Search Results for 'አዲስ አበባ'

Home Forums Search Search Results for 'አዲስ አበባ'

Viewing 15 results - 46 through 60 (of 495 total)
  • Author
    Search Results
  • Anonymous
    Inactive

     ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የምርጫ ውጤት

    ሰኔ 14 ቀን፥ 2013 ዓ.ም. የተካሄደው የስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውጤት ይፋ ተደረገ። ይህ ውጤት የሚገለፀው ባገኙት ወንበር ልክ ሲሆን በዚህም መሠረት፦

    • የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር
      – መስተዳድሩ ያለው የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ: 23
      – ሰኔ 14 ቀን ምርጫ የተከናወነበት የተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ክልል ብዛት: 23
      □ ብልፅግና ፓርቲ ያገኘው መቀመጫ: 22
      □ የግል ተወዳዳሪ ያገኘው መቀመጫ: 1
    • የአፋር ብሔራዊ ክልል
      – ክልሉ ያለው የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ: 8
      – ሰኔ 14 ቀን ምርጫ የተከናወነበት የተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ክልል ብዛት: 6
      □ ብልፅግና ፓርቲ ያገኘው መቀመጫ: 6
    • የአማራ ብሔራዊ ክልል
      – ብሔራዊ ክልሉ ያለው የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ: 138
      – ሰኔ ቀን ምርጫ የተከናወነበት የተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ክልል ብዛት: 125
      □ ብልፅግና ፓርቲ ያገኘው መቀመጫ: 114
      □ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ፓርቲ ያገኘው መቀመጫ: 5
      – ድጋሚ ቆጠራ የሚከናወንበት ምርጫ ክልል ብዛት: 1
      – ድጋሚ ምርጫ የሚከናወንበት ምርጫ ክልል ብዛት: 5
    • የቤኒሻንጉል-ጉሙዝ ብሔራዊ ክልል
      – ብሔራዊ ክልሉ ያለው የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ: 9
      – ሰኔ 14 ቀን ምርጫ የተከናወነበት የተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ክልል ብዛት: 3
      □ ብልፅግና ፓርቲ ያገኘው መቀመጫ: 3
      – ድጋሚ ምርጫ የሚከናወንበት ምርጫ ክልል ብዛት: 2
    • የድሬዳዋ ከተማ መስተዳድር
      – መስተዳድሩ ያለው የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ: 2
      – ሰኔ 14 ቀን ምርጫ የተከናወነበት የተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ክልል ብዛት: 2
      □ ብልፅግና ፓርቲ ያገኘው መቀመጫ: 1
      – ድጋሚ ቆጠራ የሚከናወንበት ምርጫ ክልል ብዛት: 1
    • የጋምቤላ ብሔራዊ ክልል
      – ብሔራዊ ክልሉ ያለው የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ: 3
      – ሰኔ 14 ቀን ምርጫ የተከናወነበት የተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ክልል ብዛት: 3
      □ ብልፅግና ፓርቲ ያገኘው መቀመጫ: 3
    • የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል
      – ብሔራዊ ክልሉ ያለው የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ: 178
      – ሰኔ 14 ቀን ምርጫ የተከናወነበት የተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ክልል ብዛት: 170
      □ ብልፅግና ፓርቲ ያገኘው መቀመጫ: 167
      □ የግል ተወዳዳሪዎች ያገኙት መቀመጫ: 3
    • የሲዳማ ብሔራዊ ክልል
      – ብሔራዊ ክልሉ ያለው የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ: 19
      – ሰኔ 14 ቀን ምርጫ የተከናወነበት የተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ክልል ብዛት: 19
      □ ብልፅግና ፓርቲ ያገኘው መቀመጫ: 19
    • የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ብሔራዊ ክልል
      – ብሔራዊ ክልሉ ያለው የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ: 104
      – ሰኔ 14 ቀን ምርጫ የተከናወነበት የተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ክልል ብዛት: 85
      □ ብልፅግና ፓርቲ ያገኘው መቀመጫ: 75
      □ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ ያገኘው መቀመጫ: 4
      □ የጌዴኦ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት: 2
      – ድጋሚ ቆጠራ የሚከናወንበት ምርጫ ክልል ብዛት: 1
      – ድጋሚ ምርጫ የሚከናወንበት ምርጫ ክልል ብዛት: 3

    በዚህ ሐምሌ 3 ቀን፥ 2013 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ባደረገው የምርጫ ውጤት መሠረት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመቀመጫ ብዛት በአጠቃላይ 484 ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ በስልጣን ላይ የሚገኘው ብልፅግና ፓርቲ 410 መቀመጫ አሸንፏል። ይህም ውጤት ፓርቲውን መንግሥት ለመመሥረት ያስችለዋል።

    ይህን የምርጫ ውጤት እና የፓርቲያቸው ማሸነፍን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ያስተላለፉትን መልዕክት ለማንበብ እዚህ ጋር ይጫኑ

    የምርጫ ክርክር የምርጫ ውጤት

    Anonymous
    Inactive

    አዋሽ ባንክ እ.ኤ.አ. በ2020/21 የሂሣብ ዓመት ብር 5.58 ቢሊዮን ዓመታዊ ትርፍ አስመዘገበ

    አዲስ አበባ (አዋሽ ባንክ) – ላለፉት አምስት ተከታታይ ዓመታት ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ የግል ባንኮች የመሪነት ስፍራውን ይዞ የቆየው አዋሽ ባንክ አሁን በተገባደደው የሂሣብ ዓመትም በዋና ዋና የባንኪንግ ዘርፎች የመሪነት ስፍራውን ይዞ መቀጠሉን ሰኔ 29 ቀን 2013 ዓ.ም ባካሄደው ዓመታዊ የበጀት መዝጊያ ስብሰባ ላይ አስታውቋል።

    ባንኩ በተጠናቀቀው ሂሣብ ዓመት ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ የተቀማጭ ሂሣብ መጠን በማስመዝገብ በባንኩም ሆነ በግል ባንኮች ታሪክ የመጀመሪያው የሆነውን ውጤት አስመዝግቧል። የባንኩ አጠቃላይ ተቀማጭ ሂሣብ ኤልሲ ማርጅንን (letter of credit margin) ጨምሮ ብር 107.7 ቢሊዮን ሲሆን፣ ይህም አሀዝ ከባለፈው ሂሣብ ዓመት ተመሣሣይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የብር 33.8 ቢሊዮን /የ46 በመቶ/ ዕድገት አሣይቷል።

    አዋሽ ባንክ ባሣለፍነው የሂሣብ ዓመት 100 አዳዲስ ቅርንጫፎችን ከፍቶ ለአገልግሎት ማብቃት የቻለ ሲሆን፤ ከሁለት ሚሊዮን በላይ አዳዲስ የተቀማጭ ሂሣብ ደንበኞችን በማፍራት ጠቅላላ የተቀማጭ ሂሣብ ደንበኞቹን ከ5 ሚሊዮን በላይ ማድረስ ችሏል። የቅርንጫፎች መስፋፋት ሕብረተሰባችን በየአካባቢው የባንክ አገልግሎቶችን እንዲያገኝ ከማስቻሉም በተጨማሪ አዳዲስ ደንበኞች የቁጠባ ባህላቸውን እንዲያሳድጉ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል። አዋሽ ባንክ ሕብረተሰቡ በቦታና በጊዜ ሳይገደብ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ የኤቲኤም (ATM)፣ የሞባይል እና የኢንተርኔት አገልግሎቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ባደረገው ጥረት እ.ኤ.አ. ሰኔ 2021 መጨረሻ ላይ 4 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ አድርጓል። ይህም መንግሥት የፋይናንስ አካታችነትን እና ተደራሽነትን ለማስፋፋት የሚያደርገውን ብርቱ ጥረት አጋዥ እንደሆነ ይታመናል።

    አዋሽ ባንክ ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች የሰጠው ብድር መጠን በ2020/21 የሂሣብ ዓመት መጨረሻ ላይ የብር 30 ቢሊዮን /የ53 በመቶ/ እድገት በማሣየት ብር 87.1 ቢሊዮን ደርሷል።

    በውጭ ምንዛሪ ረገድም በ2020/21 የሂሣብ ዓመት ከተለያዩ የውጭ ምንዛሪ ምንጮች ከ906 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ማግኘት የቻለ ሲሆን፤ ይህም አሀዝ ከአምናው ተመሣሣይ ጊዜ አንጻር የ37 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ጭማሪ አሳይቷል። ለዚህም ዋና ዋና ምክንያቶች የአለም ኢኮኖሚ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተጽዕኖ ማገገም፣ የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ማደግ እና ባንኩ የወሰዳቸው የተለያዩ የፖሊሲ እርምጃዎች ናቸው።

    አዋሽ ባንክ ከዛሬ 5 ዓመት በፊት በኢትዮጵያ የግል ባንኮች ታሪክ ከብር 1 ቢሊዮን በላይ ያልተጣራ ትርፍ አስመዝግቦ ታሪክ እንደሠራው ሁሉ ባሳለፍነው በጀት ዓመትም ከብር 5.58 ቢሊዮን በላይ ያልተጣራ ትርፍ በማስመዝገብ ሌላ ታሪክ ሠርቷል። ለዚህም ዋናው ምክንያት የባንኩ ገቢ አምና ከነበረበት ከብር 10.2 ቢሊÄን ወደ ብር 13.7 ቢሊዮን ማደጉ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ።

    ባንኩ በተቀማጭ ሂሣብ፣ በብድር እና በትርፋማነት ብቻ ሳይሆን በተከፈለ ካፒታል መጠኑም የመሪነት ሥፍራውን እንደያዘ ቀጥሏል። የአዋሽ ባንክ የተከፈለ ካፒታል በዓመቱ በብር 2.23 ቢሊዮን ያደገ ሲሆን፤ እ.ኤ.አ. ሰኔ 2021 መጨረሻ ላይ ብር 8.2 ቢሊዮን ደርሷል። ይህ መጠን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሁሉም ነባር የግል ባንኮች ለወደፊቱ በ5 ዓመት ጊዜ ውስጥ እንዲደርሱበት ካስቀመጠው የ5 ቢሊዮን ብር መጠን በእጅጉ የላቀ ነው። አዋሽ ባንክ በአሁኑ ጊዜ በ566 ቅርንጫፎች እና ከ12 ሺህ በላይ በሆኑ ሠራተኞች አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።

    በየዓመቱ ከፍተኛ በጀት በመመደብ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን በመወጣት የሚታወቀው አዋሽ ባንክ እ.ኤ.አ. በ2020/21 የሂሣብ ዓመት በተለያዩ የማኅበረሰብ ልማት ሥራዎች እና በበጎ አድራጎት ሥራዎች ላይ ለተሰማሩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ከብር 30 ሚሊዮን በላይ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉ ይታወሳል።

    ምንጭ፦ awashbank.com

    አዋሽ ባንክ

    Anonymous
    Inactive

    ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

    ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን ) የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ
    ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣
    ለሁሉም የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሉች፤
    የኢትዮጵያ ጉዳይ ለሚያሳስባችሁ አፍሪካውያን ወንድሞቻችንና ዓለምአቀፍ አጋሮቻችን፤
    በመላው ዓለም ለምትገኙ ሰላም ወዳድ ኃይሎች በሙሉ !

    የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በሰኔ 26 እና 27 ቀን 2013 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ጥልቅና ዙሪያ መለስ ውይይት በማድረግና፤

    • የሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ፖለቲካ መሠረት ለመጣልና በሕዝብ ይሁንታ ብቻ ሥልጣን የሚይዝ ሥርዓት ለመፍጠር የተደረገውን 6ኛውን ሀገራዊ የምርጫ ሂደት በመገምገም፤
    • የታላቁን የአባይ ግድብን በማጠናቀቅና እንደ ሀገር የተፈጥሮ ፀጋችንን ተጠቅመን የመልማት መብታችንን ለማረጋገጥ በተያያዝነው ጥረት ረገድ የተጋረጡብንን ተግዳሮቶች በመገንዘብ፤
    • ሕዝባችን በሰላምና ደህንነት እጦት፣ በኮቪድ-19 ወረርሽኝና መረን በለቀቀ የኑሮ ውድነት እየደረሰበት ያለውን ምጣኔ ሀብታዊ ድቀት ግምት ውስጥ በማስገባት፤
    • ከሁሉም በላይ ሀገራችን ከውስጥ በከሃዲያንና እኩያን ኃይሎች ቅንጅት፣ ከውጭ በታሪካዊ ጠላቶቻችንና ዓለምአቀፍ አጋሮቻቸው አይዞህ ባይነትና ድጋፍ የተደቀነባትን የህልውና ስጋት ተቀዳሚ ትኩረት በመስጠት፤

    የፓርቲው ሥራ አስፈፃሚ የደረሰባቸውን አቋሞች ለተከበረው ሕዝባችን፣ ለአፍሪካውያን ወንድሞቻችንና በአጠቃላይም ለዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ለማሳወቅ ይወዳል።

    1. ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ በተመለከተ

    አብን እንደ ድርጅት የመጀመሪያው አብይ የፖለቲካ ተመክሮው በሆነው በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ውስጥ ለመሳተፍ ሲያቅድ፥ ገና ከመነሻው ሀገራችን የምትገኝበትን የፖለቲካ አውድ በመገምገም በምርጫው የመሳተፉን ውሳኔ ያደረገው በዋነኝነት ከድርጅታዊ ፋይዳዎች ይልቅ ለሀገራዊ ፖለቲካው መረጋጋትና ለዴሞክራሲያዊ ተመክሮ ግንባታ ከሚኖረው ፋይዳ አንፃር እንደሆነ በይፋ አሳውቋል።

    አብን ሀገራዊ ፓርቲ እንደመሆኑ መጠን የምርጫ ዘመቻውን ስትራቴጂክ ግቦችና ማስፈፀሚያ ስልቶችን በዝርዝር በመንደፍ፣ አማራጭ ፖሊሲዎቹን በማኒፌስቶ በመሰነድና ሙሉ ድርጅታዊ ኃይሉን በማንቀሳቀስ በምርጫ በሚሳተፍባቸው በአማራና ሌሎችም የሀገሪቱ ክፍሎች 510 እጩዎችን በማቅረብ ሰፊውን መራጭ ሕዝብ ለመድረስ ያልተቆጠበ ጥረት አድርጓል።

    በዚህም መሠረት የምርጫ ዘመቻው ከነተግዳሮቶቹ ተጠናቅቆ፣ በሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ፓርቲያችን በሚወዳደርባቸው ክልሎች ድምፅ ተሰጥቶና በከፊል ጊዜያዊ ውጤት ተገልጾ በድኅረ ምርጫ ሂደት ላይ እንገኛለን።

    ፓርቲያችን በመላ ሀገሪቱ በተወዳደረባቸው አካባቢዎች በምርጫው ሂደት የተፈፀሙትን አበይት ጥሰቶች በማሰባሰብና በዝርዝር ቅሬታዎችን በመሰነድ በህግ አግባብ ለብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አቅርቧል። የምርጫ ቦርድ ከተጣለበት ታላቅ ሀገራዊ ኃላፊነት አኳያ ከሰው፣ ከፋይናንስ፣ ከተመክሮና ከሎጂስቲክ አቅም ውሱንነት ቢታይበትም በአጠቃላይ ከቅድመ ምርጫው ጀምሮ አንፃራዊ አዎንታዊነት እንዳሳየ እናምናለን። በቦርዱ የበላይ አመራር የታየው ገለልተኝነት፣ ግልፅነትና ፍትሃዊነት መንፈስ እንደ ተቋም የሚፈተንበት ወቅት እንደሆነም እንገነዘባለን።

    የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ ሕዝባችን ይህንን ሁሉ ጫና ተቋቁሞ በምርጫው ሂደት ውስጥ በመሳተፍ ላሳየው ፅናት ልባዊ አድናቆቱን በመግለፅ፣ የመራጩ ድምፅ እንዲከበር ተገቢውን ሰላማዊና ህጋዊ ጥረት እንደሚያደርግና የሕዝባችንንም ሀቀኛ ውሳኔ ያለማወላወል እንደሚቀበል ለማሳወቅ ይወዳል።

    በሌላ በኩል 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ የሥርዓቱን እውነተኛ ባህርይ በተግባር መፈተንና ማጋለጥ መቻሉን ትልቁ ውጤት አድርጎ መውሰድ ይቻላል። በምርጫው ሂደት የታየው ጎዶሎነትና ክፍተት ከምርጫ ውጤት አኳያ የምንመዝነው ከሆነ የሀገራችንን ተጨባጭ ሁኔታና የሃሳብ ብዝሃነት የማያመለክት መሆኑን መናገር ይቻላል።

    አብን እንደ ድርጅት በምርጫ በመሳተፉ ምን አገኘ፣ አሳካ የሚለውን ስንገመግም አንዳንድ ተስፋ ሰጭ ነገሮች እንዳሉ መካድ አይቻልም። ከሁሉም በላይ የሕዝባችን እውነተኛ ወኪል ስለመሆናችን ሕዝባችን የነበሩትን ጫናዎች ተቋቁሞ በሰጠን የመተማመኛ ድምፅ በቂ ማረጋገጫ አግኝተናል። ይህም የመጪው ዘመን ፓርቲ መሆናችንን ይመሰክራል። በሐገር አቀፍ ድረጃ በተሻለ ሕዝብን የማስተባበር አቅም እንዳለንና ጠንካራ ተገዳዳሪ የፖለቲካ ኃይል መሆናችንን በማያሻማ ሁኔታ አረጋግጠናል።

    የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ የምርጫው ሂደት አጠቃላይ ድርጅታዊ ቁመናውን የሚፈትሽበት መልካም አጋጣሚ መሆኑንም ይገነዘባል። በቀጣይም ከሂደቱ ያገኛቸውን ተመክሮዎችና ትምህርቶች በማካተትና ሁለገብ የማሻሻያ እርምጃዎች በመውሰድ ለብሔራዊ ፖለቲካችን ሁነኛ ሚና መጫወቱን እንደሚቀጥል አያጠራጥርም።

    1. ብሔራዊ ደህንነትን በተመለከተ

    የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ በተለይ በሀገር ሉዓላዊነትና አንድነት፣ በሕዝብ ጥቅምና ክብር፣ በሀገረ መንግሥቱ ቀጣይነት ረገድ ግልፅና የማያሻማ አቋም ያራምዳል። በገዥው ፓርቲ ግልፅ ፍረጃ፣ ወከባና ጥቃት እየደረሰበትም ቢሆን የፖለቲካ ማዕከሉ እንዲረጋጋና በአፍሪካ ረዥሙንና ደም አፋሳሹን የእርስ በርስ ጦርነት ያደረገች ሀገር ተመልሳ ወደ ቀውስ እንዳትገባ ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል።

    አብን ወቅታዊው የሀገራችን ብሔራዊ ደህንነት ከጊዜ ጊዜ እየከፋና እጅግ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ይገነዘባል። የውጭ ወራሪዎችና የውስጥ ቦርቧሪዎች ከተቻለ ኢትዮጵያን ለየዘውጉ አምበሎች በታትኖ ከዓለም ካርታ ለማጥፋት፤ ካልሆነ ደግሞ ውስጣዊ አንድነት የሌላት፣ ደካማና ፍላጎታቸውን ያለማንገራገር የምትቀበል አድርገው ለማሽመድመድ እየተረባረቡ ይገኛሉ።

    ከዚህ አንፃር የብልጽግና አገዛዝ የሀገሪቱን፣ የዜጎችና የመንግሥቱን ሰላምና ደህንነት፣ ጥቅምና ክብር በማስጠበቅ ረገድ ጉልህ ክፍተቶች እየተስተዋለበት ነው። በአሁኑ ወቅት መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ባደረገው ከፍተኛ ተጋድሎ ከአፈናና ጭቆና መንበሩ የተባረረውና በሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ በአማራ እና አፋር ልዩ ኃይልና ሕዝባዊ ሚሊሺያ ድባቅ የተመታው የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግንባር (ትህነግ) ተመልሶ በማንሰራራት በብሔራዊ ደህንነታችን ላይ ተቀዳሚ አደጋ ሊሆን በቅቷል።

    አብን ማዕከላዊ መንግሥትና በየደረጃው ያሉ መንግሥታዊ አካላት ሀገሪቱ ከተደቀነባት የህልውና አደጋ ለመታደግ በሚደረገው ርብርብ የራሳቸውን ሚና በግልፅ ከመወሰን አንስቶ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያካተተ የብሔራዊ ደህንነት እርምጃ እንዲወስዱ ጥሪ ያቀርባል።

    መንግሥት ልዩ የደህንነት ስጋት ያለባቸው አካባቢዎች ላይ ትኩረት እንዲያደርግ፤ በተለይም አሸባሪው የትህነግ ቡድን መልሶ በተቆጣጠረው በትግራይ የተማሪዎችንና የሲቪል ዜጎችን፤ በአጠቃላይም የትግራይን ሕዝብ ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ይጠይቃል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በትግራይ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ተመድበው ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙ ተማሪዎች ሁኔታ አብንን በእጅጉ ያሳስበዋል። የትግራይ ሕዝብ በመካከሉ ለሚገኙ ተማሪ ልጆቹ አስፈላጊውን ጥበቃና ክብካቤ እንዲያደርግ ጥሪ እናደርጋለን።

    አብን መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ሀገር ወዳድ ዜጎችና በተለይም ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል ሀገራችን ስለገጠማት የብሔራዊ ደህንነት አደጋ ግልፅ ግንዛቤ እንዲኖራቸውና ኢትዮጵያን ለመታደግ በአንድነት እንዲሰለፉ ጥሪ ያደርጋል።

    በወታደራዊ ኃይል የሚገኘው ድል ዳግም በዲፕሎማሲው አውድማ እንዳይነጠቅ መላው ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን የሀገራቸው አምባሳደር በመሆን በዓለምአቀፍ የዲፕሎማሲ ትግል እንዲሳተፉ ጥሪ ያቀርባል።

    በተለይም ደግሞ በፀረ – ኢትዮጵያው ጎራ በጠላትነት ተፈርጆ ዘርፈ ብዙ ጥቃት የተሰነዘረበት የአማራ ሕዝብ የሚገኝበትን ወቅታዊ የስጋት ደረጃ በውል ተገንዝቦ የበኩሉን ጥንቃቄና ዝግጅት እንዲያደርግ፣ የአማራ ዲያስፖራ በሕዝባችንና በሀገራችን ላይ የተቃጣውን አደጋ ለመቀልበስ ሁለገብ የሃሳብ፣ የፋይናንስ፣ የዲፕሎማሲ ተሳትፎውን አጠንክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ያቀርባል።

    አብን አፍሪካውያን ወንድሞቻችን፣ መላው የኢትዮጵያ ወዳጆችና አጋሮች የጥንታዊ ሥልጣኔ፣ አኩሪ የነፃነት ታሪክ ያላት ሀገር በእኩያን ኃይሎች የተከፈተባትን ወታደራዊ፣ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ጥቃት ለመመከት ከጎናችን እንዲሰለፉ ጥሪ ያደርጋል። በዚህ ረገድ በአካባቢው ጉዳይ ትኩረት አድርገው የሚንቀሳቀሱ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ዓለምአቀፍ ተቋማት በአፍራሽ የሀሰት ፕሮፓጋንዳ እንዳይደለሉና የችግሩን ዙሪያ ገብ በፍትሃዊነት በመገምገም እንዲንቀሳቀሱ ጥሪ ያቀርባል።

    የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ በሀገራችን ላይ የተደቀነውን ፅኑ የብሔራዊ ደህንነት ስጋት ለመመከትና ከምንም በላይ የቆመለትን የሀገር አንድነትና ሉዓላዊነት፣ የሕዝብ ጥቅምና ክብር እንዲሁም የሀገረ መንግሥቱን ቀጣይነት ለማረጋገጥ የሚጠበቅበትን ሁሉ ድርጅታዊ አስተዋፅኦ ለማድረግ ቁርጠኝነቱን በአፅንኦት ለመግለፅ ይወዳል።

    የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)
    አዲስ አበባ፣ ሸዋ፣ ኢትዮጵያ
    ሰኔ 28 ቀን 2013 ዓ.ም

    ምንጭ፦ አብን

    የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ

    Anonymous
    Inactive

    ትግራይ ክልል – የሲቪል ሰዎችን ሁኔታ ለማሻሻል አፋጣኝ እርምጃዎች ሊወሰዱ ይገባል

    አዲስ አበባ (ኢሰመኮ) – የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ሰኔ 21 ቀን፥ 2013 ዓ.ም. የፌዴራል መንግሥት በትግራይ ክልል የተኩስ አቁም ማወጁን ተከትሎ የግንኙነት መሰመሮች በመቋረጣቸው፣ በክልሉ ነዋሪዎች የሚገኙበት ሁኔታ እንደሚያሳስበውና መንግሥት የነዋሪዎችን ደኅንነት ለማስጠበቅ የሚረዱ እርምጃዎች በአፋጣኝ ሊወስድ እንደሚገባ ገለጸ። በክልሉ የተቋረጡ መሠረታዊ አገልግሎቶችን መመለስና በትግራይ ክልል ስላለው ተጨባጭ የፀጥታ ሁኔታና የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት በቂ መረጃ መስጠት፣ በዚህ ረገድ ያሉ ክፍተቶችን ለማረምና የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ትብብር ለመፍጠር ቀዳሚ እርምጃዎች ናቸው።

    ለግጭቱ ሰላማዊ መፍትሔ ለማፈላለግ የሚደረገው ጥረት አስፈላጊነት እንደተጠበቀና በክልሉ ለሚደረጉ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦቶች ጥበቃና ለተደራሽነቱ ትብብር እንደሚቀጥል መገለጹ የሚበረታታ ሆኖ፣ የሲቪል ሰዎች ደኅንነትና ሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል። በአሁኑ ወቅት በአብዛኛዎቹ የትግራይ አከባቢዎች የመብራት፣ የስልክ እና የውሃ አገልግሎት በመቋረጡ በክልሉ ነዋሪዎች ላይ ከባድ የኑሮ ጫና እያስከተለ ይገኛል። የባንክ አገልግሎት መቋረጥና የጤና አገልግሎት አቅርቦትና ተደራሽነት ውሱንነት ችግሩን አባብሶታል።

    በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሱ ሀገራዊና ዓለምአቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች የኤሌክትሪክ እና የስልክ አገልግሎት መቋረጥን ጨምሮ የሌሎች አቅርቦቶች እጥረት የሰብዓዊ ድጋፉን በከፍተኛ ደረጃ እንደጎዳውና በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ ነዋሪዎች፣ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና ስደተኞች ስለሚገኙበት ሁኔታ ማወቅ አስቸጋሪ እንዳደረገው ይገልጻሉ።

    በአዲስ አበባ ከተማ የትግራይ ክልል ተወላጅ የሆኑ ነዋሪዎችና የሚዲያ ሰዎችን ጨምሮ፣ ሌሎች ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል ተጠርጥረው የታሰሩ ሰዎችን ሁኔታ ኮሚሽኑ በመከታተል ላይ ይገኛል። ይህም በነዋሪዎች ላይ ማንነትን በመለየት ለጥርጣሬ እና መድልዎ የሚያጋልጥ ተግባር እንዳይሆን ስጋት የሚያሳድር ነው።

    በተጨማሪም፥ በክልሉ ዩኒቨርሲቲዎች የሚማሩ ወጣቶች ወላጆችና ቤተሰቦች ተማሪዎቹ በአሁኑ ወቅት ስለሚገኙበት ሁኔታ ተገቢው ምላሽ እና ማብራሪያ እንዲሰጣቸው የሚመለከታቸውን የመንግሥት አካላት በመጠየቅ ላይ ይገኛሉ።

    የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ የነዋሪዎችን ደኅንነት ማረጋገጥ ቀዳሚው የመንግሥት ግዴታ መሆኑን አስታውሰው፥ “በክልሉ የሚገኙ ነዋሪዎች ስላሉበት ሁኔታ የተገቢው መረጃ ማነስ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ከሚደመጡ ዘገባዎችና ንግግሮች ጋር ተዳምሮ ነዋሪዎችን ስጋት ላይ የሚጥል ነው። የተኩስ አቁሙ በሁሉም በግጭቱ ተሳታፊ በነበሩ ወገኖች ሁሉ በቁርጠኝነት መከበር እና የመሠረታዊ አገልግሎቶች በአፋጣኝ መመለስ፣ አጠቃላይ ሁኔታውን ለማሻሻል፣ በትግራይ ክልል ለተፈጠረው ችግር ዘላቂ መፍትሔ ለማፈላለግ፣ እንዲሁም ሰብዓዊ አቅርቦቱ እንዳይቋረጥ የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ነው። በተጨማሪም ማንኛውም አይነት እስር ሁልጊዜም ሕጋዊ ሥርዓትን የተከተለ ሊሆን ይገባል” ብለዋል። ዋና ኮሚሽነሩ አክለውም በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል የሚገኙ የመንግሥት እና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት ሁሉ ሁኔታውን የሚያባብሱ፣ በሕዝቦች መካከል ጥላቻና ጥርጣሬን ሊፈጥሩ ከሚችሉ ንግግሮች እንዲቆጠቡ ጥሪ አቅርበዋል።

    ምንጭ፦ ኢሰመኮ

    ትግራይ ክልል – የሲቪል ሰዎችን ሁኔታ ለማሻሻል አፋጣኝ እርምጃዎች ሊወሰዱ ይገባል – ኢሰመኮ

    Anonymous
    Inactive

    በ2013 ዓ.ም. ሀገራዊ ምርጫ ድምጽ መስጫ ቀን የተደረገ የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ክትትል (ቀዳሚ ሪፖርት)
    የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)

    በ2013 ዓ.ም. ሀገራዊ ምርጫ የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ላይ የታዩ ክፍተቶች በተገቢው የሕግ እና የአሠራር ማሻሻያ ሊታረሙ ይገባል

    የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከሰኔ 12 እስከ ሰኔ 16 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ ምርጫ በተካሄደባቸው በሁሉም ክልሎች በሚገኙ የተመረጡ አካባቢዎች ተንቀሳቃሽ የክትትል ቡድን በማሰማራት ያጠናቀረውን የሰብዓዊ መብቶች ክትትል ሪፖርት ይፋ ሲያደርግ፤ ክትትሉ በተከናወነባቸው የተወሰኑ የምርጫ ጣቢያዎችና አካባቢዎች የተመለከታቸው ክፍተቶች ተገቢው ትኩረት እንዲያገኙና አስፈላጊውን የሕግና የአተገባበር መፍትሔ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ገለጸ።

    ኮሚሽኑ ለሀገራዊ ምርጫ 2013 ዓ.ም. ባለ6 ነጥብ የሰብዓዊ መብቶች አጀንዳ ይፋ በማድረግና ለሰብዓዊ መብቶች ትኩረት እንዲሰጥ ከመወትወት በተጨማሪ፥ በቅድመ ምርጫውና በምርጫው ቀን የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ክትትል ሲያከናውን ቆይቷል። በተለይም ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ፣ የመዘዋወር፣ የመሰብሰብ እና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብቶችን በተመለከተና የሴቶችን ተሳትፎ ማሳደግ፣ እንዲሁም ምርጫው የአካል ጉዳተኞችን እና የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ያሳተፈና ለእነሱ ተደራሽ የሆነ በማድረግ ረገድ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ክትትል ሲያደርግ ቆይቷል።

    በዚህም መሠረት 94 ባለሞያዎችን ያካተተው ቡድን በአጠቃላይ በአዲስ አበባ፣ በድሬዳዋ ከተሞችና በሁሉም ምርጫ በተካሄደባቸው ክልሎች በሚገኙ 99 የምርጫ ክልሎችና 404 የምርጫ ጣቢያዎች ተዘዋውሮ፥ የአካባቢውን አስተዳደር፣ ነዋሪዎችን፣ የፀጥታ ኃይሎችን እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮችን፣ እጩዎችንና አባላት እንዲሁም የምርጫ አስፈጻሚ አካላትና ሌሎች ባለድርሻዎችን አነጋግሯል። በዋና ጽሕፈት ቤቱ በተመደቡ ባለሞያዎች አማካኝነት በ7037 የስልክ ቁጥሩ ጥቆማዎችንና አቤቱታዎችን ተቀብሎ አስተናግዷል።

    ምርጫው የተካሄደበት አውድ በሀገር ውስጥ የተደራረቡ ችግሮች የገጠሙበት እና በትግራይ ክልል የተከሰተውን ግጭት ጨምሮ በሌሎችም አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶች ባሉበት፥ በተወሰኑ አካባቢዎች በጸጥታ ችግር ምርጫው እንዲተላለፍ አስገዳጅ በሆነበት፣ የተወሰኑ የፖለቲካ ቡድኖች እራሳቸውን ከምርጫው ሂደት ባገለሉበት፣ ሌሎች የፖለቲካ ቡድን አመራሮች በቀረበባቸው የወንጀል ክስ ምክንያት በእስር በሚገኙበት ወቅት መሆኑ የማይዘነጋ መሆኑንና ከግምት ውስጥ ማስገባት እንደሚገባ ኮሚሽኑ ገልጿል። ይህ ተግዳሮት እንዳለ ሆኖ፤ ኢሰመኮ በምርጫው መዳረሻ ቀናት እና በምርጫው ዕለት ክትትል ባደረገባቸው  አካባቢዎች የተወሰኑ የሰብዓዊ መብቶች አጠባበቅ ክፍተት የታየ ቢሆንም፤ በአብዛኛዎቹ ቦታዎች  የጎላ ወይም የተስፋፋ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት እንዳልታየ ገልጾ፤ ክትትል ባደረገባቸው በአብዛኛዎቹ አካባቢዎች የምርጫው ዕለት ሂደት ያለ የጎላ ችግር በሰላም ተጀምሮ የተጠናቀቀና በሰብዓዊ መብቶች አጠባበቅ ረገድ በብዙ መልኩ የተሳካ የድምጽ አሰጣጥ ሂደት እንደነበር አሳውቋል። በተጨማሪም በምርጫው ሂደት በሕጋዊና ሰላማዊ መንገድ ለተሳተፉና አስተዋጽኦ ላደረጉ ወገኖች ሁሉ እውቅና ሰጥቶ፤ በቀሪው ሂደትም በሕጋዊና ሰብዓዊ መብቶችን ባከበረ መንገድ እንዲቀጥሉ ጥሪውን በድጋሚ አቅርቧል።

    እነዚህን አዎንታዊና አበረታች እርምጃዎች እንደተጠበቁ ሆነው፥ በተወሰኑ የምርጫ ክልሎች እና ጣቢያዎች ከምርጫው ዕለት ጥቂት ቀናት በፊት፣ በምርጫው ዕለትና ከምርጫው ቀን በኋላ የደረሰ የሰው ሕይወት መጥፋትና የአካል ጉዳት፣ ተገቢ ያልሆነ እስር፣ በመራጮች ላይ የደረሰ ማስፈራራት፣ በምርጫ ታዛቢዎችና ጋዜጠኞች ላይ ስለደረሰ መጉላላትና ማዋከብ፣ የምርጫው ሂደት ለአካል ጉዳተኛ ሰዎች ያለው ተደራሽነትና የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን የተሳትፎ መጠን በሚመለከት ባወጣው የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት አስረድቶ፤ ሊወሰዱ ስለሚገባቸው እርምጃዎች ምክረ ሃሳብ ሰጥቷል።

    በተጨማሪም ጥፋተኛ በሆኑ ሰዎች ላይ በአፋጣኝ ምርመራ በማድረግ ተጠያቂነታቸው እንዲረጋገጥ እና ኮሚሽኑ በሕግ የተሰጠውን በምርጫ ወቅት የሰብዓዊ መብቶች ክትትል የማድረግ ኃላፊነቱንና ተግባሩን በአግባቡ እንዳይወጣ የሚያግዱ፣ የሚገድቡ ወይም የሚያሰናክሉ ሁኔታዎች በተለይም የምርጫ ጣቢዎችን ያለ እንቅፋት የመጎብኘት አስፈላጊነት እና የእስር ቦታዎችን ያለ ቅድሚያ ማስታወቂያ የመጎብኘት አስፈላጊነት በሚመለከት ለወደፊቱ ማናቸውም ዓይነት እንቅፋት እንዳይከሰት ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ተገቢውን እርምጃ እንዲወስዱና ሁሉም ሰዎችና ተቋማት ለኮሚሽኑ ሥራ የመተባበር ግዴታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ አሳስቧል።

    ኢሰመኮ ያወጣውን ሪፖርት እዚህ ጋር በመጫን ያግኙ።

    ምንጭ፦ ኢሰመኮ

    በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ድምጽ መስጫ ቀን የተደረገ የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ክትትል

    Anonymous
    Inactive

    ከባልደራስ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ
    ኢትዮጵያ መቼ ይሆን ነፃ፣ ፍትሀዊና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ የሚኖራት?!

    ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ከተመሠረተ ጊዜ ጀምሮ ፍትህ እንዲሰፍን ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ፣ አድሎአዊነትና ዘረኝነት እንዲወገድ፣ ሕዝብ ከመፈናቀልና ከድህነት እንዲላቀቀቅ፣ አዲስ አበባ የራስ ገዝ አስተዳደር እንድትሆን እና ሌሎችም ዲሞክራሲያዊ መብቶች እንዲሰፍኑ የሚያስችል ሥርዓት ለማምጣት ጠንክሮ ሠርቷል፤ እየሠራም ነው። የሀገሪቱ መሪ “ከባልደራስ ጋር ግልጽ ጦርነት እንከፍታለን” እያሉ በተናገሩበት ወቅት እንኳን ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ከመታገል ቁርጠኛ አቋሙ ወደ ኋላ አላለም።

    ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) በ6ኛው ሀገር አቀፍ ቅድመ ምርጫ ሂደት (pre-election process) ላይ በተለያዩ ጊዜያት ሳይንሳዊ ጥናቶች አካሂዶ ዝቅተኛውን ዓለም አቀፍ የምርጫ መስፈርት የማያሟላ መሆኑን አረጋግጧል። የምርጫ ሂደቱ የተበላሸ ከሆነ ውጤቱም በተመሳሳይ መንገድ ሊሆን እንደሚችል የሚጠበቅ ቢሆንም ባልደራስ በኢትዮጵያ ሰላም ለማስፈን የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማበርከት ሲል በምርጫው የተሳተፈ መሆኑን ለማሳወቅ እንወዳለን።

    ፓርቲያችን ከአራት ወራት በፊት ጀምሮ ባካሄዳቸው ከፍተኛ የምርጫ እንቅስቃሴዎች ወቅት ሕዝብ ከጎኑ መሆኑን በተለያዩ መንገዶች አረጋግጧል። አዲስ አበቤ ለድርጅታችን ባሳየው ደጀንነትም ፓርቲያችን እጅጉን ኮርቷል። ያነሳነውን አዲስ አበባን ራስ ገዝ የማድረግ ጉዞ ሕዝባችን ከጎናችን በመሆን ስለሰጠን ድጋፍ ከልብ እናመሰግናለን። ለሰጣችሁንም ድምፅ ምስጋናችን ከፍ ያለ ነው። ይህንኑ ወደ ፊትም አጠናክረን እንደምንሄድ በዚሁ አጋጣሚ እንገልፃለን ።

    ዓላማችንን ከግብ ለማድረስ ደከመኝ፣ ሰለቸኝ ሳትሉ፥ ዕውቀታችሁን፣ ጊዜያችሁን፣ ገንዘባችሁንና ልዩ ልዩ ቁሳቁሶችን ጭምር የለገሳችሁ የፓርቲው አመራሮች፣ የሕዝብ ተወካዮችና የአዲስ አበባ ምክር ቤቶች እጩዎች፣ የምርጫው የቅስቀሳና የሎጂስቲክስ አካላት፣ የባልደራስ የዴሞክራሲ ማዕዘን በመሆን የምርጫውን ሂደት ከሁለት ቀንና ሌሊት በላይ የተከታተላችሁ ወኪሎቻችን እና በተለያዩ እንቅስቃሴዎቻችን ላይ የተሳተፋችሁ ሁሉ የላቀ ምስጋና የምናቀርብላችሁ በታላቅ ደስታ ነው። በሰሜን አሜሪካ፣ በአውሮፓ እና በሌሎችም ዓለማት የምትኖሩ የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ የድጋፍ ሰጭ ኮሚቴ እና የአማካሪ ቦርድ አባላት ላደረጋችሁት ሁሉን አቀፍ ድጋፍ፣ ምክር እና አስተዋፆኦ ምስጋናችን እጅጉን ከፍ ያለ ነው።

    “አዲስ አበባን ማዳን ኢትዮጵያን ማዳን ነው” በሚል ዓላማ የጀመርነውን ጉዞ ገዥው ፓርቲ መሪዎቻችንን በማሰር ለማሰናከል ጥረት አድርጓል። ነገር ግን ትግሉ የተነሳበትን ዓላማ ይበልጥ ከፍ አድርጎ በመቀጠሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች የሚገዙት ሃሳብ ሆኗል። በሀገር ውስጥ ያላችሁ አባላት እና በውጭ ሀገር የምትኖሩ ድጋፍ ሰጭዎች የተሸረበውን ሴራ በጣጥሳችሁ በመውጣት፣ በሰላማዊ ትግሉ ፋና ወጊ የሆኑ መሪዎችን ቀንዲል ከፍ ብሎ እንዲታይ ያደረጋችሁ ናችሁና በድጋሚ የባልደራስ አመራር በእናንተ ደስታና ኩራት እንደሚሰማው ይገልጻል ።

    በባልደራስ ፓርቲ ቅድመ ምርጫ ሂደት ጥናት እንደተረጋገጠው በብዙ ውጥንቅጥ ውስጥ የታጀበው ዝቅተኛውን የምርጫ መመዘኛ ደረጃዎች ያላሟላው የሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ምርጫ የመጣውን ውጤት ማሳየት ችሏል። እንደሌሎቹ ጊዜዎች ሁሉ የዘንድሮውንም ምርጫ ነፃ፣ ፍትሃዊ እና ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ ከመንግሥት በኩል ምንም ቁርጠኝነት አለመኖሩን ፓርቲያችን ተገንዝቧል።

    ከምርጫው ቀን ዋዜማ ጀምሮ በአዲስ አበባ ነዋሪ ላይ የፍርሃት ድባብ ለመፍጠር በከፍተኛ ደረጃ የታጠቁ የፓሊስ እና የመከላከያ አባላት የጦር መሣሪያቸውን ወድረው በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር የሥነ ልቦና ጫና ሲፈጥሩ ሰንብተዋል። ይህም “ሊበሏት ያሰቧትን አሞራ ይሏታል ጅግራ” እንደሚባለው በምርጫው ሰሞን ከነበሩ ኢ-ዲሞክራሲያዊ ትዕይንቶች አንዱ ነበር።

    ምርጫውን ነፃ፣ ፍትሃዊ እና ዴሞክራሲያዊ ማድረግ ጠቀሜታው በሥልጣን ላይ ላለው መንግሥት እና ተወዳድረው ለማሸነፍ ለሚፎካከሩት ፓርቲዎች ብቻ ሳይሆን ለሚወክሉት ሕዝብ ጭምር መሆኑ ይታወቃል። ምርጫው ነፃ፣ ፍትሃዊ እና ዴሞክራሲያዊ ሳይሆን ሲቀር የሕዝብ ነፃነት ይገፈፋል፤ ሥርዓት አልበኝነት ይነግሣል። በዜጐች መካከል የደረጃ ልዩነት እና መሰል ችግሮች ተፈጥረው ሕዝብ በፍርሃት አረንቋ ውስጥ ይወድቃል። እነዚህን ችግሮችን ለማስወገድ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ከፍተኛ ኃላፊነት ያለበት መሆኑ ይታወቃል።

    በ6ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ የተከሰቱ ችግሮችን ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ በጥልቀት እየመረመረው ይገኛል። እስካሁን በደረሰበት ሁኔታ ምርጫው ነፃ፣ ፍትሃዊ እና ዴሞክራሲያዊ አልነበረም የሚል መደምደሚያ ላይ የሚያደርሱ ተግባራት መኖራቸውን ፓርቲያችን ያምናል። ለአብነትም፡-

    1. ድምፅ አሰጣጥን በተመለከተ ግንዛቤ ለመስጠት የተሰየሙት የምርጫ አስፈፃሚዎች የገዢው ፓርቲ እንዲመረጥ የሚረዳ ገለጻ ሲያካሂዱ የፓርቲዎች ወኪሎች እርምት እንዲያደርጉ ቢያስገነዝቡም አስፈፃሚዎች ብልሹ አሠራራቸውን አለማስተካከላቸው በችግርነት የታየ ጉዳይ ነው፤
    2. በመራጮች ምዝገባ ወቅት ያልነበሩ አዳዲስ ንዑስ የምርጫ ጣቢያዎችን ከመክፈት በተጨማሪ ማንነታቸው የማይታወቁ የምርጫ ጣቢያዎች ተከፍተው በድምፅ መስጫ ቀን ድምፅ ሲሰጡባቸው መቆየታቸው፣
    3. አቅመ ደካሞችን፣ በእድሜ የገፉትን እና የአካል ጉዳተኞችን የመንግሥት ካድሬዎች ከምርጫ ሕጉ ውጭ በማገዝ ስም በሚስጥር ድምፅ በሚሰጥባቸው ክፍሎች ይዘዋቸው በመግባት ጫና እየፈጠሩ የሚፈልጉትን ማስመረጣቸው፣
    4. በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች የባልደራስን የምርጫ ውጤት ቁጥሮች እየቀነሱ እንዲጻፉ መደረጋቸው፣
    5. ባልደራስ የተመረጠባቸውን ወረቀቶች በስልት ከጥቅም ውጭ እንዲሆኑ ወይም የባከኑ ውጤቶች እንዲሆኑ መደረጋቸው፣
    6. በእያንዳንዱ የምርጫ ጣቢያ ያለው የመራጩ ቁጥር ቀድሞ የሚታወቅ ሆኖ እያለ በብዙ የምርጫ ጣቢያዎች የመራጮች ድምፅ መስጫ ወረቀቶች ከመራጮች ቁጥር እንዲያንስ መደረጉና ወረቀቱ እስኪመጣ መራጮች በፀሐይ፣ በዝናብና በብርድ በርካታ ሰዓታት እንዲቆዩ መሆናቸው የተወሰኑት ሳይመርጡ ወደ የቤታቸው እንዲሄዱ አስገድዷቸዋል።
    7. ለአዲስ አበባ ምክር ቤት ለውድድር የቀረቡ ፓርቲዎች በርካታ በመሆናቸውና በምርጫ ወረቀቱ ላይ በምርጫ አስፈፃሚዎች በቂ እና ግልጽ ማብራሪያ ባለመሰጠቱ የምርጫ ወረቀቱ በውስጡ ምን ያህል እጩዎች እንደያዘ አለመታወቁ ለመራጮች አስቸጋሪ ሁኔታን የሚፈጥር ሆኗል። ይህም መራጩ በግልጽ ድምፅ የመስጠት ነፃነት እንዳይኖረው አድርጓል።በዚህም የድምፅ መስጫ ወረቀቶች እንዲባክኑ ወይም መራጩ ላልፈለገው ድምፅ እንዲሰጥ ሆኗል። ከላይ የተጠቀሱት በምሳሌነት ከሚነሱት ችግሮች እጅግ በጣም ጥቂቶቹ ናቸው።

    የገዥው ፓርቲ በምርጫ ወቅት ለችግረኛ ሰዎች የተለያዩ መደለያዎች በመስጠት የሕዝብን ገንዘብ ለሥልጣን መሸመቻ ማድረጉ በምድር ቀርቶ በፈጣሪ ዘንድ ይቅር የማያሰኝ ተግባር ነው። በሌሎች ጊዜዎች የድሆችን ችግር ለማስወገድ ትኩረት የማይሰጠው ገዥው ፓርቲ በምርጫ ሰዓት ብቻ ማባበያ ይዞ መቅረቡ ነዋሪውን ለመደገፍ ሳይሆን ሥልጣኑን ለማቆየት የተጠቀመበት ዘዴ መሆኑ ግልጽ ነው።

    ከምርጫ 97 ወዲህ የምርጫ ጣቢያዎች እንዲበዙ የተደረገባቸው ምክንያቶች ኗሪዎች በረጃጅም ሰልፎች ላይ በመቆየት እንዳይንገላቱ ለማድረግ መሆኑ ይታወቃል። ነገር ግን ዛሬ ምርጫ ጣቢያዎች እንደአሸን እንዲፈሉ በተደረገበት ወቅት መራጮችን ለማሰላቸትና ለማስመረር ይሁን ተብሎ የተከናወኑት ማጓተቶች ድምፅ ሰጭዎች እንዲንገላቱ ማድረጉ የሚያስተዛዝብ ሁኔታን ፈጥሯል። ቀን በፀሐይና በዝናብ፣ በምሽት እና በሌሊት ደግሞ በብርድ እንዲንገላታ የተደረገበትን ደባ ተቋቁሞ የተሰለፈው አዲስ አበቤ ድምፁን ለማን እንደሰጠ ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ጠንቅቆ ያውቃል ።

    በገዥው ፓርቲና በምርጫ ቦርድ ለማሰላቸት ሆን ተብሎ በተፈጠረው ተስፋ የማስቆረጥ ሂደት ሳትመርጡ ለቀራችሁ፣ ሆን ተብሎ በተሠራ ደባ ካርድ እንዳታወጡ የተደረጋችሁ እና መምረጥ ያልቻላችሁ፣ ጊዜ በማጣት ካርድ ላልወሰዳችሁ፣ እንዲሁም በሀገራችን ሁኔታ ተስፋ በመቁረጥ የዜግነት ግዴታ መወጣት ያልቻላችሁ የእናንተ ድምፅ ሀገራችን ከገባችበት ውጥንቅጥ ችግሮች መውጫ ከፍተኛ ሚና የሚጫወት ሆኖ ሳለ በመቅረቱ በእጅጉ ያስቆጫል።

    የአሁኑ የኦህዴድ/ብልጽግና አባት የሆነው ህወሓት/ኢህአዴግ በምርጫ 2007 የ100% የአሸነፍኩ ጉዞ ከ2 ዓመት በላይ በሥልጣን መቆየት እንዳልቻለ የ3 ዓመት ትውስታችን ነው። በሕዝብ ያልተመረጠ መንግሥት ራሱን ይሸነግል ይሆናል እንጂ ረጅም ርቀት እንደማይጓዝ ከዚሁ ከሀገራችን ታሪክ መረዳት ይቻላል። ለነፃ፣ ፍትሀዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ዳኝነት የሚሰጠው ሕዝብ ነውና።

    6ኛውን ሀገር አቀፍ ምርጫ “ነፃ፣ ፍትሃዊ እና ዴሞክራሲያዊ አደርጋለሁ” ይል የነበረው ኦህዴድ/ብልጽግና በምርጫው ዙሪያ እየተፈጸሙ ያሉት ድርጊቶች የማያልቅ ሀሰቱ ማሳያዎች ሆነዋል። ዜጎች እየተገደሉ፣ ሰብዓዊ መብታቸው እየተጣሰ፣ ንብረታቸው እየወደመ፣ እየተራቡ እና እየተደፈሩ፣ የውጭ ወራሪ ኃይሎች ድንበር ጥሰው ሀገራችን ውስጥ ገብተው እንደፈለጉ እየሆኑ “ኢትዮጵያ አሸንፋለች፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም ሰፍኗል።…” የተሰኙት አባባሎች ዓይናችሁን ጨፍኑ ላሞኛችሁ ከማለት ያለፈ ትርጉም የላቸውም።

    የአዲስ አበባ ሕዝብ ለሰጠን ታላቅ ድጋፍና ፍቅር፣ ክብርና ሞገስ አሁንም ደግመን እናመሰግነዋለን። የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ አመራሮች እና አባላት በሕዝብ ፊት በተግባር ጭምር እየተፈተንን የሰላማዊ ትግል አርበኞች መሆናችንን አስመስክረናል።

    የዴሞክራሲ ኃይሎች ትንንሽ ልዩነቶችን ወደ ጎን በመተው ለማይቀረው የሰላማዊ ትግል ተደጋግፈን ሕዝብን በማስተባበር እንድንታገል ዛሬም እንደቀድሞው ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ጥሪውን ያቀርባል።

    ብሔራዊ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. የተካሄደወን የምርጫ ውጤት ይፋ ካደረገ በኋላ ከምርጫው ጋር በተያያዘ በዝርዝር ጉዳዮች ላይ ባልደራስ መግለጫ የሚሰጥ መሆኑን በአክብሮት ይገልጻል።

    የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ
    ድል ለእውነተኛ ዴሞክራሲ!!!
    ሰኔ 18 ቀን 2013 ዓ.ም.

    ምንጭ፦ ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ

    ነፃ፣ ፍትሀዊና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ

    Anonymous
    Inactive

    የ6ኛውን ሀገራዊ ምርጫ “ሰላምና ደህንነት” አስመልክቶ ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የተሰጠ መግለጫ

    የተከበርከው የኢትዮጵያ ሕዝብ፥

    የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በቅድሚያ ለታሪካዊው 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ እንኳን በሰላም አደረሳችሁ እያለ የምርጫው ሂደት ተጀምሮ አሁን ያለበት ደረጃ እስኪደርስ በጨዋነትና በትዕግስት ላደረጋችሁት ድጋፍና ትብብር የላቀ ምስጋናውን እያቀረበ በቀሪው የምርጫ ሂደትም ምርጫውን የሚያደናቅፉ አጠራጣሪ ጉዳዮች ሲያጋጥሙ እንደተለመደው ሁሉ መረጃ በመስጠትና አስፈላጊውን ድጋፍ ለፀጥታ እና ለደህንነት ኃይሉ በማድረግ የበኩላችሁን ድርሻ እንድትወጡ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

    የተከበራችሁ የሀገራችን ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፥

    የምርጫ ሕጉንና የሥነ-ምግባር ደንቡን አክብራችሁ እስከ አሁን ለምርጫው ሰላማዊነት የበኩላችሁን ገንቢ አስተዋፅኦ በማበርከታችሁ ኮሚሽኑ ምስጋናውን እያቀረበ በቀጣይም በሚኖረው የምርጫ ሂደት እስከመጨረሻው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሀገራዊ ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ ኮሚሽኑ አጥብቆ ይጠይቃል።

    የተከበራችሁ የፌዴራልና የክልል የፀጥታና የደህንነት አካላት፥

    መስዋዕትነት በመክፈል ጭምር ፍፁም ገለልተኛ ሆናችሁ ሌት ተቀን እያበረከታችሁት ላላችሁት አስተዋፅኦ ኮሚሽኑ ከልብ እያመሰገነ፤ በቀጣይ ለሚኖረው የድምፅ አሰጣጥና አጠቃላይ ለምርጫው ሂደት ስኬታማነት የተሰጣችሁን ሰላምና ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነታችሁን ልክ እንደቀደመው ጊዜ ሁሉ እንድትወጡ ከአደራ ጭምር ያሳስባል፡፡

    ኮሚሽኑ ሀገራችን ኢትዮጵያ የምትገኝበትን ወሳኝ ምዕራፍ ከግምት ውስጥ በማስገባት የምርጫ ሂደቶች ከሁከትና ብጥብጥ የጸዱ እንዲሆኑ ከፀጥታና የደህንነት መዋቅሩ ጋር የተቀናጀ የምርጫ ደህንነት ዕቅድ በማዘጋጀት፣ በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫ ዕለት እና በድኅረ-ምርጫ ወቅት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ውስጣዊና ውጫዊ የፀጥታ ሁኔታዎችን በአግባቡ በመተንተን እና በመለየት አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ ሲሠራ ቆይቷል።

    ከዚህ አንፃር 6ኛውን ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ ማጠናቀቅ ለሀገራችን ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም የሀገራችንን ታላቅነት ለመላው ዓለም የምናሳይበት ታላቅ ኩነት መሆኑንና ለገጽታችን ግንባታ ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑን የተረዳው ኮሚሸኑ የውስጥና የውጭ ፀረ-ሰላም ኃይሎች ፀጥታውን ለማናጋት፣ የምርጫውን ሰላማዊነት ለማደፍረስና የሁከትና ብጥብጥ መንስዔ ለማድረግ እንደሚንቀሳቀሱ ከወዲሁ በመረዳት ምንም ዓይነት ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴ በየትኛው አካባቢ እንዳይኖር ከፌዴራል እስከ ክልል ያሉ የሀገራችን የፀጥታና የደህንነት መዋቅሮች በከፍተኛ ኃላፊነትና ተጠያቂነት የተሰጣቸውን ሀገራዊ ተልዕኮ በብቃት መወጣት የሚያስችላቸው ሁለንተናዊ አቅም በመገንባት ሙሉ ዝግጅቱን አጠናቆ ወደ ስምሪት ገብቷል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ ለሕዝቡ እና ለሥራችን ከፍተኛ እገዛ የሚያደርጉት አስፈላጊ እና ወሳኝ የሆኑት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች በምርጫ ወቅት ያለ በቂ ምክንያት እንዳይቋረጡ የሚመለከታቸው አካላት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ኮሚሽኑ በአንክሮ ያሳስባል፡፡

    በመጨረሻም መላው የሀገራችን ሕዝብ እና የፀጥታ ኃይሉ ከመቼውም ጊዜ በላይ በመቀናጀት ይህንን ታሪካዊ ምርጫ በሰላማዊ መንገድ እንድንወጣ ጥሪያችንን በከፍተኛ አክብሮት እያቀረብን፥ በድምጽ መስጫ ዕለትና በድኅረ-ምርጫ ወቅት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ሁሉ በሕግ አግባብ ብቻ እንዲሆኑ ኮሚሽን በጥብቅ ያስታውቃል፡፡

    ኮሚሽኑ በድጋሚ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንኳን ለ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ በሰላም አደረሳችሁ ይላል።

    የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን
    ሰኔ 12 ቀን 2013 ዓ.ም.
    አዲስ አበባ

    ምንጭ፦ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን

    6ኛውን ሀገራዊ ምርጫ -- ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የተሰጠ መግለጫ

    Anonymous
    Inactive

    በሳይንስና ሂሳብ ትምህርቶች ዙሪያ ጥራትን ማስጠበቅ ያስችላል የተባለ ረቂቅ ስትራቴጂያዊ ዕቅድ ተዘጋጀ
    በ2014 ዓ.ም. ከ50ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የመንገድ ደህንነት ትምህርት ይሰጣል

    አዲስ አበባ (ትምህርት ሚኒስቴር) – በሳይንስና ሂሳብ ትምህርቶች ዙሪያ ጥራትን ማስጠበቅ ያስችላል የተባለ ረቂቅ ስትራቴጂያዊ ዕቅድ ተዘጋጀ። በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሂሳብና ሳይንስ ትምህርቶች ማዕከላትን ለማቋቋም የትምህርት ቤት ማኅበረሰብ ያላቸውን ፍላጎት እና የቤተ ሙከራ ኬሚካሎች አጠቃቀም እንዲሁም አወጋገድ ሥርዓት ዙሪያ ጥናታዊ ዳሰሳ ግኝት ቀርቦ ውይይት መካሄዱን የትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል።

    መድረኩ የማዕከሉ አምስት ዓመት ስትራቴጂያዊ ዕቅድ እና ዓመታዊ የዕቅድ አፈጻፀም ለመገምገም ያለመ ነበር፡፡

    በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሂሳብና ሳይንስ ትምህርቶች ማዕከል የሥነ ህይወት ትምህርት ባለሙያ የሆኑት አቶ ጌታዬ ሞላልኝ የአምስት ዓመት ስትራቴጂያዊ እቅዱ ዘመናዊ የአሠራር ሥርዓቶችን ተግባራዊ በማድረግ የሂሳብ፣ የሳይንስ፣ የምህንድስና ትምህርቶችን ከጥበብ እና በቴክኖሎጂ በማስደገፍ ለመስጠት የሚያግዝ ነው ብለዋል።

    ቤተ ሙከራ ተማሪዎች በፅንሰ ሃሳብ የተማሩትን የትምህርት ይዘት በተግባር ሙከራ አስደግፈው ይበልጥ ትምህርቱን በቀላሉ እንዲረዱ ጉልህ ድርሻ እንዳለው ባለሙያው ጠቁመዋል፡፡ በክልል ደረጃ በቴክኖሎጂ የተደገፉ ስምንት የስልጠና ማዕከላት እንደሚቋቋሙ አቶ ጌታዬ ተናግረዋል፡፡

    በትምህርት ቤቶች የቤተ ሙከራ ኬሚካሎች አጠቃቀምና አወጋገድ ሥርዓት ዙሪያ አንዳንድ ችግሮች እንዳሉ ከቀረበው ጥናታዊ ዳሰሳ ለማወቅ ተችሏል፡፡

    በመድረኩ ከክልል እና ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮዎች የተውጣጡ የዘርፉ ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

    ከዚህ ቀደም በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በምህንድስና፣ በጥበብና ሂሳብ ዘርፍ የሚቀርቡትን የተማሪዎችን የፈጠራ ውጤቶች በአግባቡ መምራት የሚያስችል ረቂቅ መመሪያ መዘገጀቱንም ሚኒስቴሩ አስታውሷል።

    ከትምህርት ዜና ሳንወጣ፥ በ2014 ዓ.ም ከ50ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የመንገድና ትራንስፖርት ደህንነት ትምህርት እንደሚሰጥ ትምህርት ሚኒስቴር ሰኔ 7 ቀን፥ 2013 አስታውቋል።

    የትምህርት ሚኒስቴርና የትራንስፖርት ሚኒስቴር በትብብር ያዘጋጁት “የመንገድ ደህንነት ለሁሉም” በሚል የመንገድ ደህንነት ሥርዓተ ትምህርት ማስጀመሪያ መርሃ ግብር በሳምንቱ ውስጥ ተካሂዷል።

    የመንገድ ደህንነት ሥርዓተ ትምህርት ከቅደመ መደበኛ እስከ 12ኛ ክፍል፣ እንዲሁም በጎልማሶች ትምህርት እንዲካተት ተደርጎ በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት የተቀረፀ ሲሆን በ2014 ወደ ሥራ ይገባል።

    የትምህርት ሚኒስትሩ ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር ኢንጂ) በ2014 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን ወደ ትግበራ የሚገባው አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት፣ የትምህርት ጥራትን ታሳቢ ያደረገና ባለፉት ዓመታት የታዩ ችግሮችን ነቅሶ ያወጣ መሆኑን ተናግረዋል።

    በቀጣይ ዓመት ከ50ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የመንገድ ደህንነት ትምህርት ተግባራዊ እንደሚደረግ የገለፁት ሚኒስትሩ፥ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የትራፊክ ደህንነት ትምህርት በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ መካተቱ በዜጎች ላይ የሚደርሰውን አደጋ እንዲቀንስ ያስችላል ብለዋል።

    የትራንስፖርት ሚነስትሯ ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ ደህንነቱ የተጠበቀ የመንገድ አጠቃቀምን ባህል ለማድረግና የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ ሚኒስቴሩ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በጋራ እየሰራ መሆኑን ገለፀዋል።

    የመንገድ ደህንነት ትምህርት በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ መካተቱ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ከማምጣቱም በላይ የመንገድ አጠቃቀምን ባህል ለማድረግ የሚረዳ መሆኑን ሚኒስትሯ ገልፀዋል።

    ሥርዓተ ትምህርቱ ዜጎች የመንገድ ትራፊክ ሕግና ደንብን በአግባቡ አውቀው ተግባራዊ እንዲያደርጉ እና ሌሎችንም እንዲያሳውቁ ዕድል እንደሚፈጥርም ተገልጿል። በዝግጅቱም የመንገድ ደህንነት ትምህርትን ለማስተማር  የሚያስችሉ ቋሳቁሶችን ትምህርት ሚኒስቴር ከትራንስፓርት ሚኒስቴር ተረክቧል።

    በበ2014 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን ተግባራዊ በሚደረገው የመንገድና ትራንስፖርት ደህንነት ትምህርት ላይ በ11 የትምህርት ዓይነቶች የመንገድ ደህንነት ትምህርት የሚተገበር ሲሆን ከ34 ሚሊዮን  በላይ ተማሪዎችን ለመድረስ ያስችላል።

    ምንጭ፦ የኢፌዲሪ ትምህርት ሚኒስቴር

    የመንገድ ደህንነት ትምህርት

    Anonymous
    Inactive

    የሰሞኑ “ቃል በተግባር” የተሰኘው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ዘጋቢ /ገላጭ/ ፊልም በሁለት ኢትዮጵያውያን አተያይ
    [ቃል በተግባር ― በዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ እና በአቶ ያሬድ ኃይለማርያም አተያይ]

    • ቃል በተግባር ― ኢትዮጵያን ሀገር ሆና አየኋት
      [በድሉ ዋቅጅራ (/)]

    ኢትዮጵያን እንደሀገር ያገለገልኳት፣ ያፈቀርኳት በ1970ዎቹ መጨረሻ (1976-79) ባለው ጊዜ ነበር፤ በመጀመሪያው ዙር የብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት ዘመኔ። ከትምህርት ቤት በግዴታ ታፍሼ የገባሁበት የብሔራዊ ውትድርና ከሀገሬ ጋር ልብ ለልብ አስተዋወቀኝ፤ አፈቀርኳት።

    ግዳጄን ፈጽሜ፣ ዩኒቨርሲቲ ተምሬ፣ በ1983 አ.ም. ወደ ሥራ ስሰማራ ኢትዮጵያን አጣኋት። በብሔር ፖለቲካ ሴራ የተካኑ፣ ስሟን መጥራ የሚዘገንናቸው መሪዎች እጅ ወድቃለች። ለጎሳና ቋንቋ ድንበር ከልላ፣ ባንዲራ [ሰንደቅ ዓላማ] ሰቅላ እሷ ፈዝዛለች።… ለብሔረሰቦችና ለቋንቋዎች እኩልነትና ለሰብዓዊ መብት መከበር ዝም ብዬ አላውቅም፤ እሟገታለሁ። ባንዲራቸው ሲከልላት፣ የምትተነፍሰው አየር ሲያጥራት፣ ኢትዮጵያን ሲረሷት ግን አዝናለሁ፤ ያመኛል።

    ከረዥም ጊዜ በኋላ በትላንትናው ዘጋቢ ፊልም ውስጥ ኢትዮጵያን ሀገር ሆና አየኋት። ዘመንን መስላ፣ ተስፋ አዝላ አነበብኳት። በሦስት ዓመት፣ ያለጥላቻና ግጭት ዜና ነግቶ በማይመሽበት ሀገር፣ ‘የእኔ ሀሳብ ካልሆነ ሀገሬ ትበተን’ በሚል ጽንፍ ረገጥ ፖለቲካዊ መርገምት ውስጥ፣ እንኳን በልዕልና መሥራት፥ በትክክል ማሰብስ ይቻላል ወይ? ያውም ይህ ሁሉ ኃላፊነት ለተጫነበት መሪ?!

    የእያንዳንዳችን አመለካከትና እይታ የሚመነጨው ከቆምንበት ቦታ ነው!

    አዎ፣ ሀገራችን የብሔር ፖለቲካው ካጣባት ደዌ አልተፈወሰችም። አዎ አሜሪካ ማእቀብ ጥላብናለች። አዎ ሱዳን ድንበራችንን ተሻግራ መሬታችንን ይዛለች። አዎ የትግራይ ወገኞቻችን በከፍተኛ ሰብዓዊ ችግር ላይ ናቸው። አዎ የኤርትራ ወታደሮች ከሀገራችን ጨርሶ አልወጡም። አዎ ሸኔና የጁንታው ርዝራዦች በሚሰነዝሩት ጥቃት አሁንም ዜጎች ህይወታቸውን እያጡ ነው። አዎ የኑሮ ውድነት ጣራ ነክቷል።… ሀገራችን ውስጥ በርካታ ችግሮች፣ በርካታ ያልተመለሱ ጥያቄዎች አሉ።

    እነዚህ ሁሉ ችግሮች እያሉ እነዚህ አስደናቂ ፕሮጀክቶች መሠራታቸው አግባብ አይደለም በማለት ሰዎች ለጥላቻቸው የሰበብ ድር ያዳውራሉ። እኔን የሚገርመኝ በዚህ ሁሉ ችግር ውስጥ መሠራት መቻላቸው ነው።

    መሠራት የነበረበት ያልተሠራ አለ። ካልተሠራው የበለጠ የተሠራው የወደፊት መንገዳችንን ያሳያል። ጠቅላይ ሚንስትሩ ከሀገሪቱ ባጀት ሳይነካ፣ የተሸለመውን የግል ገንዘብ ሳይሰስት፣ ወዳጆቹን ለምኖ በሦስት ዓመት፣ ጥላቻና ዘለፋን ቁብ ሳይል ይህንን ሠራ። ባለቤቱ ቀዳማዊ እመቤት ዝናሽ ታያቸው እንዲሁ ከሀያ በላይ ትምህርት ቤቶችን በገጠር ቀበሌዎች ገነባች። ለመሆኑ እነዚህን ሰዎች የማናደንቀው ከእነማን ጋር እያወዳደርናቸው ነው? እንኳን በሦስት ዓመት፣ በሦስት አስርታት ውስጥ የዚህን ግማሽ የሠራ መሪ ኖሮን ያውቃል?

    እንደመሪ እነሱ ይህን ሠሩ፤ ያልመለሷቸው ችግሮችም አሉ። እኛስ! እንደ ዜጋ ባለፉት ሦስት ዓመታት ምን ሠራን? እኛ እንደዜጋ ያለነው የት ነው? የሠሩት በጎ ተግባር ወይስ ያልመለሷቸው ችግሮች አካል ነን? በዋናነት የእያንዳንዳችን አመለካከትና እይታ የሚመነጨው ከቆምንበት ቦታ ነው። ሀገራችን በውስጥና ውጭ ችግር ተተብትባለች፤ ፈተና ላይ እንደሆነችም እናውቃለን። ዋናው፣ እያንዳንዳችን ማወቅ ያለብን ጉዳይ ግን ሀገራችንን የተበተባት ችግር፣ የተጋረጠባት ፈተና አካል አለመሆናችንን ነው። እና እንጠይቅ! እንደዜጋ የቆምነው የት ነው?!

    /ር በድሉ ዋቅጅራ ደራሲና ገጣሚ ሲሆኑ፥ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የሂዩማኒቲስ፤ የቋንቋዎች ጥናት የጆርናሊዝምና የኮሚኒኬሽን ኮሌጅ ውስጥ ደግሞ መምህር ናቸው። ከዚህ ቀደም ለህትመት ከበቁላቸው ሥራዎች ውስጥ የማይፃፍ ገድል፣ የራስ ምስል፣ ያልተከፈለ ስለት፣ የወይራ ስር ጸሎት፣ የማይጻፍ ገድል፣ የተስፋ ክትባት፣ እና ፍካት ናፋቂዎች የጠቀሳሉ። በተጨማሪም በብሔራዊ ቲያትር ቀርቦ በተመልካች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነትን ያገኘውደብተራውየተሰኘው የሁለት ገጸባሕርያት ቲያትር (two-handler theater) ደራሲ ናቸው።

    • ቃል በተግባር ― እያደነቅን ስጋታችንንም እንገልጻለን፤ አቧራው መሬት ላይ ያለ ግፍ፤ ሃሜቱም ሃቅ ነው
      [አቶ ያሬድ ኃይለማርያም]

    ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በአዲስ አበባ የሠሯቸውን እና እየሠሯቸው ያሉ ድንቅ ነገሮችን አደንቃለሁ። ለዚህ ሥራቸው ሊመሰገኑ ይገባል። ከሠሯቸው ሥራዎቹ አንዱ የሆነውን የእንጦጦ ፖርክን የመጎብኘት ዕድል ገጥሞኛል። የሚያስደምም ድንቅ ሥራ ነው።

    ከትላንት መግለጫቸውም ሁለት ነገር መረዳት ይቻላል። አንደኛው ሀገር ለማልማት ብዙ እቅድ እና ህልም እንዳላቸው ነው። ሁለተኛው ደግሞ ይህን ህልማቸውን እውን ለማድረግ አንባገነን እሰከመሆን የሚሄዱ መሆናቸውን ነው። አገሪቱ አሁን ያለችበትን ውጥንቅጥ እና አሳሳቢ ችግር፣ የተቃዋሚዎቻቸውን ቅሬታ እና በመንግሥታቸው ላይ የሚሰነዘሩ ቅሬታዎችን ‘አቧራ’ በሚል ገልጸውታል። “ሀሜት አቧራ እንጂ አሻራ መሆን አይችልም። አቧራውን ንቀን አሻራ ማኖራችንን እንቀጥላለን” የምትለዋ ንግግራቸው አለቃቸው የነበሩትን መለስን [የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን] አስታወሱኝ። ባጭሩ የመለስን የመታበይ ንግግር ነው የደገሙት። መለስ ‘ውሾቹ ይጮኻሉ፤ ግመሎቹም ጉዟቸውን ይቀጥላሉ’ ነበር ያሉት?

    ታቃዋሚዎቻቸውን ውሻ አድርገው እና ተቋውሟቸውንም እንደ ውሻ ጩኸት ቆጥረው እሳቸው ከጉዟቸው ምንም አይነት ምድራዊ ኃይል እንደማያስቆማቸው ሊያውም በፓርላማ ፎክረው ነበር። የመሠረት ድንጋይ ጥለው ያስጀመሩትን የሕዳሴ ግድብ መጨረሻ ለማየትና ሪባን ለመቁረጥ ግን አልታደሉም። ግመሎቹስ ዛሬ ወዴት አሉ? አብይም ያች በሽታ እየታየችበት ነው። ሀገሪቱ ውስጥ ያለውን ያፈጠጠ እና አሳሳቢ ችግር እንደ አቧራ መቁጠር መጥፎ መታበይ ነው። አቧራው እንዲሰክን የሚቀርቡ ምክርና ወቀሳዎችንም እንደ ሀሜት መቁጠር ሌላው አሳሳቢ የክሽፈት ምልክት ነው።

    ሕዝብ እየተራበ ነው፤ የኑሮ ውድነት ሌላ የቀውስ ምንጭ ነው፤ ያልተረጋጋ ፖለቲካም የልማት ጸር ነው፤ ጦርነትም አውዳሚ ነው፤ የመብት ጥሰቶች መበራከት የአፈና ሥርዓት መሳለጫ ነው። እነዚህ ችግሮች አቧራ አይደሉም። በእነዚህ ጉዳዮች ዙሪያ የሚቀርብብዎት ወቀሳና ነቀፌታዎች ሀሜት አይደለም። ልማቱን ግፉበት፤ መታበይዎን አቁመው ለዲሞክራሲ፣ ለሕግ የበላይነት፣ ለሰብዓዊ መብቶች እና ለፍትህ ቀናዕይ በመሆን እንደ ልማቱ አፋጣኝ መልስ ይስጡ። ካልሆነ ግን መካር እንደሌለው ንጉሥ… ይሆናሉ።

    አቶ ያሬድ ኃይለማርያም መቀመጫውን ጄኔቭ ከተማ፥ ስዊዘርላንድ ያደረገ ስብስብ ለሰብዓዊ መብቶች በኢትዮጵያ (Association for Human Rights in Ethiopia) የተባለ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ናቸው።

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forums) ላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።

    ቃል በተግባር

    Anonymous
    Inactive

    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግን ማብራሪያ ጠየቀ

    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በቅርቡ የተቋቋመው የአዲስ አበባ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ወረዳ ፍርድ ቤት ሥልጣን እና ተግባራት ላይ ማብራሪያ ይሰጠኝ ሲል የኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግን ጠየቀ።

    ኢዜማ ለጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በላከው ደብዳቤ፣ በተለያዩ መንግሥታዊና የግል ሚዲያዎች ‹‹የፊንፊኔ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት›› በይፋ ተከፍቶ አገልግሎት መስጠት ጀመረ በማለት የተሰሩት ዘገባዎች፣ በሕገ-መንግሥቱ ለአዲስ አበባ ከተማ የተሰጠውን ራስን በራስ የማስተዳደር ሥልጣን የሚጋፋ ሆኖ አግኝቼዋለሁ ብሏል።

    የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ (ኦቢኤን) የአዲስ አበባ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ኩመላ ቡላን ጠቅሶ በሰራው ዘገባ «…በፊንፊኔ ከተማ የሚኖሩ የኦሮሞ ብሄር ተወላጆችም ሕገ-መንግሥታዊ መብታችውን በመጠቀም በዚህ ፍርድ ቤት በቋንቋቸው የመዳኘትና ተደራሽ የሆነ የፍትህ አገልግሎት የማግኘት መብትም ያገኛሉ ብለዋል።» በማለት መዘገቡን ያስታወሰው ኢዜማ፣ ይህንን ዘገባ ተከትሎ አዲስ የተከፈተው ፍርድ ቤት ሥልጣንና ተግባራት ላይ የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግን ማብራሪያ ጠይቋል።

    የኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 49 (2 እና 3) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ ሥልጣን እንዳለው ተጠሪነቱም ለፌደራል መንግሥት አንደሆነ በግልጽ ደንግጓል ያለው ኢዜማ፥ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ራሱን በራሱ ያስተዳድራል ሲባል ከተማው የራሱ ሕግ አውጭ፣ ሕግ አስፈጻሚ እና ሕግ ተርጓሚ ይኖረዋል ማለት መሆኑን ጠቁሞ፤ ተጠሪነቱ ለፌደራል መንግሥት ነው ማለት ደግሞ በአዲስ አበባ ጉዳዮች ላይ የመጨረሻ የመወሰን ሥልጣን ያለው አካል የፌደራል መንግሥቱ ብቻ ነው ማለት ነው ሲል አመላክቷል።

    የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችን ለሚገጥማቸው ማናቸውም ጉዳይ የትኛውም ብሔር ጀርባ ቢኖራቸውም የመዳኘት ሥልጣኑ የከተማ መስተዳደሩ ፍርድ ቤቶችና የፌደራል ፍርድ ቤቶች መሆኑን የጠቀሰው ኢዜማ፣ አንድ ክልል የዚህ ብሔር ተወላጆችን ነዋሪነታቸው በአዲስ አበባ ከተማ ቢሆንም የመዳኘት ሥልጣን ይኖረኛል ማለቱ በሕገ-መንግሥቱ ለፌደራል መንግሥቱ የተሰጠውን ሥልጣን የሚጋፋ፤ በአዲስ አበባ ቻርተር አዋጅ ቁጥር 87/1989 እንዲሁም እሱን ያሻሻለው አዋጅ ቁጥር 361/1995 የአዲስ አበባ አስተዳደር ራስ ገዝ ከመሆኑም ባሻገር በፌደራሉ መንግሥት የዳኝነት ፈቃደ ሥልጣን ሥር በማይወድቁ ጉዳዮች ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ፍርድ ቤቶች አና የቀበሌ ማኅበራዊ ፍርድ ቤቶች ብቻ ሥልጣን እንደሚኖራቸው ተብሎ የተደነገገውን በግልጽ የሚቃረን ሆኖ አግኝቼዋለሁ ብሏል።

    አሁን ለተቋቋመው ፍርድ ቤት የሕግ መሰረት ተደርጎ የተጠቀሰው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፍርድ ቤቶች አደረጃጀት ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጣው አዋጅ ቁጥር 216/2011 በአንቀጽ 24 ላይ ከተዘረዘሩት የኦሮሚያ ፍርድ ቤቶች የተሰጣቸው ሥልጣን እና ተግባራት ላይ በአዲስ አበባ የሚኖሩ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆችን ጉዳይ የማየት ሥልጣን እንዳላቸው ባልጠቀሰበት ሁኔታ፣ በአዲስ አበባ የሚኖሩ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆችን ጉዳይ የማየት የዳኝነት ፈቃደ ሥልጣን የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፍርድ ቤቶች አላቸው ተብሎ መገለጹ ኢ-ሕገ-መንግሥታዊ እና ምንም ዓይነት የሕግ መሰረት የሌለው ነው ያለው ኢዜማ፣ በአንድ ከተማ ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች የብሔር ማንነታቸው ላይ በመመስረት የተለያየ የዳኝነት መብት ይኖራቸዋል ብሎ ፍርድ ቤት መክፈት የዜጎቸን በሕግ ፊት በእኩልነት የመታየት ሰብአዊና ሕገ-መንግሥታዊ መብትን የሚጥስ ከመሆኑም ባለፈ የዜጎችን ተከባብሮ የመኖር እሴት የሚሸረሽር ነው የሚል እምነት እንዳለው ኢዜማ በደብዳቤው ገልጿል።

    በአንድ ከተማ ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች የብሔር ማንነታቸው ላይ በመመስረት የተለያየ የዳኝነት መብት ይኖራቸዋል ብሎ ፍርድ ቤት መክፈት የዜጎችን በሕግ ፊት በእኩልነት የመታየት ሰብዓዊና ሕገ-መንግሥታዊ መብትን የሚጥስ ተግባር መሆኑን የጠቀሰው ኢዜማ፣ ይህ ዓይነቱ ድርጊት የዜጎችን ተከባብሮ የመኖር ዕሴት ይሸረሽራል ብሎ እንደሚያምን ገልጿል።

    የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ መሥሪያ ቤት በአፋጣኝ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያውን እንዲሰጠው የጠየቀው ኢዜማ፣ ‹‹ጠቅላይ አቃቤ፣ ይህንን ከሕገ-መንግሥት ማዕቀፍ ውጪ የሆነ ኢ-ሕገ-መንግስታዊ ተግባር እንዲያስቆም ሲል ለጠቅላይ አቃቤ ሕግ በላከው ደብዳቤ ጥያቄውን አቅርቧል።

    ምንጭ፦ ኢዜማ

    ኢዜማ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግን ማብራሪያ ጠየቀ

    Anonymous
    Inactive

    ሚያዝያ 11 ቀን፥ 2013 ዓ.ም.
    አቶ ልደቱ አያሌው
    ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን
    አዲስ አበባ

    ጉዳዩ:- በድጋሚ አቤቱታ ማቅረብን ይመለከታል

    በቅድሚያ በእኔ በአመልካቹ ላይ በተደጋጋሚ እየደረሰ የሚገኘውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፍትሄ እንዲያገኝ መሥሪያ ቤታችሁ እያደረገ ስላለው ያልተቋረጠ ጥረት ልባዊ ምስጋናየን አቀርባለሁ። ሆኖም በእኔ ላይ እየተፈፀመ የሚገኘው የሰብዓዊ መብት ጥሰት አሁንም ያልተቋረጠና ለሕይወቴ አስጊ በሆነ ደረጃ ተጠናክሮ የቀጠለ በመሆኑ፥ ይሄንን አቤቱታ በድጋሚ ለማቅረብ ተገድጃለሁ።

    የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በሀገሪቱ የተፈጠረውን የፖለቲካ ቀውስ ሰበብ በማድረግ በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንድውል ከተደረገበት ከሐምሌ 17 ቀን፥ 2012 ዓ.ም. ጀምሮ በሀገሪቱ ሕግና የሕግ የበላይነት የለም ሊያስብል በሚባል ደረጃ በርካታና ተከታታይ የሰብዓዊ መብት መብት ጥሰት በእኔ ላይ እየተፈፀመ ይገኛል። ለማስታወስ ያህል…

    1. ሕጋዊ ነዋሪነቴ ተመዝግቦ የሚገኘው በአዲስ አበባ ከተማ ሆኖ እያለ፥ እንድታሰር የተደረገው ግን ያለ አግባብ በኦሮሚያ ክልል ነው።
    2. በስልክ ተጠርቼና ለፌደራሉ ፖሊስ ኮሚሽን በእራሴ ፈቃድ እጄን ሰጥቼ በቁጥጥር ስር ከዋልኩ በኋላም በሕጉ መሠረት በ48 ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት እንድቀርብ አልተደረገም።
    3. በቁጥጥር ስር ከዋልኩ በኋላ ያለምንም ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በስልክና በኢንተርኔት አማካይነት ያደረኳቸው የግል የመልዕክት ልውውጦች በሕገ-ወጥ መንገድ እንዲበረበሩና በሲዲ እንዲቀዱ ተደርገዋል። የግል ማስታወሻወቼና ረቂቅ የፅሁፍ ሰነዶቸ ሳይቀሩ በፖሊስ ተወስደዋል።
    4. በቁጥጥር ውስጥ ውዬ ገና ክስ እንኳ ባልተመሠረተብኝ ወቅት የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኛ ነን የሚሉ ሰዎች ወንጀለኛ እንደሆንኩ አድርገው ሰፊ የስም ማጥፋት ዘመቻ እንዲያካሂዱብኝ ተደርጓል።
    5. በምርመራ ወቅትና የምርመራ ፋይሌ ከተዘጋ በኋላም የዋስ መብት ተከልክዬና ክስ ሳይመሠረትብኝ በጊዜ ቀጠሮ ሰበብ ከሁለት ወራት በላይ ለሆነ ጊዜ በሕገ-ወጥ መንገድ በእስር ቤት እንድቆይ ተደርጓል።
    6. በፍርድ ሂደቱ ወቅት በግልፅ እንደታየው፥ በቢሾፍቱ ከተማ አመፅ አስነስተሀል፤ ሕገ-ወጥ መሣሪያ ታጥቀህ ተገኝተሀል፤ መንግሥትን በሕገ-ወጥ መንገድ አፍርሰሀል የሚሉ የፈጠራ ክሶች እንዲቀርቡብኝ ተደርጓል።
    7. “መንግሥትን በሕገ-ወጥ መንገድ አፍርሰሀል” በሚል የተከሰስኩበት ወንጀል አዲስ አበባ በሚገኝ የፌደራሉ ፍርድ ቤት መታየት ሲገባው ያለ አግባብ በአዳማ ከተማ የሚገኘው የኦሮሚያ ክልል ጥቅላይ ፍርድ ቤት በውክልና እንዲያየው ተደርጓል። ይህም መሆኑ የፍርድ ሂደቱ በማልናገረው ቋንቋ እንዲካሄድና ብዙ ውጣ ውረድ እንዲደርስብኝ አድርጓል።
    8. በፍርድ ሂደቱ ወቅት ለሁለት ጊዜ ያህል የዋስ መብት በፍርድ ቤት ቢፈቀድልኝም ፖሊስ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ በመጣስ ለሁለት ወራት ያህል በእስር አቆይቶኛል። ከዋስትና መብቴ ጋር በተያያዘም ፍርድ ቤት ለአምስት ጊዜ የሰጣቸው የተለያዩ ትዕዛዞች በፖሊስ እምቢተኝነት ሳይፈፀሙ ቀርተዋል።
    9. ለሕይወት አስጊ የሆነ ከፍተኛ የልብ ህመም ያለብኝ ሰው መሆኔ እየታወቀም የኮቪድ ወረረሽኝ ተጠቂ ከሆኑ ሰዎች ጋር በአንድ ጠባብ ግቢ ውስጥ ታስሬ ለረጅም ጊዜ እንድቆይ ተደርጓል።
    10. ከአምስት ወራት መታሰር በኋላ የዋስ መብቴ ተጠብቆ ከተፈታሁ ከጥቂት ቀናት በኋላም እኔንና የትግል ጓደኞቼን ከሀገሪቱ የፖለቲካ ሂደት ለማግለል ሲባል አባል የሆንኩበት የፖለቲካ ፓርቲ በሕገ-ወጥ መንገድ እንዲሰረዝና ህልውናውን እንዲያጣ ተደርጓል።
    11. ከእስር ቤት ወጥቸ አስቸኳይ የቀዶ ጥገና የሕክምና እርዳታ ለማግኘት ወደ ውጭ ሀገር ለመጓዝ ለሁለት ጊዜ ያደረኩት ሙከራም ምንም አይነት የፍርድ ቤት እገዳ ባልተጣለብኝና እንዲያውም ጉዳዩን ይመለከት የነበረው ፍርድ ቤት ወደ ውጭ ሀገር ሄጀ የመታከሜን አስፈላጊነት በማመን ረዥም ቀጠሮ ሰጥቶኝ እያለ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት መሥሪያ ቤት በሕግ ባልተሰጠው ሥልጣን ባደረገብኝ ሕገ-ወጥ ክልከላ ምክንያት ከሀገር የመውጣት ሕገ- መንግሥታዊ መብቴ ተጥሷል።
    12. ይህ የተጣለብኝ ሕገ-ወጥ እገዳ እንዲነሳልኝ ለማድረግ የተለያዩ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን የመንግሥት ባለ ስልጣናት ቀጠሮ ይዤ ለማነጋገር በተደጋጋሚ ብሞክርም ባለስልጣናቱ ሊያናግሩኝ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ሙከራዬ ሳይሳካ ቀርቷል።
    13. መሥሪያ ቤታችሁ ባደረገው ጥረት ምክንያት የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት መሥሪያ ቤት በእኔ ላይ ምንም ዓይነት የጉዞ ክልከላ እንዳላደረገ የሚክድ ደብዳቤ ለመሥሪያ ቤታችሁ ከፃፈ በኋላም ለሦስተኛ ጊዜ ከሀገር ለመውጣት ያደረኩት ሙከራ የኢሚግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ክልከላ ስላደረገብኝ ጉዞዬ ሳይሳካ ቀርቷል። የጉዞ ፓስፖርቴም በመሥሪያ ቤቱ ባልደረቦቼ ተወስዶብኛል።
    14. የኢሚግሬሽን መሥሪያ ቤት ለምን የጉዞ ክልከላ እንዳደረገብኝና እንደቀማኝ በማግስቱ ዋናው መሥሪያ ቤት ድረስ ሄጄ ለመጠየቅ ባደረኩት ሙከራ የፌዴራሉ ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ክፍል ባቀረበው ጥያቄ መሠረት በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውዬ ምርመራ እስከሚካሄድብኝ ድረስ የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የአራዳ ምድብ አንደኛ ችሎት የካቲት 4 ቀን፥ 2013 ዓ.ም. በዋለው ችሎት ወደ ውጭ እንዳልጓዝ እገዳ የጣለብኝ ስለመሆኑ ተነግሮኛል።

    ከእነዚህ ከዚህ በላይ ከተዘረዘሩት ተደጋጋሚ የመብት ጥሰቶች በግልፅ መረዳት እንደሚቻለውና በእኔ በኩል እንደምገነዘበውም መንግሥት በእኔ ላይ ይህን ሁሉ የመብት ጥሰት እየፈፀመ የሚገኘው የፈፀምኩት ወንጀል ስላለ ሳይሆን መብቴን በሕገ-ወጥ መንገድ በመጣስና በመገደብ ከፖለቲካ ተሳትፎ ውጭ እንድሆን ስለፈለገ ነው።

    እኔ አመልካቹ የአለፈ ታሪኬ እንደሚያሳየው ለሃያ ስምንት ዓመታት በሀገሪቱ ፖለቲካ በነበረኝ ተሳትፎ ስድስት ጊዜ በሕገ-ወጥ መንገድ በፈጠራ ክስ የታሰርኩ ቢሆንም አንድም ጊዜ በወንጀለኝነት ተፈርዶብኝ አያውቅም። የኢትዮጵያ ህዝብ በግልፅ እንደሚያውቀው በዚህ የረጅም ጊዜ የፖለቲካ ተሳትፎዬ ስታገል የኖርኩት በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም፣ እርቅና የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን ሲሆን፤ በአንፃሩም ሕገ-ወጥነትን፣ አመጽንና የኃይል አማራጭን በግልፅና በድፍረት በማውገዝ የምታወቅ ሰላማዊ የፖለቲካ ሰው ነኝ። ሆኖም መንግሥት ከላይ በተገለፀው ሁኔታ በፈጠረብኝ ተከታታይ ሕገ-ወጥ ጫና ምክንያት በአሁኑ ወቅት ከፖለቲካ ተሳትፎዬ ሙሉ በሙሉ ለመገለል የተገደድኩ ሲሆን ከዚያም በላይ ያለብኝን ከፍተኛ የልብ ህመም ወደ ውጭ ሀገር ሄጀ መታከም ባለመቻሌ ምክንያት በህይወት የመኖር ዕድሌ ከፍተኛ አደጋ ላይ ወድቋል። በአጠቃላይም እየደረሰብኝ ባለው ተደጋጋሚ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ምክንያት ለከፍተኛ የጤና መታወክ፣ የሞራል ውድቀት፣ የገንዘብና የጊዜ ብክነት ተዳርጊያለው።

    ይህ ሁሉ በተደጋጋሚ የተፈጸመብኝ በደል አልበቃ ብሎም እኔ አመልካቹ ፈጽሞ ባልተነገረኝና በማላውቀው ሁኔታ፣ ምንም ዓይነት ጥያቄ ባልቀረበልኝና ምርመራ ባልተካሄደበት ሁኔታ፣ ከዚያም በላይ ተፈልጌ የጠፋሁ ወንጀለኛ የሆንኩ በሚያስመስል ሁኔታ የጉዞ እገዳ የተጣለብኝ ስለመሆኑ የአራዳ ፍርድ ቤት ሰጠ የተባለው ትዕዛዝ አሁንም በእኔ ላይ የፈጠራ ክስ እንደገና በመመሥረት እንድታሰርና ሕይወቴ አደጋ ውስጥ እንዲወድቅ እየታሰበና ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ነው።

    በአንድ ሰው የደረሰ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በሁሉም ሰው ላይ እንደደረሰ ጥሰት የሚቆጠር መሆኑን ታሳቢ በማድረግና በእኔ ላይ እየተፈፀመ ያለው ተደጋጋሚ መቋጫ ያጣ የሰብዓዊ መብት ጥሰትም የፖለቲካና ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ ሕገ-መንግሥታዊ መብቴን ከመጣስም በላይ በሕይወት ለመኖር ያለኝን የማይገሰስ ሰብዓዊ መብቴን አደጋ ላይ የጣለ መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት፥ መሥሪያ ቤታችሁ በጉዳዩ ልዩ ትኩረት በመስጠት ምርመራ እንዲያካሂድልኝና አስቸኳይ መፍትሔ እንዳገኝ እንዲያግዘኝ በድጋሚ በአክብሮት እጠይቃለሁ።

    ከሰላምታ ጋር!
    ልደቱ አያሌው

    ግልባጭ፦
    ለመገናኛ ብዙሀን

    አቶ ልደቱ አያሌው ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የጻፉት ደብዳቤ

    Anonymous
    Inactive

    ሕዝባችን ከመቼውም ጊዜ በላይ የተጋረጠበትን መንግሥታዊ ሽብር በተደራጀ አግባብ እንዲከላከል ጥሪ እናቀርባለን!
    የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)

    ድርጅታችን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በአንድ በኩል በሕዝባችን ላይ ለበርካታ አስርተ ዓመታት የቀጠለውን ሕግና መዋቅር ሠራሽ የፖለቲካ ሸፍጥ በዘላቂነት ለመቅረፍ፣ በሌላ በኩል ሕዝባችንና ሀገራችን ከተጋረጠባቸው የኅልውና አደጋዎች ለመታደግ በሚደረገው ሀገራዊ የበጎ ኃይሎች ጥምረት አካል በመሆንና በትጋት በመሥራት ላይ የሚገኝ መሆኑን በሀቅ የሚፈርድ ሁሉ የሚረዳው እውነታ ነው።

    ምንም እንኳን ትጋታችን ለማንም አካል በመታያነት የቀረበ ባይሆንም፥ እጅግ ፈታኝ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ እንኳ ሆነን “የተሻለ ነገ” ሊመጣ ይችላል የሚል እሳቤን አንግበን እዚህ ደርሰናል።

    ቀደም ሲል በተደጋጋሚ ለመንግሥት እንዳሳሰብነው መሠረታዊ የሆኑ የለውጥ ሀሳቦችን መሬት ለማስረገጥና የተሳሳተውን የማደራጃ ትርክት፣ የተዛነፈውን መዋቅራዊና ሥርዓታዊ ማእቀፍ በማስተካከል ሕዝብን ለዘላቂ ሰላምና ሥልጣን ለማብቃት የበኩላችንን ያልተቋረጠ ጥረት ከማድረግ ጎን ለጎን በተለይ ሀገራችንና ማዕከላዊ ሥርዓቱ እንዳይፈርሱ ለማድረግ በተደረጉ ጥረቶች ሁሉ አብንና የአማራ ሕዝብ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል።

    ሆኖም፦

    1/ መንግሥታዊ ሽብሩን በማባባስ፣ በመደገፍ እና ትእዛዝ በመስጠት ጭምር የሚሳተፉት የሀገራችን ጠቅላይ ሚንስቴርና የሚመሩት የኦሮሞ ብልጽግና ክፍል መንግሥታዊ መዋቅርንና የሀገር ሀብትን በመጠቀም የአማራን ሕዝብ የማሸበር ተግባር አጠናክረው ቀጥለዋል። ሕዝባችንን ለማሸበር የተከፈተው መጠነ-ሰፊ የዘር ፍጅት በመንግሥት መዋቅር በቀጥታ የሚደገፍና የሚመራ መሆኑን አብን ያምናል። ለዚህም የሚከተሉትን ነጥቦች በጉልህ ማሳያነት ማቅረብ ይቻላል።

    ሀ/ በአማራ ሕዝብ ላይ የተቀናጁ የጅምላ ፍጅት ጥቃቶችን የከፈተው በተለምዶ “ኦነግ ሸኔ” ተብሎ በጠቅላይ ሚንስትሩ የሚጠራው አካል ከመነሻው ከነትጥቁ ወደ ሀገር ቤት የገባበትን አሻጥር፤

    ለ/ ከዚያ ቀደም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጭምር እንደገለጹት ከተጠቀሰው ድርጅት ጋር የነበራቸው መረጃን የመለዋወጥ ድብቅ ግንኙነት የሚታወቅ በመሆኑ ከልጅነት እስከ እውቀት አጋር የሆናቸውን ድርጅት አሁንም በልዩ ስልት የማደራጀት፣ የመደገፍ እና የመንከባከብ ሚናቸውን እየተጫወቱ እንደሆነ ንቅናቄያችን በጽኑ ያምናል።

    ሐ/ የ“ኦነግ ሸኔ” ኮር ስትራቴጂክ አመራር በመሀል አዲስ አበባ ውስጥ ተቀምጦ እየመራ ባንኮችን ጭምር በጠራራ ፀሐይ በመዝረፍ ኃይል እንዲያጎለብት የተፈቀደበትና የተመቻቸበት አግባብ መኖሩ፤

    መ/ በአማራ ሕዝብ ላይ እየተፈፀመ ያለውን ተደጋጋሚ የዘር ጥቃት ማስቆም ይቅርና ጅምላ ፍጅቱ በሀገር ደረጃ ለሀዘን መግለጫ እንኳ እንዳይበቃ የተደረገ ከመሆኑም በላይ በሀዘን ድንኳናችን ላይ ቀይ ምንጣፍ አንጥፈው ሕንፃ እና አበባ የሚመርቁበት አስደንጋጭ ማኅበራዊ ስላቅ ሳይቋረጥ መቀጠሉ፤

    ሠ/ በአማራ ሕዝብ ላይ የተከፈተው ዘር-ተኮር ጥቃት የታቀደና የተቀናጀ ሲሆን፥ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጭምር የዘር ማጥፍት ወንጀል ለማስፈጸም አመላካች የሆኑ የመግቢያ ንግግሮችን በይፋ ሲያሰሙ መቆይታቸውና ለዚህም ምንም ዓይነት አስተዳደራዊም ይሁን ፖለቲካዊ እርምት አለመሰጠቱ፤

    ጠቅላይ ሚንስትሩና የሚመሩት መንግሥት በዚህ የአማራን ሕዝብ የማሸበርና የዘር ፍጅት እንቅስቃሴ ውስጥ ሚና አላቸው ብሎ ንቅናቄያችን ለማመን ተገዷል።

    2/ የአማራ ክልል መንግሥት ከተፈጥሯዊውና መደበኛው የታዛዥነት መንፈስ አለመውጣቱ፣ ደንታ ቢስነቱና አቅመ ቢስነቱም እየበረቱበት መሆኑ ሕዝባችንን አቻ ለማይገኝለት ማኅበራዊ ውርደት ያበቃ በመሆኑ፤

    አብን የአማራ ሕዝብ ትግል ከተለመደው አካሄድ ተላቆ ኅልውናውን የመታደግና የማስከበር የተቀናጀና የተጠናከረ የትግል ምእራፍ ውስጥ መግባት አለበት የሚል ድምዳሜ ደርሷል። ትግሉንም ለመምራት ንቅናቄያችን ከፊት ይሰለፋል።

    መላው የአማራ ሕዝብም የተከፈተበትን አጠቃላይ የኅልውና አደጋ በመገንዘብ እና ለደኅንነቱ የሚያስብለት መንግሥት እንደሌለው በመረዳት ራሱን የመከላከል ተፈጥሯዊ መብቱን እንዲሠራበት አብን በአጽንዖት ያሳስባል። ሕዝባችንም በዚህ ፈታኝ ወቅትም ወዳጅ መስለው በጠላትነት በቆሙ ቡድኖችና ግለሰቦች ግፊት ፈተና ላይ እንዲወድቅ የሚፈለገውን አንድነቱን አጠናክሮ እንዲጠብቅ እናሳስባለን።

    በሀገር ውስጥም ይሁን በውጭ ሀገራት የምትገኙ ወገን ወዳድ ኢትዮጵያውያን፥ በመሠረቱ ያንዣበበው አደጋ በአማራ ሕዝብ ላይ ብቻ ተወስኖ የሚቆም አለመሆኑን በመገንዘብ በአማራ ሕዝብ ላይ በተቀናጀ ሁኔታ እየተፈፀመ ያለውን የዘር ፍጅት ጥቃት እንድታወግዙና የመልሶ ማቋቋም ሥራዎችን እንድታግዙ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።

    በተለያዩ ስምሪቶች በቅንነት ሀገራችሁን የደገፋችሁ መስሏችሁ ለሥርዓቱ እገዛ የምታደርጉ ወገኖች ሂደቱን በመገምገም ጥያቄ እንድታነሱና ከተገፉ ወገኖች ጎን እንደትሰለፉ ጥሪ እናቀርባለን።

    በሀገር ውስጥም ይሁን በውጭ ሀገራት የምትኖሩ የአማራ ተወላጆች በእያንዳንዱ ቀን የአማራ ሕዝብ ደም እንደጅረት የሚፈስበት ሀገር መሆኑን በመረዳት፥ አማራው ለአጠቃላይ የኅልውና አደጋ የተጋለጠ መሆኑን በመቀበልና መሠረተ-ቢስና መናኛ ከሆኑና የሞራልና የታሪክ ተጠያቂነት ከሚያስከትሉ ልማዳዊ የፖለቲካ ዘይቤዎች በአስቸኳይ በመላቀቅ ሰብዓዊ፣ ወገናዊና ሀቀኛ የሆነ የፖለቲካ አቋም በመውሰድ ሕዝብ የመታደግ ድርሻችሁን እንድትወጡ የሚል ታሪካዊ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።

    ኅልውናችንን በትግላችን እናስከበራለን!
    እጣፋንታችንን በራሳችን እጆች እንጽፋለን!
    የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)

    የፖለቲካ ፓርቲዎች ድምጽ (ኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች)

    ሕዝባችን ከመቼውም ጊዜ በላይ የተጋረጠበትን መንግሥታዊ ሽብር በተደራጀ አግባብ እንዲከላከል ጥሪ እናቀርባለን

    Anonymous
    Inactive

    ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የተሰጠ ወቅታዊ መግለጫ

    የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንና ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር አዲስ አበባ ከተማን ከማንኛውም የፀጥታ ስጋት የፀዳች ለማድረግ ባካሄደው የአንድ ሳምንት የተቀናጀ የጋራ የፀጥታ ኦፕሬሽን ውጤት ማስመዝገቡን ገለፀ።

    ኮሚሽኑ የፀጥታ ሥራውን በብቃት ለማከናወን የሚያስችል ዕቅድ አዘጋጅቶ የጋራ በማድረግ በተግባር ምዕራፉ የመጀመሪያ ሳምንት ባካሄደው ሁለንተናዊ ሰላምና ደህንነትን የማረጋገጥ ሂደት ባከናወናቸው ጠንካራ የወንጀል መከላከል ተግባራት

    1. በተደራጀ መንገድ ታቅደው የሚፈፀሙ የዘረፋና የግድያ ወንጀሎች፣
    2. የግል ትራንስፖርት አሽከርካሪዎች ላይ የሚፈፀም አፈና እና ግድያ፣
    3. የተሽከርካሪ ስርቆት፣
    4. ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ እና ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ወንጀሎችን መቀነስ መቻሉን ገልጿል።

    ኮሚሽኑ እንደገለፀው በእነዚህ ወንጀሎች የተጠረጠሩ 359 ተጠረጣሪዎች ተከታትሎ በሕግ ቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝና ከዚህ ውስጥ

    ትግራይ ላይ በተፈፀመው የጁንታው ጥቃት የተሳተፉና በተለያየ መንገድ አምልጠው ወደ አዲስ አበባ ከተማ በመግባት በተለያየ የወንጀል ተገባር ሲሳተፉ በተገኘ የሕዝብ ጥቆማ 135 ተጠርጣሪዎች እንዲሁም ከዚሁ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ሰባት የኦነግ ሸኔ አባላት በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ በማጣራት ላይ መሆኑን ኮሚሽኑ ገልጿል።

    ኮሚሽኑ ኅብረተሰቡን ከጎኑ በማሰለፍ በተቀናጀ የጋራ ኦፕሬሽን በተለያዩ በወንጀል የተጠረጠሩ የነፍስ ወከፍና የቡድን ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያዎች፣ የሀገር ውስጥ ሀሰተኛ ገንዘብ እና የተለያዩ የውጭ ሀገራት ገንዘቦች፣ በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ሀገር ውስጥ ገብተዋል ተብለው የተጠረጠሩ ተሽከርካሪዎች፣ በዘረፋና በግድያ ከተወሰዱ 10 ራይድ ተሽከርካሪዎች ስምንቱ እንደተያዙና የሁለቱ አካላቸው እንደተፈታ ፖሊስ ደርሶበት በቁጥጥር ስር አውሎ በዚህ ወንጀል የተጠረጠሩ 11 ግለሰቦችን ይዞ ምርመራ እየተጣራባቸው መሆኑን አመልክቷል።

    ኮሚሽኑ ባካሄደው የጋራ ኦፕሬሽን የኑሮ ውድነት ለማባባስ እና የንግድ ስር-ዓቱን ለማዛባት የሚንቀሳቀሱ አካላትን በዚህ ኦፕሬሽን በቀጥጥር ስር አውሎ ከእነሱም ብዛት ያላቸው ሸቀጦችና ቁሳቁሶችን በቁጥጥር ስር አውሏል።

    በሌላ በኩል ኮሚሽኑ ባካሄደው በዚህ የጋራ ኦፕሬሽን በቁጥጥር ስር ካዋላቸው ንብረቶች መካከል በዝርፊያ የተወሰደ አንድ ሲኖ-ትራክ ከባድ መኪናንና ከግለሰቦች የተነጠቁና ከድርጅቶች የተዘረፉ ባርካታ ተንቀሳቃሽ ስልኮችን በመያዝ ለባለ ንብረቶቹ ተመላሽ ማድረግ የተቻለ ሲሆን ሐሰተኛ መታወቂያ በመቀያየርና በመጠቀም በተለያዩ የተሽከርካሪ መሸጫ ድርጅቶች እየተቀጠሩ ተሽከርካሪዎችን በሌሎች በማሰረቅ የተጠረጠሩ አራት ግለሰቦች መያዛቸውንም ጨምሮ ገልጿል።

    በመጨረሻም ኮሚሽኑ ይህ ከጅምሩ ውጤት ያስመዘገበ የተቀናጀ የጋራ የፀጥታ ኦፕሬሽን ወደ ፊትም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ገልፆ የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ደህንነት አስተማማኝና ዘላቂ ይሆን ዘንድ የሰላሙ ባለቤት የሆነው መላው የከተማው ህዝብ ለሁከትና ብጥብጥ የሚያነሳሱ መረጃዎችን ባለመቀበልና ሀሰተኛ መረጃዎችንም ባለመጋራት እንዲሁም ለፖሊስ ዓይንና ጆሮ ሆኖ ለፀጥታ ስጋት የሆኑ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙት በፍጥነት እንደተለመደው መረጃ በመስጠት እንዲተባበር እየጠየቀ ለዚህ ኦፕሬሽን መሳካት የከተማው ህዝብ ላደረገው ከፍተኛ አሰተዋጽኦ ኮሚሽኑ ሌሎች የፀጥታ ሀይሎችንም በመወከል የላቀ ምስጋና ያቀርባል።

    የኢፌዲሪ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን
    መጋቢት 18 ቀን 2013 ዓ.ም

    የኢፌዲሪ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን

    Anonymous
    Inactive

    የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ እና የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ በጋራ ለመሥራት የሚያስችል የትብብር ስምምነት ተፈራረሙ
    ባልደራስ እና አብን ትብብርን አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ

    የሀገራችን ሕዝብ ለዘመናት በተጫኑበት ኢዲሞክራሲያዊና አምባገነን አገዛዞች የተነሳ፥ በነፃነት እጦት፣በስቃይ እና በመከራ ኑሮውን እንዲገፋ ተደርጓል። ጭቆናን አስወግዶ የሚፈልገውን ፍትህ እና እኩልነት እውን ለማድረግ ከፍትኛ ዋጋ መክፈሉም እሙን ነው።

    ይሁንና የሀገራችን የለውጥ ፍላጎት እና እንቅስቃሴ ጅማሮው ሳይሳካ፥ ለቀጣዩ ዴሞክራሲያዊ ትግል ተስፋ ሊሆን የሚችል መሠረታዊ የትርክትና የመዋቅር ክለሳ እንኳ ሳይደረግ አምባገነንነትና ዘረኝነት የእጅ ለውጥ ብቻ እያደረጉ የሚፈራረቁባት ሆናለች። በዚህ ሁሉ ፈተና ውስጥ ያለፈው ሕዝባችን አሁንም ዲሞክራሲን፣ እኩልነትንና ዘላቂ ሰላምን በመሻት ለነፃነት የሚያደርገውን ትግል አጠንክሮ እንደቀጠለ ይገኛል።

    የዚህ ዓይነት መልክና ይዘት ተላብሶ የተደራጀው የተፎካካሪ ኃይል ለሰርጎ ገቦች የተጋለጠ፣ በተፈጥሮው ደካማና ተሰባሪ ከመሆኑም በላይ የአምባገነኑን ሥርዓት ራዕይ አቀንቃኝ እስከመሆን ደርሶ እንደነበር ይታወሳል። በተጨማሪ የተቃውሞው ጎራ እርስ በርሱ በፍረጃና በሴራ መጠላለፍ ምክንያት በቁርሾ እንዲሞላ በማድረግ የጋራ ሀገራዊ ስምሪት መውሰድ እንዳይችል አድርጎት ቆይቷል።

    በዚህ ሂደት ውስጥ አምባገነኖችን በጋራ መታገል ጥረት ከማድረግ ወርደው በመናኛ ፍላጎቶችና በጥቃቅን ልዩነቶች ዙሪያ ታጥረው ሲሻኮቱ በመካከል የባከነው ጊዜ እና የሰው ህይወት የሚያስቆጭ ነው።

    የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሀገራችንን ለእድሜ ልክ ዝቅታ የዳረጋት የጥላቻ ትርክት፣ ትርክቱን መሠረት አድርገው የተደነገጉ ሕግጋትና የተዘረጉ መዋቅሮች ተከልሰው መላ ኢትዮጵያውያን በእኩልነት፣ በወንድማማችነት፣ በፍትህና በሰላም የሚተዳደሩነት ዘላቂ ሥርዓት በማስፈን በተለምዶ “መንታ ቅኝት” ያለው የትግል እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል። የአብን ስትራቴጂክ ግብ መላውን ኢትዮጵያዊ የፍትሀዊ አማካኝ ተጠቃሚ በማድረግ ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግ የፖለቲካ ማዕቀፍ እንዲፈጠር ሲሆን የድርሻውን ለማበርከት አበክሮ እየሠራ ያለ ንቅናቄ ነው።

    ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) ደግሞ የኢትዮጵያዊ ኅብር ዓይነተኛ መገለጫ የሆነችውን የአዲስ አበባ ከተማ ሕዝብ ከከፋፋይና ከጥላቻ ፖለቲካ ነፃ ለማድረግና ሕዝቡ ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብቱ እንዲረጋገጥ ለማስቻል በሚል የተደራጀ ስለመሆኑ በሰፊው የሚታወቅ ነው።

    አዲስ አበባ ከተማ የኗሪዎቿ መሆኗን ለማረጋገጥ የሚያደርጉት የጋራ ትግል መነሻ ዴሞክራሲን፣ ነፃነትን፣ ፍትህንና እኩልነትን በማስፈን ላይ የተመሠረተ ሲሆን፥ አንዳች ቅቡልነት ያለው መርህ ወይም ምክንያት ማጣቀስ የማይችሉ ኃይሎች ከተማዋ የአንድ ንጥል ብሔር ንብረት መሆኗን በይፋ በመግለፅ የማታገያ አጀንዳ በማድረግ ሕዝቡ በነሱ ፍቃድና ይሁንታ መኖር እንዳለበት አድርገው ያወጁት ያልተገራ ፍላጎት የጋረጠበትን የህልውና ስጋት መቀረፍ እንዳለበት አብን እና ባልደራስ የጋራ ፖለቲካዊ አቋም ወሰደዋል።

    የሀገራችን ኢትዮጵያ መድናና የመላ ሕዝቧ ሰላማዊ መኖሪያ ሆና ዘመናትን የተሻገረችው አዲስ አበባ መደበኛና ነባር ምልከታ ሊቸራት ሲገባ ከልቦለድ የመነጨ የዘረኞች “የልዩ ጥቅም”ቀንበር ጊዜ በረዘመ ቁጥር የሕግና የፖለቲካ ቋጠሮው እየጠበቀ መምጣቱና ይዘቱ “በኦሮሚያ ክልል አስተዳደርና በአዲስ አበባ መስተዳደር ስምምነት” እንደሚወሰን በተሻሻለው ቻርተር መደንገጉ ከተማዋንና ሕዝቧን ከአንድ ወገን በተሰባሰበ የፖለቲካ ኃይል ይሁንታ፣ ፍፁም ቁጥጥርና ጥበቃ ስር ለማዋል የተወሰነ መሆኑን ያሳያል። አብን እና ባልደራስ ይሄን አምባገነናዊ፣ ፍትህ አልቦ፣ ዘረኛ፣ አግላይና በመጨረሻም የግጭትና የብሔራዊ ደህንነት አደጋ የሆነ አፍራሽ እንቅስቃሴ በጋራ ተሰልፈው ለመታገል ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።

    ትብብሩ በቀጣይ እንዲፈጠርና እንዲጎለብት ለምንፈልገው የሀገራዊ በጎ ኃይሎች ጥምረት እርሾ ሆኖ እንዲያገለግል የታለመ ነው። አስቻይነት የሌለውና በሕግ የተደነገገው የጊዜ ገደብ ጉዳይ በነባራዊ ተግዳሮቶች ምክንያት የተፈጠረ መሆኑን በማረጋገጥ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተመሳሳይ አንድምታ ያላቸውን ጉዳዬች ባስተናገደበት ሁኔታ ትብብሩ ለህጋዊ እውቅና ሲቀርብ በመፍቀድና በመመዝገብ እንዲያፀድቀው የሚቀርብ ይሆናል።

    በዚህ መነሻነት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እውን ለማድረግ ለሚደረገው ትግል በመጪው ሀገራዊ ምርጫ የመራጮችን የጋራ ፍላጎትና ራዕይ ለማሳካት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ /አብን/ እና ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ /ባልደራስ/ በጋራ የምንሠራበት የፖለቲካ ትብብር ፈጥረን ለመሥራት መወሰናችንን ለመላው ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን፣ ለመላው አማራ ሕዝብና ለአዲስ አበባ ሕዝብ ስናበስር በታላቅ ደስታ ነው። ሌሎች ፓርቲዎችን ጨምሮ በሁለቱ ፓርቲ አመራሮች መሃከል ለወራት ሲካሄድ የነበረው ረዥምና አድካሚ ድርድር ፍሬ አፍርቶ መጪውን ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ የአብን እና የባልደራስ ትብብር አሸናፊ ሆኖ መውጣት የሚያስችላቸውን የጋራ ስልቶች ቀይሰው በይፋ መንቀሳቀስ ጀምረዋል።

    አብን እና ባልደራስ፣ አጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ የአማራ ሕዝብ እና የአዲስ አበባ ከተማ ኗሪ ሕዝብ በበደል ውስጥ አምጠው የወለዷቸው የቁርጥ ቀን ልጆቹ እንደመሆናቸው መጠን በተባባረ ክንድ በሕዝባችን ላይ የተጫነውን የመከራ ቀንበር እንዲወርድ ከመቼውም ግዜ በላይ በጋራ ትብብር ለመታገል በቁርጠኝነት ተሰልፈዋል።

    አብን በጽንፈኞች የተሳሳተ ትርክት መነሻነት በአማራ ሕዝብ ላይ በተከታታይ የሚደርሰው ግፍ ድምጽ በመሆን በመጀመሪያው ረድፍ ሆኖ ትግሉን እየመራ ይገኛል። አብን የሀገራችን ኢትዮጵያን ደህንነት ለማረጋገጥና ህልውናዋን ለማስቀጠል አንድ ወሳኝ አምድ የሆነው የአማራ ሕዝብ በልዩ ሁኔታ ተፈርጆ የሚጠቃበትን የፅንፈኞች ስሁት ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ለመግታት የሚያስችል ልዩ ማዕቀፍ ሆኖ የተደራጀ ሲሆን ታሪካዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ስሪቱ በኢትዮጵያዊነት፣ ምልከታውም በወንድማማችነት፣ በፍትህና በዴሞክራሲ የተቃኘ ስለመሆኑ ውሎ ያደረ ጉዳይ ነው።

    ከላይ በሰፊው እንደተመላከተው ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ በአዲስ አበባ ከተማ ሕዝብ ላይ የተጋረጡ የህልውና አደጋዎችን ለመከላከል፣ የከተማዋ ሕዝብም ራሱ በዴሞክራሲያዊ መንገድ በመረጣቸው እንደራሴዎቹ የመተዳደር መብቱን ለማስከበር ባሚያደርገው እልህ አስጨራሽ ትግል ውስጥ በብቃትና በንቃት በነሳተፍ አያሌ መስዋዕቶችን በመክፈል የቀጠለ መሆኑን ራሱ ሕዝቡ በተግባር ኖሮ ያረጋገጠው ሀቅ ነው። ከላይ በተጠቀሱት መሠረታዊ ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ ግቦች ዙሪያ ሁለቱ ድርጅቶች በፅኑ የሚጋሯቸውን አቋሞች መሠረት በማድረግ ቀጣይ ለሚደረገው ጠንካራና የተቀናጀ የሕዝብ ትግል ወሳኝ የማታገያ አጀንዳ እንዲሆኑ ስምምነት ላይ ደርሰዋል።

    በሀገር አቀፍ ደረጃ ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው ምርጫ መላው የሀገራችን ሕዝብ፣ በተለይም የአማራ ሕዝብና የአዲስ አበባ ሕዝብ የተደቀነባቸውን የህልውና አደጋ በትብብር ከመታገል ውጭ ሌላ ተጨባጭ የመፍትሄ አማራጭ እንደሌለ መተማመን ላይ ደርሰዋል።

    ከዚህ ቀደም በጋራ አብረውን ለመሥራት ንግግር ጀምረው ሳለ በተለያዩ ምክንያቶች በትብብሩ ለመዝለቅ ያልቻሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሁንም ጊዜው አለመርፈዱን ተገንዝበው በጎ ፍላጎት ካሳዩን ከግማሽ መንገድ ባላይ ተጉዘን ለመቀበል ዝግጁ መሆናችንን በዚህ አጋጣሚ ለማረጋገጥ እንወዳለን።

    የፈጠርነው ትብብር አርአያ መሆን የሚችልና ከትላንት ለተሻለ አዲስ የፖለቲካ ባህል ማሳያ ፈር ቀዳጅ እንደመሆኑ ከምርጫ በኃላም ትብብሩ ጎልብቶ፤ የሀገራችንን ሕዝብ ለዘመናት የቆየ የፍትህ ትግል ዳር ለማድረስ እንዲሁም የመላው ኢትዮጵያዊ የሆነችውን የአዲስ አበባ ከተማን ዓለም አቀፍነት የሚመጥን አመራር ለመስጠት ለመፍጠር ከወዲሁ አብረን መቆም ጀምረናል።

    አብን እና ባልደራስ የአዲስ አበባ ሕዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር ዴሞክራሲያዊ መብት አክብረው ከሚቀበሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ትብብር በመፍጠር የከተማዋ ሕዝብ በፌደራል መንግሥቱ ውስጥ ተወክሎ እንደሁሉም ሕዝብ ጥቅሙን ለማስጠበቅ የሚያደርገውን ትግል የማሳለጥ ሚና እንደሚኖረው ለማሳወቅ እንወዳለን።

    አዲስ አበባ በሁሉም ኢትዮጵያውያን ጥረት የተገነባች፣ የአፍሪካ የዲፕሎማሲ ዋና ከተማ ብትሆንም፥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተነሱ ተረኞች ከተማይቷን በልዩ ጥቅም ስም የአንድ ቋንቋ ተናጋሪ ብቸኛ ንብረት ለማድረግ የሚደረገው እንቅስቃሴ በጋራ አጥብቀን እናወግዛለን። በከተማይቱ እና ነዋሪዎቿ ላይ የተደቀነውን ይህ አደጋ ለመከላከል ባልደራስ በዋነኛነት እያካሄደ ያለውን ትግል አብን የሚያድንቅ እና በሙሉ ልብ ከጎኑ እንደሚሰለፍ ቃል ይገባል። በአንጻሩም ባልደራስ ፓርቲ በጽንፈኞች ሴራ ዒላማ እንዲሆን በተደረገው የአማራ ሕዝብ ላይ የሚደርሰውን ግፍ እና በደል ለማስቀረት በቁርጠኝነት አብን ለሚያደርገው ትግል ክብርና እውቅና እንደሚሰጥ ለመግለፅ እንወዳለን፡፡

    ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው ስምምነታችን የተበላሸውን የሀገራችንን ፖለቲካ ባሕል በማስተካከል፣ በውይይትና በሰጥቶ መቀበል መርህ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል አብሮ መቆም እንደሚገባ ከማሳየት ባሻገር፥ ሌሎች ለተመሳሳይ አላማ ያነገቡ ፓርቲዎችም ይህን ፈለግ ተከትለው የትብብሩ አካል እንዲሆኑ ፅኑ ፍላጎት አለን።

    በመጨረሻም በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች ጽንፈኛ ኃይሎች በሚፈጽሟቸው የሽብር ድርጊቶች ምክንያት እየደረሰ ያለውን ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ መፈናቀል እና የንብረት ውድመት ለማስቆም በየእርከኑ ያሉ የፌደራል እና የክልል መንግሥታት ኃላፊዎች ተግተው እንዲሠሩ ጥሪ እናቀርባለን።

    በተለይ ችግሩ ተባብሶ በሚገኝባቸው የኦሮሚያ፣ የቤንሻንጉል እና አንዳንድ የደቡብ ክልል አካባቢዎች የሚገኙ የመንግሥት አስተዳደርና የፀጥታ አካላት ችግሩን የሚመጥን ኃላፊነት በመውሰድ ንፁኃንን ከጥቃት እንዲከላከሉና ወንጀለኞችን ለሕግ እንዲያቅርቡ በአፅንኦት እንጠይቃለን።

    መሠረተ-ቢስ በሆነ ክስ ተወንጅለው ለእስር የተዳረጉትንና የመምረጥና መመረጥ መብታቸውን የተነፈጉ የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ አመራሮች በአስቸኳይ እንዲፈቱ እናሳስባለን። ትህነግ በለኮሰው ጦርነት በትግራይ ክልል ሕግ ለማስከበር እየተካሄደ ባለው ዘመቻ የንጹኃን ዜጎቻችንን ደህንነት እና የሰብዓዊ መብት እንዳይጣስ ልዩ ትኩረት እንዲደረግና የሰብዓዊ ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለማሳሰብ እንወዳለን።

    መጋቢት 9 ቀን 2013 ዓ.ም.
    የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ /ባልደራስ/
    የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ /አብን/

    ባልደራስ እና አብን በጋራ ለመሥራት

    Anonymous
    Inactive

    ሀገራችን ኢትዮጵያ ያለችበት የሕልውና አደጋ በአቶ ልደቱ አያሌው እይታ

    ስንብት፥ ለመሰንበት
    ልደቱ አያሌው
    የካቲት 29 ቀን 2013 ዓ.ም.

    ሀገራችን ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የሕልውና አደጋ ውስጥ ትገኛለች። ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ የሆነ የዕውቀት፣ የአቅምና የቅንነት ድክመት ያለበት በመሆኑ ሀገሪቱ የገጠማትን ችግር ከማቃለልና ከመፍታት ይልቅ፥ የበለጠ እያባባሰውና እያወሳሰበው ይገኛል። በዚህም ምክንያት ሀገራችን ሕልውናዋን የሚፈታተን አሳሳቢ የእርስ በርስ ግጭት ውስጥ ከመግባቷም በላይ፥ ከኤርትራና ከሱዳን መንግሥታት ግልጽ ወረራ ተፈጽሞባታል። ከታሪኳና ከማንነቷ በተቃራኒም ይህንን ግልጽ ወረራ  ለመቀልበስ የሚያስችል አቅምና ወኔ ያጣች ደካማ ሀገር ሆናለች። ይህ ክስተት ሀገሪቱ ምን ያህል በሂደት ውስጣዊ አንድነቷ እየተዳከመ እንደመጣና ወደ መበታተን አደጋ ውስጥ እየገባች ስለመሆኑ አንድ ማሳያ ነው።

    ብልጽግና ፓርቲ እያራመደ በሚገኘው የተሳሳተ የውጭ ግንኙነት ምክንያትም ሀገራችን ለከፍተኛ የዲፕሎማሲ ጫና ተጋላጭ በመሆን ብሔራዊ ጥቅሞቿንና ሉዓላዊነቷን በአግባቡ ማስከበር የማትችልበት ሁኔታ ውስጥ ገብታለች። ‘በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ’ እንዲሉም ሀገራዊ ሕልውናችንን በሚፈታተን መጠን ኢኮኖሚያችን ወደ ጥልቅ ቀውስና ኪሣራ ውስጥ እየገባ ይገኛል።

    ይህ ሁሉ እየሆነ ያለው በብዙ የሕይወት መሥዋዕትነት የተገኘውና የዛሬ ሦስት ዓመት ገደማ ተጀምሮ የነበረው የለውጥ ሂደት በአመራር ድክመትና በአምባገነናዊ ባህርይ ምክንያት እንዲከሽፍ በመደረጉ ነው። በሥልጣን ላይ የሚገኘው ብልጽግና ፓርቲ ለለውጡ መምጣት ምክንያት የሆኑትን ፖለቲካዊ ችግሮች ሕጋዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ በሆነ አግባብ ከመፍታት ይልቅ አማራጭ ሀሳቦችን በማፈን፣ በፖለቲካ ተቀናቃኞቹ ላይ የስም ማጥፋት ዘመቻ በማካሄድና የፈጠራ ክስ በመመሥረት፣ በሕገ-ወጥ መንገድ ተቀናቃኞቹን በማሰርና ‘ለሕልውናዬ ስጋት ናቸው’ ብሎ የሚፈራቸውን የፖለቲካ ድርጅቶች ሕጋዊ ዕውቅና በመሠረዝ ጭምር ካለፈው የ27 ዓመቱ የኢሕአዴግ ሥርዓት የባሰ እንጂ የተሻለ አለመሆኑን በተግባር አሳይቷል። ባጭሩ፥ ሀገራችን ከእንግዲህ በብልጽግና ፓርቲ ወይም በዶ/ር ዐቢይ አሕመድ እየተመራች ከአንድ ቀውስ ወደ ሌላ የባሰ ቀውስ የመሸጋገር እንጂ ወደ በጎና የተሻለ ሥርዓታዊ ለውጥ የመሸጋገር ዕድል እንደሌላት በማያሻማ ሁኔታ ግልጽ ሆኗል።

    እኔም ሆንኩ አባል የሆንኩበት ፓርቲ፥ በአንድ በኩል የተጀመረው የለውጥ ሂደት ስኬታማ እንዲሆን ከተፈለገ ምን ዓይነት መዋቅራዊ ለውጦች በቅደም ተከተል መካሄድ እንዳለባቸው፤ በሌላ በኩል ደግሞ በአመራር ብቃት ማነስ ምክንያት የተጀመረው የለውጥ ሂደት ከከሸፈ በሀገራችን አጠቃላይ ሕልውና ላይ ሊያስከትል የሚችለው አደጋ ምን ያህል ከባድና አደገኛ እንደሚሆን የሚያሳስብ የሀሳብ ትግል ላለፉት ሦስት ዓመታት ስናካሂድ ቆይተናል።

    ነገር ግን የወቅቱ የሀገራችን ፖለቲካ በዕውቀት፣ በምክንያታዊነትና በሐቀኝነት የሚካሄድ ሳይሆን ብሔርተኝነት፣ ጽንፈኝነት፣ ሤረኝነት፣ ጥላቻና ውሸት የነገሠበት በመሆኑ ጩኸታችን የቁራ ጩኸት ሆኖ ቀርቷል። ሆኖም ቀደም ብለን ስናቀርበው የነበረው ስጋት ከተራ ሟርተኝነት ሳይሆን፥ ከተጨባጭ የፖለቲካ ግምገማ፣ ግንዛቤና ትንታኔ የመነጨ ስለነበር እንደፈራነው የለውጥ ሂደቱ ከሽፎ አሁን ሀገሪቱ ወደባሰና ውስብስብ የሕልውና አደጋ ውስጥ ገብታለች።

    የለውጥ ሂደቱን መክሸፍ ተከትሎ ሀገራችን ወደ ከፍተኛ የእርስ በርስ ጦርነት የገባችና በውጭ ኃይሎች ወረራ ሥር የወደቀች ቢሆንም፥ ግብዞቹ የብልጽግና አመራሮችና የእነርሱ የፕሮፓጋንዳ ሰለባ የሆኑ ተከታዮቻቸው ግን ዛሬም ጭምር ሀገሪቱ ወደላቀ የብልጽግና ጎዳና እየገሰገሰች እንደሆነ ሊነግሩን ሲደፍሩ እያየን ነው። ብልጽግና ፓርቲ የከሸፈን የለውጥ ሂደት ተከትሎ የሚካሄድ ሀገራዊ ምርጫ፥ የተጨማሪ ቀውስ ምንጭ ከመሆን ባለፈ ለሀገሪቱ መዋቅራዊ የፖለቲካ ችግሮች የሚያስገኘው ምንም ዓይነት አዎንታዊ ፋይዳ የሌለ መሆኑን መገንዘብ ተስኖት የሥልጣን ቅቡልነት ልባስ ለመደረብ ሲል ብቻ ትርጉም የለሽ ምርጫ ለማካሄድ እየተጣደፈ ይገኛል። ይህም ሀገሪቱ ወደባሰና ከቁጥጥር ውጭ ወደሆነ የፖለቲካ ቀውስ ልትገባ ትችላለች የሚል ተጨማሪና ምክንያታዊ ስጋት ፈጥሯል።

    በእኛ በኩል ውጤታማ ሽግግር ባልተካሄደበትና አንጻራዊ ሰላምና መረጋጋት ባልተፈጠረበት ሁኔታ በችኮላ ወደ ምርጫ ውስጥ መግባት አደገኛና ኃላፊነት የጎደለው ውሳኔ ነው የሚል የጠነከረ አቋም ያለን ቢሆንም፥ ምርጫው መካሔዱ የማይቀር ከሆነ ግን ቢያንስ በምርጫው ሂደት ሊፈጠር የሚችልን አደጋ ለመቀነስ በሚያስችል አግባብ በምርጫው ተሳታፊ ለመሆን በዝግጅት በማድረግ ላይ ነበርን።

    ነገር ግን ከሁሉም ነገር በላይ ሀሳብን አብዝቶ የሚፈራውና ከሀገሪቱ ደኅንነት በላይ ለራሱ የሥልጣን የበላይነት ሰፍሳፋ የሆነው የወቅቱ መንግሥት በመጭው ምርጫም ሆነ በቀጣዩ የትግል ሂደት ተሳትፎ እንዳይኖረን ስለፈለገና ስለወሰነ በሕገ-ወጥ መንገድ ፓርቲያችን እንዲሰረዝና ከትግሉ ሜዳ እንዲወገድ አድርጓል።

    በእኔ ላይም በባለቤትነት በሚቆጣጠራቸውና ለልዩ ተልዕኮ ባቋቋማቸው የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ቅጥረኞቹን አሰማርቶ ሰፊ የስም ማጥፋት ዘመቻ በማካሄድ፣ የዛቻና ማስፈራራት ድርጊት በመፈጸም፣ የፈጠራ ክስ በመመሥረትና በሕገ-ወጥ መንገድ በማሰር የትግል ተሳትፎዬን ለመገደብ ሞክሯል። ይህም አልበቃ ብሎት በፖለቲካ መድረኩ ላይ ብቻ ሳይሆን በሕይወትም እንዳልኖር ስለፈለገ፥ ያለምንም ሕጋዊ ድጋፍ ያለብኝን ከፍተኛ የልብ ሕመም ወደውጭ ሀገር ሄጄ እንዳልታከም እገዳ ጥሎብኛል። ይህ ሕገ-ወጥ እገዳ እንዲነሳልኝ የተለያዩ የመንግሥት ተቋማትንና ባለሥልጣናትን ለማነጋገርና ለመማጸን ያደረግኩት ጥረትም ስኬታማ ሳይሆን ቀርቷል። በዚህም ምክንያት ከፍተኛ የልብ ቀዶ ጥገና ሕክምና ለማድረግ የነበረኝ ቀጠሮ በመስተጓጎሉ በእያንዳንዱ ሰዓትና ዕለት ሕይወቴ ለዕልፈት ሊጋለጥ በሚችልበት አደጋ ውስጥ እገኛለሁ። በዚህ ድርጊቱም የወቅቱ መንግሥት አምባገነናዊ ብቻ ሳይሆን ምን ያህል ኢ-ሰብአዊ መሆኑን በተግባር አሳይቷል። በርግጥም ሥርዓቱ ከግለሰብ ግድያ ጀምሮ እስከ የሕዝብ ጅምላ ጭፍጨፋ ከሚደርስ ቀውስ የፖለቲካ ትርፍ ለመቃረም የሚጥር ኃይል በመሆኑ በእኔ ላይ ይህንን ማድረጉ እምብዛም አያስደንቅም።

    ሰሞኑን የምገኝበትን አሳሳቢ የጤና ሁኔታ በተመለከተ ከሐኪም ጋር ባደረግሁት ምክክርም ለሕመሜ አስተማማኝ ሕክምና እስካገኝ ድረስ በአካሌም ሆነ በአዕምሮዬ ላይ ምንም ዓይነት ጫናና ውጥረት የሚፈጥር ሥራ እንዳልሠራና በቂ ረፍት እንዲኖረኝ ከባድ ማስጠንቀቂያና ምክር ተሰጥቶኛል። ጤናዬ ከሚገኝበት አሳሳቢ ደረጃ (risk) አኳያ በሕይወት ለመሰንበት የምፈልግ ከሆነ፥ ለጊዜው ያለኝ ብቸኛ አማራጭ ይህንን ማድረግ እንደሆነ ተነግሮኛል።

    ሀገራችን የምትገኝበትን እጅግ አሳሳቢ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት በእኔ በኩል አስቸኳይ የሕክምና እርዳታ አግኝቼና ጤናዬ ተስተካክሎ በትግሉ ሂደት የጎላ ተሳትፎ እንዲኖረኝ ከፍተኛ ፍላጎት የነበረኝና አሁንም ያለኝ ቢሆንም የሕክምና እርዳታ እንዳላገኝ ራሳቸውን በፈጣሪ ቦታ ሊተኩ በሚፈልጉ ገዥዎች በመከልከሌ ምክንያት ይህንን ምኞቴን ማሳካት የማልችልበት እንቅፋት ገጥሞኛል። ስለሆነም ተገቢውን የሕክምና እርዳታ አግኝቼ ጤናዬ እስኪመለስ ድረስ በሕይወት የመሰንበት ዕድሌን ለመሞከር ስል ከማንኛውም ዓይነት የትግል እንቅስቃሴ (ገንዘብ ወይም ምክር ከማዋጣት ባለፈ) ራሴን ለጊዜው ለማቀብ የተገደድኩ ስለመሆኑ በከፍተኛ ቁጭትና ሐዘን እገልጻለሁ።

    በዚህ ጉዳይ ላይ የሚሰማኝ ቁጭትና ሐዘን ልብን የሚሰብር የሆነብኝ ያለምክንያት ሳይሆን፥ ሀገራችን ከመቼውም ጊዜ በላይ የሕልውና አደጋ ውስጥ በገባችበትና ዋጋ የሚከፍልላት ዜጋ በሚያስፈልጋት በአሁኑ ወቅት ከአቅሜ በላይ በሆነ የጤና ችግር ምክንያት ራሴን ከትግሉ ሜዳ ለማግለል መገደዴ ያልጠበቅሁትና ከፍላጎቴ ውጭ የሆነ መጥፎ ገጠመኝ ስለሆነ ነው።

    የሆነው ሆኖ ይህንን መጥፎ አጋጣሚ እንደ አንድ ጊዜያዊ ስንብት ልቁጠረውና ስለ ዛሬዋ ኢትዮጵያ ሕዝቡ ግንዛቤ ሊወስድ ይገባዋል ብዬ በማምንባቸው በሚከተሉት ስምንት ነጥቦች ዙሪያ የሚሰማኝን በመግለጽ ለመሰናበት ልሞክር።

    1. ከእንግዲህ በብልጽግና ፓርቲ የሚባባስ እንጂ የሚፈታ ችግር የለንም

    በአሁኑ ወቅት ሀገራችን ለገጠማት የሕልውና አደጋ በአስተሳሰብና በመዋቅር ደረጃ ዋናዎቹ ተጠያቂ ምክንያቶች የጽንፈኝነት ፖለቲካ፣ ብሔርተኝነትና የፖለቲካ አመራር ድክመቶች ናቸው። ስለሆነም ለወቅቱ የለውጥ ሂደት መክሸፍ ዋናው ተጠያቂ የእነዚህ መዋቅራዊ ድክመቶች ሰለባ የሆነው የቀድሞው ኢሕአዴግ፣ የአሁኑ ብልጽግና ፓርቲ ነው።

    ብልጽግና ፓርቲ በእጁ የገባውን ወርቃማ የለውጥ ዕድል በአግባቡ መጠቀም ሳይችል የቀረበት ተጨማሪ ምክንያትም ፓርቲው ከሀገሪቱ ጥቅምና ደኅንነት በላይ ለራሱ የፖለቲካ ሥልጣን የበላይነት ቅድሚያ በመስጠት ውስጣዊ አንድነቱን በማዳከሙና ወደ የእርስ በርስ የሥልጣን ሽኩቻ ውስጥ በመግባቱ ነው። የፓርቲው ውስጣዊ ክፍፍል በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች እየተፈጠሩ ላሉ የእርስ በርስ ግጭቶችና በትግራይ ክልል ለተከሰተው ጦርነት ዋናው ምክንያት ሲሆን፥ ውስጣዊ ችግሩ አሁንም የተሻለ ትኩረት አግኝቶ ካልተፈታ በስተቀር ሀገሪቱን ለባሰ ቀውስና ጦርነት የሚዳርጋት ይሆናል። የራሱን ውስጣዊ ችግር መፍታት ያልቻለና ከራሱ የፖለቲካ ሥልጣን በላይ የሀገሪቱን ጥቅም ማስቀደም የተሳነው ደካማ ገዥ ፓርቲ የለውጥ ሂደቱን ስኬታማ ሊያደርግም ሆነ ሀገሪቱን ከጥፋት ሊታደጋት አይችልም።

    ቀደም ሲል ብልጽግና ፓርቲ ይህንን መሠረታዊ ድክመቱን አምኖ በመቀበልና በማረም ራሱንም ሆነ ሀገሪቱን ከጥፋት ሊታደጋት ይችላል የሚል ግምት (ምናልባትም የሞኝነት) የነበረን ቢሆንም ግምታችን ስህተት እንደነበር ያለፉት ሦስት ዓመታት ሂደት በተግባር አሳይቶናል። በዚህም ምክንያት ብልጽግና ፓርቲ እንደ ፈጣሪውና አሳዳጊው ህወሓት ሁሉ፥ ከመሞት መዳን ያለመቻል መዋቅራዊ ችግር ያለበት ግትርና ጀብደኛ ድርጅት እንደሆነ መገንዘብ ችለናል። ምክንያቱም ብልጽግና ፓርቲ አምባገነን የሆነው አምባገነን እንዲሆን ያስገደዱት ነባራዊ ሁኔታዎች ስላሉ ሳይሆን በራሱ ፍላጎትና ውሳኔ አምባገነን መሆንን የመረጠ ድርጅት ስለሆነ ነው።

    ከይቅርታ ጋር፥ እዚህ ላይ በከፍተኛ ድፍረትና ርግጠኛነት ልናገር የምችለው፥ የ21ኛዋን ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያን በ16ኛው ክፍለ ዘመን የማክያቬሊ የፖለቲካ ሤራ ስልት (conspiracy theory) እና የንግርት አምልኮት ለመግዛት እየሞከረ ያለው ብልጽግና ፓርቲ አሁን በያዘው አቅጣጫ መጓዝ ከቀጠለ ራሱንም ሆነ ሀገሪቱን የማፍረስ እንጂ ወደ ዘላቂ ለውጥ የማሸጋገር ሚና ከቶውንም ሊኖረው አይችልም። በአሁኑ ወቅት ትግራይ ውስጥ የገባንበትን ከባድ ጦርነት፣ በኤርትራናና በሱዳን መንግሥት የተፈጸመብንን ወረራ፣ በሕዳሴ ግድብ ምክንያት ከግብጽና ከሱዳን ጋር የገባንበትን ፍጥጫ፣ በተለያዩ የሀገሪቱ ክልሎች እየተፈጸመ የሚገኘውን የሕዝብ መፈናቀልና የጅምላ ጭፍጨፋ፣ በገዥው ፓርቲና በበርካታ ተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል የሚታየውን ፍጥጫ፣ ከዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ እየደረሰብን ያለውን ከባድ ተጽዕኖ፣ የኮሮና ወረርሽኝ እያስከተለብን ያለውን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውስ፣ ከፊታችን እየመጣ ያለውን ሁለንተናዊ ኢኮኖሚያዊ ውድቀትና ሌሎች ተመሳሳይ ፈተናዎቻችንን በጥቅሉ ደምረን ስናያቸው እንኳንስ ብልጽግና ፓርቲ ብቻውን ሆኖ ሁላችንም ተባብረን በአንድነት ብንቆም የወቅቱን የሀገሪቱን ፈተና በቀላሉ መወጣት አዳጋች ነው። ስለሆነም የውስጥ ችግራችንን ፈተን በአንድነት እስካልቆምን ድረስ በብልጽግና ፓርቲ የተናጠል ጥረት ችግራችን ፍጹም ሊፈታ እንደማይችል መገንዘብ ያስፈልጋል።

    1. ወቅቱ ኢትዮጵያውያን በአስተሳሰብና በሞራል ዝቅታ ላይ የምንገኝበት ነው

    የምንገኝበት ወቅት ኢትዮጵያውያን ከመቼውም ጊዜ በላይ ጭካኔን፣ ጅምላ ግድያን፣ የሤራ ፖለቲካን፣ የጥላቻ ንግግርን፣ ውሸትንና የግለሰብ አምልኮትን እየተለማመድን የምንገኝበት ነው። እነዚህን እኩይ ተግባራት በፊት አውራሪነት እያለማመደን የሚገኘው መንግሥት ሲሆን፥ ጋሻጃግሬዎቹ ደግሞ ሀይማኖተኛ፣ ብሔርተኛና ምሁራን ነን ባይ “ልሂቃን” መሆናቸውን እያየን ነው።

    በርግጥም ወቅቱ የ“ዝቅታችን” ወቅት ነው። ለአንድ “ህወሓት” የተባለ አምባገነናዊ የሆነና በሕዝብ ትግል ከሥልጣን ለተወገደ ኃይል ባለን ገደብ የለሽ ጥላቻ ምክንያት ዓይነልቦናችን ታውሮ የዛሬ ገዥዎቻችን በሕዝብና በሀገር ላይ እየፈጸሙት ያለን የዛሬ ግፍና በደል ፈጽሞ ማየትና መረዳት ተስኖናል። የወቅቱ ገዥዎቻችን ለራሳቸው የሥልጣን የበላይነት ሲሉ በሀሰትና በአስመሳይነት በጥብጠው የሚግቱንን ሥልታዊ ፕሮፓጋንዳ፣ በሀገር ጥቅምና በሕግ ማስከበር ሰበብ እየፈጸሙት ያለን በውጤቱ ሀገር በታኝ የሆነ የሤራና የበቀል ተግባር መገንዘብ ተስኖን እንደ ሕዝብ የአዲስ አምባገነናዊ ኃይል አዋላጅና ወላጅ ሆነናል። እወደድ ባይና ደካማ በሆነው የብልጽግና ፓርቲ አመራርና ተከታዮቹ በሆኑት የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል ያለው የጋራ አጀንዳ፥ በዋናነት ህወሓትን በመጥላትና በመበቀል ዙሪያ የተቃኘ ቢሆንም፥ ዋናውና የጋራ መገለጫቸው የሆነው ባሕርያቸውና ግብራቸው ግን የህወሓት አውዳሚ አመለካከትና ውርስ (legacy) አራማጅና አስቀጣይ መሆን ነው። እነዚህ ግብዝ ኃይሎች በህወሓት መንገድ መጓዝ ህወሓት በከፋፋይ አጀንዳው ያዳከማትን ሀገር ለይቶላት እንድትፈርስ ከማድረግ ያለፈ ውጤት እንደማያመጣ መገንዘብ ተስኗቸዋል። ይህም በራሱ ኢትዮጵያውያን ከሌሎችም ሆነ ከራሳችን ያለፈ ስህተትና ውድቀት የመማር አቅማችን እጅግ አናሳ መሆኑን ያሳያል።

    በአጠቃላይም ወቅቱ ኢትዮጵያውያን በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በራሳችን ታሪክ፣ አንድነት፣ ሉዓላዊነት፣ ሰላም፣ የወደፊት ዕድገትና ጥቅም ላይ ራሳችን ጦርነት ያወጅንበት ወቅት ነው ማለት ይቻላል። በአጭሩ የራሱን ፍላጎትና ዘለቄታዊ ጥቅም የማያውቅ ግብዝ ሕዝብ ሆነናል። ከገባንበት ዝቅጠት ጥልቀትና ስፋት አኳያም አንዳንዶች “ኢትዮጵያውያን እርስ በርስ ተጨራርሰን ከምንጠፋ በስምምነት ተለያይተን መኖር የምንችልበት ዕድል ይኖር ይሆን?” ብለው ራሳቸውን ለመጠየቅ የተገደዱበት ወቅት ላይ ደርሰናል። ኢትዮጵያውያን እንደ “ሕዝብ” በዚህ ዓይነት የአስተሳሰብና የሞራል ዝቅታ ላይ እንደምንገኝ ተገንዝበን ስክነትና ብስለት ወደተላበሰ የፖለቲካ አቅጣጫ በፍጥነት ካልገባን በስተቀር ሀገራችንን ከገጠማት የመፈራረስ አደጋ ልንታደጋት አንችልም። እጅግ አማላይና መሠሪ በሆነው የሥርዓቱ የፕሮፓጋንዳ ስልት ሰለባ በመሆን፣ ወይም በአድር ባይነት፣ ወይም በጥቅመኝነትም ሆነ በማንኛውም ሌላ ምክንያት የወቅቱን ሥርዓት እየደገፍን የምንገኝ ዜጎች በታሪክና በትውልድ ፊት የየራሳችን የተጠያቂነት ድርሻ እንደሚኖርብን ተገንዝበን፥ ሥርዓቱን መቃወምና መታገል ቢያቅተን እንኳን ቢያንስ ዝም በማለት የሀገሪቱ ጥፋትና ውድቀት ቀጥተኛ ተጋሪ ከመሆን ልንቆጠብ ይገባል።

    1. በይስሙላ ምርጫ የሚፈታ ችግር የለንም

    ነጻና ፍትሐዊ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል ውጤታማ የሽግግር ሂደት ባላካሄድንበት ሁኔታ የሚካሄደው የዘንድሮው ሀገራዊ ምርጫ ሂደትም ሆነ ውጤት የሀገሪቱን የፖለቲካ ቀውስ የበለጠ የማባባስ እንጂ የመፍታት አንደምታ አይኖረውም። ምርጫው ሳይጀመር ያለቀና ውጤቱም ሀገሪቱን ወደ ባሰ ቀውስ ማስገባት ወይም አምባገነናዊነትን ማጽናት መሆኑ አስቀድሞ የታወቀ ነው። ይህ ምርጫ ብልጽግና ፓርቲ በማንኛውም መንገድ አሸናፊ ሆኖ በሥልጣን ላይ ለመቀጠል ወስኖና ተዘጋጅቶ የገባበት ምርጫ ስለሆነ፥ የዚችን ደሃ ሀገር በጀት ከማባከን ያለፈ ፋይዳ አይኖረውም። በአጭሩ መጭው ምርጫ ነጻና ፍትሐዊ እንደማይሆን ሳይሆን እንዳልሆነ የቅድመ ምርጫው ሂደት በማያሻማ ሁኔታ አሳይቷል። የወቅቱ የፖለቲካ ችግር በዘላቂነት ሊፈታ የሚችለው በአንጻራዊነት ነጻ፣ ገለልተኛና ጠንካራ የዴሞክራሲ ተቋማትን ለመገንባት፣ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በነጻነትና በእኩልነት ምርጫ የሚወዳደሩበትን ሁኔታ ለማመቻቸት፣ ብሔራዊ መግባባትና ዕርቅን ለማስፈን፣ ብሎም ሕገ-መንግሥታዊ ማሻሻያ ለማድረግ በሚያስችል ሁሉን አቀፍ በሆነ የሽግግርና የሀሳብ ግብይት ሂደት (national dialogue) ነው እንጂ በተለመደው ዓይነት የታይታ የምርጫ ግርግር አይደለም።

    ወደ መዋቅራዊና ዘላቂ ለውጥ ለመግባት ከተፈለገ መፍትሔው የችኮላ ምርጫ ማካሄድ ሳይሆን በቅድሚያ ከፖለቲካ ጉዳይ ጋር በተያያዘ በመላው ሀገሪቱ የታሠሩ የፖለቲከኛ እስረኞችን መፍታት፣ ዜጎች ላይ የሚደረግ አፈናና ግድያን ማስቆም፣ የሀገሪቱ ሕግጋትና ተቋማት ሀገር ጠቀም በሆነ አግባብ እንዲሻሻሉ ማድረግና ቢያንስ ዶ/ር ዐቢይ ወደ ሥልጣን በመጡባቸው በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ሳምንታት የታየው ዓይነት የዕርቅና የመቻቻል መንፈስ በሀገሪቱ እንዲሰፍን ማድረግ ያስፈልጋል።

    1. ልዩ ትኩረት አዲስ አበባ ከተማን ለማሸነፍ

    በተግባር እየተፈጸመ ከሚገኘው ግልጽ ድርጊት እንደምንረዳው ብልጽግና ፓርቲ ነጻና ፍትሐዊ በሆነ ምርጫ ተወዳድሮ በማሸነፍ ሳይሆን በአፈናና በኃይል በሥልጣን ላይ ለመቀጠል የወሰነ አምባገነን ኃይል ነው። ገዥው ፓርቲ የሚጠላቸውንና የሚፈራቸውን የፖለቲካ ፓርቲዎች ከፖለቲካ መድረኩ በማስወገድና የፓርቲ አመራሮችን በማሰር በወሰደው እርምጃ መጭው ምርጫ ነጻና ፍትሐዊ እንዳልሆነ ከወዲሁ በተግባር አረጋግጧል። ሆኖም ምርጫው በታሰበበት ጊዜ የሚካሄድ ከሆነ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ራሳቸውን ከሂደቱ ከማግለል ይልቅ አቅማቸውና ሁኔታው በፈቀደላቸው መጠን በምርጫው ተሳታፊ ቢሆኑ የተሻለ ይሆናል እላለሁ።

    ነገር ግን በቂ ዝግጅት አድርገውና የገዥውን ፓርቲ ሁለንተናዊ ተጽዕኖ በብቃት ተቋቁመው በሀገር ደረጃ መንግሥት ለመሆን በሚያስችል መጠን ምርጫውን ለማሸነፍ የሚኖራቸው ዕድል እጅግ ጠባብ መሆኑን በመገንዘብ ሙሉ ትኩረታቸውን አዲስ አበባ ከተማን ለማሸነፍ ማድረግ ይኖርባቸዋል። አዲስ አበባ ከተማን አሸንፎ ለመረከብም አንድነት ተኮር የሆኑ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የመተባበር ጉዳይ ምንም ዓይነት ቅድመ ሁኔታ ሊቀርብበት የማይገባና ምትክ የለሽ እርምጃ መሆኑን መገንዘብ አለባቸው። ግለሰብን በመጥላት የሀገርን ጥቅም ጥያቄ ውስጥ ማስገባት ከማንኛውም ኃላፊነት ከሚሰማው ፓርቲ የማይጠበቅ ተግባር ቢሆንም ምናልባት የእኔ ለጊዜውም ቢሆን ከምርጫውና ከትግሉ ሂደት ገለል ማለት ለተቃዋሚው ጎራ መተባበር አንድ ጥሩ አጋጣሚ ሊሆን እንደሚችል እገምታለሁ።

    የአንድነት ኃይሉ ምንም ዓይነት ድምጽ ሊባክን በማይችልበት ሁኔታ እርስ በርስ ላለመፎካከር አስቀድሞ ካልተስማማ በስተቀር፥ ብልጽግና ፓርቲና አጋሮቹ (በፓርቲም ሆነ በግል የሚወዳደሩ) አዲስ አበባን የማሸነፍ ዕድል እንደሚኖራቸው መገንዘብ ያስፈልጋል። ብልጽግና ፓርቲና አጋሮቹ አዲስ አበባን የማሸነፍ ዕድል ካገኙም የአዲስ አበባ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ ጥቅምና ሕልውና አደጋ ውስጥ እንደሚገባ መገንዘብ ያስፈልጋል። በተጨማሪም በምርጫ 97 ሲሆን እንደታየው “ምርጫው ስለተጭበረበረ ያሸነፍነውን ወንበር ወይም ምክር ቤት አንረከብም” በሚል የተሠራው ታሪካዊ ስህተት በዘንድሮውም ምርጫ እንዳይደገም ፓርቲዎች ከወዲሁ በጉዳዩ ላይ መተማመንና መወሰን ይኖርባቸዋል።

    1. መፍትሔው ሁሉን አቀፍ የሆነ የሽግግር ሂደት መፍጠር ነው

    በአሁኑ ወቅት ሀገራችን በሁለት የጎረቤት ሀገራት (በኤርትራና ሱዳን) ሉዐላዊነቷ ተደፍሮ የግዛት ወረራ ተፈጽሞባታል። ይህ ወረራ ከማንኛውም ውስጣዊ ችግሮቻችን በላይ ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጠውና በአስቸኳይ ሊቀለበስ የሚገባው ነው። ይህንን ማድረግ ሳንችል ኢትዮጵያውያን እንደ ሀገርና ሕዝብ የነጻነት ታሪክም ሆነ ሉዐላዊ ሕልውና አለን ብለን መናገር አስቸጋሪ ይሆናል። የወቅቱ መንግሥት በሀገር ውስጥ እየተፈጸመ ያለውን ብሔር ተኮር ጭፍጨፋ ማስቆምም ሆነ የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ማስከበር ስላለመቻሉ የሚያቀርበው ማንኛውም ምክንያትም ተቀባይነት ሊኖረው አይገባም። የወቅቱ መንግሥትም ሆነ መንግሥትን በዋናነት የሚመሩት ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ እነዚህን ሁለት ቁልፍና መሠረታዊ የአንድ መንግሥት ኃላፊነቶች በአግባቡ መወጣት ስላልቻሉ ከእንግዲህ የሚኖራቸው ብቸኛ አማራጭ ችግሩን ለመፍታት የሚያስችል ሀገራዊ የሀሳብ ግብይት ሂደት (national dialogue) መጀመርና ሁሉን ዐቀፍ የሆነ የሽግግር ሂደት ማካሄድ ነው።

    የወቅቱ መንግሥት ቀደም ሲል በኢሕአዴግ ስም፣ አሁን ደግሞ በብልጽግና ፓርቲ ስም ሕዝባዊ ይሁንታ ሳይኖረው ለ30 ዓመታት በሥልጣን ላይ ያለ ኃይል ነው። ይህ መንግሥት የሀገሪቱን መሠረታዊ ፖለቲካዊ ችግሮች መፍታት ካለመቻሉም በላይ ይበልጥ እያባባሰውና እያወሳሰበው ይገኛል። ስለሆነም የወቅቱ ብልጽግና ፓርቲ በአንድ በኩል የሀገሪቱን አንድነትና ሉዓላዊነት ማስከበር ባልቻለበት ሁኔታ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ነጻና ፍትሐዊ ምርጫ አካሒዶ የሕዝብ እውነተኛ ውክልና ለማግኘት በሐቅ ባልተዘጋጀበት ሁኔታ የሀገሪቱን የፖለቲካ ሥልጣን በቋሚ ርስትነት ይዞ ሊቀጥል አይገባውም።

    ገዥው ብልጽግና ፓርቲ ከግለሰብ በላይ የሆነ ሚና አለኝ ብሎ የሚያምንና ድክመቱ የኔ ሳይሆን የመሪዎቼ ወይም የመሪዬ ነው ብሎ የሚያስብ ከሆነም ሀገሪቱ ለይቶላት ከመፍረሷ በፊት መሪዎቹን ወይም መሪውን የመቀየር ርምጃ ሊወስድ ይገባዋል። ይህንን ማድረግ ካልቻለ ግን ለሀገሪቱ ውድቀት ፓርቲውም እንደ ድርጅት ተጠያቂ ይሆናል።

    ከዚህ ውጭ በአንድ ሀገር የዘር ጭፍጨፋን ማስቆምና የውጭ ወረራን መከላከል ያልቻለ ማንኛውም መንግሥት በሥልጣን ላይ መቀጠል የሚችልበት ሕጋዊ፣ ፖለቲካዊም ሆነ ሞራላዊ ምክንያት የለም። ከዚህ በተጻራሪ የዘር ጭፍጨፋን ማስቆምና ሀገሪቱን ከውጭ ወራሪ መከላከል ያልቻለ መንግሥት፥ “ሌላ አማራጭ የለንም” በሚል ሰበብ በሥልጣን ላይ ሊቀጥል የሚችለው ኢትዮጵያ ሕልውናዋን ከጥፋት አድኖ የሚያስቀጥላት ትውልድና ዜጋ ያልፈጠረች መካን ሀገር መሆኗን አምነን ከተቀበልን ብቻ ይሆናል።

    በተጨማሪም በቅርቡ ትግራይ ክልል ውስጥ የገባንበት ጦርነት የሀገሪቱን አንድነት ከፍተኛ ጥያቄ ውስጥ የሚጥልና ከኛ ዘመንም አልፎ ምናልባትም ለልጅ ልጆቻችን የሚተርፍ ጣጣ የሚያስከትል አሳሳቢ ክስተት ነው። ስለሆነም ይህ ችግር በዘላቂነት በጦርነት ሊፈታ እንደማይችል በመገንዘብ ከሥልጣን ጥያቄ፣ ከበቀል፣ ከስሜትና ከጀብደኝነት በራቀ አተያይ ለችግሩ አስቸኳይ ሰላማዊና ፖለቲካዊ መፍትሔ መፈለግ ይኖርበታል።

    1. ሀገሪቱን ከሕልውና አደጋ መታደግ የሚችል ጠንካራ ፓርቲ መፈጠር አለበት

    ኢትዮጵያውያን ሁልጊዜም በሀገሪቱ በጎ የፖለቲካ ለውጥ እንዲመጣ የምንመኝና የምንፈልግ ቢሆንም ይህንን የሁልጊዜ ምኞታችንን ዕውን ለማድረግ የሚያስችል ጠንካራና ለመርህ ታማኝ የሆነ ፓርቲ መፍጠር እስካሁን አልቻልንም። ዛሬም እንደ ትናንቱ የሥርዓቱን ድክመቶችና ጥፋቶች ስንቆጥር የምንውል የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች፣ ምሁራን፣ ጋዜጠኞችና አክቲቪስቶች ብንኖርም ያለጠንካራ ፓርቲ መኖር ሀገሪቱን ከጥፋት መታደግም ሆነ ዘላቂ ለውጥ ማምጣት እንደማይቻል መገንዘብ የቻልን አይመስልም። በምሬት፣ በጩኸትና በውግዘት ብቻ ሊመጣ የሚችል ዘላቂ ለውጥ እንደማይኖር ተገንዝበን ለመጭው ትርጉም የለሽ ምርጫ ከምንሰጠው ትኩረት በላይ ለሀገሪቱ ችግሮች የሚመጥን ጠንካራና ታማኝ ፓርቲ በመፍጠር ሥራ ላይ ማተኮር አለብን። በተለይም አንድነት ተኮር የሆነው የፖለቲካ ኃይል ከመቼውም ጊዜ በላይ በተዳከመበትና በተበታተነበት ሁኔታ ኢትዮጵያን ከጥፋት ለመታደግ የሚያስችል አስተማማኝ ለውጥ ማምጣት እንደማይቻል በመገንዘብ አዲሱ ትውልድ ዋና ተዋናይ የሚሆንበት ጠንካራና ታማኝ ፓርቲ መፍጠር ቀዳሚና ለነገ የማይባል አጀንዳችን መሆን ይገባዋል እላለሁ። ይህንን ማድረግ ካልቻልን “አማራጭ የለም” በሚል ሰበብ አምባገነኖችና የሀገርን ሕልውና አደጋ ላይ የሚጥሉ ፓርቲዎች ወይም መሪዎች ሁልጊዜም በሥልጣን ላይ የሚቀጥሉበትን ዕድል እንፈጥራለን።

    1. የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረት ለሰላም

    የወቅቱ የሀገራችን ፖለቲካዊ ሁኔታ በብዙ ውጥረቶች የተሞላና በቀላሉ ተሰባሪ ነው። በዚህ ምክንያት ውጤታማ በሆነ የሽግግር ሂደት ሳይታለፍ የሚካሄደው መጪው ምርጫ ሀገራችንን ወደ ባሰ ግጭትና ትርምስ ሊያስገባ የሚችልበት ሰፊ ዕድል አለ። ይህ ስጋት በቂ መነሻ ምክንያት ያለው መሆኑን በመረዳት ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች የምርጫ ሂደቱ ወደ ግጭትና ብጥብጥ እንዳያመራ የማድረግ የጋራ ኃላፊነት አለባቸው። ይህንን በመገንዘብ ከፍተኛ ጥንቃቄ የተሞላበትና የሰከነ ሰላማዊ የምርጫ ቅስቀሳ ሊያካሒዱ ይገባል። አሁን ከምንገኝበት እጅግ ከባድና ውስብስ የፖለቲካ ሁኔታ አንጻር የሰላም እጦት የሀገሪቱን ሕልውና የሚፈታተን አደጋ ይዞብን ሊመጣ ስለሚችል፥ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምርጫውን አሸናፊ ለመሆን ከመሥራት በላይ ለሰላም መኖር የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረት መስጠት ይኖርባቸዋል።

    በአግባቡ ካልተጠቀምንበትም በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋ ያለው ማኅበራዊ ሚዲያ የብሔራዊ ደኅንነታችን ዋና የአደጋ ምንጭ ሊሆን ይችላል። ይህንን እውነታ በመገንዘብ ማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ የሆኑ ዜጎቻችን በምርጫው ወቅት የሚኖራቸው ሚና ለሰላም ቅድሚያ በሚሰጥ የኃላፊነት ስሜት ሊካሄድ ይገባዋል። በአጠቃላይ ሀገራችን በአሁኑ ወቅት በውስጥም በውጭም ከፍተኛና አሳሳቢ ውጥረት ውስጥ የምትገኝ መሆኑን በመገንዘብ ለሰላም መኖር የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረት መስጠት ግዴታችን መሆኑን መገንዘብ ያስፈልገናል።

    1. ሕገ-መንግሥቱ ሳይሻሻል የፖለቲካ ችግራችን አይፈታም

    የወቅቱ የሀገራችን የፖለቲካ ችግር የሀገራዊ ብሔርተኞችንና የንዑስ ብሔር ብሔርተኞችን የተካረረ የፖለቲካ ቅራኔ በአንጻራዊነት በሚያቻችል አግባብ የወቅቱን ሕገ-መንግሥት ከማሻሻል ባነሰ ሌላ የመፍትሔ ርምጃ ሊፈታ አይችልም። ሕገ-መንግሥቱ እስካልተሻሻለ ድረስ ከማንነት ጋር በተያያዘ በአሁኑ ወቅት የተነሱትም ሆነ ወደ ፊት ባልተቋረጠ ሁኔታ ሊነሱ የሚችሉ ጥያቄዎች የሀገሪቱን ሰላምና ሕልውና እያወኩ መቀጠላቸው አይቀርም። ይህ ችግር ዘላቂ መፍትሔ እስካላገኘ ድረስም የሀገሪቱ ሰላም፣ አንድነት፣ ሕልውናና የኢኮኖሚ እጥረት በዘላቂነት መፍትሔ ሊያገኝ አይችልም።

    ከዚህ ግንዛቤ ጋር በተያያዘ በኔ በኩል ለውይይት መነሻ የሚሆን የሕገ-መንግሥት አማራጭ ረቂቅ ሰነድ በመጽሐፍ መልክ በማሳተም ላይ እገኛለሁ። የሕገ-መንግሥቱ መሻሻል ለሀገሪቱ የፖለቲካ ችግሮች መፈታት የሚኖረውን ምትክ የለሽ አዎንታዊ አስተዋዕፆ የምትገነዘቡ መገናኛ ብዙኃን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ምሁራንና ዜጎች በረቂቅ ሰነዱ ላይ ውይይት በማድረግ ትችት እንድታቀርቡበትና እንድታዳብሩት፣ ከተቻለም ሰነዱን በመጭው ምርጫም ሆነ በቀጣዩ የትግል ሂደት የጋራ የትግል አጀንዳ አድርጋችሁ እንድትጠቀሙበት በዚህ አጋጣሚ ጥሪዬን አቀርባለሁ።

    በመጨረሻም ከአቅም በላይ በሆነ የጤና ምክንያት ቢሆንም ሀገራችን ከመቼውም ጊዜ በላይ ዋጋ የሚከፍልላት ዜጋ በሚያስፈልጋት በአሁኑ ወቅት ለጊዜውም ቢሆን ከትግል ተሳትፎዬ ለመታቀብ በመገደዴ፥ የትግል አጋሮቼንና የዐላማ ደጋፊዎቼን ሁሉ ከልብ ይቅርታ እጠይቃለሁ። ይህንን የምለው ከእኔ ብዙ እንደምትጠብቁና ለእኔ ለራሴ እንደሆነብኝ ሁሉ ለእናንተም ይህ ክስተት ድንገተኛ መርዶ እንደሚሆንባችሁ ስለምገነዘብ ነው። ወደፊት የጤና ሁኔታዬ ተሻሽሎ እስከመጨረሻው በፖለቲካ ሂደቱ ለመቀጠል ለራሴ የገባሁትን ቃል ለመፈጸም ፈጣሪ ዕድል እንደሚሰጠኝ ተስፋ እያደረግኹ ሀገራችን ኢትዮጵያ መልካሙ ሁሉ እንዲገጥማት ያለኝን ልባዊ ምኞት በዚህ አጋጣሚ እገልጻለሁ።

    ልደቱ አያሌው

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forums) ላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።

    ሀገራችን ኢትዮጵያ ያለችበት የህልውና አደጋ በአቶ ልደቱ አያሌው እይታ

Viewing 15 results - 46 through 60 (of 495 total)