-
AuthorSearch Results
-
November 2, 2020 at 11:11 pm #16609
In reply to: የፖለቲካ ፓርቲዎች ድምጽ (ኢትዮጵያ ውስጥ የሚነቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች)
AnonymousInactiveምዕራብ ኦሮሚያ የተፈጸመውን ግድያ በጽኑ እናወግዛለን
የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)ከትላንት በስትያ ህዳር 1 ቀን 2020 [ጥቅምት 22 ቀን 2013 ዓ.ም] ምዕራብ ኦሮሚያ ውስጥ በዜጎች ላይ ግድያ መፈጸሙን ከመገናኛ ብዙሃን የሰማን ሲሆን፥ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ይህንን የግድያ ተግባር በጽኑ እያወገዘ፤ የተሰማውን ጥልቅ ሀዘንም ይገልጻል።
መንግሥት ነኝ የሚለው አካል ከአሁን ቀደም እንደለመደው ይህንን ግድያ የፈጸሙት ህወሓት እና ኦነግ-ሸኔ ናቸው በሚል ገልጿል። ኦነግ-ሸኔ በሚል የሚታወቅም ይሁን በዚህ ስም እራሱን የሚጠራ ድርጅት ግን አላገኘንም። ለኢትዮጵያ ሕዝቦችም ይሁን ለዓለም ማኅበረሰብ በዚህ ስም የሚከሰሰው ድርጅት ማንነት ግልጽ አይደለም።
ይህ የግድያ ድርጊት እና ሌሎች መሰል ድርጊቶች ሁሉም ነጻና ተዓማኒነት ባለው ገለልተኛ አካል በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጣርተው ለተጎጂዎችና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች፥ እንዲሁም ለዓለም ማኅበረሰብ ግልጽ እንዲሆኑ እንጠይቃለን። ከዚህ ባሻገር ሁሉም አካላት ሕዝቦችን የሚያጋጩና በብሔሮች መካከል መጠራጠርን የሚፈጥሩ ማናቸውንም ዓይነት መረጃ ከማሰራጨት እንዲቆጠቡ መልዕክታችንን እናስተላልፋለን።
በመጨረሻም ዜጎችን ለከፋ አደጋ እያጋለጠ ያለው ቀውስና የደህንነት ችግር ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት መፍትሄ ካልተበጀለት፥ ይበልጥ እየተባባሰ እንደሚሄድ ኦነግ በመግለጫው ሲያሳስብ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፤ አሁን እያየን ያለነውን አደጋ ለማስቀረት እና ኦሮሚያና ዜጎችን ከባሰ ቀውስ ለመታደግ ያለው ብቸኛው መፍትሄ የኦሮሚያ ሽግግር መንግሥት ማቋቋም በመሆኑ ሁሉም ዜጋ ድርሻውን እንዲወጣ ጥሪያችንን በድጋሚ እናድሳለን።
በድጋሚ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) በምዕራብ ኦሮሚያ በዜጎች ላይ የተፈጸመውንና ካሁን ቀደምም በተመሳሳይ መልኩ የተፈጸሙ ግድያዎችን ሁሉ በጥቅብ እንደሚያወግዝ እያሳሰበ፥ ለሟች ቤተሰቦችና ዘመዶች እንዲሁም ሰላም ወዳዶች ሁሉ መጽናናትን ይመኛል።
ድል ለሰፊው ሕዝብ!
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)
ህዳር 3 ቀን 2020 ዓ.ም- በአማራ ሕዝብ ላይ በየቦታው እየተፈፀመ ላለው የዘር ማጥፋት ወንጀል ሙሉ ኃላፊነቱን መንግሥት ይወስዳል ― አብን
- ንጹሃን ዜጎችን በማንነታቸዉ በጅምላ ማጥቃት የሽብር እንጂ የፖለቲካ ትግል ሊሆን አይችልም ― ብልጽግና ፓርቲ
- የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን በምዕራብ ወለጋ ዞን በተፈጸመው ጥቃት ህይወታቸው ያለፉ ሰዎች ቁጥር 32 እንደሆነ ገለጸ
- የምንገኝበት የፖለቲካ ቀውስ፣ ፈጣን ፖለቲካዊ መፍትሔ ይፈልጋል! – ከኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ሥራ አስፈፃሚ የተሰጠ መግለጫ
- ሰላማችንን በማስጠበቅ እና ቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ ላይ በንቃት በመሳተፍ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠረት እንጣል! ― ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የተሰጠ መግለጫ
November 2, 2020 at 2:36 pm #16595In reply to: የፖለቲካ ፓርቲዎች ድምጽ (ኢትዮጵያ ውስጥ የሚነቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች)
AnonymousInactiveንጹሃን ዜጎችን በማንነታቸዉ በጅምላ ማጥቃት የሽብር እንጂ የፖለቲካ ትግል ሊሆን አይችልም
ብልጽግና ፓርቲባለፉት ሁለት ዓመታት ተኩል በሀገራችን እዉነተኛ የዲሞክራሲ ሥርዓት ሽግግር ለማደረግ የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋትን ጨምሮ በርካታ ተግባራዊ እርምጃዎች ሲወሰዱ መቆየታቸዉ ይታወሳል።
በዚህም በሀገራችን ሕዝቦች ዘንድ ትልቅ ተስፋና መነቃቃት መታየት የጀመረ ሲሆን ሀገራችን በሰላማዊ፣በሰለጠነና በሰከነ የፖለቲካ አስተሳሰብ በሚመራ ነጻ፣ፍትሃዊና ገለልተኛ ምርጫ ወደ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ልትሸጋገር እንደምትችን የተስፋ ብርሃን የታየበት የፖለቲካ ሪፎርም ሲካሄድ መቆየቱ አይዘነጋም።
ይሁን እንጂ ሰላማዊና የሰለጠነ የፖለቲካ ስርዓት የማይዋጥላቸዉና ግድያን፣ ማፈናቀልን፣ ንብረት ማዉደምንና ንጹሃን ዜጎችን ማሸማቀቅን እንደ ዋነኛ የስልጣን ምንጭ አድርገዉ የሚንቀሳቀሱ የኢትዮጵያን መረጋጋትና የዜጎቿን ሰላም የማይፈልጉ ሃይሎች ቅንጅት በመፍጠር ምንም ዓይነት የፖለቲካ ወገንተኝነት የሌላቸዉን ንጹሃን ዜጎች በማንነታቸዉ ብቻ ኢላማ በማድረግ ጥቃት በማደረስ ላይ ይገኛሉ።
በዚህ እኩይና ጭካኔ የተሞላበት አረመኔያዊ የጥፋት ተግባራቸዉ ባለፉት አመታት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የዜጎች ህይወት እንዲጠፋ፣ አካል እንዲጎድል፣ ንብረት እንዲወድምና ዜጎች የሰላም ስሜት እንዳይሰማቸዉ ሲደረግ ቆይቷል።
በተለይም ሰሞኑን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል ዞን እና በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በቤንች ሸኮ ዞን በጉራ ፈርዳ ወረዳ የበርካታ ንጹሃንን ህይወት የቀጠፈ ጨካኝ የሽብር ተግባር ተፈጽሟል።
የንጹንን ደም በማፍሰስ ስልጣን መያዝን ካልሆነም አገርን መበታተንን ዋነኛ ዓላማቸዉ አድርገዉ ከሚነቀሳቀሱ ቡድኖች መካከል አንዱ የሆነዉ ኦነግ ሸኔ የተባለዉ አሸባሪ ቡድን በሀይል ወደ ስልጣን ለመመለስ ከሚፈልጉ ካልተሳካላቸዉም ኢትዮጵያን ለመበታተን ሌት ተቀን ከሚሰሩ ተቀናጅተዉና በትጥቅ ተደግፈዉ በትናንትናዉ ዕለት ማታ [ጥቅምት 22 ቀን 2013 ዓ.ም] በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ ጋዋ ጋንቃ በተባለዉ ቀበሌ ባደረሱት ጥቃት የዜጎች ህይወት ያለፈ ሲሆን በርካታ የአካል ጉዳትም ደርሷል።
ይህ የሽብር ጥቃት ፍጹም ሰላማዊ በሆኑ ንጹሃን ዜጎች ላይ የተቃጣ መሆኑ አጥፊ ቡድኑ የሚከተለዉ መንገድ ምን ያህል ያልሰለጠነ፣ ኋላ ቀርና ጭካኔ የተሞላበት መሆኑን ለአለም ሕዝብ ያጋለጠበት ነዉ።
በዚህ አረመኔዊ ተግባር ህይወታቸዉን ላጡ ዜጎቻችን የተሰማንን ጥልቅ ሃዘን እየገለጽን ለተጎጂዎች ቤተሰቦችና ወዳጅ ዘመዶች እንዲሁም ለመላዉ ኢትዮጵያዊያን መጽናናትን እንመኛለን።
መንግሥት እነዚህን ነብሰ ገዳዮች ከያሉበት አድኖ ሕጋዊ እርምጃ የሚወስድ መሆኑን እያረጋገጥን የፓርቲያችን አመራሮች፣ አባላት፣ ደጋፊዎችና መላዉ የሀገራችን ሕዝቦች የንጹሃን ዜጎችን ህይወት ያጠፉና አካል ያጎደሉ ሽብርተኛ ቡድኖችን አድነን እርምጃ በመዉሰድ የህግ የበላይነትን ለማስከበርና ህብረ-ብሄራዊ ፌዴራላዊ አንድነታችንን ለማስቀጠል በምናደርገዉ እርምጃ ዉስጥ ከጎናችን በመሆን አስፈላጊዉን ትብብርና ድጋፍ እንድታደርጉልን ጥሪያችንን እናቀርባለን።
ብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽ/ቤት
ጥቅምት 23 ቀን 2013 ዓ.ምNovember 2, 2020 at 1:48 pm #16584In reply to: በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ውስጥ እየደረሰ ያለው የሰላማዊ ሰዎች ጥቃት
AnonymousInactiveየኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን በምዕራብ ወለጋ ዞን በተፈጸመው ጥቃት ህይወታቸው ያለፉ ሰዎች ቁጥር 32 እንደሆነ ገለጸ
- የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መልዕክት
- የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን መልዕክት
- የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ጋዜጣዊ መግለጫ
- የብልጽግና ፓርቲ ጋዜጣዊ መግለጫ
- የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) መልዕክት
- የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) መግለጫ
- የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) መግለጫ
የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ ጋዋ ቃንቃ ቀበሌ በተፈጸመው ጥቃት ህይወታቸው ያለፉ ሰዎች ቁጥር 32 እንደሆነ ገለጸ።
የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል አራርሳ መርዳሳ ጥቅምት 23 ቀን 2013 ዓ.ም. ማምሻውን ለኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) እንዳሉት፥ በጥቃቱ የተነሳ የተፈናቀሉ 200 ያህል አባወራዎችን የማረጋጋትና ሥራ እየተሠራ ነው።
በተፈጸመው ጥቃት 23 ወንድ እና 9 ሴቶች በድምሩ 32 ሰዎች ህይወታቸው ማለፉን የገለጹት ኮሚሽነር ጄኔራሉ፥ 10 ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸው ሕክምና እየተከታተሉ እንደሚገኙ አመልክተዋል።
በጥቃቱ የመኖሪያ ቤቶችና አንድ ትምህርት ቤት እንደተቃጠለ ተናግረው፥ ከአካባቢው ሕብረተሰብ ጋር በመተባበር መልሶ የማቋቋም ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል።
የጥቃት ድርጊቱን የፈጸመው አካል ኦነግ ሸኔ መሆኑን ገልጸው፥ ከጀርባ በመሆን የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) እየደገፈው እንደሚገኝ ተናግረዋል። በተለይም ቡድኑ የታጠቃቸው እንደ ስናይፐርና ብሬል ያሉ የጦር መሳሪያዎች ህወሓት ያስታጠቀው እንደሆነ ገልጸዋል። ከኦነግ ጀርባ በመሆን ህወሓት በህብረተሰቡ ላይ ጥፋት እያደረሰ እንደሆነም አክለዋል።
ጥቃት የተፈጸመበት ቀበሌ ከወረዳ ከተማ በ75 ኪሎ ሜትር የሚርቅ መሆኑን ገልጸው፥ ህወሓት በብሔሮች መካከል ግጭት ለመፍጠር በስሌት የፈጸመው ተግባር ስለመሆኑ ተናግረዋል።
ከድርጊቱ ፈጻሚዎች መካከል የተወሰኑት መያዛቸውን ተናግረው ቀሪዎቹን ለመያዝ እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸው፥ ተመሳሳይ ጥቃት እንዳይፈጸም ከሕብረተሰቡ ጋር እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
- የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መልዕክት
በተያያዘ ዜና፥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ኢትዮጵያውያን ላይ እየተፈጸመ ባለው ማንነትን መሠረት ያደረገ ጥቃት ከምንጩ ለማድረቅ መንግስት የሚወስደውን ርምጃ በመደገፍ ሕዝቡ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የጸጥታ አካላት ምሁራንና ሌሎችም የሚጠበቅባቸውን እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ያሰፈሩት መልዕክት እንደሚከተለው ይነበባል።
“በኢትዮጵያውያን ላይ እየተፈጸመ ባለው ማንነትን መሠረት ባደረገው ጥቃት እጅግ ማዘኔን እገልፃለሁ።
የኢትዮጵያ ጠላቶች፤ “ወይ እኛ እንገዛለን፤ ወይ ሀገር አትኖርም” ብለው ተነሥተዋል። ለዚህም የጥፋት አቅማቸውን ሁሉ እየተጠቀሙ ነው። አንደኛው ዒላማቸውም የሕዝባችንን ቅስም መስበር ነው።
ለዚህ እየተጠቀሙበት ያለው ስልት ግራ ቀኝ የማያውቁ ሰዎችን እየሰበሰቡ በማሠልጠንና በማስታጠቅ በየአካባቢው ማንነትን መሠረት ያደረገ አረመኔያዊ ጥቃት ማድረስ ነው። ይህ ተግባር ሕዝቡ እንዲደናገጥ፣ እንዲፈራና በስሜት ያልተገባ ርምጃ እንዲወስድ የታለመ ነው።
መንግሥት በተለያዩ ቦታዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ ያላቸውን ጥፋቶች በቅድሚያ መረጃ ሰብስቦ ርምጃ በመውሰድ ሲያከሽፍ ቆይቷል። ነገር ግን ያለፈው ሥርዓት ያወረሰንን ቀዳዳዎች ሁሉ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ደፍኖ መጨረስ አልተቻለም።
የጥፋት ኃይሎች ከውጭ ላኪዎቻቸውና በመንግሥት መዋቅር ውስጥ በሚገኙ ባልጠሩ አድር ባዮች ትብብር በሕዝባችን ላይ አሳዛኝ ጥቃት እያደረሱ ነው። ሁኔታው እንደ መሪም እንደ ዜጋም ልብ ይሰብራል።
ይህ ግን ከመንገዳችን ወደኋላ፣ ከግባችን ወደ ሌላ አያደርገንም። ተስፋ ቆርጠን እንድናቆም፣ ተሸንፈን እንድናፈገፍግ አያደርገንም። ከምንጊዜውም በላይ ኃይላችንን አሰባስበን እንድንነሣ ያደርገናል እንጂ።
መንግሥት ሁሉንም ዓይነት አማራጮች ተጠቅሞ የችግሩን ሰንኮፍ ይነቅለዋል። የጸጥታ አካላት ጥቃቱ ወደተፈጸመበት አካባቢ ተሠማርተዋል። ርምጃም እየወሰዱ ነው። በቀጣይም የሕዝባችንን ደኅንነት ለማስጠበቅ መንግሥት የመንግሥትነቱን ሥራ በቁርጥና በጽናት ይሠራል።
ሕዝቡ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የጸጥታ አካላት፣ ምሁራንና ሌሎችም፧ መንግሥት ችግሩን ከምንጩ ለማድረቅ የሚወስደውን ርምጃ በመደገፍ የሚጠበቅባቸውን እንዲያደርጉ ጥሪ አቀርባለሁ።”
- የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን መልዕክት
የኢፌዲሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ በንፁኃን ዜጎች ላይ የተፈፀመውን አሰቃቂ ጭፍጨፋ በማስመልከት መልዕክት አስተላልፈዋል። አቶ ደመቀ መኮንን ባስተላለፉት መልዕክት የሚከተለውን ብለዋል።
“በምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ በንፁሃን ዜጎች ላይ የተፈፀመው አሰቃቂ ጭፍጨፋ የተሰማኝን ሀዘን እየገለፅኩ፥ ለሟች ቤተሰቦች መፅናናትን እመኛለሁ።
በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ቀደም ሲል ብሔርን፣ ሀይማኖትን እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት የማድረስ ዓላማ ያላቸው ጥቃቶችና ጭፍጨፋዎች ተካሂደዋል። በተመሳሳይ በምዕራብ ወለጋ ዞን በንፁሃን ዜጎች ላይ አሰቃቂ ጭፍጨፋ ተፈፅሟል።
በተለይ የአማራን ማኅበረሰብ ትኩረት ያደረገና በንፁሃን ዜጎች ላይ የሚካሄደው ጭፍጨፋ ፍፁም አረመኔያዊና በፍጥነት መቆም ያለበት እኩይ ድርጊት ነው። ድርጊቱ አስቀድሞ መዋቅራዊ በሆነ መልኩ ሲዘራ የቆየ በመሆኑ፥ ችግሩን የሚመጥን መፍትሄ በዘላቂነት ለማበጀት አስፈላጊው ሁሉ ይደረጋል። ከዚህ አኳያ የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ እንዲሁም ከሁሉም አቅጣጫ የሚቃጡ ጥቃቶችን ለመመከት የመንግሥትና ሕዝብ ቅንጅታዊ ርብርብ ተጠናክሮ ይቀጥላል።”
- የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ጋዜጣዊ መግለጫ
ይህንን ጥቃት ተከትሎ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ባወጣው መግለጫ በአማራ ሕዝብ ላይ በየቦታው እየተፈፀመ ላለው የዘር ማጥፉት ወንጀል ሙሉ ኃላፊነቱን መንግሥት ይወስዳል ብሏል። ሙሉ መግለጫውን እዚህ ጋር በመጫን ያንብቡ።
- የብልጽግና ፓርቲ ጋዜጣዊ መግለጫ
የብልጽግና ፓርቲ በበኩሉ፥ ንጹሃን ዜጎችን በማንነታቸው በጅምላ ማጥቃት የሽብር እንጂ የፖለቲካ ትግል ሊሆን እንደማይችል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል። ሙሉ መግለጫውን እዚህ ጋር በመጫን ያገኙታል።
- የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) መልዕክት
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) “በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ በዜጎች ላይ ማንነትን መሠረት ባደረገ ጥቃት በተገደሉት እና ጉዳት በደረሰባቸው ኢትዮጵያውያን የተሰማንን ሀዘን እንገልፃለን” በማለት የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ክፍል መልዕክቱን አስተላልፏል።
ፓርቲው በዚሁ መልዕክቱ፥ ኢትዮጵያውያን በዚህ አስቸጋሪ ወቅት በአንድነት በመቆም የዘውግ ፖለቲካ ያመጣብንን በሕይወት የመኖር እና እንደ ሀገር የመቀጠል አደጋ ልንታገለው እንደሚገባና፤ ኢዜማ አጠቃላይ የሀገራችንን ሁኔታ አስመልክቶ በቀጣይ ቀናት መግለጫ እንደሚሰጥ አመላክቷል።
በማስከተልም፥ በምዕራብ ወለጋ ጉሊሶ ወረዳ ማንነትን መሰረት አድርጎ የተፈፀመው ጥቃት የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ሐዘን ሲሆን፤ የጥቃቱ ዓላማም ሀገርን የማፍረስ መሆኑን ተረድተን ሀዘናችንን በጋራ በመግለፅ በአንድነት እንድንቆም እንጠይቃለን ሲል መልዕክቱን ቋጭቷል።
- የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) መግለጫ
የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) በሰላማዊ ሰዎች ላይ የደረሰውን ጥቃት ካወገዘ በኋላ፥ መንግሥት ጥቃቱን ያደረሱት ህወሓትና ኦነግ ሸኔ ናቸው ማለቱን በከፊል በማስተባበል፤ ይልቁንስ ኦነግ ሸኔ የሚባል ቡድን በአካል እንደሌለ ገልጿል። የኦነግን ሙሉ መግለጫ እዚህ ጋር በመጫን ያገኙታል።
- የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) መግለጫ
የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ደግሞ በሰጠው መግለጫ፥ በአማራ ሕዝብ ላይ እየደረሰ ላለው ዘር-ተኮር ጥቃት የፌደራል መንግሥቱን የሚመራው ብልጽግና ፓርቲ ግንባር ቀደም ተጠያቂ እንደሆነ አትቷል። ሙሉ መግለጫውን እዚህ ጋር ያገኙታል።
November 2, 2020 at 4:53 am #16580In reply to: ነፃ አስተያየት (ስለኢትዮጵያ በኢትዮጵያውያን)
AnonymousInactiveየወቅቱ አብይ ጥያቄ – የህወሓትን ሀገር አፍራሽ፣ ሕዝብ አጫራሽ ሴራ በጋራ ቆመን፣ በአንድነት በመንቀሳቀስ ማምከን ነው
አቶ ነአምን ዘለቀሰላም ወገኖቼ፥
የወቅቱ አብይ ጥያቄ ኢትዮጵያ ሀገራችንንና ኢትዮጵያዊነት ከህወሓት ሀገር አፍራሽ፣ ሕዝብ አጫራሽ ሴራ በጋራ ቆመን፣ ከዳር እሰክዳር በአንድነት በመንቀሳቀስ ማምከን ነው። መሆን ወይንም አለመሆን ነው ለእያንዳዱ ዜጋ የቀረበው ጥያቄ!
የክፋት፣ የነውር፣ የመሰሪነት ጥግ የሆኑት፣ ይህ ነው የማይባል ዘረፋ፣ ዘረኝነትና ግፍ በሚሊዮኖች ዜጎች ላይ የፈጸሙ፣ በእውነቱ ቃላትም የማይገልጻቸው የህወሓት መሪዎች ኢትዮጵያን በበላይነት ካልገዛን ትፈርሳለች የሚል ለዘመናት የቆየ ቅዠት እውን ለማድረግ እየተቅበዘበዙ መሆናቸውን የሰሞኑ ዋና መነጋገሪያ መሆኑ ይታወቃል። ከነበራዊ እውነታ ጋር የተጣሉ፣ የሞራልም የእእምሮም በሽተኞች በመሆናቸው የ27 ዓመት የክፋት፣ የዘረፋ፣ የከረፋ ዘረኝነታቸው ውስጥ ፍዳውን ሲያይ የነበሩ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ዜጎች የሚረዳው መሆኑ ግልጽ ነው።
ከለውጡ በኋላ ወደ ስልጣን የመጣው አመራር የነዚህን ጉዶች ባህርይና ለዘመናት የተተበተበ በሽታ በሚገባ ተገንዝቦ፣ ስትራቴጂም ነድፎ ህወሓትን የማዳከም ልዩ ልዩ እርምጃዎችን መወሰድ ይገባው ነበር። ያ ግን አልተደረገም። በተለይም ወንጀለኛውን ጌታቸው አሰፋ ሕግ ፊት እንዲቀርብ የፌደራል መንግሥቱ ሲጠይቅ አናስረክብም ባሉ ጊዜ፥ በሀገሪቱ ልዩ ልዩ ክፍሎችም ግጭት ለመፍጠር በርካታ የሳቦታጅ ሥራዎች ማደራጀታቸው፣ መቆስቆሳቸው በሚገባ የሚታወቁ ሆነው ሳለ፥ ፈዴራል መንግሥቱ ከጦርነት በመለስ ሁሉንም የመንግሥት ማድረግ አቅም መጠቀምና ህወሓትን አይቀጡ ቅጣት መቅጣት ነበረበት። በቅርብ ሳምንት በቤኒሻንጉል-ጉሙዝ ክልል በአማራ ማኅበረሰብ አባላት ላይ የተደረገውን አሰቃቂ ጭፍጨፋ በገንዘብና በመሣሪያ ያገዙ፣ በክልሉ ሰፊ መሬት ያላቸው የህወሓት አባል የሆኑ ባለሃብቶች መሆናቸው የክልሉ መንግሥት ባለስልጣን ለኢሳት ጋዜጠኛ መሳይ መኮንን የተናገረውን ልብ እንበል።
በመንግሥት አካባቢ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ተንሠራፍቶ የነበረ ‘የት ይደርሳሉ?’ መሰል የተዛባና አደጋውን የመረዳት የማይመጥን አመለካከት ሳቢያም፣ ህወሓትን የልብ ልብ ሰጥቶ ኢትዮጵያን ወደ ጦርነት ለመክተት፣ በዚህም የትግራይንም ሆነ የሌላውን ኢትዮጵያዊ በጦርነት እሳት ለመማገድ ዛሬ ላይ የደረሰበት የለየለት እብደት እንዲደርስ ዕድል ባልተሰጠው ነበር፤ አጥፍቶ ከመጥፋትም አይመለሱም። ያ በሀገርና በሕዝብ ላይ የነበራቸውንም ዓይን ያወጣ የጥቂት ዘረኞች የበላይነት፣ ፈልጭ ቆራጭነት እንዳይመለስ አጥተውታልና አዲሱን እውነታ ፈጽሞ ተቀበለው በእኩልነት፣ በአቻነት ሊኖሩ በዘረኝነት፣ በትምክህትና በትእቢት የታጨቀው አእምሮአቸው አይፈቅድላቸውም።
ለሁለት ዓመት ተኩል የተዘጋጁበት፣ ከጅምሩም ህወሓትና አጋሮቹ እንደ ጊዜ ቦንብ እንዲፈነዳ ቀብሩውት የነበሩት ሰፋፊ የማንነት ስንጥቆች፣ የብሔር ቅራኔዎችን ተጠቅመው ሀገሪቱን በቀውስ ውስጥ ለመክተት፣ ብሎም ለመበታተን ላሰፈሰፉ በየክልሉ ያደፈጡ ጽንፈኞችም ምቹ ሁኔታዎችንም ፈጥሯል። የህወሓት መሪዎች ለበርካታ ዓመታት የነደፉትን መሰሪ ‘ፕላን B’ የሆነውን አባይ ትግራይ-ትግራይ ትግሪኝ፣ ወዘተ… ለመመሥረት የሚችል መስሏቸው እየተንፈራገጡ ይገኛሉ። ለሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ግልጽ መሆን ያለበት የጦርነት እሳት ኢንዲቀጣጠል፣ ብሎም በመላው ኢትዮጵያ እንዲዛመት ያላቸውን ሁሉ በማድረግ ላይ የሚገኙት መሰሪዎቹ ጸረ-ኢትዮጵያ የህወሓት መሪዎች በጠላትነት የፈረጁት ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድን ብቻ እንዳልሆነ ግልጽ መሆን ይገባዋል፤ ወይንም ፈደራል መንግሥቱ፣ የብልጽግና ፓርቲ አይደሉም።
ይልቅስ ዓይን ቀቅሎ የበላው የሀሰትና የነውር ቋት የሆነው የስዩም መስፍንና ሌሎቹ የህወሓት መሪዎች መሠረታዊ ግብ ኢትዮጵያን የማፈራረስ ነው። በፍርስራሹም ላይ በዘረኝነት የታጨቀው የትግራይ ትግርኝ ሀገር መንግሥት የመመሥረት ቀቢጸ-ተስፋ እውን የማድረግ ግብ ነው። ይህ ነው አብይ ግባቸው። ለምን ቢባል የህወሓት መሪዎች ኢኮኖሚውን፣ መከላከያውን፣ ደህንነቱን፣ የውጭ ጉዳዩንና ባጠቃላይም በኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ላይ በበላይነት የማያሸከረክሩባት፣ ፈላጭ ቆራጭና ሁሉን አድራጊ ፈጣሪ፣ ሌላው የእነርሱ አጎብዳጅ፣ ፈርቶና ተጎናብሶ የማይኖርባት የ27 ዓመቷ ኢትዮጵያ ማስቀጠል የማይችሉበት ነባራዊ ሁኔታን እንዴት ተቀብለው ሊኖሩ ይችላሉ?
ልብ እንበል፤ ቆም ብለን በቅጡ እናስብ፤ ያቺ ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ የለችም። ይህን እጅግ መራር እውነታ ሊቀበሉ ሊውጡት ደግሞ ፈጽሞ አልቻሉም። የእነ ስዩም መስፍን “ዓይናችሁን ጨፍኑና እናሞኛችሁ” የለየለት ውሸቶች፣ ማስመሰሎች፣ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ቆመው፣ ሠርተው እንደነበር፣ ለሕዝብ ጥቅም የታገሉና ሲሠሩ እንደነበሩ ለቀባሪው ማርዳት ሙከራዎች ሁሉ ከዚህ ሃቅ የሚመነጭም ጭምር ነው። ይህን ሃቅ አስምረን ግልጽና ፍንትው አድርገን ማየት ቀዳሚው ተግባር ነው። ህወሓት ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እውነተኛ ፍትህ፣ እኩልነት፣ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሞች የቆመበትና የሠራበት ሁኔታና ጊዜስ መቼ ነበሩ? ብለን ብንጠይቅ፣ እነ ስዩም መስፍን ነጋ ጠባ ሊያጭበረብሩን ከሚሞክሩት ውጭ ማንም አፉን ሞልቶ ሊመሰክር የሚችል ኢትዮጵያዊ የሚገኝ አይመስለኝም። ሀገሪቱን እንደ ቅኝ ተገዢ ሲመዘብሩ፣ በከረፋ ዘረኝነታቸውም ትግርኛ ተናጋሪ ያልሆነውን ኢትዮጵያዊ ሁሉ እንደ የበታችና 3ኛ ዜጋ ሲያንገላቱ፣ ሲገፉ፣ በንቀት ሲመለከቱ፣ ሲዘርፉና ሲገድሉ የነበረው መራራ ታሪክ ሁሉም ያለፈበት የቅርብ ጊዜ አስነዋሪውና አሳፋሪው ትሪካቸውና የእኛም የኢትዮጵያውያን ቁስል ነውና።
ለምን? ምክንያቱም ከጅምሩም የተነሱበት መሠረት በመሆኑ ለአያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ግልጽ መሆን ይገባዋል፤ መወናበድ ማክተም አለበት። ለአወናባጆችና ውዥንብር ነዥዎችም ሰለባ መሆን የለብንም፤ ብዙዎች ከዳር ቆሞው ጉዳዩ የዐቢይ አህመድ እና የህወሓት ጠብ አድርጎ መመልክት በሀገርና በሕዝብ ላይ ትልቅና ከባድ አደጋ፣ እንደ ሀገርና ሕዝብ ለውድቀትም ሊዳርግ የሚችል፣ ይህ ነው ተብሎ ሊገመት የማችል ዋጋ የሚያስከፍል ስህተት ይሆናል። አለፍ ሲልም ቅጥረኞችና ከራሳቸው ጥቅም በላይ ለጋራ ሀገር፥ ለኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ማሰብ የማይችሉ፣ ዐቢይን ሰለጠሉ ኢትዮጵያም ሆነች ሀገረ መንግሥቱ ቢፈርስ፣ በፍርስራሹ ላይ ስልጣን የሚያገኙ የሚመስላቸው እኩዮች “ፓለቲካ ሊያስተምሩን” እንደሚዳዱት የህወሓትና የፌደራል መንግሥቱ/የብልጽግና ጠብና ግጭት ተደርጎ መወሰድ የለበትም። የህወሓት መሪዎች እንቅስቃሴ በሀገራችን ኢትዮጵያና በሕዝብ ሰላም፣ ደህነትና መረጋጋት ላይ የመጣ የህልወና አደጋ ተደርጎ መወሰድ ያለበት ነው።
የዛሬው አብይ ጥያቄ ኢትዮጵያ ሀገራችንንና ኢትዮጵያዊነት ከህወሓት ሀገር አፍራሽ፣ ሕዝብ አጫራሽ ሴራ ማምከን ነው። መሆን ወይንም አለመሆን ነው ለእያንዳዱ ዜጋ የቀረበው ጥያቄ።
ነአምን ዘለቀ
ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረ–ገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forums) ላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።
October 26, 2020 at 12:12 am #16485In reply to: የፖለቲካ ፓርቲዎች ድምጽ (ኢትዮጵያ ውስጥ የሚነቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች)
AnonymousInactiveየአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በአማራ ክልል ከተሞች እና በአዲስ አበባ ታላልቅ ሰለማዊ ሰልፎችን ለማድረግ ጥሪ አደረገ
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በአማራ ክልል ከተሞች እና በአዲስ አበባ ታላልቅ ሰለማዊ ሰልፎች እንደሚደረጉ አስታውቋል። አብን ስለሰላማዊ ሰልፎቹ እና በአጠቃላይ በአማራ ሕዝብ ላይ ከዕለት ወደ ዕለት ያልተቋረጠ በደል እየደረሰበት መሆኑን ያመላከተበት ትንታኔ የሚከተለውን ይመስላል።
ለመላው የአማራ ሕዝብ፣
ለንቅናቄያችን አባላትና ደጋፊዎች፣
ለመላው ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በሙሉ !የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) መንግሥታዊና ሥርዓታዊ ጭቆና እና የዘር ጥቃት ያንዣበበትን የአማራን ሕዝብ ከህልውና ስጋት ለመታደግና በነፃነት፣ በእኩልነት፣ በፍትህና በወንድማማችነት የሚኖርባት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት የቆመ ድርጅት ነው።
አብን ባለፉት ሁለት ከመንፈቅ ዓመታት ሕዝባችን በከፍተኛ መስዋዕትነት ያስገኘው የለውጥ ተስፋ እንዳይመክን፣ በትግላችን የተንበረከኩ አማራ-ጠል ኃይሎች ዳግም እንዳያንሰራሩና የሀገር እና የሕዝብ ህልውና በድጋሚ አደጋ ላይ እንዳይወድቅ እልህ አስጨራሽ ትግል አድርጓል። የአማራ ብሔርተኝነት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ አዎንታዊ የመረጋጋት፣ የመቻቻልና የግንባታ ሚና እንዲኖረው ያልተቆጠበ ጥረት አድርጓል።
ይሁን እንጂ ተስፋ የተጣለበት “ለውጥ” እያደር መስመሩን በመሳቱ አዲሱ አገዛዝ የአምባገነንነትና የአንድ ቡድን ፍላጎት አስፈፃሚነት አዝማሚያ ማሳየቱ ገሃድ ወጥቷል። በተለይም በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈፀመው የዘር ጥቃት እየተባባሰና አድማሱን እያሰፋ በቅርቡ እንኳን በኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና በደቡብ ጉራ ፈርዳ ተከታታይ ለሆኑ የጅምላ ጭፍጨፋዎች፣ የዘር ማጽዳትና የማፈናቀል ጥቃቶች ሰለባ ሆኗል።
አብን በሕዝባችን ላይ ስልታዊ፣ የተደራጀ፣ ሰፊ የመገናኛ ብዙኃን ቅስቀሳ የተደረገበት ዘመቻና በመንግሥት መዋቅር ጭምር የተደገፈ የዘር ማጥፋት እየተፈፀመበት መሆኑን በመግለጽ መንግሥት ችግሩን እንዲያስቆም በተደጋጋሚ ወትውቷል። እንደ ሕዝብም መቻቻልና ሀገር ወዳድነት ትርጉም እስኪያጡ ድረስ ታግሰናል። ነገር ግን ብልፅግና-መራሹ መንግሥት የሕዝባችንን ሆደ-ሰፊነትና አስተዋይነት እንደ ዓይነተኛ ድክመት በመቁጠር፥ ንቅናቄያችን ለሀገር ህልውና ሲባል የሰጠውን ይሁንታ በሰፊው በማጓደል ዛሬም አማራው መንግሥት-አልባ ሕዝብ መሆኑን አረጋግጦልናል።
አብን በሕዝባችን ላይ ለሚደርሰው ጥቃት ቀንደኛው ተጠያቂ ማዕከላዊ መንግሥት መሆኑን ያምናል። መንግሥት ‹‹የወንጀሎች ሁሉ ወንጀል›› የሚባለውን የዘር ማጥፋትን በመከላከል፣ በማስቆምና ዘላቂ መፍትሄ በመፈለግ ረገድ የረባ ሚና አልተጫወተም። እንዲያውም የዘር ጥቃቶችን “ግጭት” እያለ ለማድበስበስ፣ መረጃዎችን ለማፈንና ሰለባዎችን ጭምር ለመወንጀል ተደጋጋሚ ጥረቶችን ሲያደርግ ተስተውሏል። መንግሥት በአማራ ላይ የተፈፀሙ የዘር ጥቃቶች ልዩ ጠባሳ የሆነውን የጉራ ፈርዳ ጥቃት መሪ አቀናባሪ የነበረውን ግለሰብ ለዳግም ሹመት የመምረጡን አንድምታ እንረዳለን፤ አሁን የሚፈፀመውን ካለፈው የሚያስተሳስር ረጅም ክር አለው።
በሁለተኛ በአማራ ሕዝብ ላይ የዘር ፍጅት በተፈፀመባቸው ክልሎች ያሉ መንግሥታት በተለያየ ደረጃ ኃላፊነታቸውን ካለመወጣት አልፈው፥ በቀጥታና በተዘዋዋሪ በሕግ፣ በመዋቅር፣ በመሣሪያና በገንዘብ ጥቃቶችን መደገፋቸውና ማቀናበራቸው በገሃድ ይታወቃል። ከጥቃቱም በኋላ የየክልሎቹ የብልፅግና ፖርቲ አመራሮች በሕዝባችን ላይ በየፊናቸው በማንአለብኝነት የሚያደርጉት ዛቻና ማስፈራሪያ በድርጊቱ አለመጸጸታቸውንና ችግሩን ለማረም ፈቃደኝነት እንደሌላቸውም ያረጋግጣል።
ሦስተኛው ተጠያቂ “የአማራ ብልፅግና” የሚባለው ነው። ለአማራ ሕዝብ ብልፅግናውን ቀርቶ ህልውናውንም ሊያስጠብቅለት አልቻለም። ቀድሞ ከነበረው አጠቃላይ አቋም መሻሻል አላሳየም። ንቅናቄያችን አማራው እንደ ሕዝብ በአንድነት እንዲቆም ለማስቻል ለሁለት ዓመታት ያክል “የአማራ – ብልፅግናን” ለማግባባት ያደረገው ሰፊ እና ያላሰለሰ ጥረት ፍሬ አላፈራም። የአማራ ሕዝብንም፣ አብንንም በተደጋጋሚ ያሳዘነ ሲሆን፤ ከታሪክ ተጠያቂነትም አያመልጥም።
አብን በማዕከልም ሆነ በክልል ያሉ መንግሥታት የተጫወቱት አፍራሽ ሚና ውጤቱ በአማራው ሕዝብ ተገድቦ እንደማይቀር በውል እንዲጤን ይሻል። መንግሥት መሠረታዊ መብቶቹን የማያስጠብቅለትን ሕዝብ ማናቸውንም የሞራልም ሆነ የሕግ ግዴታ ሊጥልበት አይቻለውም። በሕዝብና በመንግሥት መካከል ያለው ማኅበራዊ ውልም ክፉኛ ይናጋል።
አብን በአማራው ላይ የሚደረገው የዘር ማጥፋት ድርጊት ዞሮ ኢትዮጵያን እንደሀገር ዋጋ እንደሚያስከፍልም ይገነዘባል። ንቅናቄያችን እስካሁን የአማራ ሕዝብ በኢትዮጵያዊነት ተስፋ እንዲቆርጥና ወደ አመፅ እንዲያመራ የሚደረገውን አሉታዊ ጥረት ሲታገል ቆይቷል። ሆኖም ከእንግዲህ ወዲያ የሕዝባችን ህልውና በምንም መልኩ ለድርድር እንደማይቀርብ ለማረጋገጥ ይወዳል።
አብን የአማራ ሕዝብ ሆደ ሰፊና አስተዋይ በመሆኑ ተፈጥሯዊ መብቱንና ነፃነቱን በልቅሶና በልመና ሳይሆን በተደራጀ ትግል እንደሚያስከብር ይተማመናል። ይህን ታላቅ ታሪካዊ ኃላፊነት በመምራት ከግብ ለማድረስ ድርጅታችን ቁርጠኝነቱን ያረጋግጣል።
አብን መንግሥት ችግሩን በአስቸኳይ ከማስቆም በተጨማሪ ጥቃቱን እንዲያምንና በስሙ እንዲጠራ፣ ጉዳዩን የሚያጣራ ገለልተኛ አካል በፍጥነት እንዲሰይም፣ ወንጀለኞችን አጣርቶ ለፍርድ እንዲያቀርብና ለተጎጂዎችም ተገቢውን ካሳ እንዲከፍል በጥብቅ ይጠይቃል። ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት መሠረታዊ ምንጭ የሆነው አማራ-ጠል ሕገ-መንግሥት የሚሻሻልበትን አግባብ በአስቸኳይ እንዲያመቻች ይጠይቃል።
አብን መንግሥት የሀገሪቱን ሰላምና ደህንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ማስከበር አለመቻሉንና በተደጋጋሚ የአማራ ተማሪዎችን ደህንነት ለመጠበቅ ችላ ማለቱን በማጤን ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ያደረገው የትምህርት መጀመር ጥሪም ያሳስበዋል። ብዙ ሽህ የአማራ ተማሪዎች በፅንፈኞች ጥቃት ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው ሲፈናቀሉ፣ ሲገደሉ፣ ሲደበደቡና ሲታገቱ በአሳፋሪ ሁኔታ አልታደጋቸውም። አሁንም ለተማሪዎች አስተማማኝ ጥበቃ እንዲያደርግ በጥብቅ እንጠይቃለን።
የአብን ብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በጥቅምት 14 እና 15 ቀን 2013 ዓ.ም ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ በወሰነው መሠረት በሀገራችንና በሕዝባችን ላይ ያንዣበበውን ከፍተኛ የደህንነት ስጋት በመቀልበስ፤ የሕዝባችንን ህልውና ለማረጋገጥ የሚያደርጋቸውን ሰላማዊና ሕጋዊ የትግል ጥረቶችና ስልቶች ለሕዝባችን ለማሳወቅ የፊታችን ረቡዕ ጥቅምት 18 በአማራ ክልል ከተሞች፤ እሁድ ጥቅምት 22 በአዲስ አበባ ታላላቅ ሕዝባዊ ትዕይንቶች ይደረጋሉ።
በእነዚህ ሰልፎች ላይ መላው የአማራ ሕዝብ ማናቸውም ልዩነት ሳይገድበው እንዲሳተፍ፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የአማራ የፖለቲካ ኃይሎች፣ የተለያዩ የአማራ የሲቪክ አደረጃጀቶች በወገናችሁ ላይ የሚደርሰውን ግፍና በደል እንድትቃወሙ ጥሪ እናደርጋለን።
አብን በአማራ ክልልና በአዲስ አበባ የተጠሩት የተቃውሞ ሰልፎች ፍፁም ሰላማዊ እንዲሆኑና ሊከተሉ የሚችሉ አላስፈላጊ ረብሻዎችንና ጥቃቶችን ለማስቀረት ሕዝቡ የራሱን ደህንነት በንቃት እንዲጠብቅ ያሳስባል።
ሰልፉን በተመለከተ ዝርዝር ጉዳዮች፣ በሰልፉ ላይ የሚተላለፉ መልዕክቶችና መፈክሮች በማዕከል ተዘጋጅተው በፓርቲያችን ይፋዊ ገፅ የሚለጠፉትና ለየአካባቢው የሚላኩት ናቸው።
ጉዳዩ የሕዝብ ህልውና ጥያቄና የራሱ ሰልፍ በመሆኑ የሀገር መከላከያና አጠቃላይ የደህንነት ኃይሉ የሕዝቡ ሰልፍ የተሳካ እንዲሆን ተገቢውን የፀጥታ ሥራ እንዲያከናውን ጥሪ እናደርጋለን።
በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ አማሮች እሁድ ጥቅምት 22 ቀን 2013 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከሚደረገው ሰልፍ ጋር በተለያዩ ክፍለ ዓለማት ድምፃችሁን እንድታሰሙ አብን ጥሪውን ያቀርባል።
ሰልፉ ለኮቪድ-19 ወረርሽኝ በማያጋልጥ መልኩ በጥንቃቄ እንዲካሄድ እያሳሰበ፥ ሕዝባችን በየአካባቢውና በየቤተሰቡ በገጠመን ፅኑ ወቅታዊ ችግር ላይ ውይይት እንዲያካሂድ፤ በቀጣይም ዘላቂ መፍትሄ ለማፈላለግ አብን ዓለምአቀፍ የመላው አማራ ሕዝባዊ ውይይት መድረኮችን እንደሚያመቻች መግለጽ ይወዳል።
በአዲስ አበባም ሆነ በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈፀመው የማናለብኝነትና የተረኝነት አካሄድ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ጉዳት በመሆኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ በወንድሙ በአማራው ሕዝብ ላይ የሚፈፀመውን ግፍና በደል በመቃወም አብሮ እንዲሰለፍ አብን ጥሪውን ያቀርባል።
አብን ከእንግዲህ ጉዳዩ የማያዳግም እልባት እስከሚያገኝ ድረስ ማናቸውንም የሰላማዊ ትግልና የሕዝባዊ እምቢተኝነት ስልቶችን በየደረጃው የሚተገብር በመሆኑ ሕዝባችን ከወዲሁ እንዲያውቀውና ወትሮ ዝግጁ እንዲሆን ጥሪያችንን እናቀርባለን።
አንድ አማራ ለሁሉም አማራ ፥ ሁሉም አማራ ለአንድ አማራ!
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)
ጥቅምት 16 ቀን 2013 ዓ.ም
ሸዋ፥ አዲስ አበባ፥ ኢትዮጵያ!October 24, 2020 at 1:53 am #16458In reply to: የፖለቲካ ፓርቲዎች ድምጽ (ኢትዮጵያ ውስጥ የሚነቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች)
AnonymousInactiveበእነ እስክንድር ነጋ ኢ-ፍትሃዊ እስር ላይ የተሰጠ መግለጫ
የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ጥቅምት 12 ቀን 2013 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ የእነ እስክንድር ነጋ የክስ ሂደትን አጀንዳ በማድረግ አስቸኳይ ስብሰባ አካሂዷል። ፓርቲው እስክንድር ነጋ (ሊቀ መንበር)፣ ስንታየሁ ቸኮል፣ ቀለብ ስዩም እና አስካለ ደምሌ በምንም ዓይነት የሚያስከስስ ወንጀል ጉዳይ እንዳልተሳተፉ እና ንጹሃን መሆናቸውን ከዚህ በፊት መግለጹ ይታወቃል፤ ይልቁንም የፍትህ ሥርዓቱን መጠቀሚያ በማድረግ በቀጣዩ [ሀገራዊ] ምርጫ ጠንካራ ተፎካካሪ የሚሆኗቸውን እነ እስክንድር ነጋ እና ፓርቲያቸውን ለማጥቃት ታስቦ እንደሆነ ገልጸናል። ይህንን አቋማችንን የበለጠ የሚያጠናክርልን ሁለት ነገሮች ደግሞ በጥቅምት 12 ቀን የችሎት ውሎ ታዝበናል፦
1ኛ. ዐቃቤ ሕግ ከዚህ በፊት ያሰማውን የምስክሮች ቃል በመተው እንደገና 21 (ሀያ አንድ) ምስክሮች ማንነታቸው ሳይገለጽ ከመጋራጃ ጀርባ እንዲሰሙ እና በዝግ ችሎት እንዲደመጡ ጥያቄ ማቅረቡ ላይ እየተደረገ ያለው የፍትህ አሰጣጡን የሚያዛባ እና የሚያጓትት ሂደት፤
2ኛ. የሚሰጡ ቀጠሮዎች (በተለይም አዳዲስ ዳኞች እንደተሾሙ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ በፓርላማም ከተናገሩ በኋላ) ረጅም መሆናቸው ሂደቱን በማጓተት እነ እስክንድር ነጋ ሳይፈረድባቸው በእስር እንዲቀጡ የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ በዚህ ዓመት በሚደረገው ምርጫ ከክሱ ነጻ ቢባሉ እንኳን እንዳይሳተፉ የሚያደርግ ሆኖ አግኝተነዋል።
እነዚህ እና መሰል ጉዳዩች በክስ ሂደቱ ላይ የአስፈጻሚው አካል ረጅም እጆች እንዳሉበት የሚያስረዱ ሆነው አግኝተናቸዋል። ከዚህም በመነሳት ፓርቲያችን መሪዎቻችን ትክክለኛ ፍትህ፣ ሳይዘገይ ያገኛሉ የሚል እምነት እንዳይኖረን አድርጎናል። ስለሆነው ፓርቲያችን የኦህዴድ/ብልጽግና ፖለቲካ ዓላማ ለማሳካት በማሰብ በሀሰት በተቀነባበረ ክስ የተያዙ አመራሮቻችንን ለማስፈታት ከዚህ በፊት ሲያደርገው ከነበረው ትግል በተለየ እና በበለጠ ሁኔታ ውጤታማ የሚያደርጉ የትግል መንገዶችን ነድፎ በሥራ ላይ ያውላል። መላው የፓርቲያችን አባላት እና ፍትህ ወዳጅ ሕዝባችን በቀጣይ ይፋ ለምናደርጋቸው የትግል እንቅስቃሴዎች እንደከዚህ ቀደሙ እራሱን እንዲያዘጋጅ እና ለነጻነት በሚደረገው ትግል ንቁ ተሳታፉ እንዲሆን ጥሪያችንን እናቀርባለን።
ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ)
አዲስ አበባ
ጥቅምት 13 ቀን 2013 ዓ.ምምንጭ፦ ባልደራስ
——
ሌሎች ተመሳሳይ ዜናዎች፦- የፖለቲካ ፓርቲዎች ድምጽ (ኢትዮጵያ ውስጥ የሚነቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች)
- ከኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) በወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታዎች ላይ የተሰጠ የአቋም መግለጫ
- የምንገኝበት የፖለቲካ ቀውስ፣ ፈጣን ፖለቲካዊ መፍትሔ ይፈልጋል! – ከኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ሥራ አስፈፃሚ የተሰጠ መግለጫ
- ሰላማችንን በማስጠበቅ እና ቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ ላይ በንቃት በመሳተፍ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠረት እንጣል! ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የተሰጠ መግለጫ
October 4, 2020 at 12:23 am #16193In reply to: ነፃ አስተያየት (ስለኢትዮጵያ በኢትዮጵያውያን)
AnonymousInactiveየሞኝ ለቅሶ መልሶ መላልሶ! ኦሪት ዘህወሓት!
(ታዬ ዳንደአ)የግራ አስተሳሰብ ሁሌ ግራ ተጋብቶ ግራ ያጋባል። ህወሓት የግራ ጁንታ መሆኑ ይታወቃል። የግራ ፖለቲካ ደግሞ ውሸት ሲደጋገም እውነት እንደሚሆን ያምናል። “መስከረም 25/30” የሚደጋገመዉ ለዚህ ይመስላል። ህወሓት ከፈረሶቹ ጋር ብቅ ጥልቅ እያለ ይፎክራል። በሕገ-መንግሥት እና በፌዴራሊዝም ስም ያለቃቅሳል። ከመስከረም 25/30 በኋላ መንግሥት ስለማይኖር “ባለአደራ መንግሥት ከሰማይ ይዉረድልኝ” ይላል። ኢትዮጵያን ወደ ሊቢያ ለመቀየር አቅዶ በሙሉ ኃይሉ ይንደፋደፋል! በእርግጥ ዋነኛ እቅዱ ሰኔ 2012 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ተሞክሮ በኢትዮጵያዊያን የተባበረ ክንድ ከሽፏል! አሁን ቅዠትን እዉነት ለማድረግ በህወሓት አሻንጉሊቶች በከንቱ ዳንኪራ ይመታል። ይህ በአማርኛ ‘የሞኝ ለቅሶ መልሶ መላልሶ’ ይባላል!
የህወሓት ህልም ሩቅ ኖሯል። ኢትዮጵያዊያንን ከፋፍሎ እየገዛ ለመቶ ዓመታት ኢትዮጵያን የመጋጥ ግልፅ ዕቅድ እንደነበረዉ ይታወቃል። በዚሁ አግባብ ለ27 ዓመታት በኢትዮጵያዊያን ሰቆቃ ውስኪ እየተራጬ ሲንደላቀቅ ኖሯል። ያ ሁኔታ መጋቢት 2010 ዓ.ም. ላይ አክትሟል። በኢትዮጵያ ሕዝብ የዘመናት ትግልና በለውጥ አመራሩ ቆራጥ ውሳኔ የህወሓት ጉልበት ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ተንኮታኩቷል፤ ነገር ግን እዉነታዉ አልዋጥ ብሎታል። የቀን ቅዠት እዉን እየመሰለዉ አስቸግሮታል! ሁሌ ድምፂ ወያኔ ላይ ወጥቶ “ከመስከረም በኋላ ከኔ ውጭ ሌላ የለም” ይላል። “የለም! የለም!” እያለ ግልፅና ተጨባጭ እዉነታን መሰረዝ ይፈልጋል። መቼስ ከዚህ በላይ የሚገርም በዓለም ላይ ምን ይኖራል? ህወሓት ከነሙሉ ጥርሱና ጥፍሩ በነበረበት ወቅት ታግሎት ያቃተዉን ለዉጥ ከሬሳ ሳጥን ደጃፍ ሆኖ “የለም!” በማለት ብቻ ለመቀልበስ ይሞክራል!
ዘንድሮ ‘ሰይጣን ለተንኮሉ ቅዱሳን መጽሐፍትን ይጠቅሳል’ የሚባለዉ በግልፅ መታየት ጀምሯል። ህወሓት በምክንያት የኢሬቻ 2013 ዋነኛ አቀንቃኝ ሆኖ ብቅ ብሏል። በኢሬቻ አስታኮ አዲስ አበባ ላይ ተጀምሮ አዲስ አበባ ላይ እንዲያልቅ ታቅዶ የከሸፈዉን ጦርነት ዳግም ለማወጅ ፈልጓል! ፍላጎቱን ለማሳካት ደግሞ በኦሮሞ ስም የሚነግዱ አሉላ የሚቀልባቸዉን ፈረሶች አዘጋጅቷል! በፈረሶቹ በኩል የኦሮሞ ወጣት ኢሬቻን አሳቦ በነቂስ በመዉጣት ሸገር ላይ እንዲረብሽ ይቀሰቅሳል። በዲጂታል ወያኔ ደግሞ “ኢሬቻ የሰይጠን አምልኮ ነዉ” እያለ በአማራ ስም ያሰራጫል። የኦሮሞን ሕዝብ ‘ጋኔን’ ያለዉ ህወሓት መሆኑ ግን ይታወቃል። በተጨማሪም “ኢሬቻ አዲስ አበባ ላይ መከበር የለበትም!” እያለ በሌላዉ አሻንጉሊቱ በኩል የሸገር ወጣቶችን ይቀሰቅሳል። ኢሬቻ 2009ን የዘነጋነዉ መስሎታል። ያኔ ቢሾፍቱ ላይ በአንድ ቀን ብቻ ከ700 በላይ የኢሬቻ ታዳሚ ኦሮሞዎች በወያኔ አግዓዚ ገደል ውስጥ ተጥለዉ ሞቷል። በዚያ ወሳኝ ወቅት “የኦሮሞ ደም ደሜ ነዉ” ያሉትን የጎንደር ወጣቶች ታሪክ መዝግቧል። ኢሬቻን መደገፍ እና ማሞገስ ከቁርጥ ቀን ወገኖች ያምራል! ዛሬ ወያኔ በግራና በቀኝ የሚያጫውታቸዉን አሻንጉሊቶች ማን ይሰማል?
ታዲያ በመጨረሻ ምን ይሆናል? ውሾቹ እየጮሁ ግመሉ ይጓዛል! ባቡሩ ፍጥነቱን እና አቅጣጫዉን ጠብቆ ወደፊት ይገሰግሳል። ኢትዮጵያዊያን ለዘመናት በከፈሉት ውድ ዋጋ የመጣዉ ለውጥ ከመስከረም 25/30 በኋላም ተጠናክሮ ይቀጥላል! የተቋማት ግንባታ እና ብሔራዊ ውይይት መሠረት ይይዛል። በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት ይፈጠራል። ህወሓት ሲያበላሸዉ የነበረዉ ብሔራዊ ምርጫም በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ግልፅ፣ አሳታፊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ ይከወናል። የማይኖረዉ ህወሓት እና ተፅዕኖዉ ብቻ ይሆናል። ጓድ ህወሓት ቀስ እያለ ወደ መቃብሩ ጠጋ ጠጋ ይላል! በትግራይ ላይ ጠባሳ ሳይጥል፤ ማንም ሳይነካዉ ራሱን ችሎ ይሞታታል! የትግራይ ሕዝብም እንደወገኖች የነፃነትን አየር ይተነፍሳል! አሉላ ፈረሶቹን የሚቀልብበት መኖ ያጣል። በዚያዉ ጋብቻዉ ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ ይፈርሳል። አሻንጉሊትም አስታዋሽና አጫዋች ያጣል! የሴራና የሸር ሥራ ብኩን ይሆናል። የሌብነት፣ የውሸት፣ የፅንፈኝነት እና የክፋት ዘመን ያበቃል! እዉነት እና ዕዉቀት መርህና መመሪያ ይሆናል! የኢትዮጵያ ኅብረ-ብሔራዊ አንድነት እና ብልጽግና ደግሞ እየጎለበተ ይሄዳል! የኢትዮጵያ ሕዝብ ወንድማማችነትን መሠረታዊ መርሁ አድርጎ በድል ላይ ድል ይጎናጸፋል! ይህ ቃል ነዉ! ቃል ይነቅላል! ቃል ይተክላል! አሜን!!
ታዬ ዳንደአ
አቶ ታዬ ዳንደአ የኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲ ቃል አቀባይ ናቸው።
ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረ–ገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forums) ላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።
September 23, 2020 at 3:55 pm #15997Topic: ባህልና ቱሪዝም በኢትዮጵያ ― የመስቀል በዓል በጉራጌ ማኅበረሰብ
in forum Semonegna StoriesSemonegnaKeymasterበጉራጌ ዞን የመስቀል በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች መከበር ተጀመረ
(የመስቀል በዓል በጉራጌ ማኅበረሰብ)
በሀገራችን በድምቀት ከሚከበሩ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ክብረ በዓላት መካከል የመስቀል በዓል አንዱ ነው። የመስቀል በዓል በጉራጌ ማኅበረሰብ ዘንድ ልዩ ቦታ የሚሰጠው እንደመሆኑ፥ በየዓመቱ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ይከበራል። የዘንድሮውን የዋዜማ ዝግጅት በዞኑ ቸሃ ወረዳ የጠናቃ ቀበሌ ለኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በማያጋልጥ መልኩ የፌዴራል እና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በሀገር ሽማግሌዎች ምርቃት ከመስከረም 11 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በድምቀት መከበር ተጀምሯል።
በመክፈቻ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሐመድ ጀማል ታዳሚዎችን እንኳን አደረሳችሁ በማለት “የመስቀል በዓል የኛነታችን መገለጫ ነው፤ የመስቀል በዓል ትውፊታዊም መንፈሳዊም ነው። በመስቀል በዓል የእርስ በእርስ የመተሳሰብ፣ የአብሮነት፣ የፍቅር፣ የሰላም እንዲሆን የመልካም ምኞት ማብሰሪያ አበባ የሚሰጣጡበት ጊዜ ነው። እንዲሁም በሥራም ሆነ በሌላ አጋጣሚ ተራርቆ የቆየ ሰው የሚገናኝበት፣ ዘመድ ከዘመዱ የሚጠያየቅበት፣ የሚረዳዳበት እንዲሁም አዲስ ጎጆ የሚቀለስበት ጊዜ መሆኑ ማኅበረሰባችን ልዩ ቦታ ይሰጠዋል። አያይዘውም በበዓሉ ባህላዊ እሴቶቻችንን በደንብ አልምተን እንደ አንድ የቱሪዝም ገቢ ምንጭ በማድረግ ለሀገራዊ ብልጽግናችን መሠረት የምንጥልበት ነው ብለዋል።
የመስቀል በዓል ከሀይማኖታዊ ክዋኔ ባሻገር ባህላዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያለው ሲሆን በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት የሚከበር ቢሆንም መስቀል በጉራጌ በተለየ የአከባበር ሁኔታ ይከበራል ብለዋል – አቶ መሐመድ።
እንደ አቶ መሐመድ ገለፃ እንደ መስቀል ያሉ ቱባ ባህሎቻችን ታሪካቸው ሳይሸራረፍ ለትውልድ በማስተላለፍ ዘረኝነት፣ ጥላቻና ቂም በቀል በማስወገድ የሀገራችን ብልፅግና ለማረጋገጥ ሁሉም ዜጋ የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።
መርሀ-ግብሩን በጋራ ያዘጋጁት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፤ የጉራጌ ዞን አስተዳደር እና የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በመተባበር ሲሆን፥ የዚህ ክብረ በዓል አከዋወን በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ድርጅት /UNESCO/ ከማይዳሰሱ የሰው ልጅ ወካይ ባህላዊ እሴቶች (“intangible heritages of Ethiopia”) ተርታ መመዝገቡን በማስመልከት ሲሆን፥ በአከባበሩ ሥርዓት ውስጥ ያሉት ትውፊቶች በትውልድ ቅብብሎሹ ውስጥ ተጠብቀው ያለ ምንም ተፅዕኖ ክዋኔዎቹ እየቀጠሉ እንዲሄዱ የማስተማር ዓላማ ያለው እንደሆነ ተነግሯል።
በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የባህል እሴቶች ልማት ዳይሬክተር ወ/ሮ እስከዳር ግሩም በበኩላቸው፥ ሀገራችን ኢትዮጵያ የበርካታ ባህላዊና ታሪካዊ ሀብት ባለቤት ብትሆንም በተገቢው ማልማትና ማስተዋወቅ ባለመቻላችን ከዘርፉ የምናገኘው ገቢ እንዳላደገ ገልጸዋል።
አንድነታችን አጠናክረን ሀብቶቻችን ማልማት፣ መጠበቅና መንከባከብ አለብን። ይህ ደግሞ የቱሪዝም ዘርፍ እንዲነቃቃ ያደርገዋል። በተጨማሪም ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር ይቻላል ብለዋል።
የቸሀ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ፈለቀ የመስቀል በዓል በጉራጌ ሁሉም በድምቀት ከማክበር ባለፈ የጉራጌ እሴት የሚገለፅበት በመሆኑ የረጅም ጊዜ ቅድመ ዝግጅት እንደሚደረግበት በማስታወስ፤ በዓሉንም በድምቀት ለማክበር ሁሉም የቤተሰብ አባል የድርሻውን ኃላፊነት እየተወጣ እንደሚከበር ገልጸዋል።
ለበዓሉ ማብሰሪያ የጉራጌ ዞን የባህል ቡድንም ያሰናዳቸውን ሙዚቃዊ ክዋኔዎች እንደነ “ጊቻዌ፣ ጊቻዌ”፣ “አዳብና” የመሳሰሉት ተውኔታዊ ክዋኔዎች በሴቶችና ወንዶች የታየበት፣ የሥራ ባህልን፣ ሠርቶ ማደግን የሚያወድሱ፣ የሚያስተምሩ ማሳያዎች፣ ኢትዮጵያዊነትን የሚያቀነቅኑ በአንድነት በአብሮነት ባህላዊ እሴቶች የሚጎለብቱበት ተውኔታዊ ትዕይንቶች የተንፀባረቁበት ነበር።
September 20, 2020 at 4:27 pm #15946In reply to: የፖለቲካ ፓርቲዎች ድምጽ (ኢትዮጵያ ውስጥ የሚነቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች)
AnonymousInactiveበወቅታዊ ጉዳዮች ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የተሰጠ መግለጫ
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ መስከረም 9 እና 10 ቀን 2013 ዓ.ም ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ ሕዝባችንን ባጋጠሙት ወቅታዊ ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ላይ ተወያይቶ የሚከተሉትን ውሳኔዎች አሳልፏል።
1] በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሕዝባችን ላይ የተፈፀመውን የዘር ጥቃት በተመለከተ፦
አብን በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል ዞን ቡለን ወረዳ ከጳጉሜን 1 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ ቀናት ማንነትን መሠረት አድርገው የተፈፀሙ ጥቃቶችን በተመለከተ ተጨባጭ መረጃዎችን ሲያሰባስብ ቆይቷል። በዚህም ከ160 በላይ ወገኖቻችን በአሰቃቂ ሁኔታ እንደተጨፈጨፉ ተገንዝቧል።
የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የአማራው ሕዝብ ጥንተ ርስቱን ተነጥቆ፣ ሰብዓዊና ዜግነታዊ መብቱ ተገፎ ለሦስት አስርት ዓመታት ለዝርፊያ፣ ለመፈናቀል እና ለተደጋጋሚ የዘር ፍጅት የተጋለጠበት ነው። በተለይም “ለውጥ” እየተባለ በሚጠራው ባለፉት ሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ በክልሉ ውስጥ ባለው የአማራ ሕዝብ ላይ የሚደረገው የዘር ማጽዳትና ሰብዓዊ ጥቃት ከመቼውም ጊዜ በላይ ተባብሶ ቀጥሏል።
ንቅናቄያችን ልክ ከሰኔ 22 እስከ 24 ቀን 2012 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በአማራው ሕዝብ ላይ የደረሰውን ጥቃት አስመልክቶ እንደገለገፀው ሁሉ በቤንሻንጉል ክልል የተፈፀመው ጥቃት ተራ የማኅበረሰቦች ግጭት ወይም የሽፍቶች ድርጊት ውጤት ሳይሆን በአማራ-ጠል ትርክት ላይ የተመሠረተ፣ ስልታዊ የሆነ እና በመንግሥታዊ መዋቅር ጭምር የተደገፈ የሽብርና የዘር ማጥፋት ድርጊት መሆኑን ያምናል።
በዚህ አሰቃቂ ጥቃት የትህነግ ተቀጥላ የሆኑ በተለያዩ ደረጃዎች የሚገኙ የቤንሻንጉል ክልል መንግሥት ኃላፊዎችን ጨምሮ የአማራ ሕዝብንና የሀገሪቱን ሰላም ለማሳጣት የሚታትሩ ባዕዳንና ውስጣዊ ኃይሎች ያሰማሯቸው የሽብር ቡድኖች እጃቸው እንዳለበት አብን ያምናል።
የጥቃቱ ፈፃሚዎች ለተከታታይ ቀናት ሕዝባችንን (አማራ/አገው) በማንነታቸው እየመረጡ በአካባቢው ባሉ ትምህርት ቤቶች ውስጥ በኃይል አሰባስበው ለጅምላ ጭፍጨፋ ሲያዘጋጁ የክልሉ መንግሥት መረጃ እና ጥሪ እየቀረበለት ባለመድረሱ፤ የፌዴራል መንግሥቱም ባለው የደኅንነት መረጃ ተመርኩዞ ጥቃቱን ለመከላከል ፈጥኖ እርምጃ ባለመውሰዱ ተጠያቂ መሆን እንዳለባቸው አብን በጥብቅ ያምናል።
አብን በሕዝባችን ላይ ከእንግዲህ ማናቸውንም ዓይነት ማንነቱን መሠረት አድርገው የሚፈፀሙ ጥቃቶች ሊታገስ የማይችልበት ደረጃ መድረሱን እየገለፀ፤ ለችግሩ አስቸኳይ መፍትሄ ካልተበጀለት ጉዳዩ ከአማራው አልፎ ታላቅ ብሔራዊ ቀውስ ሊያስከትል እንደሚችል በመገንዘብ፦
(ሀ) መሣሪያ የታጠቁ ገዳዮችን በመደገፍና እንዳላዩ በማለፍ ለጥቃቱ መዋቅራዊ ከለላ የሰጡና በቀጥታም ሆነ በእጅ አዙር የዘር ማጥፋቱ ተባባሪ የሆኑ የክልሉ ባለሥልጣናት በአስቸኳይ በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ፤
(ለ) በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ለሚኖረው ሕዝባችን አስተማማኝ የደህንነት ዋስትና እንዲሰጥ፣ በየአካባቢያቸው የፖሊስና የደኅንነት መዋቅሮች ውስጥ የመሳተፍ መብታቸው እንዲከበር፣ በማኅበረሰብም ደረጃ ደህንነታቸውን የሚያስጠብቁበት አስቸኳይ መፍትኄ እንዲፈለግ፤
(ሐ) የፌደራል መንግሥቱና ገዥው ብልፅግና ፓርቲ በአማራው ሕዝብ ላይ በሚፈፀሙ የዘር ጥቃቶች ላይ የያዘውን ዳተኝነት እንዲያቆምና ችግሩን ለመከላከልና ከመሠረቱ ለመቅረፍ ተጨባጭ እርምጃ እንዲወስድ፤
(መ) የአማራ ብልጽግና ፓርቲና የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በአማራ ሕዝብ ላይ በሦስት ወራት ውስጥ ብቻ ሁለት እጅግ አሰቃቂ የዘር ማጥፋት ድርጊቶች ሲፈፀሙ ወንጀሉን በስሙ ከመጥራት ጀምሮ ለችግሩ ዘላቂ መፍትኄ በመፈለግ ረገድ ያሳየው አቅም እና ፍላጎት ከደረጃ በታች መሆኑና ከእንግዲህም ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ ከዚህ አካል ሊመጣ እንደማይችል ሕዝባችን በግልፅ እንዲገነዘበው፤
(ሠ) ሕዝባችን በተከታታይ ለዘር ማጥፋት እና ዘር ማጽዳት ጥቃቶች የተጋለጠበት የቤንሻንጉል ክልል አማራው ፍጹም ሥነ-ሕዝባዊ አብላጫ እያለው ፖለቲካዊ ውክልና በማጣቱ የተነሳ በመሆኑ ችግሩን በዘላቂነት ለማስወገድ የክልሉ መዋቅር የነዋሪዎቹን መብቶች በሚያረጋግጥ ሁኔታ እንዲከለስ ድርጅታችን አብን ያሳስባል።
2] በአማራ ክልል የደረሰውን በጎርፍ የመጥለቅለቅ አደጋ በተመለከተ፦
በአማራ ክልል በዘንድሮ ክረምት ዝናብ ምክንያት በተፈጠሩ የመሬት መንሸራተትና የጎርፍ አደጋዎች በአጠቃላይ በ6 ዞኖች በሚገኙ 36 ወረዳዎች ውስጥ ባሉ 164 ቀበሌዎች በተለያዩ ደረጃዎች የሚገለፁ ጉዳቶች እንዳደረሱ ይታወቃል።
በተለይ ደግሞ በማዕከላዊ ጎንደር በምሥራቅ ደምቢያ ወረዳ፣ እንዲሁም በደቡብ ጎንደር በሊቦከምከም፣ ደራና ፎገራ ወረዳዎች በከፍተኛ የጎርፍ መጥለቅለቅ በመጠቃታቸው በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ወገኖች ከመኖሪያ ቤታቸው ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያዎች ይገኛሉ።
አብን እነዚህ በጎርፍና በመጥለቅለቅ የተፈናቀሉ ወገኖች በአስቸኳይ የእለት እርዳታ እንዲያገኙ የበኩሉን አስተዋፅኦ እንደሚያደርግ እየገለፀ፤ በመላው ዓለም የሚገኙ የድርጅታችን አባላትና ደጋፊዎች፣ መላው የአማራ ሕዝብና ኢትዮጵያውያን ወገኖች ለድጋፍ እጃቸውን እንዲዘረጉ ይጠይቃል።
በጎርፉ ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች ሊነሱ በሚችሉ የወባ እና ሌሎች ውሃ-ወለድ በሽታዎች ሕዝቡ እንዳይጋለጥ ጥንቃቄ እንዲደረግ ይጠይቃል።
ተጎጂዎች ሰብሎቻቸው እና ንብረቶቻቸው የወደሙባቸው በመሆኑ አፋጣኝ ድጋፍ እና የመልሶ ማቋቋም ተግባራት እንዲከናወኑ፣ ለመጪው ዘመንም የሚያስፈልጋቸውን ሁለገብ እርዳታ የማዘጋጀት ሥራ እንዲሁም ለዘለቄታው በየዓመቱ የክረምት ወቅት ሊከሰቱ ከሚችሉ ተመሳሳይ አደጋዎች ለመጠበቅ ዘላቂ መፍትኄ እንዲፈለግ ይጠይቃል።
በመጨረሻም በአማራ ሕዝብ ታላቅ መስዋዕትነት የተገኘው ለውጥ አቅጣጫውን በመሳቱ በሕዝባችን ላይ ሥርዓት እና መዋቅር ሠራሽ ጥቃቶቹ ስጋት ደቅነውበት እንደቀጠሉ አብን ይገነዘባል።
እጅግ ራስ-ወዳድ በሆነው ሰፊ የፖለቲካ ውቅር ውስጥ ጨካኞች እና ያልተገሩ ስብስቦች በአማራው ላይ ጥቃታቸውን ባስቀጠሉበት አግባብ፣ ለኩርፊያቸው እና ለደም ጥማታቸው አማራ ቋሚ ግብር ወይም ማስያዥያ የሚሆንበት የፖለቲካ ድባብ በትግላችን መገፈፍ ይኖርበታል።
በተፈፀመው የዘር ማጥፋት ወንጀል ውስጥ ያሉ ተዋንያንንና በቸልተኝነትና በሴራ ተባባሪ የሆኑ አካላትን ጭምር ለማጋለጥ እና በኃላፊነት እንዲጠየቁ ለማድረግ አብን እንደሚሠራ በአፅንዖት ለማስገንዘብ ይወዳል።
በመጨረሻም አብን በቤንሻንጉል ጉሙዝና በኦሮሚያ ክልሎች በአሰቃቂ ሁኔታ የዘር ጭፍጨፋ ወንጀል ሰለባ ለሆኑ ወገኖቻችን የተሰማንን ጥልቅ ሐዘን ለመግለፅ ለመላው የአማራ ሕዝብና ለሕዝባችን ወዳጆች ከነገ ሰኞ መስከረም 11 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ማክሰኞ መስከረም 12 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ ለሁለት ቀናት በምናደርገው ጥቁር የመልበስ እና ተያያዥ የሐዘን መግለጫ ሥርዓቶች እንዲካፈሉ አብን የአክብሮት ጥሪውን ያቀርባል።
አንድ አማራ ለሁሉም አማራ ፥ ሁሉም አማራ ለአንድ አማራ!
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) /NaMA/
መስከረም 9 ቀን 2013 ዓ.ም
አዲስ አበባ ፣ ሸዋ ፣ ኢትዮጵያSeptember 18, 2020 at 1:06 am #15904In reply to: የፖለቲካ ፓርቲዎች ድምጽ (ኢትዮጵያ ውስጥ የሚነቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች)
AnonymousInactiveየሀገር ሰላምና መረጋጋት፣ የዜጎች ሰብዓዊ-መብትና ክብር ከሁሉም ይቀድማል፤ ብሔራዊ መግባባት እና ውይይት በአስቸኳይ!
ከአብሮነት ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት (አብሮነት) የተሰጠ መግለጫበቅድሚያ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንኳን ለ2013 ዓ.ም አዲስ ዓመት በሰላም አደረሳችሁ በማለት መልካም ምኞቱን ይገልፃል። አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የጤና፣ የፍቅር፣ የመተሳሰብ፣ የመከባበር፣ የመግባባት፣ የሀገራችንን ዘርፈ ብዙ ችግሮች በመወያየት፣ በመነጋገርና በእርቅ የምንፈታበት ዘመን እንዲሆንልን ይመኛል።
አብሮነት ላለፉት 27 ዓመታት በሀገራችን ተንሰራፍቶ የነበረው የህወሓት/ኢህአዴግ አፋኝ አገዛዝ ሥርዓት “የለውጥ ኃይል” በሚባለው የብልጽግና የሪፎርም አካሄድ ከተተካ ባለፍነው ሁለት ዓመት ከግማሽ ያህል ጊዜ የሀገራችንን አጠቃላይ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ሁኔታዎች፥ በአጠቃላይ ወቅታዊ ጉዳዮችን በተለይ በአዲሱ ዓመት መባቻ ገምግሟል።
በአጠቃላይ የሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ግምገማው አብሮነት የሀገራችን ሕዝብ በሪፎርሙ ጅማሬ የተገባውን ቃል እና የፈነጠቀውን የፖለቲካ ምህዳር መሻሻል ተከትሎ የቋጠረው ተስፋ፣ ያሳደረው እምነት በጊዜ ውስጥ እየሟሸሸ፣ በሀገሪቱ የሚታየው ሁኔታ ከቁጥጥር ውጪ እየሆነ “የሽግግሩ መንግሥት” የሀገሪቱ ፍኖተ-ካርታ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በበዓለ ሲመታቸው ያደረጉት ንግግር ነው ከተባለው ጋር በከፋ ተቃርኖ ውስጥ ገብቷል። የሕግ የበላይነትን አክብሮ ስለማስከበር፣ የዜጎች ሀሳብን በነፃ መግለጽና መቀበል መብት፣ “አሸባሪዎች እኛ ነን” በማለት ይቅርታ ጠይቀው የሽብር ሕጉን ያወገዙበትና በዚህ ሕግ የታሰሩ ፍርደኞች የተፈቱበት፣ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት የፖለቲካ ፓርቲዎችን ተሳትፎ ያበረታቱበት፣ የሰብዓዊ መብት መከበር ለጥያቄ የሚቀርብ አይሆንም የተባለበት… ሌሎች አዎንታዊ ቃል-ኪዳኖች በፈጣን ሁኔታ ተቀልብሰው [ቀድሞ] ወደ ነበርንበት፣ ሲያልፍም ከድጡ ወደ ማጡ ሊያስብል በሚችል ወደ ከፋ ደረጃ መድረሳችንን ተረድቷል።
በሀገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ የሚታየው ሁለንተናዊ ምስቅልቅል፣ ያጋጠሙን ፈተናዎች ከውስጥም ከውጪም እየገዘፉ፣ እየሰፉና እየተወሳሰቡ መጥተው ከመንግሥት የቁጥጥር አቅም በላይ በመሆናቸው ችግሮቹን የብልጽግና መንግሥት በተናጠል ሊሸከማቸውም ሆነ ሊያስተካክላቸው ከሚቻለው በላይ ሆነዋል፤ መፍትሄውም አብሮነት ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ሲያቀነቅነው የነበረው “በሁሉን-አቀፍ የብሔራዊ መግባባት ውይይት ሕገ-መንግሥታዊና መዋቅራዊ ለውጥ የሚመጣበትን ሥርዓት የመዘርጋት ፖለቲካ መፍትሄ እንጂ በምርጫም ሆነ ሌላ ከብልጽግና ብቻ በሚቀርብ መፍትሄ አያገኝም። ከአማራጭ መፍትሄዎች አንዱ የሽግግርና እርቅ መንግሥት ነው” የሚለው አቋሙ ትክክልና ዛሬ የበለጠ ግልጽ መሆኑን አረጋግጧል።
በመሆኑም አብሮነት ሰላማዊ ትግሉን አጠናክሮ የመቀጠል ዓላማና ተልዕኮውን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትና ለዚህም ግንኙነቱን በማጽናት፣ ማጠናከርና በማስፋት ለመሥራት ቃልኪዳኑን አድሷል። ወደ ወቅታዊ ሁኔታዎች ስንገባ አብሮነት የፖለቲካ ፓርቲዎችን እንቅስቃሴና የፖለቲካ እስረኞችን፣ የሀገራችን ቀጣይ ምርጫና የትግራይ ምርጫ፣ በአዲስ አበባ የሚፈጸመውን ዘርፈ ብዙ ሕገ-ወጥ ተግባራት፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና በሀገራችን በጎርፍና በዜጎች ላይ በሚፈጸም ጥቃት እየደረሰ ያለውን አደጋ፣ የሚመለከቱ ጉዳዮችን ገምግመናል።
የፖለቲካ ፓርቲዎችን እንቅስቃሴ በሚመለከት፥ ከጅምሩ ታይቶ የነበረው የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሕጋዊና ሰላማዊ መንገድ ተደራጅተው እንዲንቀሳቀሱ የማበረታታት አካሄድ ተቀልብሶ ፓርቲዎች በሕጋዊ መንገድ በነፃነት ተንቀሳቅሰው ብቃት ያላቸው ተፎካካሪ ሆነው ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚያደርጉት አስተዋጽኦ በሕግ ማስከበር ስም በገዢው ፓርቲ እንዲገደብ ተደርጓል።
ለዚህም እንደቅድመ 2010 ከገዢው ፓርቲ በሀሳብ የሚለዩትን፣ የሚተቹና የሚቃወሙትን፣ በገዢ ፓርቲውና መንግሥት ባለሥልጣናት በተጨባጭ የሚፈጸሙ ሕገ-ወጥ ተግባራት እንዲቆሙ፣ እንዲስተካከሉና አጥፊዎች በሕግ እንዲጠየቁ የሚጠይቁትን፣ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችንና አባላት በፈጠራ ውንጀላ ማሰርና ማሰቃየት፣ ትናንት ከተወገዘው ባልተናነሰ፥ እንዲያውም በከፋ ሁኔታ እየተፈጸሙ ነው። በዚህም ከሰላማዊ ታጋይነታቸው ውጪ የማይታሙት የአብሮነት ከፍተኛ አመራሮች በፈጠራ ውንጀላ ለእሥራትና ሥቃይ ተዳርገዋል።
በፖለቲካ ሀሳብ ጥራታቸውና ነገሮችን አስቀድመው አርቀው በማስተዋላቸው የሚታወቁት ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ያለምንም ማስረጃ ተሰቃይተው በነፃ ተለቀዋል፤ ትናንት የብልጽግና ፓርቲ አባል እንዲሆኑ ተጠይቀው ያልተቀበሉት የሰላማዊ አማራጭ መፍትሄ ሀሳብ አፍላቂ እውቁ ፖለቲከኛ አቶ ልደቱ አያሌው በተጠረጠሩበት ወንጀል ፖሊስ ማስረጃ ሊያቀርብ ባለመቻሉ ነፃ መሆናቸው በፍርድ ቤት ቢረጋገጥም ለህይወታቸው አስጊ የልብ ህመምተኛ በመሆናቸው የቅርብ የሐኪም ክትትል እንደሚያስፈልጋቸው ማስረጃ አቅርበውም የፍትህ ሥርዓቱን ግምት ላይ በጣለ፣ ሰብዓዊነትን በረገጠ አሳፋሪ ሁኔታ ዛሬም በከፍተኛ ስቃይ ውስጥ ይገኛሉ። አዲስ አበባ ውስጥ በማስረጃ አስደግፎ እንዲያቆም ችግሩን አደባባይ ያወጣው፣ በቀዳሚነት የታገለው የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ሊቀ-መንበሩን ጨምሮ ከፍተኛ አመራሮችም የዚሁ ፈጠራ ወንጀል ሰለባ ከመሆን አልፈው በተወገዘው “የፀረ-ሽብር ሕግ” እንዲከሰሱ ተበይኖባቸዋል። በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከፖለቲካ አመለካከታቸውና አቋማቸው ጋር በተያያዘ ጉዳይ ክስ ሳይመሠረትባቸው፣ በትምህርት ቤቶች ጭምር ታስረው ይገኛሉ የሚሉ መረጃዎች በስፋት ይቀርባሉ።
አብሮነት ኮሮና ቫይረስ /ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከመከሰቱ አስቀድሞም “የሀገራችን ነባራዊና ወቅታዊ ሁኔታ በሀገራችን ነፃ፣ ዲሞክራሲያዊና ፍትሃዊ ምርጫ ማካሄድ አያስችልም፤ ምርጫ ቢደረግ የሀገሪቱን ችግሮች ከሚያባብስ በቀር መፍትሄ አይሆንም፤ ያሳለፍናቸው ተደጋጋሚ ምርጫዎች ለውስብስብ ችግራችን መፍትሄ አላመጡም፤ በቀጣይም ምርጫ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ቢደረግ ለውጥ አያመጣም፤ ለሀገራችን ዘላቂና አስተማማኝ መፍትሄው ሕገ-መንግሥታዊና መዋቅራዊ ለውጥ ነው፤ ይህ ፖለቲካዊ መፍትሄ ማለት ሁሉን አቀፍ የብሔራዊ መግባባት ውይይት ነው” የሚል ግልጽ አቋም መውሰዱ ይታወቃል። ይህንን አቋም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት አግዞት ሀገራዊ ምርጫው እንዲራዘም ተደርጓል። ይሁን እንጂ ብዙ ፓርቲዎች የእኛን የብሔራዊ መግባባት ውይይት መፍትሄ ሀሳብ ቢቀበሉትም ገዢው የብልጽግና ፓርቲ/መንግሥት ባለመቀበላቸው መንግሥት ዕድሜውን በሕገ- መንግሥት ትርጉም ስም ላልተወሰነ ጊዜ ሲያራዝም፣ ህወሓት ደግሞ ሕገ-መንግሥትን ማክበር በሚል የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የፌደሬሽን ምክር ቤትም ሆነ አስፈጻሚው እንዳይደረግ ቢወስኑም፣ ቢያሳስቡም፤ እምቢኝ በማለት ምርጫ በክልሉ አካሂዷል። ለዚህ ችግር ምላሽ ይሆናል፣ የውጥረቱን ጊዜ ያሳጥራል በሚል ይመስላል መንግሥት ከሰሞኑ ምርጫው በዚህ ዓመት ይደረጋል ሲል እየሰማን ነው፤ አንዳንድ እንቅስቃሴዎችም እየታዘብን ነው።
አብሮነት መንግሥት በሕገ- መንግሥት ሥም ዕድሜውን ያለገደብ ማራዘሙም ሆነ ህወሓት /የትግራይ ክልል መንግሥት ያቀረብነውን የብሔራዊ መግባባት ውይይት ቢቀበልም፥ ተግባራዊ ለማድረግ ከመታገል ይልቅ የተናጠል ምርጫ ማድረጉ ትክክል አይደለም፤ የሁለቱም – ብልጽግና እና ህወሓት – የእልህ አካሄድ የሀገሪቱን ፖለቲካ ወደ ከፋ ውጥረት ከማሸጋገር ያለፈ ሰላማዊና ዘላቂ አስተማማኝ መፍትሄ ሊያመጡ አይችሉም ብሎ ያምናል።
የሀገራችንና የአፍሪካ ዋና ከተማ በሆነችው አዲስ አበባ የሚፈጸሙት ዘርፈ-ብዙ ሕገ-ወጥ ተግባራት ካለፈው ጥፋት በቀጠለ ስህተት እና በዕውቀትና የፖለቲካ ዓላማ መሠረት አድርጎ በተነደፈ ስልት በስፋት እየተካሄደ ነው። በተለይ የመሬት ወረራና የኮንድሚኒየም ቤቶች ዝርፊያ ጎልተው ከወጡና አደባባይ ከዋሉ በርካታ ወራት ተቆጥረዋል። ዛሬ አቤቱታ አቅራቢዎች ቢበራከቱም የመጀመሪያው በማስረጃ የተደገፈ አቤቱታ አቅራቢዎች – የባልደራስ አመራሮች – ዛሬ ወህኒ ተጥለዋል። ችግሩ መፍትሄ አላገኘም፤ ጥያቄዎች አልተመለሱም፤ በቀረቡት ማስረጃዎች መሠረት የከንቲባ ሹም ሽር ከመደረግ ያለፈ አጥፊዎች ለሕግ አልቀረቡም፤ በቀጣይም ይህን ለማስተካከል ቁርጠኝነት ስለመኖሩ አመላካች እርምጃዎች አልታዩም፤ ይልቁንም በነበረው መሠረት ለማስቀጠልና “‹በከተማዋ የባለቤትነት ጥያቄ” ላይ የሚደረገው ሽኩቻ ሲባባስ እንጂ ለማስቆም የሚደረግ ጥረት አልተስተዋለም። በመሆኑም ችግሩ ወደ ከፋ ደረጃ እንዳያድግና በፍጥነት እንዳይስፋፋ፥ ብሎም ጥፋትና ስርቆቱን እንዳያባብስ አብሮነት ሥጋት ገብቶታል። አፋጣኝ ሕጋዊ የእርምት እርምጃ በመውሰድ የሕግ የበላይነት ማስከበር፣ ከተማይቱንም በግልጽ የአስተዳደራዊ ባለቤት ለሆኑት ነዋሪዎቿ ማስረከብ እንደሚያስፈልግ በጽናት ያምናል።
የኮቪድ-19/ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በሚመለከት በተለይ ከወረርሽኙ መከሰትጋርተያይዞ ተጥሎ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መነሳትን ተከትሎ በሕብረተሰቡ ላይ እየታየ ያለው መዘናጋት አብሮነትን አሳስቦታል። መንግሥት በአዋጁ መነሳት ሕብረተሰቡ እንዳይዘናጋ በቂ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን መሥራት ባለመቻሉ ሕብረተሰቡ ወረርሽኙ የለም የተባለ ይመስል ከፍተኛ መዘናጋት ውስጥ ገብቷል። ሕብረተሰቡ የበሽታው መከላከያ የሆኑትን እርምጃዎች ሁሉ በመተው እራሱን ለበሽታው በሚያጋልጡ እንቅስቃሴዎች ውስጥ በማስገባቱ በሽታው የበለጠ እንዳይስፋፋ አብሮነትን አስግቶታል። በመሆኑም መንግሥትም ሆነ ሕብረተሰቡ የወረርሽኙን አደገኛነት በመገንዘብ ለበሽታው የሚመጥን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ በአንክሮ ያሳስባል።
በሀገራችን በጎርፍ እየደረሰ ያለውን አደጋ፣ በተለያዩ የሀገራችን ክልሎች/አካባቢዎች ከመጠን በላይ በጣለው ዝናብ የአዋሽ ወንዝ፣ የኦሞ ወንዝ፣ የባሮ ወንዝ፣ የአባይ ገባር ወንዞች ከመሙላታቸው በተጨማሪ ከግድቦች በተለቀቀ ውሃ ከ580,000 በላይ ዜጎች ለጉዳት ተዳርገዋል፤ ከዚህ ውስጥ ግማሽ ያህሉ ተፈናቅለዋል። በሌላ በኩል በተለያዩ አካባቢዎች (ኦሮሚያ ክልል፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ ደቡብ ክልል/ኮንሶ…) በዜጎች ላይ ጥቃት እየተፈጸመ ነው፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በአሰቃቂ መንገድ እየተገደሉና በሺዎች ህይወታቸውን ለማትረፍ ከቀዬአቸው እየተፈናቀሉ ነው። በመንግሥት በኩል ለመከላከል በቂ ዝግጅት፣ አደጋው ከደረሰም በኋላ በቂ ክትትልና ድጋፍ ያለመደረጉን፣ እንዲሁም በቀጣይ ሊደርሱ ለሚችሉ አደጋዎች በቂ የመከላከል ዝግጅት እየተደረገ ያለመሆኑን፣ ከአካባቢው የሚደርሱን መረጃዎች ያመለክታሉ። በሌላ በኩል የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በዚህ ልክ በሀገራችን በደረሰው አደጋና ጉዳት ምንም ሳይሉ በጎረቤት ሀገር ሱዳን በደረሰው ሀዘናቸውን ገልጸዋል፣ እንዳይቀጥልም ከጎናቸው እንደሚቆሙ ቃል ገብተዋል። ዜጎች በማያውቁት በተፈጸመባቸው ጥቃት ለሞት ተዳርገዋል፤ እየተዳረጉም ነው። በተረፉት ዜጎቻችን የደረሰው አደጋን ተከትሎ የሚመጣው የጤናና ምግብ ችግር፣ እንዲሁም ሊደርስ የሚችለው አደጋ በአንድ በኩል፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ዝምታና “የራሷ እያረረባት፣ የሰው ታማስላለች” አካሄድ በሌላው፣ በእጅጉ ያሳስበናል። ስለዚህ መንግሥት በራሱ እና ሕዝቡንና ዓለምአቀፍ ማኅበረሰቡን በማስተባበር በአፋጣኝ እንዲደርስላቸው ያስፈልጋል።
በመጨረሻ ገዢው ፓርቲ /መንግሥት በአፈናና የሸፍጥ ፖለቲካ በተመሳሳይ መንገድ እየተጓዘ በፕሮፖጋንዳና ባዶ የተስፋ ቃላት ጋጋታ ፣ የተለየ ውጤትም ሆነ ችግሮቻችን መፍታት እንደማይችል በተደጋጋሚ ተመልክተናል። ስለዚህ አብሮነት ችግሮቻችንን በአስተማማኝና ዘላቂ መንገድ ለመፍታት፣ ሃቀኛ የብሔራዊ መግባባት ውይይት ለነገ የማይባል ተግባር እንደሆነ ያምናል፤ ገዢው ፓርቲ ለዚህ ያለውን ከፍተኛ ኃላፊነት እንዲወጣ በአጽንኦት ጥሪ ያደርጋል።
ለዚህ እንዲረዳም፡-
1ኛ/ በፖለቲካ አመለካከታቸው ከገዢው ፓርቲ በመለየታቸውና በሀገሪቱ ለሚታዩት ችግሮችና በሕዝብና ሀገር ሀብት ላይ እየደረሰ ያለውን በደል በማስረጃ አስደግፈው ተቃውሞ በማሰማታቸውና ጥያቄ በማቅረባቸው ብቻ የታሰሩ የፖለቲካና የኅሊና እስረኞች በአስቸኳይ እንዲፈቱ፤
2ኛ/ ለ27 ዓመታት አንድ ሆነው ሕዝባችን ሲያሰቃዩ የነበሩትና ዛሬ በሥልጣን ጥያቄና ያለፈውን በማስቀጠል ስልት ላይ ባለመስማማታቸው በተለያዩት በህወሓት እና በብልጽግና ፓርቲዎች መካካል ትናንትም ሆነ ዛሬ በሚደፈጥጡት ሕገ-መንግሥትና አምስት ጊዜ ባጭበረበሩት ምርጫ ሥም የሚታየው መካረርና ፍጥጫ በአስቸኳይ ተገትቶ፥ ለብሔራዊ መግባባት ውይይት ችግሮቻቸው እንዲፈታ የፖለቲካ ቁርጠኝነታቸውን እንዲያረጋግጡ፤
3ኛ/ የሀገራችን ችግሮች ምንጭ ምርጫ ባለመሆኑ፥ በምርጫም የሚፈቱ ያለመሆናቸው ባለፉት አምስት ምርጫዎች በመረጋገጡ፥ ለሕገ-መንግሥታዊና መዋቅራዊ የፖለቲካ መፍትሄ ምርጫ ለማድረግ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችም ሆነ እንዲደረግ የሚደረጉ ግፊቶች በአስቸኳይ ቆመው ሁሉንም ወገኖች የሚያሳትፍ የውይይት መድረክ እንዲመቻች ለዚህም ሁሉም ዜጋ አስፈላጊውን ተፅዕኖ በመንግሥት ላይ እንዲያሳርፍ፤
4ኛ/ መንግሥትም ሆነ ሕብረተሰቡ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን በመከላከል ረገድ እያሳዩ ያሉትን ቸልተኝነት በማቆም አስፈላጊውን የመከላከል ጥንቃቄና የመለየት ምርመራ እንዲያደርጉ፣ ለተጠቂዎች አገልግሎት ማቅረቡንና የግንዛቤ ማሳደግ ተግባራት በስፋት እንዲያከናውኑ፤
5ኛ/ በሀገራችን በተፈጥሮና ሰው-ሠራሽ ምክንያት ጎርፍ እያደረሰ ላለው ከፍተኛ አደጋ መንግሥት “የራሷ እያረረባት የሰው ታማስላለች” ከሚያስብል አካሄድ ወጥቶ በዜጎች ህይወት፣ ሥቃይ፣ የንብረት ውድመትና ቀጣይ ህይወት ላይ ትኩረት እንዲያደርግ፤
6ኛ/ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች እንደየቱም ክልል ነዋሪ የከተማቸው አስተዳዳራዊ ባለቤት መሆናቸው እንዲረጋገጥ፣ በከተማዋ የባለቤትነት መብት የሚደረገው በብልጽግና ውስጥ ጭምር የሚደረገው ሽኩቻ እንዲቆም፣ የተበዘበዘውና የተዘረፈው የከተማዋ ሀብት በሕግ ተመልሶ ለከተማዋ ልማት እንዲውል፣ አጥፊዎች ለሕግ እንዲቀርቡ፣ እንዲደረግ፤
7ኛ/ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች በዜጎች ላይ የደረሰው ጥቃት በገለልተኛ ወገን በአስቸኳይ እንዲጣራና ተገቢው ካሳ እንዲደረግላቸው፥ እንዲሁም አጥቂዎችና ተባባሪዎቻቸው በሕግ እንዲጠየቁ እንዲደረግ፣ ለጥቃቱ ሰለባዎች አስፈላጊው የዕለት ደራሽ ዕርዳታና የማቋቋሚያ ድጋፍ በአስቸኳይ እንዲደርሳቸው፤ ለዚህ ተፈጻሚነትም የፖለቲካ ፓርቲዎች ጅምሩ የብሔራዊ መግባባት ውይይት እንዳይነጠቅና በገዢው ፓርቲ እጅ እንዳይወድቅ፣ ከላይ ያቀረብናቸው እንዲፈጸሙ በልዩነታችን ውስጥ በሀገራዊ ጉዳዮች በቅድሚያ በሕግ የበላይነትን በማክበርና ማስከበር ለሰላምና መረጋጋት፣ ለሰብዓዊ መብት መከበር ተባብረን እንድንቆም ጥሪያችንን እናቀርባለን፤ ለተግባራዊነቱ ያለንን ቁርጠኝነት እናረጋግጣለን።
ከአሳታፊ ሁሉን አቀፍ ሃቀኛ የብሔራዊ መግባባት ውይይት ውጪ የቱም አንድ ፓርቲና ከብሔራዊ መግባባት ውይይት በፊት የሚደረግ የይስሙላ ምርጫ ለሀገራችን ችግሮች ዘላቂና አስተማማኝ መፍትሄ አያመጣም።
ከሁሉም በፊት መንግሥት የሕግ የበላይነት በማክበርና በማስከበር በሃቀኛ ሕዝባዊ ተሳትፎ የሀገራችን ሰላምና መረጋጋት፣ የዜጎችን የመኖር ሰብዓዊ መብት የማረጋገጥ ኃላፊነቱን ይወጣ፤ ከሥልጣኑ ይልቅ ለሀገርና ሕዝብ ጉዳይ ቅድሚያ ይስጥ።
አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌደራላዊ አንድነት (አብሮነት)
መስከረም 07 ቀን 2013 ዓ.ም
አዲስ አበባSeptember 9, 2020 at 1:47 pm #15795In reply to: ሰሞነኛ በተለያዩ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች የተማሪዎች ምርቃት
SemonegnaKeymasterሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ በተለያየ የትምህርት ዘርፎች ያስተማራቸውን 659 ተማሪዎችን አስመረቀ
ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች በቅድመ- እና ድኅረ- ምረቃ መርሀግብሮች ያሰለጠናቸውን 659 ተማሪዎችን ጳጉሜን 3 ቀን 2012 ዓ.ም አስመረቀ። ዩኒቨርሲቲው ለ12ኛ ዙር ለምረቃ ካበቃቸው ተማሪዎች መካከል 515 ወንዶች ሲሆኑ 144 ደግሞ ሴቶች ናቸው።
ዩኒቨርሲቲው በእጽዋት ሳይንስ፣ በእንስሳት ሳይንስ፣ በተፈጥሮ ሀብት አጠባበቅ፣ በኢኮኖሚክስ፣ በሥራ አመራር (Management)፣ እንዲሁም በጂኦግራፊና አካባቢ-ነክ ጥናቶች (Environmental Studies) በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ አስተምሮ አስመርቋል።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አህመድ ሙስጠፋ እንደገለጹት፥ ዩኒቨርሲቲው ከተቋቋመበት ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ የመማር ማስተማር፣ የምርምር እና የማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራዎችን ተግባራዊ ሲያደርግ ቆይቷል። እንደ ዶ/ር አህመድ ገለጻ፥ ዩኒቨርሲቲው ከዚህ ቀደም ከ15 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በማስመረቅ ለውጤት አብቅቷል።
እንደ ተጠባባቂ ፕሬዝደንቱ ገለጻ፥ ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ በተያዘው ዓመት በ46 የመጀመሪያ ዲግሪና በ23 የሁለተኛኛ ዲግሪ ፕሮግራሞች ከ17ሺ በላይ ተማሪዎችን በማስተማር ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
በጥናትና ምርምር ሥራዎች በሀገር አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ጭብጦች 18 የምርምር ንድፈ ሀሳቦች የቀረቡ ሲሆን፥ ከእነዚህ ውስጥ 15ቱ ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል ብለዋል – ዶ/ር አህመድ። የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከልም ከ3 ሺህ ሊትር በላይ የንጽህና መጠበቂያ ፈሳሽ (ሳኒታይዘር) በማምረት አገልግሎት ላይ እንዲውል ተደርጓልሲሉ አስረድተዋል።
የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ እና የዩኒቨርሲቲው ምክትል የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ፍቅሬ አማን በክብር እንግድነት ተገኝተው ባስተላለት መልዕክት፥ እንዳሉት የዘንድሮው የምረቃ በዓል ለዓለማችን፣ ብሎም ለሀገራችን ህዝቦች የኮርና ቫይረስ ወረርሽኝ ፈታኝ በሆነበት በዚህ ወቅት ተመራቂዎች የጥናትና ምርምር ሥራዎችን በማጠናቀቅ ለውጤት በመብቃታቸው የተሰማቸውን ልባዊ ደስታ ገልጸዋል።
ሀገራችን በመደመር ፍልስፍና ከነበረችበት ችግር ወጥታ ወደ ብልጽግና ጎዳና እየተጓዘች ባለችበት በዚህ የይቅርታና የምኅረት ወር በሆነችው በጳጉሜ ወር ተማሪዎች ለምረቃ በመብቃታቸው እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል።
ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞውን ሚዛን ተፈሪ ግብርና ኮሌጅ መሠረት አድርጎ በደቡብ ክልል ሚዛን ተፈሪ እና ቴፒ ከተሞች በ1999 ዓ.ም የተቋቋመ ዩኒቨርሲቲ ነው።
September 8, 2020 at 7:25 pm #15784In reply to: የፖለቲካ ፓርቲዎች ድምጽ (ኢትዮጵያ ውስጥ የሚነቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች)
AnonymousInactiveአዲስ አበባ በራሷ ግዛተ-መሬት ላይ የፌዴራል አድያምነት /ክልልነት/ መብት ሊረጋገጥላት ይገባል!
ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲየኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አወቃቀር በመመዘኛዎቹ ላይ በኢትዮጵያ ተፃራሪ አቋም ባላቸው ልሂቃን ዘንድ ስምምነት ላይ ሊደርስ ቢችል፣ ፌዴራላዊ የመንግሥት አደረጃጀት የፖለቲካ አለመግባባት መንስ ዔ ሊሆን የሚችል አልነበረም። ይህ ጥያቄ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግር ዋነኛ መገለጫ ሊሆን የበቃው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ልሂቃን በዚህ ጥያቄ ዙሪያ ላለፉት ሃምሳ ዓመታት ሊግባቡ ባለመቻላቸው ነው። ሊግባቡ ያልቻሉበትም ምክንያት በኢትዮጵያ ሀገረ-መንግሥት የግንባታ ታሪክ ላይ ልዩነታቸውን ማጥበብ ባለመቻላቸው ነው። ይህ ትውልድ ደግሞ በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት በ1940ዎቹ ዓመታት ተወልዶ በ1950ዎቹ መጨረሻና በ1960ዎቹ መጀመሪያ ላይ ለዩኒቨርሲቲ ደረጃ የደረሰው ትውልድ ነበር። እንደ አጋጣሚ ሆኖ በ1960ዎቹ ሁኔታ ደግሞ ዓለም በሁለት ተፃራሪ የካፒታሊዝምና የሶሻሊዝም ጎራዎች ፉክክር ተቀስፋ ተይዛ የነበረችበት ወቅት ነበር። በ1960ዎቹ ለጉልምስና ከደረሰው ትውልድ ውስጥ አብዛኛው ነው ባይባልም ተራማጅ የሆነ አስተሳሰብ አለኝ ብሎ ያቀነቅን የነበረው የትውልዱን የአመራር ሚና የተጫወተው የማርክሲዝም ሌኒኒዝም (Marxism–Leninism) አስተምህሮ የተቀበለው ነበር።
ይሁንና የዚህ የ1960ዎቹ የተማሪ አብዮተኞች እና የ እ ነሱ ከፊል ውጤት ሆነው ያቆጠቆጡት የነገድ ድርጅት መሪዎች የኢትዮጵያን ታሪክ በተፃረረና ባልተገናዘበ ሁኔታ የሶቭየት ሕብረትን የኮሚኒስት ፓርቲ መሪ የስታሊንን “የብሔርና የቅኝ ግዛት ጥያቄ” መጽሐፍ ቃል በቃል በመገልበጥ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ዋነኛ ችግር “የጨቋኝና የተጨቋኝ ብሔረሰቦች መስተጋብር ነው” የሚል የሀሰት የታሪክ ትርክት ይዘው ተነሱ። እነዚህ ከተማሪ አብዮተኝነት ወደ ነገድ ድርጅትነት የተሸጋገሩት ከደርግ መንግሥት ጋር ለ17 ዓመታት ጦርነት አድርገው በታሪካዊ የኢትዮጵያ ጠላቶች ያላሰለሰ ድጋፍ በ1983 ዓ.ም በኢትዮጵያ ጦር ላይ ድል ሊቀዳጁ በቁ። አነዚህ ኃይሎች በተጠናወታቸው “የጨቋኝና የተጨቋኝ ብሔረሰቦች” የሀሰት ትርክት ውጤት የሆነውን የመገንጠል መብት ሕገ-መንግሥታዊ መብት ያደረገ፣ ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ ያለመ ቋንቋን መሠረት ያደረገ መንግሥታዊ የፌዴራል አወቃቀር በኢትዮጵያ ላይ አነበሩ።
በሀገራችን ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ የጐሳና የዘረኝነት ፖለቲካዊ አደረጃጀት የመንግሥት የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ አደረጃጀት ዓይነተኛ መገለጫ ከመሆን አልፎ ይኸው ዓይነት አደረጃጀት ወደ እምነት ተቋማት ሳይቀር ዘልቆ እንዲገባ ተደረገ። በሀገሪቱ ታሪክ በማይታወቅ ሁኔታ በተረኝነት መንፈስ የተቃኘ ተቋማዊ/መንግሥታዊ ሙስና እና የፍትህ መዛባት የሥርዓት መገለጫ ሊሆን በቃ። ከሕዝቡ ታሪካዊ አሠራር ጋር ባልተገናዘቡ የክልል አደረጃጀቶች ምክንያት በሀገራችን እንግዳ በሆነ መልኩ ማንነትን እና እምነትን መሠረት ያደረጉ ግጭቶች እንዲበራከቱ፣ ሕዝብ የተረጋጋ ሕይወት እንዳይኖረው በፌዴራል መንግሥቱና በክልል መንግሥታት መካከል የኃላፊነትና የተጠያቂነት ጉዳይ አሻሚ በማድረግ፣ የሀገሪቱ ብሔራዊ ስሜት እንዲላሽቅ በምትኩ ጠባብና ክልላዊ አስተሳሰብ እንዲሰፍን ተደረገ። በኢትዮጵያ የዘውግ ፌዴራሊዝም ሥርዓት ችግር ብሔረሰብን ዋነኛው የፌዴራል ሥርዓቱና የሀገር መንግሥት ግንባታ መሠረት ማድረጉ ነው።
እዚያው ተወልዶ ያደገውና ከአራቱም የኢትዮጵያ ማዕዘናት የመጣውን የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ አንድ ብሔረሰብን እና አንድ ቋንቋ ተናጋሪነትን መሠረት አድርጎ በተዋቀረ ክልል ውስጥ አስገብቶ እንዲተዳደር ማድረግ ፍትሃዊነት የለውም። የአዲስ አበባ ሕዝብ ጥያቄ ከራሴ ውጭ በእኔ ዕጣ ሌላ ሊወስንብኝ አይገባም የሚል ነው። አዲስ አባባ በኦሮሚያ ምድረ ፅፋዊ (geographic) ክልል ውስጥ በመገኘቷ ብቻ ለአዲስ አበባ ባለቤትነት የመብት መብለጫ፣ ለተፈጠረ ውጥንቅጥ ደግሞ የአዲስ አበባ ሕዝብን መብት ማሳነሻ ማድረግ በምንም መመዘኛ ተገቢነትም ሆነ ተቀባይነት የለውም።
የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት በአንቀጽ 69 “የፌዴራሉ መንግሥት ርዕሰ ከተማ አዲስ አበባ ነው። የከተማው አስተዳደር ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ ሥልጣን ይኖረዋል። ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል” ይላል። የአዲስ አበባ ከተማ ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ ሥልጣን እንዳለው ቢታወቅም የህወሓት እና የኦነግ በሆነው ሕገ-መንግሥት ውስጥ “በአዲስ አበባ ከተማ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ጥቅም ይኖረዋል” በሚል መካተቱ ችግሩን ሆን ተብሎ እንዲወሳሰብ አድርጎታል።
በ1989 ዓ.ም የወጣው የአዲስ አበባ ከተማ አስተደደር ማቋቋሚያ ቻርተር መሠረት አዲስ አበባ ራሷን በራሷ እንድታስተዳድር ሲደነገግ፣ በሕገ-መንግሥቱም ሆነ በአዲስ አበባ ከተማ ቻርተር መሠረት የከተማዋ ስምና ስያሜ አዲስ አበባ እንደሆነ ተደንግጓል። ይሁንና ቻርተሩን መሠረት በማድረግ ተዘጋጅቶ የቀረበው ረቂቂ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ የመጽደቅ ሂደቱ በደባ እንዲቀር ተደርጓል። አዲስ አበባ እንደ ዋሽንግተን ዲሲ እና እንደ ካንቤራ (Washington, DC and Canberra) የፌዴራል መንግሥት ግዛት ናት የሚል የሕግ አንቀጽ የለም። ይህ አይደለም እንዳይባል በወንጀልም ሆነ በፍትሀ-ብሔር ጉዳይ በአዲስ አበባ የግዛት ክልል ውስጥ የተፈፀመ ወይም የተከናወነ የሕግ ጥሰት ግን ልክ የፌዴራል መንግሥት ይዞታ አንደሆነችው ዋሽንግተን የመዳኘት ሥልጣንን ለፌዴራል መንግሥቱ ይሆን ዘንድ በሕግ ተለይቶ ተሰጥቷል። ማለትም በተግባር የፌዴራል መንግሥቱ አዲስ አበባን እና ድሬደዋን የራሱ ግዛት አድርጓቸዋል።
ሕገ-መንግሥቱ አዲስ አበባ እራሱን የማስተዳደር ሙሉ ሥልጣን የሰጠው መሆኑ ከላይ የተጠቀሰው የወንጀልና የፍትሀ-ብሔር ጉዳዮችን ለመዳኘት ከተሰጠው ሥልጣን ጋር ሲዳመር አዲስ አበባ ልክ እንደ ዋሽንግተን የፌዴራል ግዛት እንደሆነች ለመረዳት ይቻላል። በተጨባጭ ግን አዲስ አበባ ከተማ የተተወላት የከተማ-ነክ አስተደደርና ከማዘጋጃ ቤት አገልግሎት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን የመዳኘት ሥልጣን ነው። ማለትም ስለ ዳኘነት ሲሆን መሬቱ የፌዴራል መንግሥት፣ ስለ ሌሎች አስተዳደራዊ ጉዳዮች ሲሆን የከተማ መስተዳድሩ ሆኗል።
አዲስ አበባ ራሷን የማስተዳደር መብት በሕገ-መንግሥቱ የታወቀ ቢሆንም፤ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ጭምር ኢ-ፍትሀዊ በሆነ መንገድ ውክልና የላትም። ሕገ-መንግሥቱ ከሚደነገገው ውጭ ስትደዳደር የቆየችው በህወሓት/ኢህአዴግ፣ አሁን ደግሞ በኦህዴድ/ብልጽግና ነው። በሌሎች ክልሎች ክልሎችን የሚያስተዳድሩ የክልል ፓርቲዎች አሉ /ትግራይ፣ ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብ ወዘተ…/ አዲስ አበባ ላይ ግን የሚወክላት የፖለቲካ ፓርቲ የለም። ገዥ ፓርቲዎች ፍላጎታቸውን የሚጭኑባት ከተማ ናት። ቀደም ሲል ህወሓት/ኢህአዴግ አሁን ደግሞ ኦህዴድ/ብልጽግና ፓርቲ አዲስ አበባን ማስተዳደሩን ቀጥሎበታል። ይህ ሁኔታ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በሕገ-መንግሥቱ የተሰጣቸውን ራሳቸውን የማስተዳደር መብት ፍፁም የሚጥስ ነው።
አዲስ አበባን እንዲመራ የሚመደበው በገዢው ፓርቲ ውስጥ ከነበሩ ወይም ካሉ የክልል ገዢ ፓርቲዎች እንጂ በከተማው ሕዝብ ነፃ ምርጫ አልነበረም፤ አሁንም አይደለም። አዲስ አበባ ቀደም ሲል ከሁለቱ ክልሎች /ትግራይ፣ ኦሮሚያ/ አሁን ከ “ለውጡ” ወዲህ ደግሞ ከኦሮሚያ ክልል በሚመጡ ተሹዋሚዎች እንድትደዳደር መደረጉ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ጥቅምና ፍላጎት እንዳይከበር ያደረገ የፖለቲካ ደባ ነው። ከዚህም ባሻገር ከ7 ሚሊዮን የሚልቀውን የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ በኢኮኖሚ እንቅስቃሴው በግብር መልክ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ለመንግሥት ካዝና የሚያስገባውን ነዋሪ የፖለቲካ ባይተዋር ያደረገ እና በዕጣ ፈንታው ላይ እንዳይወስን ያደረገ ኢ-ፍትሀዊ የሆነ የፖለቲካ አካሄድ ነው። የአሜሪካን አብዮት እንደቀሰቀሰው /Taxation without Political Representation/ እንደሚለው መፈክር ሠርቶ ግብሩን እየገበረ የፖለቲካ ባይተዋር በማድረግ በዕጣ ፈንታው ላይ እንዳይወስን አድርጎታል። ይህ ፍትሀዊ ያልሆነ የፖለቲካ አካሄድ ከመሆኑም በተጨማሪ በግልጽ የሕገ-መንግሥቱን አንቀጽ 49 እና አንቀጽ 89 ይጥሳል።
የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት ትልቁ ወለፈንዲ የአዲስ አበባ ጉዳይ ነው። በአንቀጽ 69 መሠረት የአዲስ አበባ ከተማ የፌዴራሉ ርዕሰ ከተማ እና የከተማው ነዋሪ ሕዝብ እራሱን በራሱ የማስተዳደር መብት ይኖረዋል ሲል ደንግጓል። ማለትም፥ አዲስ አበባ የተወላጆቿና እና የሁሉም ከ80 በላይ የሆኑት የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች በባለቤትነት የሚኖሩባት ከተማ ናት። የአዲስ አበባን አስተዳደር ስንት አማራ፣ ስንት ኦሮሞ፣ ስንት ትግሬ፣ ስንት ጉራጌ፣ ስንት ወላይታ፣ ስንት ሱማሌ፣ ስንት አደሬ፣ ስንት ጋምቤላ፣ ስንት ቤንሻንጉል፣ ስንት ማኦ ወዘተ… እንደሚኖሩባት በተጨባጭ የተረጋገጠ አሃዛዊ መረጃ (statistics) ስለሌለ የአዲስ አበባ ባለቤትነት ሊሰጥ የሚችለው ከሕገ-መንግሥቱ መንፈስ ውጭ ለመላ ቋሚ ነዋሪዎቿ ነው ሊሆን የሚችለው። ይሁንና የአዲስ አበባን ከተማ ባለቤትነት በተመለከተ እንደ ሌሎች የፌዴራል መንግሥት ዋና ከተማዎች እንደሆኑት እንደ ሞስኮ፣ በርሊን፣ ቪየና እና ብራስልስ ለፌዴራል መንግሥት ተጠሪ ያልሆኑ፣ በኢትዮጵያም ከ1983 ዓ.ም ሰኔ ወር ጀምሮ ሕገ-መንግሥቱ ተግባራዊ እስከ ተደረገበት 1987 ዓ.ም ነሐሴ ወር ድረስ ክልል 14 ተብላ የክልልነት ደረጃ የተሰጠበትን ሁኔታ መልሶ ተግባራዊ ማድረግ ፍትሃዊ እና የነዋሪዎቿን ሕጋዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ነው።
አዲስ አበባ እንደ ፌዴራል መንግሥት ርዕሰ ከተማነቷ የግዛተ-መሬቷ ባለቤትነትን ለፌዴራል መንግሥቱ ሳይሆን በሽግግር ወቅት እንደነበረው በፌዴራል አድያምነት /በክልልነት/ ደረጃ እንደገና እንድትዋቀር ባልደራስ እውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) ለከተማዋ ሕዝብ ጥሪውን ያቀርባል።
ከሀገራችን ዘመናዊ የታሪክ ጅማሮ ጋር የተሰናሰለ እድሜ ያላት አዲስ አበባ ከተማ፥ በመልክ-ዕምድር አቀማመጧ የሀገሪቱ እምብርት ላይ መገኘቷ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታዋን የጎላ አድርጓታል። ይህ ሁኔታዋ ለሀገራችን ዜጎች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ለመስጥ የሚያስችል አቅም ያላት ከተማ እንድትሆን ሰፊ ዕድል ሰጥቷታል። ነገር ግን ከተማዋ ያላትን ሰብዓዊና ቁሳዊ አቅም አሟጣ በመጠቀም ለነዋሪዎቿ ተስፋ መሆን እንዳትችል በሀገራቸን የነበሩ እና ያሉት ገዢዎች አተያይ እና የአመራር ፈሊጥ ትልቅ ተግዳሮት ሆኗል። “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ ጎሳን መሠረት ያደረገው የባለፉት 30 ዓመታት የሀገራችን ፖለቲካን ያነበረው ሥርዓት የአዲስ አበባ ከተማን ህልውና የበለጠ ተፈታትኖታል፤ ከባድ አደጋንም የፈጠረ ሆኗል።
አዲስ አበባ የሀገራችን ርዕሰ መዲና ከመሆኗ ባሻገር፣ የአፍሪካ ሕብረት እና የጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ተምሳሌትና መናኸሪያ፣ የትላልቅ ዓለም አቀፍ ተቋማት መታደሚያ ናት። የሀገራችን 65% ምጣኔ-ሀብት በአንበሳ ድርሻነት ይዛለች፤ በሀገሪቱ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ቤተ-እምነቶች እና የእምነቱ ተከታዮች ተቻችለው የሚኖሩባት የአብሮነት መገለጫ ከተማ ስትሆን፥ የታሪካችን መገለጫ የሆኑ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርስ እና ትውፊት የተመዘገበባት፣ እንዲሁም የተለያዩ ቋንቋዎችና ባህሎች ሕብር ፈጥረው በነፃነት የሚንጸባረቁባት የኢትዮጵያ ብዝሃነት ማሳያ ፈርጥ ናት።
ከተማችን አዲስ አበባ ባለፉት 3 አስርት ዓመታት ሲመሯት የነበሩት ሁሉ ምን ልጠቀምባት እንጂ ምን ላድርግላት የሚል ኃላፊነት የሚሰማቸው ባለመሆኑ ችግሮቿን የተወሳሰቡ አደርጎታል። እንደ ፓርቲያችን እምነት፥ ለዚህ ችግር በዋነኝነት ያጋለጣት በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠ አስተዳድር ተሰይሞ ሊያስተዳድራት አለመቻሉ ጉልህ ስፍራ ይይዛል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን በከንቲባነት ሲመሩ የቆዩት ግለሰቦች በአብዛኛው የከተማውን ነዋሪ ሥነ-ልቦና በቅጡ ያልተረዱ፣ ራዕይ-አልባ የሆኑ እና ከፍተኛ የብቃት ጉድለት የሚስተዋልባቸው ናቸው።
አዲስ አበባ ከተማ ራስ ገዝ (በአሁኑ አጠራር ክልል) እንድትሆን መሆኑ እውነተኛ ፌዴራላዊ አስተዳደር በኢትዮጵያ ውስጥ ለማንበር በሚደረገው ጥረት ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ያምናል፤ በመሆኑም አዲስ አበባ ራስ ገዝ አስተዳደር እንዲኖረው በላቀ መንገድ መታገል አስፈላጊ ሆኗል።
የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ላለፉት ዘመናት በተለይም የህወሓት/ኢህአዴግ ሥልጣን ዘመን ጀምሮ በመረጠው የመተዳደር መብቱን ተነፍጎ፣ ከኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ኦህዴድ በውክልና ተቀብሎ አስተዳድራለሁ በሚል የተረኝነት፣ የሙስና፣ የባህል በአጠቃላይ የዘረኝነት ሰለባ ሆኗል። የተረኛነት ስሜት ነቀርሳ የሆነበት ኦህዴድ/ብልጽግና የአዲስ አበባን ሕዝባዊ አውቃቀር (demography) ከመቀየር ጀምሮ ተጠንቶ የከተማው ሕዝብ ባልመከረበት የትምህርት ሥርዓት ውስጥ ረጅም እጁን ሕገ-ወጥ በሆነ መንገድ በመስደድ፣ የከተማውን መሬት በማስወረር እና ነዋሪው ጥሮ ግሮ ቆጥቦ የሠራውን ቤት አንዴ ለኦሮሚያ የመንግሥት ሠራተኞች በሚል ሌላ ጊዜ ደግሞ የተለየ ምክንያት በመስጠት እየዘረፈ መሆኑ የከተማዋን ነዋሪ በደል ጫፍ አድርሶታል።
ዛሬ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞካራሲ ፓርቲ ይህንን የዘመናት የአዲስ አበባ ሕዝብ ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ መብቱን የሚጠይቅበት ጊዜ ላይ መድረሱን ተገንዝቧል። በኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ፍትህ ማግኘት የሚቻለው የከተማው ነዋሪ ራሱ የመረጠው ሥርዓት ሲዘረጋ መሆኑን በቅርቡ ተረድቷል። አሁን እየደረሰበት ያለው ግፍ መነሻው ለሕዝብ ተጠያቂነት ያለው ትክክለኛ አስተዳደር አለመኖሩና ይህንን ተገን በማድረግ ወደ ዝርፊያ የገቡና ለዚሁ ሁኔታ እንዲያመቻቸው ብቻ የሚሠሩ የውክልና መሪዎች በመሆናቸው ከእነዚህ አስተዳደር ውጭ እንዲሆን ለማስቻል ዴሞክራሲን ለማስፈን እንዲረዳ ነው።
ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ አዲስ አበባ ከተማ ራስ ገዝ እንድትሆን ብዙ ዜጎች ጥያቄ ሲያነሱ እንደነበረ ያምናል። ይህ የከተማው ነዋሪ ጥያቄም፣ ፓርቲው እንዲመሠረት ገፊ ምክንያት እንደሆነ በመገንዘብ፣ ትላንት ዜጎች ሲያነሱት የነበረው ጥያቄ ወደላቀ ምዕራፍ መሸጋገሩን በማብሰር፤ የአዲስ አበባ ሁለንተናዊ ችግር አስጨንቋቸው እና እንቅልፍ ነስቷቸው ለነበሩ ዜጎች ሁላ ይህ የእናንተ የትላንትና የትግል ጥያቄ በመሆኑ ከፍ ያለ ምስጋና ይገባችኋል። የዜጎች በደልና ጭቆና እንዳንገበገባችህ እናምናለን፤ ይህንንም ለመቅረፍ በጋራ እንድንቀሳቀስ እንጠይቃለን።
ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ የከተማችንን ነዋሪ የሚመጥን አስተዳደር እንዲዘረጋ የሚያደርገው ጥረት፣ ከአንድ የፖለቲካ ድርጅት ጥያቄ በላይ እንደሆነ ያምናል። በመሆኑም በሀገራችን የምትገኙ የፖለቲካ ኃይሎች፣ ለከተማው ነዋሪ የራሱን ራስ ገዝ አስተዳደር እንዲመሠረት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍና ትብብር እንድታደርጉለት፤ ምሁራን እና ታዋቂ ግለሰቦችም የሚመሠረተው አስተዳደር የሚያስፈልገውን ድጋፍና አወቃቀር በአግባቡ እንዲይዝ መልክ ለማስያዝ የሚረዳ ልምዳችሁን፣ እውቀታችሁን እንዲሁም ተፅዕኖ የመፍጠር አቅማችሁን እንድታበረክቱ ጭምር አደራ ይላል።
በዋነኝነት የአዲስ አበባ ራስ ገዝ አስተዳደር ባለቤት ሁሉም የከተማው ነዋሪ እንደሆነ ባልደራስ በጽኑ ያምናል። ይህንንም ለማድረግ የሚያስችል ሕጋዊና ሰላማዊ ትግል በማድረግ የፌዴራል መንግሥት ጥያቄውን እንዲቀበልና በሀገሪቱ አሁን ባለው ሥርዓት መሠረት ሕዝበ-ውሳኔ ተካሂዶ የራስ ገዝ አስተዳደር (ክልል) እንዲሆን እንጠይቃለን። ይህንንም ጥያቄ እውን ለማድረግ እና በሕጉ አግባብ እንዲስተናገድ ለማድረግ የተከማው ነዋሪ የስምምነት ፊርማ የማሰባሰብ ሂደት ውስጥ ተሳታፊ እንዲሆን ጥሪ እናቀርባለን። ጥሪውም በነዋሪ ሕዝቧ ፍላጎት ላይ የተመሠረተ መሆኑን ለማስረገጥ ድጋፉን በፊርማ የሚያቀርብበት የአሠራር ዘዴ ይቀይሳል።
በመጨረሻም ይህንን የጳጉሜን ሣምንት በግፍ ለታሰሩ የፓርቲያችን መሪ አቶ እስክንድር ነጋ፣ አቶ ስንታየሁ ቸኮል፣ ወ/ሮ ቀለብ ስዩም እና ሌሎች የፓርቲው አባላትና አመራሮች በግፍ ከታሰሩበት እንዲፈቱ በተለያዩ መንገድ ግፊት ለምታደርጉ ወገኖች ምስጋናችንን እያቀረብን፥ መንግሥት በማን አለብኝነት ያለኃጢያታቸው አስሯቸው የሚገኙ ንፁሃን መሪዎቻችንን እና አባላቶቻችንን በአስቸኳይ እንዲፈቱ በድጋሚ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
መጪው የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት፣ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት ተላቀን በሰላም ወጥተን የምንገባበት፣ ለሀገራችን ዜጎች ሰብዓዊ መብት የሚከበርባት፣ ለተበደሉ ፍትህ የሚሰፍንበት፣ ዴሞክራሲ የሚያብብበት እንዲሆን እንመኛለን፤ ለብሔራዊ መግባባት ሁሉም የፖለቲካ ወገኖች አንድ ላይ ተቀምጠው ስምምነት ላይ የሚያደርስ ተጨባጭ ሥራዎች የምናከናውንበት ዘመን እንዲሆን መልካም ምኞቱን ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ይገልጻል።
ድል ለእውነተኛ ዲሞክራሲ!
ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ)
ጳጉሜ 3 ቀን 2012 ዓ.ምSeptember 5, 2020 at 11:54 pm #15731In reply to: ሰሞነኛ በተለያዩ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች የተማሪዎች ምርቃት
AnonymousInactiveወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ መርሀግብሮች ያስተማራቸውን ከ900 በላይ ተማሪዎችን አስመረቀ
ወልቂጤ (ሰሞነኛ) – የሦስተኛ ትውልድ ዩኒቨርሲቲ የሆነው ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ መርሀግብሮች ያስተማራቸውን 929 ተማሪዎች ነሐሴ 30 ቀን 2012 ዓ.ም ለሰባተኛ ጊዜ ባካሄደው የምረቃ ሥነ ሥርዓት አስመርቋል።
በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ በክብር እንግድነት ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሙሉ ነጋ እንዳሉት፥ እውቀትና ብቃት ያለው የሰለጠነ የሰው ኃይል ለአንድ ሀገር እድገትና ቀጣይነት የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው። በዚህ ረገድ ጥራትና አግባብነት ያለው ትምህርት በተለይ ደግሞ ከፍተኛ ትምህርት ማስፋፋት ወሳኝ ነው ብለዋል።
ዶ/ር ሙሉ አክለውም፥ መንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሀገራችንን ሕዝብ ህይወት ቀላልና ዘመናዊ በማድረግ ወደተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር ቁልፍ ሚና እንዳላቸው በማመን በየዓመቱ ከፍተኛውን የሀገሪቱን በጀት ለትምህርት መድቦ እየሠራ ይገኛል ብለዋል።
ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የለውጥ ሃሳቦችን በማፍለቅና በመተግበር መልካም አርአያ የሚሆኑ ዜጎችን ማፍሪያ፣ የዲሞክራሲያዊ አስተሳሰቦችና ቴክኖሎጂዎች መፍለቂያ፣ የባህላዊ እሴቶቻችን መጎልበቻ፣ የሕዝቦች የመተሳሰብ፣ የመቻቻልና የአብሮነት ባህል የሚቀመርባቸው ማዕከላት እንዲሆኑ ማድረግ አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው ብለዋል – ዶ/ር ሙሉ።
ሚኒስትር ዴኤታው ሰላም በምንም ነገር የማይተካ መሆኑን ገልጸው፥ ተመራቂዎች የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት እንዲደግፉና በህይወት ጎዳናቸው ከጽዩፍ አስተሳሰብና እና ድርጊት ተጠብቀው በተሰማሩበት መስክ የችግሮች መፍትሄ በመሆን ሀገራቸውን እንዲያገለግሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዶ/ር ሙሉ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸው፤ ተመራቂዎች ሀገራችሁንና ሕዝባችሁን በሚጠቅሙ ሥራዎች ላይ በመሰማራት ታታሪ፣ የሀገራችሁን ሁለንተናዊ እድገት እና ብልጽግና የምታረጋግጡ ሰላም ወዳድ እንድትሆኑ አደራ እላለሁ ብለዋል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፋሪስ ደሊል በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በአዋጅ የተሰጠውን ተልዕኮ ለማሳካት በምርምር፣ በማኅበረሰብ-አቀፍ አገልግሎት (community-based service) እና መማር-ማስተማር መስክ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ገልጸው፤ በተለይም ኮቪድ-19 ከመጣ በኋላ የዩኒቨርሲቲው ሠራተኞች የአንድ ወር ደመወዛቸውን በማዋጣት አቅመ ደካሞችን መርዳታቸውን ገልጸዋል። ዩኒቨርሲቲው ከ3,000 ሊትር በላይ ሳኒታይዘር፣ 4,000 የፊት ጭንብል (face-mask)፣ 1800 ብሊች (bleach) የማምረት ሥራዎችን ሠርቶ በጉራጌ ዞን ለሚገኙና በሥራ ጸባያቸው ለቫይረሱ ተጋላጭ ለሆኑ ተቋማት ማበርከቱን ጠቁመዋል። ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የለይቶ ማቆያ ማዕከል (quarantine center) ሆኖ በማገልገል ላይም ይገኛል ብለዋል።
በምርምር ረገድም ድርቅን በመቋቋም የሚታወቀውን ቆጮን ጨምሮ በተለያየ መልኩ ለምግብነት የሚውለውን እና የአከባቢው ማኅበረሰብ የኑሮ አለኝታ የሆነውን የእንሰት ተክል እንዳይጠፋ፣ እንዲሁም ዝርያው እንዲጠበቅና እንዲሻሻል የእንሰት ማዕከል በማደራጀት ዝርያዎችን የማሰባሰብ ሥራዎችን እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
ዶ/ር ፋሪስ ባስተላለፉት መልዕክት ተመራቂ ተማሪዎች ሥራ ወዳድና ታታሪ፣ በሕግ የበላይነት ላይ የማትደራደሩ፣ የጥላቻን ዘር የማትዘሩ በጥላቻ ሳይሆን የተዘራውን ክፉ አረም በፍቅርና አብሮነት የምትነቅሉ በሥነ-ምግባር የታነጻችሁ ሀገር ተረካቢ ብቻ ሳትሆኑ አሻጋሪ ናችሁ ብለዋል።
በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የዛሬው ምረቃ ሥነ ሥርዓት የተሳተፉት በክረምትና በማታ መርሀግብሮች በአምስት ኮሌጆች ስር በሚገኙ 15 ትምህርት ክፍሎች ከዓለምአቀፉ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ (ኮቪድ-19) በፊት ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ወንድ 597፣ ሴት 143፤ በድምሩ 840 የቅድመ ምረቃ ተማሪዎች እና በቢዝነስና ኢኮኖሚክስ እንዲሁም በግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጆች ስር በሚገኙ አራት ትምህርት ክፍሎች ከወረርሽኙ በኋላም በቴክኖሎጂ አማራጮች ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ በመደበኛና በማታው የድኅረ ምረቃ መርሀግብሮች ወንድ 81፣ ሴት 8፤ በድምሩ 89 ምሩቃን ናቸው።
በ2004 ዓ.ም በ13 የትምህርት መስኮች 595 መደበኛ ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር የጀመረው ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በአሁኑ ጊዜ በስምንት ኮሌጆችና አንድ ትምህርት ቤት በቅድመ ምረቃ 50 መርሀግብሮች እንዲሁም ሁለተኛ ዲግሪ እና 12 ፕሮግራሞች በጠቅላላው ከ14 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በመደበኛ፣ በማታና በክረምት መርሃ ግብሮች እያስተማረ ይገኛል።
ምንጭ፦ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር
September 1, 2020 at 12:00 pm #15682In reply to: ነፃ አስተያየት (ስለኢትዮጵያ በኢትዮጵያውያን)
AnonymousInactiveግልፅ ደብዳቤ ለኢንጂነር ታከለ ኡማ (ቢደርስም ባይደርስም)
ወንድማገኘሁ አዲስሰላምታዬንና አክብሮቴን በማስቀደም የተከበሩ ሚኒስትር ኢንጂነር ታከለ ኡማ፥ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በጥናት ደረስኩበት ብሎ ይፋ ላደረገው ሰነድ በሰጡት መልስ የተገነዘብኩት እንደ አንድ ተራ ዜጋ ላቀርብልዎት እወዳለሁ።
ሲጀመር የሰጡት ርዕስ ራሱ ችግር እንዳለበት ይሰማኛል። ማስረጃ አጠናቅሬያለሁ ያለ ድርጅት መግለጫ ከማውጣቱ ሰነዱን ለሚመለከታቸው አቅርቦ ይመሩት የነበረው ፅሕፈት ቤት መልስ ስላልሰጠ። ኢዜማ ከዚህ ቢሮ መልስ አግኝቶ ቢሆን ኖሮ አንደኛ መልሱን ሪፖርቱ ላይ ያካትት ነበር፤ አሳማኝ የሆኑ ጉዳዮች ከቀረቡም ፓርቲው ከሪፖርቱ ላይ የተወሰኑትን እንዲያርም ወይም እንዲያሻሽል ዕድሉ ክፍት ይሆን ነበር ብዬ አምናለሁ።
በመቀጠልም ምላሽ ለመስጠት ተገቢው ቦታ ባልገኝም ሲሉ ተገቢው ቦታ ለመሆኑ የቱ ነው? ሰነዱ በቀጥታ ከሚመለከታቸው ግለሰቦች አካላት እርስዎና እርስዎ ይመሩት የነበረው ተቋም በመሆናቸው መልስ እንዳይሰጡ ቦታ ምክንያት ይሆናል ብዬ አላስብም ።
በመቀጠልም የመሬት ወረራን በተመለከተ ስልጣን ላይ ከወጣንበት የመጀመሪያ ቀን ጀምሮ እስከ መጨረሻዋ ቀን ድረስ ጠንካራ እርምጃዎች ስንወስድበት የነበረ ጉዳይ ነው ብለዋል። ለእርስዎ አድልተን ያሉትን ብንቀበል እንኳን “የመሬት ወረራውን አስቆሙት ወይ? የኮንዶሚኒየሙን አድሎአዊ እደላ አስወገዱት ወይ ነው?” ጥያቄው በራስዎ አንደበት የሀይማኖት ተቋማት ሳይቀሩ በኢ-መደበኛ አደረጃጀቶች ሲወረሩና በመንግሥት አካላት ሲፈርሱ በተነሳብዎት ተቃውሞ ምክንያት እርስዎ ራስዎ ይቅርታ አልጠየቁም ወይ? ከፍተኛ የሆነ የመሬት ወረራ እንዳለ በይፋ አልተናገሩም ወይ? ባለፉበት ባገደሙበት ሁሉ የከተማዋን መሬት ለግለሰቦችና ለተቋማት ሲያድሉ አልነበር ወይ?
ሌላው ክቡር ኢንጂነር ታከለ ኡማ፥ የተፈናቀሉትን አርሶ አደሮች በመታከክ እንደ ህወሀቶቹ የቀን ጅቦች ብሄርዎን ዋሻ ለማድረግ የሄዱበት መንገድ በጣም ከእርስዎ በጭራሽ ያልጠኩት ነበር። ለመሆኑ የትኛው የኢዜማ የመግለጫው ክፍል ላይ ነው “የተፈናቀሉት ገበሬዎች የመኖሪያ ቤት ተጠቃሚ አይሆኑ” የሚለው። ማነው በቃለ መጠይቁስ ላይ “ለተፈናቀሉት ቤት አይሰጥ” ያለው? በእርስዎ የስልጣን ዘመን በገፍ ቤት የታደላቸው በሺዎች የሚቆጠሩት የኦሮሚያ ባለስልጣናት የተፈናቀሉ አርሶ አደሮች ነበሩ ወይ? እስከ ልጅ ልጅ የሚሰጠው መሬት ፍትሀዊ ነበር ወይ? ለስፖርት ክለቦች የታደለውስ? ይህ ሁሉ እየሆነ ያለው እኮ “በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ድሆች ከዛሬ ነገ አንገታችንን ማስገቢያ፣ ልጆቻችንን ማሳረፊያ ቤት ልናገኝ ነው” በማለት ቤትን የህልውናቸውና የተስፋቸው ጥግ አርገው እየጠበቁ ሳለ ነው።
“እኛ ሕጋዊ እርምጃ ስንወስድ የዛሬ ተችዎቻችን የሰብዓዊ መብት ተነካ፤ ዜጎች ተፈናቀሉ ብለው ዘመቻ የከፈቱብን አካላት ናቸው” ብለዋል። በመጀመሪያ ደረጃ እርምጃ ሲወሰድ የሰብዓዊ መብት መከበር አለበት የሚለው ዓለም-አቀፋዊ መርህ እንደተጠበቀ ሆኖ ‘ዘመቻ’ ላሉት ቃል ግን ይቅርታ ያድርጉልኝና ማፈር ይኖርብዎታል። ለእርስዎም ሆነ ለመንግሥትዎ የኢዜማን ያክል ዕድል የሰጠ አንድም ድርጅት የለም። መወቀስ ካለበትም በሰጣችሁ ሰፊ ዕድልና በታገሳችሁ ልክ መሆን አለበት፤ ምንም እንኳን ሁለቱም ምክንያታዊ ናቸው ብዬ ባምንም።
ሌላው እጅግ አስገራሚ የሆነው ደሞ “አንድም ቀን ለተናቀሉት የመቆርቆር ስሜት አሳይቶ የማያውቅ ድርጅት” ሲሉ የጠቀሱት ለመሆኑ ኢዜማ የጠቀሷቸው ዜጎች ሲፈናቀሉ ህልው ፓርቲ ነበር ወይ? ያፈናቀላቸው እኮ የራስዎ ድርጅት የዛሬው የኦሮሚያ ብልጽግና የትናንቱ ኦህዴድ ነበር! ተረሳ ክቡር ሚኒስትር? አርበኞች ግንቦት 7 (አግ7) እንዲሁም ከስመው ኢዜማን የመሠረቱት እኔ የማቃቸው ፓርቲዎች እና ግለሰቦች ሁሉ እናንተ ስታፈናቅሉ እነሱ ከተፈናቃዮች ጎን ሆነው ድምፃቸውን ሲያሰሙ የነበሩ መሆናቸውን አስረግጬ መናገር እችላለሁ። እንደ አንድ ለወገኑ እንደሚቆረቆር ኢትዮጲያዊ እኔም ከእነሱ ባለሁበት ያቅሜን ስጮህ ነበር። ለምን ይዋሻል ኢንጂነር?!
“የአርሶ አደሮችን ጉዳይ ለተቀባይነት ማግኛ” በማለት የፃፉት እና “መጀመሪያ ላይ በሀሰተኛ መረጃ ሀገር ማፍረስ እንጂ አይገነባም” ላሉት ደሞ ትንሽ ማለት አለብኝ። ለመሆኑ ኢዜማ እርስዎ ባሉት መልኩ ተቀባይነት ማግኘት እንደሚቻል ጠፍቶት ነው በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ደጋፊዎቹን ያጣው? ሌላው ቢቀር በእናት ድርጅትዎ መዋቅር በአብዛኛው ኦሮሚያና እርስዎ ሲያስተዳድሯት በነበረችው በአዲስ አበባ ከተማ በፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች ላይ ሲደርሱ የነበሩት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በማስጮህ ብቻ ተከታይን ማፍራት አይቻልም ብለው ያስባሉ? ይልቅስ ከላይ እንደጠቀስኩት የተፈናቃዮችን ልብ በፀረ-ኢዜማ ትርክት ለማነፅና ጭፍን ተከታይ ለማፍራት የኳተኑት እርስዎ ራስዎ ነዎት። በነገራችን ላይ፥ ለሀገር ሰላምና መረጋጋት ዕድል መስጠት ከመንግሥታዊ ኢ-ሕገመንግሥታዊ ተግባራት ጋር ማበር አይደለም።
ክቡር ኢንጂነር፥ አሁን ላይ በደንብ የገባኝ ከስልጣን ሲወርዱ፣ በሀሳብ መሟገት ሲያቅታቸውና ፖለቲካ ፊት ስትነሳቸው “ብሔርን መደበቂያ ዋሻ” ማድረግ በስፋት እየተዛመተ ያለ አስፈሪ ፖለቲካዊ ባህል መሆኑን ነው። እርስዎም ይሄን መንገድ በመከተል የእነ ሀይለመስቀል ሸኚን ፣ የእነ አቦይ ስብሀትን የእነ ልደቱ አያሌውን ዱካ እንደተከተሉ ተረድቻለሁ።
የአሿሿምዎ ሂደት አጠያያቂነት እንደተጠበቀ ሆኖ ክቡር ሚኒስትር፥ እርስዎ የታላቋ አዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ነበሩ። ሲያስተዳድሯት የነበረችው አዲስ አበባ ማለት የ AU፣ የ ECA እና የመሳሰሉት ታላላቅ ዓለም-አቀፋዊ ድርጅቶች መቀመጫና በዓለም ላይ 3ኛዋ ወይም 4ኛዋ የዲሎማሲና የፖለቲካ ከተማ እንደሆነች ዓለም የሚያውቀው ሀቅ ነው። አሁንም ቢሆን ሚኒስትር እንጂ እንደኔ አክቲቪስት አይደሉም። ቢሆን ደስ የሚለኝ ‘ቀረበ’ የተባለውን ሰነድ በሚገባ ፈትሸው ተመጣጣኝ በሆነ አግባብ መልስ ቢሰጡ ነበር። ሰነዱን በሙሉም ሆነ በከፊል ወይም በተወሰነ ደረጃ ተቀብለው፥ ያም ካልሆነ ተቃውመው የነበሩበትንና ያሉበትን ወንበር የሚመጥን አጸፋ ይሰጣሉ ብዬ ጠብቄ ነበር። በእኔ በኩል ያደረጓቸውን በጎ ተግባራት በዜሮ የማጣፋ ሰው አይደለሁም። የዛሬው መልስዎ ስሜቴን በእጅጉ ቢበርዘውም ለበጎ ለበጎዎቹ ሥራዎችዎ ዛሬም ክብር እሰጣለሁ። ይሁን እንጂ በቀረበብዎ ክስ እና በሰጡት መልስ ምክንያት የተደበቀውን “ኢንጂነር ታከለ ኡማን” ማየቴን ደሞ አልሸሽግዎትም። አሁን ለደረስኩበት ግንዛቤ ትልቁ ግብአቴ ደግሞ እርስዎ ራስዎ የነገሩንን ጭምር በመካድዎ ነው። ይሄ ሁሉ ሆኖም የነበሩበትንና ያሉበትን ደረጃ የሚመጥን መልስ ካለ ለመስማት አሁንም ፍቃደኛ ነኝ።
ክቡር ሚኒስትር፥ ስንብቴን አስቀድሜ እያቀረብኩ ደብዳቤዬን ከማጠናቀቄ በፊት እርስዎ ወይም ይመሩት የነበረው አስተዳደር ስለተሞገታችሁ ብቻ ሀገር እንደማትፈርስ በርግጠኝነት ልነግርዎ እወዳለሁ። ይልቅስ ሀገር የሚያፈርሰው የዜጎችን ድምፅ ለማፈን ይመሩት የነበረው ተቋም እየወሰደ ያለው ኢ-ሕገመንግሳታዊና ኢ-ዴሞክራሲያዊ እርምጃ ነው። የኢዜማ መግለጫዎች መታገድ የከንቲባ አዳነች አቤቤ ሳይሆን የእስዎ የሁለት ዓመታት የከንቲባነት ዘመን ውጤት ነው። የክብርት ከንቲባዋን ውጤት ደሞ ሰነባብተን እናየዋለን።
አክባሪዎ ወንድማገኘሁ አዲስ
- ኢ/ር ታከለ ኡማ ኢዜማ ላወጣው የመሬት ወረራ ሪፖርት የሰጡት ምላሽ
- እውነታውን በማድበስበስ ከተጠያቂነት ማምለጥ አይቻልም! ― የኢዜማ ሕዝብ ግንኙነት
- አዲስ አበባ ― ዳቦ፣ የመኖሪያ ቤት፣ መብራት እና ውሃ፣ የመሬት ቅርምት፣ ተረኝነተ፣ ሙስና፣ ግፍ፣ ወዘተ…
- የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ― በአዲስ አበባ ከተማ መሬት ወረራ እና የጋራ መኖሪያ ቤቶች ኢፍትሃዊ ዕደላ ጥናት አንኳር
- የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በአዲስ አበባ መሬት ወረራ እና የጋራ መኖሪያ ቤቶች ኢፍትሃዊ ዕደላ ላይ ያደረገው ጥናት ውጤት
ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረ–ገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forums) ላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።
August 30, 2020 at 10:21 pm #15644In reply to: የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በኢትዮጵያ ― ዜናዎችና ጠቃሚ መረጃዎች
SemonegnaKeymasterበሁለቱ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች ያሉ የልህቀት ማዕከላት የሚሹትን ትኩረት ለይቶ ለመደገፍ ያለመ ጉብኝት ተካሄደ
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ ዳይሬክተር ጄኔራሎች፣ ከፍተኛ አማካሪዎች እና ሌሎች ባለሙያዎችን የያዘ ቡድን በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ እና በአዳማ ሳይንስና ቴክሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች የሥራ ጉብኝት አድርጓል።
በጉብኝቱ በሁለቱም ዩኒቨርሲቲዎች በአካል በመገኘት ዩኒቨርሲቲዎቹ የልህቀት ማዕከላት ሆነው ከተፈጠሩ ጊዜ አንስቶ ‘የመንግሥትን ተልዕኮ ተሸክመው የት ደርሰዋል? ምን ውጤት አስመዝግበዋል? ያጋጠማቸው ማነቆ ካለስ ምንድን ነው?’ የሚሉትን ጉዳዮች ለመለየትና መፍትሄ ለማስቀመጥ እንደተካሄደ ተገልጿል።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፕ/ር አፈወርቅ ካሱ የጉብኝቱ ዓላማ በሀገራችን 16 የተለያዩ የልህቀት ማዕከላትን የያዙት አዲስ አበባ እና አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች ከተቋቋሙለት ዓላማ አንፃር የሚገባቸውን ያህል እየሠሩ ነው ወይ የሚለውን ለማየት፣ ያጋጠሟቸውን ችግሮች ለመለየትና በዚያው መጠን ድጋፍ ለማድረግ መሆኑን ገልፀዋል።
ሁለቱን ዩኒቨርሲቲዎች ሐምሌ 2006 ዓ.ም መንግሥት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ተቋም እንዲሆኑ አድርጎና ተጠሪነታቸውን በወቅቱ ለሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አድርጎ ሲያዋቅራቸው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ስርጸት ዩኒቨርሲቲዎች ተብለው በልዩ ሁኔታ የተመሠረቱ ሲሆን፤ ከመማር-ማስተማር ሥራ ጎን ለጎን በጥናትና ምርምር ልህቀት ማዕከልነት (centers of excellence) በኢንዱስትሪ-ዩኒቨርሲቲ ትስስር (industry-university linkages) እና በኢንኩቤሽን ማዕከልነት (incubation centers) እንዲያገለግሉ ታስበው ነው ብለዋል።
በልህቀት ማዕከላቱ ተማሪዎች ተምረው ሲወጡ ኢንዱስትሪውን በቀጥታ መቀላቀል የሚችሉበት አቅም እንዲያፈሩ ታልሞ መሠራት እንዳለበት ጠቁመው፥ ይህ እውን እንዲሆን ከመቼውም ጊዜ በተለየ ሁኔታ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሥራዎች ጋር አገናዝበን በቋሚነት በዕቅድ እንድናግዛቸው እንሠራለን ብለዋል ፕ/ር አፈወርቅ። የልህቀት ማዕከላት በሀብት መደገፍ እንዳለባቸው ገልጸው፥ ነገር ግን ከመንግሥት ቋት ብቻ ሊሆን ስለማይቻል ሀብቶች ማፈላለግ ላይ በጋራ መሥራት ይጠበቃል ብለዋል።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ በበኩላቸው፥ የተደራጀ ተቋማዊ አሠራር በመፍጠርና ተቋማዊ አቅምን በመገንባት ተቋማቱን ወደ ትክክለኛ የልህቀት ማዕከልነት መለወጥ ይቻላል ብለዋል። በአከባቢያቸው ከሚገኙ ኢንዱስትሪዎች ጋር ትስስር በመፍጠር መሥራት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል። የሀገራችን የቴክኖሎጂ፣ ምህንድስና፣ ሳይንስና ምርምር ተቀባይ ብቻ ሆኖ መቀጠል የለበትም ያሉት ዶ/ር ሳሙኤል፥ መሪ እንዲሆኑ ሀብት አፈላልጎ ዩኒቨርሲቲ-ኢንዱስትሪ ትስስር ፈጥሮ መሥራት ሚናው የጎላ ነው ብለዋል። ቴክኖሎጂ ላይ ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩ በሁሉም የልዕቀት ማዕከላት የሰው ኃይል ችግር መፍታት እንደሚገባ ጠቁመው፤ ለዚህም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥልና ለሀገር ብልጽግና ካላቸውም ፈይዳ አንጻር በየደረጃው ካሉ ባለድርሻ አካላት ጋር በመነጋገር አስፈላጊው ድጋፍና ክትትል እንዲሚደረግላቸውም ገልፀዋል።
ቡድኑ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በነበረው ጉብኝት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደረጀ እንግዳ በዩኒቨርሲቲው ያለውን ነባራዊ ሁኔታ የገለፁ ሲሆን፤ ዓለምአቀፍ እውቅና ለማግኘት የሚያግዙ የአሠራር ሂደቶችን ተከትለው ለመሥራት እየጣሩ መሆኑን ገልፀው፥ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ቢያግዘን ያሏቸውን ተግዳሮቶች አቅርበው ውይይቶች ተካሂደው የመፍትሄ ኃሳቦችም ተጠቁመዋል። ዩኒቨርሲቲው ግቢ ውስጥ ያሉ የልህቀት ማዕከላት፣ ቤተ-ሙከራዎች እና የግንባታ ሥራዎችም ተጎብኝተዋል።
በተመሳሳይ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ጉብኝት ሲካሄድ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ለሚ ጉታ ዩኒቨርሲቲው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተብሎ ከተሰየመበት ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ የተሰሩ ሥራዎችን እና ያጋጠሙ ችግሮችን፥ እንዲሁም የተፈጠሩ ትስስሮችን (partnerships) እና አጠቃላይ በዩኒቨርሲቲው ያለውን የሰው ሀብትና ተማሪዎች መረጃ አቅርበው ውይይት ተካሂዷል። በዩኒቨርሲቲው ልዩ ነው ያሉትን የደብል ሜጀር እና ፋስት ትራክ የትምህርት አሰጣጥ ሁኔታንም ጨምረው አብራርተዋል። ፕሬዚዳንቱ እንዳሉት፥ በአሁኑ ጊዜ በዩኒቨርሲቲው 161 የሦስተኛ ዲግሪ (doctoral) ተማሪዎች አሉ።
በሁለቱ ጉብኝቶች ከተነሱት ዋና ዋና ድጋፍ የሚሹ ጉዳዮች ውስጥ የግዥ ሥርዓት ችግሮች፣ የተሽከርካሪዎች እጥረት፣ ብቁ መምህራን ከገበያ ላይ በቀላሉ ያለማግኘት፣ በፋይናንስ ምክንያት የግንባታ ሥራዎች መዘግየት ይገኙበታል።
በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በነበረው ቆይታ ማጠቃለያ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሙሉ ነጋ እንዳሉት፥ የልህቀት ማዕከላት ሲባል አንድ ተቋም በአገሪቱ መሪ የሆነ የቴክኖሎጂ ማዕከል መሆን ማለት ነው። ይሄንን ደግሞ ከኢንዱስትሪ ጋር ትስስር በመፍጠር፣ ከቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና (TVET) ማዕከላት ጋር በመቀናጀት ኢንዱስትሪውን የሚመጥን፣ የኢንዱስትሪውን ፍላጎት ያሟላ ሰልጣኝ ለገበያ የሚያቀርብ፣ ተግባራዊ ምርምሮች የሚካሄዱበት መሆን ሲቻል ነው ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲዎቹ ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ድጋፍ እንፈልጋለን ብለው ያቀረቧቸውን በመውሰድ እንሠራበታለን ሲሉም ዶ/ር ሙሉ አክለዋል። ዩኒቨርሲቲዎቹ ዘመናዊ የሳይንሳዊ አስተሳሰቦች እና የቴክኖሎጂ ውጤቶች ተገናኝተው ለሀገር ብልጽግና የሚውሉባቸው እንደመሆናቸው አስፈላጊው ክትትልና ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።
በሁለቱም ዩኒቨርሲቲዎች ያሉ የልህቀት ማዕከላት በቡድኑ የተጎበኙ ሲሆን፤ በጉብኝቱም ዩኒቨርሲቲዎቹ የተለያዩ የሀገር ሀብት የሆኑና ምናልባትም በኢትዮጵያ ውስጥ በሌሎች ተቋማት የሌሉና በተለይ ለምርምር ትልቅ ፋይዳ ያላቸው እንደ ኤሌክትሮማይክሮስኮፕ ያሉ መሣሪያዎች መኖራቸው ተመልክቷል። ይሄንንም ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር ትስስር በመፍጠር በጋራ ለመጠቀም የሚቻልባቸው ሁኔታዎች ማመቻቸት ያስፈልጋል ተብሏል። በቀጣይም ተቋማቱ የተፈጠሩበትን ዓላማ ማሳካት እንዲችሉ እና ውጤታማ ሥራዎችን ለመሥራት እንዲቻላቸው የሚያግዙ የታቀዱ ድጋፍና ክትትሎች ከሌላው ጊዜ በተለየ ይካሄዳሉ ተብሏል።
አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚገኙ የልህቀት ማዕከላት፦
- Sustainable Energy
- Mineral Exploration, Extraction and Processing
- Nano Technology
- Bioprocessing and Biotechnology
- Construction Quality and Technology
- High Performance Computing and Big Data Analysis
- Artificial Intelligence and Robotics
- Nuclear Reactor and Technology
አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚገኙ የልህቀት ማዕከላት፦
- Space Technology Institute
- Institute Of Pharmaceutical Science
- Institute Of Water Resource and Irrigation Engineering
- Electrical System and Electronics
- Advanced Manufacturing Engineering
- Advanced Material Engineering
- Urban Housing and Development
- Transportation and Vehicle
ምንጭ፦ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር
-
AuthorSearch Results
Search Results for 'ብልጽግና'
-
Search Results
-
በጉራጌ ዞን የመስቀል በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች መከበር ተጀመረ
(የመስቀል በዓል በጉራጌ ማኅበረሰብ)
በሀገራችን በድምቀት ከሚከበሩ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ክብረ በዓላት መካከል የመስቀል በዓል አንዱ ነው። የመስቀል በዓል በጉራጌ ማኅበረሰብ ዘንድ ልዩ ቦታ የሚሰጠው እንደመሆኑ፥ በየዓመቱ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ይከበራል። የዘንድሮውን የዋዜማ ዝግጅት በዞኑ ቸሃ ወረዳ የጠናቃ ቀበሌ ለኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በማያጋልጥ መልኩ የፌዴራል እና የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በሀገር ሽማግሌዎች ምርቃት ከመስከረም 11 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በድምቀት መከበር ተጀምሯል።
በመክፈቻ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሐመድ ጀማል ታዳሚዎችን እንኳን አደረሳችሁ በማለት “የመስቀል በዓል የኛነታችን መገለጫ ነው፤ የመስቀል በዓል ትውፊታዊም መንፈሳዊም ነው። በመስቀል በዓል የእርስ በእርስ የመተሳሰብ፣ የአብሮነት፣ የፍቅር፣ የሰላም እንዲሆን የመልካም ምኞት ማብሰሪያ አበባ የሚሰጣጡበት ጊዜ ነው። እንዲሁም በሥራም ሆነ በሌላ አጋጣሚ ተራርቆ የቆየ ሰው የሚገናኝበት፣ ዘመድ ከዘመዱ የሚጠያየቅበት፣ የሚረዳዳበት እንዲሁም አዲስ ጎጆ የሚቀለስበት ጊዜ መሆኑ ማኅበረሰባችን ልዩ ቦታ ይሰጠዋል። አያይዘውም በበዓሉ ባህላዊ እሴቶቻችንን በደንብ አልምተን እንደ አንድ የቱሪዝም ገቢ ምንጭ በማድረግ ለሀገራዊ ብልጽግናችን መሠረት የምንጥልበት ነው ብለዋል።
የመስቀል በዓል ከሀይማኖታዊ ክዋኔ ባሻገር ባህላዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያለው ሲሆን በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በድምቀት የሚከበር ቢሆንም መስቀል በጉራጌ በተለየ የአከባበር ሁኔታ ይከበራል ብለዋል – አቶ መሐመድ።
እንደ አቶ መሐመድ ገለፃ እንደ መስቀል ያሉ ቱባ ባህሎቻችን ታሪካቸው ሳይሸራረፍ ለትውልድ በማስተላለፍ ዘረኝነት፣ ጥላቻና ቂም በቀል በማስወገድ የሀገራችን ብልፅግና ለማረጋገጥ ሁሉም ዜጋ የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።
መርሀ-ግብሩን በጋራ ያዘጋጁት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፤ የጉራጌ ዞን አስተዳደር እና የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በመተባበር ሲሆን፥ የዚህ ክብረ በዓል አከዋወን በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ድርጅት /UNESCO/ ከማይዳሰሱ የሰው ልጅ ወካይ ባህላዊ እሴቶች (“intangible heritages of Ethiopia”) ተርታ መመዝገቡን በማስመልከት ሲሆን፥ በአከባበሩ ሥርዓት ውስጥ ያሉት ትውፊቶች በትውልድ ቅብብሎሹ ውስጥ ተጠብቀው ያለ ምንም ተፅዕኖ ክዋኔዎቹ እየቀጠሉ እንዲሄዱ የማስተማር ዓላማ ያለው እንደሆነ ተነግሯል።
በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የባህል እሴቶች ልማት ዳይሬክተር ወ/ሮ እስከዳር ግሩም በበኩላቸው፥ ሀገራችን ኢትዮጵያ የበርካታ ባህላዊና ታሪካዊ ሀብት ባለቤት ብትሆንም በተገቢው ማልማትና ማስተዋወቅ ባለመቻላችን ከዘርፉ የምናገኘው ገቢ እንዳላደገ ገልጸዋል።
አንድነታችን አጠናክረን ሀብቶቻችን ማልማት፣ መጠበቅና መንከባከብ አለብን። ይህ ደግሞ የቱሪዝም ዘርፍ እንዲነቃቃ ያደርገዋል። በተጨማሪም ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር ይቻላል ብለዋል።
የቸሀ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ፈለቀ የመስቀል በዓል በጉራጌ ሁሉም በድምቀት ከማክበር ባለፈ የጉራጌ እሴት የሚገለፅበት በመሆኑ የረጅም ጊዜ ቅድመ ዝግጅት እንደሚደረግበት በማስታወስ፤ በዓሉንም በድምቀት ለማክበር ሁሉም የቤተሰብ አባል የድርሻውን ኃላፊነት እየተወጣ እንደሚከበር ገልጸዋል።
ለበዓሉ ማብሰሪያ የጉራጌ ዞን የባህል ቡድንም ያሰናዳቸውን ሙዚቃዊ ክዋኔዎች እንደነ “ጊቻዌ፣ ጊቻዌ”፣ “አዳብና” የመሳሰሉት ተውኔታዊ ክዋኔዎች በሴቶችና ወንዶች የታየበት፣ የሥራ ባህልን፣ ሠርቶ ማደግን የሚያወድሱ፣ የሚያስተምሩ ማሳያዎች፣ ኢትዮጵያዊነትን የሚያቀነቅኑ በአንድነት በአብሮነት ባህላዊ እሴቶች የሚጎለብቱበት ተውኔታዊ ትዕይንቶች የተንፀባረቁበት ነበር።