-
Search Results
-
ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ መቀመጫውን አሜሪካን ሀገር፣ ሚኖሶታ ግዛት ካደረገው ቡክስ ፎር አፍሪካ (Books for Africa) ከተሰኘው ግብረ-ሰናይ ድርጅት ጋር ባደረገው ግንኙነት፥ በዕርዳታ ያስመጣቸውን የሳይንስ፣ የሂሳብ፣ የቋንቋ እና ስነ-ፅሁፍ መጽሐፎችን በይልማና ዴንሳ ወረዳ ለሚገኙ ትምህርት ቤቶች አከፋፍሏል።
የዚህ ድጋፍ ተጠቃሚ የሆኑት አዴት ከተማ የሚገኙ ትምህርት ቤቶችና ብርአዳማ ከተማ አካባቢ ደግሞ በሰከላል ጃንባራ መድኃኔዓለም ቀበሌ የሚገኘው ገብረን አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ በስማርጋ ቀበሌ የሚገኘው ቼመን አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤትና በአይቫር ቀበሌ የሚገኘው መጣቅር አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሲሆኑ እርዳታው ለሌሎችንም የመንግስት ትምህርት ቤቶች ያካተተ እንደነበር ታውቋል። መጽሐፎቹ ለመምህራን እና ለተማሪዎች ማጣቀሻነት የሚሆኑ ከ1ኛ እስከ 4ኛ ክፍል እና ከ5ኛ እስከ 8ኛ ክፍል እንዲሁም ለጎልማሶች ትምህርት የሚያገለግሉ እንደሆኑ ማወቅ ተችሏል። በዕለቱም ከ10 ካርቶን በላይ የሚሆኑ የሳይንስ፣ የሂሳብ፣ የቋንቋ፣ የሥነ-ፅሑፍ እና የማኅበራዊ ሳይንስ ይዘት ያለቸው መጽሐፎች ለእያንዳንዱ ትምህርት ቤት ቦታው ድረስ በመሄድ ለርዕሳነ መምህራን ርክክብ ተፈፅሟል።
በርክክቡ ወቅት በሰከላል ጃንባራ መድኃኔዓለም ቀበሌ የሚገኘው ገብረን አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር የሆኑት አቶ አዱኛ አጥናፉ እንዳሉት፥ የተደረገላቸው የመጽሐፍ እርዳታ በገንዘብ ሊተመን የማይችልና የተማሪዎችን ብሎም የመምህራንን የዕውቀት ክፍተት ለመሙላት የሚያግዝ ነው ብለዋል። ይህም የተማሪዎቻቸውን በሀገር ደረጃ የመወዳደር አቅም የሚያጎለብት በመሆኑ የመጽሐፍ እርዳታው ለትምህርት ቤቱ ትልቅ ትርጉም እንዳለው ተናግረዋል። ርዕሰ መምህሩ አክለውም በትምህርት ቤታቸው ያሉባቸውን፦ (1ኛ) ለሳይንስ ትምህርቶች የሚያገለግሉ ኬሚካሎች፣ (2ኛ) በፀሀይ የሚሰራ የኃይል ማመንጫ ችግር ለመቅረፍ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የበኩሉን አስተዋፅዖ እንዲያደረግላቸው ጠይቀዋል።
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ካደረገው የመጽሐፍ እርዳታ በተጨማሪ በይልማና ዴንሳ ወረዳ ውስጥ ለሚገኙ ከስድስት በላይ የችግኝ ጣቢያዎች ግብዓት የሚሆኑ የተለያዩ በሰው የሚገፉ ጋሪዎች፣ አካፋዎች ፣የመጎንደያ መቀሶች፣ የአሸዋ መንፊያ ወንፊቶችና መጋዞችን ለጣቢያዎቹ አበርክቷል። የይልማና ዴንሳ ወረዳ የስማርጋ ችግኝ ጣቢያ ሠራተኛና የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተወካይ የሆኑት ወ/ሮ ዳሳሽ ላቃቸው እንዳሉት፥ ችግኝ ጣቢያው በዓመት ከ80 ሺህ በላይ የተለያዩ አገር በቀል ችግኞችን በማፍላት ለአካባቢው ማኅበረሰብ በነፃ እንደሚያቀርብ ገልፀው፥ እስካሁን ባለው የሥራ ሂደት ምንም ዓይነት የቁሳቁስም ሆነ የግብዓት ችግር እንዳላጋጠማቸው ተናግረዋል።
የመጽሐፍ ድጋፉ በጎንደር አካባቢ ለሚገኙ የወረዳ የመንግስት ትምህርት ቤቶችም የተደረገ ሲሆን መጽሐፎች ተመሳሳይ ይዘት ያለቸው መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል።
ምንጭ፦ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ (አዲስ ዘመን) – የውጭ ጉዲፈቻ በመታገዱ የሀገር ውስጥ ጉዲፈቻ መጨመሩን የአዲስ አበባ ሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ።
በቢሮው የሕፃናት ድጋፍ ክብካቤ ቡድን መሪ አቶ ኢያሱ ሳሙኤል በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ ብሔራዊ የሕፃናት ፖሊሲ ተቀርጾ ከወጣበት ከ2009 ዓ.ም. ጀምሮ የውጭ ሀገር ጉዲፈቻ በመታገዱ የሀገር ውስጡ እየጨመረ መጥቷል።
ከእገዳው በፊት በተለያየ መንገድ ከሀገር ይወጡ የነበሩት ሕፃናት ቁጥር ከፍተኛ ነበር የሚሉት አቶ ኢያሱ፥ የሀገር ውስጡ ግን በአዲስ አበባ በ2007 ዓ.ም. ስድስት በአደራ ሶስት በጉዲፈቻ እንዲሁም በ2008 ዓ.ም. አምስት በአደራ ብቻ ነበር።
ከአዋጁ በኋላ ግን በየአመቱ ቁጥሩን በመጨመር በ2009 ዓ.ም. በአደራ 160 በጉዲፈቻ 150፤ በ2010 ዓ.ም. በጉዲፈቻ 148 በአደራ 138 እንዲሁም በ2011 ዓ.ም. በጉዲፈቻ 172 በአደራ 156 ማስተላለፍ መቻሉን ተናግረዋል።
እንደ አቶ ኢያሱ ገለጻ፥ እገዳው የተደረገው ሕፃናቱ በማያውቁት ባህል፣ ቋንቋና ማኅበረሰብ ውስጥ ማደጋቸው ከማንነት ጋር ተያይዞ የሚነሱባቸው ማኅበራዊና ሥነ ልቦናዊ ቀውሶች ስለሚያጋጥማቸው ነው። ለክትትልና ለቁጥጥር አመቺ ስለማይሆን፣ ብሎም በሀገር ውስጥ መሥራት እየተቻለ ለውጭ መደረጉ በሀገር ገጽታ ላይ የሚያመጣውም ተጽዕኖ በመኖሩ መሆኑን ጠቁመዋል።
እስካሁንም የሀገር ውስጥ ጉዲፈቻ ዝቅተኛ ሊሆን የቻለው በአግባቡ ባለመሠራቱና የግንዛቤ ክፍተት ስለነበር ሲሆን፥ በአሁኑ ወቅት ግን ቁጥሩ ከመጨመሩም ባለፈ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ እና ባለቤታቸው ወ/ሮ ዝናሽ ታያቸውን ጨምሮ ሌሎች ታዋቂ ሰዎችም በጉዲፈቻ ልጆች ከወሰዱ በኋላ ወሳጅ ቤተሰቦች ወረፋ እስከመጠበቅ መድረሳቸውን ጠቁመዋል።
አቶ እያሱ ጨምረው እንደተናገሩት፥ ቢሮው አምስቱን የጉዲፈቻ የአደራ፣ የማዋሀድ፣ የማኅበረሰብ አቀፍ ድጋፍና አማራጭ የድጋፍ አገልግሎቶች በመጠቀም ሕፃናትን ከችግር የመታደግና ተጠቃሚ የማድረግ ሥራ ይሠራል።
ለዚህም በስሩ ያሉትን ቀጨኔ የሴቶች፣ ኮልፌ የወንዶች፣ ክበበ ጸሐይ የጨቅላ ሕፃናት ማቆያና ክብካቤ ማዕከል እንዲሁም በወንጀል ውስጥ ገብተው የተገኙ ታዳጊዎች ተሀድሶ ማዕከላትን ይጠቀማል። በተጨማሪም ሰላሳ የሚደርሱ ከቢሮው ጋር በስምምነት የሚሠሩ እንደ አበበች ጎበና እና ሰላም የሕፃናት መንደር ያሉ በተመሳሳይ ተግባር የተሰማሩ የሕፃናት ማሳደጊያ ተቋማት ጋርም በትብበር የሚሠራ ሲሆን ክትትልና ቁጥጥርም ያደርጋል።
የሕፃናቱን ደኅንነትና ሥነ ልቦና ለማስጠበቅና ለክትትል እንዲያመች ለወሳጅ ቤተሰቦች መስፈርቶች ተቀምጠዋል የሚሉት አቶ እያሱ፥ ከነዚህም መካከል አዲስ አበባ ነዋሪ መሆን፣ ሙሉ የጤና ምርምራ ማድረግ፣ ገቢው ከአምስት ሺ ብር በላይ የሆነና ቢቻል ሌላ የገቢ አማራጭ ያለው፣ የራሳቸው ቤት ያላቸው ቢሆን ይመረጣል፥ ከወንጀል ነጻ አሻራ የሚያቀርብ፣ የጋብቻ የምስክር ወረቀት (marriage certificate) እና የተጋቢዎች ስምምነት፣ አካባቢው ለሕፃናቱ ምቹ መሆን እንዲሁም ወሳጆቹ ቤተሰቦች ከማኅበረሰቡ ጋር ያላቸው ግንኙነት ሰላማዊ መሆኑ፣ ከእድር፣ ከሃይማኖት ተቋማት፣ ወይንም ከወረዳ ሴቶችና ሕፃናት ቢሮ እንዲያቀርቡ እንደሚደረግም ጠቁመዋል።
አቶ እያሱ እንዳሉት፤ የሕፃናት ቤተሰብ መገኘት አለመገኘቱን ለማረጋገጥ የፖሊስ ሪፖርት ይዘገያል፤ የጤና ምርመራን በተመለከተም አጠቃላይ ምርመራ ውጤት በጽሁፍ እንዲሰጥ ሲጠየቅ በከተማው ካሉ ጤና ጣቢያዎች ፈቃደኛ ሆኖ የተገኘው አንድ ብቻ ነው። ከሆስፒታሎችም ፈቃደኛ የሚሆኑት ሦስት ብቻ ናቸው፤የምርመራ ውጤት እየሰጡ ያሉት በቃል ብቻ ነው። ይሄ ቢሮውን ብቻ ሳይሆን ቤተሰብንም ለእንግልት እየዳረገ በመሆኑ ከጤና ሚኒስቴር ጋር የመግባቢያ ሰነድ በመፈራረም በየክፍለ ከተሞቹ ለማስቀመጥ በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛሉ።
በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት አብዛኛው የመራጮች ፍላጎት ሴት በመሆኑ ወንዶች ሳይመረጡ የሚቆይበት ሁኔታ አለ። ይህንንም ለማስተካከል የማግባባት ሥራ እየተሠራ ይገኛል ሲሉ ተናግረዋል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ (ኢቢሲ) በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ እየተካሄደ በነበረው ድርድር ግብጽ አዳዲስ ሀሳቦችን በማምጣቷ ኢትዮጵያ ሳትቀበል ቀርታለች። ድርድሩ ለአራተኛ እና ለመጨረሻ ጊዜ የተካሄደ በመሆኑ ስምምነት ላይ ይደረሳል ተብሎ ተጠብቆ ነበር።
ግብፅ ያቀረበችው ዋነኛው የማያግባባ ሀሳብ የሙሌት ሰንጠረዡ ከ12 ዓመት እስከ 21 ዓመት ይሁን ብላ እንደ አዲስ ማቅረቧ ነው። ግብፅ እስካሁን ወደ መስማማቱ ስትቃረብ ቆይቷ ነው በዛሬው ዕለት (ታህሳስ 30 ቀን 2012 ዓ.ም.) በተደረገው ድርድር አዲሱን ሀሳብ ያነሳችው። ኢትዮጵያ በበኩሏ የሙሌት ጊዜው ከ4 ዓመት እስከ 7 ዓመት የሚል ሀሳብ አቅርባ ስትደራደር ቆይታለች።
በድርቅ ጊዜ የውሃ አለቃቀቅ እና አሞላል ሂደቱ ምን ይምሰል የሚለው ጉዳይም ኢትዮጵያን እና ግብፅን ያላግባባ ሆኗል። የድርቅ ብያኔ /definition/ ላይም ስምምነት ላይ አልተደረሰም። ግብፅ “የውሃ መጠኑ ከ40 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ በታች ሲሆን ‘ድርቅ ነው’ ተብሎ የተሻለ ውሃ ይለቀቅልኝ” የሚል ሀሳብ ያቀረበች ሲሆን፥ ኢትዮጵያ በበኩሏ “‘ድርቅ’ የሚለው ብያኔ መሰጠት ያለበት የውሃ መጠኑ ከ35 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ በታች ሲሆን ነው” በሚል መከራከሪያ ሀሳብ አቅርባለች። በድርድሩ ላይ እነዚህ ሀሳቦች የማይታረቁ ሆነው ቀርተዋል።
የኢትዮጵያ ውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በጉዳዩ ላይ በሰጡት አስተያየት “የግብፅ ተደራዳሪዎች ካቀረቡት ሀሳብ አንፃር በአዲስ አበባው ድርድር ላለመስማማት የመጡ ይመስላል” ብለዋል። ከዚህ በፊት የነበረውን መቀራረብ በዚህ ድርድር እንደገና እንዲራራቅ ማድረጋቸውንም ነው ያከሉት ሚኒስትሩ።
በድርቅ ጊዜ የውሃ አሞላል ሂደት ምን ይምሰል የሚለውም በኢትዮጵያ በኩል ግድቡ ከፍተኛ የውሃ መጠን ከያዘ በኋላ ወደ ግድቡ የሚገባው ውሃ በቀጥታ የማመንጫ ተርባይኑን እየመታ እንዲሄድ እና እንዲለቀቅ እንደሚደረግ ኢትዮጵያ አቋሟን ገልጻለች። ግብፅ ግን ይህ ተቀባይነት የለውም ብላለች። በከፍተኛ ድርቅ ወቅት ደግሞ እስከ 13 ነጥብ 5 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ ውሃ ይለቀቃል የሚል ሀሳብም ከኢትዮጵያ በኩል ቀርቧል። ግብፅ በበኩሏ ወደ 14 ነጥብ 5 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ ከፍ ሊል ይገባል ስትል ተከራክራለች።
የቴክኒክ ኮሚቴው ውጤት ሪፖርት በሚቀጥለው ሰኞ (ጥር 4 ቀን 2012 ዓ.ም.) ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ በሚካሄድ ስብሰባ ላይ ይፋ ይደረጋል። ይህንን ተከትለሎም የየሀገራቱ መሪዎች የሚወስኑት ውሳኔ በሀገራቱ መካከል ቀጣይ ምን ዓይነት ድርድር ሊካሄድ ይችላል የሚለውን የሚወስን ይሆናል።
ኢትዮጵያ በዚህ የቴክኒክ ኮሚቴ ላይ በመመሥረት ቀጣይ ድርድሮችን ለማድረግ እንደምትፈልግ ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ ተናግረዋል። በአዲስ አበባው ድርድር መግባባት ላይ ይደረሳል የሚል እሳቤ የነበረ ቢሆንም ተፈላጊው ውጤት አለመገኘቱን ነው ሚኒስትሩ የገለጹት።
የሆነው ሆኖ የግድቡ ሂደት የማይቋረጥ መሆኑን እና ኢትዮጵያ ከሚቀጥለው ሐምሌ ወር ጀምሮ ግድቡን ውሃ የመሙላት ሂደት እንደምትጀምር ተገልጿል።
ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ)/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
ባሕር ዳር (ሰሞነኛ) – ዶክተር መሐሪ ታደሰ ወልደጊዮርጊስ አቶ አየነው በላይን በመተካት የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሆነው ተሾሙ።
ዶክተር መሐሪ ታደሰ ወልደጊዮርጊስ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ የሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በአሜሪካው ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኖርዝ ቴክሳስ (The University of North Texas) ተከታትለዋል። በዩኒቨርሲቲ ኦፍ ቴክሳስ አት ኦስተን (The University of Texas at Austin) እና በሌሎችም በተመራማሪነት ማገልገላቸውም ታውቋል። የተለያዩ የምርምር ሥራዎችን በአሜሪካና ካናዳ ማቅረባቸውም በግለ ታሪካቸው ተብራርቷል።
ዶክተር መሐሪ የተለያዩ ዓለማቀፍ የሙያ ማኅበራት አባል መሆናቸውም ነው የተገለጸው። የአሜሪካ የስታትስቲክስ ማኅበር (American Statistical Association)፣ የአሜሪካ የትምህርት ጥናት ማኅበር (American Educational Studies Association)፣ የተቋማዊ ጥናት ማኅበር፣ የከፍተኛ ትምህርት ጥናት ማኅበር፣ የደቡብ ምዕራብ የትምህርት ጥናት ማኅበርና የቴክሳስ የትምህር ጥናት ማኅበር አባል እንደሆኑም ነው የተገለጸው።
ከ13 ዓመታት የአሜሪካ ቆይታ በኋላ ባለፉት አምስት ዓመታት በኢትዮጵያ በተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በምርምርና የተለያዩ ትምህርቶችን በማስተማር እንደቆዩም ተገልጿል፤ በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት በኃላፊነት ደረጃ ማገልገላቸውም ነው የተነገረው።
ዶክተር መሐሪ ታደሰ ወልደጊዮርጊስን ልምዳቸውንና የአመራር ብቃታቸውን ግምት ውስጥ በማስገባት የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ታኅሳስ 25 ቀን 2012 ዓ.ም. ማካሄድ በጀመረው መደበኛ ጉባኤው የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አድርጎ ሾሟቸዋል።■
ከአማራ ክልል ሳንወጣ፥ በደብረ ብርሃን ከተማ የሚገነባው የበላይ ባለ ኮኮብ 5 ሆቴልና ቢዝነስ ሴንተር ፕላን በዘርፉ ባለሙያዎች ተገመገመ። የፕሮጀክቱ ዲዛይንና አማካሪ የሆኑት አቶ ነቢዩ ሰለሞን እንዳብራሩት፥ ሆቴሉ በ3,690 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ እንደሚያርፍ፣ 3 ደረጃቸውን የጠበቁ የመሰብሰቢያ አዳራሾች፣ 120 የመኝታ ክፍሎች፣ 2 ሬስቶራንቶች፣ ባር፣ ጂም እና ሌሎች አገልግሎቶችን የሚሰጡ ክፍሎች እንደሚኖሩት፣ ዲዛይኑ አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረገ እንደሆነ ገልጸዋል።
የደብረ ብርሃን ከተማ ህንጻ ሹም ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አምሳሉ መኮንን በበኩላቸው በቀረበው ዲዛይን መሠረት ገንቢ አስያየት በመስጠት ሆቴሉ ከታሰበው በላይ ተሻሽሎና ዳብሮ እንዲሠራ ባለሙያዎች የድርሻቸውን አንዲወጡ አሳስበዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎችም የቡና ስኒ በዲዛይኑ ላይ መካተቱ ከደብረብርሃን ጋር ምን ያገናኘዋል? የሠራተኞች ማረፊያ ክፈል፣ ሕፃናት መዝናኛ፣የመዋኛ ገንዳ መካተት አለበት የሚሉና እና ሌሎችም በርካታ ሀሳብ አስተያየቶች ተሰጥተዋል። በመድረኩ ከደብረብርሃን ዩኒቨርስቲ፣ ከኢንቨስትመንት፣ ከህንጻ ሹም፣ ከህንጻ ዲዛይን አማካሪዎች፣ ከባህል ቱሪዝም ጽሕፈት ቤቶች የመጡ የሥራ ኃላፊዎችና የዘርፉ ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል።
የበላይ ባለ 5 ኮኮብ ሆቴልና ቢዝነስ ሴንተር ከ2 መቶ ሚሊየን ብር በላይ በጀት እንደተያዘለት የመሠረት ድንጋው ሲጣል መገለጹ የሚታወስ ነው።
ምንጮች፦ የአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት እና የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
ደብረ ታቦር (ሰሞነኛ) – “የኪነጥበብ (የአዝማሪ) ሚና ትናንት፣ ዛሬና ነገ” በሚል ርዕስ የሰላም እና የኪነጥበብ መድረክ በርከት ያሉ ታዳሚዎች በተገኙበት በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ተካሄደ።
በአዝማሪ ላይ የተሠሩ ጥናቶች እንደሚሉት የአዝማሪዎች አገልግሎት በማኅበራዊ ሕይወት ላይ ብቻ የተወሰነ አልነበረም፡፡ አዝማሪዎች ዘፈንን ከሚከውኑበት ሰውን የማዝናናት ተለምዷዊ ተግባር ባሻገር በኢትዮጵያ ባህላዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ስፍራ ነበራቸው፡፡ ለዚህም ምክንያቱ Kimberlin (1983) እንደሚገልፁት፥ ዘፈን ከኢትዮጵያ ሕዝብ አኗኗር፣ ይትብሃልና ሕይወት ጋር ከፍተኛ ቁርኝት ያለው በመሆኑ ነው፡፡ እንደ Ashenafi (1971) እና Teclehaimanot (1986) ትንታኔ አዝማሪዎች ዋና ሥራቸው ማዝናናት ቢሆንም በተጨማሪ ግን ዜናና ታሪክ ነጋሪዎች፣ ሃያሲዎች፣ የፖለቲካ ተንታኞች፣ መዝጋቢዎች፣ አዝማቾች፣ ሆነው አገልግለዋል፡፡ ይህንን ታሳቢ ያደረገው የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ከሰላም ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር “የኪነጥበብ (አዝማሪ) ሚና ትናንት፣ ዛሬና ነገ” በሚል ርዕስ ታህሳስ 20 ቀን 2012 ዓ.ም. የግማሽ ቀን መርሐ-ግብር አካሂዷል።
ሰላም ኢትዮጵያ፣ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ እና ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ በመተባበር ባዘጋጁት መድረክ የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አነጋግረኝ ጋሻው የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፥ በንግግራቸውም እንደገለፁት ኪነጥበብ ለዕድገት ወሳኝ መሆኑንና፣ ኪነጥበብንና ባህልን ያላካተተ ዕድገት ሙሉ ሊሆን እንደማይችል እና ይህ ሰላምና ባህልን አጣምሮ የያዘ መድረክ የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚከታተለው ገልጸዋል።
በመርሐ-ግብሩ “የኪነጥበብ (አዝማሪ) ሚና ትናንት፣ ዛሬና ነገ” በሚል ርዕስ የተካሄደ ሲሆን ከውይይቱ በተጨማሪ በመድረኩ የቀረቡት ልዩ ልዩ የኪነጥበብ ሥራዎች ድምቀት ሰጥተውታል።
በመርሐ-ግብሩ መጨረሻ የመዝጊያ ንግግር ያደረጉት የደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ የም/ማ/አ/ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር መንበሩ ተሾመ ባህሉንና ትውፊቱን የማያውቅና እነዚህን ሀብቶቹን የማያለማ ማኅበረሰብ ሁልግዜም አያድግም፤ በመጤ ባህሎች የራሱን ወርቃማ የሆኑ ሀብቶቻችንን እያጣንሁልግዜ የውጭ ናፋቂ እየሆንን፤ ስልጣኔ የሚመስለን የሌሎቹ ነው። ግን እኛ ወርቃማ የሆነ ጥበብ አለን፤ እናም ይኸ ለማኅበራዊ፣ ለኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፋይዳው ከፍተኛ ለሆነው ባህል ሁላችንም የበኩላችንን ድጋፍ ማድረግ፣ መስመር ማሳየት፣ ስልጠናዎችን ማዘጋጀት ባለሙያዎችን አይዟቹህ ማለት አለብን ሲሉ ገልጸዋል። ባለሙያዎችን ለወደፊቱ እንዴት እንደግፋቸው? እንዴት እናበረታታቸው? የውጭና የውስጥ ሀይሎችን እንዴት እናስተሳስራቸው የሚለውን ለቀጣይ የሁላችንም የቤት ሥራ መሆን አለበት ያሉ ሲሆን በመጨረሻም ለመርሐግብሩ መሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱትን አካላት በሙሉ አመስግነዋል – ዶ/ር መንበሩ ።
ማጣቀሻዎች፦
- Ashenafi Kebede: The music of Ethiopia: its development and cultural setting. Dissertation, Wesleyan University. (1971)
- Cynthia Tse Kimberlin: “The Music of Ethiopia“, in Music of Many Cultures, E. May, ed., Berkeley, Los Angeles: University of California Press. (1983).
- Teclehaimanot G. Selassie: A brief survey study of the Azmaris in Addis Ababa. Proc. of the International Symposium on the Centenary of Addis Ababa. (1986).
ምንጭ፦ ደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – ኢትዮ ቴሌኮም በዩኒቨርሲቲ የሚገኙ ተማሪዎች የድጋፍ መርሐ ግብርን በ2006 ዓ.ም. የጀመረ ሲሆን የተጠቃሚዎችም ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በ2011 በጀት ዓመት መጨረሻ በ13 ዩኒቨርስቲዎች ለ840 ተማሪዎች ድጋፍ ሲያደርግ የቆየ ሲሆን ይህ ድጋፍ የሚኖረውን ጠቀሜታ ታሳቢ በማድረግ በመላው ሀገሪቱ በሚገኙ 45 ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚማሩ አራት ሺህ (4000) ተማሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የድጋፍ መርሐ ግብር አዘጋጅቶ ጥሪ የተደረገላቸው የመንግሥት ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንቶች፣ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት ታኅሣሥ 21 ቀን 2012 ዓ.ም. ይፋ አድርጓል። ለዚህም ፕሮጀክት የሚውል በዓመት ብር 16 ሚሊዮን ብር መድቧል።
ኢትዮ ቴሌኮም ማኅበራዊ ኃላፊነቱን (corporate social responsibility) ለመወጣት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራባቸው ከሚገኙ ጉዳዮች መካከል የትምህርት ዘርፍ አንዱ ሲሆን ከዚህም ውስጥ በመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ለሚገኙና ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ተማሪዎች ወርኃዊ የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋል።
ኩባንያው በትምህርት ዘርፍ በተለያዩ አካባቢዎች ድጋፍ ለሚሹ ከአሥራ አራት ሺህ በላይ ተማሪዎች የምገባ፣ የትምህርት ቁሳቁስና የኪስ ገንዘብ ድጋፍ እንዲሁም በያዝነው 2012 በጀት ዓመት በመላው ሀገሪቱ በሚገኙ 93 ትምህርት ቤቶች ለሚማሩ 32,974 ተማሪዎች ለእያንዳንዳቸው የአንድ ደርዘን ደብተር ድጋፍ እንዲሁም ከአምስት ሺህ በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች የዩኒፎርምና ቦርሳ ድጋፍ አድርጓል።
ከዚሁ በተጨማሪ ኢትዮ ቴሌኮም ሴቶች በኢኮኖሚው መስክ ያላቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ ከአዲስ አበባ ክፍለ ከተሞች ለተውጣጡ አንድ መቶ ሴቶች የፋሽን ዲዛይን ሥልጠና እንዲወስዱ ሙሉ ወጪውን በመሸፈን ድጋፍ አድርጓል። የሥልጠና ዕድሉ የተመቻቸው ሴቶች በትምህርት፣ በሥራ እንዲሁም በአጠቃላይ የምጣኔ ሀብት (የኢኮኖሚ) መስኮች ያለባቸውን ተጽእኖ ከግምት በማስገባት ሴቶችን ማስተማር እና በኢኮኖሚ በማብቃት ራሳቸውን እንዲችሉና ልጆቻቸውን ማስተማር እንዲችሉ እገዛ ለማድረግ ነው።
ኩባንያው በተለይ ከ2011 በጀት ዓመት ጀምሮ በተደራጀ መልኩ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ለዋና ሥራ አስፈጻሚ ተጠሪ የሆነ የሥራ ክፍል በማደራጀት ማኅበረሰባችን ድጋፍ የሚሻባቸውን የትኩረት መስኮች በመለየት የማኅበራዊ ኃላፊነት ሥራዎችን አጠናክሮ በመሥራት ላይ ይገኛል። በዚህም ረገድ:-
- በሰብዓዊ እና ማኅበረሰብ አቀፍ ድጋፎች ለሴቶች፣ ለአረጋውያን፣ ለሕፃናት፣ ለአካል ጉዳተኞች፣ ለጎዳና ተዳዳሪዎች እና ለመሳሰሉት የማኅበረሰብ ክፍሎች ድጋፍ አድርጓል፤
- በአረንጓዴ ልማትና በአካባቢ ጥበቃ ዘርፍ “በአረንጓዴ ኢትዮጵያ ፕሮጀክት” አማካኝነት በመላ ሀገሪቱ ከ17 ሺ በላይ ሠራተኞችን በማሳተፍ ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ተክሎ እንክብካቤ በማድረግ ላይ ይገኛል፤
- ኢትዮ ቴሌኮም ሸገርን ለማስዋብ ፕሮጀክት ካደረገው የገንዘብ ድጋፍ በተጨማሪ ከቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ እስከ ብሔራዊ ቤተመንግሥት የመንገድ ላይ መብራቶች ድጋፍ በማድረግ አዲስ አበባ ከተማ ውብና ጽዱ ለማድረግ የበኩሉን አስተዋፅኦ በማድረግ ላይ ይገኛል። ከዚህም ጋር በተያያዘ ኩባንያው ሌሎች የሀገራችን ከተሞች ጽዱና አረንጓዴ አካባቢን ለመፍጠር የሚያደርጉትን ጥረት በመደገፍ ላይ ይገኛል፤ ለወደፊትም ይህንኑ አጠናክሮ ይቀጥላል፤
- በተጨማሪም ኩባንያው ለሌሎች የመንግሥት ፕሮጀክቶችም በሄልዝ ኔት (Health Net)፣ በወረዳ ኔትና (Woreda Net) በስኩል ኔት (School Net) ፕሮጀክቶች አማካኝነት ድጋፉን እያደረገ ይገኛል፡
ማኅበራዊ ኃላፊነትን የመወጣት ባህል ኩባንያው ብቻ ሳይወሰን በሠራተኞቻችንም በበጎ ፈቃደኝነት የሚሠራ ሲሆን፥ በዚህም ረገድ በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ ሠራተኞቻችን በየአካባቢያቸው በጤና፣ በሰብዓዊነት፣ በትምህርት፣ በአካባቢ ጥበቃ እና በመሳሰሉት ዘርፎች ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
በዩኒቨርሲቲ እንዱስትሪ ትስስር፣ በተመራቂ ተማሪዎች የኤክስተርንሺፕ (externship) እና በተለያዩ ዩኒቨርሲቲ መምህራን የጥናት ፕሮጀክቶች ላይ ኢትዮ ቴሌኮም በሀገራችን ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር እንደሚሠራ ይታወቃል። በቀጠይም ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በቅንጅት ማኅበረሰቡን የሚጠቅሙ ፕሮጀክቶች ላይ በመሳተፍ የሀገራችን ዜጎች ከሁለቱ ተቋማት የሚጠቀሙበትን ሁኔታዎች በጋራ እንደሚያመቻች ኩባንያው በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል።
ምንጭ፦ ኢትዮ ቴሌኮም/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
ዘመን ባንክ ባለፈው የበጀት ዓመት ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች የሰጠው ብድር 7.6 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፥ ይህም ከቀዳሚው ዓመት የ50.7 በመቶ እድገት የተመዘገበበት እንደሆነ ባንኩ ጨምሮ ገልጿል።
አዲስ አበባ (አዲስ አድማስ) – ዘመን ባንክ ባለፈው የበጀት ዓመት የትርፍ መጠኑን ወደ 86 በመቶ ማሳደጉን አስታወቀ። ባንኩ በ2011 ዓ.ም. የበጀት ዓመት ከሰጣቸው የአገር ውስጥና የውጭ አገር የባንክ አገልግሎት ዘርፎች ከ1.5 ቢሊዮን ብር በላይ ያገኘ ሲሆን ሊያገኝ ካቀደው የ1 ቢ. 492 ሚሊዮን ብር ገቢ አንጻር፣ የ6 በመቶ ብልጫ እና ከ2010 ዓ.ም. አንፃር የ39 በመቶ ብልጫ ወይም የ447 ሚሊዮን ብር እድገት ማሳየቱን ባንኩ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።
ለትርፉ ማደግ እንደ ምክንያት ከተቆጠሩት መካከል የወጪ ቅነሳ፣ የብድር አቅርቦትና በአገልግሎት ዘርፍ የተመዘገበው መልካም አፈፃፀም ዋና ዋናዎቹ እንደሆኑ የጠቀሰው ባንኩ፥ በበጀት ዓመቱ 1 ቢሊዮን 84 ሚሊዮን ብር ወጪ ይኖረዋል ተብሎ የነበረ ቢሆንም በዓመቱ ውስጥ በተሠሩ የወጪ ቅነሳ መርሃ ግብሮች አጠቃላይ ወጪው 947 ሚሊዮን ብር እንዲሆን በማድረግ ትርፋማነቱን ለማሻሻል እንደረዳውም ተገልጿል።
ዘመን ባንክ በበጀት ዓመቱ ከታክስ በፊት 635.9 ሚሊዮን ያልተጣራ ትርፍ ያስመዘገበ ሲሆን፥ ይህም ከቀዳሚው 2010 ዓ.ም የ86 በመቶ ወይም የ293.5 ሚሊዮን ብር ብልጫ ማሳየቱንና ከዕቅዱ ደግሞ የ55 በመቶ ብልጫ ያለው አፈፃፀም ሆኖ መመዝገቡን አስታውቋል።
ባለፈው የበጀት ዓመት ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች የሰጠው ብድር 7.6 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፥ ይህም ከቀዳሚው ዓመት የ50.7 በመቶ እድገት የተመዘገበበት እንደሆነ ባንኩ ጨምሮ ገልጿል። ባንኩ በበጀት ዓመቱ ካገኘው ከ1.5 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ውስጥ 1 ቢሊዮን 15 ሚሊዮን ከወለድ፣ ከዓለም አቀፍ ባንክና ከሌሎች አገልግሎቶች ያገኘው እንደሆነም አስታውቋል።
የዘመን ባንክ አጠቃላይ ሀብት እ.ኤ.አ በ2019 ዓ.ም. መጨረሻ 14.7 ቢሊዮን የደረሰ ሲሆን ይህም ከቀዳሚው ዓመት በ18 በመቶ ወይም በ2.2 ቢሊዮን ብር ጭማሪ ማሳየቱ የተገለፀ ሲሆን፥ በ2010 ዓ.ም ከነበረው የ10.2 ቢሊዮን ብር ተቀማጭ ገንዘብ፣ በ2011 ዓ.ም. ወደ 11.6 ቢሊዮን ብር ማደጉም ታውቋል።
በሌላ በኩል ባንኩ በ2011 ዓ.ም. የበጀት ዓመት የደንበኞቹን የባንክ አገልግሎት ፍላጎት ለማሟላትና በቅርበት ለማገልገል ባደረገው ጥረት፣ የቅርጫፎቹን ብዛት ኪዮስኮችን ጨምሮ ወደ 43 ያሳደገ ሲሆን በተያዘው አዲስ የበጀት ዓመትም ይህንኑ የቅርንጫፍ ቁጥር የማሳደግ ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።
◌ SEMONEGNA on Social Media: Facebook | Twitter | Instagram | Pinterest | Video | Forum
ምንጭ፦ አዲስ አድማስ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ
ጉራጌ በክልል የመደራጀት ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄ የክልሉ መንግሥት በሰላማዊና በሰለጠነ መንገድ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጠው የብሔሩ ተወላጆች ጠየቁ።
ኧዣ ወረዳ ፥ጉራጌ ዞን (ሰሞነኛ) – የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ ርስቱ ይርዳው ከጉራጌ ማኅበረሰብ ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በጉራጌ ዞን ኧዣ ወረዳ በደሳለኝ ሎጅ ውይይት አካሄዱ። የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ጉራጌ በክልል የመደራጀት ሕገ መንግሥታዊ መብቱ በሰላማዊና በሰለጠነ መልኩ የክልሉ መንግሥት አፋጣኝ ምላሽ ሊሰጠው እንደሚገባ ጥሪ አቀረቡ።
በጠንካራ የሥራ ባህሉና ከየትኛውም ብሔር ብሔረሰቦች ጋር ተግባብቶ፣ ተቻችሎና ተከባብሮ የመኖር የቆየ ልማድ ያለው የጉራጌ ብሔር ባለፋት 27 ዓመታት በማኅበራዊ፣ በፓለቲካዊና በኢኮኖሚው ከፍተኛ በደልና ጭቆና ሲደርስበት እንደነበር ያስታወሱት አስተያየት ሰጪዎቹ፥ አሁን በመጣው የሀገሪቱ ለውጥ ፍትሃዊ የኢኮኖሚና የፓለቲካ ተጠቃሚነቱ ሊረጋገጥለት እንደሚገባ ተናግረዋል።
አክለውም ብዙ ጊዜ በክልል የመደራጀት ጥያቄ ሲነሳ ጉራጌ ክልል አያስፈልገውም የሚል አስተያየት የሚሰጥ መሆኑን የገለጹት ተሳታፊዎቹ፥ ክልል የማያስፈልግ ከሆነ አሁን ያለው የዞን አስተዳደር ለምን ያስፈልጋል፣ ጉራጌ በክልል ቢደራጅ ስጋቱ ምንድን ነው የሚል ጥያቄዎች ተነስተው በመድረክ አወያዮቹ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።
የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ጀማል እንደገለጹት፥ ዞኑ የብዙ ብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ ስትሆን መንግሥት እንኳ ባይኖር ሕዝቡ ራስ በራሱ መምራት የሚችልበት ቱባ ባህል፣ እሴትና እምነት እንዲሁም ባህላዊ የዳኝነት ሥርዓት ያለው ነው ብለዋል።
የዞኑ ሰላም ለማስጠበቅ የሀይማኖት አባቶችና ሽማግሌዎች እየሠሩት ያለው ሥራ የሚበረታታ መሆኑን የገለጹት አቶ መሀመድ፥ በቀጣይም የሕዝቦች አንድነት ለማጠናከር በትኩረት ይሠራል ብለዋል። ጉራጌ በክልል የመደራጀት ጥያቄ የሚጠይቀው ለቅንጦት ሳይሆን ሕገ መንግሥታዊ መብቱ ስለሆነ መንግሥት አፈጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ አቶ መሀመድ ጠይቀዋል።
በክብር እግድነት የዞኑ ማኅበረሰብ ለማወያየት የመጡት የደቡብ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ እንደተናገሩት፥ የጉራጌ ብሔር ለሥራ እንጂ ለግጭትና ለንትርክ ጊዜ የሌለው ከየትኛውም ብሔር ብሔረሰብ ጋር ተከባብሮና ተዋዶ በፍቅር የሚኖር ነው ብለዋል። ጉራጌ በክልል እንዲደራጅ ለተጠየቀው ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት አሁን አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ መልስ መስጠት እንደማይችሉና በቀጣይ በመመካከር ለህብረተሰቡ ምላሽ እንደሚሰጠው አቶ ሞገስ ተናግረዋል።
የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ ርስቱ ይርዳው ከውይይቱ ተሳታፊዎች ለተነሳላቸው ጥያቄዎች መልስ ሲሰጡ እንደተናገሩት፥ በመስቃን ቤተ ጉራጌና በማረቆ መካከል የተፈጠረው ግጭት ለመፍታት ከሀይማኖት አባቶች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች እና ከሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመሆን ጥረት እየተደረገ መሆኑንና በአጭር ጊዜ መፍትሄ ያገኛል ብለዋል።
ክቡር ርዕሰ መስተዳድሩ የሕዝቡ በክልል የመደራጀት ጥያቄ ሲመልሱ እንደተናገሩት፥ ጉራጌ በክልል የመደራጀት መብት እንዳለው ጠቁመው ጥያቄው የሀገሪቱ የለውጥ ጉዞ በማያደናቅፍ መልኩ መሆን አለበት በማለት አቋማቸውን ተናግረዋል።
በመድረኩ የደቡብ ክልል የካቢኔ አባላት፣ ከአዲስ አበባ የመጡ አመራሮችና ተወላጆች፣ ባለሀብቶች፣ የዞን፣ የወረዳና የከተማ አስተዳደር አመራሮች ፣ የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ ነበሩ ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን አስተዳደር ሕዝብ ግንኙነት ጽህፈት ቤት ነው።
ምንጭ፦ የጉራጌ ዞን አስተዳደር ሕዝብ ግንኙነት ጽህፈት ቤት / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ