Search Results for 'አማራ ክልል'

Home Forums Search Search Results for 'አማራ ክልል'

Viewing 15 results - 46 through 60 (of 120 total)
  • Author
    Search Results
  • Anonymous
    Inactive

    አዲስ አበባ በራሷ ግዛተ-መሬት ላይ የፌዴራል አድያምነት /ክልልነት/ መብት ሊረጋገጥላት ይገባል!
    ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ

    የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አወቃቀር በመመዘኛዎቹ ላይ በኢትዮጵያ ተፃራሪ አቋም ባላቸው ልሂቃን ዘንድ ስምምነት ላይ ሊደርስ ቢችል፣ ፌዴራላዊ የመንግሥት አደረጃጀት የፖለቲካ አለመግባባት መንስ ዔ ሊሆን የሚችል አልነበረም። ይህ ጥያቄ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግር ዋነኛ መገለጫ ሊሆን የበቃው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ልሂቃን በዚህ ጥያቄ ዙሪያ ላለፉት ሃምሳ ዓመታት ሊግባቡ ባለመቻላቸው ነው። ሊግባቡ ያልቻሉበትም ምክንያት በኢትዮጵያ ሀገረ-መንግሥት የግንባታ ታሪክ ላይ ልዩነታቸውን ማጥበብ ባለመቻላቸው ነው። ይህ ትውልድ ደግሞ በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት በ1940ዎቹ ዓመታት ተወልዶ በ1950ዎቹ መጨረሻና በ1960ዎቹ መጀመሪያ ላይ ለዩኒቨርሲቲ ደረጃ የደረሰው ትውልድ ነበር። እንደ አጋጣሚ ሆኖ በ1960ዎቹ ሁኔታ ደግሞ ዓለም በሁለት ተፃራሪ የካፒታሊዝምና የሶሻሊዝም ጎራዎች ፉክክር ተቀስፋ ተይዛ የነበረችበት ወቅት ነበር። በ1960ዎቹ ለጉልምስና ከደረሰው ትውልድ ውስጥ አብዛኛው ነው ባይባልም ተራማጅ የሆነ አስተሳሰብ አለኝ ብሎ ያቀነቅን የነበረው የትውልዱን የአመራር ሚና የተጫወተው የማርክሲዝም ሌኒኒዝም (Marxism–Leninism) አስተምህሮ የተቀበለው ነበር።

    ይሁንና የዚህ የ1960ዎቹ የተማሪ አብዮተኞች እና የ እ ነሱ ከፊል ውጤት ሆነው ያቆጠቆጡት የነገድ ድርጅት መሪዎች የኢትዮጵያን ታሪክ በተፃረረና ባልተገናዘበ ሁኔታ የሶቭየት ሕብረትን የኮሚኒስት ፓርቲ መሪ የስታሊንን “የብሔርና የቅኝ ግዛት ጥያቄ” መጽሐፍ ቃል በቃል በመገልበጥ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ዋነኛ ችግር “የጨቋኝና የተጨቋኝ ብሔረሰቦች መስተጋብር ነው” የሚል የሀሰት የታሪክ ትርክት ይዘው ተነሱ። እነዚህ ከተማሪ አብዮተኝነት ወደ ነገድ ድርጅትነት የተሸጋገሩት ከደርግ መንግሥት ጋር ለ17 ዓመታት ጦርነት አድርገው በታሪካዊ የኢትዮጵያ ጠላቶች ያላሰለሰ ድጋፍ በ1983 ዓ.ም በኢትዮጵያ ጦር ላይ ድል ሊቀዳጁ በቁ። አነዚህ ኃይሎች በተጠናወታቸው “የጨቋኝና የተጨቋኝ ብሔረሰቦች” የሀሰት ትርክት ውጤት የሆነውን የመገንጠል መብት ሕገ-መንግሥታዊ መብት ያደረገ፣ ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ ያለመ ቋንቋን መሠረት ያደረገ መንግሥታዊ የፌዴራል አወቃቀር በኢትዮጵያ ላይ አነበሩ።

    በሀገራችን ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ የጐሳና የዘረኝነት ፖለቲካዊ አደረጃጀት የመንግሥት የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ አደረጃጀት ዓይነተኛ መገለጫ ከመሆን አልፎ ይኸው ዓይነት አደረጃጀት  ወደ እምነት ተቋማት ሳይቀር ዘልቆ እንዲገባ ተደረገ። በሀገሪቱ ታሪክ በማይታወቅ ሁኔታ በተረኝነት መንፈስ የተቃኘ ተቋማዊ/መንግሥታዊ ሙስና እና የፍትህ መዛባት የሥርዓት መገለጫ ሊሆን በቃ። ከሕዝቡ ታሪካዊ አሠራር ጋር ባልተገናዘቡ የክልል አደረጃጀቶች ምክንያት በሀገራችን እንግዳ በሆነ መልኩ ማንነትን እና እምነትን መሠረት ያደረጉ ግጭቶች እንዲበራከቱ፣ ሕዝብ የተረጋጋ ሕይወት እንዳይኖረው በፌዴራል መንግሥቱና በክልል መንግሥታት መካከል የኃላፊነትና የተጠያቂነት ጉዳይ አሻሚ በማድረግ፣ የሀገሪቱ ብሔራዊ ስሜት እንዲላሽቅ በምትኩ ጠባብና ክልላዊ አስተሳሰብ እንዲሰፍን ተደረገ። በኢትዮጵያ የዘውግ ፌዴራሊዝም ሥርዓት ችግር ብሔረሰብን ዋነኛው የፌዴራል ሥርዓቱና የሀገር መንግሥት ግንባታ መሠረት ማድረጉ ነው።

    እዚያው ተወልዶ ያደገውና ከአራቱም የኢትዮጵያ ማዕዘናት የመጣውን የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ አንድ ብሔረሰብን እና አንድ ቋንቋ ተናጋሪነትን መሠረት አድርጎ በተዋቀረ ክልል ውስጥ አስገብቶ እንዲተዳደር ማድረግ  ፍትሃዊነት የለውም። የአዲስ አበባ ሕዝብ ጥያቄ ከራሴ ውጭ በእኔ ዕጣ ሌላ ሊወስንብኝ አይገባም የሚል ነው። አዲስ አባባ በኦሮሚያ ምድረ ፅፋዊ (geographic) ክልል ውስጥ በመገኘቷ ብቻ ለአዲስ አበባ ባለቤትነት የመብት መብለጫ፣ ለተፈጠረ ውጥንቅጥ ደግሞ የአዲስ አበባ ሕዝብን መብት ማሳነሻ ማድረግ በምንም መመዘኛ ተገቢነትም ሆነ ተቀባይነት የለውም።

    የኢፌዲሪ ሕገ-መንግሥት በአንቀጽ 69 “የፌዴራሉ መንግሥት ርዕሰ ከተማ አዲስ አበባ ነው። የከተማው አስተዳደር ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ ሥልጣን ይኖረዋል። ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል” ይላል። የአዲስ አበባ ከተማ ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ ሥልጣን እንዳለው ቢታወቅም የህወሓት እና የኦነግ በሆነው ሕገ-መንግሥት ውስጥ “በአዲስ አበባ ከተማ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ጥቅም ይኖረዋል” በሚል መካተቱ ችግሩን ሆን ተብሎ እንዲወሳሰብ አድርጎታል።

    በ1989 ዓ.ም የወጣው የአዲስ አበባ ከተማ አስተደደር ማቋቋሚያ ቻርተር መሠረት አዲስ አበባ ራሷን በራሷ እንድታስተዳድር ሲደነገግ፣ በሕገ-መንግሥቱም ሆነ በአዲስ አበባ ከተማ ቻርተር መሠረት የከተማዋ ስምና ስያሜ አዲስ አበባ እንደሆነ ተደንግጓል። ይሁንና ቻርተሩን መሠረት በማድረግ ተዘጋጅቶ የቀረበው ረቂቂ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ የመጽደቅ ሂደቱ በደባ እንዲቀር ተደርጓል። አዲስ አበባ እንደ ዋሽንግተን ዲሲ እና እንደ ካንቤራ (Washington, DC and Canberra) የፌዴራል መንግሥት ግዛት ናት የሚል የሕግ አንቀጽ የለም። ይህ አይደለም እንዳይባል በወንጀልም ሆነ በፍትሀ-ብሔር ጉዳይ በአዲስ አበባ የግዛት ክልል ውስጥ የተፈፀመ ወይም የተከናወነ የሕግ ጥሰት ግን ልክ የፌዴራል መንግሥት ይዞታ አንደሆነችው ዋሽንግተን የመዳኘት ሥልጣንን ለፌዴራል መንግሥቱ ይሆን ዘንድ በሕግ ተለይቶ ተሰጥቷል። ማለትም በተግባር የፌዴራል መንግሥቱ አዲስ አበባን እና ድሬደዋን የራሱ ግዛት አድርጓቸዋል።

    ሕገ-መንግሥቱ አዲስ አበባ እራሱን የማስተዳደር ሙሉ ሥልጣን የሰጠው መሆኑ ከላይ የተጠቀሰው የወንጀልና የፍትሀ-ብሔር ጉዳዮችን ለመዳኘት ከተሰጠው ሥልጣን ጋር ሲዳመር አዲስ አበባ ልክ እንደ ዋሽንግተን የፌዴራል ግዛት እንደሆነች ለመረዳት ይቻላል። በተጨባጭ ግን አዲስ አበባ ከተማ የተተወላት የከተማ-ነክ አስተደደርና ከማዘጋጃ ቤት አገልግሎት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን የመዳኘት ሥልጣን ነው። ማለትም ስለ ዳኘነት ሲሆን መሬቱ የፌዴራል መንግሥት፣ ስለ ሌሎች አስተዳደራዊ ጉዳዮች ሲሆን የከተማ መስተዳድሩ ሆኗል።

    አዲስ አበባ ራሷን የማስተዳደር መብት በሕገ-መንግሥቱ የታወቀ ቢሆንም፤ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ጭምር ኢ-ፍትሀዊ በሆነ መንገድ ውክልና የላትም። ሕገ-መንግሥቱ ከሚደነገገው ውጭ ስትደዳደር የቆየችው በህወሓት/ኢህአዴግ፣ አሁን ደግሞ በኦህዴድ/ብልጽግና ነው። በሌሎች ክልሎች ክልሎችን የሚያስተዳድሩ የክልል ፓርቲዎች አሉ /ትግራይ፣ ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብ ወዘተ…/ አዲስ አበባ ላይ ግን የሚወክላት የፖለቲካ ፓርቲ የለም። ገዥ ፓርቲዎች ፍላጎታቸውን የሚጭኑባት ከተማ ናት። ቀደም ሲል ህወሓት/ኢህአዴግ አሁን ደግሞ ኦህዴድ/ብልጽግና ፓርቲ አዲስ አበባን ማስተዳደሩን ቀጥሎበታል። ይህ ሁኔታ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በሕገ-መንግሥቱ የተሰጣቸውን ራሳቸውን የማስተዳደር መብት ፍፁም የሚጥስ ነው።

    አዲስ አበባን እንዲመራ የሚመደበው በገዢው ፓርቲ ውስጥ ከነበሩ ወይም ካሉ የክልል ገዢ ፓርቲዎች እንጂ በከተማው ሕዝብ ነፃ ምርጫ አልነበረም፤ አሁንም አይደለም። አዲስ አበባ ቀደም ሲል ከሁለቱ ክልሎች /ትግራይኦሮሚያ/ አሁን ከ “ለውጡ” ወዲህ ደግሞ ከኦሮሚያ ክልል በሚመጡ ተሹዋሚዎች እንድትደዳደር መደረጉ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ጥቅምና ፍላጎት እንዳይከበር ያደረገ የፖለቲካ ደባ ነው። ከዚህም ባሻገር ከ7 ሚሊዮን የሚልቀውን የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ በኢኮኖሚ እንቅስቃሴው በግብር መልክ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ለመንግሥት ካዝና የሚያስገባውን ነዋሪ የፖለቲካ ባይተዋር ያደረገ እና በዕጣ ፈንታው ላይ  እንዳይወስን ያደረገ ኢ-ፍትሀዊ የሆነ የፖለቲካ አካሄድ ነው። የአሜሪካን አብዮት እንደቀሰቀሰው /Taxation without Political Representation/ እንደሚለው መፈክር ሠርቶ ግብሩን እየገበረ የፖለቲካ ባይተዋር በማድረግ በዕጣ ፈንታው ላይ እንዳይወስን አድርጎታል። ይህ ፍትሀዊ ያልሆነ የፖለቲካ አካሄድ ከመሆኑም በተጨማሪ በግልጽ የሕገ-መንግሥቱን አንቀጽ 49 እና አንቀጽ 89 ይጥሳል።

    የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት ትልቁ ወለፈንዲ የአዲስ አበባ ጉዳይ ነው። በአንቀጽ 69 መሠረት የአዲስ አበባ ከተማ የፌዴራሉ ርዕሰ ከተማ እና የከተማው ነዋሪ ሕዝብ እራሱን በራሱ የማስተዳደር መብት ይኖረዋል ሲል ደንግጓል። ማለትም፥ አዲስ አበባ የተወላጆቿና እና የሁሉም ከ80 በላይ የሆኑት የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች በባለቤትነት የሚኖሩባት ከተማ ናት። የአዲስ አበባን አስተዳደር ስንት አማራ፣ ስንት ኦሮሞ፣ ስንት ትግሬ፣ ስንት ጉራጌ፣ ስንት ወላይታ፣ ስንት ሱማሌ፣ ስንት አደሬ፣ ስንት ጋምቤላ፣ ስንት ቤንሻንጉል፣ ስንት ማኦ ወዘተ… እንደሚኖሩባት በተጨባጭ የተረጋገጠ አሃዛዊ መረጃ (statistics) ስለሌለ የአዲስ አበባ ባለቤትነት ሊሰጥ የሚችለው ከሕገ-መንግሥቱ መንፈስ ውጭ ለመላ ቋሚ ነዋሪዎቿ ነው ሊሆን የሚችለው። ይሁንና የአዲስ አበባን ከተማ ባለቤትነት በተመለከተ እንደ ሌሎች የፌዴራል መንግሥት ዋና ከተማዎች እንደሆኑት እንደ ሞስኮ፣ በርሊን፣ ቪየና እና ብራስልስ ለፌዴራል መንግሥት ተጠሪ ያልሆኑ፣ በኢትዮጵያም ከ1983 ዓ.ም ሰኔ ወር ጀምሮ ሕገ-መንግሥቱ ተግባራዊ እስከ ተደረገበት 1987 ዓ.ም ነሐሴ ወር ድረስ ክልል 14 ተብላ የክልልነት ደረጃ የተሰጠበትን ሁኔታ መልሶ ተግባራዊ ማድረግ  ፍትሃዊ እና የነዋሪዎቿን ሕጋዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ነው።

    አዲስ አበባ እንደ ፌዴራል መንግሥት ርዕሰ ከተማነቷ የግዛተ-መሬቷ ባለቤትነትን ለፌዴራል መንግሥቱ ሳይሆን በሽግግር ወቅት እንደነበረው በፌዴራል አድያምነት /በክልልነት/ ደረጃ እንደገና እንድትዋቀር ባልደራስ እውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) ለከተማዋ ሕዝብ ጥሪውን ያቀርባል።

    ከሀገራችን ዘመናዊ የታሪክ ጅማሮ ጋር የተሰናሰለ እድሜ ያላት አዲስ አበባ ከተማ፥ በመልክ-ዕምድር አቀማመጧ የሀገሪቱ እምብርት ላይ መገኘቷ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታዋን የጎላ አድርጓታል። ይህ ሁኔታዋ ለሀገራችን ዜጎች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ለመስጥ የሚያስችል አቅም ያላት ከተማ እንድትሆን ሰፊ ዕድል ሰጥቷታል። ነገር ግን ከተማዋ ያላትን ሰብዓዊና ቁሳዊ አቅም አሟጣ በመጠቀም ለነዋሪዎቿ ተስፋ መሆን እንዳትችል በሀገራቸን የነበሩ እና ያሉት ገዢዎች አተያይ እና የአመራር ፈሊጥ ትልቅ ተግዳሮት ሆኗል። “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ ጎሳን መሠረት ያደረገው የባለፉት 30 ዓመታት የሀገራችን ፖለቲካን ያነበረው ሥርዓት የአዲስ አበባ ከተማን ህልውና የበለጠ ተፈታትኖታል፤ ከባድ አደጋንም የፈጠረ ሆኗል።

    አዲስ አበባ የሀገራችን ርዕሰ መዲና ከመሆኗ ባሻገር፣ የአፍሪካ ሕብረት እና የጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ተምሳሌትና መናኸሪያ፣ የትላልቅ ዓለም አቀፍ ተቋማት መታደሚያ ናት። የሀገራችን 65% ምጣኔ-ሀብት በአንበሳ ድርሻነት ይዛለች፤ በሀገሪቱ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ቤተ-እምነቶች እና የእምነቱ ተከታዮች ተቻችለው የሚኖሩባት የአብሮነት መገለጫ ከተማ ስትሆን፥ የታሪካችን መገለጫ የሆኑ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርስ እና ትውፊት የተመዘገበባት፣ እንዲሁም የተለያዩ ቋንቋዎችና ባህሎች ሕብር ፈጥረው በነፃነት የሚንጸባረቁባት የኢትዮጵያ ብዝሃነት ማሳያ ፈርጥ ናት።

    ከተማችን አዲስ አበባ ባለፉት 3 አስርት ዓመታት ሲመሯት የነበሩት ሁሉ ምን ልጠቀምባት እንጂ ምን ላድርግላት የሚል ኃላፊነት የሚሰማቸው ባለመሆኑ ችግሮቿን የተወሳሰቡ አደርጎታል። እንደ ፓርቲያችን እምነት፥ ለዚህ ችግር በዋነኝነት ያጋለጣት በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠ አስተዳድር ተሰይሞ ሊያስተዳድራት አለመቻሉ ጉልህ ስፍራ ይይዛል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን በከንቲባነት ሲመሩ የቆዩት ግለሰቦች በአብዛኛው የከተማውን ነዋሪ ሥነ-ልቦና በቅጡ ያልተረዱ፣ ራዕይ-አልባ የሆኑ እና ከፍተኛ የብቃት ጉድለት የሚስተዋልባቸው ናቸው።

    አዲስ አበባ ከተማ ራስ ገዝ (በአሁኑ አጠራር ክልል) እንድትሆን መሆኑ እውነተኛ ፌዴራላዊ አስተዳደር በኢትዮጵያ ውስጥ ለማንበር በሚደረገው ጥረት ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ያምናል፤ በመሆኑም አዲስ አበባ ራስ ገዝ አስተዳደር እንዲኖረው በላቀ መንገድ መታገል አስፈላጊ ሆኗል።

    የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ላለፉት ዘመናት በተለይም የህወሓት/ኢህአዴግ ሥልጣን ዘመን ጀምሮ በመረጠው የመተዳደር መብቱን ተነፍጎ፣ ከኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ኦህዴድ በውክልና ተቀብሎ አስተዳድራለሁ በሚል የተረኝነት፣ የሙስና፣ የባህል በአጠቃላይ የዘረኝነት ሰለባ ሆኗል። የተረኛነት ስሜት ነቀርሳ የሆነበት ኦህዴድ/ብልጽግና የአዲስ አበባን ሕዝባዊ አውቃቀር (demography) ከመቀየር ጀምሮ ተጠንቶ የከተማው ሕዝብ ባልመከረበት የትምህርት ሥርዓት ውስጥ ረጅም እጁን ሕገ-ወጥ በሆነ መንገድ በመስደድ፣ የከተማውን መሬት በማስወረር እና ነዋሪው ጥሮ ግሮ ቆጥቦ የሠራውን ቤት አንዴ ለኦሮሚያ የመንግሥት ሠራተኞች በሚል ሌላ ጊዜ ደግሞ የተለየ ምክንያት በመስጠት እየዘረፈ  መሆኑ የከተማዋን ነዋሪ በደል ጫፍ አድርሶታል።

    ዛሬ ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞካራሲ ፓርቲ ይህንን የዘመናት የአዲስ አበባ ሕዝብ ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ መብቱን የሚጠይቅበት ጊዜ ላይ መድረሱን ተገንዝቧል። በኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ፍትህ ማግኘት የሚቻለው የከተማው ነዋሪ ራሱ የመረጠው ሥርዓት ሲዘረጋ መሆኑን በቅርቡ ተረድቷል። አሁን እየደረሰበት ያለው ግፍ መነሻው ለሕዝብ ተጠያቂነት ያለው ትክክለኛ አስተዳደር አለመኖሩና ይህንን ተገን በማድረግ ወደ ዝርፊያ የገቡና ለዚሁ ሁኔታ እንዲያመቻቸው ብቻ የሚሠሩ የውክልና መሪዎች በመሆናቸው ከእነዚህ አስተዳደር ውጭ እንዲሆን ለማስቻል ዴሞክራሲን ለማስፈን እንዲረዳ ነው።

    ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ አዲስ አበባ ከተማ ራስ ገዝ እንድትሆን ብዙ ዜጎች ጥያቄ ሲያነሱ እንደነበረ ያምናል። ይህ የከተማው ነዋሪ ጥያቄም፣ ፓርቲው እንዲመሠረት ገፊ ምክንያት እንደሆነ በመገንዘብ፣ ትላንት ዜጎች ሲያነሱት የነበረው ጥያቄ ወደላቀ ምዕራፍ መሸጋገሩን በማብሰር፤ የአዲስ አበባ ሁለንተናዊ ችግር አስጨንቋቸው እና እንቅልፍ ነስቷቸው ለነበሩ ዜጎች ሁላ ይህ የእናንተ የትላንትና የትግል ጥያቄ በመሆኑ ከፍ ያለ ምስጋና ይገባችኋል። የዜጎች በደልና ጭቆና እንዳንገበገባችህ እናምናለን፤ ይህንንም ለመቅረፍ በጋራ እንድንቀሳቀስ እንጠይቃለን።

    ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ የከተማችንን ነዋሪ የሚመጥን አስተዳደር እንዲዘረጋ የሚያደርገው ጥረት፣ ከአንድ የፖለቲካ ድርጅት ጥያቄ በላይ እንደሆነ ያምናል። በመሆኑም በሀገራችን የምትገኙ የፖለቲካ ኃይሎች፣ ለከተማው ነዋሪ የራሱን ራስ ገዝ አስተዳደር እንዲመሠረት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍና ትብብር እንድታደርጉለት፤ ምሁራን እና ታዋቂ ግለሰቦችም የሚመሠረተው አስተዳደር የሚያስፈልገውን ድጋፍና አወቃቀር በአግባቡ እንዲይዝ መልክ ለማስያዝ የሚረዳ ልምዳችሁን፣ እውቀታችሁን እንዲሁም ተፅዕኖ የመፍጠር አቅማችሁን እንድታበረክቱ ጭምር አደራ ይላል።

    በዋነኝነት የአዲስ አበባ ራስ ገዝ አስተዳደር ባለቤት ሁሉም የከተማው ነዋሪ እንደሆነ ባልደራስ በጽኑ ያምናል። ይህንንም ለማድረግ የሚያስችል ሕጋዊና ሰላማዊ ትግል በማድረግ የፌዴራል መንግሥት ጥያቄውን እንዲቀበልና በሀገሪቱ አሁን ባለው ሥርዓት መሠረት ሕዝበ-ውሳኔ ተካሂዶ የራስ ገዝ አስተዳደር (ክልል) እንዲሆን እንጠይቃለን። ይህንንም ጥያቄ እውን ለማድረግ እና በሕጉ አግባብ እንዲስተናገድ ለማድረግ የተከማው ነዋሪ የስምምነት ፊርማ የማሰባሰብ ሂደት ውስጥ ተሳታፊ እንዲሆን ጥሪ እናቀርባለን። ጥሪውም በነዋሪ ሕዝቧ ፍላጎት ላይ የተመሠረተ መሆኑን ለማስረገጥ ድጋፉን በፊርማ የሚያቀርብበት የአሠራር ዘዴ ይቀይሳል።

    በመጨረሻም ይህንን የጳጉሜን ሣምንት በግፍ ለታሰሩ የፓርቲያችን መሪ አቶ እስክንድር ነጋ፣ አቶ ስንታየሁ ቸኮል፣ ወ/ሮ ቀለብ ስዩም እና ሌሎች የፓርቲው አባላትና አመራሮች በግፍ ከታሰሩበት እንዲፈቱ በተለያዩ መንገድ ግፊት ለምታደርጉ ወገኖች ምስጋናችንን እያቀረብን፥ መንግሥት በማን አለብኝነት ያለኃጢያታቸው አስሯቸው የሚገኙ ንፁሃን መሪዎቻችንን እና አባላቶቻችንን በአስቸኳይ እንዲፈቱ በድጋሚ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

    መጪው የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት፣ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት ተላቀን በሰላም ወጥተን የምንገባበት፣ ለሀገራችን ዜጎች ሰብዓዊ መብት የሚከበርባት፣ ለተበደሉ ፍትህ የሚሰፍንበት፣ ዴሞክራሲ የሚያብብበት እንዲሆን እንመኛለን፤ ለብሔራዊ መግባባት ሁሉም የፖለቲካ ወገኖች አንድ ላይ ተቀምጠው ስምምነት ላይ የሚያደርስ ተጨባጭ ሥራዎች የምናከናውንበት ዘመን እንዲሆን መልካም ምኞቱን ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ ይገልጻል።

    ድል ለእውነተኛ ዲሞክራሲ!
    ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ)
    ጳጉሜ 3 ቀን 2012 ዓ.ም

    ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ

    Anonymous
    Inactive

    ከአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

    የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ድርጅታዊ ህልውና ባገኘባቸው ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ የአማራ ሕዝብ እውነተኛ ድምፅ በመሆን ሕዝባችንን ከህልውና ስጋት ለመታደግ፣ አንድነቱን ለማረጋገጥና ጥቅሞቹን ለማስጠበቅ የተቀጣጠለውን ንቅናቄ ጠንካራና የማይቀለበስ መሠረት በማስያዝ ረገድ የበኩሉን አስተዋጽዖ አድርጓል። የአማራውን ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ምጣኔ ሀብታዊ ጥያቄዎች ከፍ አድርጎ በመያዝና ለነፃነት፣ ለፍትህና ለእኩልነት የሚደረገውን ትግል በመምራት ሕዝባዊ አመኔታን ለማትረፍ ችሏል።

    አብን ጠንካራ ኢትዮጵያዊ ርእይ የሰነቀ ንቅናቄ በመሆኑ በሀገራዊ የሽግግር ሂደት ውስጥ አዎንታዊ ሚና ለመጫወት ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። አማራው በታላቅ መስዕዋትነት ያስገኘው ለውጥ መስመሩን እንዳይስት፣ በትግላችን የተንበረከኩ ጠላቶች መልሰው እንዳያንሰራሩ፣ የፈነጠቀው የለውጥ ተስፋ እንዳይጨነግፍና ዳግም የሀገራችንና የሕዝባችን ህልውና አደጋ ላይ እንዳይወድቅ ያላሰለሰ ትግል ሲያደርግ ቆይቷል።

    ይሁን እንጂ ጥረቶቻችን እንደሚጠበቀው ያህል ፍሬ ከማፍራት ይልቅ እየመከኑና የሀገራዊው የፖለቲካ አውድ ከጊዜ ጊዜ ተስፋ አስቆራጭ እየሆነ መምጣቱን የሚጠቁሙ በርካታ ምልክቶችን አስተውለናል። ንቅናቄያችን በዚህ ረገድ በአማራ ሕዝብና በኢትዮጵያ ላይ ያንዣበበውን ጽኑ አደጋ በሚያሳዩ ሦስት አበይት ጉዳዮች ላይ ያለውን አቋም በግልፅ ለማሳወቅ ይሻል።

    1. በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈፀሙ በደሎችና የዘር ጥቃቶችን በተመለከተ፦

    አብን በሀገራችን በየትኛውም ክፍል፣ በማናቸውም ኃይልና በየትኛውም ሕዝብ ላይ የሚፈፀሙ የሽብርና የዘር ጥቃቶችን ያለማመንታት አውግዟል። የጋሞ ተወላጆች በቡራዩ በግፍ ሲጨፈጨፉ፣ የአዲስ አበባ ወጣቶች ታፍሰው ወደ ጦር ካምፕ ሲጋዙ፣ የጌዴዖ ወገኖቻችን ሰብዓዊ እርዳታ ተነፍገው በርሀብ ሲረግፉ፣ ቤተ እምነቶች በእሳት ሲጋዩና አማኞች በጭካኔ ሲታረዱ ድምፃችንን ከፍ አድርገን ለኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ እንዲሁም ለዓለም ማኅበረሰብ በማሰማት ዜጎች ከጥቃት እንዲጠበቁና ሰብዓዊ መብቶቻቸው ተከብረው እንዲኖሩ ጥረት አድርገናል።

    በተለይ በኦሮሚያ ክልል በተደጋጋሚ የተከሰቱትን ማንነትና እምነት ተኮር የዘር ማፅዳት፣ የዘር ፍጅትና ሰብዓዊ ወንጀሎችን ለመከላከልና ለማስቆም ሰፊና ያላሰለሰ ትግል አድርገናል። ዜጎች በአማራነታቸው ተመርጠው ቤታቸው ሲፈርስና ሲፈናቀሉ፣ አማራ ተማሪዎች ከኦሮሚያ ክልል ዩኒቨርሲቲዎች በዘር ጥቃት ተገደው ሲለቁና እገታ ሲፈፀምባቸው፣ በኦሮሚያና በሌሎች ክልሎች በሚኖረው ሕዝባችን ላይ የዘር ማጽዳትና ሰብዓዊ ወንጀሎች ሲፈጸሙ ከማውገዝና ማዕከላዊና ክልላዊ መንግሥታት ጥቃቶቹን በአስቸኳይ እንዲያስቆሙ ግፊት ከማድረግ ባለፈ አደጋውን አስቀድሞ መከላከልና ማስቀረት በሚቻልበት መንገድ ላይ ሰፊና የተቀናጁ ጥረቶችን ስናደርግ ቆይተናል።

    በዚህ ረገድ ንቅናቄያችን ካደረጋቸው በርካታ ጥረቶች መካከል ለአብነት ሚያዚያ 29 ቀን 2012 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል የሽብር ኃይሎች ማንነት ተኮርና በተለይም አማራውን ዒላማ ያደረጉ የዘር ጥቃቶች ሊፈፅሙ እንደሚችሉ ከሁኔታዎች ጥናት በመተንበይ ለዚህ ማዕከላዊ መንግሥቱ ልዩ ቅድመ ዝግጅት እንዲያደርግ በአካል ለሀገሪቱ ከፍተኛ መሪዎች ከማስረዳት ባለፈ በመግለጫ ጭምር በአንክሮ ማሳሰቡ ይታወሳል።

    1.1. ከሰኔ 22 ለሊት እስከ ሰኔ 25 ቀን 2012 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል የተደረገው የዘር ማጥፋት፦

    መንግሥት ተቀዳሚ የሆነውን ሰላምና ደኅንነት የማሰከበር ኃላፊነቱን በአግባቡ ሊወጣ ባለመቻሉ የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ሽፋን በማድረግ ጽንፈኛ ኃይሎች ጥምረት ፈጥረውና ተዘጋጅተው በኦሮሚያ ክልል በሚኖሩ በዋነኝነት በአማሮች ላይ፣ በተጓዳኝም በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ላይ ከሰኔ 22 ሌሊት እስከ ሰኔ 25 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ በሽፋኑም ባስከተለው ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመትም እስከዛሬ ከታየው እጅግ ሰፊና አሰቃቂ የዘር ጥቃት ፈፅመዋል።

    አብን ይህን መረን የለቀቀ የዘር ማጥፋት ድርጊት በወቅቱ ከማውገዝ ባሻገር ጭፍጨፋው በተፈፀመባቸው አካባቢዎች የጥናት ቡድን ልኮ በደረሰው ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት ላይ ዝርዝር መረጃዎችን በማሰባሰብና በማጠናቀር ሰነድ አዘጋጅቷል። ሰነዱ በአማርኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች ተዘጋጅቶ ለሚመለከታቸው የሀገር ውስጥና ዓለማቀፍ አካላት በተለይም ለዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ ፣ ለሰብአዊ መብት ተቋማትና ለአማራ አደረጃጀቶች እየተሰራጨ ሲሆን ፣ ንቅናቄያችን የዘር ፍጅቱ እውቅናና ትኩረት እንዲያገኝና ፍትህ እንዲረጋገጥ ቀጣይ እርምጃዎችን የሚወስድ ይሆናል።

    ሀ. የጥፋቱ አድማስ፦

    ንቅናቄያችን ያደረገው ጥናት በወቅቱ በኦሮሚያ ክልል ከተፈፀመው ሰፊ የዘር ጥቃት ውስጥ በስድስት ዞኖች በሚገኙ በ26 ከተሞችና አካባቢዎች የደረሰውን ያካትታል። በምሥራቅ ሸዋ ዞን ደብረዘይት፣ ናዝሬት፣ መተሐራ፣ ዝዋይ፣ አዳሚ ቱሉ፣ ቡልቡላ፣ መቂ ከተሞችን፤ በምዕራብ አርሲ ዞን ሻሸመኔ፣ አርሲ ነገሌ፣ አሳሳ፣ ዶዶላ ከተሞችን፤ በምሥራቅ ሃረርጌ ዞን ሃረማያ፣ ባቴ፣ ከምቦልቻ፣ ጉርሱም ከተሞችን፤ በሃረማያ ወረዳ ኦዳ በሊናና መልካ ገመቹ አካባቢዎችን፤ በጃርሶ ወረዳ አሌ ከተማን፣ ሚደጋ ቶላ ወረዳን፤ በባቢሌ ወረዳ የተለያዩ ስፍራዎችን፤ እንዲሁም በሃረሪ ክልል ሃረር ከተማን፤ በምዕራብ ሃረርጌ ዞን ጭሮ ወይም አሰበ ተፈሪ፣ ሚኤሶ፣ አሰቦት ከተሞችና አካባቢዎችን፤ በምዕራብ ሸዋ ዞን በተለይም ወሊሶ፤ በጅማ ዞን በጅማ ከተማ የደረሱትን የዘር ጥቃቶች ያካትታል።

    በጥቃቱ ከወደመው ሀብትና ንብረት መካከል 378 መኖሪያ ቤቶች፣ 111 ከብቶችና በርካታ የእርሻ ማሳዎች፣ የእህልና የሸቀጣሸቀጥ ክምችቶች፤ ከ300 በላይ ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ የንግድ ድርጅቶችና ህንፃዎች፣ 189 ሆቴሎችና ፔንሲዮኖች፣ 5 ትምህርት ቤቶች፣ 15 መድሃኒት ቤቶችና የህክምና ተቋማት፣ 8 ባንኮችና የኢንሹራንስ ተቋማት፣ 117 የተለያዩ ተሸከርካሪዎች ተዘርፈዋል፤ ተሰባብረዋል፤ በእሳት ተቃጥለዋል። አብያተ ክርስቲያናት፣ የእምነት መገልገያዎችና ታሪካዊ ቅርሶች ሳይቀር የጥቃቱ ሰለባ ሆነዋል። በተፈፀመው እጅግ ከፍተኛ ጥቃት በብዙ ቢሊዮን ብር የሚገመት ሀብትና ንብረት ወድሟል።

    አብን በተጨባጭ መረጃና ማስረጃ ባጠናቀረው ዘገባ ግኝት መሠረት ከሰኔ 22 ለሊት እስከ ሰኔ 25 ቀን 2012 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል የተፈፀመው ጥቃት ዓለምአቀፍ የዘር ማጥፋት መስፈርቶችን የሚያሟላና የማያሻማ የዘር ማጥፋት ድርጊት መሆኑን ያምናል።

    ጥቃቱ በዘርና በእምነት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ‹‹ነፍጠኛ›› እና ‹‹የነፍጠኛ ኃይማኖት›› በሚል የዘር ፍጅት መለያ በዋነኝነት በተጠቀሱት ዞኖች የሚኖሩትን በሚሊዮን የሚቆጠሩ አማሮችን ዒላማ ያደረገ ነው። ሙስሊም አማሮችም የጥቃቱ ሰለባ ሆነዋል። የኦርቶዶክስ ኃይማኖት ተከታይ ኦሮሞዎችና ሌሎችም ኢትዮጵያውያን ለጥቃት ተዳርገዋል።

    በዚህ የዘር ማጥፋት ጥቃት ከ200 በላይ አማሮች በአሰቃቂ ሁኔታ በሜንጫ፣ በዱላና በድንጋይ እየተጨፈጨፉ ሕይወታቸው አልፏል።

    በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የጥቃቱ ሰለባዎች ከቀላል እስከ ፅኑ አካላዊ ጉዳት ደርሶባቸዋል። በጥቂቱ ከ20 ሺህ የሚበልጡ ወገኖችም አስቸኳይ የእለት እርዳታ ፈላጊ ሆነው ሜዳ ላይ ተጥለዋል።

    የአማሮች ሀብትና ንብረቶች እየተመረጡ በመውደማቸው ጥቃቱ በተፈፀመባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ሆን ተብሎ የህይወት ዋስትና እንዲያጡ ተደርገዋል። ችግሩ በነዚህ አካባቢዎች ብቻ የሚወሰን ሳይሆን በመላው ኦሮሚያ የሚኖሩ ወደ 15 ሚሊዮን የሚጠጉ አማሮችና ኦርቶዶክስ አማኞችን ለከፍተኛ የህልውና ስጋትና ሥነ-ልቡናዊ ጉዳት ዳርጓቸዋል።

    ለ. የጥፋቱ ተዋንያን፦

    በሁሉም አካባቢዎች ጥቃቱን በተቀናጀ ሁኔታ በመምራት፣ በማስተባበርና በመፈፀም በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል። በተለይ በኦሮሞ ፅንፈኛ የፖለቲካ ቡድኖች፣ ድርጅቶችና ታዋቂ ግለሰቦች ሳይቀር ‹‹ቄሮ›› በሚል ስም የተደራጁ ወጣቶች ዋነኛ የጥቃት ኃይሎች ነበሩ።

    እነዚህ ቡድኖች ከአንዱ ከተማ ወደ ሌላው አቅራቢያ ከተማ ወይም ከገጠር ቀበሌዎች ወደ ከተማ እየተሰማሩ የሚያጠቁ ፣ በከተማው የሚገኙ ዒላማ የተደረጉ ሰዎችን ቤቶችና ንብረቶችን ዝርዝር የያዙ ጠቋሚዎች በቅንጅት የሚሰሩበት ነው። ለንብረቶች ማቃጠያ ቤንዚንና መሰል ግብአቶችንም የሚያቀርቡ ነበሩበት።

    በተለያዩ ደረጃ ያሉ የመንግሥት ኃላፊዎች፣ የክልሉ የፀጥታ መዋቅር አመራሮችና አባላት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በጥቃቱ ከመሳተፋቸውም በላይ ጭፍጨፋውን ለማስቆም ፍላጎት አጥተው ቆመው መመልከታቸውንም ከፍጅቱ የተረፉ እማኞች አስረድተዋል። የፌዴራል መከላከያ ሰራዊት አመራሮችም እንደ ሻሸመኔና አርሲ ነገሌ ባሉ አካባቢዎች ለቀረበላቸው የድረሱልን ጥያቄ ‹‹ከበላይ ትዕዛዝ አልተሰጠንም›› በሚል ለእርዳታ አልተገኙም።

    የዘር ፍጅቱን ተከትሎ የኦሮሚያ ክልልም ሆነ የፌዴራሉ መንግሥት ወንጀሉን በስሙ በመጥራት ወንጀለኞችን ለሕግ ከማቅረብ ይልቅ ድርጊቱን ተራ ግጭት በማስመል ወደ ማስተባበል ገብተዋል። ከዘር ፍጅቱ የተረፉ ተጠቂ ወገኖችንም በተገቢው ሁኔታ በማቋቋም ረገድ ዳተኝነት ይስተዋላል።

    1.2. የአብን አቋም፦

    በአጠቃላይ አብን በጥናቱ ባረጋገጠው መሠረት በኦሮሚያ ክልል የተደረገው የዘር ማጥፋት ተገቢውን ትኩረት ያለማግኘቱና ችግሩን በአጭር ጊዜም ይሁን በዘለቄታ ለመፍታት የሚታየው ዳተኝነት ፓርቲያችንን ክፉኛ ያሳስበዋል። ስለሆነም፦

    ሀ) የተፈፀመው ወንጀል የዘር ማጥፋት መሆኑ ታምኖበት በስሙ እንዲጠራና ለተፈፀመው ወንጀልም ይፋዊ ይቅርታ እንዲጠየቅ፤

    ለ) መንግሥት የተፈፀመውን የዘር ፍጅት የሚያጣራና የሚመረምር ልዩ የምርመራ ኮሚሽንና አቃቤ ሕግ ጽ/ቤት እንዲያቋቁምና ወንጀለኞች የሚዳኙበት ልዩ ችሎት እንዲሰይም፤

    ሐ) መንግሥት በንፁሃን ዜጎች ላይ የተፈፀመውን አሰቃቂ ወንጀል የሚዘክር ቋሚ መታሰቢያ እንዲያቆም፤

    መ) ችግሩን በዘለቄታ ለመፍታት በክልሉ በሚኖሩ የተለያዩ ማህበረሰቦችና ሕዝቦች መካከል የእርቅና የመግባባት ስራዎች እንዲጀመሩ ፤

    ሠ) የኦሮሚያ ክልልም በክልሉ ለሚኖሩ ኦሮሞ ያልሆኑ ማህበረሰቦችና ሕዝቦች ሰብአዊና ህገ መንግሥታዊ መብቶቻቸው የሚከበሩበት ዋስትና እንዲሰጥ ፤

    ረ) መንግሥት የዘር ፍጅቱን በመዘገባቸው ምክንያት ያሰራቸውን የአስራት ሚዲያ ጋዜጠኞች ያለምንም ቅድመሁኔታ በአስቸኳይ እንዲለቅ አብን ይጠይቃል።

    2. በአዲስ አበባ የሚፈፀሙ ወንጀሎችና ብክነቶችን በተመለከተ፦

    ፓርቲያችን አብን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና በፌዴራል መንግሥቱ በከተማዋ ውስጥ የሚፈፅሙትን ወንጀሎች ፣ ሙስናና ብክነቶች የሚመረምር ቡድን በማቋቋም ሰፊ ጥናት እያካሄደ ይገኛል። ከዚህ ጥናት የተገኘ መረጃን መሠረት በማድረግ በከተማዋ ከፍተኛ ሕገ-ወጥ የመሬት ወረራ፣ ተቋማትን በአንድ ብሔር ተወላጆች የመሙላት፣ ሕገ-ወጥ የመታወቂያ እደላና በርካታ ተያያዥ ወንጀሎች እንደተፈፀሙ አረጋግጧል። ይህም በተለይ ከሰኔ 2011 ወዲህ እጅግ የተባባሰ እንደነበር ተገንዝቧል።

    2.1. ሕገ-ወጥ ወረራ፣ ሰፈራና ማፈናቀል

    የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በአንጡራ ሃብታቸው ያቆሙት ጎጇቸውና ድርጅቶቻቸው ያለርህራሄና ያለሕግ አግባብ የሚፈርሱባትና ዜጎች ሜዳ ላይ የሚወረወሩበት፤ ከፊሎች ደግሞ በዘር፣ በፖለቲካ ወገንተኝነትና በጥቅም ትስስር በገፍ መሬት የሚቸራቸው፤ የከተማዋ ነዋሪ ከእለት ጉርሱ ቀንሶ የገነባው የጋራ መኖሪያ ቤት በልዩ መብት የሚታደላቸው ከተማ ሆናለች።

    አብን በከተማዋ የሚፈፅሙትን ሕገወጥነቶች ከማውገዝና በተለያዩ መድረኮችና መገናኛ ብዙሃን አማካኝነት ከማጋለጥ ባሻገር አቅም በፈቀደ መጠን የሰብአዊ ርዳታዎችን በማቅረብ ኢትዮጵያውያን ወገኖችን ለመታደግ ጥረት አድርጓል። መላው ሕዝባችን በተለይም ለሕዝብና ለሀገር ጥቅሞች ፣ መብቶችና ፍላጎቶች ቆመናል የሚሉ የፖለቲካ ኃይሎች ከንቅናቄያችን ሀገርን የማዳን ታሪካዊ ጥሪ ጎን እንዲቆሙ ወትውተናል።

    ከዚህም ባለፈ ንቅናቄያችን ጉዳዩን ትኩረት ሰጥቶ በማጥናት ለሀገሪቱ ከፍተኛ የመንግሥት አካላት በተደጋጋሚ አቤት ብሏል። ታህሳስ 2 ቀን 2011 ዓ.ም በብሔራዊ ቤተመንግሥት በመገኘት ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ጋር እስከመወያየት ደርሷል። በወቅቱም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ችግሮች መኖራቸውን በማመን አስቸኳይ መፍትሔ እንደሚበጅላቸው ቃል ቢገቡም አንዳችም ሳይደረግ አሁን ካለንበት ሁኔታ ላይ ተደርሷል።

    ሰለዚህም የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ይህ እጅግ አሳሳቢ ጉዳይ በአስቸኳይ መፍትሄ ካላገኘ ፅኑ ብሔራዊ ቀውስ የሚፈጥር በመሆኑ፦

    ሀ) አዲስ አበባ ላይ የተፈፀመውን ሁሉንአቀፍ ወረራ በተመለከተ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ጨምሮ ሌሎች የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት ያካተተ አንድ አጣሪ ኮሚቴ እንዲቋቋም፤

    ለ) ባለፉት ሁለት ዓመታት የነበረውን የመሬት አስተዳደርና ማስተላለፍ፣ የመታወቂያ አወጣጥ፣ የቅጥርና ዝውውር እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን እንዲያጣራ/ኦዲት እንዲደረግ፤

    ሐ) በኦዲት ግኝቱ በሚመጣው መሠረት ጥፋተኛ ሆነው የሚገኙ ሁሉም አካላት ለፍትህ እንዲቀርቡ፤

    መ) በኦዲት ግኝቱ ለተለዩ ጉድለቶች አጣሪ ኮሚቴው በሚያቀርበው ምክረ ሐሳብ መሠረት የማስተካከያ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ፤ እንዲሁም

    ሠ) ምርጫ ተካሂዶ ቅቡልነት ያለው ሕጋዊ የከተማ አስተዳደር ምክርቤትና ካቢኔ እስኪዋቀር ድረስ አሁን ያለው የሽግግር አስተዳደር ዘላቂ ውጤት ሊኖራቸው ከሚችሉ ውሳኔዎች እንዲታቀብ፤ አብን ጥሪውን ያቀርባል።

    2.2. ሜጋ ፕሮጀክቶችን በተመለከተ፦

    ፓርቲያችን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ በጠቅላይ ሚኒስቴር ፅ/ቤትና በከተማ አስተዳደሩም በኩል የሚሰሩ ዋና ዋና 15 ሜጋ ፕሮጀክቶችን ሁኔታ በንቃት በመከታተል ስለፕሮጀክቶቹ ዝርዝር መረጃዎችን ሲያሰባስብ ቆይቷል።

    በዚህም መሠረት በጀታቸው/ወጪያቸው የታወቁ ፕሮጀክቶች የገንዘብ መጠን በአጠቃላይ 5.737 ቢሊዮን ዶላር (ወቅታዊ ምንዛሪው ከ212 ቢሊዮን ብር በላይ) እና ተጨማሪ 59.2 ቢሊዮን ብር በአንድ ላይ ወደ 271 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ እንደሆነ ተረድቷል። በጀታቸው ካልታወቁ ጋር ሲደመር ከዚህ ከፍተኛ መሆኑ አያጠራጥርም።

    አዲስ አበባ ተመራጭ የቱሪዝም መዳረሻ ከተማ እንድትሆን የሚደረገውን መንግሥታዊ እንቅስቃሴ በመርኅ ደረጃ አብን ይደግፋል።

    ይሁንና የሜጋ ፕሮጀክቶቹ እጅግ የተጋነነ ወጭ የሚወጡባቸው በመሆናቸው (White Elephant Projects)፤ ይኸው ከፍተኛ በጀት ሀገራችን በብድርና እርዳታ የምታገኘው በመሆኑ፤ አንዳንዶቹ ፕሮጀክቶች ሀገራችን አሁን ካለችበት ሁኔታ አንፃር የቅደም ተከተል ችግር ያለባቸው መሆናቸው ፤ ከአዋጭነት፣ ባለድርሻዎችን ከማሳተፍ፣ ከዲዛይንና ግንባታ አካሄድ፣ ከብክነትና ሙስናን ከማስቀረት፣ በግልጽ ጨረታ የግንባታ ኮንትራክተሮችን ከመለየት እንዲሁም በየጊዜው ስለፕሮጀክቶቹ ለሕዝብ ግልጽ መረጃ ከመስጠት አንፃር ክፍተቶች ያሉባቸው መሆናቸውን አብን ያምናል።

    መንግሥት ይህን ያህል ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ግልጽነት ባልተሞላበትና የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን አንገብጋቢ ጉዳዮች ባላስቀመጠ መልኩ ማዋሉ ፓርቲያችንን ክፉኛ ያሳስበዋል። ስለሆነም፦

    ሀ) መንግሥት ስለፕሮጀክቶቹ ለሕዝብ ግልፅ ማብራሪያ እንዲሰጥ፤

    ለ) በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት የሀገራችን ኢኮኖሚ ክፉኛ እየተደቆሰ በመሆኑ ቀውሱ ሀገርን ለከፋ አደጋ የሚዳርግ ማኅበራዊ ቀውስ ከማደጉ በፊት አስፈላጊ የኢኮኖሚ ድጋፍ ማእቀፎችን ቀርፆ ወደ ሥራ እንዲገባ፤

    ሐ) የተጋነኑና አንገብጋቢ ያልሆኑ ሜጋ ፕሮጀክቶችን በማጠፍ በጀቱን የነፍስ አድን ርዳታ ለሚፈልጉ ወደ 18 ሚሊዮን ዜጎች ድጋፍ እንዲያውለው፤

    መ) በሀገራችን ያለው የሥራ አጥነት በአስከፊ ሁኔታ ላይ መገኘቱን በማጤን መንግሥት ጊዜውንና አቅሙን ለወጣቶች ሥራ እድል ፈጠራና ለኢኮኖሚ ሽግግር እንዲያውል አብን ጥሪውን ያቀርባል።

    3. ብሔራዊ ውይይትና መግባባትን በተመለከተ፦

    አብን የሀገራችን የፖለቲካ ቀውስ በምርጫ ብቻ እልባት ያገኛል የሚል አቋም የለውም። ስለዚህም ከምርጫ በፊት እንደ ሀገር መደማመጥ፣ መከባበርና መተማመን እንዲቻልና አሁን የተፈጠረው የሽግግር ጊዜም እንዳለፉት ዘመናት እድሎች እንዳይከሽፍ ሁሉን አቀፍ ሀገራዊ የሰለጠነ ውይይት፣ ምክክርና ድርድር እንዲዘጋጅ፤ ለዚህም ግልጽ ማእቀፍ እንዲኖርና ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያሳተፈ የብሔራዊ ውይይት መድረክ እንዲከፈት ወትውቷል።

    መንግሥት ለእውነተኛ የፖለቲካ ድርድርና ብሄራዊ መግባባት ዳተኝነት በማሳየቱ ምክንያት ፅንፈኛ ኃይሎች ሀገር አፍራሽ ድርጊታቸውን በማናለብኝነት እንዲቀጥሉ እድል ሰጥቷቸዋል። በዚህ ረገድ ትሕነግ የሚዘጋጅበት ሕገ-ወጥ ምርጫ በወረራ በተያዙ የአማራ መሬቶች በወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምትና ራያ የሚኖረው ሕዝባችን ላይ የሚያደርሰውን ፅኑ አፈናና ግፍ መንግሥት እንዲያስቆም በተደጋጋሚ ጥሪ አቅርበናል።

    የፌዴሬሽን ም/ቤት ዘግይቶም ቢሆን የወሰነውን ውሳኔ የፌዴራል መንግሥቱ በአስቸኳይ ተግባራዊ እንዲያደርግና ትህነግ በህገወጥ ምርጫ በወልቃይትና ራያ ሕዝባችን ላይ የሚያደርሰውን ሰብአዊ ቀውስ እንዲያስቆም የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ጥሪ ያቀርባል።

    በተጨማሪም ፡-

    ሀ) ሀገርን ወደ ዴሞክራሲ ለማሻገር ሁሉም ባለድርሻ አካላት የማይተካ ሚና እንዳላቸው በማመን መላው የፖለቲካ ኃይሎች የሀገራችን አደገኛ ወቅታዊ ሁኔታ ባጤነ መልኩ በኃላፊነት እንዲንቀሳቀሱ፤

    ለ) መንግሥት በውል የታወቀና የታቀደ ሁሉንአቀፍ ብሔራዊ ውይይት፣ ምክክርና ድርድር የማስተባበርና የማመቻቸት ኃላፊነቱን እንዲወጣ፤

    ሐ) ሁሉም ዜጎች በተለይም ሲቪክ አደረጃጀቶች፣ የሚዲያ ተቋማት፣ ምኁራን፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ ወጣቶችና ሴቶች እንዲሁም ባለሀብቶች ለሚደረገው ብሔራዊ ውይይት፣ ምክክርና ድርድር ውጤታማነት የየድርሻቸውን አስተዋፅኦ እንዲኖራቸው፤

    መ) የዓለምአቀፍ ማኅበረሰቡ የሁሉንአቀፍ ብሔራዊ ውይይት፣ ምክክርና ድርድር ሂደት እንዲደግፍና መንግሥት የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እንዲወጣም ጫና እንዲፈጥር የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ታሪካዊ ጥሪውን ያስተላልፋል።

    “አንድ አማራ ለሁሉም አማራ ፤ ሁሉም አማራ ለአንድ አማራ!›”
    የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)
    አዲስ አበባ፣ ሸዋ፤ ኢትዮጵያ!
    ጳጉሜ 2 ቀን 2012 ዓ.ም

    የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)

    Anonymous
    Inactive

    በኢትዮጵያ የሀገረ-መንግሥት ግንባታ የታሪክ ዳራ፥ በእኩልነት ላይ የተመሠረተች ሀገር ለመፍጠር የተደረጉ ሙከራዎች፣
    ያጋጠሙን የታሪክ ፈተናዎችና ያመለጡን ዕድሎች በብሔራዊ መግባባት መነፅር ሲታይ

    መረራ ጉዲና (ፕሮፌሰር)
    ለብሔራዊ መግባባት ውይይት የቀረበ ጥናት
    ነሐሴ 2012

    አብዛኛዎቹ የሀገራችን የታሪክ ምሁራን የኢትዮጵያ ታሪክ ከክርስቶስ ልደት በፊት፣ በአስረኛው ምዕተ ዓመት የንግስት ሳባ እና የንጉሥ ሰለሞን ግንኙነት በሚባለው ጊዜ ይጀምራል ይላሉ። ይህ ለአንዳንዶቹ የሚታመን ታሪክ ተደርጎ የሚወሰደው፤ ለሌሎች ደግሞ ተረት እንደነበረ የሚነገረው ክስተት የማስመሰያ ትርክቱ የእስራኤል አምላክ የቀባቸው ገዥዎች ተብሎ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት ንጉሦቹ ቅቡልነትን አግኝተውበታል። በትርክቱም ሀገሪቷን እስከ 1966 ሕዝባዊ አብዮት ድረስ ያለ ብዙ ጭንቀት ገዝተውበታል።

    የዛሬይቱ ሰፊዋ ኢትዮጵያ እንደ ሕብረ ብሔራዊ የነገሥታት መንግሥት (multi-ethnic empire state) የተፈጠረችው በ2ኛው የ19ኛው ክፍለ ዘመን ግማሽ፤ የዘመነ መሳፍንት ከሚባለው ዘመን በኋላ ስለሆነና ዛሬም በጣም ሰፊ ቀውስ ውስጥ የከተተን ታሪካዊ ዳራም ከዚሁ ጊዜ ጀምሮ ስለሆነ፥ ጽሑፌም ከዘመናዊ ኢትዮጵያ መፈጠር ጋር በተፈጠሩ ችግሮች ላይ ያተኩራል።

    የዘመነ መሳፍንትን ክስተት በመለወጥ የተጀመረው የዛሬዋን ሰሜናዊ ኢትዮጵያን አንድ የማድረግ ሕልም በግማሽ ምዕተ ዓመት ውስጥ ከሦስት እጥፍ በላይ የሰፋች ኢትዮጵያን መፍጠር ችሎዋል። ይህ የታሪክ ክስተት የሦስት ምኞቶች ዉጤት ነበር። እነዚህም፡-

    1ኛ/ ተበታትና የነበረችውን የዛሬዋን ሰሜናዊ ኢትዮጵያ ሕዝቦችን ለማሰባሰብ የታለመ ምኞት፣
    2ኛ/ የኦሮሞና የሶማሌ ሕዝቦችን ጨምሮ ሰፊውን የደቡብ ክፍል የማስገበር ምኞት፣
    3ኛ/ አፍሪካን ለመቀራመት የመጡትን የአውሮፓ ሀገሮች ጋር የመፎካከር ምኞት ነበሩ።

    እነዚህን ሦስት ምኞቶች ለማሳካት የመጀመሪያ የሆነውን ሙከራ የጀመሩት እንደምታውቁት አፄ ቴዎድሮስ ነበሩ። ቴዎድሮስ ሕልሞቹን ለማሳካት ጠንካራና ሰፊ ሠራዊት ማደራጀት ነበረባቸው፤ ለዚህም ሰፊ መሬት የያዙትን ቄሶች መሬት መቀማትና ዘመናዊ መሣሪያን ከክርስቲያን አውሮፓ ለማግኘት ጥረት ማድረግ ነበር። የአዉሮፓ መሪዎችን ማሳመን ሲያቅታቸው ደግሞ ሙያው የሌላቸውን አውሮፓዊያንን ሳይቀር በቤተ መንግሥታቸው ሰብስበው ከባድ የጦር መሣሪያ ውለዱ እስከማለት ደርሰዋል። ይህም ምኞታቸዉ ይሳካ ዘንድ በነበራቸዉ የጦር መሣሪያ የአካባቢ ገዥዎችንም ለማንበርከክ ተንቀሳቅሰዋል።

    ቄሶችን ለመግፋት ያደረጉት ሙከራ እግዚአብሔርን የካዱ ንጉሥ ተብሎ ተሰባከባቸዉ። የአውሮፓውያንን ዘመናዊ መሣሪያ ለማግኘት ገደብ ያለፈ ጉጉታቸው ከእንግሊዘኞች ጋር ያለጊዜ አላተማቸው። የየአከባቢውን ገዥዎች በጉልበት ለማንበርከክ እጅና አንገት በመቁረጥ የገፉበት ሙከራ ከእንግሊዞች ጋር ለመዋጋት የቁርጥ ቀን ሲመጣ፥ የትግራይ፣ የወሎ፤ የጎጃም፣ የሸዋ፣ የጎንደር ገዥዎች ሁሉም በሚባልበት ደረጃ ካዷቸው። በአጭሩ የየአከባቢዉ ገዥዎች በእንግሊዞች እጅ መሞታቸውን ሲሰሙ ከማዘን ይልቅ ተገላገልን ያሉ ይመስላል። ለዚህም ይመስለኛል ዕውቁ የታሪክ ምሁር ፕሮፌሴር ባህሩ ዘውዴ የቴዎድሮስን ሚና በተሻለ የታሪክ ሚዛን ላይ ለማስቀመጥ ሲሞክር፥ “የተወናበዱ የለዉጥ ነቢይ” (“confused prophet of change”) ያላቸዉ።

    በዚህ የቴዎድሮስ የታሪክ ሚና ላይ ብዙ ሰው ልብ የማያደርገውን የታሪክ ማስታወሻ አስቀምጬ ልለፍ። ይኼውም ቴዎድሮስ በጊዜው ለነበሩ የአውሮፓ ኃያላን መንግሥታት በፃፉት ደብዳቤ ውስጥ፥ “አባቶቼ በሠሩት ኃጢአት ምክንያት እግዚአብሔር “ጋሎችን” በሀገሬ ላይ ለቆ፣ እነሱ ጌቶች ሆነው፣ እኛ የእስራኤል ልጆች የነሱ አሽከሮች ሆነን እንኖር ነበር። አሁን እግዚአብሔር ከትቢያ አንስቶኝ የኢትዮጵያ ንጉሥ አድርጎኛል። እናንተ ከረዳችሁኝ በጋራ እየሩሳሌምንም ነፃ ልናወጣ እንችላለን” ማለታቸዉ ነዉ (ትርጉም የኔ ነው)። እዚህ ላይ ሁለት ነገሮችን ልበል፦

    1) “ጋሎቹ” የሚባሉት በዘመነ መሳፍንት የጎንደርን ቤተ መንግሥት በበላይነት ሲቆጣጠሩ የነበሩ የየጁ ኦሮሞዎች መሆናቸውና እየሩሳሌም በጊዜው በእስላሞች እጅ የነበረች መሆንዋን ነው።
    2) ከዚህ አንጻር ማስታወስ የሚያስፈልገው ትልቁ ጉዳይ አፄ ቴዎድሮስ የብሔረሰብ (የዘር) ፖለቲካን በግልፅ የተናገሩ የመጀመሪያዉ የኢትዮጵያ መሪ መሆናቸው ነው።

    ከቴዎድሮስ ሞት በኋላ ለሦስት ዓመታት በተክለጊዮርጊስ እና ካሣ (አማቾች የነበሩ ይመስለኛል) ከተካሄደው የሥልጣን ትግል በኋላ በአሸናፊነት የወጡት አፄ ዮሐንስ (ካሣ ምርጫ) ነበሩ። አፄ ዮሐንስ ከሀገር ውስጥ ከወሎ፣ ከጎጃም፣ ከጎንደር፣ ከሸዋ ገዢዎች ጋር እየተጋጩ፥ ከውጭ ደግሞ ከጣሊያኖች፣ ከግብፆችና ከሱዳን መሐዲስቶች (ደርቡሾች ) ጋር ሲዋጉ በመጨረሻ በመሐዲስቶች እጅ ወድቋዋል።

    በአጭሩ ዮሐንስ ለትግራይ ሊሂቃን የኢትዮጵያ ማዕከል ነበርን፤ የአክሱም ሀቀኛ ወራሾች እኛ ነን የሚለውን የፖለቲካ ስሜት መፍጠር ቢችሉም፥ በኢትዮጵያ የሀገረ-መንግሥት ግንባታ ታሪክ ውስጥ የተለየ ሚና መጫወት አልቻሉም።

    በማያሻማ ቋንቋ፥ የዛሬዋ ኢትዮጵያ በዋናነት የተፈጠረችውና የዛሬው የታሪክ ጣጣችንም በዋናነት የተፈጠረው በአፄ ምኒልክ ነው። ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ዮሐንስን የሱዳን መሐዲስቶች እስኪገድሉላቸው ድረስ ከአውሮፓ መንግሥታት፥ በተለይም ከጣሊያን በገፍ ባገኙት የጦር መሣሪያ እነራስ ጎበና የመሳሰሉ የኦሮሞ የጦር መሪዎችን በመጠቀም በጊዜው ጠንካራ የሚባል ግዙፍ ሠራዊት መገንበት ችለዋል። ይህንን ግዙፍ ሠራዊትን ከዮሐንስ ጋር በመዋጋት ከማድከም ይልቅ፥ በአንድ በኩል ዮሐንስን እየገበሩ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ያኔ የነበረችውን ኢትዮጵያ ሦስት እጅ እጥፍ የሆነ ሰፊ ግዛት መፍጠር ችሎዋል። በዚህም መጀመሪያ ሳይጠቀለሉ የቀሩትን የሸዋ ኦሮሞዎችን ጠቅልለው ያዙ። ከዚያ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር (እ.አ.አ) በ1876 ጉራጌን ብዙ ሕይወት ከጠየቀ ጦርነት በኋላ አስገበሩ። ብዙ ዝርዝር ውስጥ ሳይገባ የምኒልክን የመስፋፋት ጦርነቶች እንደሚከተለው ማጠቃለል ይቻላል። ይኸውም በምኒልክና ጀኔራሎቹ ብዙ የግዛት መስፋፋት ጦርነቶችን ቢወጉም ሦስቱ ወሳኝ ጦርነቶች ነበሩ።

    አንደኛው በምዕራብ በኩል በእማባቦ (ዛሬ ሆሮ ጉዱሩ በሚባለው ላይ በጎበና መሪነት እ.አ.አ በ1882 የተዋጉት ጦርነት ነበር። ይህ ጦርነት ኦሮሞን ጨምሮ የምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦችን ዕድልና የጎጃም መሪዎች ከሸዋ ጋር የነበራቸውን ፉክክር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የወሰነና የሸዋንም የበላይነት ያረጋገጠ ነበር።

    ሌላው የምኒልክ ጦርነት በአርሲ ላይ እ.አ.አ በ1886 የተደመደመዉ ነው። አርሲዎች ከሌሎች የኦሮሞ አካባቢዎች በተለየ መንገድ ለአምስት ዓመታት በጀግንነት ተዋግተዋል። በመጨረሻም በራሳቸው በምኒልክ በተመራ ጦር የአውሮፓ መሣሪያ በፈጠረው ልዩነት ሊሸንፉ ችለዋል። ተመሳሳይ የመከላከል ጦርነት እንዳይገጥማቸው ይመስላል ምኒልክ ዛሬ አለ፣ የለም የሚባለውን የአኖሌ ዓይነት የጭካኔ በትር በአርሲዎች ላይ አሳርፈዋል። እዚህ ላይ ዛሬ እየተነጋገርንበት ላለው የብሔራዊ መግባባት መሳካት፥ የለም ከሚለው አጉል ክርክር ወጥተን የትናንትናውን የታሪክ ቁስላችንን በሚያክም መልኩ እንድናስተካክል መምከርን እወዳለሁ።

    ሦስተኛው የምኒልክ ትልቁ ጦርነት አሁንም በእሳቸው የተመራውና እ.አ.አ በ1887 የተካሄደው የጨለንቆ ጦርነት ነበር። የዚህ ጦርነት ውጤት በጊዜው የሀብታሟ የሐረር ከተማ መንግሥት (the Harari city-state) ጨምሮ ምስራቅ ኢትዮጵያ ያለ ደረሰኝ ምኒልክ እጅ የገባበት ሁኔታን ፈጥሯል። ከዚህም በኋላ ከፋን፣ ወላይታን፣ ወዘተ ለመያዝ ብዙ ደም የፈሰሰባቸው ጦርነቶች ነበሩ። እንደሚባለው በእንግሊዝ ተስፋፊዎችና በምኒልክ ኢትዮጵያ መካከል የመምረጥ ዕድል የገጠማቸው የቦረና ኦሮሞዎች፥ ‘ማንን ትመርጣላችሁ?’ ሲባሉ፥ የፊታወራሪ ሀብተጊዮርጊስ ፊትን አይተው፥ የእኛኑ ፊት የሚመስለው ይሻላል ብለው በሪፈረንደም (referendum) እየሰፋ በመጣው የኢትዮጵያ መንግሥታዊ ግዛት ውስጥ የተቀላቀሉበት ሁኔታም እንዳለ ይነገራል።

    እ.አ.አ በ1889 አፄ ዮሐንስ በመሐዲስቶች ሲገደሉ፥ ኦሮሞን ጨምሮ አብዛኛው ደቡብን የተቆጣጠሩት ምኒልክ ለሰሜኑ ወንድም መሪዎች ፈረንጆች እንደሚሉት “ካሮትና ዱላን ማስመረጥ” (carrot-and-stick approach) ብቻ በቂ ነበር። የሰሜኑ መሪዎች ምርጫም በማያሻማ መንገድ ካሮት ነበር። ስለካሮቱም በግልፅ ቋንቋ ለማስቀመጥ፥ የኦሮሞ አከባቢዎችን ጨምሮ በደቡብ የተገኘውን እጅግ በጣም ሰፊ ግዛት ዉስጥ በታናሽ ወንድምነት ሹማቶችን መቀራመት ነበር።

    በብሔራዊ መግባባታችን ውይይት አንፃር በምኒልክ በተፈጠረው ሰፊ አፄያዊ ግዛት ጋር የተፈጠሩ ችግሮችን ወደ ማንሳቱ ልለፍ። አንደኛው ችግር ከላይ እንዳነሳሁት፥ በጉልበት የግዛት ፈጠራ ላይ አኖሌን የመሳሰሉ የታሪክ ጠባሳዎች መፈጠራቸው። ሁለተኛውና ዋናው ነገር ግን ከማቅናቱ ጋር የተፈጠረው የፖለቲካል ኤኮኖሚው ነው። ይህም በነፍጥ ላይ የተመሠረተዉ የፖለቲካ ኤኮኖሚ ዛሬም እያወዛገበን ያለው የነፍጠኛ ሥርዓት በሚባለው ላይ የተመሠረተዉ ነዉ። ለማቅናት የተሰማራው የፊውዳሉ ሥርዓት ሠራዊት የገባር ሕዝቦችን ነፃነት ቀምተዋል፤ መሬታቸዉን ዘርፈዋል፤ ሕዝቦችን በገዛ መሬታቸው ላይ ጭሰኛና አሽከር አድርገዋል፤ ቋንቋቸውን አፍነው በ’ስማ በለው’ ገዝቷቸዋል። በአጭሩ፥ እጅግ በጣም ዘግናኝና ጨካኝ የሆነ የፖለቲካ ሥርዓት ጭነውባቸዋል። አንዳንዱ ነፍጠኛ በሃያ ሺዎች የሚቆጠር ጋሻ መሬትም ነበረው። ወረ-ገኑ የመሳሰሉ የቤተ መንግሥት መሬቶች እጅግ በጣም ብዙ ነበሩ። እዚህ ላይ ማስታወስ የሚያስፈልገው የሰሜንና የደቡብ ኢትዮጵያ የመሬት ይዞታም በፍጹም የተለያዩ መሆናቸው ነው። አነሰም በዛ የሰሜኑ ገበሬ የዘር ግንዱን ቆጥሮ መሬት ያገኛል። መሬት አያያዙም የወል ነበር። ሌላው ቢቀር የሚገዛውም በራሱ ቋንቋ ነበር። በደቡቡ ያለው ግን የመሬት ሥርዓቱ የግል ሆኖ፥ ጭሰኝነት እጅግ የተንሠራፋበት ነበር። ሲሶ ለነጋሽ፣ ሲሶ ለቀዳሽ፣ ሲሶ ለአራሽ የሚባለው የኢትዮጵያ ነገሥታት የመሬት ፖሊሲ እጅግ በጣም ዘግናኝ በሆነ ሁኔታ ሥራ ላይ የዋለው በደቡቡ የሀገራችን ክፍል ላይ ነው።

    በ1960ዎቹ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ዘመን “መሬት ላራሹ” እና “የብሔረሰቦች እኩልነት” የተባሉ ሕዝባዊ መፈክሮች የተወለዱት ከዚሁ ጨቋኝ ሥርዓት ነበር። ዛሬ የታሪክ ክለሳ ውስጥ ብንገባም፥ በእውነቱ ከሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብራክ የወጡ ወጣቶች፥ እንዲያውም በወቅቱ ‘አማራ’ ከሚባለው ክፍል የሚበዙ ይመስለኛል፤ መፈክሮቹን በጋራ አስተጋብተዋል።

    ለማንኛውም ከብሔራዊ መግባባታችን አንፃር አንድ ነገር ግልፅ ላድርግ። ‘ነፍጠኛ’ የሚባለው ሥርዓት ገዝፎ የነበረ ሥርዓት መሆኑና፥ ይህም ሥርዓት ከደቡቡ አርሶ አደር የተሻለ ኑሮ የማይኖሩትን፥ ቢፈልጉ እንኳን የደቡቡን ገበሬ ለመዝረፍ አቅሙም ሆነ ዕድሉን ያልነበራቸውን የአማራ አርሶ አደርን አይጨምርም፤ መጨመሩም ጩቡ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ዛሬ አንዳንድ የአማራ ሊሂቃን “እኔም ነፍጠኛ ነኝ” የሚለውን መፈክር ሲያሰሙ፥ ጥቅሙ ኦሮሞን ጨምሮ የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦችን ከአማራ ሕዝብ ጋር ከማጋጨት የዘለለ የፖለቲካ ትርፍ የሚኖረው አይመስለኝም። ስለሆነም የምንችለውን ያክል ሁላችንም ከሁለቱም ጩቡዎች እንጠንቀቅ ዘንድ አደራ እላለሁ።

    ወደ ሌሎች ነጥቦች ከማለፌ በፊት በዋናናት በምኒልክ የተፈጠረችዉ ኢትዮጵያን ለማስተካከል ያቃታቸዉና መሪዎች ማለፍ ያልቻሉት የታሪክ ፈተና ምንድን ነው? የሚለውን ጥያቄ በንጽጽር እንደ ታሪክ ቁጭት ማንሳትን እወዳለሁ። አፄ ቴዎድሮስ የሞቱት እ.አ.አ በ1868 ነበር። ጃፓንን ከታላላቅ የዓለም መንግሥታት ተርታ ያሰለፏት መጅ (Meiji) የሚባሉ የንጉሣውያን ቤተሰብ ወደ ሥልጣን የተመለሱት (The Meiji Restoration) በዚሁ ዓመተ ምኅረት ነበር። የጃፓን ንጉሣዊ ቤተሰቦች በሰላሳ ዓመታት ውስጥ በኢኮኖሚ የበለፀገች ታላቋ ጃፓንን ፈጠሩ። የጃፓኖች የሀገር ፍቅር ግንባታቻውም ባዶ አልነበረም። ትዝ እስከሚለኝ ድረስ አንድ የጃፓን ወታደር ንጉሤ የጃፓንን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት መሸነፍ አልነገሩኝም ብሎ ከሃምሳ ዓመታት በኋላ በፊሊፕንስ ይሁን፤ በኢንዲኔዢያ ጫካ ውስጥ ተገኝቷል። ለሀገር ፍቅር ሲባል እራስን በራስ ማጥፋት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በትናንሽ አይሮፕላኖችን የአሜሪካን መርከቦች ውሰጥ እየጠለቁ አጥፍቶ መጥፋትን የጀመሩት የጃፓን ካሚከዞች (Kamikaze) የሚበሉ ነበሩ። የኢትዮጵያ መሪዎች ግን በተመሳሳይ ጊዜ (እ.አ.አ 1868-1900) ድረስ ሀገሪቷን ከዓለም ጭራነት አላላቀቋትም። በነገራችን ላይ ጃፓንና ኢትዮጵያ በ1868 ላይ ተመሳሳይ የዕድገት ደረጃ ላይ ነበሩ።

    ሌላው ንጽጽሬና የታሪክ ቁጭታችን መሆን ያለበት፥ ታላቋ ጀርመንን የፈጠሩት ቢስማርክ (Otto von Bismarck) እና ምኒልክ የአንድ ዘመን ሰዎች ነበሩ። ምንም ይሁን ምን እነ ቢስማርክ ዓለምን ሁለት ጊዜ ጦርነት ውስጥ መክተት የቻለች ኃያሏን ጀርመን ሲፈጥሩ፥ የኢትዮጵያ ገዥዎች ግን ኋላቀር ኢትዮጵያን ትተውልን ሄደዋል። በነገራችን ላይ ሀገር ትፈርሳለች ተብሎ ስለተሰጋ፥ የምኒልክ ሞት ለሕዝብ ይፋ የሆነው ከዓመታት በኋላ ነበር ይበላል።

    በአጠቃላይ ከብሔራዊ መግባባት ፈጠራችን አንፃር መረሳት የሌለበት ቁመነገር፥ በምኒልክና ጣይቱ የተመራው የአድዋው የጋራ ድል እንኳ ያልፈቱት የሚጋጩ ሦስት አመለካከቶች ዛሬም ከእኛ ጋር መኖራቸዉ ነዉ።

    አንደኛው፥ የሀገራችን ሀገረ-መንግሥት ግንባታ አንድ የነበሩና የተበታተኑ ሕዝቦችን አንድ ላይ መልሶ ያመጣ ነዉ የሚላዉ አመላካከት (reunification)፤
    ሁለተኛው፥ በአንድ ላይ ያልነበሩ ሕዝቦችን ወደ አንድ ማምጣት ነዉ የሚለዉ አመላካከት (unification and/or expansion)፤
    ሦስተኛው፥ ነፃ ሕዝቦችን ጨፍልቆ በኃይል ማቅናት ነዉ የሚላዉ አመላካከት (colonial thesis) ናቸው። የበለጠ ግልፅ ለማድረግ፥ የኢትዮጵያ አንድነት አጥባቂዎች ነን የሚሉ በዋናነት የምኒልክን ኃጢአቶች አይቀበሉም። እንደሚሉት እምዬ ምኒልክ በዓለም ከተደረጉት የሀገር ግንባታዎች ምን የተለየ ነገር ሠራ የሚለውን ሐሳብ ያራምዳሉ። ከዚያም አልፈዉ ምኒልክ የሠራዉ ሥራ ተለያይተዉ የነበሩትን የኢትዮጵያ ግዛቶችን መመለሰ ነበር ይላሉ። በአንፃሩ የኢትዮጵያ አንድነትን የማያጠብቁ ብሔረተኞች ደግሞ የአቶ ሌንጮ ለታን አባባል ለመጠቀም (አሁን አቋማቸዉ ያ መሆኑን አላዉቅም)፥ ሲያንስ “ኢትዮጵያዊ ለመሆን እንደራደራለን ሲበዛ ደግሞ ነፃ መንግሥታትን እስከ መፍጠር ድረስ እንሄደለን” የሚሉ ናቸው። በጥቅሉ እነዚህ አመለካከቶች በፖለቲካችን ለሚጋጩ ሕልሞቻችን መሠረት የሆኑና ካልተገደቡ የሥልጣን ሕልሞች ጋር ተደምሮ የብሔራዊ መግባባት ጥረታችንን የሚያወሳስቡ አመለካከቶች መሆናቸውን በውል መገንዘብ ያስፈልጋል።

    በእነምኒልክ የተፈጠረችዉን ኢትዮጵያን ለማስተካከል የተደረጉ ሙከራዎችና ያመለጡን ዕድሎች፡-

    1) የልጅ ኢያሱ ሙከራ

    ልጅ ኢያሱ የምኒልክ ልጅ ልጅ ሲሆን፥ በእኩልነት ላይ የተመሠረተች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ልዩ ዕድል የነበረውና ያንንም ልዩ ዕድል አውቆ ለመጠቀም ሲሞክር በወጣትነት ዕድሜው ላይ የተቀጨ መሪ ነበር። በብሔር ግንዱ ኦሮሞና አማራ የነበረ፣ በሃይማኖት ጀርባዉ ክርስቲያንና ሙስሊም የነበረ ሰዉ ነዉ። ከወሎም በመወለዱ፣ ትግራይንና ሸዋን ለማገናኘት የተሻለ ድልድይ ለመሆን ይችል ነበር። የሚገርመው ግን፥ የልጅ ኢያሱ ወንጀሎች የሚመነጩት እነዚህኑ አዎንታዊ እሴቶችን ለሀገረ-መንግሥት ግንባታ ለመጠቀም መሞከሩ ነበር። ለምሳሌ አንዳንድ የታሪክ ማስታወሻዎች እንደሚያስረዱት፥ አርሲዎች እንደልጃቸው ይመለከቱት ነበር ይባላል። ከሱማሌዎችና ከአፋሮች ጋር ጥብቅ ግንኙነት እንደነበረው በቂ የሆነ የታሪክ ማስረጃ አለ። ከጎጃሙ ራስ ኃይሉና ከወለጋው ደጃዝማች ጆቴ ቱሉ ጋር የጋብቻ ዝምድና እንደነበረው ይታወቃል። ቤተ ክርስቲያንን ለማሠራት የሚጥረውን ያክል (ለምሳሌ የቀጨኔውን መድሃኔዓለምን እሱ ነው ያሠራው ይባላል) መስግዶችን ያሠራ ነበር። ከሥልጣን ላወረዱት የሸዋ ሊሂቃን ግን፤ አንዱና ትልቁ የልጅ ኢያሱ ወንጀል መስጊዶችን ማሠራቱ ነበር። የመጨረሻው ትልቁ ወንጀል ደግሞ ኢትዮጵያን ለመቀራመት ያንዣበቡ የቅኝ ገዥ ኃይሎች ከሰሜንና ምስራቅ ጣሊያን፣ በምዕራብ፣ በደቡብና በምስራቅ እንግሊዝ፣ በምስራቅ ፈረንሳይ የሦስትዮሽ ስምምነት (tripartite treaty) የሚባለውን እ.አ.አ በ1903 ፈርሞ የምኒልክን ሞት ይጠብቁ ከነበሩት መራቅና በአንደኛው የዓለም ጦርነት በአከባቢያችን ግዛት ካልነበራቸው ከነጀርመንና ቱርክ ጋር ለመደጋገፍ መሞከሩ ነበር።

    በጥቅሉ ከሁሉም በላይ ወንጀሎቹ ሰፊዋን ኢትዮጵያን የፈጠርን እኛ ነን የሚሉትን የሸዋ ልሂቃንን መጋፋቱ ነበር። በግልፅ ቋንቋ ለማስቀመጥ፥ የኢያሱ ወንጀሎች የሸዋ ልጅ አለመሆኑ (የኢያሱ አባት ወሎ ነው)፣ ሐቀኛ የክርስቲያን ልጅ አለመሆኑ (አባቱ የግድ ክርስቲያን ከመሆናቸው በፊት መሐመድ ዓሊ ነበሩና) እንዲሁም የአውሮፓ የቅኝ ገዥ ኃይሎችን ማስቀየሙ ናቸው።

    እ.አ.አ በ1916 በመስቀል ቀን ኢያሱን ለማውረድ ሁሉም መሣሪያዎቻቸውን ይዘው ተሰለፉ። ቄሶቹ ኢያሱ ሐቀኛ የክርስቲያን ልጅ አይደለም በማለት በማውገዝ፣ የሸዋ ሊሂቃን ሠራዊታቸውን በመሳለፍ፣ የአውሮፓዊያኑ መንግሥታት ምክርና ጥበባቸውን ይዘው ተሰለፉ። የአውሮፓዊያኑ ጥበብ የሚገርም ነበር፤ ኢያሱ በኢትዮጵያ ባንዲራ ላይ የእስልምና ምልክት የሆነውን ግማሽ ጨረቃ ለጥፎ ለቱርኮች ዲፕሎማት ሲሰጥ የሚያሳይ ፎቶ ሾፕ የሆነ ሥዕል (ፎቶ ሾፕም፣ የባንድራ ፖለቲካም በልጅ ኢያሱ ዘመንም ነበር) መፈንቅለ መንግሥት እንድያከሄዱ የሸዋ ሊሂቃንን መርዳት ነበር። እዚህ ላይ ለታሪክ ትዝብት አንድ ነገር ልብ በሉልኝ። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ሳስተምር፥ የሀገረ-መንግሥት ግንባታ ችግሮቻችንን በሚመለከት ፈተናም ፈትኜበታለሁ፤ የሸዋው ጦር መሪ የነበሩት ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ የመፈንቅለ መንግሥቱም መሪ ነበሩ፤ ልጅ ኢያሱን ሲያወርዱ ባስተላለፉት መልዕክት ውስጥ የሚከተለው ይገኝበታል።

    “He claims that he eats flesh of cattle slain by Muslims in order to extend frontiers and to win hearts. But these Somali and Muslims have already been brought to heel [and do not need such diplomacy]”

    በጥሬው ሲተረጎም፥ ግዛትን ለማስፋፋትና ልቦችን ለመሳብ ብዬ በሙስሊም የታረደውን የከብት ሥጋ እባላለሁ ይላል። ነገር ግን እነዚህን ሱማሌዎችና ሙስሊሞችን ቀድሞውኑ ስላንበረከክን እንዲህ ዓይነቱ ዲፕሎማሲ አያስፈልጋቸውም።

    ይህንን የሀብተጊዮርጊስን ንግግር በሚመለከት ሰፊውን ትንተና ለናንተ ትቼ፥ በዚህ ዓይነት የተዛባ አመለካከት ላይ የተገነባችውን ኢትዮጵያን አስተካክሎ በሰፊ መሠረት ላይ የተገነባችውን ኢትዮጵያን ለመፍጠር የተደረገው የመጀመሪያ ሙከራ፥ ልጅ ኢያሱን ለሥልጣን ተብሎ በተጠነሰሰው ሤራ መውረዱን እንዳትረሱት አደራ ማለት እፈልጋለሁ። ያመለጠንን ዕድል ትርጉም ግን ለታሪክ መተውን አመርጣለሁ።

    2) ኢያሱን በወሳኝነት የተኩት ንጉሥ ኃይለ ሥላሴ

    የሀገራችንን ሀገረ-መንግሥት ግንባታን በተሻለ መሠረት ላይ ለመገንባት ረጅም ጊዜ (ለ60 ዓመታት ገደማ አገሪቷን መርተዋል) በልጅነታቸው የተሻለ የፈረንጅ ዕውቀት የቀመሱና ከማንም የበለጠ ተደጋጋሚ ዕድል ያገኙ ነበሩ። ነገር ግን በእኔ ግምት ታሪክ የሰጣቸዉን ዕድል አልተጠቃሙበትም። ንጉሥ ኃይለ ሥላሴን የተለያዩ ሰዎች በተለያዩ የታሪክ ሚዛን ላይ ቢያስቀጣቸውምና እኔም ቢሆን በዘመናዊ ትምህርትና በመሳሰሉት ላይ የነበራቸውን አሻራ ቀላል ነው ብዬ ባላስብም፥ ንጉሡ ሕይወት ዘመናቸውን በሙሉ የግል ዝናንና ሥልጣንን ማዕከል ማድረጋቸው ኢትዮጵያዉያንን የ20ኛው ክፍለ ዘመን ሕዝቦች ማድረግ አልተቻላቸውም። ስለዘር ግንዳቸው ሀሜቱ እንዳለ ሆኖ፥ ከኢያሱ በተሻለ ደረጃ ኦሮሞም፣ ጉራጌም አማራም ነበሩ። ይህንን ስረ ግንድ አልተጠቀሙም። በተለይ ኦሮሞ ከሚባል ሕዝብ ሲሸሹ እንደኖሩ ብዙ ማስረጃዎች አሉ። ለማንኛዉም፤ አንድንድ ወሳኝ ነገሮችን እንመልከት።

    አምቦ 2ኛ ደረጃ ተማሪ በነበርኩበት ጊዜ የሰማሁት ይመስለኛል፤ አንድ ጋዜጠኛ ካነበቡት መጽሐፍት ዉስጥ የትኛውን እንደሚያደንቁ ሲጠይቃቸው፥ ቀልባቸውን በጣም የሳበውና ብዙ ጊዜ ደጋግመው ያነበቡት በኒኮሎ ማኪያቬሊ (Niccolò Machiavelli) የተፃፈውን “The Prince” የተባለውን እንደነበረ ትዝ ይለኛል። ንጉሡ አብዘኛዉን የሕይወት ዘመናቸዉን የተመሩት በማኪያቬሊ ምክር ነበር ብዬ እጠረጥራለሁ። በማክያቬሊ ትምህርት በመመራትም የሥልጣን ተቀናቃኞቻቸውን አንድ በአንድ አስወግደው ከአስራ አራት ዓመታት በኋላ እ.አ.አ በ1930 ጥቁር ማክያቬሊ ፈላጭ ቆራጭ ንጉሥ ሆነው ወጡ።

    እንደ ሀብተጊዮርጊስ ዓይነቱን እግዚአብሔር በጊዜ ሲገላገልላቸው፣ እንደ ጎንደሩ ራስ ጉግሳና ባለቤታቸው ንግስት ዘዉድቱን ያስወገዱበት የፖለቲካ ጥበብ፣ በጊዜው በርግጥም አስደናቂ ነበር። ይህ የንጉሡ ጥበብ፤ አርባ ዓመታትን ቆጥራ የአድዋን ሽንፈት ለመበቀል የመጣቸውን ጣሊያንን ለመከላከል አልረዳም። መንግሥታቸዉንም፤ ሀገሪቷንም ለክፉ ቀን አላዘጋጁም።

    አድዋ ላይ ታሪካዊ ድል ያስገኙ ጀግኖችም የሉም። አንድ ለታሪክ የተረፉት ደጀዝማች ባልቻ ሣፎም በንጉሡ ዉሰኔ እስር ቤት ነበሩ። እዚህም ላይ አንድ የታሪክ ትዝብት አስቀምጬ ማለፍ እፈልጋለሁ። ኃይለ ሥላሴ ለሥልጣናቸዉ ብሎ የገፏቸው ብዙ የአከባቢ መሪዎች፥ ከትግራዩ ደጃዝማች ኃይለሥላሴ ጉግሳ ጀምሮ የጎንደር፣ የጎጃም፣ የሸዋ፣ የጅማ፣ የወለጋ ገዥዎች የጣሊያን ባንዳ ሆኑ። ከሚታወቁት ውስጥ ለታሪክ ‘ተፈሪ ሌላ፣ ሀገር ሌላ’ ብለው ሲዋጉ የሞቱት ደጃዝማች ባልቻ ብቻ ነበሩ። በንጉሡ ስህተት ሀገሪቷ ውድ ዋጋ ከፍላለች። ለዚህ ነው ጠቅላይ ሚኒስቴሩን ጨምሮ የብልጽግና ፓርቲ ባለሥልጣናት ጠዋትና ማታ ባንዳ፣ ባንዳ ሲሉ፥ ግብፅ ሱዳንን ይዛ የምር ከመጣች ሰው ያላሰበውን አሳስበው ለኪሳራ እንዳይዳርጉን የሚፈራው።

    ያም ሆነ ይህ፥ ኃይለ ሥላሴ ለጦርነት ያላዘጋጇትን ሀገር በክፉ ቀን ጥለው ሸሹ። ሐረርጌ ላይም የጂቡቲን ባቡር ሲሳፈሩ ከጦር ሜዳ መሸሻቸውን ለመሸፈን፥ ‘የት ይሄደሉ?’ ብሎ ለጠያቀቸዉ የፈንሳይ ጋዜጠኛ፡ “Je ne suis pas né soldat” (“ወታደር አይደለሁም”) ብለው ያለፉት። ለሳቸዉም ፍትሃዊ ለመሆን፥ የአውሮፓ ዲፕሎማቶች ቢክዷቸውም በዓለም መንግሥታት ማኅበር ላይ የሚያስመካ ሥራ ሠርተዋል። ሆኖም ከጦር ሜዳ የመሸሻቸው ጉዳይ እስከ መንግሥታቸው ፍፃሜ ድረስ እንደ ጥቁር ነጥብ ስትከታላቸዉ ኖራለች። የአርበኞችም ሆነ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ዋናው የተቃውሞ መፈክርም ይህች የሽሸት ጉዳይ ነበረች። ከጣሊያን ወረራ በኋላም ንጉሥ ኃይለ ሥላሴ በሁለት መሠረታዊ ነገሮች ምክንያት፥ ጋዜጣቸውን “አዲስ ዘመን” ብለው እንደሰየሙ፥ በእርግጥም አዲስ ዘመን፤ ለአዲስቷ ኢትዮጵያ ይፈጠራሉ ብሎ የጠበቁ ብዙ መሆናቸውን ብሎ መገመት አስቸጋሪ አይመስለኝም።

    ለአምስት ዓመታት በእንግሊዝ ሀገር በስደት ሲኖሩ ስለራሳቸው ስህተትም ሆነ የሰለጠነው ዓለም ንጉሦች እንዴት ሕዝቦቻቸውን እንደሚመሩና በዚያም ምክንያት በሕዝቦቻቸው ዘንድ ተከብረው እንዴት እንደሚኖሩ ተምረዋል ብሎ መጠበቅ ይቻል ነበር። ከሁሉም በላይ በጣሊያን ወረራ ምክንያት እሳቸውንም ሆነ ሀገራቸውን ከገጠመው ውርደትና ኪሳራ ይማራሉ ተብሎ ይጠበቅም ነበር። ከሁሉም አልተማሩም። በባሰ ሁኔታና ፍጥነት ወደ ድሮአቸው ተመለሱ። ለዓቢይነት፥ አስተዳደራቸውን የተቃወሙ የራያ ገበሬዎችን (ቀዳማይ ወያኔ የሚባለዉ ነዉ) ከየመን በመጡ የእንግሊዝ አይሮፕላኖች አስደበደቡ። የሪፐብሊካን አስተሳሰብ ነበራቸው የሚባሉትን አርበኛ ደጃዝማች ታከለን (ደጃዝማች ታከለ ወልደሀዋርያት) አሰሩ። እኚህ ሰው ከተደጋጋሚ እስር በኋላ በመጨረሻም ሊይዟቸው ከተላኩ የንጉሡ ወታደሮች ጋር ሲዋጉ ሞቱ። ሌላው ስመጥር አርበኛ የነበሩ በላይ ዘለቀንም ያለርህራሄ ሰቀሉ።

    የአምባሳደር ብርሃኑ ድንቄ ግልፅ ደብዳቤ እንኳን (አምባሳደር ብርሃኑ፤ በአሜሪካ አምባሳደር የነበሩና ንጉሡ የገፉበት መንገድ ዉሎ አድሮ ንጉሡንም ሆነ ሀገሪቷን ለዉርደት እንደሚያበቃ የመጀመሪያ የማስጠንቃቂያ ደወል በአደባባይ የሰጡ ባለስልጣን ነበሩ) አሠራራቸውን አላስለወጧቸውም።

    በፖለቲካ ሥርዓታቸው ላይ በተከታታይ ቦንቦች ፈነዱ። የመጀመሪያዉ ትልቁ ቦንብ በራሳቸው ቤተ መንግሥት ውስጥ የፈነዳው የነመንግሥቱ ንዋይ ያውም የእሳቸውን ክብርና ሞገስ ለመጠበቅ ከፈጠሩት የክብር ዘበኛ ጦር ነበር። ንጉሡ ከክስተቱ ከመማር ይልቅ ጀኔራል መንግሥቱ ንዋይን በሞት ቀጡ፤ የታናሽ ወንድማቸውን ሬሳ እኔን ያየህ ተቀጣ በሚመስል መንገድ በስቅላት ቀጡ። የበሉበትን [ወጭት] ሰባሪዎች ናቸው ብለውም በአዝማሪ አዘለፏቸው።

    ማን እንደመከራቸው ባይታወቅም ትልቁን የመንግሥታቸውን የዲፕሎማሲ ውጤትን ያበላሸውና ለትልቅ ኪሳራ ያበቃንን የኤርትራን ፌዴሬሽንን አፈረሱ። ውጤቱም ሁላችንም እንደምናውቀው የኤርትራ ነፃ አውጪ ግንባር መፈጠር ሆነ። ትንሽ ቆይቶ ደግሞ ኦሮሞዎች የሜጫና ቱለማ ልማት ማኅበር በመፍጠራቸው ጠገቡ ተብሎ መሪዎቹ እነ መቶ አለቃ ማሞ መዘምር ተሰቀሉ፤ ኃይለማርያም ገመዳ እስር ቤት ውስጥ በተፈፀመበት ድብዳባ ሞተ። ጀኔራል ታደሰ ብሩ ሞት ተፈርዶባቸው በአማላጅ ወደ ሐረርጌ በግዞት ተላኩ። እኔ እስከ ማውቀው ድረስ ሁሉም በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ጥያቄ አልነበራቸውም። ውጤቱ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)ን መፍጠር ሆነ። በነገራችን ላይ በእነ ኤሌሞ ቅልጡ በኦነግ ስም የመጀመሪያዋ ጥይት የተተኮሰችው ጀኔራል ታደሰ ብሩ የታሰሩበት ሥፍራ ሐራርጌ ዉስጥ ነበር። በዚሁ ጊዜ ሰፋፊ ማኅበራዊ ፍትህን የሚጠይቁ ተከታታይ ጥያቄዎችም መቅረብ ጀመሩ። እ.አ.አ በ1965 የንጉሡ ፊውዳላዊ ሥርዓት የተመሠረተበት ላይ በመሬት ላራሹ ሰልፍ ድንገተኛ የፖለቲካ ቦንብ ፈነዳ። ከአራት ዓመት በኋላ ደግሞ እስከዛሬ ኢትዮጵያን እያመሰ ያለው በእነ ዋለልኝ መኮንን የብሔረሰቦች ጥያቄ ታወጀ። ይህችኛውን ንጉሡና ሥርዓቱ በቀላሉ የተመለከቷት አይመስልም። ንጉሡ የቀ.ኃ.ሥ ዩኒቨርሲቲ፥ የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ማኅበር ፕሬዝደንት የነበረውን ጥላሁን ግዛዉን በማሰገደል “ልጆቼ” ከሚሏቸው ተማሪዎች ጋር ደም መቃባት ዉስጥ ገቡ። በዚህም የታሪክ ጎማው ወደፊት እንዳይሽከረከር ጣሩ።

    አሳዛኙ ጉዳይ መካሪዎቻቸውም ሆኑ እሳቸው አስተዳደራቸው ለሃያኛዉ ክፍለ ዘመን የማይመጥን መሆኑን፣ በጣም እወዳታለሁ የሚሏትም ኢትዮጵያ በታሪክ ፍራሽ ላይ ተኝታ የምትሸሞነሞን ሀገር መሆኗን አልተረዱም። የኤርትራ ግንባሮች ጥይትም ከረጅም ዘመን እንቅልፋቸው አላነቋቸውም። የባሌና የጎጃም ሕዝብ አመፅም አልቀሰቀሳቸውም። ለዓመታት የቆየው የተማሪዎች ንቅናቄ ጩኸትም አላነቃቸውም። ከኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ በቀጥታ የወጡ የመኢሶንና የኢህአፓ የሶሻሊስት አብዮት ደወልም አላነቃቸውም። በመጨረሻም በመቶ ሺዎች የሚቆጠረው የወሎ ሕዝብ እልቂት እንኳን ከእንቅልፋቸዉ አላበነናቸውም።

    በነገራችን ላይ፥ ብልጡ ደርግ በጠዋቱ ሊያወርዳቸው፣ ማታ ያሳየው የወሎ ሕዝብ እልቂት፥ በአንድ በኩል የንጉሡ ውሻ በጮማ ሥጋ ሲጫወት፣ በሌላ በኩል ደግሞ በረሃብ በተረፈረፈ ሕዝብ ውስጥ ሕፃን ልጅ የሞተች እናቷን ጡት ስታጠባ የሚያሳየዉን የጆናታን ዲምበልቢ (Jonathan Dimbleby, “The Unknown Famine”) ፊልም ነበር። ያንን ፊልም ደርግ በቅድሚያ ንጉሡና የኢትዮጵያ ሕዝብን እንዲያዩ ስለጋበዘ ቴሌቪዥን ያልነበረን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በስድስት ኪሎና አራት ኪሎ አካባቢዎች ያሉትን ቡና ቤቶችን አጣብበን ስንመለከት ነበር። የንጉሡ ደጋፊዎች እንኳ ጃኖሆይ እንዲህ ጨካኝ ነበሩ እንዴ? የሚሉትን ይዘን ወደ ዶርማችን እንደገባን ትዝ ይለኛል። ምናልባት ከእንቅልፋቸው የነቁት በማግስቱ የደርግ አባላቱ በኩምቢ ቮልስዋገን ከቤተ መንግሥታቸው ወደ አራተኛ ክፍለ ጦር ሲወስዷቸው በሠሩባቸው ድራማ ይመስለኛል። ብልጣብልጦቹ ደርጎች የተጠቀሙት ቮልስ መጀመሪያ መስኮቷ ዝግ ነበር ይባላል።

    ንጉሡ ከውጭ ብዙ ሰው ሲጮህ ተመልክተው፥ “እናንተ ልጆች የሚወደን ሕዝባችን ንጉሤን የት እየወሰዳችሁ ነው እያለ ነዉ” ሲሉ፥ ብልጦቹ ደርጎችም መስኮቱን ከፍተው የሕዝቡን ድምፅ ሲያሰሟቸው ጩኼቱ “ተፈሪ ሌባ፤ ተፈሪ ሌባ” የሚለውን ሰምተው፥ “አይ ኢትዮጵያ ይኼን ያክል በድዬሻለሁ እንዴ?” አሉ ይባላል። በዚህ ሽኝታቸው ድሮ ቤተ ክርስቲያን ሲሄዱ ዳቦ የሚጥሉላት ለማኝ ዳቦዋን ስትጠብቅ፥ ‘ንጉሡ ወረዱ፤ ንጉሡ ወረዱ’ ሲባል ሰምታ፥ ‘ለዚህ ያበቃኸኝ አንተ ነህ!’ ብላ በቮልሷ አቅጣጫ የወረወረችው ዳቦ ብቻ ነበር ይባላል። የንጉሡ ሬሳም ከ17 ዓመታት በኋላ ከመንግሥቱ ኃይለማርያም ሽንት ቤት ሥር ተቆፍሮ እንደተገኘ ይታወቃል። እዚህ ላይ ልብ አድርገን ማለፍ ያለብን የፖለቲካ ቁም ነገር ለ60 ዓመታት ገደማ (የአምስት ዓመቱ የጣሊያን ወረራ እንዳለ ሆኖ) በፈላጭ ቆራጭነት ኢትዮጵያን ሲገዙ የሀገረ መንግሥታቸው ግንባታ ፕሮጀክት በአጉል ምክርም ይሁን በራሳቸው ገታራ አቋም ከሽፎ ሽኝታቸው በለማኟ ዳቦ፣ ቀብራቸው ደግሞ በአሳደጓቸው ወታደሮች ሽንት ቤት ሥር መሆኑ ነው።

    3) አብዮቱ እና የደርግ የሀገረ-መንግሥት ግንባታ ሙከራ

    አዲስቷን ኢትዮጵያን ለመፍጠር ሕዝባዊ አብዮቱ ልዩ ዕድል ፈጥሮ ነበር። አብዮቱ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ማኅበረሰቦች የመጡ የአዲሱ ትዉልድ ምሁራን ድጋፍና ተሳትፎ ነበረው። እንደ አብዮቱ መሪ ወደፊት የመጣውን መንግሥቱ ኃይለማርያምም ‘ቪቫ መንግሥቱ፣ ቪቫ መንግሥቱ!’ ብለን ተቀብለን ነበር።

    የኢትዮጵያ አብዮትን አብዮት ያደረገው የጭሰኝነት ሥርዓትን ያስወገደውና የደርግ እርምጃ (ውለታው የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ቢሆንም) እስከዛሬ በኢትዮጵያ የሕዝቦች የትግል ታሪክ ውስጥ ልዩ ሥፍራ አለው ብዬ ባምንም፥ ነገሮችን በቶሎ የሚያዩ ወጣቶች “ተፈሪ ማረኝ፤ የደርጉ ነገር አላማረኝ ” ማለት የጀመሩት ብዙዉም ሳይቆዩ ነበር። በአጭሩ ለማስቀመጥ፥ የደርግ የሥልጣን ፍቅር፣ የመኢሶንና የኢህአፓ አሳዛኝ ክፍፍል፣ የኤርትራ ግንባሮችና የህወሓት የተናጠል የፖለቲካ ፕሮጀክቶች በአብዮቱ መፈንዳት የተፈጠረውን ልዩ ታሪካዊ ዕድል አምክኖታል።

    ደርግ መሃይምነትና የሥልጣን ፍቅር ስለተደባለቀበት፥ የሶሻሊስት አብዮቱን እንደሰው ማሰርና መግደል ወሰደው። በዚህ ሶቭዬት ህብረት ድረስ ሄዶ የሌኒን ሐውልት አይተው የመጡት ባለሥልጣኖቹ ስለሶሻሊዝም የተማርነው ከበሰበሰ ከቡርዧ ቤተ መፃሕፍት ሳይሆን ከምንጩ ከሌኒን ሀገር ነው እያሉ ተዘባበቱ። ካደሬዎቻቸው ድንቅ የሶሻሊስት ዕውቀታቸውን ከፍተኛነት ለማሰየት በሚመስል መንገድ የስታሊን ቀይ በትር ሥራ ላይ ይዋል አሉ። ደርግ የሱማሌ ወረራን፣ የኤርትራ ግንባሮችና የህወሓት እንቅስቃሴዎች በኢትዮጵያ አንድነት እንዲነግድ ልዩ ሁኔታ ስለፈጠሩለት “አብዮታዊት እናት ሀገር፥ ወይም ሞት!” አለ።

    ከኤርትራ ግንባሮች እስከ ኢህአፓ እና መኢሶን (ኢጭአት/ ኦነግን ጨምሮ ሌሎች ድርጅቶች እዚህ መሃል ናቸው) የኢትዮጵያ ሕዝቦች የአንድነትና የአብዮት ጠላቶች ሆነው ልዩ ልዩ ስሞች ተለጣፈበቸው። በአጭሩ የኢህአፓና መኢሶን መከፋፈልም ደርግን ብቻኛ የሀገር አንድነትና የአብዮት ተወካይ አደረገው። ሌሎች ዝርዝሮችን ትቼ ለኢትዮጵያ አንድነትና አብዮት ግንባታ ወሳኝ የሆኑ እርምጃዎችን ላንሳ።

    የደርግ የመጀመሪያው ሊቀ መንበር አማን አንዶም የሚባሉ ኤርትራዊ ጀኔራል ነበሩ። የደርግ ሊቀ መንበር ተብሎ ከደርግ ውጭ የተመረጠትም ለኢትዮጵያ አንድነት ብሎ እስከ ሞቃዲሾ ድረስ ሄዶ ካልተዋጋሁ ብሎ ንጉሡን ያስቸገሩ መኮንን ስለነበሩ ነዉ። በወታደሮቹ ዘንድም ተወዳጅ ስለነበረ በራሳቸው በደርግ አባሎቹ ጥያቄ መጀመሪያ መከላከያ ሚኒስቴር፣ ከዚያም ከደርግ ውጭ የደርግ ሊቀ መንበር የሆነው የተመረጡትና በአደባባይ እስከሚታወቀውም በኢትዮጵያ አንደነት ላይም (መቼም በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ልዩ ፍቅር አለን የሚሉ ብዙ ቢኖሩም፥ ፍቅራቸውን የሚለካልን መሣሪያ በሜዲካል ሳይንስ እስካሁን አልተፈጠረልንም) ምንም ዓይነት ጥያቄ ያልነበራቸውና የኤርትራን ችግር በሰላም ለመፍታት አሥመራ ድረስ ሄዶ ሕዝቡን ያወያዩ ነበሩ። ለኢትዮጵያ ልዩ ፍቅር አለኝ የሚሉ እነሻለቃ መንግሥቱ ኃይለማርያም ግን ጠረጠሯቸዉ፤ በታንክ እቤታቸው ውስጥ ገደሉት። በእኔ ግምት ውጤቱ የኤርትራና የኢትዮጵያን አንድነት መግደል ነበር። በዚህም ኤርትራ የደም ምድር ሆነች። ዛሬ እንዲህ ልንሆን የፈሰሰው የሰው ደም ዋጋም ሆነ ለጠፋው ሀብትና ንብረት ሂሳብ ለፈረደበት ታሪክ መተው ይመረጣል።

    የብሔራዊ አንድነት መንግሥትን ልታመጡብኝ ብሎ መንግሥቱ ኃይለማርያም ሁለተኛውን የደርግ ሊቀ መንበር የነበሩትን ጀኔራል ተፈሪ በንቲን ከደጋፊዎቻቸው የደርግ አባላት ጋር ረሸናቸው።

    ኮሎኔል አጥናፉ አባተንም ቅይጥ ኢኮኖሚ ልታመጣብን ነው ብሎ መንግሥቱ ኃይለማርያም በፀረ-አብዮታዊነት ረሸነዉ። በነገራችን ላይ የመጨረሻ ጭንቅ ሲመጣ መንግሥቱ ኃይለማርያም የአጥናፉን ቅይጥ ኢኮኖሚ ላይ ለመንጠላጠል ሞክሮ ነበር።

    በዛሬው የኦሮሞ ፖለቲካ ውስጥ ልዩ ሥፍራ ያላቸው ጀኔራል ታደሰ ብሩ ለሁለተኛ ጊዜ ሞት ተፈርዶባቸው ተረሸኑ። እኔ መከታተል እስከቻልኩ ድረስ ታደሰ ብሩ በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ፍጹም ጥያቄ ያልነበራቸው፤ ለኢትዮጵያ ብሎ ከሰላሌ ጫካ እሰካ ሞቃዲሾ ድረስ ተወስደው የታሰሩ እንግሊዞች ኢትዮጵያን ነፃ እናወጣለን ብለው ሲመጡ ከነሱ ጋር እየተዋጉ የመጡ አርበኛ ነበሩ። ከተራ ወታደርነት እስከ ጀኔራል ማዕረግ ድረስ ሀገራቸውን ያገለገሉም ነበሩ። እግር ጥሏቸው አብዮቱ ውስጥ የገቡት መንግሥቱ ኃይለማርያም ያላርህራሄ ገደሏቸዉ። በነገራችን ላይ ከጀኔራል ታደሰ ብሩ ጋር በፀረ አንድነት ክስ የተገደለ፣ ብዙ ሰው የማያስታውሰው መለስ ተክሌ የሚባል በቀ.ኃ.ሥ ዩኒቨርሲቲ ከተማሪ መሪዎች አንዱ የሆነ የትግራይ ተወላጅ ነበር (በጊዜዉ ከነበረዉ አቋም ተነስቼ፥ ይህ ሰው ቢቆይ ኖሮ የትኛው ድርጅት ውስጥ ሊገባ እንደሚችል ዶክተር አረጋዊን ደግሜ መጠየቄን አስታውሳለሁ)። ይህ ሰዉ ሌላ ተከታይ ቢያጣ ለሩብ ምዕተ ዓመት አከባቢ የምኒልክ ቤተ መንግሥትን ተቆጣጥሮ በፈላጭ ቆራጭነት ሀገሪቷን የገዛው ለገሠ ዜናዊ ስሙን አንስቶ ትግራይ በረሃ ገብቷል። ይህም ደርግ በኢትዮጵያ አንድነት ስም ያመጣብን የታሪክ ዕዳ ነው።

    በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ምንም ዓይነት ጥያቄ እንዳልነበራቸው በተሻለ የማውቃቸውን የመኢሶን መሪዎችን ላንሳ። ለሥልጣን ተብሎ በደርግና ብዙ የፖለቲካ ተቀናቃኞቹ ዘንድ እንደ ኦሮሞ ድርጅት፥ በኦሮሞ ደግሞ እንደነፍጠኛ ድርጅት የሚታየው መኢሶን በዘመኑ በየትኛውም ሚዛን የተሻለ ትምህርት የነበራቸው መሪዎች ነበሩት፤ በስብጥራቸውም ኤርትራዊ የዘር ግንድ አላቸው ከሚባሉት ኅሩይ ተድላ እና አበራ የማነአብ እስከ ሲዳማው እሼቱ አራርሶ የነበሩበት ነው። ሽኩሪ የሚባል አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አብረን የነበርነው ልጅ በስተቀር ሰፊ ተሳትፎ እንደልነበራቸዉ የማዉቀዉ የሱማሌ ምሁራንን ብቻ ነበር።

    የመጀመሪያዉ የመኢሶን ሊቀ መንበር የሰሜን ሸዋ አማራ ከሚባለው የተወለዱ፥ ዶ/ር ወርቁ ፈረደ፣ ሁለተኛው ኃይሌ ፊዳ፣ ሦስተኛው የወሎ አማራ ከሚባለው የመጡ ዶ/ር ከበደ መንገሻ ነበሩ። ሕብረ ብሔር ነን፤ ለሀገረ- መንግሥት ግንባታው የተሻለ ግንዛቤም እዉቀትም አለን ለሚሉ የመኢሶን ምሁራንም ደርጎች ርህራሄ አላደረጉም። በተለይ የመጀመሪያው የኦሮሞ የምሁር ትዉልድ የሚባሉት ኃይሌ ፊዳን ጨምሮ አብዱላህ ዩሱፍ፣ ዶ/ር ከድር መሀመድ፣ ዶ/ር ተረፈ ወልደፃዲቅ፣ ዶ/ር መኮንን ጆቴ የመሳሰሉት ሕበረ ብሔር በሚባለው መኢሶን ውስጥ አልቀዋል። በእኔ እምነት ብዙዎች ሊቀየሙኝ ቢችሉም፥ እንደስማቸው በኢትዮጵያ ምድር ሕብረ ብሔር የነበሩ ድርጅቶች መኢሶንና ኢህአፓ ብቻ ነበሩ። አላስፈላጊ ክርክር ዉስጥ ሳልገባ፥ እኔ እስከ ማምነው ድረስ ኢሠፓ የወታደሮች ፓርቲ ነበር። የኢህአዴግን ምንነት ለብልጽግና አበላት እተዋለሁ። የብልጽግናን ምንነት ደግሞ የታሪክ ፈተናዉን ሲያልፍ ብንነጋገርበት የተሻለ ይመስለኛል።

    ደርግ ሕበረ ብሔር ድርጅቶችን በቀላሉ አንድ በአንድ ቀርጥፎ በላቸው። ኢህአፓን ቁርስ አደረገ፤ መኢሶንን ምሳ አደረገ:: ብሔር ሆኖ ለመውጣት ገና ዳዴ የሚሉትን ወዝሊግንና ማሌሪድን እራት አደረጋቸው። ከደርግ ዱላ የተረፉት በደርግ አስተዋጽኦ ጭምር በተሸለ ሁኔታ ኃይል ሆነዉ የወጡት የብሔር ንቅናቄዎች ናቸው። ኢጭአት (የኢትዮጵያ ጭቁኖች አብዮታዊ ትግል) ወደ ኦነግ ተጠቃልሎ ገብቶ ዛሬ የምናውቀው ኦነግን ፈጠረ። የሱማሌ ድርጅቶች ኦብነግ ዓይነትን ፈጠሩ። የሲዳማ አርነት ንቅናቄ ቢያንስ ዋናው ክንፍ ዛሬ ሲአን (የሲዳማ አርነት ንቅናቄ) የሚለው ሆነ። አፋሮችም የአፋር ግራ ክንፍ አርዱፍ እያሉ በሕይወት ያሉ ድርጅቶች አሏቸው። በጣም የተሳካላቸው የብሔር ንቅናቄዎች በኢትዮጵያና ኤርትራ ላይ ደርግን ለሁለት ቀብረው መንግሥታት ሆኑ።

    የደረግ ዘመንን ስናጠቃልል መረሳት የሌለባቸው ሦስት ዋና ዋና ጉዳዮች፥ ለሥልጣን ብሎ ደረግ ባካሄዳቸው ጦርነቶች፡-

    የሀገረ-መንግሥት ግንባታውን የበለጠ አወሳስቦ መሄዱን፣
    ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ በፃፉት መጽሐፍ በትክክል እንዳስቀመጡት፥ ደርግ ትቶት የሄደው በደም እምባ የታጠበች ሀገር መሆንዋን፣
    በሀገር አንድነት ስም ባካሄደው ትርጉም-የለሽ ጦርነት የባከነው የሀገር ሀብት ብቻ ሳይሆን በዓለም ትልቋ ወደብ-አልባ ሀገር ኢትዮጵያን ትቶ መሄዱን ነዉ።

    ደርግ ለ17 ዓመታት የተጫወተዉ የአጥፍቶ መጥፋት ፖለቲካን እንደ ኑዛዜም፣ እንደ ቁጭትም የደርግ ከፍተኛ ባለሥልጣን የነበሩት ኮሎኔል ፍስሃ ደስታ (ኮ/ል መንግሥቱ ኃይለማርምም ሆነ ሻምበል ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ እድፋቸውን ከታጠቡበት በጣም ይሻላል) በፃፉት መጽሐፍ ልዝጋ።

    የኢህአፓ ወጣቶችን የትግል ስሜት፣ የመኢሶን መሪዎች ዕውቀትና የእኛን የወታደሮቹን የሀገር ወዳድነት ብንጠቀምበት ኖሮ ሀገራችን እንዲህ አትሆንም ማለታቸውን እስር ቤት ሆኜ ማንበቤ ትዝ ይለኛል። ምክራቸው ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይም የሚሆን ይመስለኛል። በነገራችን ላይ በታሪክ አጋጣሚ ወደ አስር ወሮች ገደማ በኢህአዴግ እስር ቤት የተኛሁበት አልጋ ኮ/ል ፍስሃ ደስታ ይተኙበት እንደነበረ ሰምቻለሁ።

    4) የኢህአዴግ ዘመን የሀገረ-መንግሥት ግንባታ

    ለአራተኛ ጊዜ የሀገራችን ፖለቲካን ማሰልጠንና የተሻለ የሀገረ-መንግሥት ግንባታ ዕድል ያመለጠን የኢህአዴጉ ዘመን ነው (ይህ የመለስ እና የኃይለማርያም ዘመንን ይጨምራል)። የኢህአዴግ ዘመን ሌላው ቢቀር የብሔረሰቦች ጥያቄን ለሁሉም ሕዝቦች ተቀባይነት ባለው መንገድ ይመልሳል ብሎ (እኔን ጨምሮ) የጠበቁ ብዙ ናቸው። ይህም ለሀገረ-መንግሥት ግንባታ የተሻለ ዕድል ይፈጠራል ተብሎም ተገምቶ ነበር።

    ገና የሽግግር መንግሥቱ ሲመሠረት፥ የኢህአዴግ ባለሥልጣናት እንደግል ሠርጋቸው የፈለጉትን ጠርተው፣ ያልፈለጉትን በመተው የሠሩት የፖለቲካ ቲያትር ጫካ ሆነው ስደግፋቸው ከነበሩት የኢህአዴግ መሪዎች ተለየሁ። እኔም ብቻ ሳልሆን ብዙ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህራን ጓደኞቼ በዚህ ጊዜ የተለዩዋቸዉ ይመስለኛል። ኢህአዴግ መጀመሪያ በጦርኛነት፤ ቀጥሎ ደግሞ በዘመኑ ቋንቋ የሽብርተኝነት ታርጋ እየለጠፈ ለ27 ዓመታት ሕዝብና ሀገርን አመሰ። ዝርዝር ነገሮች ውስጥ ሳልገባ፥ በኦሮሚያ እና በሱማሌ ክልሎች፤ በሲዳማ፣ በሀዲያ፤ በወላይታ፣ በጋምቤላ፣ በአፋር፣ ቁጥራቸውን የኢህአዴግ ባለሥልጣናት እንኳ የማያውቁት ሕይወት ጠፋ። የአፍሪካ መዲና የምትባለው አዲስ አበባ/ፊንፊኔም ሆነች የኢህአፓን ጠበል በቀመሱ ብአዴኖች የሚመራው የአማራ ክልልም ውሎ አድሮ ከኢህአዴግ ዱላ አልተረፉም።

    በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም (ነገርየው መሬት ላይ ሲፈተሽ፥ የአብዮታዊነትም የዴሞክራሲያዊነትም ባህርይ አልነበረውም) የተተበተበው የሞግዚት አስተዳደር እውነተኛ የፌዴራል ሥርዓት ሊሆን አልቻለም። የሕዝቦችን እራስን በራስ ማስተዳደር ጋር ምንም ግንኙነት ያልነበረው፥ ጆርጅ ኦርዌል የእንስሳት እርሻ (George Orwell, “Animal Farm”) በሚለዉ መጽሐፉ ላይ፥ ሁሉም እንስሶች እኩል ናቸው፤ አንዳንድ እንስሶች የበለጠ እኩል ናቸው “All animals are equal, but some are more equal than others” ከሚለው ያለፈ የፖለቲካ ፋይዳ አልነበረውም። ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ተብዬዎቹም ከ97ቱ በስተቀር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መፍጠር ይቅርና ቅርጫ እንኳ ሊ ሆኑ አልቻሉም። ዉጤቱም ዴሞክራሲያዊ የሀገረ-መንግሥት ግንባታ ዕድል መጨናገፉ ብቻም ሳይሆን ለ27 ዓመታት ውድ የሕይወት ዋጋ ጭምር ሲያስከፍለን ኖሯል። በዚህም ምክንያት የታሪክ ጣጣችንን አስተካክለን በእኩልነት ላይ የተመሠረተ ዴሞክራሲያዊ ፌዴራሊዝም የመፍጠር ተስፋችን ሕልም ሆኖ ቀርቷል።

    5) በማምለጥ ላይ ያለ አዲስ የሀገረ-መንግሥት ግንባታ ሙከራ

    አሁን እየገጠመን ያለውን የታሪክ ፈተናን ለማለፍ፥ ጨክነን በቁርጠኝኘት ብሔራዊ መግባባት ውስጥ መግባት ወይም ኢትዮጵያን እንደ ሀገረ-መንግሥት የምታበቃበት የሚጨምር ቀውስ ውስጥ መግባት ይመስለኛል። እዚህ ላይ የሌሎች ሀገሮችን ፖለቲካ በድኅረ ቅኝ ግዛት ዘመን ብቻ እንኳን በመቀኛት ብጀምር፥ ችግሮቻቸውን ለመፍታት በቁርጠኝነት የሠሩት ተሳክቶላቸዋል። ያንን ያልቻሉት ወይ ፈርሰዋል ወይም አሁንም በቀውስ ውስጥ እየዳከሩ ነዉ። ቅኝታችንን በላቲን አሜሪካ ብንጀምር፥ ቀዉስ ገጥሟቸዉ አነ አርጀንቲና፣ ቺሌ፣ ፔሩ፣ ኒካራጓ፣ ኮሎምቢያ የመሰሰሉ ሀገሮች በተለያየ ደረጃ ፖለቲካቸውን ያስተካከሉ ሀገሮች ናቸው። ከ60 ዓመታት በላይ ለልዕለ ኃያሏ አሜሪካ ሳትበገር በአሜሪካ አፍንጫ ሥር የኖረችው አስደናቂዋ ሶሻሊስት ኩባና በአሜሪካ ጣልቃ ገብነት ምክንያት አሁን በሁለት ፕሬዝዳንቶች የምትገዛዋ ሶሻሊስት ቬኔዙዌላም በዚሁ ክፍለ ዓለም ይገኛሉ። በአውሮፓ ፖርቹጋል፣ ስፓኝ፣ ግሪክ፣ ፖለቲካቸዉን ማስተካከል ችለዋል። ዩጎዚላቪያ ውድ ዋጋ ብትከፍልም ከመፍረስ አልደነችም። ሶቭዬት ህበረትና (ግማሽ አውሮፓ ነች) ቼኮዝላቫኪያ በሰላማዊ መንገድ ፈርሰዋል። በኤዥያ፥ ኔፓል የፓለቲካ ችግርዋን በብሔራዊ መግባባት ስትፈታ፥ፓኪስታን፣ ቬየትናም፣ ካምቦዲያና ላኦስ ደግሞ ችግሮቻቸውን በጦርነት ፈተዋል። አፍጋኒስታን፣ ኢራቅ፣ ሶሪያና የመን አሁንም እየቀወሱ ነው። ወደ አፍሪካችን ስንመጣ፥ ደቡብ አፍሪካና ጋና ከመሳሰሉት በስተቀር አብዘኛዎቹ በይስሙላ ምርጫ ላይ የተመሠረቱ አምባገነን መንግሥታት ሲሆኑ፥ የአፍሪካ ሕብረትም የዲክታተሮች ማኅበር (trade union of dictators) ከመሆን አላለፈም (በኢህአዴግ ጊዜ የተከሰስኩበት አንዱ ወንጀሌ የአፍሪካ መሪዎችን ተሰደብክ የሚል ነበር)። ሱማሊያና ሊቢያ ፈረንጆች የወደቁ መንግሥታት (failed states) የሚሏቸው ሲሆኑ፤ ሩዋንዳ ጊዜውን ጠብቆ የሚፈነዳ ሌላ ቦንብ የምትጠብቅ ይመስለኛል።

    በዚህ የአፍሪካ ፖለቲካ ምስቅልቅል ጉዞ ውስጥ አንዱ የሚገርመኝ ላለፉት 60 ዓመታት ፖለቲካቸውን ማስተካከል አቅቷቸው በቀውስ ሲናጡ የኖሩ ሁለት ሀገሮች፥ በተፈጥሮ ፀጋ እጅግ ሀብታሟ የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፑቢሊክና የሦስት ሺህ ዓመታት ዕድሜ አለኝ የምትለዋ ድሃዋ ኢትዮጵያ መሆናቸው ነው።  ከንጉሡ ዘመን ጀምሮ ይህንኑ የሀገራችንን የፖለቲካ እንቆቅልሾችን የተከታተለ፣ ያጠና፣ ያስተማረና ብዙ ጽሑፎችን የፃፈበት ጆን ማርካከስ (John Markakis) የሚባል ፈረንጅ፥ የታሪክና ፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሴር “Ethiopia: The Last Two Frontiers” (የኢትዮጵያ፥ የመጨረሻዎቹ ሁለት ድንበሮች) ብሎ ፅፏል። ምሳ ጋብዞኝ መፅሐፉን ለዶ/ር ዓቢይ ስጥልኝ ብሎኝ፥ ዶ/ር ዓቢይ ያንብበው አያንብበው ባላውቅም፥ እሳቸውን ማግኘት ለሚችል ለኦፒድኦ ባለሥልጣን ልኬላቸው እንደነበርም አሰታዉሰለሁ። መፅሐፉ በአጭሩ የኢትዮጵያ መሪዎች የሀገረ-መንግሥት ግንባታ የንጉሦቹ ሞዴል (the Imperial model) ፣ የደርግ የሶሻሊስት ሞዴልና የኢህአዴጉ ፌዴራሊስት ሞዴል በሙሉ ከሽፈዋል ይላል። የከሸፉበትም ዋናዉ ምክንያት የባለጊዜ ገዥዎችን ሥልጣን ለማሳካት የተገፋበት መንገድ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን እኩልነት ያላጎናፀፈና የልማት ጥማታቸውንም ያላረካ በመሆኑ ነው ይላል።

    ይህ የፈረንጅ ምሁር እንዳለው፥ ፖለቲካችንን ማሰልጠን ባለመቻላችን ሚሊየኖች ሕይወታቸውን አጥተዋል፤ ሚሊዮኖች ከቀዬያቸው ተፈናቅለዋል፤ ሚሊዮኖችም ተሰደዋል። እኔም ከላይ ባነሳሁት ከዚሁ ምሑር ዕይታ ተነስቼ ሀገራችን ስለገባችበት የፖለቲካ ቅርቃርና በብሔራዊ መግባባት አንፃር ከቅርቃሩ ለማውጣት በሌኒን ቋንቋ ምን መደረግ አለበት (What is to be done?) የሚለውን መሠረታዊ ጥያቄ የሀገራችን ፖለቲካ እስከገባኝ ድረስ ልመልስ።

    1. መሠረታዊ ችግራችን በታሪክ አጋጣሚ ሥልጣን ላይ የወጡ መሪዎቻችን ሀገርን የመምራት ሕልማቸው፤ ሥልጣንን ጨምድዶ ከመቆየት ሕልማቸው ጋር ሁሌ ስለሚጋጭባቸው ነው። ለሕዝብ አለን ከሚሉት ፍቅር የሥልጣን ፍቅራቸው ስለሚበልጥባቸው ነው። ለዚህ ነው ንጉሥ ኃይለ ሥላሴ የሚወደንና (ሕዝቡ ምን ያከል እንደሚወደቸዉ እንዴት እነዳወቁ ባናዉቅም) የምንወደው ሕዝባችን ሲሉ ኖረው ለ60 ዓመታት ገደማ የገዟትን ኢትዮጵያ ለ20ኛዉ ክፍለ ዘመን ሳያበቁ ከዓለም ሀገሮች ጭራ ደረጃ ትተዋት የሄዱት። የሕዝብ ፍቅራቸውንም ደረጃ በረሃብ በመቶ ሺህዎች ያለቀው የወሎ ሕዝብ ይመሰክራል። ይህን የመሳሰሉ የመሪዎቻችን ባዶ የሕዝብና የሀገር ፍቅር፥ የንጉሡ ሕይወቴና የኢትዮጵያ እርምጃ፣ የመንግሥቱ ኃይለማርያም አብዮታዊት እናት ሀገር ወይም ሞት የመለስ ዜናዊ በቀን ሦስት ጊዜ የሚመገቡ ዜጎችን እፈጠራለሁ ወ.ዘ.ተ መሸፈን አይችልም። ለዚህ አሁን ያሉ መሪዎቻችንም ሆኑ ተስፈኛ መሪዎች ይህንን የታሪክ እውነታ በውል እንዲገነዘቡት እፈልጋለሁ።
    2. የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችና የተቀሩት ልሂቃን በተለያየ ደረጃ የሚጋጩ ሕልሞቻቸውን ይዘው መጓዛቸው ነው። ከመኢሶንና ኢህአፓ ዘመን እስከዛሬ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶቻችንና መሪዎቻቸው ይህንን እውነታ በውል መገንዘብ ይኖርባቸዋል። የሕልሟን ጉዳይ በፈንጆቹ አባባል ከዜሮ ድምር ፖለቲካ (zero-sum game politics) የመውጣቱን ጉዳይና የፖለቲካ ፍላጎቶቻቸዉን በገደብ የማድረጉን ነገር በጥብቅ እንዲያስቡበት እመክራለሁ። ዋና ጉዳያችን ሥልጣን ሆኖ ከፊንፊኔ እስከ መቀሌ ባንዳ፣ ባንዳ እየተባባሉ መካሰሱ ሕዝባችንን ከማደናገር በላይ ብዙ የፖለቲካ ትርፍ የለውም። ዛሬ በአሜሪካና በአውሮፓ በሚደረጉ ሰልፎች ላይ በአንድ እጅ እስክንድር ነጋ ይፈታ፣ በሌላ እጅ ጃዋር ሽብርተኛ ነው የሚሉት መፈክር ዓይነቶቹ ለሀገረ-መንግሥት ግንባታችንም ሆነ ለብሔራዊ መግባባት ሥራችን ብዙ የሚጠቅሙ አይመስሉኝም። በእኔ በኩል እንዲህ ዓይነቱ ጉዳይ ስላስቸገረኝ ነበር በ2008 በፃፍኩት መፅሐፍ ላይ ለቡዳ ፖለቲካችን መላ እንፈልግ ብቻ ሳይሆን የሚጋጩ ሕልሞች ሊታረቁ ወይስ ኢትዮጵያን ሊያፈርሱ በሚል ግልፅ ጥያቄ የደመደምኩኝ። ለእኔ መፍትኼው ለአዲስቷ ኢትዮጵያ ፈጠራ የሚሆን አዲስ ማኅበራዊ ውል (new social contract) ከመፈራረም ውጭ የተሻለ የማጂክ ፎርሙላ ያለን አይመስለኝም። ይህንን እውነታ የምኒልክ ቤተ መንግሥት ያሉ የብልጽግና ወንድሞቻችንም ሆኑ ከአዲስ አበባ/ፍንፍኔም እስከ አውሮፓና አሜሪካ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ግፋ በለው የሚሉ ሁሉ እንዲረዱልኝ አደራ እላለሁ። በቅርብ ጊዜ በተፈጠረው ቀውስ በሁሉም በኩል ላለቁትም የተሻለ የሐዘን መግለጫ የሚሆነውና ዕንባቸውን የሚያብሰው የችግሮቻችን ምንጭ አዉቀን ዘለቂ መፍትኼ ስንፈልግ ይመስለኛል።
    1. ከላይ ካነሳኋቸው ሁለት ነጥቦች ጋር ተያይዞ ሺህ ጊዜ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ እየተባለ በሕዝብ ላይ የሚሠራዉ የፖለቲካ ትያትር መቆም አለበት።
      የንጉሡ ዘመን የምርጫ ትያትሮች፣ የደርግ ዘመን የምርጫ ትያትሮች፣ የኢህአዴግ ዘመን የምርጫ ትያትሮች በግልፅ ቋንቋ ለማስቀመጥ፥ ሲያንሱ በዴሞክራሲ ስም የተቀለዱ  ቀልዶች፣ ሲበዙ ደግሞ በኢትዮጵያ ሕዝቦች ላይ የተሠሩና ታሪክ ይቅር የማይላቸው ወንጀሎች ነበሩ። በሰለጠነው ዓለም የሕዝብን ድምፅ ከመስረቅ በላይ ወንጀል የለም። እዚህ ላይ ሁለት ነገሮችን አስታውሼ ልለፈው። በ“ኢህአዴግ-1” ዘመን አቶ በረከት፥ “ኢህአዴግ ከስድስት ሚሊዮን በላይ አባላት አሉትና በዝረራ ያሸንፋል” ብሎ ሲያስቸግረኝ፤ አቶ በረከት፥ “ኢህአዴግ ሁለት ምርኩዞች አሉት፤ አንደኛው ምርጫ ቦርድ ነው። ሁለተኛው ጠመንጃችሁ ነው። ሁለቱን ምርኩዞቻችሁን አስቀምጣችሁ ተቃዋሚዎችን ካሸነፋችሁ፥ እኔ በግሌ እናንተ የምትሉትን 20 ና 30 ዓመታት ብቻ ሳይሆን ለሃምሳ ዓመታት እንድትገዙን እፈርምልሀለሁ” እንዳልኩት አሰታዉሰለሁ። በ“ኢህአዴግ-2” ጊዜ ደግሞ ዶ/ር ዓቢይ በጠሩት ድንገተኛ ስብሰባ ላይ ገለልተኛ የሆነው ጠቋሚ ኮሚቴ ስምንት ሰዎች አጣርቶ ስላቀረበ አራት ሰዎች መመረጥ ስላለባቸው በተጠቆሙት ሰዎች ላይ አስተያየት ስጡ አሉን። ሌሎች ስብሰባው ላይ የተገኙ የየድርጅት መሪዎች ያሉትን ብለዋል፤ እኔ ጨዋታው ስላላማረኝ፥ “አብዛኛዎቹን ዕጩዎች ብዙዎቻችን አናዉቃቸውምና ከየት እንደመጡ እንኳ ለማወቅ የ24 ሰዓት ጊዜ ስጡኝ” ብዬ አጥብቄ ጠየኩኝ። ዶ/ር አቢይ ‘አይቻልም’ አሉ። ነገ የምናገረው እንዳይጠፋኝና ለታሪክም ቢሆን ተአቅቦ (reservation) መዝግቡልኝ ማለቴ ትዝ ይለኛል። ምስክሮችም አሉኝ። የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መጥቶ የምርጫ ቦርድ ኃላፊዎች የምርጫ ጊዜውን ሰሌዳ ለማስተላለፍ በጠሩት የምክክር ስብሰባ ላይ እንደተናገርኩኝ፥ መለኮታዊ ጣልቃ ገብነት (divine intervention) ነው እንዳልኩኝ ምርጫው ባይተላለፍ ኖሮ የአዲሱ ምርጫ ቦርድ አካሄድ ሌላ ከበድ ቀውስ ሊያስከትል ይችል እንደነበረ ዛሬ ላይ ሆኜ በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ። ይህንኑ ደግም ብዙ ጊዜ በታጋይነቷ ለምናውቃት ክብርት ብርቱካንም ጭምር መናገሬን አስታውሳለሁ።

    ስለሆነም የሚመጣውን ምርጫ አዲስቷን ዴሞክራትክ ኢትዮጵያ እንድትወለድበት ካላደረግን፥ የንጉሥ የማክያቬሊ ምክር፣ የመንግሥቱ ኃይለማርያም፣ የጆሴፍ ስታሊን ቀይ በትር፣ የመለስ ዜናዊ፣ የሊቀ መንበር ማኦ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ውሰት፣ ኢትዮጵያን ለመለወጥ የታሪክ ፈተናውን ለማለፍ እንዳላስቻላቸዉ፥ የዶ/ር ዓቢይም የመደመር የፖለቲካ ቀመር አዛውንቱ የፈረንጅ ምሁር የሚለውን የኢትዮጵያ ፖለቲካ የመጨረሻ ሁለት ድንበሮችን የሚያሻግረን አይመስለኝም። እሱን ካልተሻገርን ደግሞ ሁሌም እንደምለው ለሁላችንም የምትሆን ዴሞክራትክ ኢትዮጵያ የምትፈጠር አይመሰልኝም።

    ከማጠቃለሌ በፊት የብሔረታዊ መግባባቱ የፖለቲካ ጥረታችን ይሳካ ዘንድ መፍትሄ የሚሹ ቁልፍ ጉዳዮች ላስቀምጥ፦

    1. ያለ ሀገራዊ ስምምነት በዋናነት በአንድ ቡድን ሕልምና ፍላጎት (በተለይ የአንድ ቡድን ፍኖተ-ካርታ /road map/) የመመረቱ ጉዳይ ለዉጡን አጣብቂኝ ዉስጥ ማስገበቱን የማወቅ ጉዳይ፤
    2. ለውጡን ለማምጣት በዋናነት የላቀ አስተዋጽኦ ያላቸው ኃይሎች (ለምሳሌ እንደ ኦሮሞ ቄሮ ዓይነቶቹ) ወደ ዳር የመገፋታቸው ጉደይ፤
    3. ለውጡን እየመራ ያለው ከራሱ ከኢህአዴግ የወጣ ቡድን ቢሆንም፥ በለውጡ ምንነት፣ ፍጥነት፣ ስፋትና ጥልቀት ላይ የተለያዩ የኢህአዴግ ክንፎች ስምምነት ማጣታቸውና በዚህም ምክንያት እያመጣ ያለው አደገኛ ሁኔታ፤
    4. በሚጋጩ ሕልሞቻችን ምክንያት ላለፉት 50 ዓመታት መፍትሄ ያላገኘንለት የመከፋፈል ፖለቲካችን (political polarization) ጉዳይ፤
    5. ዴሞክራሲያዊ ለውጡ ለአብዛኛዉ የኢትዮጵያ ሕዝቦችና የፓለቲካ ኃይሎች ተቀባይነት ያለዉ፣ ሰላማዊና የተሳካ እንዲሆን የጋራ ፍኖተ-ካርታ (roadmap) የመቀየስ አስፈላጊነት ጉዳይና፤ የተቀየሰዉን በጋራ ሥራ ላይ የማዋል ጉደይ፤
    6. ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ማለት በእርግጥም በሕዝቦች ይሁንታ ላይ የተመሠረተ የፓለቲካ ጨዋታ መሆኑን የመረዳት ጉዳይ፤
    7. ሀገራችን እዉነተኛ ዲሞክራሲያዊ የፈድራል ሥርዓት ያስልጋታል ስንል፥ ከሕልሞቻችን በሻገር በሕዝቦቻችን ፍላጎት ላይ የተመሠረተ የፖሊቲካ ሥርዓት መሆኑን የማረጋገጥ ጉዳይ፤
    8. ብሔራዊ መግባባቱ በተሻለ መንገድ የሚሳካው፥ በደቡብ አፍሪካ እና ኮሎምቢያ በመሰሰሉት ሀገሮች እንዳየነው የፖለቲካ እስረኞችንና የጫካ አማፅያንን መጨመርን የማስፈለጉ ጉዳይ፤
    9. የተሳካ ብሔራዊ እርቅን ለመምጣት ከሥልጣን በሻገር የምር የፖለቲካ ቁረጠኝነት (political will) የማስፈለጉ ጉዳይ፤
    10. ስለኢትዮጵያ አንድነት ያለን ግንዘቤ ከፊታዉራሪ ሀብተጊዮርጊስ እይታ የሰፋና ለሀገሪቷ ያለን ፍቅርም ገደብ የማድረጉ ጉደይ ናቸዉ።

    በመደምደሚያዬም፥ እዚህ ያደረሰንን የሀገራችንን ፖለቲካ ጉዞ ታሪክ ወደኋላ እያየሁ፥ የወደፊቱን የሀገራችንን ዕጣ ፈንታንም እያማተርኩ ለጠቅላይ ሚኒስትሩም፣ ለሁላችንም የታሪክ የግርጌ ማስታወሻ ልተዉ።

    በቅርብ ቀን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‘ኢትዮጵያ አትፈርስም፤ ኢትዮጵያን የሚያፈርሷት እኛን ቀድሞ ሲያፈርሱ ነው፤ ኢትዮጵያን ለማፍረስ አይፈቀድላቸውም’ ሲሉ አዳምጫለሁ። ሀገርን ለመፍረስ የሚፈልጉ ኃይሎች መጀመሪያኑ ፈቃድ ይጠይቃሉ፤ አይጠይቁም የሚለዉን ክርክር ውስጥ ሳልገባ፥ በጨዋ ቋንቋ ንግግራቸውን አልወደድኩላቸውም። ንግግራቸውንም ተከትሎ የኢሳት ቴሌቪዥን የፖለቲካ ተንታኞች የሚታወቁ የአዛውንት ምሁርን በመጥቀስ (ይህኑን ምሁር መንግሥቱ ሀይለማርያምም ያዉቃል ብለን ስለተሠሩ የንጉሡ ባለስልጣኖች ምክር ጠይቀነዉ፥ ጠመንጃዉ በእናንተ እጅ ነዉ፤ የምን ምክር ትጠይቁናላችሁ ብሎኛል ማለቱን አንብቤአለሁ) ዶ/ር ዓቢይ ጥሩ ይዘዋል፤ ሕጉንም ሰይፉንም እየተጠቀሙ ነው ያሉት የበለጠ ሥጋት ፈጥሮብኛል። እዚህ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ሁላችንም ደጋግመን ማሰብ ያለብን ጨዋታው ከተበላሸ አብዛኛው ዓለምን በሰዓታት ውስጥ ወደ አመድነት የሚለወጥ ወይም ሕይወት-አልባ ሊያደርግ የሚችል የኒዩክሊየርር መሣርያ የታጠቀ፣ ነፍሷን ይማርና የሶቭዬት ህብረት ሠራዊት ዓይኑ እያየ ሀገራቸው መበቷን ነው። የሀገራችንን ፖለቲካ በጋራ አስተካክለን ሁላችንንም በእኩልነት የምታስተናግድ ዴሞክራቲክ ኢትዮጵያን ለመፍጠር እግዚአብሔር ይርዳን እላለሁ።

    ዋቢ መፃሕፍት:

    1. Bahiru Zewde (1991) A History of Modern Ethiopia, 1885 -1991.
    2. Gebru Tareke (1996) Ethiopia: Power and Protest, Peasant Revolts in the Twentieth Century.
    3. John Markakis, (2011) Ethiopia: The Last Two Frontiers.
    4. Merera Gudina, (2002) Ethiopia: Competing Ethnic Nationalisms and the Quest for Democracy, 1960-2000.
    5. Teshale Tibebu, (1995), The Making of Modern Ethiopia, 1896-1974.

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forumsላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።

    በኢትዮጵያ የሀገረ-መንግሥት ግንባታ የታሪክ ዳራ… መረራ ጉዲና (ፕሮፌሰር)

    Semonegna
    Keymaster

    “የወላይታ ዞን ነዋሪዎች ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ሕጋዊ ነው።”
    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)

    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በወላይታ ዞን የተቀሰቀሰውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ሕይወታቸውን ያጡና ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች ጉዳይ በአስቸኳይ እንዲጣራና ለሕዝብ ይፋ እንዲሆን ጠየቀ።

    ፓርቲው በሕዝብ ግንኙነት ክፍሉ በኩል ነሐሴ 05 ቀን 2012 ዓ.ም «በወላይታ ዞን የተፈጠረው አለመረጋጋት በሰላማዊ መንገድ ይፈታ» በሚል ርዕስ ባወጣው መግለጫ በዞኑ በተፈጠረው አለመረጋጋት ሕይወታቸውን ባጡ ዜጎች ምክንያት የተሰማውን ሐዘን ገልፆ፥ መንግሥት በአስቸኳይ ጉዳዩን አጣርቶ ይፋ ያድርግ ሲል ጠይቋል። «የመንግሥት የፀጥታ ኃይል ተገቢ ያልሆነ ኃይል በፍጹም እንዳይጠቀም እና የዜጎችን ሕይወት ለአደጋ ሳይዳርግ ሕግን በማስከበር ዞኑን ለማረጋጋት ከማኅበረሰቡ ጋር በቅርበት እንዲሠራ» በማለት ኢዜማ ማሳሰቢያውን ሰጥቷል።

    በክልሉ የሚገኙ ማኅበረሰቦች የሚያነሷቸውን የራስን በራስ የማስተዳደር ተገቢ ጥያቄዎች ቀጥተኛ እና ዘላቂ በሆነ መልኩ መመለስ ይገባል ማለቱን ያስታወሰው ኢዜማ፥ ይህን ለማድረግ ግን ማኅበረሰቡ በነፃ እና ገለልተኛ በሆነ መንገድ የመረጣቸው፣ የሚፈልገውን የሚፈጽሙለት ተወካዮች መኖራቸው እና በጉዳዩ ላይ ሰፊ ሕዝባዊ ውይይቶች መደረጋቸው አስፈላጊ ስለሆነ ሕዝቡ ተወካዮቹን መርጦ ሰፊ ሕዝባዊ ውይይቶች ተደርገው ሕዝበ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ በትዕግስት እንዲጠብቅም ጠይቆ እንደነበር አስታውሷል። ፓርቲው ይህንን ጥያቄውን አቅርቦ የነበረውም ሰኔ 9 ቀን 2012 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ እንደነበር ጠቁሟል።

    የዞኑ ነዋሪዎች ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ሕጋዊ መሆኑን እንደሚያምን በመግለጫው ላይ የጠቆመው ኢዜማ፥ ሀገሪቷ እና ዓለም ያለበት ሁኔታ ግን ሕገ መንግሥቱ የሚፈቅደውን የክልልነት ሒደት ለማሟላት የሚያስችል እንዳልሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል ብሏል። ለዚህም በምክንያትነት ኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰትን አንስቷል። ኮቪድ ወረርሽኝ ተከትሎ በታወጀው አስቸኳይ ግዜ አዋጅ የተነሳ ውይይት ማድረግም ሆነ ሕዝበ ውሳኔ ማድረግ የሚቻልበት ሁኔታ እንደሌለ ያስታወሰው ኢዜማ፥ በክልሉ በአጠቃላይ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ በሕጋዊ መንገድ ለመፍታት የሕዝብ ውክልና ያላቸው ተወካዮች መኖራቸው እንዲሁም በቂ ውይይት እና መግባባት ስለሚያስፈልግ በትዕግስት መጠበቁ የተሻለ አማራጭ መሆኑን ለማስታወስ እወዳለሁ ብሏል።

    ጥያቄውን የሚያነሱት ወገኖችም ሰላማዊ ከሆነ መንገድ ውጪ ዘላቂ መፍትሄ እንደማይገኝ መረዳት እንዳለባቸው እና እንቅስቃሴያቸውን ሁሉ በሰላማዊ መንገድ ማድረግ እንደሚገባቸው ፓርቲው አሳስቧል።

    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ገዢው ፓርቲ የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰብ እና ሕዝቦች ክልልን መልሶ ለማዋቀር ለፌደሬሽን ምክር ቤት ያቀረበው ምክረ ሀሳብ ክልል ለመሆን ጥያቄ ያቀረቡትን የዞን አስተዳደሮች ጥያቄን የማይመልስ፣ ክልሉ መጀመሪያ ሲዋቀር የተሠራውን ስህተት መልሶ የሚደግም፣ ሕገ ወጥ እና ግጭት የሚጋብዝ እንዲሁም እንደሀገር ካሉ ውስብስብ ችግሮች ላይ ሌላ ችግር የሚጨምር መሆኑን በማስረዳት ወደትግበራ እንዳይገባ በማለት ሰኔ 9 ቀን 2012 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ማሳሰቡ የሚታወስ ነው።

    ምንጭ፦ ኢዜማ

    ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ

    Semonegna
    Keymaster

    በደቡብ ክልል ወላይታ ዞን የክልልነት ጥያቄ በማንሳት የሚንቀሳቀሰው የዞኑ አመራርና ሕዝብ
    በሕገ-መንግሥቱ ድንጋጌ መሠረት ተገቢ መልስ በሰላማዊ አግባብ ሊሰጠው ይገባል!
    የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ)

    ከኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) የተሰጠ መግለጫ

    የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ራስን በራስ የማስተዳደርና ክልላዊ መንግሥት የማቋቋም መብት እንዳላቸው በሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ 47(2) ላይ ተደንግጓል። ይህን ሕገ-መንግሥታዊ መብት ለማስከበር ከአስር በላይ የሆኑ የደቡብ ብሔራዊ ክልል ዞኖች፣ በየዞናቸው ምክር ቤት በማስወሰን ለክልሉ ምክር ቤት ጥያቄዎቻቸውን ማቅረባቸውንና ውሳኔ እንዲሰጣቸው በመጠየቅ ላይ መሆናቸውን ከተለያዩ ምንጮች ስንሰማ ቆይተናል።

    እስከ አሁን ጥያቄያቸውን ካቀረቡት ዞኖች መካካል በሕገ-መንግሥቱ መሠረት ሕዝበ-ውሳኔ ተካሂዶ በክልልነት የመደራጀት መብት የተከበረለት የሲዳማ ዞን ብቻ ሲሆን፥ የሌሎች ዞኖችን በተመለከተ በአሁኑ ወቅት የተለያዩ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን በቡድን /በክላስተር/cluster/ በማሰባሰብ ከአንድ በላይ በሚሆኑ ክልሎች ለማደራጀት በመንግሥት እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑ ይታወቃል። ይህ እየሆነ ባለበት ሁኔታ በመንግሥት እየተደረገ ያለውን በክላስተር የማደራጀትን አማራጭ የሚቃወሙ እንቅስቃሴዎች በአንዳንድ ዞኖች እየታዩ ናቸው። በመሆኑም ከሚመለከተው አካል ፈጣን ምላሽ አልተሰጠንም ከሚል ተስፋ መቁረጥ ተነስቶ፥ ሕዝቡ ወደ ግጭት እንዳይገባ የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ከዚህ ቀደም ባወጣው መግለጫ ሥጋቱን ገልጿል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ፥ የተፈራው ስጋት እውን ሁኖ የወላይታ ዞን አመራር የመንግሥትን የመፍትሄ አቅጣጫ በመቃወም የምክክር ስብሰባ እያደረገ ባለበት ወቅት መንግሥት በወሰደው እርምጃ በቁጥጥር ስር እንዳዋላቸው ተሰምቷል። በዚህ መነሻነትም ሕዝቡ ተቃውሞ እያሰማ እንደሆነና ከፀጥታ አስከባሪ ኃይሎች ጋር በሚፈጠሩ ግጭቾች የሰው ሕይወት እስከ መጥፋት እየደረሰ መሆኑም በእጅጉ አሳስቦናል።

    ስለሆነም፥ መንግሥት የጉዳዩን ሰፊ እንደምታ በጥልቀት በመመልከት፣ በዞኑ ለተነሳው ሕገ-መንግሥታዊ ጥያቄ ተገቢ ምላሽ በመስጠት፣ ጥያቄውን በማንገብ ምላሽ ለመሻት የተንቀሳቀሱትን የወላይታ ዞን አመራር አካላትን እና በጉዳዩ ሳቢያ የታሰሩትን ሁሉ በመፍታት፣ ለተከሰተው ችግር ሰላማዊ መፍትሄ በአስቸኳይ እንዲፈልግ ኢሶዴፓ ያሳስባል። አስተዋዩ ሰፊ የወላይታ ሕዝባችንም ጉዳዩን በወትሮ ጥበቡ በትዕግስት በመያዝ፣ የሰላማዊ መፍትሄ አካል እንዲሆን ኢሶዴፓ በአክብሮት ጥሪ ያደርጋል!!

    የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ)
    ነሐሴ 6 ቀን 2012 ዓ.ም.
    አዲስ አበባ

    *የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) በሀገራችን ኢትዮጵያ ሕዝባዊ፣ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት በመመሥረት ለመሠረታዊ ችግሮች መፍትሔ ለመስጠት ርዕዮተ-ዓለሙ ማኅበረ-ዴሞክራሲ (social democracy) ሆኖ ኢኮኖሚያዊና ማኅብራዊ ፍትህን በሀገሪቱ እውን ለማረግ የሚንቅሳቅስ ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲ ነው።

    የፖለቲካ ፓርቲዎች ድምጽ (ኢትዮጵያ ውስጥ የሚነቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች)

    የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ

    Semonegna
    Keymaster

    በአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ አፈጻጸም ወቅት የታዩ ክፍተቶች አፋጣኝ ማስተካከያ ሊደረግባቸው ይገባል!
    የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ)

    የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መንግሥት የኮሮና ቫይረስ ‹COVID-19› በኢትዮጵያ ሊያደርስ የሚችለውን ተፅዕኖ ለመቆጣጠርና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ በማሰብ ሚያዝያ 2 ቀን 2012 ዓ.ም የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ቁጥር 3/2012 ማወጁ ይታወሳል። የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ ከታወጀ ወዲህ በመላው ሀገሪቱ ወጥነት ባለው መልኩ እየተተገበረ ካለመሆኑም በላይ የቫይረሱን ስፋት እና የስርጭት መጠን መሠረት በማድረግ በየጊዜው በአስፈጻሚው አካል የሚወጡ መመሪያዎችም በጥናት ያልተደገፉ እና ለሕግ አስከባሪው ኃይል የተለጠጠ የማስፈጸም ሥልጣን የሚሰጡ ሆነው ታይተዋል። በዚህም ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ ከታወጀበት ጊዜ ጀምሮ ባሉት አስር ሳምንታት የታዩት የዐዋጁ አፈጻጸም ሂደቶችም ሆኑ የመመሪያ አወጣጥ ሂደቱ ማሻሻያ ሊደረግባቸው የሚገቡ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) በጽኑ ያምናል።

    ዓለም-አቀፉ የጤና ድርጅት እና የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጤና ሚኒስቴር የኮሮና ቫይረስን አስመልክተው በየጊዜው ይፋ ከሚያደርጓቸው መግለጫዎች ለመረዳት እንደሚቻለው ቫይረሱ ገና በቅጡ ተጠንቶ ያልታወቀ ተለዋዋጭ ባሕርይ ያለው መሆኑ ነው። ከዚህ የተነሣ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት እንዲያስችሉን የምንወስዳቸው እርምጃዎች በበቂ ጥናት ላይ የተመረኮዙ መሆን ይኖርባቸዋል። ቫይረሱ በኢትዮጵያ መገኘቱ ከታወቀበት ጊዜ አንሥቶ ፍ/ቤቶች በከፊል ዝግ ሆነው መቆየታቸው የዜጎች ፍትሕ የማግኘት መብት እንዲገደብ ከማድረጉ በላይ ጉዳያቸው በአፋጣኝ ታይቶ በነጻ መሰናበት እንዲሁም በዋስ መለቀቅ የሚችሉ ዜጎች ያለ አግባበብ በእሥር እንዲቆዩ ምክንያት ሆኗል። በዚሁ ምክንያት አንዳንድ ማረፊያ ቤቶች በመጨናነቃቸው ዜጎች ለቫይረሱ ይበልጥ ተጋላጭ ሆነዋል።

    የዐዋጁ አፈጻጸም ሲገመገም የዜጎችን በሕይወት የመኖር፣ ከማንኛውም ጥቃት ነጻ-የመሆን፣ ፍትሕ የማግኘት፣ እንዲሁም ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብቶች ላይ ያልተመጣጠነ ገደብ ያስቀመጠ በመሆኑ እነዚህ ጉዳዮች አስቸኳይ የማስተካከያ እርምጃዎችን እንዲሁም ዘላቂ መፍትሔዎችን የሚሹ መሆናቸውን ኢሰመጉ በጥብቅ ያምናል። ከዚህም በተጓዳኝ በቀጥታ በዐዋጁ ምክንያት ባይሆንም፤ የቫይረሱ መስፋፋት ባስከተላቸው ማኅበራዊ፣ ሥነ-ልቦናዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎች የተነሳ በጤና ባለሙያዎች፣ በሴቶች እና ሕጻናት፣ እንዲሁም በድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች ላይ ዓይነተ-ብዙ የመብት ጥሰቶች እየደረሱ በመሆኑ ትኩረት እና መፍትሔ የሚሹ መሆናቸውን ኢሰመጉ ያምናል። እንዲሁም በዐዋጁ አፈጻጸም ወቅት እና በአጠቃላይ ቫይረሱ ከተከሰተ ወዲህ ባሉ ጊዜያት ከታዩት ጉልህ የመብት ጥሰቶች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡-

    በትግራይ ክልል ናዕዴር ዓዴት ወረዳ ቀደም ብሎ በክልሉ ታውጆ የነበረውን አስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ለማስከበር በሚል አንድ የፖሊስ ባልደረባ በወሰደው የኃይል እርምጃ መጋቢት 19 ቀን 2012 ዓ.ም የአንድ ሰው ሕይወት ያለፈ ሲሆን፤ በተመሳሳይ ግንቦት 9 ቀን 2012 ዓ.ም መቐለ ከተማ ሰሜን ክፍለ ከተማ ልዩ ቦታው 05 ቀበሌ አካባቢ አንድ የፖሊስ ባልደረባ በወሰደው የኃይል እርምጃ የሰው ሕይወት ጠፍቷል፤ ተጨማሪ ሌሎች ሰዎች ደግሞ ቆስለው ሕክምና ላይ ናቸው። በአማራ ክልል በጎንደር ከተማ አንድ የባጃጅ ሹፌር በጸጥታ ኃይሎች በተፈጸመበት ጥቃት አንድ እጁ ላይ በጥይት ጉዳት ደርሶበታል።

    በተለያዩ አካባቢዎች “የአፍ መሸፈኛ ጭምብል አላደረጋችሁም” በሚል ምክንያት ፖሊስ ተመጣጣኝ ባልሆነ እርምጃ በዜጎች ላይ ከፍተኛ እንግልት እና ለቫይረሱ አጋላጭ በሆነ መንገድ የጅምላ እስር ፈጽሟል። “ዐዋጁን ተላልፈዋል” በሚል ምክንያት ንግድ ቤቶች የሚታሸጉበት እና በሰዓት ገደብ እንዲዘጉ የሚደረጉበት ሂደት አንድ ወጥ አለመሆኑ አድሎአዊ እና ሕገ-ወጥ ለሆነ አፈጻጸም አጋልጧል።

    ቫይረሱን ግንባር-ቀደም ሆነው እየተከላከሉ ላሉት የጤና ባለሙያዎች በቂ ራስን የመከላከያ ግብዓቶች እየቀረቡ ባለመሆኑ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ በሚጥል መልኩ እንዲሰሩ በመደረጋቸው ለቫይረሱም ተጋላጭ ሆነዋል። በጤና ሚንስቴር ይፋ በተደረጉ መረጃዎች መሠረት እስከአሁን ድረስ ወደ አንድ መቶ የሚጠጉ የጤና ባለሙያዎች እና የጤና ተቋም ሠራተኞች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል። “ንክኪ አላቸው” በሚል በየጊዜው ወደ ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ የሚደረጉ የጤና ባለሙያዎች ቁጥርም በየጊዜው እየጨመረ ነው።

    በአዲስ አበባ ቦሌ አየር ማረፊያ በኩል የሀገር ውስጥ በረራ ሊያደርጉ የነበሩ የተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና ተወካዮች “ዓለም-አቀፍ በረራ አድርጋችኋል” በሚል ወደ አስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ለአስራ ስድስት ቀናት ያህል እንዲገቡ፣ ለተወሰኑ ቀናትም ቤተሰብ ያሉበትን እንዳያውቅ ተደርጓል። ሌሎች ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶችም የቫይረሱን መከላከያ ሥራዎች ሽፋን በማድረግ በአባላትና አመራሮቻቸው ላይ ልዩ ልዩ ተጽዕኖዎች እየደረሱባቸው ነው። ለአብነት፥ ወደ ደቡብ ክልል ቁጫ ወረዳ ሰላም በር ከተማ ለቤተሰባዊ ጉዳይ የሄዱትን አንድ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ አባል ወደ ከተማዋ ለሚገቡ ሌሎች ሰዎች ወጥነት ባለው መልኩ ተግባራዊ በማይሆን አሰራር ከግንቦት 9 – 11 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ ለሦስት ቀናት በለይቶ ማቆያ ውስጥ እንዲቆዩ ተደርጎ ተለቀዋል። ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ (ባልደራስ) ፓርቲ ግንቦት 27 ቀን 2012 ዓ.ም በአዲስ አበባ ኮልፌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 አካባቢ ለሚገኙ ዜጎች እርዳታ ለማድረግ ሲንቀሳቀስ ፖሊስ ጣልቃ በመግባት እንዲቆም ተደርጓል።

    የቫይረሱ ስርጭት ባስከተለው ተጽዕኖ የዜጎች የሥራ ዋስትና ጥያቄ ውስጥ ከመውደቁም በላይ፥ አንዳንድ አሰሪዎች ሠራተኞቻቸውን ከሕግ አግባብ ውጪ በሆነ መንገድ ከሥራ ገበታቸው እንዲሰናበቱ እና አስገዳጅ ፈቃድ ያለክፍያ እንዲወጡ ተደርጓል።

    የድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች ማኅበር ይፋ ባደረገው መረጃ በተለይም በጅቡቲ በኩል የሚገቡ አንዳንድ አሽከርካሪዎች ከሚደርስባቸው መገለል በተጨማሪ በአንዳንድ ከተሞች የማደሪያ እና የምግብ አገልግሎት እንዳያገኙ፣ መኪና እንዳያቆሙ ክልክላ ይደረግባቸዋል።

    መንግሥት ቀዳሚ ትኩረቱን በሽታውን በመከላከል እና ተያያዥ ሥራዎች በማድረጉ በሴቶች እና ሕጻናት ላይ የሚደርሱ የቤት ውስጥ ጥቃቶች፣ የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎች እና ያለ ዕድሜ ጋብቻን የመሳሰሉት ልማዳዊ ጎጂ ድርጊቶች እየተበራከቱ እና እየተስፋፉ ነው። የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶች እና ሕጻናት ቢሮ ብቻ ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት 101 ያህል ህጻናት የመደፈር ጥቃት ደርሶባቸዋል። በተመሳሳይ መልኩ በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎችም መሰል የመብት ጥሰቶች እንዳሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

    በመሆኑም፥ ዐዋጁን ለማስፈጸም የተቋቋመው የሚኒስትሮች ኮሚቴ እና በየደረጃው ያለው ግብረ-ኃይል ለእነዚህ የመብት ጥሰቶች እና የአፈጻጸም ችግሮች ተገቢውን ትኩረት በመስጠት አስቸኳይ መፍትሔ እንዲያገኙ በትኩረት እንዲሠራ ኢሰመጉ ያሳስባል። መንግሥት በዐዋጁ አፈጻጸም ምክንያት ሊጎዱ ለሚችሉ የጎዳና ተዳዳሪዎች፣ ዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎች፣ ለድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች፣ በተለያየ ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች አስፈላጊውን የምግብ፣ የንጽህና መጠበቂያ፣ የትራንስፖርት አገልግሎት እርዳታ እና ድጋፍ እንዲያደርግ ኢሰመጉ ጥሪውን ያቀርባል።

    ቫይረሱን ከፊት ሆነው እየተከላከሉ ላሉ የሀገራችን የጤና ባለሙያዎች ቫይረሱ አሁን ካለበትም ደረጃ የከፋ የሚሆንበትም ጊዜ ሳይጠበቅ አስፈላጊ የሆነውን ራስን የመከላከያ ግብዓት በበቂ ሁኔታ በአፋጣኝ እንዲያገኙ መንግስት እና የጤና ሚኒስቴር በትኩረት እንዲንቀሳቀሱ ኢሰመጉ ጥሪውን ያቀርባል። በተጨማሪም በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጦ በለይቶ ሕክምና ላይ የሚገኙ ዜጎች የምግብ አገልግሎት፣ የመኖሪያ እና የንፅህና መስጫ ስፍራ ጽዳት፣ የአፍ መሸፈኛ ጭምብሎችን ጨምሮ የሌሎች የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች አቅርቦትና የመሳሰሉ የአገልግሎት ችግሮች መኖራቸውን የሚያሳዩ መረጃዎች በመኖራቸው መንግሥት በትኩረት ችግሮቹን እንዲያስተካከል ኢሰመጉ ጥሪ ያቀርባል። በየጊዜው ዐዋጁን በመተላለፍ ተይዘው እንደ ትምህርት ቤት ባሉ መሠረተ ልማቶች ውስጥ የታሰሩ ዜጎች የሚቆዩበት ሥፍራ እንደ ምግብ፣ አልጋ፣ መጸዳጃና የመሳሰሉት መሠረታዊ አገልግሎቶች ለመስጠት በሚያስችል መልኩ መደራጀታቸውን እንዲያረጋግጥ ኢሰመጉ ያሳስባል።

    በዐዋጁ ድንጋጌ መሠረት የመንግስትም ሆነ የግል ትምህርት ተቋማት ተዘግተው ተማሪዎች እና መምህራን በአካል ተገናኝተው ትምህርት የሚሰጥበት ሂደት ተቋርጧል። ሆኖም ተማሪዎች ከቤታቸው ሆነው ትምህርት እንዲከታተሉ እየተደረገበት ያለው መንገድ ጥራቱን በጠበቀ፣ ተማሪዎች ትምህረቱን ለማስተላለፍ የሚረዱትን ነገሮች የማግኘት አቅማቸውን ታሳቢ ያደረገ እና የብሔራዊ ፈተና ተፈታኞችን ፍትሐዊ እድል ለመስጠት በሚያስችል መልኩ እንዲሰጡ መንግሥት እንዲያመቻች ኢሰመጉ ጥሪ ያቀርባል።

    በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተሰየመው የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ መርማሪ ቦርድም ሁኔታዎቹን በየጊዜው እየተከታተለ፣ በዐዋጁ ይዘት እና አፈጻጸም ላይ የሚሰጡ አስተያየቶችን በአግባቡ እንዲስተካከሉ ኃላፊነቱን እንዲወጣ እናሳስባለን። መንግሥት ቫይረሱን የመከላከል ሥራዎችን አስመልክቶ በየደረጃው የሚሠሩ ሥራዎች ለሕዝብ ይፋ እንዲሆኑ እና የሲቪል ማኅበረሰቡንም ሌላውን የሕብረተሰብ ክፍል ተሳትፎ በሚጠይቁ ጉዳዮች ላይ እንዲሳተፉ የሚያስችሉ ሁኔታዎችን እንዲያመቻች ኢሰመጉ ጥሪ ያቀርባል።

    ከዚህ በኋላ የሚወጡ መመሪያዎች የበሽታውን ባህርይ ታሳቢ ያደረጉ፣ በበቂ ጥናት እና መረጃ ላይ የተመሠረቱ፣ ለሕግ አስከባሪ ኃይሎች የሚሰጡት ሥልጣን ውስን እንዲሆን፣ ብሎም ክልከላ የተደረገባቸውን ነገሮች በግልጽ የሚያመላክቱ እንዲሆን ኢሰመጉ በጥብቅ ያሳስባል። ዐዋጁን በማስፈጸም ወቅት የፖሊስና ሌሎች የፀጥታ አካላት ሚና የጤና ባለሙያዎችን የማገዝ እንዲሆን ቅጣት እንኳን አስፈላጊ ቢሆን ሕይወትን የማዳን ዓላማ እንጂ የባሰ አደጋ ውስጥ በማይከት ሁኔታ መሆን ስለሚገባው፤ ተጠያቂነትን በሚያሰፍን መልኩ በጥብቅ ዲሲፕሊን እንዲመራ የሚያሳስብ ድንጋጌ በያዘ መልኩ ማሻሻያ እንዲደረግባቸው ኢሰመጉ ያሳስባል።

    በተጨማሪም በአዲስ አበባ ከተማ የሚደረጉ የመሬት ወረራን ታሳቢ አድርገው የሚሠሩ የሕግ ማስከበርና የቤት ማፍረስ እርምጃዎች ያለንበት ወቅት ክረምት እንደመሆኑ እና ዜጎችን ለበሽታውም ስርጭት የበለጠ ተጋላጭ እንዲሆኑ የሚያደርግ በመሆኑ በጥንቃቄ እና ወጥነት ባለው እንዲታዩ ኢሰመጉ ጥሪውን ያቀርባል።

    ሁሉም መብቶች ለሁሉም!!

    ምንጭ፦ ኢሰመጉ

    የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ)
    የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) በኢትዮጵያ የሽግግር ወቅት ቻርተር አንቀጽ 1(ሀ) እና በኢትዮጵያ ፍትሐ-ብሔር ሕግ ቁጥር ከ404-482 በተጻፉት ድንጋጌዎች መሠረት መስከረም 29 ቀን 1984 ዓ.ም.  በአባላት የተመሠረተ የመጀመሪያው መንግሥታዊ ያልሆነ ተሟጋች ተቋም ነው።

    የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ)

    Anonymous
    Inactive

    በሀገራዊ ወቅታዊ ጉዳይ የተሰጠ መግለጫ ― በድር ኢትዮጵያ

    ለረጅም ዘመናት በታሪክ እንደምንረዳዉ በኢትዮጵያ ሕብረተሰቡ በጥሩ ማኅበራዊ ሁኔታ በመቀራረብ፣ በመተሳሰብ፣ በመቻቻል እና በመሳሰሉ ሁኔታዎች ተሳስሮ በጋራ ይኖር እንደነበር በሰፊዉ ሲተረክ ይታወሳል። ይኸዉ ማኅበራዊ ኑሮአቸዉንም ሀይማኖት፣ ዘር፣ ቋንቋ፣ አካባቢና መሰል ጉዳዮች ሳይገድባቸዉ ሕዝቦች አንድነታቸዉን ጠብቀዉ ኖረዋል፤ ምንም እንኳን በነበሩ መንግሥታት በኩል ይደረጉ የነበሩ ልዩነቶች፣ ጫናዎች፣ ጭቆናዎች እንደተጠበቁ ሆነዉ ማለታችን ነዉ።

    ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገራችን የተለያዩ የልዩነት ክስተቶች ቢንጸባረቁም ሕዝቡ ግን ችግሮቹን ወደ ጎን በማድረግ ከሀይማኖት ዉጭ እንዲሆኑ ትግል ሲያደርግ ቢቆይም፥ በአሁኑ ወቅት ግን ይዘቱን ቀይሮ የመጣዉ ለችግሮች ሁሉ መነሻዉ ሀይማኖት እንደሆነ የሚዘምሩ አካላት እየተበራከቱ ይገኛል።

    የታዋቂዉ አርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ በግፍ መገደልን ተከትሎ በሀገሪቱ በተከሰተዉ አለመግባባትና ብጥብጥ የበርካታ ንጹሀን ዜጎች ህይወት እጅግ አሰቃቂ በሆነ መልኩ አልፏል። ለሟቾች ነብስ ይማር እያልን ለቤተሰቦቻቸዉና ለመላዉ ኢትዮጵያዉያን መጽናናትን እንመኛለን። በሌላ መልኩ ከፍተኛ የአካል ጉዳት የደረሰባቸዉ ንጹሀን ዜጎች እንዲሁም የወደመዉ የሀገር ንብረት ቁጥሩ እጅግ ከፍተኛ ከመሆኑ አንጻር የጉዳዩ አስከፊነት ስፋቱን ይጠቁማል።

    መንግሥት ባለበት ሀገር እንደዚህ አይነት ልቅ የሆነ ሥርዓተ-አልበኝነት ሲፈጠር መንግሥት አለን? ያስብላል። መንግሥት ሆይ የታሰሩ አካላት ፈጣን ፍትህ እንዲያገኙና መፈታት ያለባቸዉ አካላትም ያለምንም መጉላላት በሕግ የበላይነት መፍትሄ ሊቸራቸዉ ይገባልም እያልን፥ በሌላ መልኩም የጥላቻ ንግግር የሚያስተጋቡ አካላትን መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ የማስቆም ኃላፊነቱን እንዲወጣ አደራ እንላለን።

    ችግሩ የተከሰተበትን መንስኤ በማጥናት መፍትሄ መሻት ሲገባ፥ አንዳንድ የግል ዓላማ ያላቸውና እስላም-ጠል የሆኑ ጽንፈኛ አካላት የጉዳዩን አቅጣጫ ለማስቀየር የተለያዩ የዜና ማሰራጫ ዘዴዎችን በመጠቀም ጸረ-ሰላም ብሎም ጸረ-ኢስላም የሆነ ፕሮፓጋንዳቸዉን በማሰራጨት ላይ ይገኛሉ። በእምነት ተቃርኖ የማያዉቀዉ የሀገራችን አማኞች በእምነታቸዉ ከተመጣባቸዉ ሁሌም ቢሆን ወደ ኋላ የማይሉ እንደሆነ ስለሚያዉቁ በሌሎች ነገሮች ሁሉ ሞክረዉ አልሳካ ቢላቸዉ መጨረሻ ላይ ሕዝቡን በእምነት ለማጋጨት ሌት ተቀን እየዳከሩ ይገኛሉ።

    በድር ኢትዮጵያ የማንኛዉም ቤተ-እምነት ወይም ተቋም ሲደፈር በጽኑ ተቃዉሞዉን ያሰማል። የእምነት ተቋማት ሊከበሩ ስለሚገባም ጭምር ነዉ። አንዱ ተቋም ከአንዱ አይበልጥም፤ የትኛዉም ተቋም ከማንኛዉም አያንስም፤ በእምነት ተቋምነታቸዉ ሁሉም እኩል ናቸዉ። ይህንን መገንዘብ የተሳናቸዉ የጽንፍ አራማጆች ግን በእምነቶች መካከል ጣልቃ በመግባት እኔ አዉቅልሀለሁ አባዜያቸዉን በመንዛት ሙስሊሙን ማኅበረሰብ ለማሸማቀቅ በሚያስችል ደረጃ የችግሩ አካል ለማድረግ ብዙ ለፍተዋል፤ ሆኖም ግን አይሳካላቸዉም። ሙስሊሙ ማኅበረሰብ የማንም አካል ተቀጥላ ሆኖም አያዉቅም፤ መብቱን ለማስከበር ደግሞ ማንም ሊነግረዉ አይችልም፤ በቂ ተሞክሮም አለዉ።

    በሀገሪቱ የመጣዉን አንጻራዊ ለዉጥ ያልተዋጠላቸዉ ለዉጡን  ለመቀልበስና ዳግም ላይመለስ ያከተመዉን የአጼዎችን ስርዓት ለማንገስ ለሚድሁ ያለን ምክረ-ሀሳብ ሀገራችን በተያያዘችዉ የለዉጥ ጎዳና የሚያራምዳት እንጂ ለነዉጥ የሚዳርጋትን ስለማትሻ ከእኩይ ተግባራችሁ እንድትቆጠቡ እያልን የሰላም ሰባኪ በመምሰል በሕዝቡ መካከል አሉባልታ የሚነዙና ጽንፈኝነትን የሚያራምዱ አካላት ከሚያስቡት ባልታሰበ መልኩ በተቃራኒዉ ብዙ አላስፈላጊ ዋጋ ሊያስከፍላቸዉ ይችላልና ለሀገሪቱ ሉዓላዊነት ለሕዝቦቿ አንድነት እንዲሁም ለሰላም ሲባል ቆም ብላችሁ እንድታስቡ መልካም መሆኑን ለመጠቆም እንወዳለን።

    በአማራ ክልል በሞጣ የሚገኙ አራት መስጂዶችን አቃጥሎ የሙስሊም ማኅበረሰብ ድርጅቶችን በመለየት በማዉደምና ንብረታቸዉን በመዝረፍ እሳት እየሞቁ ይጨፍሩ የነበሩትን የሥነ ምግባር ሞራል የጎደላቸዉን ኢስላም-ጠል ጽንፈኞችን ለመገሰጽ እንኳ የሞራል ብቃት ያጡ አካላት አሁን በሀገሪቱ በተከሰተዉ ብጥብጥ ሙስሊሙ ማኅበረሰብ በሞተበትና ንብረቱ የወደመበት ሆኖ ሳለ የግል ድብቅ አጀንዳቸዉን ለማሳካት በበሬ ወለደ ትርክታቸዉ የእምነት ጥቃት አድርጎ ክፍፍልን መዝራት ፍጹም ተቀባይነት የሌለዉ እኩይ ተግባር ነዉ።

    ስለዚህ እየተካሄደ ያለዉ አላስፈላጊ ቅስቀሳ ሕዝቡን ከማበጣበጥ፣ ሀገር ከማፈራረስ እና በሕዝቦች መካከል ሊፈታ የማይችል ጠባሳ ከማኖር ውጭ እንደ ሀገር እና ሕዝብ የማያስተሳስር ለሰላምና ፍትህ ያልቆመ መሆኑ ብቻ ሳይሆን እንደ እምነትም ቢሆን በየትኛዉም የእምነት አስተምህሮት የማይደገፍ አጸያፊ ተግባር መሆኑን በመረዳት ሁሉም ሊገነዘበዉ የሚገባና ማንኛዉም አካል  ከዚህ መሰል ሂደት ጥፋትን እንጂ ትርፋማነትን ማሰብ እንደማይገባ በቅጡ መገንዘብ ያሻል።

    በመጨረሻም ለሙስሊሙ ማኅበረሰብ የምናስተላልፈዉ መልእክት ኢስላም ሰላም እንደመሆኑ መጠን፥ ለሰላም መከፈል የሚገባዉ ዋጋም እንደተጠበቀ ሆኖ፥ በሁለንተናዊ መልኩ ተጠናክሮ መገኘት እና በጽንፈኞች ለሚሰነዘሩብን የዉሸት ፕሮፓጋንዳ ለኛ አዲስ ባለመሆኑ ትኩረት ባለመስጠት የሚቃጣብንን በጥበብ፣ በሰከነ መንፈስ እንደ ሀገር በማሰብ የመመከት ኃይል ማዳበር ለሰላም ዘብ መቆም ግድ ይላል እንላለን።

    ሀገራችንን ፈጣሪ  አላህ (ሱ.ወ) በሰላም ይጠብቅልን።

    በድር ኢትዮጵያ
    ሰሜን አሜሪካ
    24 ጁላይ 2020

    በድር ኢትዮጵያ

    Anonymous
    Inactive

    [በዚህ ጽሑፍ ላይ አማራ ብዬ የጠቀስኩት ማኅበረሰብ በአሰፋ ጨቦ ትንታኔ መሠረት ሲሆን፥ ዘርን ሳይሆን የአባቶቻችንን ድል እና ኃያልነት የተቀበለውን፣ የማሸነፍ መንፈሱ የማይደረመስ ተራራ የሆነውን፣ በየሄደበት ሁሉ የአባቶቹን ድል አድራጊነት እያሰበ የበታችነትን እንቢ ያለውን ኢትዮጵያዊ ሁሉ የሚመለከት ነው።]

    አሸናፊን የራሱ የሚያደርግ ብልህ ሕዝብ

    (ሙሉዓለም ጌታቸው)

    የዛሬ አንድ ወይም ሁለት ዓመት ፌስቡክ ላይ በአንድ የኦሮሞ አክቲቪስት ተጽፎ ብዙ ሰው የተለዋወጠው ጽሑፍ ነበር። ጽሑፉ ኦሮሞ ጀግኖቹን አሳልፎ የሚሰጥ ባህል አለው ብሎ ይከራከራል። አማራ* ደግሞ የሌላን ጀግና ሳይቀር የራሱ የማድረግ፣ የማጠጋጋት ባህል አለው ይላል። ይሄ ጽሑፍ ባሰብኩት ጊዜ ሁሉ ይገርመኛል። በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ በየትኛውም ዘርፍ አንቱታን ያተረፉ ጀግኖች አብዛኛው ከኦሮሞ ናቸው፤ ነገር ግን የሚያከብራቸው እና የሚወዳቸው አማራው ወይም ሌላው ብሔር ነው። በተቃራኒው በሕይወት በነበሩበት ዘመን ሳይቀር ከሃዲ፣ የአማራ ተላላኪ እያለ ሲሰድባቸው የነበሩትን ልክ ሲሸነፉ ወይም ሲመቱ የራሱ አድርጎ የመቀበል እና ሞታቸውን የእሱ የማድረግ ባህል ቢያንስ በእኔ ዕድሜ በማውቀው የኦሮሞ ማኅበረሰብ ውስጥ የሰረጸ ባህል ይመስላል።

    ኃይሌ ፊዳ ጎበና እየተባለ መከራውን እንዳየ እንደተሰደበ ደረግ ጭዳ አደረገው። አሁን ደግሞ ለብዙ የኦሮሞ የዘመኑ ጎበዞች ጃዋርን ጨምሮ ኃይሌ ፊዳ የኦሮሞ ጀግና እየተደረገ ሲቀርብ እና ለትግል ማነሳሻ ሲውል መመልከት የተለመደ ሆኗል። “The Ethiopian Revolution and Its Implication” በሚል ርዕስ በአሜሪካው የስለላ ተቋም ሲ.አይ.ኤ. (CIA) እ.ኤ.አ. በማርች 1977 (March 1977) ተዘጋጅቶ በጥብቅ ምስጢርነት ለአሜሪካው የሥራ አስፈጻሚው አካል የቀረበው ሰነድ መንግስቱ ኃይለማርያም ኦሮሞ እንደሆነ ከገለጸ በኋላ፥ በንጉሡ ወዳጆች ከስልጣን የሚፈነቀል ከሆነ “በኦሮሞነቴ” ወይም “ኦሮሞ” ስለሆንኩ ከስልጣን አባረሩኝ ብሎ ዘሩን ሊጠቀምበት እንደሚችል ትንቴውን ያቀርባል። “እንደዚህ ዓይነት አደጋ ካልገጠመው ግን ኦሮሞነቱን የማሳየት (ለስልጣን ሲል ማለቱ ነው) ዝንባሌ አይታይበትም” ይላል የስለላው ሰነድ። ተመልከቱ የሚሸነፍ ከሆነ በኦሮሞ የዘር ጉርጓድ ውስጥ ሊደበቅ ይችላል እያለን ነው (ሽንፈቱን እንጂ ድሉን ለኦሮሞ ለመስጠት ፈቃደኛ አልነበረም ማለቱ ነው)። ይሄ በዘመኑ ሳይቀር በራሳቸው የዓለም ትግል ሲሸነፉ ኦሮሞነታቸውን (ዘራቸውን) ለውድቀታቸው ሰበብ የማቅረብ ዝንባሌ እንዳለ ከማሳየቱ ባሻግር፥ ሲሸነፉ የራሱ የሚያደርጋቸው ማኅበረሰብ እንዳለ ይነግረናል።

    ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከአባታቸው መኮንን ጉዲሳ የተወለዱ ኦሮሞ ናቸው። በዓለም የተደነቁ፣ ዘመናዊ ኢትዮጵያን በዘመናዊ ተቋም የመሠረቱ፣ እጅግ አስደናቂ መሪ ናቸው። ኢትዮጵያ በእሳቸው ጊዜ የነበራትን ዝና ለመመለስ ቢያንስ 100 ዓመት በትንሹ ሊያስፍልጋት ይችላል፤ እሱም ጠንክረን ከሠራን። በርግጥ ፍጹም ሥልጣን የሚወዱ በመሆናቸው ፍጻሜያቸውን ክፉ አደረጉት። ንጉሡን የሚወዳቸው እና የራሱ ያደረጋቸው ግን ማነው? አማራው! በእሳቸው ዘመን ክፉኛ የተጨፈጨፉ ሁለት አመጾች አሉ። አንዱ የቀዳማይ ወያኔ ትግል በትግራይ ሲሆን ሌላኛው የጎጃም አመጽ ነው። የጎጃምን አመጽ ድባቅ የመቱበት ዘግናኝ ክስተት የታሪክ ጸሐፊዎች እንኳ ቃላት ያጡለት ነው። ግን ዛሬ ለሃውልታቸው መሠራት፣ ለስማቸው ክብር የሚቆመው ይሄው አማራው ነው። ምክንያቱም ጀግናን የራሱ የማድረግ ሥነ-ልቦና አለው። ሰቅለው ለገደሉት ለበላይ ዘለቀ እየዘፈነ ፥ ለእሳቸው ክብርና ዝና ዜማ ሲያወርድ ምንም አይጣላበትም። ድንቅ ሥነ-ልቦና። ኦሮሞው ደግሞ የመኮንን ጉዲሳን ሃውልት ሐረር ላይ አፍርሶ፣ ሰው ሀገር ላይ ሎንደን (London) ደግሞ የሳቸውን ያፈርሳል። ምክንያቱም ተሸናፊን እንጂ አሸናፊን የመቀበል ሥነ-ልቦና አላወረሱትም። የተቆረጠ የጡት ሃውልት ለልጆቹ ዘወትር እያሳየ፥ በባዶ እግሩ የሚሄድ ከእሱ በምንም የማይሻለው አማራ አደረገው ይላቸዋል። ልጅ በውስጡ ፍርሃት ይሰርጽበታል። የተሸናፊው ዘር አባል መሆኑ በራሱ የሚፈጥርበት የሥነ-ልቦና ቀውስ ቀላል አይደለም። ከዛ ሕይወቱን በጥላቻ መነጽር መመልከት ይጀምራል። ጥላቻ ደግሞ የሽንፈት ዋስታና ነው።

    በቅርቡ ቤት ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በእናቱ አማራ ነው እያለች አንድ ዘመዳችን በደስታ ትፈነድቃለች። ጠቅላዩ ብዙም አልቆየም፤ በOBN ላይ ቀርበው በእናታቸውም በአባታቸውም ኦሮሞ እንደሆኑ ገለጹ። ይሄውልሽ ተሳስተሻል ስላት፥ እሱ ነው የተሳሳተው አለችኝ። ቀጥላም የሰላም ኖቤል ሽልማት ሲቀበል አስተዋዋቂዋ በእናቱ አማራ እንዲሁም በአባቱ ኦሮሞ እያለች የተናገረችውን አሳየችኝ። ይሄ እኮ እሱ የተናገረው ሳይሆን እነሱ በስማ በለው ጽፈው ያቀረቡት ነው። ደግሞ ካስተዋልሽው በእናቱ አማራ ስትል እኮ ሳቀ። ይሄም የሚጠቁምሽ ነገር አለ ስላት፥ “ችግር የለውም እኔ ነው ብያለው፤ ነው!” አለችኝ። ይሄ አሸናፊን፣ ጀግናን የራስ የሚያደርግ፣ የሚቀበል ሥነ-ልቦና እንዲሁ በከንቱ የመጣ አይደለም፤ ሲገነባ የቆየ እንጂ። በእውቀቱ ስዩም ኢትዮጵያውያን ‘እኛ በዚህ ነገር አንደኛ ነን’ የማለት ሥነ-ልቦና አለን ይላል። “ለምሳሌ እኔ የቤቱ ሦስተኛ ልጅ ብሆንም ለሰው ስናገር ግን” ይላል፥ “ከቤታችን ሦስተኛ በመሆን አንደኛ ነኝ ብዬ ነው” በማለት የባህላችንን ራስን ከፍ የማድረግ ድንቅ ሥነ-ልቦና ይገልጸዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ነገ ቢገደል ወይም አንድ ነገር ቢያደርጉት ኦሮሞ ስለሆነ ተገደለ ብለው አሁን የምታይዋቸው እሱን የሚቃወሙ የኦሮሞ ጎበዞች የራሳቸው ጀግና ያደርጉታል። እሱም ይሄን ሥነ-ልቦና ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ሥልጣኑ ባልጸናበት ወቅት “ከቡራዩ ጠቅላያችን ተነካ ብለው ወጣቶች ሲመጡ፥ ኦሮሞ መምራት አይችልም እያሉ” ምናምን እያለ ሆዳቸውን እያባባው ነበር። በበታችነት ሥነ-ልቦና ትልቅ ሀገር መገንባት እንደማይቻል ጠንቅቆ የሚያውቀው አብይ ይሄን “rhetoric” ብዙ አልገፋበትም። ደካማ አድርጎ ራሱን ዘወትር የሚስል ማንም፥ በዙሪያው ባሉ ሊከበር እንደማይችል ያውቃል’ና፤ በተለይ በፖለቲካ። አብይ ጠንክሮ ሲወጣ፣ ኮስታራ መሪ ሲሆን፣ ቀጥ ለጥ አድርጎ ሲገዛ ሲሰድቡት የነበሩ የአማራ አክቲቪስቶች ሳይቀሩ መልሰው በፍቅሩ እያበዱለት ነው። አማራው የተቀረጸበት እና ያደገበት ሥነ-ልቦና ከጀግንነት እና ከቆራጥነት ጋር እጅግ የተሳሰረ ነው። ባለፉት 30 ዓመታት በኦሮምኛ የተዘፈኑ እና የአማርኛ (በተለይ የባህል) ዘፈኖችን ቁጭ ብላችሁ አነጻጽሩ። አሁን የምናገረው እንደ ጉድ ይታያችኋል።

    ሀጫሉ ሁንዴሳ ከሌላው ዘፈኝ በተለየ ይሄ በጣም የገባው አዋቂ ዘፋኝ ነበር። ኦሮሞ ተገፋ፤ ጡት አስቆረጠ፤ ተኮረኮመ የሚሉ ዘፈኖች እምብዛም የሉትም። የአድዋ ድል ሲመጣ እነ ግርማ ጉተማ ይሄ ድል እኛን አይመለከተንም፤ እነ ጸጋዬ አራርሳ እኛ ለሌላ ቅኝ ግዛት የተዳረግንበት ነው ብለው በድል ቀን ሲያለቃቅሱ ሀጫሉ ግን ፈረሱ ላይ ጉብ ብሎ ባለፉት 28 ዓመታት ባልተለመደ መልኩ ይሄ ድል ከማንም በላይ የኛ ነው እያለ መስቀል አደባባይ ወጣ። የአድዋ ተራራ ሄደን ትግራይ የኛ ናት ያልነው ኦሮሞዎች ነን አለን። ታሪክ ብዙ ነገሩ ተረት ነው። ዋናው ቁም ነገር የሰው ልጅ እጅግ ኢ-ምክንያታዊ ስለሆነ ተረትም ተነገረው ታሪክ ‘አንተ እኮ ልዩ ነህ፤ አሸናፊ ነህ’ ከተባለ የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የአልያንስ ኃይሎች (the Allies) ጀርመንን ወደ አመድነት ከቀየሯት በኋላ አንድ የጀርመን ፖለቲከኛ ለጀርመኖች ያለው ነገር ነበር። “አገራችንን ከፈሏት። ሕንጻዎቻችንን አፈራረሱት። ስልጣኔያችንን አመድ አደረጉት። ጀርመናዊ አዕምሮአችንን ግን ከኛ መውሰድ አልቻሉም” ነበር ያለው። ጀርመን ዛሬ ካፈረሰቻት እንግሊዝ በተሻለ የኢኮኖሚ ቁመና ላይ ትገኛለች። በአውሮፓ ሕብረት በኩል ትልቅ ኢምፓየር ሆና ብቅ ብላለች። እዚህ ላይለመድረስ ከአራት አስርት ዓመታት በላይ አልፈጀባትም። አይሁዶችንም በተመሳሳይ መመልከት ነው። ከናዚ (Nazi) በኋላ የመጡት የጀርመን መሪዎች ብዙዎቻችን እንደምንገምተው በናዚ በተፈጸመ በደል ክፉኛ የሚጸጸቱ አልነበሩም። ይልቁስ ያን ሁሉ ተዓምር ጀርመን መሥራቷ ኩራት የወጠራቸው፣ ድጋሚ ኃያል ሀገር እንደሚሆኑ ለአፍታም ያልተጠራጠሩ ሕዝቦች ነበሩ። Paul Berman የተባለ አሜሪካዊ ጸሐፊ  “Power and the Idealist” ብሎ በጻፈው ድንቅ መጽሐፍ መጸጸት የጀመረ ትውልድ የመጣው ጀርመን በድጋሚ በኢኮኖሚ ከአበበች በኋላ በመጣው ትውልድ ነው ይላል። ዛሬ ለገጠማቸው ከስደተኛ ጋር ለተያያዘ መጠነ ሰፊ ችግር የጸጸት ሥነ-ልቦና ያለውን አስተዋጽኦ ያብራራል። ጄኔቫ (Geneva) እያለው አለቃዬ አይርሻዊ (Irish) ነበር። እንግሊዞች እንደ እኛ የበደሉት የለም ይለኛል። ለብዙ ዘመን እንግሊዝ እንዲህ አደረገን እያልን የተበዳይነት ፖለቲካ (victim politics) ስንሠራ ኖርን። ከእንግሊዝ ተላቀን እንኳ አዕምሮአችን ከእነሱ ነጻ አልወጣም ነበር። የገነቡትን ሃውልት ማፍረስ ሥራችን አደረግን። ወይ መልሰን የራሳችንን ሃውልት አላቆምን። መንገዶቹንም ሃውልቱን በማፍረስ ከትላንት የተሻለ ውብ አላደረግናቸውም፤ አስቀየሙ እንጂ። በኋላ ግን ባነንን አለ። ያኔ ነው ማደግ እና መለወጥ የጀመርነው። ከታሪካችን ጋር ታረቅን። የእንግሊዝን ድል የእኛ ድል አድርገን መቀበል እና መተረክ ጀመርን አለኝ። ከዚያ በብዙ ነገር ለመመንደግ ጊዜ አልፈጀብንም አለኝ።

    ኢትዮጵያኖች ራሳቸውን ከድል አድራጊ እና ከትልቅ ነገር ማጠጋጋት ነበር ታሪካቸው። ይሄ ተራ ጉራ የሚመስለው ሞኝ ይኖራል። በቅርብ ያገኘሁት አንድ ሸምገል ያለ ጥቁር አሜሪካዊ ዳኛ ጋር ስናወራ ለብዙ ጊዜ በራሴ እጠራጠር ነበር አለኝ። ውስጤ ውስጥ “ትችላለህ፣ አትችልም” የሚል ከባድ ትግል ነበር። ብዙ ምሳሌ እና እኔን የሚመስሉ አርአያ የሉኝም። ቀለሜ ያለመቻል ምሳሌ ሆኖ አሜሪካ ውስጥ ቆሟል። ይሄ የውስጥ ትግል ለእኔ አሰልቺ ነበር አለኝ። ኢትዮጵያኖች “ፑሽኪንን” ኢትዮጵያዊ ነው ሲሉ ለኢትዮጵያ ሥነ-ጽሑፍ ያበረከተው ነገር ኖሮ አይደለም። ነገ ለሚወለዱት፣ ከዛም ለሚሰደዱት ልጆቻቸው ‘የትም ሄደክ በሄድክበት ሀገር ካሉ ዜጎች በላይ አንተ የመብለጥ አቅም አለህ፤ አንተ ልዩ ነህ’ የሚል ታሪክ እየነገሩት ነው። ይሄ ትርክት ነው ነገ ልዩ የሚያደርገው። አስጨናቂውን የሕይወት ትግል አሸናፊ የሚያደርገው። የውብሸት ወርቃለማሁ ልጅ ዶ/ር ዳግማዊ ውብሸት በአሜሪካ ውስጥ ካሉ ስምንት ምርጥ ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ በሆነው Cornell University የእንግሊዘኛ ሥነ-ጽሑፍ አስተማሪ ነው። በአንድ ቃለ-መጠይቁ ላይ ወደ አሜሪካ ሲመጣ እንግሊዘኛ ካለመቻሉ በላይ አንብብ ሲባል ተማሪዎቹ በሳቅ ይወድቁ እንደነበረ ይገልጻል። “እነሱ ሲስቁ ጣልያንን ማሸነፋችን ትዝ እያለኝ፥ ‘ምናለ በሉኝ በራሳችሁ ቋንቋ እናንተን ካልበለጥኩ’ እያልኩ ለውስጤ እነገረው ነበር” ይላል። እንዳለውም በCornell University ታሪክ በእድሜ ትንሹ የእንግሊዘኛ ሥነ-ጽሑፍ ፕሮፌሰር ሆነ። ይሄ ተራ ዩኒቨርሲቲ አይደለም። አይደለም አስተማሪ ለመሆን ተማሪ ለመሆን እራሱ አስደናቂ አዕምሮ ሊኖርህ ይገባል። በነገራችን ላይ ከዚሁ ዩኒቨርሲቲ በኮምፒውተር ሳይንስ እና አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ በቅርብ በዶክትሬት ዲግሪ የተመረቀች የመጀመሪያዋ ጥቁር፥ ኢትዮጵያዊት ናት። ዶ/ር ረድኤት አበበ ትባላለች። ነገርን ነገር ያነሳዋል እንደሚባለው የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ተወዳዳሪ የምክትል ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን (Joe Biden) የሽግግር ካቢኔ መሪ ከታዋቂው ዬል ዩኒቨርሲቲ (Yale University) እና ሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ (Harvard University) የተመረቀው ዮሐንስ አብርሃም የተባለ ኢትዮጵያዊ መሆኑን ታውቃላችሁ። ይሄ ማለት ጆ ባይደን ካሸነፈ በዋይት ሀውስ (White House) ውስጥ ካሉት ትልልቅ ስልጣኖች ቁልፉ ቦታን የሚይይዘው ኢትዮጵያዊው ዮሐንስ አብርሃም ይሆናል ማለት ነው። ደግሞም አምናለው በእኛ የእድሜ ዘመን ውስጥ ከኦባማ ቀጥሎ የአሜሪካ ጥቁር ፕሬዝዳንት የሚሆነው ኢትዮጵያዊ ሊሆን ይችላል። ብዙ ድንቅ ኢትዮጵያውያን በሪፖብሊካንም ሆነ በዲሞክራቶች የፓርቲ መስመር የስልጣን መሰላሉን እየወጡ እየተመለከትን ነው።

    ወደ ቀደመ ነገሬ ልመለስ እና – የኦሮሞ ባህል ይሄን ነገር ካልመረመረ የብዙ አቅመ ድኩማን መደበቂያ እና የሽንፈት ታሪክ ወራሽ ልጆች መፈልፈያ ይሆናል። እስቲ ተመልከቱ – ብርሃነመስቀል አበበ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የአብይ ደጋፊ እና ደንበኛ የኢትዮጵያዊነት አቀንቃኝ ነበር። በአቅም ማነስ ከስልጣን ሲባረር ግን ኦሮሞነቱ ትዝ አለው። የወጣለት የኦሮሞ የመብት አቅንቃኝ ሆነ። ኦሮሞዎቹም ዓይንህን ለአፈር ብለው መስኪድ እንደገባ ውሻ እንዳላባረሩት፥ በአቅም ማነስ ተባሮ ሲመጣ ጀግና አድርገው ተቀበሉት። በተመሳሳይ አማራን እንይ፤ ልክ እንደ ብርሃነመስቀል አበበ ሲባረሩ አማራ ጉያ ውስጥ ለመደበቅ የፈለጉ ሰዎች በቅርብ ታሪካችን ነበሩ። ለምሳሌ ታምራት ላይኔ አንዱ ነው። አማራው ግን ከታምራት ላይኔ ይልቅ መለስ ዜናዊን ይወዳል። በተመሳሳይ ልደቱ አያሌውም ከፖለቲካው መድረክ ሲገለል፥ አማራ ስለሆንኩ ነው ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ የጠላኝ አለ። ዶ/ር ብርሃኑ እኮ የተደነቀ አዋቂ ሰው ነው። ምን ዓይነት ጅል ቢሆን ነው የድጋፍ ማዕከሉ የሆነውን የአማራን ሕዝብ የሚጠላው? የአማራ ሕዝብ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋን እንደሚያፈቅር ለማወቅ በአማራ ክልል እሱ የተገኘባቸውን ሠልፎች እና ስብሰባዎች ማየት ነው። ከልደቱ ይልቅ የአማራው ሕዝብ የብርሃኑ አመለካከት ይስበዋል። ሽንፈት፣ውድቀትን በዘር ቅርፊት ማሳበብ አማራው አምርሮ የሚጸየፈው ነገር ነው። ተሸንፈህ ከመጣ አማራነትህ ይነጠቃል።

    አጼ ቴዎድሮስ በመጀመሪያ በአማራው ሕዝብ እጅግ የተጠላ መሪ እንደነበረ ታሪክን ማገላበጥ ብቻ በቂ ነው። እነ ዮፍታሔ እና ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን ግን ቴዎድሮስን በጀግንነት ካባ አዲስ ሰው አድርገው አቀረበቱ። የቋራ ሰው እየተባለ፣ የኮሶ ሻጭ ሲባል ሲሰደብ የከረመው ቴዎድሮስ ህልሙ እና ጀግንነቱ ለሕዝቡ ተብራርቶ በአዋቂዎች ሲቀርብለት አማራ የሆነው በፍቅር አበደለት። ጀግና እና ዘመን ተሻጋሪ አዋቂን የሱ እንኳ ባይሆን እንደምንም የራሱ የማድረግ ባህል አለውና።

    በምድር ላይ እንደእሱ ዓይነት ጠቢብ የለም ብሎ መጽሐፍ ቅዱስ የሰበከለትን ሰሎሞን የተባለ ሌጀንድ የኢትዮጵያ ጠበብት ሲመለከቱት ጊዜ አላጠፉም። ኢትዮጵያዊ አጋቡት። በዓለም ታሪክ የዓለምን ፖለቲካ በመቀየር ፈጽሞ አቻ የሌለው የPlato “The Republic” መጽሐፍ ድንቅ ሕዝብ እና ታላቅ ሀገር በፈላስፋ ይመራል በሚል አስደናቂውን መጽሐፍ ይዘጋል። አባቶቻችን ይሄን ለመረዳት ከባድ የሆነን መጽሐፍ ያነበቡ ስለነበሩ ፥ በኢትዮጵያ ታሪክ የሚነግሰውን ሁሉ ከፈላስፋው ሰሎሞን ወልደ ዳዊት ጋር ሲያዛምዱት ቆዩ። ኢትዮጵያኖች ልጆቻችሁን አዎ ልዩ ናችሁ እያላችሁ አሳድጓቸው። አንብበው፣ ተመራምረው አዋቂ ሲሆኑ ሁሉን በራሳቸው ይደርሱበታል። እስከዛ ግን ይሄን ሥነ-ልቦና ፈጽማችሁ አትንጠቋቸው። እነሱን እዚህ አሜሪካ እንደሚወለደው ከአንጎላ በመርከብ ከመጣው ጥቁር አሜሪካዊ ጋር የተገዢነት ሥነ-ልቦና አታላብሷቸው። ጥቁሩን ሁሉ ነጻ የሚያወጣው ኢትዮጵያዊው እሱ መሆኑን ከልጅነቱ ጀምራችሁ ስበኩት።

    በመጨረሻም በአንድ አፈ-ታሪክ ምሳሌ ጹሑፌን ልዝጋ። ጅብ አህያን ለብዙ ጊዜ ሲፈራት ይኖር ነበር። ለዚህ ዋናው ምክንያት ደግሞ የአህያ ጆሮ ቀንድ እየመሰለው ነው። አህያ ጅብን መወዳጀት ስለምትፈልግ ለብዙ ጊዜ እንዲቀርባት ትሻ ነበር። አንድ ቀን ግን ለምን እንደሚሸሻት ጨክና ጠየቀችው። እሱም ቀንዶቿን እጅግ እንደሚፈራው ለዛም እንደሚሸሻት ነገራት። በመገረም “ይሄ እኮ ቀንድ አይደለም፤ ጆሮዬ ነው፤ ስጋ እንጂ አይዋጋም አለችው።” ከዚያ ቀን ጀምሮ አባራሪ እና ተባራሪ ቦታ ተለዋወጡ። ኢትዮጵያኖች ታሪኮቻችን፣ ድሎቻችን፣ ሃውልቶቻችን፣ ሃይማኖታችን ጅብ ከሆኑ ጠላቶቻችን መጠበቂያ ጋሻዎቻችን፣ ምሽጎቻችን ናቸው። ይሄን አጥተን ከመኖር ሁላችን ማለቅን መምረጥ ይሻለናል። ጆን ስቱዋርት ሚል (John Stuart Mill) እንዳለው “የተደሰተ አሳማ ከመሆን የተከፋ ሰው መሆን ይሸላል፣ ጅል ሆኖ ከመደሰት ሶቅራጦስን ሆኖ ዕድሜ ልክን ማዘን ይሻላል።” ለልጆቻችን የባርነትን፣ የተሸናፊነትን ሥነ-ልቦናን ከምናወርስ ሁላችን ቀድመን ማለቅ ይሻለናል። አባቴ ጀግና ነው እያለ ካላባት ያደገ ልጅ በፈሪ አባት ካደገ ልጅ በላይ በራስ መተማመኑ ኃያል ነው።

    * በዚህ ጽሑፍ ላይ አማራ ብዬ የጠቀስኩት ማኅበረሰብ በአሰፋ ጨቦ ትንታኔ መሠረት ሲሆን፥ ዘርን ሳይሆን የአባቶቻችንን ድል እና ኃያልነት የተቀበለውን፣ የማሸነፍ መንፈሱ የማይደረመስ ተራራ የሆነውን፣ በየሄደበት ሁሉ የአባቶቹን ድል አድራጊነት እያሰበ የበታችነትን እንቢ ያለውን ኢትዮጵያዊ ሁሉ የሚመለከት ነው።

    አማራ ብዬ የጠቀስኩት...

    Anonymous
    Inactive

    ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ መሠረታዊ፣ የምንደግፈው እና ተግባራዊ እንዲሆን የምንታገልለት መብት ነው!
    ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የተሰጠ መግለጫ

    አንኳር

    • ዘላቂ ውጤት ያላቸውን ሥራዎች የሕዝብ ፈቃድ ያላገኘ አስተዳደር የሕዝብ ፍላጎት ሳይታወቅ በዚህ የሽግግር ወቅት ሊተገብር እንደማይገባ በጽኑ እናምናለን።
    • ገዢው ፓርቲ በደቡብ ክልል የተነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ ያዘጋጀው የክላስተር አወቃቀር/ምደባ አሁን በሥራ ላይ ባለው ሕገ-መንግሥት ሕገ-ወጥ የሆነ፣ ደቡብ ክልል ሲዋቀር የተሠራውን ስህተት በመድገም ተመሳሳይ ችግርን በአንድ ዓይነት መፍትሄ ለመቅረፍ ደግሞ የሚሞክር (የትልቁን ደቡብ ችግር ትንንሽ ደቡቦች በመፍጠር ለመፍታት)፣ ከባለፈው ችግር ትምህርት ያልወሰደ ሂደት ነው።
    • በዚህ ከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት እና ጥንቃቄ በሚፈልግ ወቅት በደቡብ ክልል ራስን በራስ ለማስተዳደር የቀረቡ ግልጽ ጥያቄዎችን በፍፁም መመለስ የማይችል፣ ለችግሩ መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኝት ዓላማ ያደረገ ጥረት አመፅ እና ብጥብጥ ለማንሳት ለሚሞክሩ ኃይሎች ስንቅ እንደማቀበል የሚቆጠር ነው።
    • ከሕብረተሰቡ ለሚነሱ ጥያቄዎች ቀጥተኛ እና ዘላቂ መፍትሄ መስጠት ሲገባ ጊዜያዊ እና የሕዝቡን ጥያቄ የማይፈቱ አማራጮችን በማቅረብ የሕዝብን እውነተኛ የፍትህ እና የዴሞክራሲ ጥያቄዎችን ማፈን ተገቢ አይደለም።
    • ገዢው ፓርቲ ከሕግ አግባባ ውጪ በሆነ የመብት ሰጪ እና ነሺነት የሕዝብን ተቀባይነት ለማግኘት የሚያደርገውን ሩጫ በአስቸኳይ እንዲያቆም ኢዜማ አጥብቆ ያሳስባል። ይህ ሳይሆን ቀርቶ በዚህ ምክንያት በሰው ሕይወት እና ንብረት ላይ ለሚደርስ እያንዳንዱ ጉዳት ቀጥተኛ ተጠያቂ በራሱ ተነሳሽነት ጉዳዩን እየገፋ ያለው ገዢው ፓርቲ እንደሚሆን በግልፅ መታወቅ አለበት።

    ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ መሠረታዊ፣ የምንደግፈው እና ተግባራዊ እንዲሆን የምንታገልለት ጥያቄ ነው!
    ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የተሰጠ መግለጫ

    ሀገራችን ኢትዮጵያ ከረጅም ጊዜ የአምባገነን ሥርዓቶች መፈራረቅ እና ሥርዓቶቹን አስወግዶ ሕዝብን እውነተኛ የስልጣን ባለቤት ለማድረግ ከተደረገ የብዙዎችን መስዕዋትነት የጠየቀ ትግል በኋላ ወደእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግር ለማደርግ የሚያስችል ዕድል ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት አግኝታለች። ለ27 ዓመታት ሀገራችንን ዘውግን መሠረት ባደረገ አምባገነናዊ ፖለቲካዊ ሥርዓት ሲመራ የነበረው አገዛዝ ውስጥ የነበሩ የለውጥ አይቀሬነትን የተረዱ ግለሰቦች ለረጅም ጊዜ ሲደረግ የነበረውን ትግል በተወሰነ ደረጃ አግዘው ስልጣን መያዛቸው የሚታወስ ነው። እነዚህ ኃይሎች ስልጣን ላይ ከመውጣታቸው በፊት ለተፈፀሙ ጥፋቶች ይቅርታ ጠይቀው ሀገራችን ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግር ማድረግ እንዳለባት እንደሚያምኑ እና ይህንንም ሽግግር ጠንካራ መደላድል ላይ ለማስቀመጥ ነፃ እና ፍትሃዊ ምርጫ እስከሚደረግ ድረስ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚጠቅሙ የመንግሥት ተቋማት ጠንካራ እና ገለልተኛ ሆነው እንዲዋቀሩ እንዲሁም ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ማነቆ የሆኑ የፖለቲካ ምህዳሩን ያጠበቡ ሕጎችን እና አሠራሮችን ለመቀየር (ለማሻሻል) ቃል ገብተው ነበር።

    ሥርዓቱን ለመቀየር ትግል ሲያደርግ እና መስዕዋትነት ሲከፍል የነበረው ሕዝብ እና አብዛኞቹ የፖለቲካ ኃይሎችም ይህንን ዕድል በአጭር ጊዜ የፖለቲካ ስሌት ከማየት ይልቅ ስልጣን ላይ የወጣው ኃይል ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚደረገውን ሽግግር የሚያግዙ ሥራዎች ለመሥራት ቃል እስከገባ እና ይህንን ቃል የሚጠብቅ እስከሆነ ድረስ በረጅም ጊዜ ቀስ በቀስ የሚገነባ ሀገራዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ከፉክክር ውጪ በሆነ መልኩ ማገዝ እንደሚያስፈልግ አምኖ ምንም እንኳን ስልጣን የያዙት ከሕዝብ ውክልና ውጪ ቢሆንም እስከ ምርጫው ድረስ ስልጣን ላይ እንዲቆዩ ዕድል መስጠትን መርጧል።
    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህም (ኢዜማ)ከተመሠረተ ጀምሮ ለሀገር መረጋጋት እና ሰላም ቅድሚያ በመስጠት የፉክክር ጉዳዮችን ምርጫው ለሚደረግበት ጊዜ አቆይቶ ለሁላችንም የሚበጀውን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት ከሚፈልጉ አካላት ሁሉ ጋር በትብብር መንፈስ ሲሠራ ቆይቷል። በኢዜማ እምነት ቀጣዩ ምርጫ እስኪደረግ ድረስ ያለው የሽግግር ወቅት በዋነኛነት ሀገርን ለማረጋጋት እና ምርጫውን ነፃ እና ፍትሃዊ ለማድረግ መሠራት ያለባቸው ሥራዎች ማከናወኛ ነው። ዘላቂ ውጤት ያላቸውን ሥራዎች የሕዝብ ፈቃድ ያላገኘ አስተዳደር የሕዝብ ፍላጎት ሳይታወቅ በዚህ የሽግግር ወቅት ሊተገብር እንደማይገባ በጽኑ እናምናለን።

    የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰትን ተከትሎ ምርጫው በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መካሄድ እንደማይችል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ካሳወቀ በኋላ የኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት ባስቀመጠው የአምስት ዓመት ገደብ ውስጥ ምርጫው መደረግ ስላልቻለ ምርጫ ተደርጎ የሕዝብ ውክልና ያለው መንግሥት እስኪኖር ድረስ ሀገራችንን ማን ያስተዳድር የሚል ጥያቄ መነሳቱ ይታወሳል። ይህን ጥያቄ ተከትሎ ከነበሩት አማራጮች መካከል በድንገተኛ እና ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ምርጫ በተያዘለት ጊዜ ማድረግ ሳይቻል ሲቀር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የራሱን እና የአስፈጻሚውን አካል ስልጣን የዜጎችን ደህንነት፣ የሀገር ሉዓላዊነትን እና ምርጫውን ነፃ እና ፍትሃዊ ከማድረግ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ብቻ ገድቦ ምርጫውን እስከ አንድ ዓመት ለሚደርስ ጊዜ ማራዘም የሚያስችለውን ስልጣን ሕገ-መንግሥቱን በማሻሻል እንዲሰጠው ምክረ-ሀሳብ አቅርበን ነበር። ነገር ግን መንግሥት በወሰደው የሕገ-መንግሥት ትርጉም አማራጭ የሕገ-መንግሥት አጣሪ ጉባዔ ያቀረበለት ምክረ-ሀሳብ ላይ ተመሥርቶ የኢፌዴሪ ፌደሬሽን ምክር ቤት ምርጫው የሚካሄድበትን ጊዜም ሆነ የመንግሥትን ስልጣን ያልገደበ ውሳኔ አሳልፏል። የፌደሬሽን ምክር ቤት ምርጫው የሚካሄድበትን ጊዜ በወረርሽኙ ምክንያት ክፍት አድርጎ የተወው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ወረርሽኙ ባይጠፋም እንኳን በተጨማሪ ጥንቃቄ፣ ጊዜ እና በጀት ምርጫውን ማድረግ የሚቻልበት ሁኔታ (scenario) እንዳለ ለሕገ-መንግሥት አጣሪ ጉባዔ ከገለፀ በኋላ እና ምርጫው ያለገደብ እንዲራዘም የመጨረሻ ውሳኔ የሰጡት የምክር ቤቱ አብዛኛዎቹ አባላት «ምርጫው በቶሎ እንዲካሄድ እፈልጋለሁ» ብሎ በይፋ የተናገረው ገዢ ፓርቲ አባል መሆናቸው ውሳኔው የተሳሳተ ብቻ ሳይሆን ግልፅ ያልሆነ ዓላማ እንዳነገበም እንድንጠራጠር አድርጎናል።

    ይህ የ«ሕገ-መንግሥት ትርጉም» ለመንግሥት ያልተገደበ ስልጣን በሰጠ ማግስት በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ውስጥ የሚገኙ ዞኖች ካነሱት ራስን በራስ ማስተዳደር ጥያቄ ጋር ተያይዞ መንግሥት አስጠናሁ ያለውን ክልሉን ወደ አምስት የሚከፍል ምክረ-ሀሳብ ለመተገበር እንቅስቃሴ ላይ እንደሆነ ተረድተናል።

    ገዢው ፓርቲ በደቡብ ክልል የተነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ ያዘጋጀው የክላስተር አወቃቀር/ምደባ አሁን በሥራ ላይ ባለው ሕገ-መንግሥት ሕገ-ወጥ የሆነ፣ ደቡብ ክልል ሲዋቀር የተሠራውን ስህተት በመድገም ተመሳሳይ ችግርን በአንድ ዓይነት መፍትሄ ለመቅረፍ ደግሞ የሚሞክር (የትልቁን ደቡብ ችግር ትንንሽ ደቡቦች በመፍጠር ለመፍታት)፣ ከባለፈው ችግር ትምህርት ያልወሰደ ሂደት ነው። ከሁሉ በላይ ሀገራችን ኢትዮጵያ ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ ያላገናዘበ፣ ጭራሹንም የረሳ ነው።

    ሀገራችን በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ባለው ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መያዛቸው የተረጋገጡ እና ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር በእጅጉ እየጨመረ የሚገኝበት፣ ወረርሽኙን በቁጥጥር ስር ለማዋል በተወሰዱ እርምጃዎች ምክንያት 6ኛውን ሀገራዊ ምርጫ ለመግፋት የተገደድንበት፣ የንግድ እና አጠቃላይ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በከፍተኛ ደረጃ የተቀዛቀዘበት ሁኔታ ውስጥ ትገኛለች። ከዚህ በተጨማሪ ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር ተያይዞ የሚመጣብንን ጫና ለመቋቋም ከመቼውም ጊዜ በላይ ሀገራዊ አንድነት የሚያስፈልግበት እና ጫፍ የረገጠ ፅንፈኛ አመለካከት ያላቸው ኃይሎች ምርጫው መራዘሙን እንደሽፋን በመጠቀም ብጥብጥ ለማስነሳት ቀጠሮ በያዙበት ከፍተኛ ጥንቃቄን የሚፈልግ ወቅት ላይ እንገኛለን።

    በዚህ ከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት እና ጥንቃቄ በሚፈልግ ወቅት በደቡብ ክልል ራስን በራስ ለማስተዳደር የቀረቡ ግልጽ ጥያቄዎችን በፍፁም መመለስ የማይችል፣ ለችግሩ መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኝት ዓላማ ያደረገ ትልቁን ደቡብ ክልል ወደ አነስተኛ ደቡብ ክልሎች ለመቀየር የሚደረግ ጥረት አመፅ እና ብጥብጥ ለማንሳት ለሚሞክሩ ኃይሎች ስንቅ እንደማቀበል የሚቆጠር ነው።

    በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀፅ 47 ንዑስ አንቀፅ 2 መሠረት የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች የየራሳቸውን ክልል የማቋቋም መብት እንዳላቸው ይደነግጋል። ከሁለት አስር ዓመታት በላይ በተግባር የተፈተሸው ሕገ-መንግሥት ያረጋገጠው የብሔር ብሔረሰቦችን መብት አስከብራለሁ ብሎ ካስቀመጠው ተቃራኒ የሕዝቦች መብት ከመከበር ይልቅ የብሔራዊ አንድነት፣ ሰላም እና የሕዝቦች አብሮ መኖርን አደጋ ላይ መጣሉን ነው። ይህ ሕገ-መንግሥት በስልጣን እስከቆየ ድረስ ሀገራችን ኢትዮጵያ ተረጋግታ እንደ ሀገር የመቀጠሏ ብሎም ሕዝቦቿ በነፃነት ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው የመኖር መብታቸው የሚከበርበት መንገድ እንደሌለ በተግባር ተፈትኖ ግልጽ ሆኗል። ይልቁንም የተለያዩ አጀንዳ ያላቸው የፖለቲካ ኃይሎች ይህንን የሕገ-መንግሥት ክፍተት ተጠቅመው ወደማያባራ እና መጨረሻ ወደሌለው የማንነት፣ የክልልነት እንዲሁም የሀገር እንሁንነት ጥያቄዎችን ሊያስከትል ይችላል።

    ሕገ-መንግሥቱ በራሱ ምሉዕ ካለመሆኑም በተጨማሪ ከፍተኛ የአፈፃፀም ጉድለት አለበት። በስልጣን ላይ የነበረው መንግሥት እራሱ ባረቀቀው ሕገ-መንግሥት ውስጥ ከተቀመጡት አካሄዶች ባፈነገጠ መልኩ የተወሰነ ቡድን ፍላጎትን ለማሟላት እና በፖለቲካ ጥቅም አሳዳጅነት ብሎም ለሕዝብ እና ለሀሳቡ ካለው ንቀት በሕዝብ ቁጥር አነስተኛ የሆኑ አካባቢዎችን በክልልነት ሲያካልል እና እውቅና ሲሰጥ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ያላቸውን አካባቢዎች በመጨፍለቅ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልልን መሥርቷል። በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት መሠረት አሁን ለፌደሬሽን ምክር ቤት «ክልል እንሁን» የሚል ጥያቄ ያስገቡት ዞኖችን ክልል እንዳይሆኑ ለመከልከል ምንም ሕጋዊም ሆነ የሞራል ምክንያት የለም።

    ከምሥረታው ጀመሮ በብዙሃን ቅቡልነት ያልነበረው የዚህ ክልል አደረጃጀት ክልሉ ከተመሠረተ በኋላ ሲተገበሩ በነበሩ አግላይ ፖሊሲዎች፣ የሀብት እና የስልጣን ከፍፍል ኢ-ፍትሃዊነት እናም የመልካም አስተዳደር እጦት በብዙ የክልሉ ማኅበረሰብ ዘንድ የክልልነት ጥያቄዎች እንዲነሱ ከፍተኛ አስተዋፅዖ አድርጓል። ለዚህም ከሕብረተሰቡ ለሚነሱ ጥያቄዎች ቀጥተኛ እና ዘላቂ መፍትሄ መስጠት ሲገባ ጊዜያዊ እና የሕዝቡን ጥያቄ የማይፈቱ አማራጮችን በማቅረብ የሕዝብን እውነተኛ የፍትህ እና የዴሞክራሲ ጥያቄዎችን ማፈን ተገቢ አይደለም።

    በኢዜማ እምነት ራስን በራስ ማስተዳደር ጥያቄ መሠረታዊ፣ የምንደግፈው እና ተግባራዊ እንዲሆን የምንታገልለት ጥያቄ ነው። በእርግጥ አሁን በሥራ ላይ ባለው የፌደራል አወቃቀር መሠረት ዘውግን መሠረት አድርጎ የሚደረግ የአስተዳደር አከላለል ራስን በራስ ከማስተዳደር ይልቅ አካባቢውን ለዘውግ ማንነት የባለቤትነት ካርታ መስጫ መንገድ እንደሆነ ግልጽ ነው። ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ በክልል ወይም በዞን ደረጃ ብቻ የሚመለስ አለመሆኑንም በጽኑ እናምናለን። በደቡብ ክልል የተነሱ ጥያቄዎችን የወለደው የተዛባው ሕገ-መንግስታዊ የመስፈርት አጣብቂኝ፣ በሌብነት የተዘፈቀ ሥርዓት፤ ፍትህ ማጣት፤ የሀብት ክፍፍል ኢ-ፍትሃዊነት፤ እንደልብ ተንቀሳቅሶ ሰርቶ ሀብት በማፍራት የንብረቱ ሕጋዊ ባለቤት የመሆን ብሎም በሰላም የመኖር መሠረታዊ መብት መነፈግ እና የመሳሰሉት አስተዳደራዊ በደሎች ጥርቅም መሆኑን እንረዳለን። አሁን የተጀመረው እንቅስቃሴ ችግሮቹን ማከፋፈል እና ማሰራጨት እንጂ ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት የሚያስችል ስላልሆነ ከበደሎቹም ባሻገር የወደፊት መጪ ስጋቶች ፍንትው ብለው እየታዩ ነው። ወደፊት ሀብት የሚፈስባቸው ከተሞች ባለቤትነት እና በሕዝብ ስም የሚፈፀሙ የበጀት ምዝበራዎች ከስጋቶቹ መካከል ዋነኞቹ ናቸው። በራስ የሚተዳደደር ክልል እና ዞን መሆንን መፈለግ የእነዚህ በደሎች እና መጪ ስጋቶቸ ውጤት መሆኑን በቅጡ እንደሚረዳ ፓርቲ አሁን ለመሄድ እየታሰበበት ያለው መንገድ ለበደሎቹም ሆነ ለስጋቶቹ መፍትሄ እንደማይሆን ጠንቅቀን እናውቃለን።

    እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ የሕዝቦች በየትኛውም ደረጃ ያለ የስልጣን እርከን ባለቤትነት መረጋገጥ ቁልፍ እርምጃ ነው። ይህ ደግሞ ሊሳካ የሚችለው እያንዳንዱ ዜጋ ከታችኛው የስልጣን እርከን ጀምሮ የሚያሰተዳድሩትን አመራሮች መምረጥ ሲችል ነው። መሰል የዜጎች ሕጋዊ የስልጣን ባለቤትነት ባልተረጋገጠበት ሁኔታ በየትኛውም ቦታ የሚካሄድ የትኛውም ዓይነት ዘላቂ ውጤት ያለው ውሳኔ የዜጎችን መሠረታዊ ጥያቄ መልስ መስጠት የሚችል እንዳልሆነ ፍንትው ያለ ሃቅ ነው።

    ዛሬም ቢሆን በአብዛኛው ሕዝብ ዘንድ ከሚነሳው፤ እኛም እንደ ሀገራዊ ፓርቲ ካሉን መዋቅሮች ከሚደርሱን መረጃዎች እንደተገነዘብነው ትላንት አፋኝ እና ኢ-ዴሞክራሲያዊ ከሆነው ሥርዓት ጋር ተባባሪ በመሆን በሕዝባቸው ላይ ለደረሰው መከራ ቀዳሚ ተጠያቂ የሆኑ ግለሰቦች፣ በየደረጃው ያሉ አመራሮችና ካድሬዎች በውሳኔ ሰጪነት ስልጣን ላይ ናቸው። ለውጥ እንዲመጣ ዋጋ የከፈሉ፣ ለፍትህ እና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት እንዲሁም ለሕዝባቸው እኩል ተጠቃሚነት የታገሉ ግለሰቦችም ሆኑ ድርጅቶች በየደረጃው ባሉ የመንግሥት ውሳኔዎች ላይ ሀሳባቸው ሊሰማ ሲገባ ዛሬም በእነዚህ የመንግሥት አካላት ተፅዕኖ እየደረሰባቸው እንደሆነም ጭምር የምንረዳው ሃቅ ነው።

    ገዢው ፓርቲ ይሄን ያልታደሰና የመለወጥም ፍላጎት እያሳየ ባልሆነው የካድሬና የባለሥልጣናት መዋቅሩ በደቡብ ክልል እየቀረበ ያለውን ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ለማፈን እያደረገ ያለው ሩጫ የሕዝብን መሠረታዊ ጥያቄ የማይመልስ ብቻ ሳይሆን ፓርቲው እያሳየ ያለውን የመብት ሰጪ እና ነሺነት ፍላጎትንም የሚያሳይ ነው። ይህ በየግዜው ከለውጡ አጠቃላይ መንፈስ እየራቀ የመጣው የገዢው ፓርቲ ፍላጎት በሀገራችን እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት የሚያደናቅፍም ጭምር ነው።

    ገዢው ፓርቲ በአንድ በኩል በኮቪድ-19 ወረርሸኝ እና ከህዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ ባለው ጫና እግር ከወረች ተይዣለው በማለት ስድሰተኛውን ሀገር አቀፍ ምርጫ ላልተወሰነ ግዜ እያራዘመ በሌላ በኩል በዚሁ ጭንቅ ጊዜ ዘላቂ ውጤታ ያላቸው ትልልቅ ሥራዎችን ያለሕዝብ ምክክር እና ውሳኔ በራሱ እያከናወነ ይገኛል። ገዢው ፓርቲ ከሕግ አግባባ ውጪ በሆነ የመብት ሰጪ እና ነሺነት የሕዝብን ተቀባይነት ለማግኘት የሚያደርገውን ሩጫ በአስቸኳይ እንዲያቆም ኢዜማ አጥብቆ ያሳስባል። ይህ ሳይሆን ቀርቶ በዚህ ምክንያት በሰው ሕይወት እና ንብረት ላይ ለሚደርስ እያንዳንዱ ጉዳት ቀጥተኛ ተጠያቂ በራሱ ተነሳሽነት ጉዳዩን እየገፋ ያለው ገዢው ፓርቲ እንደሚሆን በግልፅ መታወቅ አለበት።

    በደቡብ ክልል የምትኖሩ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን፥ ኢዜማ ደቡብ ክልል የሕዝቡን ፍላጎት ባሟላ መልኩ እንደገና እንዲዋቀር እንደሚፈልግ እንድትረዱ እና ለምታነሱት ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ትክክለኛ እና ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት አሁን ያለንበት ጊዜ እንደማይፈቅድ እና የእናንተን ፍላጎት የሚያስፈጽሙ በእናንተው የተመረጡ ወኪሎቻችሁ ሳይኖሩ እኔ አውቅልሃለው በሚሉ ካድሬዎች ሊከወን የሚቻል እንዳልሆነ በመረዳት፣ ቀጣዩ ምርጫ ተደርጎ ፍላጎቶቻችሁን የሚያስፈጽሙ ወኪሎቻችሁን እስክትመርጡ እና በጥያቄያችሁ ላይ ሰፊ ውይይት አድርጋችሁ በሕዝበ-ውሳኔ መወሰን የምትችሉበት ሁኔታ እስኪመቻች በተለመደው ኢትዮጵያዊ ጨዋነት እና ትዕግስት እንድትጠብቁ አበክረን እንጠይቃለን። ይህንን ተረድታችሁ ለጋራ ሀገራችን መረጋጋት እና ሰላም በማሰብ ጥያቄዎቻችሁን በሰከነ መንገድ ለመፍታት ለምታሳዩት ትዕግስት ከወዲሁ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የከበረ ምስጋና ያቀርባል።

    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)
    ሰኔ 9 ቀን 2012 ዓ.ም.

    ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ

    Anonymous
    Inactive

    የዜጎች ሰብዓዊ መብት መከበር በምንም ምክንያት እና በማንኛውም ጊዜ ለድርድር የማይቀርብ ነው!
    ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

    አምነስቲ ኢንተርናሽናል (Amnesty International) «ሕግን ከማስከበር ባሻገር» በሚል ርዕስ ባወጣው ዘገባ በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች ሁለት አካባቢዎች በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ተፈጽመዋል ያላቸውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ዘርዝሯል። በዘገባው ውስጥ በፀጥታ አስከባሪዎች እርምጃ በአሰቃቂ እና ከሕግ ውጪ በሆነ ሁኔታ የዜጎች ሕይወት መጥፋቱን፣ ሴቶች መደፈራቸውን፣ በማቆያ ካምፖች ውስጥ ሰቆቃ መፈፀሙን፣ ከሕግ አግባብ ውጪ እስር መፈጸሙን፣ ዜጎች ከሚኖሩበት እንደተፈናቀሉ እና ንብረታቸው እንደወደመ ተዘርዝሯል። በተጨማሪም በተለያዩ ማኅበረሰቦች መካከል የእርስበርስ ግጭት ሲከሰት የአካባቢ አስተዳዳሪዎች እና ፀጥታ ኃይሎች የዜጎችን ደኅንነት ከማስጠበቅ ይልቅ በግጭቱ ውስጥ እንደተሳተፉ እንዲሁም ኃላፊነታቸውንም በአግባቡ እንዳልተወጡ ተጠቅሷል። እነዚህ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ጉባዔ በአካባቢው ይፈፀማሉ ብሎ ካወጣው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ዘገባ ጋር ተመሳሳይነት አላቸው።

    በዘገባው ውስጥ የተጠቀሱት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተ ዘገባውን በሠራው ተቋም ምላሽ ወይንም ማብራሪያ ከተጠየቁ የፌደራል እና የክልል ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቶች መካከል የአማራ ክልል የሰላም እና ደህንነት ግንባታ ቢሮ ብቻ መልስ እንደሰጠ ዘገባው ጠቅሷል። በሁሉም ደረጃ ያሉ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በተሰማሩበት የኃላፊነት ዘርፍ የተከሰቱ ችግሮችን በተመለከተ የሚቀርብላቸውን የማብራሪያ ጥያቄዎች በቀናነት መቀበል እና ምላሽ መስጠት ግዴታቸው እንደሆነ እናምናለን። የሚቀርቡ ጥያቄዎችን በርን ክፍት አድርጎ መቀበል እና ግልጽነት የተሞላው ምላሽ መስጠት፣ እንዲሁም የተሠሩ ስህተቶችን ለማረም ዝግጁ መሆን በሂደት ለምንገነባው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አስፈላጊ እሴቶች ናቸው። በዚህ ረገድ የአማራ ክልል ሰላም እና ደህንነት ግንባታ ቢሮ ላሳየው አርኣያ የሚሆን ተግባር ያለንን አክብሮት መግለጽ እንወዳለን። የፌደራል መንግሥቱን ጨምሮ በሁሉም ደረጃ የሚገኙ የመንግሥት አካላት በተለይ ከሰብዓዊ መብት ጋር በተያያዘ ለሚነሱላቸው ጥያቄዎች እና ጥቆማዎች ከዳተኝነት እና ተጠያቂነትን ለመሸሽ ከሚደረግ ማንኛውም ሙከራ በመታቀብ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው ምላሽ መስጠት ይጠበቅባቸዋል።

    የአምነስቲ ዘገባ በሁለት የተወሰኑ ቦታዎች እና ውስን ክስተቶች ላይ ያጠነጠነ መሆኑ ተከሰቱ የተባሉትን ጥሰቶችም ሆነ ሌላ በሀገራችን የተከሰቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ሙሉ በሙሉ ለመረዳትም ሆነ የእርምት እርምጃ ለመውሰድ በቂ መረጃ የያዘ ነው ተብሎ ባይወሰድም በውስጡ የያዛቸው የከፍተኛ ሰብዓዊ መብት ጥሰት ሰለባ የሆኑ ዜጎች ስም፣ የተፈጸመበት ቦታ እና ጥሰቱን እንደፈጸሙ የተጠቀሱት ተቋማት በግልጽ መቀመጥ ግን የመረጃውን ትክክለኛነት ለማጣራት ቀላል ከማድረጉም በላይ ተጨማሪ ምርመራ ተደርጎ የተጠቀሱት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸው ከተረጋገጠ የእርምት እርምጃ መወሰድ እንዳለበት ከበቂ በላይ አመላካች ናቸው። በአምነስቲ ዘገባ ያልተካተቱ በየጊዜው ለዜጎች ሕይወት መጥፋት፣ የአካል መጉደል፣ ከመኖሪያቸው መፈናቀል፣ የተማሪዎች መታፈን፣ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት መታሰር እና መንገላታትን ጨምሮ በተለያየ መንገድ ይፋ የተደረጉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዳሉም ይታወቃል።

    በመሆኑም የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በአምነስቲ ኢንተርናሽናል ዘገባ ውስጥ የተካተቱትን ጨምሮ የለውጡ አስተዳደር ሥልጣን ላይ ከወጣበት ጊዜ አንስቶ በፌደራል እና የክልል መንግሥት የጸጥታ ኃይሎች፣ የፖለቲካ ዓላማ ባነገቡ ታጣቂዎች እንዲሁም በየአካባቢው በተደራጁ ኢ-መደበኛ ቡድኖች ዜጎች ላይ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የሚመረምር ልዩ ቡድን በአስቸኳይ እንዲያቋቁም እና ምርመራ አድርጎ ውጤቱን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ለክልሎቹ ምክር ቤቶች እና ለሕዝብ ይፋ እንዲያደርግ እንጠይቃለን። በዘገባው በተጠቀሱ እና ከዛም ውጪ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደተፈጸመባቸው በሚታወቁ (በሚጠረጠሩ) ቦታዎች የተከሰቱት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በቦታው ድረስ በመገኘት ከተጎጂዎች እና ከተጎጂ ቤተሰቦች፣ በጊዜው በአካባቢው ግዳጅ ላይ ከነበሩ የፀጥታ አስከባሪዎች፣ የአካባቢው አስተዳዳሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻዎችን በማግኘት ሰፊ ምርመራ እንዲደረግ እንጠይቃለን።

    የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ይህንን ኃላፊነት እንዲወስድ ማድረግ እና አስፈላጊውን ድጋፍ መስጠት የሀገራችንን ችግሮች አውድ በበለጠ የሚገነዘብ እና በዜጎች ዘንድ ያለው ተዓማኒነት በሂደት እያደገ የሚሄድ ሀገር በቀል የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ተቋም እንዲሆን እንዲሁም የተቋሙን አቅም በሂደት በመገንባት ለምናደርገው የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ በጎ አስተዋፅዎ እንደሚያደርግ እናምናለን።

    የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በዜጎች ዘንድ ያላቸው አመኔታ እና የሕዝብ ወገንተኝነት ስሜት መገንባት ለምንፈልገው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን በመረዳት በሚደረግው ምርመራ ውስጥ ኃላፊነታቸውን የሚመጥን ትብብር እንዲያደርጉ እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተፈጽመው በሚገኙበት ጊዜ ሁሉ ጥፋቱን በቀጥታ የፈፀሙ፣ እንዲፈፀም ትዕዛዝ የሰጡ እና ዜጎችን ከአደጋ የመጠበቅ ኃላፊነታቸውን በማንኛውም መንገድ ያልተወጡ አባሎቻቸው ላይ አስተማሪ የሆነ እርምጃ ወስደው ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እና ለሕዝብ ወገተኝነታቸውን እንዲያረጋግጡ አንጠይቃለን።

    በዚህ አጋጣሚ በተለይ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የሀገራችንን ድንበር እና ሉዓላዊነት ለማስከበር እና በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች የሚነሱ ችግሮችን ለመቆጣጠር እና መፍትሄ ለመስጠት እየከፈለ ላለው መስዕዋትነት ከፍተኛ አድናቆት እና ክብር እንዳለን ለመግለጽ እንወዳለን። ሠራዊቱ በመደበኛነት ሥልጠና ከወሰደበት የግዳጅ ዓይነት የተለየ እና ሰላማዊ ዜጎች በሚኖሩበት ቦታዎች የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅ እና የሕግ የበላይነትን ለማስፈን የሚወስዳቸው ግዳጆች የሚፈልጉትን ተጨማሪ ሥልጠናዎች በአግባቡ ማግኘት እንዳለበት ለማሳሰብ እንወዳለን። ነገር ግን የሠራዊቱን መስዕዋትነት እና ያለበትን ኃላፊነት በፍፁም በማይመጥን መልኩ የዜጎች ሰብዓዊ መብት ላይ ጥቃት እንዳደረሱ የተረጋገጡ እና በምንም መልኩ እጃቸው ያለበትን አባላቱ ላይ አስተማሪ እርምጃ በመውሰድ የሕዝብ አለኝታነቱን እንዲያረጋግጥ አጥብቀን እንጠይቃለን።

    ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ግልጽ እንዳደረግነው፣ ምንም ሕገ መንግሥታዊ መሰረት የሌለው የክልል ልዩ ኃይል አደረጃጀት የዜጎችን ደህንነት ከማስጠበቅ ይልቅ እራሱን የአንድ ወገን ጠባቂ እና ተከላካይ አድርጎ በመቁጠር ለዜጎች ደህንነት ስጋት ሆኖ መቀጠሉን የሚያሳዩ ተደጋጋሚ ማስረጃዎች እያየን ነው። ስለዚህም መንግሥት ይህን በየክልሉ የተደራጀ ልዩ ኃይል ወደክልሎቹ መደበኛ የፖሊስ ኃይል አልያም የፌደራል ፖሊስ እና የሀገር መከላከያ ሠራዊት እንዲቀላቅል አሁንም ደግመን እናሳስባለን።

    የኢትዮጵያ መንግሥት የዜጎች ሰብዓዊ መብት መከበር በምንም ምክንያት እና በማንኛውም ጊዜ ለድርድር የማይቀርብ መሆኑን እና ዜጎች ላይ ጥፋት የሚያደርሱ አካላትን ተጠያቂ ማድረግ መገንባት ለምንፈልገው ሥርዓት ያለውን ከፍተኛ ዋጋ በመረዳት ለዜጎች ደህንነት እና ሰብዓዊ መብቶች መጠበቅ እና ተጠያቂነት እንዲሰፍን ያለውን ቁርጠኝነት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ለሚያደርገው ልዩ ምርመራ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ በማድረግ እና በምርመራው ውጤት ላይ በመመስረትም አስፈላጊውን የእርምት እርምጃ በመውሰድ ቁርጠኝነቱን በድጋሚ እንዲያረጋግጥ እናሳስባለን።

    የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችም የሰብዓዊ መብት ጥሰትን እና በየጊዜው የሚከሰቱ ጉዳዮችን ሰበብ በማድረግ የሀገር መረጋጋትን እና ሰላምን እንዲሁም የዜጎችን ደህንነት አደጋ ውስጥ ሊጥል ከሚችል የፖለቲካ ትርፍን ዓላማ ካደረገ ማንኛውም እንቅስቃሴ እንዲታቀቡ አጥብቀን እንጠይቃለን።

    የኢዜማ ሕዝብ ግንኙነት
    ግንቦት 25 ቀን 2012 ዓ.ም

    የዜጎች ሰብዓዊ መብት መከበር

    Anonymous
    Inactive

    ከአብሮነት ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት (አብሮነት) የተሰጠ መግለጫ
    ስልጣንን በሕገ-ወጥ መንገድ ለማራዘም የሚደረግ ሙከራ በአስቸኳይ ይቁም!

    ሀገራችን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር ሆና የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከፍተኛ ጥረት እያደረገች በምትገኝበት በአሁኑ ወቅት ገዥው ብልፅግና ፓርቲ ግን የስልጣን ዘመኑን በሕገ-ወጥ መንገድ ለማራዘም የሚያስችለውን ጥረት ለሕዝብ ይፋ ባልሆነ መንገድ እያደረገ ስለመሆኑ መረጃዎች እየደረሱን ነው። ገዥው ፓርቲ በአገሪቱ ሕገ-መንግሥት ከተሰጠው ስልጣንና መብት ውጭ በሦስት አማራጮች ስልጣኑን ለማራዘም እየሞከረ እንደሚገኝ ታውቋል።
    እነዚህ አማራጮችም፤-

    1. በዓመቱ መጨረሻ ላይ የአገሪቱ ፓርላማ እንዲበተን ማድረግና በ6ወር ጊዜ ውስጥ ሀገራዊ ምርጫ እንዲካሄድ ማድረግ፤
    2. የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እንደገና በማራዘም የመንግሥትን የሥራ ዘመን ለማራዘም መሞከር፤
    3. የአገሪቱን ሕገ-መንግሥት በማሻሻል የመንግሥትን የሥራ ዘመን ለተወሰነ ጊዜ ማራዘም የሚሉ ናቸው።

    ከእነዚህ አማራጮች ውስጥ በየትኛው መንገድ የመንግሥትን ስልጣን ለማራዘም እንደሚቻልም ገዥው ፓርቲ ከራሱ መዋቅሮችና በዙሪያው ከሚገኙ የሕግ ባለሙያዎች ጋር እየመከረ እንደሆነ ታውቋል።

    አብሮነት ከዚህ ቀደም ደጋግሞ ለመግለፅ እንደሞከረው ከመስከረም 30 ቀን 2013 ዓ.ም. በኋላ ለአንድም ቀን በስልጣን ላይ የሚገኘውን መንግሥት ዕድሜ ለማራዘም የሚያስችል ምንም ዓይነት ድንጋጌ በሀገራችን ሕገ-መንግሥት ውስጥ የለም። በሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ 58/3 እና አንቀፅ 72/3 መሠረት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሥራ ዘመን አምስት ዓመት ብቻ ስለመሆኑ በግልፅ ተቀምጧል። አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ወይም ምርጫ ማካሄድ የማይቻልበት አስገዳጅ ሁኔታ ሲገጥም የመንግሥትን ዕድሜ እንዴት ማራዘም እንደሚቻል ሕገ-መንግሥቱ ምንም ዓይነት ድንጋጌ አላስቀመጠም። ስለሆነም ብልፅግና ፓርቲ እንዲህ ዓይነት ሕገ-መንግሥታዊ ቀውስ እንዲከሰት ምክንያት የሆኑትን የሕገ-መንግሥቱን አርቃቂዎች እና ለሕገ-መንግሥቱ ክፍተት መታየት ምክንያት የሆነውን ኮሮና ቫይረስን “ከመርገም” ውጭ በሕጋዊ መንገድ የስልጣን ዘመኑን ለአንድም ቀን የሚያራዝምበት ምንም ዓይነት መብትና ስልጣን በሕገ-መንግሥቱ አልተሰጠውም።

    በሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ 60 ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን በትነው በ6ወር ጊዜ ውስጥ ምርጫ እንዲያካሂዱ ስልጣን የተሰጣቸውም በሕገ-መንግሥቱ የተቀመጠውን አምስት ዓመት የመንግሥት የስልጣን ዘመን ለመጨረስ ነው እንጂ ከአምስት ዓመት በላይ የመንግሥትን የሥራ ዘመን ለማራዘም አይደለም። እንዲያውም በሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ 60/1 ላይ በግልፅ እንደተቀመጠው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሳኔ ድጋሜ ምርጫ መካሄድ የሚችለው በስልጣን ላይ ያለው መንግሥት የሥራ ዘመን ከመጠናቀቁ በፊት ብቻ ነው። ስለዚህ ይህ ሕገ-መንግሥታዊ ድንጋጌ በሕግ የተሰጠን የሥራ ዘመን ለማጠናቀቅ ከመቻል ጋር እንጂ የሥራ ዘመንን ከማራዘምና የመንግሥት የሥራ ዘመን ካለቀ በኋላ ከሚካሄድ ምርጫ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የለውም።

    በሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ 93/1፣ ሀ እና ለ ላይ በግልፅ እንደተደነገገውም የመንግሥትን የስልጣን ዘመን ለማራዘም ተብሎ ሊታወጅ የሚችል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የለም። አሻሚና አከራካሪ ባልሆነ መንገድ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለምን ዓይነት ጉዳዮች ሊታወጅ እንደሚችል ሕገ-መንግሥቱ በዝርዝርና በግልፅ ስላስቀመጠ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማዎጅ ስልጣኑን ለአንድም ቀን ለማራዘም የሚያስችለው ሕጋዊ መብትና ስልጣን የለውም።

    እንደ ሦስተኛ አማራጭ እየታየ ያለው ሕገ-መንግሥቱን አሻሽሎ የመንግሥትን የሥራ ዘመን ለማራዘም መሞከርም ሕጋዊነትን የተከተለ አሠራር አይደለም። አንድ በስልጣን ላይ የሚገኝ መንግሥት የራሱን የስልጣን ዘመን ለማራዘም ሲል በሥራ ላይ ያለውን ሕገ-መንግሥት የሚያሻሽል ከሆነ፣ እንዲህ ዓይነቱ ድርጊት እንደ አንዳንድ አምባገነን የአፍሪካ መሪዎች በዓለም ፊት መሳቂያ እና መሳለቂያ የሚያደርግ የአምባገነኖች ድርጊት እንጂ ሕጋዊ አሠራር ተደርጎ ሊቆጠር አይችልም። እንዲህ ዓይነቱ የስልጣን ዘመንን ለማራዘም ሲባል ሕገ-መንግሥትን ለማሻሻል የመሞከር እርምጃም ከሕግ መኖርና አስፈላጊነት መሠረታዊ መርህ ጋር የሚጋጭ ሕገ-ወጥ ተግባር ነው። በእንዲህ ዓይነቱ ሂደትም ማንኛውም የፖለቲካ ኃይል የሕዝብ ቅቡልነት ሊያገኝ አይችልም። እንዲህ ዓይነቱን ከባድ ሀገራዊ ጉዳይ አሳታፊና ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ለመወሰን መሞከርም ሀገራችን በአሁኑ ወቅት ምን ያህል ሁለንተናዊ የህልውና ፈተና ውስጥ እንደምትገኝ አለመረዳት ነው። ይህም እንደተለመደው የገዥውን ፓርቲ ከሀገር ጥቅም ይልቅ የራሱን ስልጣን የማስቀደም ኃላፊነት የጎደለው ፍልጎት የሚያሳይ ነው።

    ስለዚህ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የሕገ-መንግሥቱ አርቃቂዎች በሠሩት ስህተት እና በኮሮና ቫይረስ ወደ ሀገራችን መግባት ምክንያት በአሁኑ ወቅት በሀገራችን የመንግሥት የሥራ ዘመንን አስመልክቶ ሕገ-መንግሥታዊ ቀውስ (constitutional crisis) መፈጠሩን አምኖ መቀበል ያስፈልጋል። እንዲህ ዓይነት ሕገ-መንግሥታዊ ቀውስ በአንድ አገር ሲፈጠር ደግሞ ለችግሩ መፍትሄ መስጠት የሚቻለው በመደበኛ የሕግ አሠራር ሳይሆን ከመደበኛ የሕግ አሠራር ውጭ (extra-constitutional) በሆነ መንገድ ነው። እንዲህ ዓይነቱን መፍትሄ ለመስጠትም በተለየ ሁኔታ በሕግ መብት የተሰጠው የፖለቲካ ፓርቲ ወይም መንግሥታዊ ተቋም ስለሌለ የተፈጠረውን ሕገ-መንግሥታዊ ቀውስ እንዴት እንፍታው? በሚለው ጥያቄ ተነጋግሮ የመፍትሄ አቅጣጫ የሚያስቀምጥ ሁሉን አቀፍ ሀገራዊ የምክከር ሂደት (national dialogue) መጥራት ያስፈልጋል። ከመስከረም 30 ቀን 2013 ዓ.ም. በኋላ በሀገራችን በሕጋዊም ይሁን በይስሙላ ምርጫ የተመረጠ መንግሥት ስለማይኖር የወደፊቱን የአገሪቱን ዕጣ-ፈንታ በመወሰን ረገድ ገዥው ብልፅግና ፓርቲ ከማንኛችንም በአገሪቱ ከምንገኝ ፓርቲዎች የተለየ መብትና ስልጣን ስለሌለው በጉዳዩ ላይ ምንም ዓይነት ውሳኔ ብቻውን መወሰን አይችልም። ገዥው ፓርቲ ይህንን ማድረግ ከሞከረ በሀገራችን ከፍተኛ የፖለቲካ ቀውስ እና ትርምስ ሊፈጠር እንደሚችል ቆም ብሎ ማሰብ ያስፈልጋል።

    ስለሆነም፦

    1ኛ. በአሁኑ ወቅት ዋናውና ቀዳሚው ትኩረታችን የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን መከላከልና መቆጣጠር መሆን ስላለበት ቢያንስ እስከ ነሃሴ መጨረሻ 2012 ዓ.ም. ድረስ ብልፅግና ፓርቲ የተፈጠረውን ሕገ-መንግሥታዊ ቀውስ በተመለከተ ምንም ዓይነት አጀንዳ ይዞ እንዳይነጋገርም ሆነ የተናጠል ውሳኔ እንዳያስተላልፍ፤

    2ኛ. የትግራይ ክልላዊ መንግሥት በዘንድሮው ዓመት በተናጠል ምርጫ ለማካሄድ ማሰቡ ሕገ-መንግሥታዊ ውሳኔ አይደለም። በሀገሪቱ ሕገ-መንግሥት መሠረት በፌደራልም ሆነ በክልል ደረጃ ምርጫ ለማካሄድ ብቸኛ መብት የተሰጠው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ መሆኑን በመገንዘብ የትግራይ ክልላዊ መንግሥትም ሆነ ህወሓት ከዚህ ዓይነቱ ሕገ-ወጥ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ፤

    3ኛ. ብልፅግና ፓርቲ ይህንን አጀንዳ በሚመለከት በድብቅ የሚፈፅማቸውን ተግባራት ሁሉም ተቃዋሚ ፓርቲዎች በንቃት እንዲከታተሉ፣ ገዥው ፓርቲ ይህንን አጀንዳ በተመለከተ ሕገ-ወጥ እርምጃ መውሰዱን የሚቀጥልበት ከሆነም ተቃዋሚ ፓርቲዎች አመቺ የመገናኛ መንገድ ፈጥረው በአስቸኳይ መመካከር እንዲችሉና በጉዳዩ ላይ የራሳቸውን አቋም እንዲይዙ፣ ከዚህ በኋላም በሀገራችን ጉዳይ አንዳችን ጋባዥ ሌላችን ተጋባዥ የምንሆንበት ምክንያት እንደሌለ ተገንዝበን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከገዥው ፓርቲ ጋር የምናደርገው ማንኛውም ግንኙነትና ድርድር በእኩልነት መንፈስ ብቻ እንዲሆን የሚያስችል አቋም እንድንይዝ፤

    4ኛ. የኢትዮጵያ ሕዝብ ላለፉት 29 ዓመታት በአፈናና በይስሙላ ምርጫ በስልጣን ላይ የኖረው ገዥው ፓርቲ ከመስከረም 30 ቀን 2013 ዓ.ም. በኋላ ለአንድም ቀን በስልጣን ላይ ሊቀጥል የሚችልበት ምንም ዓይነት ሕጋዊ መብት የሌለው መሆኑን ተገንዝቦ በሕገ-ወጥ መንገድ ስልጣን ላይ ለመቆየት የሚደረገውን ጥረት አጥብቆ እንዲቃወም፣ መቃወምም ብቻ ሳይሆን የገዥውን ፓርቲ ሕገ-ወጥ እርምጃ በጠንካራ ሕጋዊና ሰላማዊ ትግል ለማስቆም እንዲዘጋጅ አብሮነት ጥሪውን ያቀርባል።

    አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት (አብሮነት)
    ሚያዚያ 21 2012 ዓ.ም
    አዲስ አበባ

    አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት

    Anonymous
    Inactive

    የምንሰጠው ሕጋዊና ፖለቲካዊ አማራጭ ከወቅታዊው የኮሮና ወረርሽኝ የሚታደገን፣ ሀገረ-መንግሥቱን የሚያስቀጥልና ወደ ተረጋጋ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የምናደርገውን ሽግግር የሚያግዝ ሊሆን ይገባል! ― የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)

    ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የተሰጠ የአቋም መግለጫ

    የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከባድ ጉዳት እያደረሰ እንደሆነ ይታወቃል። ወረርሽኙ በሰዎች ጤና እና ደኅንነት ላይ ካደረሰው እና እያደረሰ ካለው ጉዳት ባልተናነሰ የዓለምን እና የሀገራትን ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ መስተጋብሮች እና ሥርዓትን ከባድ አደጋ ውስጥ ከቷል። ወረርሽኙ በሀገራችን ኢትዮጵያ እስከካሁን ያስከተለው ጉዳት ከሌሎች ሀገሮች ጋር ሲነጻጸር አስከፊ የሚባል ባይሆንም የደቀነው አደጋ ግን ከፍተኛ መሆኑ እርግጥ ነው። በሌሎች ሀገር ከታየው ተሞክሮ አንፃር ወረርሽኙ ድንገት በከፍተኛ ቁጥር ዜጎችን ሊያጠቃ እና የጤና ሥርዓት ቀውስ ውስጥ ሊከተን የሚችልበት አደጋ አሁንም አለ። የጎረቤት ሀገሮች (ሱዳን፣ ጅቡቲ እና ሶማሊያ) የኮሮና ቫይረስ ስርጭት በፍጥነት መዛመት የጀመረበትና በተለይ ከጅቡቲ ጋር ካለን የቀረበ የኢኮኖሚ ትስስር አንፃር በምሥራቁ የሀገራችን ክፍል ላይ የደቀነው ስጋት ከፍተኛ እንደሆነ ግልጽ ነው።

    ወረርሽኙን ለመቆጣጠር የሚወሰዱ እርምጃዎች በሀገራችን ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳርፉት ጫና ከአሁኑ እየታየ ነው። ወረርሽኙ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያደርሰው ጫናም በወጪ እና ገቢ ንግድ ዘርፍ ላይ ጫና እያሳደረ ሲሆን ይህም በቶሎ ወደቀድሞ ሁኔታው የሚመለስ አይሆንም። የበረሀ አንበጣ በኢትዮጵያ የግብርና ምርት ላይ እንደዚሁም የአገር ውስጥ ጥቅል ምርት ዕድገት ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተጽዕኖ ከፍተኛ ነው። በተጨማሪም በኮሮና ምክንያት ከፍተኛ የኢኮኖሚ መቀዛቀዝና እስከ ሰኔ ድረስ ከሁለት ሚሊዮን በላይ የሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዋስትና የማጣት ስጋት/አደጋ እንዳንዣበበባቸው በቅርቡ ተገልጿል። በአጠቃላይ ቫይረሱ በኢኮኖሚው ላይ የሚያስከትለው መጠነ ሰፊ መቀዛቀዝና የአገራዊ ጥቅል አመታዊ ምርትና እድገት ማሽቆልቆል ሀገራችን ላይ የከፋ ጉዳት ማስከተሉ አይቀሬ ነው።

    በሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ የወረርሽኙ ተጽዕኖ ከኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ ጫና በተጨማሪ በፖለቲካው ዘርፍም በታሪካችን አጋጥሞን የማያውቅ ሁኔታ ውስጥ ከቶናል።

    ከወረርሽኙ በተጨማሪ ከዚህ ቀደም የነበሩ የውስጥ ፖለቲካዊ ችግሮች እና በዓባይ ወንዝ ላይ እየገነባን ካለነው የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ጋር በተያየዘ ከሌሎች ሀገሮች የተደቀነብን አደጋ በፍፁም በቀላሉ የሚታይ አይደለም። በተለይም ከግድቡ የውሃ ሙሌት ጋር ተያይዞ የሚመጣው ተጽዕኖ እየጨመረ እንደሚሄድ ይጠበቃል።

    የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ምክንያት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም ሊደረግ ታስቦ የነበረውን 6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ማካሄድ እንደማይችል መጋቢት 22 ቀን 2012 ዓ.ም አስታውቋል። ምርጫው በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መካሄድ አለመቻሉ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የክልል ምክር ቤቶች የሥራ ዘመን ከተጠናቀቀ በኋላ ሀገርን ማን ያስተዳድራል የሚል ሕገ-መንግሥታዊ ጥያቄ አስነስቷል። በዚህም ምክንያት የተለያዩ አካላት ለዚህ ጉዳይ መፍትሄ ነው የሚሉትን ሀሳብ እያቀረቡ ይገኛሉ።

    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በዚህ ጉዳይ ላይ ከሕግ ባለሙያዎች ጋር በተለይም ከሕገ-መንግሥት ጠበቆች (constitutional lawyers) ጋር ሰፊ ውይይት አድርጓል። ባለሙያዎቹ የተፈጠረውን ሕገ-መንግሥታዊ ክፍተት በሕገ-መንግሥታዊ አግባብ እንዴት ሊፈታ ይችላል የሚለውን የወቅቱ ትልቅ ጥያቄ ጊዜ ሰጥተው እንዲመክሩበት የከፍተኛ የባለሙያዎች ጉባዔ (high level panel of experts) በማቋቋም ለአንድ ወር ያህል ጉዳዩን ሲያስጠናና ምክክር ሲያስደርግበት ቆይቷል። ኢዜማ ከገባንበት የፖለቲካ አጣብቂኝ ለመውጣት ልንከተለው የሚገባው የመፍትሔ ሀሳብ የሚከተሉትን ታሳቢዎች ከግምት ያስገባ መሆን እንዳለበት በጽኑ ያምናል፤

    1. አገራችን ከምትገኝበት የሕግም የፖለቲካ አጣብቂኝ በአጭር ጊዜ ለመውጣት የሚረዳ መሆን እንዳለበት፣
    2. ተቋማዊ አሠራሮችን ከማጎልበት አንፃር የተሻለ ዕድል የሚፈጥር መሆን እንዳለበት፣
    3. አጠቃላይ ችግሩ በአጭር ጊዜ ፈቶ አገራችን ወደተረጋጋ የምርጫ ሂደት ለመግባት የሚያስችል መሆን እንዳለበት፣
    4. ከወጪም ከጊዜም አንፃር አገሪቱን ብዙ ዋጋ የማያስከፍል የተሻለው አማራጭ ላይ ትኩረት መደረግ እንዳለበትና በፍጥነት የተቀያየሩት የአገራችንንና የቀጠናውን ጂኦ-ፖለቲካዊና የደኅንነት ስጋቶች በሚገባ ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆን እንዳለበት።

    ኢዜማ ከላይ የገለፅናቸውን ሀገራዊ ፈተናዎች ለማለፍ ሕዝብን አስተባብሮ ሊመራ የሚችል ጠንካራ መንግሥት እንደሚያስፈልገን ያምናል። ለዚህም እንደፓርቲ ልንከተለው የሚገባን የመፍትሄ ሀሳብ ይህንን የሚያረጋግጥ መሆን እንደሚገባው በፅኑ ይረዳል። ለዚህም ይረዳ ዘንድ የፓርቲያችንን የሕግ ባለሙያዎች ጨምሮ በሌሎች አካላትም የቀረቡትን የመፍትሔ ሀሳቦች እንደሚከተለው ተመልክተናቸዋል።

    1. ከሕግ አማራጭ ውጪ የፖለቲካ መፍትሄ በሚል በተለያዩ አካላት የቀረበ የመፍትሄ ሀሳብ

    በዋናነት በዚህ ረገድ የቀረበው ሀሳብ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት የሥልጣን ዘመን ከመስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም. በኋላ የሚያበቃ በመሆኑ እና ሕገ-መንግሥቱም ከመስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም. በፊት መንግሥት በሥልጣን ላይ የሚቆይበትን ሁኔታ ክፍተት ስለማይሰጥ በፖለቲካ ፓርቲዎች ንግግር ላይ የተመሠረተ የሽግግር መንግሥት ሀገሪቱን ሊመራ ይገባል የሚል ነው። ይህ መፍትሄ ሀሳብ አሁን ያሉትን የፖለቲካ ፓርቲዎች የእርስ በርስ ግንኙነት እና የቁጥር ብዛት ከግምት ያላስገባ በመሆኑ ተግባራዊ ለማድረግ የማይቻል ነው። ከዚህም በላይ እንደ ሀገር ያሉብንን ከላይ የጠቀስናቸውን ፈተናዎች ተጋፍጦ ለማለፍ የሚያስፈልገንን ጠንካራ የመንግሥት መዋቅር የሚፈጥር አይደለም። ይህም የገባንበትን ችግር ከመፍታት ይልቅ ወደባሰ ሀገራዊ ቀውስ ሊከተን የሚችል አማራጭ ያደርገዋል።

    1. በሕገ-መንግሥቱ ማዕቀፍ ሥር ያሉ አማራጮች

    2.1. በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 60/1 እና 3 መሠረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን በትነው በ6 ወር ውስጥ ምርጫ ማድረግ፦ ይሄ አማራጭ በ6 ወር ውስጥ ሊፈጠሩ የሚችሉ እና ሕግ ማውጣት የሚያስፈልጋቸው ድንገተኛ የሀገር እና ሕዝብን ደኅንነት እና ጥቅም አደጋ ውስጥ ሊከቱ የሚችሉ ሁኔታዎች ከግምት የማያስገባ፣ የፌደራል መንግሥትን እንጂ ሥልጣናቸው አብሮ የሚጠናቀቀውን የክልል ምክር ቤቶች ተመሳሳይ ችግር ያላገናዘበ አማራጭ በመሆኑ የምንፈልገውን ጠንካራ መንግሥት የሚፈጥር አማራጭ ሆኖ አላገኘነውም።

    2.2. በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 93 መሠረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ እና ምርጫውን ማራዘም፦ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመንግሥትን የሥልጣን ዘመን ለማራዘም የተቀመጠ አንቀጽ አይደለም። አስቸኳይ ግዜ ማዋጅም በቀጥታ የመንግሥትን ሥልጣን ማራዘምን አያስከትልም። እንዲሁም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጥላ ስር የሚደረግ ምርጫን ነፃ እና ፍትሃዊ ማድረግ አይቻልም።

    2.3. በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 83 እና 84 መሠረት የሕገ-መንግሥት ትርጉም ከፌደሬሽን ምክር ቤት መጠየቅ፦ በዚህ አማራጭ መሠረት የሕገ-መንግሥት ትርጉም ሥራ የሚሠራው የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ በሙሉ ነፃነት እና ያለማንም ጣልቃ ገብነት የተመራለትን ጉዳይ በመመርመር የውሳኔ ሀሳብ አቅርቦ የፌደሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ የሚሰጥ ከሆነ ያ ውሳኔ ምን ሊሆን እንደሚችል በእርግጠኝነት ማወቅ አይቻልም። አሁን ካለንበት አጣብቂኝ ክብደት አንጻር ጉዳዩን መዳረሻ ውጤቱ አስቀድሞ በእርግጠኝነት ለማይታወቅ እና ምናልባትም መልሶ እዚህ ከተጠቀሱት አማራጮች መካከል አንደኛውን እንድንከተል ሊያደርግ ለሚችል ሂደት መስጠት ተገቢ ሆኖ አላገኘነውም።

    2.4. በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 104 እና 105/2 መሠረት የሕገ-መንግሥት ማሻሻያ ማድረግ፦ ይህ አማራጭ በሕገ-መንግሥቱ ውስጥ በግልጽ የተቀመጠ የማስፈጸሚያ ሥነ ሥርዓት ያለው እና አሁን ለገባንበት አጣብቂኝ የማያዳግም ምላሽ የሚሰጥ ሆኖ አግኝተነዋል።

    ምንም እንኳን ኢዜማ በሕገ-መንግሥቱ ውስጥ ሊሻሻሉ የሚገባቸው በርካታ አንቀጾች እንዳሉ በፅኑ ቢያምንም፥ አሁን ያለንበት ወቅት ሁሉን አቀፍ ሕገ-መንግሥታዊ ማሻሻያ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል አይደለም። አሁን ለገባንበት ሕገ-መንግሥታዊ አጣብቂኝም ቀልጣፋ ምላሽ የሚሰጥ አይደለም። በኢዜማ እምነት ሁሉን አቀፍ ሕገ-መንግሥታዊ ማሻሻያ ለማድረግ ሀገራዊ መረጋጋት፣ በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት እና ሰፊ ሕዝባዊ ተሳትፎ የሚጠይቅ ነው። እንዲሁም በከፍተኛ በጥንቃቄ ሊሠራ እንደሚገባው ሀገራዊ ጉዳይ በዚህ ወቅት ሊከወን አይገባም ብለን እናምናለን። ሆኖም አሁን የገጠመንን አጣብቂኝ ለመሻገር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱን የሥራ ዘመን እና ምርጫ የሚደረግበትን ወቅት የሚደነግገው አንቀጽ 58ን ጊዜውን ጠብቆ ምርጫ ለማድረግ የማያስችል ድንገተኛ እና ከአቅም በላይ የሆነ ችግር በሚያጋጥምበት ጊዜ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከ1 ዓመት ላልበለጠ ጊዜ ምርጫውን ማራዘም እና ምርጫው እስኪደረግ ድረስ ዘላቂ ውጤት ያላቸውን እና በቀጣይ ምርጫውን አሸንፎ ሥልጣን በሚይዘው መንግሥት ላይ ተጨማሪ ኃላፊነትን የሚጥሉ ተግባራትን ከመከወን በከለከለ መልኩ የመንግሥትን ቀጣይነት በግልፅ የሚደነግግ አድርጎ በማሻሻል ቀጥተኛ፣ ሕገ-መንግሥታዊ፣ የማያዳግም እና ተቀባይነት ያለው መፍትሄ መስጠት አስፈላጊ ሆኖ አግኝተነዋል።

    በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 105/2 ሀ እና ለ መሠረት የሕዝብ ተወካዮች እና የፌደሬሽን ምክር ቤቶች በጋራ ስብሰባ በ2/3ኛ ድምፅ ማሻሻያውን ሲያጸድቁ እንዲሁም ከክልል ምክር ቤቶች ውስጥ 2/3ኛ ክልሎች (6 ክልሎች) በአብላጫ ድምፅ ሲያጸድቁት በሕገ-መንግሥቱ ምዕራፍ 3 ስር ከሚገኙት እና አንቀጽ 104 እና 105 ውጪ ያሉትን የሕገ-መንግሥት አንቀጾች ማሻሻል እንደሚቻል ተደንግጓል። በዚሁ መሠረት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱን የሥራ ዘመን እና ምርጫ የሚደረግበትን ወቅት የሚደነግገው አንቀጽ 58/3 ከላይ በተገለጸው መሠረት ማሻሻል የተሻለ መፍትሄ እንደሆነ እናምናለን።

    ይህ መፍትሄ ተግባራዊ ከተደረገ በሥራ ላይ ያለውን ሕገ-መንግሥት ተከትሎ የሚፈፀም በመሆኑ ሕገ ምንግሥታዊ ጥያቄ የሚያስነሳ አይሆንም። እንዲሁም በቅርቡ ልናደርገው ከምናስበው ምርጫ እና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አንፃርም አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል ብለን እናምናለን። በዚህ አማራጭ ላይ በተለያዩ አካላት የሚነሳው ጥያቄ በዚህ የወረርሽኝ ወቅት በአንቀጽ 104 ድንጋጌ መሠረት ህዝብን ለማወያየት አያስችልም የሚል ሲሆን ይህንን ክፍተት ግን ሕዝቡን በወኪሎቹ አማካኝነትና በተለያዩ የቴክኖሎጂ አማራጮች በማወያየት መሸፈን ይቻላል።

    ከዚህ ቀደም በሕገ-መንግሥቱ ውስጥ የጋራ የታክስ እና የግብር ሥልጣንን የሚደነግገው አንቀጽ 98 እና የሕዝብ ቆጠራን በሚመለክት የሚካሄድበት የጊዜ ገደብን የሚደነግገው አንቀጽ 103/5 በሕገ-መንግሥቱ የተጠቀሰውን የማሻሻያ ሥነ ሥርዓት ሙሉ በሙሉ ሳይከተሉ ለየብቻ በተለያየ ጊዜ ማሻሻያ ተደርጎባቸው እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፥ አሁን መደረግ ያለበት ማሻሻያ ግን የሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 104 እና 105/2 ያስቀመጡትን ድንጋጌዎች በሙሉ አሟልቶ ሊሆን እንደሚገባው እናምናለን።

    ይህ የሕገ-መንግሥት ማሻሻያ ተግባራዊ የሚደረግ ከሆነ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተጨማሪ የክልል ምክር ቤቶችንና የፌድሬሽን ምክር ቤትንም የሥልጣን ዘመን በሚያራዝም መልኩ መተግበር አለበት።

    የፓርቲያችን እምነት የሕገ-መንግሥቱን አንቀጽ 58/3 ማሻሻል የተሻለ አማራጭ ነው የሚል ቢሆንም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከላይ በተራ ቁጥር 2.3 ላይ የጠቀስነውን አማራጭ በመውሰድ የሕገ-መንግሥቱን አንቀጥ 54/1፤ 58/3 እና 93 ላይ ትርጉም እንዲሰጥ ለፌደሬሽን ምክር ቤት እንደመራው ታውቋል። ምንም እንኳን ኢዜማ ይህንን አማራጭ የተሻለ አማራጭ ነው ብሎ ባያምንም አማራጩ ተግባራዊ የሚደረግ ከሆነ የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔው ሕገ-መንግሥቱን በሚተረጉምበት ወቅት ከመንግሥትም ሆነ ከሌላ ማንኛውም አካል ተፅዕኖ ነፃ ሆኖ ተግባሩን ማከናወን አለበት። የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ በሚያቀርበው የውሳኔ ሀሳብ የፌደሬሽን ምክር ቤት የሚያጸድቀው ትርጉም የመንግሥትን ሥልጣን በማንኛውም መልኩ የሚያራዘም ከሆነ ማራዘሚያውን እጅግ ቢገፋ ከ1 ዓመት እንዳይበልጥ ማድረግ አለበት። ውሳኔው በዚህ የማራዘሚያ ወቅት ሥልጣን ላይ የሚቆየው መንግሥት ዘላቂ ውጤት ያላቸውን እና በቀጣይ ምርጫውን አሸንፎ ሥልጣን በሚይዘው መንግሥት ላይ ተጨማሪ ኃላፊነትን የሚጥሉ ተግባራትን ከመፈፀም እንዲቆጠብ የሚያስገድድ መሆንም አለበት።

    በአጠቃላይ እንደሀገር የሚወሰዱ ማንኛውም አማራጮች አሁን ያለንበትን አስቸጋሪ እና ፈታኝ ወቅት ከግምት ያስገቡ፣ የሀገር መረጋጋት፣ ሰለም እና ቀጣይነትን የሚያረጋግጡ፣ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሂደቱን የሚያስቀጥሉ እንዲሁም አሁን ከገባንበት ሕገ-መንግሥታዊ አጣብቂኝ በአስተማማኝ ሁኔታ የሚያስወጡን መሆን እንዳለባቸው ኢዜማ ለማሳሰብ ይወዳል። በተጨማሪም በተመሳሳይ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚወሰኑ ውሳኔዎች የተለያየ አመለካከት ካላቸው የፖለቲካ ኃይሎች ጋር በሚደረግ ውይይት መዳበራቸው መፍጠር የምንፈልገውን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንድንለማመድ በር የሚከፍት እና ሁሉንም ኃይሎች የባለቤትነት ስሜት እንዲሰማን የሚያደርግ በመሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተመሳሳይ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ በቂ እና ቀጣይነት ያለው ውይይት የምናደርግበት መድረክ እንዲመቻች ጥሪ እናቀርባለን።

    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)
    ሚያዝያ 28 ቀን 2012 ዓ.ም
    አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)

    Anonymous
    Inactive

    የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የምርጫ 2012 ኦፕሬሽን እቅድ እና የጊዜ ሰሌዳ ላይ የፈጠረውን ችግር ገምግሞ ያሳለፈው ውሳኔ መግለጫ

    የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በ2012 ዓ.ም የሚካሄደውን አጠቃላይ ምርጫ ለማስፈፀም የቅድመ ምርጫ ዝግጅት ሥራዎች ሲያከናውን ከቆየ በኋላ የምርጫ የጊዜ ሰሌዳውን ይፋ አድርጓል።

    በዚህ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ መሠረት ምርጫው ነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም. እንዲካሄድ ተወስኖ ቦርዱ በጊዜ ሰሌዳው የተገለጹ ተግባራትን በተያዘላቸው ጊዜ እያከናወነ ለሕዝብ እያሳወቀ እንደቆየ ይታወሳል። በዚህም መሠረት በያዝነው መጋቢት እና በሚመጣው ሚያዝያ ወራት 2012 ዓ.ም. መጠናቀቅ ያለባቸው በርካታ ሥራዎች አሉ። መከናወን ካለባቸው ሥራዎች ዋና ዋናዎቹ የመራጮች ምዝገባ፤ የምርጫ አስፈፃሚዎች ምልመላ፤ ስልጠናና ስምሪት፤ የመራጮች ትምህርት፤ ለመራጮች ምዝገባ የሚያስፈልጉ ቁሳቁስ ስርጭት የመሳሰሉት ናቸው።

    እነዚህን ሥራዎች በጊዜ ሰሌዳው መሠረት ለማከናወን ቦርዱ ተገቢ ጥረት እያደረገ በሚገኝበት ወቅት ባለፉት ሳምንታት በሃገራችን እና በዓለም ላይ የተከሰተው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እንቅስቃሴዎች እንዲቋረጡ አስገድዷል። ከዚሁ የወረርሽኝ ሥጋት የተነሳ በርካታ ሃገራት ምርጫን ጨምሮ መንግሥታዊ ዕቅዶቻቸውን ለማቋረጥ ተገደዋል። በሃገራችንም መንግሥት ወረርሺኙን ለመከላከል የሰዎች ግንኙነትን የመቀነስ እርምጃዎች እንዲወሰዱ በመወሰኑ የመንግሥት ሠራተኞች አብዛኛውን ሥራ ከቤት ሆነው እንዲሠሩ ተደርጓል፡መንግሥት የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የተለያዩ ጥብቅ እርምጃዎችን እየወሰደ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም በክልል መንግሥት መስተዳድሮች ደረጃ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ የውስጥና የአገር አቋራጭ የትራንስፓርት ገደቦች፣ የመሰብሰብ ገደቦችን የመሳሰሉ ጥብቅ ክልከላዎች ይፋ ሆነዋል።

    በመንግሥት ከተላለፉ የክልከላ ውሳኔዎች በተጨማሪ ለቦርዱ ድጋፍ የሚያደርጉ ዓለምአቀፍ አጋር ድርጅቶች አብዛኞቹ ሠራተኞቻቸው ከቤት ሆነው እንዲሠሩ ሲደረጉ አንዳንዶቹ ደግሞ ጥቂቶቹን ብቻ በማስቀረት ሠራተኞቻቸው ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ አድርገዋል። ከላይ የተጠቀሱት ድምር ሁኔታዎች በሚያዚያ ሊጀመር በታቀደው የመራጮች ምዝገባ እና ተያያዥ የዝግጅት ሥራዎች ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳድሯል። ከዚህ የሚከተሉት ከችግሩ ማሳያ ከሚሆኑት ጥቂቶቹ ናቸው።

    • በኢትዮጵያ አየር መንገድ መጋዘን የሚገኙ የምርጫ ቁሳቁሶችን የማሸግ ሥራ በሁለት ሳምንት ዘግይቷል፤
    • የቀሪ ህትመት ውጤቶች ግዥ በቫይረሱ ምክንያት በተፈጠረ የአቅርቦት ሰንሰለት መደናቀፍ ምክንያት ተጓቷል፤
    • ለምርጫ አስፈፃሚዎች ስልጠና ቁጥራቸው 1000 /አንድ ሺ/ በላይ የሚሆን አሰልጣኞችን ክክልሎች ወደ አዲስ አበባ በማምጣት የአሰልጣኞች ስልጠና መስጠት አልተቻለም፤
    • ለ150,000 (አንድ መቶ ሃምሳ ሺህ) የምርጫ አስፈፃሚዎች በየክልሎቹ መሰጠት ያለበትን ስልጠና መጀመር አልተቻለም፤
    • ቦርዱ የሚሰጠው የመራጮች ትምህርት ኮቪድ-19 ቫይረስን አስመልክቶ በሚወጡ የማኅበረሰብ ጤና መልእዕቶች ሊዋጡ የሚችሉበት ዕድል ከፍተኛ ሆኖ ተገኝቷል።

    የቫይረሱ ስጋት በቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ በአጠቃላይ በተለይም በአፋጣኝ መፈጸም ባለባቸው የመራጮች ምዝገባ፤ የምርጫ አስፈፃሚዎች ስልጠና፤ የመራጮች ትምህርት ተግባራት አፈፃፀም ላይ ሊኖረው የሚችለውን ተፅዕኖ አስመልክቶ ቦርዱ ከሕግ አውጪው አካል፤ በጉዳዩ ላይ ከሚሠሩ የጤና ሚኒስቴር ከፍተኛ የማኅበረሰብ ጤና ባለሞያዎች፣ ከዓለምአቀፍ አጋሮች እና ከፖለቲካ ፓርቲዎች እና ጋር ተመካክሯል።

    ከፓለቲካ ፓርቲዎች ጋር በተደረገው ውይይት አብዛኞቹ ፓርቲዎች የችግሩን ግዝፈት እና በምርጫ ላይ የሚኖረውን ተጽዕኖ ተገንዝበው ቦርዱ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር ተመካክሮ አማራጭ የአፈጻጸም ዕቅድ ሊኖረው እነደሚገባ መክረዋል። ይሁን እና በዚህ አግባብ የሚወሰደው እርምጃ ችግሩ ከሚጠይቀው በላይ የሆነ መዘናጋት እንዳያመጣ ቦርዱ በወረርሽኙ አፈጻጸማቸው የማይስተጓጎል ሥራዎችን እንዲያጠናቅቅ አሳስበዋል።

    ቦርዱ ለውሳኔው መሠረት የሚሆነው የዳሰሳ ጥናት በአማካሪ ባለሙያዎቹ ተሠርቶ እንዲቀርብለትም አድርጓል ። የተፈጠረው አጠቃላይ ሁኔታ ከታቀደው የምርጫ ምዝገባና ቀጣይ እርምጃዎች ላይ ሊያሳድር የሚችለውን ተፅዕኖ ባግባቡ ለመዳሰስ ያስችለው ዘንድ በዳሰሳ ጥናቱ ላይ ተመሥርቶ ቦርዱ ሁለት የቢሆን ሁኔታ ግምቶች (scenarios) ተመልክቷል።

    የመጀመሪያው የቢሆን ሁኔታ ግምት መሠረት የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመግታት በኢትዮጵያ መንግሥት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች ለአራት ሳምንት ብቻ ማለትም እስከ ሚያዚያ 7 ሊቆይ ይችላል በሚል ግምት ላይ የተመሠረተ ነው። ክልከላው የአራት ሳምንት ብቻ የሚቆይ ከሆነ አሁን ባለው የጊዜ ሰሌዳ ዋና የሆነውን የመራጮች ምዝገባ ቢያንስ በአራት ሳምንት የሚገፋው ሲሆን ምዝገባው ቢከናወን የማኅበረሰቡ ተሳትፎ፣ የምርጫው ተአማኒነት ማግኘትን እና የኦፕሬሽን ድጋፍ የሚያደርጉ ተቋማት ድጋፍን ሙሉ ለሙሉ ማግኘትን በጣም አስቸጋሪ መሆኑን ያሳያል።

    ቫይረሱ በቁጥጥር ስር ካልዋለም የመራጮች ምዝገባን ማካሄድ የማኅበረሰብ ደኅንነትን አደጋ ውስጥ የሚጥል ከመሆኑም በተጨማሪ ከማኅበረሰብ የጤና ደኅንነት ከመጠበቅ አንጻር ጥቂት እንኳን ክልከላዎች የሚኖሩ ከሆነ ይህንን ዕቅድ ወደ ተግባር መለወጥ አስቸጋሪ ያደርገዋል።

    በተጨማሪም በያዝነው ሳምንት መንግሥት ተጨማሪ እርምጃ እየወሰደ መቀጠሉ፣ እንዲሁም ቦርዱ ከጤና ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለሙያዎች ጋር ባደረገው ውይይት እስከ ሚያዚያ መጨረሻም ሁኔታው የመሻሻል ዕድል እንደሌለ የተገለጸለት በመሆኑ፣ በዚህ የቢሆን ሁኔታ ግምት በታየው መልኩ የመራጮች ምዝገባን በተያዘለት ጊዜ ማከናወን እንደማይቻል ቦርዱ መረዳት ችሏል።

    የዳሰሳ ጥናቱ ሁለተኛ የቢሆን ሁኔታ ግምት የሚያሳየው ወረርሽኙን ለመቆጣጠር መንግሥት የሚወስዳቸው እርምጃዎች ከሚያዚያ 7 ቀን 2012 ዓ.ም. በኋላ ላልተወሰነ ጊዜ ሊቆዩ ይችላሉ፤ በመሆኑም በመንግሥት የሚደረግ ማንኛውም ከአራት ሳምንት የበለጠ ክልከላ ቢኖር ምርጫውን በተያዘለት ሕገ-መንግሥታዊ የጊዜ ሰሌዳ ማከናወን እንዳይቻል ያደርገዋል፤ ስለዚህም ወረርሽኙን መቆጣጠር በሚቻል ጊዜ ቦርዱ ዕቅዶቹ ላይ የተለያዩ ማሻሻያ ሊደርግ ይገባል የሚል ነው።

    በመሆኑም ቦርዱ እነዚህን የቢሆን ሁኔታ ግምቶች መርምሮ እንዲሁም ከባለድርሻ አካላት ጋር ካደረጋቸው ምክከሮች ያገኘውን ግብአት ታሳቢ በማድረግ የሚከተለውን ወስኗል።

    1. በተፈጠረው ሁኔታ የተነሳ ቦርዱ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ምርጫውን ማካሄድ የማይቻለው መሆኑን በመረዳት ያወጣውን የጊዜ ሰሌዳ በመሰረዝ በሰሌዳው መሠረት መከናወን ያለባቸው ተግባራት ለጊዜው እንዲቆሙ ወስኗል፤
    2. ቦርዱ የወረርሽኙ ሥጋት ተወግዶ ሁኔታዎች ሲመቻቹ እንደገና ግምገማ በማድረግ አዲስ የምርጫ ኦፕሬሽን ዕቅድና ሰሌዳ በማውጣት እንቅስቀሴውን የሚያስጀምር ይሆናል፤
    3. ቦርዱ ባደረጋቸው ምክክሮችና የዳሰሳ ጥናት ላይ በግልጽ የተለዩ፣ በኮቪድ-19 የማይስተጓጎሉ፣ የቦርዱን የምርጫ አፈጻጸም ዝግጁነት የሚጨምሩ፣ ሁኔታው ተቀይሮ ተቋሙ ወደ መደበኛ ተግባሩ ሲመለስ በተገቢው ሁኔታ ምርጫን ለማስፈጸም የሚያሥችል ሁኔታን የሚፈጥሩ ተግባራትን እያከናወነ መቆየት እንዳለበት ወስኗል።
    4. በሕገ መንግሥቱ በተቀመጠው መሠረት በሥራ ላይ የሚገኘው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የስልጣን ጊዜው ከሚያበቃበት አንድ ወር አስቀድሞ ቦርዱ አጠቃላይ ምርጫውን ማድረግ የማይችል መሆኑን ምክር ቤቱ ተገንዝቦ፣ ከዚህ አንጻር የሚሰጠው ውሳኔ ቢኖር ለመነሻነት ያገለግለው ዘንድ ይህ ውሳኔ እንዲሁም ቦርዱ ያደረገው የዳሰሳ ጥናት ሰነድ ለሕዝብ ተወካዮች እንዲተላለፍለት ወስኗል።

    የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
    መጋቢት 22 ቀን 2012 ዓ.ም

    የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

    Semonegna
    Keymaster

    በ2013 ዓ.ም የጉራጊኛ ቋንቋ ከቅድመ መደበኛ የትምህርት ደረጃ ጀምሮ እንዲሰጥ እየተሠራ ነው

    ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በ2013 ዓ.ም. የጉራጊኛ ቋንቋ ከቅድመ መደበኛ የትምህርት ደረጃ ጀምሮ እንዲሰጥ እየሠራ መሆኑን ገለጸ። ዩኒቨርሲቲው ከ135 በላይ ለመድኃኒት የሚሆኑ እጽዋት ላይ ምርምር እያደረገ መሆኑን ጨምሮ ገልጿል።

    ወልቂጤ (ኢዜአ) – ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የአገር በቀል እውቀት ዳይሬክተር አቶ ካሳሁን ጥሩውሃ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እንደተናገሩት፥ እስካሁን የጉራጊኛ ቋንቋ በትምህርት ቤት፣ በመሥሪያ ቤት እንዲሁም በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ አልተካተተም። በቋንቋው ውስጥ የተለያየ የአነጋገር ዘዬ መኖር በትምህርት እንዳይሰጥ ካደረጉት ዋነኛው ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል።

    በዚህም አብዛኛው የማኅበረሰብ ክፍል ጉራጊኛ ቋንቋን እየረሳ በመምጣቱ ከዞኑ ባህልና ቱሪዝም እንዲሁም ትምህርት መምሪያ ጋር በመተባበር የፊደል ገበታ መቀረጹን ገልጸዋል። የተወሰኑ ፎነቲኮች በአማርኛ ፓወር ግዕዝ ላይ ባለመኖራቸው ዩኒቨርሲቲው “የተንቢ” የተሰኘ የኮምፒተር መተየቢያ አበልጽጓል።

    በጉራጊኛ ቋንቋ 13 የአነጋገር ዘዬ የሚገኝ ሲሆን በየትኛው መጀመር እንዳለበት ዩኒቨርሲቲው ለማኅበረሰቡ አማራጭ ሃሳቦችን ለማቅረብ ተዘጋጅቷል።

    ”የኮምፒተር መተየቢያና የፊደል ገበታን በማሰልጠን እንዲሁም ሌሎች ግብአቶች እንዲሟሉ በመጠቆም  የጉራጊኛ ቋንቋ በቀጣዩ የትምህርት ዘመን ከቅድመ መደበኛ ክፍል ጀምሮ እንዲሰጥ ለማስቻል እየተሠራ ነው” ብለዋል አቶ ካሳሁን።

    በሌላ በኩል ዩኒቨርሲቲው ከ135 ዓይነት በላይ ለመድኃኒትነት የሚውሉ ተክሎች ላይ ምርምር እያደረገ መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። ለዚህም የተፈጥሮ መድኃኒት ማምረት የሚያስችል የስልት ሰነድ (strategic document) እየተዘጋጀ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

    እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፥ መድኃኒቱን ማምረት የሚያስችሉ ቅድመ ሁኔታዎች እየተመቻቹ ነው። በዚህም ንጥረ ነገሮችን የመሥራትና የአሠራር ዘዴ ሙከራ እየተደረገ እንደሆነ ጠቁመዋል።

    ምርምር እየተደረገባቸው ያሉ እጽዋት ለደም ብዛት፣ ጋንግሪን፣ አስም፣ አጥንት ካንሰርና ለሌሎች በሽታዎች ፈውስ ያስገኛሉ የተባሉ ናቸው።

    ቀደም ሲል ከእጽዋት የባህላዊ መድኃኒቶች ልኬት እንደማይታወቅ ያነሱት አቶ ካሳሁን፥ የፋርማሲና የኬሚስትሪ ባለሙያዎች ከአካባቢው የባህል መድኃኒት አዋቂዎች ጋር በምርምሩ እንዲሳተፉ ተደርጓል።

    በሌላ በኩል የማኅበረሰቡ ለበርካታ ዓመታት ይተዳደርበት የነበረው ባህላዊ የሕግና አስተዳደር ዘዴ እየቀነሰ በመምጣቱ መልሶ እንዲያንሰራራ ለማስቻል ዩኒቨርሲቲው ምርምር እያደረገ ነው።

    ቋንቋና ሥነ-ጹህፍ፣ አገር በቀል መድኃኒት፣ አስተዳደርና ሕግ፣ ባህልና የማይዳሰሱ ቅርሶች በዩኒቨርሲቲው ትኩረት ተሰጥቷቸው ምርምርና ጥናት እየተካሄደባቸው ነው።

    ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በደቡብ ክልል የሚገኝ የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ሲሆን የተመሠረተው በ2004 ዓ.ም. ነው።

    ምንጭ፦ ኢዜአ / ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የጉራጊኛ ቋንቋ

    Semonegna
    Keymaster

    በዓመት 500 ሚሊዮን ሊትር የምግብ ዘይት የሚያመርተው ፋብሪካ ዘንድሮ ሥራ ይጀምራል

    ቡሬ (አዲስ ዘመን) – የአገር ውስጥ የምግብ ዘይት ፍጆታን ከ50 እስከ 60 በመቶ መሸፈን የሚያስችልና በቡሬ ከተማ እየተገነባ የሚገኘው የምግብ ዘይት ፋብሪካ ከሁለት እስከ አራት ወራት ውስጥ ተጠናቆ ወደ ምርት ይገባል ተባለ። የውጭ ምንዛሬ በማዳን የጎላ ፋይዳ እንደሚኖረውም አዲስ ዘመን ጋዜጣ ዘግቧል።

    በፌዴራልና በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ከፍተኛ አመራሮች የካቲት ወር አጋማሽ፣ 2012 ዓ.ም. የተጎበኘው በኢትዮጵያዊ ባለሃብት አቶ በላይነህ ክንዴ በመገንባት ላይ ያለው ፋብሪካው፤ የአገር ውስጥ የምግብ ዘይት ፍጆታን ከ50 እስከ 60 በመቶ ይሸፍናል ተብሏል።

    በአገር ውስጥ ያለውን የምግብ ዘይት አቅርቦት ችግርን ለመፍታት ወደ ዘርፉ መግባታቸውን የገለጹት አቶ በላይነህ ክንዴ፥ ከአንድ ፋብሪካ በስተቀር ቀሪዎቹ እንደተገጣጠሙም ተናግረዋል። በዓመት 500 ሚሊዮን ሊትር ዘይት የማምረት አቅም እንዳለውና አገር ውስጥ ያለውን የምግብ ዘይት አቅርቦት እንደሚፈታም ተናግረዋል።

    ድርጅቱ ላለፉት 13 ዓመታት ሰሊጥ ወደ ውጭ በመላክ ግንባር ቀደም እንደነበር በማስታወስ፥ በተደጋጋሚ በመንግሥትና በሕዝብ ይቀርብ የነበረው ጥያቄ እውን የሚያደርገው አቀነባብሮ የሚያቀርበው ፋብሪካ ዘንድሮ ወደ ምርት እንደሚገባ ነው ባለሀብቱ የተናገሩት። ማንኛውንም አይነት የቅባት እህሎችን እንደሚያጣራና በአሁኑ ወቅት ለአምስት መቶ ሰዎች የሥራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን ወደ ምርት ሲገባ ቁጥሩ እስከ ሦስት ሺህ ከፍ እንደሚልም አብራርተዋል። ፋብሪካው በግብአትነት 20 ሚሊዮን ኩንታል እህል እንደሚያስፈልገው በመጠቆም፥ ከጉትን እስከ ጎንደር ጫፍ ያሉ አርሶ አደሮችም ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉ በጋራ እንሠራለን ብለዋል።

    የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተካ ገብረየሱስ፥ አሁን ባለው ሁኔታ የሕዝቡን ፍላጎት ለማሟላት አቅም ያለው የምግብ ዘይት ፋብሪካ አለ ማለት ይከብዳል፤ አብዛኛው የምግብ ዘይት ፍላጎት ከውጭ በሚገቡ ምርቶች እየተሸፈነ እንደሚገኝም ተናግረዋል። በባለሀብቱ አቶ በላይነህ ክንዴ የሚገነባው 50 በመቶ ፍላጎትን ከሸፈነ ቀሪውንም ሌሎች ወደ ምርት የሚገቡ ፋብሪካዎች ይሸፍኑታል ብለዋል። ፋብሪካዎች ማሽን ስላስገቡ ይጠናቀቃል ማለት አይደለም ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፥ የመብራት ችግር እንዳያስተጓጉል ጎን ለጎን እየተሠራ መሆኑንና ፋብሪካው ወደ ምርት ሲገባ የውጭ ምንዛሬ በማዳን በኩል ፋይዳው የጎላ እንደሚሆንም ጠቁመዋል።

    በአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ የፕሮሞሽንና ሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ይሄነው አለም፥ ባህር ዳር ዙሪያና ቡሬ ከተማም እንደቅደም ተከተላቸው ሰፊ የኢንቨስትመንት ማዕከል መሆናቸውን ተናግረዋል። ባለሀብቱ ትልቅ የዘይት ፋብሪካ እንዲተክሉ ያነሳሳቸው አካባቢው ትርፍ አምራች መሆኑ ነውም ብለዋል።

    እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፥ ከሱዳን ጠረፍ እስከጃዊ አኩሪ አተር፣ ኑግ፣ ሰሊጥ፣ ሱፍ፣ ስንዴና በቆሎ በከፍተኛ ደረጃ ይመረታል፤ ፋብሪካው ምርቶቹን በግብአትነት በመጠቀም ዘይት በከፍተኛ ደረጃ በማምረት በዕቅዱ መሠረት የአገሪቱን ከ50 እስከ 60 በመቶ ፍላጎት እንደሚሸፍንም ተናግረዋል። ምሥራቅ ጎጃም፣ ምዕራብ ጎጃምና አዊ ደቡባዊ ጎንደር እስከ ሱዳን ጠረፍ ከፍተኛ ምርት በመኖሩ የፌዴራልና የክልሉ መንግሥት የግብርና ምርት አቀነባባሪዎች ትኩረታቸውን ወደ አካባቢዎቹ እንዲያርጉም ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል።

    በላይነህ ክንዴ ግሩፕ በተለያዩ ዘርፎች የተሰማራ ድርጅት ሲሆን፤ በገላን ከተማ የጀመረው የመኪና መገጣጠሚያ፣ ሆቴልና እርሻ ሥራ ተጠቃሽ ናቸው። በቡሬ ከተማ በግንባታ ላይ ያለው የዘይት ፋብሪካ በ2006 ዓ.ም የተጀመረና በ30 ሄክታር ላይ ያረፈ ነው። የጀሪካን፣ የማሸጊያ፣ የሳሙና፣ የማርጋሪንና የካርቶንን ጨምሮ ሰባት የተለያዩ ፋብሪካዎችን ይዟል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    በላይነህ ክንዴ የምግብ ዘይት ፋብሪካ

Viewing 15 results - 46 through 60 (of 120 total)