-
AuthorSearch Results
-
February 25, 2023 at 3:36 pm #56094
In reply to: ንግድና ኢንዱስትሪ ነክ ዜናዎች ― ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
SemonegnaKeymasterኢስት አፍሪካን ሆልዲንግ አክስዮን ማኅበር በቢሾፍቱ ከተማ የኢንዱስትሪ ፓርክ ሊገነባ ነው
አዲስ አበባ – ኢስት አፍሪካን ሆልዲንግ አክስዮን ማኅበር በ108 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ኦሮሚያ ክልል ውስጥ በቢሾፍቱ ከተማ የኢንዱስትሪ ፓርክ ለመገንባት ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር የካቲት 17፥ ቀን 2015 ዓ.ም ስምምነት ተፈራረመ።
በስምምነቱ ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዳንኤል ተሬሳ፥ ኢትዮጵያ ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት ዘርፈ ብዙ ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሀብት-ተኮር (ኢኮኖሚያዊ) ማሻሻያዎችን እያደረገች እንደምትገኝ ጠቁመው፤ ማሻሻያዎቹ አዳዲስ እና ያሉትንም ኢንቨስትመንቶች አቅም ለማሳደግ ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ ብለዋል።
እንደ ምክትል ኮሚሽነሩ ገለጻ፥ ኢንቨስትመንትን የበለጠ ለማጠናከር ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች እና የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በልዩ ሁኔታ የሚደግፉ ፖሊሲዎች እና ማሻሻያዎች ጸድቀው ወደ ሥራ በመግባት አመርቂ ውጤቶች እየተመዘገበ ነው። ለአብነትም ባለፉት ስድስት ወራት ከሁለት ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ የውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት (foreign direct investment) መሳብ ተችሏል ብለዋል ።
የኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ አክስዮን ማኅበር ሊቀመንበር ዶክተር ብዙአየሁ ታደለ በበኩላቸው እንደገለጹት፥ የፓርኩ ግንባታ ሲጠናቀቅ ስፋቱ ወደ 100 ሄክታር የሚያድግ ሲሆን ለ15 ሺህ የሰው ኃይል የሥራ ዕድል ከመፍጠሩም ባሻገር ለቴክኖሎጂ ሽግግር ዕድል የሚፈጥር ነው።
የማስፋፊያ ፕሮጀክቱ በ108 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚለማ ሲሆን ንድፉ የኢንዱስትሪያል ፓርክ አጠቃቀም ሥርዓትን የተከተለ፣ መሠረተ ልማት የተሟላለት፣ 40 ሜጋ ዋት የኃይል አቅርቦት የሚኖረው እና ታዳሽ ኃይል (renewable energy) ላይ በትኩረት የሚሠራ እንዲሁም ኤክስፖርትን የሚያሳድግ ነው ሲሉ አብራርተዋል። በተጨማሪም የአካባቢውን አርሶ አደሮች በምርት አቅርቦት የሚያስተሳስር እና ለሀገር ውስጥ ግብዓት ልዩ ትኩረት የሚሰጥ ነው ሲሉ አክለዋል።
እንደ ዶክተር ብዙአየሁ ገለጻ፥ የኢንዱስትሪ ፓርኩ ሙሉ ለሙሉ ወደሥራ ሲገባ ምርቶችን ለሀገር ውስጥ ፍጆታ ከማቅረብ ባሻገር ኤክስፖርት በማድረግ የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኝ ይሆናል።
የኢንዱስትሪ ፓርኩ ከአዲስ አበባ በ40 ኪሎ ሜትር ላይ መገኘቱ እና ከኢትዮ-ጂቡቲ ምድር ባቡር ጣቢያ በቅርብ ርቀት እንደሚገኝ ገልጸው፤ ከአዲስ አበባ – አዳማ ፈጣን መንገድ በሦስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገነባ መሆኑ እና ከሞጆ ደረቅ ወደብ በ15 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ መሆኑ ፓርኩን ልዩ እንደሚያደርገው ገልጸዋል።
ኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ አክስዮን ማኅበር በውስጡ የተለያዩ ኢንቨስትመንቶችን የያዘ የሀገር በቀል ኩባንያ ሲሆን፤ ከዚህም መካከል የኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት፣ ሲሚንቶ ምርት፣ አላቂ እቃዎች፣ የሪል ስቴት ልማት፣ ማዕድን ልማት እና ሎጀስቲክ የንግድ ዘርፍ የያዘ እና ከስድስት ሺህ በላይ ቋሚ እና ጊዜያዊ ሠራተኞች የሥራ ዕድል መፍጠር የቻለ ድርጅት ነው።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት
February 25, 2023 at 2:48 pm #56088In reply to: ትምህርት፣ ጤና እና ሕብረተሰብ ― ሰሞነኛ ዜናዎች፣ መረጃዎች
SemonegnaKeymasterቦረና ዞን ውስጥ በተከሰተው ድርቅ ተጎጂ ለሆኑ ዜጎች የተሟላ ድጋፍ ለማድረግ በቅንጅት እየተሠራ ነው
ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ቦረና ዞን በተከሰተው ድርቅ ተጎጂ ለሆኑ ዜጎች በሚፈለገው ደረጃ ድጋፍ ማሠራጨት የሚያስችል የቅንጅት ሥራ እየተሠራ መሆኑን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ። እስካሁን ከ204 ሺህ በላይ ኩንታል እህል ለተጎጂ ዜጎች መሠራጨቱም ተጠቁሟል።
የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደበበ ዘውዴ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት በቦረና ዞን በድርቅ አደጋ ጉዳት ከደረሰባቸው ዜጎች ውስጥ በ13 ወረዳዎች ውስጥ ለሚገኙ ወደ 604 ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች የዕለት ድጋፍ ቀርቦላቸዋል። ካለፉት ሁለት ወራት በ15 ቀናት ውስጥም ለእነዚሁ ወገኖች 204 ሺህ 765 ኩንታል ምግብ ወደ አካባቢው ተልኮ ተሠራጭቷል። ከጉዳቱ አንጻርና የተጎጂዎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ በመንግሥትና በአጋር አካላት ቀጣይ ድጋፍ ማድረግ የሚያስችል የቅንጅት ሥራ እየተሠራ ነው።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፥ ኮሚሽኑ በተለይ ለአደጋ ተጋላጭ ለሆኑ ሕፃናት፣ ነፍሰ ጡሮች፣ አጥቢ እናቶችና አቅመ ደካሞች የሚሆን 10 ኩንታል አልሚ ምግብ ወደ አካባቢው ተልኳል። ከዚህ በተጨማሪ የአካባቢው ሕብረተሰብ፣ ባለሀብቱ፣ ድጋፍ ሰጪዎችና መንግሥትም በዚሁ መልኩ ለወገኖች ሊደርስ የሚችለውን ድጋፍ እያቀረቡ ይገኛሉ።
የኦሮሚያ ክልል 800ሺህ ለሚጠጉ ዜጎች የዕለት ድጋፍ መጠየቁን ገልጸው፥ በዚሁ ቁጥር ልክ ድጋፉ እንዲሰጥ ከአጋር አካላት ጋር አብሮ የሚሠራ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ድርቅን በሚመለከት በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ክስተቱ እንዳለ የገለጹት ዳይሬክተሩ፥ ክስተቱ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ጉዳት እያስከተለ ይገኛል ብለዋል።
በኢትዮጵያ የተፈጥሮ አደጋዎች በሚያጋጥሙበት ጊዜም በሦስት አካላት ድጋፍ እንደሚደረግ ጠቁመው፤ እነዚህም መንግሥት፣ የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል። እነዚህም በየአካባቢው ጉዳት ባጋጠመባቸው ስፍራዎች የየድርሻቸውን በመያዝ ምግብና ምግብ-ነክ ያልሆኑ ድጋፎችን ከክልል ጋር በመሆን ለሥርጭት እንዲበቃ ያደርጋሉ ነው ያሉት።
እንዲህ ዓይነት ችግሮች በሚያጋጥሙበት ጊዜ እንደ ኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የማስተባበር ሥራን በመሥራት ከሌሎች ሴክተር መሥሪያ ቤቶችና ከክልሎች ጋር አብሮ የሚሠራባቸው ስልቶች እንዳሉ ዳይሬክተሩ አክለው ገልጸዋል። ከእነዚህ ሥራዎች ውስጥም በክልል ደረጃ የአስቸኳይ ጊዜ ማስተባበሪያ ማዕከል ማቋቋም አንዱ እንደሆነና በዞን ደረጃ ብዙ ቁጥር ያላቸው ወገኖች ጉዳት ሲደርስባቸው የአስቸኳይ ጊዜ ኮማንድ ፖስት እንደሚቋቋም ጠቅሰዋል።
ይህም በክልል የሚመራና ኮሚሽኑ የሚደግፈው የጤና፣ የግብርና፣ የውሃ፣ የትምህርትና ሌሎች ጉዳዮች እንደመኖራቸው ሌሎች ሴክተር መሥሪያ ቤቶችን አስተባብሮ ማስኬድ የሚያስችል ድጋፍ በቅንጅት እየተሠራ እንዳለ አመላክተዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ባሉ ሁኔታዎች ምክንያት በአጋር አካላት የሚደርሰው ድጋፍ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳርፉ ይችላሉ ያሉት ዳይሬክተሩ፥ የተበታተነውን ሁኔታ መሰበሰብ የሚያስችል ከሀገር ቤት እስከ ውጭ ያሉ አካላት የሚሳተፉበት ተግባራትም እንዳሉ ጠቁመዋል።
አምባሳደር ዶክተር ሽፈራው ተክለማርያምን ጨምሮ በየቢሯቸው በመገኘት አጋር አካላትን፣ ኤምባሲዎችን፣ የመንግሥታቱ ኅብረት ተወካዮችን እያነጋገሩ እንዳለ ገልጸዋል። በዚህ መልክ ድጋፉ እንዲጠናከር ይደረጋል ሲሉም አስታውቀዋል።
ዳይሬክተሩ እንዳሉት፥ በሀገሪቷ ድርቅና ሌሎች ተዛማች ችግሮች አሉ። በመሆኑም እነዚህን ችግሮች ለመቋቋም ከሀገር ውስጥ አቅም ባሻገር የአጋር አካላት አስተዋጽኦ ወሳኝ ነው። ለዚህም አጋር አካላት የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ጥረት እየተደረገ ነው። በአሁኑ ወቅትም ድጋፉ እየመጣ ነው፤ ለዚህም በሚፈለገው ደረጃ ማሠራጨት የሚያስችል የቅንጅት ሥራ እየተሠራ ነው።
ከመንግሥት እንቅስቃሴ በተጨማሪ የተለያዩ ኢትዮጵያውያን እና ኢትዮጵያዊ ተቋማት ቦረና ዞን ውስጥ በተከሰተው ድርቅ ለተጎዱ ወገኖች በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር የተለያዩ እርዳታዎችን እያሰባሰቡ ይገኛሉ። እርስዎም በዚህ ድጋፍ ለመሳተፍ የሚከተሉትን ማስፈንጠሪያዎች ይጫኑ።
- ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት (GARE) በጎፈንድሚ (GoFundMe) በኩል፦ GARE4Borena
- በሀገር ውስጥ ደግሞ የጉዞ አድዋ ማኅበር አስተባባሪ ያሬድ ሹመቴ (Yared Shumete) እና መምህር ታዬ ቦጋለ አረጋ “ዓድዋ 127 ለቦረና” በሚል እንቅስቃሴ በመጀመር የተለያዩ ድጋፎችን (ገንዘብ፣ የምግብ ምርቶችን፣ ወዘተ) እያሰባሰቡ ነው። ያግኟቸው፦ http://www.facebook.com/shumeteyared እና http://www.facebook.com/tayebogale.arega
November 18, 2022 at 1:22 am #54201In reply to: ንግድና ኢንዱስትሪ ነክ ዜናዎች ― ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
SemonegnaKeymasterበኢትዮ-ኬንያ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር በይፋ የኤሌክትሪክ ሽያጭ ተጀመረ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የኢትዮ-ኬንያ ባለ 500 ኪሎ ቮልት የኃይል ማስተላለፊያ መስመር እና የኮንቨርተር ማከፋፈያ ጣቢያ ኅዳር 8 ቀን፥ 2015 ዓ.ም በይፋ የኤሌክትሪክ ሽያጭ መጀመሩን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።
በማስተላለፊያ መስመሩ ላይ ኃይል የማስተላለፍ የሙከራ ሥራ ከጥቅምት 29 ቀን 2015 ዓ/ም ጀምሮ ሲከናወን መቆየቱንም ኩባንያው አስታውሷል።
ኅዳር 8 ቀን፥ 2015 ዓ.ም በይፋ ኃይል ማስተላለፍ የጀመረው የኢትዮ-ኬንያ ባለ 500 ኪሎ ቮልት (500 kilovolt) የማስተላለፊያ መስመር በዓመት እስከ አንድ መቶ ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ማስገባት አቅም ያለው ሲሆን፤ ከኬንያ አልፎ ከታንዛኒያ እስከ ደቡብ አፍሪካ ላሉት ሀገራት እስከ ሁለት ሺህ ሜጋ ዋት (2000 MW) ኤሌክትክ የማስተላለፍ አቅም አለው፡፡
የኢትዮ-ኬንያ የኃይል ማስተላለፊያ መስመርና ኮንቨርተር ጣቢያ ፕሮጀክት ለአማካሪ ድርጅቱ፣ ለካሳ ክፍያና የተሰረቁ መሰረተ ልማቶችን ለመተካት የወጣውን ወጪ ጨምሮ ወደ አምስት መቶ ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ወጪ ተደርጎበታል፡፡
ከዚህ ውስጥ 214 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላሩ ለኮንቨርተር ስቴሽኑና ለግራውንድ ኤሌክትሮድ መስመር የግንባታ ሥራ እንዲሁም 120 ሚሊዮን ዶላሩ ደግሞ ለማስተላለፊያ መስመሩ የዋለ ነው፡፡
የኢትዮ-ኬንያ ባለ 500 ኪሎ ቮልት የማስተላለፊያ መስመር የግንባታ ሥራ “China Electric Power Equipment and Technology Co. Ltd (CET)” በተሰኘ የቻይና ኩባንያ የተከናወነ ሲሆን፤ የኮንቨርተር ማከፋፈያ ጣቢያውና የግራውንድ ኤሌክትሮድ መስመሩ ደግሞ ሲመንስ (Siemens AG) በተሰኘው የጀርመን ኩባንያ ተከናውኗል፡፡
በኢትዮጵያ በኩል የተዘረጋው የማስተላለፊያ መስመር እና የፕሮቴክሽንና የዳታ ኮሙዩኒኬሽን መስመር (ኦፕቲካል ግራውንድ ፋይበር) 440 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን 994 የከፍተኛ ኃይል ተሸካሚ የብረት ታወሮች አሉት።
ኢትዮጵያ የምታስተላልፈው ኃይል ያልተቆራረጠና አስተማማኝ እንዲሆን የሚያግዙ ተግባራትን ያጠናቀቀች ሲሆን በኬንያ በኩል ተመሳሳይ ሥራዎች ተሰርተው በቅርቡ ወደተግባር እንደሚገባ ይጠበቃል፡፡
የማስተላለፊያ መስመሩ ከደቡብ ህዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የወላይታ፣ ጋሞ እና ኮንሶ ዞን እንዲሁም ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የቦረና ዞን አቋርጦ ነው ወደ ኬንያ ኃይል የሚያስተላልፈው።
ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ከሱዳን እና ከጅቡቲ ጋር የኃይል ሽያጭ እያካሔደች ሲሆን ከሶማሌ ላንድ፣ ታንዛኒያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ለማከናወን የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርማለች።
ባለፈው ዓመት ለሱዳን እና ለጅቡቲ ኤክስፖርት ከተደረገው የኤሌክትሪክ ኃይል 95 ነጥብ 4 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ተገኝቷል፡፡
November 1, 2022 at 2:06 am #53771In reply to: የሰብዓዊ መብቶች እና ተያያዥ ጉዳዮች ― ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
SemonegnaKeymasterኢሰመኮ የሴቶችና የሕፃናት ሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ዓመታዊ ሪፖርት ይፋ አደረገ
የኮቪድ ወረርሽኝ፣ ድርቅ፣ ጦርነትና ግጭት ሳቢያ በሴቶችና ሕፃናት መሰረታዊ መብቶች ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደራቸውን ኮሚሽኑ ገልጿልአዲስ አበባ (ኢሰመኮ) – የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከመስከረም 2014 ዓ.ም. እስከ ነሐሴ 2014 ዓ.ም. ያለውን ጊዜ የሚሸፍን የሴቶችና የሕፃናት ሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ዓመታዊ ባለ 36 ገጽ ሪፖርት ይፋ አድርጓል።
ይህ ዓመታዊ የሴቶችና የሕፃናት መብቶች የዘርፍ ሪፖርት ኢሰመኮ ሐምሌ 1 ቀን 2014 ዓ.ም. ይፋ ካደረገው አጠቃላይ የኢትዮጵያ ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርት በተጨማሪነት በተለይ የሴቶችና የሕፃናት ሰብአዊ መብቶች አያያዝ ላይ በዝርዝር በማተኮር ኮሚሽኑ የለያቸውን አበረታች እመርታዎችን፣ ዋና ዋና አሳሳቢ ጉዳዮችን እና ምክረ-ሃሳቦችን አካቷል፡፡ ኮሚሽኑ ሪፖርቱን ያዘጋጀው ባከናወናቸው ክትትሎች፣ ምርመራዎችና የመስክ ምልከታዎች፣ ባስተናገዳቸው የግለሰቦች አቤቱታዎች፣ የሕግና የፖሊሲ ግምገማዎች፣ ጥናቶች እና ምክክሮች፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች እንዲሁም የውትወታ እና ሌሎች ሥራዎቹ ላይ በመመስረት ነው።
የሴቶችና የሕፃናት ሰብአዊ መብቶችን ከማስጠበቅ እና ከማስፋፋት አንፃር በሕግ ረገድ የታዩ ክፍተቶች፣ የሴቶችና የሕፃናት ከጥቃት እና ከብዝበዛ የመጠበቅ፣ ፍትሕ እና ውጤታማ መፍትሔ የማግኘት፣ ሕዝባዊ ተሳትፎ የማድረግ፣ በፍትሕ ሥርዓት ውስጥ ያለው አያያዝ፣ የቤተሰብ መብቶች እንዲሁም የሴት ሠራተኞች ሁኔታ ሪፖርቱ ትኩረት ያደረገባቸው ርዕሰ ጉዳዮች ናቸው።
በኢትዮጵያ በተከሰቱት ሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ ችግሮች ምክንያት ሕፃናት ከመንግሥት፣ ከማኅበረሰብ እና ከቤተሰብ ማግኘት ያለባቸው ጥበቃ በመጓደሉ ለተደራራቢ የመብቶች ጥሰት መጋለጣቸው እና ሴቶች በተፈጸሙባቸው ጾታዊ መድሎዎችና ጥቃቶች ምክንያት መሰረታዊ መብቶቻቸውን የሚጥሱ፣ ነጻነቶቻቸውን የሚገድቡ እንዲሁም ሰብአዊ ክብራቸውን የሚያጎድፉ በደሎች እንደደረሱባቸው በሪፖርቱ ተገልጿል። በተጨማሪም በብሔራዊ የሕግ ማዕቀፍ ውስጥም ለሕፃናትና ለሴቶች ሰብአዊ መብቶች በቂ የሕግ ከለላ በመስጠት ረገድ የተለያዩ ክፍተቶች መስተዋላቸው ተጠቅሷል።
በኢትዮጵያ የሰሜኑ ክፍል በተነሳው ጦርነትና ቀጥሎም በየመሀሉ ማገርሸቱ በሴቶች እና በሕፃናት ላይ መጠነ-ሰፊ ጥቃቶች፤ በአንዳንድ ሁኔታዎች ለጦርነት ዓላማ ስልታዊ በሆነ መልኩ ጭምርም መፈጸማቸውን ተዘግቧል። ይሁን እንጂ ለተፈጸሙ ጥቃቶች ውጤታማ ፍትሕ እና መፍትሔ የሚያስገኝ የወንጀልና የፍትሐ-ብሔር የሕግ ማዕቀፍ አለመኖር፣ ዓለም አቀፍ መመዘኛዎችን ያሟላ የወንጀል ምርመራና የክስ አመሰራረት መጓደል በሪፖርቱ ከተዘረዘሩት ዋና ዋና አሳሳቢ ጉዳዮች መካከል ናቸው። በሌላም በኩል በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በሶማሌ፣ በአፋር፣ በኦሮሚያ፣ በጋምቤላ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልሎች በተለያየ ወቅት በተነሱ ግጭቶችም ሴቶችና ሕፃናት ለተለያዩ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች መጋለጣቸው ተጠቅሷል።
ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሴቶችና ሕፃናት ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸው፣ በተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥም ለጾታዊ ጥቃቶች እና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ተጋላጭ መሆናቸውና ልዩ ፍላጎታቸውን መሰረት ያደረጉ የሰብአዊ ድጋፎች አለማግኘታቸው ተደራራቢ የመብቶች ጥሰትን አስከትሏል። በሀገሪቱ በተከሰቱ የኮቪድ ወረርሽኝ፣ ድርቅ፣ ጦርነትና ግጭት ሳቢያ የትምህርት እና የጤና አገልግሎቶች በመቋረጣቸው፣ ወይም የተለያዩ ገደቦች መኖራቸው በሴቶችና ሕፃናት ትምህርትና ጤና የማግኘት መሰረታዊ መብቶች ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደራቸውን ኮሚሽኑ ገልጿል። እንዲሁም ሴቶችና ሕፃናት ለሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር እና ለብዝበዛ መጋለጥ፣ በኢንደስትሪ ፓርኮች የሚሠሩ ሴት ሠራተኞች መሰረታዊ መብቶች ጥሰቶች መቀጠል እና በእነዚህ የመብቶች ጥሰት ረገድ የቁጥጥርና የተጠያቂነት መላላት ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ መሆኑ በሪፖርቱ ።
በሕዝባዊ ጉዳዮች ላይ ከመሳተፍ መብት ጋር በተያያዘም፣ ሕፃናት በማናቸውም ጉዳይ ላይ ሃሳባቸውን በነፃ የመግለጽና በሚመለከታቸው ጉዳዮች ላይ ተሳትፎ የማድረግ መብታቸውን ለመተግበር የሚያስችል ሕግ አለመኖር፤ ሴቶችም በምርጫና በፖለቲካ ውስጥ ውጤታማ ተሳትፎ እንዳያደርጉ የአመለካከት ችግሮች እና ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች እክል መፍጠራቸው፤ እንዲሁም በሰላም ግንባታ እና በሀገራዊ ምክክር እና ሌሎች የሕዝባዊ ውይይት መዋቅሮች ውስጥም ጾታዊ አካታችነት በእጅጉ ውስን በመሆኑ፣ የሴቶች ተሳትፎ ተገድቧል፡፡
ከወንጀል ጉዳይ ጋር በተያያዘ በፍትሕ ሥርዓት ውስጥ የሚያልፉ ልጆች አያያዝ ከሕፃናት ፍትሕ መርሆዎችና መመዘኛዎች ውጪ መሆን፣ በወንጀል ተጠርጥረው የታሰሩ ሴቶች ሁኔታ ከመሰረታዊ የሴት እስረኞች አያያዝ መስፈርቶች ጋር አለመጣጣም፣ ከእናቶቻቸው ጋር በእስር ቤት የሚቆዩ ሕፃናት ትምህርትና አማራጭ እንክብካቤ የማግኘት መብቶች መጓደል፣ በወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ሥርዓት ውስጥ ያሉ ክፍተቶች በሪፖርቱ ከተለዩ ጉድለቶች መካከል ናቸው። ከዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች መስፈርቶች ጋር በተጣጣመ ሁኔታ ለሕፃናት ነፃና ለሁሉ ተደራሽ የሆነ የልደት ምዝገባ አሠራር በሀገር አቀፍ ደረጃ በሕግ አለመደንገጉ እንዲሁም በተወሰኑ ክልሎች ደግሞ የቤተሰብ ሕግ አለመውጣቱ ከተስተዋሉት የሕግ ክፍተቶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።
በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የደኅንነት ሥጋቶች መቀጠላቸው የሴቶችን እና ሕፃናትን ሁኔታ በሚፈለገው ቅርበት እና ፍጥነት ለመከታተል እንዳይቻል እንቅፋት የፈጠረ መሆኑ፣ በእነዚህ አካባቢዎች የሚሠሩ የሲቪል ማኅበራት እና አጋሮች አቅምም መዳከሙና በኮሚሽኑ የሚሰጡ ምክረ ሃሳቦችን ተግባራዊ ከማድረግ አኳያ በቅንጅት ለመሥራት የሚያስችል ጠንካራ የጋራ መድረክ አለመኖር ፈታኝ ሁኔታ መፍጠሩም ተጠቁሟል፡፡
የኢሰመኮ የሴቶችና የሕፃናት መብቶች ኮሚሽነር መስከረም ገስጥ የሴቶችንና የሕፃናት መብቶችን በተመለከተ ኮሚሽኑ ባከናወናቸው ክትትሎች፣ ምክክሮች እና የተለያዩ ክንውኖች ትብብር በማድረግ እና ግብዓት በመስጠት ኃላፊነታቸውን ለተወጡ መንግሥታዊም ሆነ መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበው በኢትዮጵያ ለሚገኙ ሕፃናትና ሴቶች ከግጭት፣ ከጥቃትና ከመድልዎ ነፃ የሆነ፤ ዘላቂ ሰላምና እኩልነት የሰፈነበት ሕይወትን እውን ለማድረግ በሪፖርቱ የተካተቱትን ምክረ-ሃሳቦች በመፈጸምና በማስፈጸም የተቀናጀ ጥረት እና ርብርብ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡
ኮሚሽነር መስከረም አክለውም “ሰብአዊ መብቶችን ማክበር፣ ማስጠበቅ እና ማሟላት የመንግሥት ዋነኛ ግዴታ በመሆኑ የሕግ ማዕቀፎችን፣ ተቋማትን እና አሠራሮችን በማሻሻል፣ ፍትሕን ተደራሽ በማድረግ፣ በግጭቶች የወደሙ የትምህርትና የጤና ተቋማትን እና ሌሎች መሰረተ-ልማቶችን መልሶ በመገንባት እና ለተጎጂዎች ሁለንተናዊ ተሐድሶን በማመቻቸት የሕፃናትንና የሴቶችን ሰብአዊ መብቶች የማሻሻል ኃላፊነቱን መወጣት አለበት። በተጨማሪም መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ፣ እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላትና ጠቅላላ ማህበረሰቡ በሰብአዊ መብቶች ማዕቀፍ በተቀመጠው አግባብ በሀገሪቱ የሴቶችና የሕፃናት መብቶች አፈጻጸምን በማረጋገጥ ረገድ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ አቀርባለሁ” ብለዋል።
[caption id="attachment_53773" align="aligncenter" width="600"] የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ሪፖርት[/caption]
September 25, 2022 at 2:30 am #51329In reply to: የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በኢትዮጵያ ― ዜናዎችና ጠቃሚ መረጃዎች
SemonegnaKeymasterባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለብፁዕ አቡነ ኤርምያስ የክብር ዶክትሬት ሽልማታቸውን አስረከበ
ባሕር ዳር – የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ባሳለፍነው ነሐሴ 21 ቀን፥ 2014 ዓ.ም የተማሪዎችን ምርቃ ሥነ-ሥርዓት ላይ ለሀገራችን ኢትዮጵያ በማኅበረሰብ አገልግሎት ጉልህ አስተዋፅዖ ላበረከቱት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ-ክርስቲያን (የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ) የሰሜን ወሎ እና በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የኦሮሚያ ልዩ ዞን ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ለሆኑት ለብፁዕ አቡነ ኤርምያስ የክብር ዶክትሬት ሽልማት ለተወካያቸው መስጠቱ ይታወሳል። ሆኖም ግን ብፁዕ አባታችን በአሁኑ ሰዓት የሐዋርያዊ ተልዕኮአቸውን ጨርሰው በመመለሳቸው መስከረም14 ቀን፥ 2015 ዓ.ም በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጥበብ ሕንፃ ተገኝተው የክብር ዶክትሬት ሽልማታቸውን ተቀብለዋል።
የሽልማት አሰጣጥ ሥነ-ሥርዓቱ የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ፣ የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ አባል እና የዕለቱ የክብር እንግዳ በሆኑት በብፁዕ አቡነ አብርሃም ፀሎትና ቡራኬ ተጀምሯል።
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶክተር ፍሬው ተገኘ በሽልማት አሰጣጥ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንዳሉት በጭንቅ እና በመከራ ወቅት ሀይማኖትና ዘር ሳይለዩ የከበረ ሥራን ሠርተው የከበሩትን ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ በማክበራችን እኛም ብዙ አትርፈናል ሲሉ ተናግረዋል። በወቅቱ አቅም ያላቸው በርካታ ነዋሪዎች ከአካባቢያቸው በሚሸሹበት ወቅት በጦርነት፣ በችግር እና መከራ ውስጥ ወደ ሚገኘው ሕዝባቸው ጋር በመሄድ የመከራው ቀንበር እንዳይሰማቸው ከሕዝቡ ጋር በመሆን የመጣውን ክፉ ቀን እንዲያልፍ በማድረጋቸው ታሪክ የማይረሳው ሥራን ሠርተዋል ሲሉ ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።
የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፥ እንዲሁም ዕለቱ የክብር እንግዳ የሆኑት ብፁዕ አቡነ አብርሃም በበኩላቸው የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሀይማኖት፣ ዘር እና ቀለም ሳይለይ በሥራቸው ብቻ መዝኖ ለብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ የክብር ዶክትሬት በመስጠቱ በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ ስም ምስጋና አቅርበዋል። ብፁዕ አቡነ ኤርሚያስ በዚያ ሽብር እና ጭንቅ በነገሰበት ወቅት ክርስቲያን፣ ሙስሊም፣ አማኝ እና ኢ-አማኝ ሳይሉ ሁሉንም የሰው ዘር በእኩል ዓይን በማየት የመከራውን ቀን ከሕዝባቸው ጋር ያሳለፉትን ድንቅ አባት የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ዕውቅና ሽልማት በመስጠቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መደሰቷን ተናግረዋል።
አቡነ ኤርምያስ በበኩላቸው የተሰጠኝ የክብር ዶክትሬት ለእኔ ሳይሆን በሁለቱም ወገን በጦርነቱ ወቅት ቆስለው በየጫካው የወደቁ ወገኖችን ቁስል በማጠብ እና ከልጆቻቸው ጉሮሮ ቀንሰው ለቁስለኞች በማብላት ትልቅ ፍቅር ላሳዩን እናቶች እና በጸሎት ሲጠብቁኝ ለነበሩት ለብጹዕ አቡነ ቄርሎስ፣ ከጎኔ ሆነው በምክር ለረዱኝ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ለሀዋርያዊ ተልዕኮ ዘወትር ለሚፋጠኑት ካህናት፣ ዲያቆናት፣ ከሙስሊሙ ማኅበረሰብ ጋር ድልድይ ሆነው ላገናኙኝ የመስጊድ ኮሚቴ አባላት፣ ሰብዓዊ ግዴታቸውን ለተወጡ አባቶቻችን እና እናቶቻችን ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የሰሜን ወሎ የባህር ዳር ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች፣ የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት የአድባራት እና ገዳማት አስተዳዳሪዎች እንዲሁም የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ም/ፕሬዚዳንቶች መምህራን እና ሠራተኞች በተገኙበት በደማቅ ሁኔታ ተካሂዷል።
ምንጭ፦ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ
August 8, 2022 at 1:14 am #49343In reply to: ትምህርት፣ ጤና እና ሕብረተሰብ ― ሰሞነኛ ዜናዎች፣ መረጃዎች
SemonegnaKeymasterበሦስት ዓመታት ከ70 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ ያገኛሉ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) – በኢትዮጵያ በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት ከ70 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ እንዲኖራቸው የሚደረግ መሆኑን የብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ ፕሮጀክት አስታወቀ።
የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት ከኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጋር በመተባበር በዲጅታል መታወቂያ የሕግ አግባብነት፣ ዓላማና አዋጅ ጋር በተያያዘ ውይይት አድርጓል።
የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት የባለድርሻ አካላት ግንኙነት መሪ ሚና አወል፤ ብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ አንድን ሰው ማንነት በእርግጠኝነት መለየት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል። መታወቂያው ዕድሜ፣ ፆታ፣ የአስር ጣቶች አሻራ፣ የመኖሪያ አድራሻና ሌሎች ገላጭ መረጃዎችን የሚይዝ መሆኑንም አስረድተዋል።
በአሁኑ ወቅት አርሶ አደሮችና በገጠር አካባቢ ያሉ ሰዎች እንዴት መመዝገብ ይችላሉ የሚለውን ለማወቅ በአዲስ አበባ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብና ሲዳማ ክልሎች 125 ሺህ ዜጎች በሙከራ ደረጃ ተመዝግበው ውጤታማነቱ ተረጋግጧል ብለዋል። በ2015 ዓ.ም በኢትዮጵያ የሚኖሩ 12 ሚሊዮን ዜጎችን የብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ ባለቤት ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጸዋል። ለዚህም በንግድ ባንክ፣ ኢትዮ-ቴሌኮም እና መሰል አገልግሎት በሚሰጥባቸው ተቋማት አገልግሎት ለማግኘት ሲሄዱ በቀላሉ መመዝገብ ይችላሉ ብለዋል።
የብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ ፕሮጀክት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮዳሄ ዘሚካኤል፥ ዲጅታል መታወቂያ በኢትዮጵያ የሚኖር ማንኛውም ዜጋ የራሱን ማንነት የሚገልጽበት መለያ ነው። ብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ በኪስ የሚያዝ ወረቀት ሳይሆን የራሱ መለያ /ፋይዳ/ የሚባል ቁጥር ብቻ ይዞ በማንኛውም ቦታ በቁጥሩ ምክንያት አገልግሎት ማግኘት የሚችሉበት ዘመናዊ አሠራር መሆኑንም አስረድተዋል። ከቤቱ ሆኖ የባንክ አካውንት መክፈት፣ የኢንሹራንስ አገልግሎት ማግኘትና በአገልግሎት ሰጭውና ተቀባዩ ዘንድ መተማመን መፍጠር ያስችላል ብለዋል።
በዚህም እስከ 2018 ዓ.ም ከ70 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ እንዲኖራቸው ለማስቻል ዕቅድ መያዙን አቶ ዮዳሄ ተናግረዋል። የፎቶ ኮፒና ሌሎች የህትመት ሥራዎች ሁሉ የንግዱ ማኅበረሰብ በየሱቆቹ ማስመዝገብ የሚችልበትን አሠራር እንዘረጋለን ሲሉም ተናግረዋል።
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ፥ ብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ ብዙ ትኩረት ሳይሰጠው የቆየ መሆኑን ገልጸው፤ በተለይም ለጤናው ዘርፍ የጎላ ሚና ያለው መሆኑን ገልጸዋል። በኢትዮጵያ ብሔራዊ የዲጅታል መታወቂያ ባለመኖሩ ምክንያት ዲጅታል የጤና መሣሪያዎችን ወደ ሥራ ማስገባት እንዳልተቻለም ጠቅሰዋል። በመሆኑም ብሔራዊ የዲጅታል መታወቂያው ሥራ መጀመር በመላ ሀገሪቱ ያሉ ከ40 ሚሊየን በላይ የጤና መድህን ተጠቃሚዎች መታወቂያቸውን በቀላሉ አድሰው የተቀላጠፈ የጤና አገልግሎት ማግኘት ያስችላቸዋል ብለዋል። የብሔራዊ ዲጅታል መታወቂያ የኢትዮጵያን የጤና አገልግሎት አሰጣጥ በማዘመን የጎላ ሚና እንዳለው ገልጸው በቅርቡ ወደ ሥራ እንዲገባ አስፈላጊውን ሁሉ እገዛና ትብብር እናደርጋለን ሲሉ አረጋግጠዋል። ዘገባው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ነው።
July 18, 2021 at 2:53 am #19938In reply to: የፖለቲካ ፓርቲዎች ድምጽ (ኢትዮጵያ ውስጥ የሚነቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች)
AnonymousInactiveየኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታ ላይ የሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ
የኦሮሚያ ክልል ሕዝብና መንግሥት ኢትዮጵያን በመገንባት ዉስጥ የሚመጥነዉን አስተዋፅኦ ሲያበረክት ቆይቷል። የሀገርና የሕዝብ ሉአላዊነትና ነፃነትን ለማስከበር በሚከፈለዉ መስዋዕትነት ላይ እራሱን ቆጥቦ አያውቅም። በዉጪ ወረራና በታሪክ አጋጣሚ የባንዳነትን ተግባር ሲፈጽሙ በነበሩት ኃይሎች ላይ በየታሪክ ምዕራፉ ራሱን ሰጥቶ ኢትዮጵያን የገጠሟትን ችግሮች ለማክሸፍ መስዋዕትነትን ከፍሏል። እንደሀገር ስናስመዘግብ በቆየናቸው ድሎች ዉስጥ ተወራራሽ ታሪክ አስመዝግቧል።
ዛሬም እንደ ትናንቱ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የክልሉን ሕዝብ በማቀናጀት በወንድሞቻችን አብሮነት በኢትዮጵያ ላይ የሚቃጣውን የውስጥና የውጪ ትንኮሳ ለማክሸፍ ዝግጁነቱን ይገልፃል።
የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የፌደራል መንግሥቱ የወሰደውን የአንድ ወገን ተኩስ የማቆም እርምጃ ለሕዝብ ጥሩ የጥሞና ጊዜ የፈጠረ መሆኑን አምኖ ሲደግፍ ቆይቷል። ይሁን እንጂ ከአፈጣጠሩ የተጣመመው ህወሓት ለሕዝብ ጥቅም ተብሎ ለተደረገው ጥሪ ቦታ እንደሌለዉ በግልፅ አሳይቷል። ዛሬም እንደ ትናንቱ በአሮጌ የፖለቲካ እይታ ተሞልቶ የጦርነት ነጋሪት እየጎሰመ ይገኛል።
የህወሓት የፖለቲካ ፅንሰ-ሐሳብ ሕዝብን እንደ ጠላት በመፈረጅ ላይ ያተኮረ ነው። የግጭት መነሻ የአንድነት ፀርና ለሀገራዊ ብሔርተኝነት መውደቅ ምክንያት ሆኗል።
የህወሓት ፀረ አንድነት ፈንጂ በየቀኑ እየፈነዳ ለዜጎች ሞትና ስቃይ ምክንያት በመሆን ዓመታትን አስቆጥሯል። የድህነትና የኋላ ቀርነትን እሽክርክሪት ዘመን አራዝሞብናል። ለእድገታችንና የብልፅግና ጉዞ እንቅፋት በመሆን እንድንሸማቀቅ አርጎናል። በዚህ ሁኔታ ዉስጥ ሀገርና ሕዝብ በቀዳሚነት እየተጎዱ ነው።
አሸባሪው ህወሓት ‘እታገልላቸዋለሁ’ ብሎ የሚናገረውና በስማቸው እየኖረ ያለውን የትግራዋይ ሕዝብን ጨምሮ አስቦላቸው ወይም ተቆርቁሮላቸው አያውቅም። ይህ ቡድን ትናንት የሓውዜን ሕዝብ በሚገበያይበት ቦታ ላይ ቦምብ በማዝነብ የጅምላ ጭፍጨፋ ሲፈፅም ለፕሮፖጋንዳ ግብአትነት እንጂ ለሉአላዊነት ትግል አልነበረም። ሕዝብን በመጨፍጨፍ ሕዝብን ነፃ ማውጣት በየትኛውም መስፈርት የሚታረቅ አስተሳሰብ አይደለም።
ዛሬም ቢሆን በተባበሩት መንግሥታት የወጣውን የሕፃናት መብት ድንጋጌ በመጣስ ጨቅላ ሕፃናትን ለጦርነት ከፊት አሰልፈው በመማገድ ላይ ይገኛል። አዛውንቶችን፣ እናቶችን እና የሀይማኖት አባቶችን እንደ ጋሻ ከፊት በማሰለፍ በእልቂታቸው የጀግንነት አክሊል ለመድፋት ይሞክራል። አሁንም ቢሆን አሸባሪው ህወሓት የፌደራል መንግሥት ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን ካሳየው ፍላጎት በተቃራኒ በመሄድ ላይ ይገኛል። በፌደራል መንግሥት የታወጀው የተናጠል የተኩስ አቁም ስምምነት አርሶአደሩ በክረምት ወቅት ተረጋግቶ እንዲያርስ፣ ለዜጎች እርዳታ እንዲደርስና ግጭት እንዳይባባስ ቢሆንም፥ ህወሓት የተፈጠረበትን የጥፋት ስሜትና እጅ መቆጣጠር አልቻለም።
የ1967ቱ ህወሓት ማኒፌስቶ ሕዝብና ሕዝብን በማጋጨት ሰላምና መረጋጋትን ለመንፈግ የተወጠነ ነበር። ለኢትዮጵያ ግንባታ ቋሚና ማገር በመሆን ለዛሬ ያደረሳትን ሕዝብ ለመበታተን ያለመ ነው።
አሸባሪው ህወሓት ላለፉት 27 ዓመታት ሀገር ሲመራ በነበረበት ወቅት በሕዝብ ውስጥ ትቶት ያለፈው ሰቆቃ ሳያንስ፥ ዛሬም በሀገር ላይ የጭካኔ ተግባራትን እየፈፀመ ነው። ሕወሓት በማይካድራ የፈፀመው የዘር ማጥፋት ተግባር በብሔር ላይ ያተኮረ የሕዝብ ጠላትነት ላይ የተመሠረተ እኩይ ተግባር ነው። አሁንም በተደጋጋሚ ተመሳሳይ ድርጊት ለመፈፀም ሲቅበዘበዝ ይታያል።
የሕወሓት ኃይል የሕዝብና የሀገር ጥቅምን አሳልፎ ከመስጠት አይመለስም። እድገታችንንና ልማታችንን ለመግታት ከሚታገሉ የውስጥና ውጪ ጠላቶች ጋር በማበር የጥፋትና የማፍረስ ሴራዎችን በዋና ተዋናይነት ሲፈፅም እንደነበረ በገሀድ ታይቷል። አሸባሪው ህወሓት ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከማስተጓጎል ጀምሮ ከነአካቴው እስከ ማደናቀፍ ድረስ የተላላኪነት እና የባንዳነት ትወና ድርሻውን ተወጥቷል።
የአሸባሪው ህወሓት ክህደት በሕዝብ ንቀት ብቻ የተገታ አልነበረም፤ የሀገር ሉዓላዊነትን ጭምር ጥያቄ ውስጥ እስኪገባ አስነዋሪ ተግባር ፈጽሟል። ኢትዮጵያ ብትፈርስም፣ በውጪ ወራሪ ብትወረርም ደንታ እንደሌለው እስከ መግለፅ ደርሷል።
ስለሆነም ህወሓት ለአንዱ የሚያስብ፣ ሌላውን የሚነፍግ ሳይሆን በጅምላ የመጨፍጨፍ እና የማፈራረስ አቅጣጫን ይከተላል። ከእሱ ተወልዶ፣ ከእጁ በልቶ ላደገዉ ሕዝብ የማይራራ፣ ሌላ ዘመድ ሊኖረውም ሆነ ሊያፈቅር አይችልም። “ጅግራ ዘመድ መስሎ ወፊቱን በላት” እንደሚባለው ሁሉ፥ ለአንዱ አዝኖ፣ ሌላውን አኩርፎ፣ ሌሎችን ደግሞ የተጸየፈ መስሎ የሚቀርበውን ፕሮፖጋንዳ አምኖ መቀበል ሞኝነት ነው።
የአሸባሪው ህወሓት ኃይል ተሸንፏል፤ በፖለቲካ ሜዳው አሸናፊ ሀሳብ ማቅረብ ተስኖት ለቆ ስደትን መርጧል። በማግስቱ የጦርነት ነጋሪትን መጎሰም ጀመረ። ውሎ ሳያድር በዜጎቻ ላብ የተገዛውን የሀገር ሉዓላዊነት የሚጠበቅበት መሣርያ በመዝረፍ ኢትዮጵያን ለማንበርከክ ዛተ። በከሀዲዎችና የውጪ ኃይሎች ማበረታቻ የሰከረው ሕወሓት በመከላከያ ሠራዊቱ ለይ የጥቃት እርምጃ ወሰደ። ከትግራይ ሕዝብ ጋር ከ20 ዓመታት በላይ የኖረውን የመከላከያ ሠራዊት በከባድ የጭነት መኪናዎች ከመጨፍለቅ ጀምሮ እጅግ አስነዋሪ እርምጃዎችን ወስዷል።
የክልልና የሀገራችን ሕዝብ በመከላከያ ሠራዊታችን ላይ የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ መከላከያ ሠራዊቱን ለመደገፍ ሁሉ አቀፍ ድርሻውን ተወጥቷል። ዛሬም ቢሆን የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትና ሕዝብ የሀገር ሉዓላዊነት ጋሻ ከሆነው የመከላከያ ሠራዊታችን ጎን በመሆን ማናቸዉንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነው። መንግሥትም የሕዝብ ተሳትፎን በማቀናጀት ሁለንተናዊ ስኬት ለማስመዝገብ ያላሰለሰ ጥረት ያደርጋል።
ትናንት በችግር ውስጥ የመንግሥትን ጥሪን በመስማት ሁለንተናዊ ድርሻችሁን የተወጣችሁና የአሸባሪዎች የጥፋት መርዝ እንዲደፋ ያደረጋችሁ የክልላችን የኅብረተሰብ ክፍሎች ዛሬም እንደ ትናንቱ የጎላ ተሳትፎአችሁን እንድታበረክቱ መንግሥት ጥሪውን ያቀርባል።
በሕዝባችን የተባበረ ክንድ ዘላቂ ሉዓላዊነታችን ይረጋገጣል!!
የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት
ሐምሌ 2013
ፊንፊኔJuly 10, 2021 at 6:05 pm #19898AnonymousInactiveስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የምርጫ ውጤት
ሰኔ 14 ቀን፥ 2013 ዓ.ም. የተካሄደው የስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውጤት ይፋ ተደረገ። ይህ ውጤት የሚገለፀው ባገኙት ወንበር ልክ ሲሆን በዚህም መሠረት፦
- የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር
– መስተዳድሩ ያለው የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ: 23
– ሰኔ 14 ቀን ምርጫ የተከናወነበት የተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ክልል ብዛት: 23
□ ብልፅግና ፓርቲ ያገኘው መቀመጫ: 22
□ የግል ተወዳዳሪ ያገኘው መቀመጫ: 1 - የአፋር ብሔራዊ ክልል
– ክልሉ ያለው የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ: 8
– ሰኔ 14 ቀን ምርጫ የተከናወነበት የተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ክልል ብዛት: 6
□ ብልፅግና ፓርቲ ያገኘው መቀመጫ: 6 - የአማራ ብሔራዊ ክልል
– ብሔራዊ ክልሉ ያለው የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ: 138
– ሰኔ ቀን ምርጫ የተከናወነበት የተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ክልል ብዛት: 125
□ ብልፅግና ፓርቲ ያገኘው መቀመጫ: 114
□ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ፓርቲ ያገኘው መቀመጫ: 5
– ድጋሚ ቆጠራ የሚከናወንበት ምርጫ ክልል ብዛት: 1
– ድጋሚ ምርጫ የሚከናወንበት ምርጫ ክልል ብዛት: 5 - የቤኒሻንጉል-ጉሙዝ ብሔራዊ ክልል
– ብሔራዊ ክልሉ ያለው የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ: 9
– ሰኔ 14 ቀን ምርጫ የተከናወነበት የተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ክልል ብዛት: 3
□ ብልፅግና ፓርቲ ያገኘው መቀመጫ: 3
– ድጋሚ ምርጫ የሚከናወንበት ምርጫ ክልል ብዛት: 2 - የድሬዳዋ ከተማ መስተዳድር
– መስተዳድሩ ያለው የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ: 2
– ሰኔ 14 ቀን ምርጫ የተከናወነበት የተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ክልል ብዛት: 2
□ ብልፅግና ፓርቲ ያገኘው መቀመጫ: 1
– ድጋሚ ቆጠራ የሚከናወንበት ምርጫ ክልል ብዛት: 1 - የጋምቤላ ብሔራዊ ክልል
– ብሔራዊ ክልሉ ያለው የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ: 3
– ሰኔ 14 ቀን ምርጫ የተከናወነበት የተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ክልል ብዛት: 3
□ ብልፅግና ፓርቲ ያገኘው መቀመጫ: 3 - የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል
– ብሔራዊ ክልሉ ያለው የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ: 178
– ሰኔ 14 ቀን ምርጫ የተከናወነበት የተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ክልል ብዛት: 170
□ ብልፅግና ፓርቲ ያገኘው መቀመጫ: 167
□ የግል ተወዳዳሪዎች ያገኙት መቀመጫ: 3 - የሲዳማ ብሔራዊ ክልል
– ብሔራዊ ክልሉ ያለው የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ: 19
– ሰኔ 14 ቀን ምርጫ የተከናወነበት የተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ክልል ብዛት: 19
□ ብልፅግና ፓርቲ ያገኘው መቀመጫ: 19 - የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ብሔራዊ ክልል
– ብሔራዊ ክልሉ ያለው የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ: 104
– ሰኔ 14 ቀን ምርጫ የተከናወነበት የተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ክልል ብዛት: 85
□ ብልፅግና ፓርቲ ያገኘው መቀመጫ: 75
□ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ ያገኘው መቀመጫ: 4
□ የጌዴኦ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት: 2
– ድጋሚ ቆጠራ የሚከናወንበት ምርጫ ክልል ብዛት: 1
– ድጋሚ ምርጫ የሚከናወንበት ምርጫ ክልል ብዛት: 3
በዚህ ሐምሌ 3 ቀን፥ 2013 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ባደረገው የምርጫ ውጤት መሠረት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመቀመጫ ብዛት በአጠቃላይ 484 ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ በስልጣን ላይ የሚገኘው ብልፅግና ፓርቲ 410 መቀመጫ አሸንፏል። ይህም ውጤት ፓርቲውን መንግሥት ለመመሥረት ያስችለዋል።
ይህን የምርጫ ውጤት እና የፓርቲያቸው ማሸነፍን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ያስተላለፉትን መልዕክት ለማንበብ እዚህ ጋር ይጫኑ።
June 5, 2021 at 8:32 pm #19554In reply to: የፖለቲካ ፓርቲዎች ድምጽ (ኢትዮጵያ ውስጥ የሚነቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች)
AnonymousInactiveየኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግን ማብራሪያ ጠየቀ
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በቅርቡ የተቋቋመው የአዲስ አበባ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ወረዳ ፍርድ ቤት ሥልጣን እና ተግባራት ላይ ማብራሪያ ይሰጠኝ ሲል የኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግን ጠየቀ።
ኢዜማ ለጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በላከው ደብዳቤ፣ በተለያዩ መንግሥታዊና የግል ሚዲያዎች ‹‹የፊንፊኔ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት›› በይፋ ተከፍቶ አገልግሎት መስጠት ጀመረ በማለት የተሰሩት ዘገባዎች፣ በሕገ-መንግሥቱ ለአዲስ አበባ ከተማ የተሰጠውን ራስን በራስ የማስተዳደር ሥልጣን የሚጋፋ ሆኖ አግኝቼዋለሁ ብሏል።
የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ (ኦቢኤን) የአዲስ አበባ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ኩመላ ቡላን ጠቅሶ በሰራው ዘገባ «…በፊንፊኔ ከተማ የሚኖሩ የኦሮሞ ብሄር ተወላጆችም ሕገ-መንግሥታዊ መብታችውን በመጠቀም በዚህ ፍርድ ቤት በቋንቋቸው የመዳኘትና ተደራሽ የሆነ የፍትህ አገልግሎት የማግኘት መብትም ያገኛሉ ብለዋል።» በማለት መዘገቡን ያስታወሰው ኢዜማ፣ ይህንን ዘገባ ተከትሎ አዲስ የተከፈተው ፍርድ ቤት ሥልጣንና ተግባራት ላይ የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግን ማብራሪያ ጠይቋል።
የኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 49 (2 እና 3) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ ሥልጣን እንዳለው ተጠሪነቱም ለፌደራል መንግሥት አንደሆነ በግልጽ ደንግጓል ያለው ኢዜማ፥ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ራሱን በራሱ ያስተዳድራል ሲባል ከተማው የራሱ ሕግ አውጭ፣ ሕግ አስፈጻሚ እና ሕግ ተርጓሚ ይኖረዋል ማለት መሆኑን ጠቁሞ፤ ተጠሪነቱ ለፌደራል መንግሥት ነው ማለት ደግሞ በአዲስ አበባ ጉዳዮች ላይ የመጨረሻ የመወሰን ሥልጣን ያለው አካል የፌደራል መንግሥቱ ብቻ ነው ማለት ነው ሲል አመላክቷል።
የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችን ለሚገጥማቸው ማናቸውም ጉዳይ የትኛውም ብሔር ጀርባ ቢኖራቸውም የመዳኘት ሥልጣኑ የከተማ መስተዳደሩ ፍርድ ቤቶችና የፌደራል ፍርድ ቤቶች መሆኑን የጠቀሰው ኢዜማ፣ አንድ ክልል የዚህ ብሔር ተወላጆችን ነዋሪነታቸው በአዲስ አበባ ከተማ ቢሆንም የመዳኘት ሥልጣን ይኖረኛል ማለቱ በሕገ-መንግሥቱ ለፌደራል መንግሥቱ የተሰጠውን ሥልጣን የሚጋፋ፤ በአዲስ አበባ ቻርተር አዋጅ ቁጥር 87/1989 እንዲሁም እሱን ያሻሻለው አዋጅ ቁጥር 361/1995 የአዲስ አበባ አስተዳደር ራስ ገዝ ከመሆኑም ባሻገር በፌደራሉ መንግሥት የዳኝነት ፈቃደ ሥልጣን ሥር በማይወድቁ ጉዳዮች ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ፍርድ ቤቶች አና የቀበሌ ማኅበራዊ ፍርድ ቤቶች ብቻ ሥልጣን እንደሚኖራቸው ተብሎ የተደነገገውን በግልጽ የሚቃረን ሆኖ አግኝቼዋለሁ ብሏል።
አሁን ለተቋቋመው ፍርድ ቤት የሕግ መሰረት ተደርጎ የተጠቀሰው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፍርድ ቤቶች አደረጃጀት ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጣው አዋጅ ቁጥር 216/2011 በአንቀጽ 24 ላይ ከተዘረዘሩት የኦሮሚያ ፍርድ ቤቶች የተሰጣቸው ሥልጣን እና ተግባራት ላይ በአዲስ አበባ የሚኖሩ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆችን ጉዳይ የማየት ሥልጣን እንዳላቸው ባልጠቀሰበት ሁኔታ፣ በአዲስ አበባ የሚኖሩ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆችን ጉዳይ የማየት የዳኝነት ፈቃደ ሥልጣን የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፍርድ ቤቶች አላቸው ተብሎ መገለጹ ኢ-ሕገ-መንግሥታዊ እና ምንም ዓይነት የሕግ መሰረት የሌለው ነው ያለው ኢዜማ፣ በአንድ ከተማ ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች የብሔር ማንነታቸው ላይ በመመስረት የተለያየ የዳኝነት መብት ይኖራቸዋል ብሎ ፍርድ ቤት መክፈት የዜጎቸን በሕግ ፊት በእኩልነት የመታየት ሰብአዊና ሕገ-መንግሥታዊ መብትን የሚጥስ ከመሆኑም ባለፈ የዜጎችን ተከባብሮ የመኖር እሴት የሚሸረሽር ነው የሚል እምነት እንዳለው ኢዜማ በደብዳቤው ገልጿል።
በአንድ ከተማ ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች የብሔር ማንነታቸው ላይ በመመስረት የተለያየ የዳኝነት መብት ይኖራቸዋል ብሎ ፍርድ ቤት መክፈት የዜጎችን በሕግ ፊት በእኩልነት የመታየት ሰብዓዊና ሕገ-መንግሥታዊ መብትን የሚጥስ ተግባር መሆኑን የጠቀሰው ኢዜማ፣ ይህ ዓይነቱ ድርጊት የዜጎችን ተከባብሮ የመኖር ዕሴት ይሸረሽራል ብሎ እንደሚያምን ገልጿል።
የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ መሥሪያ ቤት በአፋጣኝ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያውን እንዲሰጠው የጠየቀው ኢዜማ፣ ‹‹ጠቅላይ አቃቤ፣ ይህንን ከሕገ-መንግሥት ማዕቀፍ ውጪ የሆነ ኢ-ሕገ-መንግስታዊ ተግባር እንዲያስቆም ሲል ለጠቅላይ አቃቤ ሕግ በላከው ደብዳቤ ጥያቄውን አቅርቧል።
ምንጭ፦ ኢዜማ
April 19, 2021 at 10:24 pm #19108In reply to: ነፃ አስተያየት (ስለኢትዮጵያ በኢትዮጵያውያን)
AnonymousInactiveሚያዝያ 11 ቀን፥ 2013 ዓ.ም.
አቶ ልደቱ አያሌው
ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን
አዲስ አበባጉዳዩ:- በድጋሚ አቤቱታ ማቅረብን ይመለከታል
በቅድሚያ በእኔ በአመልካቹ ላይ በተደጋጋሚ እየደረሰ የሚገኘውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፍትሄ እንዲያገኝ መሥሪያ ቤታችሁ እያደረገ ስላለው ያልተቋረጠ ጥረት ልባዊ ምስጋናየን አቀርባለሁ። ሆኖም በእኔ ላይ እየተፈፀመ የሚገኘው የሰብዓዊ መብት ጥሰት አሁንም ያልተቋረጠና ለሕይወቴ አስጊ በሆነ ደረጃ ተጠናክሮ የቀጠለ በመሆኑ፥ ይሄንን አቤቱታ በድጋሚ ለማቅረብ ተገድጃለሁ።
የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በሀገሪቱ የተፈጠረውን የፖለቲካ ቀውስ ሰበብ በማድረግ በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንድውል ከተደረገበት ከሐምሌ 17 ቀን፥ 2012 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገሪቱ ሕግና የሕግ የበላይነት የለም ሊያስብል በሚባል ደረጃ በርካታና ተከታታይ የሰብዓዊ መብት መብት ጥሰት በእኔ ላይ እየተፈፀመ ይገኛል። ለማስታወስ ያህል…
- ሕጋዊ ነዋሪነቴ ተመዝግቦ የሚገኘው በአዲስ አበባ ከተማ ሆኖ እያለ፥ እንድታሰር የተደረገው ግን ያለ አግባብ በኦሮሚያ ክልል ነው።
- በስልክ ተጠርቼና ለፌደራሉ ፖሊስ ኮሚሽን በእራሴ ፈቃድ እጄን ሰጥቼ በቁጥጥር ስር ከዋልኩ በኋላም በሕጉ መሠረት በ48 ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት እንድቀርብ አልተደረገም።
- በቁጥጥር ስር ከዋልኩ በኋላ ያለምንም ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በስልክና በኢንተርኔት አማካይነት ያደረኳቸው የግል የመልዕክት ልውውጦች በሕገ-ወጥ መንገድ እንዲበረበሩና በሲዲ እንዲቀዱ ተደርገዋል። የግል ማስታወሻወቼና ረቂቅ የፅሁፍ ሰነዶቸ ሳይቀሩ በፖሊስ ተወስደዋል።
- በቁጥጥር ውስጥ ውዬ ገና ክስ እንኳ ባልተመሠረተብኝ ወቅት የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኛ ነን የሚሉ ሰዎች ወንጀለኛ እንደሆንኩ አድርገው ሰፊ የስም ማጥፋት ዘመቻ እንዲያካሂዱብኝ ተደርጓል።
- በምርመራ ወቅትና የምርመራ ፋይሌ ከተዘጋ በኋላም የዋስ መብት ተከልክዬና ክስ ሳይመሠረትብኝ በጊዜ ቀጠሮ ሰበብ ከሁለት ወራት በላይ ለሆነ ጊዜ በሕገ-ወጥ መንገድ በእስር ቤት እንድቆይ ተደርጓል።
- በፍርድ ሂደቱ ወቅት በግልፅ እንደታየው፥ በቢሾፍቱ ከተማ አመፅ አስነስተሀል፤ ሕገ-ወጥ መሣሪያ ታጥቀህ ተገኝተሀል፤ መንግሥትን በሕገ-ወጥ መንገድ አፍርሰሀል የሚሉ የፈጠራ ክሶች እንዲቀርቡብኝ ተደርጓል።
- “መንግሥትን በሕገ-ወጥ መንገድ አፍርሰሀል” በሚል የተከሰስኩበት ወንጀል አዲስ አበባ በሚገኝ የፌደራሉ ፍርድ ቤት መታየት ሲገባው ያለ አግባብ በአዳማ ከተማ የሚገኘው የኦሮሚያ ክልል ጥቅላይ ፍርድ ቤት በውክልና እንዲያየው ተደርጓል። ይህም መሆኑ የፍርድ ሂደቱ በማልናገረው ቋንቋ እንዲካሄድና ብዙ ውጣ ውረድ እንዲደርስብኝ አድርጓል።
- በፍርድ ሂደቱ ወቅት ለሁለት ጊዜ ያህል የዋስ መብት በፍርድ ቤት ቢፈቀድልኝም ፖሊስ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ በመጣስ ለሁለት ወራት ያህል በእስር አቆይቶኛል። ከዋስትና መብቴ ጋር በተያያዘም ፍርድ ቤት ለአምስት ጊዜ የሰጣቸው የተለያዩ ትዕዛዞች በፖሊስ እምቢተኝነት ሳይፈፀሙ ቀርተዋል።
- ለሕይወት አስጊ የሆነ ከፍተኛ የልብ ህመም ያለብኝ ሰው መሆኔ እየታወቀም የኮቪድ ወረረሽኝ ተጠቂ ከሆኑ ሰዎች ጋር በአንድ ጠባብ ግቢ ውስጥ ታስሬ ለረጅም ጊዜ እንድቆይ ተደርጓል።
- ከአምስት ወራት መታሰር በኋላ የዋስ መብቴ ተጠብቆ ከተፈታሁ ከጥቂት ቀናት በኋላም እኔንና የትግል ጓደኞቼን ከሀገሪቱ የፖለቲካ ሂደት ለማግለል ሲባል አባል የሆንኩበት የፖለቲካ ፓርቲ በሕገ-ወጥ መንገድ እንዲሰረዝና ህልውናውን እንዲያጣ ተደርጓል።
- ከእስር ቤት ወጥቸ አስቸኳይ የቀዶ ጥገና የሕክምና እርዳታ ለማግኘት ወደ ውጭ ሀገር ለመጓዝ ለሁለት ጊዜ ያደረኩት ሙከራም ምንም አይነት የፍርድ ቤት እገዳ ባልተጣለብኝና እንዲያውም ጉዳዩን ይመለከት የነበረው ፍርድ ቤት ወደ ውጭ ሀገር ሄጀ የመታከሜን አስፈላጊነት በማመን ረዥም ቀጠሮ ሰጥቶኝ እያለ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት መሥሪያ ቤት በሕግ ባልተሰጠው ሥልጣን ባደረገብኝ ሕገ-ወጥ ክልከላ ምክንያት ከሀገር የመውጣት ሕገ- መንግሥታዊ መብቴ ተጥሷል።
- ይህ የተጣለብኝ ሕገ-ወጥ እገዳ እንዲነሳልኝ ለማድረግ የተለያዩ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን የመንግሥት ባለ ስልጣናት ቀጠሮ ይዤ ለማነጋገር በተደጋጋሚ ብሞክርም ባለስልጣናቱ ሊያናግሩኝ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ሙከራዬ ሳይሳካ ቀርቷል።
- መሥሪያ ቤታችሁ ባደረገው ጥረት ምክንያት የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት መሥሪያ ቤት በእኔ ላይ ምንም ዓይነት የጉዞ ክልከላ እንዳላደረገ የሚክድ ደብዳቤ ለመሥሪያ ቤታችሁ ከፃፈ በኋላም ለሦስተኛ ጊዜ ከሀገር ለመውጣት ያደረኩት ሙከራ የኢሚግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ክልከላ ስላደረገብኝ ጉዞዬ ሳይሳካ ቀርቷል። የጉዞ ፓስፖርቴም በመሥሪያ ቤቱ ባልደረቦቼ ተወስዶብኛል።
- የኢሚግሬሽን መሥሪያ ቤት ለምን የጉዞ ክልከላ እንዳደረገብኝና እንደቀማኝ በማግስቱ ዋናው መሥሪያ ቤት ድረስ ሄጄ ለመጠየቅ ባደረኩት ሙከራ የፌዴራሉ ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ክፍል ባቀረበው ጥያቄ መሠረት በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውዬ ምርመራ እስከሚካሄድብኝ ድረስ የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የአራዳ ምድብ አንደኛ ችሎት የካቲት 4 ቀን፥ 2013 ዓ.ም. በዋለው ችሎት ወደ ውጭ እንዳልጓዝ እገዳ የጣለብኝ ስለመሆኑ ተነግሮኛል።
ከእነዚህ ከዚህ በላይ ከተዘረዘሩት ተደጋጋሚ የመብት ጥሰቶች በግልፅ መረዳት እንደሚቻለውና በእኔ በኩል እንደምገነዘበውም መንግሥት በእኔ ላይ ይህን ሁሉ የመብት ጥሰት እየፈፀመ የሚገኘው የፈፀምኩት ወንጀል ስላለ ሳይሆን መብቴን በሕገ-ወጥ መንገድ በመጣስና በመገደብ ከፖለቲካ ተሳትፎ ውጭ እንድሆን ስለፈለገ ነው።
እኔ አመልካቹ የአለፈ ታሪኬ እንደሚያሳየው ለሃያ ስምንት ዓመታት በሀገሪቱ ፖለቲካ በነበረኝ ተሳትፎ ስድስት ጊዜ በሕገ-ወጥ መንገድ በፈጠራ ክስ የታሰርኩ ቢሆንም አንድም ጊዜ በወንጀለኝነት ተፈርዶብኝ አያውቅም። የኢትዮጵያ ህዝብ በግልፅ እንደሚያውቀው በዚህ የረጅም ጊዜ የፖለቲካ ተሳትፎዬ ስታገል የኖርኩት በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም፣ እርቅና የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን ሲሆን፤ በአንፃሩም ሕገ-ወጥነትን፣ አመጽንና የኃይል አማራጭን በግልፅና በድፍረት በማውገዝ የምታወቅ ሰላማዊ የፖለቲካ ሰው ነኝ። ሆኖም መንግሥት ከላይ በተገለፀው ሁኔታ በፈጠረብኝ ተከታታይ ሕገ-ወጥ ጫና ምክንያት በአሁኑ ወቅት ከፖለቲካ ተሳትፎዬ ሙሉ በሙሉ ለመገለል የተገደድኩ ሲሆን ከዚያም በላይ ያለብኝን ከፍተኛ የልብ ህመም ወደ ውጭ ሀገር ሄጀ መታከም ባለመቻሌ ምክንያት በህይወት የመኖር ዕድሌ ከፍተኛ አደጋ ላይ ወድቋል። በአጠቃላይም እየደረሰብኝ ባለው ተደጋጋሚ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ምክንያት ለከፍተኛ የጤና መታወክ፣ የሞራል ውድቀት፣ የገንዘብና የጊዜ ብክነት ተዳርጊያለው።
ይህ ሁሉ በተደጋጋሚ የተፈጸመብኝ በደል አልበቃ ብሎም እኔ አመልካቹ ፈጽሞ ባልተነገረኝና በማላውቀው ሁኔታ፣ ምንም ዓይነት ጥያቄ ባልቀረበልኝና ምርመራ ባልተካሄደበት ሁኔታ፣ ከዚያም በላይ ተፈልጌ የጠፋሁ ወንጀለኛ የሆንኩ በሚያስመስል ሁኔታ የጉዞ እገዳ የተጣለብኝ ስለመሆኑ የአራዳ ፍርድ ቤት ሰጠ የተባለው ትዕዛዝ አሁንም በእኔ ላይ የፈጠራ ክስ እንደገና በመመሥረት እንድታሰርና ሕይወቴ አደጋ ውስጥ እንዲወድቅ እየታሰበና ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ነው።
በአንድ ሰው የደረሰ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በሁሉም ሰው ላይ እንደደረሰ ጥሰት የሚቆጠር መሆኑን ታሳቢ በማድረግና በእኔ ላይ እየተፈፀመ ያለው ተደጋጋሚ መቋጫ ያጣ የሰብዓዊ መብት ጥሰትም የፖለቲካና ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ ሕገ-መንግሥታዊ መብቴን ከመጣስም በላይ በሕይወት ለመኖር ያለኝን የማይገሰስ ሰብዓዊ መብቴን አደጋ ላይ የጣለ መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት፥ መሥሪያ ቤታችሁ በጉዳዩ ልዩ ትኩረት በመስጠት ምርመራ እንዲያካሂድልኝና አስቸኳይ መፍትሔ እንዳገኝ እንዲያግዘኝ በድጋሚ በአክብሮት እጠይቃለሁ።
ከሰላምታ ጋር!
ልደቱ አያሌውግልባጭ፦
ለመገናኛ ብዙሀንApril 19, 2021 at 12:56 am #19091In reply to: ከመንግሥታዊ ተቋማት የሚወጡ ሰሞነኛ ዜናዎችና መግለጫዎች
AnonymousInactiveከኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር በሀገራችን ወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታ የተሰጠ መግለጫ
በአንዳንድ የሀገራችን አከባቢዎች ሕዝብን ከሕዝብ በማጋጨት በንጹሃን ዜጎች ላይ የህይወት እና ንብረት አደጋ ባደረሱ የጥፋት ቡድኖች ላይ እርምጃ መወሰድ ተጀምሯል።
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊታችን በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ትግራይ ክልል ውጤታማ ሕግ የማስከበር ተልእኮውን በጀግንነት በመፈጸም ላይ በሚገኝበት በአሁኑ ወቅት፣ በአንዳንድ የሀገራችን አከባቢዎች የጸጥታ ችግሮች እየተስተዋሉ ይገኛሉ።
እነዚህ ሆን ተብሎ የሠራዊታችንን ሕገ-መንግሥታዊ ተልእኮ ለማስተጓጎል ታስበው የተሠሩ የጥፋት ሴራዎች፣ በሰላም ወዳዱ ሕዝባችን እና በመከላከያ ሠራዊታችን የተቀናጀ ሥራ ሊከሽፉ ችለዋል።
አንደኛ በመተማ መስመር ለዘመናት አብረው በኖሩ የቅማንት እና የአማራ ተወላጆች መካከል የተፈጠሩ የጸጥታ ችግሮችን የፈዴራል እና የክልል የጸጥታ ኃይሎች ከኅብረተሰቡ እና ከአካባቢው የሀገር ሽማግሌዎች ጋር የተቀናጀ ሥራ በመሥራት የተከሰቱ የጸጥታ ችግሮን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ከፍተኛ ሥራ እየተሠራ ይገኛል ።
ሁለተኛ፥ በወለጋ ቡሬ መስመር፣ በጊዳ አያና፣ አንገር ጉቴ አዋሳኝ አከባቢዎች ለረዥም ጊዜ አብሮ በኖሩ የአማራ እና የኦሮሚያ ክልል ነዋሪዎችን ሆን ብሎ ለማጋጨት ታስቦ የተደረገው ሙከራ በአከባቢው ኅብረተሰብ ትብብር ወደ ሰላማዊ ሁኔታ ለመመለስ ተችሏል።
ሦስተኛ፥ የሀገራችንን የገቢ እና ወጪ የንግድ እንቅስቃሴን ለመገደብ በማሰብ፣ በሱማሌ እና የአፋር ኢሳ ሕዝቦችን ለማጋጨት የተሴረው ሴራ በሰላም ወዳዱ ሕዝባችን የተቀናጀ ተሳትፎ በቁጥጥር ስር ለመዋል ችሏል።
አራተኛ፥ ሰሞኑን በሰሜን ሸዋ እና በደቡብ ወሎ የኦሮሞ ልዩ ዞን ወረዳዎች በተለይም በዚህ ሁለት ሶስት ቀን በአጣዬ ከተማ እና በአከባቢው በታጠቁ ኃይሎች በሰው ህይወት እና ንብረት ላይ በደረሰው ውድመት፣ የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን እየገለጸ፥ በዚህ አደጋ ለተጎዱ ወገኖች መጽናናትን ይመኛል።
በዚህ የጸጥታ ችግር ተሳታፊ የሆኑ ወንጀለኞችን በቁጥጥር ስር የማዋል እና መሣርያ ይዘው በጸጥታ አካላት ላይ ተኩስ የከፈቱ፣ የሠራዊቱን እንቅስቃሴ የገደቡ ጸረ-ሰላም ኃይሎች ላይ ሠራዊታችን እርምጃ መውሰድ መጀመሩን እየገለጽን፤ መንገድ መዝጋትን ጨምሮ የኅብረሰተሰቡን ሰላም በማወክ ላይ የተሰማሩ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር በጥብቅ ለማሳሰብ ይወዳል።
በዚህም መሠረት፥ በሰሜን ሸዋ እና በደቡብ ወሎ የኦሮሞ ልዩ ዞን ወረዳዎች ከተከሰተው የጸጥታ ችግር ጋር ተያይዞ ከክልል እና ከፌዴራል የጸጥታ ተቋማት ጨምሮ ሶስቱንም ዞኖች ያካተተ ኮማንድ ፖስት ተቋቁሟል። ኮማንድ ፖስቱ የአካባቢውን ጸጥታ በማደፍረስ ሥራ ላይ በተሰማሩ የጥፋት ቡድኖች ላይ እርምጃ በመውሰድ የሕግ የበላይነት የማረጋገጥ ሥራን ይሠራል።
በዚህም መሠረት የአከባቢውን ሰላም ወደ ነበረበት ለመመለስ ሲባል የሚከተሉት ክልከላዎች የተደረጉ መሆኑን ኮማንድ ፖስቱ ይገልጻል።
1ኛ ከደብረ ሲና እስከ ኮምቦልቻ አዋሳኝ ወረዳዎች መንገድ ላይ፣ ከመንገዱ ግራ እና ቀኝ እስከ 20 ኪሎ ሜትር ውስጥ የጦር መሣሪያ ይዞ መንቀሳቀስ በጥብቅ የተከለከለ ነው።
2ኛ መንገድ መዝጋትን ጨምሮ አብያተ ክርስቲያናትን እና የመንግሥት ተቋማትን፣ የግለሰብ መኖሪያ ቤትን እና ንብረት ማውደም ወይም ለዚህ ተግባር በተናጠልም ይሁን በቡድን መንቀሳቀስ በጥብቅ የተከለከለ ነው።
ከላይ የተዘረዘሩትን እና ቀጣይ በኮማንድ ፖስቱ ለኅብረተሰቡ የሚገለጹ ክልከላዎችን ተላልፎ የተገኘ የፖለቲካ ድርጅት፣ የመንግሥት መዋቅር እና በድኖች ላይ ሕጋዊ እርምጃ የሚወሰድበት መሆኑ መታወቅ አለበት።
በመጨረሻም መላው ኅብረተሰባችን እንደ ወትሮው ሁሉ ከጸጥታ ተቋማት ጎን በመሰለፍ ለገሀራችን ሰላም እና ደህንነት የበኩሉን ገንቢ ሚና እንዲጫወት ጥሪያችንን እናቀርባለን።
የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር
ሚያዝያ 10፥ ቀን 2013 ዓ.ም.March 19, 2021 at 12:44 am #18664In reply to: የፖለቲካ ፓርቲዎች ድምጽ (ኢትዮጵያ ውስጥ የሚነቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች)
AnonymousInactiveየባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ እና የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ በጋራ ለመሥራት የሚያስችል የትብብር ስምምነት ተፈራረሙ
ባልደራስ እና አብን ትብብርን አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫየሀገራችን ሕዝብ ለዘመናት በተጫኑበት ኢዲሞክራሲያዊና አምባገነን አገዛዞች የተነሳ፥ በነፃነት እጦት፣በስቃይ እና በመከራ ኑሮውን እንዲገፋ ተደርጓል። ጭቆናን አስወግዶ የሚፈልገውን ፍትህ እና እኩልነት እውን ለማድረግ ከፍትኛ ዋጋ መክፈሉም እሙን ነው።
ይሁንና የሀገራችን የለውጥ ፍላጎት እና እንቅስቃሴ ጅማሮው ሳይሳካ፥ ለቀጣዩ ዴሞክራሲያዊ ትግል ተስፋ ሊሆን የሚችል መሠረታዊ የትርክትና የመዋቅር ክለሳ እንኳ ሳይደረግ አምባገነንነትና ዘረኝነት የእጅ ለውጥ ብቻ እያደረጉ የሚፈራረቁባት ሆናለች። በዚህ ሁሉ ፈተና ውስጥ ያለፈው ሕዝባችን አሁንም ዲሞክራሲን፣ እኩልነትንና ዘላቂ ሰላምን በመሻት ለነፃነት የሚያደርገውን ትግል አጠንክሮ እንደቀጠለ ይገኛል።
የዚህ ዓይነት መልክና ይዘት ተላብሶ የተደራጀው የተፎካካሪ ኃይል ለሰርጎ ገቦች የተጋለጠ፣ በተፈጥሮው ደካማና ተሰባሪ ከመሆኑም በላይ የአምባገነኑን ሥርዓት ራዕይ አቀንቃኝ እስከመሆን ደርሶ እንደነበር ይታወሳል። በተጨማሪ የተቃውሞው ጎራ እርስ በርሱ በፍረጃና በሴራ መጠላለፍ ምክንያት በቁርሾ እንዲሞላ በማድረግ የጋራ ሀገራዊ ስምሪት መውሰድ እንዳይችል አድርጎት ቆይቷል።
በዚህ ሂደት ውስጥ አምባገነኖችን በጋራ መታገል ጥረት ከማድረግ ወርደው በመናኛ ፍላጎቶችና በጥቃቅን ልዩነቶች ዙሪያ ታጥረው ሲሻኮቱ በመካከል የባከነው ጊዜ እና የሰው ህይወት የሚያስቆጭ ነው።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሀገራችንን ለእድሜ ልክ ዝቅታ የዳረጋት የጥላቻ ትርክት፣ ትርክቱን መሠረት አድርገው የተደነገጉ ሕግጋትና የተዘረጉ መዋቅሮች ተከልሰው መላ ኢትዮጵያውያን በእኩልነት፣ በወንድማማችነት፣ በፍትህና በሰላም የሚተዳደሩነት ዘላቂ ሥርዓት በማስፈን በተለምዶ “መንታ ቅኝት” ያለው የትግል እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል። የአብን ስትራቴጂክ ግብ መላውን ኢትዮጵያዊ የፍትሀዊ አማካኝ ተጠቃሚ በማድረግ ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግ የፖለቲካ ማዕቀፍ እንዲፈጠር ሲሆን የድርሻውን ለማበርከት አበክሮ እየሠራ ያለ ንቅናቄ ነው።
ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) ደግሞ የኢትዮጵያዊ ኅብር ዓይነተኛ መገለጫ የሆነችውን የአዲስ አበባ ከተማ ሕዝብ ከከፋፋይና ከጥላቻ ፖለቲካ ነፃ ለማድረግና ሕዝቡ ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብቱ እንዲረጋገጥ ለማስቻል በሚል የተደራጀ ስለመሆኑ በሰፊው የሚታወቅ ነው።
አዲስ አበባ ከተማ የኗሪዎቿ መሆኗን ለማረጋገጥ የሚያደርጉት የጋራ ትግል መነሻ ዴሞክራሲን፣ ነፃነትን፣ ፍትህንና እኩልነትን በማስፈን ላይ የተመሠረተ ሲሆን፥ አንዳች ቅቡልነት ያለው መርህ ወይም ምክንያት ማጣቀስ የማይችሉ ኃይሎች ከተማዋ የአንድ ንጥል ብሔር ንብረት መሆኗን በይፋ በመግለፅ የማታገያ አጀንዳ በማድረግ ሕዝቡ በነሱ ፍቃድና ይሁንታ መኖር እንዳለበት አድርገው ያወጁት ያልተገራ ፍላጎት የጋረጠበትን የህልውና ስጋት መቀረፍ እንዳለበት አብን እና ባልደራስ የጋራ ፖለቲካዊ አቋም ወሰደዋል።
የሀገራችን ኢትዮጵያ መድናና የመላ ሕዝቧ ሰላማዊ መኖሪያ ሆና ዘመናትን የተሻገረችው አዲስ አበባ መደበኛና ነባር ምልከታ ሊቸራት ሲገባ ከልቦለድ የመነጨ የዘረኞች “የልዩ ጥቅም”ቀንበር ጊዜ በረዘመ ቁጥር የሕግና የፖለቲካ ቋጠሮው እየጠበቀ መምጣቱና ይዘቱ “በኦሮሚያ ክልል አስተዳደርና በአዲስ አበባ መስተዳደር ስምምነት” እንደሚወሰን በተሻሻለው ቻርተር መደንገጉ ከተማዋንና ሕዝቧን ከአንድ ወገን በተሰባሰበ የፖለቲካ ኃይል ይሁንታ፣ ፍፁም ቁጥጥርና ጥበቃ ስር ለማዋል የተወሰነ መሆኑን ያሳያል። አብን እና ባልደራስ ይሄን አምባገነናዊ፣ ፍትህ አልቦ፣ ዘረኛ፣ አግላይና በመጨረሻም የግጭትና የብሔራዊ ደህንነት አደጋ የሆነ አፍራሽ እንቅስቃሴ በጋራ ተሰልፈው ለመታገል ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።
ትብብሩ በቀጣይ እንዲፈጠርና እንዲጎለብት ለምንፈልገው የሀገራዊ በጎ ኃይሎች ጥምረት እርሾ ሆኖ እንዲያገለግል የታለመ ነው። አስቻይነት የሌለውና በሕግ የተደነገገው የጊዜ ገደብ ጉዳይ በነባራዊ ተግዳሮቶች ምክንያት የተፈጠረ መሆኑን በማረጋገጥ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተመሳሳይ አንድምታ ያላቸውን ጉዳዬች ባስተናገደበት ሁኔታ ትብብሩ ለህጋዊ እውቅና ሲቀርብ በመፍቀድና በመመዝገብ እንዲያፀድቀው የሚቀርብ ይሆናል።
በዚህ መነሻነት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እውን ለማድረግ ለሚደረገው ትግል በመጪው ሀገራዊ ምርጫ የመራጮችን የጋራ ፍላጎትና ራዕይ ለማሳካት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ /አብን/ እና ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ /ባልደራስ/ በጋራ የምንሠራበት የፖለቲካ ትብብር ፈጥረን ለመሥራት መወሰናችንን ለመላው ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን፣ ለመላው አማራ ሕዝብና ለአዲስ አበባ ሕዝብ ስናበስር በታላቅ ደስታ ነው። ሌሎች ፓርቲዎችን ጨምሮ በሁለቱ ፓርቲ አመራሮች መሃከል ለወራት ሲካሄድ የነበረው ረዥምና አድካሚ ድርድር ፍሬ አፍርቶ መጪውን ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ የአብን እና የባልደራስ ትብብር አሸናፊ ሆኖ መውጣት የሚያስችላቸውን የጋራ ስልቶች ቀይሰው በይፋ መንቀሳቀስ ጀምረዋል።
አብን እና ባልደራስ፣ አጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ የአማራ ሕዝብ እና የአዲስ አበባ ከተማ ኗሪ ሕዝብ በበደል ውስጥ አምጠው የወለዷቸው የቁርጥ ቀን ልጆቹ እንደመሆናቸው መጠን በተባባረ ክንድ በሕዝባችን ላይ የተጫነውን የመከራ ቀንበር እንዲወርድ ከመቼውም ግዜ በላይ በጋራ ትብብር ለመታገል በቁርጠኝነት ተሰልፈዋል።
አብን በጽንፈኞች የተሳሳተ ትርክት መነሻነት በአማራ ሕዝብ ላይ በተከታታይ የሚደርሰው ግፍ ድምጽ በመሆን በመጀመሪያው ረድፍ ሆኖ ትግሉን እየመራ ይገኛል። አብን የሀገራችን ኢትዮጵያን ደህንነት ለማረጋገጥና ህልውናዋን ለማስቀጠል አንድ ወሳኝ አምድ የሆነው የአማራ ሕዝብ በልዩ ሁኔታ ተፈርጆ የሚጠቃበትን የፅንፈኞች ስሁት ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ለመግታት የሚያስችል ልዩ ማዕቀፍ ሆኖ የተደራጀ ሲሆን ታሪካዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ስሪቱ በኢትዮጵያዊነት፣ ምልከታውም በወንድማማችነት፣ በፍትህና በዴሞክራሲ የተቃኘ ስለመሆኑ ውሎ ያደረ ጉዳይ ነው።
ከላይ በሰፊው እንደተመላከተው ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ በአዲስ አበባ ከተማ ሕዝብ ላይ የተጋረጡ የህልውና አደጋዎችን ለመከላከል፣ የከተማዋ ሕዝብም ራሱ በዴሞክራሲያዊ መንገድ በመረጣቸው እንደራሴዎቹ የመተዳደር መብቱን ለማስከበር ባሚያደርገው እልህ አስጨራሽ ትግል ውስጥ በብቃትና በንቃት በነሳተፍ አያሌ መስዋዕቶችን በመክፈል የቀጠለ መሆኑን ራሱ ሕዝቡ በተግባር ኖሮ ያረጋገጠው ሀቅ ነው። ከላይ በተጠቀሱት መሠረታዊ ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ ግቦች ዙሪያ ሁለቱ ድርጅቶች በፅኑ የሚጋሯቸውን አቋሞች መሠረት በማድረግ ቀጣይ ለሚደረገው ጠንካራና የተቀናጀ የሕዝብ ትግል ወሳኝ የማታገያ አጀንዳ እንዲሆኑ ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው ምርጫ መላው የሀገራችን ሕዝብ፣ በተለይም የአማራ ሕዝብና የአዲስ አበባ ሕዝብ የተደቀነባቸውን የህልውና አደጋ በትብብር ከመታገል ውጭ ሌላ ተጨባጭ የመፍትሄ አማራጭ እንደሌለ መተማመን ላይ ደርሰዋል።
ከዚህ ቀደም በጋራ አብረውን ለመሥራት ንግግር ጀምረው ሳለ በተለያዩ ምክንያቶች በትብብሩ ለመዝለቅ ያልቻሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሁንም ጊዜው አለመርፈዱን ተገንዝበው በጎ ፍላጎት ካሳዩን ከግማሽ መንገድ ባላይ ተጉዘን ለመቀበል ዝግጁ መሆናችንን በዚህ አጋጣሚ ለማረጋገጥ እንወዳለን።
የፈጠርነው ትብብር አርአያ መሆን የሚችልና ከትላንት ለተሻለ አዲስ የፖለቲካ ባህል ማሳያ ፈር ቀዳጅ እንደመሆኑ ከምርጫ በኃላም ትብብሩ ጎልብቶ፤ የሀገራችንን ሕዝብ ለዘመናት የቆየ የፍትህ ትግል ዳር ለማድረስ እንዲሁም የመላው ኢትዮጵያዊ የሆነችውን የአዲስ አበባ ከተማን ዓለም አቀፍነት የሚመጥን አመራር ለመስጠት ለመፍጠር ከወዲሁ አብረን መቆም ጀምረናል።
አብን እና ባልደራስ የአዲስ አበባ ሕዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር ዴሞክራሲያዊ መብት አክብረው ከሚቀበሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ትብብር በመፍጠር የከተማዋ ሕዝብ በፌደራል መንግሥቱ ውስጥ ተወክሎ እንደሁሉም ሕዝብ ጥቅሙን ለማስጠበቅ የሚያደርገውን ትግል የማሳለጥ ሚና እንደሚኖረው ለማሳወቅ እንወዳለን።
አዲስ አበባ በሁሉም ኢትዮጵያውያን ጥረት የተገነባች፣ የአፍሪካ የዲፕሎማሲ ዋና ከተማ ብትሆንም፥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተነሱ ተረኞች ከተማይቷን በልዩ ጥቅም ስም የአንድ ቋንቋ ተናጋሪ ብቸኛ ንብረት ለማድረግ የሚደረገው እንቅስቃሴ በጋራ አጥብቀን እናወግዛለን። በከተማይቱ እና ነዋሪዎቿ ላይ የተደቀነውን ይህ አደጋ ለመከላከል ባልደራስ በዋነኛነት እያካሄደ ያለውን ትግል አብን የሚያድንቅ እና በሙሉ ልብ ከጎኑ እንደሚሰለፍ ቃል ይገባል። በአንጻሩም ባልደራስ ፓርቲ በጽንፈኞች ሴራ ዒላማ እንዲሆን በተደረገው የአማራ ሕዝብ ላይ የሚደርሰውን ግፍ እና በደል ለማስቀረት በቁርጠኝነት አብን ለሚያደርገው ትግል ክብርና እውቅና እንደሚሰጥ ለመግለፅ እንወዳለን፡፡
ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው ስምምነታችን የተበላሸውን የሀገራችንን ፖለቲካ ባሕል በማስተካከል፣ በውይይትና በሰጥቶ መቀበል መርህ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል አብሮ መቆም እንደሚገባ ከማሳየት ባሻገር፥ ሌሎች ለተመሳሳይ አላማ ያነገቡ ፓርቲዎችም ይህን ፈለግ ተከትለው የትብብሩ አካል እንዲሆኑ ፅኑ ፍላጎት አለን።
በመጨረሻም በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች ጽንፈኛ ኃይሎች በሚፈጽሟቸው የሽብር ድርጊቶች ምክንያት እየደረሰ ያለውን ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ መፈናቀል እና የንብረት ውድመት ለማስቆም በየእርከኑ ያሉ የፌደራል እና የክልል መንግሥታት ኃላፊዎች ተግተው እንዲሠሩ ጥሪ እናቀርባለን።
በተለይ ችግሩ ተባብሶ በሚገኝባቸው የኦሮሚያ፣ የቤንሻንጉል እና አንዳንድ የደቡብ ክልል አካባቢዎች የሚገኙ የመንግሥት አስተዳደርና የፀጥታ አካላት ችግሩን የሚመጥን ኃላፊነት በመውሰድ ንፁኃንን ከጥቃት እንዲከላከሉና ወንጀለኞችን ለሕግ እንዲያቅርቡ በአፅንኦት እንጠይቃለን።
መሠረተ-ቢስ በሆነ ክስ ተወንጅለው ለእስር የተዳረጉትንና የመምረጥና መመረጥ መብታቸውን የተነፈጉ የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ አመራሮች በአስቸኳይ እንዲፈቱ እናሳስባለን። ትህነግ በለኮሰው ጦርነት በትግራይ ክልል ሕግ ለማስከበር እየተካሄደ ባለው ዘመቻ የንጹኃን ዜጎቻችንን ደህንነት እና የሰብዓዊ መብት እንዳይጣስ ልዩ ትኩረት እንዲደረግና የሰብዓዊ ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለማሳሰብ እንወዳለን።
መጋቢት 9 ቀን 2013 ዓ.ም.
የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ /ባልደራስ/
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ /አብን/February 28, 2021 at 2:57 am #18367SemonegnaKeymasterየምርጫ ክርክር ለማዘጋጀት ፍላጎት ላላቸው የሲቪል ማኅበራት እና ሚዲያዎች የተደረገ ጥሪ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 6ተኛው ጠቅላላ ምርጫ ተግባራትን እያከናወነ እንደሆነ ይታወቃል፤ በዚህም መሠረት የተወሰኑ ተቋማት በተወዳዳሪዎች መካከል የምርጫ ክርክር ለማከናወን ከቦርዱ ፍቃድና አቅጣጫ ለማግኘት ጥያቄዎችን አቅርበዋል።
ይህንን፥ እንዲሁም ሌሎች ልምዶችን መሠረት በማድረግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የእጩዎች ምዝገባ ተጠናቆ ተወዳዳሪ ፓርቲዎች ከታወቁ በኋላ ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ክርክር ሂደትን ለማስተባበር ይፈልጋል። በመሆኑም ከዚህ በፊት ጥያቄ/ ማብራሪያ ያስገባችሁም ሆነ በዚሁ ጉዳይ ላይ ፍላጎት ያላችሁ መንግሥታዊ ያልሆናችሁ ተቋማት እና ሚዲያዎች በተናጠል ወይም በጋራ የምርጫ ክርክር ዝርዝር የፍላጎት መግለጫ ወረቀት (expression of interest) ለቦርዱ እንድታቀርቡ ጥሪ ያቀርባል።
የፍላጎት መግለጫ ማካተት የሚገባቸው ዋና ዋና ሃሳቦች
ማንኛውም የምርጫ ክርክር ለማከናወን የሚያስብ ተቋም የሚመለከቱትን ዋና ዋና ነገሮችን ያሟላ የፍላጎት መግለጫ ሊያቀርብ ይገባል።
- ሊያከናውኑት ያቀዱት የምርጫ ክርክር ግልጽ ዓላማ፣
- ሊያከናውኑት ያቀዱት ክርክሩ የሚከናወንበት መንገድ (mode of engagement)፣
- ሊያከናውኑት ያቀዱት የክርክሩ ሥነ-ምግባር ደንብ (code of conduct)፣
- የክርክሩ ቁጥር ብዛት፣ የተሳታፊዎች ሁኔታ፣ ለሕዝብ የሚቀርብበት ሁኔታ፣
- የአከራካሪ አመራረጥ ሂደት፣ መስፈርት እና መመዘኛ፣
- ክርክሩ ለሕዝብ የሚቀርብበት መንገድ፣
- በጀት እና የገንዘብ ምንጭ፣
- ክርክሩን የሚከናወንባቸው ቋንቋዎች እና የመሳሰሉት፣
ከላይ ከተጠቀሱት ዋና ዋና ጉዳዮች በተጨማሪ ምክረ-ሃሳብ የሚያስገቡ ተቋማት አስፈላጊ ነው የሚሉትን ዝርዝር ዕቅድ በምክረ-ሃሳባቸው ውስጥ አካተው ማቅረብ ይችላሉ። ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ክርክሩን በማመቻቸት ብሔራዊ ክርክር መከናወንን ከማመቻቸት በተጨማሪ ለክርክር ዝግጅት የሚሆን የፋይናንስ ድጋፍ አያደርግም።
የፍላጎት መግለጫ ወረቀት እስከ የካቲት 26 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ (በአምስት የሥራ ቀናት ውስጥ) በቦርዱ ዋና መሥሪያ ቤት በግንባር ወይም በ media@nebe.org.et ኢ-ሜይል አድራሻ ሊቀርብ እንደሚችል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።
ከምርጫ ቦርድ መግለጫ ሳንወጣ፥ ቦርዱ ለ6ተኛው አጠቃላይ ምርጫ የእጩዎች ምዝገባን እያከናወነ ባለበት በአሁኑ ወቅት የመጀመሪያ ዙር የእጩ ምዝገባ የሚከናውንባቸው ክልሎች እና የከተማ መስተዳድሮች ማለትም፦
- የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር
- የድሬደዋ ከተማ መስተዳድር
- የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል
- የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ብሔራዊ ክልል
- የጋምቤላ ብሔራዊ ክልል
- ሃሪሪ ብሔራዊ ክልል ለእጩዎች ምዝገባ የተቀመጠው የጊዜ ገደብ መሠረት የካቲት 08- 21 ድረስ እንደሚከናወን ማሳወቁ ይታወቃል።
ቦርዱ የእጩዎች ምዝገባ ሂደትን በመገምገም የምርጫ ክልል ቢሮዎች ለመከፈት በመዘግየታቸው፥ የትራንስፓርት መጓተት የተወሰኑ የምርጫ ክልሎች ላይ የምዝገባ ቀንን በማራዘሙ እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለያዩ ምክንያቶች እጩዎችን ለመመዝገብ ችግር ስላጋጠመን ይራዘምልን ብለው ጠይቀዋል። በመሆኑም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከላይ የተጠቀሱትን አሳማኝ ምክንያቶች በማየት የመጀመሪያ ዙር ምዝገባ በጀመሩት ከላይ በተጠቀሱት ክልሎች/የከተማ መስተዳድሮች ላይ የሚካሄደው የእጩዎች ምዝገባ ለ4 ቀናት ያህል እስከ የካቲት 25 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ መራዘሙን አስታወቋል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
February 14, 2021 at 4:44 am #18207In reply to: የፖለቲካ ፓርቲዎች ድምጽ (ኢትዮጵያ ውስጥ የሚነቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች)
AnonymousInactiveሱዳን በኢትዮጵያ ላይ ያደረገችውን ወረራ አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) የተሰጠ መግለጫ
“ከድንበሩ ቆሞ ጌታ ካልመለሰው፥
መሬትም ይሄዳል እግር አለው እንደ ሰው።”የሀገራችን ዳር ድንበር በአባቶቻችንና በእናቶቻችን ደምና አጥንት ተለስኖ የተሠራ የማይነቃነቅ አምድ እንጂ፥ እንደ ሰንበሌጥ አጥር ማንም በፈለገው ጊዜ እየጣሰው የሚገባ ድንበር አይደለም። ሀገሩንና ድንበሩን የማያስከብር ሕዝብ ለባርነት እንደተዘጋጀ ይቆጠራል። ለአንድ ዜጋ ሀገርና ድንበር የክብሩ ከፍተኛ መገለጫው ነውና።
ኢትዮጵያ ሀገራችን በትግራይ ከአሸባሪው የህወሓት ቡድን እንዲሁም በመተከል በኦሮሚያ ክልል ጽንፈኞችን ለማጽዳት ከፍተኛ ግብግብ በምታደርግበት ወቅት፣ ሱዳን ድንበራችንን ተሻግራ ጦሯን ማስፈሯንና በአካባቢው በነበሩ ኢትዮጵያውን ገበሬዎች ላይ ጥቃት መፈጸሟን የተለያዩ የዜና አውታሮች የዘገቡት ሃቅ ነው። አሁን በቅርቡ ደግሞ በምዕራብ አርማጭሆ በደለሎ የገበሬዎችን የእርሻ ምርት ማቃጠሏን በከፍተኛ ቁጭት ሰምተናል። ይህ የሱዳን ድፍረት ማንኛውንም ኢትዮጵያጵያዊ ዜጋ እጅግ የሚያስቆጣ እርምጃ በመሆኑ ሁላችንንም እንቅልፍ የሚነሳ ድፍረት ነው ይላል ኢሕአፓ።
የድንበር ውዝግቡ ለረዥም ጊዜ እልባት ሳያገኝ የቆየ መሆኑ ቢታወቅም፥ ኢትዮጵያ አንድም ጊዜ ድንበሯን አልፋ አንድ ጋት መሬት ከሱዳን ፈልጋ አታውቅም። ሱዳን ግን አጋጣሚ እየጠበቀች በተደጋጋሚ ከመተንኮስ ቦዝና አታውቅም። በሰላማዊ ጊዜም ከብቶቿን ወደ ኢትዮጵያ መሬት አሻግራ እንዲግጡ በመድረግ፣ ለእጣን የሚሆን ሙጫ በመሰብሰብ፣ ለቤትና ለማገዶ የሚሆን እንጨት እየቆረጠች በመውሰድ የምትፈጽማቸውን ድርጊቶች ኢትዮጵያውያን ገበሬዎች በመቃወማቸው በተደጋጋሚ ስትጋጭ ኖራልች። ኢሕአፓ በአካባቢው በሚንቀሳቀስበት ጊዜም ይህን ለማስቆም ለሱዳን መንግሥት ገበሬዎቻቸው ድንበራችንን እየተሻገሩ የሚያደርጉትን የጥሬ ሀብት ስብሰባና የከብት ግጦሽ እንዲያስቆሙ በተደጋጋሚ ጠይቆ አሻፈረኝ ስላሉ፤ የአካባቢውን የምዕራብ በጌምድርን (መተማ፣ ቋራ፣ ጫቆ) ሕዝብ አስተባብሮ የሱዳንን ጦር በመውጋት ድል አድርጎ የኢትዮጵያን ድንበር አስከብሮ አንደነበረ የሚታወቅ ነው። በዚህም ምክንያት ሱዳን የነበሩ የድርጅቱ አባሎች ለእስርና እንግልት ተዳርገዋል፤ የተወሰኑትንም ለህወሓት በማስረከብ ለሰቆቃ/ግርፋትና እስር እንዲዳረጉ አድርገዋል። ገዳሪፍ የነበረውን የድርጅቱን ጽሕፈት ቤት በርብረው የድርጅቱን ንብረቶች ወስደዋል። ከህወሓት ጋር በመተባበር ኢሕአፓን ከበው ወግተዋል። ህወሓትንም አጅበው አዲስ አበባ አስገብተው ተመልሰዋል።
ህወሓት እና የሱዳን መንግሥት ከመጀመሪያ ጀምረው የጠበቀ ወዳኝነት እንደነበራቸው ይታወቃል። በደርግ ዘመን ህወሓት ጉልበት ያገኘውና የኢትዮጵያን ጦር አሸነፍኩ ያለው ሱዳን ከፍተኛ መከታና ደጀን ሆና ስለረዳቻቸው ጭምር ነው። ለዚህ ውለታ ሱዳኖች ድንበራችን ጥሰው በደለሎ በኩል ገብተው ኢትዮጵያውያን ገበሬዎችን አፈናቆለው ለረዥም ዓመታት ሲያርሱ ኖረዋል። የአካባቢው ገበሬዎች ድርጊቱን በመቃወም ሲከላከሉ፣ የህወሓት ካድሬዎች “መንግሥትና መንግሥት ይነጋገራል እንጂ ገበሬውን አያገባውም” በማለት ኢትዮጵያውያንን ገበሬዎችን ያስሩና ያንገላቱ ነበር። እውነታው ግን ሱዳን እንደፈለገች የኢትዮጵያን መሬት እንድትጠቀም በነአባይ ፀሐዬ የተሸረበ ሤራ መሆኑ ነው። የገበያ ግርግር ለሌባ ያመቻል እንዲሉ፥ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የህወሓትን አሸባሪ ቡድን ለማፅዳት ጦርነት እያደረገ በነበረበት ወቅት ሱዳን ድንበራችንን ተሻግራ ኢትዮጵያውያን ገበሬዎችን ከማሳቸው ያፈናቀለችው የወዳጇ የህወሓት መመታት ስለከነከናትና በአጋጣሚውም የረጅም ጊዜ ምኞቷን ለማሳካት የወሰደችው እርምጃ ነው።
ሱዳን ድንበራችንን የጣሰችበት ሌላው ምክንያት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሥራ ለማደናቀፍ እንዲቻል ከሱዳን ጀርባ ተጫማሪ ገፊ ኃይል ሊኖር እንደሚችል መገመት አይቸግርም። ከዚህ በተጨማሪ ህወሓትና የውጭ ደጋፊዎቻቸው ትግራይ ውስጥ የሚደረገውን የሀገር አፍራሹን ቡድን የማጽዳት ዘመቻ ቀጣናዊ መልክ ለማስያዝ የሚጥሩትን እውን ለሜድረግ ሱዳን የጦስ ዶሮ ሆና መቅረቧ አጠራጣሪ አይደለም እንላለን።
በጦርነቱ ሳቢያ በትግራይ ውስጥ የተጎዳው ሕዝባችን አስፈላጊው እርዳታ እንዲደርሰው መንግሥት እስካሁን እያደረገ ያለው ድጋፍ በተጠናከረ መልክ እንዲቀጥልና የዓለምአቀፍ የሰብዓዊ ድርጅቶችም እርዳታና ድጋፋቸውን በመንግሥት በኩል ለሕዝቡ የሚደርስበትን መንገድ እንዲያመቻች እናሳስባለን።
የኢትዮጵያ መንግሥት ሱዳን መሬታችንን ለቃ እስክትወጣ ድረስ የሱዳንን ትንኮሳ ጥንቃቄ በተሞላበት በሰላማዊና ዲፕሎማሲያዊ መንገድ በመያዝ ከፍጻሜ ለማድረስ ከፍተኛ ትግል ማድረግ ይኖርበታል። ድንበራችን በቋሚነት የሚከለልበትንም መንገድ እንዲያመቻች እናሳስባለን።
የኢትዮጵያ ሕዝብ የሀገሩን ዳር ድንበር ለማስከበርና የሀገሩን አንድነት ለማስጠበቅ ሊፋለም እንደሚችል ግልጽ መሆን አለበት። ሕዝባችን በተደጋጋሚ እንዳስመሰከረው ሱዳን ከሀገራችን ክልል እስክትወጣ ድረስ አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ በመሆን፥ ከመከላከያ ሠራዊታችን ጎን እንደሚቆም አንጠራጠርም። ኢሕአፓም በማንኛውም መንገድ ከሕዝባችን ጎን ዘብ ለመቆም ዝግጁ መሆኑን ያረጋግጣል። አባቶቻችን ስለሀገርና ድንበር ሲነሳ እንደ እግር እሳት ሲያንግበግባቸው፦
“ከደንበሩ ቆሞ ጌታ ካልመለሰው፥
መሬትም ይሄዳል እግር አለው እንደ ሰው”ይሉ ነበር።
ኢትዮጵያ በልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘለዓለም ትኖራለች!
የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)
ጥር 29 ቀን፥ 2013 ዓ. ም.February 5, 2021 at 1:34 am #18107AnonymousInactiveበብልፅግና ሰልፎች ላይ ፓርቲዎች የሚመሩባቸው ሥነ ምግባሮች ተጥሰዋል
ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰጠ መግለጫጥር 25 ቀን 2013 ዓ.ም. በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች ለብልፅግና ፓርቲ ድጋፍ ለማሳየት የተለያዩ ሰልፎች መካሄዳቸው ይታወቃል። እነዚህን ሰልፎች ተከትሎ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) “ፓርቲያችን ያለአግባብ ተወንጅሏል፤ ይህም ፓርቲዎች የፈረሙትን የጋራ የሥነ ምግባር ደንብ የጣሰ ነው” ሲል አቤቱታውን ለቦርዱ አቅርቧል። ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም ከአቤቱታው በተጨማሪ በዕለቱ የተደረጉ የተለያዩ ሰልፎችን በሚዲያ ክትትል ክፍሉ አማካኝነት ክትትል በማድረግ በአሜሪካ ድምጽ፣ በዋልታ፣ በፋና፣ በኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ እንዲሁም በእነዚሁ ሚዲያዎች የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች በቀጥታ የተላለፉ መልእክቶችን በማየት፦
- ሠልፎቹ በዋልታ ቴሌቪዥን እና በኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ በቀጥታ መተላለፋቸውን እንዲሁም የመንግሥት አመራር አካላት፣ የብልፅግና ፓርቲ አመራሮች እና ደጋፊዎች መሳተፋቸውን ተረድቷል፤
- ከሚዲያዎቹ በቀጥታ ከመተላለፉም በተጨማሪ የተለያዩ የመንግሥት አመራር አባላት በሰልፎቹ ላይ ያደረጓቸውን ንግግሮች ተመልክቷል፤
- በሰልፎቹ የተለያዩ መፈክሮች፣ በተወሰኑ የመንግሥት የዞን፣ የከተማ አስተዳድር አመራር አካላት እና ብልፅግናና ፓርቲ ኃላፊዎች ንግግሮች በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተመዘገቡ እና የምርጫ ምልክቶቻቸውን የመረጡ ፓርቲዎች በአሉታዊ መልኩ መነሳታቸውን ተገንዝቧል።
እነዚህ ሰልፎች ላይ የተነሱ ንግግሮች እና መፈክሮች በሕጋዊነት ተመዝግበው፣ በፖለቲካ ፓርቲነት የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎችን ማለትም አማራ ብሔራዊ ንቅናቄ፣ ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ እና የኦሮሞ ነጻነት ግንባር በአመፃ ተግባር በመሳተፍ ከምርጫ ቦርድ ከተሰረዘው ጁንታ በማለት ከሚጠሩ ህወሓት ፓርቲ ጋር አንድ በማድረግ፣ የኢትዮጵያ ጠላት ናቸው ብሎ በመፈረጅ እና ሕገ ወጥ ናቸው በማለት የምርጫ፣ ፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና ሥነ ምግባር ሕግ 1162/2011 ላይ ያሉ ድንጋጌዎችን ጥሰዋል።
ቦርዱ ሰልፎቹ ላይ የተንጸባረቁት ንግግሮች እና መፈክሮች በአዋጁ አንቀጽ 132 ንዑስ 2(ሀ) ላይ የተጠቀሰውን ስም የሚያጠፋ ንግግርን ክልከላ ድንጋጌ አንዲሁም በዚሁ ሕግ አንቀጽ 143 (2) ላይ የተጠቀሰውን ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ሀሳባቸውን በነጻነት እንዳያሰራጩ ስጋት እና ፍርሀት የመፍጠር የሥነ ምግባር ጥሰት ፈጽሞ አግኝቶታል። ከዚህም በተጨማሪ ከላይ ስማቸው የተጠቀሱት የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ገዥው ፓርቲ በጋራ ተስማምተው በፈረሙት የቃልኪዳን ሰነድ አንቀጽ 8 ንዑስ አንቀጽ 1 ላይ የተጠቀሰውን “የሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በየትኛውም ጉዳይ ላይ ሊኖር የሚችል የዓላማ፣ የሃሳብ ወይም የዘር ልዩነትን፣ ወይም ሌላ ምክንያት መሠረት በማድረግ የሌሎች ፓርቲዎችን መብቶች የሚፃረሩ ወይም የሚያጣብቡ ድርጊቶችን ከመፈፀም የመቆጠብ ግዴታ አለባቸው” የሚለውን አንቀጽ የሚጥስ ተግባር ነው።
ይህ ተግባር በተለይ ቦርዱ የመጨረሻ የጊዜ ሰሌዳ አውጥቶ የምርጫ ተግባራት በይፋ መፈጸም ከጀመረ በኋላ በምንገኝበት የምርጫ ወቅት መከሰቱ በምርጫ ውድድር ላይ ፓርቲዎች በእኩልነት የመወዳደር መብታቸውን ችግር ላይ የሚጥል በመሆኑ ቦርዱን በእጅጉ አሳስቦታል። በመሆኑም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በየደረጃው ያሉ የገዥው ፓርቲ አመራሮች እና በየአስተዳደር እርከኑ ያሉ የመንግሥት ኃላፊዎች በተመሳሳይ ተግባራት ከመሳተፍ እንዲቆጠቡ ያሳውቃል።
ለወደፊትም በተመሳሳይ በምርጫ፣ ፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና ሥነ ምግባር ሕግ 1162/2011 እና ተያያዥ መመሪያዎች መሠረት የፓርቲዎች የቅስቀሳ የንግግር እና ሌሎች ለሕዝብ የሚያሰራጯቸውን መልዕክቶች ላይ ክትትል በማድረግ አስፈላጊውን እስከእጩ መሠረዝ የሚደርስ አስተዳደራዊ እርምጃ ሊወስድ እንደሚችል ያሳውቃል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
ጥር 26 ቀን 2013 ዓ.ም. -
AuthorSearch Results