Search Results for 'ኢትዮጵያ'

Home Forums Search Search Results for 'ኢትዮጵያ'

Viewing 15 results - 211 through 225 (of 730 total)
  • Author
    Search Results
  • Semonegna
    Keymaster

    በአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ አፈጻጸም ወቅት የታዩ ክፍተቶች አፋጣኝ ማስተካከያ ሊደረግባቸው ይገባል!
    የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ)

    የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መንግሥት የኮሮና ቫይረስ ‹COVID-19› በኢትዮጵያ ሊያደርስ የሚችለውን ተፅዕኖ ለመቆጣጠርና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ በማሰብ ሚያዝያ 2 ቀን 2012 ዓ.ም የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ቁጥር 3/2012 ማወጁ ይታወሳል። የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ ከታወጀ ወዲህ በመላው ሀገሪቱ ወጥነት ባለው መልኩ እየተተገበረ ካለመሆኑም በላይ የቫይረሱን ስፋት እና የስርጭት መጠን መሠረት በማድረግ በየጊዜው በአስፈጻሚው አካል የሚወጡ መመሪያዎችም በጥናት ያልተደገፉ እና ለሕግ አስከባሪው ኃይል የተለጠጠ የማስፈጸም ሥልጣን የሚሰጡ ሆነው ታይተዋል። በዚህም ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ ከታወጀበት ጊዜ ጀምሮ ባሉት አስር ሳምንታት የታዩት የዐዋጁ አፈጻጸም ሂደቶችም ሆኑ የመመሪያ አወጣጥ ሂደቱ ማሻሻያ ሊደረግባቸው የሚገቡ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) በጽኑ ያምናል።

    ዓለም-አቀፉ የጤና ድርጅት እና የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጤና ሚኒስቴር የኮሮና ቫይረስን አስመልክተው በየጊዜው ይፋ ከሚያደርጓቸው መግለጫዎች ለመረዳት እንደሚቻለው ቫይረሱ ገና በቅጡ ተጠንቶ ያልታወቀ ተለዋዋጭ ባሕርይ ያለው መሆኑ ነው። ከዚህ የተነሣ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት እንዲያስችሉን የምንወስዳቸው እርምጃዎች በበቂ ጥናት ላይ የተመረኮዙ መሆን ይኖርባቸዋል። ቫይረሱ በኢትዮጵያ መገኘቱ ከታወቀበት ጊዜ አንሥቶ ፍ/ቤቶች በከፊል ዝግ ሆነው መቆየታቸው የዜጎች ፍትሕ የማግኘት መብት እንዲገደብ ከማድረጉ በላይ ጉዳያቸው በአፋጣኝ ታይቶ በነጻ መሰናበት እንዲሁም በዋስ መለቀቅ የሚችሉ ዜጎች ያለ አግባበብ በእሥር እንዲቆዩ ምክንያት ሆኗል። በዚሁ ምክንያት አንዳንድ ማረፊያ ቤቶች በመጨናነቃቸው ዜጎች ለቫይረሱ ይበልጥ ተጋላጭ ሆነዋል።

    የዐዋጁ አፈጻጸም ሲገመገም የዜጎችን በሕይወት የመኖር፣ ከማንኛውም ጥቃት ነጻ-የመሆን፣ ፍትሕ የማግኘት፣ እንዲሁም ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብቶች ላይ ያልተመጣጠነ ገደብ ያስቀመጠ በመሆኑ እነዚህ ጉዳዮች አስቸኳይ የማስተካከያ እርምጃዎችን እንዲሁም ዘላቂ መፍትሔዎችን የሚሹ መሆናቸውን ኢሰመጉ በጥብቅ ያምናል። ከዚህም በተጓዳኝ በቀጥታ በዐዋጁ ምክንያት ባይሆንም፤ የቫይረሱ መስፋፋት ባስከተላቸው ማኅበራዊ፣ ሥነ-ልቦናዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎች የተነሳ በጤና ባለሙያዎች፣ በሴቶች እና ሕጻናት፣ እንዲሁም በድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች ላይ ዓይነተ-ብዙ የመብት ጥሰቶች እየደረሱ በመሆኑ ትኩረት እና መፍትሔ የሚሹ መሆናቸውን ኢሰመጉ ያምናል። እንዲሁም በዐዋጁ አፈጻጸም ወቅት እና በአጠቃላይ ቫይረሱ ከተከሰተ ወዲህ ባሉ ጊዜያት ከታዩት ጉልህ የመብት ጥሰቶች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡-

    በትግራይ ክልል ናዕዴር ዓዴት ወረዳ ቀደም ብሎ በክልሉ ታውጆ የነበረውን አስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ለማስከበር በሚል አንድ የፖሊስ ባልደረባ በወሰደው የኃይል እርምጃ መጋቢት 19 ቀን 2012 ዓ.ም የአንድ ሰው ሕይወት ያለፈ ሲሆን፤ በተመሳሳይ ግንቦት 9 ቀን 2012 ዓ.ም መቐለ ከተማ ሰሜን ክፍለ ከተማ ልዩ ቦታው 05 ቀበሌ አካባቢ አንድ የፖሊስ ባልደረባ በወሰደው የኃይል እርምጃ የሰው ሕይወት ጠፍቷል፤ ተጨማሪ ሌሎች ሰዎች ደግሞ ቆስለው ሕክምና ላይ ናቸው። በአማራ ክልል በጎንደር ከተማ አንድ የባጃጅ ሹፌር በጸጥታ ኃይሎች በተፈጸመበት ጥቃት አንድ እጁ ላይ በጥይት ጉዳት ደርሶበታል።

    በተለያዩ አካባቢዎች “የአፍ መሸፈኛ ጭምብል አላደረጋችሁም” በሚል ምክንያት ፖሊስ ተመጣጣኝ ባልሆነ እርምጃ በዜጎች ላይ ከፍተኛ እንግልት እና ለቫይረሱ አጋላጭ በሆነ መንገድ የጅምላ እስር ፈጽሟል። “ዐዋጁን ተላልፈዋል” በሚል ምክንያት ንግድ ቤቶች የሚታሸጉበት እና በሰዓት ገደብ እንዲዘጉ የሚደረጉበት ሂደት አንድ ወጥ አለመሆኑ አድሎአዊ እና ሕገ-ወጥ ለሆነ አፈጻጸም አጋልጧል።

    ቫይረሱን ግንባር-ቀደም ሆነው እየተከላከሉ ላሉት የጤና ባለሙያዎች በቂ ራስን የመከላከያ ግብዓቶች እየቀረቡ ባለመሆኑ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ በሚጥል መልኩ እንዲሰሩ በመደረጋቸው ለቫይረሱም ተጋላጭ ሆነዋል። በጤና ሚንስቴር ይፋ በተደረጉ መረጃዎች መሠረት እስከአሁን ድረስ ወደ አንድ መቶ የሚጠጉ የጤና ባለሙያዎች እና የጤና ተቋም ሠራተኞች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል። “ንክኪ አላቸው” በሚል በየጊዜው ወደ ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ የሚደረጉ የጤና ባለሙያዎች ቁጥርም በየጊዜው እየጨመረ ነው።

    በአዲስ አበባ ቦሌ አየር ማረፊያ በኩል የሀገር ውስጥ በረራ ሊያደርጉ የነበሩ የተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና ተወካዮች “ዓለም-አቀፍ በረራ አድርጋችኋል” በሚል ወደ አስገዳጅ ለይቶ ማቆያ ለአስራ ስድስት ቀናት ያህል እንዲገቡ፣ ለተወሰኑ ቀናትም ቤተሰብ ያሉበትን እንዳያውቅ ተደርጓል። ሌሎች ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶችም የቫይረሱን መከላከያ ሥራዎች ሽፋን በማድረግ በአባላትና አመራሮቻቸው ላይ ልዩ ልዩ ተጽዕኖዎች እየደረሱባቸው ነው። ለአብነት፥ ወደ ደቡብ ክልል ቁጫ ወረዳ ሰላም በር ከተማ ለቤተሰባዊ ጉዳይ የሄዱትን አንድ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ አባል ወደ ከተማዋ ለሚገቡ ሌሎች ሰዎች ወጥነት ባለው መልኩ ተግባራዊ በማይሆን አሰራር ከግንቦት 9 – 11 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ ለሦስት ቀናት በለይቶ ማቆያ ውስጥ እንዲቆዩ ተደርጎ ተለቀዋል። ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ (ባልደራስ) ፓርቲ ግንቦት 27 ቀን 2012 ዓ.ም በአዲስ አበባ ኮልፌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 አካባቢ ለሚገኙ ዜጎች እርዳታ ለማድረግ ሲንቀሳቀስ ፖሊስ ጣልቃ በመግባት እንዲቆም ተደርጓል።

    የቫይረሱ ስርጭት ባስከተለው ተጽዕኖ የዜጎች የሥራ ዋስትና ጥያቄ ውስጥ ከመውደቁም በላይ፥ አንዳንድ አሰሪዎች ሠራተኞቻቸውን ከሕግ አግባብ ውጪ በሆነ መንገድ ከሥራ ገበታቸው እንዲሰናበቱ እና አስገዳጅ ፈቃድ ያለክፍያ እንዲወጡ ተደርጓል።

    የድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች ማኅበር ይፋ ባደረገው መረጃ በተለይም በጅቡቲ በኩል የሚገቡ አንዳንድ አሽከርካሪዎች ከሚደርስባቸው መገለል በተጨማሪ በአንዳንድ ከተሞች የማደሪያ እና የምግብ አገልግሎት እንዳያገኙ፣ መኪና እንዳያቆሙ ክልክላ ይደረግባቸዋል።

    መንግሥት ቀዳሚ ትኩረቱን በሽታውን በመከላከል እና ተያያዥ ሥራዎች በማድረጉ በሴቶች እና ሕጻናት ላይ የሚደርሱ የቤት ውስጥ ጥቃቶች፣ የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎች እና ያለ ዕድሜ ጋብቻን የመሳሰሉት ልማዳዊ ጎጂ ድርጊቶች እየተበራከቱ እና እየተስፋፉ ነው። የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶች እና ሕጻናት ቢሮ ብቻ ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት 101 ያህል ህጻናት የመደፈር ጥቃት ደርሶባቸዋል። በተመሳሳይ መልኩ በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎችም መሰል የመብት ጥሰቶች እንዳሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

    በመሆኑም፥ ዐዋጁን ለማስፈጸም የተቋቋመው የሚኒስትሮች ኮሚቴ እና በየደረጃው ያለው ግብረ-ኃይል ለእነዚህ የመብት ጥሰቶች እና የአፈጻጸም ችግሮች ተገቢውን ትኩረት በመስጠት አስቸኳይ መፍትሔ እንዲያገኙ በትኩረት እንዲሠራ ኢሰመጉ ያሳስባል። መንግሥት በዐዋጁ አፈጻጸም ምክንያት ሊጎዱ ለሚችሉ የጎዳና ተዳዳሪዎች፣ ዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎች፣ ለድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች፣ በተለያየ ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች አስፈላጊውን የምግብ፣ የንጽህና መጠበቂያ፣ የትራንስፖርት አገልግሎት እርዳታ እና ድጋፍ እንዲያደርግ ኢሰመጉ ጥሪውን ያቀርባል።

    ቫይረሱን ከፊት ሆነው እየተከላከሉ ላሉ የሀገራችን የጤና ባለሙያዎች ቫይረሱ አሁን ካለበትም ደረጃ የከፋ የሚሆንበትም ጊዜ ሳይጠበቅ አስፈላጊ የሆነውን ራስን የመከላከያ ግብዓት በበቂ ሁኔታ በአፋጣኝ እንዲያገኙ መንግስት እና የጤና ሚኒስቴር በትኩረት እንዲንቀሳቀሱ ኢሰመጉ ጥሪውን ያቀርባል። በተጨማሪም በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጦ በለይቶ ሕክምና ላይ የሚገኙ ዜጎች የምግብ አገልግሎት፣ የመኖሪያ እና የንፅህና መስጫ ስፍራ ጽዳት፣ የአፍ መሸፈኛ ጭምብሎችን ጨምሮ የሌሎች የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች አቅርቦትና የመሳሰሉ የአገልግሎት ችግሮች መኖራቸውን የሚያሳዩ መረጃዎች በመኖራቸው መንግሥት በትኩረት ችግሮቹን እንዲያስተካከል ኢሰመጉ ጥሪ ያቀርባል። በየጊዜው ዐዋጁን በመተላለፍ ተይዘው እንደ ትምህርት ቤት ባሉ መሠረተ ልማቶች ውስጥ የታሰሩ ዜጎች የሚቆዩበት ሥፍራ እንደ ምግብ፣ አልጋ፣ መጸዳጃና የመሳሰሉት መሠረታዊ አገልግሎቶች ለመስጠት በሚያስችል መልኩ መደራጀታቸውን እንዲያረጋግጥ ኢሰመጉ ያሳስባል።

    በዐዋጁ ድንጋጌ መሠረት የመንግስትም ሆነ የግል ትምህርት ተቋማት ተዘግተው ተማሪዎች እና መምህራን በአካል ተገናኝተው ትምህርት የሚሰጥበት ሂደት ተቋርጧል። ሆኖም ተማሪዎች ከቤታቸው ሆነው ትምህርት እንዲከታተሉ እየተደረገበት ያለው መንገድ ጥራቱን በጠበቀ፣ ተማሪዎች ትምህረቱን ለማስተላለፍ የሚረዱትን ነገሮች የማግኘት አቅማቸውን ታሳቢ ያደረገ እና የብሔራዊ ፈተና ተፈታኞችን ፍትሐዊ እድል ለመስጠት በሚያስችል መልኩ እንዲሰጡ መንግሥት እንዲያመቻች ኢሰመጉ ጥሪ ያቀርባል።

    በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተሰየመው የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ መርማሪ ቦርድም ሁኔታዎቹን በየጊዜው እየተከታተለ፣ በዐዋጁ ይዘት እና አፈጻጸም ላይ የሚሰጡ አስተያየቶችን በአግባቡ እንዲስተካከሉ ኃላፊነቱን እንዲወጣ እናሳስባለን። መንግሥት ቫይረሱን የመከላከል ሥራዎችን አስመልክቶ በየደረጃው የሚሠሩ ሥራዎች ለሕዝብ ይፋ እንዲሆኑ እና የሲቪል ማኅበረሰቡንም ሌላውን የሕብረተሰብ ክፍል ተሳትፎ በሚጠይቁ ጉዳዮች ላይ እንዲሳተፉ የሚያስችሉ ሁኔታዎችን እንዲያመቻች ኢሰመጉ ጥሪ ያቀርባል።

    ከዚህ በኋላ የሚወጡ መመሪያዎች የበሽታውን ባህርይ ታሳቢ ያደረጉ፣ በበቂ ጥናት እና መረጃ ላይ የተመሠረቱ፣ ለሕግ አስከባሪ ኃይሎች የሚሰጡት ሥልጣን ውስን እንዲሆን፣ ብሎም ክልከላ የተደረገባቸውን ነገሮች በግልጽ የሚያመላክቱ እንዲሆን ኢሰመጉ በጥብቅ ያሳስባል። ዐዋጁን በማስፈጸም ወቅት የፖሊስና ሌሎች የፀጥታ አካላት ሚና የጤና ባለሙያዎችን የማገዝ እንዲሆን ቅጣት እንኳን አስፈላጊ ቢሆን ሕይወትን የማዳን ዓላማ እንጂ የባሰ አደጋ ውስጥ በማይከት ሁኔታ መሆን ስለሚገባው፤ ተጠያቂነትን በሚያሰፍን መልኩ በጥብቅ ዲሲፕሊን እንዲመራ የሚያሳስብ ድንጋጌ በያዘ መልኩ ማሻሻያ እንዲደረግባቸው ኢሰመጉ ያሳስባል።

    በተጨማሪም በአዲስ አበባ ከተማ የሚደረጉ የመሬት ወረራን ታሳቢ አድርገው የሚሠሩ የሕግ ማስከበርና የቤት ማፍረስ እርምጃዎች ያለንበት ወቅት ክረምት እንደመሆኑ እና ዜጎችን ለበሽታውም ስርጭት የበለጠ ተጋላጭ እንዲሆኑ የሚያደርግ በመሆኑ በጥንቃቄ እና ወጥነት ባለው እንዲታዩ ኢሰመጉ ጥሪውን ያቀርባል።

    ሁሉም መብቶች ለሁሉም!!

    ምንጭ፦ ኢሰመጉ

    የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ)
    የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) በኢትዮጵያ የሽግግር ወቅት ቻርተር አንቀጽ 1(ሀ) እና በኢትዮጵያ ፍትሐ-ብሔር ሕግ ቁጥር ከ404-482 በተጻፉት ድንጋጌዎች መሠረት መስከረም 29 ቀን 1984 ዓ.ም.  በአባላት የተመሠረተ የመጀመሪያው መንግሥታዊ ያልሆነ ተሟጋች ተቋም ነው።

    የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ)

    Anonymous
    Inactive

    ኦርቶዶክሳዊ እንደ ወንጀለኛ የሚቆጠርበት ክልል
    (ጴጥሮሳውያን የቤተ ክርስቲያን ክብርና መብት አስጠባቂ ኅብረት)

    የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በኢትዮጵያ ታሪክ፣ ሀገራችን ኢትዮጵያም በኦርቶዶክስ ታሪክ ውስጥ ያላቸው ውሕደት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ እንደማለት ነው። የኢትዮጵያ ታሪክ እና ቅርስ ሙሉ ለሙሉ ማለት በሚቻልበት ሁኔታ የቤተ ክርስቲያኗ በመሆኑ ቤተ ክርስቲያኗ ሀገር መሆኗን እኛ ብቻ ሳንሆን ምዕራባውያን ጸሐፊዎችም የመሰከሩት እውነታ ነው። ኢትዮጵያ እና ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በፍጹም አንድነት ሲገለጡ ኖረዋል።

    ካለፉት 40 ዓመታት በኋላ ግን ለዘመናት የኖረው እውነት ተገፍቶና ተሽሮ ቤተ ክርስቲያኗን የማይወክል የሐሰት ትርክት ሲነገር ኖሯል። ከ1983 ዓ.ም. በኋላ ደግሞ ቤተ ክርስቲያኗን በጠላትነት በመፈረጅ “ቀና እንዳትል አከርካሪዋን ሰብረነዋል” ብለው በአደባባይ እስከ መናገር ደረሱ። አብያተ ክርስቲያናትን ለመቃጠል፣ ክርስቲያኖችን ለሞት፣ ለስደት፣ ለመፈናቀል እንዲሁም ለንብረት ውድመት ተዳረጉ። በሁለተኛው እና በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ክርስቲያኖች ያለፉበትን ሰማዕትነት እና ትላንት በሌላው ዓለም ስንሰማውና በቴሌቪዥን መስኮት ብቻ ስናየው የነበረው አሰቃቂ ግድያ ኦርቶዶክስ በመሆናቸው ብቻ በሀገራችን ተፈጽሞ የሞትን ጽዋ ተጎነጩ ።

    በክርስቶስ ደም የተመሠረተችው ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሐዋርያት ስበከት ወደ ዓለም ሁሉ መድረሷ እና በሰማዕታት ደም መጽናቷ ይታወቃል። ሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. ማታ የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን መገደል ምክንያት በማድረግ አስቀድመው አቅደውት የነበረውን ኦርቶዶክሳውያንን የማጥፋት እኩይ ድርጊት በአሰቃቂ ሁኔታ ፈጽመውታል፤ ቤት ንብረታቸውን አቃጥለዋል። ቅዱስ ሲኖዶስ የተረፉትን ክርስቲያኖች ለማጽናናት እና የደረሰውን ጉዳት ለማየት በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የተመራ የሀገር ሽመግሌዎች እና የማኅበራት የተካተቱበት በሦስት አቅጣጫ ጉዞ አድርጓል። ልዑኩ በሦስት ተከፍሎ ጉዞ ካደረገባቸው መካከል ይህ ዘገባ በምዕራብ አርሲ እና በምሥራቅ ሸዋ የተደረገውን የሚያስገነዝብ ነው። የማጽናናት እና የተበተኑን ለመሰብሰብ ታልሞ በተካሔደው ሐዋርያዊ ጉዞ ጴጥሮሳውያን የቤተ ክርስቲያን ክብርና መብት አስጠባቂ ኅብረት የደረሰውን ጉዳት እንደሚከተለው እናቀርባለን። ከሐምሌ 24-26 በተደረገው ሐዋርያዊ ጉዞ የተመለከትናቸው ዝዋይን፣ አዳሚ ቱሉን፣ አርሲ ነገሌን ፣ ኩየራን፣ ፍልቻን፣ ሻሸመኔን፣ አዳባን ፣ ሄረሮን፣ አሳሳን፣ ሽሬን፣ ቆሬን እና ኮፈሌን ነው።

    ዝዋይ
    በዝዋይ ከተማ የአንድ ቤተሰብ አባል የሆኑ አምስት ኦርቶዶክሳውያን በአሰቃቂ ሁኔታ ተቆራርጠው በመገደል ሰማዕትነትን ተቀብለዋል። ገዳዮቹ ጭካኔያቸውን የሰማዕታቱን አስከሬን በመሬታችን አይቀበርም በማለት አንገላተዋል። የኦርቶዶክሳውያን የንግድ ቦታቸው እና የመኖሪያ ቤታቸው ሙሉ በሙሉ በእሳት ጋይቷል። በሁሉም ከተሞች እና ወረዳዎች የክርስቲያኖች የንግድ ቦታቸው እና የመኖሪያ ቤቶቻቸው ሙሉ ለሙሉ የወደሙ ሲሆን፥ ጥቃቱ የተፈጸመባቸው ክርስቲያኖቹ “ላዩ ሣር ውስጡ ባህር” በሚባልለት ክረምት በየአጥቢያ ቤተ ክርስቲያኑ ተጠልለው በብርድ ይሰቃያሉ።

    ፍልቻ
    በፍልቻ ቅድስተ ማርያም ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ካህን በዱላ ተደብድበው፣ ቤታቸው ሙሉ ለሙሉ መቃጠሉን ለማየት ችለናል። በዚሁ ደብር አገልጋይ የሆኑትን ካህን እና ከዘጠና ዓመት በላይ የሆናቸውን የዕድሜ ባለጸጋ ገፍትረው ጥለው ‘እስከ ዛሬ አንተ አጥምቀሃል፤ ዛሬ እኛ እናጥምቅህ’ በማለት በባልዲ ውሃን እየደፉ እንዳሰቃዩዋቸው ነግረውናል።

    ሻሸመኔ
    በሻሸመኔ የሚገኘው የቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴ አባላት ሆቴሎቻቸው እና ትምህርት ቤታቸው በእሳት ጋይቷል። ወ/ሮ ሜሮን የተባለች የ፱ ወር ነፍሰ-ጡር ልብሷን በመቅደድ እና ቢላን ሆዷ ላይ በማድረግ ክርስቲያን እንደማይወለድ ስላስፈራሯት የተፈጸመባት ድርጊት ጭንቀት እና ቅዠት ዳረጓት ሕይወቷ ዐልፏል።

    በጠቅላላው በሻሸመኔ የተፈጸመውን ውድመት መልሶ ለማልማት ከፍተኛ ገንዘብን እና ብዙ ጊዜ ይወስዳል። ጥፋት ፈጻሚዎች አሁን ድረስ የማስፈራራት እና ክርስቲያኖችን የማሳቀቅ ተግባር እየፈጸሙ መሆኑን ተጎጂዎች ተናግረዋል። የሻሸመኔ ውድመትና ጥቃት በመንግሥት መዋቅር ውስጥ በተሰገሰጉ ባለሥልጣናት እና በፓሊስ ቸልተኝነት የተፈጠረ በመሆኑ ዘወትር በታሪክ ሲታወስ ይኖራል።

    አዳባ
    የክርስቲያኖች ቤት ተቃጥሏል፤ አንድ ወጣት ክርስቲያንም በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድሏል። ወጣቱ ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ታርዶ የተሰዋ ሲሆን፥ ቤተሰብም ‘አስከሬኑን አታነሱም’ ተብለው እስከ ረፋዱ አምስት ሰዓት ዝናብ እና ፀሐይ ተፈራርቆበታል። በተጨማሪም የወጣቱን ደም ውሾች ሲልሱት ቤተሰብ በመመልከቱ ለአእምሮ መረበሽ ተዳርገዋል። በመጨረሻም ለአራት በመሆን የሰማዕቱን አስከሬን አንሥተው ለመቅበር ችለዋል። ንብረቶቻቸው እና ቤቶቻቸው የተቃጠለባቸው ክርስቲያኖች በቤተ ክርስቲያን ተጠልለዋል። የተጎዱትን ምእመናንን የሚመግቡት አስተባባሪዎች ታስረው እንደ ነበር ለማወቅ ተችሏል።

    አሳሳ
    በአሳሳ እና ሄረሮም የክርስቲያኖች ቤት እና ንብረት ሙሉ ለሙሉ የወደመ ሲሆን፥ በአሳሳ አራት ሰዎች፣ በሄረሮ አንድ ሰው በአሰቃቂ ሁኔታ ተጨፍጭፈውና ታርደው ተገድለዋል። በሽሬ፣ በቆሬ እና በኮፈሌ የሚገኙ ክርስቲያኖችም የተጎዱ ሲሆን፥ ለዘመናት ያፈሩት ቤት ንብረት ሙሉ ለሙሉ ወድሟል። ኦርቶዶክሳውያን በሙሉ በየአብያተ ክርስቲያኑ በመቃብር ቤትና በደጀ ሰላም ለመጠለል ተግድደዋል። ለዓመታት የቀጠለው ኦርቶዶክሳውያንን የማሳደድ እና የማጥፋት ድርጊት እልባት ባለማግኘቱ፥ የመንግሥት የጸጥታ አካላት የክርስቲያኖችን ደኅነነት ማስጠበቅ ባለመቻላቸው ዛሬም ድረስ ጭንቀት ፈጥሮባቸዋል። ዛሬም የማስፈራርያና የውጡልን ዛቻው እነደቀጠለ መሆኑን ተናግረዋል።

    መንግሥት መቆጣጠር እና የኦርቶዶክሳውያንን ደኅንነት ማስጠበቅ ለምን ተሳነው?

    በተለይ በኦሮሚያ ክልል የሚፈጸሙ ጥቃቶች ማቆም እና ኦርቶዶክሳውያንን መታደግ ያልተቻለበት ምክንያት ጥቃቱ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ባሉ ኃላፊዎች ይመራ እና ከለላ ይደረግለት ስለነበር ነው። የሚፈጸምን ወንጀል ማቆም የተሳነው የጸጥታ አካል ‘ትዕዛዝ አልተሰጠኝም’ በማለት ኦርቶዶክሳውያን ሲጨፈጨፉ እና ሀብት ንብረታቸው ሲወድም ይመለከት ነበር።

    መፍትሔ

    መንግሥት ኃላፊነቱን በመወጣት ሕግ ማስከበር ይኖርበታል። የሰዎችን የመኖር ተፈጥሯዊም ሕገ መንግሥታዊ መብት ማስጠበቅ አለበት። ወንበዴዎችን ተከታትሎ በመያዝ የጀመረውን ሥርዓት የማስጠበቅና ሕግ የማስከበር ተግባሩን አጠናክሮ መቀጠል፣ የኦርቶዶክሳውያንን ስጋት ማቃለል ኖርበታል፤ ለተፈናቀሉ እና ሀብት ንብረት ለወደመባቸው ወገኖች ተገቢው ካሳ በመስጠት መልሶ ማቋቋም ይኖርበታል፤ በፍጥነት በመሥራት የእኩይ ተግባር ተቃዋሚነቱን ማሳየት ይገባዋል። ይህ ካልተደረገ ኦርቶዶክሳዊ መሆኑ እንደ ወንጀለኛ እየተቆጠረ ሲሳደድ ይኖራል።

    ኦርቶዶክሳዊ ኅብረት እንዲጠናከር እና እራስን የመጠበቅ የመከላከል ሥራ ተግባር እንዲፈጽም ማንቃት ያስፈልጋል። በየአካባቢው የሚኖረው ክርስቲያን ቅንጅት የመፍጠር እና የመሳተፍ ግዴታ ይኖርበታል።

    በመጨረሻም፡-

    የተፈጸመው ኦርቶዶክሳውያንን የማጥፋት ተግባር መሆኑን ለማረጋገጥ ችለናል። ተመሳሳይ ጥቃት እንዳይፈጸምብን መንቃት ይኖርብናል። የተጠናከረ ጥበቃ በማድረግ ወገኖቻችንን መታደግ ግድ ይለናል። ወደ ፊት ለሚፈጸመው ጥቃት መንግሥት ኃለፊነቱን እንዲወስድ ማድረግ ይገባል።

    ይቆየን…

    መጋቤ ሥርዓት ዮሴፍ ዓባይ
    ጴጥሮሳውያን የቤተ ክርስቲያን ክብርና መብት አስጠባቂ ኅብረት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ

    ጴጥሮሳውያን የቤተክርስቲያን መብትና ክብር አስጠባቂ ኅብረት

     

    Semonegna
    Keymaster

    የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን በ2012 በጀት ዓመት 715 ኪ.ሜ. የመንገድ ግንባታና ጥገና ሥራዎችን ማከናወኑን አስታወቀ

    አዲስ አበባ (አዲስ ዘመን) – በ2012 ዓ.ም. በጀት ዓመት 715 ኪ.ሜ. የመንገድ ግንባታና ጥገና ሥራዎችን ማከናወኑን፣ 21 የመንገድ ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቁንና አዳዲስና ግዙፍ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶችን ማስጀመሩን የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን አስታወቀ።

    ባለስልጣኑ ለአዲስ አድማስ ዕለታዊ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፥ በበጀት ዓመቱ 706 ኪ.ሜ. የመንገድ ግንባታና ጥገና ሥራዎችን ለማከናወን አቅዶ 715 ኪ.ሜ. በማከናወን ከዕቅድ በላይ አፈፃፀም አስመዝግቧል። በዚሁ በጀት ዓመት ከተሠራው አጠቃላይ የመንገድ ሥራ ውስጥ 167 ኪ.ሜ. አዳዲስ የአስፓልት መንገድ ግንባታ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ 544 ኪ.ሜ. ልዩ ልዩ የመንገድ ጥገና ሥራዎች ናቸው።

    ባለስልጣኑ በግንባታ ላይ ከነበሩ የመንገድ ፕሮጀክቶች መካከል 21 የሚሆኑትን በማጠናቀቅ አስመርቆ ለትራፊክ ክፍት ያደረገበት በጀት ዓመትም መሆኑን ጠቅሶ፥ በሁለት ዙር በይፋ የተመረቁት የመንገድ ግንባታዎች በድምሩ ከ33 ኪ.ሜ. በላይ ርዝመት እና የእግረኛ መንገድን ጨምሮ ከ10 እስከ 30 ሜትር የጎን ስፋት ያላቸውና ለግንባታቸውም ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የሆነባቸው መሆኑን አመልክቷል።

    በ2012 ዓ.ም. በጀት ዓመት በዓይነታቸው ለሀገሪቱም ሆነ ለመዲናዋ አዲስና ግዙፍ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶችን ማስጀመሩንም የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን አስታውሶ፥ ከእነዚህም መካከል የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎትን ለማስፋፋት የተጀመረው የዊንጌት–ጀሞ ሁለት የፈጣን አውቶቡስ መንገድ እና የፑሽኪን አደባባይ–ጎተራ መንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች እንደሚገኙበት ገልጿል።

    በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚደረግባቸው እና ከ90 ኪ.ሜ. በላይ ርዝመት ያላቸው 22 የመንገድ ፕሮጀክቶች መጀመራቸውንም ባለስልጣኑ ጠቅሷል። በ2012 ዓ.ም. በጀት ዓመት የተጀመሩት እነዚህ ታላላቅ የመንገድ ፕሮጀክቶች በሁለት ዓመት ውስጥ ተጠናቀው አገልግሎት እንዲሰጡ እየተሠራ እንደሚገኝም ባለስልጣኑ ጠቁሟል።

    በበጀት ዓመቱ በመንገድ መሠረተ ልማት ሀብቶች ላይ በርካታ ጉዳቶች መድረሳቸውንም አያይዞ የጠቀሰው ባለስልጣኑ፥ በ12 ወራት ውስጥ በተሽከርካሪ ግጭት ብቻ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ጉዳት በመንገድ መሠረተ ልማት ሀብቶች ላይ መድረሱንና ይህም በመንገድ መሠረተ ልማት ሀብቶች ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን እንደሚያሳይ አመልክቷል።

    በተሽከርካሪ ግጭት በብዛት ጉዳት ከደረሰባቸው የመንገድ ሀብቶች መካከል የመንገድ ዳር መብራት ምሰሶዎች፣ የትራፊክ ምልክቶች፣ የአቅጣጫና ርቀት አመላካች ሰሌዳዎች፣ የእግረኛ መከላከያ አጥሮች፣ የመንገድ ማካፈያ ግንቦች፣ ውሃ መውረጃ ቱቦዎችና ክዳኖች ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውን የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን ዘርዝሯል።

    የወሰን ማስከበር ችግር፣ የተቋራጮች አቅም ውስንነት፣ የገልባጭ መኪና እና ግብዓት እጥረትና የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በመንገድ ግንባታና ጥገና ሥራ ወቅት የገጠሙ ዋነኛ ፈተናዎች እንደነበሩም ባለስልጣኑ አስታውሶ፥ ችግሮቹን በመፍታት በአፈፃፀም ላይ ሊያሳድሩ የነበረውን ተፅዕኖ መቀነስ መቻሉን አስታወቋል። በበጀት ዓመቱ ለመንገድ ፕሮጀክቶች እና ለመደበኛ ሥራዎች አስከአሁን ከስድስት ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጉንም ባለስልጣኑ ጠቅሷል።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት

    የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን

    Anonymous
    Inactive

    ወላይታ ዞን ውስጥ የጸጥታ ኃይሎች በተቃውሞ ሰልፈኞች ላይ ተመጣጣኝ ያልሆነ ኃይል ከመጠቀም ሊቆጠቡ ይገባል!
    የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)

    አዲስ አበባ (ኢሰመኮ) – ወላይታ ዞን ውስጥ በአንዳንድ ከተሞች ነሐሴ 4 ቀን 2012 ዓ.ም. በተደረጉት ተቃውሞዎች የፀጥታ ኃይሎች በተቃውሞ ሰልፈኞች ላይ የወሰዱት እርምጃ ተመጣጣኝነት አጠያያቂ መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ።

    የተለያዩ ምንጮች እንደጠቆሙት የተቃውሞ ሰልፉ የተቀሰቀሰው ሰኞ ዕለት በፌዴሬሽኑ ውስጥ አዲስ የክልል መንግሥት መመሥረትን በተናጠል ለማወጅ በፈለጉ በርካታ ከፍተኛ የዞኑ ባለስልጣናት እስርን ተከትሎ ነው። የመንግሥት ባለስልጣናት እንደሚሉት ከሆነ ግን ታሳሪዎቹ በአካባቢው አለመረጋጋት ለመፍጠር ሲያሴሩ ተይዘዋል ብለዋል።

    የኮሚሽኑ የመረጃ ምንጮች እንዳስረዱት የባለስልጣናቱን እስር ተከትሎ የተቃውሞ ሰልፈኞች በዞኑ ዙሪያ በሚገኙ በርካታ ከተሞች ወደ ጎዳናዎች የወጡ ሲሆን፥ በዞኑ ዋና ከተማ በሶዶ አንድ ሰው እንዲሁም በቦዲቲ ከተማ አምስት ሰዎች መሞታቸው ታውቋል ።

    በሰኞው እስር ወቅት በጠቅላላው 178 ሰዎች የተያዙ ሲሆን፥ ከእነዚህም ውስጥ 28ቱ የዞኑ ከፍተኛ ባለስልጣናት መሆናቸው እና በወላይታ ሶዶ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኮሌጅ ውስጥ በቁጥጥር ስር የሚገኙ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

    የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ቃል አቀባይ አቶ አሮን ማሾ እንደገለጹት፥ “የፀጥታ ኃይሎች ሰላማዊ ሰልፎችን በሚቆጣጠሩበት ወቅት የሞት አደጋን የሚያስከትል የኃይል እርምጃ ከመውሰድ ሊቆጠቡ ይገባል፤ እንደነዚህ ያሉ እርምጃዎች ቀድሞውኑን የነበረ ውጥረትን ያባብሱ እንደሆን እንጂ መፍትሔ አይሆኑም” ብለዋል።

    አቶ አሮን አያይዘውም በግጭቱ ወቅት የተከሰተው የ6 ሰልፈኞች አሟሟትን እና የጸጥታ ኃይሎች የኃይል አጠቃቀምን አስመልክቶ ፈጣን ምርመራ የሚያስፈልግ መሆኑን አስረድተዋል። እንዲሁም የታሳሪዎችን መብቶች ማክበርና በአፋጣኝ ወደ ፍርድ ቤት መቅረብ ማረጋገጥ ያስፈልጋል ብለዋል።

    ለስረ-ችግሩ ዘላቂ መፍትሔ ከመፈለግ አንጻርም የፌዴራልና የክልሉ መንግሥታት በክልሉ ውስጥ ለተነሱት የክልልነት ጥያቄዎች ወቅታዊና ሰላማዊ መፍትሔ በሥራ ላይ እንዲውል ከፍተኛ ጥረትና ትኩረት ሊያደርጉ ይገባል።

    ወላይታ ዞን ውስጥ በተቀሰቀሰው ግጭት የተከሰተው ምንድን ነው?

    ባለፈው እሁድ (ነሐሴ 3 ቀን 2012 ዓ.ም.) ከወላይታ ዞን የክልልነት ጥያቄ መልስ አልተሰጠንም በሚል በተነሳ የተቃውሞ ሰልፍ፥ በነጋታው (ነሐሴ 4 ቀን) በተቃዋሚዎችና በጸጥታ ኃይሎች መካከል በተነሳ ግጭት ቢያንስ የአስር ሰዎች ሕይወት ማለፉን ሮይተርስ ዘግቧል።

    ሮይተርስ የዜና ወኪል የጠቀሳቸው የቦዲቲ ከተማ የጤና ቢሮ ከፍተኛ ባለሥልጣን ተመስገን ሕሊና ነሐሴ 4 ቀን በቦዲቲ ከተማ ቢያንስ ስድስት ሰዎች የጸጥታ ኃይሎች በከፈቱት ተኩስ መገደላቸውን ተናግረዋል። ለሌሎችም (ለተጎዱ ሰዎች) የመጀመሪያ ደረጃ የሕክምና እርዳታ መስጠታቸውን የተናገሩት አቶ ተመስገን፥ የጥቃቱ ሰለባዎች ጭንቅላታቸው፣ ሆዳቸውንና ደረታቸው ላይ መመታታቸውን ገልጸዋል። ከሞቱት መካከል የ14 ዓመት ታዳጊ ወጣት እንደሚገኝበትና የቆሰሉትም በቁጥር እንደሆኑ አክለው ተናግረዋል።

    ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል የጤና መኮንን ደግሞ፥ በሶዶ ከተማ አራት ሰዎች በጸጥታ ኃይሎች ተተኩሶባቸው የተገደሉ ሰዎች ማየታቸውን ለሮይተርስ ተናግረዋል።

    ከዚሁ ዜና ጋር በተያያዘ፥ የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አንዱዓለም ታደሰ በተቀሰቀሰው ተቃውሞ 21 ሰዎች መገደላቸውን እና ከ105 በላይ መቁሰላቸውን እንዳረጋገጡ ለዶይቼ ቬለ የአማረኛ ዝግጅት ክፍል ገልጸዋል።

    ወላይታ ዞን

    Semonegna
    Keymaster

    ኢትዮ ሊዝ ከሰባት ሚሊዮን ዶላር በላይ ዋጋ ያላቸው የእርሻ ሜካናይዜሽን መሣሪያዎች ለገበሬዎች አስረከበ

    አዲስ አበባ – በኢትዮጵያ በሊዝ ፋይናንስ ዘርፍ በመሰማራት የመጀመርያው የውጭ ኩባንያ የሆነው ኢትዮ ሊዝ የተሰኘው የአሜሪካ ኩባንያ 16 ኮምባይነሮችን ለአርሶ አደሮች እና ለማኅበራት አስረከበ። የግብርና ሜካናይዜሽን መሣሪያዎቹን ወደ አገር ውስጥ ያስገባው የኢትዮጵያ መንግሥት በግብረናው ዘርፍ ለማዘመን የያዘውን ስትራቴጂ ለመደገፍ ከግብርና ሚኒስቴር እና ከኢትዮጵያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጄንሲ ጋር ያደረውን ሰምምንት ተከትሎ ሲሆን፥ ስምምነቱም እነዚህን ውድ የሆኑ የግብርና ማቀነባበሪያ መሣሪያዎችን መግዛት የማይችሉትን አርሶ አደር ገበሬዎችን በአጭር ጊዜ ባለቤት የሚያደርግ ይሆናል።

    በዚህኛው ዙር የተካሄደው ርክክብ እስካሁን ድረስ ያስረከባችውን የግብርና መሣሪያዎች ቁጥር ወደ አንድ መቶ ያደረሰ ሲሆን፥ አጠቃላይ ወጪያቸው ከ7 ሚሊዮን ዶላር በላይ ነው። ከእነዚህም በተጨማሪ ኩባንያው በመጪው መስከረም እና በጥቅምት ወራት (2013 ዓ.ም.) ከ10 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጡ ተጨማሪ መሣሪያዎችን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት የሚያስፈልጉትን ሥራዎች እያከናወነ ይገኛል።

    የኢትዮ ሊዝ ዋና ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ግሩም ፀጋዬ በርክክቡ ውቅት እንደተናግሩት፥ “በተከታታይ ወደ ሀገር ውስጥ እያስገባናቸው ያሉት የግብርና መሣሪያዎች ኩባንያችን የሀገሪቱን የግብርና ዘርፍ የማዘመን ዕቅድ ለማሳካት የበኩሉን እየሠራ እንደሆነ የሚያሳይ ሲሆን፥ በዚህም እንቅፋት የሆነውን የውጭ ምንዛሪ እጦት መፍታት ችለናል” በማለት አስረድተዋል።

    አቶ ግሩም አክለውም፥ “ዘላቂነት ያለው ግብርናን ማዘመን ሥራ  የአርሶ አደሩን አቅም በመገንባት ረገድ ቁልፍ ሚና ሊጫወትና ምርታማነትን እና ገቢን ሊያሻሽል እንዲሁም የምግብ ዋስትናን እና አኗኗር ለማሻሻል ይረዳል” ብለዋል። የኢትዮ ሊዝ አርሶ አደሮች ከመደገፍ በተጨማሪ ለኦፕሬተሮች፣ ለረዳቶች ኦፕሬተሮች እና ለተለያዩ ባለሙያዎች፣ የሥራ ዕድልን የሚፈጥር እንደሆነ በሻሽመኔ ከተማ በተደረገው ርክክብ ላይ ተነግሯል።

    አትዮ ሊዝ አፍሪካን አሴት ፋይናንስ ካምፓኒ (African Asset Finance Company/AAFC) በተሰኘ የአሜሪካ ኩባንያ በ400 ሚሊዮን ብር ካፒታል የተመሠረተ ኩባንያ ነው። ኩባንያው ለእርሻ፣ ለሕክምናና አምራች ኢንዱስትሪ የሚውሉ ዘመናዊ መሣሪያዎች በኪራይ ለማቅረብ የሚያስችለውን የሥራ ፈቃድ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሐምሌ ወር 2011 ዓ.ም. አግኝቷል።

    ኢትዮ ሊዝ የካፒታል እቃዎችን እንደአስፈላጊነቱ በመለየት እና በመግዛት፣ አስፈላጊ ጥገናዎችን እና አግባብነት ባለው ሁኔታ አገልግሎት ላይ መዋላቸውን የመቆጣጠር ኃላፊነት ይኖረዋል። በተጨማሪም ተከራዩ ወይንም አገልግሎቱን ያገኘው አካል መሣሪያዎችን መግዛት የሚችልበትን መንገድ ያመቻቻል። ኢትዮ ሊዝ ወደሥራ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ፥ ለግብርና፣ ለጤና፣ ለኃይል አቅርቦት (energy)፣ ለምግብ ማቀነባበር (food processing) አገልግሎት ሰጪዎች የካፒታል እቃዎችን አቅርቧል። ድርጅቱ እስካሁን ከ60 በላይ ከሚሆኑ ደንበኞች ጋር የካፒታል እቃዎች አቅርቦት ስምምነት አድርጓል።

    ስለ ኢትዮ ሊዝ
    ኢትዮ ሊዝ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የግል የሊዝ ፋይናንስ አቅራቢ ኩባንያ ሲሆን፥ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፈቃድ አግኝቶ እ.አ.አ በ2017 የአፍሪካ አሴት ፋይናንስ ኩባንያ አካል በመሆን ሥራው ጀምሯል። ኩባንያው በአፍሪካ የሊዝ አገልግሎት ያልተዳረሰባቸውን ገበያዎች ለማገልገልና አቅምን ያገናዘበ ብድር ለማቅረብ የሚሠራ ኩባንያ ነው። ለበለጠ መረጃ http://www.ethiolease.com ይጎብኙ።

    ስለ አፍሪካን አሴት ፋይናንስ ካምፓኒ (AAFC)
    የአፍሪካ አሴት ፋይናንስ ኩባንያ (AAFC) ዋና መቀመጫውን በአሜሪካ ኒው ዮርክ በማድረግ በተለያዩ ሀገራት ያሉ ኩባንያዎች የፋይናንስ አቅርቦት አገልግሎት ይሰጣል። በመላው አፍሪካም የደንበኞችን ፍላጎትና አቅምን መሰረት ያደረገ የቁስ ውሰት አገልግሎቶችን ይሰጣል። ለበለጠ መረጃ http://www.aafc.com ይጎብኙ።

    ኢትዮ ሊዝ

    Anonymous
    Inactive

    ወሎ ዩኒቨርሲቲ በሁለተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን 419 ተማሪዎችን አስመረቀ

    ደሴ (ኢዜአ/ወ.ዩ.) – ወሎ ዩኒቨርሲቲ (ወ.ዩ.) በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች በሁለተኛ ዲግሪ (Masters program) ያሰለጠናቸውን 350 ወንድ 69 ሴት በድምሩ 419 ተማሪዎችን ነሐሴ 2 ቀን 2012 ዓ.ም. ተማሪዎቹ ባሉበት ቦታ በኦንላይን (online) አስመረቀ።

    የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር አባተ ጌታሁን በምረቃው ሥነ ሥርዓት ወቅት እንደተናገሩት ተቋሙ በየዓመቱ በርካታ ተማሪዎችን አሰልጥኖ ቢያስመርቁም ዘንድሮ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ (ኮቪድ-19) ከፍተኛ ጫና አሳድሯል። በወቅታዊ የወረርሽኝ ምክንያት የመማር ማስተማሩ ሥራ ቢቋረጥም አጋዥ ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅሞ ተማሪዎችን በማስተማር የጀመሩትን ትምህርት እንዲያጠናቅቁ መደረጉን አስታውቀዋል።

    ተማሪዎች በመደበኛ፣ በማታ እና ሳምንታዊ መረሃ ግብር ትምህርታቸውን የተከታተሉ መሆናቸውን አመልክተው ትምህርታቸውን አጠናቀው ከተመረቁት መካከል 69 ሴቶች እንደሚገኙበት ዶ/ር አባተ ገልጸዋል።

    ዶ/ር አባተ የዘንድሮ ተመራቂ ተማሪዎች ዓለም በኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ በተናወጠበት እና የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት በተከሄደበት ዓመት መመረቃቸው ታሪካዊና ልዩ ያደርጋቸዋል ብለዋል። አያይዘውም፥ ፕሬዝዳንቱ ዩኒቨርሲቲው ዕቅዱን በአዲስ መልክ በማዋቀር ሀገር-በቀል እውቀቶችን ከምርምር ጋር በማቀናጀት ለውጥ በሚያስመዘግብ መልኩ ለመሥራት የተዘጋጀ በመሆኑ፥ ተመራቂዎች በቆይታቸው ያገኙትን እውቀት በሚሰማሩበት የሙያ ዘርፍ ተግባራዊ ከማድረግ ጀምረው አዳዲስ ምርምሮችን ከዩኒቨርሲቲው ጋር የመሥራት ዕድል ሊኖር እንደሚችል ጠቁመዋል።

    ተመራቂዎች በትምህርት ቆታቸው ያገኙትን እውቀት ወደ ተግባር ቀይረው ሀገራቸውን እና ሕዝባቸውን እንዲያገለግሉና የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን በመከላከሉም የድርሻቸውን እንዲወጡ ዶ/ር አባተ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

    ወሎ ዩኒቨርሲቲ ነሐሴ 2 ቀን ያስመረቃቸው ተማሪዎች 12ኛ ዙር ሲሆኑ፥ በሕግ፣ ተፈጥሮ ሳይንስ፣ ሕክምና እና ጤና ሳይንስ፣ ማኅበራዊ ሳይንስ፣ የተፈጥሮ ቀመር፣ ቢዝነስ እና ምህንድስና የሰለጠኑ ናቸው።

    የደሴ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አበበ ገብረ መስቀል በበኩላቸው፥ ምሩቃን በቆይታቸው በቀሰሙት እውቀት በታማኝነት እኩል ሕብረተሰቡን ሊያገለግሉ ይገባል ብለዋል። የኢትዮጵያ የአንድነትና የሰላም እሴት ተጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፍም በእውቀት ላይ የተመሠረተ እገዛ በማድረግ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አቶ አበበ አመልክተዋል።

    ከተመራቂዎች መካከል መላኩ በላይ በሰጠው አስተያየት ምንም እንኳ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ (ኮቪድ-19) በትምህርቱ ዘርፍ ጫና ቢያሳድርም፥ በቴክኖሎጂ ታግዘው በዕለቱ ለመመረቅ በመብቃቱ መደሰቱን ገልጿል። በተማረበት ሕክምና እና ጤና ሳይንስም ሕብረተሰቡን በታማኝነት ለማገልገል መዘጋጀቱን ጠቁሞ፥ “በተለይ ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የድርሻዬን እወጣለሁ” በማለት አክሏል።

    ሌላዋ የፕሮጀክት አመራር (project management) ተመራቂ ገነት ኪሮስ በበኩሏ፥ በሙያዋ ሕዝቡን በማገልገል የበኩሏን አስተዋጽኦ እንደምታደርግ ተናግራለች። ወቅቱ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ዓለምን የሚያስጨንቅበት ቢሆንም በተለያዩ ቴክኖሎጂዎች ታግዛ ለዚህ በመብቃቷ መደሰቷን ገልጻለች።

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ)/ ወሎ ዩኒቨርሲቲ (ወ.ዩ.)

    ወሎ ዩኒቨርሲቲ በሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን አስመረቀ

    Semonegna
    Keymaster

    ዓባይ ወንዝ የእኔም፣ የአንተም፣ የአንቺም፣ የእኛም የሁላችም ነው!!

    ኢትዮጵያ በተለያዩ የተፈጥሮ ሀብቶች የተቸረች ውብ ሀገር ብትሆንም ለበርካታ ዘመናት በራሷ የተፈጥሮ ሀብት ከመልማትና ከመጠቀም ይልቅ የበይ ተመልካች ሆና በድህነት አረንቋ ውስጥ እንድትኖር የተፈረደባት መሆኑን በድፍረት መጥቀስ ይቻላል።

    የቅኝ ገዥ ሀገራት ከ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ በዓባይ ወንዝ ላይ ዋነኛ ተጠቃሚ ለመሆን ከፍተኛ ጉጉት ያሳደሩ በመሆኑ ከጉያዋ ፈልቆ በሚፈሰው ሃብት ላይ አንዲት ብርጭቆ ውሃ እንዳትጠቀምና እንዳትለማ የሚያደርግ፣ የተጠቃሚነት መብቷን የጣሰና የከለከለ፣ በቅኝ ግዢ አስገዳጅ ውሎች አማካኝነት ባላመነችበትና ባልተሳተፈችበት ጉዳይ በወንዙ ላይ ተጠቃሚ እንዳትሆን ሲደረግ እንደነበር በማስረጃነት ማንሳት ይቻላል።

    በተለይ በወንዙ ላይ የተደረጉ ስምምነቶችን ስንመለከት የግብጽና የሱዳንን ስም ይያዝ እንጂ በዋናነት የቅኝ ገዢዎች የእጅ አዙር ተጠቃሚነትን ታላሚ ያደረገ መሆኑ ግልፅ ነው። ይህም ሲባል የቅኝ ገዥ ሀገራት በዓባይ ወንዝ (Nile River) ዙሪያ ሲያከናውኗው የነበሩት ስምምነቶች የራሳቸውን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ከማጎልበት የመነጨ እንጂ ለቅኝ ተገዥ ሀገራት ጥቅም ሲባል የተደረገ አይደለም።

    ግብፅና ሱዳን የእንግሊዝ ቅኝ ተገዢ ሀገራት ቢሆኑም በወንዙ ላይ ያላቸውን ተጠቃሚነት ስንመለከት ከፍተኛውን ድርሻ እንግሊዝ ከቅኝ ግዛት በኋላ ደግሞ ግብፅ ቀጥሎ ሱዳን ብቻ እንደነበሩ ስንመለከት፥ ተካሄዱ የተባሉት ስምምነቶች ሁሉ ምን ያህል አግላይና ከልካይ እንደነበሩ ከመጠቆሙም በላይ ኢትዮጵያ በራሷ የተፈጥሮ ሀብት እንዳትጠቀምና እንዳትለማ ይደረግ የነበረውን ሴራ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው።

    ለዚህም እንደማሳያ በዓባይ ወንዝና ገባሮቹ ላይ እ.ኤ.አ ከ1891 እስከ 1959 ድረስ የተከናወኑ የተለያዩ ስምምነቶችን ማንሳት ይቻላል። እ.ኤ.አ በ1891 በጣልያንና በእንግሊዝ የተደረገው ስምምነት ይዘትም ጣልያን ኤርትራን በያዘችበት ወቅት በአትባራ ወይም ተከዜ ወንዝ ላይ የግብፅን ጥቅም ላለመንካት ሲባል ግድብ እንደማትሠራ ከእንግሊዝ ጋር የተዋዋለችበት መሆኑ የሚታወቅ ነው።

    ሌላው እ.ኤ.አ በ1901 ከደቡባዊ አስመራ ተነስቶ አትባራ ወንዝን የሚገብርና በመጨረሻም ወደ ዓባይ ወንዝ የሚቀላቀል ጋሽ/መረብ ወንዝን በማስመልከት በእንግሊዝና በጣልያን መካከል የተከናወነ ሲሆን፥ ይዘቱም ኤርትራ በመልካም የጉርብትና መርህ ላይ ተመሥርታ በወንዙ ላይ የመጠቀም መብት እንዳላት እውቅና የሚሰጥ በመሆኑ ከሌሎች የቅኝ ገዢዎች ስምምነቶች በተሻለ ሁኔታ ፍትሀዊና የአሁኗ ኤርትራን መብት የማይጎዳ ነው ተብሎ ይታሰባል።

    እ.ኤ.አ በ1902 የሱዳን ቅኝ ገዥ በነበረችው በእንግሊዝ እና በኢትዮጵያ መካከል የተከናወነ ስምምነት እንደነበር ይጠቀሳል። በዚህ ስምምነት ላይ ኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ ውሃውን የሚያስቀር ግድብ መሥራት እንደማትችል ይጥቀስ እንጂ፥ ውሃውን ገድባ መጠቀም እንደማትችል የሚገልፅ አይደለም። በዚህ ስምምነት ላይ ግብፆች እንደሚያነሱት እርባና-ቢስ ክርክር ሳይሆን የስምምነቱ ይዘት የሚለው ውሃውን ይዞ ማስቀረት (‘arrest’ ወይም ‘block’ ማድረግ) ወይም ሙሉ በሙሉ ማስቆም እንደማይቻል እንጂ ከማንኛውም የተጠቃሚነት ዓይነት የሚከለክል ስምምነት አለመሆኑ እሙን ነው። ይህም አሁን ሃገሪቱ እየተከተለችው ላለው ፍትሃዊና ምክንያታዊ ተጠቃሚነትን የሚያጎላ ስምምነት ነው ማለት ይቻላል።

    በተጨማሪም እ.ኤ.አ የ1906 የቤልጂየም እና የእንግሊዝ ስምምነት ማንሳት ይቻላል። በዚህ ስምነት ላይ ቤልጂየም (ኮንጎን በመወከል) እና በእንግሊዝ መካከል የተከናወነ ሲሆን የኮንጎ መንግሥት ከሰምሊኪ (Semliki River) ወይም ከልሳንጎ ወንዝ (lsango River)ወደ አልበርት ሀይቅ (Lake Albert) የሚወርደውን ውሃ ከሱዳን መንግሥት ጋር ሳይስማማ ውሃውን የሚቀንስ ሥራ ለመሥራት ለማንም ፈቃድ እንዳይሰጥ የሚል ነበር።

    ሌላው እ.ኤ.አ በ1929 በእንግሊዝ እና በግብፅ መካካል የተከናወነውን ስምምነት ስንመለከት ደግሞ፥ ሱዳንን የተወሰነ ድርሻ ብቻ እንዲሰጣት በማድረግ ግብጽ እና እንግሊዝ ብቻቸውን የናይል ወንዝ (ዓባይ ወንዝ) ተጠቃሚ እንደሆኑ በተለይም ግብፅ ዓባይ ወንዝ ላይ በብቸኝነት የመወሰንና ድምፅን በድምፅ የመሻር ስልጣን (veto power) እንዳላትና ካለምንም ጣልቃ ገብነት የሚቀጥል መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው።

    እ.ኤ.አ በ1959 የተደረገው የግብጽ እና  የሱዳን ስምምነትን ስንመለከትም በዋናነት የዓባይ ወንዝ ውሃ የግብጽ እንደሆነ እውቅና የሚሰጥ ስምምነት ነበር ማለት ይቻላል። ይህም ሲባል 55.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ለግብጽ፣ 18.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ለሱዳን በመስጠት ቀሪው 10 ቢሊዮን ኩቢክ ሜትር ደግሞ የአከባቢው የኢኮሎጂካዊ ሚዛን ለመጠበቅ እንዲተን በመስማማት ኢትዮጵያ አንዲት ብርጭቆ ውኃ እንኳን የምትጠቀምበት መብት ያላገኘችበት አስገራሚና አሳዛኝ ውል ነበር። ይህ ስምምነት ሌሎች ተፋሰስ ሀገራትን ያገለለና ፍፁም የሁለትዮሽ ውል ስለነበር በኢትዮጵያ በኩል ተቀባይነት እንደሌለው ተደጋግሞ ተገልጿል።

    እንግዲህ በዚህ የፍርደ ገምድል ስምምነት መሠረት ኢትዮጵያ በራሷ የተፈጥሮ ሀብት መልማት እንዳትችልና እንዳትጠቀም የተለያዩ ጫናዎችና እገዳዎች ቢደረግም ይህን የዘመናት ቁጭት በራስ አቅም ገንብቶ እውን ለማድረግ ቆርጦ የተነሳው የአሁኑ ትውልድ ቀደም ሲል ይደረጉ የነበሩ ክልከላዎችና እገዳዎች ሳይበግሩት በራስ የገንዘብ አቅምና ጉልበት እንዲሁም እውቀት የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሥራውን ከጀመረ እነሆ ዘጠኝ ዓመታትን አስቆጥሯል።

    እስካሁን በነበረው ሂደት ምንም አንኳን ውስጣዊና ውጫዊ ፈተናዎች ያጋጠሙት ቢሆንም፥ ያሰበውንና የጀመረውን ነገር ከዳር ሳያደርስ መተኛት የማይወደው ይህ ትውልድ ፈተናዎቹን ተቋቁሞ የዘመናት ቁጭቱን በደስታ ቀይሮ ድሃ እያሉ ለተሳለቁበትና የልማት ጥሙን ለመወጣት የድል ብሥራት ዜናውን “ሀ” ብሎ ማሰማት ጀምሯል።

    ታሪክን መሥራት ከአባቱ የወረሰው ይህ ትውልድ የአደራ ቃሉን በብርቱ ለመወጣትና ታሪክ ሠሪነቱን ዳግም በዓለም አደባባይ ለማስመስከር የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሕያው ምስክር እንደሚሆን የሚያጠራጥር አይደለም። በተለይም ቀጣዩ ትውልድ የዓባይ ወንዝን የዘመናት ቁጭት እንዳይወርስ “ቁጭት በእኔ ይብቃ!” በሚል ከፍተኛ ወኔ ዓባይ ወንዝን በሀገሩ ዋል አደር ብሎ ለሚሰነብትበት ማረፊያ ጎጆ ቀልሶ ዓባይ ወንዝን እንደሰው “ቤት ለእንግዳ” ብሎ “እንቦሳ እሰር” ሊባል ከጫፍ መድረሱ ዛሬም እንደጥንቱ ታሪክ ሠሪ ትውልድ ስለመሆኑ አንዱ ማሳያ ነው።

    በመጨረሻም ለባዕዳን ሀገር የዘመናት ሲሳይ የነበረው የአባይ ውሃን ከ”ዓባይ ዓባይ፥ ያ’ገር ሲሳይ” የቁጭት እንጉርጉሮ ወደ “ዓባይ ዓባይ፥ የእኛም ሲሳይ” የድል ዜማነት ለመቀየር የተተባበረ ክንዳችን ዓባይ ወንዝ ላይ ለማሳረፍ የሚከለክለን አንዳችም ነገር የለምና ዛሬም እንደትናንቱ በምንችለው ነገር ሁሉ ድጋፋችን አጠናክረን በመቀጠል አዲስ ታሪክ ለመፃፍ እንነሳ በማለት ጽሁፌን በዚሁ እቋጫለሁ።

    አዎ ዓባይ ወንዝ የእኔም፣ የአንተም፣ የአንቺም፣ የእኛም በአጠቃላይ የሁላችንም ነው!!
    እንደጀምርነው እንጨርሰዋለን!!

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል

    ዓባይ ወንዝ

    Anonymous
    Inactive

    ፖሊስ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ቀድሞ የሕግ የበላይነትን እራሱ ሊያከብር ይገባል!
    ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የተሰጠ መግለጫ

    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ሕዝብ ለዘመናት የታገለለትን የፍትሃዊ እና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ምሥረታ ግቡን እንዲመታ ለማገዝ ከየትኛውም በሀገራችን ካለ የፖለቲካ ፓርቲ በላይ እራሱን በማደራጀት እያዘጋጀ የሚገኝ የፖለቲካ ፓርቲ ነው።

    የፓለቲካዊ ለውጥ ወይንም ሽግግር አስተማማኝ ዋስትና ተቋማት ብቁ፣ ነፃ እና ገለልተኛ ሆነው መቆም መጀመራቸው እና መቀጠላቸው ትልቁን ድርሻ እንደሚይዝ አያጠራጥርም። እነዚህ ለአንድ ሀገር ሕዝብ በሰላም እና በአንድነት የመኖር ዋስትናን የሚያረጋግጡ ተቋማት ከየትኛውም የግለስብም ሆነ የፓርቲ ፍላጎት ራሳቸውን በማላቀቅ በሂደት በሕግና በሕግ ብቻ የሚሠሩበት ሁኔታ እየፈጠሩ መሄድ እንዳለባቸው ኢዜማ ያምናል፤ ለሂደቱም ውጤታማነት በፅናት ይታገላል። በተለይም የሕግ የበላይነትን ማስከበር ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ፤ የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅ እና የሀገር አንድነትን ለማረጋገጥ ዋነኛው ግብዓት ነው። በዚህ ደረጃ የሚሠሩ ተቋሞችን መገንባት የረጅም ጊዜ ሥራ እንደሚፈልጉ ብንረዳም ሕግን ማስከበር የሚገባቸው ተቋማት የሕግ የበላይነትን የሚሸረሽር ተግባር ላይ ሲሳተፉ መመልከት ደግሞ አሰዛኝ ክስተት ይሆናል፡፡

    ባለፉት ሁለት ዓመታት ከአንባገነናዊ ሥልጣኑ የተባረረው እና ለውጡ የመጣባቸው ኃይሎች እንዲሁም ለውጡን ራሳቸው በቆፈሩት ቦይ ብቻ እንዲፈስ የፈለጉ ቡድኖች በጋራም ሆነ በተናጥል በፈጠሯቸው ትርምሶች ክቡር የሆነው የዜጎች ሕይወት ጠፍቷል፤ አካል ጎድሏል፤ ንብረት ጠፍቷል። በእነዚህ ግዚያት ውስጥ የክልልም ሆነ የፌደራል መንግሥት አስተዳደሮች እንዲሁም የፀጥታ እና የፍትህ አካላት ባሳዩት ከፍተኛ የዝግጅትና የአፈፃፀም አቅም ውሱንነት ለደረሰው ከፍተኛ ጉዳት በግልፅ ይቅርታ ሊጠይቁና አስፈላጊውን ካሳ ሊከፍሉ እንደሚገባ ማሳሰባችን ይታወሳል።

    ሕዝብ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እስክንሻገር ድረስ ከቀጥተኛ ውክልና ፍጹም ባነሰ ስምምነት ሥልጣን ላይ እንዲቆይ ፈቅዶ ከለውጡ በፊት ያጠፋውን ጥፋት ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የምናደርገውን ሽግግር አግዞ እንዲክስ ሌላ ዕድል የተሰጠው ገዢው ፓርቲ እንዲሁም ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች (እኛንም ጨምሮ) ከዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሊያዘገዮን ከሚችሉ እንቅስቃሴዎች ሁሉ መታቀብ የሚገባን ወቅት ላይ ደርሰናል። በተለይ ገዢው ፓርቲ ከመቼውም ጊዜ በላይ የያዘው ሥልጣን የሰጠውን የሕግ የበላይነትን የማስከበር ዋነኛ ኃላፊነት እና ታሪካዊ አደራ አሁን የደረስንበት ወቅት ግድ የሚለውን ከፍተኛ ጥንቃቄ እና ብስለት ጋር መወጣት ይገባዋል። የሕግ የበላይነትን ማክበር በጣም አስፈላጊው ግን ደግሞ በጣም ትንሹ ግዴታው ነው ብለን እናምናለን።

    በሀገራችን ያሉ የፍትህ ተቋማት በተግባር የሚፈተኑበት ወቅት አሁን ነው። ከየትኛውም አካል የተፈጠርን ወይምን ሊፈጠር ይችላል ከሚሉት ሥጋት ወይንም ከግለሰብም ሆነ ከየትኛውም የፓለቲካ ፓርቲ ከሚመጣ ሙገሳም ሆነ ወቀሳ በራቀ መልኩ ፓሊስ በቁጥጥር ስር ያዋላቸው ዜጎች የተቀላጠፈ እና እውነተኛ ፍትህ የማግኘት ሕገ መንግሥታዊ መብት የሚከበርበትን መንገድ በማረጋገጥ ማኅበረሰቡ በፍትህ ተቋማት እና ሥርዓቱ ላይ ለረጅም ጊዜ ያጣውን ዕምነት መልሶ መገንባት የሚጀምሩበት ወቅት መሆን ይገባዋል።

    የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ሥራ እስፈፃሚ አባል እና የሙያ ማኅበራት ተጠሪ ሂሩት ክፍሌ ከሐምሌ 7 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ለ22 ቀናት በፓሊስ ቁጥጥር ሥር ቆይተው ሐምሌ 29 ቀን በ6,000 ብር ዋስ ከእስር ተለቀዋል። ሂሩት በቁጥጥር ስር ከዋሉበት ቀን ጀምሮ «ለምን ታሰሩ?» ወይንም «ይፈቱ!» የሚል ጥያቄ ከማቅረብ ይልቅ ጉዳዩን በቅርበት ስንከታተል እና ሁሉም ተጠርጣሪዎች ሰብዓዊ መብታቸው ተጠብቆ የተፋጠነ ፍትህ እንዲያገኙ ስንጠይቅ ቆይተናል።

    ፓሊስ የዜጎችን መብት ለማስከበር እና አጥፊዎችን ለመለየት የሚረዳው ዜጎችን ከማሰሩ በፊት ከጥርጣሬ በላይ በወንጀል መሳተፋቸውን የሚያስረዳ ማስረጃ እንዲኖረው የሚያስገድደውን መሠረታዊ መርህ በመተው ሂሩት በወንጀል ድርጊት ተሳታፊነት ጠርጥሬያቸዋለው በማለት ለሁለት ግዜ የምርመራ ጊዜ ጠይቆ ተፈቅዶለታል። ለሁለተኛ ጊዜ ተጨማሪ የምርመራ ቀን ለፖሊስ የፈቀደው ፍርድ ቤት በተጨማሪው ቀናት ፖሊስ ምርመራውን አጠናቆ እንዲቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር። ፖሊስ የተሰጠውን ትዕዛዝ ሳያከብር ተፈጽሟል ያለው ወንጀል 35 ቀን ካለፈው በኋላ ሐምሌ 28 ቀን 2012 ዓ.ም. ለሦስተኛ ጊዜ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ጠይቋል። የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ 2ኛ ወንጀል ችሎት የፖሊስ ጥያቄን ውድቅ አድርጎ ሂሩት በ6,000 ብር ዋስ ከእስር እንዲለቀቁ ትዕዛዝ ሰጥቷል። ፖሊስ ፍርድ ቤቱ በግልጽ የሰጠውን ትዕዛዝ የመፈቻ ወረቀቱን አልቀበልም በማለት ጥሷል። ሂሩትንም ያለምንም ምክንያት በእስር እንዲቆዩ በማድረግ መሠረታዊ መብታቸውን ረግጧል። ይህ ድርጊት በምንም ዓይነት ተቀባይነት የሌለው እና ሕግን አስከብራለው ከሚል ተቋም በፍጹም የማይጠበቅ እንዲሁም አልፈነዋል ያልነውን የፖሊስ እራሱን ከሕግ በላይ አድርጎ የመቁጠር ፍጹም የሆነ የማን አለብኝነት ትዕቢት አሁንም እንዳለ የሚያረጋግጥ ተግባር ሆኖ አግኝተነዋል። ፖሊስ ተመሳሳይ ድርጊት ሌሎች ዜጎች ላይ በተከታታይ ይህ ድርጊት ለሕግ ግድ የማይሰጠው አንድ ፖሊስ ወይንም ጥቂት ፖሊሶች ያደረጉት ሳይሆን እጅግ አሳሳቢ የሆነ ተቋማዊ ችግር እንደሆነ ተገንዝበናል።

    አሁንም ፖሊስ የፍርድ ቤት ትዕዛዝን ያለመቀበል መደበኛ ተግባር እንዳያደርገው ስጋት ያለን ሲሆን፥ ፖሊሶች በመንገድ ላይ ዜጎችን ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብት እንዲሁም ዜጎች ሃሳባቸውን በሚመቻቸው መንገድ የመግለፅ መብትን ለማፈን የሚያደርጉት እንቅስቃሴ፥ ተቋሙ ለለውጥ ሩቅ መሆኑን የሚያመላክት ሆኖ አግኝተነዋል። መንግሥት ይህን ተቋም በማረም ማስተካከያ የማያድረግ ከሆነ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ጅምሮቻችን አደጋ ላይ እንደሚወድቁ ሊታወቅ ይገባል፡፡

    ፖሊስ በሕብረተሰቡ ዘንድ ያለውን አመኔታ መልሶ መገንባት ትልቁ የቤት ሥራው መሆኑን የሚገነዘብ እና ቅንጣት ታክል የሚያሳስበው ጉዳይ ከሆነ፥ ይህንን ድርጊት የፈጸሙ አባላቱ ላይ የማያዳግም እርምጃ ወስዶ ለሕዝብ ይፋ እንዲያደርግ፣ ለሂሩት እና ተመሳሳይ ድርጊት ለፈጸመባቸው ዜጎች ሁሉ በይፋ ይቅርታ እንዲጠይቅ እንዲሁም ከእንደዚህ ዓይነት አይን ያወጣ ማን አለብኝነት ከአሁን በኋላ እንዲታቀብ እናሳስባለን።

    በዚህ አጋጣሚ የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ እና ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ፖሊስ ለዜጎች መብት ግድ ሳይሰጥ በእስር ላይ ለማቆየት ያቀረበውን ጥያቄ ውድቅ በማድረግ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር እና የዜጎችን መብት ለመጠበቅ ለሰጡት ውሳኔ ያለንን አክብሮት እና ምስጋና እንገልጻለን።

    በመጨረሻም ከፍትሃዊ እና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ውጪ አሰተማማኝ ሰላም፣ ዕድገት እና አንድነት የተጎናፀፈች ኢትዮጵያን መገንባት የማይታሰብ መሆኑን ሁላችንም ተረድተን ለፍትሃዊ እና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት ሁላችንም ባለድርሻ አካላት የበኩላችንን አውንታዊ አስተዋፅዖ እንድናደርግ አጥብቀን እንጠይቃለን።

    ነሐሴ 1 ቀን 2012 ዓ.ም
    የኢዜማ ሕዝብ ግንኙነት

    Anonymous
    Inactive

    ቁጥጥር ወይ ድርድር! ― አብርሃ ደስታ

    በሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) እና በፌደራል መንግሥት መካከል ውጥረት ነግሷል። የኦሮሚያ ጉዳይም አሳሳቢ ነው። በዚሁ ከቀጠልን የሀገር አንድነት እና የሕዝቦች ደህንነት አደጋ ላይ ይወድቃል።

    ምን መደረግ አለበት?

    ዘርፈ ብዙ ፖለቲካዊ ችግሮች ቢኖርቡንም ለአሁኑ ወቅታዊውና አንገብጋቢው ውጥረት መንስዔ ከምርጫ መራዘም በኋላ የፌደራል መንግሥት ከሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ጋር መነጋገር/ መወያየት ሲገባው “ሁሉም ነገር በሕግ አግባብ ይፈታል” ብሎ የሕገ መንግሥት ትርጉም ወደ መጠየቅ መጣደፉ ነው።

    መንግሥታዊ ተቋምና መዋቅር (government institutions and structure) እንዲሁም ሁነኛ የመንግሥትቁጥጥር (effective government control) በሌለበት ሀገር ሁሉም ነገር በሕግ አግባብ አይፈታም።

    የፌደራል መንግሥት “የፖለቲካ ውይይት አልቀበልም፤ ስልጣን ልትጋሩኝ ነው” ብሎ ወደ “ሕገ መንግሥት ትርጉም” ሮጦ ብቻውን ባይወስን ኖሮ፥ ብዙ ነገር ቀላል ይሆን ነበር። “ትርጉም” ከመጠየቁ በፊት “ይህን ውሳኔዬን የማይቀበሉ ቢኖሩስ? አመፅ ቢቀሰቀስስ?” ብሎ ማሰብ ነበረበት። በሁሉም አከባቢ “መንግሥታዊ ቁጥጥር” እንደሌለው እያወቀ!? ብቻውን ከመወሰኑ በፊት ከሌሎች ጋር መወያየት ቢችል ኖሮ ብዙ ችግሮቻችን መፍትሔ ያገኙ ነበር።

    አንድ መንግሥት መሥራት ያለበት የመጀመርያ ሥራ በሁሉም አከባቢ መንግሥታዊ መዋቅር ዘርግቶ ሰላምና መረጋጋትን ማስፈን ነው። ለዚህም ጠንካራ እና ገለልተኛ የሆኑ (ለፖለቲካ ፓርቲ የማያዳሉ) መንግሥታዊ ተቋማት በመገንባት ሕዝብ በመንግሥት ላይ እምነት እንዲኖረው ማሳየት አለበት። መንግሥት ይህን ባልሠራበት ወቅት ችግር የሚያጋጥም ከሆነ ግን በውይይት/ እውነተኛ ድርድር ነው መፈታት የሚችለው/ ያለበት።

    መንግሥት “መንግሥት” መሆን ካቃተው ዜጎች ዋስትና ያጣሉ። እናም ራሳቸው በራሳቸው ለመከላከል ይታጠቃሉ። ራሳቸው መልስ ይሰጣሉ፣ ይበቀላሉ። በዚህም ሕዝብ ይጎዳል፤ ሀገር ይፈርሳል። የህወሓት ወታደራዊ ትእይንት የምርጫ ጉዳይ አይደለም፤ በመንግሥታዊ ሥርዓቱ ላይ ዋስትና ማጣት ነው። የኦሮሞ ዓመፅ በመንግሥት ላይ እምነት ማጣት ነው። እንደ ውጤቱም እጅግ ዘግናኝ ክስተቶች አየን።

    ሀገር እንዲፈርስና ሕዝብ እንዲጎዳ አልፈልግም፤ ስለዚህ የፖለቲካ ችግሮቻችን ለመፍታት መደራደር ይኖርብናል። መንግሥት ከስልጣን በላይ የሀገር አንድነትና የሕዝቦች ደህንነት የሚያሳስበው ከሆነ ለእውነተኛ ድርድር ዝግጁ መሆን አለበት። አለበለዚያ ግን ችግሮቻችን ይቀጥላሉ።

    ወይ አልተደራደረ ወይ አልተቆጣጠረ?!

    አብርሃ ደስታ

    * አቶ አብርሃ ደስታ በትግራይ ክልል ውስጥ በዕድሜ አንጋፋነታቸው ሁለተኛ የሆነው ዓረና ትግራይ ለዲሞክራሲ እና ሉዓላዊነት (ዓረና ትግራይ) በመባል የሚጠራው የፖለቲካ ፓርቲ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚታ አባል ናቸው። የፌስቡክ ገጻቸውን እዚህ ጋር ያገኙታል።

    ሰሞነኛ ኢትዮጵያ፦ በሰሞነኛ ድረ-ገጽ የአማርኛ ፎረም (semonegna.com/forums) ላይ የሚገኝ ማንኛውም ጽሑፍ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንጸባርቅ ሲሆን፥ ጽሑፉ የሰሞነኛ ኢትዮጵያንንም ሆነ የተሳታፊዎችን አመለካከትና ምልከታ ላይወክል ይችላል።

    Abraha Desta አብርሃ ደስታ

    Semonegna
    Keymaster

    የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የሚያስገነባቸው ቤቶች አፈጻጸም በጥሩ ደረጃ ላይ መሆኑን ገለጸ

    አዲስ አበባ (አዲስ ዘመን)፦ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በአዲስ አበባ ከተማ አምስት ሳይቶች የሚያካሂደው የቤቶች ግንባታ አፈጻጸም በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ አስታወቀ።

    የኮርፖሬሽኑ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ክብሮም ገብረመድኅን በተለይ ለአዲስ ዘመን ዕለታዊ ጋዜጣ እንዳስታወቁት፥ የቤቶቹ ግንባታ በአቧሬ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ፋብሪካ አካባቢ፣ በመካኒሳ፣ ብሪቲሽ ካውንስልና ቦሌ ላይ እየተካሄደ ነው፤ ህንፃዎቹም እስከ 10 ፎቅ የሚደርሱና ለቅይጥ አገልግሎት (ለንግድ እና ለመኖሪያ) በሚል እየተገነቡ ያሉ ናቸው።

    ግንባታዎቹ እንደየቦታው ስፋት የተለያዩ ዓይነቶች መሆናቸውን ጠቅሰው፥ መንታ /twin/ ተደርገው የሚገነቡም እንዳሉ ጠቁመዋል። የመካኒሳው፣ የጊዮርጊስ ቢራ ፋብሪካ አካባቢውና የብሪቲሽ ካውንስሉ ፕሮጀክቶች ባለሁለት መንታ ግዙፍ ህንፃዎች መሆናቸውን አስታውቀው፥ የቦሌው አንድ ግዙፍ ህንፃ መሆኑን ጠቁመዋል።

    እንደ የግንኙነት ኃላፊው ገለጻ፥ አንዳንዶቹ ህንፃዎች ባለሰባት፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ባለ 10 ወለሎች ሲሆኑ፥ እየተገነቡ ያሉት በከተማ አስተዳደሩ የየአካባቢው ፕላን መሠረት ነው። በአጠቃላይ ግን የንግድ ተቋማቱ ብዛት በካሬ ሆኖ ወደፊት የሚለይ ሲሆን፥ የተቀሩት ግን ለቀቅ ባለ /luxurious/ በሆነ መልኩ ወደ አንድ ሺ ሰዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ቤቶች እየተገነቡ ነው።

    በግንባታው ላይ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ተደጋጋሚ ጉብኝት በማድረግ ክትትል እንደሚደረግ ጠቅሰው፥ የተቋሙ ማኔጅመንት ካውንስል /የስራ አመራር ኮሚቴው/፣ እንዲሁም የተቋሙ ቦርድ ክትትልና ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን አስታውቀዋል። የፓርላማው የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽንና ትራንስፖርት ቋሚ ኮሚቴም ክትትል እንደሚያደርግ ተናግረው፥ ሠራተኛው፣ ተቋራጮቹ፣ መሀንዲሶቹ እንዲሁ ሁሉም በጋራ በመረዳዳት መንፈስ እየተሠራ በመሆኑ አፈጻጸሙ ስኬታማ መሆን መቻሉን ተናግረዋል። የፓርላማ አባላት ፕሮጀክቶቹን እንደጎበኙትና በአፈጻጸሙም አድናቆቱ እንዳላቸው መግለጻቸውንም የግንኙነት ኃላፊው ተናግረዋል።

    “በቀጣይ ደግሞ ሰፋፊ ፕሮጀክቶች እንደሚኖሩ ይጠበቃል” ያሉት የግንኙነት ኃላፊው፥ የአሁኖቹ ፕሮጀክቶች ልምድ የሚቀሰምባቸው፣ አቅም እና ካፒታል የሚሰባሰብባቸው መሆናቸውን አስታውቀዋል።

    ኮርፖሬሽኑ ማኅበራዊ ኃላፊነቱንም እየተወጣ መሆኑን ጠቅሰው፥ ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ ለንግዱ ማኅበረሰብ 50 በመቶ የኪራይ ቅናሽ ማድረጉን አስታውሰዋል። ባለፉት አራት ወራት በኮቪድ-19 ምክንያት በየወሩ ከኪራይ መሰብሰብ የሚገባውን 60 ሚሊየን ብር ከተከራዮች አለመሰብሰቡን ተናግረዋል።

    የግንኙነት ኃላፊው በዚህ ፈተና ውስጥ እንዴት ከማኅበረሰቡ ጎን መቆም አለብኝ ብሎ በማሰብ ኮርፖሬሽኑ በሚያስተዳድራቸው በአዲስ አበባና በድሬዳዋ የሚገኙ 18,153 የመኖሪያና የድርጅት ቤቶች ተከራይ ደንበኞች የኮቪድ-19 የኮረና ቫይረስ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የፈጠረባቸውን ማኀበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተፅእኖ በመረዳት ኪራይ የመቀነስ ውሳኔ ላይ መድረሱን አስታውሰዋል። በኪራይ ዋጋ ቅነሳም በየወሩ ከአጠቃላይ ገቢው 50 በመቶውን እያጣ መሆኑን ጠቅሰው፥ በወር ከሚያገኘው 120 ሚሊየን ብር ገቢ እየሰበሰበ ያለው 60 ሚሊየን ብር ብቻ መሆኑን አስታውቀዋል።

    እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፥ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወደ ሀገራችን ከገባ አንስቶ ባሉት አራት ወራት ኮርፖሬሽኑ ማግኘት ከነበረበት 480 ሚሊየን ብር የሰብሰበው ግማሹን ብቻ መሆኑን ጠቁመዋል። ኮርፖሬሽኑ በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ብሔራዊ ንቅናቄ ሲቋቋም ድጋፍ ካደረጉት የመጀመሪያ አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፥ በወቅቱም 10 ሚሊየን ብር መስጠቱንም ጠቅሰዋል።

    የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በአዲስ አበባና በድሬዳዋ 18,153 ቤቶች እንዳሉት ከኮርፖሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ከእነዚህ መካከል ወደ 6ሺ 500 አካባቢ የንግድና የድርጅት ሲሆኑ፥ የተቀሩት ደግሞ የመኖሪያ ቤቶች ናቸው። ኮርፖሬሽኑ በደንብ ቁጥር 398/2009 የተለያዩ ተግባርና ኃላፊነቶች ተሰጥተዉት በራሱ ገቢ እንዲተዳደር የተቋቋመ የመንግሥት የልማት ድርጅት ነው

    ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን Federal Housing Corporation

    Semonegna
    Keymaster

    ከክረምቱ ወቅት መግባት ጋር ተያይዞ መንገዶች ላይ የሚደረጉ ማንኛውም ቁፋሮዎች እንደማይከናወኑ
    የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን (አአመባ) አስታወቀ

    አዲስ አበባ (አአመባ) – የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን (አአመባ) የክረምት መግባት ጋር በተያያዘ በመንገድ መሠረተ ልማቶች ላይ የሚካሄዱ የቁፋሮ ሥራዎችን ከግንቦት 30 ቀን 2012 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት 1 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ ማስቆሙን ገልፆ፥ ለተግባራዊነቱም የክትትልና ቁጥጥር ሥራ እያከናወነ መሆኑን አስታውቋል።

    የክረምት ወራት መግባትን ተከትሎ ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ ከመሠረተ ልማት አቅራቢ ተቋማትና ግለሰቦች ለተለያዩ የልማት ሥራዎች የሚቀርቡለትን የመንገድ መሠረተ ልማት ቁፋሮ ፈቃድ ማቆሙ ይታወቃል።

    ከመንገድ መሠረተ ልማት ጋር ተያይዞ የቁፋሮ ፈቃድ ይሰጥባቸው ከነበሩት ውስጥ የመጠጥ ውሃ ዝርጋታ፣ የዝናብ ውሃ ከቆሻሻ ፍሳሽ ማስወገጃ መስመር (drainage system) ጋር ይገናኝልኝ ጥያቄ፣ የፍሳሽ መስመር ለማገናኘት፣ የመግቢያ መውጫ ይከፈትልንና ከመሠረተ ልማት ዘርጊ ተቋማት የሚቀርቡ የመንገድ መቁረጥ ፈቃድ ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

    የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን በክረምት የሚደረጉ ቁፋሮዎች በነዋሪው የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ላይ እክል እንዳይፈጥሩ፣ ከአደጋ ለመጠበቅና የትራፊክ ፍሰት እንዳይስተጓጎል የቁፋሮና የአስፋልት መቁረጥ ፍቃድ መስጠት እስከ ጥቅምት 1 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ ማቆሙን አስታውቋል።

    ከዚሁ ጋር በተያያዘ ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ በ2012 ዓ.ም. በጀት ዓመት በቁጥር 443 የሚሆኑ ከተለያዩ አካላት የቀረቡለትን የመንገድ መቁረጥ ጥያቄ ፍቃድ ሰጥቷል። በተጨማሪም የመንገድ ሃብት ላይ ሕገ-ወጥ ድርጊቶችን በመፈጸም ጉዳት የሚያደርሱ አካላት ላይ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ የመንገድ መብት ጥሰቶችና ጉዳቶች ለመከላከል የሚያስችል አሠራርን በመዘርጋት እንቅስቃሴ እያደረግ ይገኛል።

    በመንገድ ሀብት ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን ለመቅረፍና መንገዶችን ለመንከባከብ ባለስልጣኑ ከመሠረተ ልማት ቅንጅት ግንባታ ፈቃድ እና ቁጥጥር ባለስልጣን ጋር እና ከመሠረተ ልማት ዘርጊ ተቋማትና ሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተናቦ በመሥራት ከፍተኛ የሕዝብ ሀብት ፈሶባቸው የተገነቡ መንገዶችን ከሚደርስባቸው የተለያዩ የመንገድ መብት ጥሰቶችና ጉዳቶች ለመከላከል ሰፊ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል። ይህም የመንገድ መሠረተ ልማቶች በሚፈለገው መጠን ከጉዳት ተጠብቀው አገልግሎት እንዲሰጡ ከማስቻሉም ባለፈ የመንገዶችን የጥገና ወጪ በመቀነስ የጎላ አስተዋፅኦ አድርጓል።

    በመጨረሻም ሕብረተሰቡ የተገነቡ እና በግንባታ ላይ የሚገኙ የመንገድ ፕሮጀክቶችን ከመንገድ መብት ጥሰቶችና ከሚፈፀሙ ሕገ-ወጥ ተግባራት በመከላከልና በመጠበቅ ከባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ በጋራ እንዲሠሩ ጥሪውን ያስተላልፋል።

    ከዚሁ ዜና ጋር በተያያዘ፥ የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን በ2012 ዓ.ም. በጀት ዓመት ከ375.2 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የግንባታ ግብዓቶችን አምርቶ ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረጉንአስታውቋል።

    ባለስልጣኑ ባለፉት 12 ወራት ውስጥ በ134.9 ሚሊዮን የካባ፣ በ73.7 ሚሊዮን ብር ሲሚንቶ፣ በ166.6 ሚሊዮን ብር የሚገመት የአስፋልት ምርቶችን አምርቶ ለተለያዩ የግንባታ ሥራዎች ያሰራጨ ሲሆን፥ አጠቃላይም የዕቅዱን 89 በመቶ አፈፃፀም አስመዝግቧል።

    በባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ በራስ አቅም ተመርተው ሥራ ላይ ከሚውሉ የተለያዩ ምርቶች መካከል፥ ገረገንቲ፣ ቤዝ ኮርስ (base course)፣ ሰብቤዝ (subbase)፣ ጠጠር፣ ነጭ ድንጋይ፣ የተለያዩ መጠን ያላቸው ቱቦዎች፣ ሲሚንቶ ኮንክሪት፣ ከርብስቶን (curbstone)፣ የማንሆል ክዳን (manhole cover)፣ ፍርግርግ፣ ቦላርድ (bollard)፣ ታይልስ (tiles)፣ ባይንደር ሚክስ (binder mix)፣ ሰርፊስ ሚክስ (surface mix) የመሳሰሉት ይገኙበታል።

    ባለስልጣኑ የግንባታ ግብዓቶችን በራሱ አቅም ማምረት መቻሉ በራሱ አቅም እየገነባቸው ለሚገኙ የግንባታና የጥገና ሥራዎች የአቅርቦት እጥረት እንዳይፈጠር በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል። በቀጣይም የግብዓት ምርቶች እጥረት እንዳይፈጠርም አሁን ላይ ባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ የተለያዩ ሥራዎችን ሊሰሩ የሚችሉ በርካታ ማሽነሪዎችን በመግዛት በትጋት እየሠራ ይገኛል።

    ምንጭ፦ አአመባ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን

    Anonymous
    Inactive

    ኢትዮጵያ ውስጥ በሚቀጥሉት 3 ወራት በኮቪድ-19 ምክንያት ወደ 8,000 የሚጠጉ ሰዎች ሊሞቱ ይችላሉ፤ ቢሆንም የፊት ጭምብል (ማስክ) መጠቀም ሞትን በ65% ሊቀንስ ይችላል ― የ IHME ትምበያ

    ለኢትዮጵያ የሚደረጉት አዳዲስ የ IHME COVID-19 ትምበያዎች እንደሚያሳዩት፣ እስከ ጥቅምት 22 ባለው ጊዜ ድረስ ወደ 8,000 የሚጠጉ ሰዎች (በኮቪድ-19 ምክንያት) ይሞታሉ፣ ቢሆንም የፊት ጭምብል (ማስክ) መጠቀም ሞትን በ 65% ሊቀንስ ይችላል።

    ሲያትል፥ ዋሽንግተን ግዛት (IHME) – በዩኒቨርሲቲ ኦፍ ዋሺንግተ የሚገኘው Institute for Health Metrics and Evaluation (የጤና ሜትሪክስና ግምገማ ተቋም) (IHME)፥ ሀገሪቱ የማኅበራዊ መራራቅ ፖሊሲን ላላ የማድረጉን ፖሊሲ ማስተግበሩን ከቀጠለች፥ በኢትዮጵያ ውስጥ እስከ ጥቅምት 22 ባለው ጊዜ ውስጥ፣ 7,872 ሰዎች (ከ 1,115 እስከ 31,971 የሚሆኑ ) በኮቪድ-19 ምክንያት እንደሚሞቱ ይተነብያል።

    ቢሆንም ጭምብልን መጠቀም ስርጭትን መቆጣጠርን ሊረዳና የመከላከል አገልግሎት ይሰጣል ብለው የ IHME ዳይሬክተር፥ ዶ/ር ክርስቶፈር መሪ (Dr. Christopher Murray) ተናግረዋል። ተቋሙ እንደ ሞዴል የተጠቀመበት እጅግ ከፍተኛ የፊት ጭምብል ጥቅም ላይ መዋልን ሲሆን፥ 95% የሚሆነው ሕብረተሰብ ጭምብል እውጭ በሚንቀሳቀስበት ወቅት ቢጠቀም፥ ሞትን በ 65%፣ ማለትም በ 2,790 ሰዎች (ከ 675 እስከ 9,341 የሚሆኑ) ይቀንሳል ተብሎ ይገምታል።

    “ኢትዮጵያ ገና በመጀመሪያው የወረርሽኝ ደረጃ ላይ ነው ያለችው፤ እናም ሞትን አስመልክቶ ገና ጣርያውን አልነካነውም፣ ስለሆነም ሀገሪቱ እነዚህን አዋጆችን ላላ እያረገች በሄደችበት ወቅት፣ ይህ አስከፊ ቫይረስ በመላው ሀገሪቱ፣ በተለይም በአዲስ አበባ በፍጥነት ይሰራጫል የሚል ስጋት አለኝ” ብለው የ IHME ዳይሬክተር ዶ/ር ክሪስቶፈር መሪ ተናግረዋ። “ይህንን አዝማሚያ ለመቀልበስና ቫይረሱን በቁጥጥር ስር አውሎ ህይወትን ለማዳን የሚያስችሉ እርምጃዎች መወሰድ ይኖርባቸዋል።”

    የተደረገው ትንበያ ለእያንዳንዱ ሚሊዮን ሰው 8 ሰው በሚሞትበት ወቅት ላይ፣ ሀገሪቱ፣ የማኅበራዊ መራራቅን አዋጅ ለስድስት ሳምንታት አስተግብራለች ብሎ በመገመት ነው። ቢሆንም ሀገሪቱ ገና እዚያ ደረጃ ላይ ከጥቅምት 22 ቀን 2013 ዓ.ም. በፊት አትደርስም ተብሎ ነው የሚገመተው።

    ትንበያው ምን ያህል የሀኪም ቤት አልጋዎችና የ ICU አልጋዎች እንደሚይስፈልጉ ደግሞ ይገምታል። ወረርሽኙ አሁን ባለበት የአካሄድ ፍጥነት ከቀጠለ፥ ኢትዮጵያ ያሏት ለኮቪድ-19 በሽተኞች የተዘጋጁ የ ICU አልጋዎች በሐምሌ መጀመሪያዎች (2012 ዓ.ም.) ላይ ይሞላሉ ተብሎ ይጠበቃል።

    “ኢትዮጵያና ሌሎች የአፍሪቃ መንግሥታት ከባድ ሁኔታ ገጥሟቸዋል” ብለው ዶ/ር መሪ ይናገራሉ። “ጭንብልን መጠቀም፣ የምርመራ ቁጥርን መጨመርና ሌሎች እርምጃዎች፣ በተለይም በሽታን የመከላክል አቅማቸው የተዳከሙ ሰዎች፣ አረጋውያን፣ እና ሌሎች መሃል ቫይረሱ እንዳይሰራጭ ለመግዳት የሚረዱ ዋና መሣርያዎች ናቸው።”

    እነዚህ አዳዲስ ግምቶች በመላው ከሳሃራ በታች ያሉ የአፍሪቃ ሀገራት ውስጥ ያለውን የወረርሽኝ እድገትን ያሳያል። የማኅበራዊ መራራቅ አዋጅ ተግባራዊ ከሆነ እስከ ጥቅምት 22 ቀን 2013 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ፣ ደቡብ ኣፍሪቃ ውስጥ፣ 34,757 ሟች (ከ 13,263 እስከ 64,199 የሚሆን)፣ እንዲሁም ኬንያ 5,613 ሟች (1,613 እስከ 18,493) ይኖራል ተብሎ ይጠበቃል።

    እነዚህ አዳዲስ የሟች ቁጥር ግምታዊ ኣሃዞችና ሌሎች መረጃዎችን በ https://covid19.healthdata.org ላይ ሊገኙ ይችላሉ።

    IHME ይህንን የኮቪድ-19 ግምታዊ አሃዝን እውን ለማድረግ የረዱንን የእነዚህንና የሌሎችን ጥረቶችን ለመጥቀስ ይፈልጋል።

    ስለ Institute for Health Metrics and Evaluation (የጤና ሜትሪክስና ግምገማ ተቋም)

    የ Institute for Health Metrics and Evaluation (IHME)፣ በ University of Washington School of Medicine ውስጥ የሚገኝ፣ በአለም አቀፍ ደረጃ የሚገኙ የጤና ችግሮችን አስመልክቶ በጣም ትክክለኛና ተነጻጻሪ የመጠን ደረጃ የሚሰጥና፣ ለእነዚህ ችግሮች የመፍትሄዎችን ስትራተጂዎችን የሚገመግም፣ ገለልተኛ የሆነ አለማቀፋዊ የጤና ምርመር ድርጅት ነው። IHME ግልጽና፣ ፖሊሲ ነዳፊዎች፣ የሕዝብን ጤና ለማሻሻል የሚያስችሉ አቅርቦቶችን በአግባቡ ለማቅረብ የሚያስችሉ፣ እውቀትን የተሞረከዙ ውሳኔዎችን ለማስተላለፍ የሚያስችሏቸውን ማስረጃዎችን ለሆሉም ለማቅረብ በታታሪነት ይሠራል።

    ምንጭ፦ healthdata.org

    [caption id="attachment_15277" align="aligncenter" width="600"]IHME COVID-19 Ethiopia Update በኮቪድ-19 ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች IHME COVID-19 Ethiopia Update[/caption]

    Anonymous
    Inactive

     ጤናችን በእጃችን! ― 1.2 ሚሊዮን ሰዎችን ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ የሚከላከል ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

    አዲስ አበባ – በግል የንግድ ዘርፍ፣ በመንግሥት እና በመንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች መካከል የተመሠረተው ጥምረት ሐምሌ 16 ቀን 2012 ዓ.ም. የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የሚያስከትለውን ከፍተኛ አደጋ ለመከላከል የሚያስችል ለሚቀጥሉት ቀጣይ ወራት የሚሠራ እና እስከ 6 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወጪ ሊኖረው የሚችል <ጤናችን በእጃችን!> የተሰኘው ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ። ፕሮጀክቱ የውሃ፣ የሳሙና እና ሌሎች ተመሳሳይ ተግዳሮቶች እጥረት የሚያጋጥማችውን እና በጣም ጥቅጥቅ ያሉ የመኖሪያ አካባቢዎች ውስጥ የሚገኙ የከተማዋ ነዋሪዎችን ለማገዝ ብሎም ራሳቸውን ከወረርሽኙ እንዲጠብቁ የሚያስችል ይሆናል።

    የፕሮጀክቱ አባል የሆኑት አምራች ኩባንያዎች በፕሮጀክቱ የመጀመሪያዎቹ 6 ወራት ውስጥ ትርፍን መሰርት ያላደረገ ሥራ ለመሥራት እና ሠራተኞቻቸውን በሥራ መደብ ላይ ለማቆየት ተስማምተዋል። ይህንን ለማካካስ ጥምረቱ ለተሳታፊ ኩባንያዎች ወሳኝ ከሆኑ ጥሬ ዕቃዎች እና ከማምረት ጋር ለተያያዙ የክንዋኔ ወጪዎችን የሚሸፍን ይሆናል።

    ጤናችን በእጃችን! ፕሮጀክት በይፋ መጀመርን ተከትሎ ይህ አዲስ ጥምረት የፊት ጭምብሎችን እና ሳሙናዎችን የማምረት እና ማሠራጨት፣ የውሃ ገንዳዎችን መትከል፣ ብሎም የባህሪ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችሉ የግንዛቤ ለውጥ ፈጣሪ ትምህርቶችን ለ1.2 ሚሊዮን ለሚሆኑ ከፍተኛ ተጋላጭ ተበለው ለተለዩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የኮቪድ-19 ወረርሽኝን የመከላከል ሥራን በሚያጠናክር መልኩ የሚያደርስ ይሆናል።

    ዳልበርግ ግሩፕ (Dalberg Group) እና ሮሃ ግሩፕ (Roha Group) የተባሉ የግል ድርጅቶች ተነሳሽነት በመውሰድ በሀገሪቱ በአሁኑ ጊዜ ያለውን የወረርሽኝ የመከላከል ብሔራዊ ምላሽ ላይ ዘላቂ ተፅዕኖ ለመፍጠር በሚያስችል መልኩ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነውን የግል እና የመንግሥት ተቋማት በጋራ በማደራጀት ወደ ሥራ ገብተዋል። የፕሮጀክቱ የሙከራ ጊዜ የሚያስፈልገውን 1 ሚሊዮን ዶላር በሮሃ ግሩፕ በኩል የተገኘ ሲሆን፥ ቀሪው 5 ሚሊዮን ዶላር ከለጋሽ ድርጅቶች፣ የግሉ ዘርፍ እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች የሚሰበሰብ ይሆናል። ጥምረቱ የንፅህና መጠበቂያ የሆኑ ልዩ ልዩ ቁሳቁሶችን ማምረትና በጣም ተጋላጭ ለሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች በማከፋፈል በዓይነቱ ለየት ያለ የንግድ ሥራ ሞዴሎችንም ማስተዋወቅ ችሏል።

    መንግሥት በበኩሉ በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል ለፕሮጀክቱ የሚመረቱ ዕቃዎች ላይ የተጨማሪ እሴት ታክስን ያነሳ ሲሆን፥ ዓላማውም የግል ተቋማት በኮቪድ-19 ወረርሽኝላይ ለሚደረገው የመከላከል ሥራ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበርክቱ ለማስቻል ነው።

    ፕሮጀክቱ እስካሁን ድረስ 15 የሚሆኑ ሀገር በቀል በማምረቻ ዘርፍ የተሰማሩ ኩባንያዎችን በአንድ ላይ በማሰባሰብ አነጋግሯል። ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና ሴቭ ዘ ችልድረን (Save the Children) በጎ አድራጊ ድርጅት ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል።

    የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር የከንቲባ ጽ/ቤት ውስጥ ብሎክን መሠረት ያደረገ የማኅበረሰብ አደረጃጀት ኤጀንሲ በከተማው ውስጥ የሚገኙ 24,934 አካባቢዎችን በመለየት የሚገኙበትን ጊዜያዊ ሁኔታ መረጃ ሰብስቦ አዘጋጅቷል። በተጨማሪም በ10 ክፍለ ከተማዎች የሚገኙ 121 ወረዳዎች ውስጥ 1,357 የተደራጁ ማዕከላትን በመጠቀም የፊት ጭንብሎችን እና ሳሙናዎችን ለከፍተኛ ተጋላጭ ተበለው ለተለዩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የሚያከፋፍል ይሆናል።

    በተጨማሪም ሴቭ ዘ ችልድረን (Save the Children) ለጥምረቱ የቴክኒክ ድጋፍ፣ መመሪያ እና የሕብረተሰቡ ተሳትፎን በተመለከተ ድጋፍ ይሰጣል። የሚሠራጨው በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የፀደቁ የእጅ መታጠብ፣ የፊት ጭንብል መልበስ እና አካላዊ ርቀት መጠበቅን የሚመለከቱ መልዕክቶችን ያካትታል። የሠራተኞቹን እና የሕብረተሰብ አካላትን ጤና እና ደህንነት ለመጠበቅ ከ260 በላይ የክፍለ ከተማና የወረዳ ቡድን አመራሮችም ስልጠና ተሰጥቷቸዋል።

    በተያያዘም ሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ ፕሮጀክቱ የሙከራ ጊዜውን ጨርሶ ሙሉ በሙሉ ከመጀመሩ በፊት የፈንድ አስተዳደርና የሥራ ሂደት ለመቆጣጠር የፕሮጀክቱን ውጤታማነት ለመገምገም ከጥምረቱ ጋር አብሮ የሚሠራ ይሆናል።

    የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ማኅበረሰባችን ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት ለመከላከል የበኩላችንን ማድረግ በመቻላችን ከፍተኛ ደስታ ይሰማናል። ጥምረቱን የተቀላቀሉና ኃላፊነታቸውን በመወጣት አዳዲስ መፍትሄዎችን በማምጣት ይህን አስቸጋሪ ጊዜ ለማለፍ አብረውን እየሠሩ ያሉትን አጋሮቻችንን እናመሰግናለን” ብለው የጥምረቱ መሥራቾች ተናግረዋል።

    አክለውም ይህ ጥምረት ወረርሽኙን ለመዋጋት የሚያስፈልገውን ቁሳቁሶች ብሎም የባህሪ ለውጥ ትምህርት ድጋፍ የሚሰጥ ሲሆን፥ ሌሎችም በንግዱ ዘርፍ የተሰማሩ ድርጅቶች እና ተቋማት ይህን ጥምረት በመቀላቀል የበኩላቸውን እንዲያደርጉ ጥሪ እናቀርባለን።

    ፍሰሃ አለማየሁ የፍሪ ዞን ኢንተርናሽናል (Free Zone International) ዋና ሥራ አስኪያጅ በበኩላቸው “የጥምረቱ አባል በመሆናችን የማምረት ሥራችን ሳይስተጓጎል በ ሀ ገራችን ውስጥ ኮቪድ-19 ወረርሽኝ የመከላከል እንቅስቃሴ እንድንደግፍ አስችሎናል” ብለው ተናግረዋል።

    ጤናችን በእጃችን!

    ጤናችን በእጃችን! በዳልበርግ ግሩፕ እና በሮሃ ግሩፕ የተመሰረት የግል እና የመንግሥት ተቋማትን አንድ ላይ የያዘ ጥምረት ነው። በሀገራችን የኮሮና ወረርሽኝ መከላከል ሥራ ላይ ለውጥ ለማምጣት ሁለቱ ኩባንያዎች የግሉ ሴክተር አቅምን እና ብቃቶችን ለማደራጀት ተነሳሽነት ወስደው ወደ ሥራ ገብተዋል።፡

    ጥምረቱ ተጋላጭ የሆኑትን የሕብረተሰብ ክፍሎችን በመለየት ባሉበት ቦታ መፍትሄ ለማቅረብ የሚቻልበትን መንገድ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ በከፍተኛ አደጋ ላይ ከሚገኙ ንዑስ ምድቦች በተጨማሪ የህብረተሰባችንን ኢኮኖሚያዊ ጤና ለማረጋገጥ አካል የሆኑት የንግድ ድርጅቶችም የዚህ ጥምረት ትኩረት ናቸው። ስለሆነም ጤናችን በእጃችን! የተሰኘው ፕሮጀክት ከፍተኛ አደጋ ተጋላጭ ማኅበረሰቦችን የሚረዱ አስፈላጊ የንፅህና እና የመከላከያ ምርቶችን በማምረት እና በማሠራጨት ረገድ ልዩ የንግድ ሥራ ሞዴል በማስተዋወቅ የንግድ ተቋማት ይህ አስጨናቂ ጊዜ የፈጠረውን የገበያ እጦት ለመቋቋም የሚያስችላቸው መንገዶችን በማዘጋጀት የንግድ ድርጅቶች ወጪያቸውን ለመሸፈን እና ሠራተኞቻቸውን ለማቆየት የሚያስችል ይሆናል። https://www.tenachinbejachin.org

    [caption id="attachment_15265" align="aligncenter" width="600"]ጤናችን በእጃችን! (Tenachin Bejachin!) Initiative ጤናችን በእጃችን! (Tenachin Bejachin!) Initiative[/caption]

    Semonegna
    Keymaster

    የኮቪድ-19 ስርጭት ማሻቀብን ተከትሎ ለአንድ ወር የሚቆይ ሀገር አቀፍ የምርመራ ዘመቻ ይጀመራል – የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት

    አዲስ አበባ (ሰሞነኛ) – የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሃምሌ 25 ቀን 2012 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ፥ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ (ኮቪድ-19) ስርጭት እጅግ ማሻቀብን ተከትሎ ለአንድ ወር የሚቆይ ሀገር አቀፍ የምርመራ ዘመቻ ይጀመራል። የጽሕፈት ቤቱ መግለጫ እንደሚከተለው ይነበባል።

    ባለፉት ሁለት ሳምንታት የኮቪድ-19 ስርጭት ማሻቀቡ ይስተዋላል። በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሰብሳቢነት ሥራውን የሚከውነው እና ቫይረሱን የመከላከል ሥራዎችን የሚያስተባብረው የሚኒስቴሮች ኮሚቴ፥ ሃምሌ 25 ቀን 2012 ዓ.ም. ከሰዓት በወቅታዊው ሁኔታ ላይ ተወያይቷል። የጤና ሚኒስቴር እና የትምህርት ሚኒስቴር ወረርሽኙ በዓለም አቀፍ እና በሀገር አቀፍ ደረጃ ያለውን አካሄድ በተመለከተ ገለጻ አቅርበዋል።

    የጤና ሚኒስቴር ባቀረበው ሪፖርት መሠረት፥ እስከ አሁን [ሃምሌ 25 ቀን] ድረስ በኢትዮጵያ 17,500 በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች የተገኙ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 70 በመቶው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ናቸው። በቫይረሱ ከተያዙት ሰዎች መካከል፣ 84 በመቶው ዕድሜያቸው ከ50 ዓመት በላይ ሲሆን፣ ከመመርመራቸው በፊት በቫይረሱ የመያዝ ምልክቶች አልታዩባቸውም። ይህም ምልክት ሳይታይባቸው ቫይረሱን የሚያስተላልፉ ብዙ ሰዎች መኖራቸውን ያመላክታል።

    የትምህርት ሚኒስቴር የመጀመሪያ፣ የሁለተኛ እና የሦስተኛ ደረጃ ትምህርት ሁኔታዎችን መረጃ አጠቃልሎ አቅርቧል። በዚህም መሠረት፥ ትምህርት ቤቶች [በ2013 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን] ተመልሰው ከመከፈታቸው በፊት ሊተኮርባቸው የሚገቡ ቅድመ ሁኔታዎችን አመላክተዋል። ከእነዚህም ውስጥ የቫይረሱ የስርጭት መጠን መቀነስ ዋነኛው ነው።

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የምርመራ መጠንን ከፍ ማድረግ የወረርሽኙን አካሄድ ለመረዳት ወሳኝ ተግባር መሆኑን በአጽንዖት ተናግረዋል። ለአንድ ወር የሚቆይ ሀገር አቀፍ የምርመራ ዘመቻ እንዲካሄድም አቅጣጫ ሰጥተዋል።

    ADDIS ABABA (Semonegna) – The Office of Prime Minister – Ethiopia issued a press statement on 1st August 2020 stating that the country will carry out nationwide mass testing of COVID-19 for one month amid the surge of COVID-19 cases in the country, especially in recent weeks. The press statement reads as follows.

    Over the past couple of weeks there has been a noticeable increase in the number of positive COVID-19 cases. The ministerial committee overseeing prevention activities and chaired by Prime Minister Abiy Ahmed, met this afternoon to discuss the current status, where the Ministers of Health and Education presented on the international and domestic trends of the pandemic.

    According to Ministry of Health reports, there are currently 17,500 positive COVID-19 cases confirmed [in the country] as of date with 70% located in Addis Ababa. While 84% of positive cases are above the age of 50 years, 92% of positive cases showed no symptoms prior to testing, which indicates the presence of many silent spreaders.

    The Minister for Education, combining data for primary, secondary and tertiary education, highlighted that a number of issues need to be factored before considering opening schools [for the coming academic year], with declining rate of cases being the key number one factor to enable an opening decision.

    Prime Minister Abiy Ahmed emphasized the critical importance of increased testing to understand the trends better for effective decision making, and gave direction for the launch of a one-month nationwide mass testing.

    የኮቪድ-19 ስርጭት ማሻቀብ

    Anonymous
    Inactive

    የትግራይ ክልል ለምርጫ የጀመረውን ኢ-ሕገ-መንግሥታዊ እንቅስቃሴ እንዲያቆም የፌዴሬሽን ምክር ቤት አሳሰበ

    አዲስ አበባ (ኤፍ.ቢ.ሲ) – የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምርጫ ለማካሄድ የጀመረውን ኢ-ሕገ መንግሥታዊ እንቅስቃሴ በአፋጣኝ እንዲያቆም ሲል የፌዴሬሽን ምክር ቤት አሳሰበ።

    ምክር ቤቱ ለትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምክር ቤት በላከው ደብዳቤ፥ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ስድስተኛውን ሀገራዊ ምርጫ ማካሄድ እንደማይችል ያቀረበውን ሪፖርት መነሻ በማድረግ የሕገ-መንግሥት ትርጉም እንደተሰጠበት አስታውሷል።

    በዚህም የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢፌዴሪ) ሕገ-መንግሥት ምርጫን በወቅቱ ለማካሄድ ከአቅም በላይ የሆነ እክል ሲያጋጥም ምን መደረግ እንዳለበት በግልጽ ባለመደንገጉ እና ሕገ-መንግሥቱ በሚፈቅደው መሠረት ክፍተቱን በሕገ-መንግሥት ትርጉም መሙላት ተገቢ መሆኑን በማመን ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ እንዲራዘም መወሰኑንም አስታውሷል።

    ይሁንና የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ይህን ውሳኔ ወደጎን በመተው በክልሉ ምርጫ ለማካሄድ ወስኖ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን አረጋግጠናል ያለው የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 102 መሠረት በፌዴራል እና በክልል ነፃና ትክክለኛ ምርጫ በገለልተኛነት ማካሄድ የሚችለው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ብቻ እንደሆነና፥ በክልል ደረጃ የሚቋቋም ምርጫ ቦርድ አለመኖሩን ጠቅሷል።

    በመሆኑም የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የትግራይ ክልል ምርጫን በሚመለከት የወሰነው ውሳኔና የራሱን የምርጫ ኮሚሽን በማቋቋም ጭምር እያካሄደ ያለው እንቅስቃሴ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ስድስተኛውን ሀገራዊ ምርጫ በተመለከተ ሰኔ 3 ቀን 2012 ዓ.ም. ያሳለፈውን ውሳኔ ያላከበረ ከመሆም ባሻገር ግልጽ የሆነ የሕገ-መንግሥት ጥሰት ነው ብሏል ምክር በቤቱ በደብዳቤው።

    በተጨማሪም በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 62 (9) መነሻ በማድረግ፥ ማንኛውም ክልል ሕገ-መንግሥቱን በመጣስ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ እንደሆነ የፌደራሉ መንግሥት ጣልቃ የሚገባበትን ሥርዓት ለመደንገግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 359/1995 አንቀጽ 12 መሠረት፥ በአንድ የክልል መንግሥት ተሳትፎ ወይም እውቅና ሕገ-መንግሥቱን ወይም ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን ባለማክበር የሚደረግ እንቅስቃሴ ወይም ድርጊት ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ እንቅስቃሴ ወይም ድርጊት እንደሆነ በግልጽ መደንገጉን ጠቅሷል።

    በመሆኑም የትግራይ ክልል ምርጫን ለማካሄድ የጀመረው እንቅስቃሴ ሕገ-መንግሥቱን የሚቃረን፣ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል እና የኢትዮጵያን የፌዴራል ሥርዓት የሚጎዳ አካሄድ ነው ብሎታል።

    በተጨማሪም በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 50 (8) መሠረት፥ ለፌደራል መንግሥት የተሰጠው ስልጣን በክልሎች መከበር ያለበት መሆኑና የሕገ-መንግሥት የበላይነት በሚደነግገው የሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 9 (1) መሠረት፥ ማንኛውም ሕግ ወይም የመንግሥት አካል ውሳኔ ከሕገ-መንግሥቱ ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈጻሚነት እንደማይኖረው ታውቆ የክልሉ መንግሥት ሕገ-መንግሥ ቱንና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ያሳለፈውን ውሳኔ እንዲያከብር እና የጀመረውን ኢ-ሕገ መንግሥታዊ እንቅስቃሴ በአፋጣኝ እንዲያቆም ሲል ምክር ቤቱ አሳስቧል።

    ምንጭ፦ ኤፍ.ቢ.ሲ/ ሰሞነኛ ኢትዮጵያ

    የፌዴሬሽን ምክር ቤት

Viewing 15 results - 211 through 225 (of 730 total)