-
AuthorSearch Results
-
October 26, 2020 at 12:12 am #16485
In reply to: የፖለቲካ ፓርቲዎች ድምጽ (ኢትዮጵያ ውስጥ የሚነቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች)
AnonymousInactiveየአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በአማራ ክልል ከተሞች እና በአዲስ አበባ ታላልቅ ሰለማዊ ሰልፎችን ለማድረግ ጥሪ አደረገ
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በአማራ ክልል ከተሞች እና በአዲስ አበባ ታላልቅ ሰለማዊ ሰልፎች እንደሚደረጉ አስታውቋል። አብን ስለሰላማዊ ሰልፎቹ እና በአጠቃላይ በአማራ ሕዝብ ላይ ከዕለት ወደ ዕለት ያልተቋረጠ በደል እየደረሰበት መሆኑን ያመላከተበት ትንታኔ የሚከተለውን ይመስላል።
ለመላው የአማራ ሕዝብ፣
ለንቅናቄያችን አባላትና ደጋፊዎች፣
ለመላው ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በሙሉ !የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) መንግሥታዊና ሥርዓታዊ ጭቆና እና የዘር ጥቃት ያንዣበበትን የአማራን ሕዝብ ከህልውና ስጋት ለመታደግና በነፃነት፣ በእኩልነት፣ በፍትህና በወንድማማችነት የሚኖርባት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት የቆመ ድርጅት ነው።
አብን ባለፉት ሁለት ከመንፈቅ ዓመታት ሕዝባችን በከፍተኛ መስዋዕትነት ያስገኘው የለውጥ ተስፋ እንዳይመክን፣ በትግላችን የተንበረከኩ አማራ-ጠል ኃይሎች ዳግም እንዳያንሰራሩና የሀገር እና የሕዝብ ህልውና በድጋሚ አደጋ ላይ እንዳይወድቅ እልህ አስጨራሽ ትግል አድርጓል። የአማራ ብሔርተኝነት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ አዎንታዊ የመረጋጋት፣ የመቻቻልና የግንባታ ሚና እንዲኖረው ያልተቆጠበ ጥረት አድርጓል።
ይሁን እንጂ ተስፋ የተጣለበት “ለውጥ” እያደር መስመሩን በመሳቱ አዲሱ አገዛዝ የአምባገነንነትና የአንድ ቡድን ፍላጎት አስፈፃሚነት አዝማሚያ ማሳየቱ ገሃድ ወጥቷል። በተለይም በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈፀመው የዘር ጥቃት እየተባባሰና አድማሱን እያሰፋ በቅርቡ እንኳን በኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና በደቡብ ጉራ ፈርዳ ተከታታይ ለሆኑ የጅምላ ጭፍጨፋዎች፣ የዘር ማጽዳትና የማፈናቀል ጥቃቶች ሰለባ ሆኗል።
አብን በሕዝባችን ላይ ስልታዊ፣ የተደራጀ፣ ሰፊ የመገናኛ ብዙኃን ቅስቀሳ የተደረገበት ዘመቻና በመንግሥት መዋቅር ጭምር የተደገፈ የዘር ማጥፋት እየተፈፀመበት መሆኑን በመግለጽ መንግሥት ችግሩን እንዲያስቆም በተደጋጋሚ ወትውቷል። እንደ ሕዝብም መቻቻልና ሀገር ወዳድነት ትርጉም እስኪያጡ ድረስ ታግሰናል። ነገር ግን ብልፅግና-መራሹ መንግሥት የሕዝባችንን ሆደ-ሰፊነትና አስተዋይነት እንደ ዓይነተኛ ድክመት በመቁጠር፥ ንቅናቄያችን ለሀገር ህልውና ሲባል የሰጠውን ይሁንታ በሰፊው በማጓደል ዛሬም አማራው መንግሥት-አልባ ሕዝብ መሆኑን አረጋግጦልናል።
አብን በሕዝባችን ላይ ለሚደርሰው ጥቃት ቀንደኛው ተጠያቂ ማዕከላዊ መንግሥት መሆኑን ያምናል። መንግሥት ‹‹የወንጀሎች ሁሉ ወንጀል›› የሚባለውን የዘር ማጥፋትን በመከላከል፣ በማስቆምና ዘላቂ መፍትሄ በመፈለግ ረገድ የረባ ሚና አልተጫወተም። እንዲያውም የዘር ጥቃቶችን “ግጭት” እያለ ለማድበስበስ፣ መረጃዎችን ለማፈንና ሰለባዎችን ጭምር ለመወንጀል ተደጋጋሚ ጥረቶችን ሲያደርግ ተስተውሏል። መንግሥት በአማራ ላይ የተፈፀሙ የዘር ጥቃቶች ልዩ ጠባሳ የሆነውን የጉራ ፈርዳ ጥቃት መሪ አቀናባሪ የነበረውን ግለሰብ ለዳግም ሹመት የመምረጡን አንድምታ እንረዳለን፤ አሁን የሚፈፀመውን ካለፈው የሚያስተሳስር ረጅም ክር አለው።
በሁለተኛ በአማራ ሕዝብ ላይ የዘር ፍጅት በተፈፀመባቸው ክልሎች ያሉ መንግሥታት በተለያየ ደረጃ ኃላፊነታቸውን ካለመወጣት አልፈው፥ በቀጥታና በተዘዋዋሪ በሕግ፣ በመዋቅር፣ በመሣሪያና በገንዘብ ጥቃቶችን መደገፋቸውና ማቀናበራቸው በገሃድ ይታወቃል። ከጥቃቱም በኋላ የየክልሎቹ የብልፅግና ፖርቲ አመራሮች በሕዝባችን ላይ በየፊናቸው በማንአለብኝነት የሚያደርጉት ዛቻና ማስፈራሪያ በድርጊቱ አለመጸጸታቸውንና ችግሩን ለማረም ፈቃደኝነት እንደሌላቸውም ያረጋግጣል።
ሦስተኛው ተጠያቂ “የአማራ ብልፅግና” የሚባለው ነው። ለአማራ ሕዝብ ብልፅግናውን ቀርቶ ህልውናውንም ሊያስጠብቅለት አልቻለም። ቀድሞ ከነበረው አጠቃላይ አቋም መሻሻል አላሳየም። ንቅናቄያችን አማራው እንደ ሕዝብ በአንድነት እንዲቆም ለማስቻል ለሁለት ዓመታት ያክል “የአማራ – ብልፅግናን” ለማግባባት ያደረገው ሰፊ እና ያላሰለሰ ጥረት ፍሬ አላፈራም። የአማራ ሕዝብንም፣ አብንንም በተደጋጋሚ ያሳዘነ ሲሆን፤ ከታሪክ ተጠያቂነትም አያመልጥም።
አብን በማዕከልም ሆነ በክልል ያሉ መንግሥታት የተጫወቱት አፍራሽ ሚና ውጤቱ በአማራው ሕዝብ ተገድቦ እንደማይቀር በውል እንዲጤን ይሻል። መንግሥት መሠረታዊ መብቶቹን የማያስጠብቅለትን ሕዝብ ማናቸውንም የሞራልም ሆነ የሕግ ግዴታ ሊጥልበት አይቻለውም። በሕዝብና በመንግሥት መካከል ያለው ማኅበራዊ ውልም ክፉኛ ይናጋል።
አብን በአማራው ላይ የሚደረገው የዘር ማጥፋት ድርጊት ዞሮ ኢትዮጵያን እንደሀገር ዋጋ እንደሚያስከፍልም ይገነዘባል። ንቅናቄያችን እስካሁን የአማራ ሕዝብ በኢትዮጵያዊነት ተስፋ እንዲቆርጥና ወደ አመፅ እንዲያመራ የሚደረገውን አሉታዊ ጥረት ሲታገል ቆይቷል። ሆኖም ከእንግዲህ ወዲያ የሕዝባችን ህልውና በምንም መልኩ ለድርድር እንደማይቀርብ ለማረጋገጥ ይወዳል።
አብን የአማራ ሕዝብ ሆደ ሰፊና አስተዋይ በመሆኑ ተፈጥሯዊ መብቱንና ነፃነቱን በልቅሶና በልመና ሳይሆን በተደራጀ ትግል እንደሚያስከብር ይተማመናል። ይህን ታላቅ ታሪካዊ ኃላፊነት በመምራት ከግብ ለማድረስ ድርጅታችን ቁርጠኝነቱን ያረጋግጣል።
አብን መንግሥት ችግሩን በአስቸኳይ ከማስቆም በተጨማሪ ጥቃቱን እንዲያምንና በስሙ እንዲጠራ፣ ጉዳዩን የሚያጣራ ገለልተኛ አካል በፍጥነት እንዲሰይም፣ ወንጀለኞችን አጣርቶ ለፍርድ እንዲያቀርብና ለተጎጂዎችም ተገቢውን ካሳ እንዲከፍል በጥብቅ ይጠይቃል። ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት መሠረታዊ ምንጭ የሆነው አማራ-ጠል ሕገ-መንግሥት የሚሻሻልበትን አግባብ በአስቸኳይ እንዲያመቻች ይጠይቃል።
አብን መንግሥት የሀገሪቱን ሰላምና ደህንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ማስከበር አለመቻሉንና በተደጋጋሚ የአማራ ተማሪዎችን ደህንነት ለመጠበቅ ችላ ማለቱን በማጤን ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ያደረገው የትምህርት መጀመር ጥሪም ያሳስበዋል። ብዙ ሽህ የአማራ ተማሪዎች በፅንፈኞች ጥቃት ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው ሲፈናቀሉ፣ ሲገደሉ፣ ሲደበደቡና ሲታገቱ በአሳፋሪ ሁኔታ አልታደጋቸውም። አሁንም ለተማሪዎች አስተማማኝ ጥበቃ እንዲያደርግ በጥብቅ እንጠይቃለን።
የአብን ብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በጥቅምት 14 እና 15 ቀን 2013 ዓ.ም ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ በወሰነው መሠረት በሀገራችንና በሕዝባችን ላይ ያንዣበበውን ከፍተኛ የደህንነት ስጋት በመቀልበስ፤ የሕዝባችንን ህልውና ለማረጋገጥ የሚያደርጋቸውን ሰላማዊና ሕጋዊ የትግል ጥረቶችና ስልቶች ለሕዝባችን ለማሳወቅ የፊታችን ረቡዕ ጥቅምት 18 በአማራ ክልል ከተሞች፤ እሁድ ጥቅምት 22 በአዲስ አበባ ታላላቅ ሕዝባዊ ትዕይንቶች ይደረጋሉ።
በእነዚህ ሰልፎች ላይ መላው የአማራ ሕዝብ ማናቸውም ልዩነት ሳይገድበው እንዲሳተፍ፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የአማራ የፖለቲካ ኃይሎች፣ የተለያዩ የአማራ የሲቪክ አደረጃጀቶች በወገናችሁ ላይ የሚደርሰውን ግፍና በደል እንድትቃወሙ ጥሪ እናደርጋለን።
አብን በአማራ ክልልና በአዲስ አበባ የተጠሩት የተቃውሞ ሰልፎች ፍፁም ሰላማዊ እንዲሆኑና ሊከተሉ የሚችሉ አላስፈላጊ ረብሻዎችንና ጥቃቶችን ለማስቀረት ሕዝቡ የራሱን ደህንነት በንቃት እንዲጠብቅ ያሳስባል።
ሰልፉን በተመለከተ ዝርዝር ጉዳዮች፣ በሰልፉ ላይ የሚተላለፉ መልዕክቶችና መፈክሮች በማዕከል ተዘጋጅተው በፓርቲያችን ይፋዊ ገፅ የሚለጠፉትና ለየአካባቢው የሚላኩት ናቸው።
ጉዳዩ የሕዝብ ህልውና ጥያቄና የራሱ ሰልፍ በመሆኑ የሀገር መከላከያና አጠቃላይ የደህንነት ኃይሉ የሕዝቡ ሰልፍ የተሳካ እንዲሆን ተገቢውን የፀጥታ ሥራ እንዲያከናውን ጥሪ እናደርጋለን።
በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ አማሮች እሁድ ጥቅምት 22 ቀን 2013 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከሚደረገው ሰልፍ ጋር በተለያዩ ክፍለ ዓለማት ድምፃችሁን እንድታሰሙ አብን ጥሪውን ያቀርባል።
ሰልፉ ለኮቪድ-19 ወረርሽኝ በማያጋልጥ መልኩ በጥንቃቄ እንዲካሄድ እያሳሰበ፥ ሕዝባችን በየአካባቢውና በየቤተሰቡ በገጠመን ፅኑ ወቅታዊ ችግር ላይ ውይይት እንዲያካሂድ፤ በቀጣይም ዘላቂ መፍትሄ ለማፈላለግ አብን ዓለምአቀፍ የመላው አማራ ሕዝባዊ ውይይት መድረኮችን እንደሚያመቻች መግለጽ ይወዳል።
በአዲስ አበባም ሆነ በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈፀመው የማናለብኝነትና የተረኝነት አካሄድ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ጉዳት በመሆኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ በወንድሙ በአማራው ሕዝብ ላይ የሚፈፀመውን ግፍና በደል በመቃወም አብሮ እንዲሰለፍ አብን ጥሪውን ያቀርባል።
አብን ከእንግዲህ ጉዳዩ የማያዳግም እልባት እስከሚያገኝ ድረስ ማናቸውንም የሰላማዊ ትግልና የሕዝባዊ እምቢተኝነት ስልቶችን በየደረጃው የሚተገብር በመሆኑ ሕዝባችን ከወዲሁ እንዲያውቀውና ወትሮ ዝግጁ እንዲሆን ጥሪያችንን እናቀርባለን።
አንድ አማራ ለሁሉም አማራ ፥ ሁሉም አማራ ለአንድ አማራ!
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)
ጥቅምት 16 ቀን 2013 ዓ.ም
ሸዋ፥ አዲስ አበባ፥ ኢትዮጵያ!October 24, 2020 at 1:53 am #16458In reply to: የፖለቲካ ፓርቲዎች ድምጽ (ኢትዮጵያ ውስጥ የሚነቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች)
AnonymousInactiveበእነ እስክንድር ነጋ ኢ-ፍትሃዊ እስር ላይ የተሰጠ መግለጫ
የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ጥቅምት 12 ቀን 2013 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ የእነ እስክንድር ነጋ የክስ ሂደትን አጀንዳ በማድረግ አስቸኳይ ስብሰባ አካሂዷል። ፓርቲው እስክንድር ነጋ (ሊቀ መንበር)፣ ስንታየሁ ቸኮል፣ ቀለብ ስዩም እና አስካለ ደምሌ በምንም ዓይነት የሚያስከስስ ወንጀል ጉዳይ እንዳልተሳተፉ እና ንጹሃን መሆናቸውን ከዚህ በፊት መግለጹ ይታወቃል፤ ይልቁንም የፍትህ ሥርዓቱን መጠቀሚያ በማድረግ በቀጣዩ [ሀገራዊ] ምርጫ ጠንካራ ተፎካካሪ የሚሆኗቸውን እነ እስክንድር ነጋ እና ፓርቲያቸውን ለማጥቃት ታስቦ እንደሆነ ገልጸናል። ይህንን አቋማችንን የበለጠ የሚያጠናክርልን ሁለት ነገሮች ደግሞ በጥቅምት 12 ቀን የችሎት ውሎ ታዝበናል፦
1ኛ. ዐቃቤ ሕግ ከዚህ በፊት ያሰማውን የምስክሮች ቃል በመተው እንደገና 21 (ሀያ አንድ) ምስክሮች ማንነታቸው ሳይገለጽ ከመጋራጃ ጀርባ እንዲሰሙ እና በዝግ ችሎት እንዲደመጡ ጥያቄ ማቅረቡ ላይ እየተደረገ ያለው የፍትህ አሰጣጡን የሚያዛባ እና የሚያጓትት ሂደት፤
2ኛ. የሚሰጡ ቀጠሮዎች (በተለይም አዳዲስ ዳኞች እንደተሾሙ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ በፓርላማም ከተናገሩ በኋላ) ረጅም መሆናቸው ሂደቱን በማጓተት እነ እስክንድር ነጋ ሳይፈረድባቸው በእስር እንዲቀጡ የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ በዚህ ዓመት በሚደረገው ምርጫ ከክሱ ነጻ ቢባሉ እንኳን እንዳይሳተፉ የሚያደርግ ሆኖ አግኝተነዋል።
እነዚህ እና መሰል ጉዳዩች በክስ ሂደቱ ላይ የአስፈጻሚው አካል ረጅም እጆች እንዳሉበት የሚያስረዱ ሆነው አግኝተናቸዋል። ከዚህም በመነሳት ፓርቲያችን መሪዎቻችን ትክክለኛ ፍትህ፣ ሳይዘገይ ያገኛሉ የሚል እምነት እንዳይኖረን አድርጎናል። ስለሆነው ፓርቲያችን የኦህዴድ/ብልጽግና ፖለቲካ ዓላማ ለማሳካት በማሰብ በሀሰት በተቀነባበረ ክስ የተያዙ አመራሮቻችንን ለማስፈታት ከዚህ በፊት ሲያደርገው ከነበረው ትግል በተለየ እና በበለጠ ሁኔታ ውጤታማ የሚያደርጉ የትግል መንገዶችን ነድፎ በሥራ ላይ ያውላል። መላው የፓርቲያችን አባላት እና ፍትህ ወዳጅ ሕዝባችን በቀጣይ ይፋ ለምናደርጋቸው የትግል እንቅስቃሴዎች እንደከዚህ ቀደሙ እራሱን እንዲያዘጋጅ እና ለነጻነት በሚደረገው ትግል ንቁ ተሳታፉ እንዲሆን ጥሪያችንን እናቀርባለን።
ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ)
አዲስ አበባ
ጥቅምት 13 ቀን 2013 ዓ.ምምንጭ፦ ባልደራስ
——
ሌሎች ተመሳሳይ ዜናዎች፦- የፖለቲካ ፓርቲዎች ድምጽ (ኢትዮጵያ ውስጥ የሚነቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች)
- ከኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) በወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታዎች ላይ የተሰጠ የአቋም መግለጫ
- የምንገኝበት የፖለቲካ ቀውስ፣ ፈጣን ፖለቲካዊ መፍትሔ ይፈልጋል! – ከኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ሥራ አስፈፃሚ የተሰጠ መግለጫ
- ሰላማችንን በማስጠበቅ እና ቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ ላይ በንቃት በመሳተፍ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠረት እንጣል! ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የተሰጠ መግለጫ
October 20, 2020 at 3:06 am #16418In reply to: ነፃ አስተያየት (ስለኢትዮጵያ በኢትዮጵያውያን)
AnonymousInactiveይድረስ ለትግራይና ለአማራ ምሁራን
“ሀገርን ለማዳን እስከጠቀመ ድረስ ተቃራኒን ግማሽ መንገድ ድረስ ሄዶ ማግኘት ጥበበኝነት እንጂ ተሸናፊነት አይደለም”
አወል እንድሪስ (ዶ/ር)ውድ የትግራይና የአማራ ምሁራን፥ እንደምን አላችሁ? ይህ ዛሬ የምፅፍላችሁ ሀሳብ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማችሁት እንዳልሆነ እረዳለሁ። በየግላችሁም የሀገራችንን ሁኔታ እያሰላሰላችሁ ምን ማድረግ እንደሚሻል እየተጨነቃችሁበት እንደሆነ እገምታለሁ። ሀገራችን በአጭር ተመልካች ፖለቲከኞችና እሳቱ ላይ ቤንዚን መጨመርን የመማርና የመመራመር ጥግ አድርገው የሚያዩ ኃላፊነት የማይሰማቸው የተማሩ ዜጎቻችን በሚያራግቡት የጥላቻና የመለያየት ሀሳብ ተገፍታ፣ ተገፍታ ገደሉ አፋፍ ላይ ትገኛለች። ይህን ሁኔታ ባወጣ ያውጣው ብሎ መተው ዛሬ እኛ፣ ነገ ደግሞ ልጆቻችን የሚያዝኑበትን ሁኔታ መጋበዝ ነው።
ያለንበት ጊዜ በሁለቱም ወገን የተለሳለሰ አቋም መያዝን መሸነፍ አድርጎ የሚያሳይ በመሆኑና የማንቀበለውንም ሀሳብ ለመስማት መዘጋ ጀትን እንደ ክህደት የሚያስቆጥር በመሆኑ አብዛኞቻችን ዝምታን መርጠን ተቀምጠናል። ዝምታ ግን አሁን ባለንበት ሁኔታ በፍፁም፣ በፍፁም ተመራጭ አይደለም። ምስኪን ገበሬ ከልጆቹ አፍ እየነጠቀ በከፈለው ግብር ተምረን፣ የሚለኮሰውም እሳት ይበልጥ የሚያቃጥለው እሱን ሆኖ እያለ፥ ዝም ማለት እንደሆነ እንጂ ይሻላል የሚባልን ሀሳብ መናገር በፍፁም፣ በፍፁም ክህደት ሊሆን አይችልም። እንዲያውም ክህደት የሚሆነው ምስኪኑን ገበሬና ልጆቹን በሚለኮሰው እሳት ውስጥ መማገድ ነው። ይህ እንዳይሆን ሁላችንም የግል ኩራታችንንና እብሪታችንን ወይም የምን ይሉኛል ፍርሀታችንን ወዲያ ጥለን የመፍትሄው አካል መሆን አለብን። ይህን በማድረግም በግል ለራሳችን ህሊና፣ በወል ደግሞ ሀገራችንን ከጥፋት በማዳናችን ለዜጎቻችን እረፍትና ሰላም እናስገኛለን።
በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ውስጥ በሁኔታዎች አስገዳጅነት የመጣው ለውጥ ከፈጠራቸው አሳሳቢ ጉዳዮች ዋነኛው በፌዴራሉ መንግሥትና በትግራይ ክልላዊ መንግሥት መካከል የተፈጠረው መፋጠጥ ነው። ይህ ለምን እንደሆነ ሁለቱም ወገኖች የየራሳቸውን ምክንያት ይደረድራሉ፤ ግን ፖለቲካችን የቁጭት፣ የብሽሽቅና የአብሪት ሆኖ ቁጭ ስላለ ማንኛቸውም ወገን ሌላውን ሊሰማ ፈቃደኛ የሆነ አይመስልም። ታዲያ በዚህ መካከል ሁሉም የሚሆነውን ለማየት እጁን አጣጥፎና አፉን ዘግቶ ከተቀመጠ መፍትሄ ሊሆን የሚችል ነገር ለማግኘት አስቸጋሪ ነው። ይህ ሁኔታ እንዲቀየር ለማድረግ ይጠቅም እንደሆነ የግሌን አስተያየት ከዚህ በታች በአጭሩ አቀርባለሁ። ቀድሜ መናገር ያለብኝ ነገር የማቀርበው ሀሳብ መፍትሄ አይደለም፤ ወደ መፍትሄው ለመድረስ ግን አንደኛው መንገድ ነው ብዬ አምናለሁ። እንደኔ ሀሳብ መፍትሄው በአንድ ሰው ወይም በአንድ ቡድን እጅ ውስጥ አይደለም፤ መፍትሄው የሁሉም ወገኖች ግልፅና ቅን ውይይት ብቻ ነው።
አቤቱታዬን ከፖለቲከኞቹ ይልቅ ለምሁራኑ ማድረግ የመረጥኩት ምናልባት ለግልፅነትና ለምክንያታዊነት እናንተ ትቀርቡ ይሆናል በሚል እምነት ነው። ፖለቲካ ማለት ውሸት ማለት መሆኑ በሚነገርባት ሀገር ፖለቲከኞቹም የትርጉሙን ትክክለኛነት እያረጋገጡልን በመምጣታቸው እነሱን ማመን አስቸጋሪ እየሆነብን መጥቷል። በሀገራችን ያለፉት አርባ እና ሀምሳ ዓመታት የፖለቲካ ታሪካችን ምሁራን ተብዬዎች የየራሳቸውን እንጂ የተለየ ሀሳብ ያለውን ወገን ለመስማት አለመፈለግ ትልቁ በሽታቸው ሆኖ ስለኖረ ፖለቲከኞችን ባናምን አይፈረድብንም። ለማንኛውም የመሰለኝን ላካፍላችሁና የሚሆነውን እንይ።
ለትግራይ ምሁራን
- ውጥረቱ ከዚህ በላይ ከቀጠለ ምን እንደሚፈጠር መገመት ባይቻልም “ትግራይን ለመክበብና ለማንበርከክ ዘመቻ ተከፍቶብናል” የሚለውን ትርክት ከበቂ በላይ ወስደው የህልውና አደጋ ተደቅኖብናል በሚል ሀሳብ መውጫ የለኝም የሚል ሰው የሚያደርገውን አጉል ነገር እንዳያደርጉ ባላችሁ ሁሉ የግንኙነት መስመር ተጠቅማችሁ የፖለቲካ መሪዎቻችሁን ሀሳብ ለማረጋጋት መሞከር አለባችሁ። አሁን ባለንበት ሁኔታ ሊበጠስ ትንሽ የቀረው መካረር መሀል የምትለኮስ ትንሽ ፍንጣሪ እሳት ልናቆመው ወደማንችል የሰደድ እሳት የመቀየሯ ዕድል ከፍተኛ ስለሆነ በምንም ዓይነት ሁኔታ ግጭት የሚቀሰቅስ ርምጃ መውሰድ ይቅርታ የማያሰጠው ስህተት መሥራት ይሆናል። ተቃዋሚ ሆኖ የራስን ሀሳብ እያራመዱ በክርክሩና በውይይቱ መቀጠል እንደሚቻልና እንደሚገባ ሁሉም ማወቅ ይኖርባቸዋል።
- ከህወሓት መሪዎችና አክቲቪስቶች የሚሰማው የትግራይ ዋና ጠላት ብአዴንና አብን ናቸው የሚለውን አስተሳሰብ እንዳለ በመቀበል ለግጭት የሚጋብዝ አቋም ከመያዝ በመቆጠብ እንኳን የብዙ ሺህ ዘመናት የቅርብ ግንኙነት ያላቸው የአማራና የትግራይ ሕዝቦች ቀርቶ ምንም በማይተዋወቁ ወገኖች መካከል የሚነሳ ልዩነት ከጦርነትም በኋላ እንኳ የሚፈታው በጠረጴዛ ዙሪያ በሚደረግ ድርድር መሆኑን ተገንዝባችሁ ከከፍተኛ ጥፋት በፊት ለውይይትና ድርድር ራስን ማዘጋጄት እንደሚገባ ለትግራይ ፖለቲካ መሪዎች በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ማስረዳት ይኖርባችኋል። ምንም እንኳ ከትግራይ መንግሥት መሪዎች በተደጋጋሚ ለውይይት ዝግጁ ነን የሚል ነገር ቢሰማም ለውይይቱ ቅድመ ሁኔታ የማስቀመጥ አካሄድ መከተል ዝግጁነቱ ከልብ ለመሆኑ ጥርጣሬን ይፈጥራል። ፌደራል መንግሥቱን አጣብቂኝ ውስጥ የመክተት አካሄድ ቅንነት የጎደለው አካሄድ ነው። ስለዚህ በአሁኑ የሀገራችን ሁኔታ ከፍተኛ ስጋት ሆኖ የሚገኘው በፌዴራል መንግሥትና በትግራይ ክልላዊ መንግሥት መካከል ያለው ልዩነትና ፍጥጫ ስለሆነ ለሱ መፍትሄ እስካመጣ ድረስ ውይይቱና ድርድሩ በሁለቱ መካከል መካሄዱ ይጠቅም እንደሆነ እንጂ ጉዳት የሚኖረው አይመስለኝም።
- ምንም እንኳ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በፖለቲከኞች ግፊት በተፈጠሩ ልዩነቶች ምክንያት መራራቅ የተፈጠረ ቢሆንም በአማራና በትግራይ ምሁራን መካከል መሠረታዊና የማይታረቅ ልዩነት አለ ለማለት ስለማይቻል ተቀራርቦ ለመነጋገር የሚቻልበትን መንገድ ሁሉ ቅድሚያውን በመውሰድ ማመቻቸት አስፈላጊና ጠቃሚ ነው። ሀገር ማለት ቀላል ነገር እንዳልሆነ፥ አንዴ መናድ ከጀመረ ማንም ኃይል ሊያቆመው የማይችል መሆኑን ተገንዝበን አለብን የምንላቸውን ልዩነቶች በውይይትና በመተሳሰብ መንገድ እንጂ በሌላ በምንም መንገድ እንደማንፈታቸው መቀበል አለብን። ተያይዘን ከመውደቅ ተያይዘን መቆም ይመረጣል።
ለአማራ ምሁራን
- ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታት አማራው የእኩልነት ፀር እንደሆነ በመወሰዱና ከክልሉ ውጭ ያለው ተራና ለፍቶ አዳሪ የአማራ ተወላጅ የጥቃት ሰለባ በመሆኑ አማራው ድሮ ያልነበረውን የአማራነት ስሜት ይዞ ራሱን ለመከላከል በአማራነት በመደራጀቱ የትግራይም ሆነ ሌሎች የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች አማራው “ያጣውን የበላይነት ለማስመለስ የሚታገል” ሆኖ እንዲታይ አድርጎታል። በዚህ የተነሳ የአማራውን መደራጀት የስጋት ምንጭ አድርጎ ማየት የተለመደ ሆኗል። ይህ ስሜት ለውይይትና ድርድር እንቅፋት እንዳይሆን አማራው ሌላውን የመጫን ምንም ዓይነት ፍላጎት እንደሌለው ደጋግሞ ማስረዳትና በተግባርም ከሌሎች ወንድም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጎን በመቆም ማረጋገጥ ይገባል። አሁን እየታየ ያለው ሁሉም ደረሰብኝ የሚለውን ችግርና አደጋ በተናጠል ለመቋቋም የሚደረግ አካሄድ አንዱ የሌላው ችግርና ጉዳት የሱም መሆኑን በሚያሳይ አካሄድና ተግባር መቀየር አለበት። ለዚህም አማራው ምንም እንኳ በሱ ላይ የደረሰውና እየደረሰ ያለው ችግር ከፍተኛና ጊዜ የማይሰጥ ቢሆንም የሌሎች ወንድምና እህቶቹ ኢትዮጵያውያን ችግርና ጉዳት የሱም መሆኑን፥ ለመፍትሄውም የራሱን አስተዋፅዖ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን በተቻለው ሁሉ ማሳየት አለበት።
- በዚህ ረገድ ከትግራይ ወንድም ሕዝብና ከልጆቹ ምሁራን ጋር ተቀራርቦ ለመነጋገርና ልዩነቶችን ለማጥበብ ያለውን ዝግጁነት ቅድሚያ በመውሰድ በተግባር ማሳየት ተገቢ ነው። ይህ የሚደረገው በተሸናፊነትና በአጎብዳጅነት ስሜት እንዳልሆነ አስረግጦ በመናገር የጋራ የሆነ ሀገር የማዳን ጥረቱን በሆደ ሰፊነትና በከፍተኛ የኃላፊነት መንፈስ ማራመድ ያስፈልጋል። ይህን ለማድረግም አሉ የተባሉ የግንኙነት መስመሮችን ሁሉ በመጠቀም ከትግራይ ምሁራን ጋር ለመወያየት ዝግጁነትን መግለፅ ይጠቅማል። ሀገርን ለማዳን እስከጠቀመ ድረስ ተቃራኒን ግማሽ መንገድ ድረስ ሄዶ ማግኘት ጥበበኝነት እንጂ ተሸናፊነት ሊሆን አይችልም።
- ፅንፈኛ የሆነ አቋም በማንም ይያዝ በማን አውዳሚ መሆኑን ማወቅና ፅንፈኛ ወደሆነ አቋም የሚደረግን ግፊት መቋቋም እጅግ አስፈላጊ ነው። በዚህ ረገድ ልክ እንደ አንዳንድ የትግራይና የኦሮሞ አክቲቪስቶች አንዳንድ የአማራ አክቲቪስቶችም የሚያራምዱትን ፅንፈኛ አቋም መታገል ተገቢ ነው። የሁሉም ጥሩ ነገር ምንጭ አማራ፥ የዚች ሀገርም መሥራችና ጠባቂ አማራ ነው የሚል አቋም ሌሎች ኢትዮጵያውያንን የሚያስከፋና የሚያርቅ፣ በመጨረሻም ሀገራችንን የሚጎዳ መሆኑን ማመን ያስፈልጋል። ሀገራችን የምትድነው በሁላችንም ጥረት እንደሆነ፥ ለዚህም ሁሉም እኩል ድርሻ እንዳለው መቀበል ይገባል። ይህ ሲሆን ጠንካራና ሁሉንም በእኩል ዓይን የምታይ ሀገር ይኖረናል። ለዚህ ውጤት የትግራይና የአማራ ምሁራን ትልቅ ድርሻ አላችሁ። ይህንን ኃላፊነታችሁን ለመወጣት አንዱ አንዱን ሳይጠብቅ ቅድሚያውን ወስዶ በመነጋገር መፍትሄ መፈለግ ይጠበቅባችኋል። ሀገራችን ከአንድ ወይም ሌላ የፖለቲካ ድርጅት፣ ከአንድ ወይም ሌላ የፖለቲካ ሰው፣ ከአንድ ወቅት የፖለቲካ እብደት በላይ ነች። ይህ ሁሉ ሲያልፍ “ሊያልፍ ውሀ አደረገኝ ድሀ” ከማለት ያውጣን!!
አወል እንድሪስ (ዶ/ር)
ዶ/ር አወል እንድሪስ የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (UNESCO) አቅም ግንባታ ዓለምአቀፍ ተቋም የአፍሪካ መርሀግብር ተጠሪ (Program Officer, UNESCO International Institute for Capacity Building, Africa) ናቸው።
ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረ–ገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forums) ላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።
October 19, 2020 at 2:36 pm #16408In reply to: የፖለቲካ ፓርቲዎች ድምጽ (ኢትዮጵያ ውስጥ የሚነቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች)
AnonymousInactiveከኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) በወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታዎች ላይ የተሰጠ የአቋም መግለጫ
የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ሀገራዊ ምክር ቤት አንደኛ ዓመት ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባዉን ከመስከረም 29 ቀን እስከ ጥቅምት 1 ቀን 2013 ዓ.ም ሲያካሂድ በወቅታዊ የኢትዮጵ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የሰላም መደፍረስ ጉዳዮች ላይ በስፋትና በጥልቀት መክሯል፤ ፓርቲው የሚተገብራቸውን የተለያዩ መመሪያዎች፣ እንዲሁም የ2013-2017 ዓ.ም የፓርቲዉን የአምስት ዓመት ስልታዊ ዕቅድና የ2013 ዓ.ም የአንድ ዓመት ዕቅድ በስፋት እና በጥልቀት በመመርመር ወደተግባር እንዲገቡ በሙሉ ድምጽ ዉሳኔ ካሳለፈ በኋላ የሚከተሉትን የአቋም መግለጫዎች አዉጥቷል።
- ሁሉንም ተግባራት ማከናወን የሚቻለዉ በሀገሪቱ አራቱም ማዕዘኖች ሰላም ሲኖርና የሕግ የበይላነት ሲከበር መሆኑ ለሁሉም ግልጽ ነዉ፤ ነገር ግን በመላ ኢትዮጵያ ሀገሪቱን ለ27 ዓመታት ሲዘርፍና የዜጎችን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በመንፈግ እንደፈለገ ሲያስር ሲገድልና ሲያኮላሽ የነበረዉ ዘረኛዉ ህወሓት ከጠቅላይ አምባገነንቱ ተባሮ መቀሌ ከመሸገበት እና በዶ/ር ዐቢይ አህመድየሚመራዉ “የለዉጡ ቡድን” መንግሥታዊ ስልጣን ከተቆናጠጠበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ ሁነቶች ተከስተዋል። በሀገራችን ኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታ እጅግ ዘግናኝ ግድያዎችና የዘር ማጥፋት ወንጀሎች ነፍስ ባላወቁ እምቡጥ ሕፃናት ሳይቀር በጽንፈኛ ብሔርተኞችና እነሱ በሚደግፏቸዉ ታጣቂ ቡድኖች፤ በኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ (በተለይ በመተከል በተደጋጋሚ) እንዲሁም በደቡብ ክልሎች እስካሁን ድረስ እየተፈጸሙ ነዉ። ዜጎች በገዛ ሀገራቸዉ እንደሁለተኛ ዜጋ እየታዩ ሀብት ንብረታቸዉ እየተዘረፈና እየወደመ፣ ከመኖሪያ ቀያቸዉ እየተፈናቀሉ ነዉ። ኢሕአፓ ከዚህ በፊት ባወጣቸዉ ተደጋጋሚ አቋሞቹ እንደገለጸዉ፥ መንግሥት የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ያሳየዉ ቸልተኝነትና መዘግየት እነዚህ ሁሉ ዘግናኝ ድርጊቶች እንዲፈጸሙ በር እንደከፈተ ያምናል። ስለዚህ ሉዓላዊነታችንንና የሕግ የበላይነትን የማስከበር፣ ሀገራዊ ሰላምን የማረጋገጥ እና የዜጎችን ደህንነነት የመጠበቅ ኃላፊነት ያለባቸዉን የተለያዩ የጸጥታ መዋቅሮች የሚመራዉ መንግሥት ስለሆነ፥ አሁን የጀመረዉን ሕግ የማስከበር ሥራ አጠናክሮ እንዲቀጥል፣ በአጥፊዎችም ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወስድ፣ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በተለይም በቤኒሻንጉልና በኦሮሚያ መሽገው የዜጎችን ህይወት የሚቀጥፉ ሕገ-ወጥ ታጣቂ ቡድኖች ላይ ትጥቅ የማስፈታት እና ወደሕግ የማቅረብ፤ በወንጀል ድርጊት ያልተሳተፉትን አጣርቶ ወደ ሰላማዊ ኑሯቸዉ እንዲመለሱ የማድረግ የማያዳግም እርምጃ እንዲወስድ ይጠይቃል፤ ፓርቲያችን ኢህአፓም ጸረ-ሰላም ኃይሎችን በጽናት ይታገላል።
- በሀገራችን ኢትዮጵያ ላለፉት በርካታ ዓመታት የሚፈጸሙት ዘግናኝ የሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች መጣስ መንስዔው በዋነናት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግሥት ስለመሆኑ በተደጋጋሚ ተገልጧል። ከሁለት ዓመታት በፊት፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አስተዳደርም ሕገ-መንግሥቱን ለማሻሻል በተደጋጋሚ ቃል ገብቶ እንደነበረ ይታወቃል። ነገር ግን ያ ሁሉ ቃል-ኪዳንና ያ ሁሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ወደጎን ተትቶ፥ በፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድርና ውይይት ወቅት ይታያል ተብሎ የነበረው ሕገ-መንግሥት ምንም ዓይነት ማሻሻያም ሆነ ማስተካከያ ሳይደረግበት ከሃያ አምስት ዓመታት በላይ ለሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ሁሉ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ዋነኛው መንስዔ እንደሆነ አለ። ኢሕአፓ ኢትዮጵያ ውስጥ በገዢው ፓርቲና በአጋሮቹ ለሚፈጸሙት ግፎች ሁሉ የመጀመሪያው ተጠያቂ ይህ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግሥትና ይዘቱ ስለሆነ አስቸኳይ ማሻሻያ እንዲደረግበት መንግሥትን ይጠይቃል።
- በተጨማሪም፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር በተደጋጋሚ ይደረጋል እያለ ቃል ሲገባ የነበረው የብሔራዊ ዕርቅና የሀገራዊ መግባባት አጀንዳ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ አጀንዳ እንደሆነ ኢሕአፓ ጽኑ እምነት አለው። በኢትዮጵያ የሚገኙት ሕጋዊና ሰላማዊ የሆኑት የፖለቲካ ኃይሎች በሙሉ የሚሳተፉበት፣ ሀገራዊ መግባባትን ትኩረቱ ያደረገ የፓርቲዎችና የሲቪክ ማኅበራት የጋራ መድረክ አስፈላጊነት ሳይታለም የተፈታ በመሆኑ፥ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መንግሥት ለዚህ አጀንዳ ቅድሚያ ሰጥቶ የውይይትና የድርድር መድረኩ በአፋጣኝ እንዲካሄድ ኢሕአፓ ጥሪውን ያስተላልፋል።
- በያዝነው የ2013 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ይካሄዳል የተባለውና የሚጠበቀው 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ሕጋዊና ሰላማዊ ሆኖ እንዲተገበር ኢሕአፓ ከፍተኛ የሆነ ፍላጎት አለው። በመሆኑም፥ ምርጫ የአንድ ቀን ተግባር ሳይሆን የብዙ ወራትን የመደራጀትና የማደራጀት ተግባራት ከእያንዳንዱ የፖለቲካና የሲቪክ ማኅበር የሚጠይቅ ክንውን መሆኑ ግልጽ ነው። ሆኖም ግን ከ5ኛው ሀገራዊ ምርጫ ማግስት ጀምሮ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መንግሥት ሰላምንና ጸጥታን ማስከበር ተስኖት በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ውስጥ ሁከትና ብጥብጥ እየተከሰተ ይገኛል። በዚህ ያለመረጋጋትና የሰላም እጦት ውስጥ ሆኖ ምርጫን የሚያክል ከፍተኛ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማድረግም አጅግ አዳጋች ነው። በመሆኑም መንግሥት ሁሉም ዜጎች በሕግ ፊት እኩል የሚሆኑበትንና የሚዳኙበትን የፖለቲካ-ኢኮኖሚ ምህዳር አስፍቶ የዜጎችን በሕግ የበላይነት ሥር ብቻ የመምረጥና መመረጥ መብታቸውን እንዲያከናውኑ የማድረግ ኃላፊነቱን በተግባር እንዲወጣ ኢሕአፓ ጥሪውን ያስተላልፋል።
- በየጊዜዉ እያሻቀበ ያለዉ የዋጋ ግሽበትና በኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰት ምክንያት በከፍተኛ ደረጃ ቁጥሩ የጨመረዉ ሥራ አጥነት የዜጎችን የእለት ተእለት ኑሮ በሰቆቃ የተሞላ አድረጓል፤ ከዚህ በተጨማሪ ባሳለፍነዉ 2012 ዓ.ም በተከሰቱ ሰው-ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችም ለከፋ የርሀብ አደጋ ተጋላጭ ሆነዋል። በመሆኑም ኢሕአፓ መንግሥት በረዥም ጊዜ ለዜጎች በተለይም ለወጣቶች በርካታ የሥራ ዕድል መፍጠር የሚችሉ ሀገር በቀል ኢንቨስትመንቶችን እንዲያስፋፋ፣ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ እና ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርን በመቆጣጠር የዋጋ ግሽበቱን ከ2 ዲጂት በታች የሚወርድበትን የኢኮኖሚ አማራጭ እንዲተገበር፣ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸዉም ተገቢዉን ድጋፍ በወቅቱ እንዲያቀርብ በአጽንኦት ይጠይቃል።
- ከደንቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ወደ ትዉልድ ቀያቸዉ ሲመለሱ ታፍነዉ ተወስደዉ እስካሁን ድረስ ደብዛቸዉ የጠፋዉ ተማሪዎች ጉዳይ አሁንም ድረስ የኢሕአፓ የእግር እሳት ነዉ፤ ስለዚህ መንግሥት ልዩ ተኩረት ሰጥቶ ተማሪዎቹ እዉነት በህይወት ካሉ የማስመለስ ሥራ እንዲሠራ፥ አለያም እዉነቱን ለቤተሰቦቻቸዉ፣ ለኢትዮጵያና ለዓለም ሕዝብ እንዲያሳውቅ ኢሕአፓ የዘወትር ጥያቄዉን ዛሬም ያቀርባል።
- ኢሕአፓ ሕብረ-ብሔራዊ ፓርቲ እንደመሆኑ በኢትዮጵያ አንድነትና ሉአላዊነት፣ በሕዝቧ ዉህድ ማንንነት የማይጠራጠሩ፣ በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ትግል ለሚያምኑና በሕጋዊ መንግድ ለተደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሁሉ ኑ! ሀገራችን ከገባችበት ጽንፈኛ የጎሳ እና የጥላቻ ፖለቲካ ቅርቃር በጋራ እንታደጋት፤ ሀገራዊ ብሔራዊ መግባባትን በመፍጠርና የፖቲካ ቁርሾን በማስወገድ ዘላቂ ሰለማና እድገት የሰፈነባት ሀገር እናድርጋት፤ የሚል የአክብሮት ጥሪዉን ያስተላልፋል።
- በሀገር ቤትና በዉጪ ሀገር ለምትገኙ ቀደምት የኢሕአፓ አባላትና መሥራቾች ዘላለማዊ ከሆነዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ህላዌ ጋር በየጊዜዉ እየታደሰ የሚዘልቅ ዘመን ተሸጋሪ ሀሳብ ያነገበዉ ኢሕአፓ ከዉጪ ሀገር ወደ ሀርቤት ከገባ ጊዜ ጀምሮ በሀገሩ ምድር ላይ ትግሉን በጽናትና ቁርጠኝነት እያካሄደ መሆኑን ተገንዝባችሁ ፓርቲያችን ኢሕአፓን በተለያየ መንገድ በመደገፍና በማጠናከር የትግላችሁን ፍሬ ማፍራት እውን ታደርጉ ዘንድ ጥሪዉን ያስተላልፋል።
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!
ኢሕአፓ ለተሻለ ነገ!የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)
ጥቅምት 5 ቀን 2013 ዓ.ም
አዲስ አበባOctober 19, 2020 at 3:21 am #16398In reply to: አዲስ አበባ ከተማን የተመለከቱ ሰሞነኛ ዜናዎችና መረጃዎች
AnonymousInactiveአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት ተጨማሪ 560 አውቶቡሶች ተሰማሩ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚታየውንና እጅግ ስር የሰደደውን የሕዝብ ትራንስፖርት ችግር በጥቂቱ ለመቅረፍ ተጨማሪ 560 አውቶቡሶች ለአገልግሎት መሰማራታቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስታውቋል።
“የትራንስፖርት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከአውቶብስ አቅርቦት በተጨማሪ ዘመናዊ የትራንስፖርት የመሠረተ ልማት ሥርዓት እንዲዘረጋ በልዩ ትኩረት እየተሠራ ነው” በማለት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ተናግረዋል።
ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በኪራይ ወደ ስምሪት የገቡትን እነዚህን 560 አውቶብሶች ሥራ አስጀምረዋል።
በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ እንደገለጹት፥ በአዲስ አበባ ከተማ የሚታየው የትራንስፖርት ችግር በነዋሪዎች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑን ገልጸዋል።
የትራንስፖርት ችግሩን በተወሰነ ደረጃ ለመፍታት በመንግሥት እና በግሉ ዘርፍ የጋር ትብብር 560 አውቶብሶችን በኪራይ ለሕብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ የከተማ አስተዳደሩ በልዩ ሁኔታ መወሰኑን ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ተናግረዋል።
ለዚህም የከተማ አስተዳደሩ ከአሁን ቀደም በየወሩ ለብዙኃን ትራንስፖርት አገልግሎት 58 ሚሊዮን ብር ድጎማ በማድረግ ላይ ሲሆን፤ አሁን ደግሞ ለአውቶቡሶች ኪራይ 63 ሚሊየን ብር በጠቅላላው 121 ሚሊዮን ብር ድጎማ እንደሚያደርግ ምክትል ከንቲባዋ አመልክተዋል።
የትራንስፖርት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትም ከአውቶብስ አቅርቦት በተጨማሪ ዘመናዊ የትራንስፖርት የመሠረተ ልማት ሥርዓት እንዲዘረጋ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በልዩ ትኩረት እየተሠራ መሆኑን ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ጠቁመዋል። በቀጣይ ሁለት ዓመታትም በ12 ቢሊዮን ብር ወጪ 3 ሺህ የሚሆኑ አውቶብሶችን በግዢ ለማስገባት የከተማ አስተዳደሩ በሂደት ላይ መሆኑንም ምክትል ከንቲባዋ ተናግረዋል። ወደፊትም የነዋሪዎቻችንን ችግር በቅርበት አዳምጠን እና ተረድተን ተጨባጭ መፍትሄ የመስጠቱን ሥራ አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል – ወ/ሮ አዳነች።
በኪራይ ወደ ስምሪት የ560 አውቶብሶች ከጥቅምት 9 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ሥራ የሚጀምሩ ሲሆን ለአንድ ሳምንት ያህል ለሁሉም የከተማዋ ነዋሪ የነፃ አገልግሎት እንደሚሰጡ ተገልጿል።
በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ አስተባባሪ አቶ ጃንጥራር አባይ እና ሌሎች የከተማዋ ከፍተኛ የሥራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል።
ምንጭ፦ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክሪታሪያት/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
October 16, 2020 at 1:58 pm #16366AnonymousInactiveዶክተር ድረስ ሣህሉ ጎሹ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሆነው ተሾሙ
ባህር ዳር (ሰሞነኛ)– የባህር ዳር ከተማ ምክር ቤት ጥቅምት 6 ቀን 2013 ዓ.ም ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ ዶክተር ድረስ ሣህሉ ጎሹን የባህር ዳር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ በማድረግ በሙሉ ድምፅ ሹሟል።
በባህር ዳር ከተማ ምክር ቤት በከተማው የተቀዳሚ ከንቲባነት የተሾሙት ዶክተር ድረስ ሣህሉ ጎሹ የመጀመሪያ ድግሪያቸውን በምድረ ፅፍ እና አካባቢ ጥናት (geography and environmental study) ከሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ያገኙ ሲሆን፤ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በአመራር እና መልካም አስተዳደር (leadership and good governance) ከኢትዮጵያ ሲቪል ሠርቪስ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል። በመቀጠልም የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በሥራ አመራር (management) ቻይና ከሚገኘው ኋጆንግ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂያገኙ ዩኒቨርሲቲ (Huazhong University of Science and Technology) ሲሆን፥ ሁሉንም የትምህርት ደረጃዎች በከፍተኛ ማዕረግ የተመረቁ ናቸው።
ዶክተር ድረስ ሣህሉ የአማራን ሕዝብና መንግሥት በተለያዩ የሥራ ኃላፊነት ቦታዎች ከወረዳ እስከ ክልል ድረስ ባሉ የተለያዩ የመንግሥት መዋቅሮች በውጤታማነት እና በታማኝነት ያገለገሉ ሲሆን፥ ከእነዚህም መካከል በዞን ደረጃ የምዕራብ ጎጃምዞን የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ እንዲሁም የዞኑ የሕዝብ ግንኙነትና የከተማ አደረጃጀት አማካሪ በመሆን አገልግለዋል። ከዚህ በተጨማሪም በክልሉ የምሁራን ተሳትፎና አደረጃጀት ዘርፍ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ አማካሪ ሆነው አገልግለዋል። በአጠቃላይ የዶክተር ድረስ ሣህሉ የሥራ ልምድ የሚከተለውን ይመስላል፦
- በምስራቅ ጎጃም ዞን በደባይ ጥላት ግን እና በባሶ ሊበን ወረዳ የደን እርቻ ልማት (agro forestry) እና የመሬት አስተዳደር ባለሙያ በመሆን ለአራት ዓመታት አገልግለዋል፤
- በምስራቅ ጎጃም ዞን በባሶ ሊበን ወረዳ የአስተዳደር እና ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ በመሆን አገልግለዋል፤
- በአነደድ ወረዳ የግብርና ኃላፊ፣ የመሬት አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ፣ የሕዝብ ተሳትፎና አደረጃጃት አማካሪ በመሆን አገልግለዋል፤
- በምዕራብ ጎጃም ዞን ቋሪት ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ በመሆን አገልግለዋል፤
- በጃቢ ጠህናን ወረዳ የመሬት አስተዳደር ጽኅፈት ቤት ኃላፊና የሕዝብ ግንኙነት አማካሪ በመሆን አገልግለዋል።
- የምዕራብ ጎጃም ዞን ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ፣ የሕዝብ ግንኙነትና የከተማ አደረጃት አማካሪ በመሆን አገልግለዋል፤
- በአማራ ክልል የምሁራን ተሳትፎና አደረጃጀት ዘርፍ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አማካሪ ሆነው አገልግለዋል።
ዘገባው የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት እና የአማርኛ መገናኛ ብዙሃን ኤጀንሲ ቤት ነው።
October 15, 2020 at 1:39 am #16351In reply to: ነፃ አስተያየት (ስለኢትዮጵያ በኢትዮጵያውያን)
AnonymousInactiveበአዳራሽ ስብሰባ ለማድረግ ፈቃድ ከልክሎ በአደባባይ ቢልቦርድ እንዲሰቀል እንዴት ፈቀዳችሁ?
አቶ ግርማ ሰይፉ ማሩ“መስከረም 30 መአት ይወርዳል” ከሚሉት ጋር የማልስማም መሆኔን አስረድቻለሁ። መስከረም 30 በአዲስ አበባ ጎዳና ወጥተው የተመለከትኩት፥ በየአደባባዩ የተሰቀለው የማስታወቂያ ሰሌዳ (billboard) ግን አንድ ነገር አስታዋሰኝ። የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ አደራጅ ኮሚቴ (ኢሠፓአኮ) ማብቂያው ደርሶ፣ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ (ኢሠፓ) ሊመሠረት ዋዜማው ላይ በከተማቸን የምናየው መፈክር ሁሉ፥ “ከጓድ መንግሥቱ ኃይለማርያም አመራር ጋር ወደፊት!”፣ “ብልሁ፣ አስተዋዩ መሪ መንግሥቱ ኃይለማርያም…” ወዘተ… የሚሉ ነበሩ። አልቀረልንም… ከዝሆን እና አንበሳ ምረጡ ተባለና ዝሆን ተመረጠ፤ አለቀ ደቀቀ። ይህ በሁለት የአንድ ፓርቲ አባላት መካከል በሚደረግ ምርጫ ዝሆን ቢመረጥ፣ አንበሳ ወይም ሚዳቋ ብዙ ትርጉም የለውም። ኢሠፓ ያለውን መንግሥቱን መርጧል።
ዛሬም ብልፅግናዎች ዐቢያቸውን “ብልሁ መሪ” የማለት መብታቸውን አከበራለሁ። ያላቸውን የመምረጥ መብት አላቸው። በአጠቃላይ ለሀገሩ እና ለከተማው ነዋሪ ይህን በግድ መጫን ግን መብታቸው አይደለም። በመጀመሪያ ደረጃ የምርጫ ቅስቀሳ ሳይጀመር ምርጫ ቅስቀሳ ማድረግ፣ ሌላውን በቢሮ ለሚደረግ ውይይት ፍቃድ ሰጪና ነሺ የሆነ መንግሥት፥ በትራፊክ መንገድ አዘግቶ “ዐቢይ ለዘላለም ይኑር!” መፈክር ተገቢና ትክክል አይደለም። ይህ መንገድ የመንግሥቱ ኃይለማርያም መንገድ ነው። ብልፅግና ኢሠፓአኮን/ኢሠፓን መሆን ካማረው ሕጉን ይለውጥና ምርጫ ቦርድን ዘግቶ መጫወት ይችላል። የሚከተለውን ለመቀበል መዘጋጀት ብቻ ነው የሚጠበቅበት።
አስገራሚው ዛሬም በየቀበሌና ወረዳው በዚህ ደረጃ ወርደው የሚያዋርዱ ካድሬዎች መኖራቸው ነው። “ታላቁ መሪ መንግሥቱ ኃይለማርያም!”፣ “ታላቁ መሪ ዐቢይ አህመድ!” ብሎ ለመፃፍ ልብ የሚያገኙ ካድሬዎች እንዴት ነው ማፍራት የተቻለው? መክሸፍ ማለት ይህ ነው፤ ከታሪክ መማር ያለመቻል። የሀገርን መሪ በሕዝብ ድምፅ ቢቻል በቀጥታ ድምፅ ይሰጥ የምንለው አብዛኛው ይሁንታ የሰጠው እንዲመራን እንጂ፥ ካድሬ እንዳይመርጥልን ሰለምንፈልግ ነው። ዶ/ር ዐቢይ አህመድ የአዲስ አበባ ተመራጭ አይደሉም፤ በቀጣይ አዲስ አበባም የሚወዳደሩ ከሆነ በወረዳቸው ይህን ማድረግ ይቻላል። ግን ገና ለገና መስከረም 30 መንግሥት የለም ካሉት ጋር ብሽሽቅ ለመግባት የዚህን ያህል መውረድ አያስፈልግም። የዚህ ዓይነት ድርጊቶች ሳይቃጠል በቅጠል ካልተባለ፥ ምርጫ ሲጀመር በየወረዳው ኃላፊነት ላይ ያሉት የብልፅግና ሰዎች መላወሻ ሊከለክሉን ግድ አይሰጣቸውም። ይህ መስመር ግን በወረዳ የብልፅግና ካድሬዎችንም ቢሆን አይጠቅምም፤ አያኗኑርም ብሎ መመከር ደግ ነው።
የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፣ ምርጫ ቦርድ፣ ወዘተ… በዚህ ዓይነት ጉዳይ ላይ የማረሚያ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል። የአዲስ አበባ መስተዳደር ለዚህ ጉዳይ ፈቃድ የሰጠ መሆኑን ጋዜጠኞች እባካችሁ አጣሩልን። ሥራችሁን ብትሠሩ ጥሩ ነው። ‘በአዳራሽ ስብሰባ ከልክሎ በአደባባይ እንዴት ፈቀዳችሁ?’ በሉልን፤ የዚህ ዓይነት ድርጊት “ብልግና” ነው በሏቸው።
ግርማ ሰይፉ ማሩ
አቶ ግርማ ሰይፉ ማሩ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) አመራር አባል (የብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ አባል) ሲሆኑ፤ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ፓርላማ) በቸኛው ተቃዋሚ አባል በመሆን አገልግለዋል።
ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረ–ገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forums) ላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።
October 15, 2020 at 12:02 am #16344In reply to: ነፃ አስተያየት (ስለኢትዮጵያ በኢትዮጵያውያን)
AnonymousInactiveየሰላም ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል ሃሳብ ሊደገፍ የሚገባው ነው
የሺዋስ አሠፋወ/ሮ ሙፈሪሃት የፌደራል መንግሥቱን (ብልፅግና) እና የትግራይ ክልል አስተዳደርን (ህወሓት) መካረር በተመለከተ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የገለፁትን አይቼ በግሌ ጥሩ ጅምር ነው – ይበርቱ ብያለሁ። ስድብ፣ ፉከራ እና ይዋጣልን ሀገርን እና ሕዝብን ምስቅልቅል ውስጥ ከመክተት ውጭ ምንም ፋይዳ የለውም። “እልህ ምላጭ ያስውጣል” እንዲሉ ለራሳችሁም ቢሆን ውስጣችሁን የሚቆራርጥ ከሚሆን በስተቀር አይጠቅምም። የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አቋራጭ መንገድ የለውም፣ ውይይት/ድርድር ብቻ! በጉልበት/በጠመንጃ የሚሆን ቢሆን ኢትዮጵያን የሚቀድም ባልነበረም ነበር። ልብ በሉ ለውይይት አሻፈረኝ የሚሉ ወገኖች በስተመጨረሻ ቢፈልጉ አያገኙትም፤ ምክንያቱም አይበለው እንጂ ጦርነትም ቢሆን መቋጫው ውይይት/ድርድር ነው።
በ2009 ዓ.ም ራሳቸው ወ/ሮ ሙፈሪሃት የነበሩበትን የፓርቲዎች ውይይት/ድርድር (ስያሜው ራሱ አወዛጋቢ ነበር) ባስታውሳቸው ጠቃሚ የሚሆን ይመስለኛል። ሙከራው የተቀጨው ከጅምሩ ነበር። የቀድሞ ገዢ ፓርቲን ጨምሮ 22 ሀገር አቀፍ ፓርቲዎች ለሚያደርጉት ውይይት/ድርድር የመሀል ዳኛ (mediators) ያስፈልጋሉ/አያስፈልጉም በሚለው የጦፈ ክርክር ተደርጎ ኢህአዴግ እና ሌላ አሁን ስሙን የማላስታውሰው አንድ ፓርቲ አያስፈልግም ሲሉ 20 ፓርቲዎች ያስፈልጋል ብለን በከፍተኛ ቁጥር አሸነፍን፣ mediators ሊሆኑ የሚችሉትን ወገኖች የሥራ ልምድና የትምህርት ደረጃ መግለጫ (ማለትም፥ CV) እና ዝርዝር ማዘጋጀት ጀመርን።
በዚህ የተናደዱት የሂደቱ ፊትአውራሪ የነበሩት የተከበሩ አቶ አስመላሽ ወልደሥላሴ [የህወሓት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል] ለሳምንት እንደገና እንየው ብለው በተኑት። በሳምንቱ ራሳቸው አጀንዳውን አንስተው mediators ያስፈልጋሉ/አያስፈልጉም እጅ አውጡ ሲሉ ጠየቁ። ከመድረክና ሰማያዊ ፓርቲ ውጭ ሁሉም አያስፈልጉም አሉ። በሳምንት ልዩነት 20 ለ 2 ውጤቱ ሲገለበጥ ወ/ሮ ሙፈሪሃት እጃቸውን በአፋቸው ጭነው ይታዘቡ ነበር። እኔም በጣም ተበሳጭቼ “የተከበሩ አቶ አስመላሽ! ሳምንቱን ሙሉ ሲደልሉና ሲያስፈራሩ ሰንብተው ውጤቱን በጉልበት አስቀየሩት! ይሄ ጉልበት ግን አይቀጥልም፤ ነገ በሌላ ጉልበት ይሰበራል!” ብዬ ትቻቸው ወጣሁ። ሂደቱም ተጨናግፎ ቀረ (በወቅቱ ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 ሬድዮ ዘግቦታል)። ከ3 ዓመታት በኋላ እነአቶ አስመላሽን ወክለው አቶ አዲስዓለም ባሌማ ሁሉን አካታች ውይይት/ድርድር እናድርግ ብለው ሲጠይቁም፣ ያልተገባ ምላሽ ሲሰጣቸውም በተራዬ በትዝብት ተመለከትኩ።
ዛሬ የመንግሥት አካል ከሆነው የሰላም ሚኒስትር መፍትሄው ውይይት/ድርድር ነው የሚል ተነሳሽነት ሲመጣ አያስፈልግም ብሎ መታበይም ሆነ ተለመንኩ ብሎ ማጣጣል አይገባም። ሚኒስትሯ እንዳሉት፥ ከስሜት ወጥቶ፣ ሰከን ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል። በእኔ እምነት ይሄ ትልቅ እርምጃ ነው፤ ቀጣዩን ታሪክ ለመሥራት መሽቀዳደም ለኢትዮጵያ ውለታ ነውና ማን ይሆን ፈጥኖ ወደ መቀሌ ከተማ ወይም ወደ ወለጋ ጫካዎች ነጭ ባንዲራ ይዞ የሚዘምተው? (የኬንያው Building Bridges Initiative (BBI) ጥሩ መማሪያ ይሆነናል) ወይም ወደአዱ ገነት የሚመጣው? የወጣቶቻችንን ህይወት ከመቀጠፍ፣ የእናቶቻችንን እንባ ከመፍሰስ የሚታደገው? ከፌደሬሽን ምክር ቤት? ከሰላም ሚኒስትር? ከሀይማኖት አባቶች? ከእርቀ-ሰላም ኮሚሽን? ከሀገር ሽማግሌዎች? ከግብረ ሰናይ ድርጅቶች? ከአባ ገዳዎች? ከጋሞ አባቶች? እናቶች? ከወጣቶች? ከህፃናት?… ማን ይሆን በሞራል ልዕልና እና በመንፈስ ከፍታ ቆሞ ከኢትዮጵያ ሰማይ ሥር የሚጥመለመለውን የጥላቻ አውሎ ነፋስ ገስፆ የሚያስቆመው? እስኪ “እኔ አለሁ” በሉ! (እኔ እንዳልሞክር ፓርቲ ውስጥ መሆን ይሄን ነፃነት አይሰጥም) ግን ኢትዮጵያ የሰው ድሃ አይደለችምና ፍጠኑ። ሰላም!
የሺዋስ አሠፋ
አቶ የሺዋስ አሠፋ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ሊቀ መንበር ሲሆኑ፤ ከዚያ በፊት ደግሞ የቀድሞው ሰማያዊ ፓርቲ ሊቀ መንበር ነበሩ።
ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረ–ገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forums) ላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።
October 13, 2020 at 5:14 pm #16337In reply to: የፖለቲካ ፓርቲዎች ድምጽ (ኢትዮጵያ ውስጥ የሚነቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች)
AnonymousInactiveየምንገኝበት የፖለቲካ ቀውስ፣ ፈጣን ፖለቲካዊ መፍትሔ ይፈልጋል!
ከኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ሥራ አስፈፃሚ የተሰጠ መግለጫበኢትዮጵያ ሕዝብ የረዥም ጊዜ መራራ ትግል 2010 ዓ.ም ላይ የመጣው ለውጥ ሕዝቡ ከነበረው ተስፋ በተቃራኒ የመክሸፍ አደጋ አጋጥሞታል።
ከእንግዲህ በሀገራችን እውነተኛ ዴሞክራሲ እውን እንዲሆን፣ የዜጎች ሰብዓዊና ፖለቲካዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን፥ በእርግጠኝነት ደጋግሞ ቃል በመግባት ከፍተኛ የሕዝብ ድጋፍ አግኝቶ የነበረው የዶ/ር ዐቢይ አህመድ መንግሥት ለሕዝብ የገባቸውን ቃሎች ሁሉ በማጠፍ የለየለት አምባገነናዊ መንግሥት መሆን ጀምሯል።
በዚህም ምክንያት የሀገራችንን ሰላምና መረጋጋት ክፉኛ የሚፈታተንና የሀገሪቱን አጠቃላይ ህልውና አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል ከፍተኛ የፖለቲካ ውጥረትና ቀውስ በሀገራችን ተከስቷል። በብዙ ዜጎች ከፍተኛ መስዋዕትነት የተገኘው ለውጥ መክሸፉና ሀገሪቱ ተመልሳ በሌላ አምባገነናዊ ሥርዓት ስር መውደቋ እጅግ ልብ የሚሰብር አሳዛኝ ክስተት ቢሆንም፥ የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ሀገራችንን ከውድቀት ለማዳን ዛሬም ዕድሉ በእጃችን ነው ብሎ ያምናል።
ይህ ከውድቀት የመዳን እድል እውን ሊሆን የሚችለውም በአንድ ገዥ ፓርቲ የበላይነትና ፈላጭ ቆራጭነት፣ ወይንም ባለፉት 27 ዓመታት ያየነው ዓይነት ውጤቱ አስቀድሞ የሚታወቅ የይስሙላ ምርጫ በማካሄድ አይደለም።
በኢዴፓ እምነት ከዚህ አሳሳቢ የህልውና አደጋ ወጥተን ወደ ተሻለ ሁኔታ ለመሸጋገር ቢያንስ የሚከተሉት አራት ተጨባጭ እርምጃዎች ሊወሰዱ ይገባል ብለን እናምናለን፤
- በሀገራችን የሕግ የበላይነት የመጥፋት ችግር እጅግ አሳሳቢ ወደ ሆነ የከፋ ደረጃ እየተሸጋገረ ነው። በኢዴፓ አመራር በአቶ ልደቱ አያሌው እና በሌሎችም የፖለቲካ ሰዎች ላይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሲሆን እንደታየው ሰዎች በፈጠራ ክስ ያለአግባብ የሚንገላቱበትና የፍርድ ቤቶች ውሳኔና ትዕዛዝ የማይከበርበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ያለ ፍርድ ቤት ነፃነት በአንድ ሀገር ላይ የሕግ የበላይነት ሊከበር ስለማይችል ፍርድ ቤቶችን ለፖለቲካ ጉዳይ ለመጠቀም፤ እና የፍርድ ቤቶችን ውሳኔ በመጣስ እየተፈፀመ ያለው ሕገ-ወጥ ድርጊት በአስቸኳይ መቆም አለበት።
- በአሁኑ ወቅት የኢዴፓ/አብሮነት፣ የኦፌኮ፣ የኦነግና የባልደራስ ከፍተኛ ዓመራሮች፣ እንዲሁም በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች /በተለይም በኦሮሚያ ክልል/ ከፖለቲካ ጋር በተያያዘ በእስር ላይ ስለሚገኙ በሀገራችን ከፍተኛ የፖለቲካ ውጥረት ነግሷል። ይህ አሳሳቢ ውጥረት ወደ ሌላ አሳሳቢ ደረጃ ከመሸጋገሩ በፊት ሁሉም ከፖለቲካ ጉዳይ ጋር በተያያዘ በእስር ላይ የሚገኙ ዜጎች ያለምንም ቅድመ-ሁኔታ በአስቸኳይ መፈታት አለባቸው።
- ሀገራችን በዚህ ዓይነት የፖለቲካ ውጥረት ውስጥ ሆና በፍፁም ሀገራዊ ምርጫ ለማካሄድ መታሰብ የለበትም። ከአሁን ጀምሮ እስከሚቀጥለው ሀገራዊ ምርጫ ድረስ ሀገሪቱ እንዴት ትተዳደር? ምርጫው ከመካሄዱ በፊት በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ ምን ዓይነት ውይይት እና ድርድር ይካሄድ? ከክልልነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ በደቡቡ የሀገራችን ክፍል ያለው የፖለቲካ ውጥረት እንዴት ይርገብ? ሀገሪቱ ቋሚ መንግሥት እስከሚኖራት ድረስ የኢኮኖሚ ደህንነቷን የሚያስጠብቅ ምን ዓይነት እርምጃ ሊወሰድ ይገባል? ያልለየለትን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭት በተመለከተ ምን ልናደርግ ይገባል? በሚሉትና በመሳሰሉ መሠረታዊ ጥያቄዎች ዙሪያ መፍትሄ ማመንጨት የሚያስችል አንድ ሁሉን አቀፍ የውይይትና የድርድር ሂደት /national dialogue / በአስቸኳይ መጀመር አለበት።
- በአሁኑ ወቅት በፌደራሉ መንግሥትና በትግራይ ክልል መካከል እየታየ ያለው ተገቢ ያልሆነና አሳሳቢ ፍጥጫ በአስቸኳይ መቆም አለበት። ጉዳዩ ከሀገሪቱ ሰላምና አንድነት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ እንደምታ ያለው እጅግ አሳሳቢ ጉዳይ በመሆኑ ያለምንም ቅድመ-ሁኔታ በውይይትና በድርድር መፈታት አለበት።
በአጠቃላይ እነዚህ መሠረታዊ ጥያቄዎች በአግባቡ መመለስ ሳይችሉ ከቀሩና በሀገሪቱ ላይ የሚታየው ውጥረት የበለጠ ተባብሶ በዜጎችና በሀገር ላይ ለሚደርሰው ለማንኛውም የከፋ ጉዳት ዋናው ተጠያቂ ብልፅግና ፓርቲ መሆኑን እንገልፃለን። ከማንም በላይ የጉዳዩ እና የሀገሪቱ ባለቤት ሕዝቡ ነውና ከፍ ሲል የዘረዘርናቸው ጥያቄዎች በአስቸኳይ ተገቢ ምላሽ አግኝተው ሀገራችን ከውድቀት እንድትድን ሁሉም ሀገር ወዳድ ዜጋ በብልፅግና ፓርቲ ላይ ሕጋዊ እና ሰላማዊ ተፅዕኖ እንዲያደርግ ኢዴፓ ጥሪውን ያቀርባል።
የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ
ጥቅምት 3 ቀን 2013 ዓ.ም
አዲስ አበባOctober 13, 2020 at 2:04 am #16325In reply to: ንግድና ኢንዱስትሪ ነክ ዜናዎች ― ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
AnonymousInactiveኩታ ገጠም እርሻ ― ከዕቅድ በላይ መሬት በዘር ለመሸፈን ያስቻለ ተሞክሮ
አዲስ አበባ (አዲስ ዘመን) – ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘ ወቅታዊ መረጃ እንደሚያመለክተው፥ በዘንድሮው የምርት ዘመን በተለያዩ አካባቢዎች የተተገበረው ኩታ ገጠም እርሻ በሰብል ለመሸፈን ከታቀደው በላይ መሬት መሸፈን ተችሏል፤ ኩታ ገጠም እርሻ በመጠቀም ከሚታረሰው መሬት የሚገኘው ምርትም እያደገ ነው።
በሚኒስቴሩ የሰብል ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ኢሳያስ ለማ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደሚሉት፥ በተያዘው የምርት ዘመን ኩታ ገጠም እርሻ በ300 ወረዳዎች፣ በ31 ክላስተሮች ላይ አየተካሄደ ነው። ከተገኙ ውጤታማ ተሞክሮዎችም በመነሳት ክልሎች ክላስተሮችን የጨመሩበት ሁኔታ አለ።
በምርት ዘመኑ ኩታ ገጠም እርሻ ለመጠቀም ሦስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ማረስ ታቅዶ እንደነበረ ዳይሬክተሩ ጠቅሰው፥ ክልሎች የራሳቸውን ሰብሎችና ክላስተሮች የጨመሩበት ሁኔታ በመፈጠሩ፥ አፈጻጸሙ ከዕቅዱ በላይ 3.79 ሚሊዮን ሄክታር ደርሷል። በሰብል ዓይነትም እንደ ክልሎች ተጨባጭ ሁኔታ ተጨማሪ ሰብል እና አትክልቶች ተካተዋል።
በክላስተር ደረጃ ይህን ያህል ምርት ይገኛል ተብሎ የተያዘ ዕቅድ የለም ያሉት አቶ ኢሳያስ፥ በሀገር-አቀፍ ደረጃ በመኽር እርሻ በአጠቃላይ 12.85 ሚሊየን ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን ግብ መያዙን አመልክተዋል።
በክላስተር ማረስ (ኩታ ገጠም እርሻ ለመጠቀም) የዛሬ 10 ዓመት እንደተጀመረ አቶ ኢሳያስ አስታውሰው፥ ሥራው በአግባቡ ከገበያ ጋር የተሳሰረ ባለመሆኑ ውጤታማ መሆን ሳይችል መቅረቱን ያስታውሳሉ። አሁን የተጀመረው የክላስተር አሠራር ገበያ-መር መሆኑን ጠቅሰው፥ የገበያው ሁኔታ በሁለት መልኩ እንደሚታይም አመልክተዋል።
አንደኛው የሚያመርተው የሰብል ዓይነት በአካባቢው በቂ ገበያ አለው ወይ ለሚለው ተገቢውን ምላሽ የሚሰጥ ሲሆን፤ ሌላው ደግሞ ከአካባቢው ባለፈ ምርቱ በገበያ ውስጥ ሊኖረው የሚችለውን ተፈላጊነት ታሳቢ ያደረገ ነው ሲሉ ያብራራሉ። ከዚህም ባለፈው ምግብ ዋስትናን ማረጋገጥን፣ የገቢ ምርት መተካትንና የመሳሰሉትን ሀገራዊ የመንግሥት መርሀግብሮች ታሳቢ ተደርጎ እንደሚሠራም አብራርተዋል።
ኩታ ገጠም እርሻ ምርታማነቱ እየጨመረ መምጣቱን ያስታወቁት ዳይሬክተሩ፥ የጤፍ ምርታማነት ከአራት ዓመት በፊት ከነበረበት በሄክታር 16.64 ኩንታል ወደ 18.5 ኩንታል፣ ስንዴ ከ26.7 ወደ 29.71 ኩንታል፣ በቆሎ ከ36.75 ኩንታል ወደ 42.39 ኩንታል ማደጉን አስታወቀዋል። የምርት እድገቱ በኩታ ገጠም እርሻ የመጣ መሆኑንም ተናግረዋል።
ኩታ ገጠም እርሻ ገበያ-መር በሚል ከሁለት ዓመት በፊት ከግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ጋር በመተባበር በ178 ወረዳዎች መጀመሩን አስታውሰው፥ እርሻው ሁለት ሚሊዮን ሄክታር አካባቢ በሚጠጋ መሬት ላይ መጀመሩን፤ በወቅቱም በክላስተር ደረጃ በሄክታር በአማካይ 35 ኩንታል ማግኘት መቻሉን ጠቁመዋል። ከዚያ በፊት በአማካይ ይገኝ የነበረው 27 ኩንታል እንደነበር ያስታውሳሉ።
አሁን ደግሞ የአምስት ዓመት ዕቅድ 500 ወረዳዎችን ያካተተ 31 ክላስተሮችን የያዘ የኩታ ገጠም እርሻ ለማካሄድ መታቀዱን አቶ ኢሳያስ ጠቅሰው፥ የተገኙ ውጤታማ ተሞክሮዎችን በማየት የእርሻ መሬት መጨመሩን አመልክተዋል።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ማንደፍሮ ንጉሴ በበኩላቸው፥ ኩታ ገጠም እርሻ ሲባል እንደ ስሙ የተቀራራበ እርሻ ማለት ሳይሆን ብዙ ሰው መሬቱን አንድ ላይ በተመሳሳይ ሰብል አልርቶ፣ በተመሳሳይ ግብዓት ተጠቅሞ፣ ተመሳሳይ እንክብካቤ አድርጎ የተሻለ ገቢ እና ምርት ማግኘት የሚችልበት አሠራር መሆኑን ይናገራሉ።
ኩታ ገጠም እርሻ የማምረት አቅምን ተመሳሳይ በማድረግ ምርታማነት እንዲያድግ የሚደረግበት መሆኑን ጠቅሰው፥ አርሶ አደሮች የኩታ ገጠም እርሻን ከምርታማነት መጨመርና ገበያውን በጋራ ከማግኘት አኳያ በመመልከት ጥቅሙን እየተረዱት መምጣቸውን ይናገራሉ። ይህን ተከትሎም በፍላጎታቸው መሬታቸውን በኩታ ገጠም ማልማት ውስጥ እያስገቡ መሆናቸውን ይገልጻሉ። ዶ/ር ማንደፍሮ ሁሉም ቦታ በእዚህ ደረጃ ከሠራ ግብርናው ወደ ኮሜርሻል እርሻ እየተቀየረ እንደሚሄድ እምነታቸው ነው።
ዶ/ር ማንደፍሮ የኩታ ገጠም እርሻው ሕጋዊ ማዕቀፍ እንዲኖረው ለማድረግ እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል። ለዚህም የኮንትራት እርሻ ፖሊሲ በግብርና ሚኒስቴር ደረጃ እየተዘጋጀ መሆኑን ጠቅሰው፥ ፖሊሲው አንዴ መገምገሙንና ቶሎ ጸድቆ ወደ ሥራ እንደሚገባ ይናገራሉ።
መሬትን በጋራ አድርጎ የማምረቱ እና የመከፋፈሉ ሥራ እስከአሁን በመተማመን ላይ ተመሥርቶ ሲሠራ መቆየቱን አስታውቀው፥ ሁሉም ሰው ለጥቅምም ለግዴታም ተገዢ የሚሆንበት ሕግ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል። “አንዱ ከዚያ ውስጥ ቢያፈነግጥ በሕግ ማዕቀፍ ልትከሰውና ልታሸንፈው የሚያስችል ደንብና መመሪያ መኖር አለበት” ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፥ የጋራ ተጠያቂነት መኖር እንዳለበትም ገልጸዋል።
ማሳ በዘር ከተሸፈነ በኋላ አላርስም፣ አልኮተኩትም… የሚል ቢያጋጥም ችግሩን ለመፍታት የሕግ ማዕቀፍ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፥ በዚህ ፖሊሲ ላይ በቀጣይም ውይይት ይካሄድበታል ይላሉ። በዘርፉ ባለሙያ ብቻ ሳይሆን የሕግ ሰዎችና ሌሎች ተዋንያንም እንደሚሳተፉበትም አመልክተዋል።
ግብርናውን በማዘመን በኩል በመንግሥት ዋስትና ለአርሶ አደሮች ትራክተሮች የሚቀርቡበት ሁኔታ እንዳለ ሚኒስትር ዴኤታ ጠቅሰው፥ ይህም ራሱን የቻለ የሕግ ማዕቀፍ እንደሚያስፈልገው ነው ያስገነዘቡት። ለትራክተር የወጣው ወጪ ሳይከፈል ከቀረ መንግሥት ‘እኔ እከፍላለሁ’ እያለ ለአርሶ አደሩ ትራክተር እያቀረበ መሆኑን አስታውቀው፥ ይህ ሥራ ተግዳሮት እንዳይገጥመው ለማድረግ አሁን የሕግ ማዕቀፍ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
“አርሶ አደሮች በጋራ ሆነው አንድ ትራክተር መግዛት እንዲችሉ፤ አንድም ሰው አቅሙ ካለው መግዛት እንዲችል የሕግ ማዕቀፍ ይፈልጋል” ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፥ “እነዚህን በደንብና በመመሪያ ካጠናከርናቸው ዘላቂነት ያለው ለውጥ ሊታይ ይችላል” ሲሉ ያስገነዝባሉ።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት
October 11, 2020 at 11:10 pm #16310In reply to: ነፃ አስተያየት (ስለኢትዮጵያ በኢትዮጵያውያን)
AnonymousInactiveበማንኛውም ዜጋ ላይ የሚፈፀም ኢፍትሃዊነት በሁላችንም ላይ እንደተፈፀመ ይቆጠራል
አንዱዓለም አራጌከዚህ ቀደም በጣም በአመዛኙ የፓርቲዬን አቋም ካልሆነ በስተቀር እምብዛም የግል አቋሜን አንፀባርቄ አላውቅም።
ብዙውን ጊዜ ተቋሞቻችን ሕጸጻቸውን እያረሙ ሁላችንም የምንደገፍባቸው ተቋማት እንዲሆኑ እድልም ሆነ ጊዜ መስጠት ተገቢ መሆኑን አምናለሁ። ይሁን እንጂ፥ ትናንት የኢትዮጵያ ሕዝብ በነፍስና በስጋው ተወራርዶ መራር ሕዝባዊ ትግል ያደረገው ዝቅ ብለን የምንመለከተውን ዓይነት ግፍ ለማስተናገድ አለመሆኑ እሙን ነው።
በ1993 ዓ.ም በጊዮርጊስ የጊዜ ቀጠሮ ፍርድ ቤት በተለያዩ ሁለት ችሎቶች፣ በተመሳሳይ ዕለት፣ በተመሳሳይ ሰዓት የተፈፀሙ ሁለት ውሳኔወችን ለማስታወስ እወዳለሁ። አንደኛው ችሎት በሀቪየስ ኮርፐስ (habeas corpus) ክስ አማካኝነት፣ እነአቶ ታምራት ታረቀኝን ካሰረበት አምጥቶ ለፍርድ ቤቱ ያቀርብ ዘንድ ፓሊስን ፍርድ ቤት በተደጋጋሚ ቢያዝም፥ ትዕዛዙ ባለመፈፀሙ በወቅቱ የፍትህ ሚንስትር የነበሩት አቶ ወረደወልድ ወልዴ ታስረው እንዲቀርቡ ባዘዘው መሠረት ታስረው ቀረቡ። ፍርድ ቤቱም የአንድ ወር እሥራት ፈረደባቸው። በሌላ ደግሞ የዳኛ ብርቱካን ሚደቅሳ ችሎት አቶ ስዬ አብርሃ ቀርበው የወ/ት ብርቱካን ችሎት አርነት ሰደዳቸው። ይሁን እንጂ ለቤታቸው ሊበቁ የተገባቸው አቶ ስዬ አብርሃ በአፈሙዝ አስገዳጅነት ወህኒ እንዲወርዱ ተገደዱ። ሚኒስትር ወረደወልድ ወልዴ ደግሞ ሳይገባቸው ለሞቀ ቤታቸው በቁ።
ይህን የሃያ ዓመት ታሪክ ያለምክንያት አላነሳሁትም። ከእልህ አስጨራሽ ሕዝባዊ ትግል በኋላ የለውጥ ሽራፊ ለማየት ብንጓጓም ከሃያ ዓመት በኋላ ተመሳሳይ ለከት ያጣ ግፍ እያስተናገድን ነው። በ”ለውጡ” የመጀመሪያ ወራት ሕዝቡ የተራበ አንጀቱን አስሮ ይስቅ የነበረው፣ ድጋፉንም የቸረው ከእንግዲህ በፍትህ፣ በእውነትና በእኩልነት የምጠግብበት ዘመን ጠባ ብሎ በማመኑ ይመስለኛል። ከፈጣሪ በታች ተስፋችን በእጃችን መሆኑ የቀትር ያህል ግልፅ ቢሆንም፣ ከሃያ ዓመት በኋላ ተመሳሳይ የፍትህን መጨንገፍን ሳይ ጥልቅ ሀዘን አልተሰማኝም ብል ግን እውነቱን አልናገርም።
በቅርቡ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ሥራ አስፈፃሚ አባል ወ/ሮ ሂሩት ክፍሌ ፍርድ ቤት የዋስትና መብቷን ቢያከብርላትም፥ ፓሊስ ላለመልቀቅ ያሳየውን ዳተኝነት እናስታውሳለን። በተመሳሳይ የአሥራት ቴሌብዥን ጋዜጠኞችንም እንዲሁ በመከራ መልቀቁ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው።
ዛሬ ብዕሬን እንዳነሳ ያደረገኝ ጉዳይ የአቶ ልደቱ አያሌው ጉዳይ ነው። ስለአቶ ልደቱ ከእኔ በላይ ብዙ ነገሮችን አጣቅሶ ማቅረብ የሚችል ሌላ ማን እንዳለ በእውነት አላውቅም። በፓርቲዬም ላይ ቢሆን በተደጋጋሚ ምን ያደርጉ እንደነበር ፈፅሞ ዘንግቼው አይደለም። አቋማቸው ከአቋሜ ስለገጠመም አይደለም። ይልቅስ አቶ ልደቱ እራሳቸውን መከላከል በማይችሉበት በዚህ ሁኔታ አንዳች አሉታዊ ጉዳይ አንስቼ እሞግታቸው ዘንድ ፈፅሞ ህሊናዬ አይፈቅድልኝም።
በተወሰነ መልኩ የቀደመውን ለአንባቢ ያስታወስኩትም ቢሆን፥ የቆምኩበትን የሀሳብ ማዕዘን ለማሳየት ይረዳኝ ዘንድ ግድ ሆኖብኝ እንጂ ምቾት ተሰምቶኝ አይደለም። ይልቅስ ከላይ ከፍ ብዬ ከጠቀስኳቸው ወገኖቻችንም በከፋ ሁኔታ የ“ፓሊስ ጢባጢቤ” መጫወቻ ሆነው ሳይ፥ እርሳቸውን የወጋ ጦር እኔንም እንደወጋኝ ተሰምቶኛል። በተለያየ ደረጃ የሚገኙ የኦሮሚያ ክልል ፍርድ ቤቶች የዋስትና መብታቸው ተከብሮ ከእስር እንዲለቀቁ ቢያዙም በፓሊስ እንቢተኝነት ግን በእስር ላይ ይገኛሉ። ውርደቱ፣ መረገጡ፣ ንቀቱና ኢፍትሃዊነቱ፣ የኢፍትሃዊነትን ስቃይ ለምናውቅ ዜጎች ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያውያን ሁሉ ነው። በማንኛውም ዜጋ ላይ የሚፈፀም ኢፍትሃዊነት በሁላችንም ላይ እንደተፈፀመ የሚጠራጠር ካለ እርሱ ፍፁም ማስተዋል የጎደለው ነው።
በኢትዮጵያችን እየታየ ያለው ለከት ያጣ ግፍ ቅስም የሚሰብርና በምንም ዓይነት መንገድ ልንታገሰው የማይገባ ኢፍትሃዊ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን ያዋረደ ወደር-አልባ የነውረኝነት ተግባርም ነው።
በፈጣሪ እንደምትታመኑ ደጋግማችሁ የነገራችሁን ወገኖች፥ በሚፈፀመው ግፍ ፈጣሪ የሚደሰትበት ይመስላችኋል? የሚሠራውን ኢፍትሃዊነት በአስቸኳይ እስካላስቆማችሁ የፈጣሪም ሆነ የሕዝብም ቁጣ እሩቅ እንደማይሆን ለመናገር ነቢይነትን አይጠይቅም።
Free Lidetu Ayalew
አንዱዓለም አራጌአቶ አንዱዓለም አራጌ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ምክትል መሪ ሲሆኑ፤ ከዚያ በፊት ደግሞ የቀድሞው የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት እና ፕሬስ ሴክሬተሪ ነበሩ።
ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረ–ገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forums) ላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።
October 10, 2020 at 12:26 am #16289In reply to: የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በኢትዮጵያ ― ዜናዎችና ጠቃሚ መረጃዎች
SemonegnaKeymasterበኢትዮጵያ ስምንት ዩኒቨርሲቲዎች የምርምር ልህቀት ማዕከል ተብለው ተለዩ
ጎንደር (ኢዜአ) – በኢትዮጵያ ስምንት የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የምርምር ልህቀት ማዕከል (Center of Excellence) በመባል መለየታቸውን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በተመረጡ ትምህርት ቤቶች በትምህርት ጥራት ዙሪያ ያካሄደውን የምርምር ግኝቶች ላይ መስከረም 29 ቀን 2013 ዓም ከባለድርሻዎች ጋር ተወያይቷል።
የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከፍተኛ አማካሪ ዶ/ር ወርቁ ነጋሽ በወቅቱ እንደገለጹት፥ በሀገሪቱ የሚገኙ 46 ዩኒቨርሲቲዎች በምርምር፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም በአጠቃላይ ትምህርት በሚል በሦስት ደረጃዎች ተለይተዋል።
ባለፉት ዓመታት በርካታ ችግር ፈቺ የምርምር ውጤቶችን ሲያበረክቱ የቆዩና ወደፊትም አስተዋጽዖ ይኖራቸዋል የተባሉ ስምንት ዩኒቨርሲቲዎች በምርምር ዘርፍ የልህቀት ማዕከል እንዲሆኑ መለየታቸውን ተናግረዋል።
“ጎንደር፣ አዲስ አበባ፣ ባህር ዳር፣ መቀሌ፣ ጅማ፣ ሀዋሳ፣ አርባ ምንጭ እና ሐረማያ ዩኒቨርሲቲዎች የምርምር ልህቀት ማዕከል እንዲሆኑ ተለይተዋል” ብለዋል ዶ/ር ወርቁ።
ለአንድ ሀገር ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ችግር ፈቺ ምርምር ቁልፍ ሚና እንዳለው የገለጹት ዶ/ር ወርቁ፥ “ያደጉ ሀገሮች የእድገት ምስጢርም ከዚህ የመነጨ ነው” ብለዋል። የምርምር (Research) ዩኒቨርሲቲዎቹ በዓለምአቀፍ ደረጃ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር አቻ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ አቅማቸውን ለመገንባት በትኩረት እንደሚሠራ አመላክተዋል።
ሌሎች 15 የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ደግሞ በሳይንስና ቴክኖሎጂ (Science and Technology) ዘርፍ ትምህርትና ስልጠና እንዲሰጡ መለየታቸውን ተናግረዋል። ዩኒቨርሲቲዎቹ በቂ እውቀትና ክህሎት ያዳበረ ዜጋ ማፍራት እንዲችሉ ተከታታይ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው አመላክተዋል።
ቀሪዎቹ 23 ዩኒቨርሲቲዎች ደግሞ አጠቃላይ ትምህርትና ስልጠና እንዲሰጡ የተለዩ መሆኑን ዶ/ር ወርቁ አስታውቀዋል።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር መርሻ ጫኔ ዩኒቨርሲቲው በርካታ ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምር በማካሄድ ለማህበረሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረጉን ተናግረዋል።
ላለፉት ሶስት አመታት ጎንደር ከተማን ጨምሮ በሰሜን፣ በማእከላዊና በምዕራብ ጎንደር ዞኖች በተመረጡ 1,343 የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ በትምህርት ጥራት ዙሪያ ጥናትና ምርምር መካሄዱን ገልጸዋል። በምርምር ውጤቶቹ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይትና ምክክር እየተካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል።
“በዩኒቨርሲቲው የሥነ-ትምህርት ኮሌጅ መምህራን የተዘጋጀው የምርምር ውጤት ለፖሊሲ አውጪዎች ጠቃሚ ግብዓት ሆኖ የሚያገለግል ነው” ያሉት ደግሞ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር አሥራት አጸደወይን ናቸው።
ባለፈው ዓመት ዩኒቨርሲቲው ከ200 በላይ የምርምር ሥራዎችን ማካሄዱን ዶ/ር አሥራት አስታውሰዋል፤ ዘንድሮም በተለያዩ ዘርፎች ምርምር ለማካሄድ የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት እያካሄደ እንደሚገኝ ፕሬዝዳንቱ ማሳወቃቸውን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ዘግቧል።
ለአንድ ቀን በተካሄደው ውይይት የዩኒቨርሲቲው መምህራንና የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም ከጎንደር ከተማ አስተዳደር የተውጣጡ መምህራንና የትምህርት አመራሮች ተሳትፈዋል።
ምንጭ፦ ኢዜአ
October 9, 2020 at 11:47 am #16280AnonymousInactiveበተባበረ ሀገራዊ አቅም የእንቦጭ አረምን ከጣና ሐይቅ ላይ ለማስወገድ የሚስችል ዘመቻ ሊጀመር ነው
የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴርአዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – በተባበረ ሀገራዊ አቅም የእንቦጭ አረምን ከጣና ሐይቅ ላይ ለማስወገድ የሚስችል ዘመቻ ሊጀመር ነው፤ ዘመቻውን አስመልክቶ የኢፌዲሪ የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር መስከረም 29 ቀን 2013 ዓ.ም ውይይት አካሂዷል። በውይይት መድረኩም ላይ የአማራ ክልላዊ መንግሥት አመራሮችን ጨምሮ የዩንቨርሲቲ ምሁራንና ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።
በዘመቻው እንቦጭን ከጣና ሐይቅ ላይ ለማስወገድ ሁሉንም ክልሎች፣ የከተማ አስተዳደሮች እና የፌደራል እና የክልል ተቋማት እንዲሁም መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ለማስቻል የተዘጋጀ ዕቅድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
በውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተፋሰስ ልማት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር አዳነች ያሬድ የሚደረገውን ዘመቻ ዕቅድ ባቀረቡበት ወቅት፥ እንደገለጹት እንቦጭ በጣና ሐይቅና በአባይ ተፋሰስ የውሃ አካላት ላይ እጅግ በሰፊው ተንሠራፍቶ እንደሚገኝ አሳውቀው፤ እንቦጭ የተንሠራፋበትን ይህንን የውሃ አካል ለማጽዳት ሁሉም ክልሎች፣ የከተማ አስተዳደሮች እና የፌደራል እና የክልል ተቋማት እንዲሁም መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት እንቦጭ የተንሠራፋበትን የሐይቁን አካል በመከፋፈል በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ የሚስወግዱት ይሆናል። አረሙን ከውሃው ላይ ማስወገድ፣ መንቀል፣ በአንድ ቦታ ማከማቸትና ማቃጠል ወይንም መቅበር በዘመቻው የሚሠራበት መፍትሄ ነው።
የውሃ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢነጂነር ስለሺ በቀለ ለአንድ ወር በሚካሄደው በዚህ ዘመቻ ላይ ሁሉም ክልሎች፣ የከተማ አስተዳደሮች፣ ተቋማትና ሁሉም ኢትዮጵያውያን በዘመቻው በንቃት እነዲሳተፍበት ጥሪ አቅርበዋል።
በተለይ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው ተቋማት ለዘመቻው ስኬታማነት ከተለመደው አሠራር ባሻገር ማቀድና ስራውን መፈጸም ይጠበቅብናል ብለዋል። ከክልል እስከ ቀበሌ ያለውን መዋቅርም በከፍተኛ ንቅናቄ መምራት ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።
በዚሁ መድረክ ላይ የተገኙት የአማራ ክልላዊ መንግሥት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ፋንታሁን ማንደፍሮ ይህ እቅድ በአግባቡ የምንተገብረው ከሆነ እንቦጭ የሚስከትለውን ጉዳት መቀነስ እንችላለን በማለት ሀሳባቸውን ገልጸዋል። በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለሚካሄደው ለዚህ ዘመቻ 92 ሚሊዮን ብር የሚያስፈልግ እንደሆነም ተመላክቷል። ለዘመቻውም እስከ 10 ሺህ የሚጠጉ ሰዎችን ለማሳተፍ ታቅዷል።
የእንቦጭ አረም በተፋሰሱ በሚገኙ 30 ቀበሌዎች በሚያዋስኑት የሐይቁ አካል ላይ ተንሠራፍቶ ይገኛል።
ምንጭ፦ የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
October 8, 2020 at 1:32 am #16251In reply to: የፖለቲካ ፓርቲዎች ድምጽ (ኢትዮጵያ ውስጥ የሚነቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች)
AnonymousInactiveሰላማችንን በማስጠበቅ እና ቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ ላይ በንቃት በመሳተፍ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠረት እንጣል!
ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የተሰጠ መግለጫስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ሊካሄድ የግዜ ሰሌዳ ወጥቶለት ሁሉም ባለድርሻ አካላት እንቅስቃሴ ከጀመሩ በኋላ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመታወጁ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያወጣውን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ እንዲሰርዝ መገደዱ ይታወሳል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በታወጀበት እና የምርጫ ሰሌዳው በተሰረዘበት ወቅት ወረርሽኙ በሌሎች የዓለማችን ሀገራት የጤና ሥርዓት ላይ ያስከተለውን ከፍተኛ ጫና እና በሰው ሕይወት ላይ ሲያደርስ የነበረውን ጉዳት በተጨባጭ በማየት የተለያዩ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ገደብ መደረጉ እና በዚህ ምክንያት ምርጫው መራዘሙ ተገቢ ነበር ብለን አምነናል።
ምርጫው አለመካሄዱን ተከትሎ የመንግሥት ቀጣይነትን ለማረጋገጥ በተለያዩ ወገኖች የተለያዩ አማራጮች መቅረባቸው የሚታወስ ነው። የተለያዩ ፖለቲካ ፖርቲዎችም ከሕገ-መንግሥት ውጪ ያሉ አማራጮችን አቅርበው ነበር። ኢዜማ የመንግሥት ቀጣይነትን በሕጋዊ ማዕቀፍ ውስጥ መፍታት እንደሚቻል ጠቅሶ፥ አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ-መንግሥት ከሚሰጣቸው የመፍትሄ አማራጮች ውስጥ ደግሞ የመንግሥትን የሥልጣን ጊዜ እና ምርጫ የሚደረግበትን ጊዜ የሚደነግገውን የሕገ-መንግሥት አንቀጽ ከአቅም በላይ እና በድንገተኛ ምክንያት ምርጫ ማድረግ የማይቻልበት ሁኔታ ሲፈጠር የመንግሥትን ሥልጣን ከአንድ ዓመት ላልበለጠ ጊዜ ማራዘም እንዲያስችል አድርጎ ማሻሻል የተሻለ አማራጭ እንደሆነ ማቅረቡ ይታወሳል። ማሻሻያው ሥልጣን ላይ የሚቆየው መንግሥት የሥልጣን ጊዜ ገደብ ያስቀመጠ እና ውሳኔ የሚሰጥባቸው ጉዳዮች በቀጣይ ምርጫ አሸንፎ ሥልጣን የሚይዘው መንግሥት ላይ ግዴታ የማይጥሉ መሆናቸውን ባረጋገጠ መልኩ መሆን እንዳለበትም ምክረ-ሀሳብ አቅርበን ነበር።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ክፍተቱን በሕገ-መንግሥት ትርጉም ለመሙላት ወስኖ የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ባቀረበው የውሳኔ ሀሳብ እና በፌደሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ምርጫውን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስጋት አለመሆኑ በጤና ሚኒስቴር እና የኅብረተሰብ ጤና ተቋም እስኪረጋገጥ ድረስ አራዝሞ የፌደራል እና የክልል መንግሥታት እና ምክር ቤቶችን የሥራ ጊዜ ያለገደብ እንዲቀጥል መወሰኑ ይታወሳል።
ይህን ውሳኔ ተከትሎ ኢዜማ የጊዜ እና ውሳኔ የሚያሳልፍባቸው ጉዳዮች ላይ ወሰን ሳይደረግ ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት የሥራ ዘመን መራዘሙ ላይ ያለውን ተቃውሞ ገልፆ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለሕገ-መንግሥት አጣሪ ጉባዔ በገለጸው መሠረት አስፈላጊው ጥንቃቄ ተደርጎ ምርጫው መደረግ በሚችልበት ቅርብ ጊዜ እንዲደረግ ጠይቋል።
በቅርቡ የጤና ሚኒስትር አስፈላጊው ጥንቃቄ እየተደረገ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ እንደሚቻል ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባሳወቀው መሠረት ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ በያዝነው ዓመት እንዲካሄድ ውሳኔ ተላልፏል።
ይህ በእንዲህ እያለ፥ “ሥልጣን ለማራዘም የተሄደበት መንገድ ሕገ-መንግሥታዊ አይደለም፤ በዚህም ምክንያት ከመስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም በኋላ መንግሥት የለም፤ ሕዝብ እና የመንግሥት መዋቅር ለፌደራል እና የክልል መንግሥታት ሊታዘዙ አይገባም» በሚል ቅስቀሳ ሲደረግ መቆየቱን እና አሁንም እየተደረገ እንደሚገኝ ለማስተዋል ችለናል።
ይህ ቅስቀሳ የሀገራችንን ሰላም እና መረጋጋት ከማወክ እና የዜጎችን ሕይወት አደጋ ላይ ከመጣል በዘለለ ፋይዳ እንደሌለው የኢትዮጵያ ሕዝብ በደንብ እንደሚገነዘብ እናውቃለን። ይህንን ቅስቀሳ እያደረጉ ያሉ አካላትም ከዚህ ተግባራቸው ተቆጥበው የጋራ ሀገራችን ሰላም እና የዜጎች ደህንነት ተጠብቆ በሰላማዊ መንገድ ችግሮቻችንን መፍታት ወደምንችልበት የውይይት መድረክ ከመምጣት ውጪ በሁከት እና በጉልበት ወደሥልጣን ለመውጣት የሚደረግ ማንኛውም እንቅስቃሴ ለራሳቸውም ቢሆን የማይጠቅም አደገኛ መንገድ መሆኑን ሊረዱ ይገባል። መንግሥትም እነዚህን ቅስቀሳዎች በንቃት እየተከታተለ አደጋ ከመድረሱ በፊት የመከላከል እና አደጋ ለማድረስ የሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ ሕጋዊ እርምጃ በመውሰድ የሀገር ሰላምን እና የዜጎችን ደህንነት የማስከበር ኃላፊነቱን እንዲወጣ እናሳስባለን።
ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ዘንድሮ እንዲካሄድ የተወሰነውን ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ነፃ እና ፍትሃዊ ማድረግን ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባው እና ምርጫው እስከሚካሄድ እና የሕዝብ ድምፅ ያገኘው ተለይቶ እስከሚታወቅ ድረስ የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ፣ የሀገር ሉዓላዊነትን ማስከበር እና ምርጫውን ነፃ እና ፍትሃዊ ከማድረግ ጋር በቀጥታ ግንኙነት የሌላቸውን በተለይም በምርጫው የሚወዳደሩ ፓርቲዎች የተለያየ ፖሊሲ አቅርበው የሕዝብን ቅቡልነት ለማግኘት በሚወዳደሩባቸው ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ከማሳለፍ እና ከመተግበር እንዲቆጠብ እናሳስባለን።
እኛንም ጨምሮ በሀገራችን የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሙሉ በነፃነት ተንቀሳቅሰው ሃሳባቸውን መግለፅ እንዲችሉ ከዚህ ቀደም በተስማማንበት የፖለቲካ ፓርቲዎች የቃል ኪዳን ሰነድ መሠረት የምናደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ሰላማዊ፣ ሕጋዊ እና የሌሎችን መብት ያከበረ መሆኑን እያረጋገጥን ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ነፃ እና ፍትሃዊ እንዲሆን የሚጠበቅብንን ሁሉ እንድናደርግ እንጠይቃለን። በሀገራችን የምትንቀሳቀሱ የሲቪክ ተቋማትም የፖለቲካ ፓርቲዎች የተስማሙበትን የቃልኪዳን ሰነድ እንዲያከብሩ ግፊት እንድታደርጉ እና በጋራ ሊሠሯቸው እና ሊስማሙባቸው በሚገቡ ተጨማሪ ጉዳዮች ላይ ውይይት ማድረግ የሚችሉበት መድረክ እንድታዘጋጁ የአደራ ጥሪያችንን እያስተላለፍን፥ በመድረኮቹ ላይ በንቃት ለመሳተፍ ያለንን ፍላጎት ከወዲሁ ለመግለጽ እንወዳለን።
መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ በሀገራችን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ለምንገነባው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መደላድል የምንጥልበት ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑን በመገንዘብ የምርጫውን ሂደት ከአሁን ጀምሮ በንቃት እንዲከታተል እና ምርጫው ሰላማዊ፣ ነፃ እና ፍትሃዊ መሆኑን ለማረጋገጥ የሚጠበቅባችሁን ሁሉ እንድታደርጉ የአደራ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)
መስከረም 26 ቀን 2013 ዓ.ምOctober 5, 2020 at 3:04 am #16206In reply to: ነፃ አስተያየት (ስለኢትዮጵያ በኢትዮጵያውያን)
AnonymousInactiveህወሓት እና ISIS
ታደሰ ብሩ ኬርሰሞ (ዶ/ር)
ህወሓት እና ISIS
ታደሰ ብሩ ኬርሰሞ (ዶ/ር)Islamic State of Iraq and Syria (ISIS) እስካሁን ከፍተኛው ደረጃ የደረሰ (አራተኛ ትውልድ/ 4th generation) የሽብር ድርጅት ነው። ISIS ቀድሞ ከነበሩት የሽብር ድርጅቶች በተለየ መንገድ ከሌሎች የሽብር ድርጅቶች ጋር አይጣላም፤ ይልቁንም ሌሎችን እያቀፈ፣ እያስተባበረ ራሱን ያባዛል። እስከ 14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ወደኋላ ተመልሶ የኦቶማን ኢምፓየርን (Ottoman Empire)፤ ጥንታዊቷና ገናናዋን ሌቫንት (Levant/ የዛሬዎቹን ኢራቅ፣ ሶሪያ፣ ዮርዳኖስ፣ ሊባኖስ፣ እስራኤል) በማስታወስ የመካለኛው ምስራቅ፣ ሰሜንና ሰሜን ምስራቅ አፍሪቃ አገራት ሕዝቦች “በምዕራባዊያን ተበደልን፤ ተገፋን” ቁጭት ውስጥ እንዲገቡና ‘የጥንቱን ገናናነት ለማስመለስ’ ከጎኑ እንዲሰለፉ ያደርጋል። ISIS ብሶትንና ቁጭትን በመጠቀም ቁጥሩ ቀላል ያልሆነ የሕዝብ ድጋፍ የነበረው፤ በርካታ ወጣቶችንና ምሁራንን ያሰባሰበ ድርጅት ነበር፤ አሁንም ነው። ISIS አስደንጋጭና ዘግናኝ ርምጃዎችን በመውሰድ በሽብር ራሱን አግንኗል፤ ጭካኔ እንደ ፕሮፓጋንዳ መሳሪያ ጭምር ተጠቅሟል።
ISIS በያዛቸው ቦታዎች የሕዝብ አስተዳደር ሥራዎችን ያከናውናል፤ ‘ልማትን’ ያፋጥናል፤ ግብር ይሰበስባል፤ ከመንግሥታትና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር ይዋዋላል፤ ይነግዳል… በዚህም ምክንያት ሽብርተኛ ከፊል መንግሥት (Terrorist Semi-State/ TSS) የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል። በብዙ ሀገራት ትብብርና ርብርብ አቅሙ እንዲዳከም ባይደረግ ኖሮ ISIS በ2015 (እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር) በዓለም ላይ ጥሎ የነበረው ስጋት እጅግ ከፍተኛ ነበር። የዛሬ 5 ዓመት ከነበረው ቀነስ ይበል እንጂ ዛሬም ስጋቱ ሙሉ በሙሉ አልጠፋም።
በእኔ ግምት ህወሓት የአፍሪቃ ቀንድ ISIS የመሆን ዕድሉ ከፍተኛ ነው። የጥንታዊ የአክሱም ስልጣኔን ትርክት እየመገበ የትግራይ ወጣቶችን በቁጭትና ብሶት እያነሳሳ ነው። ለወደፊቱ ትልቅ ግዛትን (ኤርትራን፣ ከፊል አማራንና ከፊል አፋርን) እያመላከተ ለጊዜው በያዘው አነስተኛ ግዛት ውስጥ እንደ መንግሥት ከሌሎች መንግሥታትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር ይዋዋላል፤ ‘ልማትን’ ያፋጥናል፤ ይደራደራል፥ ይነግዳል። ሌሎች አባሪ ድርጅቶችን በመላው ኢትዮጵያ እየፈለገ ያደራጃል፤ ያስተባብራል፣ ያሰለጥናል። ይህን በማድረጉም “ጥቂት” እየተባለ መናናቅ የማይገባው የሕዝብ ድጋፍ ያለው ድርጅት ነው። ልክ እንደ ISIS ሁሉ ህወሓትና አባሪዎቹ አስደንጋጭና ዘግናኝ ርምጃዎችን እየወሰዱ እያሸበሩን ነው። ህወሓትና አባሪዎቹ ሽብርን እንደ አዋጪ ታክቲክ እየተጠቀሙ ነው። በእኔ ግምት ህወሓት የአፍሪቃ ቀንድ ISIS የመሆን መንገዱን ጀምሮታል።
ISIS በዓለም ላይ የጋረጠውን አደጋ ለመቋቋም የተደራጀ ርብርብ እንደተደረገ ሁሉ በህወሓት ምክንያት አደጋ ውስጥ ሊገቡ የሚችሉ ሁሉ መተባበር ይኖርባቸዋል። ህወሓት የሚፈጥረው አደጋ ከኢትዮጵያ አልፎ ለአካባቢው አገሮች ሊተርፍ የሚችል መሆኑ የቀጠናው መንግሥታት እንዲረዱ መደረግ ይኖርበታል።
ህወሓትን ማዳከም ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ የሀገርና የሕዝብ ደህንነት ጉዳይ ነው የሚል ብርቱ እምነት አለኝ። ‘ህወሓትን ማዳከም’ ምን ማለት እንደሆነም ሊብራራ ይገባል። እኔ የህወሓት በማናቸውንም ደረጃ ካለ የመንግሥት ስልጣን መውጣት የመዳከው ማሳያ መሆን ይኖርበታል ብዬ አምናለሁ። ህወሓት የክልል ይቅርና የዞን ስልጣን እንኳን ይዞ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላማዊ ምርጫ ይደረጋል የሚል ግምት የለኝም። ህወሓት የክልል ስልጣን ይዞ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም ይኖራል ማመን ሞኝነት ነው።
ስለሆነም የፌደራል መንግሥቱ ቀዳሚ ተግባር መሆን ያለበት ህወሓትን ማዳከም ነው። ከትግራይ ጋር የሚዋሰኑ የክልል መንግሥታትና የፌደራል መንግሥት ተናበውና ተቀናጅተው መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል። ይህን በአፋጣኝ፣ በተጠናና በተደራጀ መንገድ መፈፀም ይኖርበታል፤ ለውጥ ፈላጊ ትግራዋይ ወገኖቻችን በዚህ ትግል ውስጥ ግንባር ቀደም ሚና መጫወት ይኖርባቸዋል።
ታደሰ ብሩ ኬርሰሞ (ዶ/ር)
ዶ/ር ታደሰ ብሩ ኬርሰሞ ነዋሪነቱ ለንደን፥ ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ሲሆን፤ እዚያው ለንደን በሚገኘው ግሪንዊች የሥራ አመራ ተቋም (Greenwich School of Management) ውስጥ በመምህርነት ይሠራል።
ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረ–ገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forums) ላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።
-
AuthorSearch Results
Search Results for 'ኢትዮጵያ'
-
Search Results
-
በተባበረ ሀገራዊ አቅም የእንቦጭ አረምን ከጣና ሐይቅ ላይ ለማስወገድ የሚስችል ዘመቻ ሊጀመር ነው
የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴርአዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – በተባበረ ሀገራዊ አቅም የእንቦጭ አረምን ከጣና ሐይቅ ላይ ለማስወገድ የሚስችል ዘመቻ ሊጀመር ነው፤ ዘመቻውን አስመልክቶ የኢፌዲሪ የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር መስከረም 29 ቀን 2013 ዓ.ም ውይይት አካሂዷል። በውይይት መድረኩም ላይ የአማራ ክልላዊ መንግሥት አመራሮችን ጨምሮ የዩንቨርሲቲ ምሁራንና ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።
በዘመቻው እንቦጭን ከጣና ሐይቅ ላይ ለማስወገድ ሁሉንም ክልሎች፣ የከተማ አስተዳደሮች እና የፌደራል እና የክልል ተቋማት እንዲሁም መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ለማስቻል የተዘጋጀ ዕቅድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
በውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተፋሰስ ልማት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር አዳነች ያሬድ የሚደረገውን ዘመቻ ዕቅድ ባቀረቡበት ወቅት፥ እንደገለጹት እንቦጭ በጣና ሐይቅና በአባይ ተፋሰስ የውሃ አካላት ላይ እጅግ በሰፊው ተንሠራፍቶ እንደሚገኝ አሳውቀው፤ እንቦጭ የተንሠራፋበትን ይህንን የውሃ አካል ለማጽዳት ሁሉም ክልሎች፣ የከተማ አስተዳደሮች እና የፌደራል እና የክልል ተቋማት እንዲሁም መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት እንቦጭ የተንሠራፋበትን የሐይቁን አካል በመከፋፈል በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ የሚስወግዱት ይሆናል። አረሙን ከውሃው ላይ ማስወገድ፣ መንቀል፣ በአንድ ቦታ ማከማቸትና ማቃጠል ወይንም መቅበር በዘመቻው የሚሠራበት መፍትሄ ነው።
የውሃ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢነጂነር ስለሺ በቀለ ለአንድ ወር በሚካሄደው በዚህ ዘመቻ ላይ ሁሉም ክልሎች፣ የከተማ አስተዳደሮች፣ ተቋማትና ሁሉም ኢትዮጵያውያን በዘመቻው በንቃት እነዲሳተፍበት ጥሪ አቅርበዋል።
በተለይ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው ተቋማት ለዘመቻው ስኬታማነት ከተለመደው አሠራር ባሻገር ማቀድና ስራውን መፈጸም ይጠበቅብናል ብለዋል። ከክልል እስከ ቀበሌ ያለውን መዋቅርም በከፍተኛ ንቅናቄ መምራት ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።
በዚሁ መድረክ ላይ የተገኙት የአማራ ክልላዊ መንግሥት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ፋንታሁን ማንደፍሮ ይህ እቅድ በአግባቡ የምንተገብረው ከሆነ እንቦጭ የሚስከትለውን ጉዳት መቀነስ እንችላለን በማለት ሀሳባቸውን ገልጸዋል። በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለሚካሄደው ለዚህ ዘመቻ 92 ሚሊዮን ብር የሚያስፈልግ እንደሆነም ተመላክቷል። ለዘመቻውም እስከ 10 ሺህ የሚጠጉ ሰዎችን ለማሳተፍ ታቅዷል።
የእንቦጭ አረም በተፋሰሱ በሚገኙ 30 ቀበሌዎች በሚያዋስኑት የሐይቁ አካል ላይ ተንሠራፍቶ ይገኛል።
ምንጭ፦ የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ