካላት ሕዝቦችን የሚያጋጩና በብሔሮች መካከል መጠራጠርን የሚፈጥሩ ማናቸውንም ዓይነት መረጃ ከማሰራጨት እንዲቆጠቡ መልዕክታችንን እናስተላልፋለን።

    በመጨረሻም ዜጎችን ለከፋ አደጋ እያጋለጠ ያለው ቀውስና የደህንነት ችግር ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት መፍትሄ ካልተበጀለት፥ ይበልጥ እየተባባሰ እንደሚሄድ ኦነግ በመግለጫው ሲያሳስብ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፤ አሁን እያየን ያለነውን አደጋ ለማስቀረት እና ኦሮሚያና ዜጎችን ከባሰ ቀውስ ለመታደግ ያለው ብቸኛው መፍትሄ የኦሮሚያ ሽግግር መንግሥት ማቋቋም በመሆኑ ሁሉም ዜጋ ድርሻውን እንዲወጣ ጥሪያችንን በድጋሚ እናድሳለን።

    በድጋሚ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) በምዕራብ ኦሮሚያ በዜጎች ላይ የተፈጸመውንና ካሁን ቀደምም በተመሳሳይ መልኩ የተፈጸሙ ግድያዎችን ሁሉ በጥቅብ እንደሚያወግዝ እያሳሰበ፥ ለሟች ቤተሰቦችና ዘመዶች እንዲሁም ሰላም ወዳዶች ሁሉ መጽናናትን ይመኛል።

    ድል ለሰፊው ሕዝብ!
    የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)
    ህዳር 3 ቀን 2020 ዓ.ም

    ምዕራብ ኦሮሚያ የተፈጸመው ግድያ

    Anonymous
    Inactive

    ንጹሃን ዜጎችን በማንነታቸዉ በጅምላ ማጥቃት የሽብር እንጂ የፖለቲካ ትግል ሊሆን አይችልም
    ብልጽግና ፓርቲ

    ባለፉት ሁለት ዓመታት ተኩል በሀገራችን እዉነተኛ የዲሞክራሲ ሥርዓት ሽግግር ለማደረግ የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋትን ጨምሮ በርካታ ተግባራዊ እርምጃዎች ሲወሰዱ መቆየታቸዉ ይታወሳል።

    በዚህም በሀገራችን ሕዝቦች ዘንድ ትልቅ ተስፋና መነቃቃት መታየት የጀመረ ሲሆን ሀገራችን በሰላማዊ፣በሰለጠነና በሰከነ የፖለቲካ አስተሳሰብ በሚመራ ነጻ፣ፍትሃዊና ገለልተኛ ምርጫ ወደ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ልትሸጋገር እንደምትችን የተስፋ ብርሃን የታየበት የፖለቲካ ሪፎርም ሲካሄድ መቆየቱ አይዘነጋም።

    ይሁን እንጂ ሰላማዊና የሰለጠነ የፖለቲካ ስርዓት የማይዋጥላቸዉና ግድያን፣ ማፈናቀልን፣ ንብረት ማዉደምንና ንጹሃን ዜጎችን ማሸማቀቅን እንደ ዋነኛ የስልጣን ምንጭ አድርገዉ የሚንቀሳቀሱ የኢትዮጵያን መረጋጋትና የዜጎቿን ሰላም የማይፈልጉ ሃይሎች ቅንጅት በመፍጠር ምንም ዓይነት የፖለቲካ ወገንተኝነት የሌላቸዉን ንጹሃን ዜጎች በማንነታቸዉ ብቻ ኢላማ በማድረግ ጥቃት በማደረስ ላይ ይገኛሉ።

    በዚህ እኩይና ጭካኔ የተሞላበት አረመኔያዊ የጥፋት ተግባራቸዉ ባለፉት አመታት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የዜጎች ህይወት እንዲጠፋ፣ አካል እንዲጎድል፣ ንብረት እንዲወድምና ዜጎች የሰላም ስሜት እንዳይሰማቸዉ ሲደረግ ቆይቷል።

    በተለይም ሰሞኑን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል ዞን እና በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በቤንች ሸኮ ዞን በጉራ ፈርዳ ወረዳ የበርካታ ንጹሃንን ህይወት የቀጠፈ ጨካኝ የሽብር ተግባር ተፈጽሟል።

    የንጹንን ደም በማፍሰስ ስልጣን መያዝን ካልሆነም አገርን መበታተንን ዋነኛ ዓላማቸዉ አድርገዉ ከሚነቀሳቀሱ ቡድኖች መካከል አንዱ የሆነዉ ኦነግ ሸኔ የተባለዉ አሸባሪ ቡድን በሀይል ወደ ስልጣን ለመመለስ ከሚፈልጉ ካልተሳካላቸዉም ኢትዮጵያን ለመበታተን ሌት ተቀን ከሚሰሩ ተቀናጅተዉና በትጥቅ ተደግፈዉ በትናንትናዉ ዕለት ማታ [ጥቅምት 22 ቀን 2013 ዓ.ም] በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ ጋዋ ጋንቃ በተባለዉ ቀበሌ ባደረሱት ጥቃት የዜጎች ህይወት ያለፈ ሲሆን በርካታ የአካል ጉዳትም ደርሷል።

    ይህ የሽብር ጥቃት ፍጹም ሰላማዊ በሆኑ ንጹሃን ዜጎች ላይ የተቃጣ መሆኑ አጥፊ ቡድኑ የሚከተለዉ መንገድ ምን ያህል ያልሰለጠነ፣ ኋላ ቀርና ጭካኔ የተሞላበት መሆኑን ለአለም ሕዝብ ያጋለጠበት ነዉ።

    በዚህ አረመኔዊ ተግባር ህይወታቸዉን ላጡ ዜጎቻችን የተሰማንን ጥልቅ ሃዘን እየገለጽን ለተጎጂዎች ቤተሰቦችና ወዳጅ ዘመዶች እንዲሁም ለመላዉ ኢትዮጵያዊያን መጽናናትን እንመኛለን።

    መንግሥት እነዚህን ነብሰ ገዳዮች ከያሉበት አድኖ ሕጋዊ እርምጃ የሚወስድ መሆኑን እያረጋገጥን የፓርቲያችን አመራሮች፣ አባላት፣ ደጋፊዎችና መላዉ የሀገራችን ሕዝቦች የንጹሃን ዜጎችን ህይወት ያጠፉና አካል ያጎደሉ ሽብርተኛ ቡድኖችን አድነን እርምጃ በመዉሰድ የህግ የበላይነትን ለማስከበርና ህብረ-ብሄራዊ ፌዴራላዊ አንድነታችንን ለማስቀጠል በምናደርገዉ እርምጃ ዉስጥ ከጎናችን በመሆን አስፈላጊዉን ትብብርና ድጋፍ እንድታደርጉልን ጥሪያችንን እናቀርባለን።

    ብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽ/ቤት
    ጥቅምት 23 ቀን 2013 ዓ.ም

    ንጹሃን ዜጎችን በማንነታቸዉ በጅምላ ማጥቃት

    Anonymous
    Inactive

    የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በአማራ ክልል ከተሞች እና በአዲስ አበባ ታላልቅ ሰለማዊ ሰልፎችን ለማድረግ ጥሪ አደረገ

    የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በአማራ ክልል ከተሞች እና በአዲስ አበባ ታላልቅ ሰለማዊ ሰልፎች እንደሚደረጉ አስታውቋል። አብን ስለሰላማዊ ሰልፎቹ እና በአጠቃላይ በአማራ ሕዝብ ላይ ከዕለት ወደ ዕለት ያልተቋረጠ በደል እየደረሰበት መሆኑን ያመላከተበት ትንታኔ የሚከተለውን ይመስላል።

    ለመላው የአማራ ሕዝብ፣
    ለንቅናቄያችን አባላትና ደጋፊዎች፣
    ለመላው ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በሙሉ !

    የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) መንግሥታዊና ሥርዓታዊ ጭቆና እና የዘር ጥቃት ያንዣበበትን የአማራን ሕዝብ ከህልውና ስጋት ለመታደግና በነፃነት፣ በእኩልነት፣ በፍትህና በወንድማማችነት የሚኖርባት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት የቆመ ድርጅት ነው።

    አብን ባለፉት ሁለት ከመንፈቅ ዓመታት ሕዝባችን በከፍተኛ መስዋዕትነት ያስገኘው የለውጥ ተስፋ እንዳይመክን፣ በትግላችን የተንበረከኩ አማራ-ጠል ኃይሎች ዳግም እንዳያንሰራሩና የሀገር እና የሕዝብ ህልውና በድጋሚ አደጋ ላይ እንዳይወድቅ እልህ አስጨራሽ ትግል አድርጓል። የአማራ ብሔርተኝነት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ አዎንታዊ የመረጋጋት፣ የመቻቻልና የግንባታ ሚና እንዲኖረው ያልተቆጠበ ጥረት አድርጓል።

    ይሁን እንጂ ተስፋ የተጣለበት “ለውጥ” እያደር መስመሩን በመሳቱ አዲሱ አገዛዝ የአምባገነንነትና የአንድ ቡድን ፍላጎት አስፈፃሚነት አዝማሚያ ማሳየቱ ገሃድ ወጥቷል። በተለይም በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈፀመው የዘር ጥቃት እየተባባሰና አድማሱን እያሰፋ በቅርቡ እንኳን በኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና በደቡብ ጉራ ፈርዳ ተከታታይ ለሆኑ የጅምላ ጭፍጨፋዎች፣ የዘር ማጽዳትና የማፈናቀል ጥቃቶች ሰለባ ሆኗል።

    አብን በሕዝባችን ላይ ስልታዊ፣ የተደራጀ፣ ሰፊ የመገናኛ ብዙኃን ቅስቀሳ የተደረገበት ዘመቻና በመንግሥት መዋቅር ጭምር የተደገፈ የዘር ማጥፋት እየተፈፀመበት መሆኑን በመግለጽ መንግሥት ችግሩን እንዲያስቆም በተደጋጋሚ ወትውቷል። እንደ ሕዝብም መቻቻልና ሀገር ወዳድነት ትርጉም እስኪያጡ ድረስ ታግሰናል። ነገር ግን ብልፅግና-መራሹ መንግሥት የሕዝባችንን ሆደ-ሰፊነትና አስተዋይነት እንደ ዓይነተኛ ድክመት በመቁጠር፥ ንቅናቄያችን ለሀገር ህልውና ሲባል የሰጠውን ይሁንታ በሰፊው በማጓደል ዛሬም አማራው መንግሥት-አልባ ሕዝብ መሆኑን አረጋግጦልናል።

    አብን በሕዝባችን ላይ ለሚደርሰው ጥቃት ቀንደኛው ተጠያቂ ማዕከላዊ መንግሥት መሆኑን ያምናል። መንግሥት ‹‹የወንጀሎች ሁሉ ወንጀል›› የሚባለውን የዘር ማጥፋትን በመከላከል፣ በማስቆምና ዘላቂ መፍትሄ በመፈለግ ረገድ የረባ ሚና አልተጫወተም። እንዲያውም የዘር ጥቃቶችን “ግጭት” እያለ ለማድበስበስ፣ መረጃዎችን ለማፈንና ሰለባዎችን ጭምር ለመወንጀል ተደጋጋሚ ጥረቶችን ሲያደርግ ተስተውሏል። መንግሥት በአማራ ላይ የተፈፀሙ የዘር ጥቃቶች ልዩ ጠባሳ የሆነውን የጉራ ፈርዳ ጥቃት መሪ አቀናባሪ የነበረውን ግለሰብ ለዳግም ሹመት የመምረጡን አንድምታ እንረዳለን፤ አሁን የሚፈፀመውን ካለፈው የሚያስተሳስር ረጅም ክር አለው።

    በሁለተኛ በአማራ ሕዝብ ላይ የዘር ፍጅት በተፈፀመባቸው ክልሎች ያሉ መንግሥታት በተለያየ ደረጃ ኃላፊነታቸውን ካለመወጣት አልፈው፥ በቀጥታና በተዘዋዋሪ በሕግ፣ በመዋቅር፣ በመሣሪያና በገንዘብ ጥቃቶችን መደገፋቸውና ማቀናበራቸው በገሃድ ይታወቃል። ከጥቃቱም በኋላ የየክልሎቹ የብልፅግና ፖርቲ አመራሮች በሕዝባችን ላይ በየፊናቸው በማንአለብኝነት የሚያደርጉት ዛቻና ማስፈራሪያ በድርጊቱ አለመጸጸታቸውንና ችግሩን ለማረም ፈቃደኝነት እንደሌላቸውም ያረጋግጣል።

    ሦስተኛው ተጠያቂ “የአማራ ብልፅግና” የሚባለው ነው። ለአማራ ሕዝብ ብልፅግናውን ቀርቶ ህልውናውንም ሊያስጠብቅለት አልቻለም። ቀድሞ ከነበረው አጠቃላይ አቋም መሻሻል አላሳየም። ንቅናቄያችን አማራው እንደ ሕዝብ በአንድነት እንዲቆም ለማስቻል ለሁለት ዓመታት ያክል “የአማራ – ብልፅግናን” ለማግባባት ያደረገው ሰፊ እና ያላሰለሰ ጥረት ፍሬ አላፈራም። የአማራ ሕዝብንም፣ አብንንም በተደጋጋሚ ያሳዘነ ሲሆን፤ ከታሪክ ተጠያቂነትም አያመልጥም።

    አብን በማዕከልም ሆነ በክልል ያሉ መንግሥታት የተጫወቱት አፍራሽ ሚና ውጤቱ በአማራው ሕዝብ ተገድቦ እንደማይቀር በውል እንዲጤን ይሻል። መንግሥት መሠረታዊ መብቶቹን የማያስጠብቅለትን ሕዝብ ማናቸውንም የሞራልም ሆነ የሕግ ግዴታ ሊጥልበት አይቻለውም። በሕዝብና በመንግሥት መካከል ያለው ማኅበራዊ ውልም ክፉኛ ይናጋል።

    አብን በአማራው ላይ የሚደረገው የዘር ማጥፋት ድርጊት ዞሮ ኢትዮጵያን እንደሀገር ዋጋ እንደሚያስከፍልም ይገነዘባል። ንቅናቄያችን እስካሁን የአማራ ሕዝብ በኢትዮጵያዊነት ተስፋ እንዲቆርጥና ወደ አመፅ እንዲያመራ የሚደረገውን አሉታዊ ጥረት ሲታገል ቆይቷል። ሆኖም ከእንግዲህ ወዲያ የሕዝባችን ህልውና በምንም መልኩ ለድርድር እንደማይቀርብ ለማረጋገጥ ይወዳል።

    አብን የአማራ ሕዝብ ሆደ ሰፊና አስተዋይ በመሆኑ ተፈጥሯዊ መብቱንና ነፃነቱን በልቅሶና በልመና ሳይሆን በተደራጀ ትግል እንደሚያስከብር ይተማመናል። ይህን ታላቅ ታሪካዊ ኃላፊነት በመምራት ከግብ ለማድረስ ድርጅታችን ቁርጠኝነቱን ያረጋግጣል።

    አብን መንግሥት ችግሩን በአስቸኳይ ከማስቆም በተጨማሪ ጥቃቱን እንዲያምንና በስሙ እንዲጠራ፣ ጉዳዩን የሚያጣራ ገለልተኛ አካል በፍጥነት እንዲሰይም፣ ወንጀለኞችን አጣርቶ ለፍርድ እንዲያቀርብና ለተጎጂዎችም ተገቢውን ካሳ እንዲከፍል በጥብቅ ይጠይቃል። ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት መሠረታዊ ምንጭ የሆነው አማራ-ጠል ሕገ-መንግሥት የሚሻሻልበትን አግባብ በአስቸኳይ እንዲያመቻች ይጠይቃል።

    አብን መንግሥት የሀገሪቱን ሰላምና ደህንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ማስከበር አለመቻሉንና በተደጋጋሚ የአማራ ተማሪዎችን ደህንነት ለመጠበቅ ችላ ማለቱን በማጤን ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ያደረገው የትምህርት መጀመር ጥሪም ያሳስበዋል። ብዙ ሽህ የአማራ ተማሪዎች በፅንፈኞች ጥቃት ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው ሲፈናቀሉ፣ ሲገደሉ፣ ሲደበደቡና ሲታገቱ በአሳፋሪ ሁኔታ አልታደጋቸውም። አሁንም ለተማሪዎች አስተማማኝ ጥበቃ እንዲያደርግ በጥብቅ እንጠይቃለን።

    የአብን ብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በጥቅምት 14 እና 15 ቀን 2013 ዓ.ም ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ በወሰነው መሠረት በሀገራችንና በሕዝባችን ላይ ያንዣበበውን ከፍተኛ የደህንነት ስጋት በመቀልበስ፤ የሕዝባችንን ህልውና ለማረጋገጥ የሚያደርጋቸውን ሰላማዊና ሕጋዊ የትግል ጥረቶችና ስልቶች ለሕዝባችን ለማሳወቅ የፊታችን ረቡዕ ጥቅምት 18 በአማራ ክልል ከተሞች፤ እሁድ ጥቅምት 22 በአዲስ አበባ ታላላቅ ሕዝባዊ ትዕይንቶች ይደረጋሉ።

    በእነዚህ ሰልፎች ላይ መላው የአማራ ሕዝብ ማናቸውም ልዩነት ሳይገድበው እንዲሳተፍ፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የአማራ የፖለቲካ ኃይሎች፣ የተለያዩ የአማራ የሲቪክ አደረጃጀቶች በወገናችሁ ላይ የሚደርሰውን ግፍና በደል እንድትቃወሙ ጥሪ እናደርጋለን።

    አብን በአማራ ክልልና በአዲስ አበባ የተጠሩት የተቃውሞ ሰልፎች ፍፁም ሰላማዊ እንዲሆኑና ሊከተሉ የሚችሉ አላስፈላጊ ረብሻዎችንና ጥቃቶችን ለማስቀረት ሕዝቡ የራሱን ደህንነት በንቃት እንዲጠብቅ ያሳስባል።

    ሰልፉን በተመለከተ ዝርዝር ጉዳዮች፣ በሰልፉ ላይ የሚተላለፉ መልዕክቶችና መፈክሮች በማዕከል ተዘጋጅተው በፓርቲያችን ይፋዊ ገፅ የሚለጠፉትና ለየአካባቢው የሚላኩት ናቸው።

    ጉዳዩ የሕዝብ ህልውና ጥያቄና የራሱ ሰልፍ በመሆኑ የሀገር መከላከያና አጠቃላይ የደህንነት ኃይሉ የሕዝቡ ሰልፍ የተሳካ እንዲሆን ተገቢውን የፀጥታ ሥራ እንዲያከናውን ጥሪ እናደርጋለን።

    በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ አማሮች እሁድ ጥቅምት 22 ቀን 2013 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከሚደረገው ሰልፍ ጋር በተለያዩ ክፍለ ዓለማት ድምፃችሁን እንድታሰሙ አብን ጥሪውን ያቀርባል።

    ሰልፉ ለኮቪድ-19 ወረርሽኝ በማያጋልጥ መልኩ በጥንቃቄ እንዲካሄድ እያሳሰበ፥ ሕዝባችን በየአካባቢውና በየቤተሰቡ በገጠመን ፅኑ ወቅታዊ ችግር ላይ ውይይት እንዲያካሂድ፤ በቀጣይም ዘላቂ መፍትሄ ለማፈላለግ አብን ዓለምአቀፍ የመላው አማራ ሕዝባዊ ውይይት መድረኮችን እንደሚያመቻች መግለጽ ይወዳል።

    በአዲስ አበባም ሆነ በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈፀመው የማናለብኝነትና የተረኝነት አካሄድ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ጉዳት በመሆኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ በወንድሙ በአማራው ሕዝብ ላይ የሚፈፀመውን ግፍና በደል በመቃወም አብሮ እንዲሰለፍ አብን ጥሪውን ያቀርባል።

    አብን ከእንግዲህ ጉዳዩ የማያዳግም እልባት እስከሚያገኝ ድረስ ማናቸውንም የሰላማዊ ትግልና የሕዝባዊ እምቢተኝነት ስልቶችን በየደረጃው የሚተገብር በመሆኑ ሕዝባችን ከወዲሁ እንዲያውቀውና ወትሮ ዝግጁ እንዲሆን ጥሪያችንን እናቀርባለን።

    አንድ አማራ ለሁሉም አማራ ፥ ሁሉም አማራ ለአንድ አማራ!
    የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)
    ጥቅምት 16 ቀን 2013 ዓ.ም
    ሸዋ፥ አዲስ አበባ፥ ኢትዮጵያ!

    የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)

    Anonymous
    Inactive

    በእነ እስክንድር ነጋ ኢ-ፍትሃዊ እስር ላይ የተሰጠ መግለጫ

    የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ጥቅምት 12 ቀን 2013 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ የእነ እስክንድር ነጋ የክስ ሂደትን አጀንዳ በማድረግ አስቸኳይ ስብሰባ አካሂዷል። ፓርቲው እስክንድር ነጋ (ሊቀ መንበር)፣ ስንታየሁ ቸኮል፣ ቀለብ ስዩም እና አስካለ ደምሌ በምንም ዓይነት የሚያስከስስ ወንጀል ጉዳይ እንዳልተሳተፉ እና ንጹሃን መሆናቸውን ከዚህ በፊት መግለጹ ይታወቃል፤ ይልቁንም የፍትህ ሥርዓቱን መጠቀሚያ በማድረግ በቀጣዩ [ሀገራዊ] ምርጫ ጠንካራ ተፎካካሪ የሚሆኗቸውን እነ እስክንድር ነጋ እና ፓርቲያቸውን ለማጥቃት ታስቦ እንደሆነ ገልጸናል። ይህንን አቋማችንን የበለጠ የሚያጠናክርልን ሁለት ነገሮች ደግሞ በጥቅምት 12 ቀን  የችሎት ውሎ ታዝበናል፦

    1ኛ. ዐቃቤ ሕግ ከዚህ በፊት ያሰማውን የምስክሮች ቃል በመተው እንደገና 21 (ሀያ አንድ) ምስክሮች ማንነታቸው ሳይገለጽ ከመጋራጃ ጀርባ እንዲሰሙ እና በዝግ ችሎት እንዲደመጡ ጥያቄ ማቅረቡ ላይ እየተደረገ ያለው የፍትህ አሰጣጡን የሚያዛባ እና የሚያጓትት ሂደት፤

    2ኛ. የሚሰጡ ቀጠሮዎች (በተለይም አዳዲስ ዳኞች እንደተሾሙ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ በፓርላማም ከተናገሩ በኋላ) ረጅም መሆናቸው ሂደቱን በማጓተት እነ እስክንድር ነጋ ሳይፈረድባቸው በእስር እንዲቀጡ የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ በዚህ ዓመት በሚደረገው ምርጫ ከክሱ ነጻ ቢባሉ እንኳን እንዳይሳተፉ የሚያደርግ ሆኖ አግኝተነዋል።

    እነዚህ እና መሰል ጉዳዩች በክስ ሂደቱ ላይ የአስፈጻሚው አካል ረጅም እጆች እንዳሉበት የሚያስረዱ ሆነው አግኝተናቸዋል። ከዚህም በመነሳት ፓርቲያችን መሪዎቻችን ትክክለኛ ፍትህ፣ ሳይዘገይ ያገኛሉ የሚል እምነት እንዳይኖረን አድርጎናል። ስለሆነው ፓርቲያችን የኦህዴድ/ብልጽግና ፖለቲካ ዓላማ ለማሳካት በማሰብ በሀሰት በተቀነባበረ ክስ የተያዙ አመራሮቻችንን ለማስፈታት ከዚህ በፊት ሲያደርገው ከነበረው ትግል በተለየ እና በበለጠ ሁኔታ ውጤታማ የሚያደርጉ የትግል መንገዶችን ነድፎ በሥራ ላይ ያውላል። መላው የፓርቲያችን አባላት እና ፍትህ ወዳጅ ሕዝባችን በቀጣይ ይፋ ለምናደርጋቸው የትግል እንቅስቃሴዎች እንደከዚህ ቀደሙ እራሱን እንዲያዘጋጅ እና ለነጻነት በሚደረገው ትግል ንቁ ተሳታፉ እንዲሆን ጥሪያችንን እናቀርባለን።

    ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ)
    አዲስ አበባ
    ጥቅምት 13 ቀን 2013 ዓ.ም

    ምንጭ፦ ባልደራስ
    ——
    ሌሎች ተመሳሳይ ዜናዎች፦

    በእነ እስክንድር ነጋ ኢ-ፍትሃዊ እስር ላይ የተሰጠ መግለጫ

    Anonymous
    Inactive

    ከኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) በወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታዎች ላይ የተሰጠ የአቋም መግለጫ

    የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ሀገራዊ ምክር ቤት አንደኛ ዓመት ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባዉን ከመስከረም 29 ቀን እስከ ጥቅምት 1 ቀን  2013 ዓ.ም ሲያካሂድ በወቅታዊ የኢትዮጵ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የሰላም መደፍረስ ጉዳዮች ላይ በስፋትና በጥልቀት መክሯል፤ ፓርቲው የሚተገብራቸውን የተለያዩ መመሪያዎች፣ እንዲሁም የ2013-2017 ዓ.ም የፓርቲዉን የአምስት ዓመት ስልታዊ ዕቅድና የ2013 ዓ.ም የአንድ ዓመት ዕቅድ በስፋት እና በጥልቀት በመመርመር ወደተግባር እንዲገቡ በሙሉ ድምጽ ዉሳኔ ካሳለፈ በኋላ የሚከተሉትን የአቋም መግለጫዎች አዉጥቷል።

    1. ሁሉንም ተግባራት ማከናወን የሚቻለዉ በሀገሪቱ አራቱም ማዕዘኖች ሰላም ሲኖርና የሕግ የበይላነት ሲከበር መሆኑ ለሁሉም ግልጽ ነዉ፤ ነገር ግን በመላ ኢትዮጵያ ሀገሪቱን ለ27 ዓመታት ሲዘርፍና የዜጎችን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በመንፈግ እንደፈለገ ሲያስር ሲገድልና ሲያኮላሽ የነበረዉ ዘረኛዉ ህወሓት ከጠቅላይ አምባገነንቱ ተባሮ መቀሌ ከመሸገበት እና በዶ/ር ዐቢይ አህመድየሚመራዉ “የለዉጡ ቡድን” መንግሥታዊ ስልጣን ከተቆናጠጠበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ ሁነቶች ተከስተዋል። በሀገራችን ኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታ እጅግ ዘግናኝ ግድያዎችና የዘር ማጥፋት ወንጀሎች ነፍስ ባላወቁ እምቡጥ ሕፃናት ሳይቀር በጽንፈኛ ብሔርተኞችና እነሱ በሚደግፏቸዉ ታጣቂ ቡድኖች፤ በኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ (በተለይ በመተከል በተደጋጋሚ) እንዲሁም በደቡብ ክልሎች እስካሁን ድረስ እየተፈጸሙ ነዉ። ዜጎች በገዛ ሀገራቸዉ እንደሁለተኛ ዜጋ እየታዩ ሀብት ንብረታቸዉ እየተዘረፈና እየወደመ፣ ከመኖሪያ ቀያቸዉ እየተፈናቀሉ ነዉ። ኢሕአፓ ከዚህ በፊት ባወጣቸዉ ተደጋጋሚ አቋሞቹ እንደገለጸዉ፥ መንግሥት የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ያሳየዉ ቸልተኝነትና መዘግየት እነዚህ ሁሉ ዘግናኝ ድርጊቶች እንዲፈጸሙ በር እንደከፈተ ያምናል። ስለዚህ ሉዓላዊነታችንንና የሕግ የበላይነትን የማስከበር፣ ሀገራዊ ሰላምን የማረጋገጥ እና የዜጎችን ደህንነነት የመጠበቅ ኃላፊነት ያለባቸዉን የተለያዩ የጸጥታ መዋቅሮች የሚመራዉ መንግሥት ስለሆነ፥ አሁን የጀመረዉን ሕግ የማስከበር ሥራ አጠናክሮ እንዲቀጥል፣ በአጥፊዎችም ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወስድ፣ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በተለይም በቤኒሻንጉልና በኦሮሚያ መሽገው የዜጎችን ህይወት የሚቀጥፉ ሕገ-ወጥ ታጣቂ ቡድኖች ላይ ትጥቅ የማስፈታት እና ወደሕግ የማቅረብ፤ በወንጀል ድርጊት ያልተሳተፉትን አጣርቶ ወደ ሰላማዊ ኑሯቸዉ እንዲመለሱ የማድረግ የማያዳግም እርምጃ እንዲወስድ ይጠይቃል፤ ፓርቲያችን ኢህአፓም ጸረ-ሰላም ኃይሎችን በጽናት ይታገላል።
    2. በሀገራችን ኢትዮጵያ ላለፉት በርካታ ዓመታት የሚፈጸሙት ዘግናኝ የሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች መጣስ መንስዔው በዋነናት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግሥት ስለመሆኑ በተደጋጋሚ ተገልጧል። ከሁለት ዓመታት በፊት፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አስተዳደርም ሕገ-መንግሥቱን ለማሻሻል በተደጋጋሚ ቃል ገብቶ እንደነበረ ይታወቃል። ነገር ግን ያ ሁሉ ቃል-ኪዳንና ያ ሁሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ወደጎን ተትቶ፥ በፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድርና ውይይት ወቅት ይታያል ተብሎ የነበረው ሕገ-መንግሥት ምንም ዓይነት ማሻሻያም ሆነ ማስተካከያ ሳይደረግበት ከሃያ አምስት ዓመታት በላይ ለሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ሁሉ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ዋነኛው መንስዔ እንደሆነ አለ። ኢሕአፓ ኢትዮጵያ ውስጥ በገዢው ፓርቲና በአጋሮቹ ለሚፈጸሙት ግፎች ሁሉ የመጀመሪያው ተጠያቂ ይህ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግሥትና ይዘቱ ስለሆነ አስቸኳይ ማሻሻያ እንዲደረግበት መንግሥትን ይጠይቃል።
    3. በተጨማሪም፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር በተደጋጋሚ ይደረጋል እያለ ቃል ሲገባ የነበረው የብሔራዊ ዕርቅና የሀገራዊ መግባባት አጀንዳ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ አጀንዳ እንደሆነ ኢሕአፓ ጽኑ እምነት አለው። በኢትዮጵያ የሚገኙት ሕጋዊና ሰላማዊ የሆኑት የፖለቲካ ኃይሎች በሙሉ የሚሳተፉበት፣ ሀገራዊ መግባባትን ትኩረቱ ያደረገ የፓርቲዎችና የሲቪክ ማኅበራት የጋራ መድረክ አስፈላጊነት ሳይታለም የተፈታ በመሆኑ፥ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መንግሥት ለዚህ አጀንዳ ቅድሚያ ሰጥቶ የውይይትና የድርድር መድረኩ በአፋጣኝ እንዲካሄድ ኢሕአፓ ጥሪውን ያስተላልፋል።
    4. በያዝነው የ2013 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ይካሄዳል የተባለውና የሚጠበቀው 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ሕጋዊና ሰላማዊ ሆኖ እንዲተገበር ኢሕአፓ ከፍተኛ የሆነ ፍላጎት አለው። በመሆኑም፥ ምርጫ የአንድ ቀን ተግባር ሳይሆን የብዙ ወራትን የመደራጀትና የማደራጀት ተግባራት ከእያንዳንዱ የፖለቲካና የሲቪክ ማኅበር የሚጠይቅ ክንውን መሆኑ ግልጽ ነው። ሆኖም ግን ከ5ኛው ሀገራዊ ምርጫ ማግስት ጀምሮ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መንግሥት ሰላምንና ጸጥታን ማስከበር ተስኖት በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ውስጥ ሁከትና ብጥብጥ እየተከሰተ ይገኛል። በዚህ ያለመረጋጋትና የሰላም እጦት ውስጥ ሆኖ ምርጫን የሚያክል ከፍተኛ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማድረግም አጅግ አዳጋች ነው። በመሆኑም መንግሥት ሁሉም ዜጎች በሕግ ፊት እኩል የሚሆኑበትንና የሚዳኙበትን የፖለቲካ-ኢኮኖሚ ምህዳር አስፍቶ የዜጎችን በሕግ የበላይነት ሥር ብቻ የመምረጥና መመረጥ መብታቸውን እንዲያከናውኑ የማድረግ ኃላፊነቱን በተግባር እንዲወጣ ኢሕአፓ ጥሪውን ያስተላልፋል።
    5. በየጊዜዉ እያሻቀበ ያለዉ የዋጋ ግሽበትና በኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰት ምክንያት በከፍተኛ ደረጃ ቁጥሩ የጨመረዉ ሥራ አጥነት የዜጎችን የእለት ተእለት ኑሮ በሰቆቃ የተሞላ አድረጓል፤ ከዚህ በተጨማሪ ባሳለፍነዉ 2012 ዓ.ም በተከሰቱ ሰው-ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችም ለከፋ የርሀብ አደጋ ተጋላጭ ሆነዋል። በመሆኑም ኢሕአፓ መንግሥት በረዥም ጊዜ ለዜጎች በተለይም ለወጣቶች በርካታ የሥራ ዕድል መፍጠር የሚችሉ ሀገር በቀል ኢንቨስትመንቶችን እንዲያስፋፋ፣ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ እና ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርን በመቆጣጠር የዋጋ ግሽበቱን ከ2 ዲጂት በታች የሚወርድበትን የኢኮኖሚ አማራጭ እንዲተገበር፣ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸዉም ተገቢዉን ድጋፍ በወቅቱ እንዲያቀርብ በአጽንኦት ይጠይቃል።
    6. ከደንቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ወደ ትዉልድ ቀያቸዉ ሲመለሱ ታፍነዉ ተወስደዉ እስካሁን ድረስ ደብዛቸዉ የጠፋዉ ተማሪዎች ጉዳይ አሁንም ድረስ የኢሕአፓ የእግር እሳት ነዉ፤ ስለዚህ መንግሥት ልዩ ተኩረት ሰጥቶ ተማሪዎቹ እዉነት በህይወት ካሉ የማስመለስ ሥራ እንዲሠራ፥ አለያም እዉነቱን ለቤተሰቦቻቸዉ፣ ለኢትዮጵያና ለዓለም ሕዝብ እንዲያሳውቅ ኢሕአፓ የዘወትር ጥያቄዉን ዛሬም ያቀርባል።
    7. ኢሕአፓ ሕብረ-ብሔራዊ ፓርቲ እንደመሆኑ በኢትዮጵያ አንድነትና ሉአላዊነት፣ በሕዝቧ ዉህድ ማንንነት የማይጠራጠሩ፣ በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ትግል ለሚያምኑና በሕጋዊ መንግድ ለተደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሁሉ ኑ! ሀገራችን ከገባችበት ጽንፈኛ የጎሳ እና የጥላቻ ፖለቲካ ቅርቃር በጋራ እንታደጋት፤ ሀገራዊ ብሔራዊ መግባባትን በመፍጠርና የፖቲካ ቁርሾን በማስወገድ ዘላቂ ሰለማና እድገት የሰፈነባት ሀገር እናድርጋት፤ የሚል የአክብሮት ጥሪዉን ያስተላልፋል።
    8. በሀገር ቤትና በዉጪ ሀገር ለምትገኙ ቀደምት የኢሕአፓ አባላትና መሥራቾች ዘላለማዊ ከሆነዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ህላዌ ጋር በየጊዜዉ እየታደሰ የሚዘልቅ ዘመን ተሸጋሪ ሀሳብ ያነገበዉ ኢሕአፓ ከዉጪ ሀገር ወደ ሀርቤት ከገባ ጊዜ ጀምሮ በሀገሩ ምድር ላይ ትግሉን በጽናትና ቁርጠኝነት እያካሄደ መሆኑን ተገንዝባችሁ ፓርቲያችን ኢሕአፓን በተለያየ መንገድ በመደገፍና በማጠናከር የትግላችሁን ፍሬ ማፍራት እውን ታደርጉ ዘንድ ጥሪዉን ያስተላልፋል።

    ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!
    ኢሕአፓ ለተሻለ ነገ!

    የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)
    ጥቅምት 5 ቀን 2013 ዓ.ም
    አዲስ አበባ

    የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)

    Anonymous
    Inactive

    በአዳራሽ ስብሰባ ለማድረግ ፈቃድ ከልክሎ በአደባባይ ቢልቦርድ እንዲሰቀል እንዴት ፈቀዳችሁ?
    አቶ ግርማ ሰይፉ ማሩ

    “መስከረም 30 መአት ይወርዳል” ከሚሉት ጋር የማልስማም መሆኔን አስረድቻለሁ። መስከረም 30 በአዲስ አበባ ጎዳና ወጥተው የተመለከትኩት፥ በየአደባባዩ የተሰቀለው የማስታወቂያ ሰሌዳ (billboard) ግን አንድ ነገር አስታዋሰኝ። የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ አደራጅ ኮሚቴ (ኢሠፓአኮ) ማብቂያው ደርሶ፣ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ (ኢሠፓ) ሊመሠረት ዋዜማው ላይ በከተማቸን የምናየው መፈክር ሁሉ፥ “ከጓድ መንግሥቱ ኃይለማርያም አመራር ጋር ወደፊት!”፣ “ብልሁ፣ አስተዋዩ መሪ መንግሥቱ ኃይለማርያም…” ወዘተ… የሚሉ ነበሩ። አልቀረልንም… ከዝሆን እና አንበሳ ምረጡ ተባለና ዝሆን ተመረጠ፤ አለቀ ደቀቀ። ይህ በሁለት የአንድ ፓርቲ አባላት መካከል በሚደረግ ምርጫ ዝሆን ቢመረጥ፣ አንበሳ ወይም ሚዳቋ ብዙ ትርጉም የለውም። ኢሠፓ ያለውን መንግሥቱን መርጧል።

    ዛሬም ብልፅግናዎች ዐቢያቸውን “ብልሁ መሪ” የማለት መብታቸውን አከበራለሁ። ያላቸውን የመምረጥ መብት አላቸው። በአጠቃላይ ለሀገሩ እና ለከተማው ነዋሪ ይህን በግድ መጫን ግን መብታቸው አይደለም። በመጀመሪያ ደረጃ የምርጫ ቅስቀሳ ሳይጀመር ምርጫ ቅስቀሳ ማድረግ፣ ሌላውን በቢሮ ለሚደረግ ውይይት ፍቃድ ሰጪና ነሺ የሆነ መንግሥት፥ በትራፊክ መንገድ አዘግቶ “ዐቢይ ለዘላለም ይኑር!” መፈክር ተገቢና ትክክል አይደለም። ይህ መንገድ የመንግሥቱ ኃይለማርያም መንገድ ነው። ብልፅግና ኢሠፓአኮን/ኢሠፓን መሆን ካማረው ሕጉን ይለውጥና ምርጫ ቦርድን ዘግቶ መጫወት ይችላል። የሚከተለውን ለመቀበል መዘጋጀት ብቻ ነው የሚጠበቅበት።

    አስገራሚው ዛሬም በየቀበሌና ወረዳው በዚህ ደረጃ ወርደው የሚያዋርዱ ካድሬዎች መኖራቸው ነው። “ታላቁ መሪ መንግሥቱ ኃይለማርያም!”፣ “ታላቁ መሪ ዐቢይ አህመድ!” ብሎ ለመፃፍ ልብ የሚያገኙ ካድሬዎች እንዴት ነው ማፍራት የተቻለው? መክሸፍ ማለት ይህ ነው፤ ከታሪክ መማር ያለመቻል። የሀገርን መሪ በሕዝብ ድምፅ ቢቻል በቀጥታ ድምፅ ይሰጥ የምንለው አብዛኛው ይሁንታ የሰጠው እንዲመራን እንጂ፥ ካድሬ እንዳይመርጥልን ሰለምንፈልግ ነው። ዶ/ር ዐቢይ አህመድ የአዲስ አበባ ተመራጭ አይደሉም፤ በቀጣይ አዲስ አበባም የሚወዳደሩ ከሆነ በወረዳቸው ይህን ማድረግ ይቻላል። ግን ገና ለገና መስከረም 30 መንግሥት የለም ካሉት ጋር ብሽሽቅ ለመግባት የዚህን ያህል መውረድ አያስፈልግም። የዚህ ዓይነት ድርጊቶች ሳይቃጠል በቅጠል ካልተባለ፥ ምርጫ ሲጀመር በየወረዳው ኃላፊነት ላይ ያሉት የብልፅግና ሰዎች መላወሻ ሊከለክሉን ግድ አይሰጣቸውም። ይህ መስመር ግን በወረዳ የብልፅግና ካድሬዎችንም ቢሆን አይጠቅምም፤ አያኗኑርም ብሎ መመከር ደግ ነው።

    የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፣ ምርጫ ቦርድ፣ ወዘተ… በዚህ ዓይነት ጉዳይ ላይ የማረሚያ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል። የአዲስ አበባ መስተዳደር ለዚህ ጉዳይ ፈቃድ የሰጠ መሆኑን ጋዜጠኞች እባካችሁ አጣሩልን። ሥራችሁን ብትሠሩ ጥሩ ነው። ‘በአዳራሽ ስብሰባ ከልክሎ በአደባባይ እንዴት ፈቀዳችሁ?’ በሉልን፤ የዚህ ዓይነት ድርጊት “ብልግና” ነው በሏቸው።

    ግርማ ሰይፉ ማሩ

    አቶ ግርማ ሰይፉ ማሩ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) አመራር አባል (የብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ አባል) ሲሆኑ፤ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ፓርላማ) በቸኛው ተቃዋሚ አባል በመሆን አገልግለዋል።

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forums) ላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።

    አቶ ግርማ ሰይፉ ማሩ

    Anonymous
    Inactive

    የምንገኝበት የፖለቲካ ቀውስ፣ ፈጣን ፖለቲካዊ መፍትሔ ይፈልጋል!
    ከኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ሥራ አስፈፃሚ የተሰጠ መግለጫ

    በኢትዮጵያ ሕዝብ የረዥም ጊዜ መራራ ትግል 2010 ዓ.ም ላይ የመጣው ለውጥ ሕዝቡ ከነበረው ተስፋ በተቃራኒ የመክሸፍ አደጋ አጋጥሞታል።

    ከእንግዲህ በሀገራችን እውነተኛ ዴሞክራሲ እውን እንዲሆን፣ የዜጎች ሰብዓዊና ፖለቲካዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን፥ በእርግጠኝነት ደጋግሞ ቃል በመግባት ከፍተኛ የሕዝብ ድጋፍ አግኝቶ የነበረው የዶ/ር ዐቢይ አህመድ መንግሥት ለሕዝብ የገባቸውን ቃሎች ሁሉ በማጠፍ የለየለት አምባገነናዊ መንግሥት መሆን ጀምሯል።

    በዚህም ምክንያት የሀገራችንን ሰላምና መረጋጋት ክፉኛ የሚፈታተንና የሀገሪቱን አጠቃላይ ህልውና አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል ከፍተኛ የፖለቲካ ውጥረትና ቀውስ በሀገራችን ተከስቷል። በብዙ ዜጎች ከፍተኛ መስዋዕትነት የተገኘው ለውጥ መክሸፉና ሀገሪቱ ተመልሳ በሌላ አምባገነናዊ ሥርዓት ስር መውደቋ እጅግ ልብ የሚሰብር አሳዛኝ ክስተት ቢሆንም፥ የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ሀገራችንን ከውድቀት ለማዳን ዛሬም ዕድሉ በእጃችን ነው ብሎ ያምናል።

    ይህ ከውድቀት የመዳን እድል እውን ሊሆን የሚችለውም በአንድ ገዥ ፓርቲ የበላይነትና ፈላጭ ቆራጭነት፣ ወይንም ባለፉት 27 ዓመታት ያየነው ዓይነት ውጤቱ አስቀድሞ የሚታወቅ የይስሙላ ምርጫ በማካሄድ አይደለም።

    በኢዴፓ እምነት ከዚህ አሳሳቢ የህልውና አደጋ ወጥተን ወደ ተሻለ ሁኔታ ለመሸጋገር ቢያንስ የሚከተሉት አራት ተጨባጭ እርምጃዎች ሊወሰዱ ይገባል ብለን እናምናለን፤

    1. በሀገራችን የሕግ የበላይነት የመጥፋት ችግር እጅግ አሳሳቢ ወደ ሆነ የከፋ ደረጃ እየተሸጋገረ ነው። በኢዴፓ አመራር በአቶ ልደቱ አያሌው እና በሌሎችም የፖለቲካ ሰዎች ላይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሲሆን እንደታየው ሰዎች በፈጠራ ክስ ያለአግባብ የሚንገላቱበትና የፍርድ ቤቶች ውሳኔና ትዕዛዝ የማይከበርበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ያለ ፍርድ ቤት ነፃነት በአንድ ሀገር ላይ የሕግ የበላይነት ሊከበር ስለማይችል ፍርድ ቤቶችን ለፖለቲካ ጉዳይ ለመጠቀም፤ እና የፍርድ ቤቶችን ውሳኔ በመጣስ እየተፈፀመ ያለው ሕገ-ወጥ ድርጊት በአስቸኳይ መቆም አለበት።
    2. በአሁኑ ወቅት የኢዴፓ/አብሮነት፣ የኦፌኮ፣ የኦነግና የባልደራስ ከፍተኛ ዓመራሮች፣ እንዲሁም በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች /በተለይም በኦሮሚያ ክልል/ ከፖለቲካ ጋር በተያያዘ በእስር ላይ ስለሚገኙ በሀገራችን ከፍተኛ የፖለቲካ ውጥረት ነግሷል። ይህ አሳሳቢ ውጥረት ወደ ሌላ አሳሳቢ ደረጃ ከመሸጋገሩ በፊት ሁሉም ከፖለቲካ ጉዳይ ጋር በተያያዘ በእስር ላይ የሚገኙ ዜጎች ያለምንም ቅድመ-ሁኔታ በአስቸኳይ መፈታት አለባቸው።
    3. ሀገራችን በዚህ ዓይነት የፖለቲካ ውጥረት ውስጥ ሆና በፍፁም ሀገራዊ ምርጫ ለማካሄድ መታሰብ የለበትም። ከአሁን ጀምሮ እስከሚቀጥለው ሀገራዊ ምርጫ ድረስ ሀገሪቱ እንዴት ትተዳደር? ምርጫው ከመካሄዱ በፊት በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ ምን ዓይነት ውይይት እና ድርድር ይካሄድ? ከክልልነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ በደቡቡ የሀገራችን ክፍል ያለው የፖለቲካ ውጥረት እንዴት ይርገብ? ሀገሪቱ ቋሚ መንግሥት እስከሚኖራት ድረስ የኢኮኖሚ ደህንነቷን የሚያስጠብቅ ምን ዓይነት እርምጃ ሊወሰድ ይገባል? ያልለየለትን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭት በተመለከተ ምን ልናደርግ ይገባል? በሚሉትና በመሳሰሉ መሠረታዊ ጥያቄዎች ዙሪያ መፍትሄ ማመንጨት የሚያስችል አንድ ሁሉን አቀፍ የውይይትና የድርድር ሂደት /national dialogue / በአስቸኳይ መጀመር አለበት።
    4. በአሁኑ ወቅት በፌደራሉ መንግሥትና በትግራይ ክልል መካከል እየታየ ያለው ተገቢ ያልሆነና አሳሳቢ ፍጥጫ በአስቸኳይ መቆም አለበት። ጉዳዩ ከሀገሪቱ ሰላምና አንድነት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ እንደምታ ያለው እጅግ አሳሳቢ ጉዳይ በመሆኑ ያለምንም ቅድመ-ሁኔታ በውይይትና በድርድር መፈታት አለበት።

    በአጠቃላይ እነዚህ መሠረታዊ ጥያቄዎች በአግባቡ መመለስ ሳይችሉ ከቀሩና በሀገሪቱ ላይ የሚታየው ውጥረት የበለጠ ተባብሶ በዜጎችና በሀገር ላይ ለሚደርሰው ለማንኛውም የከፋ ጉዳት ዋናው ተጠያቂ ብልፅግና ፓርቲ መሆኑን እንገልፃለን። ከማንም በላይ የጉዳዩ እና የሀገሪቱ ባለቤት ሕዝቡ ነውና ከፍ ሲል የዘረዘርናቸው ጥያቄዎች በአስቸኳይ ተገቢ ምላሽ አግኝተው ሀገራችን ከውድቀት እንድትድን ሁሉም ሀገር ወዳድ ዜጋ በብልፅግና ፓርቲ ላይ ሕጋዊ እና ሰላማዊ ተፅዕኖ እንዲያደርግ ኢዴፓ ጥሪውን ያቀርባል።

    የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ
    ጥቅምት 3 ቀን 2013 ዓ.ም
    አዲስ አበባ

    የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ)

    Anonymous
    Inactive

    ሰላማችንን በማስጠበቅ እና ቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ ላይ በንቃት በመሳተፍ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠረት እንጣል!
    ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የተሰጠ መግለጫ

    ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ሊካሄድ የግዜ ሰሌዳ ወጥቶለት ሁሉም ባለድርሻ አካላት እንቅስቃሴ ከጀመሩ በኋላ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመታወጁ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያወጣውን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ እንዲሰርዝ መገደዱ ይታወሳል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በታወጀበት እና የምርጫ ሰሌዳው በተሰረዘበት ወቅት ወረርሽኙ በሌሎች የዓለማችን ሀገራት የጤና ሥርዓት ላይ ያስከተለውን ከፍተኛ ጫና እና በሰው ሕይወት ላይ ሲያደርስ የነበረውን ጉዳት በተጨባጭ በማየት የተለያዩ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ገደብ መደረጉ እና በዚህ ምክንያት ምርጫው መራዘሙ ተገቢ ነበር ብለን አምነናል።

    ምርጫው አለመካሄዱን ተከትሎ የመንግሥት ቀጣይነትን ለማረጋገጥ በተለያዩ ወገኖች የተለያዩ አማራጮች መቅረባቸው የሚታወስ ነው። የተለያዩ ፖለቲካ ፖርቲዎችም ከሕገ-መንግሥት ውጪ ያሉ አማራጮችን አቅርበው ነበር። ኢዜማ የመንግሥት ቀጣይነትን በሕጋዊ ማዕቀፍ ውስጥ መፍታት እንደሚቻል ጠቅሶ፥ አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ-መንግሥት ከሚሰጣቸው የመፍትሄ አማራጮች ውስጥ ደግሞ የመንግሥትን የሥልጣን ጊዜ እና ምርጫ የሚደረግበትን ጊዜ የሚደነግገውን የሕገ-መንግሥት አንቀጽ ከአቅም በላይ እና በድንገተኛ ምክንያት ምርጫ ማድረግ የማይቻልበት ሁኔታ ሲፈጠር የመንግሥትን ሥልጣን ከአንድ ዓመት ላልበለጠ ጊዜ ማራዘም እንዲያስችል አድርጎ ማሻሻል የተሻለ አማራጭ እንደሆነ ማቅረቡ ይታወሳል። ማሻሻያው ሥልጣን ላይ የሚቆየው መንግሥት የሥልጣን ጊዜ ገደብ ያስቀመጠ እና ውሳኔ የሚሰጥባቸው ጉዳዮች በቀጣይ ምርጫ አሸንፎ ሥልጣን የሚይዘው መንግሥት ላይ ግዴታ የማይጥሉ መሆናቸውን ባረጋገጠ መልኩ መሆን እንዳለበትም ምክረ-ሀሳብ አቅርበን ነበር።

    የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ክፍተቱን በሕገ-መንግሥት ትርጉም ለመሙላት ወስኖ የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ባቀረበው የውሳኔ ሀሳብ እና በፌደሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ምርጫውን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስጋት አለመሆኑ በጤና ሚኒስቴር እና የኅብረተሰብ ጤና ተቋም እስኪረጋገጥ ድረስ አራዝሞ የፌደራል እና የክልል መንግሥታት እና ምክር ቤቶችን የሥራ ጊዜ ያለገደብ እንዲቀጥል መወሰኑ ይታወሳል።

    ይህን ውሳኔ ተከትሎ ኢዜማ የጊዜ እና ውሳኔ የሚያሳልፍባቸው ጉዳዮች ላይ ወሰን ሳይደረግ ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት የሥራ ዘመን መራዘሙ ላይ ያለውን ተቃውሞ ገልፆ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለሕገ-መንግሥት አጣሪ ጉባዔ በገለጸው መሠረት አስፈላጊው ጥንቃቄ ተደርጎ ምርጫው መደረግ በሚችልበት ቅርብ ጊዜ እንዲደረግ ጠይቋል።

    በቅርቡ የጤና ሚኒስትር አስፈላጊው ጥንቃቄ እየተደረገ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ እንደሚቻል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባሳወቀው መሠረት ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ በያዝነው ዓመት እንዲካሄድ ውሳኔ ተላልፏል።

    ይህ በእንዲህ እያለ፥ “ሥልጣን ለማራዘም የተሄደበት መንገድ ሕገ-መንግሥታዊ አይደለም፤ በዚህም ምክንያት ከመስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም በኋላ መንግሥት የለም፤ ሕዝብ እና የመንግሥት መዋቅር ለፌደራል እና የክልል መንግሥታት ሊታዘዙ አይገባም» በሚል ቅስቀሳ ሲደረግ መቆየቱን እና አሁንም እየተደረገ እንደሚገኝ ለማስተዋል ችለናል

    ይህ ቅስቀሳ የሀገራችንን ሰላም እና መረጋጋት ከማወክ እና የዜጎችን ሕይወት አደጋ ላይ ከመጣል በዘለለ ፋይዳ እንደሌለው የኢትዮጵያ ሕዝብ በደንብ እንደሚገነዘብ እናውቃለን። ይህንን ቅስቀሳ እያደረጉ ያሉ አካላትም ከዚህ ተግባራቸው ተቆጥበው የጋራ ሀገራችን ሰላም እና የዜጎች ደህንነት ተጠብቆ በሰላማዊ መንገድ ችግሮቻችንን መፍታት ወደምንችልበት የውይይት መድረክ ከመምጣት ውጪ በሁከት እና በጉልበት ወደሥልጣን ለመውጣት የሚደረግ ማንኛውም እንቅስቃሴ ለራሳቸውም ቢሆን የማይጠቅም አደገኛ መንገድ መሆኑን ሊረዱ ይገባል። መንግሥትም እነዚህን ቅስቀሳዎች በንቃት እየተከታተለ አደጋ ከመድረሱ በፊት የመከላከል እና አደጋ ለማድረስ የሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ ሕጋዊ እርምጃ በመውሰድ የሀገር ሰላምን እና የዜጎችን ደህንነት የማስከበር ኃላፊነቱን እንዲወጣ እናሳስባለን።

    ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ዘንድሮ እንዲካሄድ የተወሰነውን ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ነፃ እና ፍትሃዊ ማድረግን ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባው እና ምርጫው እስከሚካሄድ እና የሕዝብ ድምፅ ያገኘው ተለይቶ እስከሚታወቅ ድረስ የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ፣ የሀገር ሉዓላዊነትን ማስከበር እና ምርጫውን ነፃ እና ፍትሃዊ ከማድረግ ጋር በቀጥታ ግንኙነት የሌላቸውን በተለይም በምርጫው የሚወዳደሩ ፓርቲዎች የተለያየ ፖሊሲ አቅርበው የሕዝብን ቅቡልነት ለማግኘት በሚወዳደሩባቸው ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ከማሳለፍ እና ከመተግበር እንዲቆጠብ እናሳስባለን።

    እኛንም ጨምሮ በሀገራችን የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሙሉ በነፃነት ተንቀሳቅሰው ሃሳባቸውን መግለፅ እንዲችሉ ከዚህ ቀደም በተስማማንበት የፖለቲካ ፓርቲዎች የቃል ኪዳን ሰነድ መሠረት የምናደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ሰላማዊ፣ ሕጋዊ እና የሌሎችን መብት ያከበረ መሆኑን እያረጋገጥን ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ነፃ እና ፍትሃዊ እንዲሆን የሚጠበቅብንን ሁሉ እንድናደርግ እንጠይቃለን። በሀገራችን የምትንቀሳቀሱ የሲቪክ ተቋማትም የፖለቲካ ፓርቲዎች የተስማሙበትን የቃልኪዳን ሰነድ እንዲያከብሩ ግፊት እንድታደርጉ እና በጋራ ሊሠሯቸው እና ሊስማሙባቸው በሚገቡ ተጨማሪ ጉዳዮች ላይ ውይይት ማድረግ የሚችሉበት መድረክ እንድታዘጋጁ የአደራ ጥሪያችንን እያስተላለፍን፥ በመድረኮቹ ላይ በንቃት ለመሳተፍ ያለንን ፍላጎት ከወዲሁ ለመግለጽ እንወዳለን።

    መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ በሀገራችን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ለምንገነባው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መደላድል የምንጥልበት ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑን በመገንዘብ የምርጫውን ሂደት ከአሁን ጀምሮ በንቃት እንዲከታተል እና ምርጫው ሰላማዊ፣ ነፃ እና ፍትሃዊ መሆኑን ለማረጋገጥ የሚጠበቅባችሁን ሁሉ እንድታደርጉ የአደራ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።

    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)
    መስከረም 26 ቀን 2013 ዓ.ም

    ሀገራዊ ምርጫ

Viewing 15 results - 31 through 45 (of 116 total)