Semonegna

Forum Replies Created

Viewing 15 posts - 106 through 120 (of 132 total)
  • Author
    Posts
  • Semonegna
    Keymaster

    በዓመት 500 ሚሊዮን ሊትር የምግብ ዘይት የሚያመርተው ፋብሪካ ዘንድሮ ሥራ ይጀምራል

    ቡሬ (አዲስ ዘመን) – የአገር ውስጥ የምግብ ዘይት ፍጆታን ከ50 እስከ 60 በመቶ መሸፈን የሚያስችልና በቡሬ ከተማ እየተገነባ የሚገኘው የምግብ ዘይት ፋብሪካ ከሁለት እስከ አራት ወራት ውስጥ ተጠናቆ ወደ ምርት ይገባል ተባለ። የውጭ ምንዛሬ በማዳን የጎላ ፋይዳ እንደሚኖረውም አዲስ ዘመን ጋዜጣ ዘግቧል።

    በፌዴራልና በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ከፍተኛ አመራሮች የካቲት ወር አጋማሽ፣ 2012 ዓ.ም. የተጎበኘው በኢትዮጵያዊ ባለሃብት አቶ በላይነህ ክንዴ በመገንባት ላይ ያለው ፋብሪካው፤ የአገር ውስጥ የምግብ ዘይት ፍጆታን ከ50 እስከ 60 በመቶ ይሸፍናል ተብሏል።

    በአገር ውስጥ ያለውን የምግብ ዘይት አቅርቦት ችግርን ለመፍታት ወደ ዘርፉ መግባታቸውን የገለጹት አቶ በላይነህ ክንዴ፥ ከአንድ ፋብሪካ በስተቀር ቀሪዎቹ እንደተገጣጠሙም ተናግረዋል። በዓመት 500 ሚሊዮን ሊትር ዘይት የማምረት አቅም እንዳለውና አገር ውስጥ ያለውን የምግብ ዘይት አቅርቦት እንደሚፈታም ተናግረዋል።

    ድርጅቱ ላለፉት 13 ዓመታት ሰሊጥ ወደ ውጭ በመላክ ግንባር ቀደም እንደነበር በማስታወስ፥ በተደጋጋሚ በመንግሥትና በሕዝብ ይቀርብ የነበረው ጥያቄ እውን የሚያደርገው አቀነባብሮ የሚያቀርበው ፋብሪካ ዘንድሮ ወደ ምርት እንደሚገባ ነው ባለሀብቱ የተናገሩት። ማንኛውንም አይነት የቅባት እህሎችን እንደሚያጣራና በአሁኑ ወቅት ለአምስት መቶ ሰዎች የሥራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን ወደ ምርት ሲገባ ቁጥሩ እስከ ሦስት ሺህ ከፍ እንደሚልም አብራርተዋል። ፋብሪካው በግብአትነት 20 ሚሊዮን ኩንታል እህል እንደሚያስፈልገው በመጠቆም፥ ከጉትን እስከ ጎንደር ጫፍ ያሉ አርሶ አደሮችም ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉ በጋራ እንሠራለን ብለዋል።

    የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተካ ገብረየሱስ፥ አሁን ባለው ሁኔታ የሕዝቡን ፍላጎት ለማሟላት አቅም ያለው የምግብ ዘይት ፋብሪካ አለ ማለት ይከብዳል፤ አብዛኛው የምግብ ዘይት ፍላጎት ከውጭ በሚገቡ ምርቶች እየተሸፈነ እንደሚገኝም ተናግረዋል። በባለሀብቱ አቶ በላይነህ ክንዴ የሚገነባው 50 በመቶ ፍላጎትን ከሸፈነ ቀሪውንም ሌሎች ወደ ምርት የሚገቡ ፋብሪካዎች ይሸፍኑታል ብለዋል። ፋብሪካዎች ማሽን ስላስገቡ ይጠናቀቃል ማለት አይደለም ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፥ የመብራት ችግር እንዳያስተጓጉል ጎን ለጎን እየተሠራ መሆኑንና ፋብሪካው ወደ ምርት ሲገባ የውጭ ምንዛሬ በማዳን በኩል ፋይዳው የጎላ እንደሚሆንም ጠቁመዋል።

    በአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ የፕሮሞሽንና ሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ይሄነው አለም፥ ባህር ዳር ዙሪያና ቡሬ ከተማም እንደቅደም ተከተላቸው ሰፊ የኢንቨስትመንት ማዕከል መሆናቸውን ተናግረዋል። ባለሀብቱ ትልቅ የዘይት ፋብሪካ እንዲተክሉ ያነሳሳቸው አካባቢው ትርፍ አምራች መሆኑ ነውም ብለዋል።

    እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፥ ከሱዳን ጠረፍ እስከጃዊ አኩሪ አተር፣ ኑግ፣ ሰሊጥ፣ ሱፍ፣ ስንዴና በቆሎ በከፍተኛ ደረጃ ይመረታል፤ ፋብሪካው ምርቶቹን በግብአትነት በመጠቀም ዘይት በከፍተኛ ደረጃ በማምረት በዕቅዱ መሠረት የአገሪቱን ከ50 እስከ 60 በመቶ ፍላጎት እንደሚሸፍንም ተናግረዋል። ምሥራቅ ጎጃም፣ ምዕራብ ጎጃምና አዊ ደቡባዊ ጎንደር እስከ ሱዳን ጠረፍ ከፍተኛ ምርት በመኖሩ የፌዴራልና የክልሉ መንግሥት የግብርና ምርት አቀነባባሪዎች ትኩረታቸውን ወደ አካባቢዎቹ እንዲያርጉም ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል።

    በላይነህ ክንዴ ግሩፕ በተለያዩ ዘርፎች የተሰማራ ድርጅት ሲሆን፤ በገላን ከተማ የጀመረው የመኪና መገጣጠሚያ፣ ሆቴልና እርሻ ሥራ ተጠቃሽ ናቸው። በቡሬ ከተማ በግንባታ ላይ ያለው የዘይት ፋብሪካ በ2006 ዓ.ም የተጀመረና በ30 ሄክታር ላይ ያረፈ ነው። የጀሪካን፣ የማሸጊያ፣ የሳሙና፣ የማርጋሪንና የካርቶንን ጨምሮ ሰባት የተለያዩ ፋብሪካዎችን ይዟል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    በላይነህ ክንዴ የምግብ ዘይት ፋብሪካ

    Semonegna
    Keymaster

    አዳማ ሪፈራል ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ የሕክምና ዶክተሮችን አስመረቀ
    ጅማ ዩኒቨርሲቲ 3ሺህ 185 ተማሪዎችን መተመሳሳይ ዕለት አስመርቋል

    አዳማ (ኢዜአ) – አዳማ ሪፈራል ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ የውስጥ ደዌና ከፍተኛ የቀዶ ሕክምና ስፔሻልስቶችን ጨምሮ በተለያዩ ሙያዎች ያሰለጠናቸውን 140 ዶክተሮችን የካቲት 14 ቀን 2012 ዓ.ም. አስመረቀ። ከተመራቂዎቹ መካከል ደቡብ ሱዳን የሕክምና ስፔሻልስቶች ይገኙበታል።

    በምረቃው ሥነ ሥርዓት የተገኙት የኦሮሚያ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ነጋሽ ስሜ እንደገለጹት፥ በክልሉ ከተሞችና ገጠራማ አካባቢዎች ካንሰርና ስኳርን ጨምሮ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች (noncommunicable diseases) እየተስፋፉ መጥተዋል። በክልሉ በሚገኙ የመጀመሪያና ሪፌራል ሆስፒታሎች የሕክምና መሣሪያና መድኃኒትን ጨምሮ የውስጥ ደዌና የቀዶ ሕክምና ሐኪሞች እጥረት መኖሩንም ተናግረዋል።

    ለዚህም አዳማ ሪፈራል ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ግንባር ቀደም መሆኑን ጠቅሰው ኮሌጁ የሰው ሕይወት ለማዳን የሚያስችል እውቅትና ክህሎት ለማስታጠቅ ተግባር ተኮር ስልጠናና ምርምር ሥራዎችን ማከናወን እንደሚገባው አቶ ነጋሽ ጠቁመዋል። ሰልጣኞቹ በቆይታቸው ያገኙትን እውቀት ወደ ተግባር በመተርጎም ማህበረሰቡን በማገልገል ምሳሌ መሆን አለባቸው ብለዋል።

    የአዳማ ሪፈራል ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መኮንን ፈይሳ በማህፀን፣ በውስጥ ደዌ፣ በህፃናትና በከፍተኛ ቀዶ ሕክምና እንዲሁም በጠቅላለ ሐክም ስፔሻልስቶችን እያሰለጠነ ነው፤ ዛሬ ለምረቃ የበቁት 140 የሕክምና ዶክተሮች አሁን በስፋት የሚስተዋለውን አጣዳፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ተናግረዋል።

    በተለይ በክልሉ የመጀመሪያ፣ ስፔሻላይዝድና ሪፌራል ሆስፒታሎች የሚታዩትን የማህፀን፣በውስጥ ደዌ፣ የህፃናትና ከፍተኛ ቀዶ ሕክምና ያለው የከፍተኛ ሙያተኞች እጥረት የሚፈታ ነው ብለዋል – ዶ/ር መኮንን።

    ሰልጣኞቹ በቆይታቸው ለህብረተሰቡ የጠቅላላ ሕክምና አገልግሎት፣ መካከለኛና ከፍተኛ የቀዶ ጥገና ሕክምና በመስጠት ሙያዊ ብቃታቸውን በተግባር ያስመሰከሩ በማለት አስረድተዋል።

    አዳማ ሪፈራል ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ ከ400 በላይ አልጋ ያለው፣ ማስፋፊያ ግንባታ፣ የጥናትና ምርምር ማዕከላት፣የተማሪዎች መኖሪያና መመገቢያ ህንፃዎች ከአንድ ቢሊዮን 300 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በመገንባት ለአገልግሎት ዝግጁ አድርጓል።

    ከተመራቂዎቹ መካከል በከፍተኛ ማዕረግ የተመረቀችው ዶ/ር አያንቱ በቀለ በሰጠችው አስተያየት በአሁኑ ወቅት በሀገራችን አሳሳቢ እየሆነ ያለው ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች እንደሆነ ገልጻ ባገኘሁ እውቀት የድርሻዬን እወጣለሁ በማለት ተናግራለች።

    ከከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች ምርቃት ጋር በተያያዘ፥ ጅማ ዩኒቨርሲቲ 3ሺህ 185 ተማሪዎችን መተመሳሳይ ዕለት አስመርቋል። የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ዶ/ር ጀማል አባፊጣ በምረቃው ሥነ ሥርዓቱ ወቅት እንደተናገሩት “ዛሬ ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂዎች ሀገራችሁ ከእናንተ ከምንግዜውም በላይ እንድታገለግሏት ትፍልጋለች” ብለዋል።

    ዩኒቨርሲቲው ያስመረቀው ከስድስት ኮሌጆች፣ ሁለት ኢንስቲትዩቶች እና ድኅረ ምረቃ ትምህርት ቤት በተለያዩ ሙያዎች ስልጠናቸው ነው። ከተመራቂዎቹ መካከል 834 ሴቶች እንዲሁም 11 የሱማሌላንድና የሩዋንዳ ዜጎች ይገኙበታል። ዩኒቨርሲቲው ከተለያዩ የዓለም ሀገራት የተወጣጡ አንድ መቶ ስልሳ ስምንት ሰዎችን እያስተማረ እንደሚገኝም ተመልክቷል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    አዳማ ሪፈራል ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ

    Semonegna
    Keymaster

    “እኔ ለወገኔ” የወሎ ዩኒቨርሲቲ የበጎ አድራጎት ማኅበር በደሴ ከተማ ድጋፍ አደረገ

    በወሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የተመሰረተው “እኔ ለወገኔ” ማኅበር ድጋፍ ለሚሹ አቅመ ደካሞችና ሕፃናት የአልባሳት ድጋፍ አድርጓል። በቀጣይም አረጋውያንን በማዕከል በማሰባሰብ በቋሚነት የሚጦሩበትና የጎዳና ተዳዳሪ ወጣትና ሕፃናትን ደግሞ ወደ ትምህርት ቤት በማስገባት ለማስተማር ይሠራል።

    ደሴ (ኢዜአ) – በወሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የተመሠረተው “እኔ ለወገኔ” የበጎ አድራጎት ማኅበር ከ700 ሺህ ብር በላይ ግምት ያላቸው አልባሳትና ቁሳቁሶችን አቅመ ደካሞችና ለዳና ተዳዳሪዎችን ጨምሮ ድጋፍ ለሚሹ የደሴ ከተማ ኗሪዎች ድጋፍ አደረገ። የማህበሩ አባላት በተለያዩ የመንግስት ተቋማት፣ ድርጅቶችና ግለሰቦች ያሰባሰቡትን ቁሳቁስ በከተማዋ ለሚኖሩ አቅመ ደካሞችና ሕፃናት አሰራጭተዋል።

    የማኅበሩ አባል ተማሪ አቡሽ ግርማ እንዳለው የዛሬ ሁለት ዓመት የተመሠረተው “እኔ ለወገኔ” ማኅበር ደሴ ከተማ እና በአካባቢው የሚገኙ አቅመ ደካሞችንና ችግረኛ የሕብረተሰብ ክፍሎችን በማገዝ ሥራ ተሰማርቷል። በዚህም ተማሪዎች ከባለሃብቶች፣ ፋብሪካዎችና ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች በማሰባሰብና ጫማ በመጥረግ ሥራ የሚያገኙትን ገንዘብ በመቆጠብ ለ300 አቅመ ደካሞችና የጎዳና ተዳዳሪዎች የካቲት 2 ቀን 2012 ዓ.ም. ድጋፍ አበርትቷል። ድጋፉ የተደረገውም የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች፣ ብርድ ልብስ፣ አንሶላ እና ሌሎች አልባሳት የመሳሰሉት ናቸው። በቀጣይም አረጋዊያንን በማዕከል በማሰባሰብ በቋሚነት የሚጦሩበትና የጎዳና ተዳዳሪ ወጣትና ሕፃናትን ደግሞ ወደ ትምህርት ቤት በማስገባት ለማስተማር እንደሚሠሩ ተናግሯል።

    ሌላው የ3ኛ ዓመት የሥራ አመራር (management) ተማሪ ምትኩ ደጉ በበኩሉ፥ ቁሳቁሱንና አልባሳቱን ማሰባሰብ የተቻለው የትምህርት ጊዜያቸውን በማይነካ መልኩ በመንቀሳቀስ ነው። የኢትዮጵያውያን አኩሪ እሴት ከሆኑት መካከል መረዳዳትና መደጋገፍ መሆኑን በሌሎች ተማሪዎች ዘንድ ለማስረጽ ማኅበር መሥርተው መንቀሳቀሳቸውን አስረድቷል።

    የወሎ ዩንቨርሲቲ አስተዳደርና ተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር አማረ ምትኩ በበኩላቸው፥ ተማሪዎች ከትምህርታቸው ጎን ለጎን የሚያደርጉት የተለያየ በጎ ተግባር የሚደነቅ ነው። ዩኒቨርሲቲዎች በግጭት በሚታመሱበት በዚህ አስቸጋሪ ወቅት የማኅበሩ አባላት ተማሪዎች በአንድ ላይ ሕብረተሰቡን አስተባብረውና የሌሎችን ጫማ ጠርገው ደካሞችን መደጋገፋቸው አርአያነት ያለው ተግባር ነው ብለዋል። አያይዘውም ፕሬዚዳንቱ በትውልዱ እየተሸረሸረ የመጣውን መረዳዳት፣ መተዛዘን እና የተገኘውን ተካፍሎ የመጠቀም ተግዳሮቶች ምላሽ የሰጠ ሊበረታታና ሊስፋፋ የሚገባው መልካም ተግባር እንደሆነ ገልጸዋል። በቀጣይም ተማሪዎቹ ለሚያከናውኑት መልካም ምግባር ዩኒቨርሲቲው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል ገብተዋል።

    የድጋፉ ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል አቶ ጸጋዬ ቢያድግልኝ እንደ ገለጹት፥ ረዳትና ተንከባካቢ ቤተሰብ ስለሌላቸው አንድ ሱሪና ጃኬት ለብሰው ለዓመታት ኖረዋል። በወሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች አማካኝነት ብርድ ልብስ፣ ሱሪ፣ ሸሚዝና ጃኬት በማግኘታቸው እየቀያየሩ በመልበስ ንጽህናና ጤንነታቸውን ለመጠበቅ እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል።

    ምንጮች፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)/ ወሎ ዩኒቨርሲቲ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    እኔ ለወገኔ ወሎ ዩንቨርሲቲ

    Semonegna
    Keymaster

    የኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለቦች የስታዲየም መገንቢያ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተረከቡ

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለቦች የስታዲየም መገንቢያ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ አስረከበ።

    በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ በርካታ ደጋፊዎችን በመያዝና የአዲስ አበባ ከተማ ተወካዮች በመሆን በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ እየሳተፉ ለሚገኙት ለኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለቦች የይዞታ ማረጋገጫ ካርታውን ያስረከቡት የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በንቲ ናቸው። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለሁለቱ ክለቦች ከወራት በፊት የስታድየም እና ሁለገብ የስፖርት ማዕከል መገንቢያ የሚሆኑ የመሬት ይዞታዎችን እንደሚሰጣቸው ቃል ገብቶላቸው ነበር።

    የሁለቱ ክለቦች የቦርድ የሥራ አመራሮች፣ የደጋፊ ማኅበር ተወካዮች፣ የክለቦቹ ደጋፊዎች እና የከተማ  የአስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት በከንቲባው ጽሕፈት ቤት በተካሄደ ሥነ ሥርዓት ላይ ምክትል ከንቲባው ባደረጉት አጠር ያለ ንግግር ሁለቱን ክለቦች መደገፍ እና የከተማዋን አብዛኛውን ወጣቶች ፍላጎት መደገፍ ተገቢ እንደሆነ አስገንዝበዋል። ኢንጂነር ታከለ ኡማ በንቲ እንደገለጹት፥ ሁለቱ ክለቦች የከተማዋ አምባሳደር ከመሆናቸውም ባለፈ በስፖርታዊ ጨዋነት እና በከተማዋ ሁለንተናዊ ሰላምን በማረጋገጥ፣ ወንድማማችነትን በመስበክ የበኩላቸው ሚና እየተወጡ ይገኛሉ ብለዋል። ከዚህ ጋር ተያይዞም ሁለቱ ክለቦች በከተማዋ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች እንዲጎለብት እና ወጣቱ ጊዜውን አልባሌ ስፍራ በመዋል ወይም አልባሌ ሥራ በመሥራት እንዳያሳልፍና እንዲቆጠብ ለሚያርጉት አዎንታዊ ተግባር የከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ኢንጂነር ታከለ ተናግረዋል።

    ‘የከተማው አስተዳደር ከሁለቱ ክለቦች ጋር መሥራት ግዴታው ነው፤ የስታድየም ማስፋፊያ የመሬት ይዞታውን ከመስጠት ባሻገርም ክለቦቹ ለሚያከናውኗቸው ግንባታዎች በመዋዕለ አቅም ለመደገፍም አስተዳደሩ ዝግጁ ነው። ለክለቦቹ ከመሬት ይዞታው በተጨማሪም በአዲስ አበባ ከተማ ስር ከሚገኙ የወጣት ማዕከላት መካከል ሁለት የወጣት ማዕከላትን ለሁለቱ ክለቦች በመስጠት ኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ የስፖርት ክለቦች እንዲያስተዳድሯቸው በስጦታ ለመስጠት ዕቅድ አለው” ብለዋል ኢንጂነር ታከለ።

    የኢትዮጵያ ቡና እና የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ አመራሮችም በበኩላቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተለይ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በንቲ ለስታዲየም መገንቢያ የቦታ ይዞታ መረጋገጫ ከመስጠት ጀምሮ ሌሎች አስፈላጊ ድጋፎችን በማድረጉ በደጋፊዎቻቸው እና በእግር ኳስ ክለቦቹ ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለቦች


    Semonegna
    Keymaster

    ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ከማሳቹሴትስ ኢንስቲትዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ (MIT) በትብብር ለመሥራት ስምምነት አደረገ

    ወልቂጤ (ሰሞነኛ) – ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ አሜሪካን ሀገር ካምብሪጅ ከተማ ከሚገኘው ማሳቹሴትስ ኢንስቲትዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ (MIT) ከተሰኘው ዕውቅ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ጋር በትብብር ለመሥራት የሚያስችል የውል ስምምነት ተፈራረመ።

    ሁለቱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የገቡትን ውል በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ተግባር ለማሸጋገር የሚያስችላቸውን የቅድመ-ዝግጅት ሥራዎች ማከናወንም ጀምረዋል።

    በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚደንት ዶ/ር ሐብቴ ዱላ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው ከማሳቹሴትስ ኢንስቲትዩት ኦፍ ቴክኖሎጂ ጋር የሚኖረው የትብብር ሥራ በዋናነት በኮምፒዩቲንግና ኢንፎርማቲክስ ኮሌጅ የሚሰጡትን የትምህርት ፕሮግራሞች በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በታገዘ የቤተ-ሙከራ ትምህርት ለማስደገፍ የሚያስችልና በመምህራንና በተማሪዎች የሚሠሩትን የምርምር ሥራዎች እና ፕሮጀክቶች ውጤታማነት ለማሻሻል ወሳኝ ሚና ይኖረዋል።

    እንዲሁም የትብብር ሥራው የኮሌጁን የመማር-ማስተማር ሥራ ለማዘመንና ዓለም ዓቀፍ ደረጃውን ለማስጠበቅ የሚያግዘው ከመሆኑም ባሻገር በምርምርና የማኅበረሰብ አገልግሎት፣ በዕውቀት እና በቴክኖሎጂ ሽግግር መስኮች ለሚከናወኑ ሥራዎች ስኬታማነት የላቀ ፋይዳ እንደሚኖረው ዶ/ር ሐብቴ አስረድተዋል።

    በዩኒቨርሲቲው የኮምፒዩቲንግና ኢንፎርማቲክስ ኮሌጅ ዲን አቶ ኮርአብዛ ሸዋረጋ በበኩላቸው እንደተናገሩት፥ ኢንስቲትዩቱ ከዩኒቨርሲቲው ጋር በገባው ውል መሠረት በያዝነው የ2012 የትምህርት ዘመን ከሁለተኛው መንፈቀ-ዓመት /ሴሚስተር/ ጀምሮ ዓመታዊ ክፍያው ከ160 ሺህ በላይ የሆነውን የኦንላይን ትምህርት በነጻ በመስጠት የኮምፒዩቲንግና ኢንፎርማቲክስ ኮሌጅን ተጠቃሚ ማድረግ ይጀምራል። ለዚህም ዕቅድ ተግባራዊነት ኢንሰቲትዩቱ ድጋፍ ሰጪ ቡድን ወደ ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በመላክ ተግባራዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛል።

    በዚህም መሠረት ድጋፍ ሰጪው ቡድን የኦንላይን ትምህርቱን ለመስጠት ወሳኝ የሆኑት የቤተ-ሙከራ ዕቃዎችን ይዞ በመምጣት ለዩኒቨርሲቲው በእርዳታ አበርክቷል። የተበረከቱት ዕቃዎች እስካሁን ድረስ በንድፈ-ሐሳብ /theory/ ብቻ ሲሰጡ የነበሩትን የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ /artificial intelligence/፣ ሮቦቲክስ /robotics/ እና ተዛማጅ የትምህርት ዓይነቶች የማስተማር ዘዴ በተግባር የታገዘ አንዲሆን ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው አቶ ኮርአብዛ ገልጸዋል።

    ድጋፍ ሰጪ ቡድኑ ለዩኒቨርሲቲው ያበረከታቸውን የቤተ-ሙከራ መሣሪያዎችን በአግባቡ ሥራ ላይ ለማዋል ከኮምፒዩቲንግና ኢንፎርማቲክስ ኮሌጅና ከኢንጅነሪንግና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ ለተውጣጡ 10 መምህራን ከጥር 4 ቀን 2012 ዓ.ም. እስከ ጥር 8 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ለአምስት ተከታታይ ቀናት ያዘጋጀውን በኮምፒዩተር ፕሮግራም ቋንቋ አጠቃቀም ላይ ያተኮረ የአሰልጣኞች ሥልጠና በመስጠት ላይ ይገኛል።

    በመጨረሻም ዶ/ር ሐብቴ አክለውም፥ ሁለቱ ተቋማት በጋራ ለመሥራት እንዲችሉ በማገናኘቱ ሥራ በአሜሪካ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልድ ኢትዮጵያውያን ሚና ከፍተኛ እንደነበረ በመግለፅ ይህንን የዜግነት ግዴታቸውን ለተወጡት የዲያስፖራ አባላት በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ እና በራሳቸው ስም አመስግነዋል።

    ምንጭ፦ ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ

    Semonegna
    Keymaster

    በጋሞ ዞን ገረሴ ወረዳ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚውሉ የከበሩ ማዕድናት መገኘታቸውን አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ

    አርባ ምንጭ (አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ) – የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል መንግሥት ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ከኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ኤጀንሲ ጋር በ2010/11 በጀት ዓመት በጋሞ፣ በወላይታና በኮንሶ ዞኖች ያካሄደውን የማዕድን አለኝታ ጥናት ውጤት ታህሳስ 2 ቀን 2012 ዓ.ም. ለባለድርሻ አካላት ይፋ አድርጓል። በመርሀግብሩ ላይ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በጋሞ ዞን ገረሴ ወረዳ ከተሌ ቀበሌ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚውሉ የከበሩ ድንጋዮችና ማዕድናት መገኘታቸውን አስታውቋል።

    በክልሉ የሚገኘውን ማዕድን በዓይነት፣ በመጠንና በቦታ ለይቶ ለክልሉ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ለማሳወቅ ጥናቱ መከናወኑን የዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ ተናግረዋል።

    የዩኒቨርሲቲው ጂኦሎጂ ትምህርት ክፍል መምህርና የጥናት ቡድኑ አባል ረዳት ፕሮፈሰር ጎሳዬ ብርሃኑ እንደገለጹት፥ ጥናቱ በዋናነት ለሴራሚክ ኢንዱስትሪ የሚውሉ የከበሩ ድንጋዮች ላይ ትኩረት በማድረግ የተለያዩ ባለሙያዎችን ባካተቱ 5 ቡድኖች ለ1 ዓመት ያህል የተከናወነ ሲሆን በጥናቱም ከፍተኛ ጥራት ያላቸው “aquamarine”፣ “tourmaline” እና “garnet” የተሰኙ የከበሩ የድንጋይ ናሙናዎች እንዲሁም “feldspar” ማዕድን ውጤታማ ግኝት ተመዝግቧል። “Feldspar” ማዕድን ለሴራሚክ እና ብርጭቆ ኢንዱስትሪዎች ግብዓት የሚሆን ማዕድን ሲሆን በአካባቢው ከ101 ሚሊየን ቶን በላይ ክምችት እንዳለ በጥናቱ ታውቋል።

    የአካባቢው ወጣቶች በመደራጀት አካፋ፣ ዶማና የመሳሰሉትን ባህላዊ መሣሪያዎች ተጠቅመው በተለይም “aquamarine” የተባለውን ማዕድን እያወጡ መሆኑን የጠቀሱት ረዳት ፕሮፈሰር ጎሳዬ፥ ይህም የማዕድኑን ጥራት በከፍተኛ ሁኔታ እየጎዳው ነው ብለዋል። ማዕድናቱ ጥራታቸውን እንደጠበቁ እንዲወጡ የሚመለከተው አካል ለወጣቶቹ ሥልጠና ቢሰጥ መልካም መሆኑን ተናግረዋል።

    በጥናቱ የማዕድናቱ መገኛ፣ ጥራትና ክምችት በሚገባ የተዳሰሰ በመሆኑ የሚመለከተው የመንግሥት አካል አዋጭ የማውጫ ዘዴ በመለየት ማዕድናቱ የሚወጡበትን ሁኔታ ቢያመቻች ኢንዱስትሪውን በከፍተኛ ሁኔታ የሚጠቅምና ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ረዳት ፕሮፈሰር ጎሳዬ ገልጸዋል።

    የምርምር ውጤቱን የማኀበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ እና የዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ ዩኒቨርሲቲውን ወክለው ለኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ኤጀንሲ ተወካይና ለደቡብ ክልል ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ አስረክበዋል።

    ምንጭ፦ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ

    Semonegna
    Keymaster

    ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ጥፋት ፈፅመው በተገኙ 77 ተማሪዎች ተማሪዎች ላይ ዛሬ እርምጃ ወሰደ

    ሐረማያ (ሰሞነኛ) – ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተወሰኑት የአገራችን ዩኒቨርሲቲዎች ሰላማዊ መማር ማስተማርን ለማረጋገጥ አስቸጋሪ ችግሮች እንደጋጠማቸው ይታወቃል። በተለይ በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ያለምንም ምክንያት ውድ የሆነው የሰው ሕይወት በሚያሳዝን ሁኔታ ጠፍቷል።

    ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ይህ እንዳይሆን ጠንካራ እና ሁሉን አቀፍ ቅንጅት በማድረግ ሲሠራ በመቆየቱ የሰው ሕይወት ባያልፍም የጥፋት አላማን አንግበው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ጥቂት ተማሪዎች ግን ሰላማዊ መማር ማስተማር እንዲታወክ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ የዩኒቨርሲቲውን አጠቃላይ ህልውናን ጭምር አደጋ ውስጥ በመክተት የጥፋት ተልዕኮአቸውን ሲያከናውኑ ቆይተዋል። እነዚህ ለጥፋት የተሰማሩ ተማሪዎች ከጥፋታቸው እንዲመለሱና እንዲታረሙ ተደጋጋሚ ምክርና ጊዜ የተሰጣቸው ቢሆንም ከጥፋታቸው ሊታረሙ አልቻሉም።

    በመሆኑም የዩኒቨርሲቲውን ሰላማዊ መማር ማስተማርን ለማስቀጠል እንዲቻል በተለያዩ ጊዜያት በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማር ሥራው እንዲስተጓጎል ምክንያት በሆኑ 77 ተማሪዎች ላይ እርምጃ የተወሰደባቸው ሲሆን ለእርምጃው መወሰድ ምክንያቶች በዋናነት የሚከተሉትን ያካትታል፦

    • በዩኒቨርሲቲው ሰላማዊ መማር ማስተማር እንዳይኖር በተደራጀ ሁኔታ ሰላማዊ ተማሪ ላይ ጥቃት በማድረስ፣ ሕገ-ወጥ ሰልፍ በማደራጀት እና መማር ማስተማር እንዳይካሄድ የተለያዩ እንቅፋቶችን በመፍጠር፣
    • በቡድን ተደራጅተው በማንነት ላይ የተመሠረተ ጥቃት ማድረስ ፣ የማሸማቀቅ እና የማስፈራራት ተግባርን በመፈፀም፣
    • በሕገ-ወጥ ሰልፍ በዩኒቨርሲቲው ንብረት ላይ ውድመት ማድረስ፥ ለምሳሌ፡- ታህሳስ 30 ቀን 2012 ዓ.ም. ከሰዓት በኋላ በዩኒቨርሲቲው የቴክኖሎጂ ተቋም 3 (ሦስት) ተሸከርካሪዎችን አውድመዋል፤ የባንክ ኤቲኤም (ATM) ማሽን ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጪ አድርገዋል፤ ዩኒቨርሲቲው ላይም ከፍተኛ ውድመት እንዲከሰት እሳት አቀጣጥለዋል።
    • የብሔር ግጭት የሚቀሠቅሱ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸውን ንግግሮችን በማጉላት በተማሪዎች መሀከል የስጋት ድባብ እንዲነግስ ማድረግ እና ብሔርን መሠረት አድርጎ ተማሪን በመከፋፈል ትምህርት አቋርጠው እንዲበተኑ ማድረግ ይጠቀሳል።

    በዚሁ መሠረት ሰላማዊ ተማሪዎችን ሕይወት ለመጠበቅና ሰላማዊ የመማር ማስተማሩን ሥራ ለማስቀጠል ሲባል እርምጃ ከተወሰደባቸው አጥፊ ተማሪዎች መካከል 2 (ሁለቱ) ሙሉ ለሙሉ እንዲሰናበቱ የተደረገ ሲሆን 75 ተማሪዎች ደግሞ ለ2 (ሁለት) ዓመት ከትምህርት ገበታቸው እንዲታገዱ ተወስኗል።

    በተጨማሪም ሁለት መምህራን ተማሪዎችን በማስኮብለል ድርጊት ላይ ተሳትፈው በመገኘታቸው በደመወዝ ቅጣትና የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ እንዲደርሳቸው ተደርጓል።

    ዩኒቨርሲቲው ድብቅ ዓላማን አንግበው በተለያዩ ማደነጋገሪያ ሽፋኖች የሚንቀሣቀሱ እና ተቋሙ የጥፋት ዓላማዎች ማራመጃ ሜዳ እንዲሆን ሁኔታዎችን ለማመቻቸት የሚሠሩ ተማሪዎች፣ መምህራን እና የአስተዳደር ሠራተኞች ላይ በቀጣይ የማጣራት ሥራ የሚሠራ ሲሆን፥ እንደጥፋታቸው ደረጃ እና ጥልቀት ሕጋዊ እና ተቋሟዊ እርምጃ ለመውሰድ በቁርጠኝነት እንደሚሠራ እያሳወቅን፥ ዩኒቨርሲቲው የሚያደርገው ጥረት ስኬታማ እንዲሆን ሁሉም ጉዳዩ የሚመለከታቸው እና የሀገራቸው እና የዩኒቨርሲቲያቸው ሰላም የሚያሳስባቸው የአስተዳደር፣ ፀጥታ እና ማኅበረሰብ አካላት እንደተለመደው ከዩኒቨርሲቲው ጐን እንዲቆሙ በአክብሮት እንጠይቃለን። በተጨማሪም የተማሪ ቤተሰቦች ልጆቻችሁን በመምከር እንድታግዙን ዩኒቨርሲቲው ጠይቋል።

    ምንጭ፦ ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ


    Semonegna
    Keymaster

    ወሎ ዩኒቨርሲቲ በተቋሙ በተከሰተ ግጭት ምክንያት ተቋሙን ለቀው የሄዱ ተማሪዎችን በድጋሚ ለመቀበል ዝግጅቱን ያጠናቀቀ ሲሆን የተቋሙ መምህራንም ለተማሪዎች የማካካሻና የማካካሻ ስልጠናዎችን ለመስጠት መዘጋጀታቸው ተገልጿል።

    ደሴ (ወሎ ዩኒቨርሲቲ) – የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን የትርምስ ማዕከል ለማድረግ ጥቅመኞችና የፖለቲካ ቁማርተኞች ገንዘብ የጥፋት ተልዕኮ ፈጻሚ መልምለው መንቀሳቀስ ከጀመሩ ውለው አድረዋል። ይህም የጥፋት ተልዕኮ በአማራና በኦሮሚያ ክልል ያሉ ሁሉንም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለማንኳኳት ሞክሯል። ይህንኑ እኩይ ተግባር እልባት ለመስጠት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኔስተር አጀንዳና ተልዕኮ ቀርጾ በሁለቱ ክልሎች በሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያሉ አካላትን የማወያየት ሥራ ሠርቷል።

    በዚሁ ውይይት በወሎ ዩኒቨርሲቲ በተማሪዎች መካከል የተከሰተው አለመግባባት በእርቀ ሰላም ተፈቶ ወደ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደቱ ተጀምሯል። የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አባተ ጌታሁን በዚህ የይቅርታና የፍቅር መድረክ ‘የሰላም መሠረቱ ይቅርታ ነው፣ በጋራ ስንሆን ብዙ ሀብት ያለን ህብር ነን፣ አባቶቻችን ቋንቋና ሀይማኖት ሳይገድቧቸው ኩርማን ዳቦ ተካፍለው ያስረከቡንን ሀገር ያልኖርንበትን ዘመን ታሪክ በመጥቀስ እርስ በርስ ከሚያጠፋፋና ሀገርን ከሚያፈርስ መጥፎ ታሪክ በመቆጠብ በይቅርታ ሀገርን የማዳን ሥራ መሥራት ይጠበቅብናል’ ሲሉ ገልጸዋል። ታላላቆችን የአማራና የኦሮሞ ሕዝቦች ለማጋጨት ገንዘብ መድበው የሚንቀሳቀሱ አካላት ተማሪዎች መጠቀሚያ መሆን የለባቸውም ያሉት የደሴ ከተማ ከንቲባ አቶ አበበ ገ/መስቀል የከተማ አስተዳደሩ የውጭ ተልዕኮ አንግበው የሚቀሳቀሱ አካላትን ከዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ጋር በመተባበር የተቋሙን ሰላም ለማረጋገጥ እንደሚሠሩ ተናግረዋል።

    የፌደራል መንግሥት ተወካይ የሆኑት አቶ ብሩክ ከበደ በበኩላቸው በወቅቱ እየታየ ያለው ሁኔታ ሀገራችን ኢትዮጵያ በተስፋና በስጋት ውስጥ እንድትሆን አድርጓታል በማለት ሀገር በማፍረስ ላይ የተጠመዱ አካላት ያልኖርንበትን ዘመን ታሪክ እያመገሉ ከሚያጋጩ አካላት እኩይ ሴራ በመጠንቀቅ ኢትዮጵያን እንደ ሀገር የማስቀጠል ታሪካዊ ኃላፊነት እንድወጡ ለተማሪዎች ጥሪ አስተላልፈዋል። አያይዘውም አቶ ብሩክ የፌደራል መንግሥት በአማራና በኦሮሚያ ክልል ያሉ 22ቱም ዩኒቨርሲቲዎች ሰላም እንዲጠበቅና ተማሪዎች በተመደቡበት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመልሰው ገብተው እንዲማሩ እየሠራ እንደሆነ ገልጸዋል። በዚህ የእርቅ ሥነ-ሥርዓት የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ተማሪዎችን ወደ አንድነት የሚያመጡ መልዕክቶችን አስተላልፈዋል። ወሎ ዩኒቨርሲቲ በተቋሙ በተከሰተ ግጭት ምክንያት ተቋሙን ለቀው የሄዱ ተማሪዎችን በድጋሚ ለመቀበል ዝግጅቱን ያጠናቀቀ ሲሆን የተቋሙ መምህራንም ለተማሪዎች የማካካሻ (tutor) ስልጠናዎችን ለመስጠት መዘጋጀታቸው ተገልጿል።

    ምንጭ፦ ወሎ ዩኒቨርሲቲ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ወሎ ዩኒቨርሲቲ

    Semonegna
    Keymaster

    የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ እና አሞሌ ዲጂታል ዋለት ድርጅት የአዲስ አበባ ስታዲየም የትኬት ሽያጭን በጋራ ለማከናወን ስምምነት አደረጉ
    —–

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ)– የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ እና አሞሌ ዲጂታል ዋለት ድርጀት (ዳሸን ባንክ) [Amole Digital Wallet] የአዲስ አበባ ስታዲየም የትኬት ሽያጭን በዘመናዊ መንገድ ለማከናወን የሚያስችላቸውን ስምምነት በተወካዮቻቸው ተፈራርመዋል። በዚህም መሠረት የአዲስ አበባ ስታዲየም የመግቢያ ትኬቶች በሙሉ በአሞሌ የገንዘብ መቀበያዎች ማለትም በሁሉም የፖስታ ቤቶች፣ ሸዋ ሱፐር ማርኬት፣ ህዳሴ ቴሌኮም እና ዳሽን ባንክ (በሁሉም ቅርንጫፎች) እና አሞሌ በሚያዘጋጃቸው ሌሎች ተቋማት የሚከናወን ይሆናል።

    በዚህም መሠረት ስፖርት ክለቡ አዲስ አበባ ስታድየም ውስጥ ለሚያደርጋቸው ውድድሮች የእጅ በእጅ የትኬት ሸያጭ በየትኛዎቹም የስታዲየሙ በሮች እንደማይከናወን ክለቡ አስታውቋል።

    ክለቡ በተጨማሪ እንዳስታወቀው፥ የዓመት የስታዲየም ቅድመ-ክፍያ ሲከፍሉ የነበሩ 289 ደንበኞች አሁንም በቅድሚያ ቦታቸውን ማስከበር የሚችሉ ሲሆን ከዚህ ቀደም ለሁሉም በስታዲየሙ ለሚደረጉ ውድድሮች አጠቃላይ ሲጠየቅበት የነበረው የክፍያ ሂደትም ማስተካከያ ተደርጎበታል። ይህም የዓመት ክፍያ ከሁለቱ የከተማው ቡድኖች የደርሶ-መልስ ውድድር ውጪ የሚፈልጉትን ቡድን የዓመት ክፍያ መክፈል የሚያስችል ማሻሻያን ማድረግ ተችሏል።

    በመሆኑም የዓመት ክፍያው 9,000 (ዘጠኝ ሺህ) ብር ሲሆን ይህም የሁለቱንም ቡድኖች ሙሉ ጨዋታዎችን (30 ጨዋታዎች) ለመመልከት የሚያስፈልግ የብር መጠን ነው። ከዚህ ውስጥ የኢትዮጵያ ቡናን ጨዋታ ብቻ ለመመልከት የፈለገ ተመልካች የ14 ጨዋታዎች 4,200 (አራት ሺህ ሁለት መቶ) ብር የሚከፍል ሲሆን የሁለቱን የከተማው ደርቢ ጨዋታዎችን እንደ ማንኛውም ተመልካች ከአሞሌ የገንዘብ መቀበያዎች ገዝቶ የሚገባ ይሆናል። ከሌሎች የዓመት ክፍያ ከሌላቸው ቅድሚያ የሚሰጣቸው ይሆናል። ሁለቱም የከተማው ቡድኖች ጨዋታዎች በሁለቱ ክለቦች ስምምነት የሚፈፀም ይሆናል።

    በዚህም መሠረት የአዲስ አበባ ስታዲየም የመግቢያ ዋጋ የሚከተለው ይሆናል

    • ክቡር ትሪቡን፦ 300 ብር
    • ጥላ ፎቅ፦ 200 ብር
    • ከማን አንሼ ባለ ወንበር፦ 100 ብር
    • ከማን አንሼ ወንበር የሌለው፦ 50 ብር
    • ካታንጋ፦ 30 ብር
    • ሚስማር ተራ እና የንጋት ኮከብ፦ 20 ብር

    የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብዓመታዊ የክቡር ትሪቢዩን የመግቢያ ትኬቶች ከኅዳር 27 ቀን 2019 ዓ.ም. ጀምሮ ጀምሮ እየተሸጠ ይገኛል።

    ስለ አሞሌ ዲጂታል ዋለት ለማንበብ እዚህ ይጫኑ

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ 

    አሞሌ ዲጂታል ዋለት

    Semonegna
    Keymaster

    ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ የ2012 ዓ.ም. የመማር ማሰተማር ሥራውን በይፋ ጀመረ
    —–

    ቦንጋ ከተማ፣ ከፋ ዞን (ሰሞነኛ) – ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ከመስከረም 24 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ነባር ተማሪዎችን ተቀብሎ የምዝገባ ሂደቱን ካጠናቀቀ በኋላ ጥቅምት 6 ቀን 2012 ዓ.ም. ለ2ኛ እና 3ኛ ዓመት ተማሪዎች የመጀመሪያ መንፈቅ ዓመት ትምህርትን (first day, first class) በይፋ መስጠት ጀምሯል። በዕለቱም የዩኒቨርሲቲው የመ/ማ/ም/ፕሬዝዳንት በመማሪያ ክፍል አካባቢ በመገኘት የመማር ማስተማር ሥራው በአግባቡ መጀመሩን ዞረው የጎበኙ ሲሆን ለተማሪዎችም መልካም የትምህርት ዘመን እንዲሆንላቸው በመግለፅ የመማር ማስተማሩም ተግባር በተያዘለት የጊዜ ገደብ መሠረት እንዲጀምር አስተዋፅኦ ላበረከቱ ለዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብና ባለድርሻ አካላት በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

    ከዚሁ ጋር በተያያዘ የዩኒቨርሲቲው ሴኔት አባላት በ2012 ዓ.ም. የመጀመሪያውን ውይይት አማድረጋቸውን ዩኒቨርሲቲውስ አስታውቋል። የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት የሴኔት አባላትን በማሰባሰብ የ2012 ዓ.ም. የአንደኛ ሩብ አመት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ግምገማ፣ ከተማሪዎችና ከትምህርት ክፍል ቁጥር መጨመር ጋር በተያያዘ በአካዳሚክ ዘርፍ ያለውን መዋቅር ማስፋትን እና የአዲስ ተማሪዎች ቅበላ ዝግጅትን በተመለከተ በሚሉ አጀንዳዎች ላይ ውይይት አድርገዋል።

    በመድረኩም በያዝነው የትምህርት ዘመን ከተማሪዎች ቁጥር እና የትምህርት ክፍል መጨመር ጋር በተያያዘ የአካዳሚክ ዘርፍ መዋቅርን ማስፋት በሚለው አጀንዳ ላይ በመወያየት የየዘርፉን ሥራ ለማሳለጥ የመዋቅሩ መስፋት አስፈላጊ መሆኑን በጋራ በመስማማት ለአምሰቱም ኮሌጆች በምክትል ዲን ማዕረግ የሚሠራ፣ በጥናትና ምርምር ዘርፍና በትምህርት ጥራት ዘርፍም በምክትል ዲን ማዕረግ የየኮሌጆች አስተባባሪ በመሆን እና በሬጅስትራር ዘርፍም በተባባሪ ሬጅስትራር ማዕረግ ተጨማሪ ሰው በመሰየም ሥራው በአግባቡ እንዲሠራ ተወስኗል።

    በመጨረሻም አዲስ የሚመጡ የመደበኛ መርሀ ግብር ተማሪዎችን (freshman students of the regular program) ቅበላ ዝግጅትን አስመልክቶ በቀረበው አጀንዳ ላይ ውይይት ከተደረገ በኋላ እንደተለመደው የተዋጣለትን አቀባበል ለማድረግ የተዋቀሩ ኮሚቴዎች የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ አሳስበዋል።

    ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ለአዲስ ገቢ ተማሪዎች የምዝገባ ጊዜ ከጥቅምት 8 እስከ ጥቅምት 10 ቀን፥ 2012 ዓ.ም. ድረስ እምደሆነ አስታውቋል።

    * Bonga University is one of the Public Higher Education Institution in Ethiopia. It is established with its own legal personality by the Proclamation No. 349/2015 of the Council of Ministers of the Federal Democratic Republic of Ethiopia. It is found in the South Western part of Ethiopia, in the Southern Nations, Nationalities and Peoples (SNNP) region.

    Semonegna
    Keymaster

    ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን የፈረንሳይኛ ቋንቋ አስተምሮ በዲፕሎማ ፕሮግራም ተቀብሎ ለማሰልጠን ተቀማጭነቱ አዲስ አበባ ውስጥ ከሆነው የፈረንሳይ ኤምባሲ ጋር ስምምነት ላይ መድረሱን ዩኒቨርስቲው አስታወቋል።
    —–

    ጎንደር (ኢዜአ) – ጎንደር ዩንቨርሲቲ የፈረንሳይኛ ቋንቋ የስልጠና ማእከል ለመክፈት ከፈረንሳይ ኤምባሲ በኢትዮጵያ ጋር ስምምነት መድረሱን አስታወቀ።

    ጎንደር ዩኒቨርሲቲ በፈረንሳይኛ ቋንቋ ተማሪዎችን በዲፕሎማ ፕሮግራም ተቀብሎ ለማሰልጠን ተቀማጭነቱ አዲስ አበባ ውስጥ ከሆነው የፈረንሳይ ኤምባሲ ጋር ስምምነት ላይ መድረሱን ዩኒቨርስቲው አስታወቋል።

    የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ጽሕፈት ቤት በበኩሉ የስልጠና ማዕከሉ መከፈት ፈረንሳይኛ ተናጋሪ ቱሪስቶችን በቋንቋቸው ለማስጎብኘትም ሆነ በሆቴሎችና በመዝናኛ ስፍራዎች ቀልጣፋ የቱሪስት መስተንግዶ ለመስጠት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ብሏል።

    የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስራት አጸደወይን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እንዳስታወቁት፥ የትምህርት ስልጠናው የሚሰጠው ከኢምባሲው ጋር በመተባበር ነው። ስልጠናውን በተቀናጅ አግባብ ለመስራት ማዕከል ይቋቋማል ያሉት ፕሬዚዳንቱ፥ ማዕከሉን ለመክፈት የሚያስችለው ስምምነት ከኤምባሲው ጋር ጥቅምት 11 ቀን 2012 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ይፈራረማል።

    በሚደረገው ስምምነቱም የፈረንሳይኛ ቋንቋ አስተማሪዎችን ከመመደብ ጀምሮ የማስተማሪያ ግብአቶችን በራሱ ወጪ ለዩኒቨርሲቲው እንደሚያሟላ ገልፀዋል። የማዕከሉ መከፈት ዋና ዓላማ በፈረንሳይኛ ቋንቋ የሰለጠኑ አስጎብኚዎችና የሆቴል አስተናጋጆችን እጥረት ለመቅረፍ እንዲያስችል የታሰበ መሆኑን ተናግረዋል።

    ዩኒቨርሲቲው ከቱሪዝም ትምህርት ክፍሉ ጋር በመቀናጀት ከዚህ ዓመት አጋማሽ ጀምሮ ቋንቋውን በሰርተፊኬትና በዲፕሎማ ደረጃ ለመስጠት ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን አብራርተዋል። ኢትዮጵያና ፈረንሳይ ከ100 ዓመታት በላይ የዘለቀ ዲፖሎማሲያዊ ግንኙነት አላቸው ያሉት ፕሬዘዳንቱ፥ በአፍሪካም ከ20 በላይ ፈረንሳይኛ ተናጋሪ ሀገሮች መኖራቸውን አመልክተዋል።

    የጎንደር ከተማ በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ የአጼ ፋሲል ቤተ-መንግስትና የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ መዳረሻ በመሆኑ በርካታ ቁጥር ያላቸው የፈረንሳይ ቱሪሰቶች ለጉብኝት እንደሚመጡ ተናግረዋል።

    የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ጽህፈት ቤት የህብረተሰብና ቱሪዝም ሃላፊ አቶ ታደሰ ይግዛው እንዳሉት ከሆነ በአካባቢው ካሉት 80 አስጎብኚዎች መካከል የፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ከ2 አይበልጡም።

    በርካታ ፈረንሳይኛ ተናጋሪዎች ፓርኩን ለመጎብኘት እንደሚመጡ የተናገሩት ኃላፊው፥ ዩኒቨርሲቲው ለመክፈት ያሰበው የፈረንሳይኛ ቋንቋ ማሰልጠኛ የፓርኩን የፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪ አስጎብኚ እጥረት እንደሚያቃልል ተናግረዋል።

    የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከፈረንሳይኛ ቋንቋ በተጨማሪ የመጥፋት አደጋ የተጋረጠበትን የግእዝ ቋንቋ ለመታደግ በዚህ ዓመት የግእዝ ቋንቋ ትምህርት ቤት ለመክፈት መዘጋጀቱ በቅርቡ መገለጹ የሚታወስ ነው።

    ምንጭ፦ ኢዜአ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    Semonegna
    Keymaster

    በተማሪዎች አቀባበል ዙሪያ ከባሕር ዳር ከተማ ወጣት ማህበራት ጋር ምክክር ተደረገ

    ባህር ዳር (ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ) – የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮች በ2012 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን ወደ ዩኒቨርሲቲው ለሚመጡ ተማሪዎች አቀባበል በማድረግ ዙሪያ ከዘጠኝ በላይ ከሚሆኑ የባህር ዳር ከተማ ወጣት ማኅበራት ጋር በዩኒቨርሲቲው የጥበብ ህንፃ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ምክክር አደረጉ።

    የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ኢንፎርሜሽን ስትራቴጂክ ኮምንኬሽ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዘውዱ እምሩ እንዲሁም የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደር ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃኑ ገድፍ የባህር ዳር ወጣቶች በዩኒቨርሲቲው ፀጥታ ጉዳይና የተማሪዎችን ደህንነት ከመጠበቅ አንፃር እያበረከቱት ያለውን አስተዋፅኦ አድንቀዋል። አቶ ብርሃኑ አክለውም ዩኒቨርሲቲውም የሥራ ዕድሎችን በመፍጠርና የወጣቶችን አቅም በመገንባት የሚጠበቅበትን እንደሚያደርግ ጠቁመው ወጣቶችም የባህር ዳር ከተማና የዩኒቨርሲቲው ስም በበጎ እዲነሳ አሁንም ከዚህ ቀደም ሲያደርጉት የነበረውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አደራ ብለዋል።

    ከባህር ዳር ከተማ የተወጣጡ የወጣት ማኅበራት ተወካዮች እንደገለጹት፥ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሞባይልና የላፕቶፕ ዘረፋዎች የሚደርስባቸው ተብለው የተለዩ ዋና ዋና የሚባሉ መስመሮች የመንገድ መብራቶቻቸው የጠፉ እና አንዳንዶችም መስመር ሊዘረጋላቸው የሚገባ ስለሆነ ዩኒቨርሲቲው ከመብራት ኃይል እና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን እንዲሠራ ጠይቀዋል። አክለውም፥ ወጣቶቹ በባህር ዳር ከተማም ሆነ በዩኒቨርሲቲው ምንም ዓይነት የፀጥታ ችግር እንዳይኖር ተግተው እንደሚሠሩ ተናግረዋል። በመጨረሻም፥ በተማሪዎች አቀባበል ዙሪያ ለተነሱት ጥያቄዎች በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮች መላሽ ተሰጥቷል።

    ምንጭ፦ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    Semonegna
    Keymaster

    ሰላም ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ለ25ኛ ጊዜ አስመረቀ
    —–

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – ሰላም ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች አሰልጥኖ ሀምሌ 13 ቀን 2011 ዓ.ም አስመረቀ። በያዝነዉ 2011 ዓ.ም ለ25ኛ ጊዜ በቀን እና ማታው መርሀ ግብር ከደረጃ አንድ እስከ ደረጃ አራት ወንዶች 177 ሴቶች 69 በድምሩ 246 ሰልጣኞች፤ እንዲሁም በአጫጭር ፕሮግራም ወንድ 480 ሴት 532 በድምሩ 1012፣ በአጠቃላይ ወንድ 657 ሴት 601 በድምሩ 1258 ሰልጣኞች ተመርቀዋል።

    የሰላም ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ በተለያዩ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ምክንያት ትምህርት በማቋረጣቸዉ እና የ10ኛ ክፍል ትምህርትን ባለማጠናቀቃቸዉ በመንግስት የተቀመጠዉን ዝቅተኛዉን መግቢያ መመዘኛ ማሟላት ባለመቻላቸዉ በመደበኛ ስልጠና ፕሮግራም መግባት ለማይችሉ አጫጭር ስልጠና እየሰጠ ይገኛል። ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበርና ድጋፍ በማግኘት የሚሰጣቸዉ አጫጭር ስልጠናዎች አንዱ Save the Children እና SNV ከተባሉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የሴቶችና የወጣቶች የኑሮ ደረጃ ማሻሻል ላይ ያተኮረ Livelihood Improvement of Women and Youth/LI-WAY/ የተሰኘ ፕሮጀክት በመቅረፅ በልብስ ስፌት፣ ምግብ ዝግጅት እና በተለያዩ የቴክኒክ እና ሙያ የስልጠና ዘርፍ ያሰለጠናቸዉን የመጀመሪያ ዙር አስመርቋል።

    በምርቃቱ መርሀ ግብር ላይ የፌደራል ቴክኒክ ሙያ ትምህርት እና ስልጠና ኤጀንሲ ዳይሬክተር አቶ ጌታቸዉ ነጋሽ፣ የጃፓን አምባሳደር በኢትዮጵያ ሚስተር ዳይሱኬ ማትሱናጋ (Daisuke Matsunaga)፣ የሰላም ሕፃናት መንደር መሥራች ወ/ሮ ፀሀይ ሮሽሊ (Tsehay Röschli)፣ ከሰላም ጋር የሚሠሩ አጋር ድርጅቶች ተወካዮች፣ የሰላም ቦርድ አባላት እና ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት በደመቀ ሁኔታ ተከብሯል።

    በዕለቱ የማነቃቂያ ንግግር በአቶ ደምረዉ መታፈሪያ የተደረገ ሲሆን በመርሀ ግብሩ የተለያዩ የሰላም የአጋር ድርጅቶች ንግግር አድርገዋል። በተጨማሪም በስልጠናዉ ዘርፍ የላቀ ዉጤት ላስመዘገቡ ሰልጣኞች እና አሰልጣኞች ሽልማት ተሰጥቷል። በመርሀ ግብሩ ማጠቃለያ የፎቶ ፕሮግራም እና ችግኝ በመትከል ፕሮግራሙ ተጠናቋል።

    ምንጭ፦ ሰላም የሕፃናት መንደር

    Semonegna
    Keymaster

    ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ተቀብሎ ያሰለጠናቸውን 198 ተማሪዎች ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ አስመረቀ
    —–

    ፍቼ (ሰሞነኛ) – ሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ተቀብሎ ያሰለጠናቸውን 198 ተማሪዎች ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ቅዳሜ ሀምሌ 6 ቀን 2011 ዓ.ም በታላቅ ድምቀት አስመርቋል። በምርቃት ሥነ-ስርዓቱ ላይ የተለያዩ ጥሪ የተደረገላቸዉ እንግዶችና ከፍተኛ ባለስልጣናት ተገኝተዋል።

    በምርቃት መርሀግብሩ ላይ የተገኙት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ ለተመራቂዎች ባስተላለፉት መልዕት ‛ከጀግናው ጀነራል ታደሰ ብሩ መገኛና ከየዋኋ እናት አበበች ጎበና አገር የምትመረቁ ተማሪዎች በጀግንነት ሀገርን ማሻገር፣ በየዋህነት ሁሉን ማቀፍ መርሀችሁ ሊሆን ይገባል’ ብለዋል።

    የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት በበኩላቸው ‛መማር ለራስ ብቻ መኖርና መለወጥ ሳይሆን ለሀገራችን ህዝብ ችግር መፍትሄ መፈለግ ነው’ በማለት የዕለቱ ተመራቂዎች የሀገራቸውን ችግር የሚፈቱ ብርቱ ዜጎች እንዲሆኑ አበክረው ተናግረዋል።

    የዕለቱ የክብር እንግዳም በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ዘርፍ አስተባባሪ የሆኑት ዶ/ር ግርማ አመንቴ ሲሆኑ በዕለቱ ባስተላለፉት መልዕክት ‛በዓለም ላይ ያለምንም ድንበር ከሀገራችሁ ጀምሮ በየትኛዉም ቦታ የመሥራትና ማንኛዉንም ዕድሎች በመለየትና በመጠቀም በምክንያታዊነት፤ ከስሜታዊነት የወጡ ዉሳኔዎችን በመዉሰድ ለዓለም ትልቅ አስተዋጽኦ የምታደርጉ ዜጎች ለመሆን ራሳችሁን ማዘጋጀት ይጠበቅባችኋል’ ብለዋል።

    ዩኒቨርሲቲው ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ ለሦስት ዓመታት በሁለት ኮሌጆች፥ ማለትም በቢዝነስና ኢኮኖሚክስ እንዲሁም በእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጆች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች በታላቅ ድምቀት አስመርቋል።

    በምርቃት ሥነ-ስርዓቱ ላይ የተለያዩ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና ከፍተኛ ባለስልጣናት ተገኝተዋል።

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    Semonegna
    Keymaster

    የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎቻቸውን አስመርቀዋል
    —–

    አዲስ አበባ – የተለያዩ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠኗቸውን ተማሪዎቻቸውን ሰኔ 22 ቀን 2011 ዓ.ም. አስመርቀዋል።

    በዕለቱ ተማሪዎቻቸውን ካስመረቁ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥም የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ፣ ጅማ ዩኒቨርሲቲ፣ ወለጋ ዩኒቨርሲቲ፣ መቱ ዩኒቨርሲቲ፣ ዲላ ዩኒቨርሲቲ እና አሶሳ ዩኒቨርሲቲ ይገኙበታል።

    የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በተለያየ የትምህርት መስክ ያሰለጠናቸውን 1 ሺህ 313 ተማሪዎቹን በዕለቱ አስመርቋል። ከተመረቁት ውስጥም 1 ሺህ 112 በቅድመ ምረቃ መርሃ ግብር (በመጀመሪያ ዲግሪ) ያስመረቀ ሲሆን፥ 201 ተማሪዎችን ደግሞ በድህረ ምረቃ መርሃ ግብር ነው ያስመረቀው።

    ጅማ ዩኒቨርሲቲም በዕለቱ በመጀመሪያ ዙር ዩኒቨርሲቲ በተለያየ የትምህርት መስክ ያሰለጠናቸውን 2 ሺህ 683 ተማሪዎቹን አስመርቋል። ከእነዚህም ውስጥ 341 በድህረ ምረቃ ሲሆን፥ 1 ሺህ 11 ደግሞ ሴቶች መሆናቸው ታውቋል።

    በተመሳሳይ ዲላ ዩኒቨርሲቲም በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን 4 ሺህ 726 ተማሪዎቹን በዕለቱ አስመርቋል። በዲላ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች የምረቃ በዓል ላይ የተገኙት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስተር ዲኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ፥ በዘንድሮው ዓመት በመላው ሀገሪቱ ከ175 ሺህ በላይ ተማሪዎች እንደሚመረቁ አንስተዋል። ተመራቂ ተማሪዎች ለሀገራቸው የሚሰሩ ሊሆኑ እንደሚገባም ፕሮፌሰር አፈወርቅ መልእክት አስተላልፈዋል። ዲላ ዩኒቨርሲቲ በዕለቱ ካስመረቃቸው ተማሪዎቹ ውስጥ 500 ተማሪዎችን በሁለተኛ ዲግሪ ነው ያስመረቃቸው።

    ወለጋ ዩኒቨርሲቲም በዕለቱ በተለያየ የትምህርት መስክ ያሰለጠናቸውን 3 ሺህ 682 ተማሪዎቹን በዕለቱ አስመርቋል። ከተመረቁት ተማሪዎች ውስጥ 2 ሺህ 139 ሴቶች ሲሆኑ 1 ሺህ 543 ደግሞ ወንዶች መሆናቸው ተገልጿል። በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲው 295 ተማሪዎችን በሁለተኛ ዲግሪ ያስመረቀ2 ሲሆን፥ 8 ተማሪዎችን ደግሞ በ3ኛ ዲግሪ ወይም በዶክትሬት ዲግሪ አስመርቋል።

    መቱ ዩኒቨርሲቲም በተለያየ የትምህርት መሰኮች ሲያሰለጥናቸው የነበረውን ከ2 ሺህ 300 በላይ ተማሪዎቸ በዛሬው ዕለት አስመርቋል። በምረቃ ሥነ-ስርዓት ላይ የተገኙት ግብርና ሚኒስተር ዲኤታና የመቱ ዩኒቨርሰቲ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሳኒ ሬዲ መንግስት ለሰው ሀብት ልማት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥው እየሠራ ባለበት መመረቃቸውንና ከተመራቂ ተማሪዎች የሚጠበቀው ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል።

    የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ተካልኝ ቃጄላ በበኩላቸው፥ ዩኒቨርሲቲው በዚህ ዓመት ብዙ ፈታኝ የሆኑ የውስጥና የውጭ ተግዳሮቶችን አልፎ ለዚህ መብቃቱን አስታውሰዋል።

    በተመሳሳይ አሶሳ ዩኒቨርሲቲ 2 ሺህ 714 ተማሪዎችን በተለያዩ የትምህርት መርሓ ግብሮች አስመርቋል። ከነዚህ ውስጥ 930 ሴት ተመራቂዎች መሆናቸው ታውቋል። ዩኒቨርሲቲው አሁን ለ6ኛ ጊዜ እያስመረቀ ሲሆን ከተመሰረተበት ከ2004 ዓም ጀምሮ አጠቃላይ 12 ሺ 450 ተማሪዎችን አስመርቋል። በዕለቱ በተካሄደው የምረቃ ሥነ-ስርዓት ላይ የሳይንስ እና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያምን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች ተገኝተዋል። ፕሮፌሰር ሂሩት ኢትዮጵያ ካለችበት ሁኔታ እንድትወጣ የተማረው ሀይል ዋነኛ አካል ነው ብለዋል።

    ምንጭ፦ ኤፍ.ቢ.ሲ

Viewing 15 posts - 106 through 120 (of 132 total)