-
AuthorSearch Results
-
October 15, 2020 at 12:02 am #16344
In reply to: ነፃ አስተያየት (ስለኢትዮጵያ በኢትዮጵያውያን)
AnonymousInactiveየሰላም ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል ሃሳብ ሊደገፍ የሚገባው ነው
የሺዋስ አሠፋወ/ሮ ሙፈሪሃት የፌደራል መንግሥቱን (ብልፅግና) እና የትግራይ ክልል አስተዳደርን (ህወሓት) መካረር በተመለከተ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የገለፁትን አይቼ በግሌ ጥሩ ጅምር ነው – ይበርቱ ብያለሁ። ስድብ፣ ፉከራ እና ይዋጣልን ሀገርን እና ሕዝብን ምስቅልቅል ውስጥ ከመክተት ውጭ ምንም ፋይዳ የለውም። “እልህ ምላጭ ያስውጣል” እንዲሉ ለራሳችሁም ቢሆን ውስጣችሁን የሚቆራርጥ ከሚሆን በስተቀር አይጠቅምም። የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አቋራጭ መንገድ የለውም፣ ውይይት/ድርድር ብቻ! በጉልበት/በጠመንጃ የሚሆን ቢሆን ኢትዮጵያን የሚቀድም ባልነበረም ነበር። ልብ በሉ ለውይይት አሻፈረኝ የሚሉ ወገኖች በስተመጨረሻ ቢፈልጉ አያገኙትም፤ ምክንያቱም አይበለው እንጂ ጦርነትም ቢሆን መቋጫው ውይይት/ድርድር ነው።
በ2009 ዓ.ም ራሳቸው ወ/ሮ ሙፈሪሃት የነበሩበትን የፓርቲዎች ውይይት/ድርድር (ስያሜው ራሱ አወዛጋቢ ነበር) ባስታውሳቸው ጠቃሚ የሚሆን ይመስለኛል። ሙከራው የተቀጨው ከጅምሩ ነበር። የቀድሞ ገዢ ፓርቲን ጨምሮ 22 ሀገር አቀፍ ፓርቲዎች ለሚያደርጉት ውይይት/ድርድር የመሀል ዳኛ (mediators) ያስፈልጋሉ/አያስፈልጉም በሚለው የጦፈ ክርክር ተደርጎ ኢህአዴግ እና ሌላ አሁን ስሙን የማላስታውሰው አንድ ፓርቲ አያስፈልግም ሲሉ 20 ፓርቲዎች ያስፈልጋል ብለን በከፍተኛ ቁጥር አሸነፍን፣ mediators ሊሆኑ የሚችሉትን ወገኖች የሥራ ልምድና የትምህርት ደረጃ መግለጫ (ማለትም፥ CV) እና ዝርዝር ማዘጋጀት ጀመርን።
በዚህ የተናደዱት የሂደቱ ፊትአውራሪ የነበሩት የተከበሩ አቶ አስመላሽ ወልደሥላሴ [የህወሓት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል] ለሳምንት እንደገና እንየው ብለው በተኑት። በሳምንቱ ራሳቸው አጀንዳውን አንስተው mediators ያስፈልጋሉ/አያስፈልጉም እጅ አውጡ ሲሉ ጠየቁ። ከመድረክና ሰማያዊ ፓርቲ ውጭ ሁሉም አያስፈልጉም አሉ። በሳምንት ልዩነት 20 ለ 2 ውጤቱ ሲገለበጥ ወ/ሮ ሙፈሪሃት እጃቸውን በአፋቸው ጭነው ይታዘቡ ነበር። እኔም በጣም ተበሳጭቼ “የተከበሩ አቶ አስመላሽ! ሳምንቱን ሙሉ ሲደልሉና ሲያስፈራሩ ሰንብተው ውጤቱን በጉልበት አስቀየሩት! ይሄ ጉልበት ግን አይቀጥልም፤ ነገ በሌላ ጉልበት ይሰበራል!” ብዬ ትቻቸው ወጣሁ። ሂደቱም ተጨናግፎ ቀረ (በወቅቱ ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 ሬድዮ ዘግቦታል)። ከ3 ዓመታት በኋላ እነአቶ አስመላሽን ወክለው አቶ አዲስዓለም ባሌማ ሁሉን አካታች ውይይት/ድርድር እናድርግ ብለው ሲጠይቁም፣ ያልተገባ ምላሽ ሲሰጣቸውም በተራዬ በትዝብት ተመለከትኩ።
ዛሬ የመንግሥት አካል ከሆነው የሰላም ሚኒስትር መፍትሄው ውይይት/ድርድር ነው የሚል ተነሳሽነት ሲመጣ አያስፈልግም ብሎ መታበይም ሆነ ተለመንኩ ብሎ ማጣጣል አይገባም። ሚኒስትሯ እንዳሉት፥ ከስሜት ወጥቶ፣ ሰከን ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል። በእኔ እምነት ይሄ ትልቅ እርምጃ ነው፤ ቀጣዩን ታሪክ ለመሥራት መሽቀዳደም ለኢትዮጵያ ውለታ ነውና ማን ይሆን ፈጥኖ ወደ መቀሌ ከተማ ወይም ወደ ወለጋ ጫካዎች ነጭ ባንዲራ ይዞ የሚዘምተው? (የኬንያው Building Bridges Initiative (BBI) ጥሩ መማሪያ ይሆነናል) ወይም ወደአዱ ገነት የሚመጣው? የወጣቶቻችንን ህይወት ከመቀጠፍ፣ የእናቶቻችንን እንባ ከመፍሰስ የሚታደገው? ከፌደሬሽን ምክር ቤት? ከሰላም ሚኒስትር? ከሀይማኖት አባቶች? ከእርቀ-ሰላም ኮሚሽን? ከሀገር ሽማግሌዎች? ከግብረ ሰናይ ድርጅቶች? ከአባ ገዳዎች? ከጋሞ አባቶች? እናቶች? ከወጣቶች? ከህፃናት?… ማን ይሆን በሞራል ልዕልና እና በመንፈስ ከፍታ ቆሞ ከኢትዮጵያ ሰማይ ሥር የሚጥመለመለውን የጥላቻ አውሎ ነፋስ ገስፆ የሚያስቆመው? እስኪ “እኔ አለሁ” በሉ! (እኔ እንዳልሞክር ፓርቲ ውስጥ መሆን ይሄን ነፃነት አይሰጥም) ግን ኢትዮጵያ የሰው ድሃ አይደለችምና ፍጠኑ። ሰላም!
የሺዋስ አሠፋ
አቶ የሺዋስ አሠፋ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ሊቀ መንበር ሲሆኑ፤ ከዚያ በፊት ደግሞ የቀድሞው ሰማያዊ ፓርቲ ሊቀ መንበር ነበሩ።
ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረ–ገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forums) ላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።
October 8, 2020 at 1:32 am #16251In reply to: የፖለቲካ ፓርቲዎች ድምጽ (ኢትዮጵያ ውስጥ የሚነቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች)
AnonymousInactiveሰላማችንን በማስጠበቅ እና ቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ ላይ በንቃት በመሳተፍ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠረት እንጣል!
ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የተሰጠ መግለጫስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ሊካሄድ የግዜ ሰሌዳ ወጥቶለት ሁሉም ባለድርሻ አካላት እንቅስቃሴ ከጀመሩ በኋላ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመታወጁ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያወጣውን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ እንዲሰርዝ መገደዱ ይታወሳል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በታወጀበት እና የምርጫ ሰሌዳው በተሰረዘበት ወቅት ወረርሽኙ በሌሎች የዓለማችን ሀገራት የጤና ሥርዓት ላይ ያስከተለውን ከፍተኛ ጫና እና በሰው ሕይወት ላይ ሲያደርስ የነበረውን ጉዳት በተጨባጭ በማየት የተለያዩ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ገደብ መደረጉ እና በዚህ ምክንያት ምርጫው መራዘሙ ተገቢ ነበር ብለን አምነናል።
ምርጫው አለመካሄዱን ተከትሎ የመንግሥት ቀጣይነትን ለማረጋገጥ በተለያዩ ወገኖች የተለያዩ አማራጮች መቅረባቸው የሚታወስ ነው። የተለያዩ ፖለቲካ ፖርቲዎችም ከሕገ-መንግሥት ውጪ ያሉ አማራጮችን አቅርበው ነበር። ኢዜማ የመንግሥት ቀጣይነትን በሕጋዊ ማዕቀፍ ውስጥ መፍታት እንደሚቻል ጠቅሶ፥ አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ-መንግሥት ከሚሰጣቸው የመፍትሄ አማራጮች ውስጥ ደግሞ የመንግሥትን የሥልጣን ጊዜ እና ምርጫ የሚደረግበትን ጊዜ የሚደነግገውን የሕገ-መንግሥት አንቀጽ ከአቅም በላይ እና በድንገተኛ ምክንያት ምርጫ ማድረግ የማይቻልበት ሁኔታ ሲፈጠር የመንግሥትን ሥልጣን ከአንድ ዓመት ላልበለጠ ጊዜ ማራዘም እንዲያስችል አድርጎ ማሻሻል የተሻለ አማራጭ እንደሆነ ማቅረቡ ይታወሳል። ማሻሻያው ሥልጣን ላይ የሚቆየው መንግሥት የሥልጣን ጊዜ ገደብ ያስቀመጠ እና ውሳኔ የሚሰጥባቸው ጉዳዮች በቀጣይ ምርጫ አሸንፎ ሥልጣን የሚይዘው መንግሥት ላይ ግዴታ የማይጥሉ መሆናቸውን ባረጋገጠ መልኩ መሆን እንዳለበትም ምክረ-ሀሳብ አቅርበን ነበር።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ክፍተቱን በሕገ-መንግሥት ትርጉም ለመሙላት ወስኖ የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ባቀረበው የውሳኔ ሀሳብ እና በፌደሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ምርጫውን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስጋት አለመሆኑ በጤና ሚኒስቴር እና የኅብረተሰብ ጤና ተቋም እስኪረጋገጥ ድረስ አራዝሞ የፌደራል እና የክልል መንግሥታት እና ምክር ቤቶችን የሥራ ጊዜ ያለገደብ እንዲቀጥል መወሰኑ ይታወሳል።
ይህን ውሳኔ ተከትሎ ኢዜማ የጊዜ እና ውሳኔ የሚያሳልፍባቸው ጉዳዮች ላይ ወሰን ሳይደረግ ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት የሥራ ዘመን መራዘሙ ላይ ያለውን ተቃውሞ ገልፆ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለሕገ-መንግሥት አጣሪ ጉባዔ በገለጸው መሠረት አስፈላጊው ጥንቃቄ ተደርጎ ምርጫው መደረግ በሚችልበት ቅርብ ጊዜ እንዲደረግ ጠይቋል።
በቅርቡ የጤና ሚኒስትር አስፈላጊው ጥንቃቄ እየተደረገ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ እንደሚቻል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባሳወቀው መሠረት ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ በያዝነው ዓመት እንዲካሄድ ውሳኔ ተላልፏል።
ይህ በእንዲህ እያለ፥ “ሥልጣን ለማራዘም የተሄደበት መንገድ ሕገ-መንግሥታዊ አይደለም፤ በዚህም ምክንያት ከመስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም በኋላ መንግሥት የለም፤ ሕዝብ እና የመንግሥት መዋቅር ለፌደራል እና የክልል መንግሥታት ሊታዘዙ አይገባም» በሚል ቅስቀሳ ሲደረግ መቆየቱን እና አሁንም እየተደረገ እንደሚገኝ ለማስተዋል ችለናል።
ይህ ቅስቀሳ የሀገራችንን ሰላም እና መረጋጋት ከማወክ እና የዜጎችን ሕይወት አደጋ ላይ ከመጣል በዘለለ ፋይዳ እንደሌለው የኢትዮጵያ ሕዝብ በደንብ እንደሚገነዘብ እናውቃለን። ይህንን ቅስቀሳ እያደረጉ ያሉ አካላትም ከዚህ ተግባራቸው ተቆጥበው የጋራ ሀገራችን ሰላም እና የዜጎች ደህንነት ተጠብቆ በሰላማዊ መንገድ ችግሮቻችንን መፍታት ወደምንችልበት የውይይት መድረክ ከመምጣት ውጪ በሁከት እና በጉልበት ወደሥልጣን ለመውጣት የሚደረግ ማንኛውም እንቅስቃሴ ለራሳቸውም ቢሆን የማይጠቅም አደገኛ መንገድ መሆኑን ሊረዱ ይገባል። መንግሥትም እነዚህን ቅስቀሳዎች በንቃት እየተከታተለ አደጋ ከመድረሱ በፊት የመከላከል እና አደጋ ለማድረስ የሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ ሕጋዊ እርምጃ በመውሰድ የሀገር ሰላምን እና የዜጎችን ደህንነት የማስከበር ኃላፊነቱን እንዲወጣ እናሳስባለን።
ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ዘንድሮ እንዲካሄድ የተወሰነውን ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ነፃ እና ፍትሃዊ ማድረግን ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባው እና ምርጫው እስከሚካሄድ እና የሕዝብ ድምፅ ያገኘው ተለይቶ እስከሚታወቅ ድረስ የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ፣ የሀገር ሉዓላዊነትን ማስከበር እና ምርጫውን ነፃ እና ፍትሃዊ ከማድረግ ጋር በቀጥታ ግንኙነት የሌላቸውን በተለይም በምርጫው የሚወዳደሩ ፓርቲዎች የተለያየ ፖሊሲ አቅርበው የሕዝብን ቅቡልነት ለማግኘት በሚወዳደሩባቸው ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ከማሳለፍ እና ከመተግበር እንዲቆጠብ እናሳስባለን።
እኛንም ጨምሮ በሀገራችን የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሙሉ በነፃነት ተንቀሳቅሰው ሃሳባቸውን መግለፅ እንዲችሉ ከዚህ ቀደም በተስማማንበት የፖለቲካ ፓርቲዎች የቃል ኪዳን ሰነድ መሠረት የምናደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ሰላማዊ፣ ሕጋዊ እና የሌሎችን መብት ያከበረ መሆኑን እያረጋገጥን ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ነፃ እና ፍትሃዊ እንዲሆን የሚጠበቅብንን ሁሉ እንድናደርግ እንጠይቃለን። በሀገራችን የምትንቀሳቀሱ የሲቪክ ተቋማትም የፖለቲካ ፓርቲዎች የተስማሙበትን የቃልኪዳን ሰነድ እንዲያከብሩ ግፊት እንድታደርጉ እና በጋራ ሊሠሯቸው እና ሊስማሙባቸው በሚገቡ ተጨማሪ ጉዳዮች ላይ ውይይት ማድረግ የሚችሉበት መድረክ እንድታዘጋጁ የአደራ ጥሪያችንን እያስተላለፍን፥ በመድረኮቹ ላይ በንቃት ለመሳተፍ ያለንን ፍላጎት ከወዲሁ ለመግለጽ እንወዳለን።
መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ በሀገራችን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ለምንገነባው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መደላድል የምንጥልበት ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑን በመገንዘብ የምርጫውን ሂደት ከአሁን ጀምሮ በንቃት እንዲከታተል እና ምርጫው ሰላማዊ፣ ነፃ እና ፍትሃዊ መሆኑን ለማረጋገጥ የሚጠበቅባችሁን ሁሉ እንድታደርጉ የአደራ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)
መስከረም 26 ቀን 2013 ዓ.ምSeptember 18, 2020 at 1:06 am #15904In reply to: የፖለቲካ ፓርቲዎች ድምጽ (ኢትዮጵያ ውስጥ የሚነቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች)
AnonymousInactiveየሀገር ሰላምና መረጋጋት፣ የዜጎች ሰብዓዊ-መብትና ክብር ከሁሉም ይቀድማል፤ ብሔራዊ መግባባት እና ውይይት በአስቸኳይ!
ከአብሮነት ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት (አብሮነት) የተሰጠ መግለጫበቅድሚያ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንኳን ለ2013 ዓ.ም አዲስ ዓመት በሰላም አደረሳችሁ በማለት መልካም ምኞቱን ይገልፃል። አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የጤና፣ የፍቅር፣ የመተሳሰብ፣ የመከባበር፣ የመግባባት፣ የሀገራችንን ዘርፈ ብዙ ችግሮች በመወያየት፣ በመነጋገርና በእርቅ የምንፈታበት ዘመን እንዲሆንልን ይመኛል።
አብሮነት ላለፉት 27 ዓመታት በሀገራችን ተንሰራፍቶ የነበረው የህወሓት/ኢህአዴግ አፋኝ አገዛዝ ሥርዓት “የለውጥ ኃይል” በሚባለው የብልጽግና የሪፎርም አካሄድ ከተተካ ባለፍነው ሁለት ዓመት ከግማሽ ያህል ጊዜ የሀገራችንን አጠቃላይ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ሁኔታዎች፥ በአጠቃላይ ወቅታዊ ጉዳዮችን በተለይ በአዲሱ ዓመት መባቻ ገምግሟል።
በአጠቃላይ የሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ግምገማው አብሮነት የሀገራችን ሕዝብ በሪፎርሙ ጅማሬ የተገባውን ቃል እና የፈነጠቀውን የፖለቲካ ምህዳር መሻሻል ተከትሎ የቋጠረው ተስፋ፣ ያሳደረው እምነት በጊዜ ውስጥ እየሟሸሸ፣ በሀገሪቱ የሚታየው ሁኔታ ከቁጥጥር ውጪ እየሆነ “የሽግግሩ መንግሥት” የሀገሪቱ ፍኖተ-ካርታ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በበዓለ ሲመታቸው ያደረጉት ንግግር ነው ከተባለው ጋር በከፋ ተቃርኖ ውስጥ ገብቷል። የሕግ የበላይነትን አክብሮ ስለማስከበር፣ የዜጎች ሀሳብን በነፃ መግለጽና መቀበል መብት፣ “አሸባሪዎች እኛ ነን” በማለት ይቅርታ ጠይቀው የሽብር ሕጉን ያወገዙበትና በዚህ ሕግ የታሰሩ ፍርደኞች የተፈቱበት፣ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት የፖለቲካ ፓርቲዎችን ተሳትፎ ያበረታቱበት፣ የሰብዓዊ መብት መከበር ለጥያቄ የሚቀርብ አይሆንም የተባለበት… ሌሎች አዎንታዊ ቃል-ኪዳኖች በፈጣን ሁኔታ ተቀልብሰው [ቀድሞ] ወደ ነበርንበት፣ ሲያልፍም ከድጡ ወደ ማጡ ሊያስብል በሚችል ወደ ከፋ ደረጃ መድረሳችንን ተረድቷል።
በሀገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ የሚታየው ሁለንተናዊ ምስቅልቅል፣ ያጋጠሙን ፈተናዎች ከውስጥም ከውጪም እየገዘፉ፣ እየሰፉና እየተወሳሰቡ መጥተው ከመንግሥት የቁጥጥር አቅም በላይ በመሆናቸው ችግሮቹን የብልጽግና መንግሥት በተናጠል ሊሸከማቸውም ሆነ ሊያስተካክላቸው ከሚቻለው በላይ ሆነዋል፤ መፍትሄውም አብሮነት ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ሲያቀነቅነው የነበረው “በሁሉን-አቀፍ የብሔራዊ መግባባት ውይይት ሕገ-መንግሥታዊና መዋቅራዊ ለውጥ የሚመጣበትን ሥርዓት የመዘርጋት ፖለቲካ መፍትሄ እንጂ በምርጫም ሆነ ሌላ ከብልጽግና ብቻ በሚቀርብ መፍትሄ አያገኝም። ከአማራጭ መፍትሄዎች አንዱ የሽግግርና እርቅ መንግሥት ነው” የሚለው አቋሙ ትክክልና ዛሬ የበለጠ ግልጽ መሆኑን አረጋግጧል።
በመሆኑም አብሮነት ሰላማዊ ትግሉን አጠናክሮ የመቀጠል ዓላማና ተልዕኮውን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትና ለዚህም ግንኙነቱን በማጽናት፣ ማጠናከርና በማስፋት ለመሥራት ቃልኪዳኑን አድሷል። ወደ ወቅታዊ ሁኔታዎች ስንገባ አብሮነት የፖለቲካ ፓርቲዎችን እንቅስቃሴና የፖለቲካ እስረኞችን፣ የሀገራችን ቀጣይ ምርጫና የትግራይ ምርጫ፣ በአዲስ አበባ የሚፈጸመውን ዘርፈ ብዙ ሕገ-ወጥ ተግባራት፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና በሀገራችን በጎርፍና በዜጎች ላይ በሚፈጸም ጥቃት እየደረሰ ያለውን አደጋ፣ የሚመለከቱ ጉዳዮችን ገምግመናል።
የፖለቲካ ፓርቲዎችን እንቅስቃሴ በሚመለከት፥ ከጅምሩ ታይቶ የነበረው የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሕጋዊና ሰላማዊ መንገድ ተደራጅተው እንዲንቀሳቀሱ የማበረታታት አካሄድ ተቀልብሶ ፓርቲዎች በሕጋዊ መንገድ በነፃነት ተንቀሳቅሰው ብቃት ያላቸው ተፎካካሪ ሆነው ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚያደርጉት አስተዋጽኦ በሕግ ማስከበር ስም በገዢው ፓርቲ እንዲገደብ ተደርጓል።
ለዚህም እንደቅድመ 2010 ከገዢው ፓርቲ በሀሳብ የሚለዩትን፣ የሚተቹና የሚቃወሙትን፣ በገዢ ፓርቲውና መንግሥት ባለሥልጣናት በተጨባጭ የሚፈጸሙ ሕገ-ወጥ ተግባራት እንዲቆሙ፣ እንዲስተካከሉና አጥፊዎች በሕግ እንዲጠየቁ የሚጠይቁትን፣ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችንና አባላት በፈጠራ ውንጀላ ማሰርና ማሰቃየት፣ ትናንት ከተወገዘው ባልተናነሰ፥ እንዲያውም በከፋ ሁኔታ እየተፈጸሙ ነው። በዚህም ከሰላማዊ ታጋይነታቸው ውጪ የማይታሙት የአብሮነት ከፍተኛ አመራሮች በፈጠራ ውንጀላ ለእሥራትና ሥቃይ ተዳርገዋል።
በፖለቲካ ሀሳብ ጥራታቸውና ነገሮችን አስቀድመው አርቀው በማስተዋላቸው የሚታወቁት ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ያለምንም ማስረጃ ተሰቃይተው በነፃ ተለቀዋል፤ ትናንት የብልጽግና ፓርቲ አባል እንዲሆኑ ተጠይቀው ያልተቀበሉት የሰላማዊ አማራጭ መፍትሄ ሀሳብ አፍላቂ እውቁ ፖለቲከኛ አቶ ልደቱ አያሌው በተጠረጠሩበት ወንጀል ፖሊስ ማስረጃ ሊያቀርብ ባለመቻሉ ነፃ መሆናቸው በፍርድ ቤት ቢረጋገጥም ለህይወታቸው አስጊ የልብ ህመምተኛ በመሆናቸው የቅርብ የሐኪም ክትትል እንደሚያስፈልጋቸው ማስረጃ አቅርበውም የፍትህ ሥርዓቱን ግምት ላይ በጣለ፣ ሰብዓዊነትን በረገጠ አሳፋሪ ሁኔታ ዛሬም በከፍተኛ ስቃይ ውስጥ ይገኛሉ። አዲስ አበባ ውስጥ በማስረጃ አስደግፎ እንዲያቆም ችግሩን አደባባይ ያወጣው፣ በቀዳሚነት የታገለው የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ሊቀ-መንበሩን ጨምሮ ከፍተኛ አመራሮችም የዚሁ ፈጠራ ወንጀል ሰለባ ከመሆን አልፈው በተወገዘው “የፀረ-ሽብር ሕግ” እንዲከሰሱ ተበይኖባቸዋል። በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከፖለቲካ አመለካከታቸውና አቋማቸው ጋር በተያያዘ ጉዳይ ክስ ሳይመሠረትባቸው፣ በትምህርት ቤቶች ጭምር ታስረው ይገኛሉ የሚሉ መረጃዎች በስፋት ይቀርባሉ።
አብሮነት ኮሮና ቫይረስ /ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከመከሰቱ አስቀድሞም “የሀገራችን ነባራዊና ወቅታዊ ሁኔታ በሀገራችን ነፃ፣ ዲሞክራሲያዊና ፍትሃዊ ምርጫ ማካሄድ አያስችልም፤ ምርጫ ቢደረግ የሀገሪቱን ችግሮች ከሚያባብስ በቀር መፍትሄ አይሆንም፤ ያሳለፍናቸው ተደጋጋሚ ምርጫዎች ለውስብስብ ችግራችን መፍትሄ አላመጡም፤ በቀጣይም ምርጫ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ቢደረግ ለውጥ አያመጣም፤ ለሀገራችን ዘላቂና አስተማማኝ መፍትሄው ሕገ-መንግሥታዊና መዋቅራዊ ለውጥ ነው፤ ይህ ፖለቲካዊ መፍትሄ ማለት ሁሉን አቀፍ የብሔራዊ መግባባት ውይይት ነው” የሚል ግልጽ አቋም መውሰዱ ይታወቃል። ይህንን አቋም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት አግዞት ሀገራዊ ምርጫው እንዲራዘም ተደርጓል። ይሁን እንጂ ብዙ ፓርቲዎች የእኛን የብሔራዊ መግባባት ውይይት መፍትሄ ሀሳብ ቢቀበሉትም ገዢው የብልጽግና ፓርቲ/መንግሥት ባለመቀበላቸው መንግሥት ዕድሜውን በሕገ- መንግሥት ትርጉም ስም ላልተወሰነ ጊዜ ሲያራዝም፣ ህወሓት ደግሞ ሕገ-መንግሥትን ማክበር በሚል የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የፌደሬሽን ምክር ቤትም ሆነ አስፈጻሚው እንዳይደረግ ቢወስኑም፣ ቢያሳስቡም፤ እምቢኝ በማለት ምርጫ በክልሉ አካሂዷል። ለዚህ ችግር ምላሽ ይሆናል፣ የውጥረቱን ጊዜ ያሳጥራል በሚል ይመስላል መንግሥት ከሰሞኑ ምርጫው በዚህ ዓመት ይደረጋል ሲል እየሰማን ነው፤ አንዳንድ እንቅስቃሴዎችም እየታዘብን ነው።
አብሮነት መንግሥት በሕገ- መንግሥት ሥም ዕድሜውን ያለገደብ ማራዘሙም ሆነ ህወሓት /የትግራይ ክልል መንግሥት ያቀረብነውን የብሔራዊ መግባባት ውይይት ቢቀበልም፥ ተግባራዊ ለማድረግ ከመታገል ይልቅ የተናጠል ምርጫ ማድረጉ ትክክል አይደለም፤ የሁለቱም – ብልጽግና እና ህወሓት – የእልህ አካሄድ የሀገሪቱን ፖለቲካ ወደ ከፋ ውጥረት ከማሸጋገር ያለፈ ሰላማዊና ዘላቂ አስተማማኝ መፍትሄ ሊያመጡ አይችሉም ብሎ ያምናል።
የሀገራችንና የአፍሪካ ዋና ከተማ በሆነችው አዲስ አበባ የሚፈጸሙት ዘርፈ-ብዙ ሕገ-ወጥ ተግባራት ካለፈው ጥፋት በቀጠለ ስህተት እና በዕውቀትና የፖለቲካ ዓላማ መሠረት አድርጎ በተነደፈ ስልት በስፋት እየተካሄደ ነው። በተለይ የመሬት ወረራና የኮንድሚኒየም ቤቶች ዝርፊያ ጎልተው ከወጡና አደባባይ ከዋሉ በርካታ ወራት ተቆጥረዋል። ዛሬ አቤቱታ አቅራቢዎች ቢበራከቱም የመጀመሪያው በማስረጃ የተደገፈ አቤቱታ አቅራቢዎች – የባልደራስ አመራሮች – ዛሬ ወህኒ ተጥለዋል። ችግሩ መፍትሄ አላገኘም፤ ጥያቄዎች አልተመለሱም፤ በቀረቡት ማስረጃዎች መሠረት የከንቲባ ሹም ሽር ከመደረግ ያለፈ አጥፊዎች ለሕግ አልቀረቡም፤ በቀጣይም ይህን ለማስተካከል ቁርጠኝነት ስለመኖሩ አመላካች እርምጃዎች አልታዩም፤ ይልቁንም በነበረው መሠረት ለማስቀጠልና “‹በከተማዋ የባለቤትነት ጥያቄ” ላይ የሚደረገው ሽኩቻ ሲባባስ እንጂ ለማስቆም የሚደረግ ጥረት አልተስተዋለም። በመሆኑም ችግሩ ወደ ከፋ ደረጃ እንዳያድግና በፍጥነት እንዳይስፋፋ፥ ብሎም ጥፋትና ስርቆቱን እንዳያባብስ አብሮነት ሥጋት ገብቶታል። አፋጣኝ ሕጋዊ የእርምት እርምጃ በመውሰድ የሕግ የበላይነት ማስከበር፣ ከተማይቱንም በግልጽ የአስተዳደራዊ ባለቤት ለሆኑት ነዋሪዎቿ ማስረከብ እንደሚያስፈልግ በጽናት ያምናል።
የኮቪድ-19/ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በሚመለከት በተለይ ከወረርሽኙ መከሰትጋርተያይዞ ተጥሎ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መነሳትን ተከትሎ በሕብረተሰቡ ላይ እየታየ ያለው መዘናጋት አብሮነትን አሳስቦታል። መንግሥት በአዋጁ መነሳት ሕብረተሰቡ እንዳይዘናጋ በቂ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን መሥራት ባለመቻሉ ሕብረተሰቡ ወረርሽኙ የለም የተባለ ይመስል ከፍተኛ መዘናጋት ውስጥ ገብቷል። ሕብረተሰቡ የበሽታው መከላከያ የሆኑትን እርምጃዎች ሁሉ በመተው እራሱን ለበሽታው በሚያጋልጡ እንቅስቃሴዎች ውስጥ በማስገባቱ በሽታው የበለጠ እንዳይስፋፋ አብሮነትን አስግቶታል። በመሆኑም መንግሥትም ሆነ ሕብረተሰቡ የወረርሽኙን አደገኛነት በመገንዘብ ለበሽታው የሚመጥን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ በአንክሮ ያሳስባል።
በሀገራችን በጎርፍ እየደረሰ ያለውን አደጋ፣ በተለያዩ የሀገራችን ክልሎች/አካባቢዎች ከመጠን በላይ በጣለው ዝናብ የአዋሽ ወንዝ፣ የኦሞ ወንዝ፣ የባሮ ወንዝ፣ የአባይ ገባር ወንዞች ከመሙላታቸው በተጨማሪ ከግድቦች በተለቀቀ ውሃ ከ580,000 በላይ ዜጎች ለጉዳት ተዳርገዋል፤ ከዚህ ውስጥ ግማሽ ያህሉ ተፈናቅለዋል። በሌላ በኩል በተለያዩ አካባቢዎች (ኦሮሚያ ክልል፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ ደቡብ ክልል/ኮንሶ…) በዜጎች ላይ ጥቃት እየተፈጸመ ነው፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በአሰቃቂ መንገድ እየተገደሉና በሺዎች ህይወታቸውን ለማትረፍ ከቀዬአቸው እየተፈናቀሉ ነው። በመንግሥት በኩል ለመከላከል በቂ ዝግጅት፣ አደጋው ከደረሰም በኋላ በቂ ክትትልና ድጋፍ ያለመደረጉን፣ እንዲሁም በቀጣይ ሊደርሱ ለሚችሉ አደጋዎች በቂ የመከላከል ዝግጅት እየተደረገ ያለመሆኑን፣ ከአካባቢው የሚደርሱን መረጃዎች ያመለክታሉ። በሌላ በኩል የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በዚህ ልክ በሀገራችን በደረሰው አደጋና ጉዳት ምንም ሳይሉ በጎረቤት ሀገር ሱዳን በደረሰው ሀዘናቸውን ገልጸዋል፣ እንዳይቀጥልም ከጎናቸው እንደሚቆሙ ቃል ገብተዋል። ዜጎች በማያውቁት በተፈጸመባቸው ጥቃት ለሞት ተዳርገዋል፤ እየተዳረጉም ነው። በተረፉት ዜጎቻችን የደረሰው አደጋን ተከትሎ የሚመጣው የጤናና ምግብ ችግር፣ እንዲሁም ሊደርስ የሚችለው አደጋ በአንድ በኩል፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ዝምታና “የራሷ እያረረባት፣ የሰው ታማስላለች” አካሄድ በሌላው፣ በእጅጉ ያሳስበናል። ስለዚህ መንግሥት በራሱ እና ሕዝቡንና ዓለምአቀፍ ማኅበረሰቡን በማስተባበር በአፋጣኝ እንዲደርስላቸው ያስፈልጋል።
በመጨረሻ ገዢው ፓርቲ /መንግሥት በአፈናና የሸፍጥ ፖለቲካ በተመሳሳይ መንገድ እየተጓዘ በፕሮፖጋንዳና ባዶ የተስፋ ቃላት ጋጋታ ፣ የተለየ ውጤትም ሆነ ችግሮቻችን መፍታት እንደማይችል በተደጋጋሚ ተመልክተናል። ስለዚህ አብሮነት ችግሮቻችንን በአስተማማኝና ዘላቂ መንገድ ለመፍታት፣ ሃቀኛ የብሔራዊ መግባባት ውይይት ለነገ የማይባል ተግባር እንደሆነ ያምናል፤ ገዢው ፓርቲ ለዚህ ያለውን ከፍተኛ ኃላፊነት እንዲወጣ በአጽንኦት ጥሪ ያደርጋል።
ለዚህ እንዲረዳም፡-
1ኛ/ በፖለቲካ አመለካከታቸው ከገዢው ፓርቲ በመለየታቸውና በሀገሪቱ ለሚታዩት ችግሮችና በሕዝብና ሀገር ሀብት ላይ እየደረሰ ያለውን በደል በማስረጃ አስደግፈው ተቃውሞ በማሰማታቸውና ጥያቄ በማቅረባቸው ብቻ የታሰሩ የፖለቲካና የኅሊና እስረኞች በአስቸኳይ እንዲፈቱ፤
2ኛ/ ለ27 ዓመታት አንድ ሆነው ሕዝባችን ሲያሰቃዩ የነበሩትና ዛሬ በሥልጣን ጥያቄና ያለፈውን በማስቀጠል ስልት ላይ ባለመስማማታቸው በተለያዩት በህወሓት እና በብልጽግና ፓርቲዎች መካካል ትናንትም ሆነ ዛሬ በሚደፈጥጡት ሕገ-መንግሥትና አምስት ጊዜ ባጭበረበሩት ምርጫ ሥም የሚታየው መካረርና ፍጥጫ በአስቸኳይ ተገትቶ፥ ለብሔራዊ መግባባት ውይይት ችግሮቻቸው እንዲፈታ የፖለቲካ ቁርጠኝነታቸውን እንዲያረጋግጡ፤
3ኛ/ የሀገራችን ችግሮች ምንጭ ምርጫ ባለመሆኑ፥ በምርጫም የሚፈቱ ያለመሆናቸው ባለፉት አምስት ምርጫዎች በመረጋገጡ፥ ለሕገ-መንግሥታዊና መዋቅራዊ የፖለቲካ መፍትሄ ምርጫ ለማድረግ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችም ሆነ እንዲደረግ የሚደረጉ ግፊቶች በአስቸኳይ ቆመው ሁሉንም ወገኖች የሚያሳትፍ የውይይት መድረክ እንዲመቻች ለዚህም ሁሉም ዜጋ አስፈላጊውን ተፅዕኖ በመንግሥት ላይ እንዲያሳርፍ፤
4ኛ/ መንግሥትም ሆነ ሕብረተሰቡ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን በመከላከል ረገድ እያሳዩ ያሉትን ቸልተኝነት በማቆም አስፈላጊውን የመከላከል ጥንቃቄና የመለየት ምርመራ እንዲያደርጉ፣ ለተጠቂዎች አገልግሎት ማቅረቡንና የግንዛቤ ማሳደግ ተግባራት በስፋት እንዲያከናውኑ፤
5ኛ/ በሀገራችን በተፈጥሮና ሰው-ሠራሽ ምክንያት ጎርፍ እያደረሰ ላለው ከፍተኛ አደጋ መንግሥት “የራሷ እያረረባት የሰው ታማስላለች” ከሚያስብል አካሄድ ወጥቶ በዜጎች ህይወት፣ ሥቃይ፣ የንብረት ውድመትና ቀጣይ ህይወት ላይ ትኩረት እንዲያደርግ፤
6ኛ/ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች እንደየቱም ክልል ነዋሪ የከተማቸው አስተዳዳራዊ ባለቤት መሆናቸው እንዲረጋገጥ፣ በከተማዋ የባለቤትነት መብት የሚደረገው በብልጽግና ውስጥ ጭምር የሚደረገው ሽኩቻ እንዲቆም፣ የተበዘበዘውና የተዘረፈው የከተማዋ ሀብት በሕግ ተመልሶ ለከተማዋ ልማት እንዲውል፣ አጥፊዎች ለሕግ እንዲቀርቡ፣ እንዲደረግ፤
7ኛ/ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች በዜጎች ላይ የደረሰው ጥቃት በገለልተኛ ወገን በአስቸኳይ እንዲጣራና ተገቢው ካሳ እንዲደረግላቸው፥ እንዲሁም አጥቂዎችና ተባባሪዎቻቸው በሕግ እንዲጠየቁ እንዲደረግ፣ ለጥቃቱ ሰለባዎች አስፈላጊው የዕለት ደራሽ ዕርዳታና የማቋቋሚያ ድጋፍ በአስቸኳይ እንዲደርሳቸው፤ ለዚህ ተፈጻሚነትም የፖለቲካ ፓርቲዎች ጅምሩ የብሔራዊ መግባባት ውይይት እንዳይነጠቅና በገዢው ፓርቲ እጅ እንዳይወድቅ፣ ከላይ ያቀረብናቸው እንዲፈጸሙ በልዩነታችን ውስጥ በሀገራዊ ጉዳዮች በቅድሚያ በሕግ የበላይነትን በማክበርና ማስከበር ለሰላምና መረጋጋት፣ ለሰብዓዊ መብት መከበር ተባብረን እንድንቆም ጥሪያችንን እናቀርባለን፤ ለተግባራዊነቱ ያለንን ቁርጠኝነት እናረጋግጣለን።
ከአሳታፊ ሁሉን አቀፍ ሃቀኛ የብሔራዊ መግባባት ውይይት ውጪ የቱም አንድ ፓርቲና ከብሔራዊ መግባባት ውይይት በፊት የሚደረግ የይስሙላ ምርጫ ለሀገራችን ችግሮች ዘላቂና አስተማማኝ መፍትሄ አያመጣም።
ከሁሉም በፊት መንግሥት የሕግ የበላይነት በማክበርና በማስከበር በሃቀኛ ሕዝባዊ ተሳትፎ የሀገራችን ሰላምና መረጋጋት፣ የዜጎችን የመኖር ሰብዓዊ መብት የማረጋገጥ ኃላፊነቱን ይወጣ፤ ከሥልጣኑ ይልቅ ለሀገርና ሕዝብ ጉዳይ ቅድሚያ ይስጥ።
አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌደራላዊ አንድነት (አብሮነት)
መስከረም 07 ቀን 2013 ዓ.ም
አዲስ አበባAugust 17, 2020 at 10:22 am #15441In reply to: የፖለቲካ ፓርቲዎች ድምጽ (ኢትዮጵያ ውስጥ የሚነቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች)
SemonegnaKeymaster“የወላይታ ዞን ነዋሪዎች ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ሕጋዊ ነው።”
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በወላይታ ዞን የተቀሰቀሰውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ሕይወታቸውን ያጡና ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች ጉዳይ በአስቸኳይ እንዲጣራና ለሕዝብ ይፋ እንዲሆን ጠየቀ።
ፓርቲው በሕዝብ ግንኙነት ክፍሉ በኩል ነሐሴ 05 ቀን 2012 ዓ.ም «በወላይታ ዞን የተፈጠረው አለመረጋጋት በሰላማዊ መንገድ ይፈታ» በሚል ርዕስ ባወጣው መግለጫ በዞኑ በተፈጠረው አለመረጋጋት ሕይወታቸውን ባጡ ዜጎች ምክንያት የተሰማውን ሐዘን ገልፆ፥ መንግሥት በአስቸኳይ ጉዳዩን አጣርቶ ይፋ ያድርግ ሲል ጠይቋል። «የመንግሥት የፀጥታ ኃይል ተገቢ ያልሆነ ኃይል በፍጹም እንዳይጠቀም እና የዜጎችን ሕይወት ለአደጋ ሳይዳርግ ሕግን በማስከበር ዞኑን ለማረጋጋት ከማኅበረሰቡ ጋር በቅርበት እንዲሠራ» በማለት ኢዜማ ማሳሰቢያውን ሰጥቷል።
በክልሉ የሚገኙ ማኅበረሰቦች የሚያነሷቸውን የራስን በራስ የማስተዳደር ተገቢ ጥያቄዎች ቀጥተኛ እና ዘላቂ በሆነ መልኩ መመለስ ይገባል ማለቱን ያስታወሰው ኢዜማ፥ ይህን ለማድረግ ግን ማኅበረሰቡ በነፃ እና ገለልተኛ በሆነ መንገድ የመረጣቸው፣ የሚፈልገውን የሚፈጽሙለት ተወካዮች መኖራቸው እና በጉዳዩ ላይ ሰፊ ሕዝባዊ ውይይቶች መደረጋቸው አስፈላጊ ስለሆነ ሕዝቡ ተወካዮቹን መርጦ ሰፊ ሕዝባዊ ውይይቶች ተደርገው ሕዝበ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ በትዕግስት እንዲጠብቅም ጠይቆ እንደነበር አስታውሷል። ፓርቲው ይህንን ጥያቄውን አቅርቦ የነበረውም ሰኔ 9 ቀን 2012 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ እንደነበር ጠቁሟል።
የዞኑ ነዋሪዎች ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ሕጋዊ መሆኑን እንደሚያምን በመግለጫው ላይ የጠቆመው ኢዜማ፥ ሀገሪቷ እና ዓለም ያለበት ሁኔታ ግን ሕገ መንግሥቱ የሚፈቅደውን የክልልነት ሒደት ለማሟላት የሚያስችል እንዳልሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል ብሏል። ለዚህም በምክንያትነት ኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰትን አንስቷል። ኮቪድ ወረርሽኝ ተከትሎ በታወጀው አስቸኳይ ግዜ አዋጅ የተነሳ ውይይት ማድረግም ሆነ ሕዝበ ውሳኔ ማድረግ የሚቻልበት ሁኔታ እንደሌለ ያስታወሰው ኢዜማ፥ በክልሉ በአጠቃላይ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ በሕጋዊ መንገድ ለመፍታት የሕዝብ ውክልና ያላቸው ተወካዮች መኖራቸው እንዲሁም በቂ ውይይት እና መግባባት ስለሚያስፈልግ በትዕግስት መጠበቁ የተሻለ አማራጭ መሆኑን ለማስታወስ እወዳለሁ ብሏል።
ጥያቄውን የሚያነሱት ወገኖችም ሰላማዊ ከሆነ መንገድ ውጪ ዘላቂ መፍትሄ እንደማይገኝ መረዳት እንዳለባቸው እና እንቅስቃሴያቸውን ሁሉ በሰላማዊ መንገድ ማድረግ እንደሚገባቸው ፓርቲው አሳስቧል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ገዢው ፓርቲ የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰብ እና ሕዝቦች ክልልን መልሶ ለማዋቀር ለፌደሬሽን ምክር ቤት ያቀረበው ምክረ ሀሳብ ክልል ለመሆን ጥያቄ ያቀረቡትን የዞን አስተዳደሮች ጥያቄን የማይመልስ፣ ክልሉ መጀመሪያ ሲዋቀር የተሠራውን ስህተት መልሶ የሚደግም፣ ሕገ ወጥ እና ግጭት የሚጋብዝ እንዲሁም እንደሀገር ካሉ ውስብስብ ችግሮች ላይ ሌላ ችግር የሚጨምር መሆኑን በማስረዳት ወደትግበራ እንዳይገባ በማለት ሰኔ 9 ቀን 2012 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ማሳሰቡ የሚታወስ ነው።
ምንጭ፦ ኢዜማ
June 16, 2020 at 3:46 pm #14811AnonymousInactiveራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ መሠረታዊ፣ የምንደግፈው እና ተግባራዊ እንዲሆን የምንታገልለት መብት ነው!
ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የተሰጠ መግለጫአንኳር
- ዘላቂ ውጤት ያላቸውን ሥራዎች የሕዝብ ፈቃድ ያላገኘ አስተዳደር የሕዝብ ፍላጎት ሳይታወቅ በዚህ የሽግግር ወቅት ሊተገብር እንደማይገባ በጽኑ እናምናለን።
- ገዢው ፓርቲ በደቡብ ክልል የተነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ ያዘጋጀው የክላስተር አወቃቀር/ምደባ አሁን በሥራ ላይ ባለው ሕገ-መንግሥት ሕገ-ወጥ የሆነ፣ ደቡብ ክልል ሲዋቀር የተሠራውን ስህተት በመድገም ተመሳሳይ ችግርን በአንድ ዓይነት መፍትሄ ለመቅረፍ ደግሞ የሚሞክር (የትልቁን ደቡብ ችግር ትንንሽ ደቡቦች በመፍጠር ለመፍታት)፣ ከባለፈው ችግር ትምህርት ያልወሰደ ሂደት ነው።
- በዚህ ከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት እና ጥንቃቄ በሚፈልግ ወቅት በደቡብ ክልል ራስን በራስ ለማስተዳደር የቀረቡ ግልጽ ጥያቄዎችን በፍፁም መመለስ የማይችል፣ ለችግሩ መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኝት ዓላማ ያደረገ ጥረት አመፅ እና ብጥብጥ ለማንሳት ለሚሞክሩ ኃይሎች ስንቅ እንደማቀበል የሚቆጠር ነው።
- ከሕብረተሰቡ ለሚነሱ ጥያቄዎች ቀጥተኛ እና ዘላቂ መፍትሄ መስጠት ሲገባ ጊዜያዊ እና የሕዝቡን ጥያቄ የማይፈቱ አማራጮችን በማቅረብ የሕዝብን እውነተኛ የፍትህ እና የዴሞክራሲ ጥያቄዎችን ማፈን ተገቢ አይደለም።
- ገዢው ፓርቲ ከሕግ አግባባ ውጪ በሆነ የመብት ሰጪ እና ነሺነት የሕዝብን ተቀባይነት ለማግኘት የሚያደርገውን ሩጫ በአስቸኳይ እንዲያቆም ኢዜማ አጥብቆ ያሳስባል። ይህ ሳይሆን ቀርቶ በዚህ ምክንያት በሰው ሕይወት እና ንብረት ላይ ለሚደርስ እያንዳንዱ ጉዳት ቀጥተኛ ተጠያቂ በራሱ ተነሳሽነት ጉዳዩን እየገፋ ያለው ገዢው ፓርቲ እንደሚሆን በግልፅ መታወቅ አለበት።
ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ መሠረታዊ፣ የምንደግፈው እና ተግባራዊ እንዲሆን የምንታገልለት ጥያቄ ነው!
ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የተሰጠ መግለጫሀገራችን ኢትዮጵያ ከረጅም ጊዜ የአምባገነን ሥርዓቶች መፈራረቅ እና ሥርዓቶቹን አስወግዶ ሕዝብን እውነተኛ የስልጣን ባለቤት ለማድረግ ከተደረገ የብዙዎችን መስዕዋትነት የጠየቀ ትግል በኋላ ወደእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግር ለማደርግ የሚያስችል ዕድል ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት አግኝታለች። ለ27 ዓመታት ሀገራችንን ዘውግን መሠረት ባደረገ አምባገነናዊ ፖለቲካዊ ሥርዓት ሲመራ የነበረው አገዛዝ ውስጥ የነበሩ የለውጥ አይቀሬነትን የተረዱ ግለሰቦች ለረጅም ጊዜ ሲደረግ የነበረውን ትግል በተወሰነ ደረጃ አግዘው ስልጣን መያዛቸው የሚታወስ ነው። እነዚህ ኃይሎች ስልጣን ላይ ከመውጣታቸው በፊት ለተፈፀሙ ጥፋቶች ይቅርታ ጠይቀው ሀገራችን ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግር ማድረግ እንዳለባት እንደሚያምኑ እና ይህንንም ሽግግር ጠንካራ መደላድል ላይ ለማስቀመጥ ነፃ እና ፍትሃዊ ምርጫ እስከሚደረግ ድረስ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚጠቅሙ የመንግሥት ተቋማት ጠንካራ እና ገለልተኛ ሆነው እንዲዋቀሩ እንዲሁም ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ማነቆ የሆኑ የፖለቲካ ምህዳሩን ያጠበቡ ሕጎችን እና አሠራሮችን ለመቀየር (ለማሻሻል) ቃል ገብተው ነበር።
ሥርዓቱን ለመቀየር ትግል ሲያደርግ እና መስዕዋትነት ሲከፍል የነበረው ሕዝብ እና አብዛኞቹ የፖለቲካ ኃይሎችም ይህንን ዕድል በአጭር ጊዜ የፖለቲካ ስሌት ከማየት ይልቅ ስልጣን ላይ የወጣው ኃይል ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚደረገውን ሽግግር የሚያግዙ ሥራዎች ለመሥራት ቃል እስከገባ እና ይህንን ቃል የሚጠብቅ እስከሆነ ድረስ በረጅም ጊዜ ቀስ በቀስ የሚገነባ ሀገራዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ከፉክክር ውጪ በሆነ መልኩ ማገዝ እንደሚያስፈልግ አምኖ ምንም እንኳን ስልጣን የያዙት ከሕዝብ ውክልና ውጪ ቢሆንም እስከ ምርጫው ድረስ ስልጣን ላይ እንዲቆዩ ዕድል መስጠትን መርጧል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህም (ኢዜማ)ከተመሠረተ ጀምሮ ለሀገር መረጋጋት እና ሰላም ቅድሚያ በመስጠት የፉክክር ጉዳዮችን ምርጫው ለሚደረግበት ጊዜ አቆይቶ ለሁላችንም የሚበጀውን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት ከሚፈልጉ አካላት ሁሉ ጋር በትብብር መንፈስ ሲሠራ ቆይቷል። በኢዜማ እምነት ቀጣዩ ምርጫ እስኪደረግ ድረስ ያለው የሽግግር ወቅት በዋነኛነት ሀገርን ለማረጋጋት እና ምርጫውን ነፃ እና ፍትሃዊ ለማድረግ መሠራት ያለባቸው ሥራዎች ማከናወኛ ነው። ዘላቂ ውጤት ያላቸውን ሥራዎች የሕዝብ ፈቃድ ያላገኘ አስተዳደር የሕዝብ ፍላጎት ሳይታወቅ በዚህ የሽግግር ወቅት ሊተገብር እንደማይገባ በጽኑ እናምናለን።የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰትን ተከትሎ ምርጫው በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መካሄድ እንደማይችል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ካሳወቀ በኋላ የኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት ባስቀመጠው የአምስት ዓመት ገደብ ውስጥ ምርጫው መደረግ ስላልቻለ ምርጫ ተደርጎ የሕዝብ ውክልና ያለው መንግሥት እስኪኖር ድረስ ሀገራችንን ማን ያስተዳድር የሚል ጥያቄ መነሳቱ ይታወሳል። ይህን ጥያቄ ተከትሎ ከነበሩት አማራጮች መካከል በድንገተኛ እና ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ምርጫ በተያዘለት ጊዜ ማድረግ ሳይቻል ሲቀር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የራሱን እና የአስፈጻሚውን አካል ስልጣን የዜጎችን ደህንነት፣ የሀገር ሉዓላዊነትን እና ምርጫውን ነፃ እና ፍትሃዊ ከማድረግ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ብቻ ገድቦ ምርጫውን እስከ አንድ ዓመት ለሚደርስ ጊዜ ማራዘም የሚያስችለውን ስልጣን ሕገ-መንግሥቱን በማሻሻል እንዲሰጠው ምክረ-ሀሳብ አቅርበን ነበር። ነገር ግን መንግሥት በወሰደው የሕገ-መንግሥት ትርጉም አማራጭ የሕገ-መንግሥት አጣሪ ጉባዔ ያቀረበለት ምክረ-ሀሳብ ላይ ተመሥርቶ የኢፌዴሪ ፌደሬሽን ምክር ቤት ምርጫው የሚካሄድበትን ጊዜም ሆነ የመንግሥትን ስልጣን ያልገደበ ውሳኔ አሳልፏል። የፌደሬሽን ምክር ቤት ምርጫው የሚካሄድበትን ጊዜ በወረርሽኙ ምክንያት ክፍት አድርጎ የተወው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ወረርሽኙ ባይጠፋም እንኳን በተጨማሪ ጥንቃቄ፣ ጊዜ እና በጀት ምርጫውን ማድረግ የሚቻልበት ሁኔታ (scenario) እንዳለ ለሕገ-መንግሥት አጣሪ ጉባዔ ከገለፀ በኋላ እና ምርጫው ያለገደብ እንዲራዘም የመጨረሻ ውሳኔ የሰጡት የምክር ቤቱ አብዛኛዎቹ አባላት «ምርጫው በቶሎ እንዲካሄድ እፈልጋለሁ» ብሎ በይፋ የተናገረው ገዢ ፓርቲ አባል መሆናቸው ውሳኔው የተሳሳተ ብቻ ሳይሆን ግልፅ ያልሆነ ዓላማ እንዳነገበም እንድንጠራጠር አድርጎናል።
ይህ የ«ሕገ-መንግሥት ትርጉም» ለመንግሥት ያልተገደበ ስልጣን በሰጠ ማግስት በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ውስጥ የሚገኙ ዞኖች ካነሱት ራስን በራስ ማስተዳደር ጥያቄ ጋር ተያይዞ መንግሥት አስጠናሁ ያለውን ክልሉን ወደ አምስት የሚከፍል ምክረ-ሀሳብ ለመተገበር እንቅስቃሴ ላይ እንደሆነ ተረድተናል።
ገዢው ፓርቲ በደቡብ ክልል የተነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ ያዘጋጀው የክላስተር አወቃቀር/ምደባ አሁን በሥራ ላይ ባለው ሕገ-መንግሥት ሕገ-ወጥ የሆነ፣ ደቡብ ክልል ሲዋቀር የተሠራውን ስህተት በመድገም ተመሳሳይ ችግርን በአንድ ዓይነት መፍትሄ ለመቅረፍ ደግሞ የሚሞክር (የትልቁን ደቡብ ችግር ትንንሽ ደቡቦች በመፍጠር ለመፍታት)፣ ከባለፈው ችግር ትምህርት ያልወሰደ ሂደት ነው። ከሁሉ በላይ ሀገራችን ኢትዮጵያ ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ ያላገናዘበ፣ ጭራሹንም የረሳ ነው።
ሀገራችን በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ባለው ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መያዛቸው የተረጋገጡ እና ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር በእጅጉ እየጨመረ የሚገኝበት፣ ወረርሽኙን በቁጥጥር ስር ለማዋል በተወሰዱ እርምጃዎች ምክንያት 6ኛውን ሀገራዊ ምርጫ ለመግፋት የተገደድንበት፣ የንግድ እና አጠቃላይ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በከፍተኛ ደረጃ የተቀዛቀዘበት ሁኔታ ውስጥ ትገኛለች። ከዚህ በተጨማሪ ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር ተያይዞ የሚመጣብንን ጫና ለመቋቋም ከመቼውም ጊዜ በላይ ሀገራዊ አንድነት የሚያስፈልግበት እና ጫፍ የረገጠ ፅንፈኛ አመለካከት ያላቸው ኃይሎች ምርጫው መራዘሙን እንደሽፋን በመጠቀም ብጥብጥ ለማስነሳት ቀጠሮ በያዙበት ከፍተኛ ጥንቃቄን የሚፈልግ ወቅት ላይ እንገኛለን።
በዚህ ከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት እና ጥንቃቄ በሚፈልግ ወቅት በደቡብ ክልል ራስን በራስ ለማስተዳደር የቀረቡ ግልጽ ጥያቄዎችን በፍፁም መመለስ የማይችል፣ ለችግሩ መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኝት ዓላማ ያደረገ ትልቁን ደቡብ ክልል ወደ አነስተኛ ደቡብ ክልሎች ለመቀየር የሚደረግ ጥረት አመፅ እና ብጥብጥ ለማንሳት ለሚሞክሩ ኃይሎች ስንቅ እንደማቀበል የሚቆጠር ነው።
በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀፅ 47 ንዑስ አንቀፅ 2 መሠረት የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች የየራሳቸውን ክልል የማቋቋም መብት እንዳላቸው ይደነግጋል። ከሁለት አስር ዓመታት በላይ በተግባር የተፈተሸው ሕገ-መንግሥት ያረጋገጠው የብሔር ብሔረሰቦችን መብት አስከብራለሁ ብሎ ካስቀመጠው ተቃራኒ የሕዝቦች መብት ከመከበር ይልቅ የብሔራዊ አንድነት፣ ሰላም እና የሕዝቦች አብሮ መኖርን አደጋ ላይ መጣሉን ነው። ይህ ሕገ-መንግሥት በስልጣን እስከቆየ ድረስ ሀገራችን ኢትዮጵያ ተረጋግታ እንደ ሀገር የመቀጠሏ ብሎም ሕዝቦቿ በነፃነት ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው የመኖር መብታቸው የሚከበርበት መንገድ እንደሌለ በተግባር ተፈትኖ ግልጽ ሆኗል። ይልቁንም የተለያዩ አጀንዳ ያላቸው የፖለቲካ ኃይሎች ይህንን የሕገ-መንግሥት ክፍተት ተጠቅመው ወደማያባራ እና መጨረሻ ወደሌለው የማንነት፣ የክልልነት እንዲሁም የሀገር እንሁንነት ጥያቄዎችን ሊያስከትል ይችላል።
ሕገ-መንግሥቱ በራሱ ምሉዕ ካለመሆኑም በተጨማሪ ከፍተኛ የአፈፃፀም ጉድለት አለበት። በስልጣን ላይ የነበረው መንግሥት እራሱ ባረቀቀው ሕገ-መንግሥት ውስጥ ከተቀመጡት አካሄዶች ባፈነገጠ መልኩ የተወሰነ ቡድን ፍላጎትን ለማሟላት እና በፖለቲካ ጥቅም አሳዳጅነት ብሎም ለሕዝብ እና ለሀሳቡ ካለው ንቀት በሕዝብ ቁጥር አነስተኛ የሆኑ አካባቢዎችን በክልልነት ሲያካልል እና እውቅና ሲሰጥ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ያላቸውን አካባቢዎች በመጨፍለቅ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልልን መሥርቷል። በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት መሠረት አሁን ለፌደሬሽን ምክር ቤት «ክልል እንሁን» የሚል ጥያቄ ያስገቡት ዞኖችን ክልል እንዳይሆኑ ለመከልከል ምንም ሕጋዊም ሆነ የሞራል ምክንያት የለም።
ከምሥረታው ጀመሮ በብዙሃን ቅቡልነት ያልነበረው የዚህ ክልል አደረጃጀት ክልሉ ከተመሠረተ በኋላ ሲተገበሩ በነበሩ አግላይ ፖሊሲዎች፣ የሀብት እና የስልጣን ከፍፍል ኢ-ፍትሃዊነት እናም የመልካም አስተዳደር እጦት በብዙ የክልሉ ማኅበረሰብ ዘንድ የክልልነት ጥያቄዎች እንዲነሱ ከፍተኛ አስተዋፅዖ አድርጓል። ለዚህም ከሕብረተሰቡ ለሚነሱ ጥያቄዎች ቀጥተኛ እና ዘላቂ መፍትሄ መስጠት ሲገባ ጊዜያዊ እና የሕዝቡን ጥያቄ የማይፈቱ አማራጮችን በማቅረብ የሕዝብን እውነተኛ የፍትህ እና የዴሞክራሲ ጥያቄዎችን ማፈን ተገቢ አይደለም።
በኢዜማ እምነት ራስን በራስ ማስተዳደር ጥያቄ መሠረታዊ፣ የምንደግፈው እና ተግባራዊ እንዲሆን የምንታገልለት ጥያቄ ነው። በእርግጥ አሁን በሥራ ላይ ባለው የፌደራል አወቃቀር መሠረት ዘውግን መሠረት አድርጎ የሚደረግ የአስተዳደር አከላለል ራስን በራስ ከማስተዳደር ይልቅ አካባቢውን ለዘውግ ማንነት የባለቤትነት ካርታ መስጫ መንገድ እንደሆነ ግልጽ ነው። ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ በክልል ወይም በዞን ደረጃ ብቻ የሚመለስ አለመሆኑንም በጽኑ እናምናለን። በደቡብ ክልል የተነሱ ጥያቄዎችን የወለደው የተዛባው ሕገ-መንግስታዊ የመስፈርት አጣብቂኝ፣ በሌብነት የተዘፈቀ ሥርዓት፤ ፍትህ ማጣት፤ የሀብት ክፍፍል ኢ-ፍትሃዊነት፤ እንደልብ ተንቀሳቅሶ ሰርቶ ሀብት በማፍራት የንብረቱ ሕጋዊ ባለቤት የመሆን ብሎም በሰላም የመኖር መሠረታዊ መብት መነፈግ እና የመሳሰሉት አስተዳደራዊ በደሎች ጥርቅም መሆኑን እንረዳለን። አሁን የተጀመረው እንቅስቃሴ ችግሮቹን ማከፋፈል እና ማሰራጨት እንጂ ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት የሚያስችል ስላልሆነ ከበደሎቹም ባሻገር የወደፊት መጪ ስጋቶች ፍንትው ብለው እየታዩ ነው። ወደፊት ሀብት የሚፈስባቸው ከተሞች ባለቤትነት እና በሕዝብ ስም የሚፈፀሙ የበጀት ምዝበራዎች ከስጋቶቹ መካከል ዋነኞቹ ናቸው። በራስ የሚተዳደደር ክልል እና ዞን መሆንን መፈለግ የእነዚህ በደሎች እና መጪ ስጋቶቸ ውጤት መሆኑን በቅጡ እንደሚረዳ ፓርቲ አሁን ለመሄድ እየታሰበበት ያለው መንገድ ለበደሎቹም ሆነ ለስጋቶቹ መፍትሄ እንደማይሆን ጠንቅቀን እናውቃለን።
እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ የሕዝቦች በየትኛውም ደረጃ ያለ የስልጣን እርከን ባለቤትነት መረጋገጥ ቁልፍ እርምጃ ነው። ይህ ደግሞ ሊሳካ የሚችለው እያንዳንዱ ዜጋ ከታችኛው የስልጣን እርከን ጀምሮ የሚያሰተዳድሩትን አመራሮች መምረጥ ሲችል ነው። መሰል የዜጎች ሕጋዊ የስልጣን ባለቤትነት ባልተረጋገጠበት ሁኔታ በየትኛውም ቦታ የሚካሄድ የትኛውም ዓይነት ዘላቂ ውጤት ያለው ውሳኔ የዜጎችን መሠረታዊ ጥያቄ መልስ መስጠት የሚችል እንዳልሆነ ፍንትው ያለ ሃቅ ነው።
ዛሬም ቢሆን በአብዛኛው ሕዝብ ዘንድ ከሚነሳው፤ እኛም እንደ ሀገራዊ ፓርቲ ካሉን መዋቅሮች ከሚደርሱን መረጃዎች እንደተገነዘብነው ትላንት አፋኝ እና ኢ-ዴሞክራሲያዊ ከሆነው ሥርዓት ጋር ተባባሪ በመሆን በሕዝባቸው ላይ ለደረሰው መከራ ቀዳሚ ተጠያቂ የሆኑ ግለሰቦች፣ በየደረጃው ያሉ አመራሮችና ካድሬዎች በውሳኔ ሰጪነት ስልጣን ላይ ናቸው። ለውጥ እንዲመጣ ዋጋ የከፈሉ፣ ለፍትህ እና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት እንዲሁም ለሕዝባቸው እኩል ተጠቃሚነት የታገሉ ግለሰቦችም ሆኑ ድርጅቶች በየደረጃው ባሉ የመንግሥት ውሳኔዎች ላይ ሀሳባቸው ሊሰማ ሲገባ ዛሬም በእነዚህ የመንግሥት አካላት ተፅዕኖ እየደረሰባቸው እንደሆነም ጭምር የምንረዳው ሃቅ ነው።
ገዢው ፓርቲ ይሄን ያልታደሰና የመለወጥም ፍላጎት እያሳየ ባልሆነው የካድሬና የባለሥልጣናት መዋቅሩ በደቡብ ክልል እየቀረበ ያለውን ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ለማፈን እያደረገ ያለው ሩጫ የሕዝብን መሠረታዊ ጥያቄ የማይመልስ ብቻ ሳይሆን ፓርቲው እያሳየ ያለውን የመብት ሰጪ እና ነሺነት ፍላጎትንም የሚያሳይ ነው። ይህ በየግዜው ከለውጡ አጠቃላይ መንፈስ እየራቀ የመጣው የገዢው ፓርቲ ፍላጎት በሀገራችን እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት የሚያደናቅፍም ጭምር ነው።
ገዢው ፓርቲ በአንድ በኩል በኮቪድ-19 ወረርሸኝ እና ከህዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ ባለው ጫና እግር ከወረች ተይዣለው በማለት ስድሰተኛውን ሀገር አቀፍ ምርጫ ላልተወሰነ ግዜ እያራዘመ በሌላ በኩል በዚሁ ጭንቅ ጊዜ ዘላቂ ውጤታ ያላቸው ትልልቅ ሥራዎችን ያለሕዝብ ምክክር እና ውሳኔ በራሱ እያከናወነ ይገኛል። ገዢው ፓርቲ ከሕግ አግባባ ውጪ በሆነ የመብት ሰጪ እና ነሺነት የሕዝብን ተቀባይነት ለማግኘት የሚያደርገውን ሩጫ በአስቸኳይ እንዲያቆም ኢዜማ አጥብቆ ያሳስባል። ይህ ሳይሆን ቀርቶ በዚህ ምክንያት በሰው ሕይወት እና ንብረት ላይ ለሚደርስ እያንዳንዱ ጉዳት ቀጥተኛ ተጠያቂ በራሱ ተነሳሽነት ጉዳዩን እየገፋ ያለው ገዢው ፓርቲ እንደሚሆን በግልፅ መታወቅ አለበት።
በደቡብ ክልል የምትኖሩ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን፥ ኢዜማ ደቡብ ክልል የሕዝቡን ፍላጎት ባሟላ መልኩ እንደገና እንዲዋቀር እንደሚፈልግ እንድትረዱ እና ለምታነሱት ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ትክክለኛ እና ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት አሁን ያለንበት ጊዜ እንደማይፈቅድ እና የእናንተን ፍላጎት የሚያስፈጽሙ በእናንተው የተመረጡ ወኪሎቻችሁ ሳይኖሩ እኔ አውቅልሃለው በሚሉ ካድሬዎች ሊከወን የሚቻል እንዳልሆነ በመረዳት፣ ቀጣዩ ምርጫ ተደርጎ ፍላጎቶቻችሁን የሚያስፈጽሙ ወኪሎቻችሁን እስክትመርጡ እና በጥያቄያችሁ ላይ ሰፊ ውይይት አድርጋችሁ በሕዝበ-ውሳኔ መወሰን የምትችሉበት ሁኔታ እስኪመቻች በተለመደው ኢትዮጵያዊ ጨዋነት እና ትዕግስት እንድትጠብቁ አበክረን እንጠይቃለን። ይህንን ተረድታችሁ ለጋራ ሀገራችን መረጋጋት እና ሰላም በማሰብ ጥያቄዎቻችሁን በሰከነ መንገድ ለመፍታት ለምታሳዩት ትዕግስት ከወዲሁ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የከበረ ምስጋና ያቀርባል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)
ሰኔ 9 ቀን 2012 ዓ.ም.May 6, 2020 at 6:20 pm #14394AnonymousInactiveየምንሰጠው ሕጋዊና ፖለቲካዊ አማራጭ ከወቅታዊው የኮሮና ወረርሽኝ የሚታደገን፣ ሀገረ-መንግሥቱን የሚያስቀጥልና ወደ ተረጋጋ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የምናደርገውን ሽግግር የሚያግዝ ሊሆን ይገባል! ― የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)
ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የተሰጠ የአቋም መግለጫ
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከባድ ጉዳት እያደረሰ እንደሆነ ይታወቃል። ወረርሽኙ በሰዎች ጤና እና ደኅንነት ላይ ካደረሰው እና እያደረሰ ካለው ጉዳት ባልተናነሰ የዓለምን እና የሀገራትን ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ መስተጋብሮች እና ሥርዓትን ከባድ አደጋ ውስጥ ከቷል። ወረርሽኙ በሀገራችን ኢትዮጵያ እስከካሁን ያስከተለው ጉዳት ከሌሎች ሀገሮች ጋር ሲነጻጸር አስከፊ የሚባል ባይሆንም የደቀነው አደጋ ግን ከፍተኛ መሆኑ እርግጥ ነው። በሌሎች ሀገር ከታየው ተሞክሮ አንፃር ወረርሽኙ ድንገት በከፍተኛ ቁጥር ዜጎችን ሊያጠቃ እና የጤና ሥርዓት ቀውስ ውስጥ ሊከተን የሚችልበት አደጋ አሁንም አለ። የጎረቤት ሀገሮች (ሱዳን፣ ጅቡቲ እና ሶማሊያ) የኮሮና ቫይረስ ስርጭት በፍጥነት መዛመት የጀመረበትና በተለይ ከጅቡቲ ጋር ካለን የቀረበ የኢኮኖሚ ትስስር አንፃር በምሥራቁ የሀገራችን ክፍል ላይ የደቀነው ስጋት ከፍተኛ እንደሆነ ግልጽ ነው።
ወረርሽኙን ለመቆጣጠር የሚወሰዱ እርምጃዎች በሀገራችን ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳርፉት ጫና ከአሁኑ እየታየ ነው። ወረርሽኙ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያደርሰው ጫናም በወጪ እና ገቢ ንግድ ዘርፍ ላይ ጫና እያሳደረ ሲሆን ይህም በቶሎ ወደቀድሞ ሁኔታው የሚመለስ አይሆንም። የበረሀ አንበጣ በኢትዮጵያ የግብርና ምርት ላይ እንደዚሁም የአገር ውስጥ ጥቅል ምርት ዕድገት ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተጽዕኖ ከፍተኛ ነው። በተጨማሪም በኮሮና ምክንያት ከፍተኛ የኢኮኖሚ መቀዛቀዝና እስከ ሰኔ ድረስ ከሁለት ሚሊዮን በላይ የሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዋስትና የማጣት ስጋት/አደጋ እንዳንዣበበባቸው በቅርቡ ተገልጿል። በአጠቃላይ ቫይረሱ በኢኮኖሚው ላይ የሚያስከትለው መጠነ ሰፊ መቀዛቀዝና የአገራዊ ጥቅል አመታዊ ምርትና እድገት ማሽቆልቆል ሀገራችን ላይ የከፋ ጉዳት ማስከተሉ አይቀሬ ነው።
በሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ የወረርሽኙ ተጽዕኖ ከኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ ጫና በተጨማሪ በፖለቲካው ዘርፍም በታሪካችን አጋጥሞን የማያውቅ ሁኔታ ውስጥ ከቶናል።
ከወረርሽኙ በተጨማሪ ከዚህ ቀደም የነበሩ የውስጥ ፖለቲካዊ ችግሮች እና በዓባይ ወንዝ ላይ እየገነባን ካለነው የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ጋር በተያየዘ ከሌሎች ሀገሮች የተደቀነብን አደጋ በፍፁም በቀላሉ የሚታይ አይደለም። በተለይም ከግድቡ የውሃ ሙሌት ጋር ተያይዞ የሚመጣው ተጽዕኖ እየጨመረ እንደሚሄድ ይጠበቃል።
የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ምክንያት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም ሊደረግ ታስቦ የነበረውን 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ማካሄድ እንደማይችል መጋቢት 22 ቀን 2012 ዓ.ም አስታውቋል። ምርጫው በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መካሄድ አለመቻሉ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የክልል ምክር ቤቶች የሥራ ዘመን ከተጠናቀቀ በኋላ ሀገርን ማን ያስተዳድራል የሚል ሕገ-መንግሥታዊ ጥያቄ አስነስቷል። በዚህም ምክንያት የተለያዩ አካላት ለዚህ ጉዳይ መፍትሄ ነው የሚሉትን ሀሳብ እያቀረቡ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በዚህ ጉዳይ ላይ ከሕግ ባለሙያዎች ጋር በተለይም ከሕገ-መንግሥት ጠበቆች (constitutional lawyers) ጋር ሰፊ ውይይት አድርጓል። ባለሙያዎቹ የተፈጠረውን ሕገ-መንግሥታዊ ክፍተት በሕገ-መንግሥታዊ አግባብ እንዴት ሊፈታ ይችላል የሚለውን የወቅቱ ትልቅ ጥያቄ ጊዜ ሰጥተው እንዲመክሩበት የከፍተኛ የባለሙያዎች ጉባዔ (high level panel of experts) በማቋቋም ለአንድ ወር ያህል ጉዳዩን ሲያስጠናና ምክክር ሲያስደርግበት ቆይቷል። ኢዜማ ከገባንበት የፖለቲካ አጣብቂኝ ለመውጣት ልንከተለው የሚገባው የመፍትሔ ሀሳብ የሚከተሉትን ታሳቢዎች ከግምት ያስገባ መሆን እንዳለበት በጽኑ ያምናል፤
- አገራችን ከምትገኝበት የሕግም የፖለቲካ አጣብቂኝ በአጭር ጊዜ ለመውጣት የሚረዳ መሆን እንዳለበት፣
- ተቋማዊ አሠራሮችን ከማጎልበት አንፃር የተሻለ ዕድል የሚፈጥር መሆን እንዳለበት፣
- አጠቃላይ ችግሩ በአጭር ጊዜ ፈቶ አገራችን ወደተረጋጋ የምርጫ ሂደት ለመግባት የሚያስችል መሆን እንዳለበት፣
- ከወጪም ከጊዜም አንፃር አገሪቱን ብዙ ዋጋ የማያስከፍል የተሻለው አማራጭ ላይ ትኩረት መደረግ እንዳለበትና በፍጥነት የተቀያየሩት የአገራችንንና የቀጠናውን ጂኦ-ፖለቲካዊና የደኅንነት ስጋቶች በሚገባ ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆን እንዳለበት።
ኢዜማ ከላይ የገለፅናቸውን ሀገራዊ ፈተናዎች ለማለፍ ሕዝብን አስተባብሮ ሊመራ የሚችል ጠንካራ መንግሥት እንደሚያስፈልገን ያምናል። ለዚህም እንደፓርቲ ልንከተለው የሚገባን የመፍትሄ ሀሳብ ይህንን የሚያረጋግጥ መሆን እንደሚገባው በፅኑ ይረዳል። ለዚህም ይረዳ ዘንድ የፓርቲያችንን የሕግ ባለሙያዎች ጨምሮ በሌሎች አካላትም የቀረቡትን የመፍትሔ ሀሳቦች እንደሚከተለው ተመልክተናቸዋል።
- ከሕግ አማራጭ ውጪ የፖለቲካ መፍትሄ በሚል በተለያዩ አካላት የቀረበ የመፍትሄ ሀሳብ
በዋናነት በዚህ ረገድ የቀረበው ሀሳብ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት የሥልጣን ዘመን ከመስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም. በኋላ የሚያበቃ በመሆኑ እና ሕገ-መንግሥቱም ከመስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም. በፊት መንግሥት በሥልጣን ላይ የሚቆይበትን ሁኔታ ክፍተት ስለማይሰጥ በፖለቲካ ፓርቲዎች ንግግር ላይ የተመሠረተ የሽግግር መንግሥት ሀገሪቱን ሊመራ ይገባል የሚል ነው። ይህ መፍትሄ ሀሳብ አሁን ያሉትን የፖለቲካ ፓርቲዎች የእርስ በርስ ግንኙነት እና የቁጥር ብዛት ከግምት ያላስገባ በመሆኑ ተግባራዊ ለማድረግ የማይቻል ነው። ከዚህም በላይ እንደ ሀገር ያሉብንን ከላይ የጠቀስናቸውን ፈተናዎች ተጋፍጦ ለማለፍ የሚያስፈልገንን ጠንካራ የመንግሥት መዋቅር የሚፈጥር አይደለም። ይህም የገባንበትን ችግር ከመፍታት ይልቅ ወደባሰ ሀገራዊ ቀውስ ሊከተን የሚችል አማራጭ ያደርገዋል።
- በሕገ-መንግሥቱ ማዕቀፍ ሥር ያሉ አማራጮች
2.1. በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 60/1 እና 3 መሠረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን በትነው በ6 ወር ውስጥ ምርጫ ማድረግ፦ ይሄ አማራጭ በ6 ወር ውስጥ ሊፈጠሩ የሚችሉ እና ሕግ ማውጣት የሚያስፈልጋቸው ድንገተኛ የሀገር እና ሕዝብን ደኅንነት እና ጥቅም አደጋ ውስጥ ሊከቱ የሚችሉ ሁኔታዎች ከግምት የማያስገባ፣ የፌደራል መንግሥትን እንጂ ሥልጣናቸው አብሮ የሚጠናቀቀውን የክልል ምክር ቤቶች ተመሳሳይ ችግር ያላገናዘበ አማራጭ በመሆኑ የምንፈልገውን ጠንካራ መንግሥት የሚፈጥር አማራጭ ሆኖ አላገኘነውም።
2.2. በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 93 መሠረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ እና ምርጫውን ማራዘም፦ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመንግሥትን የሥልጣን ዘመን ለማራዘም የተቀመጠ አንቀጽ አይደለም። አስቸኳይ ግዜ ማዋጅም በቀጥታ የመንግሥትን ሥልጣን ማራዘምን አያስከትልም። እንዲሁም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጥላ ስር የሚደረግ ምርጫን ነፃ እና ፍትሃዊ ማድረግ አይቻልም።
2.3. በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 83 እና 84 መሠረት የሕገ-መንግሥት ትርጉም ከፌደሬሽን ምክር ቤት መጠየቅ፦ በዚህ አማራጭ መሠረት የሕገ-መንግሥት ትርጉም ሥራ የሚሠራው የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ በሙሉ ነፃነት እና ያለማንም ጣልቃ ገብነት የተመራለትን ጉዳይ በመመርመር የውሳኔ ሀሳብ አቅርቦ የፌደሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ የሚሰጥ ከሆነ ያ ውሳኔ ምን ሊሆን እንደሚችል በእርግጠኝነት ማወቅ አይቻልም። አሁን ካለንበት አጣብቂኝ ክብደት አንጻር ጉዳዩን መዳረሻ ውጤቱ አስቀድሞ በእርግጠኝነት ለማይታወቅ እና ምናልባትም መልሶ እዚህ ከተጠቀሱት አማራጮች መካከል አንደኛውን እንድንከተል ሊያደርግ ለሚችል ሂደት መስጠት ተገቢ ሆኖ አላገኘነውም።
2.4. በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 104 እና 105/2 መሠረት የሕገ-መንግሥት ማሻሻያ ማድረግ፦ ይህ አማራጭ በሕገ-መንግሥቱ ውስጥ በግልጽ የተቀመጠ የማስፈጸሚያ ሥነ ሥርዓት ያለው እና አሁን ለገባንበት አጣብቂኝ የማያዳግም ምላሽ የሚሰጥ ሆኖ አግኝተነዋል።
ምንም እንኳን ኢዜማ በሕገ-መንግሥቱ ውስጥ ሊሻሻሉ የሚገባቸው በርካታ አንቀጾች እንዳሉ በፅኑ ቢያምንም፥ አሁን ያለንበት ወቅት ሁሉን አቀፍ ሕገ-መንግሥታዊ ማሻሻያ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል አይደለም። አሁን ለገባንበት ሕገ-መንግሥታዊ አጣብቂኝም ቀልጣፋ ምላሽ የሚሰጥ አይደለም። በኢዜማ እምነት ሁሉን አቀፍ ሕገ-መንግሥታዊ ማሻሻያ ለማድረግ ሀገራዊ መረጋጋት፣ በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት እና ሰፊ ሕዝባዊ ተሳትፎ የሚጠይቅ ነው። እንዲሁም በከፍተኛ በጥንቃቄ ሊሠራ እንደሚገባው ሀገራዊ ጉዳይ በዚህ ወቅት ሊከወን አይገባም ብለን እናምናለን። ሆኖም አሁን የገጠመንን አጣብቂኝ ለመሻገር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱን የሥራ ዘመን እና ምርጫ የሚደረግበትን ወቅት የሚደነግገው አንቀጽ 58ን ጊዜውን ጠብቆ ምርጫ ለማድረግ የማያስችል ድንገተኛ እና ከአቅም በላይ የሆነ ችግር በሚያጋጥምበት ጊዜ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከ1 ዓመት ላልበለጠ ጊዜ ምርጫውን ማራዘም እና ምርጫው እስኪደረግ ድረስ ዘላቂ ውጤት ያላቸውን እና በቀጣይ ምርጫውን አሸንፎ ሥልጣን በሚይዘው መንግሥት ላይ ተጨማሪ ኃላፊነትን የሚጥሉ ተግባራትን ከመከወን በከለከለ መልኩ የመንግሥትን ቀጣይነት በግልፅ የሚደነግግ አድርጎ በማሻሻል ቀጥተኛ፣ ሕገ-መንግሥታዊ፣ የማያዳግም እና ተቀባይነት ያለው መፍትሄ መስጠት አስፈላጊ ሆኖ አግኝተነዋል።
በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 105/2 ሀ እና ለ መሠረት የሕዝብ ተወካዮች እና የፌደሬሽን ምክር ቤቶች በጋራ ስብሰባ በ2/3ኛ ድምፅ ማሻሻያውን ሲያጸድቁ እንዲሁም ከክልል ምክር ቤቶች ውስጥ 2/3ኛ ክልሎች (6 ክልሎች) በአብላጫ ድምፅ ሲያጸድቁት በሕገ-መንግሥቱ ምዕራፍ 3 ስር ከሚገኙት እና አንቀጽ 104 እና 105 ውጪ ያሉትን የሕገ-መንግሥት አንቀጾች ማሻሻል እንደሚቻል ተደንግጓል። በዚሁ መሠረት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱን የሥራ ዘመን እና ምርጫ የሚደረግበትን ወቅት የሚደነግገው አንቀጽ 58/3 ከላይ በተገለጸው መሠረት ማሻሻል የተሻለ መፍትሄ እንደሆነ እናምናለን።
ይህ መፍትሄ ተግባራዊ ከተደረገ በሥራ ላይ ያለውን ሕገ-መንግሥት ተከትሎ የሚፈፀም በመሆኑ ሕገ ምንግሥታዊ ጥያቄ የሚያስነሳ አይሆንም። እንዲሁም በቅርቡ ልናደርገው ከምናስበው ምርጫ እና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አንፃርም አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል ብለን እናምናለን። በዚህ አማራጭ ላይ በተለያዩ አካላት የሚነሳው ጥያቄ በዚህ የወረርሽኝ ወቅት በአንቀጽ 104 ድንጋጌ መሠረት ህዝብን ለማወያየት አያስችልም የሚል ሲሆን ይህንን ክፍተት ግን ሕዝቡን በወኪሎቹ አማካኝነትና በተለያዩ የቴክኖሎጂ አማራጮች በማወያየት መሸፈን ይቻላል።
ከዚህ ቀደም በሕገ-መንግሥቱ ውስጥ የጋራ የታክስ እና የግብር ሥልጣንን የሚደነግገው አንቀጽ 98 እና የሕዝብ ቆጠራን በሚመለክት የሚካሄድበት የጊዜ ገደብን የሚደነግገው አንቀጽ 103/5 በሕገ-መንግሥቱ የተጠቀሰውን የማሻሻያ ሥነ ሥርዓት ሙሉ በሙሉ ሳይከተሉ ለየብቻ በተለያየ ጊዜ ማሻሻያ ተደርጎባቸው እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፥ አሁን መደረግ ያለበት ማሻሻያ ግን የሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 104 እና 105/2 ያስቀመጡትን ድንጋጌዎች በሙሉ አሟልቶ ሊሆን እንደሚገባው እናምናለን።
ይህ የሕገ-መንግሥት ማሻሻያ ተግባራዊ የሚደረግ ከሆነ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተጨማሪ የክልል ምክር ቤቶችንና የፌድሬሽን ምክር ቤትንም የሥልጣን ዘመን በሚያራዝም መልኩ መተግበር አለበት።
የፓርቲያችን እምነት የሕገ-መንግሥቱን አንቀጽ 58/3 ማሻሻል የተሻለ አማራጭ ነው የሚል ቢሆንም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከላይ በተራ ቁጥር 2.3 ላይ የጠቀስነውን አማራጭ በመውሰድ የሕገ-መንግሥቱን አንቀጥ 54/1፤ 58/3 እና 93 ላይ ትርጉም እንዲሰጥ ለፌደሬሽን ምክር ቤት እንደመራው ታውቋል። ምንም እንኳን ኢዜማ ይህንን አማራጭ የተሻለ አማራጭ ነው ብሎ ባያምንም አማራጩ ተግባራዊ የሚደረግ ከሆነ የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔው ሕገ-መንግሥቱን በሚተረጉምበት ወቅት ከመንግሥትም ሆነ ከሌላ ማንኛውም አካል ተፅዕኖ ነፃ ሆኖ ተግባሩን ማከናወን አለበት። የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ በሚያቀርበው የውሳኔ ሀሳብ የፌደሬሽን ምክር ቤት የሚያጸድቀው ትርጉም የመንግሥትን ሥልጣን በማንኛውም መልኩ የሚያራዘም ከሆነ ማራዘሚያውን እጅግ ቢገፋ ከ1 ዓመት እንዳይበልጥ ማድረግ አለበት። ውሳኔው በዚህ የማራዘሚያ ወቅት ሥልጣን ላይ የሚቆየው መንግሥት ዘላቂ ውጤት ያላቸውን እና በቀጣይ ምርጫውን አሸንፎ ሥልጣን በሚይዘው መንግሥት ላይ ተጨማሪ ኃላፊነትን የሚጥሉ ተግባራትን ከመፈፀም እንዲቆጠብ የሚያስገድድ መሆንም አለበት።
በአጠቃላይ እንደሀገር የሚወሰዱ ማንኛውም አማራጮች አሁን ያለንበትን አስቸጋሪ እና ፈታኝ ወቅት ከግምት ያስገቡ፣ የሀገር መረጋጋት፣ ሰለም እና ቀጣይነትን የሚያረጋግጡ፣ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሂደቱን የሚያስቀጥሉ እንዲሁም አሁን ከገባንበት ሕገ-መንግሥታዊ አጣብቂኝ በአስተማማኝ ሁኔታ የሚያስወጡን መሆን እንዳለባቸው ኢዜማ ለማሳሰብ ይወዳል። በተጨማሪም በተመሳሳይ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚወሰኑ ውሳኔዎች የተለያየ አመለካከት ካላቸው የፖለቲካ ኃይሎች ጋር በሚደረግ ውይይት መዳበራቸው መፍጠር የምንፈልገውን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንድንለማመድ በር የሚከፍት እና ሁሉንም ኃይሎች የባለቤትነት ስሜት እንዲሰማን የሚያደርግ በመሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተመሳሳይ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ በቂ እና ቀጣይነት ያለው ውይይት የምናደርግበት መድረክ እንዲመቻች ጥሪ እናቀርባለን።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)
ሚያዝያ 28 ቀን 2012 ዓ.ም
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያMay 5, 2020 at 12:19 am #14365AnonymousInactiveከሚያዝያ 23 እስከ 25 ቀን 2012 ዓ.ም. በወቅታዊ ሀገራዊ እና ክልላዊ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት ተሰብስቦ የነበረው የህወሓት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባውን ሲያጠናቅቅ ባለ አምስት ነጥብ ውሳኔዎችን አሳልፏል።
ከህወሓት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ
የህወሓት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከሚያዝያ 23 እስከ 25 ቀን 2012 ዓ.ም. በክልላችንና በሀገራችን እንዲሁም በንዑስ ቀጣናው የተከሰቱ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን በስፋት በመመርመር የውሳኔ ሃሳቦችን አሳልፏል። ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በክልላችን እየተከናወኑ ያሉ የሰላምና የልማት፣ የመልካም አስተዳደር፣ የክልላችንና የሕዝባችን ድኅንነት የመታደግ ሥራዎችን እንዲሁም የኮረናን ወረርሽኝ ለመመከት የተሠሩ ሥራዎች በሚመለከት በዝርዝር የተወያየበት ሲሆን፣ እስካሁን የታዩ ጥንካሬዎችን ጠብቆ ለማቆየትና የታዩ ጉድለቶችን ለማረም የተሠሩ ሥራዎችን በመመርመር ውሳኔዎችን አሳልፏል። በክልላችን ያሉ ወይም የሚኖሩ ፈተናዎች ለመመከት አሁንም ወሳኙ ውስጣዊ ጥንካሬያችን መሆኑን በድጋሚ በማረጋገጥ በዚህ ረገድ የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ስምምነት ላይ ተደርሷል።
የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በሦስት ቀን ስብሰባው በስፋት ከመከረባቸው ጉዳዮች ዋነኛው በሀገር ደረጃ በብልፅግና ፓርቲ እየተካሄደ መጥቶ አሁን በመጨረሻ ደረጃ ላይ የደረሰውን ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት የመናድ ዘመቻ የሚመለከተው አጀንዳ የጎላ ትኩረት የተሰጠው ነበር። ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በዝርዝር ተወያይቶ እንዳስቀመጠው የብልፅግና ፓርቲ ቀድሞውኑም ለማከናወን ሙሉ ፈቃደኝነት ያላሳየበትን ሀገራዊ ምርጫ የCOVID-19 ወረርሽኝ መከሰትን እንደመልካም አጋጣሚ በመቁጠር በአንድ ሰው የሚመራ አምባገነን ሥርዓትን ለመትከልና ከሕገ-መንግሥታዊ መንገድ ውጪ የሥልጣን ዕድሜን ለማራዘም የተጀመረውን ጥረት አጠናክሮ ቀጥሎበታል። ባለፉት ጥቂት ቀናት በግልፅ እንደታየው የፓርቲዎችን ሃሳብ ለመቀበል በሚል በተጠራ የይስሙላ መድረክ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያለቀለት ያሉትን ሃሳብ ማጠናቀቂያ ክፍል ምን ሊመስል እንደሚችል በግልፅ አመላክተዋል።
የህወሓት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ይህ ያለበቂ ዝግጅትም ሆነ ያለግልፅ አጀንዳ የተጠራውና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሕግ ውጭ በሥልጣን ለመቀጠል ያላቸውን ፍላጎት ያሳዩበት መድረክ ተከትሎ በፓርላማው የተጀመረውና ሕግን ያላግባብ በመተርጎም የብልፅግና ፓርቲን ሕገ-ወጥ የስልጣን ዕድሜ የማራዘም እንቅስቃሴ ፍፁም ተቀባይነት እንደሌለው በድጋሚ አስምሮበታል። አሁንም ሥልጣን ላይ ባለው ኣካል የተጀመረውና ሕገ-መንግሥትን መተርጎም በሚል ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት የመናድ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ እንደተደረሰ ግልፅ ሆኗል።
በዚህም መሠረት የህወሓት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የሚከተሉተን ውሳኔዎች አሳልፏል።
- የብልፅግና ፓርቲ ሕገ-መንግሥቱን ለመተርጐም በሚል ሰበብ የተጀመረው ገሀድ የወጣ እንቅስቃሴ በአስቸኳይ እንዲያቆም። ሕገ-መንግሥታዊ ትርጓሜ የሚያስፈልገው ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት ባስቀመጠው ግልፅ መስፈርት መሠረት አሻሚ ሁኖ ለተገኙ አንቀፆች እንጂ የአንድን ስብስብ የሥልጣን ዕድሜ ከሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት ውጭ ለማራዘም ሊሆን አይችልም። በመሆኑም ይህንን ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት ሙሉ በሙሉ ለማፍረስ እየተደረገ ያለው ጥድፍያ በአስቸኳይ ቆሞ አሁንም የኮረና ወረርሽኝን በተቀናጀ መልኩ ለመከላከልም ሆነ ሀገራዊ ምርጫን ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱ በሚፈቅደው ማእቀፍ ውሰጥ በመሆን ለማከናወን በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ሁሉም ፓርቲዎች በሙሉ የባለቤትነት መንፈስ እንዲሳተፉ ተደርጎ ሀገርን ከለየለት የጥፋት አደጋ ለመታደግ እንዲቻል መድረክ እንዲመቻች ይጠይቃል።
- የእንደዚህ ዓይነቱ መድረክ አስፈላጊነት እንደተጠበቀ ሆኖ የብልፅግና ፓርቲ ነፃና ግልፅ ምርጫ የመምራት ምንም ዓይነት ሞራላዊ ብቃት የሌለው በመሆኑ ይህንን ለማስፈፀም የሚችል የተለየ አደረጃጀት የመፍጠር አስፈላጊነት ላይ ስምምነት ላይ ተደርሶ የሀገርን ሉዓላዊነትና ሰላም ለማስከበር አስፈላጊነት በቂ ትኩረት በሰጠ መልኩ ምርጫውን ለማከናወን የሚያስችል ዝግጅት እንዲጀመር ጥሪውን ያቀርባል።
- ይህ ሳይሆን ቀርቶ ወትሮውኑም ገዢውን ፓርቲ በሕገ-ወጥ መንገድ አፍርሶ ራሱን በወራሽነት ያስቀመጠው የብልፅግና ፓርቲ ከመስከረም 25 ቀን 2012 ዓ.ም. በኋላ በሥልጣን ላይ ለመቆየት የሚያስችለው ጠባብም ቢሆን ዕድል የማይኖር በመሆኑ የሀገሪቱ ችግር ለመፍታት ወደሚከብድ ችግር የምትገባበት ዕድል መፈጠሩ የማይቀር ይሆናል። ህወሓት እንደዚሁ ዓይነቱ ክስተት ሊፈጥረው የሚችለውን ትርምስ ለማስወገድ በሚደረጉ ሀገራዊ ጥረቶች ውስጥ ድርሻውን በቀናነት ለመጫወት ዝግጁ ቢሆንም የትግራይ ሕዝብ በመስዋዕትነቱ በተከለው ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት የተረጋገጠለትን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት እንደዋዛ እንዲጣልበት አይፈቅድም። ለዚህም ሲባል ከትግራይ ሕዝብና ለትግራይ ሕዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ሙሉ ዕውቅና ከሚሰጡ የፖለቲካ ኃይሎች ጋር በመሆን ክልላዊ ምርጫን ጨምሮ ይህንኑ የሕዝባችንን መብት ከትርምስ ለመታደግ የሚያስችሉ ሥራዎችን በክልል ደረጃ ለማድረግ ዝግጅት እንዲደረግ ወስኗል። ይህ እንቅስቃሴ የፀረ ኮረና ወረርሽኝ ዘመቻችንን እንዲሁም ተቀባይነት ያላቸውን ሕገ-መንግሥታዊ መርሆዎችን ባሟላ መልኩ የሚፈፀም ይሆናል።
- የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የተወካዮች ምክር ቤት እንዲሁም የፌደሬሽን ምክር ቤት አባላት ህልውናቸው ያረጋገጠውን ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት በጠራራ ፀሀይ ለማፍረስ የሚደረገውን እኩይ ተግባር በማስቆም ከታሪክ ተጠያቂነት ራሳቸውን እንዲያርቁ በዚህ አጋጣሚ የህወሓት ሥራ አስፈፃሚ ጥሪውን ያቀርባል።
- በመጨረሻም ህወሓት ሆነ የትግራይ ሕዝብ የሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓታችን ያረጋገጠውን ሕብረ-ብሔራዊ ፌዴራላዊ ሥርዓት ለማዳን በሚደረገው ርብርብ መሰል አጀንዳ ከሚያራምዱ ብሔር ብሔረሰቦችም ሆነ የፖለቲካ ኃይሎች ጋር ለመታገል ዝግጁ መሆናችንን አሁንም በድጋሚ ማረጋገጥ እንፈልጋለን።
የህወሓት ማዕከላይ ኮሚቴ ጽ/ቤት
ሚያዝያ 26 ቀን 2012 ዓ.ም.December 5, 2018 at 6:48 pm #8826SemonegnaKeymasterኢትዮጵያዊያን አያሌ የሚያስተሳስሯቸው ነገሮች ያሏቸው በመሆኑ የሚያለያዩዋቸውን ጥቂት ነገሮች በመቻቻል አንድነታቸውን የሚያጎለብቱ ጉዳዮችን ጎልቶ እንዲወጣ የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል አስተዋጽኦ ያበረክታል ተብሏል።
አዲስ አበባ (ኢ.ፕ.ድ) – የዘንድሮ የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል ከልዩነት በላይ ለሕዝቦች አንድነት መጠናከር ትኩረት እንደሚሰጥ የፊዴሬሽን ምክር ቤት ገለፀ።
የፊታችን ህዳር 29 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀን በአዲስ አበባ ከተማ የሚከበረው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል ዝግጅት መጠናቀቁንም ምክር ቤቱ አስታውቋል።
ዘንድሮ ለ13ኛ ጊዜ የሚከበረውን በዓል ከልዩነት በላይ ለሕዝቦች አንድነት መጠናከር ትኩረት እንደሚሰጥ በምክር ቤቱ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ገብሩ ገብረሥላሴ በተለይ ለኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢ.ቢ.ሲ) ተናግረዋል። በዚህም ብሔረሰቦች የራሳቸውን ባህል ከማስተዋወቅ በዘለለ የባህል ልውውጥ የሚያደርጉበት መድረክ እንደሚፈጠር ገልፀዋል።
በዚህም አንዱ ብሔር የሌላውን ባህል እንዲያንፀባርቅ በማድረግ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ እንዲጎለብት ይደረጋል ሲሉ ተናግረዋል ዳይሬክተሩ አቶ ገብሩ።
ኢትዮጵያዊያን አያሌ የሚያስተሳስሯቸው ነገሮች ያሏቸው በመሆኑ የሚያለያዩዋቸውን ጥቂት ነገሮች በመቻቻል አንድነታቸውን የሚያጎለብቱ ጉዳዮችን ጎልቶ እንዲወጣ በዓሉ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል።
አቶ ገብሩ አክለውም ዘንድሮ በአዲስ አበባ የሚከበረው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን የዝግጅት ሥራዎች ተጠናቀው የበዓሉ ተሳታፊዎች እየተጠበቁ መሆኑን ገልፀዋል። በበዓሉ ዕለትም በክልሎች ብሎም በሀገር አቀፍ ደረጃ ሲምፖዚየሞች፣ የተለያዩ ውይይቶችና ዝግጅቶች እንደሚካሄዱም ይጠበቃል ብለዋል።
በበዓሉ በሚካሄዱ ውይይቶች ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በግጭቶች መንስዔ ዙሪያ ምክክር ተደርጎ የመፍትሄ ሀሳቦች እንዲቀመጡም እንደሚደረግ አቶ ገብሩ አመላክተዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢፌዲሪ) ሕገ-መንግስት የፀደቀበት ቀን የሆነው ህዳር 29 ቀን‹‹በብዝሃነት የደቀመ ኢትዮጵያዊ አንድነት›› በሚል መሪ ቃል ዘንድሮ ይከበራል።
በበዓሉ ቅድመ ዝግጅት ወቅትም የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቶችን የሚያጠናክሩ የሰላም ጉባኤዎች በተለያዩ ክልሎች ሲካሄዱ መቆየታቸውንም ምክር ቤት አስታውቋል። ባለፈው ዓመት 12ኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል በአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ዋና ከተማ በሆነችው ሰመራ መከበሩ ይታወሳል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት (ኢ.ፕ.ድ) | ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
October 25, 2018 at 3:08 am #8238Topic: አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ የመጀመሪያዋ የኢፌዴሪ ሴት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ
in forum Semonegna StoriesSemonegnaKeymasterአዲስ አበባ (ሰሞነኛ ኢትዮጵያ) – የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌደሬሽን ምክር ቤቶች ጥቅምት 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ባካሄዱት ልዩ ስብሰባቸው አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴን 4ኛው የኢትዮጵያ ርዕሰ ብሄር (ፕሬዝዳንት) አድርጎ በሙሉ ድምፅ መርጧል።
ፕሬዝዳት ሳህለወርቅ ዘውዴ ቃለ መሃላ ፈፅመው ኃላፈነታቸውን በትጋትና በታኝነት አገርና ህዝብን ለማገልገል ቃል ገብተዋል።
አምባሳደር ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ላለፉት አመስት ዓመታት በፕሬዝዳንትነት ላይ የነበሩትን ዶ/ር ሙላቱ ተሾመን በመተካት አገሪቱን በፕሬዝዳንትነት የሚመሩ ይሆናል። ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመም ከተመራጯ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ጋር የስልጣን ርክክብ አድርገዋል።
አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ ማን ናቸው?
ተወልደው ያደጉት አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ሲሆን የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት በሊሴ ገብረማርያም ትምህርት ቤት ነው። አራት ሴት ልጆች ለነበሯቸው ወላጆቻቸው የመጀመሪያ ልጅ የሆኑት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገና በ17 ዓመታቸው ነጻ የትምህርት ዕደል አግኝትው ወደ ፈረንሳይ በማቅናት ሞንትፔልየር (Montpellier) በምትባለው የፈረንሳይ ከተማ በሚገኘው ዮኒቨርሲቲ ኦፍ ሞንትፔልየር (University of Montpellier) የተፈጥሮ ሳይንስን አጥንተዋል። በሀገረ ፈረንሳይ ለዘጠኝ ዓመታት ከቆዩ በኋላ ወደ ኢትዮጵይ በመመለስ በትምህርት ሚኒስቴር ውስጥ የሕዝብ ግንኙነት ክፍልን ማገልገል ጀመሩ። ቆይተውም የሕዝብ ግንኙነት ክፍሉን በበላይነት መርተዋል። ከዚያም ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመዘዋወር በተለያዩ የሥራ ኃላፊነቶች አገልግለዋል።
ወሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ በአምባሳደርነት ለመሾም ከአምባሳደር ዮዲት እምሩ ቀጥሎ ሁለተኛዋ እንስት ናቸው። በመጀመሪያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው የተሾሙትም ሴኔጋል ሲሆን የአምባሳደርነት ስልጣናቸውም ሴኔጋልን ጨምሮ ማሊን፣ ኬፕ ቨርዴን፣ ጊዚ ቢሳውን፣ ጋምብያን እና ጊኒን (እ.ኤ.አ 1989–1993) ያጠቃልል ነበር። ቀጥሎም እ.ኤ.አ 1983–2002 በጅቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደርና በኢጋድ (IGAD) የኢትዮጵያ ተጠሪ ሆነው አገልግለዋል። እ.ኤ.አ ከ2002 ጀምሮ እስከ 2006 ድረሰ በፈረንሳይ (ሞሮኮን ጨምሮ) የኢትዮጵያ አምባሳደርና በዩኔስኮ (UNESCO) የኢትዮጵያ ተጠሪ ሆነው አገልግለዋል። እ.ኤ.አ ከ2006 ጀምሮ እስከ 2009 ድረስ በአፍሪካ ህብረት (AU) እና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (UNECA) የኢትዮጵያ ተጠሪ ሆነው ሀገራቸውን አገልግለዋል።
ከሀያ ዓመታት በላይ በተለያዩ ሀገራትና ዓለማቀፋዊ ድርጅቶች የኢትዮጵያ አምባሳደርና ተጠሪ በመሆን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤትን ያገለገሉት አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ እ.ኤ.አ በ2009 የተበባሩት መንግስታት ድርጅትን (ተመድ) በመቀላቀል የድርጅቱ በመካከለኛው አፍሪካ ሪፑብሊክ የተቀናጀ ሰላም ግንባታ መሪ (Head BINUCA) በመሆን ማገልገል ጀመሩ። ይህ አገልግሎታቸውም ወደ ሚቀጥለው ኃላፊነት አሸጋግሯቸው እ.ኤ.አ በ2011 ዓም የዚያን ጊዜ የተመድ ጠቅላይ-ጸሀፊ ባን ኪ-ሙን (Ban Ki-moon) አዲስ ለተቋቃመው በናይሮቢ የተመድ ጽህፈት ቤት (UNON) የመጀመሪያዋ ጠቅላይ-መሪ አድርገው ሾማቸው። በዚያም ለሰባት ዓመታት ካገለገሉ በኋላ እ.ኤ.አ በሰኔ ወር 2010 የአሁኑ የተመድ ጠቅላይ-ጸሀፊ አንቶንዮ ጉቴሬስ (António Guterres) አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴን በተመድ ጠቅላይ-መሪ ስር (Under-Secretary-General) የአፍሪካ ህብረት ልዩ ተጠሪ (UN’s Special Representative to the AU) እና በአፍሪካ ህብረት ውስጥ የተመድ ጽህፈት ቤት ዋና ኃላፊ (Head of UNOAU) አድርገው ሾሟቸው እስካሁን ድረስ በዚሁ ሹመታቸው እያገለገሉ ይገኛሉ።
አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ ባለትዳርና የሁለት ወንድ ልጆች እናት ናቸው።
-
AuthorSearch Results
Search Results for 'ፌደሬሽን ምክር ቤት'
-
Search Results
-
ኢትዮጵያዊያን አያሌ የሚያስተሳስሯቸው ነገሮች ያሏቸው በመሆኑ የሚያለያዩዋቸውን ጥቂት ነገሮች በመቻቻል አንድነታቸውን የሚያጎለብቱ ጉዳዮችን ጎልቶ እንዲወጣ የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል አስተዋጽኦ ያበረክታል ተብሏል።
አዲስ አበባ (ኢ.ፕ.ድ) – የዘንድሮ የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል ከልዩነት በላይ ለሕዝቦች አንድነት መጠናከር ትኩረት እንደሚሰጥ የፊዴሬሽን ምክር ቤት ገለፀ።
የፊታችን ህዳር 29 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀን በአዲስ አበባ ከተማ የሚከበረው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል ዝግጅት መጠናቀቁንም ምክር ቤቱ አስታውቋል።
ዘንድሮ ለ13ኛ ጊዜ የሚከበረውን በዓል ከልዩነት በላይ ለሕዝቦች አንድነት መጠናከር ትኩረት እንደሚሰጥ በምክር ቤቱ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ገብሩ ገብረሥላሴ በተለይ ለኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢ.ቢ.ሲ) ተናግረዋል። በዚህም ብሔረሰቦች የራሳቸውን ባህል ከማስተዋወቅ በዘለለ የባህል ልውውጥ የሚያደርጉበት መድረክ እንደሚፈጠር ገልፀዋል።
በዚህም አንዱ ብሔር የሌላውን ባህል እንዲያንፀባርቅ በማድረግ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ እንዲጎለብት ይደረጋል ሲሉ ተናግረዋል ዳይሬክተሩ አቶ ገብሩ።
ኢትዮጵያዊያን አያሌ የሚያስተሳስሯቸው ነገሮች ያሏቸው በመሆኑ የሚያለያዩዋቸውን ጥቂት ነገሮች በመቻቻል አንድነታቸውን የሚያጎለብቱ ጉዳዮችን ጎልቶ እንዲወጣ በዓሉ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል።
አቶ ገብሩ አክለውም ዘንድሮ በአዲስ አበባ የሚከበረው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን የዝግጅት ሥራዎች ተጠናቀው የበዓሉ ተሳታፊዎች እየተጠበቁ መሆኑን ገልፀዋል። በበዓሉ ዕለትም በክልሎች ብሎም በሀገር አቀፍ ደረጃ ሲምፖዚየሞች፣ የተለያዩ ውይይቶችና ዝግጅቶች እንደሚካሄዱም ይጠበቃል ብለዋል።
በበዓሉ በሚካሄዱ ውይይቶች ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በግጭቶች መንስዔ ዙሪያ ምክክር ተደርጎ የመፍትሄ ሀሳቦች እንዲቀመጡም እንደሚደረግ አቶ ገብሩ አመላክተዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢፌዲሪ) ሕገ-መንግስት የፀደቀበት ቀን የሆነው ህዳር 29 ቀን‹‹በብዝሃነት የደቀመ ኢትዮጵያዊ አንድነት›› በሚል መሪ ቃል ዘንድሮ ይከበራል።
በበዓሉ ቅድመ ዝግጅት ወቅትም የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቶችን የሚያጠናክሩ የሰላም ጉባኤዎች በተለያዩ ክልሎች ሲካሄዱ መቆየታቸውንም ምክር ቤት አስታውቋል። ባለፈው ዓመት 12ኛው የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል በአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ዋና ከተማ በሆነችው ሰመራ መከበሩ ይታወሳል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት (ኢ.ፕ.ድ) | ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ ኢትዮጵያ) – የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌደሬሽን ምክር ቤቶች ጥቅምት 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ባካሄዱት ልዩ ስብሰባቸው አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴን 4ኛው የኢትዮጵያ ርዕሰ ብሄር (ፕሬዝዳንት) አድርጎ በሙሉ ድምፅ መርጧል።
ፕሬዝዳት ሳህለወርቅ ዘውዴ ቃለ መሃላ ፈፅመው ኃላፈነታቸውን በትጋትና በታኝነት አገርና ህዝብን ለማገልገል ቃል ገብተዋል።
አምባሳደር ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ላለፉት አመስት ዓመታት በፕሬዝዳንትነት ላይ የነበሩትን ዶ/ር ሙላቱ ተሾመን በመተካት አገሪቱን በፕሬዝዳንትነት የሚመሩ ይሆናል። ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመም ከተመራጯ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ጋር የስልጣን ርክክብ አድርገዋል።
አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ ማን ናቸው?
ተወልደው ያደጉት አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ሲሆን የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት በሊሴ ገብረማርያም ትምህርት ቤት ነው። አራት ሴት ልጆች ለነበሯቸው ወላጆቻቸው የመጀመሪያ ልጅ የሆኑት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገና በ17 ዓመታቸው ነጻ የትምህርት ዕደል አግኝትው ወደ ፈረንሳይ በማቅናት ሞንትፔልየር (Montpellier) በምትባለው የፈረንሳይ ከተማ በሚገኘው ዮኒቨርሲቲ ኦፍ ሞንትፔልየር (University of Montpellier) የተፈጥሮ ሳይንስን አጥንተዋል። በሀገረ ፈረንሳይ ለዘጠኝ ዓመታት ከቆዩ በኋላ ወደ ኢትዮጵይ በመመለስ በትምህርት ሚኒስቴር ውስጥ የሕዝብ ግንኙነት ክፍልን ማገልገል ጀመሩ። ቆይተውም የሕዝብ ግንኙነት ክፍሉን በበላይነት መርተዋል። ከዚያም ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመዘዋወር በተለያዩ የሥራ ኃላፊነቶች አገልግለዋል።
ወሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ በአምባሳደርነት ለመሾም ከአምባሳደር ዮዲት እምሩ ቀጥሎ ሁለተኛዋ እንስት ናቸው። በመጀመሪያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው የተሾሙትም ሴኔጋል ሲሆን የአምባሳደርነት ስልጣናቸውም ሴኔጋልን ጨምሮ ማሊን፣ ኬፕ ቨርዴን፣ ጊዚ ቢሳውን፣ ጋምብያን እና ጊኒን (እ.ኤ.አ 1989–1993) ያጠቃልል ነበር። ቀጥሎም እ.ኤ.አ 1983–2002 በጅቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደርና በኢጋድ (IGAD) የኢትዮጵያ ተጠሪ ሆነው አገልግለዋል። እ.ኤ.አ ከ2002 ጀምሮ እስከ 2006 ድረሰ በፈረንሳይ (ሞሮኮን ጨምሮ) የኢትዮጵያ አምባሳደርና በዩኔስኮ (UNESCO) የኢትዮጵያ ተጠሪ ሆነው አገልግለዋል። እ.ኤ.አ ከ2006 ጀምሮ እስከ 2009 ድረስ በአፍሪካ ህብረት (AU) እና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (UNECA) የኢትዮጵያ ተጠሪ ሆነው ሀገራቸውን አገልግለዋል።
ከሀያ ዓመታት በላይ በተለያዩ ሀገራትና ዓለማቀፋዊ ድርጅቶች የኢትዮጵያ አምባሳደርና ተጠሪ በመሆን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤትን ያገለገሉት አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ እ.ኤ.አ በ2009 የተበባሩት መንግስታት ድርጅትን (ተመድ) በመቀላቀል የድርጅቱ በመካከለኛው አፍሪካ ሪፑብሊክ የተቀናጀ ሰላም ግንባታ መሪ (Head BINUCA) በመሆን ማገልገል ጀመሩ። ይህ አገልግሎታቸውም ወደ ሚቀጥለው ኃላፊነት አሸጋግሯቸው እ.ኤ.አ በ2011 ዓም የዚያን ጊዜ የተመድ ጠቅላይ-ጸሀፊ ባን ኪ-ሙን (Ban Ki-moon) አዲስ ለተቋቃመው በናይሮቢ የተመድ ጽህፈት ቤት (UNON) የመጀመሪያዋ ጠቅላይ-መሪ አድርገው ሾማቸው። በዚያም ለሰባት ዓመታት ካገለገሉ በኋላ እ.ኤ.አ በሰኔ ወር 2010 የአሁኑ የተመድ ጠቅላይ-ጸሀፊ አንቶንዮ ጉቴሬስ (António Guterres) አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴን በተመድ ጠቅላይ-መሪ ስር (Under-Secretary-General) የአፍሪካ ህብረት ልዩ ተጠሪ (UN’s Special Representative to the AU) እና በአፍሪካ ህብረት ውስጥ የተመድ ጽህፈት ቤት ዋና ኃላፊ (Head of UNOAU) አድርገው ሾሟቸው እስካሁን ድረስ በዚሁ ሹመታቸው እያገለገሉ ይገኛሉ።
አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ ባለትዳርና የሁለት ወንድ ልጆች እናት ናቸው።